ስለ ንስሐ ጥያቄና መልስ

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ንስሐ ጥያቄና መልስ

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

ንስሓ ማለት ምን ማለት ነው?
 
ንስሓ የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን በአማርኛ ትርጓሜው ወይም የቃሉ ፍች እና ማብራሪያ፦ ማዘን፣ መፀፀት፣ መቆጨት፣ መቀጣት፣ ቀኖና መቀበል፣ ስለተሰራው ኀጢአት ካሳ መክፈል።፣ የሰሩትን በደል እና ጥፋት ማመን፣  አና በአጠቃላይ ማንኛውም ክርስቲያን ስለሰራው ኀጢአት ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው ሲመለስ የሚቀበለውን የቀኖና ንስሐ ያመለክታል።
 
አንድ ክርስቲያን ንስሓ ለመግባት ተዘጋጀ ወይም ንስሓ ገባ ሲባል ማመኑን፣ መፀፀቱን፣ ወደ እግዚአብሔር መመለሱን፣ ክፉ ፀባዩን መተዉን፣ ከጥፋት ስራ መቆጠቡን እና መታረሙን የምናውቅበት መንገድ ነው። በተጨማሪም ንስሓ ማለት አንድ ክርስቲያን በሰራው ጥፋት በፈፀመው ኅጢያት እና ባደረገው ስህተት ሰለተፀፀተ እና ስለተቆረቆረ ሌላ ጊዜ ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላውን እና ሰማያዊ የዘላለም ህይወት ሊያሳጣው የሚችል ኀጢያትን ላለመፈፀም የመጨረሻ ውሳኔ የሚደርስበት የመደምደሚያ ሃሳብ ነው።
 
በአጠቃላይ ንስሓ የቃሉ ማብራሪያ እና የጽንሰ ሃሳቡ ትንታኔ ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ሲሆን፤ የንስሓን አስፈላጊነት በሚያምኑ ክርስቲያኖች ዘንድ የንስሓ ህይወት ያለውን ጠቀሜታ ስንመለከት የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ይዞ እናገኘዋለን።
 
1/ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ማስረጃ፦
 
–       የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ሚልክያስ እንደተናገረው  “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርአቴ ፈቀቅ ብላችኋል። ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሣለሁ” በማለት ከእግዚአብሔር ሕግ በመተላለፍና ትእዛዙን በማፍረስ ለበደሉት ሰወች የንስሓ ጥሪ እንዳቀረበላቸው እንመለከታለን።(ሚል 3፥7)
 
–       ጠቢቡ ሰለሞን “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፣ የሚናዘዝባት እና የሚተዋት ግን ምህረትን ያገኛል” በማለት ስለ ኀጢአት ግልፀኝነትና ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚሆንልን ምህረት ተናግሯል። (ምሳሌ 28፥13)
 
–       ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ሲናገር በኀጢአት ወድቆ በንስሓ ስለተመለሰው  የሰው ልጅ ኅጥያቱን ተመራምሮ እና በልቡ ተጸጽቶ ወደ ሰማያዊ አምላክ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ውሳኔ ላይ ቢደርስ የምህረት እና የቸርነት አባት እግዚአብሔርም በደስታ እና በፍቅር እንዴት እንደሚቀበለው  ተመዝግቦ እናገኛለን (ሉቃ 15፥1824)
 
2/ ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅን ያመለክታል፦
 
የሰው ልጅ በ 40 እና በ 80 ቀን በጥምቀት ያገኘውን የእግዚአብሔር ልጅነት በገቢረ ኀጢአት ወይም ኀጢአት በመስራት ከእግዚአብሔር ጋር የልጅነት ክብሩን ያጣል ከፈጣሪው ጋርም ይጣላል ለክርስቲያናዊ ህይወቱ የነበረውን ክብርና ቅድስና ያጎድፋል። በእግዚአብሔር እና በእሱ መካከልም የጥል ግድግዳ ይፈጥራል፤ በመሆኑም ንስሓ የተባለውን የበደል ካሣ በመክፈል ከፈጣሪ ጋር እና ከራሱ ጋር መታረቅ ይቻላል።
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጰውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በፃፈላቸው መልእክቱ ስለዚህ ሲናገር “እንግዲህ እግዚአብሔር ለእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናችኋለን” ሲል ተናግሯል። (2ቆሮ5፥20) በመሠረቱ ንስሓ መግባት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰዎች ልቦና እንደሚያድር የምናውቅበት መንገድ ነው። የሰው ልጅ ኀጢአትና በደሉን ትቶ በንስሓ እንደገና ተቀድሶ ከህይወቱ ካላስወገደ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እና የመንግስቱ ወራሽ ሊሆን ስለማይችል ከሰማያዊ አባቱ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ለመሆን መላ ህይወቱን ማዘጋጀት አለበት። ( 2ኛ ቆሮ 5፥19)
 
3/ ንስሓ ክርስቲያን ከኀጢአት እንቅልፉ የሚነቃበት ደወል ነው፦
 
ክርስቲያን ኀጢአትን በሰራ ጊዜ በመንፈሳዊ ህይወቱ እና በክርስቲያናዊ ስነምግባሩ ማንቀላፋቱን የምናስተውልበት ምልክት ነው። “የሰው ልጅ ኅጢአተኛ መሆን ሲጀምር በክርስቲያናዊ ህይወቱ የነበሩት እሴቶች ሁሉ ከሱ ጨርሰው ስለሚጠፉ ኀጢአት የሚያሰራው የክፉ መንፈስ ባለቤት የሆነው ሰይጣን በኀጢአት የማደንዘዣ መርፌ አይምሮውን ስለሚያሣጣው የቆመበትን ስፍራ  እና የወደቀበትን ጉድጓድ ፈፅሞ ሊያውቀው አይችልምና በንስሓ ደወል እንድንቀሰቅሰው ያስፈልጋል።
 
በትምህርቱ የአለም ብርሃን የተባለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በፃፈላቸው መልእክቱ ላይ “ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ” በማለት ከኀጢአት እንቅልፍ ነቅተው ንስሓ እንዲገቡ አስረግጦ መክሯቸዋል (ሮሜ 13፥11)። የሰው ልጅ በኀጢአት አንቀላፍቶ የተኛበት ዘመን ይበቃኛል ብሎ በንስሓ ህይወት ወደ ቀደመው ማንነቱ ለመመለስ የሚችልበት የጽድቅ መንገዱ ሰፊ እና ቀና ጉዞ ስለሆነ በቤተክርስቲያን አባቶች ምክር እና ተግሳጽ ወደ ቀደመው ክብሩ መመለስ ይገባዋል (ሉቃ 15፥7)
 
4/ ንስሓ በኀጢአት ምክንያት ወድቆ የነበረ ክርስቲያን ወደ መንፈሣዊ ህይወቱ መመለሱን ያመለክታል፦
 
የኀጢአት ደዌ ያደረበት ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በንስሓ ህክምና ፈውስ ካላገኘ በመጨረሻ የሚገጥመው እድል የነፍስ ሞት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስም ያበራልሃልና ሲል ተናግሯል (ኤፌ 5፤14)። ወንጌላዊ ቅዱስ ዩሃንስም “እኛ ……ከሞት ወደ ህይወት እንደተሻገርን እናውቃለን። በማለት ስለ ህይወት መንገድ መስክሯል።
 
ሐዋርያው ቅዱስ ያእቆብ በመልእክቱ ላይ “ኅጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኀጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ” ሲል ኀጢአተኛ መሆን በነፍስ መሞት እንደሆነ በንስሓ መመለስ ደግሞ በህይወት መኖር እንደሆነ መስክሯል። (ያዕ 5፤20)
 
ስለሆነም ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ከርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ማወቅ እና መረዳት ያለበት በንስሓ ህይወት ወደ እግዚአብሔር መመለስ የህይወት ትንሳኤ ማግኘት ሲሆን ፀፀት በሌለው ኀጢአት ፀንቶ መኖር ደግሞ በመንፈሣዊ ህይወት የነፍስ ሞት መሆኑን ነው።
 
5/ ንስሓ ከሃጢያታችን እድፍ የምንታጠብበት ንጹህ ውሃ መሆኑን እና ጽድቅ እና ኩነኔን ለይተን የምናውቅበት አዲስ ልብ ነው።
 
ክርስቲያን ሁሉ በኀጢአት እድፍ የጎሰቆለውን መንፈሣዊ ማንነቱን ንስሓ በተባለ ንፁህ ውሃ ታጥቦ በጠራ ጊዜ ወደ ቀደመው ውበቱ እና ክብሩ ይመለሳል።
 
ጽድቅ እና ኩነኔን፣ ህይወት እና ሞትን፣ ብርሃን እና ጨለማን፣ ገነት እና ሲኦልን፣ ታቦት እና ጣኦትን፣ መንግስተ ሰማያትን እና ገሃነመ እሳትን፣ እግዚአብሔርን እና ሰይጣንን (ቤልሆር) ለይተን ለማወቅ እና ለማስተዋል የምንችልበትን ንጹህ የሆነ የንስሓ ልቦና እግዚአብሔር እንዲሰጠን መለመን ያስፈልጋል። (2ኛ ቆሮ 6፥14-16)
 
የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ሕዝቅኤልም ስለዚህ ሲናገር “ጥሩ ውሃንም ረጭባችኋለው እናንተም ትጠራላችሁ፣ ከርክሠታችሁ ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለው አዲስ ልብ ሰጣችኋለሁ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከስጋችሁ አወጣለሁ የስጋንም ልብ እሰጣችኋለው መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትዕዛዜም አስኬዳችኋለው ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ” በማለት አስተምሯል። (ሕዝ 36፥25-27)
 
6/ ንስሓ የዲያቢሎስን ስራ በመቃወም ከኀጢአት ባርነት ነፃ የሚወጣበት መንገድ ነው። 
 
ክርስቲያን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የክርስትና ስሙን ከተቀበለበት ቀን ጀምሮ ከዲያብሎስ አገዛዝ እና ከኀጢአት ባርነት ነፃ መውጣቱን ያረጋገጠበት ልዩ ማህተሙ ነው። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ጥንተ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በክርስቶስ የመስቀል ሞት ዳግም ያገኘነውን ክብራችንን ለማስጣል ዘወትር የምንወድቅበት የኅጥያት ወጥመድ ከፊታችን ለማጥመድ በያዘን ጊዜ በንስሓ ህይወት የተያዝንበት የኀጢአት ወጥመድን ሰባብረን ለማምለጥ እንድንችል ለንስሓ የተዘጋጀ ልቦና ያስፈልገናል። ዲያብሎስ ያደረበት ሰው ሁል ጊዜም የኀጢአት ባርያ ነው። 
 
መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኀጢአትን የሚያደርግ ሁሉ የኀጢአት ባርያ ነው፣ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም…. እንግዲህ ልጅ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። በማለት ከዚህ አለም የኀጢአት ባርነት ነፃ መውጣት የሚቻልበት ዋናው መንገድ ለንስሓ የተዘጋጀ እና የወሰነ ንፁህ ልቦና መሆኑን አስተምሯል። ከምንም በላይ ንስሓ ለመግባት የተዘጋጀ እና በቁርጠኝነት ወስኖ ኀጢአትን የተወ ሰው ለእውነትም ከኀጢአት ባርነት ነፃ እንደወጣ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛምርቴ ናችሁ እውነትንም ታቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት አስተምሯል።(ዩሐ 8፥32)። “እንግዲህ የዲያብሎስን ስራ በመቃወም ለእግዚአብሔር መታዘዝ እና መገዛት ያስፈልጋል” (ያዕ 4፥7)
 

ጌታችን በወንጌሉ ካህናትን “እናንተ የአለም ብርሃን  ናችሁ”  ማቴ 5 -14 ይላቸዋልና ከርኩሰት አረንቁዋ ከጨለማውና  ከኀጢአት ሥራ ሁሌ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚመሩንና ኀጢአትን ጠልተን በበጎ ምግባር እንድንኖር መንገዱን የሚመሩን ናቸው፡፡

 የንስሐ አባት ማለት ምስጢረኛችን በመንፈሳዊም በሥጋዊም ህይወታችን የቅርብ አማካሪዎቻያችን ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሲራክ  “ብዙ  ሰዎች ወዳጆች  ይሁኑህ  ከብዙዎች  አንዱ ምክርህን  የምትነግረው  ከልቡናህ  ጋር አንድ  ይሁን፡፡”  ሲራክ  6-6  በማለት ይናገራል፡፡ ይህ ማለት    ምእመናን ስለ  ሃይማኖትና  በጎ ምግባር የሚያስተምሩዋቸው  ብዙ  ካህናት ሊኖሩዋቸው  ቢችሉም  ከብዙዎች  አንዱ ግን  ንስሃቸውን  የሚናዘዙለት መምህረ ንስሃ  ሊሆናቸው እንደሚገባ ያስረዳልና መምህረ ንስሕ ማለት ምስጢረኛና አማካሪ ማለት ነው ፡፡

አበ ነፍስ ማለት ኃጢአታችንን የምንናዘዝለት ማለት ነው፡፡ ኀጢታችንን ለካህን ስንናዘዝ ለእግዚአብሄር መናዘዝና ክብር መስጠት ነው፡፡ ኢያሱ እንዳለ “ልጄ ሆይ ለአምላክ ከብርን ስጥ፡ ለእርሱም ተናዘዝ፡ ያደረግከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ”  ኢያሱ 7-19፡፡ ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ለእግዚአብሄር ክብር መስጠት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ አበዉ ካሀናትም ኑዛዜን ከተቀበሉ በኋላ “እግዚአብሔር ይፍታህ” እንጂ  ”ፈትቼሃለሁ ” አይሉም፡፡ ኀጢአተዘችንን በነሱ ፊት ብንናገርም ሰሚዉም ሆነ በእነርሱ እጅ ስርየተ ኀጪአት  የሚሰጠዉ እርሱ ባለቤቱ ስለሆነ ነው፡፡  በመሆኑም አበ ነፍስ ማለት ኀጢአታችንን በዝርዝር ምንም የሚያስፈራ ኀጢአት ቢኖረንም እያሰታወስን አንዳች ሳናስቀርና ሳንጠራጠር  በዝርዝር የምንነግረው የእግዚአብሔር አይን ነው ማለት ነው፡፡ 

የንስሐ አባት/አበ ነፍስ ወይም መምህረ ንስሐ ማለት የንስሐ   ልጆቹ ትክክለኛውን ዓላማ ይዘው የንስሐ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ በጎ መሪ ማለት ነው፡፡ 

መምህረ ንስሐ ማለት ልጆቹን መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያስተምርና የልጁቹን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚከታተልና ስለ በጎቹ የሚጨነቅ እረኛ ማለት ነው፡፡

የንስሐ አባት ማለት ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ፣ ምግባራቸውን እንደይስቱ በርካቶችም ለጠንቋዮችና ለአሳቾች ሰለባ እንዳይሆኑ የጠራውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከምንጩ ማስጎንጨት የሚችልና እሄንንም የማድረግ ግዴታ ያለበት ባላደራ ማለት  ነው፡፡ 

የንስሐ አባት ማለት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ያለመታከት የሚተጋ ማለት ነው፡፡ የንስሐ አባት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ሁሌም መጐትጐትና መቀስቀስ አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በኃይል፣ በማጣደፍ ወይም በማስፈራት አይደለም፡፡ ካህኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወኪል፣ የእግዚአብሔር አደረኛ ስለኾነ ሁሌም ማትጋት፣ መጐትጐት፣ መቀስቀስ ይጠበቅበታል፡፡

የንስሐ አባት ለእያንዳንዱ ልጆቹ እንደየ አቅማቸውና እንደየሃይማኖት እውቀት መጠናቸውና እንደየ መንፈሳዊ እውቀታቸው አቻ እስከሚሆኑለት ለያይቶ በማስተማር ማብቃት አለበት፡፡

የንስሐ አባት ማለት በንስሐ ልጆቹ መካከል ፍጹም መቀራረብ እንዲኖር የሚያደርገ ነው፡፡ የንስሐ ልጆች ለብዙ ችግሮች የመፍትሔ አካል ኾነው እንዲያገለግሉ ዕድል ይሰጣልና፡፡ የተቸገሩትን ከመርዳት ዠምሮ አንዱ ለሌላው አርአያ ኾኖ በተግባር እስከማስተማር ድረስ ማድረግም የንስሐ አባት ድርሻ ነው፡፡ ይህ ማለት የአንድ ካህን ንስሐ ልጆች ከአንድ የሥጋ አባትና እናት የተወለዱ እህትማመቾች እና ወንድማማቾች ያህል ከዚያም በበለጠ ሁኔታ መቀራረብ አለባቸው ማለት ነው፡፡የንስሀ አባት ማለት ይህን የሚተገብር ማለት ነው፡፡

ከቊርባን በፊት ንስሐ ይቀድማልና፡፡ ሰው ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ ስለሌለ ጧት የሠራውን ለማታ፤ ማታ የሠራውን ለጧት ለመምህረ ንስሐው ነግሮ መምህረ ንስሐው ያዘዘውን ሠርቶ ሊቀበል ይገባዋልና ይህ ታላቅ ሀላፊነት የተጣለው ደግሞ በመምህረ ንስሀው ላይ ነው፡፡

 የንስሐ አባት ማለት ባለአደራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በበረኻ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ማን ነው?” ሉቃ.15 -5 ያለው፡፡ ካህናት ከእግዚአብሔር በአደራ እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ኹሉንም ሳይዘነጉ እያንዳንዱን በነፍስ ወከፍ ሊጠብቁና ሊያገለግሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡

የንስሐ አባት ከንስሐ ልጆቹ ጋር የሚፈጥረው ግላዊ ግንኙነት ከቤተሰባዊነት ያልተሻገረ ኾኖ ሲቀነጭርና እጅጉን ያነሰ ሲሆን ነው፡፡ ብዙ ካህናት ወደ ምእመናን ቤት መጥተው ሲያበቁ መስቀል ከማሳለምና ጠበል ከመርጨት ያለፈ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ካህናት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስቀመጠላቸው ከሥራቸው ኹሉ ቅድሚያውን ሰጥተው ማስተማር፣ መምከር፣ ኑዛዜን መቀበል፣ ማጽናናትና መገሰጽ ይገባቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የንስሐ ልጃቻቸውን በጥንቃቄ ይዘው ለሥጋ ወደሙ ማብቃት ግባቸው ስለኾነ ትኩረታቸው ኹሉ ወደዚኽ ዋነኛ የክህነት ዓላማቸው መሆን አለበት ፡፡ ይህም የካህኑ ትልቁ ሀላፊነት ነው፡፡

የንስሐ አባት የንስሐ ልጀቹን የቤተ ሰብ አባላት ቁትርና እያንዳንዱን በሚገባ ማወቅ አለበት፡፡

አንድ የንስሐ አባት ልጆቹንና አጠቃላይ ቤተሰቡን እያሰታወሰ አዘውትሮ ስለ ሁለንተናቸው መጠየቅ አለበት፡፡

የንስሐ አባት ከልጆቹ ጋር አብሮ በመጸለይ ጸሎትን ማለማመድ፤ ሆኖ በማሳየት እውነተኛ የአባትና የልጅ ፍቅርን  ማሳየት፤ በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በሥጋዊም ሕየዋታቸው መጨነቅ፤  ስራቸው እንዲባረክ አዘውትሮ፤መጸለይ በአጠቃላይ ልጆቹን በቅርበት መከታተል፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ተግባሩ እሄ ነው፡፡ 

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸው የክህነት ስልጣን ማሰር እና መፍታት የሚችሉበት ረቂቅ እና ሰማያዊ ስልጣንን ነው። ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባትም ሆነ ከመንግስተ ሰማያት ለመከልከል የሚያስችል ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው ስልጣንም ነው። ይህ ማለት ስልጣን ሁሉ የራሱ ገንዘብ የሆነው የባህርይ አምላክ እየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ሐዋርያት እና 72ቱን አርድእት ከዓለም መካከል መርጦ በሾማቸው ግዜ ኀጥያት ሰርተው በደል ፈጽመው ወደ ሐዋርያት ቀርበው በኀጢአታቸው ተጸጽተው የተናዘዙትን ኀጥያታቸውን የማስተሰረይ ስልጣን ስለተሰጣቸው ኀጥያታችሁ ይቅርላችሁ ያሏቸው ሁሉ የተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ኅጥያታቸው ሁሉ እንዲደመሰስ ያደርጋል።
 
በሰሩት ጥፋት ሳይጸጸቱ እና ከበደላቸው የማይመለሱትን ደግሞ በተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ሲፈርዱባቸው በስጋቸው ሞትና ልዩ ልዩ መቅሰፍት ይቀጣሉ ማለት ነው። 
 
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፦
 
–  ግያዝ የተባለው የነብዩ ኤልሳዕ ደቀመዝሙር ከመምህሩ ተሰውሮ ከለምጽ በሽታ ካዳነው ሶርያው ንጉስ ከንዕማን ላይ የማይገባውን ጥቅም በመውሰዱ ምክንያት ነብዩ ኤልሳዕ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ ግያዝን በለምጽ ደዌ አንደቀጣው እንመለከታለን። 2ኛ ነገስት 5፥20-27
 
–  ሐናንያ እና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች በሐዋርያት ፊት ያላቸውን የሀብታቸውን እኩሌታ ለእግዚአብሔር ሊሰጡ ቃል ከገቡ በኋላ ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን አታላችኋል ብሎ በተሰጠው የክህነት ስልጣኑ የሞት ቅጣት እንዲደርስባቸው አድርጓል። የሐዋ 5፥1-10
 
–  በጥንቆላ መንፈስ የሚኖር ሲሞን መሠሪ የተባለው ሰው ሐዋርያት እጅ በመጫን  የመንፈስ ቅዱስ ኅይል የሚሰሩትን አስደናቂ ሚስጥር ባየ ግዜ እንደእናንተ ይሄንን ታላቅ አስደናቂ ስራ ለመስራት እንድችል ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን ስልጣን በገንዘብ ሽጡልኝ ባላቸው ግዜ እድል ፋንታውን ከክፉዎች ጋር እንዲሆን እና የጥፋት ሰው አንደሆነ ረግመውታል። ዩሐ 8፥18-24
 
ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ማስረጃዎች የመንግሰተ ሰማያት መክፈቻ ለሐዋርያት ተሰጠ ሲባል በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት መንግስተ ሰማያት ማስገባት እንደሚችሉ እና የማይገባቸውን መከልከል የሚችሉ መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ የቤት ወይም የበር ቁልፍ መክፈቻና መዝጊያ ቁሳዊ ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማሰር መፍታት የሚለውም በዚህ አለም ላይ ሰው በፈጸመው ወንጀል የሚታሰርበት አግር ብረት ወይም ገመድ ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን ከላይ እንደገለጽነው በተሰጣቸው ረቂቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣን ኅጥያትን የማስተሰረይ፣ የኀጥያተኞችን ኅጥያት የመያዝ ፀጋ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይቻላል ወይ? ንስሐስ በስልክ ይሆናል ወይ?
 
ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ (አማኝ) የሆነ ክርስቲያን ለአካለ መጠን ከደረሰበት ግዜ ጀምሮ የንስሐ አባት መያዝ ክርስትያናዊ ግዴታው እንደሆነ በቤተክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን ኑሮዋቸውን ለማሸነፍና የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ሲሉ ቤተክርስቲያንና ካህናት አባቶች ወደማይገኙበት ክፍለ ዓለም በልዩ ልዩ ምክንያት ተበትነው እንደሚኖሩ ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ አገራችን ሳይቀር በረሃማና ጠረፋማ በሆነ አካባቢ እንዲሁም አህዛብ በሚበዛበት ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በመከራና በፈተና ግዜ የሚያጽናናቸውና የሚመክራቸው አባት ሊያገኙ አይችሉም። የሚጸልዩበት እና ፈጣሪያቸውን የሚማፀኑበት ቤተክርስትያንም አያገኙም።
 
ስለዚህ በቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ሰውን በነፍስ የማዳን ሥራ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ቤተክርስቲያንና አባቶች ካህናት በቅርብ የማይገኙበት ክፍለ ዓለም (አካበቢ) የሚኖሩ ማለትም በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በአረብ አገሮች እና በሌላውም ክፍለ አለም ሁሉ እየኖሩ የንስሐ አባት ለመያዝ ቢፈልጉ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የኛን የውስጥ ችግር ያውቀዋልና አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ያለ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌለበት የንስሐ አባት እንዲኖረው በሃይማኖቱና በመንፈሳዊ ህይወቱ የመረጠውን ካህን እርቀት ሳይገድበው መያዝ ይችላል። ካለው ችግር አንፃርም በስልክ እና በሌላ መልእክት በመገናኘት መንፈሳዊ ትምህርት እና ከንስሐ አባት የሚሰጠውን የንስሃ ቀኖና  መቀበል ይችላል። ማንኛውንም በጎ ስራ ሁሉ አባቱ የሚመክሩትን እና የሚያዙትን ሁሉ በመፈፀም የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ስለሚችል የግድ በአካል ካላገኘኋቸው አብሬ በአንድ አጥቢያ ካልኖርኩኝ የንስሐ አባት መያዝ አልችልም በሚል ምክንያት ያለጠባቂ መኖር የለበትም።
 
ይህን በሚመለከትም ከዚህ በፊት ስለ ንስሐ አባት አያያዝ ጥያቄ ቀርቦ በአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እና በቤተክርስትያን መምህራን ንስሐ አባት በርቀት መያዝ እንደሚቻል በተደጋጋሚ ምላሽ የተሰጠበት ሃሳብ ስለሆነ ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲያሥሩና እንዲፈቱ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ጊዜና የቦታ ርቀት የማይወስነው ስለሆነ ፤ በአካባቢው አባት የሚሆን ካህን ከጠፋ ያለጠባቂ ብንኖር ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍሳችንን እንዳይነጥቃት የንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ምእመናን መጨናነቅ እንደማያስፈልጋችሁ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
 
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር አጋዥነትና ጠባቂነት ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
ንስሐ ለመግባት ፈራሁ ፍርሐቴን ላለመፍራት ምን ላድርግ? ብለው ለጠየቁን አባል የሚከተለውን መልስ ጽፈንልዎታል።
ከእውነተኛ ሃይማኖትና ምግባር ስንርቅ የንስሐ ህይወታችን ጨርሶ ይቀጭጫል። ያኔ ደግሞ በሰራነው ኀጥያት (ጥፋት) ነፍሳችን ፈፅሞ ትቃተታለች ትጨነቃለችም። ስጋችን ምድራዊ የሆነውን የስጋ ስራ ለመስራት ነፍሳችን ደግሞ ሰማያዊ የሆነውን የፅድቅ ስራ ለመስራት ለኛ ግልፅ ሆኖ በማይታወቅና በማንረዳው ሁኔታ ሁለቱም ህይወታችንን የጦር አውድማ ሲያደርጓት በኛ ላይ የፍርሃት መንፈስ ይነግስብናል። ከጥፋታችን ተመልሰን ንስሐ እንዳንገባ ደግሞ የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው እና የእኛን ፅናት የማይፈልገው ሰይጣንም ግራ እንዲገባን እና የፍርሃቶቻችን ምክንያቶች እንዲበዙ ያባብስብናል። ስለዚህ፤ ጠያቂያችን ለዚህ ችግርዎ የምንመክርዎት የሰይጣን ውግያ ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ የፍርሃት አምላክ ሳይሆን የፍቅርና የሰላም አምላክ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወምዎትን ክፉ መንፈስ እንደምንም ታገሉት። የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ በአካባቢዎ ወደመረጥንልዎ የንስሐ አባት ከድረገፃችን ያገኛሉና ቀርበው በማማከር የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለው ቢያምኑም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና ፍርሃቶትን አርቀው ወደ ይቅር ባይ አምላክ ይቅረቡ በማለት ምክሬን እለግሳለሁ። የበለጠ መንፈሳዊ ምክር እንድንሰጥዎ ከፈለጉ በውስጥ መስመር ያነጋግሩን፤ የደረሱበትንም ሂደት ይግለፁልን። ለሁሉም ነገር ወላዲት አምላክ ድንግል ማርያም በአማላጅነትዋ ታግዝዎ።
 

“እውነት ነው በዚህ አምናለሁ ዋናው ነገር የሰራሁትን ኅጢአት በማወቅም ሆነ ባለማወቅም ለበደልኩት ላጠፋሁት ጥፋት ኅጢአቴን መናዘዝ እፈልጋለሁ ከእኔ የሚጠበቀው መስፈርትስ ምንድን ነው?” ብለው ለጠየቁ አባላችን የምንሰጣቸው ምላሽና የምክር አገልግሎት እንደሚከተለው ነው።

በቅድሚያ በድያለሁ ጥፋት ሰርቻለሁ ኅጢአት ፈጽሜያለሁ ብሎ ኅጢአትን ለመናዘዝ ፈቃደኛ መሆንና የኅጢአት ሥርየት ለማግኘት መፈለግ የእውነተኛ ክርስቲያን መገለጫ ነው። በመሠረቱ በአዳማዊ ተፈጥሮ ሰው ሁኖ የተፈጠረ የሰው ልጅ ሁሉ ወዶ ጽድቅ መሥራትም ሆነ ወዶ ኅጢአት ለመሥራት የሚችልበት የተፈጥሮ ነፃነት ያለው ፍጡር ስለሆነ በለበሰው ደካማ ሥጋው ተሸንፎ ኅጢአት እንደሚሠራ ይታወቃል። ሰው ሁኖ ተፈጥሮ በሰውነቱ ፈፅሞ ኅጢአት አልሠራም ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር እራስን ከማታለል አልፎ ስለሁላችንም መዳን በመስቀል ላይ የሞተልንን የኢየሱስ ክርስቶስ አባታዊ ፍቅሩንና ውለታውን እንደመካድ ይቆጠራል። ሁላችንም የሰው ልጆች እንደምንሞት ብናምንም እንኳ፤ ነገር ግን መቼ በሞት እንደምንጠራ ቀንና ሰዓቱን (ዘመንና ጊዜውን) ለይቶ ማወቅ ከእሱ ከባለቤቱ በስተቀር ፈጽሞ የሚያውቅ የለምና ኅጢአትን ለመናዘዝ ቅድሚያ መስጠትና በንስሐ ሕይወት ራስን አዘጋጅቶ መጠበቅና ንስሐ ለመግባት መዘጋጀት ከእውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ ታማኝነት ነው።

ኅጢአት ማለት የብዙ ጥፋቶች ወይም ስሕተቶች መጠሪያ ስም ነው ኅጢአት የሥጋ ሥራ ሁኖ ነፍስን ከፈጣሪ ጋር አጣልቶ ዘለዓለማዊና ሰማያዊ ሞትን የሚያስከትል ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የኅጢአት ውጤት ሞት እንደሆነ ሲናገር “ኅጢአት ስታድግ ሞትን ትወልዳለች” (ያዕ1፥15) ካለ በኋላ “የኅጢአት ደመወዝ ሞት ነው” (ሮሜ 6፥23) በማለት ኅጢአት የሕሊናና የመንፈስ ሞት መሆኑን አረጋግጧል። 

የሥጋና የመንፈስ (የነፍስ) ሥራዎች አብዛኛዎቹን ቅዱስ ጳውሎስ ወደገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ በምዕ 5፥19-22 ላይ የሥጋ ሥራ እና የመንፈስ ፍሬዎች በማለት ዘርዝሯቸዋል።

የሰው ልጅ ኅጢአት ሰርቻለሁ እግዚአብሔርን በድያለሁ፣ ሰውንም አሳዝኛለሁ ብሎ ራሱን ካሳመነ በነፍሱ የኅጢአት ደዌ አድሮበታልና ንስሐ የመግባት ሕክምና ያስፈልገዋል ማለት ነው። “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ “(ማቴ3፥8) ኅጢአት ሠርቶ የንስሐ ሕክምና ያላገኘ ሰው በነፍሱ ምውት ነው። ሉቃ 15፥24

ከዚህ የተነሣ ኅጢአት ለመናዘዝና ንስሐ ለመግባት ከሚፈልግ አንድ ክርስቲያን የሚጠበቀው ፡-

በቅድሚያ ኅጢአት መሥራቱን አምኖ ለራሱ ሕሊና መናዘዝ (መፀፀት)።

ስለሠራው ኅጢአት ወይም በደል እየተጸጸተ ጧት ማታ በደሉን በፀሎትና በልመና ለፈጣሪው መናዘዝና ኅጢአትን በእግዚአብሔር ፊት ማመን (መዝ50 ፣ ዳን9፥5፣ ነህ1፥6-7)

ኅጢአትን (በደልን) ለካህን መናዘዝና ንስሐ መግባት። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይና እንደራሴ ስለሆነ የሠራነውን ኅጢአት ለካህኑ በመናዘዝ ንስሐ መግባት፤ ኅጢአታችን እንዲሠረይልን በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ መግባትና መናዘዝ ማለት ነው። (ኢያሱ7፥19 ማቴ3፥6 ዘሌ5፥5-6 የሐዋ19፥18)

የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት የጥል ግድግዳ አፍርሰን በፍቅር አሸንፈን ስለዘለዓለማዊ ሕይወት ብለን በፍጹም ሕሊና በሰላም መኖር ነው።

ተመልሶ በኅጢአት ላለመውደቅ አዘውትሮ የንስሐ አባትን ወይም የሚቀርቡትን የሃይማኖት መምህር ማማከር፣ ምክር ማግኘት በታቻለ መጠን መጸለይ፣ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ በቤትም ውስጥ ቢሆን መንፈሳዊ መዝሙርና ትምሕርት ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ የምናስገነዝበው ለጠየቁን ምዕመን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያን እንዲጠቅም ነው።

የእግዚአብሔር ሰላም በያላችሁበት ከእናንተጋር ይሁን።

ጠያቂያችን ምንም እንኳን በክፉ ሃሳብ መውደቅዎን አምነው በመናገርዎ እና መፍትሄ በመፈለግዎ ካንድ ለንስሃ ከተዘጋጀ ክርስቲያን የሚጠበቅ ጥሩ ሃሳብ መሆኑን እየገለፅን ነገር ግን የምንወድቅበትን የኀጥያት ጉድጓድ ሰይጣን በየጊዜው ስለሚቆፍር እና ወደ እግዚአብሔር እንዳንመለስ የጽድቅ መንገዳችንን ሁሉ ስለሚዘጋብን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማን ይችላል። ማንም ሰው በራሱ የሰራው ከባድ ኀጥያትም ቢሆን ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ወገን አብሮ ሊፈትን ስለሚችል ጥፋታችንን እጥፍ ድርብ ሊያደርገው ይችላል። ለምሳሌ ጫት የሚቅም ሰው፣ ወይም መጠጥ የሚጠጣ ሰው፣ ወይም የመሳሰሉተን ጥፋቶች የሚፈፅም ሰው ስራውን ብቻውን ስለማያደርገው በሱ ጥፋት ብዙ ሰዎችም ይወድቁበታል።ስለዚህ በበደል ላይ በደል በክፋት ላይ ክፋት እየተጨመረ በሄደ ቁጥር ሸክማችን እየከበደ እና ለመክፈል የምንችልበት አቅማችን ሳይደክም ወደ ንስሐ ህይወት ለመመለስ ማሰብዎ ታላቅነት ስለሆነ ለእርስዎ የምንመክርዎት አሁኑኑ ወስነው በሚኖሩበት በአያት ጣፎ አካባቢ የሚገኙ እርስዎን መክረው በንስሐ ህይወት ወደ እግዚአብሔር ቤት ሊያቀርብዎ የሚችሉ መምህር በአካባቢዎ ወደመረጥንልዎ መጋቢ ሀዲስ ላእከማርያም የተባሉ መምህር በቅ/ስ አማኑኤል ቤ/ክ ስለሚገኙ ከንስሐ አባት ድረገፃችን ላይ: yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ ይህን አካባቢ እና ስም ተከትለው በስማቸው የሚያገኙትን ፎርም ሞልተው ሲጨርሱ በሚደርስዎ ስልክ ቁጥራቸው ደውለው እንዲያገኙዋቸውና ለችግርዎ መፍትሔ እንዲያገኙ እንመክርዎታለን።  

ምክራችንን ተቀብለው ስራ ላይ ከአዋሉት መንፈሳዊ ህይወትዎ እንደሚስተካከል እናምናለን። የደረሱበትን በየጊዜው ሊያሳውቁን እና በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን ይችላሉ።

 

 

 

መልስ፦ያለ ንስሓ አባት ንስሓ መግባት አልችልም ወይ ብለው የጠየቁን አባላችን ምናልባት ስለ ንስሓ አባት እና ስለ ንስሓ ልጅ ብዙ ግንዛቤ ላይኖርዎት ይችላል። ነገር ግን ያለንስሓ አባት ወይም ያለ መምረ ንስሓ መኖር ያለ ባል ልጅ መውለድ ነው ወይም ከባል በፊት ልጅ ይስጥሽ ማለት ነው። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊተ ለምንሰራው መንፈሳዊ ስራ ሁሉ ምስክር ሆኖ ሊቆምልን የሚችል ካህን ያስፈልገናል። በረቂቅ እና በሚስጢር አሠራር ቅዱሳን መላዕክት የኛ ጠባቂ ሆነው ይቆማሉ። በዚህ በገሃዱ አለም ደግሞ እንደ አንድ ክርስቲያንበምንኖርበት ህይወት ውስጥ ካህናት አባቶቻችን ለእኛ የነፍስ እረኞች ሆነው በእግዚአብሔር ዘንድ ተሹመዋል።
ስለዚህ ንስሓ አባት መያዝ የሰው ትዕዛዝ ሳይሆን የፈጣሪ መመሪያ ነው። ስለንስሓ አባት አያያዝና የንስሓ ልጅ ስለመሆን እንዴት እንደሚገባን ከዚህ በፊት ደጋግመን መልዕክት ማስተላለፋችን እያስታወስን። ጠያቂያችን ያልተረዱት ነገር ካለ በውስጥ መስመር አግኝተው ሊያናግሩን እንደሚችሉ እየገለፅን፤ በይበልጥም ስለንስሓ በድረገፃችን ላይ የተላለፉና እየተላለፉ ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች እንዲያነቡ እንመክራለን።   

ትምህርት ስለ ንስሓ – ይህን ሊንክ ይጫኑ፦https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ/

ካህናት እግዚአብሔር ይፍታህ ብለውን መስቀል ሲያሳልሙን የሚሰረይልን ኀጥያት (የሃልዮ/የነቢብ/የገቢር) የቱ ነው? ብለው ለጠየቁን አባል የሚከተለውን መልስ ጽፈንልዎታል። 

 

ሰው በውስጣዊ ህሊናው አውጥቶና አውርዶ ገና በስራ ላይ ያልዋለው በሃሳቡ ብቻ ያቀደው የክፋት ምኞት ሁሉ ያሃልዮ (የሃሳብ) ኀጥያት ይባላል። በልቡ የታሰበው ኀጥያት በአፍ ሲነገር የነቢብ (የመናገር) ኀጥያት ይባላል። በአፍ የተነገረው ኀጥያት በስራ ላይ ከዋለ የገቢር (የተግባር) ኀጥያት ይባላል።

 

ስለሆነም በልብ ታስቦ ሳይናገርና ስራ ላይ ሳይውል ከቀረ የታሰበውን ኀጥያት የሚያውቀው ልብና ኩላሊትን የሚመረምር እግዚአብሔር በመሆኑ በልብ ታስቦ ስራ ላይ ስላልዋለው ኀጥያት እና አንዳንዴም ጥፋት ሳይመስለን ባለማወቅ የምንፈፅማቸው ጥቃቅን ጥፋቶች በየጊዜው ወደ ካህኑ ቀርበን እና ከልባችን አምነን መስቀሉን ተሳልመን ካህኑ እግዚአብሔር ይፍታህ ቢሉን በውስጣችን የሚዋጋን ክፉ መንፈስ እንደ አሮጌ ልብስ ተገፎ እንዲወልቅ በካህኑ ላይ ያደረው ሃብተ ክህነት ያደርግልናል። ሆኖም በመናገርም ሆነ በመስራት የፈፀምነውን ከባድ በደል ግን እንደማያስፍቅልን መረዳት ያስፈልጋል።

ንሰሐ የገባ ሰው ንሰሐውን እንደጨረሰ የግድ መቁረብ አለበት? ወይሰ በንስሐ አባቱ ከንስሐው ጋር ከታዘዘለት ነው የሚቆርበው? ብለው ለጠየቁ አባል የተሰጠ ምላሽ።

መልስ፦ በመሠረቱ ንሰሐ ማለት በለበስነው ደካማ ስጋችን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ያልተፈቀደውን ሕግ ተላልፈን ስለፈፀምነው ኀጥያታችን ከልብ ተፀፅተን ንሰሐ ለመግባት ወደ ቤተክርስቲያን ካህን (ንሰሐ አባት) ቀርበን የሰራነውን ጥፋት በተናዘዝን ግዜ ካህኑ የሚሰጠን ንሰሐ በፆም ወይም በስግደት ወይም በፀሎት ወይም በምፅዋት የቀኖና ሱባዔ ሲሰጠን በቤታችን ሆነን ወይም ወደ ገዳም ሄደን የተሰጠውን ንሰሐ ልንፈጽም እንችላለን። ሱባዔውን (ንስሐችንን) ከጨረስን በኋላ ደግሞ ያንን ኅጥያት እንዳንሰራ መጠንቀቅ እና ከአባቶች ምክር እንዲሁም ከቤተክርስቲያን እና ከበጎ ስራ መራቅ የለብንም። 

ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባንን የመቀበል መንፈሳዊ ግዴታ ቢኖረውም፤ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ራሱን የቻለ ዝግጅት ከሌለ ንስሐ ስለገባን ብቻ የክርስቶስን ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል አንገደድም። ምክንያቱም ትዳር ያለው ከኑሮ አጋሩ ጋር ተስማምቶ መዘጋጀት ስላለበት፤ ያላገባ ክርስቲያንም ከራሱ እና ከመንፈሳዊ አባቱ ተማክሮ ራሱን የቻለ ፕሮግራም ማድረግ ስላለበት ነዉ።

ኅጥያቶን በመናዘዝ ከልብ ተጸጽተው ወይም ተመልሰው፤ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት በማገልገል ላይ ለሚገኘው የንስሐ አባትዎ (ካህን) ራስዎን በማስመርመርና ከፈጸሙት በደል የሚነፁበትን ንስሐ ተቀብለው ከሄዱና ከዳግም ጥፋትም እርቀው በካህኑ የተሰጠዎትን ንስሐ በትክክል ከፈጸሙ፤ ከተያዙበት የኅጥያት ማሰሪያ ስለተፈቱ ንስሐም ገብተው ስለተናዘዙበት እንደገና ይፍቱኝ ለማለት ወደ ካህኑ የሚያስኬድ ጉዳይ አይኖርብዎትም። 

ምክንያቱም በኅጥያት እድፍ የቆሸሸውን ህይወትዎን ከካህኑ በተቀበሉት የንስሐ ውሃ ታጥበው ከኅጥያት እድፍ ፀድተዋልና። ዳግም እንዳይበድሉ፣ ኅጥያት ሰርተውም የቅድስና ሕይወትዎን እንዳያቆሽሸው፣ በየጊዜው ከቤተ ክርስቲያን መምህራንና የንስሐ አባቶች ትምህርትና ተግሳጽ እያገኙ ምንም እንኳን የኑሮ ፈተና ቢበዛብዎ ከእናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳይርቁ እየፆሙና እየፀለዩ ከገንዘብዎ፣ ከእውቀትዎ እና ከጉልበትዎም አስራት በኩራት እያወጡ በጎ ስራ በመስራት ከሰይጣን ወጥመድ ለማምለጥ የሚችሉበትን መንፈሳዊ ፀጋዎትን በተቻለ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለብዎ እመክራለው። ለዚህም ዋናውና መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ክርስቲያን ያለጠባቂና ያለመካሪ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌበት ወደ ንስሐ አባትዎ (ካህን) መሄድ ያለብዎ በየጊዜው የእለት እለት ህይወትዎን በካህኑ ምክር እንዲመራ ለማድረግ ነው።

በመሆኑም፤ ወደንስሃ አባትዎ ወይም ንስሐ ወደተቀበሉበት ካህን መሄድ የሚኖርብዎ ካህናት አባቶች የነፍሳችን እረኛ ሆነው በነፍስ ጉዳይ ላይ በሃላፊነት እግዚአብሔር ስለሾማቸው ሁልግዜም ቢሆን ከአባቶች ምክርና ተግሳጽ ላለመራቅ ነው እንጂ ቀደም ሲል ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያት ይፍቱኝ ለማለት አለመሄድዎን እንደጥፋት ቆጥረው እንደገና ንስሐ እንዲገቡበት አያስፈልግዎትም በማለት መንፈሳዊ ምክሬን እለግሳለው። (ማቴ18፤18) ዩሐ(20፤21-23) ዩሐ (21፤15-18)

ከዚህ በላይ ስላቀረቡት ጥያቄ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከፈለጉና ያልተመለሰልዎት ጥያቄ ካለም በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን ይችላሉ። ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር አጋዥነት ከእርስዎ ጋር ይሁን።

መልሱ  አይቻልም ነው ። ምክንያቱም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዱ ጥፋታችንና በደላችን ወደ መምሕረ ንስሐችን ቀርበን ኀጥያታችንን ስንናዘዝ ባጠፋነው ደረጃ ንስሐ መቀበል እንዳለብን በቀኖና ቤተክርስቲያን ተደንግጓል። ስለዚህ ማንኛውም ክርሰቲያን የፈፀመውን በደል ከእግዚአብሔር ቀጥሎ በሚስጥር ለንስሐ አባቱ መናገር አለበት፤ የሚሰጠውም ንሰሐ በጥፋቱ መጠን የሚቀበለው መሆን ይገባዋል። ስለዚህ ለንሰሐ አባቶቻችን የምንደብቀው የኀጢአት ሚስጥር የለንም። እንደምሳሌ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄድ ታማሚ ወይም ታካሚ የህመሙ አይነትና መጠን ተለይቶ በሀኪም ዘንድ ሳይረጋገጥ መድሀኒት አይታዘዝለትምና። በቀጣይነት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የምንሰጥበት መሆኑን እየገለፅን ለግዜው ለጥያቄው ምላሽ እንዲሆናቸው ይሄን ምክረ ሀሳብ ሰጥተናቸዋል።

አንድ ሰው ንስሀ ሳይገባ ጸበል መጠመቅ ይችላል? ወይንም ንስሀ ገብቶ ግን አንድ የረሳው ነገር ቢኖር ያልተናገረው፣ መጠመቅ እና ፀበል መጠጣት ይችላል? በማለት ለጠየቁን አባል ስለጸበል አጠቃቀምና አገልግሎት የተሰጠ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽና ማብራሪያ ነው።

በቅድሚያ ፀበል ምንድነው? ለሚለው ካህኑ ውሃውን በእግዚአብሔር ቃል እና በቅዱስ መስቀሉ ሲባርከውና ሲቀድሰው ተራ የነበረው ውሃ በጥምቀት የእግዚአብዜር ልጅነት ይገኝበታል።

“ሰው ከውኅና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዩሐ 3፤5) በማለት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ዳግም ለመወለድና ሰማያዊ መንግሥቱን ለመውረስ የእግዚአብሔር መንፈስ ባደረበት በውሃው (በጸበሉ) መጠመቅ እንዳለብን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት ወደ እሱ ለመጣው ለወዳጁ ለኒቆዲሞስ በስፋት እንዳስተማረው ወንጌላዊው ቅዱስ ዩሐንስ ጽፎታል።

ለጥምቀት የተዘጋጀው ውሃ (ፀበል) የቤተክርስቲያን አባቶች ለዚሁ አገልግሎት የተዘጋጀውን ጸሎት ከጸለዩበት እና በመስቀል ከባረኩት በኋላ ልዩ ልዩ ደዌ (በሽታ) ያለባቸው ሰዎች ይፈወሱበታል፣ ርኩሳን መናፍስት (አጋንንት) ያደሩበት ሰውም ሲጠመቅበት በፀበሉና በመስቀሉ ኃይል አጋንንቱ ከታመመው ሰው ዳግም ወደሰውየው እንዳይመለሱ በእግዚአብሔር ቃል ታሥረውና ተወግዘው ይለያሉ።

በጸበሉ ፈዋሽነት የሚያምን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊም ሆነ ሌላው ወገን ሳያውቅም ሆነ እያወቀው የድግምት፣ የመተት፣ የሟርት መንፈስ ቢኖርበት በጸበሉ ከተጠመቀና ቤቱም ንብረቱ ጸበል ከተረጨበት ፈጽሞ ይድናል። ክፉ መንፈስም በእርሱ ላይም ሆነ በሃብቱና በቤቱ ላይ ጥፋት ለማድረስ ስልጣን የለውም።

አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በተለያየ ምክንያት ክርስቲያናዊ ሕይወቱን የሚያጎድፍና በእምነቱ ያልተፈቀደለትን ፈጽሞ ቢገኝ ደግሞ ወደ ካህናት (ወደ ንስሐ አባቱ) ቀርቦ ጥፋቱን መናዘዝ ወይም ንስሐ በመግባት በሥርዓተ ቄዶር እንዲጠመቅ ይደረጋል። ለምሳሌ ሃይማኖቱን ቀይሮ ቢገኝ፣ በሃይማኖት የማይመስለውን ቢያገባ (በዝሙት ቢወድቅ)፣ ለክርስቲያን ያልተፈቀደውን ምግብ ቢበላ ወዘተ የመሳሰለውን ኢክርስቲያናዊ ግብር ፈጽሞ ቢገኝ የቀድር ጥምቀት ያስፈልገዋል ማለት ነው።

በርዕሱ ወደተገለጸው ጥያቄ ስንመለስ ፀበል አንዱ የንስሐ መንገድ ስለሆነ ለንስሐ ከሚያበቃን የኅጢአት ሥራችን ለመመለስ በቁርጠኝነት ከወሰንን ጠያቂው እንዳሉት ፀበል ለመጠመቅም ሆነ ለመጠጣት እንችላለን። ይህን ስንል ግን የሠራነው ኅጢአት ተለይቶ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም ለምሣሌ የወለደች ሴት፣ የሴቶች ልማድ የምታይ ሴት እስከሚነፁ መጠበቅ አለባቸው። ከዚህም በላይ ፀበሉን ብንጠጣውም ሆነ ብንጠመቅበት ከልብ በሆነ እውነተኛ መጸጸት ወደ ንስሐ ሕይወት ተመልሰን ከበደላችን ነፃ ካልሆን ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝራዎች፣ ሟርተኞች ፣ መተተኞች፣ አስማተኞች፣ ቀማኞች፣ ወንበዴዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ፍርድ አጉዳዮች፣ ከሃዲዎች ወዘተ ሁነን በአጠቃላይ ከአንድ ክርስቲያን የማይጠበቅ ክፉ ሥራ እንደፈጸምን እያወቅንና በንስሐ ሣንታጠብ እግዚአብሔርንና ራሣችንን በመደለል በአስመሣይነት ፀበሉን ብንጠመቅበትም ሆነ ብንረጭ ጥቅም አይሰጥም። እንዲያውም ከበረከት ይልቅ መርገምን ያመጣብናል። በመሆኑም ኅጢአተኛ ሰው ስለበደሉ የጊዜ ቀጠሮ ሣይሰጥ የመዳን ቀን ዛሬ ስለሆነ ባለበት ቦታ ሁኖ ያለምንም ድካምና ውጣ ውረድ ከልብ ለሚያምነውና ለነፍሱ እረኛ አባት አድርጎ ለተቀበለው አባቱ ኅጢቱን መናዘዝ አለበት። በእርግጥ የእኛ ኅጢአት የእግዚአብሔርን ቅድስና አያረክስም። እኛ ግን ንስሐ ሳንገባ በድፍረት የምናደርገው ሁሉ ተጨማሪ ኅጢአት ስለሚሆንብን፤ ወደ ቤተክርስቲያን ለመግባትና ፀበል ለመረጨትም ሆነ ለመጠጣት የሚያስከለክለውን በደላችንን ለይቶ ለማወቅ ሁልጊዜም ቢሆን መምህራንን ወይም የቤተክርስቲያን አባቶችን እንድታማክሩ በእግዚአብሔር ስም አደራ እላችኋለሁ።

የመድኅኔዓለም ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን

ካህኑ ስለ አንድ ሰዉ ወይም ሰለ ብዙ ሰዎች  በሚጸልይበት ጊዜ የክርስትና ስማቸዉን በመጥራት ወይም ዝም ብሎ ሊጸልይ ይችላል  ምከንያቱም ካህኑ ጸሎቱን   ከመጀመሩ በፊት ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ  ስለማን እንደ ሚጸለይ ያውቀዋል አባቶች ካህናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክርስትና ስም መጥራት ሳያስፈልጋቸው ዘወትር ስለ ሁላችንም ይፀልያሉ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ተቀብሎ ጥያቄያቸውን እንደሚፈፅምላቸው በቃሉ አረጋግጧል (ማቴ,16÷19) (ማር,1÷44) ዋናው ምስጢር ግን የሚጸለይለት ሰው በካህኑ ጸሎት ሐጢአቱ እንደሚሠረይለት ማመን ነው። ስለሆነም ካህኑ ንስሀ ስምዎን ቢሳሳቱም ድጋሚ ንሰሃ መግባት አየስፈልጎትም።

ጥያቄ 1 ፦ የንሰሀ አባት ነበረኝ ግን መተው አይጠይቁንም ትምህርትም አያስተምሩንም በታቸው እርቋል ምንድነው ማድረግ ያለብኝ ሌላ ለመያዝ እሳቸውን ማማከር አለብኝ ወይስ መቀየር ነው ያለብኝ ይሄንን ንገሩኝ ጥያቄ 2 ፦ንስሀ አባት እያለን ለሌላ ቄስ ብንናዘዝ ለዚህ መልሰን ንሰሀ መግባት አለብን ?

መልስ (ለጥያቄ #1) ፦ ንስሓ አባት እያለን ሳንሰናበት ወይም እስካሁንም የነበሩንን የንስሓ አባት ምንም አይነት ምክንያት ሳናገኝባቸው በራሳችን ምክንያት ብቻ ተነሳስተን ወደ ሌላ ንስሓ አባት ብንሄድ ስርአተ ቤተክርስቲያን አይፈቅድም። ምክንያቱም ጉዳዩ የነፍስ አባት እስከሆነ ደረስ የነፍስ አባት የመያዛችን ስርአትም አሰራሩ መንፈሳዊ ምሥጢር ስለሆነ የነበሩንን የንስሓ አባት ተሰናብተን ወደ ሌላው ለመሄድ በቂ ምክንያት ሊኖረንና፤ ሌላ አባት የፈለግንበትንም ምክንያት ያለምንም ማፈር ነግረናቸው ተሰናብተን መሄድ መብታችን ነው። ካህኑም በስርአት ካልጠበቁን ለምን ማለት አይችሉም።  (ለጥያቄ #2) ዝም ብሎ ተነስቶ ሳይሰናበት  የሄደ ግን እንደ ስርአተ ቤተክርስቲያን ትክክል ባይሆንም ነገር ግን የሄደውም ወደ ካህን ስለሆነ ይህ ንስሓ የሚያስገባ ጉዳይ አይደለም።

ጥያቄ 3. ፦ የንስሐ አባቶች ለንስሀ ልጆቻቸው  ለምን በደንብ አያስተምሩም ለምንስ አይጠይቁም እኛ ስንጠፋ አይፈልጉም አሁን ለምሳሌ የኛ አሉ እኔ ደውዬ ካልጠየኩኝ አይጠይቁንም እና ለምን እንደዚህ ይሆናል?

መልስ፦ መንፈሳዊ እና ክርስቲያናዊ ህይወታችንን በአባትነት እንዲጠብቁን የያዝናቸው የንስሓ አባት ያደረግናቸው ካህን በራሳቸው ምክንያት እና ስንፍና ምንደኛ ቢሆኑ ማለትም ጠዋት ማታ እየገሰጹ እየመከሩ የማይጠብቁን አና ይበልጥ ወደ መንፈሳዊ አገልገሎት የማያተጉን ከሆነ ለአውሬ ወይም ደግሞ ለነጣቂ ለዲያብሎስ የሚያሰጥ ሰነፍ እረኛ ስለማያስፈልገን ያለምንም ቅድመ ሀኔታ ትጉህ እና ቅን የሆነ ለንስሓ ልጆቹ አገልግሎት ቅድሚያ ሁኔታ የሚሰጥ አባት መያዝ አለብን። በዚህ ጉዳይ ድረድርም ሆነ ማመንታት አያስፈልግም።

መልስ ፦ አባት ያደረግናቸው የንስሓ አባት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ወደ ሌላ አባት ስንሄድ በስርአተ ቤተክርስቲያን ካህኑ በስርአት አሰናብተውን እንዲያሸጋግሩን የኃላፊነት ድርሻ አለባቸው። ያንን የማያደርጉ ከሆነ ግን ከምእመን ይልቅ ካህኑ ስለሆነ ትልቅ ኃላፊነት ያለው፣ በኛ ጉዳይም በቅድሚያ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠየቀው ካህኑ ስለሆነ የሱን ድርሻ ባለመወጣቱ በተሻለ መንፈሳዊ ጥበቃ ሊመራን እና ሊያስተምረን ወደሚችል ካህን ከመሄድ የሚያግደን ስርአት የለም። ስለዚህ ጠያቂያችን አሁን ከጠየቁት እና ከሚያሳስብዎት ጉዳይ ነፃ ስለሆኑ ሌላ አባት ይዘው ከመኖር የሚያግድዎት ሕግ ወይም ስርአት የለም።

መልስ ፦ ማንም ክርስቲያን ባለበት ደብር ወይም አካባቢ ንስሓ አባት እያለው፤ ለሌላ መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ደግሞ ወደ ገዳማት እና ቅዱሳት መካናት ወይም ቦታዎች ሄዶ በዛ ቦታ ላገኛቸው አባት፥ አለኝ የሚለውን አነጋግሮ ወይም ኅጢአቱን ተናዞ አስፈላጊውን የንስሓ ህይወት መቀበል ይችላል። የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይደለም።

ጥያቄ 6 ፦ ሰላም ፤ የሆነ ግዜ ንስሐ ገብቼ ነበር። በጣም ቆይቷል። እና ንስሐ የሰጡኝ አባት ንስሐዬን ከተቀበሉና ማድረግ ያለብኝን ነገር ከነገሩኝ በኋላ ተመልሰሽ ነይ አላሉኝም ነበር፤ ማለት ይፍቱኝ አልተባልኩም። እንደዛ መሆኑንም አሁን ቅርብ ጊዜ ነው ያወቅኩት። እና ድጋሚ ንስሐ መግባት አለብኝ?

ጥያቄ 7 ፦ ሰላም ለእርስዎ ይሁን መምህር ከንስሀ አባቴ ንስሓ ከተቀበልኩ ና ቀኖናየን ከጨረስኩ በሗላ ስትጨርስ እንገናኝ ብለውኝ ነበር ነገር ግን ሳልገናኛቸው ሌላ ቦታ ሄድኩ ምን ባደርግ ይሻለኛል ??  ።።

መልስ ፦ ማንም ክርስቲያን ባለበት ደብር ወይም አካባቢ ንስሓ አባት እያለው፤ ለሌላ መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ደግሞ ወደ ገዳማት እና ቅዱሳት መካናት ወይም ቦታዎች ሄዶ በዛ ቦታ ላገኛቸው አባት፥ አለኝ የሚለውን አነጋግሮ ወይም ኅጢአቱን ተናዞ አስፈላጊውን የንስሓ ህይወት መቀበል ይችላል። የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይደለም።

መልስ ፦ አንድ ከርስቲያን ንስሓ ገብቶ የተሰጠውን ቀኖና ከጨረሰ በኋላ፤ ጊዜ ካለው በአካል፣ ጊዜ ከሌለው ደግሞ በስልክ ወይም በሌላ መገናኛ መንገድ የተሰጠኝን ትእዛዝ ፈጽሜያለሁ ብሎ ሊነግራቸው ይችላል። ይህን ለማድረግ ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግርቢያጋጥመው ግን ፤ ለሰራው ኀጢአት ካሳ ስለከፈለ፣ ከታሰረበትም የኅጢአት ማሰሪያ ስለተፈታ ለፈጣሪው በምስጢር ነግሮ ከዛ በኋላ ከመንፈሳዊ ነገር ላለመራቅ መትጋት አንጂ ወደ አባቴ ተመልሼ ይፍቱኝ ብዬ ስላልተናገርኩኝ ወይም እግዚአብሔር  ይፍታህ ሰላላሉኝ ጥፋት ሊሆንብኝ ይችል ይሆን በማለት ሊያሳስብዎት አይገባም።

መልስ፦ ጠያቂያችን እንዲረዱት የምንፈልገው አንድ ንስሓ የሚገባ ክርስቲያን ከልቡ ተፀፅቶ እና አምኖ የሰራውን ጥፋቱን ለንስሓ አባቱ ከተናገረ በኃላ ንስሓ አባቱ ባመኑበት ነገር እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ንስሓ ይሰጥዎታል። የሚሰጠውም ንስሓ ለሰራው ኀጢአት የተመጣጠነ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ኀላፊነት መውሰድ ያለባቸው የንስሓ አባቱ ናቸው። በእያንዳንዱ የንስሓ አይነት ምን አይነት ቀኖና መስጠት እንዳለባቸው አንቀፀ ንስሓ ያዛል። ስለዚህ በዚህ ነገር ንስሓ የሚቀበለውን ሰው ሊያሳስበው የሚገባ ነገር የለም። ነገር ግን መጠንቀቅ ያለንብን አስቀድመን በእውቀት እና በሃይማኖት የበሰሉ አባቶችን ከመያዙ ላይ ነው።

መልስ፦ ኅጢአት እየፈፀሙ መሆኑን ገልፀው ከዚህ ክፉ ሃሳብ የሚወጠበትን መንገድ እንድናሳይዎት ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ ምላሽ፦

በመጀመሪያ ኅጢአት የሚስማማው ሰው ሆነን በመፈጠራችን ብቻ ጠላታችን ዲያበሎስ ይህንን እንደ ትልቅ ድክመት ቆጥሮብን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የምንታገለውን የፅድቅ ስራ እያስጣለ እሱ ወደሚፈልገው የኅጢአት መንገድ በጎተተን ቁጥር እንደ ደካማ ጎናችን ለያንዳንዳችን የምንወድቅበትን ኅጢአት ያሰራናል። የሰው ልጅ መላ ዘመኑን ለፅድቅ ስራ ከሚያሳልፈው ግዜ ይልቅ ለኅጢአት የሚያውለው ግዜ ብዙ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በኅጢአት ጠፍተን እንዳንቀር ተመልሰን ንስሓ እንድንገባ የሚፈቅድ አምላክ ስለሆነ ለዘመናት ከሰራነው ኅጢአት ይልቅ በተወሰነ የቀኖና ግዜ የሰራነው ፅድቅ ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ጥፋት ፍቆ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት እንድንበቃ ታደርጋለች። 

ስለዚህ ጠያቂያችን በኅጢአት መውደቅ የተለመደ የሰው የስጋ ባህሪ መሆኑን፥ በፅድቅ ወይም በንስሓ መነሳት ግን የክርስቲያን መንፈሳዊ ተጋድሎ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ያሳለፉት የኅጢአትና የነውር ዘመን ምንም እንኳን ሰይጣን ቢፈታተንዎትም፤ እግዚአብሔር ከእርስዎ ህይወት ጨርሶ ስላልራቀ በውስጥዎት ፀፀት እና ወደ እግዚአብሔር መመለስን እያንፀባረቁ በመሆኑ ፈፅሞ ከጠሉት ህይወት ውስጥ እንደሚወጡና እግዚአብሔርም እንደሚረዳዎት እናምናለን። ከዚህ የጠለቀ የኅጢአት ጉድጓድ ውስጥ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት እንዲችሉ በግልዎት ሊያደርጉ የሚገባዎትን ምክር እና ትምህርት እንድንሰጥዎ ደግሞም በአባቶች በኩል እርስዎን ለማዳን መደረግ የሚገባውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማከናወን ይቻል ዘንድ አሁንም በውስጥ መስመራችን ደውለው ቢያገኙን መመካከር እንችላለን በማለት በድጋሚ ለማስታወስ እንወዳለን። ።

መጀመሪያ ንስሐ አባት ለመቀየር ያሰቡበት መንገድ መታወቅ አለበት ወይም ደግሞ ግልፅ መሆን አለበት። ምክንያቱ የቦታ ርቀት ከሆነ፣ ወይም ግዜ ሰጥተው የማያስተምሩ፣ የማይመክሩ ከሆነ፣ ዘወትር ክትትል እያደረጉ የማይጠብቅዎ ከሆነና ይሄን በመሰለ በቂ ምክንያት መቀየር ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ግን ስላልፈለግኩኝ በሚል ሰበብ እንደ ምድራዊ ፍላጎት መንፈሳዊ አባትን ብዙም መቀያየሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንመክርዎታለን። በበቂ ምከንያት አባት ተሰናብቶ ሌላ ይመክሩኛል፣ ያስተምሩኛል፣ በሃይማኖት እና በስነምግባር ያበረቱኛል ብለው ያሰቡትን አባት በማነጋገር በቤተክርስቲያን ስርአት መሠረት አባት ማድረግ ይችላሉ። ከንስሐ አባትዎ እንዴት እነደሚሰናበቱና እንዴት ሌላ ንስሐ አባት እንደሚይዙ የንስሐ አባቶችን እንጂ እርስዎን ስለማይመለከትዎ አያሳስብዎትም።

በመሰረቱ ቀኖና ወይም ንስሐ የሚሰጠን በፈጸምነው ኅጥያት መጠን ተለክቶ ስለሆነ እያንዳንዱ ያጠፋነውን ጥፋት ከባድም ቢሆን ሳንፈራ፤ ቀላልም ቢሆን ሳንንቅ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለነፍሳችን እረኛ ላደረግነው ካህን መናገር እንዳለብን የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል። የኅጥያት ደረጃችን ተለይቶ ሲታወቅ ንስሐ የሚሰጡን አባቶችም በጥፋታችን መጠን ስለሆነ ንስሓ ላልገቡበት ኅጥያት እንደገና መናገርና ቀኖና መቀበል ያስፈልጎታል። 

በቅድሚያ ስለኀጢአታችን ስናስብ ትክክለኛ ሃሳብ የሚሆነው ኀጢአትን ማፈር ያለብን ስንሰራው እንጂ ስንናገረው መሆን የለበትም። እሱማ እንደ እውነቱ ካሰብነው ከኀጢአት የበለጠ ምንስ የሚያሳፍር ነገር አለ። ምክንያቱም እግዚአብሔር አሳምሮ አክብሮ ቀድሶ የፈጠረውን አካላችን በቅድስና እንዲኖር ተፈጥሮ ሳለ እራሳችንን መግዛት አቅቶን ብናደርገው ምንም ላይጠቅመን፣ ባናደርገውም የሚቀርብን ነገር ላይኖር ያው ጠላታችን ዲያብሎስ በመራን የጥፋት መንገድ ሄደን ኀጢአት ስንሰራ ለጊዜው የጠቀመን ወይም የተደሰትንበት ቢመስልም ነገር ግን ንፁህ የሆነው የቅድስና ልብሳችንን በኀጢአት እድፍ ቆሽሾ ስናየው እኛንም አንገት የሚያስደፋ በእግዚአብሔር ፊትም የሚያሳፍር ነውር ነው። ይሁን እንጂ ኀጢአት ባንሰራው መልካም ሆኖ ሳለ ከሰራነው ግን የመጨረሻ አማራጫችንና ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት መንገድ ንስሓ ነውና የነፍስ እረኛ እንዲሆኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የክህነት ስልጣን የተሰጣቸው አባቶች ካህናት ስለሆኑ ጠያቂያችን ለንስሓ አባቶ ኀጢአቶን ተናዘው ቀኖናዎትን መውሰድ አለቦት። ያን ግዜ በግል ኑሮዎትም በማህበራዊ ህይወቶትም ያለው ግንኙነት ሰላም ይሆንልዎታል፤ የተረጋጋ መንፈስም ይኖርዎታል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፀጋና ሰላም ከእርስዎ ጋር ስለሚሆን። የንስሓ አባቴን ቀርቤ ለማማከር አፈርኩ ላሉት፥ እንደ ቤተክርስትያናችን ስርዓት ከሆነ በእርስዎ እና በንስሓ አባትዎ መካከል ለመናገር እሚያሳፍርም ሆነ የማይነገር ምስጢር መኖር የለበትም። እማትታየውን ረቂቋን ነፍስ በኃላፊነት የተሰጠው ካህን ስለሆነ ለመናገር መድፈር አለብዎት እንላለን። ከዚህ ሌላ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ወይም እኛ ያልተረዳንዎት ጉዳይ ካለ መፍትሄ እንድንሰጥዎት በውስጥ መስመር የግኙን።

ጠያቂያችን በመጀመሪያ ንሰሐ መግባት ወይም ኀጥያታችንን መናዘዝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መንፈሳዊ ትርጉሙን እና ሚስጥሩን በማስተዋል እና በትእግስት ሆነው መረዳት ያሰፈልጋል። እስካሁን ስለ ንሰሐ በ ዩሐንስ ንስሐ ድረ ገፃችን ላይ ባሰፈርናቸው ፅሁፎች በቂ የግንዛቤ መልእክት እንዳስተላለፍን ተስፋ እናደርጋለን። የእርሶም ጥያቄ እስካሁን ከፃፍናቸው መልእክቶች ጋር አብሮ የሚያያዝ ቢሆንም፤ ነገር ግን ለመረዳት መጠየቅ ከምንም በላይ የሚበረታታ በመሆኑ ለእውነተኛ ንስሐ ህሊናዎትን በማሳመን ተፀፅቻለው፣ ንሰሐ ገብቻለሁ፣ ኅጥያቴን ተናዝዣለሁ ብሎ ማመን የሚቻለው ለንስሐ የሚያበቁ መስፈርቶች እና ቅደም ተከተሎች ተጠብቀው ማለትም ፦

1/  የተሰራውን ኅጥያት ጥፋት መሆኑን ማመን ፣

2/  ስለተሰራው ጥፋት ከልብ ተፀፅቶ ንሰሐ ለመግባት መዘጋጀት፣

3/  ወደ ንስሐ አባታችን በማምራት ኅጥያታችንን በመናዘዝ ንስሐ መቀበል፣

4/  የተሰጠንን ንስሐ በአግባቡ መፈጸም፣

5/ ዳግመኛ ኅጥያት ላለመስራት በአባቶች ትምህርትና በመንፈሳዊ አገልግሎት መፅናት፣

6/  በፆም፣ በፀሎት፣ በስግደት ዘወትር በመትጋት መንፈሳዊ ህይወትን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር ያስፈልጋል።

በዚህ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ስንበረታ ከግዜ ወደ ግዜ መንፈሳዊ ፀጋችን እያደገ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ ጋር ሲሆን፤ ለንስሐ እንዳንዘጋጅና ከልባችን እንዳንፀፀት ዘወትር የሚቃወመንን እና ሠይጣናዊ አዚም የሚጥልብን ክፉ መንፈስ ከዛ ርቆ ለመሄድ ይገደዳል። በአጠቃላይ መንፈሳዊ ፀጋ በሂደት እና በመንፈሳዊ ተጋድሎ የሚመጣ እንጂ በአንድ ግዜ የማይሆን ስለሆነ አባቶቻችንን በማማከር መንፈሳዊ ጉዞዎን በትእግስት እንዲቀጥሉ እንመክራለን። ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያትም ለሁለተኛ ጊዜ ደግመው መናዘዝ አያስፈልግዎትም።

የንስሐ አባት ይዘው እንደማያውቁና ንሰሐ ለመግባት ፍላጎት እያለዎት ወደ እግዚአብሔርም ለመመለስ እያሰቡ በማያዉቁት ምክንያት የፈለጉትንና የተመኙትን የንስሐ ህይወት ለመፈፀም እንዳልቻሉ በመግለፅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለጠየቁን አባላችን የሚከተለውን የምክር አገልግሎት እንዲደርስዎት አድርገናል።

እንደ ቅዱስ መፅሐፍ አስተምሮ ማንኛውም ክርስቲያን በ 40 እና በ80 ቀን የእግዚአብሔር ልጅ ከሆኑበት ቀን ጀምሮ ከእግዚአብሔር ቤት እና ከምክረ ካህን መለየት እንደሌለባቸው ይደነግጋል። በመፅሐፍ ቅዱስም ሆነ በሌሎች የሃይማኖታችን መፃህፍት እንደምንረዳው የሰው ልጅ ለመኖር ለስጋው ምግብ ፣ ልብስ ፣ መጠለያ ወዘተ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለነፍሱም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጉታል። የነፍስ ምግብ ማለት በተዋህዶ ሃይማኖት ፀንቶ መኖር፣ ንሰሐ መግባት፣ መፆም፣ መፀለይ፣ መስገድ፣ ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ መሳለም፣ አስራት በኩራት ማውጣት፣ ለነዳያን ምፅዋት (ቸርነት) ማድረግ፣ በህመምና በእስር ቤት ያሉትን መጎብኘት፣ የእለት ማስቀደሻ ላጡ አብያተ ክርስቲያናት ንዋየ ቅዱሳት ማሟላት፣ የጌታን ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ባጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስነምግባር ተወስኖ መኖር የማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ ጠያቂያችን መንፈሳዊ ሆኖ መቀጠልን እየወደዱ ወደ አስቡት በጎ ምኞት እንዳይገቡ የሚያከላክልዎት የበጎ ነገር ጠላት የሆነው ክፉ መንፈስ እየተቃወምዎት በመሆኑ መሠረታዊ የአባቶች ምክር እና በፀሎት የሚሆን የንስሐ ጥሪ ያስፈልግዎታል። በፅሁፍ በሚደርስ መልእክት ብቻ  ከገቡበት ፈተና መውጣት ስለማይችሉ ስለእርስዎ በአባቶች በኩል ፀሎት ያስፈልግዎታል። እራስዎም የሚፀልዩበት የግል እና የስግደት ፆም ወዘተ ያስፈልግዎታል። ከፈተና ሊወጡ እንዲችሉ የሚያበቃዎትን የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‘ነገር ግን ወደ ንሰሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወድዶ ስለእናንተ ይታገሳል። በማለት እግዚአብሔር የእኛን ወደ ንስሐ መመለስ በትእግስት እንደሚጠብቀን አረጋግጧል። (ጴጥ 3፥9) 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በአቴንስ ከተማ ለሚኖሩ የግሪክ ሰዎች ።”እንግዲህ እግዚአብሔር የቀድሞውንስ ያለማወቅ ዘመን አሳልፎታል (በኀጥያት የመኖር ዘመንን) ፤ ዛሬ ግን በመላው አለም ንስሐ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዟል። (የሐዋ 17፥30)

ነብዩ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር የሰውን  ሞት የማይወድ እና ሰው ወደ ንስሐ መመለሱን የሚወድ መሆኑን ሲናገር ”ንሰሐ ግቡ፤ ኀጥያትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኀጥያታችሁ ሁሉ ተመለሱ። የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ። አዲስ ልብ እና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ ..ስለምን ትሞታላችሁ የሟችን ሞት አልፈቅድምና  ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ ተመለሱ እና በህይወት ኑሩ።  (ሕዝ 18፥30-32)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በበዓለ ሃምሰ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ሰወች ሁሉ ዘለአለማዊ ህይወት እንዲቀርቡ የንስሐ ጥሪ ሲያቀብላቸዉ ”እንግዲህ  ከጌታ ፊት የመፅናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ …ኀጥያታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንሰሐ ግቡ ተመለሱም” በማለት አስተምሯል። (የሐዋ 3፥19-20)

ነብዩ ሚልክያስም “ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት ሰው በንሰሐ ሲመለሰ እግዚአብሔርም ይቅር እንደሚል ተናግሯል። (ሚል 3፥7)

ነብዩ እዩኤልም ” አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍፁም ልባችሁ በፆም በለቅሶና  በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ ልባችሁን  እንጂ ልብሳችኹን አትቅደዱ መሓሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔር ፤ ቁጣው የዘገየ ምህረቱም የበዛ ለክፋትም የተፀፀተ ነዉና ወደ እርሱ ተመለሱ” በማለት  የእግዚአብሔርን መሓሪነት እና ቸርነት ይቅር ባይነትንም አስተምሯል። 

ብርሃናተ አለም ቅዱስ ጳውሎስም የሰው ልጅ ከጥፋቱ ተፀፅቶ ወደ ንሰሐ ህይወት እንዳይመለስና ለማድረግ የፈለገዉን በጎ ስራ እንዳይፈፅም ርኩስ መንፈስ እንዴት እንደሚቃወመው ሲናገር “እኔ ግን የኃጢያት በታች ልሆን ተሽጫለሁ…የማደርገውን አላዉቅምና፤ ያንኑ የምጠላውን ብቻ አደርጋለሁና፤ ዳሩ ግን የምወደውን እሱን አላደርገውም፤ የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ…ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም በእኔ የሚያድረው ኀጥያት ነዉ እንጂ” በማለት በአገልግሎት የደረሰበትን የመንፈስ ዉግያ ምሳሌ በማድረግ መክሮናል። ( ሮሜ 7፥14-47)

በመጨረሻም የንስሐ ህይወት ለአንድ ክርስቲያን ቋሚና አስፈላጊ ተግባር ስለሆነ ከልብ በሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ይኸን አጭር መልእክት ደጋግማችሁ እንድታነቡና በተጨማሪ መረጃ ስትፈልጉም በዉስጥ መስመር ማግኘት የምትችሉ መሆኑን አበክሬ እመክራለሁ። 

ከሁሉ አስቀድሞ እንዲረዱት የሚያስፈልገው ማንኛውም ሰው ኀጥያት ሰርቶ ንስሐ ከገባ በኋላ ተመልሶ በኀጥያት መሰናከል የተለመደ ስጋዊ ተፈጥሮ ነው። ምንም እንኳን የኛ አምላክ መድኃንያለም ስለኛ ኀጥያት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ሞትና መቃብርን ሽሮ ነፃ ቢያወጣንም፤ ሰው ግን ከጠላቱ ከዲያብሎስ በየጊዜው በሚጠመድበት የኀጥያት ወጥመድ እየተያዘ፣ እግዚአብሔር ስለኛ ያደረገውን ውለታም በመዘንጋት በደል ቢፈጽምም እንኳን ቸርና መሃሪ የሆነ አምላካችን ግን አሁንም በንስሐ ወደ እሱ እንድንመለስ መንገድ ሰጥቶናል።

በዚሁ መሰረት ከሰይጣን ጋር ያለን ውግያ የማይቋረጥ ስለሆነ አንድ ግዜ ስንወድቅ፣ አንድ ግዜ ስንነሳ የምንቀጥልበት አለም የፈተና ጊዜ ስለሆነ በእርስዎ ብቻ የደረሰ አድርገው ተስፋ መቁረጥ የለቦትም። ኀጥያት ለሰው ልጅ ሞትን የሚያስከትል ክፉ ደዌ ቢሆንም ንስሐ ደግሞ የሚፈውስ መድሀኒት ነው። ስለሆነም አብዝቶ መፀለይ፣ መፆም፣ ንስሐ መግባት፣ በአጠቃላይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምህረት መጠየቅ ክርስቲያናዊ ፀባይ መሆን አለበት።

ከዚህ በላይ የተቸገሩበት ነገር ካለ በውስጥ መስመር ስልክ እንዲደርስዎ አድርገናልና ደውለው ቢያሳውቁን ምክራችንን እና ከፈተና የሚወጡበትን መንገድ እናሳይዎታለን፣ በአባቶች ዘንድም በፀሎት እንዲታሰቡ ይደረጋል።

መጀመሪያ ንስሐ አባት ለመቀየር ያሰቡበት መንገድ መታወቅ አለበት ወይም ደግሞ ግልፅ መሆን አለበት። ምክንያቱ የቦታ ርቀት ከሆነ፣ ወይም ግዜ ሰጥተው የማያስተምሩ፣ የማይመክሩ ከሆነ፣ ዘወትር ክትትል እያደረጉ የማይጠብቅዎ ከሆነና ይሄን በመሰለ በቂ ምክንያት መቀየር ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ግን ስላልፈለግኩኝ በሚል ሰበብ እንደ ምድራዊ ፍላጎት መንፈሳዊ አባትን ብዙም መቀያየሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንመክርዎታለን። በበቂ ምከንያት አባት ተሰናብቶ ሌላ ይመክሩኛል፣ ያስተምሩኛል፣ በሃይማኖት እና በስነምግባር ያበረቱኛል ብለው ያሰቡትን አባት በማነጋገር በቤተክርስቲያን ስርአት መሠረት አባት ማድረግ ይችላሉ። ከንስሐ አባትዎ እንዴት እነደሚሰናበቱና እንዴት ሌላ ንስሐ አባት እንደሚይዙ የንስሐ አባቶችን እንጂ እርስዎን ስለማይመለከትዎ አያሳስብዎትም።

ስለሰራነው ጥፋት የንስሓ ካሳ ልንከፍል ወይም ደሞ የፈፀምነውን በደል ሊየስፍቅልን የሚችለው ንስሓ ብቻ ስለሆነ ለካህን በመናገር ንስሓ መግባት ያስፈልግዎታል። የቃል ኪዳን ቦታ ያሉት ለቅዱሳን የተሰጣቸው ፀጋ ልዩ ልዩ ስለሆነ በቃልኪዳን ቦታ ስንሄድ እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት የምናገኘውን በረከት እሱ ብቻ ነው የሚያውቅ እንጂ በግላችን በሰራነው ኀጢአት የቃልኪዳን ቦታ ሄደናልና ኀጢአታችን ሊፋቅልን ይችላል ማለት አንችልም።

እርሰዎ የሚያውቁት እና ከልብ ያልፋቁት ኀጢአት ካለ ወይም ለንሰሓ ያልበቁበት ኀጢአት ካለ ለንሰሓ አባትዎ ተናግረው ቀኖና መቀበል ያስፈልጋል ። ከዚህም በላይ ክርስቲያን ኀጢአቱን አምኖ ለንስሐ አባቱ መንገር ማለት ከልብ ተጸጽቶ ኀጥአትን ተጸይፎ እጁን ለፈጣሪው መስጠቱን የሚገልጽበት መንፈሳዊ መንገድ ነው። ከምንም በላይ ውስጣችን ከሚዋጋን ኀጢአት ነጻ ይሆን ዘንድ ዘወትር ትግላችን ከረቂቅ መናፍስት ጋር ነው። ስለዚህ በዚህ አይነት መንፈሳዊ ስርአት ኀጢአት ከተናዘዝን በኋላ በእግዚአብሔርም ቤት አየተመላለስን ከምህረት አደባባዩ እንዳልተለየን እያወቅን ሰይጣን ከፉ መንፈስ ባደረባቸው ሰዎች ላይ በሚለፈልፈው እና በሚያቃዠው ቀዠት ኀጢአታችን አልተፋቀልንም ማለት አንችልም። የብዙ ሰዎች ችግራችን ምልክት ፈላጊዎች ነን። በሌላም መልኩ ሲጀመር ሰይጣን የሀሰት አባት ስለሆነ ከሰይጣን ምን አይነት እውነት ይጠበቃል? እሱ በተናገረው የሀሰት ቃል ካመንን የእግዚአብሔርንስ እንዴት እንሆናለን? ስለዚህ ይሄ እንዳያሳስብዎት አይምሮዎትን ነፃ ያድርጉ። ይልቁን ከሚያጨናንቅዎት መንፈስ ወጥተው ቸርነትና ምህረቱ ብዙ የሆነ አምላክ ስለ እኛ ያለው ፍቅርም ወሰንና ገደብ የለውምና እንደኛ ኀጢአትና በደል ሳይሆን እንዳንተ ምህረት እና ቸርነት አስበኝ እያሉ በዘወትር ጸሎት ይጠይቁት።

ወንድ የወለደች አንድ ሱባዔ (7ቀን) ፤ ሴት የወለደች (14 ቀን) ፀበል እስከምትረጭ ማንም ሰው ወደ እርሷ አይገባም እንጂ ከንስሓ መግባት ጋር ወይም ደግሞ የወለደችጋ በመግባታችን ወይም በመጠየቃችን ንስሓ የሚያስገባ ኀጢአት መሆኑ አይደለም። አራሷም ብትሆን በወለደች ጊዜ ክርስትናዋን አጥታለች ማለት አይደለም። እሰከ 7 ወይም እሰከ 14 ቀን ድረስ የተፈጥሮ ልማድ ለሰውነቷ እርኩሰት ስላመጣባት ማንም ሰው በዛን ሰአት ወደሷ መቅረብ እንደሌለበት ነብዩ ሙሴ በኦሪት ዘሌላዉያን ላይ ስለደነገገው ከዚያው ጋር ተያይዞ የመጣ ስርአት ነው። (ዘሌ 12፥1-8)

መልስ፦ ከንስሓ በኋላ ምን ላድርግ ብለው ለጠየቁን አባላችን፦ አንድ ክርስቲያን በኅጢአት የጎደፈውን ሰውነቱን ከታጠበ በኋላ መላ ህይወቱ ንፁህ ስለሆነ ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት መንገዱ ሁሉ ቀና ስለሆነ ማድረግ ያለበት ምን እንደሆነ ከዚህ በፊት በተጠየቅነው ሃሳብ ተነስተን ምላሽ የሰጠንበት ቢሆንም አላማችን ምእመናንን ማገልገል እስከሆነ ድረስ አሁንም ጠያቂያችን ከንስሓ በኋላ ምን መሆን እንዳለብዎት የምናስረዳዎት፦

 

1ኛ/ ከምንም በላይ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎትን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ፣

 

2ኛ/ እግዚአብሔር ቢፈቅድልዎት በቅዱስ ቁርባን መወሰን፣ አቅምዎት በሚፈቅደው መጠን ሳያቋርጡ እና ሳይሰለቹ መፆም፣ መፀለይ፣ እና መስገድ፣

 

3ኛ/ በአቅምዎት ከሚያገኙት ነገር ለድሆችና ለእግዚአብሔር የሚገባውን አስራተ በኩራት ማዋጣት፣

 

4ኛ/ ዘወትር ከአባቶች ምክር እና መታዘዝ አለመራቅ፣ በፕሮግራም ወደ ቤተክርስቲያን እየቀረቡ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣

 

5ኛ ሁሌ እንደቅርብ አስተማሪና መካሪ ሁነው የሚያገለግሎትን መንፈሳዊያን መፃህፍትን ማንበብ፣ ከዚህም በላይ በኑሮዎት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ በማህበራዊ ጉዳይ ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር በትዕግስት እና በጥበብ ለመኖር ድርሻዎትን መወጣት።

 

እነዚህን ሁሉ እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ነገሮችን አጠቃሎ ለመስራት የሚቻለው ሰው ህይወቱ በንስሓ ሲታደስ ስለሆነ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእርስዎን ህይወት በንፅህና በቅድስና እንደሚጠብቃት በማመን ከዚህ በላይ የተሰጠዎትን መንፈሳዊ ምክር በስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ እግዚአብሔር ይርዳዎት።

የንስሐ ሱባኤ ከተሰጣቸው በኋላ ንስሐቸውን ሳይጨርሱ የወር አበባ ቢመጣባቸው፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈፀም ንስሐ ከሆነ ወይም ደግሞ ወደ ገዳም ሄደው የሚፈፀም ከሆነ በዚህ ወቅት መቅረብ ስለማይቻል ባሉበት ቦታ ሆነው መፆምና መስገድ ይችላሉ። በቀኖና ቤተክርስቲያን እንደተወሰነው በተወሰነ ርቀት ላይ ቆመው መንፈሳዊ ስርአቱን መከታተል የችላሉ። 

የንስሐ ሱባኤ ከተሰጣቸው በኋላ ንስሐቸውን ሳይጨርሱ የወር አበባ ቢመጣባቸው፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈፀም ንስሐ ከሆነ ወይም ደግሞ ወደ ገዳም ሄደው የሚፈፀም ከሆነ በዚህ ወቅት መቅረብ ስለማይቻል ባሉበት ቦታ ሆነው መፆምና መስገድ ይችላሉ። በቀኖና ቤተክርስቲያን እንደተወሰነው በተወሰነ ርቀት ላይ ቆመው መንፈሳዊ ስርአቱን መከታተል የችላሉ። 

መልስ፦  አንድ ክርስቲያን የተፈፀመውን በደል በራሱ ግዜ አምኖ ተፀፅቶ ንስሓ ገብቶ በቀኖና ላይ እያለ ይባስ ብሎ የተሰጠውንም ቀኖና ሳይፈፅም ወደፊት ኅጢአት ላለመስራት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ ሌላ በደል ከፈፀመ ሰውነቱን የተቆራኘው የኀጢአት ደዌ ብሶበታል ማለት ነው። እጅግ ህይወቱ አሳዛኝ ቢሆንም ስለአድን ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ተስፋ ሳይቆረጥ ይሄን ሰው በተለያየ መንገድ የንስሓ አባቱ ወይም ሌላም አባት በቅርብ ውስጣዊ ችግሩን ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስሓ ህይወት እንዲቀርብ እና በተደጋጋሚ ከተፈተነበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አቤቱ ወንድሜ ምን ያህል ቢበድለኝ ምን ያህል ይቅር ልበለው እስከ 7 ጊዜ ነውን ብሎ በጠየቀው ጊዜ እስከ 7 አልልህም 7ቱን አንድ እያልክ እስከ 70 ነው እንጂ” በማለት ለኅጢአት ይቅርታ የጊዜ እና የቁጥር ገደብ እንደሌለው አረጋግጦልናል። (ማቴ 18፥21-22)
ስለዚህ በዚህ መሠረት ከኅጢያት ደዌ እስካልተፈወሱ ድረስ የንስሓ ህይወት አይቋረጥም ይቀጥላል እንጂ።
መልስ፦ በድረገፃችን ላይ የሰጠናችሁ የንስሓ አባቶች እንዲካተቱ ያደረግነው በግልፅ አላማው ተነግሯቸው በመሆኑ ለማገልገል ፈቃደኛ ናቸው። በዚህ ጉዳይ  የተቸገሩበት ነገር ካለ እንድንረዳዎት በውስጥ መስመር ያሳውቁን።  
መልስ ፦ በዮሐንስ ድረገፅ እና ቴሌግራም ቻናል ውስጥ በተከታታይ ወደ እናንተ የምናደርሳቸው የሃይማኖት ትምህርቶች እንዲሁም ከአባላቱ የቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በየቀኑ የምንሰጣቸው ምላሾች ወደእናንተ ደርሰው እንደምትመለከቷቸው እና ጠቃሚ የሆነ የሃይማኖት ትምህርት እንደምታገኙባቸው እናምናለን። በመሰረቱ በእግዚአብሔር መንገድ የመጣ ሰው የእግዚአብሔርን ስራ ይሰራል፥ በወንጌል እንደተፃፈው ከመልካም ዛፍ የሚለቀም ጣፋጭ ፍሬ ነው፥ ከክፉ ዛፍ ደሞ የሚለቀም መራራ ፍሬ ነው። ከዚህ የተነሳ ጣፋጩን እና መራራውን ፍሬ መለየት የሚቻለው እግዚአብሔር በሰጠን የተፈጥሮ ስሜት በማጣጣም ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ምናልባት ምን እንዳሳሰብዎት ግልፅ ባይሆንም እስካሁን ድረስም በዚህ ፕሮግራም ያስተላለፍናቸው መልዕክቶች የሰውን ልጅ ከነፍስ ሞት ለመታደግ አስበን እና ምርኮ ለማትረፍ እግዚአብሔር በሰጠን ትንሽ የእውቀት ፀጋ ከእናንተ ጋር በዚህ እግዚአብሔር በሚወደው መልካም ፕሮግራም ወስነን የገባንበት የውዴታ መንፈሳዊ ግዴታ ስለሆነ እንጂ በሌላ በምንም አይነት የስጋዊ ጥቅም የሚለካ አንዳች ነገር የለም። 
የክርስቲያን ወገኖቻችን አስረግጠን እውነቱን የምንነግራችሁ በዚህ አላማችን ውስጥ የመናፍቅነት፣ የክህደት፣ የስነምግባር ችግሮች ቦታ እንዳይኖራቸው ሰይጣንን ከብዙ ህይወት ውስጥ ሳይወድ በግድ ታግለን በእግዚአብሔር ሃይል እና ጥበብ ለመለየት በዘመኑ የሰለጠነውን የኀጢአት እና የክፋት መንገድ አስቀርተን ሁላችሁም የዘላለም ህይወት እንድታገኙ እስካሁንም ብዙ ተጉዘናል ወደፊትም እግዚአብሔር ከኛ ጋር እስከሆነ ድረስ የሚያቆመን ነገር የለም።
በመሆኑም ማንኛውም ክርስቲያን ጭንቀትን አስወግዶ በፕሮግራማችን በእግዚአብሔር ቸርነት እየታገዘ እንዲቀጥል እናቱ ወላዲት አምላክ እና ቅዱሳን በፀሎታቸውና በምልጃቸው እንዲያግዙን ከዚህ በላይ መንፈሳዊ ትርፍ እንድናገኝበት እንዲሁም የአውሬው መንፈስ ከሰለጠነበት ከዚህ ዘመን አሰቃቂ ፈተና እና መከራ ለመውጣት እንድንችል የእናንተ ድርሻ መሆን ያለበት በሃሳብ፣ በፀሎት በሌላም አስፈላጊ በሆነው ምክረ ሃሳብ እየተረዳዱ፥ አንዱ አንዱን እያበረታው፣ አንዱ አንዱን እያገዘው መቀጠል የምንችልበትን ሃሳብ እያሳደጉ መምጣት እንጂ ስለነገው እግዚአብሔር ያስባልና ምን የፈጠር ይሆን? ምን ይመጣ ይሆን? ምን ያጋጥማችሁ ይሆን? ማለት የኛ ድርሻ አይደለም። ስለዚህ በምንሰጠው አገልግሎት ደስ እያላችሁ እየተከታተላችሁ በነፍሳችሁም እረፍት ታገኙ ዘንድ ይህን መልዕክት አስተላልፈናል።
መልስ፦ አሁንም ለአባላቶቻችን  አጥብቀን የምንነግራችሁ ከሁሉ በፊት መታዘዝን ማስቀደም ያስፈልጋል እንደመንፈሳዊነት ስንኖርም ሁሉን ነገር ለበጎ ነው ብለን በእግዚአብሔር አሰራር ወይም በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ጊዜያዊ እና ወቅታዊ የሚባል ነገር ትርጉም አልባ ነው። ስለዚህ አባቶቻችን እኛን ለመጠበቅ ወይም እኛን ለመምከር እና እኛን ወደ መንፈሳዊ ህይወት ለመመለስ ሁል ግዜ እንደወታደር በተጠንቀቅ ቆመው ሊያገለግሉ የተዘጋጁ ናቸው። እኛ በአለም ስንኖር ስፍር ቁጥር የሌለው ጣጣ ስላለን ካንዱ አገር ወደ አንዱ አገር፣ ካንዱ ሃሳብ ወደ ሌላው ሃሳብ እየተንከራተትን ስለምንባዝን በያለንበትና በየደረስንበት ሁሉ ያለጠባቂ አንድ ቀንም እንዳናድር ባላችሁበት ቦተ ሁናችሁ በቅርብ ቦታ አባት ብታጡ እንኳን በርቀት ያሉትን አባት የመንፈስ ግንኙነትን የቦታ እርቀት ስለማይከለክለው በርቀት ንስሓ አባት እንድትይዙ ሁኔታዎችን ያመቻቸንላችሁ ለእናንተው በመጨነቅና በማሰብ ነው።
ስለዚህ ይሄን ጥርጣሬ እና ስጋትዎን አርቀው የመዳን ቀን አሁን ነውና አሁኑኑ ፈጥነው የተመደበልዎትን አባት ያናግሩ። ያገጠምዎት ችግር ካለ በውስጥ መስመር ያነጋግሩን። መዳን የጋራ ስለሆነ አገልግሎቱን የግዴታ ማድረግ አያስፈልግም።

መልስ፦ ንስሓ በስልክ ይቻላል ወይ ብለው ለጠየቁን ከዚህ በፊት ይህንን በሚመለከት ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦልን ስለነበር ተገቢውን መልስ ሰጥተንበታል። ጠያቂያችን ማወቅ ያለብዎት በስልክም ይሁን በአካልም ይሁን በሌላም መገናኛ መንገድ ይሁን ዋነኛው አላማው የሰራነውን በደላችንን እና ኀጢአታችንን በንስሓ ማጥፋት ነው። ስለዚህ በአካባቢዎ ካህን ማግኘት የማይችሉ ከሆነ በራስዎትም ሆነ በሚያምኑት ሰው በኩል ያገኙዋቸውን እውነተኛ ካህን፤ ወይም በድረገፃችን ላይ ካሉ አባቶች ንስሓ አባት በማድረግ ባሉበት ቦታ ሁነው በስልክም ይሁን በሌላ መገናኛ መንገድ ንስሓ መግባትና ተግሳፅና ምክርንም ማግኘት ይችላሉ።  በይበልጥም እንዲረዱት ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን ምላሽ እንደሚከተለው በድጋሚ ልከንልዎታል።   
“ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ (አማኝ) የሆነ ክርስቲያን ለአካለ መጠን ከደረሰበት ግዜ ጀምሮ የንስሐ አባት መያዝ ክርስትያናዊ ግዴታው እንደሆነ በቤተክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን ኑሮዋቸውን ለማሸነፍና የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ሲሉ ቤተክርስቲያንና ካህናት አባቶች ወደማይገኙበት ክፍለ ዓለም በልዩ ልዩ ምክንያት ተበትነው እንደሚኖሩ ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ አገራችን ሳይቀር በረሃማና ጠረፋማ በሆነ አካባቢ እንዲሁም አህዛብ በሚበዛበት ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በመከራና በፈተና ግዜ የሚያጽናናቸውና የሚመክራቸው አባት ሊያገኙ አይችሉም። የሚጸልዩበት እና ፈጣሪያቸውን የሚማፀኑበት ቤተክርስትያንም አያገኙም። 

ስለዚህ በቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ሰውን በነፍስ የማዳን ሥራ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ቤተክርስቲያንና አባቶች ካህናት በቅርብ የማይገኙበት ክፍለ ዓለም (አካበቢ) የሚኖሩ ማለትም በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በአረብ አገሮች እና በሌላውም ክፍለ አለም ሁሉ እየኖሩ የንስሐ አባት ለመያዝ ቢፈልጉ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የኛን የውስጥ ችግር ያውቀዋልና አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ያለ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌለበት የንስሐ አባት እንዲኖረው በሃይማኖቱና በመንፈሳዊ ህይወቱ የመረጠውን ካህን እርቀት ሳይገድበው መያዝ ይችላል። ካለው ችግር አንፃርም በስልክ እና በሌላ መልእክት በመገናኘት መንፈሳዊ ትምህርት እና ከንስሐ አባት የሚሰጠውን የንስሃ ቀኖና  መቀበል ይችላል። ማንኛውንም በጎ ስራ ሁሉ አባቱ የሚመክሩትን እና የሚያዙትን ሁሉ በመፈፀም የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ስለሚችል የግድ በአካል ካላገኘኋቸው አብሬ በአንድ አጥቢያ ካልኖርኩኝ የንስሐ አባት መያዝ አልችልም በሚል ምክንያት ያለጠባቂ መኖር የለበትም።
ይህን በሚመለከትም ከዚህ በፊት ስለ ንስሐ አባት አያያዝ ጥያቄ ቀርቦ በአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እና በቤተክርስትያን መምህራን ንስሐ አባት በርቀት መያዝ እንደሚቻል በተደጋጋሚ ምላሽ የተሰጠበት ሃሳብ ስለሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲያሥሩና እንዲፈቱ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ጊዜና የቦታ ርቀት የማይወስነው ስለሆነ በአካባቢው አባት የሚሆን ካህን ከጠፋ ያለጠባቂ ብንኖር ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍሳችንን እንዳይነጥቃት የንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ምእመናን መጨናነቅ እንደማያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።”

በተጨማሪም፤ ስለንስሓ ትምህርት በድረገፃችን ላይ የተላለፉና እየተላለፉ ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች ይህን ሊንክ በመጫን ያንብቡ።

ትምህርት ስለ ንስሓ – https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ/

የንስሓ አባት ገጽ – https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/

መልስ፦ ኅጢአት እየፈፀሙ መሆኑን ገልፀው ከዚህ ክፉ ሃሳብ የሚወጡበትን መንገድ እንድናሳይዎት ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ ምላሽ፦
 
በመጀመሪያ ኅጢአት የሚስማማው ሰው ሆነን በመፈጠራችን ብቻ ጠላታችን ዲያበሎስ ይህንን እንደ ትልቅ ድክመት ቆጥሮብን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የምንታገለውን የፅድቅ ስራ እያስጣለ እሱ ወደሚፈልገው የኅጢአት መንገድ በጎተተን ቁጥር እንደ ደካማ ጎናችን ለያንዳንዳችን የምንወድቅበትን ኅጢአት ያሰራናል። የሰው ልጅ መላ ዘመኑን ለፅድቅ ስራ ከሚያሳልፈው ግዜ ይልቅ ለኅጢአት የሚያውለው ግዜ ብዙ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በኅጢአት ጠፍተን እንዳንቀር ተመልሰን ንስሓ እንድንገባ የሚፈቅድ አምላክ ስለሆነ ለዘመናት ከሰራነው ኅጢአት ይልቅ በተወሰነ የቀኖና ግዜ የሰራነው ፅድቅ ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ጥፋት ፍቆ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት እንድንበቃ ታደርጋለች። 
 
ስለዚህ ጠያቂያችን በኅጢአት መውደቅ የተለመደ የሰው የስጋ ባህሪ መሆኑን፥ በፅድቅ ወይም በንስሓ መነሳት ግን የክርስቲያን መንፈሳዊ ተጋድሎ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ያሳለፉት የኅጢአትና የነውር ዘመን ምንም እንኳን ሰይጣን ቢፈታተንዎትም፤ እግዚአብሔር ከእርስዎ ህይወት ጨርሶ ስላልራቀ በውስጥዎት ፀፀት እና ወደ እግዚአብሔር መመለስን እያንፀባረቁ በመሆኑ ፈፅሞ ከጠሉት ህይወት ውስጥ እንደሚወጡና እግዚአብሔርም እንደሚረዳዎት እናምናለን። ከዚህ የጠለቀ የኅጢአት ጉድጓድ ውስጥ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት እንዲችሉ በግልዎት ሊያደርጉ የሚገባዎትን ምክር እና ትምህርት እንድንሰጥዎ ደግሞም በአባቶች በኩል እርስዎን ለማዳን መደረግ የሚገባውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማከናወን ይቻል ዘንድ አሁንም በውስጥ መስመራችን ደውለው ቢያገኙን መመካከር እንችላለን በማለት በድጋሚ ለማስታወስ እንወዳለን። ።
መልስ፦  አንድ ክርስቲያን የተፈፀመውን በደል በራሱ ግዜ አምኖ ተፀፅቶ ንስሓ ገብቶ በቀኖና ላይ እያለ ይባስ ብሎ የተሰጠውንም ቀኖና ሳይፈፅም ወደፊት ኅጢአት ላለመስራት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ ሌላ በደል ከፈፀመ ሰውነቱን የተቆራኘው የኀጢአት ደዌ ብሶበታል ማለት ነው። እጅግ ህይወቱ አሳዛኝ ቢሆንም ስለአድን ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ተስፋ ሳይቆረጥ ይሄን ሰው በተለያየ መንገድ የንስሓ አባቱ ወይም ሌላም አባት በቅርብ ውስጣዊ ችግሩን ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስሓ ህይወት እንዲቀርብ እና በተደጋጋሚ ከተፈተነበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አቤቱ ወንድሜ ምን ያህል ቢበድለኝ ምን ያህል ይቅር ልበለው እስከ 7 ጊዜ ነውን ብሎ በጠየቀው ጊዜ እስከ 7 አልልህም 7ቱን አንድ እያልክ እስከ 70 ነው እንጂ” በማለት ለኅጢአት ይቅርታ የጊዜ እና የቁጥር ገደብ እንደሌለው አረጋግጦልናል። (ማቴ 18፥21-22)
ስለዚህ በዚህ መሠረት ከኅጢያት ደዌ እስካልተፈወሱ ድረስ የንስሓ ህይወት አይቋረጥም ይቀጥላል እንጂ።
መልስ፦ በፆመ ፍልሰታ የፆም ንስሓን በሚመለከት ካህኑ በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት አስበው እንደ መንፈሳዊ አባትም ሃላፊነት ወስደው ያደረጉት ስለሆነ፤ አንዴ ንሰሓ ገብተው ለፈጸሙት የንስሓ ቀኖና ለሁለተኛ ግዜ ደግመው መፆም ወይም ንስሓ መግባት አያስፈልግዎትም። የንስሓ ቀኖና እንደ ጥፋታችን ታይቶ የሚሰጥ ስለሆነ በመደበኛ የፆም ጊዜ የንስሓ ፆም መስጠት የተለመደ ስርዓት ነው።
 
መልሰ፦ ጠያቂያችን እንደጠየቁት ውርጃ መፈጸም አጅግ ነውር ተግባር ነው፤ በኀጢአትም የሚያስጠይቅ ነው። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ተጠይቆ መልስ የሰጠንበት ቢሆንም አሁንም ጠያቂያችን አንዲረዱት የምንፈልገው እግዚአብሔር በማህፀን ወሰጥ ያለውን ውሀ አና ደም አርግቶ በጅማት በስጋ በአጥንት አዋህዶ በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረውን ፍጡርና ወደፊት በሱ ፈቃድ እና በሱ መግቦት የእድሉን ድርሻ ሰጥቶ የሚያኖረውን ፍጥረቱን በማህፀን ውስጥ ያልተገባ መድሀኒት በመውሰድ ወይም ሌላ መንገድ በመጠቀም ፅንስን ማስወረድ ከባድ ኀጢአት ነው ። ምናልባት በማህፀን ውስጥ ያለው ከተወለዱት የሚለየው ባለመናገሩ ነው እንጂ እሱም በእግዚአብሔር ዘንድ ህልውናው እውቅና  ያገኘ ስለሆነ በምድራዊ ሕግ እንኳን ባንጠየቅ በእግዚአብሔር በኩል ግን ትላልቅ ሰወችን ከመግደል ጋር እኩል የሚቆጠር ስለሆነ በነፍስ ጉዳይ ኀጢአት እንጠየቃለን ማለት ነው። በመሆኑም እንዲህ ያደረጉ ሰወች ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው መሬት ላይ ተኝተወ እያዘኑ እየፆሙ እያለቀሱ በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ፀባይ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል።  በሴትዋ ላይ ያለው ፈሳሽ እንዳቆመ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ንስሓ መግባት ትችላለች እንጂ በስርዓቱ እንደ ወለደ ሰው 40 እና 80 ቀን መጠበቅ አያስፈልጋትም። ወይም ደግሞ የንስሓ አባት ወይም ካህን አባትም ቢሆን ባሉበት ሆነው አስጠርተው የቀን ጋፕ ሳያስፈልግ ቀኖናዋን መቀበል ትችላለች። ዋናው አላማ ኀጢአትን ተናዝዞ በንስሓ ህይወት ከሞት መዳን ነው።
መልስ ፦  ሀገርን፣ ህዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ቤተሰብን እና ራሳችንን ለማጥፋት በጭካኔ የመጣን ጠላት በጽድቅ ምክንያት የማይሆን ዋጋ ከመክፈል ይልቅ መጋደላችን ወይም ደግሞ ይሄንን የሁሉ ነገር በጠላት እርምጃ መውሰዳችን መንፈሳዊ ተጋድሎ እንደሆነ እንጂ ኀጢአት አይደለም። በቅዱሳን መጽሐፍትም በብዙ ቦታ ተመዝግቦ እንደምናገኘው  እግዚአብሔር ሳይቀር ተገቢ በሆነ መንገድ ጠላቶቻችንን እንድናጠፋ ፈቅዷል። በአገራችን ታሪክም የአገርን ሉአላዊነት የሚደፍር፣ የሃይማኖትን ክብር የሚያዋርድና ህዝብን የሚያጠፋ ጠላት በመጣ ጊዜ ቤተክርስቲያንም ብትሆን ታቦት አክብራ፣ ካህናቶችን ልብሰ ተክኸኖ አስለብሳ፣ በጦር ሜዳ ተገኝታ ጠላትን ተከላክላለች። ጉዳዩ ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ የማንነት ጥያቄ ስለሆነ ነው። ነገር ግን ማንኛውም ክርሰቲያን መጠንቀቅ ያለበት በማህበራዊ ምክንያት በሚያጋጥመን ችግር በጥቃቅን ነገር ተነሳስተን ሊጎዳንም ሊጠቅመንም በማይችል ምክንያት እንዲህ አደረከኝ፣  እንዲህ አደረግሽኝ በሚል ሰበባሰበብ ከሰይጣን በመጣ ፈተና ተነሳስተን ደም ብናፈስ፣ ንጹህ ብንገድል፣ አጥንት ብንከሰክስ፣ መድኀኒት ብናበላ ወይም ብናጠጣ ባጠቃላይ እንዲህ አይነት ክፋ ስራ ብንሰራ እንኳንስ በሰማያዊ ህግ  በነፍሳችን ቀርቶ በምድራዊ ህግም ተጠያቂዎች እንደሆንን ማወቅ ያስፈልጋል።
 
የንስሐ አባት ለመያዝ ቢፈልጉ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የኛን የውስጥ ችግር ያውቀዋልና አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ያለ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌለበት የንስሐ አባት እንዲኖረው በሃይማኖቱና በመንፈሳዊ ህይወቱ የመረጠውን ካህን እርቀት ሳይገድበው መያዝ ይችላል። ምክንያቱም ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲያሥሩና እንዲፈቱ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ጊዜና የቦታ ርቀት የማይወስነው ስለሆነ ፤ በአካባቢው አባት የሚሆን ካህን ከጠፋ ያለጠባቂ ብንኖር ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍሳችንን እንዳይነጥቃት የንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ  መጨናነቅ እንደማያስፈልግ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
 
መልስ፦  ጠያቂያችን ንስሓ ገብቶ በቀኖና ላይ ያለ ክርስቲያን ፈፅሞ ሃይማኖትን የካደ ካልሆነ ቆሞ ማስቀደስ፣ ፀበል መጠመቅ፣ ፀበል መጠጣት፣ መስቀል መባረክ፣ በክርስቲያኖች ማህበር ጉባዔ መካከል ተገኝቶ የእግዚአብሔርን ቃል መማር፣ በቅፅረ ቤተክርስቲያን ቆሞ መፀለይ ይችላል። ከእንዲህ አይነት ስርአት የሚከለከሉ ጨርሶ ሃይማኖታቸውን ክደው የነበሩ ወይንም ደግሞ ከባድ የተባለ የመጨረሻ ኅጢአት የሰራ ሰው ከሆነ ያ ሱባኤ የሚገባበት ቦታ ሰው የማይደርስበትና ከሰው የማይገናኝበት ልዩ ቦታ ስለሚሆን ያንን ንስሓውን ጨርሶ ከፈጣሪው ዘንድ የይቅርታ ምላሽ እስከሚያገኝ የተለመደውን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማግኘት አይችልም።
 

መልስ፦ ስለ ንስሓ ህይወት የጠየቁን አባላችን ንስሓ ማለት ማንኛውም በእግዚአብሔር ሀልዎት የሚያምን እና በክርስቲያናዊ ስነምግባር የሚኖር በየጊዜው በስጋ ምኞት በሚመጣበት ፈተና ከትንሽ እስከ ትልቅ ወይም ቀላልም ይሁን ከባድ ኀጢአት እንደሰራ የሰው ምስክር ሳያስፈልግ ራሱ በህሊናው ተጸጽቶ   የፈፀመውን ኀጢአት ካመነ ወደ ንስሓ አባቱ ቀርቦ የሰራውን ጥፋት በመናዘዝ እንደ ኀጢአቱ ክብደት ንስሓ ይሰጠዋል። አስቀድመን በተደጋጋሚ እንደተናገርነው ከልብ መፀፀትና ንስሓ ለመግባት የቀጠሮ ጊዜ ሳናራዝም ወይም ባለብን የዘወትር ስጋዊ ፈተና ሳንፈራና ነገሮችን ሳናከብድ በአስቸኳይ የነፍሳችን ሃኪም ወደሆኑት የንስሓ አባት በመሄድ በፅኑ ከተያዝነው የኀጢአት ደዌ በንስሃ ህክምና የነፍስ ድህነት ማግኘት አለብን። በዚህ ንስሓ በሚቀበለው ክርስቲያን እና ንስሓ በሚሰጠው አባት መካከል የሚፈፀመው አገልግሎት የሚታይ መንፈሳዊ ስርአት ሲሆን በዚህ መታዘዝ ውስጥ እግዚአብሔር በረቂቅ መለኮታዊ ጥበቡ በካሕኑ ላይ አድሮ በፍጹም እምነት ኀጢአቴ  ይፋቅልኛል ብሎ ከልብ በመታዘዝ ለንስሓ ህይወት የቀረበውም ምእመን ያለምንም ጥርጣሬ ኀጢአቱ ይቅር ይባላል ማለት ነው። ስለዚ በመፅሐፍ ቅዱስ እና በሌሎቹ ቅዱሳን መፃሕፍት በብዙ ቦታ ላይ እንደተገለፀው እግዚአብሔር ኀጢአት ይቅር እንደሚል እኛም ከኀጢአታችን እና ከበደላችን ተፀፅተን ወደ ፈጣሪ እንድንመለስና የእግዚአብሔር እንደራሴ ለሆኑ የሃይማኖት አባቶቻችን እንድንናዘዝ ታዘናል።  ስለዚህ ጠያቂያችን በእርስዎ በኩል እኛ ያላወቅነውና ያልተረዳነው ውስጣዊ ችግር ቢኖር እንኳን ሁሉም ነገር በፈጣሪ ዘንድ ኢምንት ስለሆነ ከባድ ያሉትን ጭንቀት እና ሃሳቦትን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ሳይጠራጠሩና ሳያመነቱ ከተያዙበት የኀጢአት ደዌ በፍጥነት ለመውጣት ጊዜ ሳይሰጡ ወደ ቤተክርስቲያን እና ወደ አባቶች ይቅረቡ። ታሰር ተፈለጥ በሚል ስጋዊ ዳኝነት የሚጠየቁበት ጉዳይ ስለሌለ ምህረቱና ቸርነቱ ፍቅሩና ትእግስቱ ወደ በዛው ወደ እውነተኛው አምላክ ስለሆነ የሚቀርቡት፤ የንስሓ ህይወትም ለክርስቲያኖች እድል የሚመች አላማ ስለሆነ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲኦል ወደ መንግስተ ሰማያት፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ፅድቅ፣ ከሞት ወደ ህይወት የሚያመጣ ቀና መንገድ ስለሆነ የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጡ ወደ ቤተክርስቲያን አባቶች ቀርበው ችግሮትን በማስረዳት መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ለማግኘት ህሊናዎትን ያዘጋጁ። የንስሓ ግዜን በሚመለከት እንደተፈፀመው የኀጢአት ክብደትና ቅለት ከሰአታት ጀምሮ እስከ ቀናትና ሳምንታት የሚወሰን ይሆናል። ስለዚህ የኀጢአት አይነት ሲታወቅ በቤተክርስትያን ቀኖና በተደነገገው መሰረት ንስኃ ሚሰጡን አባቶች የንስኀውን ግዜ ይወስኑታል እና በዚህ አይነት ከባድ እንደሆነ ግን ማሰብ የለቦትም ። ባጠፋነው መንገድ እንድንቀጥል ሰይጣን ነገሮችን ሁሉ ስለሚያከብድ እና ስለሚያጨልም ብቻ ካለንበት የኀጢአት ጉድጓድ ውስጥ እንዳንወጣ ስለሚያደርግ ነው። ከዚህ በላይ እኛ ያልተረዳንዎት ከእርስዎም አቅም በላይ የሆነ ችግር ካለ መንፈሳዊ ትምህርት እንድንሰጥዎት በውስጥ መስመር ያነጋግሩን።

የንስሐ አባት ይህን የድረ ገጻችንን አድራሻ በመጫን ይያዙ: https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/

 

ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን ምላሽ እንደሚከተለው በድጋሚ ልከንልዎታልና ይመልከቱት ፦

በቅድሚያ በድያለሁ ጥፋት ሰርቻለሁ ኅጢአት ፈጽሜያለሁ ብሎ ኅጢአትን ለመናዘዝ ፈቃደኛ መሆንና የኅጢአት ሥርየት ለማግኘት መፈለግ የእውነተኛ ክርስቲያን መገለጫ ነው። በመሠረቱ በአዳማዊ ተፈጥሮ ሰው ሁኖ የተፈጠረ የሰው ልጅ ሁሉ ወዶ ጽድቅ መሥራትም ሆነ ወዶ ኅጢአት ለመሥራት የሚችልበት የተፈጥሮ ነፃነት ያለው ፍጡር ስለሆነ በለበሰው ደካማ ሥጋው ተሸንፎ ኅጢአት እንደሚሠራ ይታወቃል። ሰው ሁኖ ተፈጥሮ በሰውነቱ ፈፅሞ ኅጢአት አልሠራም ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር እራስን ከማታለል አልፎ ስለሁላችንም መዳን በመስቀል ላይ የሞተልንን የኢየሱስ ክርስቶስ አባታዊ ፍቅሩንና ውለታውን እንደመካድ ይቆጠራል። ሁላችንም የሰው ልጆች እንደምንሞት ብናምንም እንኳ፤ ነገር ግን መቼ በሞት እንደምንጠራ ቀንና ሰዓቱን (ዘመንና ጊዜውን) ለይቶ ማወቅ ከእሱ ከባለቤቱ በስተቀር ፈጽሞ የሚያውቅ የለምና ኅጢአትን ለመናዘዝ ቅድሚያ መስጠትና በንስሐ ሕይወት ራስን አዘጋጅቶ መጠበቅና ንስሐ ለመግባት መዘጋጀት ከእውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ ታማኝነት ነው።

ኅጢአት ማለት የብዙ ጥፋቶች ወይም ስሕተቶች መጠሪያ ስም ነው ኅጢአት የሥጋ ሥራ ሁኖ ነፍስን ከፈጣሪ ጋር አጣልቶ ዘለዓለማዊና ሰማያዊ ሞትን የሚያስከትል ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የኅጢአት ውጤት ሞት እንደሆነ ሲናገር “ኅጢአት ስታድግ ሞትን ትወልዳለች” (ያዕ1፥15) ካለ በኋላ “የኅጢአት ደመወዝ ሞት ነው” (ሮሜ 6፥23) በማለት ኅጢአት የሕሊናና የመንፈስ ሞት መሆኑን አረጋግጧል። 

የሥጋና የመንፈስ (የነፍስ) ሥራዎች አብዛኛዎቹን ቅዱስ ጳውሎስ ወደገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ በምዕ 5፥19-22 ላይ የሥጋ ሥራ እና የመንፈስ ፍሬዎች በማለት ዘርዝሯቸዋል።

የሰው ልጅ ኅጢአት ሰርቻለሁ እግዚአብሔርን በድያለሁ፣ ሰውንም አሳዝኛለሁ ብሎ ራሱን ካሳመነ በነፍሱ የኅጢአት ደዌ አድሮበታልና ንስሐ የመግባት ሕክምና ያስፈልገዋል ማለት ነው። “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ “(ማቴ3፥8) ኅጢአት ሠርቶ የንስሐ ሕክምና ያላገኘ ሰው በነፍሱ ምውት ነው። ሉቃ 15፥24

ከዚህ የተነሣ ኅጢአት ለመናዘዝና ንስሐ ለመግባት ከሚፈልግ አንድ ክርስቲያን የሚጠበቀው ፡-

–  በቅድሚያ ኅጢአት መሥራቱን አምኖ ለራሱ ሕሊና መናዘዝ (መፀፀት)።

–  ስለሠራው ኅጢአት ወይም በደል እየተጸጸተ ጧት ማታ በደሉን በፀሎትና በልመና ለፈጣሪው መናዘዝና ኅጢአትን በእግዚአብሔር ፊት ማመን (መዝ50 ፣ ዳን9፥5፣ ነህ1፥6-7)

–  ኅጢአትን (በደልን) ለካህን መናዘዝና ንስሐ መግባት። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይና እንደራሴ ስለሆነ የሠራነውን ኅጢአት ለካህኑ በመናዘዝ ንስሐ መግባት፤ ኅጢአታችን እንዲሠረይልን በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ መግባትና መናዘዝ ማለት ነው። (ኢያሱ7፥19 ማቴ3፥6 ዘሌ5፥5-6 የሐዋ19፥18)

–  የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት የጥል ግድግዳ አፍርሰን በፍቅር አሸንፈን ስለዘለዓለማዊ ሕይወት ብለን በፍጹም ሕሊና በሰላም መኖር ነው።

–  ተመልሶ በኅጢአት ላለመውደቅ አዘውትሮ የንስሐ አባትን ወይም የሚቀርቡትን የሃይማኖት መምህር ማማከር፣ ምክር ማግኘት በታቻለ መጠን መጸለይ፣ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ በቤትም ውስጥ ቢሆን መንፈሳዊ መዝሙርና ትምሕርት ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ የምናስገነዝበው ለጠየቁን ምዕመን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያን እንዲጠቅም ነው።

የንስሓ አባትን በሚመለከት ፦

ይመክረኛል ያስተምረኛል ያሉትን የንስሓ አባት የሚሆን ካህን በአካባቢዎ ካሉ  ይያዙ፤ በአከባቢዎ  ማግኘት የማይችሉ ከሆነ በራስዎትም ሆነ በሚያምኑት ሰው በኩል ያገኙዋቸውን እውነተኛ ካህን በርቀትም ቢሆን ይያዙ፤ ወይም ደግሞ እኛ በህይወታቸው ምሳሌ ይሆናሉ ብለን ከመረጥንልዎ በድረገፃችን ላይ ካሉ አባቶች  ንስሓ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ።

በተጨማሪም፤ ስለንስሓ ትምህርት በድረገፃችን ላይ የተላለፉና እየተላለፉ ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች ይህን ሊንክ በመጫን ያንብቡ።

ትምህርት ስለ ንስሓ – https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ/

የንስሓ አባት ገጽ – https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/

መልስ ፦ ጠያቂያችን ማንኛውንም ኀጢአት ከልብ ተፀፅተን ሳናፍርም ሳንደብቅም በፍጹም እምነት ለንስሃ አባታችን በግልፅ ተናግረን የተሰጠንን የንስሓ ቀኖናም በአግባቡ ከፈፀምነው የማይፋቅ ወይም በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅር የማይባልና ስርየት የማያገኝ ኀጢአት የለም። ጠያቂያችን ለመግለፅ የፈለጉት ነገር በግልፅ ተረድተነው ከሆነ እጅግ ከባድ የሚባል ኀጢአት ቢኖረንም እንኳን ያንን ከባድ የኀጢአት ሸክም ይቅር የሚል አምላክ ይቅር ስለሚለን ከኀጢአታችን መንፃት እንችላለን። ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “እናንተ ሸክማችሁ የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት በኅጢአት ሸክም የደከሙትን እና የዛሉትን ላንዴና ለመጨረሻ የኅጢአት ሸክማቸውን እንደሚያቀልላቸው ከበደል ሁሉ ነፃ እንደሚያወጣቸው ተነግሯል። በሌላም በኩል ነብዩ ዳዊት በመንግስቱ ዘንድ ባለሟል የነበረውንና የጦር አዛዥ የነበረውን ኦርዮንን በማስገደሉና የኦርዮንን ሚስት ደግሞ ለራሱ በመውሰዱ እግዚአብሔር በክፉ ስራው ስለተቆጣው በኅጢአት የተወለው ህፃንም በሱ ኅጢአት በተቀፀፈ ጊዜ ንጉስ ዳዊት ነፍስ በማስገደሉና ያልተፈቀደለትን የአገልጋዩን ሚስት ለራሱ ስለወሰደ በነዚህ በ 2 ከባድ የኅጢአት ስራወች ከልቡ ተፀፅቶ ምርር ብሎ በማልቀስ ከክብረ መንግስቱ ወርዶ ራሱን ዝቅ አድርጎ አመድ ነስንሶ ማቅ ለብሶ እመሬት አፈር ላይ እየተኛ ንስሓ በመግባቱ ያ ከባድ የተባለው ኅጢአት በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅር እንደተባለ በቅዱስ መፅሐፍ ተፅፎ እናገኘዋለን። ቅዱስ ጴጥሮስም በአይሁድ ዘንድ የጌታ ደቀመዝሙር እንደሆነ በተጠየቀ ግዜ ዶሮ ከመጮሁ በፊት 3 ጊዜ በመካዱ ምክንያት ወድያውኑ ኅጢአቱን እያሰበ መራራ ለቅሶ እያለቀሰ ስለፈፀመው የክህደት ስራ ይቅር እንዲለው ንስሓውን በፈጣሪው ዘንድ ያቀረበው ልመና በጌታ ዘንድ ይቅር እንደተባለ ተመልክተናል።እንግዲህ እነዚህን የሚመስሉ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በፈፀሙት ጥፋት ንስሓ ገብተው ኅጢአታቸው እንደተፋቀላቸው በመፅሐፍ ቅዱስ የብዙ ሰወችን ታሪክ እናገኛለን። በሌላም በኩል ከምንም ነገር በላይ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለኛ የከፈለውን የሞት ዋጋ ስናስብ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መምጣት የነበሩ የአዳም ልጆች ሁሉ የፈፀሙት እጅግ ከባድ እና ዘግናኝ የሆነ የኅጢአት አይነት ሁሉ ይቅር እንደተባለ እሱ በከፈለው የቤዛነት ስራ አረጋግጠናል። ስለዚህ ጠያቂያችን እውነተኛ ለንስሓ የተዘጋጀ ልብ ካለን በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅር የማይባል ኅጢአት እንደሌለ በድጋሚ ይረዱት ዘንድ ይህን መልእክት በማስተዋል ያንብቡ። ከዚህ በፊትም ስለ ንስሓ ህይወት ወደ እናንተ ያደረስነውን ትምህርት በድጋሚ እንዲመለከቱት አደራ እንላለን።
መልስ ፦ ንስሓ ለመግባት የተዘጋጀ አንድ ክርስቲያን የሚሰጠው ቀኖና እንደ ኅጢአቱ ክብደትና ቅለት የቤተክርስተያን ቀኖና ታይቶ ስለሆነ በግልፅ እና በዝርዝር መናገር አለበት። የታመመ ሰው በሽታውን በምርመራ ለማወቅ ከተቻለ በኋላ እንደበሽታው አይነት ወይም ባህሪ መድሀኒት እንደሚታዘዝለት ሁሉ የቤተክርስቲያን አባቶችም ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ንስሓ የሚሰጡት በፈፀሙት ኅጢአት አይነትና የጥፋት ደረጃ ተመልክተው ስለሆነ በጥቅሉ ሳይሆን ኅጢአትን ዘርዝሮ በግልፅ መናገር በንስሓ ህይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠያቂያችን እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 
መልስ፦ በዚህ ጥያቄ ላይ ከዚህ በፊትም መጠነኛ አጭር መልስ እንዲተላለፍ ያደረግን ሲሆን ፤ ለመረዳት እና ለማወቅ ለሚጠይቁን የቤተክርስቲያን ልጆች መልስ ለመስጠት ፈቃደኞች ስለሆንን የሚሰገድባቸውን እና የማይሰገድባቸውን በእለት ወይም በጊዜያት ተለይተው እንዲቀርቡ አሁንም ከዚህ በታች በዝርዝር ልከናል፦ 
የማይሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት፦ 
1ኛ/ እለተ ሰንበት (እሁድ)፣ 2ኛ/ በ12 በቅዱስ ሚካኤል ፣ 3ኛ/ በ21 የእመቤታችን በአል ፣ 4ኛ/በ29 ባለወልድ፣ 5ኛ/ በዘጠኙ የጌታ አበይት በአላት ለምሳሌ ጥምቀት፣ ልደት…፣ 6ኛ/ ከትንሳኤ እስከ ጴራቅሊጦስ (በአለ ሃምሳ) እነዚህ የማይሰገድባቸው ጊዜያት ናቸው። 
የሚሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት ደግሞ ፦ 
ልዩ የንስሃ ቀኖና ሲሰጠን፣ በምንፀልይበት ግዜ፣ ስለስግደት በሚነገርበት ቃል ላይ፣ ቅዳሴ በምናስቀድስበት ግዜ ስገዱ ሲባል፣ በሰሞነ ህማማት፣ እናዚህን በሚመሳስሉ በአምልኮት ስርዓት በሚከናወኑ ስግደት እንድንሰግድ በቤተክርስቲን ፍትሓ ነገስት ተደንግጓል። በተጨማሪም ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስንገባ በየትኛውም ቦታ መስቀል ስንሳለም፣ በቅዱሳን ስዕላት ፊት፣ ለቅዱስ ወንጌሉ እንሰግዳለን። 
በምንሰግድበትም ጊዜ በጌታ ላይ የደረሰውን የመስቀሉን መከራ የምናስታውስበት ጊዜ ስለሆነ የኛ መከራ ከሱ መከራ ጋር ባይወዳደርም እንኳን ግንባራችንን እና ጉልበታችንን መሬት አስነክተን እንሰግዳለን። በዚህን ግዜ ከሰውነታችን ላብ ሊወጣ ይችላል። በበአላት ግዜ እንዳንሰግድ የተደረገበት ምክንያት ስግደት በራሱ መንፈሳዊ ስራ ስለሆነ እና ነፍስ ፍሬ የምታፈራበት ስራ ስለሆነ ልክ እንደ ስራ ከበአላት ውጭ ግዜ ወስደን መፈፀም ስላለብን ይህን ለማስተማር ነው እንጂ በበአላት ቀን ሳናውቅ ብንሰግድም እንደ ኀጢአት ይቆጠርብናል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችንም እና ሌሎች አባላቶቻችን ይህን መልእክታችንን አንብባችሁ የመንፈስ ፍሬ እንድታፈሩበት ሁላችሁንም አደራ እንላለን።
 
 

መልስ፦  ንስሓ መቀበል ያለብን ስጋ ደሙን ስንቀበል ብቻ አይደለም። ስጋው ደሙ ለክርስቲያን ቋሚ የነፍስ ምግብ ስለሆነ ምግብ ደግሞ በየግዜው የሚያስፈልግና ከተቋረጠም በህይወታችን ሞትን የሚያመጣ ስለሆነ ማንም ክርስቲያን ከክርስቶስ ስጋና ደም እንዳይለይ በራሱ በባለቤቱ መለኮታዊ ቃል ሁላችን ታዘናል። ስለዚህ ክርስቲን ኀጢአትን እንደ ቋሚ ተግባር አስቦ በእቅድ የሚይዘው ፕሮግራም አይደለም። ሁሌ ክርስቲያን ከክፉ ነገርና ከኀጢአት ውረኝ ብሎ ነው መፀለይ ያለበት። በአጋጣሚ ግን በዚህ በለበስነው ደካማ ስጋችን የፈፀምነው በደል ካለ ቅዱስ ቁርባን ብንቀበልም ባንቀበልም ጀምበር ሳትጠልቅ እኛም የበደሉንን ይቅር ብለን የኛም ኀጢአት በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅር እንዲባልልን በካህኑ አማካኝነት ንስሓ እንቀበላለን እንጂ ቅዱስ ቁርባን ካልተቀበልን የፈለግነውን በደልና ኀጢአት እየፈፀምን በደለኛና ኀጢአተኛ ሆነን በውንብድና እንድንኖር የእግዚአብሔር የአምላካችን ፈቃድ አይደለም። ስለዚህ ቅዱስ ቁርባን እና የንስሓ ህይወት ለህይወታችን ያስፈልጉናል ማለት ነው። ለሁሉም ነገር ከዚህ ቀደም ስለንስሓ ሰፊ ትምህርት እና ለጥያቄዎች መልስ ገለፃ ስለተሰጠበት እሱን ከድረገፃችን ላይ መልሰው እንዲመለከቱትና እንዲረዱት እንመክራለን።

ስለ ንስሐ እዚህ ያንብቡ:  https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ/

በመሰረቱ ኀጢአት እራሱን የቻለ በነፍስም በስጋም በህግ የሚያስጠይቅ በደል ወይም ወንጀል ስለሆነ ልንረሳው የምንችል አይደለም፤ እስካሁን ድረስም ይህን አይነት ጥያቄ አጋጥሞን አያውቅም። ነገር ግን እርስዎ ይህንን ሲጠይቁን በእርግጥም ከልብዎ ተጨንቀው ወይም ለጠቅላላ እውቀት ከሆነ እንደ ቤተክርስቲያን አስተምሮ ጥቃቅን ነገሮች ካልሆኑ በስተቀር መደበኛ የንስሓ ህይወት የሚያስፈልጋቸው ጥፋታችንን መርሳትም መዘንጋትም የለብንም። በምድር ላይ ባለው ሕይወታችን ሃብታችንን ፣ ንብረታችንን፣ ኑሯችንን ፣ የሚደርስብንን በደልም ሆነ የሚያጋጥሙንን መልካም ነገሮች ሁሉ ለይተንና ተቆጣጥረን እንደምናውቅ ሁሉ ፤ የሰራናቸውንም የኀጢአት አይነቶች በስጋም በነፍስም የሚያስጠይቁ ስለሆኑ ሊረሱ አይችሉም፤ ሆኖም ጠያቂያችን እንዳሉት እንዲህ አይነት የመርሳት ነገር ወደፊት እንዳይገጥምዎ ቢቻል የመጀመርያ አቋምዎ ሊሆን የሚገባው ኀጢአት ላለመስራት ዘወትር ተግቶ መፀለይና ከጥፋትና ከኀጢአት ሁሉ መራቅ ነው። ነገር ግን አንዳንዴ ሰው ሆነን በመፈጠራችን በለበስነው ስጋ ተፈትነን የሰራነው ኀጢአት ካለ እስከሚረሳን ድረስ እንዲሁ ተኝተን እያንቀላፋን በዋዛ በፈዛዛ መክረም ስለሌለብን ወዲያውኑ ግዜ ሳንሰጥ የኀጢአት እዳችንን ስላጠፋነው ጥፋት በንስሓ ህይወት ሆነን ካሳ መክፈል አለብን ወይንም ንስሓችንን ተናዘን ከኀጢአታችን መታጠብ አለብን።  
ስለዚህ ጠያቂያችን ለተዘነጋ ወይም ለተረሳ ኀጢአት በትክክልም ከእርስዎ በላይ ስለእርስዎ ሕይወት የሚያውቅ ወይም ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ውስጥዎትን ስለሚያውቀው በትክክል ከእርስዎ አይምሮ ተሰውሮ ከሆነ ወደ መምህረ ንስሓዎ ወይም ንስሓ አባትዎ ቀርበው ይህን ሃሳብ ገልፀውላቸው በጠቅላላ ከኀጢአት ስለሚፈወሱበት የንስሓ እና የምክር አገልግሎት መቀበል አለብዎት። ከምንም በላይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን ደካማነቴን እና በደለኛነቴን አንተ ስለምታውቅ እያወቅኩም ሳላውቅም የበደልኩትን በደሌን ሁሉ ከኔ ህይወት ፋቅልኝ፣ ደምስስልኝ እያሉ ፈጣሪዎትን ይቅር እንዲልዎ በፀሎት ተግተው መለመን እንደሚያስፈልግም እንመክራለን። 
ከዚህ ጋር በተወሰነ መልኩ የሚመሳሰል ጥያቄ ከዚህ በፊት ተጠይቆ የሰጠነውን ምላሽ ለተጨማሪ ግንዛቤ እንዲሆን ከዚህ በታች አያይዘን ልከንልዎታል።
መልስ፦ በመሰረቱ ቀኖና ወይም ንስሐ የሚሰጠን በፈጸምነው ኅጥያት መጠን ተለክቶ ስለሆነ እያንዳንዱ ያጠፋነውን ጥፋት ከባድም ቢሆን ሳንፈራ፤ ቀላልም ቢሆን ሳንንቅ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለነፍሳችን እረኛ ላደረግነው ካህን መናገር እንዳለብን የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል። ንስሐ የሚሰጡን አባቶችም የኅጥያት ደረጃችን ተለይቶ ሲታወቅ በጥፋታችን መጠን ስለሆነ ንስሓ የሚሰጡን፤ ንስሓ ላልገቡበት ማለትም ንስሓ በገቡበት ጊዜ ረስተው ሳይናገሩት ለቀሩት ኅጥያት እንደገና መናገርና ቀኖና መቀበል ያስፈልጎታል።
 

መልስ፦ ጠያቂያችን እንዳሉት አሁን ለትምህርት በሄዱበት ቦታ ለአንድ ቀንም ቢሆን ያለጠባቂ ወይም ያለ ንስሓ አባት መዋልና ማደር ስለማይቻል በአካባቢው ካሉ ካህናት አባቶች ሊመክሩ፣ ሊያስተምሩ፣ ሊገስፁ የሚችሉ አባት መርጠው የንስሓ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ። ከሄዱበትም ስራዎትን ጨርሰው ወደቀድሞ ቦታዎ ሲመለሱ በንስሓ አባትነት ሲያገለግልዎት የቆዩትን አባት እንደሚሄዱ ነግረው በፀሎት ተሸኝተው እና ተሰናብተው ሲመለሱ ቀደም ሲል ይዘዋቸው የነበሩትን አባት አድርገው ለማስቀጠል እንደሚችሉ የቤተክርስቲያን ስርዓት ይፈቅዳልና ጠያቂያችን እንዳሰቡት ማድረግ ይችላሉ።
ዋናውና ቅድሚያ የሚሰጠውና የሕይወት ጉዳይ የሚሆነው ማንም ክርስቲያን በየትኛውም አካባቢ በስራ ምክንያት ወይም በሌላ አጋጣሚ ቦታ ቢቀይር ያለአባት መኖር እንደሌለበት ማረጋገጥ ብቻ ነው ያለብዎት። ስለዚህ ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን አበክሮ የነገረን እና በመለኮታዊ ቃሉ መመሪያ የሰጠበት በጎቹ ያለ ጠባቂ እንዳይኖሩ እረኞቹ ደግሞ በጎቹን በጥበብና በማስተዋል እንጂ በሃይል እና በጉልበት ወይም በማስመረር እንዳያስተዳድሯቸው የእረኞቹን እና የበጎቹን አንድነት ነግሮናል። በዚሁ መሰረት አንዳንድ መናፍቅ እና በክህደት መንገድ ውስጥ ያሉ በድፍረት በሚናገሩት የኑፋቄ ቃል የንስሓ አባት አያስፈልግም በሚል የስንፍና ቃል ብዙ ሰዎች ለተኩላ እና ለዱር አራዊት አልፈው እንደተሰጡና የግብር አባታቸው የሆነውን የዲያብሎስን ስራ የሚያስፈፅሙ ስለሆነ ከዚሁ አይነት አጉል ትምህርት መጠንቀቅና ልብ ማለትም ያስፈልጋል። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱትና በተጨማሪም ስለ ንስሓ ከዚህ በፊት የሰጠነውን ተከታታይ ትምህርት ደጋግመው እንዲያነቡትና ቀጣይ ክፍልም ስለምንልክ እንዲከታተሉ እንመክራለን።

ትምሀርት ስለ ንስሓ.፦https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ/

 

በሴቶች ልማድ ወይም የወር አበባ ለሴቶች የተፈጥሮ ፀጋ እንደሆነ እና የሰው ዘርን ለመተካትም ተፈጥሮአዊ ምክንያት ነው። በዘመነ ኦሪት በእናታችን ሄዋን በመጣብን እርግማን ምክንያት የመርገም ደም ተብሎ ስለሚታመን ሴቶች ሁሉ ሲነቀፉበት የነበረ የነውር ምልክት ነበር። በመጀመርያዋ ሄዋን የመጣው መርገም በዳግማዊት ሄዋን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለጠፋልን ሴቶች ዛሬ የወር አበባ ወይም የሴቶች ልማድ በመጣባቸው ግዜ እንደ እርኩስ አይቆጠርባቸውም፤ ሆኖም ፈሳሹ እስከሚቆም ወይም ከደም እስከሚነጹ ድረስ ቢያንስ ለ 1 ሱባኤ እስከ 7 ቀን ድረስ ከመቁረብ፣ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከማስቀደስ፣ ፀበል ከመጠጣትም ሆነ ከመጠመቅ ይቆጠባሉ። ጠያቂያችን እንዳሉት ንስሓም አንዱ መንፈሳዊ የአገልግሎት ቀኖና ስለሆነ በዚህን ሰአት የተሰጣቸውን የንስሓ ቀኖና እንዲፈፅሙ አይደረግም። በአጋጣሚ ግን የንስሓ ቀኖና ከተሰጣቸው በኋላ ንስሓቸውን ሳይጨርሱ በሰይጣን ፈተና ባልተጠበቀ ቀን የሴቶች ልማድ ቢያጋጥማቸው፤ በዚህ ወቅት መቅረብ ስለማይቻል በቤት ውስጥ የሚፈፀም ንስሓ ከሆነ ካህኑን በማማከር ሰውነታችንን በመታጠብና ንፁህ ልብስ በመልበስ ሳናቋርጥ መቀጠል እንችላለን። በቤተክርስተያን ውስጥ ወይም ደግሞ ወደ ገዳም ሄደው የሚፈፀም ከሆነ በማስተዋልና በመንፈሳዊ ፅናት ሆነው ከደረሱበት አቋርጠውት ባሉበት ቦታ ሆነው መፆምና መስገድ ይችላሉ፤  በቀኖና ቤተክርስቲያን እንደተወሰነው በተወሰነ ርቀት ላይ ቆመው መንፈሳዊ ስርአቱን መከታተል ይችላሉ። ያጋጠማቸው የሴቶች ግዳጅ የተለመደው የጊዜ ገደብ ሲያልቅም ንስሓቸውን መቀጠል ይችላሉ። ስለሆነም ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱትና በተጨማሪም ከዚህ በፊት በተማሳሳይ ጥያቄ ላይ የላክነውን ምላሽ እንዲያነቡት ከዚህ በታች አያይዘን ልከንልዎታል። 

መልስ፦ በአዲስ ኪዳን የሴቶች የወርሃዊ ግዳጅ ሲመጣ ወደ ቤተክርስቲያን ለመግባት ለራስዋም ሆነ ለተመልካች መሰናክል እንዳይሆን በሌላ መልኩ መስቀሉንም ሆነ ፀበሉን ለመጠቀም በረከት ለምናገኝበት ንዋየ ቅዱሳን ክብር ስለምንሰጥ እንጂ እንደ ኦሪቱ ስርዓቱ የወር ግዳጅ የመጣባት የተረገመች ነው ማለት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የማይገባ ልብስ ለብሰን በሰው ፊት ለመቅረብ፣ ወይም በአካላችን የሚታይ ነውር ይዘን በሰው ፊት ለመቅረብ እንደምንሳቀቅ ሁሉ ከዚህም በላይ ንጽሐ ባሕሪይ ዘላለማዊ አምላክ በሆነው አምላክ ፊት ስንቀርብ ታላቅ አክብሮትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያስፈልገናል። የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ተብሎ ተፅፏልና።

ስለዚህ ጠያቂያችን፤ የሴት ልማድ የመጣባት ሴት ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልገሎት ግዳጅዋን እስትጨርስ መራቅ አለባት። ማለትም ሌላ አደጋ ወይም ችግር ካላጋጠማት በስተቀር የተለመደው የጊዜ ገደብ እስከሚያልቅ ድረስ ፀበል ከመጠጣትም ሆነ ከመጠመቅም ወይም መስቀል ከመባረክ ትቆጠባለች። ነገር ግን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ተለይቶ ለማያውቅ ሰው አንድ ቀንም ቢሆን የሰይጣን ውግያ እንዳይኖርበት ከቤተክርስቲያን ቅፅር ራቅ ብሎ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ካህናት አባቶች ህዝቡን ሲባርኩና እግዚአብሔር ይፍታ ሲሉ ባሉበት ሁነው ይሁንልኝ ይደረግልኝ በማለት በረከቱን ማግኘት ይቻላል።

መልስ፦ ጠያቂያችን ከላይ እንደገለፁልን የንስሓ አባትዎ ወደ ውጭ አገር ሳይነግሩዎት እና ሌላ አባት ለመያዝ እንዲችሉ ሳይሰናበትዎት መሄዳቸው አግባብነት አልነበረውም። ነገር ግን በግዜው ይህን ለማድረግ ያላስቻላቸው የራሳቸው ምክንያት ስለሚኖራቸው እንደ ከባድ ጥፋት ማየት የለብንም። ስለዚህ አሁን ማድረግ ያለብዎት ሌላ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳይኖር ይህንኑ ችግርዎትን በመግለፅ በመንፈሳዊ አባትነት ጠንካራ የሆኑትና እርስዎን በመንፈሳዊ ህይወትዎ ዙርያ ዘወትር ይመክሩኛል ያስተምሩኛል ይከታተሉኛል በማለት የሚያምኑባቸውን አባት ጊዜ ሳይሰጡ ፈጥነው እንዲኖርዎት እንመክራለን። ምን አይነት አባት መያዝ እንዳለብዎ ምክር ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን ይችላሉ። 
እግዚአብሔር ሃሳብዎትን ቀና ያድርግልዎት
መልስ 
“አይዞሽ እምነትሽ አድኖሻል” ማቴ9፥20-22 
ይህን ኃይለቃል መነሻ በማድረግ ለዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ የሆናችሁ ኦርቶዶክሳዊያን አባላቶቻችን ሁሉ፤ አንድ አባላችን በውስጥ መስመር ስለጠየቁን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የተሰጠ ትምህርታዊ ምላሽ፦
ጠያቂያችን ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ከፍፁም የእምነት ፅናት የተነሳ ስለሆነ እግዚአብሔርንም በመፍራት ክርስትና ህይወትንም ከመጠበቅ የተነሳ በመሆኑ እጅግ እናደንቃለን፤ በቀጣይ ህይወትዎም በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን በመፍራትና ክርስቲያናዊ ህይወትዎን በመጠበቅ እንዲቀጥሉ እግዚአብሔር ይረዳዎት ዘንድ መልካም ምኞታችንን እንስቀድማለን። ወደ ጥያቄዎ ሃሳብ ስንመለስ አንዳንድ በፈሪሃ እግዚአብሔር የሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደ ጠያቂያችን ሁሉ ጥቃቅንም ጥፋት ሁሉ ሳይቀር እንደ ኅጢአት በመቁጠር  ሁል ግዜ የአባቶች ምክርና የንስሓ ሂይወትን ሲያስቀደሙ እንመለከታለን። አንዳንዶቹ ደግሞ ግመልና ተራራ የሚያክለውን ኅጢአታቸውን እየዋጡ በሰው ሰውኛ ምክንያት እሚሸፋፈንና ሰውን በመሸንገል እየደለሉ እራሳቸውን እንደ ፃድቅ በመቁጠር በኅጢአት ላይ ኅጢአት እየጨመሩ የጥፋት ጉዟቸውን ይቀጥሉበታል። መታወቅ ያለበት በፈጣሪ ዘንድ አንድም የሚሰወርና የምንሰውረው ነውር የለም። ሁሉም ነገር በሱ ዘንድ የተራራ ያህል ገዝፎ የሚታይ ነው። ጥቃቅንና ረቂቅ የምንላቸው ለኛ በአይን የማይታዩ ሳይቀሩ በፈጣሪ ዘንድ የግመል ወይም የዝሆን ያህል ጎልተው ይታያሉና ከፈጣሪ ዘንድ የሚያመልጥና የሚሰወር አንዳች ነገር አይኖርም። ፅድቃችንም ሆነ ኅጢአታችን በሱ ዘንድ እንደ ገንዘብ ተቆጥሮ የታወቀ ነው። ከዚህ የተነሳ የሰው ልጅ በመንፈሳዊ ህይወቱ ኅጢአት በሰራ ቁጥር የሚያዋጣው አማራጭ እየተማረከ ትጥቁን እና ወንጀሉን አምኖ እጅ በመስጠት ወይም በመማረክ በንስሓ ህይወት መኖር ነው። ማንኛውም ክርስቲያን ወይም የሰው ልጅ በፈጣሪው ዘንድ ጥፋቱንና ኅጠአቱን አምኖ ይቅር በለኝ ካለ እንደ ኅጢአቱ ክብደትና ቅለት የንስሓ ደረጃው ቢለያይም እንኳን በእግዚአብሔር ዘንድ ፍፁም ይቅር የማይባል ኅጢአት ግን የለም።   
ስለዚህ ከላይ በርእሳችን የተነሳንበት ኃይለ ቃል እንደሚያስተምረን ከ 12 ዓመት በላይ ደም እየፈሰሳትና ትዳርዋንና ንብረቷን ሁሉ ጥላ የሚያፅናናትና የሚፈውሳት አጥታ በመንከራተትና በከባድ ሀዘን ውስጥ ባለችበት ሰዓት የስጋን ደዌ በተአምራት ፤ የነፍስን ደዌን ደግሞ በቃሉ ለማዳን ሰው ሆኖ ስጋን ተዋህዶ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ እየሱስ ክርስቶስን ባገኘችው ግዜ ምንም እንኳን ወደሱ ሊያቀርባት የሚችል በጎ ምግባርና ንፁህ አካል ባይኖራትም፤ በፍፁም እምነት ብቻ መዳን እንዳለባት ወስና ብዙ ህዝብ እያጨናነቀው ባለበት ሰዓት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ ወድያውም ፈጥና ዳነች። ምክንያቱም የነበራት እምነት እሱን በመዳሰስ እድናለሁ የሚል ስለነበር። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስም ወደዚች ሴት ዞር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ አይዞሽ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ያቺ ሴት እንደተፈወሰች የወንጌሉ ቃል ይነግረናል። ሌሎችም ከዚህ ታሪክ ጋር የሚመሳሰሉ በፍጹም እምነት መዳን እንደሚችሉ ወደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ቀርበው ህይወታቸውን ሁሉ በማስመርመራቸው ችግራቸውን በግልፅ በማስረዳታቸው የጠየቁትን እንዳገኙ እንመለከታለን። (ማቴ15፥28፣ ማር 5፥34፣ ሉቃ 7፥50፣ ሉቃ 8፥48) 
 
ስለዚህ ጠያቂያችን ያቀረቧቸው 3 ጥያቄዎች ከዚህ ቀጥለን በምንሰጥዎ መንፈሳዊ ማብራሪያ ችግርዎንትን እንደሚፈቱ ማመን አለብዎት። 
 
➡1ኛ/   የሴት ልጅ በተፈጥሮ በግብረ ሄዋን በመገኘትዋ የወር አበባ ወይም የሴቶች ልማድ የሚመጣባት የተፈጥሮ ግዳጅ ስለሆነ ቢያንስ ለ 1 ሱባኤ ማለትም 7 ቀን ያህል የወር ልማድዋ እስከሚቆም ድረስ ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብታ መቁረብ ማስቀደስ፣ መስቀል መባረክ፣ ፀበል መጠመቅ ሌሎችንም መንፈሳዊ አገልግሎት በአካል ቀርባ ማግኘት አትችልም ሲባል፤ እንደ ብሉይ ኪዳን ህግ የእርግማን ደም ስለሆነ አይደለም። ያ በሄዋን እናታችን ኅጢአት ምክንያት በእንተ አብሶ በዘር የሚያልፈው የመርገም ደም (ኅጢአት) በክርስቶስ ሞት እና በዳግማዊ ድንግል ማርያም ሴቶች ሁሉ ነፃነታቸውን ስላወጁ ይሄኛው የወር አበባ የተፈጥሮ ፀጋ ስለሆነ የሚፈሰው የሴቶች ልማድ እስከሚያቆም ወይም ከፈሳሹ እስከሚነፁ ድረስ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገቡም የሚል ስርዓት በፍትሐነገስት አባቶቻችን ስለደነገጉ፤ በስርዓቱና በሕጉ ታዛዥ ለመሆንና ለሌሎቹም ሰዎች መሰናክል ላለመሆን ያቺን ግዜ ለመቆጠብ ያህል ነው። ሌላው ግን ጠያቂያችን እንዳሉት በስጋዊ ተፈጥሮ ወይም በሌላ ምክንያት ሰው ብዙ ደካማ ጎን ስላለው በህመምም ይሁን በሌላ ጉዳይ ሴት ብቻ ሳትሆን ወንድም ከአካሉ የሚወጣ ፈሳሽ ይኖራል። ለምሳሌ በአፍ በአፍንጫ ፈሳሽ  ይኖረናል። ሆኖም ይሄ ሁሉ እንደኅጢአት ስለማይቆጠር ጠያቂያችን በዚህ ነገር ተጨንቀው ፀበል ከመጠጣትም ሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት የሚከለከሉበት ነገር የለም።  
 
➡2ኛ/  ከማያውቁት ወንድ ጋር በህልመ ለሊት ግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የሰው ልጅ በራሱ ስጋዊ ስሜት አስቦበትና ፈለጎት ያደረገው ኅጢአት ስላልሆነ መደበኛ የንስሓ ቀኖና አያስፈልገውም። ነገር ግን በህልመ ሌሊት እየመጣ ለወንዱ ሴት መስሎ፣ ለሴትዋ ደግሞ ወንድ መስሎ የሚገናኝ ስጋ የለበሰ እርኩስ መንፈስ ስለሆነ ስጋዊ ህይወታችንንም ሆነ መንፈሳዊ ህይወታችንን ስለሚያበላሸው ከኛም ተለይቶ መወገድ ስላለበት ለአባቶች ቀርቦ በመናዘዝ ልዩ ፀሎት፣ ስግደት፣ እና ጥምቀት ማደረግ ያስፈልጋል። ሁሌ የሚፈታተነን ክፉ መንፈስ ከኛ ተለይቶ እስከሚጠፋልን ድረስ የተለያየ ልዩ ፀጋ ያላቸው አባቶች በፀሎት እንዲያስቡን በማድረግ እኛም በግላችን በምንችለው አቅማችን ዘወትር መፀለይ ያስፈልገናል። እንዲህ በሆነ ግዜ እርኩስ መንፈሱን የእግዚአብሔር ቃል ስለሚያቃጥለውና እኛ ጋር ያለው መንፈሳዊ ህይወትም ስለሚዋጋው ፈፅሞ ይጠፋል ፤ ስለዚህ ጠያቂያችን ይህንን ጉዳይ ንስሓ እንሚያስፈልገው አድርገው ማሰብ የለብዎትም። ስለዚህ ይህ ሲሆን ስንት ቀን ነው ጸበል ከመጠመቅ እና ሌሎች መንፈሳዊ ተግባራት የምከለከለው ላሉት፤ አንኳንስ ለመቆየት እንዲያውም ወድያውኑ ሰይጣን ሊፈትነኝ መጣ ብለን በዛኑ ቀን ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ፀበል መጠመቅና በመስቀል መዳስ እንችላለን
 
➡3ኛ/ ሁሌ ንስሓ መግባት እየሞከሩ ግን የሚረሱት ነገር እንደሚኖር ጠቅሰው ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት፤ በተቻለን መጠን የምናስታውሰውንና ያልረሳነውን ማለትም ጠዋት ማታ ውስጣችንን እረፍት የነሳንን በደላችንን እና ኅጢአታችንን መናዘዝ ከቻልን ከዚህ በላይ እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ነገር የለም። በክርስቲያናዊ ህይወት ስንኖር ሁል ግዜ ማሰብ ያለብን ስለሰራነው ኅጢአት ንስሓ በገባን ግዜ ኅጢአታችን የሚሰረይልን ከእኛ ፅድቅ የተነሳ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቸርነትና ምህረት የተነሳ ስለሆነ ከእኛ የሚጠበቀው አስቀድመን እንደተናገርነው የሰራነውን ኅጢአት መናዘዝና እግዚአብሔር ደግሞ ኅጢአታችንን ሁሉ ይቅር እንደሚል እርግጠኛ በመሆን ማመን ነው። በተቻለ መጠን ሰው የሰራውን ክፉ ስራም ሆነ በጎ ስራ ባይዘነጋ መልካም ነው። ምክንያቱም ሁሉም የህይወታችን ታሪክ ስለሆነ ሃብታችንን፣ ንብረታችንን እድሜያችንን፣ ገንዘባችንን ወዘተ የመሳሰለውን ቆጥረን እንደምናውቅ ሁሉ እና እንደማንረሳ ሁሉ ስለ ኅጢአታችንም ባንዘነጋ መልካም ነው። መክንያቱም የሚያዘናጋንና በደላችንን ችላ እንድንል የሚያደርገን በንስሓ ህይወት እንዳንመላለስ የሚያሳንፈን ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ ክርስቲያን ደግሞ ሁልግዜ የማያንቀላፋ ትጉህ እና ንቁ ሊሆን ይገባል። ለንስሓ የሚያበቁ የኅጢአት አይነቶችን ዝርዝር በሚመለከት አትስሩ የሚበል ነገር ከሰራን፣ አታድርጉ የሚባል ነገርን ካደረግን፣ እንደ ኅጢአታችን ከባድነትና ቀላልነት የሚሰጠን የንስሓ አይነት ይለያያል እንጂ የማንናዘዘው ኅጢአት አይኖርም። ምክንያቱም ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ለቀደሙት አትግደል እንደተባለ ሰምታችኋል የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። እንግዲህ መባሕህ በመሰዊያው ላይ ብታቀርብ በዚያም ወንድምህን አንዳች ባንተ ላይ ቂም እንዳለው ብታስብ በዚያ በመሰዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፤ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” በማለት ወንድምን የሚቆጣ ፣ ጨርቃም ብሎ የሚሳደብ፣ ደንቆሮ የሚል፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ እንዳለበትና መባውም ፀሎቱም ፆሙም ሌላውም መንፈሳዊ አገልግሎቱ ተቀባይነት ስለሌለው እነዚህን ዘወትር እንደ ተራ ነገር የምንጠቀምባቸው የስድብ ቃሎች ሳይቀር ንስሓ እንድንገባባቸው በቃሉ አስተምሮናል። (ማቴ 5፥21-24)
 
ጠያቂያቸን ከዚህ ጥያቄ ጋር አያይዘውም ጸበል ከመጠመቅ የሚያስከለክሉ በደሎች ምን ሞን ናቸው? ብለው ለጠየቁን ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦልን የላክነውን ምላሽ  ከዚህ በታች ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት።
 
ጥያቄው፦ ንስሀ ገብተን ቀኖና ተሰቶን፣ እሱን እየፈጸምን በመሀል ጸበል መጠመቅ መጠጣት እንችላለን ወይስ ቀኖናችን አልቆ እግዚአብሔር ይፍታ እስክንባል መጠበቅ አለብን?
 
የተሰጠው ምላሽ፦  ጠያቂያችን ንስሓ ገብቶ በቀኖና ላይ ያለ ክርስቲያን ፈፅሞ ሃይማኖትን የካደ ካልሆነ ቆሞ ማስቀደስ፣ ፀበል መጠመቅ፣ ፀበል መጠጣት፣ መስቀል መባረክ፣ በክርስቲያኖች ማህበር ጉባዔ መካከል ተገኝቶ የእግዚአብሔርን ቃል መማር፣ በቅፅረ ቤተክርስቲያን ቆሞ መፀለይ ይችላል። ከእንዲህ አይነት ስርአት የሚከለከሉ ጨርሶ ሃይማኖታቸውን ክደው የነበሩ ወይንም ደግሞ ከባድ የተባለ የመጨረሻ ኅጢአት የሰራ ሰው ከሆነ ያ ሱባኤ የሚገባበት ቦታ ሰው የማይደርስበትና ከሰው የማይገናኝበት ልዩ ቦታ ስለሚሆን ያንን ንስሓውን ጨርሶ ከፈጣሪው ዘንድ የይቅርታ ምላሽ እስከሚያገኝ የተለመደውን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማግኘት አይችልም።
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆነ ሌሎቹ የድረገፁ አባላቶቻችን ይህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መጠነኛ ግንዛቤ እንዲሆናችሁ ይህን መልእክት ወደእናንተ ስላደረስንላችሁ በመረዳት እንድትማሩበት አደራ እንላለን።
መልስ፦ ንስሓ የገባ አንድ ክርስቲያን ለ 1 ሱባኤ ለምሳሌ ለ 7 ቀን የንስሓ ግዜ ቢሰጠውና በነዚህ ቀናት ውስጥ የማይሰገድባቸው በአላት ካጋጠሙት ሱባኤውን ሳያቋርጥ ስግደት በሚሰገድባቸው ቀናት ብቻ ሊሰግድ ይችላል። በመሰረቱ ስለ የንስሓ ቀኖና አፈጻጸምና መቼ መስገድ እንዳለብንና፣ እንዴት መፆም እንዳለብንና፣ ምን መፀለይ እንዳለብን ንስሓ የሚሰጡን አባት (ካህን) ከስርዓተ ቤተክርስቲያን አንፃር ዝርዝር መመሪያ ሊሰጡ ይገባቸዋልና ንስሓ የተቀበለውም ክርስቲያን የንስሓ ጊዜውን እንዴት መጨረስ እንዳለበት ከንስሓ አባቱ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ይፈፅማል ማለት ነው።

መልስ፦ ንስሓ ለመግባት የማንኛውም ክርስቲያን መንፈሳዊ ግዴታው ነው። በሰራነው ኀጢአት የሚሰጠንን ንስሓ በሌላ ነገር ለማተካካት አንችልም። እንደ ኀጢአታችን መጠን አባቶቻችን የንስሓ ሱባኤ ሲሰጡን ማድረግ ያለብንን ነገር በቀኖና ቤተክርስቲያን በተወሰነው መሰረት ስግደት መስገድ ካለብን እንሰግዳለን፣ መፆም ካለብን እንፆማለን፣ መጸለይ ካለብን እንጸልያለን፣ ሌላም ለንስሓ ቀኖና ከተሰጠን የተባልነውን እንፈፅማለን ማለት ነው። በእርግጥ በህመም ያሉ በእርጅና ያሉ በእርግዝና ወይም በወሊድ ያሉ በጦር ሜዳ ያሉ ንስሓውን ለመፈፀም በማያመች አስቸጋሪ ቦታ ያሉ ከሆነ ችግራቸውን ለንስሓ አባታቸው በግልፅ በማስረዳት ከችግራቸው አንፃር እየታየ እንደሁኔታው ለንስሓ ቀኖና እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ጠያቂያችን የንስሓ አፈፃፀምን በዚህ አኳያ እንዲያዩት ያስፈልጋል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። ከዚህ ቀደምም ስለ ንስሓ የሰጠናቸውን ሰፊ ትምህርትና መልዕክቶች እንዲያነቡት በማለት እንመክራለን።

ትምህርት ስለ ንስሐ፦ https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ

መልስ፦ ጠያቂያችን ያቀረቡልን ጥያቄ በንስሓ ሱባኤ ላይ እያሉ ያጋጠመዎትን ፈተና ወይም መሰናክል በእርስዎ ታስቦ የተደረገ ካለመሆኑም በላይ ስላጋጠመዎት መሰናክልም በቅዠት መልክ አካል ያለው ሰው መሰል እርኩስ መንፈስ ጾታዊ ግንኙነት እንዳደረጉ በማስመሰል የጀመሩትን መንፈሳዊ አላማ ለማሰናከል ያደረገው እኩይ ተግባር በመሆኑ የጀመሩትን የንስሓ ሱባኤ እንዲያቋርጡ የሚያደርግ ጥፋት አይደለም። ይልቁንም ከተቀበሉት የንስሓ ቀኖና ፍጹም የሆነ የነፍስ ድህነት እንዳገኙና ከሰይጣን ወጥመድ እንዳመለጡ ያረጋገጠው የሰው ልጅ ሁሉ ጥንተ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ የዘወትር ቋሚ ተግባሩ በሰው ልጅ መንፈሳዊ ጉዞ የመሰናክል ወይም የፈተና ድንጋይን ማስቀመጥ ስለሆነ በዚህ ረቂቅ የጥፋት ስራው የያዙትን የተቀደሰ አላማ ያሰናከለ ቢመስለውም በያዙት የንስሓ ጉዞ ያሸነፉት ስለሆነ በህልም ያዩት የሰይጣን መንፈስ ስለሆነ የጀመሩትን አላማ ማቋረጥ የለብዎትም። ስላዩትም የህልመ ለሊት ፈተና መፀለይና ለመምህረ ንስሓዎ ያጋጠመዎትን እንቅፋት በማስረዳት በፀሎት እንዲያስቦት ማድረግ እንጂ ከዚህ ያለፈ ሌላ የእርስዎን የተቀደሰ ተግባር የሚያሰናክል አንዳችም ነገር እንደሌለ ህሊናዎትን ንፁህ ያደርጉ ዘንድ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

መልስ፦ ጠያቂያችን 1 ሳምነት ወይም አንድ ሱባኤ የተሰጠዎትን ስግደት ከፈፀሙ በኋላ በስርዓተ ጋብቻ አብራችሁ የምትኖሩት ውድ ባለቤትዎ (የትዳር አጋርዎ) ጋር ያደረጉት ተራክቦ የፈፀሙትን የንስሓ ሱባኤ ሊያሰናክልዎም ሆነ ሊያሳስብዎት የሚችል አይደለም። በእርግጥ በስግደት የተሰጠዎት የንስሓ ጊዜ ስንት ቀን እንደሆነ ባይገልፁትም ያም ሆነ ይህ በሱባኤ መካከል እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ፈተና ቢያጋጥም እንኳን በተፈተኑባቸው ጊዜያት ከልብ በመፀፀት የፈጣሪን ይቅርታ በንፅህና ጠይቀን ሱባኤያችንን መቀጠል እንጂ የሰይጣን ስራ ዋናው አላማው የጀመርነውን መንፈሳዊ ጉዞ ማሰናከል እና ማቋረጥ ስለሆነ በዚህ ተሸንፈን እጅ ከመስጠት ይልቅ እየወደቅን እና እየተነሳን መፅናት እንጂ ከአላማችን ፈቀቅ ማለት የለብንም።  
 
መታሰብ ያለበት ዋናው ነገር የስጋ ፍላጎታችንን አነሳስተን በራሳችን ላይ ፈተናውን አባብሰን የምንፈፅመው ከሆነ ተጠያቂዎች ነን። በተለይ በስርዓተ ጋብቻ ተወስነን ከምንኖራቸው የትዳር አጋራችን ውጭ የሚደረገው የወንድም ሆነ የሴት ተራክቦ በኀጢአት ሊያስጠይቀን ስለሚችል እንኳንስ በንስሓ ጊዜ ቀርቶ ከዛም ውጭ በሆነ ግዜም ከእንዲህ አይነት መሰናክል ራሳችንን መቆጣጠር እና በህገ እግዚአብሔር ማስገዛት አለብን። ስለዚህ ጠያቂያችን የጀመሩትን የንስሓ ሱባኤ መቀጠል ነው እንጂ ፤ ሱባኤውን እንዲያቋርጡ የሚያስገድድ ፈተና እንዳደረሰቦት መቁጠር የለብዎትም በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

መልስ፦ ጠያቂያችን ያቀረቡልን ጥያቄ በንስሓ ሱባኤ ላይ እያሉ ያጋጠመዎትን ፈተና ወይም መሰናክል በእርስዎ ታስቦ የተደረገ ካለመሆኑም በላይ ስላጋጠመዎት መሰናክልም በቅዠት መልክ አካል ያለው ሰው መሰል እርኩስ መንፈስ ጾታዊ ግንኙነት እንዳደረጉ በማስመሰል የጀመሩትን መንፈሳዊ አላማ ለማሰናከል ያደረገው እኩይ ተግባር በመሆኑ የጀመሩትን የንስሓ ሱባኤ እንዲያቋርጡ የሚያደርግ ጥፋት አይደለም። ይልቁንም ከተቀበሉት የንስሓ ቀኖና ፍጹም የሆነ የነፍስ ድህነት እንዳገኙና ከሰይጣን ወጥመድ እንዳመለጡ ያረጋገጠው የሰው ልጅ ሁሉ ጥንተ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ የዘወትር ቋሚ ተግባሩ በሰው ልጅ መንፈሳዊ ጉዞ የመሰናክል ወይም የፈተና ድንጋይን ማስቀመጥ ስለሆነ በዚህ ረቂቅ የጥፋት ስራው የያዙትን የተቀደሰ አላማ ያሰናከለ ቢመስለውም በያዙት የንስሓ ጉዞ ያሸነፉት ስለሆነ በህልም ያዩት የሰይጣን መንፈስ ስለሆነ የጀመሩትን አላማ ማቋረጥ የለብዎትም። ስላዩትም የህልመ ለሊት ፈተና መፀለይና ለመምህረ ንስሓዎ ያጋጠመዎትን እንቅፋት በማስረዳት በፀሎት እንዲያስቦት ማድረግ እንጂ ከዚህ ያለፈ ሌላ የእርስዎን የተቀደሰ ተግባር የሚያሰናክል አንዳችም ነገር እንደሌለ ህሊናዎትን ንፁህ ያደርጉ ዘንድ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

መልስ፦ ጠያቂያችን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በሃይማኖቱ እና በምግባሩ ፅንቶ በትክክለኛው ክርስቲያናዊ ስነምግባር ተወስኖ የሚኖር ከሆነ እንደተባለውም በደረሰበት ስፍራ ሁሉ  እውነተኛ የቤተክርስቲያን አባቶችን አነጋግሮ የፈፀመውን ኀጢአት ሳይሰውር በመናዘዝ ንስሓ መግባት ይችላል። ምክንያቱም፤ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው እንዲሉ ዋናው አላማ የተፈፀመውን በደልና ኀጢአት በንስሓ ለማስፋቅ በፍጹም ልባዊ እምነት በካህኑ አማካኝነት የተቀበልነውን የንስሃ ህይወት የኀጢያት ስርየት እንደሚያስገኝልን ማመን ብቻ ስለሆነ ነው። በእርግጥም በሰራነው ኀጢአት አፍረን እና ተሸማቀን ክብራችን እንዳይነካ ለመሰወር እና ጥፋታችንን ለመደበቅ የምናደርገው ስጋዊ አስተሳሰብ ካለ ሰውን ብናሞኝ እግዚአብሔርን ማታለል ስለማንችል የዚህ አይነት አካሄድ ከእውነተኛ ክርስቲያን የማይጠበቅ ተግባር ነው። በደረስንበት መንፈሳዊ ቦታ ሁሉ እውነተኛ የቤተክርስቲያን አባቶችን በማነጋገር የዋለው ኀጢአታችን እንዳያድርብን ያደረውም እንዳይውልብን በጊዜውም ያለጊዜውም በአባቶች ጥበቃ የንስሓ ህይወት መኖር ከሁሉም ክርስቲያን ይጠበቃል። ለጠያቂያችንም ሆነ ለሌላው ሁሉ ምክር የምንሰጠው ምናልባት የሰራነውን ኀጢአት ሁሉ ለመደበኛ የንስሓ አባታችን  ለመናዘዝ የምናፍርበት ወይም ካህኑንም የምንጠራጠራቸው ነገር ካለ ስርአታዊ መንገድ ተጠቅመን በመንፈሳዊ ጥበብና በትህትና ሁነን ተሰናብተን ፤ ሳንጠራጠር ከልብ የምናምናቸውን ሌላ አባት መርጠን መያዝ ይገባናል። ይህን የምንልበት ምክንያት ብዙዎቹ ምእመናን ለንስሓ አባቶቻቸው ግልፅ ሆነው የሰሩትን በደል ለመንገር የማይችሉበት ዋናው ምክንያት ምስጢር ይባክንብናል ብለው ከነኀጢአታቸው የሚኖሩ አሉና፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለአባቶቻቸው ግልፅ ለመሆን በአካባቢያቸው በማህበራዊ ህይወት ከመንፈሳዊ አባቶቻቸው ጋር አብረው ስለሚኖሩ የመተፋፈርም ነገር ስለሚያጋጥማቸው በዚህም ምክንያት የሚሳቀቁ ምእመናን እንዳሉ መረጃው ስላለን፤ ከዚህ ሁሉ ስጋት ነፃ ለመሆን የሚያምኑበትን እና የማይጠራጠሩበትን አባት መያዝ እንደሚገባቸው በአፅንዎት እንመክራለን። ለዘላለማዊ የነፍስ ድህነት ጉዳይ የምንሰራውና የምናደርገው ተጋድሎ በስጋዊ አመለካከት ወይም ምድራዊ በሆነ አሰራር የምንኖረው ሂደት ስላልሆነ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። በመጨረሻም ጠያቂያችን በተመሳሳይ ጥያቄ ከዚህ በፊት የላክነውን አጭር ምላሽ እና ስለንስሃ አስመልክቶ የፃፍናቸውን መልዕክቶች ተመልሰው እንዲያነቧቸው ከዚህ በታች ሊንኩን ልከንልዎታል።

ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ተጠይቆ የነበረው ጥያቄ፦ ንስሐ አባት እያለን ሌላ ቤተክርስትያን ብንሄድ በድንገት የምናስታውሰው ሀጥያት ቢኖር እዛው ላገኘናቸው አባት ሐጥያታችንን ብንናዘዝ ችግር ይኖረዋል???

የተላከው መልስ ፦ ማንም ክርስቲያን ባለበት ደብር ወይም አካባቢ ንስሓ አባት እያለው፤ ለሌላ መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ደግሞ ወደ ገዳማት እና ቅዱሳት መካናት ወይም ቦታዎች ሄዶ በዛ ቦታ ላገኛቸው አባት፥ አለኝ የሚለውን አነጋግሮ ወይም ኅጢአቱን ተናዞ አስፈላጊውን የንስሓ ህይወት መቀበል ይችላል። የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይደለም።

ስሐ ንስሓ፦https://yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ/ስለ-ንስሐ

መልስ፦ጠያቂያችን ለመግለጽ የፈለጉትን ነገር በግልፅ ተረድተነው ከሆነ ንስሓ የጊዜ ገደብ አለው ወይ፤ ወይም ለተመሳሳይ ኀጢአት ድጋሚ ንስሓ  መግባት ይቻላል ወይ ከሆነበተመሳሳይ ጥያቄ ከዚህ በፊት የላክነውን 2 አጫጭር ምላሾች እና ስለንስሃ አስመልክቶ የፃፍናቸውን ሌሐሎች መልዕክቶች ተመልሰው እንዲያነቧቸው ከዚህ በታች  ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት።

ጥያቄ፦ንስሓ በገባሁበት ጊዜ ያልተናገርኩት ኀጢአት አለ፤ ይህን ኀጢአት መናገር የለብኝም ወይ? ላሉን ጠያቂያችን የተሰጠ ምላሽ፡

መልስ፦በመሰረቱ ቀኖና ወይም ንስሐ የሚሰጠን በፈጸምነው ኅጥያት መጠን ተለክቶ ስለሆነ እያንዳንዱ ያጠፋነውን ጥፋት ከባድም ቢሆን ሳንፈራ፤ ቀላልም ቢሆን ሳንንቅ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለነፍሳችን እረኛ ላደረግነው ካህን መናገር እንዳለብን የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል። የኅጥያት ደረጃችን ተለይቶ ሲታወቅ ንስሐ የሚሰጡን አባቶችም በጥፋታችን መጠን ስለሆነ ንስሓ ላልገቡበት ኅጥያት እንደገና መናገርና ቀኖና መቀበል ያስፈልጎታል። 

ጥያቄ፦አንድ ሰው ንስሓ ገብቶ ቀኖና ተሰጥቶት እያለ በዚህ መሀል ግን በደል ስራ፤ በዚህ ሰአት ይህ ሰው ምን ቢያደርግ ይሻላል?

መልስ፦  አንድ ክርስቲያን የተፈፀመውን በደል በራሱ ግዜ አምኖ ተፀፅቶ ንስሓ ገብቶ በቀኖና ላይ እያለ ይባስ ብሎ የተሰጠውንም ቀኖና ሳይፈፅም ወደፊት ኅጢአት ላለመስራት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ ሌላ በደል ከፈፀመ ሰውነቱን የተቆራኘው የኀጢአት ደዌ ብሶበታል ማለት ነው። እጅግ ህይወቱ አሳዛኝ ቢሆንም ስለአድን ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ተስፋ ሳይቆረጥ ይሄን ሰው በተለያየ መንገድ የንስሓ አባቱ ወይም ሌላም አባት በቅርብ ውስጣዊ ችግሩን ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስሓ ህይወት እንዲቀርብ እና በተደጋጋሚ ከተፈተነበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አቤቱ ወንድሜ ምን ያህል ቢበድለኝ ምን ያህል ይቅር ልበለው እስከ 7 ጊዜ ነውን ብሎ በጠየቀው ጊዜ እስከ 7 አልልህም 7ቱን አንድ እያልክ እስከ 70 ነው እንጂ” በማለት ለኅጢአት ይቅርታ የጊዜ እና የቁጥር ገደብ እንደሌለው አረጋግጦልናል። (ማቴ 18፥21-22)

ስለዚህ በዚህ መሠረት ከኅጢያት ደዌ እስካልተፈወሱ ድረስ የንስሓ ህይወት አይቋረጥም ይቀጥላል እንጂ።

ስለ ንስሓ ጥያቄና መልስ፦https://yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ/ስለ-ንስሐ

መልስ፦ በ40 እና በ80 ቀን እንዲሁም ከሌላ ሃይማኖት የተመለሱ ሰዎች በማንኛውም የእድሜ ክልል ሁነው በጥምቀት የሚያገኙት የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ክርስትና በተነሱ ግዜ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ካህኑ ሲያጠምቅ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆናቸው የሚያወቁበት የክርስትና ስም ይሰጣቸዋል። ይህ ስም ለማንኛውም ክርስቲያን መለያ ምልክት ስለሆነ የንስሓ አባት፣ ወላጅ ቤተሰብና፣ የክርስትና አባት በዚህ ስም የመንፈስ ልጃቸው የሆነውን ክርስቲያን ይጠሩታል። ስለዚህ በክርስትና ስም ከአለም ዘንድ በምንታወቅበት ስማችን የከበረ እና በክርስቶስ ዘንድ የልጅነት ፀጋ ያጎናፀፈን ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም ስለሆነ ልንዘነጋውና ልናጠፋው አይገባም። ጌታችንና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ሐዋሪያት ከአለም መካከል ከመረጣቸው በኋላ መጀመሪያ በማህበረሰቡ ዘንድ ይጠሩበት የነበረውን ስጋዊ ስማቸውን ለውጦ በእሱ ትምህርት አምነው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ለመሆናቸው ተለይተው የሚታወቁበትና ልዩ ስም ለእያንዳንዳቸው እንደሰየማቸው በቅዱስ ወንጌል ተፅፎ እናገኘዋለን። ማቴ 10፥1 

ይሁን እንጂ ጠያቂያችን እንዳቀረቡት እኛ የቤተክርስቲያን አባቶች እና መምህራን የመንጋው (የሕዝቡ) እረኛ ሆነን እንድንጠብቅ እና እንድናገለግል የእረኞች ሁሉ አለቃ በሆነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሃላፊነት ቢሰጠንም የጥበቃውን ስራ ችላ በማለት በእኛ እና በመንፈስ ልጆቻችን ወይም በመንጋው መካከል ከፍተኛ መራራቅ በመኖሩ ከነጭራሹ ስመ ክርስትናቸው ማን እንደሆነ የንስሓ አባቶቻችንም ሆኑ እራሳቸው ምእመናኑ ጠፍቶባቸው ፤ በሆነ አጋጣሚ ችግር ሲፈጠር ብቻ ክርስትና ስምህ ማነው ወይም ክርስትና ስሜ ጠፍቶብኛል ሰይሙኝ ሲባል መስማት የተለመደ ስራ ሆኗል። ይህ ሁሉ ከመንፈሳዊነት መንገድ ያወጣን ተግዳሮት ስለሆነ በአባቶችም ዘንድ ሆነ በምእመኑም ዘንድ ሊታሰብበት ይገባል። ምክንያቱም አንድ ሰው በአይምሮው ጤነኛ ሰው ከሆነ ስምህ ማነው ተብሎ ሲጠየቅ ስሜን አላውቀውም ብሎ ቢናገር በማንኛውም የሰው አስተሳሰብ ዘንድ ያልተለመደ አጋጣሚ ስለሆነ እጅግ ያስገርማል። እና እንደዚሁ ሁሉ የክርስትና ስሜን አላውቀውም ማለት አሳፋሪ ነው። አባቶችም በዚህ ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አናሳ ስለሆነ በሰው ዘንድ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪም ዘንድ ሊያስወቅስ ይችላል። ጌታችን  መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የበጎቹን ስም እንደሚያውቅና በየስማቸው እንደሚጠራቸው በቅዱስ ወንጌል ተነግሯል። የሐ10፥1 -13  

ይሁን እንጂ እውነተኛውና ትክክለኛው ነገር ከዚህ በላይ የተገለፀው እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ጠያቂያችን እንዳሉት የክርስትና ስማችን ከጠፋብን ወይም ከረሳነው የንስሓ አባታችንን ወይም ደግሞ ስልጣነ ክህነት ያለውን ካህን ተገቢውን ፀሎት አድርሶ ፣ የመንፈሳዊ ምስጢር ተመራምሮ በፈጣሪ ስም፣ በድንግል ማሪያም ወይም በቅዱሳን ስም የክስትና ስም ዳግም ሊሰየምልን እንደሚችል የቤተክርስቲያን ስርዓት ይፈቅዳል። 

ስለዚህ ጠያቂያችን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የዚህ መንፈሳዊ ድረገፅ ተከታታዮች ይህን አጭር መልዕክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል።

እግዚአብሔር አምላክ ክርስትናችንን ያፅናልን

መልስ፦ በነፍስ ዋጋ ለምናገኝበት ነገር ዘለአለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን እና በገንዘብ የማይገዛውን የእግዚአብሔር መንግስት በገንዘብ ለመግዛት ፈጽሞ የሚቻል አይደለም :: እንዲህ ቢሆን ኖሮ በዚህ ምድር በገንዘባቸው ብዛት ምድርን ያስጨነቋት ሀብታሞች ማንም ሳይቀድማቸው መንግስት ሰማይን በእጃቸው ማድረግ ይችሉ ነበር :: ይህን ስንል ግን ጠያቂያችን እንዳሉት መረዳት ያለብን ንስኀ የሚገባው ክርስቲያን በስግደት በፆም በፀሎት የንስኀ ቀኖናውን ለመፈጸም የማይችልበት ከአቅሙ በላይ የሆነ የጤናም ይሁን የሌላ ከባድ ችግር ካጋጠመው ለቤተክርስቲያን አባቶች ተናግረው በቤተክርስቲያን ቀኖና ስለ ንስኀው የገንዘብ መባ ቢያቀርቡ ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል ወይም ላጡ ለነጡ ነዳያን ምጽዋት እንዲሰጥ ይደረጋል።ይህ ግን መደረግ ያለበት አስቀድመን እንደተናገርነው የታወቀ እና የተረዳ ችግር ሲኖር ብቻ ነው።
 
ስለዚህ የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ስጋውን እና ጉልበቱን አድክሞ ጥሮ ግሮ ባገኘው ሃብቱ እንደሚጠቀም ሁሉ ለነፍሳችንም ጉዳይ ጥረን ግረን ፈቃደ ስጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን አስገዝተን በሰራነው የፅድቅ ስራ ዋጋ እንድናገኝበት እራሳችንን ለእግዚአብሔር ብናስገዛ በረከታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ማለት ነው። 
ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር አምላካችን ያግዘን

መልስ፦ በጠያቂዎችን ለቀረበው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ለሁሉም አባላቶቻችን መሰረታዊ ግንዛቤ ማስያዝን በማሰብ ስለሆነ ሁላችሁም ትረዱት ዘንድ አደራ እያልን ከዚህ በፊትም ስለ ስግደት መልስ የሰጠን መሆኑን ብናስታውስም አሁንም ጠያቂያችን ያቀረቡት ለበጐ ስለሆነ ወይም የማያውቁትን ለመረዳት ነውና የንስኀ ስግደትም ሆነ ማንኛውም የስግደት አይነት ስንሰግድ በመንፈሳዊ ህይወታችን ዋጋ ከምናገኝበት እና አጋንንትን ከምንቃወምበት አንዱ ትልቁ ሃይላችን ከስግደት በፊት ፊታችንን በትምዕርት መስቀል በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማማተብ የዘወትር ፀሎት ከሚለው ጀምረን ከፀለይን በኋላ በአቡነ ዘበሰማያት አሳርገን ስግደቱን እንጀምራለን፤ ስንጨርስም በአቡነ ዘበሰማያት ከደመደምን በኋላ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ፣በእንተ አግዚትነ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ 12 ጊዜ እንፀልያለን:: በየጊዜው በምንሰግድበት ጊዜ ከቤተክርስቲያን ውጭ ከሆነ የምንሰግደው ስንሰግድ በፊታችን የጌታና የቅዱሳን ስእል ወይም መስቀል ወይም ቅዱስ ወንጌል ሊኖር ይገባል። በዋናነት ግን የቀኖና ንስኀ የምንቀበለው ከአባቶች ስለሆነ በአንቀፀ ንስኀ በተደነገገው መሰረት ስንሰግድ ምን ማለት እንዳለብን፣ እንዴት መፀለይ እንዳለብን እና ምን መፀለይ እንዳለብን፣ ምክር እና መመርያ ስለሚሰጡን ብዙ የሚያስጨንቅ አይደለም :: የበደልነውን ኀጥያት በልባችን እያሰብን እና እየተፀፀትን ልንሰግድም እንችለን።  ለምሳሌ ስለ ፀሎት እውቀት የሌለው ሰው በፍፁም ሃይማኖት እና በቅን ልቦና ሆኖ ቢሰግድ ለማን እንደሚሰግድ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የውስጣችንን ስለሚያውቀው ስግደቱ ተቀባይነት እንዳለው ማመን አለብን። አንዳንድ አባላቶቻችን ከቤተክርስቲያን ወይም ከአንዳንድ አባቶች ያገኙትን መንፈሳዊ እውቀት ማካፈል ተገቢ ቢሆንም መሰረታዊ እውቀት የሌላቸው አንዳንድ አስተማሪ ነን የሚሉ ሰዎች በልብ ወለድ እና በፈጠራ የፃፉትን እንደ ቤተክርስቲያን እውቀት አድርጐ ማስተላለፍ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ሁላችሁም የዚህ ድረ ገፅ ተከታታዮች ከወዲሁ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንድትማማሩ አደራ እንላለን።

መልስ፦ https://yohannesneseha.org የህንን ሊንክ ተጭነው በአካባቢዎ ካሉ አባት መያዝ ይችላሉ።  ከተቸገሩ በውስጥ መስመር በላክንሎት ስልክ ቁጥር ደውለው ያገኙን።

ንስኀ ተቀብለን ቀኖና በያዝን ጊዜ ጠያቂያችን እንዳሉትም በመጀመሪያ የራሳችንን የተለመደ ፀሎት ወይም ደግሞ የንስኀ አባታችን እንድንፀልይ ያዘዙንን የፀሎት አይነት ካለ እሱን ከፀለይን በኋላ 3 ጊዜ በትምዕርተ መስቀል ፊታችንን በማማተብ ክፉ መንፈስን ከአካባቢያችን አርቀን የተሰጠንን ስግደት እንሰግዳለን። በመጨረሻም በአቡነ ዘበሰማያት እና 12 ጊዜ እግዚአ መሀረነ ክርስቶስ እና በንተ እግዚትነ ማሪያም መሀረነ ክርስቶስ በማለት የሰገድንበትን የንስኀውን ስግደት እንዘጋለን። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ አይነት ንስኀዎን እንዲያከናውኑ ይህን መልዕክት ልከንልዎታል።ተጨማሪ ምክር ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
 
ጠያቂያችን ፤ በእምነት የማይመስለው ሰው ጋር በማህበራዊ ኑሮ መጋራት መንፈሳዊ ጥበብ ነው። የቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት በሌላቸው ሰዎች መካከል አብረው በመምሰል እየኖሩ ነገር ግን በሃይማኖታቸው እና በምግባራቸው ደግሞ ወይም በመልካም አርአያነታቸው ብዙዎቹን የእግዚአብሔር ልጆች በማድረግ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ፣ ከፈቃደ ስጋ ወደ ፈቃደ ነፍስ ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ፣ ከሞት ወደ ህይወት አሸጋግረዋል። እነሱ እንደ ኃጢአተኛ እየተቆጠሩ ብዙዎቹን የፅድቅ ሰዎች አድርገዋል። ስለዚህ ጠያቂያችን ትልቁ ጥፋትና ውድቀት በሃይማኖት ከማይመስሉን ሰዎች ጋር በግብር ስንተባበራቸው ነው።  በሌላ በኩል በፆም ጊዜ የማይፈቀደውን ምግብ እንድንበላ ቢያደርጉን፣ በእግዚአብሔር ስም ያልተባረከውንና ክርስቲያን ያላዘጋጃውን የፍስክ ምግብ እንድንበላ የምንገደድበት ሁኔታ ካለ ሃይማኖታዊ ስነምግባርና ስርዓተ ትውፊታችን አይፈቅድም። አብሮ በመኖር ፣ አብሮ በመነጋገር ፣ በተፈጥሮ ያገኘውን ነገር አብሮ በመጠጣት እና፣ ለሁሉም የተዘጋጀውን ምግብ በመጋራት የሃይማኖት ህፀፅ ስለማያመጣ በዚህ ጉዳይ ላይ አብዝቶ መጨነቅ አያስፈልግም። ብቻ ዘመንና ጊዜውን እየዋጁ እንደ እባብ ብልህ እንደ ርግብ የዋህ ሆኖ መኖር ያስፈልጋል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 
 የተሰጠውን የንስኀ ቀኖና የጨረሰ ማንኛውም ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል የሚያግደው ሥርዓት የለም። ጠያቂያችን እንዳሉት የንስኀ  አባትዎ ቅዱስ ቁርባን አትቀበልም ያሉበትን ምክንያት ግልፅ አድርገው ስላላቀረቡት ለመተቸት ባንችልም ፤ ምንም ይሁን ምን ዋናው አላማ ግን በቅዱስ ቁርባን ሆነ የንስኀ ህይወት ሁለቱም የፅድቅ መንገዶች ስለሆኑ በፈለግነው መንገድ ማከናወን እንደምንችል ክርስቲያናዊ  መብታችን ስለሆነ እኛ ያልተረዳነው ሃሳብ ካለዎት በተላከልዎት የውስጥ መስመር ደውለው ቢያነጋግሩን ተጨማሪ ምክር ለመስጠት ዝግጁ ነን።
 
ጠያቂያችን ስለ ኀጢአት ስርየትና በቅዱሳን ስለሚገኘው አማላጅነት ልዩነቱ ምን እንደሆነ ጠይቀዋል።  የካህናት አባቶች ፥ ኀጢአት የማስተሰረይ ስልጣን የተገኘው የአለምን ሁሉ ኀጢአት ይቅር ማለት የባህሪይ ስልጣኑ ከሆነው  ከእግዚአብሔር ነው። ከዚህ በፊት ስለ ካህናት የንስኀ  አባቶች ስንፅፍ ኀጢአትን እንዴት ይቅር እንደሚሉ በቅዱስ መፅሐፍ ጠቅሰን ማስረጃ ማቅረባችንን እናስታውሳለን። የኀጢአት ማስተሰረይ ስልጣን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተገኘ ስለሆነ ማንም ሰው በህሊናው ጥርጣሬና በሚያጋጥመው የሃይማኖት ህፀፅ እንዴት ይሆናል ለምን ይደረጋል በሚል የጥርጣሬ ማዕበል ውስጥ መንፈሱ እየታወከ መጠየቅ ከክህደት ጉድጓድ ውስጥ ከመውደቅ ያለፈ ቅንጣት ያህል የእግዚአብሔርን ቃል ሊያሻሽል የሚችል የለም። ምክንያቱም ራሱ የሾማቸውን ካህናቱን በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር ኀጢአታቸውን የያዛችሁባቸው በሰማይ ኀጢአታቸው ይያዝባቸዋል፤ በምድር ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው በሰማይ ኀጢአታቸው ይቅር ይባላል፤ እንዲሁም ሂድና ራስህን ለካህን አስመርምር በሚሉት ኃይለ ቃሎች ንስኀ ማንም ሰው የኀጢአት ስርየት የሚያገኝበት እውነተኛ መንገድ እንደሆነ ከራሱ የካህናት አለቃ ከሆነው ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተምረናል። ሁለተኛ ደረጃ  ቅዱሳን አማላጅነትን፤ አላማው አንድ ቢሆንም የነሱ የአማላጅነትና የአስታራቂነት ስራ ደግሞ እንደ ካህናት የእያንዳንዳችን ክርስቲያኖች የንስኀ አባት በመሆን አይደለም። የካህናት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው ካህን ሲሆኑ በነሱ ላይ በመንፈስ ቅዱስ ያደረው የካህን ስልጣን ኀጢአትን የማሰርና የመፍታት አቅም ያለው ሲሆን፤ የቅዱሳት የማስታረቅ ስራ በአፀደ ሥጋም ሆነ በአፀደ ነፍስ እያሉ በስማቸው  የተማፀነ ፣ በስማቸው መልካም ነገር ያደረገ፤ በስማቸው ለእውነተኛ አምላክ የሚገባውን መታዘዝን ያደረገን ሁሉ ሲያማልዱና ሲያስታርቁ እንደሚኖሩ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ቃል ኪዳን ተሰጥቷቸዋል።እነሱም ይህንን ቃል ኪዳን ያገኙት ዛሬ እኛ ቁጭብለን እንደምናስበው ሳይሆን አብዝተው በመፈተን፣ አብዝተው በመፀለይ፣ አብዝተው በመራብና አብዝተው በመጠማት፣ አብዝተው በመጋደል በአጠቃላይ እስከሞት ድረስ የሚያደርሰውን የክርስቶስን ነገረ መስቀል አብዝተው በመሸከም ነው። 
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረ ገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም መገንዘብ ያለባችሁ የሰው ልጅ አንዲድን እንጂ እንዳይጠፋ ለድህነታችን ምክንያት የሚሆን ብዙ መንፈሳዊ ሀብት ተሰጥቷል ማለት ነው። እለት እለት የምንሰራውን ጥቃቅንና ከባድ ኀጢአታችንን ለማስተሰረይ ንስኀ እንዲሰጡን እንዲናዝዙን በህይወታችን ሁሉ ምክር እንዲሰጡን አባቶቻችን ካህናትን የቅርብ አገልጋይ አድርጎ መያዝ ይገባል፤ እንዲሁም በስማቸው በታነፀ ቤተክርስቲያን ዘንድ በመሄድና በቅዱሳን ስእሎቻቸው የሚያማልዱን ቅዱሳንን ሰጥቶናል። ይህ ሁሉ ዋጋ ሳንከፍል እግዚአብሔር የሰጠን በጎ ስጦታ ስለሆነ ይሄ መንፈሳዊ በረከት ሳያመልጠን ይልቁንስ የጊዜ ቀጠሮ ሳናራዝም ለድህነታችን መሽቀዳደም አለብን። 
 
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ቸርነትና በረከት አይለየን
ጠያቂያችን ከሁሉ በፊት ስለ ስባኤ መረዳት ያለብን ምስጢራዊ ትርጒሙንና በሱባኤ ስለሚገኝበት መንፈሳዊ ጥቅም ነው።  ሱባኤ ማለት በግዕዝ  ቋንቋ 7 ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ይህ 7 ቁጥር ደግሞ የአንድ ሱባኤ ጊዜ ማለት ነው። 7 ቁጥር በዕብራዊያን ዘንድ ፍጹም ቁጥር ነው። የቃሉ ምስጢራዊ ትንታኔ ይህ ከሆነ፤ ሱባኤ የተጀመረው በአባታችን በአዳም ነው።  አባታችን አዳም  7  አመት ከ1ወር ከ 17 ቀን በገነት ውስጥ በደስታ ከኖረ በኋላ አታድርግ የተባለውን ትዕዛዝ በማድረጉና አትብላ የተባለውን ዕፀበለስ በመብላቱ ከገነት ርስቱ መባረሩ ምክንያት ስለ ስራው በደል ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው በማልቀሱና በመጮሁ ምክንያት ከፈጣሪው ዘንድ  ይቅርታን ያገኝ ዘንድ 5 ሱባኤ ማለትም 35 ቀናትን በሱባኤ ተወስኖ ወደፈጣሪው ያቀረበው ልመና ተቀባይነት አግኝቶ ከፈጣሪው ዘንድ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ተገብቶለታል። ስለዚህ ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ በኀጢዓትና በልዩ ልዩ ምክንያት የሱባኤ ጊዜ እየወሰኑ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ምህረትን እና ይቅርታን አግኝተውበታል። 
 
ሱባኤ የሚገባው በ2 ምክንያት ነው:- 1ኛው ማንኛውም ክርስቲያን የኀጢአት ፈተና ደርሶበት የበደለውን በደል አስቦ በመፀፀት ከሰውና ከማህበራዊ ኑሮ ራሱን ደብቆና ሰውሮ በለቅሶ በፀሎት ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት ሂደት ነው።  2ኛው ደግሞ ማንኛውም ክርስቲያን ፀጋውን ለማሳደግና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ልዩ ልመና ሲኖረው ጊዜ ወስኖ ቦታ ለይቶ ሱባኤ ይገባል ማለት ነው። በፆም በፀሎት ተወስኖም ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል። በጠየቀውና በለመነው ፍፁም ክርስቲያናዊ ሕይወት አንፃር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለግል ህይወቱና ለቤተሰቡ፣ ለወገንና ለሀገርም የሚጠቅም በጐ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።
 
ሌላው የሱባኤ አስፈላጊነት ፤ እግዚአብሔር አምላክ ስላደረገልን ነገር ሁሉ እና ስለቸርነቱ ብዛት ምስጋና ለማቅረብ፣ ወደፊትም ጠብቆቱና መግቦቱ እንዳይለየን ለመማፀን ፣ ከእናታችን ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳን ሁሉ በረከት ለማግኘት፣ በግል ህይወትም ሆነ በሀገር ላይ ከተቃጣው መቅሰፍት ለመዳን፣ በሃይማኖትና በሥነምግባር ፀንተን በፆም በፀሎት እንድንተጋ የሚዋጋንን ጥንተ ጠላታችንን ዲያብሎስን ድል ለመንሳት፣ የተሰወረና የረቀቀ ምስጢር እንዲገለጽልን በመሳሰሉት መንፈሳዊ ጉዳዮች ሰባኤ መግባት የምንችል መሆኑን በቀኖና ቤተክርስቲያን ታዟል።
 
ሱባኤ ለመግባት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ፤ በግላችን በሰራነው በደልም ሆነ ስለሀገርና ስለወገን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት ለመጠየቅ ሱባኤ ለመግባት ባሰብን ጊዜ፦ 
 
1/   ህሊናዊና አካላዊ ቁርጠኝነትና ስነልቦናዊ ውሳኔን ይጠይቃል። 
2/  ሱባኤ የምንገባበት ምክንያት እንዴትና ለምን እንደሆነ ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር መነጋገርና ምክር መቀበል ያስፈልጋል።
3/  በሱባኤ የምንቆይበት ጊዜ ምን ያህል ሰባኤ እንደሆነ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ፣ እና የሱባኤውን ቦታ (በአትን) መወስን ያስፈልጋል። 
4/   በሱባኤ ጊዜ የምናደርጋቸውን መንፈሳዊ ስርዓት ማለትም እንዴት እንደምንፆም ፣ እንዴት እንደምንፀልይ፣ እንዴት እንደምንሰግድና በመሳሰሉት በስርዓተ ቀኖና መሰረት መንፈሳዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል። 
5/    ሱባኤ በገባን ጊዜ በግል ህይወትና በቤተሰብ ጉዳይ ወይም በማህበራዊ ጉዳይ የሚያሰናክል ፈተና እንዳይመጣብን አስቀድመን ሁኔታዎችን ማስተካከል ያስፈልጋል።
6/   ሱባኤ በገባን ጊዜም እንዴት መተኛት እንዳለብን ምን መልበስ እንዳለብን ባጠቃላይ በሱባኤ የምናሳልፍበት ጊዜያችን የሚያስፈልገንን እና የማያስፈልገንን ነገር ለይተን ለማወቅ ከቤተክርስቲያን አባቶች መመሪያ መቀበል አለብን። 
 
ይህን ሁሉና የመሳሰሉትን ሱባኤ ከመግባ በፊት ልናሰባቸውና በሱባኤ ወቅት ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ናቸው። 
 
ሱባኤ ከጨረስን በኋላ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ደግሞ፦
 
1/   ሱባኤ የገባንበት ምክንያት ኀጢአት ከሆነ ደግመን ላለማድረግ በተቻለ መጠን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳችንን ለበለጠ የሃይማኖት ፅናት ማትጋት ነው። 
2/ ሱባኤ በገባንበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ያገኘነው በጎ ምላሽ ካለም የበለጠ የእግዚአብሔር ፀጋ እንዲበዛልን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ነው።
3/   ማንኛውም ክርስቲያን ቦታና ጊዜ ላይቶ በሱባኤ ፈጣሪውን የሚለምን ከሆነ በፀጋ እያደገ ከመጣ ብዙ ጊዜ ለውድቀት ከሚያበቁት የኀጢአት ምክንያቶች መራቅ።
4/   በፆም በፀሎት በቅዱስ ቁርባን በአጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስነምግባር መንፈሳዊ ጉዞን መቀጠል።
5/   ሥጋዊ ፍላጎትን እና ምኞትን ገዝቶ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝቶ የትሩፋት ሥራ መስራት። 
6/  በአጠቃላይ አለማዊ ሰዎች ከሚሰሯቸው ስራዎች ሁሉ እርቆ በመንፈሳዊ አላማ ፀንቶ መኖርን ይጠይቃል። 
 
እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ምክር የሚሰጠው በአለም እየኖሩ በሱባኤ እግዚአብሔርን ለሚለምኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንጂ ለገዳማውያን ወይም በምናኔ ለሚኖሩ መነኮሳት አይደለም፤ የነሱ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ቀኖናዊ ስርዓት ስላላቸው ነው።
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም፤ ስለ ሱባኤ መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ በዚህች አጭር ፅሁፍ መልዕክት የላክንላችሁ ሲሆን፤ አስፈላጊ ሆኖ ስናገኘው ወደፊት ስለ ሱባኤ አስፈላጊነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ ትምህርት በስፋት  እንዲደርሳችሁ ልናደርግ እንችላለን። 
 
እግዚአብሔር አምላክ በሕዝባችን እና በሀገራችን ላይ ካለው ወቅታዊ ፈተና ይጠብቀን
በቅድሚያ በድያለሁ ጥፋት ሰርቻለሁ ኅጢአት ፈጽሜያለሁ ብሎ ኅጢአትን ለመናዘዝ ፈቃደኛ መሆንና የኅጢአት ሥርየት ለማግኘት መፈለግ የእውነተኛ ክርስቲያን መገለጫ ነው። ከእውነተኛ ሃይማኖትና ምግባር ስንርቅ ግን የንስሐ ህይወታችን ጨርሶ ይቀጭጫል። ያኔ ደግሞ በሰራነው ኀጥያት (ጥፋት) ነፍሳችን ፈፅሞ ትቃተታለች ትጨነቃለችም። ስጋችን ምድራዊ የሆነውን የስጋ ስራ ለመስራት ነፍሳችን ደግሞ ሰማያዊ የሆነውን የፅድቅ ስራ ለመስራት ለኛ ግልፅ ሆኖ በማይታወቅና በማንረዳው ሁኔታ ሁለቱም ህይወታችንን የጦር አውድማ ሲያደርጓት በኛ ላይ የፍርሃት መንፈስ ይነግስብናል። ከጥፋታችን ተመልሰን ንስሐ እንዳንገባ ደግሞ የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው እና የእኛን ፅናት የማይፈልገው ሰይጣንም ግራ እንዲገባን እና የፍርሃትና የጭንቀቶቻችን ምክንያቶች እንዲበዙ ያባብስብናል። ስለዚህ፤ ጠያቂያችን የምንመክርዎት ይህ የሰይጣን ውግያ ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ የፍርሃትና የጭንቀት አምላክ ሳይሆን የፍቅርና የሰላም አምላክ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወምዎትን የጭንቀት መንፈስ እንደምንም ታገሉት በማለት ምክራችንን እንለግሳለን። ምክንያቱም እግዚአብሔር በኅጢአት ጠፍተን እንዳንቀር ተመልሰን ንስሓ እንድንገባ የሚፈቅድ አምላክ ስለሆነ፤  ለዘመናት ከሰራነው ኅጢአት ይልቅ ንስኀ ገብተን በተወሰነ የቀኖና ግዜ የሰራናት ፅድቅ ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ጥፋት አስፍቃ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት እንድንበቃ ታደርጋለችና።  
 
የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ በውስጥ መስመር በላክንልዎ ቁጥር ደውለው የመኖርያ አካባቢዎን (የሰፈርዎን ልዩ መጠርያ) ቢገልጹልን በአካባቢዎ ካሉ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን የንስኀ አባት እንሰጥዎታለን። ወይም እርስዎ ራስዎ ድረገፃችን ላይ ወደሚገኘው የንስሐ አባት ፔጅ በመግባት ወይም ይህን ሊንክ በመጫን፦ https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/ የመኖርያ አካባቢዎን መርጠው 15 ሴኮንድ ብቻ የሚወስደውን ፎርም ሞልተው ‘submit’ የሚለውን ሲጫኑ የንስኀ አባት ስልክ ይደርሶታል፤ ደውለው ቀጠሮ በመያዝ ቀርበው ያማክሯቸው። የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለው ቢያምኑም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና ፍርሃቶትን አርቀው በንስኀ ህይወት ወደ ይቅር ባይ አምላክ ይቅረቡ። እግዚአብሔር ከእርስዎ ህይወት ጨርሶ ስላልራቀ በውስጥዎት ፀፀት እና ወደ እግዚአብሔር መመለስን እያንፀባረቁ በመሆኑ ፈፅሞ ከጠሉት ህይወት ውስጥ እንደሚወጡና እግዚአብሔርም እንደሚረዳዎት እናምናለን።
 
የበለጠ መንፈሳዊ ምክር እንድንሰጥዎ ከፈለጉ በውስጥ መስመር በላክንልዎ ቁጥር ደውለው ያነጋግሩን፤ የደረሱበትንም ሂደት ይግለፁልን። ለሁሉም ነገር ወላዲት አምላክ ድንግል ማርያም በአማላጅነትዋ ታግዝዎ።

 ጠያቂያችን ወደ ገዳም መሄድ የተቀደስ ተግባር ቢሆንም ለምን እንደሚሄዱ ግን ግልፅ ስላልሆነልን የምንሰጥዎት ምክር በምን መንገድ እንደሆነ ለመወስን ያስቸግራል። የሆነ ሆኖ ገዳማት የእግዚአብሔር የቅድስና ቦታዎች ስለሆኑ በምናኔ ህይወት የሚኖሩ ፍጹማን መነኮሳት በፆምና በፀሎት ወይም በመንፈሳዊ ተጋድሎ የሚኖሩበት የቅድስና ህይወት ስለሆነ በዓለም የሚኖሩት ሰዎች ወደገዳም የሚሄዱት አንድም በገዳማት ስርዓት ተወስነው ለመኖር ሲሆን ሌላው ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ሱባኤ ገብቶ ኀጢአትን በንስኀ ህይወት ለማጠብ እና ከገዳሙ በረከት ለማግኘት ነው። ስለዚህ ገዳም በሥጋም ሆነ በነፍስ ካጋጠመን ፈተና ታክመን የምንድንበት መፍትሔ ስለሆነ ወደ ገዳም ሲሄዱ ማድረግ የሚገባዎት በፍፁም ቁርጠኝነት ልባዊ በሆነ እምነት ፀንተው በሥጋ ሲፈተኑበት የነበረ ኀጢአትም ካለ እሱንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእርስዎ በንስኀ ለማራቅ ወስነው መሄድ አለብዎት። ከላይ እንደገለፅነው ፈጽሞ ለምናኔ የሚሄዱ ከሆነ ደግሞ ማድረግ ያለብዎትን ቅድመ ሁኔታ ስለሚኖር ግልጽ የሆነ ሃሳብዎን በውስጥ መስመር በላክንልዎ ቁጥር ደውለው ቢያማክሩን ተጨማሪ ምላሽ ልንሰጥዎ እንችላለን። ለሁሉም የእግዚአብሔር ፈቃድ ከእርስዎ ጋር ይሁን።

ጠያቂያችን ወደ ገዳም ለመሄድ ያሰቡት ለተወሰነ ጊዜ ለሱባኤ እንደሆነ ስለተረዳን ያሰቡትን መንፈሳዊ አላማ በሰላም ፈፀመው እንዲመለሱ እየተመኘን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሄድ ይችላሉ። ዋናው መረዳት ያለብዎት ማንኛውም ክርስቲያን ወደ ገዳም በሄደ ጊዜ የእግዚአብሔርን በረከት እንደሚያገኝ እስካመነ ድረስ ከመሄድ የሚከለከልበት ነገር የለም።ወደ ገዳም በሄዱ ጊዜ በፍጹም እምነት ሆነው መጸለይና ለረዥም ጊዜ በቦታው የቆዩ የእግዚአብሔር ፀጋ አብዝቶ ያደረባቸው አባቶች ስለሚኖሩ ወደነርሱ ቀርበው ትምህርትና ምክር ማግኘት እንዳለብዎም እንመክራለን። ጠያቂያችን  ምናልባት ከዚህ ሌላ በውስጥ ያሳስብዎት ጉዳይ ካለና እኛ ሃሳብዎን ሳንረዳ ቀርተን ምላሽ ያልሰጠንዎት ነገር ካለ ውስጥ መስመር ደውለው ሊያማክሩን ይችላሉ።  እግዚአብሔር አምላክ ምኞትዎን ፈጽመው እንዲመለሱ እርዳታው አይለዮት።

 ስለ ምህላ ፀሎት የጠየቁን ጠያቂያችን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የሚከተለውን ምላሽ እንዲደርሳችሁ አድርገናል፡፡ የምህላ ፀሎት በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተለመደ ቀኖናዊ ሥርዓት ነው። ክርስቲያን በተለይ ክርስቲያናዊ ጉዞ ውስጥ የሚኖሩ አማኞች በሥጋቸው ሆነ በነፍሳቸው ከሚገጥማቸው ፈተናና መሰናክል ለመዳን የሚችሉበት ትልቁ ሃይላቸውና መመኪያቸው የምህላ ፀሎት ነው። የምሕላ ፀሎት ከተቃጣው ድንገተኛ መቅሰፍትና መዓት ለመሰወር የሚያስችል ጋሻ ነው። ለምሳሌ የነነዌ ሰዎች በነብዩ ዮናስ አማካኝነት የተናገራቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የተለየ የምህላ ፀሎት አውጀው ወደ ፈጣሪያቸው ጩኸታቸውን በማሰማታቸው ከታዘዘባቸው መቅስፍት ለመዳን እንደቻሉ በነብዩ ዮናስ የትንቢት መፅሐፍ ተመዝግቦ እናገኘዋለን።እስራኤል ዘሥጋም ወደ ባቢሎን ሀገር በምርኮ በሄዱ ጊዜ በነብዩ በዳንኤል አማካኝነት የምህላ አዋጅ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ያቀረቡት ፀሎትና ልመናቸው ተሰምቶ ከምርኮ ለመመለስ በቅተዋል። 
 
በአጠቃላይ የምህላ ፀሎት ማለት በግልም ሆነ በማህበር ከምንፈራውና ከምናየው የነፍስም ሆነ የሥጋ ፈተና፣ ወይም በሀገር ላይና በሕዝብ ላይ የተቃጣ ወቅታዊ መቅስፍት ሁሉ ለመዳን የሚደረግ የሱባኤ ፕሮግራም ስለሆነ  ጠያቂያችን ያቀረቡትን የጥያቄ ሃሳብ በዚህ ማብራሪያ ይረዱት ዘንድ ይህን መልዕክት ልከንሎታል።

ጠያቂያችን ስለ ተቀበሉት የንስኀ ቀኖና ለሌላ ሰው በመናገርዎ እንደ ጥፋት የሚቆጠርብዎ ስላልሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ መጨናነቅ አያስፈልግዎትም :: በእርግጥ በተቻለ መጠን በሃይማኖታችን ስለምናከናውናቸው ወይም ወደንና ፈቅደን ስለምናደርጋቸው የትሩፋት ሥራዎች ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንብን ለሌላ ወገን ማስወራትና ማስነገሩ አስፈላጊ አይሆንም። በስውር ያገለገልነውና ያደረግነው ሁሉ በፈጣሪ ዘንድ በግልፅ እና በአደባባይ ዋጋ ሰላምናገኝበት ለዝናና ለይስሙላ ለሰው ከመናገር ይልቅ ለእውነተኛው አምላክ የነገርነው ከሁሉ ስለሚበልጥ ጠያቂያችን እንደ ስርዓተ ቤተክርስቲያን ይህን ምክር ቆሚ ትምህርት አድርገው ወደፊት እንዲማሩበት ሆኖ ለአሁኑ ግን የተቀበሉትን የንስኀ ቀኖና ሊያፈርስ የሚችል ስላልሆነ በአላማዎት ፀንተው እንዲቀጥሉ ይሄንን ምክር እንዲደርስዎት አድርገናል።

 የቀኖና ንስኀ የምንቀበለው ከአባቶች ስለሆነ በአንቀፀ ንስኀ በተደነገገው መሰረት ስንሰግድ ምን ማለት እንዳለብን፣ እንዴት መፀለይ እንዳለብን እና ምን መፀለይ እንዳለብን፣ ምክር እና መመርያ ስለሚሰጡን ብዙ የሚያስጨንቀን አይደለም:: በጥቅሉ ግን መረዳት ያለብን የበደልነውን ኀጥያት በልባችን እያሰብን እና እየተፀፀትን መስገድ እንደምንችል እና በስግደቱም ምህረትን እንደምናገኝ ማመን አለብን።  ለምሳሌ ስለ ፀሎት እውቀት የሌለው ሰው በፍፁም ሃይማኖት እና በቅን ልቦና ሆኖ ቢሰግድ ለማን እንደሚሰግድ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የውስጣችንን ስለሚያውቀው ስግደቱ ተቀባይነት እንዳለው ማመን አለብን። በዋነኝነት በየጊዜው በምንሰግድበት ጊዜ ከቤተክርስቲያን ውጭ ከሆነ የምንሰግደው ስንሰግድ በፊታችን የጌታና የቅዱሳን ስእል ወይም መስቀል ወይም ቅዱስ ወንጌል ሊኖር ይገባል።
 

ስለ ንስሐ የሰጡት ትምህርቶች

👉ጥያቄ፦ ላጠፋነው ጥፋት እግዚአብሔርን በቀጥታ ይቅር በለን ማለት አንችልም ወይ ለአባቶች ከመናዘዝ ይልቅ ማለቴ ነው።

መልስ፦ ይሄ አነጋገር በአብዛኛው ከእውነተኛዋ ሃይማኖት ወይም ከቀጥተኛ መንገድ የወጡ ሰዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ችግር የሚፈጠረው የእግዚአብሔርን ቃል እያጣመሙ ከዋናው መንገድ ሊያወጡን ቀጥተኛውን ነገር የሚያጣምሙ ሰዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ እኛን ሊያሰናክለን ወይም ደግሞ መናፍቃን በሚያቀርቡልን የክህደት ትምህርት ህሊናችን ሲሰናከልብን የሚቀርብ ጥያቄ ይመስላል።

መታወቅ ያለብት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ይቅር ባይና ኃጢአትን የሚያስተሰረይ እግዚአብሔር እንደሆነ ነው። ይህን ከዚህ በፊትም ሰፋ አድርገን ማስተላለፋችንን እናስታውሳለን፤ ምናልባት ጠያቂያችን ካልተመለከቱት እንዲደርስዎ ስለምናደርግ በመስመር ሆነው እንዲከታተሉ አደራ እያልን አሁን ላቀረቡልን ጥያቄ ግን የሚከተለውን አጭር ማብራሪያ ሰጥተንበታል።

ሐዋሪያው እንዳለው በአይንህ የምታየውን በተፈጥሮ አንተን የሚመስልህን እለት እለት በማህበራዊ ኑሮና በማንኛውም ኑሮ አብሮህ ያለውን ወንድምህን የማትወድ ከሆንክ ታዲያ አንድ ቀን አይተሀው የማታውቀውን ፈጣሪን እንዴት ልትወደው ትችላለህን ይላል። ስለዚህ እኛ እዚህ እግዚአብሔር እራሱ ሾሜያቸዋለሁ ኀጢአትን እንዲናዝዙ ንስሐ እንዲሰጡ በመንጋው ላይ በህዝቡ ላይ ሾሜያችኋለሁ ኃጢአቱን የያዛችሁበት የተያዘ ይሆናል፤ ኃጢአቱን ይቅር ያላችሁለት ደግሞ ኃጢአቱ ይቅር ይባልላቸዋል። ብሎ የሾማቸው ሰዎች በአይናችን የምናያቸውን ሰዎች አምነን በእነሱ አማካኝነት እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን እንደሚማለደን ማመን ያቃተን ሰዎች ታዲያ ይሄን ያህል ለካህን ቀርቦ ኃጢአትን መናገር ለክብራችን እንደማይመጥነንና እንደሚያንስብን በመቁጠር እራሳችንን ከፈጣሪ ጋር አስተካክለን ወይም ከካህናት በላይ ብቃት እንዳለን በማሰብ ይሄን ያህል መጨናነቅና መፈላሰፍ የለብንም። መቼም የመጨረሻው መደምደምያና ሁላችንንም ሊያስማማን የሚችል የእግዚአብሔር ቃል ነው።

ስለዚህ ጠያቂያችን ወደ መልሱ የምንሄድበት መንገድ፦ ሂድና እራስክን ለካህን አሳይ፤ ሂድና የነፍስህን በሽታ ወረርሽኝ በካህን መንፈሳዊ ሀኪም በሆነው በካህኑ አስመርምር ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀጥታ ማዳን ስልጣኑ ሆኖ እያለ ማዳን እንደሚችል ሁሉ ብዙ አስገራሚ ተአምራቱን ያየንበት አምላክ ግን ያንን በማቴዎስ 8 የተጻፈውን ቃል ሂድና ራስህን አስመርምር ስላለን እኛም እንደ ሕጉ እንደ ቃሉ እንፈፅማለን ማለት ነው። በነሱ ስለሚማለድና፥ እንደሚማለድም ስለነገረን ነው። በአካለ ስጋ ያሉ አባቶቻችን ካህናትም እነሱ እንኳን ሰው እንደመሆናቸው መጠን በስጋ ቢደክሙና አንዳንድ ጥፋት አጥፍተው ብናይ በነሱ ላይ ያደረው ስልጣነ ክህነት እኛም በፍፁም እምነት ስለሆነ የምንቀርበው እኛ ኃጢአት በመናዘዝ እነሱ በሚሰጡን የኃጢአት ስርየት አምነን ወደ እነሱ እስከቀረብን ድረስ በዚህ ላይ ስልጣን ያለውና ሁሉን ነገር በረቂቅ ጥበቡ የሚፈጽመው አምላክ ነው።

ስለዚህ ጥቃቅን ነገር እየመዘዝን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጠላት ዲያብሎስ ልባችንን እያስታበየ እንዴት ለካህን ቀርቤ እናገራለሁ ደሞ እሱስ ካህኑ ከእኛ የተሻለ ህይወት ምን አለው እያልን እያብጠለጠልን በየሜዳው አፋቸውን ሲከፍቱ የሚውሉ መናፍቃን የካህንን ክብር ሲያጎድፉ እየሰማን አንዳንዱም ደግሞ እምነት እና ሃላፊነት የጎደላቸው ፤ ካህን ሳይሆኑ መነኩሴ ሳይሆኑ ካህን ነን እያሉ የሚያጭበረብሩ ለግል ጥቅማቸው የተሰለፉ የሚያደርጉት አስመሳዮችንም እያየንም የካህን ክብር በዚህ አይነት ማየት እና ማቃለል እኛን ወደበለጠ ጥፋት እና ወደ በለጠ ክህደት ያደርሰናልና በህይወታችን ስለማያንጸን መጠንቀቅ እንዳለብን እንመክራለን

ቴሌግራም ግሩፓችንን በየቀኑ ይከታተሉ፣ ለወገንዎትም ሼር ያድርጉ፡-
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

እግዚአብሕር ማስተዋሉን እና ጥበቡን ለሁላችንም ይስጠን


👉ጥያቄ፦በ #ንስሐ የማይሰረይ #ኀጢአት አለን? ወይስ የለም?

መልስ፦ ጠያቂያችን፦ ፈፅሞ በንስሐ የማይሰይ ኀጢአት የለም። ምናልባት የመጨረሻ ከባድ ኀጢአት የሰራን ኀጢአተኞች ብንኖር፤ እንደ ኀጢአቱ ክብደት እኛም በሚያልፈው በሚሞተው በሚበሰብሰው ደካማ ስጋችን የማያልፍና የማይሞት ለዘለአለም በነፍስ የሚያስጠይቀን ኀጢአት ለመስራታችን ሰው ደግሞ በሰማይ ካለው ዘለዓለማዊ ሞት ተጥሎ እንዳይቀር ከወዲሁ በዚሁ ደካማ ባህሪይ በለበስነው ስጋችን የሰራነውን ኀጢአታችንን ይሄንኑ ደካማ ስጋችንን በንስሐ ህይወት ለነፍስ ስራ በማስገዛት እግዚአብሔር በሾማቸውና እኛንም ቢሆን ከኀጢአታችን ለመናዘዝ የኀጢአት ስርየት ወደሚያስገኙልን ወደ አባቶቻችን ቀርበን ከልብ በሆነ መፀፀት አንዳችም ነገር በሰው ሰውኛ አፍረን ተሳቀን የምንደብቀው ኀጢአት ሳይኖር ከተናዘዝን እና በሰራነው የኀጢአት መጠን ቀኖናችንን ተቀብለን በስርዓት ከልብ በተሰበረ ህሊና በፍፁም መንፈሳዊ ስርዓት ሆነን ከፈፀምነው ፈፅሞ የማይሰረይ ኀጢአት የለም። እግዚአብሔር አምላካችን ሰው የሆነበት ዋናው ምስጢሩ የማይሰረይና ከእኛ የማይለይ የሚመስል በምድር ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል የኀጢአት አይነት እንድንሰራ በሰይጣን ባርነት ውስጥ ወድቀን ሰይጣን በረቂቅ መንፈሱ ያዘዘንን ሁሉ እንድንፈፅም፤ ሁላችንም ባንሰራውም በአዳማዊ የተፈጥሮ ባህሪያችን ኀጢአት በውርስ ለሁላችንም እየደረሰ 5ሺ500 ዘመን የሰይጣን ባሪያዎች ሆነን በኀጢአት ቀንበር ተይዘን ኖረን እግዚአብሔር አምላክ በራሱ መለኮታዊ ጥበብ እና እኛን ከመውደዱ የተነሳ አለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ሆኖ ስጋን ተዋህዶ አለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣልና ይህ ቀረሽ የማይባል የአባትነት የአምላክነት ስ ሰርቶ ከዚያ ከከባዱ ኀጢአታችን ነፃ አውጥቶናል። ዛሬም ቢሆን ጠፍተን እንዳንቀር ዳግም በየጊዜው የሚደርስብንን የኀጢአት ውድቀት በንስኀ እንድንነሳ ንስሐ የሚሰጡንን ከታሰርንበት የኀጢአት ማሰሪያ የሚፈቱንን አባቶች ስላስቀመጠ በፍጹም ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በንስሐ የማይሰረይ ኀጢአት አለ ብሎ ማመን እንደውም እንደ ሃይማኖት ክህደትም ይቆጠራል።
አባቶች ካህናት የጢአታችንን ክብደት የኀጢአታችንን አይነ ት ተመልክተው በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሰረት የታዘዘውን ለኀጢአታችን ስርየት ይሆን ዘንድ የሚሰጡንን ቀኖና ከፈፀምን እንዲሁም ወደ ንስሐ ህይወት ስንቀርብ ስጋዊ እና በሰው ዘንድ ለመታየት ሳይሆን ከልብ በመፀፀት ውስጣዊ ህሊናችንን መመርመር የእራሱ ባህሪይ የሆነው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከውስጥ መፀፀታችንን ከሁሉ ቀድሞ ስለሚያውቅ ልቦታችንን በፍፁም በመመለስ ለእግዚአብሔር አስገዝተን ንስሐ ከገባን የማይሰረይ ኀጢአት የለም። እነንተ የፈታችሁት የተፈታ ይሆናል እናንተ ኀጢአታቸውን የያዛችሁባቸው ደግሞ የተያዘ ይሆናል የሚል ቃል ተፅፏልና፤ ይሄን ጥያቄ ያቀረቡልን አባላችን እና ይሄን መልእክት የምትከታተሉ ኦርቶዶክሳዊ ወገኖቻችን ፥በዋናነት አስቀድመን የምንመክረው ኀጢአትን ላለመስራት ፣ በኀጢአትም ተመልሰን ላለመውደቅ፣ ራሳችንን ከኀጢአት ለመለየት የምንችለውን ጥረት ሁሉ ማድረግ አለብን። ከአቅማችን ባላይ በሆነ ምክንያት ካልወደቅን በስተቀር አስበንበት እቅድ ይዘን የምንሰራው ኀጢአት ግን መኖር የለበትም። ሁላችንም ሰይጣን በስንፍና እንድንኖር እንዳንፀፀት፣ ንስሐ እንዳንገባ ቀጠሮዋችንን እያራዘመ ወደ ንስሐ የምንቀርብበትን ቀን በብዙ ፈተናና መሰናክል እያደናቀፈ በኀጢአት ላይ ኀጢአት እየጨመረብን እንድንቀጥል የሚያደርገን እሱ ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ የዲያብሎስን ሽንገላ እና የዲያብሎስን ፈተና ፈፅሞ ልንቃወመውና ድል ልንነሳው ይገባል።

ስለዚህ ጠያቂያችን ከላይ ያብራራነውን መሰረታዊ የንስሐ ትምህርት በዋናነት እንዲረዱት እየመከርን ምናልባት አሁን እርስዎ “ይቅር ስለማይባል ኃጥያት ብታብራሩ?” በማለት ያቀረቡት የጥያቄ መነሻ ሃሳብ ፥ በመጽሐፍ ‘መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ኀጢአቱ አይሰረይለትም’ ከሚለው ቃል ተነስተው ከሆነ ይህም ለምን እና ከምን አንጻር እንደሆነ ገልጸን ያስተላለፍነውን ማብራሪያ እንደሚከተለው ልከንልዎታልና ይህን አንብበው ይረዱት።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋለ ስጋዌው ህሙማነ ስጋን በተአምራቱ ህሙማነ ነፍስን በትምህርቱ እየፈወሰና በቃሉ እያጸና ማንም ሊሰራው የማይችለውን ድንቅ ስራ እየሰራ በሚመላለስበት ጊዜ ፈሪሳውያን እና የአይሁድ ወገኖች የሚያደርገውን ተአምራቱን በእሱ መለኮታዊ ኃይል የተሰራ መሆኑን አምነው ላለመቀበል ሲሉ ሌላ ኃይል ወይም በእርኩስ መንፈስ ኃይል እንደሚሰራ በድፍረት ይናገሩ ስለነበረ ይህ ክህደታቸው ደግሞ የባህሪይ አምላክ መሆኑን ወይም እግዚአብሔርነቱን የካዱ ስለሆነ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ጋኔን ወይም እርኩስ መንፈስ አድሮበታል ብሎ ከመሳደብ የበለጠ ሌላ ምንም ክህደት ስለሌለ በዚህ ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ 1ኛ/ “ስለዚህ  እላችኋለሁ፥  ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች  ይሰረይላቸዋል፥ ነገርግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም።  በሰው ልጅ  ላይ ቃል  የሚናገር  ሁሉ  ይሰረይለታል፤  በመንፈስ  ቅዱስ  ላይ  ግን  የሚናገር  ሁሉ  በዚህ  ዓለም  ቢሆን  ወይም  በሚመጣው  አይሰረይለትም።”  በማለት የተናገረው ከዚህ አንፃር ነው። (ማቴ 12፥31፡32)

እንዲሁም 2ኛ/ “እውነት  እላችኋለሁ፥  ለሰው  ልጆች  ኃጢአት  ሁሉ  የሚሳደቡትም  ስድብ  ሁሉ  ይሰረይላቸዋል፤ በመንፈስ  ቅዱስ  ላይ  የሚሳደብ  ሁሉ  ግን  የዘላለም  ኃጢአት  ዕዳ  ይሆንበታል  እንጂ  ለዘላለም  አይሰረይለትም።  ርኵስ  መንፈስ  አለበት  ይሉ ነበርና።”  በማለት አይሁድ ፥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ፣ የባህሪይ አባቱ እግዚአብሔር የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለትን፣ እንዲሁም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያለመለየት አንድ መሆኑን በእርግብ አምሳል በራሱ ላይ መገለፁን አምነው ሳይቀበሉ ጋኔል ወይም እርኩስ መንፈስ አድሮበታል በማለት መናገራቸው መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ወይም መካድ ስለሆነ፤ የሰው ልጅ ደግሞ ከኀጢአት ሁሉ የመጨረሻ ኀጢአት እና በንስኀም የማይታጠብ ትልቁ በደል ኀጢአትን ይቅር የሚል ፈጣሪን መሳደብ ስለሆነ ፈጣሪውን የተሳደበ ከሆነ ደግሞ በማንም ሊቀር ስለማይችል መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ንስኀ የለውም የሚባለው ለዚህ ነው። (ማር 3፥28፡29)

3ኛ/ ካህኑ ኤሉ በእድሜ በሸመገለ ጊዜ እሱን ተክተው የእግዚአብሔርን ቤት ያገለግሉ የነበሩ ሁለቱ ልጆቹ በእግዚአብሔር ፊት አስጠያፊ የሆነ ኀጢአት በመፈፀማቸው ምክንያት አባታቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንደተጣሉ ሲነግራቸው “ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው?” (1ኛ ሳሙ 2፤25) በማለት ሰው ከሰው ጋር ቢጣላ ወይም ሰውን ቢሳደቡት በእግዚአብሔር ስም በመማፀን ሊታረቅ ይችላል በደሉም ይቅር ይባልለታል ፤ ከፈጣሪ ጋር ከተጣላን አስታራቂ ሽማግሌ ሊኖር ስለማይችል ለዚህ ነው በማቴዎስ ወንጌል መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ኀጢአቱ አይሰረይለትም የተባለው።

ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ባርያዎቹን አገልጋዮቹን ልጆቹን የማይዘነጋ ቸል የማይልየማይል አምላክ ስለሆነ እሱ ሃይሉን እና ጥበቡን እሱ ያድለን።

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ

ስለ ንስሐ (ጥያቄና መልስ)

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሐ ድረገጽ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላት ፤ ስለ #ንስሐ ህይወት በሚመለከት ከዚህ በፊት ቀርበው የነበሩት ጥያቄዎች ሁሉ ከነመልሶቻቸው በተከታታይ እንዲደርሳችሁ ለማድረግ “ክፍል አንድን” እንደሚከተለው የላክን ሲሆን ቀሪዎቹንም ክፍሎች በቀጣይ ቀናት ስለምንልክ በመስመር ሆናችሁ እንድትከታተሉት እንገልጻለን።

ክፍል 1 (10 ጥያቄና መልሶች)

👉👉👉ጥያቄ#1 ፦ #ንስሐ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ፦ ንስሓ የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን በአማርኛ ትርጓሜው ወይም የቃሉ ፍች እና ማብራሪያ፦ ማዘን፣ መፀፀት፣ መቆጨት፣ መቀጣት፣ ቀኖና መቀበል፣ ስለተሰራው ኀጢአት ካሳ መክፈል።፣ የሰሩትን በደል እና ጥፋት ማመን፣ አና በአጠቃላይ ማንኛውም ክርስቲያን ስለሰራው ኀጢአት ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው ሲመለስ የሚቀበለውን የቀኖና ንስሐ ያመለክታል።

አንድ ክርስቲያን ንስሓ ለመግባት ተዘጋጀ ወይም ንስሓ ገባ ሲባል ማመኑን፣ መፀፀቱን፣ ወደ እግዚአብሔር መመለሱን፣ ክፉ ፀባዩን መተዉን፣ ከጥፋት ስራ መቆጠቡን እና መታረሙን የምናውቅበት መንገድ ነው። በተጨማሪም ንስሓ ማለት አንድ ክርስቲያን በሰራው ጥፋት በፈፀመው ኅጢያት እና ባደረገው ስህተት ሰለተፀፀተ እና ስለተቆረቆረ ሌላ ጊዜ ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላውን እና ሰማያዊ የዘላለም ህይወት ሊያሳጣው የሚችል ኀጢያትን ላለመፈፀም የመጨረሻ ውሳኔ የሚደርስበት የመደምደሚያ ሃሳብ ነው።


👉👉👉ጥያቄ#2 ፦.የንስሐ ጠቀሜታ ምንድነው?

1/ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ማስረጃ፦

– የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ሚልክያስ እንደተናገረው “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርአቴ ፈቀቅ ብላችኋል። ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሣለሁ” በማለት ከእግዚአብሔር ሕግ በመተላለፍና ትእዛዙን በማፍረስ ለበደሉት ሰወች የንስሓ ጥሪ እንዳቀረበላቸው እንመለከታለን።(ሚል 3፥7)
– ጠቢቡ ሰለሞን “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፣ የሚናዘዝባት እና የሚተዋት ግን ምህረትን ያገኛል” በማለት ስለ ኀጢአት ግልፀኝነትና ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚሆንልን ምህረት ተናግሯል። (ምሳሌ 28፥13)

– ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ሲናገር በኀጢአት ወድቆ በንስሓ ስለተመለሰው የሰው ልጅ ኅጥያቱን ተመራምሮ እና በልቡ ተጸጽቶ ወደ ሰማያዊ አምላክ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ውሳኔ ላይ ቢደርስ የምህረት እና የቸርነት አባት እግዚአብሔርም በደስታ እና በፍቅር እንዴት እንደሚቀበለው ተመዝግቦ እናገኛለን (ሉቃ 15፥1824)

2/ ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅን ያመለክታል፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጰውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በፃፈላቸው መልእክቱ ስለዚህ ሲናገር “እንግዲህ እግዚአብሔር ለእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናችኋለን” ሲል ተናግሯል። (2ቆሮ5፥20) በመሠረቱ ንስሓ መግባት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰዎች ልቦና እንደሚያድር የምናውቅበት መንገድ ነው። የሰው ልጅ ኀጢአትና በደሉን ትቶ በንስሓ እንደገና ተቀድሶ ከህይወቱ ካላስወገደ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እና የመንግስቱ ወራሽ ሊሆን ስለማይችል ከሰማያዊ አባቱ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ለመሆን መላ ህይወቱን ማዘጋጀት አለበት። ( 2ኛ ቆሮ 5፥19)

3/ ንስሓ ክርስቲያን ከኀጢአት እንቅልፉ የሚነቃበት ደወል ነው፦

በትምህርቱ የአለም ብርሃን የተባለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በፃፈላቸው መልእክቱ ላይ “ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ” በማለት ከኀጢአት እንቅልፍ ነቅተው ንስሓ እንዲገቡ አስረግጦ መክሯቸዋል (ሮሜ 13፥11)። የሰው ልጅ በኀጢአት አንቀላፍቶ የተኛበት ዘመን ይበቃኛል ብሎ በንስሓ ህይወት ወደ ቀደመው ማንነቱ ለመመለስ የሚችልበት የጽድቅ መንገዱ ሰፊ እና ቀና ጉዞ ስለሆነ በቤተክርስቲያን አባቶች ምክር እና ተግሳጽ ወደ ቀደመው ክብሩ መመለስ ይገባዋል (ሉቃ 15፥7)

4/ ንስሓ በኀጢአት ምክንያት ወድቆ የነበረ ክርስቲያን ወደ መንፈሣዊ ህይወቱ መመለሱን ያመለክታል፦

የኀጢአት ደዌ ያደረበት ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በንስሓ ህክምና ፈውስ ካላገኘ በመጨረሻ የሚገጥመው እድል የነፍስ ሞት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስም ያበራልሃልና ሲል ተናግሯል (ኤፌ 5፤14)። ወንጌላዊ ቅዱስ ዩሃንስም “እኛ ……ከሞት ወደ ህይወት እንደተሻገርን እናውቃለን። በማለት ስለ ህይወት መንገድ መስክሯል።

ሐዋርያው ቅዱስ ያእቆብ በመልእክቱ ላይ “ኅጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኀጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ” ሲል ኀጢአተኛ መሆን በነፍስ መሞት እንደሆነ በንስሓ መመለስ ደግሞ በህይወት መኖር እንደሆነ መስክሯል። (ያዕ 5፤20)

ስለሆነም ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ከርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ማወቅ እና መረዳት ያለበት በንስሓ ህይወት ወደ እግዚአብሔር መመለስ የህይወት ትንሳኤ ማግኘት ሲሆን ፀፀት በሌለው ኀጢአት ፀንቶ መኖር ደግሞ በመንፈሣዊ ህይወት የነፍስ ሞት መሆኑን ነው።

5/ ንስሓ ከሃጢያታችን እድፍ የምንታጠብበት ንጹህ ውሃ መሆኑን እና ጽድቅ እና ኩነኔን ለይተን የምናውቅበት አዲስ ልብ ነው።

ጽድቅ እና ኩነኔን፣ ህይወት እና ሞትን፣ ብርሃን እና ጨለማን፣ ገነት እና ሲኦልን፣ ታቦት እና ጣኦትን፣ መንግስተ ሰማያትን እና ገሃነመ እሳትን፣ እግዚአብሔርን እና ሰይጣንን (ቤልሆር) ለይተን ለማወቅ እና ለማስተዋል የምንችልበትን ንጹህ የሆነ የንስሓ ልቦና እግዚአብሔር እንዲሰጠን መለመን ያስፈልጋል። (2ኛ ቆሮ 6፥14-16

የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ሕዝቅኤልም ስለዚህ ሲናገር “ጥሩ ውሃንም ረጭባችኋለው እናንተም ትጠራላችሁ፣ ከርክሠታችሁ ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለው አዲስ ልብ ሰጣችኋለሁ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከስጋችሁ አወጣለሁ የስጋንም ልብ እሰጣችኋለው መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትዕዛዜም አስኬዳችኋለው ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ” በማለት አስተምሯል። (ሕዝ 36፥25-27

6/ ንስሓ የዲያቢሎስን ስራ በመቃወም ከኀጢአት ባርነት ነፃ የሚወጣበት መንገድ ነው። 

ዲያብሎስ ያደረበት ሰው ሁል ጊዜም የኀጢአት ባርያ ነው። 

መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኀጢአትን የሚያደርግ ሁሉ የኀጢአት ባርያ ነው፣ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም…. እንግዲህ ልጅ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። በማለት ከዚህ አለም የኀጢአት ባርነት ነፃ መውጣት የሚቻልበት ዋናው መንገድ ለንስሓ የተዘጋጀ እና የወሰነ ንፁህ ልቦና መሆኑን አስተምሯል። ከምንም በላይ ንስሓ ለመግባት የተዘጋጀ እና በቁርጠኝነት ወስኖ ኀጢአትን የተወ ሰው ለእውነትም ከኀጢአት ባርነት ነፃ እንደወጣ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛምርቴ ናችሁ እውነትንም ታቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት አስተምሯል።(ዩሐ 8፥32)። “እንግዲህ የዲያብሎስን ስራ በመቃወም ለእግዚአብሔር መታዘዝ እና መገዛት ያስፈልጋል” (ያዕ 4፥7)
 

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ስለ-ቅዱስ-ቁርባን ላይ ያገኛሉ

👉ጥያቄ:- ሰላም እንዴት ናችሁ? የሰው ልጅ በህይወት ሲኖር ስንት ጊዜ ነው #ንስሐ መግባት ያለበት? #ገደብ አለው ወይ?

✍ መልስ:- ንስሐ ከሰባቱ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፣ የሚደገሙ፣ የማይደገሙ የሚባሉ ስላሉ ከነዚያ መካከል አንዱ ነው፣ መደገሙን እናውቃለን፣ መደገሙን እናምናለን፣ ግን እስከዚህ ቀን፣ እስከዚህ ቁጥር ተብሎ አልተቀመጠለትም።

ንስሐ ገደብ የለውም እንወድቃለን እንነሳለን፣ አቅደን አልመን ኃጢአት እንሠራለን ብለን አንሄድም፣ ማድረግም የለብንም ግን ሳናስበው፣ ሳናቅደው፣ ፍላጎቱ ሳይኖረን በኃጢአት ወድቀን ከሆነ መልሰን በንስሐ እንነሳለን፣ ነገም ከነገ ወዲያም ብንወድቅ ደግመን በንስሐ እንነሳለን እንዲህ እያልን እንቀጥላለን።

አንድ በገዳም የሚኖሩ አባት ነበሩ በተደጋጋሚ ንስሐ ይገባሉ፣መልሰው በኃጢአት ይወድቃሉ እና ወደ አባታቸው እየሄዱ ሳሉ ሰይጣን ከመንገድ ጠብቆ አታፍርም እንዴ? ሁሌ ንስሐ እያልክ ከአባትህ ፊት ስትቆም አታፍርም? ይላል፣ እኚህ አባት ሲመልሱለት ” አንተ ንስሐ የሌለህ፣ ምህረት የሌለህ እፈር እንጂ፣ እኔማ እንዴት አፍራለሁ፣ ንስሐ የተሰጠው ለእኔ ነው፣ የመዳን በር የተከፈተው ለእኔ ነው” ብለው መልሰውለታል ይባላል።

ስለዚህ ንስሐ በተደጋጋሚ የምንነሳበት የሕይወት ምርኩዛችን፣ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ልዩ ስጦታችን ነው ማለት ነው፣ ሁለተኛ የድነት በር የተከፈተበት ነው፣ ነገር ግን ኃጢአትን ለመሥራት አልመን፣ አቅደን ዛሬ ኃጢአት ብንሠራ፣ ብናጠፋ፣ ነገ ንስሐ እንገባለን ምን ችግር አለው ብለን ኃጢአትን የምንሠራ ከሆነ አይምረንም።

ይሔ አባባል ትክክል አይደለም በኖኅ ጊዜ የነበሩ ሰዎችን እናያለን፣ ኖኅ መርከብ ሲሠራ እናንተም ሥሩ ባላቸው ጊዜ እነሱም ለኖኅ መልሰው በስንት ዘመን እመጣለሁ አለህ? በለው ሲጠይቁት በመቶ ሃያ ዘመን አላቸው፣ እነሱም መልሰው እንግዲያውስ እኛ እንደፈለግን ጨፍረን በሃያው ዘመን ነው መርከብ የምንሠራው፣ አንተ ግን ብዙ ሰው ስለሌለህ፣ ጥቂት ስለሆንክ አሁኑኑ ሥራ አሉት።

ስለዚህ አልመን አቅደን ኃጢአት እየሠራን ነገ ንስሐ እንገባበታለን ችግር የለውም፣ ንስሐ ገደብ የለውም እያልን የምንሄደው ጉዞ እጅግ ከባድ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ንስሐ የለም፣ ንስሐ የሚባለው ሳናውቅ በኃጢአት ብንወድቅ እንኳን ለምን ሠራሁ ብለን፣ አዝነን፣ ተፀፅተን ቀኖናን መቀበል ነውና እዚህ ላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ማለት ነው።

ቴሌግራም ግሩፓችንን በየቀኑ ይከታተሉ፣ ለወገንዎትም ሼር አድርጉ፦
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

👉ጥያቄ፡- 1ኛ የሰው ልጅ ከስንት ዓመቱ በኋላ ነው ለሠራው ኃጢያት #ንስሐ መግባት የሚጀምረው? ወይስ ከስንት ዓመቱ ጀምሮ ነው ንስሐ መግባት ያለበት?

#የንስሐ #አባት እና #ዕድሜ

👉ጥያቄ፡- 2ኛ የንስሐ አባት መያዝ ያለበት ከስንት ዓመት በኋላ ነው? አንዳንዶቹ ስጠይቃቸው ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ ነው ይላሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሰባት ዓመት ጀምሮ ነው ይላሉ የቱ ነው ትክክለኛው?

✍መልስ፡- በእግዚአብሔር ፈቃድበአርባና በሠማኒያ ቀን ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጀች እንድንሆን በእግዚአብሔር ጉባኤ ከተቀላቀልንበት ከቆጠርንበት ጊዜ ጀምሮ የአባቶች ጥበቃ፣ እንክብካቤ፣ አመራር፣ ትምሕርት፣ ተግሣፅ ከእኛ አይለይም፡፡
ሁልጊዜ በአይምሯችን ላይ የነገሠብን ዘወትር የማንለይበት የኃጢያት ጉዳይ ስለሆነ እንቅልፍ የሚነሳንም፣ እረፍት የሚያሳጣንም. የሚያስጨንቀንም ጉዳይ እሱ ስለሆነ ለይቶልን ኃጢያት የሠራንበት ጊዜና ዘመን እግዚአብሔር ለረዳቸው ደግሞ ኃጢያታቸውን በንስሐ ሕይወት ለመታጠብ ወደ ንስሐ አባት መቅረብ ወይም የንስሐ አባት እንዲኖራቸው የማስፈለጉን ሁኔታ ብቻ ስለምናስብ ነው፡፡

ሕፃናት በዚያው እድሜያቸው እንደ ጡጦ እንደ ወተት ጠብተው የሚያድጉት ትምሕርት አለ መንፈሳዊ ትምሕርት ማለት ነው ልክ እንደ እሳትና ውኃ በባሕሪያቸው ተለይተው እንዲያውቋቸው ማለትም ይሔ የሚያቃጥል ነው፣ ይሔ ደግሞ ውኃ ነው፣ ስለዚህ ወደ ውኃው እጅህን ብትልክ አትጎዳም፣ ወደ እሳቱ ብትልክ የሚያቃጥል ነው ብለው ወላጆች ለልጆቻቸው እከሰከሚያስተምሯቸው ሁሉ በቤተክርስቲያንም ይሔ ኃጢያት ነው፣ ኃጢያት የሚሆነውም በዚህ በዚህ ምክንያት ነው የምንላቸው፡፡

የሚበላ ምግብን የሚመር፣ የሚጣፍጥ፣ ብለን እንደምናውቀው፣ የሚገድል፣ ሕይወት የሚሰጥ ብለን እንደምናሳውቃቸው እንደዚሁ በእድሜ መጠናቸው አብረው ተዋሕዷቸው እንዲያድግ ነው ቤተክርስቲያንና የቤተክርስቲያን አባቶች ማስተማር ያለባቸው፡፡

የንስሐ አባትነት ማለት ሕፃናትንም የንስሐ አባት ሆነው መሳደግ ማለት ነው ከዚህ በላይ ልንለውም አንችልም ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ ማለት እኮ መርሑ ይሔ ነው፣ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ይመጡ ዘንድ ማለትም ይሔው ነው፡፡

ብዙ ጊዜ አባቶችም፣ አስተማሪዎችም፣ በየመድረኩ ወንጌል የሚሰብኩም ሕፃናት አይምሮ ጠባያቸው በኃጢያት ስላላደፈ፣ ሌላውን ነገር ለይተው ስለማያውቁ ብዙ ጊዜ ጉባኤ የረበሹ ይመስለናል፡፡
እንደዚያ የማድረጋቸው ነገር ሁሉ እንኳን ለእኛ ይመስለናል ለእግዚአብሔር የሚያስደስተው ነገር ስለሆነ ሕፃናትን በአፀደ ቤተክርስቲያን ቦታ ሰጥተን ማሳደግ ነገ ከኃጢያት ለመለየታቸው፣ ኃጢያትን ከፅድቅ ለይተው ለማወቃቸው መሠረት ነው፡፡
አንድ ሰው አካለ መጠን ደርሶ ከእናት አባቱ ጀርባ ወርዶ ራሱን የቻለ ሕይወት፣ ኑሮ፣ ትዳር፣ ሌላ ነገር የሚመራበት ያን ጊዜ የራሱ አባት ኖረውት፣ እንደ አዋቂ ምእመን ሆኖ፣ ታዞ ተቀጥቶ፣ ተሠርቶ የሚኖርበት ያ የታወቀ ነው፡፡
እኛም አባቶችን ሳንጠይቅ በባሕላችንም እናውቀዋለን፣ የዓለሙ ጠባይም ነግሮናል ትምሕርት የሚማሩ ልጆች መቼ እንደሚጨርሱ፣ ወደ ኮሌጅ ገብተው ስንት ዓመት እንደሚቆዩ፣ ከዚያ በኋላ ከቤተሰብ ጫንቃ እንደሚወርዱ፣ በገጠርም ያሉ ልጆች ሚስት አጋብተናቸው የራሳቸው እርሻ ኖሯቸው፣ ጎጆ ኖሯቸው እንዴት እንደሚኖሩ እናውቃለን፣ ከዚያ ጀምሮ ራሱን የቻለ አባወራ ሆኗል፣ ስራ የሚሠራ የቤተሰብ ኃላፊ ነው ማለት ነው፡፡
ጠቦቶቼን ጠብቁ፣ በጎቼን ጠብቁ፣ ሕፃናቱን ጠብቁ፣ ወጣቱን ጠብቁ፣ ሽማግሌዎችን ጠብቁ ነው የተባለው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ቁጥር 15 ቅዱስ ጴጥሮስ ወይም ሐዋርያት የተሰጣቸው መጀመሪያው ስርዓት ይሔ የጥበቃ ስራ ነው፡፡
በጎቹን በየስማቸው፣ በየቁጥራቸው አውቃለሁ ነው ያለው ጌታ አንዱም እነዳይጎድል፣ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገር ድካም ሲበዛብን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በካሕናትም ይሁን በምእመናን ይነሳል፡፡
አንድ ሰው ንስሐ መግባት ያለበት እንደ ኃጢያት የሚቆጠርበት ከስንት እድሜ ጀምሮ ነው? የንስሐ አባት በቋሚነት የሚይዘው በስንት ዓመቱ ነው? ይሔ የድካም ነገር ነው፣ በቤተሰብ የንስሐ አባት ካለ፣ ጠንካራ ከሆነ እሱ ራሱ ያ የቤተሰቡ ንስሐ አባት አባት ሊሆን ይችላል፡፡
እኒህ ንስሐ አባትም ጌታ እንዳለን ሁሉ ሕፃናቱንም ወደ ቅዱስ ቁርባን አምጡ፣ ቤተክርስቲያን አምጥታችሁ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲሰሙ ታደርጋላችሁ? እንዴት ለብሰው፣ በአፀደ ቤተክርስቲያን በምን ቦታ እንደሚቆሙ፣ እንዴት እንደሚለብሱ ያያሉ፣እንዴት እንደሚጸለይ ያያሉ፣ ስርዓቱን እያዩ ይከተሉዋችኋል፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ለወጣቶቹስ እናንተስ የወጣትነት እድሜ እንዳያጠፋችሁ ይሔ የእሳት ዘመን ነው ዘመናችሁና ይሔ የወጣትነት ባሕሪ የእሳትነት ባሕሪ ነው፣ እሳት ደግሞ ሁሉንም የሚበላ ነው፣ ስለዚህ እነዚህ ወጣቶችስ ወደ ቤተእግዚአብሔር እየመጡ ነው? እየቆረቡ ነው? ምን እያሉ ነው? እንዲህ ብሎ ከጠበቀ ምንም አይደርስባቸውም፡፡

በሰንበት ትምሕርት ቤት ከታቀፉ፣ የተለየ ምክር ያገኙ ሰዎች ቶሎ ብለው የራሳቸውን አባት ቢይዙ የእናት አባቶቻቸውን ፈቃድ እንደሻሩ፣ ቀኖና ቤተክርስቲያን እንደሻሩ የሚያስቆጥር አይደለም፣ እንደ ጥበቃው ዓይነት ነው፣ በዚህ ላይ ምንም የተሰራ ድንበር የለም፣ ልጆች ለምን ሌላ አባት ኖራቸው፣ አስተማራቸው የሚባል አይደለም ፡፡
አባላቶቻችን በየደብራችሁ፣ በየአካባቢያችሁ የንስሐ አባቶቻችሁ አሉ አይደለም? የንስሐ አባት ሊሰራው የሚችለውን ሥራ እኛ ተጨማሪ አቅም ፈጠርን እንጂ ሌላ የተፈጠረም አዲስ ነገር የለም፡፡

የበለጠ ብዙ ችግሮቻችሁ በልማድ በመጣ ነገር ዛሬ የንስሐ አባትና የንስሐ ልጅ በየቀኑ፣ በየጊዜው ተገናኝተው፣ ተመካክረው አያውቁም ለዚህም ነው ዛሬ ኃጢያት በእኛ ሕይወት ላይ እየነገሠ ያለው፡፡

ግልፀኝነት ሁሉ ቀርቷል፣ መተፋፈር አለ፣ መፍራት አለ፣ አባቴ ዛሬ እንዲህ ሆኛለሁ፣ ሴቷም ወንዱም አይሉም ልነግራቸው ነበር ፈራሁ እየተባለ ስንት ነገር እየተደበቀ ነው ያለው፣ ብዙ የደበቅነው ነገር አለ ስንት ችግር አለ፡፡

ብንቀራረብ ግን ለአባት ምንም እንደማይደበቅ፣ አባትም ደግሞ የልጆቻቸው ሚስጥር እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ይሔ ልምድ፣ ይሔ ባሕል ቢኖር ስነ ስርዓት በሕይወታችን ያነግስ ነበር፡፡
ዛሬ ግን አንዳንድ ጊዜ እኛም እንዳለመታደል ሆኖ እስከ አለታመን ድረስ ሚስጥሬን ያወጡብኛል እየተባልን እስከ መጠርጠር መድረስ ይሔ ለእኛ ለአባቶች ውርደት ነው እንጂ ክብር አይደለም፡፡
በንስሐ አባትና በንስሐ ልጅ መካከል መራራቅ፣ ልጆች እንዴት ተብሎ በንስሐ አባት እንደሚኖሩ እንኳን ይሔንን ሁሉ ማወቅ ይሔ በአባቶችና በልጆቻቸው መካከል ያለው ክፍተት ነው መራራቅ ያመጣው ጣጣ ነው፡፡

ጠያቂያችን ለተጨማሪ ምክር ካስፈለግዎት በውስጥ መስመራችን ይደውሉና ያነጋግሩን ፡፡

የመከረን የገሰፀን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን አሜን

ቴሌግራም ግሩፓችንን በየቀኑ ይከታተሉ፣ ለወገንዎትም ሼር ያድርጉ፡-
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

👉ጥያቄ፡- የንስሐ መገለጫ ምንድን ነው?

#ንስሐ

✍መልስ፡- ንስሐ የሚለው ቃል ትርጓሜው ምን እንደሆነ፣ ምንን እንደሚያመለክት፣ አስፈላጊነቱ፣ ጥቅሙ ምን እንደሚመስል ከዚህ በፊት ስፍር ቁጥር የሌለው ውይይት አድርገናል፡፡

ሁሉም ሰው በአንድም በሌላም መንገድ የመነሻውም፣ የመዳረሻውም፣ ሐሳቡ ንስሐ በሚመለከት በመሆኑ በእሱ ዙሪያ ላይ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ብዙ ሥራ ሰርተናል ብለን እናምናለን፡፡

ንስሐ የሚለው ቃል የግዕዝ ቋንቋ እንደሆነ፣ ትርጓሜውና ፍቺው መመለስን፣ መፀፀትን፣ የሚያመለክት ሌሎቹም እነዚህን የመሰሉ ወርቃማ ንድፍ ሐሳቦች የያዘ እንደሆነ ተነጋግረናል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ንስሐ ትልቁና ዋናው ዓላማ ነው፣ ቤተክርስቲያናችን ብዙ ልጆቿን ከማጣት የምትድንበት መልሳ ወደ እቅፏ የምትይዝበት፣ ከገቡበት፣ ከወደቁበት፣ ከጠፉበት ሁሉ ፈልጋ የምታገኝበት፣ ለመንግሥተ እግዚአብሔር የምታበቃበት ለእውነተኛ ኃይማኖት፤ ለእውነተኛ ምግባር የምታበቃበት ትልቁ መገለጫዋ ንስሐ ነው፡፡

አንድ ክርስቲያን ማንም የማያውቅበትን፣ ማንም ያልደረሰበትን ምንም ዓይነት መረጃና ማስረጃ የሌለበት፣ በመቼም ጊዜ እሱ ስለሠራው፣ ስለፈጸመው ድርጊት ከቶም የሚያሰጋው ነገር፣ና የሚጠየቅበት መንገድ እንደሌለ እያወቀ በራሱ ልባዊ ወይም ፍፁም በሆነ እምነት ያንን የፈጸመውን ስህተት በማሰብ ተፀፅቶ፣ አዝኖ፣ ከዚህ በደሌ፣ ከዚህ ኃጥያቴ፣ ከዚህ ጥፋቴ እንዴት መውጣት እንዳለብኝ፣ ስለፈጸምኩት ኃጢያት በደልስ ተጠያቂ እንዳልሆን ምን ማድረግ አለብኝ? ይላል፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ከልብ ተፀፅቶ፣ ለዚህም ፈተና ቁልፍ የሆነው መፍትሔ በፍፁም እምነት ወደ “አበነፍስ ወይም ወደ ንስሐ አባት” በመሔድ መናዘዝና ከልብ በሆነ ፀፀት መመለሱንና ስለ ሰራው በደል ኃጢያት የሚሰጠውን ቀኖና ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ “አበስኩ ገበርኩ” በማለት ለንስሐ አባት የሚደረገው ኑዛዜና፣ የሚሰጠው የንስሐ ቀኖና የንስሐ መገለጫ ነው፡፡

በአጠቃይ ተነሳሒ ወይም ደግሞ ንስሐ ለመግባት የመጣው አማኝ፣ ምእመን፣ ለመንፈስ ቅዱስ ልጃቸው በሠራው በደል፣ ኃጥያት፣ጥፋት ሁሉ ተገቢውን ንስሐ የሚሰጡ አባት፣ የሚሰጠው የንስሐ ቀኖና “የንስሐ መገለጫ” ይባላል፡፡
በዚህ የኃይማኖት ስርዓት የሚከናወነው ነገር ሁሉም ነገር ከልብ በሆነ እምነት ስለሆነ የሚፈጸመው በቁሳዊ ነገር፣ በሥጋዊ ዳኝነት፣ በሚጨበጥ፣ በሚዳሰስ እና ከሥጋዊ ዳኝነት ወይም ማስረጃ ጋር፣ መረጃ ጋር የሚያያዝ ሆኖ የሚታይ አይደለም፡፡

ሁሉም ነገር መንፈሳዊ ነው፣ ሁሉም ነገር እንደ መንፈሳዊነቱ ለብዙዎቹ የማይገባ፣ ለብዙዎቹ የማይገለጥ፣ የማይረዳ ረቂቅ ሚስጥር ያለበት ነው ስለዚህ ነው በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ በንስሐ ቀኖና የምናልፍበት መንፈሳዊ ጉዟችን የንስሐ መገለጫ ነው፡፡

ጠያቂያችን የንስሐ መገለጫ ምንድን ነው? ያሉት ምናልባት የራሳቸው የታሰባቸውና፣ የሐሳባቸው መነሻ ያደረጉት እግዚአብሔርና እሳቸው የሚያውት ነገር ሊኖር ይችላል፤ እንደ እውነተኛው አስተምሕሯችንና፣ ሁላችንም ልንጋራ የምንችለው ሐሳብ ግን አሁን የተገለፀውና ከዚህም የሚሰፋው ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሐሳብ ነው ማለት ነው፡፡
ስለ ንስሐ ሕይወት ብዙ ነገር በቅዱስ መጻሕፍት፣ በሌሎቹም ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ንስሐ የተፃፈውን ነገር እያነሳን ስላወራን ማለት ነው፤ በዋናነት ከላይ በመግቢያችን ላይ እንዳልነው አንድ ተነሳሒ ማንም ሳያስገድደው ዝሙት ኃጢያት ነው፣ ሐሜት ኃጢያት ነው፣ አመንዝራነት ኃጢያት ነው፣ ሴሰኝነት ኃጢያት ነው፣ ስርቆት፣ አምልኮ ባእድ፣ ጥንቆላ እነዚህን የሚመስሉ ሁሉ ኃጢያቶች ናቸው፡፡

በዚህ ሁሉ በአንዱም በሌላውም በድያለሁ፣ አጥፍቻለሁ ብሎ ራሱን ማሳመንና፤ መንፈሳዊ ነገር ሁሉ በማንም የማይመረመር የማይገለጥ፣ በምድራዊ ዳኛ ዳኝነት የማይሰጥበት፣ ፍትሕ የማያገኝ ሁሉም ነገር ረቂቅና ሁሉም ነገር ድንቅ፣ ሁሉም ነገር መንፈሳዊ የሆነ ነው፣ እንዲህ ብሎ በማመን ለዚህም ችግሬ ደግሞ መፍትሔው ይሔ ነው ብሎ ወደ ንስሐ አባት መሔድ፡፡

የንስሐ አባቱ በሚቻለውና በሚሆነው ነገር ጹም፣ ጸልይ፣ ስገድ፣ መፅውት ብለው በሚሰጡት ቀኖና የኃጢያት ስርየት አገኛለሁ ብሎ፣ የኃጥያት ስርየት እንዳገኘም ደግሞ በዓይኑ ሳያየው፣ በእጁ ሳይጨብጠው፣ሳይዳስሰው፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚከናወነውን ነገር ይሆናል ብሎ ማመን ይሔ ሁሉ የንስሐ መገለጫ ነው፡፡

ከዚህ የሚሰፋ፣ ከዚህ የሚረቅ፣ ከዚህ የሚጠልቅ ወርቃማ ሐሳብ የያዘ ነው የንስሐ መገለጫ ብለናል፤ በጥቂቱ ይሔንን ሐሳባችንን ካጋራናችሁ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር በፈቀደ ብዙ ተወያያተንበታል፣ እሱንም በማከል ስለ ንስሐ በቂ ግንዛቤ ይኖራችኋል ብለን እናምናለን፡፡

የመከረን የገሰፀን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን አሜን

ቴሌግራም ግሩፓችንን በየቀኑ ይከታተሉ፣ ለወገንዎትም ሼር ያድርጉ፡-
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

ንስሐ // ከንስሐ በፊት (ጥያቄና መልስ)

👉ጥያቄ፦ #ንስሐ ከመግባታችን በፊት ምን ማድረግ አለብን?

መልስ፦

ንስሐ ለመግባት ከሚፈልግ አንድ ክርስቲያን በመጀመሪያ የሚጠበቀው ፡-

1.  በቅድሚያ ኅጢአት መሥራቱን አምኖ ለራሱ ሕሊና መናዘዝ (ከልብ መፀፀት)።

2.  ስለሠራው ኅጢአት ወይም በደል እየተፀፀተ ጧት ማታ በደሉን በፀሎትና በልመና ለፈጣሪው መናዘዝና ኅጢአትን በእግዚአብሔር ፊት ማመን (መዝ50 ፣ ዳን9፥5፣ ነህ1፥6-7)

3.  ኅጢአትን (በደልን) ለካህን መናዘዝና ንስሐ መግባት። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይና እንደራሴ ስለሆነ የሠራነውን ኅጢአት ለካህኑ በመናዘዝ ንስሐ መግባት፤ ኅጢአታችን እንዲሠረይልን በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ መግባትና መናዘዝ ማለት ነው። (ኢያሱ7፥19 ማቴ3፥6 ዘሌ5፥5-6 የሐዋ19፥18)

4. የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት የጥል ግድግዳ አፍርሰን በፍቅር አሸንፈን ስለዘለዓለማዊ ሕይወት ብለን በፍጹም ሕሊና በሰላም መኖር ነው።

4. ተመልሶ በኅጢአት ላለመውደቅ አዘውትሮ የንስሐ አባትን ወይም የሚቀርቡትን የሃይማኖት መምህር ማማከር፣ ምክር ማግኘት በታቻለ መጠን መጸለይ፣ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ በቤትም ውስጥ ቢሆን መንፈሳዊ መዝሙርና ትምሕርት ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ የምናስገነዝበው ለጠየቁን ምዕመን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያን እንዲጠቅም ነው።

የንስሓ አባትን በሚመለከት ፦

ለመንፈሳዊ ልጆቹ (ለመንጋው ጥበቃ) የማያንቀላፋና ዘወትር ቁጥጥር እና ክትትል የሚያደርግ አባት መያዝ እንደሚገባ እንመክራለን። ስለዚህ ይመክረኛል ያስተምረኛል ያሉትን የንስሓ አባት የሚሆን ካህን በአካባቢዎ ካሉ  ይያዙ፤ በአከባቢዎ  ማግኘት የማይችሉ ከሆነ በራስዎትም ሆነ በሚያምኑት ሰው በኩል ያገኙዋቸውን እውነተኛ ካህን በርቀትም ቢሆን ይያዙ፤ ወይም ደግሞ እኛ በህይወታቸው ምሳሌ ይሆናሉ ብለን ከመረጥንልዎ በድረገፃችን በሚያገኙት ስልክ ቁጥር ደውለው  ንስሓ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ።

በተጨማሪም ለጠያቂያችንም ሆነ ለሌላው ሁሉ ምክር የምንሰጠው ምናልባት የሰራነውን ኀጢአት ሁሉ ለመደበኛ የንስሓ አባታችን ለመናዘዝ የምናፍርበት ወይም በካህኑ ላይ እምነት ቢያጣ ወይም ምስጢር ይባክንብኛል ብሎ ከተጠራጠረ፤ ያ ነገር ደግሞ በህይወቱ ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ ካሰበ ከተቻለ አባቱን በደንብ አነጋግሮ መተማመን ላይ ቢደርስ፤ ይህን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ስርአታዊ መንገድ ተጠቅመን በመንፈሳዊ ጥበብና በትህትና ሁነን ተሰናብተን ፤ ሳንጠራጠር ከልብ የምናምናቸውን ሌላ አባት መርጠን መያዝ ይገባናል። ይህን የምንልበት ምክንያት ብዙዎቹ ምእመናን ለንስሓ አባቶቻቸው ግልፅ ሆነው የሰሩትን በደል ለመንገር የማይችሉበት ዋናው ምክንያት ምስጢር ይባክንብናል ብለው ከነኀጢአታቸው የሚኖሩ አሉና ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለአባቶቻቸው ግልፅ ለመሆን በአካባቢያቸው በማህበራዊ ህይወት ከመንፈሳዊ አባቶቻቸው ጋር አብረው ስለሚኖሩ የመተፋፈርም ነገር ስለሚያጋጥማቸው በዚህም ምክንያት የሚሳቀቁ ምእመናን እንዳሉ መረጃው ስላለን፤ ከዚህ ሁሉ ስጋት ነፃ ለመሆን የሚያምኑበትን እና የማይጠራጠሩበትን አባት መያዝ እንደሚገባቸው በአፅንዎት እንመክራለን። ለዘላለማዊ የነፍስ ድህነት ጉዳይ የምንሰራውና የምናደርገው ተጋድሎ በስጋዊ አመለካከት ወይም ምድራዊ በሆነ አሰራር የምንኖረው ሂደት ስላልሆነ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።

2. ንስሓ ከገቡ በኋላ ማድረግ ያለብዎት፦

አንድ ክርስቲያን በኅጢአት የጎደፈውን ሰውነቱን ከታጠበ በኋላ መላ ህይወቱ ንፁህ ስለሆነ ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት መንገዱ ሁሉ ቀና ስለሆነ ማድረግ ያለበት ምን እንደሆነ የምናስረዳዎት፦

1ኛ/ ከምንም በላይ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎትን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ፣

2ኛ/ እግዚአብሔር ቢፈቅድልዎት በቅዱስ ቁርባን መወሰን፣ አቅምዎት በሚፈቅደው መጠን ሳያቋርጡ እና ሳይሰለቹ መፆም፣ መፀለይ፣ እና መስገድ፣

3ኛ/ በአቅምዎት ከሚያገኙት ነገር ለድሆችና ለእግዚአብሔር የሚገባውን አስራተ በኩራት ማዋጣት፣

4ኛ/ ዘወትር ከአባቶች ምክር እና መታዘዝ አለመራቅ፣ በፕሮግራም ወደ ቤተክርስቲያን እየቀረቡ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣

5ኛ ሁሌ እንደቅርብ አስተማሪና መካሪ ሁነው የሚያገለግሎትን መንፈሳዊያን መፃህፍትን ማንበብ፣ ከዚህም በላይ በኑሮዎት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ በማህበራዊ ጉዳይ ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር በትዕግስት እና በጥበብ ለመኖር ድርሻዎትን መወጣት።

እነዚህን ሁሉ እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ነገሮችን አጠቃሎ ለመስራት የሚቻለው ሰው ህይወቱ በንስሓ ሲታደስ ስለሆነ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእርስዎን ህይወት በንፅህና በቅድስና እንደሚጠብቃት በማመን ከዚህ በላይ የተሰጠዎትን መንፈሳዊ ምክር በስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ እግዚአብሔር ይርዳዎት።

በተጨማሪም፤ ስለንስሓ ትምህርት በድረገፃችን ላይ የተላለፉና እየተላለፉ ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች ይህን ሊንክ በመጫን ያንብቡ።

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ

👉ጥያቄ፦ #ንስሐ ሳይገባ #ሱባዔ መግባት ይቻላል ውይ?

መልስ፦ ጠያቂያችን፤ ሱባኤ ለመግባት ከሁሉ በፊት ስለ ስባኤ ምስጢራዊ ትርጒም እና በሱባኤ ስለሚገኝበት መንፈሳዊ ጥቅም መረዳት አለብን።  ሱባኤ ማለት በግዕዝ  ቋንቋ 7 ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ይህ 7 ቁጥር ደግሞ የአንድ ሱባኤ ጊዜ ማለት ነው። 7 ቁጥር በዕብራዊያን ዘንድ ፍጹም ቁጥር ነው። የቃሉ ምስጢራዊ ትንታኔ ይህ ከሆነ፤ ሱባኤ የተጀመረው በአባታችን በአዳም ነው።  አባታችን አዳም  7  አመት ከ1ወር ከ 17 ቀን በገነት ውስጥ በደስታ ከኖረ በኋላ አታድርግ የተባለውን ትዕዛዝ በማድረጉና አትብላ የተባለውን ዕፀበለስ በመብላቱ ከገነት ርስቱ መባረሩ ምክንያት ስለ ስራው በደል ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው በማልቀሱና በመጮሁ ምክንያት ከፈጣሪው ዘንድ  ይቅርታን ያገኝ ዘንድ 5 ሱባኤ ማለትም 35 ቀናትን በሱባኤ ተወስኖ ወደፈጣሪው ያቀረበው ልመና ተቀባይነት አግኝቶ ከፈጣሪው ዘንድ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ተገብቶለታል። ስለዚህ ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ በኀጢዓትና በልዩ ልዩ ምክንያት የሱባኤ ጊዜ እየወሰኑ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ምህረትን እና ይቅርታን አግኝተውበታል። 

ሱባኤ የሚገባው በ2 ምክንያት ነው:- 1ኛው ማንኛውም ክርስቲያን የኀጢአት ፈተና ደርሶበት የበደለውን በደል አስቦ በመፀፀት ከሰውና ከማህበራዊ ኑሮ ራሱን ደብቆና ሰውሮ በለቅሶ በፀሎት ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት ሂደት ነው።  2ኛው ደግሞ ማንኛውም ክርስቲያን ፀጋውን ለማሳደግና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ልዩ ልመና ሲኖረው ጊዜ ወስኖ ቦታ ለይቶ ሱባኤ ይገባል ማለት ነው። በፆም በፀሎት ተወስኖም ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል። በጠየቀውና በለመነው ፍፁም ክርስቲያናዊ ሕይወት አንፃር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለግል ህይወቱና ለቤተሰቡ፣ ለወገንና ለሀገርም የሚጠቅም በጐ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።

ሌላው የሱባኤ አስፈላጊነት ፤ እግዚአብሔር አምላክ ስላደረገልን ነገር ሁሉ እና ስለቸርነቱ ብዛት ምስጋና ለማቅረብ፣ ወደፊትም ጠብቆቱና መግቦቱ እንዳይለየን ለመማፀን ፣ ከእናታችን ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳን ሁሉ በረከት ለማግኘት፣ በግል ህይወትም ሆነ በሀገር ላይ ከተቃጣው መቅሰፍት ለመዳን፣ በሃይማኖትና በሥነምግባር ፀንተን በፆም በፀሎት እንድንተጋ የሚዋጋንን ጥንተ ጠላታችንን ዲያብሎስን ድል ለመንሳት፣ የተሰወረና የረቀቀ ምስጢር እንዲገለጽልን በመሳሰሉት መንፈሳዊ ጉዳዮች ሰባኤ መግባት የምንችል መሆኑን በቀኖና ቤተክርስቲያን ታዟል።

ሱባኤ ለመግባት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ፤ በግላችን በሰራነው በደልም ሆነ ስለሀገርና ስለወገን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት ለመጠየቅ ሱባኤ ለመግባት ባሰብን ጊዜ፦ 

1/   ህሊናዊና አካላዊ ቁርጠኝነትና ስነልቦናዊ ውሳኔን ይጠይቃል። 

2/  ሱባኤ የምንገባበት ምክንያት እንዴትና ለምን እንደሆነ ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር መነጋገርና ምክር መቀበል፣ ንስኀ ያልገባበት ጥፋት ካለም ተናዞ ቀኖና መቀበል ያስፈልጋል።

3/  በሱባኤ የምንቆይበት ጊዜ ምን ያህል ሰባኤ እንደሆነ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ፣ እና የሱባኤውን ቦታ (በአትን) መወስን ያስፈልጋል። 

4/   በሱባኤ ጊዜ የምናደርጋቸውን መንፈሳዊ ስርዓት ማለትም እንዴት እንደምንፆም ፣ እንዴት እንደምንፀልይ፣ እንዴት እንደምንሰግድና በመሳሰሉት በስርዓተ ቀኖና መሰረት መንፈሳዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል። 

5/    ሱባኤ በገባን ጊዜ በግል ህይወትና በቤተሰብ ጉዳይ ወይም በማህበራዊ ጉዳይ የሚያሰናክል ፈተና እንዳይመጣብን አስቀድመን ሁኔታዎችን ማስተካከል ያስፈልጋል።

6/   ሱባኤ በገባን ጊዜም እንዴት መተኛት እንዳለብን ምን መልበስ እንዳለብን ባጠቃላይ በሱባኤ የምናሳልፍበት ጊዜያችን የሚያስፈልገንን እና የማያስፈልገንን ነገር ለይተን ለማወቅ ከቤተክርስቲያን አባቶች መመሪያ መቀበል አለብን። 

ይህን ሁሉና የመሳሰሉትን ሱባኤ ከመግባ በፊት ልናሰባቸውና በሱባኤ ወቅት ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ናቸው። 

ሱባኤ ከጨረስን በኋላ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ደግሞ፦

1/   ሱባኤ የገባንበት ምክንያት ኀጢአት ከሆነ ደግመን ላለማድረግ በተቻለ መጠን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳችንን ለበለጠ የሃይማኖት ፅናት ማትጋት ነው። 

2/ ሱባኤ በገባንበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ያገኘነው በጎ ምላሽ ካለም የበለጠ የእግዚአብሔር ፀጋ እንዲበዛልን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ነው።

3/   ማንኛውም ክርስቲያን ቦታና ጊዜ ላይቶ በሱባኤ ፈጣሪውን የሚለምን ከሆነ በፀጋ እያደገ ከመጣ ብዙ ጊዜ ለውድቀት ከሚያበቁት የኀጢአት ምክንያቶች መራቅ።

4/   በፆም በፀሎት በቅዱስ ቁርባን በአጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስነምግባር መንፈሳዊ ጉዞን መቀጠል።

5/   ሥጋዊ ፍላጎትን እና ምኞትን ገዝቶ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝቶ የትሩፋት ሥራ መስራት። 

6/  በአጠቃላይ አለማዊ ሰዎች ከሚሰሯቸው ስራዎች ሁሉ እርቆ በመንፈሳዊ አላማ ፀንቶ መኖርን ይጠይቃል። 

እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ምክር የሚሰጠው በአለም እየኖሩ በሱባኤ እግዚአብሔርን ለሚለምኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንጂ ለገዳማውያን ወይም በምናኔ ለሚኖሩ መነኮሳት አይደለም፤ የነሱ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ቀኖናዊ ስርዓት ስላላቸው ነው።

ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ተረድተው ፤ ለሱባኤ ወደ ገዳም ለመሄድ ያሰቡትን መንፈሳዊ አላማ በሰላም ፈፀመው የእግዚአብሔርንም በረከት እና መልስ አግኝተው እንዲመለሱ እየተመኘን፤ በገዳም በፍጹም እምነት ሆነው እንዲጸልዩና ለረዥም ጊዜ በቦታው የቆዩ የእግዚአብሔር ፀጋ አብዝቶ ያደረባቸው አባቶች ስለሚኖሩ ወደነርሱ ቀርበው ትምህርትና ምክር ማግኘት እንዳለብዎምእንመክራለን። 

በአጠቃላይ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም፤ ስለ ሱባኤ መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ በዚህች አጭር ፅሁፍ መልዕክት የላክንላችሁ ሲሆን፤ አስፈላጊ ሆኖ ስናገኘው ወደፊት ስለ ሱባኤ አስፈላጊነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ ትምህርት በስፋት  እንዲደርሳችሁ ልናደርግ እንችላለን። 


ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ ላይ ያገኛሉ

👉🏾ስለ #ቅዱስ #ቁርባን፣ የ #ንስሐ ህይወትና ስለ #ዝሙት #ፈተና

👉ጥያቄ፡- ንስሐ ገብቼ መልሼ እሳሳታለሁ፡፡ የዝሙት መንፈስ በጣም ይፈታተነኛል፡፡ እኔ ግን ንስሐ ገብቼ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል እፈልጋለሁ፡፡ ልብስም ገዝቼ ይኼው መቼ ይሆን ከአንተ ቤት የምኖረው እያልኩ እሳላለሁ፡፡ ንስሐ ገብቼ ብቆርብስ ? የድፍረት ኃጢያት ይሆናል ወይ? አንድ አባት ቢያንስ 30 ዓመት ይሙላሽ አሉኝ፡፡ እኔ ግን ከእግዚአብሔር መራቅ አልፈልግም፡፡ ግን መኖር እፈልጋለሁ እስኪ አስረዱኝ በማርያም?

መልስ፡- የጠየቁን ስለ ንስሐ ሕይወት ነው፡፡ በመቀጠልም በንስሐ ሕይወት ስለሚፈፀም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በሚመለከት ነው፡፡ ጠያቂያችን ከንስሐ የተሸለ ምን የሚያስፈልግ ነገር አለ? ሁልጊዜም ደጋግመን እንደምንለው ኃጢያት ላለመሥራት መጋደሉ፣ መታገሉ መቸስ የማይገኝ ዕድል ነው፡፡ ለሁላችን የማይቻል ነገር ስለሆነ፤ ሁላችንም ፈተና የበዛብን ተክል ስለሆንን፣ የፈለገንን ያህል ብንምል፣ ብንገዘት፣ አጥብቀን ብንጠላው ብንታገለው ሁላችንም ተሰናክለን የምንወድቅበት የጋራ የሆነ ኃጢያት ስላለ በዚያ ተጠልፎ መውደቁ የማይቀር ነገርና መጥፎ ዕድል ሆኖብን እንጂ፤ በዋናነት ከኃጢያት ርቆ መኖር ቁጥር 1 የምንመርጠው የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ ይኼ ሳይቻል ቀርቶ ደግሞ በአንድም፣ በሌላ መንገድም ወይም ከባድ በሆነ ወይም ቀላል በሆነ ኃጢያት በወደቅን ጊዜ፤ ዓይነተኛው መፍትሔ ወደ ንስሐ መምጣት ነው፡፡

በቅዱሳት መጻህፍትም የንስሐ ትርጉም ወይም የንስሐ ታላቅነት ተነግሮናል፡ ንስሐ ማለት ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ በሙሉ ልብ በፍፁም እምነት ሆነን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው.፣ መጸጸት፣ የንስሐ ሕይወት የሚባለው ነገር ይኼ ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውን አቅኑ›› እያለ በመጣ ጊዜ የአዋጁ አብሣሪ ሆኖ ሲመጣ ፤ የመጀመሪያው የስብከቱ አዋጅ ንስሐ ግቡ የማቴዎስ ወንጌል ቁጥር 1 እና 2 ላይ ንስሐ ግቡ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና፡፡ ሐዋርያትም ጌታ በተነሣ በ 50 ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው 72 ቋንቋም ተገልጦላቸው፣ ገና በጠዋቱ በአይሁድ ዘንድ ቆመው እጅግ የብዙዎቹ ልቡና የተመሰጠበትን ትምሕርት ባስተማሩ ጊዜ ብዙዎቹ አምነው ወዲያውኑ፤ ምን እናደርግ ሲሏቸው? ንስሐ ግቡ፣ እና አምናችሁ ከመጣችሁ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ተጠመቁ፡፡ ይኼን ነው እንግዲህ ያስተማረ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የዮሐንስ ትምሕርት የመጀመሪያው ነገር የበር መክፈቻው ቁልፍ ንስሐ ግቡ ነው፡፡ ሁላችንም ከነኃጢያታችን እንዲሁ ተሸፋፍነን እንድንኖር እግዚአብሔር አይፈቅድም፡፡ እና ለንስሐ የእድሜ ገደብ የለውም፡፡ ቅዱስ ቁርባን የእድሜ ገደብ የለውም፡፡ ይኼን በሚመለከት በጣም ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል፡፡ መቸስ በእያንዳንዱ ትምሕርት ሳንዘነጋ የምናስታውሰው ነገር ስለ ምስጢረ ቁርባን ነው፡፡ ማንኛውም አማኝ፣ ማንኛውም ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን መቀበል እንዳለበት፡፡ ደጋግመን እንደተነጋገርነው፤ ወንድ ልጅ በ40 ቀኑ፣ ሴት ልጅ በ 80 ቀኗ የእግዚአብሔር ልጅ ሆነው በስመ ክርስትና፣ በቅዱስ ቁርባን ታትመው ልጅነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ከቅዱስ ቁርባን አንድ ቀንም ቢሆን መለየት የለባቸውም ብለናል፡፡

ስለዚህ ጠያቂያችን፤ በተለያየ የሥጋ ድካም፣ በተለያየ የኃጢያት ምክንያት ከሥጋወደሙ መሸሽ ወይም ማቋረጥ አያስፈልግም፡፡ ከእነጭራሹ ደግሞ የምንሰማው ጉድ 30 ዓመት ይሙላችሁ፤ 40 ዓመት ይሙላችሁ፣ 25 ዓመት ይሙላችሁ አይባልም እኮ፡፡ ከምን ጋር በማያያዝ ነው የእድሜ ጣሪያ የምናስቀምጠው? ለደቂቃም፣ ለሴኪንድም ከእግዚአብሔርጋር መለየት የለበትም የሰው ልጅ እያልን ፣ ሁሉም መላ ሕይወታችን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ነው፡፡ ምናልባት ከእግዚአብሔር ክልል ውጪ፣ እርሱ ከሚገዛው፣ ከሚያስተዳድረው፣ ከፈጠረው ዓለም ውጪ ሆነ ሌላ ዓለም ኖሮ፣ ሌላ አስተዳዳሪ፣ ሌላ ገዢ ኖሮ ከእሱ ተለያይተን ከፈለግን ደግሞ ሌላ አብረን ለመኖር ውል የምንመሠርትበት ኑሮ አይደለም እኮ ይኼ፡፡ በየትኛውም ሰዓት ውስጥ፣ በኃጢያት ውስጥም እያለንም የእግዚአብሔርን ስም እንጠራለን፡፡ ከዚያ ከወደቅንበት የኃጢያት ጉድጓድ፣ የኃጢያት ማጥ ውስጥ ሊያወጣን የሚችለው፤ መፍትሔ እንዲሰጠን እግዚአብሔር ቁልፍ የሆነውም የችግራችን መፍትሔም ያለው ከእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ ስለዚህ ፈፅሞ እንዲህ ዓይነት ትምሕርት ልንሰማም አይገባንም፡፡ ቆይ ልጅ ናችሁ፣ እንዲህ፣ እንዲህ እያሉ የሚሉ ትምሕርት ያነሰው ሰው፣ ወይ ደግሞ ፈጽሞ መንፈሳዊ ምክርና ትምሕርት ተፈልጎ የታጣበት ሰው የሚናገረው የሚያስረዳው የሌለው መጽሐፍትን ጠቅሶ የማያስተምር፣ እንዲህ ዓይነት ካሕን በልብ ወለድ ስለሚናገር ምንቸገረው? እንዳንመነኩስም ገና ነሽ፣ እንዳንቆርብም ገና ነሽ፣ ባይሆን ካሕን ማስተማር ያለበት ሁል ጊዜ ለምዕመናን እግዚአብሔር ቢረዳቸው ከኃጢያት እንዲለዩ ብቻ ነው፡፡ ጊዜ ሳንሰጥ መናገር ያለብን ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበሉ፣ እንደዚህ አድርጉ ኃጢያት ላይ ወድቄያለሁ አባቴ ብንባል፤ በል ቶሎ ንስሐ ግባና ወደ እግዚአብሔር ተመለስ፣ ቶሎ ቁረብ ነው ማለት ያለብን፡፡ ሁሌ የምናገረው ቋንቋ ይኼ ነው፡፡የእግዚአብሔር ቅድስና የእኛን የረከሰውን ሕይወት ከኃጢያት ያነፃል፤ የእኛ ኃጢያት ግን የእግዚአብሔርን ቅድስና አያረክስም፡፡

ስለዚህ ጠያቂያችን፤ ቅዱስ ቁርባኑም፣ ፀበሉም፣ መስቀሉም ፣ ቃለእግዚአብሔሩም፣ ቅዳሴውም ይኼ ሁሉ እኛን ከኃጢያት የሚያነፃ ነው እንጂ ጨርሶ የሚያረክስን ኃጢያታችንን የሚያባብስብን ነገር አይደለም ይኼ፡ አሁንም ጠያቂያችን እንዲህ ዓይነት ፍላጎት፣ ምኞት እያለዎት ገና ነዎት፣ የወጣትነት ዕድሜ ነው፣ ብዙ ነገር አካብደን ፣ ተስፋ ቆርጠን የምንርቅበት የሕይወት ደረጃ አይደለም ያለነው፡፡ እርስዎ ያሉት እንግዲህ 30 ዓመት ይሙላሽ የሚለው ገና የእዚህ ዕድሜ ባለቤት እንኳን እንዳልሆኑ ፣ የልጅነት የወጣትነት ዕድሜ ላይ የተፈተኑበት ነገር ምን እንደሆነ፣ በግል ሕይወትዎ ምክርም መክረን፣ እንደ ቤተክርስቲያን መምህር፤ እንደ ቤተክርስቲያን አባት የሚስተካከለው ነገር እንዲስተካክል ይደረጋል፡፡ እግዚአብሔርም ያግዘናል፣ ቸርነቱ ፣ ምሕረቱ ብዙ ስለሆነ፣ በተለመደው የውስጥ አድራሻችን ደውለው ያግኙንና ተጨማሪ ምክር እንሰጥዎታለን፡፡ በነገሩ ሁሉ የሚመክረን እግዚአብሔር የተመሰገነ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቤት የሚለየን የሚያርቀን፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ምንድን ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ለሮሜ ክርስቲያኖች በፃፈው መልእክቱ በሮሜ መልእክት ምዕራፍ 8 ያለው ማለት ነው፡፡ ከቁጥር 35 ጀምረን ስናነብ የምናገኘው ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ ማነው? በጣም ከባድ የተባሉ ብዙ ጦርነት ነው? ረሐብ ነው? ሠይፍ ነው? ደዌ ነው? ምንድን ነው? ብሎ ዘርዝሯቸዋል፣ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ የለም ፡፡ ስለዚህ ብዙ የሥጋ ምክንያቶችን እየደረደርን ከቅዱስ ቁርባን ፍቅር የሚለየን ነገር አንዳችም የለም፡፡ይኼንን ነው ማየት ያለብን።

(ይቀጥላል)👇

ቴሌግራም ግሩፓችንን በየቀኑ ይከታተሉ፣ ለወገኖትም ሼር ያድርጉ፦
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

👉ጥያቄ፦ ኀጢአት የሰራ ሰው ድንገት #ንስሐ ሳይገባ ቢሞት #ገነት ሊገባ ይችላል ወይስ አይችልም?

መልስ፦ አባላት ሁላችሁም በዚህ ጥያቄ ላይ የራሳችሁን ተሳትፎ እንድታደርጉ እድሉ ቢገጥማችሁ ምን ማለት እንደምትችሉ መገመት አያቅታችሁም። መቼም፤ የኀአተኛን ሞት አልወድም ይላል እግዚአብሔር በንስሐ ተመልሶ ዘለአለማዊ ህይወት ያገኝ ዘንድ እንጂ። ጠያቂያችን እርስዎም ቢሆን በአካል አግኝተነዎት መወያየት ብንችል ኖሮ መቼም ቅዱሳት መፃህፍት እንዳስተማሩን አባቶቻችን እንደነገሩን ከሆነ የሚኮነነው ኀጢአተኛው ሰው እንጂ ፃድቅ አይደለም። ይሄ ሁሉ በዚህ በስጋዊ አለም ውስጥ የአለሙ ነገር እያባዘናቸው ፈቃደ ስጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው እንዲያስገዙ ይሄንኑ ጎዶሎው የማይሞላው አለም ሲቃትቱና መከራ ስቃያቸውን ሲበሉ አንድ ቀንም እግዚአብሔር አብዝቶ ከሰጣቸው ጊዜ እና ኑሮ ለንስሐ እራሳቸውን ሳያዘጋጁ ከነኀጢአታቸው ተጠቅልለው ወደ ሰማያዊ የነፍስ ሞት የሚሄዱ በጣም ብዙዎች ናቸው ። እንግዲህ ሰው ኀጢአት የሚገለፅበት ብዙ የጥፋት መንገድ አለና፤ እየተነገረው! እየተማረ! እየተመከረ! እየተገሰፀ! እውነቱን እንዲያውቅ እየተደረገ! ወደ ንስሐ ህይወትም እንዲመለስ ቤተክርስቲያን እጅዋን ዘርግታ እየለመነችው! ኀጢአት ይሻለኛል ይሄ የጥፋቱ አለም ይሻለኛል ብሎ የእኔ ህይወቴ ይህ ነው፤ በዚህ በምድር ላይ ያልቃል ብሎ የወሰነው የልተኮነነ ሰው ማን ይኮነናል?

በእርግጥ ጥፋተኞችን በ 2 መንገድ ልንከፍላቸው እንችላለን። አንዳንዶቹ ጨርሰው የድንቁርና ጨለማ ውስጥ ገብተው ማንም ሳያስተምራቸው ሳይገስፃቸው ባላዋቂነት እንዲሁ እንደተጠቀለሉ ይመጡና እውነትና ሀሰትን፣ ጽድቅንና ኩነኔን፣ ጨለማና ብርሃንን፣ ህይወትና ሞትን ለይተው ሳይነገራቸው ሳያውቁት የሚኖሩ አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ አጣጥመው ሁሉን ነገር አውቀው ተረድተው የምድሩ ነገር ይሻለናል ብለው የምድሩን ነገር ይዘው ሃይማኖታቸውን ምግባራቸውን አቃለው አርክሰው በኀጢአት ህይወት ውስጥ እድሜ ዘመናቸውን የሚኖሩ አሉ። ከነዛኞቹ ጥፋት የነዚህኞቹ እጥፍ ድርብ ነው።

እግዚአብሔር መቼስ እውነተኛ ከፋይ ፍርድ የማያዳላ ለእያንዳንዱ እንደየስራው ወጋውን የሚሰጥ እውነተኛ ዳኛ ስለሆነ በሰራነው ኀጢአት መጠን በሰራነውም ፅድቅ መጠን ተመጣጣኝ ዋጋ ይከፍላል። ኀጢአተኞችም የሚፈረድባቸው በሰሩት መጠን ነው። እነሱ ባልሰሩት በሌላው ኀጢአት አይፈረድባቸውም። ሰው ነው በፍርደ ገምድልነት የወደደውን ኀጢአተኛም ቢሆን ያፀድቃል፣ የጠላውን ደግሞ ፃድቅ ቢሆንም ይኮንናል ፍርዱም እጥፍ ድርብ አድርጎ የሚፈርድባቸው አለ የሚያቀልላቸውም አለ። እግዚአብሔር ግን አይሳሳትም። የሰው ፊትም አይቶ አያዳላም። አንተ ትቀርበኛለህ፥አንተ ትርቀኛለህ ፣ አንተ ዘመዴ ነህ ፥ አንተ ባእዴ ነህ ፣ አንተ ባለውለታዬ ነህ አንተ ውለታ አልከፈልክም አይልም። እሱ በሰጠን እኛ በምንጸድቅበት እኛ በምንድንበት በዚህ በእውነተኛ ሃይማኖታችን ምግባራችን ፀንተን እንድንኖር ነው። እሱን  መውደዳችን እሱጋር መሆናችን ለእሱ ማድረጋችን እሚገለፅበት ከዚሁ እኛው እርስ በእርሳችን በመልካም ነገር አንዱን አንዱ እያከበረው እየወደደው እየተፈቃቀርን የምንሄድበት ጉዞ ሁሉ እኛው እራሳችን የዘራነውን ስለምናጭድ መልካም ብንዘራ መልካም የስንዴ ፍሬ ያለበትን እንሰበስባለን እናጭዳለን፤ ኀጢአት ብንሰራ ደግሞ ኀጢአት እናጭዳለን መለት ነው። ጽድቅም ብንሰራ ጽድቅን ነው ኩነኔም ብንሰራ ኩነኔን እናጭዳለን ማለት ነው።

ስለዚህ እየተነገረው፣ እየሰማ፣ እውነትና ሀሰቱን ጽድቅና ኩነኔ በረሃንና ጨለማው ለይቶ የኀጢአት መጨረሻውና ፍፃሜው ሞት እንደሆነ እያወቀ ከዚህኛው አለም የተለየ አለም እንዳለ እየተነገረው፤ ከዚህኛው ህይወት የተሻለ የሚበልጥ ዘለዓለማዊ ህይወት እንዳለ እይተነገረው፤ ከዚህኛው ከስጋዊ ኩነኔ ይልቅ በነፍስ ያለው ኩነኔ እጅግ የፀና መሆኑ እየተነገረው ይሄን ሁሉ ሳይሰማ ሳይለማ የያዝኩት ይሻለኛል ብሎ አሻፈረኝ ብሎ ክብረ ቤተከርስቲያንን ንቆ ደፍሮ የኖረ ሰው ያልተኮነነ ማን ሊኮነን ይችላል?! ሁላችንም ግን ስለ ወንድሞቻችን ስለ ወገኖቻችን መፀለይ ያለብን ማንም ሰው በነፍስ እንዳይጠፋ መፀለይ ነው። በአንዳችንም ላይ ለመፍረድ አቅሙ የለንም፤ ሁላችንም ኀጢአተኞች ነን። ምንስ ጽድቅና ኀጢአትን፣ እውነትና ሀሰትን ፣ ብርሃንና ጨለማን እንደው ከትምህርትም በፊት እኮ አዋቂ ፍጥረት አድርጎ ስለፈጠረን ብቻ በተሰጠን የተፈጥሮ ፀጋችን ማወቅ እንችላለን። ይሄን ሁሉ እንዲያውም በእኛ ላይ አሳድሮብን፣ ቀርፆብን ፣የሚረዳን አይምሮ ኖሮን ወደን ፈቅደን ለመኮነን ተስማምተን በግብረ ሰይጣን ትላንትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችን ድል ነስቶ ከእኛ የለየውን ሰይጣንን ዘመድ አድርገን አሁን እሱጋር መቀጠል ከፈለግን ኀጢአተኛ ሰው እንደሚፈረድበት ቅዱሳን መፅሐፍትም አስተምረውናል። በእርግጥ እኛ በእግዚአብሔር የጽድቅ ወንበር ላይ ተቀምጠን በፍርድ አደባባይ ተሰይመን አንዳችን በአንዱ ላይ የምንፈርድበት ምንም አይነት ሁኔታ የለም። እግዚአብሔር ያከበራቸው የመረጣቸው ቅዱሳኑ በዚህ በፍርድ አደባባይ በእያንዳንዱ ላይ ሊመሰክሩበት በእርግጥ ቅዱሳን ሐዋሪያት እናንተስ በኋለኛው ዘመን በፍርድ አዳባባይ ስመጣ በ12 ወንበር ላይ ትሰየማላችሁ ብሏቸዋል። እነዚህ የተለየ ክብር ያለቸው የተለየ ረቂቁንና የተሰወረውን ነገር አጥርተው ለማየት እግዚአብሔር ፀጋወን ያሳደረባቸው ቅዱሳን ናቸውና፤ ስለዚህ ወገኖች መቼ እንደምንጠራ አናውቅምና ከወዲሁ ሳይመሽብን ሳይረፍድብን ከጠፋንበት የጨለማ ጉዞ ውስጥ ወጥተን እጅግ እግዚአብሔርን ልናይ ወደሚያስችለን ብርሀን መጥተን በእውነተኛ መንገድ ተጉዘን ወደ ንስሐ ህይወት ተመልሰን የቤተክርስቲያንን ድምፅ ሰምተን ከኀጢአት ማሰሪያ ተፈተን እውነተኛውን መንግስት ለመውረስ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን።


ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org ላይ ያገኛሉ

👉ጥያቄ፡- አባ እንዴት ነዎት? በመጀመሪያ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ምእመናን ለሚጠይቁት ጥያቄ በቂና ወደ #ንስሐ የሚመልስ፣ ልባችን ተሰብሮ ወደ ንስሐ እንድንመለስ ስለረዱን እግዚአብሔር አምላክ ረጅም እድሜ ይስጥዎት እኔ ደካማ #ኃጢአተኛ ስሆን፣ ኃጢአቴም ሁሌ እያነዘዘኝ እያቆሰለኝ መፈጠሬን ሁሉ አስጠልቶኝ ተስፋ የቆረጥኩ ሰው ነኝ፣ ግን አጋጣሚ ድረ-ገጻችሁን አግኝቼ ኃጢአቴን ሳስበው የምትሰጡትን ትምሕርት እንኳን መከታተል አልቻልኩም፣ ልፈነዳ ነው የምደርሰው ፈጣሪን እንዴት አድርጌ ብለምነው ነው ይቅር የሚለኝ? እኔ በጣም ከባድ ነው ብዘርዝረው አያልቅም፣ አባ ፈቃደኛ ከሆኑ እርስዎን በአካል ነው ማግኘት ነው የምፈልገው፡-

✍መልስ፡- ጠያቂያችን እግዚአብሔር ወዶና ፈቅዶ እንኳንስ ወደዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራማችን በሰላም መጡ ነው የምንለው፣ ወደ እዚህ የመምጣትዎ ነገር ወደ እግዚአብሔር የመቅረብዎት አጋጣሚ ነው ሁላችንም ያየነው፣ እግዚአብሔር ደግሞ ወደ እሱ የመጣውን ሰው ዝም አይለውም፡፡

በዚህ ጭንቀት ውስጥ፣ በዚህ ኃጢአት ውስጥ፣ በዚህ ፈተና ውስጥ፣ በዚህ መከራ ውስጥ እንደወደቀ አይተውም፣ ቸርና መሐሪ አምላክ ነው፣ ሁሌም ከአንደበታችን መለየት የሌለበት ኃይለ ቃል “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሣ ነው” ቤተክርስቲያናችን የንሰሐ ግምጃ ቤት ናት፣ ንስሐ ለሚገቡ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት የተዘጋጀ ማንም የማይከለክለው፣ ማንም የማይወስድብን በጎ እድል አለን፡፡

በንስሐ ሕይወት ወደ እግዚአብሔር እንመለስ ዘንድ የእግዚአብሔር የምሕረት እጆቹ፣ የይቅርታ እጆቹ የተዘረጉ ናቸው ይቅር ይለን ዘንድ አኛም የመማፀኛችን ከተማ አድርጎ በዚህ ዓለም ላይ ስለ እኛ የተከላትና፣ ስለእኛ በደሙ የዋጃት ቅድስት ቤተክርስቲያንም በሮቿ የተከፈቱ ናቸው፣ የተዘጉ በሮች የሏትም ፡፡

እግዚአብሔር የተዘጋ በር የለውም ሁላችንም እስከ ጢያታችን፣ እስከበደላችን፣ እስከጉዳችን፣ እስከኮተታችን ፣ እስከሰቀቀናችን፣ እስከ ኃፍረታችን ምሕረትና ቸርነት ወደሚያበዛልን አምላካችን ቤት እንመጣ ዘንድ የእግዚአብሔር በር ክፍት ነው፣ የእግዚአብሔር የምሕረት እጅ፣ የይቅርታ እጅ የተዘረጉ ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር ነው አኛም ብንሆን እስከነ ኃጢያታችን፣ እስከነ በደላችን በፍፁም ልጅነት፣ በፍፁም እምነት፣ በድፍረት ግድላችሁም ኑ ተያይዘን ከምንጠፋ፣ ተያይዘን እንልማ፣ ተያይዘን ኃጢያተኛ ከምንሆን ይልቅ ተያይዘን ፃድቅ እንሁን፣ እንፅደቅ እያልን ጥሪ የምናደርገው ከሌላው የተሻለ ሕይወት ያለን፣ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ መሆኑን ቀምሰን አጣጥመን ስለምናውቅ ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሔር ልጁ በጠፋበት በአንድ ሐብታም ራሱን መስሎ የጠፋውን ልጄን አግኝቼዋለሁ ደስ ይበላችሁ፣ ደስ ብሎኛል ነው ያለው፣ የልጁን መገኘት ለደስታው ወደር አጠቶለት የተለየ ዝግጅት አድርጎ ከዚህ የሚበልጥ ሌላ የደስታ ጊዜ የለኝም የሚያስደስተኝም አንዳች ነገር የለም፣በልጄ መገኘት ደስታዬ ወደር የሌለው ስለሆነ ለዚህ ደስታዬ ይሆን ዘንድ እነሆ ወደ ግብዣዬ እንድትመጡ ነው ያለው፡፡

ፍሪዳው ታርዷል፣ ተወራርዷል፣ ጠጁ ተጥሏል፣ ዳሱም ተሠርቷል፣ ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ፧ተዘጋጅቷል፣ ተሟልቷል ኑ ከእኔ ጋር ተደሰቱ ከእኔ ጋር ደስ ብሎኛል ነው ያለው፣ በንስሐ ተፈልጎ የተገኘ ሰው በእኛና በራሱ በባለቤቱ ዘንድ ብቻ ሳይሆን ደስታው በሰማይ መላእክትና በእግዚአብሔር ዘንድም ደስታ ይደረገናል ይለናል መጽሐፉ፡፡

ከዚህ የተነሳ ጠያቂያችን በእርግጥም ነው ኃጢያት ያላሳፈረው፣ ኃጢያት ያላስለቀሰው፣ ኃጢያት ያላሳዘነው ሰው ሌላ በምን ሊያዝን ይችላል? እውነትም እንዳሉት ነው እግዚአብሔር ቀድሶ በፈጠራት ምድር እንዲህ በረከሰ ሕይወት ስንኖር እስከነ ጉዳችን ወደን ፈቅደን የገባንበትን ኃጢያታችንን ተሸክመን እስከ መቼ ድረስ ነው እንዲህ ብለን ደንዝዘንስ የምንቀጥለው? እውነትም ነው ያጨናንቃል፣ ግን ከአሁን በኋላ በእርስዎ ሕይወት ላይ ጭንቀት አይሠራም፣ ሐፍረት አይሠራም፡፡

ጠያቂያችን እስካሁን የመጡበት የኃጢያት ጉዞ፣ የፈተና ጉዞም ሊቀጥሉ አያስፈልግም ወደ ንስሐ ሕይወት ይምጡና ትክክለኛውን መንገድ እግዚአብሔር ወደ እውነተኛዋ፣ ለልጆቹ ያወርሳት ዘንድ ወደ አዘጋጃት መንግሥቱ ሁላችንም እንዲያሰባስበን አሁኑኑ ፈጥኖ ወደ ንስሐ ሕይወት መምጣት ያስፈልጋል ” የመዳን ቀን ዛሬ ነው፣ ያውም አሁን ነው” ተብለናል የኃጢያት ቀጠሮ አያስፈልግም፡፡

ስለዚህ እርስዎም በትክክለኛ የእኛን ድረ-ገጽ አግኝተው፣ በእሱ ደግሞ ከእርስዎ ጉዳይ ጋር፣ ከእርስዎ ሐሳብ ጋር፣ ከእርስዎ ጭንቀት ጋር አብሮ ሊሔድ፣ ሊመክር፣ ሊገስፅ፣ ሊያስተምር የሚችል መልእክታችንን አግኝተው፣ ከልብ ተመልሰው ከሆነ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ ሳያጠፉ በቶሎ ያግኙን፡፡

እንዳሉትም በአካል አግኝተውን፣ እኛም እግዚአብሔር በእውነትም የዘራነውን ለፍሬ አብቅቶታል፣ በእኛ በደካሞቹ ጥረትና ትጋት የተዘራው ዘራችን ሠለሳ፣ ስልሳ፣ መቶ አፍርቷል የምንለው በእንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለንስሐ ሕይወት አብቅተን ማየት፣ ለቅዱስ ቁርባን አብቅተን ማየት፣ ወደ መንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ ወደ ቀደመ ክብራቸው ተመልሰው ማየት ከዚህ በላይ እኛንም እግዚአብሔርንም የሚያስደስት ነገር የለም፡፡

እግዚአብሔር ይመስገን ደግሞም እግዚአብሔር ያደርገዋል በዚችው ከሁሉ ባነሰቸው አገልግሎታችን እና ይህንን አገልግሎት ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ወገኖቻችን ከገቢረ ኃጢያት፣ ወደ ገቢረ ፅድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሐን፣ ካለማመን ወደ ማመን በጣም ብዙ መጥተዋል እግዚአብሔር ይመስገን፣
ከዚህ የተነሣ በአካልም ተገናኝተን እንዳሉትም ጊዜም አጥፍተን፣ ደክመንም ቢሆን እርስዎን ማትረፍ እንደምንችል እናምናለን፣ ባለን አድራሻ ደውለው ያግኙን፡፡

የመከረን የገሰፀን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን አሜን

ቴሌግራም ግሩፓችንን በየቀኑ ይከታተሉ፣ ለወገንዎትም ሼር ያድርጉ፡-
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q