ስለ ንስሐ ጥያቄና መልስ ቁ.2

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ንስሐ ጥያቄና መልስ ቁ.2

ስለ ንስሐ ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች

 ጠያቂያችን በድምፅ ያቀረቡት የንስኅ ሱባኤን በሚመለከት ፤ በመጀመርያ አንድ ክርስቲያን በሰራው ኅጢአት ተፀፅቶ በንስኅ ላይ እያለ ንስኅ የገባበትን ኅጢአትም ሆነ ሌላ ኅጢአት ለመስራት ራሱን ለጥፋት አጋልጦ መስጠት አይገባውም። ምንም እንኳን የሰይጣን ፈተና መምጫው ረቂቅ ቢሆንም ፤ ነገር ግን ሰው ክቡር ፍጡር እና ክፉና መልካምን መለየት የሚያስችል አይምሮ ያለው  ስለሆነ ሰይጣን በቅናት ቢፈትነን እንኳን የግድም ብለን ራሳችንን መግዛት አለብን። ይሄንን ሁሉ ትግል አድርገን በፈተናው ከተሸነፍን ግን ጠያቂያችን እንዳሉት በንስኅ ሱባኤ ሆነን ንስኅ ስለተቀበልንበት ኅጢአት ወይም ሌላ የኅጢአት ሥራ ከፈፀምን ፦

1ኛ/ ንስኅ የገባንበትን የሱባኤ ጊዜ ሳናቋርጥ የተሰጠንን ቀኖና  እስከ መጨረሻው ድረስ  መቀጠል አለብን።  

2ኛ በሱባኤው መሃል ስለፈፀምነው ተመሳሳይ ወይም ሌላ ኅጢአት እንደገና ንስኅ መግባት አለብን። 

ምክንያቱም ቀኖና የሚሰጠን በፈጸምነው ኅጢአት  መጠን ተለክቶ ስለሆነ ንስኅ ለገባንበት ኀጢአት የተሰጠንን ቀኖና እስከመጨረሻው መፈጸም አለብን፤ እንዲሁም ንስኀ ላልገባንበት ኅጢአት እንደገና ንስኀ ገብተን ቀኖና መቀበል ያስፈልገናል። 

ስለዚህ ጠያቂያችን በኛ በኩል የምንመክርዎት ከላይ እንደገለፅነው አሁንም የጀመሩትን የሱባኤ ጊዜ በፅናት ሆነው ይጨርሱ፤ ከዛ በኋላ ወደ አባቶች ቀርበው  በመሀል ስላጋጠመዎት ፈተና በግልፅ ያስረዱዋቸው። ካህኑም የእርስዎን ውስጣዊ ችግር በተለያየ መንገድ በቅርብ ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስኅ ህይወት እንዲቀርቡ እና በተደጋጋሚ ከተፈተኑበት የኅጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጡ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። እርሰስዎም ወደፊት ይህን ኅጢአት ላለመስራት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ያድርጉ። ክርስቲያን ሺ ጊዜ ፈተና ቢደርስበትና ቢወድቅም ሺ ጊዜ ከፈተናው እየተነሳ በፈጣሪው ሃይል የሰይጣንን ውጊያ ድል የሚነሳበት አቅም ስላለው በየትኛውም የሰይጣን መሰናክል ተጠልፈን ላለመውደቅና ተሸንፈን ላለመቅረት ዘወትር መትጋትና መፅናት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ምናልባት እኛ ያልተረዳንዎት ችግር ካለ በውስጥ መስመር አግኝቸው ቢያብራሩልን ተጨማሪ ምክርና መፍትሄ ልንሰጥዎት እንችላለን።

ጠያቂያችን፤ በመሰረቱ የድፍረት ኅጢአት የሚለው አገላለፅዎ ሃሳብን በግልፅ ለማብራራት አያስችልም። ይሁን እንጂ ኅጢአት ሁሉ የድፍረት ጥፋት ነው። ማንኛውም ክርስቲያን የሃይማኖትና የምግባር ጉድለት ሲያጋጥመው በአንፃሩ ኅጢአት ወደመስራት ዝንባሌ ውስጥ ይገባል። የኅጢአት መነሻው ምኞት ነው፤ ምኞት ወደ ተግባር ሲቀየር ኅጢአት ይሆናል፤ የኅጢአት ደግሞ መጨረሻው የዘለዓለም ሞት ነው። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላንን ቀርቶ ከሰው እና ከማህበረሰቡ ጋርም አብሮ የማያኖረውን እና ፍቅር የሚያሳጣውን ድፍረት መፈፀም የለብንም። መቼም ስለምንሰራው ማንኛውንም ኅጢአት ስንፈፅም በተለምዶ አነጋገር ሰይጣን አሳስቶኝ ነው ብንልም እንኳን፤ ይሄን አታድርግ ተብሎ በእግዚአብሔር የተደነገገውን ትዕዛዝ ተላልፎ የሚፈፅመው ኅጢአት መሆኑን ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን እያወቀና እየተገነዘበ ለግዜውም ቢሆን ለራሱ ምክንያት በመስጠት ኅጢአቱን በመስራት የሚያገኘውን ጥቅም በማሰብና በመቁጠር በድፍረት የሚፈፅመው ነው።

ስለዚህ ጠያቂችን ሁል ግዜ በነፍሳችን ጉዳይ ላይ እራሳችን በምንፈጥረው የጥፋት ምክንያቶችን በመደርደራችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተጠያቂነት ነፃ ስለማያደርገን ወደፊት ኅጢአትን በድፍረት ላለመስራት ማድረግ ያለብን፦

1ኛ እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር፣

2ኛ  በካህናት አባቶቻችን ትምህርት እና ምክር መኖር፣

3ኛ  ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደን ከክፉ ነገር እንዲጠብቀን መማፀን፣

4ኛ ስንወጣም ስንገባም በየእለት ተግባራችን የእግዚአብሔር ጠብቆት እንዳይለየን በትዕግስትና በማስተዋል በክርስቲያናዊ ስነምግባር በፆም በፀሎት ተወስነን መኖር ያስፈልጋል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት በንስኀ  ዙርያ ለተላኩልን ጥያቄዎች ያስተላለፍናቸውን መልእክቶች ከድረገጻችን በመመልከት ተጨማሪ ትምህርት  እንዲያገኙበት ይህን ሊንክ ልከንልዎታል።

https://yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ/

መልስ፦ ጠያቂያችን ኀጢአት አጥብቆ መፀየፍና መጥላት ክርስቲያናዊ ህይወት ነው። ይሁን እንጂ ኀጢአትን አጥብቀን ከመጥላት የተነሳ ደግሞ ኀጢአት እንዳንሰራ በሞት ለመቅደም መመኘት እና መወሰን ይህም ቢሆን እራሱን የቻለ ደካማ የሆነ የሥጋ ሀሳብ ነው። 

እግዚአብሔር እኛን በኀጢአት እንድንኖር የማይፈቅድ አምላክ ስለሆነ በዚሁ በለበስነው ደካማ ሥጋ ዘወትር እየተፈተንን በኀጢአት የምንወድቅበት ፈተና ቢበዛም እንኳን ከወደቅንበት የኀጢአት ወጥመድ ውስጥ በንስኀ ህይወት ለመነሳት መንፈሳዊ ተጋድሎ ማድረግ ክርስቲያናዊ ህይወት ነው። 

ስለዚህ ጠያቂያችን የዚህን አለም ጥፋት እና ተቆጥሮ የማያልቀውን ኀጢአት ስንመለከት በእርግጥም በሃይማኖትና በምግባር ፀንቶ ለሚኖር ክርስቲያን ያለውን መንፈሳዊ ህይወት ከሚያጣ ይልቅ ሞትን መምረጥ ሊያስመኝ ይችላል። ነገር ግን በሞት ኀጢአትን መለየት ስለማይቻል ከምንም በላይ ትጥቃችን እና ፀጋችን ይበዛልን ዘንድ በዚሁ ኀጥያትና ፅድቅ በተቀላቀሉበት ዓለም ውስጥ ፅድን ከኀጢአት፣ ህይወትን ከሞት፣ ብርሃንን ከጨለማ ለመለየት በኀጢአተኛው ዓለም ውስጥ መንፈሳዊ ሆነን ለመኖር የምናደርገው የዘወትር ተጋድሎ የእዚአብሔርን ክብር ስለሚያበዛልን እርስዎም እግዚአብሔር የልብዎትን መልካም ምኞትና ስለሚያልፈው ዓለም ያለወትን መልካም ምኞት እግዚአብሔር ስለሚያውቀው የእርሱ ቸርነት ስለማይለይዎት ሳይጨናነቁና በፀሎትና በሃይማኖትና በምግባር ፀንተው ህይወትዎትን እንዲያስቀጥሉ ይህን አጭር ምክር እንዲደርስዎት አድርገናል። 

ለተጨማሪ ምክርና ትምህርት በውስጥ መስመር በሚደርስዎ ስልክ ደውለው ሊያነጋግሩን ይችላሉ።

ጠያቂያችን ግለሰባዊ ወሲብ ወይም ከራስ ጋር የዝሙት ሃሳብ መፈፀም ከፍተኛ የኅጢአት አይነት እንደሆነ ከዚህ በፊት በቀረቡልን ጥያቄዎች መነሻነት አስታውቀናል። ይሁን እንጂ በየጊዜው በሚያጋጥም ፈተና የተቸገሩ አባላቶቻችን በእኛ በኩል የመፍትሄ ሃሳብ እንድንሰጣቸው ጥያቄ የማቅረባቸው ሁኔታ እጅግ ተገቢ ነው። ምክንያቱም እንኳንስ በሃይማኖት ጉዳይ ይቅርና በሥጋ ጉዳዮቻችን እንኳን ስንቸገር ለሚመለከተው የሃሳባችን ተጋሪ ችግራችንን ግልፅ ካላደረግን መፍትሄ ማግኘት አንችልም። አንድ ታማሚ ሰው የህመሙን መፍትሄ እና ጠቅላላ ሁኔታ ለሀኪሙ በግልፅነት ማስረዳት ካልቻለ የጤና ባለሞያው ወይም ዶክተሩ በሰውየው ያለውን በሽታ በመሳሪያ የታገዘ ምርመራና የመድሀኒት ህክምና ለማድረግ አያስችለውም። 

ስለዚህ ወደ ጥያቄው ስንመለስ ይህ ግለሰባዊ ወሲብ ወይም ደግሞ ከራስ ጋር ዝሙት መፈፀም የሚለው ሃሳብ ሲጀመር ሥነተፈጥሮን የሚዋጋ ወይም ከተፈጥሮ ስርዓት ውጭ የሆነ በሰይጣናዊ መንፈስ አነሳሽነት የሰው ልጅ የሚወድቅበት የኅጢአት አይነት ወይም በመፅሐፍ ቅዱስ እንደተገለፀው የዚህ አይነት ኅጢአት ግብረሰዶማዊነት ይባላል። በዚህ አይነት ፈተና ያለ ሰው የራሳችን ተፈጥሮ በማይፈቅደው ነገርና የራሳችን አይምሮ ስለሚቃወመን ኅጢአቱን በመፈፀም ከተላለፍነው ጥፋት ይልቅ ጠያቂያችን እንዳሉት ስነ አይምሯችን የመንፈስ እረፍት ያጣል፤ የተረጋጋ መንፈስም አይኖረንም። በዚህን ጊዜ የሰው ልጅ ተስፋ ቆርጦ ወደ በለጠ ኅጢአትና የጥፋት ጉድጓድ ውስጥ እንድንገባ እርኩስ መንፈስ ችግሩን እያባባሰ ወደ ንስኅ ህይወት እንዳንመለስ ያደርገናል። 

ስለዚህ የኅጢአት አይነት በመፅሐፍ ቅዱስ አስተምሮ መሰረት በቅርብ ቀን ሰፋ ያለ ትምህርት የምናቀርብበት ሆኖ፤ ለግዜው ግን ጠያቂያችን በእርግጠኝነት ማመን ያለብዎት ምንም እንኳን በዚህ አይነት ኅጢአት ቢወድቁም  የእግዚአብሔር መንፈስ ፈፅሞ ስላልተለየዎትና እርስዎም ወደ ንስኅ ለመቅረብ  እየተፀፀቱ በመቅረብና ግልፅ ሆነው በኛም በኩል ምክር እንድንሰጥዎ ከፍተኛ ፍላጎት ያለዎት በመሆኑ ከዚህ ክፉ የኅጢአት ፈተና ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚለዩ አይጠራጠሩ። እርስዎ ማድረግ ያለብዎትን ምክር እንድንሰጥዎት በውስጥ መስመር በሚደርስዎት ቁጥር ደውለው እንዲያገኙን ሆኖ ከዚህ ክፉ ሃሳብ ጋር አብሮ ላለመኖር በፀሎትና የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ፣ ወደ ቤተክርስቲያን በመመላለስ፣ ስርዓተ ጥምቀት በመፈፀም ፣ በመስቀል በመዳበስ፣ በአጠቃላይ ባሉበትም ቦታ ሆነው የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩ፣ በድንግል ማርያም ስም፣ በቅዱሳኑ እና በራሱ በባለቤቱ ስም ይህንን ክፉ መንፈስ ከኔ አርቅልኝ እያሉ ያለዎትን የመማፀን ፀሎት ማቅረቦትን እንዳያቋርጡ እንመክራለን። ከላይ እንደተገለፀው ኅጢአትን ለመተው እየፈለጉ እንዳይተውት የሚያደርግ መንፈስ እንዴት እንደሚታገልዎት በሽታው ረቂቅ መንፈስ ስለሆነ ከእርስዎ ጋር ስንመካከርና ምክር ስንሰጥዎት ሁሉም ነገር እየቀለለዎት ስለሚመጣ በውስጥ መስመር ያግኙን በማለት ይህ አጭር መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።

እስከዚያው ድረስ የእግዚአብሔር አጋዥነትና ጠባቂነት አይለይዎት

ጠያቂያችን ከዚህ ቀደም ስለ ሰዶማዊነት እና ተዛማጅ ጉዳዮች በሚመለከት ከፍተኛ የኅጢአት አይነት እንደሆነ መልእክት ማስተላለፉችንን እናስታውሳለን :: አሁንም ከራስም ጋር ሆነ የሰዶማዊነት መንፈስ ባለበት የዝሙት ኀጢአት ስራ ፤እንኳን ክህነት ሊኖረው ቀርቶ በነፍሱም በኩል ከባድ የንስሃ ቀኖና ካልፈጸመ በስተቀር በፈጣሪው ዘንድ ያስጠይቀዋል :: በእርግጥ የሰው ልጅ ለኅጢአት ባይፈጠርም ለኀጢአት የሚሰማማ ስጋ ስለለበስ በዚሁ ደካማ ስጋው አስቦበትም ይሁን ሳያሰበው ሰይጣን ደካማ ጐኑን ወይም የሃሳብ ዝንባሌውን ፈልጎ በሰውየው ላይ በረቂቅ መንፈሱ አድሮ ስለሚዋጋ ሁሉም ሰው በተለያ የጥፋት መንገድ ሲስናከል ማየት የተለመደ ነገር ነው።ከጥቂት ፍፁማን በስተቀር ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ ፣ከአዋቂ እስከ ህፃን ድረስ በተለያየ ጥፋት ውስጥ ሁሉም የተጠመደ ነው ::የሆነ ሆኖ ብዙ ሰዎች ኀጢአት ሰለሰሩ እና ብዙ ኀጢአት ስለተፈጸመ ፥ኀጢአትን ቀላል አያደርግም ወይም ደግሞ የእኔ ኀጢአት ከእከሌ ኀጢአት ያንሳል ወይም የእከሌ ኀጢአት ከእኔ ኀጢአት ይበልጣል በሚል የማሻሻያ ሃሳብ ሊወሰን የሚችል አይደለም ::ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ አባላቶቻችን ከኀጢአት ጋር በተያያዘ የሚኖረን አመለካከት ጥልቅና ቁርጠኝነት ሊኖረን ያስፈልጋል :: ይህ ማለት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቤተክርስቲያን ከውስጡ ክፍል ከካህናት እስከ ምእመናን ብዙ ያልተለመዱ እና የሚዘገንኑ የኀጢአት አይነቶች ማየት እየተለመደ ስለመጣ ይህ መጥፎ ልምድ ደግሞ ኀጢአትን እንድንለማመድና እንድንንቅ ወይም ቸላ እንድንል ሰይጣን በስውር ምስጢሩ ሁላችንንም የማደንዘዣ መርፌ የወጋን እስኪመስል በኀጢአት እንቅልፍ ውስጥ ያለን ሰዎች እጅግ ብዙ ነን።

ስለዚህ ካህንም ሆነ ምእመን በሰራው ኀጢአት ከክብሩ ይዋረዳል፤ በእግዚአብሔር ፀጋ የተሰጠው ክህነትም ሆነ መንፈሳዊ ሃይል ከሱ ይወስድበታል :: በንስሓ ሲመለስ ግን ለክህነታዊ አገልግሎት መብቃት ባይችልም የእግዚአብሔርን ሰማያዊ መንግስት ለመውረስ ግን ይታደላል።

ሁላችንም በዚህ ማስተዋል ውስጥ አንድንኖር አይና ህሊናችንን ያብራልን

ጠያቂያችን፤ መታወቅ ያለበት ኅጢአት እስካለ ድረስ ንስኅ ደግሞ የማይቋረጥ ሂደት ነው። ምክንያቱም ለኅጢአት ስርየት ለማግኘት ንስኅ የተባለውን የነፍስ መድኅኒት የሰጠን እራሱ ባለቤቱ መድኅኒአለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ቢቻል ማንኛውም ክርስቲያን ኅጢአት ላለመስራት አጥብቆ መጋደል አለበት። ይህ ማለት ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት አለበት። እርኩስ መንፈስ ሰይጣን ዘወትር በኅጢአት እንድንወድቅ የሚያመጣብንን ፈተና ላለመቀበል በትጋትና በንቃት ቆመን የኅጠአት ምንጭ የሆኑትን ምክንያቶች ሁሉ በማስወገድና በመራቅ ፈቃደ ሥጋችንን አሸንፈን መኖር አለብን።

ይሁን እንጂ ጠያቂያችን እንዳሉት በዚህ ሁሉ ክርስቲያናዊ ህይወት ተወስነን እየኖርን በኅጢዓት ብንወድቅ የንስኅ ቀኖና ተቀብለን እስከ መጨረሻው ድረስ የተሰጠንን የንስኅ ህይወት እንደ ቤተክርስቲያን ስርዓታችን ልናከናውን ሲገባን በመካከል የተሰጠንንም ንስኅ ሳንጨርስ ደግሞ ሌላ ሌላም ተጨማሪ ጥፋት ብንፈፅም፤ ቀኖና ተቀብለን ስላልጨረስነውም ሆነ በተጨማሪ ያጠፋነው ጥፋት ካለ ስለ ስርዓተ ቀኖና ወይም ስለ አንቀፀ ንስኅ ጠንቅቀው ወደሚያውቁ አባቶች ቀርበን በመናዘዝ እንደገና ንስኅ ልንገባ ያስፈልጋል።

 

በተደጋጋሚ እንዳየነውና እንደተረዳነው ከሆነ የብዙ ሰዎች ችግር 1ኛ በየጊዜው በሚያጋጥሟቸው ጥፋት በየጊዜው ወደ ንስኅ አባታቸው ሄደው ለመናዘዝ መሳቀቅ ወይም የፍርሃት መንፈስ ይታይባቸዋል። በ2ኛም ወይም አንድም ጥፋት በሰሩ ቁጥር ወደ ንስኅ አባት በየጊዜው እየሄዱ ንስኅ የመግባት ጉዳይ ምስጢራችን ይባክናል ብለው የማሰብ ሁኔታም እንደሚያጋጥማቸው በተደጋጋሚ ተገንዝበናል። ስለዚህ እንዲህ አይነት ችግር ያጋጠማችሁ የፕሮግራማችን አባላት ብትኖሩ በውስጥ መስመራችን እያገኛችሁን በእኛ በኩል በበጎ ፈቃደኝነት በሚያገለግሉ የቤተክርስቲያን አባቶች ማንኛውንም ንስኅ መናዘዝ እንድትችሉ የመፍትሄ አቅጣጫ መንገድ የምታገኙበትን መንገድ የምንሰጣችሁ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

.ተተጨማሪ ምላሽ

የተሰጠዎትን ቀኖና በፀጋና በክርስቲያናዊ መታዘዝ ሆነው ከፈፀሙ በኋላ የሚቀጥለውን የንስኀ ህይወት የነፍስ አባትዎ ጋር ቀርበው የፈፀሙትን የንስኀ ጊዜ ቀኖና በማስረዳት በቀጣይ መናዘዝ የሚገባዎትን የንስኀ ፀፀት በማስረዳት ቀጣዩን ቀኖና መቀበል ይችላሉ። ምክንያቱም መቼም ጊዜ ለንስኀ በተዘጋጀን ቁጥር በሥጋም ሆነ በነፍስ በረከታችን እና ሰማያዊ ክብራችንን ስለሚያበዛው የምንጠቀምበት እንጂ የምንጎዳበት ህይወት ስለማይሆን፤  በአጠቃላይ ንስኀ ማድረግ  ለብዙ ነገር ጠቃሚ ነውና በዚህ አይነት ስርዓት እንዲፈፅሙ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

ጠያቂያችን ፤ ሰው በልቡ ወይም በሀሳቡ ስለሚያስበው ነገር ቢቆጠር የሰው ልጅ ከሚኖረው እድሜ እና በዘመኑ ከሚሰበስበው ገንዘብ ቁጥር በላይ ይሆናል ማለት ይቻላል። ያሰብነውንና የተመኘነውን ሁሉ እንደ ኅጢአት ቆጥሮብን ብንጠየቅበት እንኳንስ ንስኅ ገብተን እዳ በደላችንን ማካካስ ቀርቶ የአሰብነውን እንኳን ብንጠየቅ በቃል ለማስረዳት ከምናስታውሰው ይልቅ የማናስታውሰው ሃሳብና ምኞታችን ይበዛል። ከዚህ በፊትም በተለያዩ ጥያቄዎች  ብዙ ጊዜ ደጋግመን እንዳመለከትነው ሁሉ የሱን ቸርነትና የሱን ይቅር ባይነት አስበን ካልሆነ በስተቀር እኛ በማሰብ በመናገር እና በመስራትም ስለምንሰራው ኅጢአት ሁሉ በጥፋታችን መጠን እግዚአብሔር ፍርዱን ቢያፀና በህይወታችን እንኳን ሳይቀር ልንክሰው የሚቻለን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን ከደቂቃ በሚያንስ ጊዜ ውስጥ ባለን ቦታ ላይ የማይገባንን ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ በገሀዱ ዓለም ውስጥ የማይቻለውን ነገር እንደ ምኞትና እንደ ሃሳብ ልንመኝ እንችላለን። በዚሁ ሁሉ ነገር ላይ ንስኅ ለመግባት ወይም ኅጢአት ነው ብለን ለመቁጠር የማይቻል ስለሆነ ያሰቡት የእስላምም ሆነ የክርስቲያን ልጅ ሰው ሆነን በመፈጠራችን የምናይበት ዓይን ፣ የምንሰማበት ጆሮ፣ የምናስተውልበት አይምሮ እና የተፈጥሮ ስሜታዊ አካል እስካለን ድረስ እንዲህ አይነት ነገሮች ወድያው በሃሳብ ሊፈትኑን የሚችሉና የማይቋረጥ ሂደት ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ማሰብና መጨነቅ አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን ኅጢአትን አስበንና አቅደን በተግባር ላይ ልናውለው ያሰብነው ከሆነ ወይም ከዋናው አላማችን የሚያስወጣ ከተግባር ያልተናነሰ ጥፋት ሆኖ ከተገኘ ንስኅ ሊያስገባን ይችላል፤ እንጂ በአጋጣሚ ባየነውና በተመኘነው ነገር ላይ አስፈላጊ እንዳልሆነ ከተረዳንና ከአላማችን እስካልወጣን ድረስ ውስጣችንም ስለሚፀፀትበት ወደ ልባችን ተመልሰን የህሊና ንስኅ ስለምንገባበት ወይም እንደንስሃ ፀፀት ስለሚቆጠር እንዲህ አይነት ነገሮችን አካብደን ማየት እንደሌለብን ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። 

 ጠያቂያችን ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ የማይችሉበት በቂ የሆነ ምክን ያት ካጋጠመዎ በቤትዎ ግቢ ራሱን የቻለ ቦታ ለይተው በፊትዎት የቅዱሳት ስዕልን ወይም ቅዱስ መፅሐፍ ወይም ቅዱስ መስቀሉን በማድረግ መስገድ ይችላሉ። ምክንያቱም ከምንም በላይ የኛን ችግር እግዚአብሔር ስለሚያውቀው ነው። ነገር ግን ወደ ቤተክርስቲያን ሄደን መፀለይና መስገድ እየቻልን በስንፍና ብቻ ያለበቂ ምክንያት ሄደን የማንሰግድ ከሆነ የቤተክርስቲያን ቀኖና ስለማይፈቅድ እና በንስኅ የምናጠናቅረውን ቀኖናም ከንቱ ስለሚያደርግብን መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ወደ ቤተክርስቲያን በሄድን ቁጥር እግዚአብሔርን አግኝተን እንዳነጋገርነውና በእኛ ህይወት ላይም ሰይጣን ዘወትር የሚዘረጋውን የፈተና ወጥመድ  በጣጥሰን ለመጣል የሚያስችለን መንፈሳዊ ኃይል የምናገኝበት መንገድ ስለሆነ የሰው ልጅ ይሄንን ለማድረግ የማይችለው ከባድ የጤና ወይም የስራ ፈተና ካላጋጠመው ነው።ስለዚህ ጠያቂያችን ወደ ቤተከርስቲያን ሄዶ ቀኖናን መፈፀሙ እጅግ ተመራጭ እንደሆነ እንመክራለን።

ጠያቂያችን የግል ወሲብ ወይም ከራስ ጋር የዝሙት ሃሳብ መፈፀም ወደ ሰው የሚመጣው ግብሩን እንድንፈፅም የሰይጣን እጅ ቢኖርበትም እንኳን ነገርግን የሰው ልጅ በለበሰው ደካማ ሥጋ በዝሙት ምኞት ተቃጥሎና ራሱን መግዛት አቅቶት በፈቃደኘነት የፈጠረው እንጂ ሰይጣን እጁን አስሮ አንገቱን አንቆ ያስፈፀመው ኅጢአት አይደለም። ምክንያቱም እኛ ራሳችን በነፃነት ስለተፈጠርን ወደን ኀጢአት መስራት ወይም ወደን ፅድቅ መስራት የምንችልበት ተፈጥሯዊ እውቀት አለን። ይቺ ለኛ የተሰጠችን ነፍስ አዋቂ ስለሆነች ጽድቅ እና ኩነኔን፣ ህይወት እና ሞትን፣ ብርሃን እና ጨለማን፣ ገነት እና ሲኦልን፣ ታቦት እና ጣኦትን፣ መንግስተ ሰማያትን እና ገሃነመ እሳትን፣ እግዚአብሔርን እና ሰይጣንን (ቤልሆር) ለይተን ለማወቅ እና ለማስተዋል ታስችለናለች። ግብረ ዓኦና የሚፈፅም ሰው ኅጢአቱን መተው የማይችልበት ዋናው ምክንያት የሰይጣን ግፊት ቢኖርበትም እንኳን ኀጢአቱን እንደጥቅም ወስዶ ሥጋውን ማርኪያ አድርጎ ስለሚፈልገው ብቻ ነው። ባጠቃላይ መተው የማይችልበት ዋናው  ምክንያት የሱ የራሱ ተፅኖ ፈጣሪነት ብቻ ነው።  ስለዚህ፤ ጠያቂያችን አዎ መተው ይቻላል። እኛ ራሳችን ከዚህ ኅጢአት ነፃ ለመሆን በቁርጠኝነት ከተነሳን የሰይጣንን ፈተና እና የራሳችንን የሥጋ ምኞታችንን ሁሉ ማቋረጥ የሚያስችል መንፈሳዊ ፀጋ አለን። ስለዚህ ከዚህ ፈተና እንዴት መላቀቅ እንደምንችል ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንደገለፅነው መፆም፣ መፀለይ፣ መስገድ፣ አባቶችን በማነጋገር ንስኅ መግባት፣ መጠመቅ ወደ ቤተክርስቲያን እየሄዱ እግዚአብሔርን ዘወትር መማፀን፣ በእመቤታችን እና በቅዱሳን  ስም ከዚህ ኅጢአት ለመላቀቅ ቃል ኪዳን መግባት ፣ ሁሌ ከዚህ ክፉ ሃሳብ መለየት እንዲችሉ ይህ የኀጢአት ሃሳብ ወደ እርስዎ እየመጣ በተዋጋዎት ቁጥር ፀሎት ማድረግና የእግዚአብሔርን ስም የእናታችንን የድንግል ማርያምን ስም የቅዱሳን መላዕክትን ስምና የቅዱሳን ፃድቃን ሰማእታትን ስም በመጥራት ወድያውኑ ሰይጣን አይምሮዎት ላይ የፈጠረውን ክፉ ምኞት ለመቃወም ከእርስዎ ማራቅ መቻል አለብዎት። እነዚህን የሚመሳስሉ መንፈሳዊ ተግባራትን የምናከናውን ከሆነ እርኩስ መንፈስ ከኛ ለቆ (ተለይቶ) ስለሚሄድ ያኔ ይሄን ኅጢአት ልንጠየፈው እንደምንችል አይጠራጠሩ። ስለዚህ ጠያቂያችን ይህን ተረድተው መልዕክታችንን በስራ ላይ እንዲያውሉ እየመከርን፤ ተከታታይ የሆነ ምክር እና ትምህርት ካስፈለገዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

 ህልመ ሌሊት በህልም መልክ ወደ ሰው ልጅ የሚመጣ መንፈሳዊ ውግያ ስለሆነ በጊዜውም ያለጊዜውም ጠላታችን ዲያብሎስ እኛን በኅጢአት ጠልፎ ለመጣል የማይቆፍረው ጉድጓድ የለውምና እንኳን በህልም ቀርቶ በገሀድም ቢመጣ ጠላት ያው ጠላት ስለሆነ፤ ከጠላት ደግሞ መልካም ነገር ስለማይጠበቅ በተለይም በመንፈሳዊ ህይወታችን ስንኖር በረቂቅ ምስጢር የሚወጋንን ሰይጣን ታግለን ድል መንሳት የምንችለው ዘወትር በፀሎት፣ በፆም እና በስግደት ተወስነን በምንከፍለው ክርስቲያናዊ ተጋድሎ ነው። 

እንግዲህ ጠያቂያችን እንዳሉት በህልመ ሌሊት የዝሙት ሀሳብ ይዞ የሚታገለን ክፉ መንፈስ ዋና መነሻው የእኛን ደካማ ሃሳበችንን፣ የአመለካከት ዝንባሌያችንን፣ ወይም ምኞታችንን ምክንያት በማድረግ ስለሆነ ሁሌ የሚታገለንን የኅጢአት ሃሳብ ከእኛ አውጥተን ለመጣል እንችል ዘንድ ፦

1ኛ/ የማይቋረጥ ቋሚ የፀሎት ፕሮግራም ሊኖረን ይገባል።

በ2ኛ/ ደረጃ ስለ ሃይማኖታችን የሚመክሩንን የሚያስተምሩንን ሃይማኖታዊ ስርዓት በተግባር መፈፀም አለብን።

በ3ኛ/ ደረጃ በፀበሉ ፣ በቅዱስ መስቀሉና፣ በእምነቱ ከአጋንንት ውጊያ ለመዳን እንደምንችል ተረድተን አስፈላገውን አገልግሎት ማግኘት አለብን።

4ኛ/ በህልመ ሌሊት የሚመጣው የሰይጣን ውግያ በኛ የግል ህይወት አንፃር በምን ምክንያት እንደሚዋጋን በከታታይ ከሚያጋጥመን ፈተና አንፃር መንስኤውን ለይተን ማወቅና ይሄንኑ ያጋጠመንን ፈተና ለመንፈሳዊ አባታችን ወይም ንስኅ አባታችን በግልጽ በማስረዳት አስፈላጊውን ምክርና መንፈሳዊ አገልግሎት ማግኘት አለብን።

 

በአጠቃላይ እነዚህን ምክረ ሃሳቦች በስራ ላይ እንዲያውሏቸው እየመከርን ተጨማሪ ምክርና ማብራሪያ ካስፈለገ በውስጥ መስመር ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን።

 ጠያቂያችን፤ በእርስዎ በኩል የቀረበው ጥያቄ ከዚህ በፊትም እንደገለፅነው ከራስ ጋር የዝሙት ሃሳብ ለመፈፀም ተነሳስተው በሃሳብና በምኞት ራሳቸውን በሰይጣናዊ ስራ ተገዚ የማድረጉ ተግባር ብዙ ወገኖቻችን እየተፈተኑበት ያለ ጉዳይ ነው። ማንኛውም ሰው በራሱ ፈቃድ እሚጎዳውን ለማድረግ የሚስማማ እንዳልሆነ ይታወቃል። ምክንያቱም ከህይወት ይልቅ ሞትን፣ ከፅድቅ ይልቅ ኅጢአትን ወይም ኩነኔን የሚመርጥ ሰው አይኖርምና። ስለዚህ በእርስዎም በኩል የቀረበልን ጥያቄ በዘመናችን ወቅታዊ የሆነ ብዙ ሰዎችን እየተዋጋ ያለው ኅጢአት አይነት አለምንም ሁሉ አንድ ለማድረግ በምድር ላይ ሰልጥኖ በከፍተኛ ደረጃ የሰውን ልጅ ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣት እየታገለ ያለበት ከተፈጥሮአዊ ስርአት ውጭ የሆነ ከፍተኛ የኅጢአት አይነት ወይም ደግሞ ግብረሰዶማዊነት እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። ይህ ደግሞ ከዚህ በፊትም እንደገለፅነው ከኅጢአት ሁሉ የከፋ ከባድ ውድቀት እንደሆነ በቅዱስ መፅሐፍም አስተምሮ አለምን ለጥፋት ያበቃ የኅጢአት አይነት እንደሆነ መረዳት አለብን። ይሁን እንጂ ብዙዎች የሚፈተኑበት ሴጣናዊ ሃሳብ ቢሆንም እንኳን የታመመ ሁሉ እንደማይሞት ኅጢአተኛ ሁሉ እንደማይኮነን የወደቀ ሁሉ እንደማይሰበር ሁሉ ፥ ምንም እንኳን በዚህ የኅጢአት አይነት መውደቅ  ከባድ ፈተና እንደሆነ ቢታወቅም እንኳን ልክ እንደ እርስዎ አይነት የንስኅን ፀሎት የሚሰማው፤ ክርስቲያን በነፍሱ ላይ ያጋጠውን የኅጢአት እድፍ በንስኅ ህይወት ታጥቦ ለመፅዳት እስከተዘጋጀ ድረስ ስለወዳጆቹ ወይም ስለልጆቹ አንድ ቀንም ያማይጨክነው…… የርህራሄና የምህረት አምላክ እግዚአብሔር በደላችንን ሁሉ ዘወትር ይቅር ማለት የተለመደ የባህሪ ሥራው ስለሆነ እርስዎም በዚህ አይነት አቀራረብ ስለፈፀሙት የኅጢአት ስራ በመፀፀት ለንስኅ የተዘጋጀ ህሊና ስላለዎት በእርግጠኝነት በዚህ አይነት ፈተና የሚቃወምዎትን ጠላት እንደሚያሸንፉት አይጠራጠሩ።     

በእርስዎም በኩል እንደገለፁት ሁሉ ፈተናውን ለመቋቋም እያደረጉት ያለው መንፈሳዊ ተጋድሎ እጅግ መልካም ነው። የንስኅ አባትዎ ይህንን ፈተና በንስኅ ህይወትና መንፈሳዊ ተጋድሎ ለማስወገድ ቀርበው ባስረዷቸውጊዜ ነገሩን እንደቀላል ቆጥረውት ከሆነ እንዲህ አይነት ሃላፊነት የጎደለው አባትነት ለጠላት ዲያብሎስ አሳልፎ የሚሰጥ ስለሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትጉህና ለመንፈሳዊ ልጆቹ (ለመንጋው ጥበቃ) የማያንቀላፋና ዘወትር ቁጥጥር እና ክትትል የሚያደርግ አባት መያዝ እንደሚባዎት እንመክራለን። 

በሁለተኛ ደረጃ  ከዚህ ከገቡበት ፈተና ለመውጣት  ይችሉ ዘንድ እርስዎ ከዘረዘሯቸው በተጨማሪ  ፦

1ኛ/  እርስዎ እንደገለጹት ዘወትር ሳያቋርጡ የሚፀልዩት የግል ፀሎት መኖር አለበት። ምን መፀለይ እንዳለብዎት እኛንም በውስጥ መስመር ቢያነጋግሩን ልንመክርዎት እንችላለን።

2ኛ/  ምንም እንኳን በግል ህይወትዎ ወይም በስራ አጋጣሚ ወይም በቤተሰብ ሁኔታ ጊዜ ባይኖርዎትም፥ እንደምንም ታግለውም ቢሆን እንኳን ለ አንድ ሱባኤ የተለየ የንስኅ ፕሮግራም ይዘው እየተጠመቁና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት እያገኙ ቢቆዩ

3ኛ/ ይሄንን ፈተና ፈፅሞ መተው ይችሉ ዘንድ ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርት እና ምክር እንድንሰጥዎ አሁንም በውስጥ መስመር እያገኙን ቢከታተሉ፤

4ኛ ሁሌ ከዚህ ክፉ ሃሳብ መለየት እንዲችሉ ይህ የኅጢአት ሃሳብ ወደ እርስዎ እየመጣ በተዋጋዎት ቁጥር የእግዚአብሔርን ስም፣ የእናታችንን የድንግል ማርያምን ስም፣ የቅዱሳን መላዕክትን ስም እና የቅዱሳን ፃድቃን ሰማእታትን ስም በመጥራት ወዲያውኑ ሰይጣን በአይምሮዎት ላይ የፈጠረውን ክፉ ምኞት ለመቃወምና ከእርስዎ ለማራቅ መቻል አለብዎት።

 

በአጠቃላይ በዚህ ዓለም ውስጥ በክርስትና መታመን ውስጥ ስንኖር ውግያው ከሥጋዊና ከደማዊ ጠላት ጋር ሳይሆን ረቂቅ ከሆነው ከሰይጣን ጋር ስለሆነ በተለያዩ ረቂቅ ስልት የመታገሉ ሁኔታ ከዚህ ዓለም እስከምንለይ የሚቀጥል ስለሆነ በንስኅ በመፀፀት እርኩስ መንፈስ ጋር እየታገሉ ሳይሸንፉና ሳይማረኩ መኖር ፀጋና ክብር ስለሚያሰጥ ጠየቃያችን በዚህ አንፃር ንስኅ ገብተው ዳግም በኅጢአቱ ወድቀው እግዚአብሔርን ለላለማሳዘን አጥብቀው ፈጣሪን በፀሎት በመጠየቅ ህይወትዎን እንደመመሩ ተስፋ በማድረግ መንፈሳዊ ህይወትዎንም ይበልጥ በማጠናከር ተስፋ ሳይቆርጡ ይቀጥሉ ዘንድ ይሄንን ትምህርታዊ መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል። ከላይ እንደገለፅነው ለ መንፈሳዊ አባትነት ትምህርት እና ተጨማሪ ማብራሪያ በውስጥ መስመር በላክንልዎ ስልክ ደውለው ሊያገኙን ይችላሉ።

መልስ፦ ጠያቂያችን ፤ ስለሰጠነዎት መልስ አመስግነው ወደፊት በፀሎት እንድናስብዎ የላኩት ማሳሰብያ ደርሶናል። እርስዎም በላክንልዎት መንፈሳዊ ምክር ተጠቃሚ በመሆኖት እኛም ደስ ብሎናል። በመንፈሳዊ ህይወትዎ ከዚህም በላይ እንድናገለግልዎ እንዳሉትም ወደፊት ለጥያቄዎ መልስ እና መንፈሳዊ ምክር አገልግሎት በሚያስፈልግዎት ጊዜ ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን። በጸሎት እግዚአብሔር ቢረዳን እንድናስብዎ የክርስትና ስምዎን በውስጥ መስመር ይላኩልን።

ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ (አማኝ) የሆነ ክርስቲያን ለአካለ መጠን ከደረሰበት ግዜ ጀምሮ የንስሐ አባት መያዝ ክርስትያናዊ ግዴታው እንደሆነ በቤተክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን ኑሮዋቸውን ለማሸነፍና የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ሲሉ ጠያቂያችን እንዳሉትም ቤተክርስቲያንና ካህናት አባቶች ወደማይገኙበት ክፍለ ዓለም እና አካባቢ በልዩ ልዩ ምክንያት ተበትነው እንደሚኖሩ ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ አገራችን ሳይቀር በረሃማና ጠረፋማ በሆነ አካባቢ እንዲሁም አህዛብ በሚበዙበት ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በመከራና በፈተና ግዜ የሚያጽናናቸውና የሚመክራቸው አባት ሊያገኙ አይችሉም። የሚጸልዩበት እና ፈጣሪያቸውን የሚማፀኑበት ቤተክርስትያንም አያገኙም።

ስለዚህ በቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ሰውን በነፍስ የማዳን ሥራ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። 

ስለዚህ ቤተክርስቲያንና አባቶች ካህናት በቅርብ የማይገኙበት ክፍለ ዓለም ወይም አካበቢ የሚኖሩ የንስሐ አባት ለመያዝ ቢፈልጉ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የኛን የውስጥ ችግር ያውቀዋልና አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ያለ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌለበት የንስሐ አባት እንዲኖረው በሃይማኖቱና በመንፈሳዊ ህይወቱ የመረጠውን ካህን የቦታ እርቀት ሳይገድበው መያዝ ይችላል። ካለው ችግር አንፃርም በስልክ እና በሌላ መልእክት በመገናኘት መንፈሳዊ ትምህርት እና ከንስሐ አባት የሚሰጠውን የንስሃ ቀኖና  መቀበል ይችላል። ማንኛውንም በጎ ስራ ሁሉ አባቱ የሚመክሩትን እና የሚያዙትን ሁሉ በመፈፀም የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ስለሚችል የግድ በአካል ካላገኘኋቸው አብሬ በአንድ አጥቢያ ካልኖርኩኝ የንስሐ አባት መያዝ አልችልም በሚል ምክንያት ያለጠባቂ መኖር የለበትም። 

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስለ ንስኀ ህይወት አስፈላጊነትና ንስኀ ለመግባት የንስኀ አባት ሊኖረን እንደሚገባን እና በቦታ ርቀት የንስኀ አባት ካህን ብናጣ እንኳን አባቶችን ባሉበት ቦታ መርጠን በመያዝ በስልክም ሆነ ወይም በጽሑፍ መልዕክት ብቻ ለመገናኘት ለእኛ አመቺና የተሻለ በሆነ መስመር ተጠቅመን ከንስኀ አባታችን የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ትምህርት ማግኘት፣ ንስኀ መግባት፣ ልዩ ልዩ የትሩፋት ሥራ መስራት ፣ በአጠቃላይ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ፀንተን ለመኖር እንደምንችል በስፋት መልዕክት እንዳስተላለፍን እናስታውሳለን።

በተጨማሪም ይህን በሚመለከት ከዚህ በፊት ስለ ንስሐ አባት አያያዝ ጥያቄ ቀርቦ በአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እና በቤተክርስትያን መምህራን ንስሐ አባት በርቀት መያዝ እንደሚቻል በተደጋጋሚ ምላሽ የተሰጠበት ሃሳብ ስለሆነ ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲያሥሩና እንዲፈቱ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ጊዜና የቦታ ርቀት የማይወስነው ስለሆነ ፤ በአካባቢው አባት የሚሆን ካህን ከጠፋ ያለጠባቂ ብንኖር ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍሳችንን እንዳይነጥቃት የንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ምእመናን መጨናነቅ እንደማያስፈልጋችሁ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።

በመሆኑም ጠያቂያችን ንስኀ አባት አሁን ባሉበት አገር ወይም አካባቢ ከሚገኙት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህናት ካሉ መርጠውና አጥንተው  የንስኀ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ። እንዳሉትም ይህን ለማድረግ የማይችሉበት ምክንያት ካለ ፤ አገር ቤት ካሉት አባት ጋር ተነጋግረው ወይም በቅርበት በሚያውቁት ሰው በኩል የተመሰከረላቸውን  እውነተኛ እና ለህይወታችን መድኃኒት ሊሰጡ የሚችልሉ አባትን አግኝቶ የዘላለም ሕይወት እንወርስ ዘንድ የሚያስችለንን የፅድቅ መንገድ እንዲመሩን የሚያድረጉ ትጉህ አባት ይዘው ከላይ እንደገለጽነው በስልክ ወይም በፅሁፍ መልዕክት ንስኀ መቀበል ይችላሉ።

ይህን ለማድረግ ካልቻሉ ደግሞ በዚህ ዮሐንስ ንስሓ ድረ ገፅ  ብዙዎችን በነፍስ እንዳይጠፋ ለማትረፍ እግዚአብሔር የፈቀደውን ያህል የበኩላችንን ጥረት እያደረግን መሆኑን በመረዳት ለአባትነት የመረጥናቸው የቤተክርስቲያን አባቶች በሃይማኖታቸውና በእውቀታቸው የታመነባቸው ስላሉ በውስጥ መስመር በላክንልዎት ስልክ ቁጥር ቢደውሉ  በእኛ በኩል የንስሓ አባት እንዲይዙ ልንረዳዎት እንችላለን።  ምክንያቱም የዚህ ድረገፅ ዋና አላማ የንስሓ ህይወትን ለማሳደግ የምክር እና የትምህርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በተለያየ የአለም ወጥመድ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በመንፈሳዊ ትምህርት በማነቃቃት በቅርብ ሆነው በጠዋት በማታ ምክር እና ተግሳፅ እየሰጡ የሚያገለግሉ አባቶች ጋር ማገናኘት ዋናው ቅድሚያ የምንሰጠው አገልግሎት በመሆኑ ነው።

ለሁሉም የእግዚአብሔር ፀጋና ፍቅር ባሉበት ቦታ ይብዛልዎት

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ ላይ ያገኛሉ

አንድ ከርስቲያን ንስሓ ገብቶ የተሰጠውን ቀኖና ከጨረሰ በኋላ፤ ጊዜ ካለው በአካል፣ ጊዜ ከሌለው ደግሞ በስልክ ወይም በሌላ መገናኛ መንገድ የተሰጠኝን ትእዛዝ ፈጽሜያለሁ ብሎ ሊነግራቸው ይችላል። ይህን ለማድረግ ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ቢያጋጥመው ግን ፤ ለሰራው ኀጢአት ካሳ ስለከፈለ፣ ከታሰረበትም የኅጢአት ማሰሪያ ስለተፈታ ለፈጣሪው በምስጢር ነግሮ ከዛ በኋላ ከመንፈሳዊ ነገር ላለመራቅ መትጋት አንጂ ወደ አባቴ ተመልሼ ይፍቱኝ ብዬ ስላልተናገርኩኝ ወይም እግዚአብሔር  ይፍታህ ሰላላሉኝ ጥፋት ሊሆንብኝ ይችል ይሆን በማለት ሊያሳስብዎት አይገባም። ቀኖናዎን ጨርሰው በዋናነት ወደንስሃ አባትዎ ወይም ንስሐ ወደተቀበሉበት ካህን መሄድ የሚኖርብዎ ካህናት አባቶች የነፍሳችን እረኛ ሆነው በነፍስ ጉዳይ ላይ በሃላፊነት እግዚአብሔር ስለሾማቸው ሁልግዜም ቢሆን ከአባቶች ምክርና ተግሳጽ ላለመራቅ ነው እንጂ ቀደም ሲል ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያት ይፍቱኝ ለማለት አለመሄድዎን እንደጥፋት ቆጥረው  እንደገና ንስሐ እንዲገቡበት አያስፈልግዎትም ወይም ጥፋት ሆነብኝ  በማለት መጨነቅ እንደሌለብዎ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን። (ማቴ18፤18) ዩሐ(20፤21-23) ዩሐ (21፤15-18) ምክንያቱም በኅጥያት እድፍ የቆሸሸውን ህይወትዎን ከካህኑ በተቀበሉት የንስሐ ውሃ ታጥበው ከኅጥያት እድፍ ፀድተዋልና። ዳግም እንዳይበድሉ፣ ኅጥያት ሰርተውም የቅድስና ሕይወትዎን እንዳያቆሽሸው፣ በየጊዜው ከቤተ ክርስቲያን መምህራንና የንስሐ አባቶች ትምህርትና ተግሳጽ እያገኙ ምንም እንኳን የኑሮ ፈተና ቢበዛብዎ ከእናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳይርቁ እየፆሙና እየፀለዩ ከገንዘብዎ፣ ከእውቀትዎ እና ከጉልበትዎም አስራት በኩራት እያወጡ በጎ ስራ በመስራት ከሰይጣን ወጥመድ ለማምለጥ የሚችሉበትን መንፈሳዊ ፀጋዎትን በተቻለ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለብዎ እመክራለው። ለዚህም ዋናውና መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ክርስቲያን ያለጠባቂና ያለመካሪ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌበት  ወደ ንስሐ አባትዎ (ካህን) መሄድ ያለብዎ ለዚህም ነው ፥ በየጊዜው የእለት እለት ህይወትዎን በካህኑ ምክር እንዲመራ ለማድረግ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ ሃሳብ እንዲረዱትና ከንስኀዎ በኋላም  በዋናነት ከላይ የዘረዘርናቸውን በመፈጸም፥ ከንስኀ አባትዎ ጋር ግን በቅርበት በየጊዜው መገናኘትና ንስኀ፣ ምክር እና ትምህርት መቀበል አለብዎ በማለት ይህ አጭር መልዕክት እንዲደርስዎት አድርገናል።
 
በቅዱስ መፅሐፍ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ ሳይሆን ከአፍ የሚወጣ ነው ተብሎ እንደተፃፈ፥ በማያገባን እና በማይመለከተን ነገር ውስጥ ብዙ መናገር ተገቢና አግባብ አይደለም። እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ከሌላ እኛን ከሚመስል በአርአያ ሥለሴ የተፈጠረ ከማንኛውም ሰው የስድብ ሃይለቃል ቢሰነዘርብን እንኳን ሳይቀር በትዕግስት እና ክርስቲያናዊ ስነ ምግባር ባለው አነጋገር ፣ ቁጣን ሊያበርድ የሚችል፣ እና ሌሎችንም በስነምግባር አርዓያ ሊሆን በሚችል አነጋገር መመለስ ሲገባን በሥጋዊ ስሜታችን ተነሳስተን ሰው የሚያሳዝን ስድብ ወይም ፅርፈት ቃል መናገር ፈፅሞ ከእውነተኛ ክርስቲያን አይጠበቅም። ወንድሙን ጨርቃም ብሎ የሚሳደብ ሁሉ ፍርድ እንደሚጠብቀው ተፅፏል። ከአንደበት ክፉ ነገር አይውጣ ተብሎም ተፅፏል።
 
በእርግጥ እርስዎም በምን ምክንያትና ምን የሚል የስድብ ቃል እንደፃፉም ሆነ እንደተናገሩ ዝርዝር ጉዳዩን ስላልገለፁልን የጥፋቱን መጠን መናገር ባያስችለንም፥ በጥቅሉ ግን የሰውን መንፈሳዊ ህይወት ከሚያረክሱ ጉዳዮች ከአንድ ክርስቲያን በማይጠበቅ አነጋገር የሌላውን ክብር ሊያንቋሽሽ የሚችል የስድብ ቃል መናገር እንደማይገባ እንመክራለን።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን ወደ መምህረ ንስኀዎ በመሄድ ኀጢአቱን በዝርዝር መናገር ይገባዎታል። በአንቀፀ ንስኀ በጥፋቱ መጠን እና አይነት በዝርዝር የተቀመጠ ስለሆነ፥ ካህኑ እርስዎ ያጠፋተትን የጥፋት መጠን በዚህ አንጻር ተመልክተው  የንስኀ ቀኖና የሚሰጡዎት ይሆናል። ከዚህ በፊት ንስኀ ገብቻለሁ ያሉት በዚሁ ጉዳይ ከሆነና በትክክለኛ መንገድ ከነበረ ንስኀ የገቡትና ቀኖናዎትን የፈፀሙት ዳግመኛ ለ2ኛ ጊዜ ንስኀ መግባት አየጠበቅብዎትም። ነገር ግን የንስኀ ቀኖና የተቀበሉት አለጸጸት እንደው ለይስሙላና የካህኑን ትዝዛዝ ለመፈፀም ብቻ ከሆነ ግን ሺ ጊዜ ንስኀ ገባን ብንል ይህ አይነት የንስኀ ህይወት እግዚአብሔርን እንደማታለል ነውና፤ አሁንም የምንመክርዎት ከህሊና ዕዳ ነፃ እንዲሆኑ ደግመው ከልብ በሆነ ፀፀት ውስጥ ሆነው ወደ ካህን በመቅረብ በዝርዝር ተናግረው በድጋሚ ንስኀ ሊቀበሉ ይገባል። ምናልባት ከዚህ ውጪ አኛ ያልተረዳነው ወይም ያልገለፅንልዎ ሃሳብ ካለና ተጨማሪ ምክርና መንፈሳዊ አገልግሎት ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ። 
ጠያቂያችን በመጀመሪያ ሱባኤ ለመያዝ የፈለጉት ለምንድን ነው የሚለውን እና እንዴት መያዝ እንዳለብዎት ከንስኀ አባት ጋር መመካከር አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ተገቢውን መንገድና ስርዓት በአግባቡ ካላወቅን  አንዳንዴ ሰይጣን ለመጥፎ ነገር አሳልፎ ይሰጠናል አስቀድመን ሱባኤ ስንገባ ማድረግ ያሉብንን ነገሮች ማወቅ ተገቢ ነው።  የሱባኤም ቦታ ውሱን ነው። ወደ ገዳማት ለየት ወዳለ መንፈሳዊ  ቦታ ነው ሱባኤ የሚያዘው እንጂ ዝም ብሎ ቤት ተቀምጦ ሱባኤ አይባልም። በቀን አንዴ ጭብጥ ጥሬ እየተበላ ።፣ አንድ ብርጭቆ ውሀ እየተጠጣ፣ ከ500 ፣ 600 በላይ ስግደት እየተሰገደ፣ በሰባቱም የፀሎት ጊዜያት እንደውም ከዚያም በላይ እየፈፀመ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርበት ጊዜ ነው እንጂ ዝም ብሎ ሱባኤ አይደለም። ሱባኤ ከአለማዊ ሃሳብ አይምሮን መዝጋት ነው ፥ ቤት መዝጋት አይደለም። መጀመሪያ ቀዳሚው ነገር አይንን ከመጥፎ ነገር ልቦናን ከመጥፎ ነገር እጅ እግርን ከመጥፎ ነገር መቆጠብ ነው። እርስወዎም እንደገለጹልን ሱባኤ እንደሚገቡ ለንስኀ አባትዎ መንገርዎ መልካም አድርገዋል። ስለዚህ ካህን ግባ ካለ ያን ተግባራወዊ ማድረግ መቻል አለብን አትግባ ካለንም እንደዚያው የካህኑን ትእዛዝ እንፈጽማለን። አለበለዚያ አንዳንዴ አውቃለሁ ቀድማለሁ ከካህን ማለት የሆናል።
 
ወደጥያቄዎት ሃሳብ ስንመጣ ፤ የንስኀ አባትዎ እንዳሉት ወደ ሱባኤ ገዳምም ሆነ እርስዎ ወደመረጡት የሱባኤ ቦታ በመሄድ በግልዎት ወይም በፈቃደኝነት ከሚይዙት ሱባኤ በንስኀ አባትዎ የተቀበሉትን የንስኀ ቀኖና አብረው መፈፀም ይችላሉ። ምንም አይነት ልዩነትም ሆነ ችግር የለውም። እንዲያውም በፀጋ ላይ ፀጋ በክብር ላይ ክብር ይጨምርልዎታል። ስለዚህ ጠያቂያችን ከዚህ የተለየ ሃሳብ ከሌለዎት በስተቀር የንስኀ አባትዎ በነገሩዎት መሰረት ንስኀውን ከሱባኤው ጋር መፈፀም እንደሚችሉ ገልፀን ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት  አንድ ሰው ሱባኤ ከመግባቱ በፊት እና ሱባኤ ከገባ በሗላ ምን ምን ነገሮች ሊያሟላ ይችላል ?? በሚል ተጠይቀን ያስተላለፍነውን ማብራሪያ እንደሚከተለው ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት። 
 
 ከሁሉ በፊት ስለ ስባኤ መረዳት ያለብን ምስጢራዊ ትርጒሙንና በሱባኤ ስለሚገኝበት መንፈሳዊ ጥቅም ነው።  ሱባኤ ማለት በግዕዝ  ቋንቋ 7 ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ይህ 7 ቁጥር ደግሞ የአንድ ሱባኤ ጊዜ ማለት ነው። 7 ቁጥር በዕብራዊያን ዘንድ ፍጹም ቁጥር ነው። የቃሉ ምስጢራዊ ትንታኔ ይህ ከሆነ፤ ሱባኤ የተጀመረው በአባታችን በአዳም ነው።  አባታችን አዳም  7  አመት ከ1ወር ከ 17 ቀን በገነት ውስጥ በደስታ ከኖረ በኋላ አታድርግ የተባለውን ትዕዛዝ በማድረጉና አትብላ የተባለውን ዕፀበለስ በመብላቱ ከገነት ርስቱ መባረሩ ምክንያት ስለ ስራው በደል ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው በማልቀሱና በመጮሁ ምክንያት ከፈጣሪው ዘንድ  ይቅርታን ያገኝ ዘንድ 5 ሱባኤ ማለትም 35 ቀናትን በሱባኤ ተወስኖ ወደፈጣሪው ያቀረበው ልመና ተቀባይነት አግኝቶ ከፈጣሪው ዘንድ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ተገብቶለታል። ስለዚህ ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ በኀጢዓትና በልዩ ልዩ ምክንያት የሱባኤ ጊዜ እየወሰኑ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ምህረትን እና ይቅርታን አግኝተውበታል። 
 
ሱባኤ የሚገባው በ2 ምክንያት ነው:- 1ኛው ማንኛውም ክርስቲያን የኀጢአት ፈተና ደርሶበት የበደለውን በደል አስቦ በመፀፀት ከሰውና ከማህበራዊ ኑሮ ራሱን ደብቆና ሰውሮ በለቅሶ በፀሎት ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት ሂደት ነው።  2ኛው ደግሞ ማንኛውም ክርስቲያን ፀጋውን ለማሳደግና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ልዩ ልመና ሲኖረው ጊዜ ወስኖ ቦታ ለይቶ ሱባኤ ይገባል ማለት ነው። በፆም በፀሎት ተወስኖም ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል። በጠየቀውና በለመነው ፍፁም ክርስቲያናዊ ሕይወት አንፃር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለግል ህይወቱና ለቤተሰቡ፣ ለወገንና ለሀገርም የሚጠቅም በጐ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።
 
ሌላው የሱባኤ አስፈላጊነት ፤ እግዚአብሔር አምላክ ስላደረገልን ነገር ሁሉ እና ስለቸርነቱ ብዛት ምስጋና ለማቅረብ፣ ወደፊትም ጠብቆቱና መግቦቱ እንዳይለየን ለመማፀን ፣ ከእናታችን ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳን ሁሉ በረከት ለማግኘት፣ በግል ህይወትም ሆነ በሀገር ላይ ከተቃጣው መቅሰፍት ለመዳን፣ በሃይማኖትና በሥነምግባር ፀንተን በፆም በፀሎት እንድንተጋ የሚዋጋንን ጥንተ ጠላታችንን ዲያብሎስን ድል ለመንሳት፣ የተሰወረና የረቀቀ ምስጢር እንዲገለጽልን በመሳሰሉት መንፈሳዊ ጉዳዮች ሰባኤ መግባት የምንችል መሆኑን በቀኖና ቤተክርስቲያን ታዟል።
 
ሱባኤ ለመግባት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ፤ በግላችን በሰራነው በደልም ሆነ ስለሀገርና ስለወገን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት ለመጠየቅ ሱባኤ ለመግባት ባሰብን ጊዜ፦ 
 
1/   ህሊናዊና አካላዊ ቁርጠኝነትና ስነልቦናዊ ውሳኔን ይጠይቃል። 
 
2/  ሱባኤ የምንገባበት ምክንያት እንዴትና ለምን እንደሆነ ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር መነጋገርና ምክር መቀበል ያስፈልጋል።
 
3/  በሱባኤ የምንቆይበት ጊዜ ምን ያህል ሰባኤ እንደሆነ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ፣ እና የሱባኤውን ቦታ (በአትን) መወስን ያስፈልጋል። 
 
4/   በሱባኤ ጊዜ የምናደርጋቸውን መንፈሳዊ ስርዓት ማለትም እንዴት እንደምንፆም ፣ እንዴት እንደምንፀልይ፣ እንዴት እንደምንሰግድና በመሳሰሉት በስርዓተ ቀኖና መሰረት መንፈሳዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል። 
 
5/    ሱባኤ በገባን ጊዜ በግል ህይወትና በቤተሰብ ጉዳይ ወይም በማህበራዊ ጉዳይ የሚያሰናክል ፈተና እንዳይመጣብን አስቀድመን ሁኔታዎችን ማስተካከል ያስፈልጋል።
 
6/   ሱባኤ በገባን ጊዜም እንዴት መተኛት እንዳለብን ምን መልበስ እንዳለብን ባጠቃላይ በሱባኤ የምናሳልፍበት ጊዜያችን የሚያስፈልገንን እና የማያስፈልገንን ነገር ለይተን ለማወቅ ከቤተክርስቲያን አባቶች መመሪያ መቀበል አለብን። 
 
ይህን ሁሉና የመሳሰሉትን ሱባኤ ከመግባ በፊት ልናሰባቸውና በሱባኤ ወቅት ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ናቸው። 
 
ሱባኤ ከጨረስን በኋላ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ደግሞ፦
 
1/   ሱባኤ የገባንበት ምክንያት ኀጢአት ከሆነ ደግመን ላለማድረግ በተቻለ መጠን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳችንን ለበለጠ የሃይማኖት ፅናት ማትጋት ነው። 
 
2/ ሱባኤ በገባንበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ያገኘነው በጎ ምላሽ ካለም የበለጠ የእግዚአብሔር ፀጋ እንዲበዛልን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ነው።
 
3/   ማንኛውም ክርስቲያን ቦታና ጊዜ ላይቶ በሱባኤ ፈጣሪውን የሚለምን ከሆነ በፀጋ እያደገ ከመጣ ብዙ ጊዜ ለውድቀት ከሚያበቁት የኀጢአት ምክንያቶች መራቅ።
 
4/   በፆም በፀሎት በቅዱስ ቁርባን በአጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስነምግባር መንፈሳዊ ጉዞን መቀጠል።
 
5/   ሥጋዊ ፍላጎትን እና ምኞትን ገዝቶ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝቶ የትሩፋት ሥራ መስራት። 
 
6/  በአጠቃላይ አለማዊ ሰዎች ከሚሰሯቸው ስራዎች ሁሉ እርቆ በመንፈሳዊ አላማ ፀንቶ መኖርን ይጠይቃል። 
 
እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ምክር የሚሰጠው በአለም እየኖሩ በሱባኤ እግዚአብሔርን ለሚለምኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንጂ ለገዳማውያን ወይም በምናኔ ለሚኖሩ መነኮሳት አይደለም፤ የነሱ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ቀኖናዊ ስርዓት ስላላቸው ነው።
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም፤ ስለ ሱባኤ መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ በዚህች አጭር ፅሁፍ መልዕክት የላክንላችሁ ሲሆን፤ አስፈላጊ ሆኖ ስናገኘው ወደፊት ስለ ሱባኤ አስፈላጊነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ ትምህርት በስፋት  እንዲደርሳችሁ ልናደርግ እንችላለን። 
 
ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ተረድተው ፤ ለሱባኤ ወደ ገዳም ለመሄድ ያሰቡትን መንፈሳዊ አላማ በሰላም ፈፀመው የእግዚአብሔርንም በረከት አግኝተው እንዲመለሱ እየተመኘን፤  በገዳም በፍጹም እምነት ሆነው እንዲጸልዩና ለረዥም ጊዜ በቦታው የቆዩ የእግዚአብሔር ፀጋ አብዝቶ ያደረባቸው አባቶች ስለሚኖሩ ወደነርሱ ቀርበው ትምህርትና ምክር ማግኘት እንዳለብዎምእንመክራለን። 
 
ጠያቂያችን ኅጢአትን ለመናዘዝ ቅድሚያ መስጠትና፣ ንስሐ ለመግባት መዘጋጀትና በንስሐ ሕይወት ራስን አዘጋጅቶ መጠበቅ ከእውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ ታማኝነት ስለሆነ ፥ የእርስዎን ቁርጠኝነትም ከጥያቄዎ አገላለጽ ተረድተነዋልና እጅግ እናደንቃለን። ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን ንስሓ ለመግባት ሲዘጋጅ ኀጢአቱን ማመኑን፣ መፀፀቱን፣ ወደ እግዚአብሔር መመለሱን፣ ክፉ ፀባዩን ለመተው መወሰኑን የምናውቅበት መንገድ ነው። የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ሚልክያስ እንደተናገረው  “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከስርአቴ ፈቀቅ ብላችኋል። ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሣለሁ” በማለት ከእግዚአብሔር ሕግ በመተላለፍና ትእዛዙን በማፍረስ ለበደሉት ሰወች የንስሓ ጥሪ እንዳቀረበላቸው እንመለከታለን።(ሚል 3፥7)
 
ስለዚህ ጠያቂያችን በአላማዎ ጸንተው በንስኀ ህይወት እንዲኖሩ የሚያግዝዎትን ይህን አጭር ትምህርታዊ ማብራሪያ ልከንልዎታልና ይመልከቱት።
 
ንስኀ፦ ንስኀ በሚቀበለው ክርስቲያን እና ንስኀ በሚሰጠው አባት መካከል የሚፈፀመው አገልግሎት የሚታይ መንፈሳዊ ስርአት ሲሆን በዚህ መታዘዝ ውስጥ እግዚአብሔር በረቂቅ መለኮታዊ ጥበቡ በካሕኑ ላይ አድሮ በፍጹም እምነት ኀጢአቴ  ይፋቅልኛል ብሎ ከልብ በመታዘዝ ለንስሓ ህይወት የቀረበውም ምእመን ያለምንም ጥርጣሬ ኀጢአቱ ይቅር ይባላል።
 
ኅጢአት ለመናዘዝና ንስሐ ለመግባት ከሚፈልግ አንድ ክርስቲያን የሚጠበቀው ፡-
 
– በቅድሚያ ኅጢአት መሥራቱን አምኖ ለራሱ ሕሊና መናዘዝ (መፀፀት)። ስለሠራው ኅጢአት ወይም በደል እየተጸጸተ ጧት ማታ በደሉን በፀሎትና በልመና ለፈጣሪው መናዘዝና ኅጢአትን በእግዚአብሔር ፊት ማመን (መዝ50 ፣ ዳን9፥5፣ ነህ1፥6-7)
 
– ኅጢአትን (በደልን) ለካህን መናዘዝና ንስኀ መግባት። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይና እንደራሴ ስለሆነ የሠራነውን ኅጢአት ለካህኑ በመናዘዝ ንስሐ መግባት፤ ኅጢአታችን እንዲሠረይልን በእግዚአብሔር ፊት ንስኀ መግባትና መናዘዝ ማለት ነው። (ኢያሱ7፥19 ማቴ3፥6 ዘሌ5፥5-6 የሐዋ19፥18)
 
– የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት የጥል ግድግዳ አፍርሰን በፍቅር አሸንፈን ስለዘለዓለማዊ ሕይወት ብለን በፍጹም ሕሊና በሰላም መኖር ነው።
 
– ተመልሶ በኅጢአት ላለመውደቅ አዘውትሮ የንስሐ አባትን ወይም የሚቀርቡትን የሃይማኖት መምህር ማማከር፣ ምክር ማግኘት በታቻለ መጠን መጸለይ፣ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ በቤትም ውስጥ ቢሆን መንፈሳዊ መዝሙርና ትምሕርት ማዳመጥ አስፈላጊ ነው።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን ባለዎት ውስጣዊ የሃይማኖት ፅናት እና ንስኀ ለመግባት ባሳዩት የአላማ ቁርጠኝነት የእግዚአብሔር መንገድ ክፍት ሆኖዋልና ተስፋዎትም እጅግ የበራ ነውና፤ በመሆኑም ‘የመዳን ቀን አሁን ነው’ እንደተባለ ከዚህ በኋላ ጊዜ ሳያስረዝሙ የእርስዎን ችግር በምስጢር የሚያስረዷቸው እውነተኛ የቤተክርስቲያን አባት በእኛ በኩል ስለተዘጋጀልዎት በውስጥ መስመር በሚላክልዎት አድራሻ አግኝተው እንዲያናግሯቸውና  ንስኀ እንዲገቡ እኛም አደራ እንላለን።
ለጠያቂያችን የተሰጠ ምክርና ተግሳጽ፦ ጠያቂያችን ከሁሉ በማስቀደም የሁላችንም ጠባቂና መጋቢ የሆነው መሀሪ እና ቸሩ እግዚአብሔር፥ ሰው በማንኛውም ኀጢአት ሳይቀር ቢወድቅ እንኳን ከኀጢአቱ ተጸጽቶ ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ህይወት ፣ ከባርነት ወደ ነፃነት እንድንሸጋገር የንስኀ ጊዜን አብዝቶ የሚሰጥ፣ ያንን ከገንዘብ ቁጥር የሚበዛውን ኀጢአት በአንድ ጊዜ ባዶ የሚያደርግ ፣ በህይወታችን ዙሪያ የከበበንን ድቅድቅ ጨለማ ገፎ በብርሃን እንድንመላለስ የሚያደርገን፣ ከወደቅንበት የኀጢአት ጉድጓድ የሚያነሳን ፣ በኀጢአት እድፍ የቆሸሸውን መላ ህይወታችንን ሳይጸየፍና ሳይጠላን የኀጢያት ስርየትን ሰጥቶ የሚቀድሰንና ንፁህ የሚያደርግ አምላክ ስለሆነ ማንኛውም ክርስቲያን ሲስት ቶሎ በንስኀ መመለስ  እንጂ ከእግዚአብሔር ቤት መሸሽ የለብንም።
የኀጢአት ውጤቱ ሄዶ ሄዶ ሞት ስለሆነ መፍራት ያለብን ኀጢአትን እንጂ የሁላችን እውነተኛ አባት የሆነውን አምላክ እንደሚፈርድብን እና እንደሚቀጣን እንደ ክፉ ዳኛ እያሰብነው ዘወትር ራሳችንን ስናስጨንቅና ስናሳድድ መኖር ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። 
 
አሁንም ጠያቂያችን በጥንቃቄ መረዳት ያለብዎት እዎስዎ ወደ ንስኀ እንዳይመለሱ በኀጢአት ላይ ኀጢአት፣ በጥፋት ላይ ጥፋት፣ በነውር ላይ ነውር እየጨመሩ እንዲቀጥሉና ረጅም የህይወት መንገድ  እንዲጓዙ፣ ነገሮችን ሁሉ የሚዘጋጋ፣ የሰው ሃሳብ ጠማማ ሆኖ እንዲቀጥል፣ ማስተዋልና ጥበብ ከእኛ እንዲርቅ፣ እግዚአብሔርን ማያ አይነልቦናችን እንዲታወር፣ መንፈሳዊ ህይወት ሁሉ እንዲያስጠላን የሚያደግ የሰው ልጅ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ነው።
 
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለፅነው እግዚአብሔር የሰው ልጅ ምንም ያህል ኀጢአተኛ ቢሆንም እንኳን የሚጠላው ሰውየውን ሳይሆን ኀጢአትን ብቻ ነው።  ሰውየውን ግን አንድ ቀን ወደ ንስኀ እንዲመስ እድሜ አርዝሞለት የንስኀ ጊዜ ሰጥቶት ቸርነቱ ምህረቱ በዝቶለት በንስኀ እንዲመለስ ይጠባበቀዋል።”የኀጢአተኛውን ሞት አልወድም፥ መመለሱን እንጂ” እንደተባለው አንድ ቀን በንስኀ እስከምንመለስ በትዕግስት ይጠብቀናል። “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ” ሰቆቃ ኤር 3፥22
በሌላም በኩል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ የመጣው ለኀጢአተኞች ፅድቅን ሊሰጣቸው፣ በኀጢአት ደዌ ለታመሙ መድኃኒት ሊሆናቸው እንጂ፥ በስራቸው ለጸደቁ እና በህይወታቸው ጤነኛ ለሆኑ እንዳልሆነ አራሱ በቃሉ ነግሮናል። ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር የምህረት እጁ ወደ ወዳጆቹ ነው።
ኀጢአተኛ ብንሆንም እንኳን አይኖቹም ጆሮዎቹም የእኛን ጩኸት እና ልመና ሁልጊዜ ያዳምጣሉ።   በከፍተኛ ኀጢአት ባርነት ለሚኖሩት የነፍስ እረፍት ሊሰጣቸው የኀጢአት ቀንበርን ሊሰባብርላቸው የታመነ አምላክ ነው። ።”እናንተ ሸክማችሁ የከበደ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት የኀጢአት ሽክማችንን ለማቅለል የሱ ፈቃድ እንደሆነ ነግሮናል። 
 
ስለዚህ እህታችን የምንመክርዎት ነገር ቃየል ወንድሙን አቤልን በገደለው ጊዜ ማንም በደም የሚፈልገውና ሊገድለው የሚያሳድድደው ሳይኖር የራሱ ህሊና ስለሚያሳድደው እድሜ ልኩን ሲቃዥ ይኖር እንደነበር ቅዱስ መፅኀፍ ይነግረናል።
እኛም ሰዎች ስንባል በዚሁ ደካማ በሆነው የስጋ ባህሪያችን የሰራነውን ኀጢአት ከፈጣሪ ቀጥሎ የምናውቀው እኛ ስለሆንን የኀጢያት ሸክም ሲከብደን እራሳችንን ስለሚያሳድደን ብቻ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ከመወሰን ይልቅ ወደ ተስፋ መቁረጥ እና ወደ ባሰ ጨለማ ጉዞ ራሳችንን እናዘጋጃለን። ይህ ደግሞ ለኛም በነፍሰም በስጋ ህይወትም ባዶ ሆነን እንድንቀር ሰይጣን የሚያዘጋጅልን የጥፋት መንገድ ነው። 
 
በጥቅሉ እህታችን እርስዎ እንዲህ የተጨነቁበት እና እንቅልፍ ያጡበት የኀጢአት አይነት ለመግለፅ የሞከሩት መፍትሄ እና መድኀኒት ያለው ስለሆነ እርስዎ ወደ እውነተኛ የፅድቅ መንገድ ለመመለስ እራስዎትን አዘጋጅተው፤ እኛንም ሊያገኙንና  በሚስጢር መመካከር፤ ዛሬ ከእርስዎ ላይ ተጣብቆ አልላቀቅ ያለውን የኀጢአት ልማድ በእግዚአብሔር እርዳታ ፣ በእኛ ምክር እና ተግሳፅ፣ በአባቶች ፀሎት ፥ ጨርሶ ከእርስዎ እንደሚለይ እናምናለን። አሁንም ቢሆን ይሄን ያህል የህሊና ፀፀት እንዲያድርብዎ ያደረገ እግዚአብሔር ልጁን ስላልተወ ፣ እርሱም ወደ ቤቱ እንዲመለሱ ስለሚፈልግ ነውና እግዚአብሔር ከልጁ እንደማይለይ እናምናለን።
 
በተጨማሪም ገና በልጅነት እድሜዎት እንዲህ አይነት ተስፋ መቁረጥ ራስዎትን እስከመጥላት መድረስዎትም ፈፅሞ ክርስቲያናዊ ፀባይ አይደለም። ስለዚህ እህታችን ከዚህ ሁሉ የጨለማ ህይወት የሚወጡበት የጊዜ ቀጠሮ በጣም ቅርብ ነው። አሁንም የድንግል ልጅ ቸሩ መድኃኒአለም በእኛ በአገልጋዮቹ ላይ አድሮ እርስዎን ከኀጢአት ባርነት ነፃ አንደሚያደርግዎት አንጠራጠርምና የምንገናኝበትን መንገድ ስለምናመቻች በውስጥ መስመር በሚደርስዎት አድራሻ እስከሚደውሉልን፤ እንዲሁም  ካለዎት ውስጣዊ የሃይማኖት ፅናት የእግዚአብሔር መንገድ ክፍት ሆኖዋልና ተስፋዎትም እጅግ የበራ በመሆኑ ይህን ምክር በማንበብና በመረዳት በጸሎት አንዲበረቱ እንዲሁም ወደፊት በግልዎ ሊያደርጉት የሚገባዎትን ምክር እና ትምህርት ስለምንሰጥዎ ደግሞም በአባቶች በኩል እርስዎን ለማዳን መደረግ የሚገባውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማከናወን ይቻል ዘንድ ከዚህ በኋላ ለኀጢአት ጊዜ ሳይሰጡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመመለስ ያለዎትን ፍላጎት እና አላማ ሳይለቁ ያግኙን በማለት ይህ መልእክት እንዲደርስዎት አድርገናል።
በመሰረቱ ማንኛውም ክርስቲያን የሚሰራው የኀጢአት አይነትና መጠን የተለያየ እስከሆነ ድረስ  ንስኀ ገብተን የምንቀበለውም ቀኖና እንዲሁ የተለያየ ይሆናል። ማለትም፦ ላንዱ ከፍተኛ ቀኖና የሚያስፈልገው ሲሆን ሌላው ደግሞ መካከለኛ የቀኖና አይነት የሚያስፈልገው ይሆናል፣ አንዳንዱ ደግሞ ጥቃቅን ወይም መለስተኛ አይነት ቀኖና የሚሰጥበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ፤ ንስኀ ለመስጠት ወይም ኀጢአትን ለመናዘዝ ስልጣነ ክህነት ወይም የንስኀ አባቶቻችን ካህናት ለእያንዳንዱ የኀጢአት አይነት ንስኀ ሲሰጡን የቤተክርስቲያናችን ቀኖና አንቀፀ ንስኀው በሚያዘው መሰረት ስለሆነ እንደ ኀጢአታችን አይነት ለንስኀው ቀኖና መቼ መግባት እንዳለብን የቀኑን ብዛትም ሆነ የጊዜውን ውሳኔ እነሱ በሚያዙን መሰረት ይሆናል። ንስኀውም በፆም ወይም በስግደት ፣ ወይም በፀሎት፣ ወይም በምፅዋት ፣ ወይም ደግሞ በሌላ የቱሩፋት ስራ መፈፀም ካለበት እነሱ በሚነግሩን መሰረት የሚከናወን ይሆናል።
 
በዚሁ መሰረት ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላት ስለ ንስኀ ቀኖና መረዳት ያለብን፦
 
1ኛ/ ብዙ የፆም እና የስግደት ጊዜ የሚያስፈልገው ከባድ ኀጢአት ሰርተን ብንገኝ የምንፆምበት የሰዓት ገደብ እንደመደበኛው ፆም መሆን ስለሚችልና ፣ የምንሰግደውም የንስኀ ስግደት ብዙ ከሆነ ከመደበኛው የፆም ስግደት ጋር ደምረን ብንፀፆም እና ብንሰግድ እኛም ልንጎዳ ስለምንችል የመደበኛ ፆም ጊዜ እና ለንስኀ የምንፆምበት ጊዜ ስለሚጋጭ ወይም የንስኀውን የፆም ጊዜ ስለማይሸፍን ለዚህ ነው ለያይተን መፆም ያለብን ወይም በፆም ላይ ንስኀ የማይሰጠው።  
 
ያ ማለት ግን ሰው በኀጢአት ተጨማልቆ መቼ ፈተና እንደሚገጥመው ወይም በሞት እንደሚጠራ እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ፥ መደበኛ የፆም ጊዜ እስከሚያልቅ ብሎ በስንፍና የኀጢአት ሀብት እያካበተ ወይም የኀጢአት የቀጠሮ ጊዜውን እያስረዘመ መቆየት የለበትም። ለዚህም መፍትሄው በቤተክርስቲያን ቀኖና ስለ ንስኀ የተደነገገውን በመመርመር በመደበኛ ፆምም ላይ ቢሆን የንስኀውን ፆም ጊዜ እና ሰዓት ጨምሮ በመፆም፣   የንስኀውን ስግደትም በመደበኛው የጾም ስግደት ላይ በመጨመር፣ ሌላውንም ትዕትዕዛዛችንን ከዚሁ ጋር አካተን መፈፀም እንችላለን።
 
2ኛ/ ሌላው፤ መደበኛ ፆም ገብቶ እስከሚያልቅ ከመጠበቅ ይልቅ ከመደበኛ ፆም ቀድመን ንስኀ መግባት እንችላለን። ዋናው መታወቅ ያለበት፥ ክርስቲያን መሆን ከስጋ ፆም መጾም ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ መስጠት ስለሚገባው ቅድሚያ እየሰጡ በሁሉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ለማግኘት ስጋንም ቢሆን በመጉዳት ለስጋዊ የምናውለውን ጊዜያችንን ቀንሰን ለነፍሳችን በማትረፍ ንስኀ ልንገባ ያስፈልጋል።
 
3ኛ/  ክርስቲያን በሀሳብም ፣ በንግግርም፣ በገቢርም ሳናውቅም እያወቅንም የምንሰራቸው የኀጢአት አይነቶች ብዙ ስለሆኑ ፥ ቀን የዋለው ቢያድር፣ ሌሊት ያደረው ቢውል የኀጢአት ብዛት ስለሚያመጣ በየቀኑ ወደ ንስኀ አባታችን ቀርበን መደበኛ ንስኀ ባንቀበልም እንኳን እየፀለይን፣ እየሰገድን፣ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደን የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምህረት እየጠየቅን፣ በአባቶቻችን እጅ መስቀል እየተባረክን፣ ፀበል እየተጠመቅን፣ ቃለ እግዚአብሔር እየሰማን፣ ኪዳን እያደረስን፣ ቅዳሴ እያስቀደስን፣ቅዱስ ቁርባን እየተቀበልን፣ አቤቱ ጌታ ሆይ ይቅር በለን፥ እራራልን፥ የኀጢአት ስርየት ስጠን፥ ሰው የማያውቅብንን አንተ የምታውቅብንን በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ እያልን ዘወትር ስንማፀነው በልምድም ሆነ በተለያየ ምክንያት በየሰዓቱ በየእለቱ የምንሰራውን ጥቃቅን ኀጢአታችንን በዚህ ስርዓት እንደሚደመስስልን እና የኀጢአት ስርየትም እንደምናገኝ ለነፍሳችንም እረፍት እንደሚሰጠን ማመን ይገባናል።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል፥ ተጨማሪ ማብራሪያ ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ከሁሉ አስቀድሞ እንዲረዱት የሚያስፈልገው ማንኛውም ሰው ኀጥያት ሰርቶ ንስኀ ከገባ በኋላ ተመልሶ በኀጥያት መሰናከል የተለመደ ስጋዊ ተፈጥሮ ነው። ምንም እንኳን የኛ አምላክ መድኃንያለም ስለኛ ኀጥያት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ሞትና መቃብርን ሽሮ ነፃ ቢያወጣንም፤ ሰው ግን ከጠላቱ ከዲያብሎስ በየጊዜው በሚጠመድበት የኀጥያት ወጥመድ እየተያዘ፣ እግዚአብሔር ስለኛ ያደረገውን ውለታም በመዘንጋት በደል ቢፈጽምም እንኳን ቸርና መሃሪ የሆነ አምላካችን ግን አሁንም በንስሐ ወደ እሱ እንድንመለስ መንገድ ሰጥቶናል።
 
በዚሁ መሰረት ከሰይጣን ጋር ያለን ውግያ የማይቋረጥ ስለሆነ አንድ ግዜ ስንወድቅ፣ አንድ ግዜ ስንነሳ የምንቀጥልበት አለም የፈተና ጊዜ ስለሆነ በእርስዎ ብቻ የደረሰ አድርገው ተስፋ መቁረጥ የለቦትም። ደጋግመው በአንድ ኀጢዓት መውደቅዎ እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም፤ ስለአድን ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ተስፋ ሳይቆረጡ  ወደ አባቶች ቀርበው  ውስጣዊ ችግሮን ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስሓ ህይወት እንዲቀርብ እና በተደጋጋሚ ከተፈተኑበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አቤቱ ወንድሜ ምን ያህል ቢበድለኝ ምን ያህል ይቅር ልበለው እስከ 7 ጊዜ ነውን ብሎ በጠየቀው ጊዜ እስከ 7 አልልህም 7ቱን አንድ እያልክ እስከ 70 ነው እንጂ” በማለት ለኅጢአት ይቅርታ የጊዜ እና የቁጥር ገደብ እንደሌለው አረጋግጦልናል። (ማቴ 18፥21-22)
 
ስለዚህ  ከኅጢያት ደዌ እስካልተፈወስን ድረስ የንስሓ ህይወት አይቋረጥም ይቀጥላል እንጂ። ኀጥያት ለሰው ልጅ ሞትን የሚያስከትል ክፉ ደዌ ቢሆንም ንስሐ ደግሞ የሚፈውስ መድሀኒት ነው። ስለሆነም አብዝቶ መፀለይ፣ መፆም፣ ንስሐ መግባት፣ በአጠቃላይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምህረት መጠየቅ ክርስቲያናዊ ፀባይ መሆን አለበት።
 
በተጨማሪም  ፤ አንድ ክርስቲያን በኅጢአት የጎደፈውን ሰውነቱን ከታጠበ በኋላ መላ ህይወቱ ንፁህ ስለሆነ ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት መንገዱ ሁሉ ቀና ስለሆነ ከንስኀ በኋላ ማድረግ ያለበት ምን እንደሆነ ከዚህ በፊት እንደገለጽነው፦
 
1ኛ/ ከምንም በላይ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎትን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ፣
 
2ኛ/ እግዚአብሔር ቢፈቅድልዎት በቅዱስ ቁርባን መወሰን፣ አቅምዎት በሚፈቅደው መጠን ሳያቋርጡ እና ሳይሰለቹ መፆም፣ መፀለይ፣ እና መስገድ፣
 
3ኛ/ በአቅምዎት ከሚያገኙት ነገር ለድሆችና ለእግዚአብሔር የሚገባውን አስራተ በኩራት ማዋጣት፣
 
4ኛ/ ዘወትር ከአባቶች ምክር እና መታዘዝ አለመራቅ፣ በፕሮግራም ወደ ቤተክርስቲያን እየቀረቡ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣
 
5ኛ ሁሌ እንደቅርብ አስተማሪና መካሪ ሁነው የሚያገለግሎትን መንፈሳዊያን መፃህፍትን ማንበብ፣ ከዚህም በላይ በኑሮዎት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ በማህበራዊ ጉዳይ ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር በትዕግስት እና በጥበብ ለመኖር ድርሻዎትን መወጣት።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን እነዚህን ሁሉ እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ነገሮችን አጠቃሎ ለመስራት የሚቻለው ሰው ህይወቱ በንስሓ ሲታደስ ስለሆነ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእርስዎን ህይወት በንፅህና በቅድስና እንደሚጠብቃት በማመን አሁንም እንደገና ንስኀ ገብተው ከዚህ በላይ የተሰጠዎትን መንፈሳዊ ምክር ደረጃ በደረጃ በሚችሉት አቅም በስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ በእግዚአብሔር ስም እንመክራለን።

ጠያቂያችን፤ ከጥያቄዎ ሃሳብ እንደተረዳነው ወደ ንስኀ አባት ቀርበው ንስኀ ገብተዋል፤ ቀኖናም ተቀብለዋል፤ ቀኖናዎትንም ጨርሰዋል። ነገር ግን የቀረ የረሱት ያልተናገሩት ነገር አለ። ስለዚህ ጠያቂያችን ይሄንን በተመለከተ ቀረ ያሉትን ንስኀ ለካህኑ መንገር ይጠበቅብዎታል። ካህኑ በቅርብ ከሌለ ደግሞ አካባቢዎ በሚያገኟቸው ካህን ለዚህ ለቀረው ንስኀ ላልገቡበት ኀጢአት ብቻ ንስኀ በመግባት ቀኖናውን በአግባቡ መቀበልና መጨረስ አለብዎት። ምክንያቱም ቀኖና የሚሰጠን በፈፀምነው የኀጢአት ደረጃ እና መጠን ተለክቶ ስለሆነ እያንዳንዱን ያጠፋነውን ጥፋት ከባድም ቢሆን ሳንፈራ ፤ ቀላልም ቢሆን ሳንንቅ ለካህኑ መናገር እንዳለብን  በቀኖና ቤተክርስቲያን ተደንግጓል። ስለዚህ ጠያቂያችን ምንም መፍራት የለብዎትም፤ ይልቁንስ እርስዎ እንዳሉት ህሊና ንፁህ ካልሆነና ካልፀዳ ያ ህሊና በእኛ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ድምፅ ነውና ይጠይቀናል። ህሊና ትልቁ ዳኛ ነው።  ህሊና ይገስፃል፣ ይወቅሳል፣ ይዘልፋል፤ እኛም ልንሸነግለውና ፀጥ ልናሰኘው የማንችለው ህሊናችንን በመስማት መፈፀም ይኖርብናል፤ ነጻ ስንሆንም እንደዚሁ ህሊናችን ይነግረናል ።

ስለዚህ ህሊናችን እያወቀ መናዘዝ አለብን ፤ ቀኖና መቀበል ስላለብን ይህን ለካህን ሄደን መናዘዝና ቀኖናን ተቀብለን በአግባቡ መጨረስ መቻል አለብን። ይህም ፍፁም የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ እንድንሆን ነው፤ ፍጹም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን ነው፤ ከንስኀ በኋላ እግዚአብሔር ልጆቼ እንዲለን ነው፤ የጠፋነው ልጆች ወደ እግዚአብሔር መመለስ የምንችለው እኛ ቀኖናውን በአግባቡ ስንጨርስ መንፈስ ቅዱስ ከላይ ከሰማይ ይወርዳል፣ ልጆቹን እንደገና እንደ አዲስ ይጎበኘናል የጥበብ ሁሉ ምንጭ ባለቤት ያደርገናል፣ ልጆቼ ብሎ በአባት አይን ያቅፈናል ማለት ነውና ንስኀ ገብተው ቀኖናዎን በአግባቡ እንዲጨርሱ እንመክራለን። 

አንድ ሰው ለበደለው በደል እራሱ ነው ቅጣቱን መቀጣት ያለበት። አዳም በበደለው በደል ቀኖናውን የጨረሰው እሱ ነው። አንድ ወንጀል የሰራ ሰው ወደ ወህኒ ቤት የሚገባወ እራሱ ነው እንጂ እኔ ልግባ ብሎ የሚያልፍ ሰው መኖር የለበትም። በዚህ አንፃር ካህኑ ልጁን ‘አንተ የአቅምህን ይሄን ይሄን ጹም፣ ጸልይ እኔ ደግሞ የራሴን ድርሻ አደርጋለሁ’ የሚል እንጂ ፤ ‘ይሄን ይሄን አድርግ ሌላውን እኔ አደርግልሀለሁ’ የሚል አባት ከሆነ እኝህ አባት ወይ ፍፁም መንፈሳዊ መሆን አለባቸው ፥ ወይም ደግሞ ያ ንስኀ የገባው ሰው በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የተያዘ ከሆነ፣ በሽተኛ ከሆነ፣ መስገድና መፆም የማይችል በጣም ደካማ ከሆነ፦ በእርግጥም አባቱ ‘አንተ ይሄን ይሄን እያደረግክ ኀጢአትህን አብሰልስለው፣ ኀጢአትህ በጣም ከባድ ነው፤ እግዚአብሔር እንዲምርህ እኔ የድርሻዬን እንዲህ አደርጋለው ፤ አንተ ደግሞ የድርሻህን እንዲህ አድረግ’ የሚሉ አባቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ከዚህ ውጪ አንዳንዴ ሀብታም ስለሆኑ ወይም ከተማ ላይ ነጋዴዎች ስለሆኑ በሚል ‘በል እኔ እፆምልኀለሁና አንተ ይሄን ገንዘብ ክፈል’ የሚሉ አባቶች ካሉ ይሄ ውንብድና ነውና እውነተኛ አባቶችን ቀርቦ መጠየቅ ያስፈልጋል ። ‘ስራ ስለሚባዛብኝ’ ወይም ‘የንግድ ስራ ስለሚበዛብኝ’ ቢል እንኳን ‘አንተ ስራህን ስራ ቀኖናውን እኔ ፈፅምልሀለሁ’ የሚባል ነገር የለም። ምድራዊ ስራ እርግፍ አድርጎ ስለ ነፍስ ድህነት ገዳምም ገብቶ ይሁን ቤትም ዘግቶ ይሁን በፆም በፀሎት ማልቀስ ማዘን አለበት።  ስለዚህ ተገቢነት ካለው አንዳንዴም በጣም ጫን ብሎ ያ ሰው መቀጣት መቻል አለበትና ማስተዋል አለብን።  ስጋችን መድከም መቻል አለበት መጎሳቆል አለበት ፦ አባታችን አዳምን አስቡት ከእኛ የከፋ በደል በድሎ አይደለም እፀበለስን ቆረጠ ፤ የዲያብሎስን ሃሳብ ሰምቶ እውነት መሰሎት አደረገ፥ ተሳሳተ፣ አለቀሰ ፣ ስላለቀሰ ግን ወድያው አልማረውም 5500 ዘመን  ቆየ፣ ያ 5500 ዘመን ደግሞ ደም ደም ያለቀሰበት ጊዜ ነው ፥ እንባው አልቆ ደም እስኪያለቅስ ድረስ ተጸጸተ፥ ቀኖና ማለት እንዲህ ነው ከዚያም በኋላ 5500 ዘመን ሲፈፀም እግዚአብሔር ሊታረቀው መጣ፥ ስጋን ለብሶ መጣ ፥ ‘ልጄ!’ አለው። አባትም እንዲህ ነው ፥ ካህን ልጁ ደም አልቅሶ ስለ ኀጢአቱ ያነባውን እንባ አይቶ በካህኑ አማካኝነት እግዚአብሔር ያቅፈዋል ልክ የጠፋው ልጅ ወደ እቤት እንደተመለሰ አይነት ልጄ ተመልሷል ተፀፅቷል ብሎ ያቅፈዋል። ስለዚህ በዚ መልክ መጸጸትና አብዝተን ሥጋችንን በማድከም ነው መሆን ያለበት እንጂ ሳምንት ሁለት ሳምንት ሦስት ሳምንት እስከ 6 ሰዓት እየተፆመና ምግቡም እየተመረጠ እየተበላ ፥ ይሄም በዛ ቀንሱልኝ ወይ አግዙኝ እየተባለ ቀኖና ተፈፅሟል ንስኀ ተገብቷል ለማለት በጣም ከባድ ነው።  ለዚህ ወደፊት ሰፊ ትምህርት የምንሰጥበት ሆኖ ላሁን ግን ወደ ጠያቂያችን ዋና ሃሳብ ስንመለስ ፤ ‘አንድ ሰው ኀጢአት ከሰራ ማነው ቅጣቱን ሊቀጣ የሚገባው?’ ላሉት፤ ከላይ ባብራራነው መሰረት በአሳማኝ ወይም በልዩ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሊቀጣ የሚገባው እራሱ ነው። አባቱም የራሳቸውን በድርሻቸው የሚያደርጉትን ለልጁ ላይነግሩት ይችላሉ በድብቅ በስውር ሊፆሙ ሊሰግዱ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ግን ካልቻልክ እኔ እንዲህ አደርግልሃለው አንተ ነግድ፣ በንግድ አለም ወዲያ ወዲህ በል የሚል አባት ግን አባት አይደለምና ሊታሰብበት ይገባል።

ጠያቂያችን፤ ለዚህ ጥያቄዎ ከዚህ ቀደም መልስ ልከንልዎት እንደነበር እናስታውሳለን፤ ይሁን እንጂ ምናልባት አላዩት ከሆነ ከዚህ በታች በድጋሚ ልከንልዎታልና ይመልከቱት።
 
ኅጢአቶን በመናዘዝ ከልብ ተጸጽተው ወይም ተመልሰው፤ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት በማገልገል ላይ ለሚገኘው የንስሐ አባትዎ (ካህን) ራስዎን በማስመርመርና ከፈጸሙት በደል የሚነፁበትን ንስሐ ተቀብለው ከሄዱና ከዳግም ጥፋትም እርቀው በካህኑ የተሰጠዎትን ንስሐ በትክክል ከፈጸሙ፤ ከተያዙበት የኅጥያት ማሰሪያ ስለተፈቱ ንስሐም ገብተው ስለተናዘዙበት እንደገና ይፍቱኝ ለማለት ወደ ካህኑ የሚያስኬድ ጉዳይ አይኖርብዎትም።  ምክንያቱም በኅጥያት እድፍ የቆሸሸውን ህይወትዎን ከካህኑ በተቀበሉት የንስሐ ውሃ ታጥበው ከኅጥያት እድፍ ፀድተዋልና። ዳግም እንዳይበድሉ፣ ኅጥያት ሰርተውም የቅድስና ሕይወትዎን እንዳያቆሽሸው፣ በየጊዜው ከቤተ ክርስቲያን መምህራንና የንስሐ አባቶች ትምህርትና ተግሳጽ እያገኙ ምንም እንኳን የኑሮ ፈተና ቢበዛብዎ ከእናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳይርቁ እየፆሙና እየፀለዩ ከገንዘብዎ፣ ከእውቀትዎ እና ከጉልበትዎም አስራት በኩራት እያወጡ በጎ ስራ በመስራት ከሰይጣን ወጥመድ ለማምለጥ የሚችሉበትን መንፈሳዊ ፀጋዎትን በተቻለ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለብዎ እመክራለው። ለዚህም ዋናውና መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ክርስቲያን ያለጠባቂና ያለመካሪ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌበት ወደ ንስሐ አባትዎ (ካህን) መሄድ ያለብዎ በየጊዜው የእለት እለት ህይወትዎን በካህኑ ምክር እንዲመራ ለማድረግ ነው።
 
ከዚህ ውጪ አንድ ከርስቲያን ንስሓ ገብቶ የተሰጠውን ቀኖና ከጨረሰ በኋላ፤ ጊዜ ካለው በአካል፣ ጊዜ ከሌለው ደግሞ በስልክ ወይም በሌላ መገናኛ መንገድ የተሰጠኝን ትእዛዝ ፈጽሜያለሁ ብሎ ሊነግራቸው ይችላል። ይህን ለማድረግ ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ቢያጋጥመው ግን ፤ ለሰራው ኀጢአት ካሳ ስለከፈለ፣ ከታሰረበትም የኅጢአት ማሰሪያ ስለተፈታ ለፈጣሪው በምስጢር ነግሮ ከዛ በኋላ ከመንፈሳዊ ነገር ላለመራቅ መትጋት አንጂ ወደ አባቴ ተመልሼ ይፍቱኝ ብዬ ስላልተናገርኩኝ ወይም እግዚአብሔር  ይፍታህ ሰላላሉኝ ጥፋት ሊሆንብኝ ይችል ይሆን በማለት ሊያሳስብዎት አይገባም።
በመሆኑም፤ ወደንስሃ አባትዎ ወይም ንስሐ ወደተቀበሉበት ካህን መሄድ የሚኖርብዎ ካህናት አባቶች የነፍሳችን እረኛ ሆነው በነፍስ ጉዳይ ላይ በሃላፊነት እግዚአብሔር ስለሾማቸው ሁልግዜም ቢሆን ከአባቶች ምክርና ተግሳጽ ላለመራቅ ነው እንጂ ቀደም ሲል ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያት ይፍቱኝ ለማለት አለመሄድዎን እንደጥፋት ቆጥረው  እንደገና ንስሐ እንዲገቡበት አያስፈልግዎትም በማለት መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን። (ማቴ18፤18) ዩሐ(20፤21-23) ዩሐ (21፤15-18)

ጠያቂያችን የንስኀ ቀኖና እንዴት መቀበል እንዳለብን ከዚህ ቀደም ለብዙ ጠያቂዎቻችን ስለ ንስኀ በሰጠነው ማብራሪያ ምላሽ የሰጠንበት ሲሆን፤ አሁንም ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት ንስኀ እንዲሰጡን ቀርበን የኀጢአታችንን ዝርዝር የነገርናቸው የነፍስ አባታችን እንደ ኀጢአታችን አይነት በጾም፣  ወይም በፀሎት ፣ ወይም በስግደት፣ ወይም በምፅዋት፣ ወይም በጥምቀት፣ ወይም ደግሞ በሁሉም ለንስኀ ህይወታችን ቀኖና እድንንገባ ባዘዙን መሰረት የሚፈፀም ነው። ምክንያቱም እስከ ቄደር ጥምቀት የሚያደርስ የንስኀ አይነት አለና ነው። በመሆኑም ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን ስለ ንስኀ አሰጣጥ የንስኀ ቀኖና ስለምንገባበት መንገድ እኛ በግላችን መጨነቅ የለብንም። የምእመናን ድርሻ ለእግዚአብሔር የሚሰወር እና የሚደበቅ ኀጢአት ሳይኖረን እግዚአብሔር ለሾመው አገልጋይ ወይም ካህን ቀርበን በዝርዝር ማስረዳት ብቻ ነው የሚጠበቅብን። ከዚህ ውጪ በምን አይነት መንገድ ቀኖና ተሰጥቶን ወይም እንዴት አይነት ቀኖና መፈፀም እንዳለብን የመንገር የካህኑ ድርሻ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል፥ ተጨማሪ ማብራሪያ ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

ጠያቂያችን እንደተረዳንዎት ከሆነ ልብ መሻት አለ፥ ነገር ግን ያው ንስኀ የሚለውን ሃሳብ መጀመሪያ በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል። የይቅርታ አምላክ  ማንም ወጥቶ እንዲቀር አይፈልግም ፥ ልጆቹን ይፈልጋቸዋል ” በውኑ ኀጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” (ሕዝ18፥23) እግዚአብሔር ልጆቹን ከነኀጢአታቸው እንዲሞቱ አይፈልግም እድል ይሰጣቸዋል በዚህ በምድር ላይ እንዲፀፀቱ ንስኀ እንዲገቡ ከልብ በመነጨ ንስኀ እንዲመለሱ ነው እንጂ።  ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንደገለፅነው ንስኀ ማለት ከጥምቀት በኋላ በሰሩት ኀጢአት ከልብ በማዘን፣ ወደ መምህረ ንስኀ ሄዶ መናዘዝ፣ ኀጢአትን መናገር፣ ጥፋትን ላለመድገም መወሰን ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት በካህኑ የማሰርና የመፍታት ስልጣን አምኖ አነሰ በዛ ሳይሉ የተሰጠውን ቀኖና ከቤተክርስቲያንአባቶች በምስጋና ተቀብሎ መፈፀም ነው የቤተክርስቲያናችን ስርዓት።  ስለዚህ እያዘኑ እየተከዙ አብዝቶ እያለቀሱ ንስኀን በአግባቡ መፈፀም ያስፈልጋል።አቡነ ቪኖዳ የግብፅ ፓትሪያርክ ታላቁ አባት የንስኀ አፈፃፀም ደረጃ በ3 ከፍለው አስተምረዋል፦
 
1ኛ የንስኀ ደረጃ፦ የንስኀ መጀመሪያ ደረጃ ኀጢአትን መተው ሳይሆን ንስኀ ለመግባት ማሰብ ወይም መፈለግ ነው። መጀመሪያ ማሰብ መፈለግ። ይህ ኀጢአትን ከመተው የሚቀድም ነው። ሰዎች ንስኀ ለመግባት ባልፈለጉና ባላሰቡ መጠን በኀጢአት እየተደሰቱ ኀጢአትን እየሰሩ ይኖራሉ። በነሱ አመለካከት የያዙት የኀጢአት ኑሯቸው መልካም ስለሚመስላቸው አይለወጡምና። 
 
2ኛ የንስኀ ደረጃ፦ ኀጢአትን  መተው ሲባል የኀጢአትን እርሾ ከህሊና ከልቦና ጨርሶ ፈፅሞ ማጥፋት ነው፦ ይህ ኀጢአትን ከማሰብ መለየት ማለት ነው። ምክንያቱም ሰው ምንም እንኳን ኀጢአትን በገቢር በተግባር ባይፈፅምም በልቡ ፍቅረ ኀጢአት ከነገሰ ፣ኀጢአት በልቡ ከተመላለሰ ንስኀ አያስፈልገውም አይባልም። እንግዲህ ሰው የእግዚአብሔርን ህግ ለመጠበቅ ብሎ ኀጢአትን በገቢር ባይሰራም፥ ኀጢአትን አልጠላምና ኀጢአትን ትቷል ሊባል አይችልም ። ስለዚህ በልቦናው የኀጢአት ፍቅር ፣ ቅሪት ስላለ ፀፀትና ንስኀው ልቦናው ከኀጢአት እስኪነፃ መሆን አለበት። 
 
3ኛ የንስኀ ደረጃ፦ የመጨረሻው የንስኀ ደረጃ ኀጢአትን መጥላት ነው። ይህን ኀጢአት በፍፁም ልብ መጥላት፣ አለማሰብ እና የኀጢአት ተገዢ አለመሆን ነው። ይህ ከፍተኛ የንስኀ ደረጃ ሲሆን ከዚህ ደረጃ ለመድረስ በክርስትና ህይወት የሚገለፁትን ረቂቃን ጥቃቅን ኀብታቶች ከዚያም ከፍተኛውና ዋነኛውን ኀጢአት እስኪረሳው ድረስ መሆን አለበት ማለት ነው ።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን፤ ንስኀ የሚገባ ሰው የሄንን በደንብ መረዳት አለበት። እንግዲህ እርስዎ ይሄንን በደንብ አልተረዱትም ማለት ሊሆን ይችላል። ንስኀ ሲባል ዝም ብለው ሄደው ወደ ካህኑ ቀረቡ ተመልሰው ወደኀጢአት ገቡ። አንዳንዴ በንስኀ ማፌዝ ደግሞ ቅጣትም አለው እግዚአብሔር ይፈልገና፥ በጣም ነው የሚሻን ልጆቹን ጠፍተን ወጥተን እንዳንቀርበት ይጨነቃል። ግን ደግሞ በአግባብ ትምህርቱን መቀበል ያስፈልጋል። አቅልለን ማየት አያስፈልግም ። ንስኀ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፥ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፣ ከኀጢአት እንቅልፍ መንቃት ነው፣ የዲያብሎስን የኀጢአት ኑሮ ማውገዝ እና መኮነን ነው ካልን ለምን ተመልሰን ወደ ኀጢአት እንገነዘባለን? ተመልሰን እንዳንገባ መጠንቀቅና መጨከን ያስፈልጋል እንጂ።
 
በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 8 ላይ የተገፀች ሴት ስታመነዝር አገኘናት ብለው እየጎተቱ አመጧት ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ። እንግዲህ እነርሱ አብረው ከእኳ ጋር ዝሙት ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ፥ ግን እያሰቃዩ ጎትተው አመጧትና፤ ‘አንተስ ምን ትላለህ?’ አሉት ጌታችንን፥ ምንም አላለም እያዘነ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ እየፃፈ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው፥ ሁሉም ሄዱ።” ምክንያቱም እሷ አመንዝራለች ተብላ ፍርድ ይገባታል ካላችሁ እናንተም ከሷ ጋር ያመነዘራችሁ ናችሁና ከሷ ያልተናነሰ ባለእዳ ናችሁ ማለቱ ነው፤ ሲጽፍም እንደዛ ነው። በግንባራቸው ተነበበ ነው የሚለው ፥ ከዚያም በኋላ ጌታችን ሲያይ ሁሉም የሉም ። እሷ ጥፋተኛ እንደሆነች ያውቃል ኀጢአተኛ እንደሆነች ያውቃል ፤ ግን “እኔ አሁን አልፈርድብሽም ዳግም አትበድይ” ነው ያላት። 
 
ስለዚህ አሁን ወደ ካህን ስንሄድ ህሊናችን ነው እየጎተተ ያመጣን ፤ እና ወደካህኑ ጎትቶ በግድ አመጣን እና ወንጀለኛ ነው ቢልም በካህኑ አማካኝነት ዳግም አትበድል ብሎ ቀኖና ሰጥቶናል ፤ እኛ ግን እያፌዝን እያሾፍን ኀጢአትን ደገምነው።
መፃጉን ስንመለከተው 78 አመት በአልጋ ተጣብቆ እንደቱኀን ይሰቃይ ነበርና፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልጋሀን ተሸክመህ ሂድ ብሎ በአንድ ቀን አዳነው፥ እና ‘ማነው ያዳነህ?’ ፣ ‘ማነው ያዳነህ?’ ሲሉት ያዳነውን እንኳን አላወቀውም ነበር። አንድ ቀን በመቅደስ ሲያስተምር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገኘውና ያዳነውን አላወቀውም (ዮሐ 5፥14)  መድኀኒትን የማያውቅ ትውልድ ልክ እንደ መፃጉ  አይነት ትውልድ ነው አሁንም በዘመናችንም ያለው።
 
እነሆ ድነሀል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደፊት ኀጢአት አትስራ ስንባል ደግመን በኀጢአት ማፌዝ ወይም ማሾፍ ቅጣትን እየጨመረ ያመጣል። እግዚአብሔር አንዳንዴ እምቢም ብሎ ለንስኀ ላይመለስልን ይችላል፥ ሳሙኤልም ለሳኦል እያለቀሰ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቀኝ አማልደኝ ቢለው እግዚአብሔር ደግሞ ምንድነው ያለው? ‘በፍፁም ንስኀውን አትቀበለው እርሱን እኔ  ልታረቀው አልፈልግም ጊዜውን ተጠቅሟልና ይላል።’ በእርግጥ እንዲህ ስንል ነስኀ ሁሌ መግባት አያስፈልግም ማለታችን አይደለም ካንድ ከሁለት ግን የክርስቲያን አቅም ማጣት አንዳንዴ በጣም ቅጣት ያስከትላል። 
 
ዝሙት በጣም ከባድ ኀጢአት ነው።ባለፈው እንዳስተማርነው  ከኀጢአት ሁሉ የከፋ ኀጢአት ዝሙት ነው ። በእግዚአብኤር ቤተመቅደስ ላይ እርኩሰት ሆን ብሎ አስቦ መስራት በጣም የከፋ ወንጀል ነው። የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ እያረከስንበት እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ስለዚህ አሁንም ወንድማችን ተስፋ እንዲቆርጡ ሳይሆን የንስኀን ሂደት እና ጥቅም  በአግባቡ ተምረውና አውቀው በንስኀ ህይወት ፣  ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ ወስነውና ጨክነው  መመለስ አለብዎት በአጽንዎት ለምክር ነው። እርስዎ በማያስተውሉት ረቂቅ መንገድ  ዲያብሎስ እነመራዎትና ድል እያደረገዎት ነውና።
 
እግዚአብሔር ቸር አባት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ለክርስትናውና ለድህነት ወስነው መቅረብ እና ራስን በንስኀ ማዘጋጀት የቀደመውን ትተው ዳግም ወደኀጢአት ላለመሰማራት መወሰን ያስፈልጋል። ምክንያቱም እያወቅን ስንደጋግመው  በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ይቀጣናል እግዚአብሔር። ለንስኀ ጊዜ ቢሰጠንም በማስተዋል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ነው ወደ ካህናተ ቅረቡ የተባለው። ካህን እግዚአብሔር የላከው ባለመድኀኒት ነው እና የእርሱን ትምህርትና ምክር፣ የሱን ተግሳፅ ማዳመጥ ይኖርብናል። የማሰር የመፍታት ስልጣን ያለው ፣ ከማሰረ ዲያብሎስ የሚፈታ ሰማያዊ አባት ነው ። አባቶቻችን እና እናቶቻችን የቀደሙት “ካህን እና መብራት አይንሳችሁ” ይላሉ።  ይህ ለትውልድ መዳን የሚያስቡ ካህናትን ማለት ነው  ነጋዴ ካህናትን አይደልም ። አዎ እውነተኛ ካህናት የሰው ህመም ሊያማቸው የሚችል፣ የዚህ የጠፋው ትውልድ የሚያስጨንቃቸው ቀኖናን ተቀብለው አብረው ተካፍለው የሚሰጡ የሚጾሙ፣ ስለልጃቸው እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥመው መሬት ላይ ተኝተው ‘ተታረቀው አምላኬ’ እያሉ ማልቀስ አለባቸው በእንባ! ‘ይሄ ክፉ መንፈስ አልሸሽልህ ያለውና የተጠናወተው ለምንድነው?” ብለው ካህኑ የልጁን ቀኖና ተካፍሎ መጾም መፀለይ አለበት  ፥ እሱም በእንባ በፆም በፀሎት አብዝቶ እያለቀሰ ለንስኀ መትጋት አለበት። አባትም በየሰአቱ እየደወለ “በረታህ ወይ?”፣ “አይዞህ ልጄ!” ፣” እንዴት ነህ ?” እያለ መጠየቅ አለበት እንጂ ሲወድቅ ግን አባቱ ፊቱን እንዲያዞርበት አይገባም። ይልቁንም እያስተማሩ፣ እየመከሩና እየገሰፁ መታገል ያስፈልጋልጋቸዋል። ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ ያ ተነሳሂው የማይረዳቸውና የማያግዛቸው  ከሆነ አወዳደቁ የከፋ ነው የሚሆነው። ይሁዳ በስተመጨረሻ ላይ የተባለው ፥ እናቱን ተገናኘ አባቱን ሰለበ፤  እግዚአብሔር ግን ይቅር ብሎ ወደእሱ አመጣ፥ ልጁ አደረገው። በኋላ ግን ፈጣሪውን በገንዘብ ሸጠው ፤ በመጨረሻ ግን “ባልተወለድክ በጠፋህ” ነበር የተባለው እና እንዲህ እንዳንሆን፤ እንዳንዘገይም እናስተውል።   ክርስትና ማወቅ አይደለም፥ መኖር ነውና፤ በአግባቡ ንስኀን የምንሻና የምንናፍቅ ሁሉ ንስኀ ገብተን ከሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ጋር መታረቅ መቻል አለብን። 
 
የንስሓ አባቴን ቀርቤ ለማማከር አፈርኩ ላሉት፥ እንደ ቤተክርስትያናችን ስርዓት ከሆነ በእርስዎ እና በንስሓ አባትዎ መካከል ለመናገር እሚያሳፍርም ሆነ የማይነገር ምስጢር መኖር የለበትም። እማትታየውን ረቂቋን ነፍስ በኃላፊነት የተሰጠው ካህን ስለሆነ ለመናገር መድፈር አለብዎት እንላለን። ከዚህ ሌላ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ወይም እኛ ያልተረዳንዎት ጉዳይ ካለ መፍትሄ እንድንሰጥዎት በውስጥ መስመር የግኙን።ስለአድን ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ተስፋ ሳይቆረጥ ይሄን ሰው በተለያየ መንገድ የንስሓ አባቱ ወይም ሌላም አባት በቅርብ ውስጣዊ ችግሩን ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስሓ ህይወት እንዲቀርብ እና በተደጋጋሚ ከተፈተነበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነውና። 
 
የንስኀን ቀኖናን በገንዘብ መለወጥ ይቻላል ወይ ብለው ለጠየቁን የተሰጠ መልስ። በመሰረቱ ለንስኀ ህይወት የሚቀርብ ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የፈፀመውን ኀጢአት ለንስኀ አባቱ በዝርዝር በተናዘዘ ጊዜ ለእያንዳነዱ የኀጢአት አይነት ቀኖና እንደሚያስፈልገው በቤተክርስቲያን ውስጥ ስለ ንስኀ አሰጣጥ በሚያስረዳው በፍትሐነገስት ወይም በአንቀፀ ንስኀ ወይም በሌሎቹ የቀኖና መፅሐፍት በተደነገገው መሰረት በፆም፣ በፀሎት ፣ በስግደት እና ሌላ የቱሩፋት ስራ ማለትም  በገንዘቡ ፣ በእውቀቱ ወይም በጊዜው ንስኀ መግባት ያለበት ሆኖ ከተገኘ በዚህም ሊከናወን ይችላል እንጂ፤ ጠያቂያችን እንዳሉት በቀጥታ “ንስኀ በንዘብ ሊለወጥ ይችላል ወይ?” የሚለው አገላለጽ ግን ኦርቶዶክሳዊ የንስኀ አነጋገር አይደለም። ምክንያቱም በቀጥታ አንድ ሰው በሥጋ ህይወቱ በሰራው ኀጢአት ንስኀ ሲገባ ስጋውን አድክሞ ማለትም በጾም፣ በፀሎት፣ በስግደት  ፈቃደ ስጋውን አድክሞ ለፈቃደ ነፍሱ ማስገዛት ይገባዋል እንጂ በቀጥታ ገንዘብ ስላለው ብቻ ላለመስገድ   ንስኀን በገንዘብ ለመለወጥ ማሰብ እና ገንዘብ ስለሰጠን  ብቻ የኀጢአት ስርየት ማግኘት ፈፅሞ አይቻልም።
 
አንድ ክርስቲያን በላቡ የደከመበትን የድካሙ ፍሬ የሆነውን ገንዘብ ተገቢ በሆነ መንፈሳዊ ስርዓት ከቅዱሳት መፅሐፍት እንደታዘዘ የቱሩፋት ስራ ቢሰራበት በእርግጥ የፅድቅ በር ያስከፍትለታል። ምክንያቱም ብዙ ደጋግ ቅዱሳን  በገንዘባቸው የተራበ አብልተ፣ የተጠማ አጠጥተው፣ የታረዘ አልብሰው ፣ የታሰረና የታመመ ገንዘባቸውን በማውጣት ጠይቀው ፣ ቤጠቃላይ በገንዘባቸው የፅድቅ ስራ በመስራት ሰብዓዊ ዋጋን አግኝተዋል፣ ከፈጣሪያቸውም ፀጋና ክብርን ተቀዳጅተዋል። ስለዚህ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ የሚባለው ልማዳዊ አነጋገር ውስጠ ሚስጥሩ ሲታይ እውነተም  እንደ አባታችን እንደ አብርሐም እና እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን ክብር አብዝቶላቸዋል። 
ነገር ግን በንስኀ ህይወት ጋር በተያያዘ ጠያቂያችን እንደገለፁት ንስኀ የሰጡን አባት በጉልበታችን ወይም ስጋዊ አካላችንን ለእግዚአብሔር በማስገዛት ንስኀ መግባት እየቻልን በቀጥታ ገንዘብ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ “ገንዘብ አምጣ” ካሉ፥ እንደዚህ አይነት አመለካከት ልክ አይደለም ማለት ነው።   ይሁን እንጂ ልዩ የጤና ችግር ያለበት ሰው መፆም ፣ መፀለይ ወይም መስገድ እንደማይችል የአቅሙ ጉዳይ ከተረጋገጠ እዛው ባለበት ሆኖ ፈጣሪውን ይቅርታ እየለመነ እየፀለየ ሌላውን የንስኀ ህይወት በገንዘብ እንዲለወጥለት ከተደረገም ገንዘቡ በትክክለኛ መንገድ ለቤተ እግዚአብሔር እና ለተቸገሩ ድሆች የሚውል መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ግን ንስኀ ተጥሶ እና የንስኀ ቀኖናውን በገንዘብ ሽጦ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል ማለት ካህኑንም ሆነ ምእመኑን ያስጠይቃቸዋል ማለት ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ማንም ሰው ከልቡ ተፀፅቶ ንስኀ ከገባ የቅር የማይባል በደል የለም ይሄ ቤተከርስቲያንም የምታስተምረው ነው። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አቤቱ ወንድሜ ምን ያህል ቢበድለኝ ምን ያህል ይቅር ልበለው እስከ 7 ጊዜ ነውን ብሎ በጠየቀው ጊዜ እስከ 7 አልልህም 7ቱን አንድ እያልክ እስከ 70 ነው እንጂ” በማለት ለኅጢአት ይቅርታ የጊዜ እና የቁጥር ገደብ እንደሌለው አረጋግጦልናል። (ማቴ 18፥21-22) ስለዚህ በዚህ መሠረት ከኅጢያት ደዌ እስካልተፈወሱ ድረስ የንስሓ ህይወት አይቋረጥም ይቀጥላል እንጂ።
 
በመሰረቱ ከይሁዳ በላይ የበደለ የለም፥ አምላኩን በ 30 ብር ሸጠ፣ እናቱን ተገናኘ፣ አባቱን ሰለበ፤ አምላክ ግን የቀደመውን ይህን ሁሉ በደል ይቅር ብሎ ከሐዋሪያው አንዱ አደረገው ፤ ግን እንቢ ብሎ አሻፈርኝ ብሎ ፍቅረ ነዋይ አድሮበት ጌታውን በ30 ብር አሳልፎ ሰጠ። በመጨረሻ ግን ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ፤ ይሁዳ ተፀፀተና፥ የውሸት የሆነ አይነት ፀፀት ማለት ነው ፥ ‘አምላኬን በ30 ብር አሸጡኝ’ ብሎ  ዛፍ ላይ በገመድ ታንቆ ሊሞት ፈጠነ። እና ዛፉ ሊታነቅ ሲል ንስኀ ግባ ይሁዳ እያለው ዝቅ ይል ነበር ፥ ይሁዳ ግን እንቢ አለና ሸሸ ሮጠ። እንደውም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ 6 ሰዓት ተሰቅሎ በሰርክ በ11 ሰዓት በአካለ ነፍስ ፥ ነፍሳትን ሲያወጣ ያኔ ያወጣኛል ብሎ ቶሎ ሊሞት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር አልፈቀደለትም ንስኀ ግባና ተፀፀት በደልህን እመን እና እግዚአብሔርን ‘ምን አድርጌ በደልኩት”፥ አምላኬን’ ብለህ ትንሽ አብሰልስል ቢለውም በፍፁም አላደርገውም ብሎ ሮጦ  ሮጦ በስተመጨረሻ ግን ሆዱ ተዘርግፎ ነው የሞተው፤ ያቺ ሰዓት ግን አልልፋበታለች። ስለዚህ ወገኖች እኛም በቸርነተና በፍቅሩ የተሰጠን ሰዓት እንዳያልፍብን እንጂ  በንስኀ ይቅር የማይባልበት ኀጢአት የለም። 
 
ንስኀ ስንገባ ያሳዘነውን ፈጣሪ እያብሰለሰልን ከእንባ ጋር ይቅር በለኝ በደልኩህ አሳዘንኩህ ብለን አብዝተን ምርር ብለን ከልብ በመፀፀት በእንባ መታጠብ አለብን እንባ ትልቅ ነፍስን የሚያጠራ መታጠቢያ ነው። ከእንባ ሌላ ምንም የለም ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን እንባችን ነው፥ በእንባ ከታጠብን በኋላ የፈረሰችዋ ነፍስ ትሰራለች አዲስ ሰው ትሆናለች። አንዳንዴ እንደውም አዳም ከመጀመሪያ ክብሩ ይልቅ ወድቆ የተነሳው ክብር ይበልጣል ይላሉ። እና ከበደልን በኋላ ንስኀ ስንገባ የበለጠ ፍቅረ እግዚአብሔር ያድርብናል፥ ፀጋ እንታደላለን አዳም መጀመሪያ ባይበድል ኖሮ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው አይሆንም፣  ስጋውን ደሙንም አናገኝም ነበር አዳም ከበደለ በኋላ ግን ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስጋውን ቆረሶ ሰጠን ደሙን አፍስሶ ሰጠን፤ ይህ የክርስቶስን ፍቅር የተረዳበት ነውና፤ ሰው በድሎ በንስኀ ሲመለስ የበለጠ የክርስቶስን ፍቅር  መረዳት ይችላል።  ይቅር የማይባል በደል ፈፅሞ የለም። ግን በደላችንን በአግባብ በንስኀ መግባት አለብን። ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ዶሮ ሳይጮህ 3 ጊዜ ትክደኛለህ ብሎ በነገረው ትንቢት መሰረት የፈፀመውን ስህተት አስቦ ምርር ብሎ በማልቀሱ ምክንያት የሰራውን በደል በማስተሰረይ ከፈጣሪው ጋር በመታረቁ እንባን ከልብ ምርር ብሎ በማልቀስና እንባን ማፍሰስን የንስኀ አካል መሆኑን በዚህ መረዳት እንችላለን። በአንጻሩ ይሁዳ ግን ንስኀ እንዲገባ ጊዜና ተሰጥቶት በተለያየ መንገድ ቢነገረውም አሻፈረኝ አለ። ልዩነታቸው በንስኀ መግባትና ባለመግባታቸው መካከል ያለ ነው እንጂ ሁለቱም  በድለው ነበር። ስለዚህ እኛም በአግባቡ ንስኀ ከገባን ቸሩ አምላካችን ይቅር ይለናል። ንስኀ ገብተን ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን በማህተም ካረጋገጥነው ደግሞ የበለጠ በክብር ላይ ክብር በፀጋ ላይ ፀጋ እናገኛለን ፤ይሄ ነው የቤተክርስቲያን አስተምሮ። 
 
ወላዲት አምላክ በረድኤት አትለያችሁ!
ጠያቂያችን፤ ከኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምሮ አንፃር ‘ንስሃ ኀጥሁን ፃድቅ ያደርጋል’ ወይም ደግሞ ‘ዘማውን ድንግል ያደርጋል’ ሲል በዝሙት ኀጢአት የኖረን ሰው የስጋን ድንግልና ይመልሳል ማለት አይደለም። ነገር ግን ሰው በኀጢአት የኖረ በዝሙት የኖረ ሰው ተገቢነት ያለው ንስኀ ሲገባ የነፍንስ ድንግልና ይመልሳል ፥ ለክብር ለመንግስተ ሰማይ ለገነት ያበቃዋል ማለት ነው።
 
አዳም ከገነት ተባረረ ንስኀውን በአግባብ ተቀብሎ 5500 ዘመን ሲፈፀም ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደቀደመ ክብሩ እንደመለሰው ሁሉ፥ የሰው ልጅም ሲበድል ኀጢአት ሲሰራ የስጋ ድቀት፥ የስጋ ውድቀት ቢያገኘው፣ በዝሙት ቢኖር ወደቀደመ ክብሩ ወደ ገነት መንግስተ ሰማያት ይመለሳል ለማለት ካልሆነ በስተቀር፥ የስጋ ድንግልና ይመለስለታል ወይም ድንግል ነውና ከደናግል ጋር ተክሊል ይፈፀምለታል ማለት አይደለም፥ በፍጹም! ይሄ ማንም ሰው ሊጠነቀቅ ያስፈልጋል ፥ አንዴ ሰው የስጋ ድንግልናውን ካጣ በኋላ ተመልሶ ወደዛ ክብር አይመለስምና የሄን በጥንቃቄ ልናስተውለውም ይገባል።  
 
ዲያቆን ከሆነ በዝሙት የኖረ ሰው ንስኀ ገብቷል ድንግል ነውና በድንግልና የሚሰጠውን ድቁና ክህነት ይሰጣል ማለት አይደለም፥ በቃ አንዴ ካጣው ይሄ ድንግልና ተመልሶ አይገኝም፥ በፍጹም ቢያለቅስም ሊመልሰው አይችልም። ነገር ግን ኀጥኡን ያነፃል ፃድቅ ያደርጋል ለመንግስተሰማይ ያበቃል ማለት ነው።
 
ይህ የነፍስ ድንግልና ሰው፤ ሰው ንስኀ ከተቀበለ በኋላ ስጋ ደሙን ይቀበላል። የንስኀ ማሰሪያው ስጋ ደሙ ነው። ማንም ሰው ቀኖና ከተቀበለ ንስኃ ከገባ በኋላ ስጋ ደሙን የግድ መቀበል አለበት ፍፁም ስርየት ፍፁም ድህነት ለማግኘት ስጋው ደሙን መቀበል አለበት። ንስኀ ተቀብያለው ብሎ ቢቀመጥ ይሄ ፍፁም ስርየት አይደለም። የቤተክርስቲያናችን አስተምሮ አንፃር ማሰሪያውና ማህተሙ ስጋው ደሙ ነው።
 
አንድ ሰው ሀኪም ቤት ሄዶ መድሃኒት መውሰድ አለበት፤ በአንፃሩ አንድ ሰው ደግሞ አምላኩን ካስቀየመ ከቤተመቅደሱ ከበር ቁሜ አንኳካለው የሚለውን ከበዓቱ ካስወጣው በኋላ በንስኀ ተመልሶ ያፀዳውን ቤት እንደገና አምላኩን ወደ ቤቱ ማስገባት መቻል አለበት ልቦናውን ከበር ቆሞ የሚያንኳኳውን አምላክ ግባ ማለት አለበት ግባ የሚለው ደግሞ ቅዱስሥጋውን ሲበላ ቅዱስ ደሙን ሲጠጣ ነው። ስለዚህ ቅዱስ ሥገውን ቅዱስ ደሙን መቀበል ግዴታ ነው ከንስኀበኋላ። ተክሊል ተፈፅሞ ስጋ ደሙ ይቀበላል ፣ቀንዲ ተፈፅሞ ስጋ ደሙ ይቀበላል ፣ ሚስጥረ ክህነት ተፈፅሞ ስጋ ደሙ ይቀበላል፣ ጥምቀትም ተፈፅሞ ስጋ ደሙ ይቀበላል፤ ማሰሪያው የማንኛውም ምስጢራት ሁሉ ማሰሪያ ስጋው ደሙ ነው፥ማረጋገጫ ነው። ስለዚህ ይሄንን ማድረግ መቻል አለብን ምክንያቱም የንስኀ ማሰሪያው እና ወደ ቀደመው ክብር ለመመለስ ማረጋገጫ ስጋው ደሙ ነው።  ቤተክርስቲያንም ዘወትር የምታስተምረው ይህን ነው። ነገር ግን ብዙ ስው ንስኀ ይገባል ስጋደሙን ግን ይፈራል፤ ይህ ግን መሆን የለበትም። ምስጢሩን ካለመረዳት እና በረከቱን ካለማወቅ የመጣ ስለሆነ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ ድረገፅ አባላት ሁላችሁም አሁንም የምንመክረው ከዚህ በፊትም ስለ ቅዱስ ቁርባን ያስተላለፍነውን ተከታታይ ትምህርት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ በመጫን ደጋግማችሁ በማንበብ ትምህርት እንድታገኙበት በአፅንዎት አደራ እንላለን።
ጠያቂያችን የሁላችን ጠባቂ እና መጋቢ የሆነው መኀሪው እና ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር መቼም ጊዜ የማንጠፋውና ጠፍተን የማንቀረው በእሱ ምህረት እና ቸርነት እንደሆነ ማመን አለብን። ሁሉንም ኀጢአተኞች በኀጢአት ወድቀው እንዳይቀሩ ትእግስት እና ቸርነቱን አብዝቶላቸው ወደ ንስኀ እስኪመለሱ ድረስ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ቸርነትና ምህረቱን አብዝቶ የጠመመና የደበዘዘ  ማንነታቸውን ያቀናላቸዋል፣ የጨለመውን ልቦናቸውን ያበራላቸዋል፣ ፊታቸውን ወደእሱ እንዲያዞሩና ወደሱ እንዲቀርቡ ሁሉን ነገር እንዲሳካላቸው ያደርጋል። በቅዱስ መፅሐፍ የኀጢአተኛውን ሞት አልወድም ፥ መመለሱን እንጂ ተብሎ እንደተፃፈ ሁሉ አንድ ቀን በንስኀ እስከምንመለስ በትዕግስት ይጠብቀናል።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን የእርስዎን ሃሳብ እንደተረዳነው ወደ ንስኀ ለመቅረብ የህሊና ፀፀት እንዳለወት የሚያመለክት ሲሆን ነገር ግን በቁርጠኝነት ወደ አባቶች ቀርበው ንስኀ ለመግባት ፍጹም የሆነ የኀጢአት ስርየት እንዳያገኙ ጠላት ዲያብሎስ በውስጥዎ የፍርሃት መንፈስን እየላከ ኀጢአትን መሸፈን እና መሰወር ፣ ከአባቶች ርቆ መኖር ጠቃሚ መሆኑን በማስመሰል እያዘናጋና እየተቃወመዎት ስለሆነ፤ አሁንም የምናረጋግጥልዎት ካለዎት ውስጣዊ የሃይማኖት ፅናት የእግዚአብሔር መንገድ ክፍት ሆኖዋልና ተስፋዎትም እጅግ የበራ ነው። በመሆኑም ‘የመዳን ቀን አሁን ነው’ እንደተባለ ከዚህ በኋላ ለኀጢአት ቀጠሮ ሳይሰጡ የእርስዎን ችግር በምስጢር የሚያስረዷቸው እውነተኛ የቤተክርስቲያን አባት በእኛ በኩል ስለተዘጋጀልዎት በውስጥ መስመር በሚላክልዎት አድራሻ አግኝተው እንዲያናግሯቸውና ሁሌ እሚያሰጨንቀኝ ያሉትን ችግርዎን እንዲፈቱ እንመክራለን።
ጠየቂያችን ከዚህ በፊት በንስኀ ስለሚመለሱ እና ስለማይመለሱ ፀጋዎች መልዕክት ማስተላለፋችንን እናስታውሳለን።
 
1ኛ/ አንድ ሰው የክህነት ፀጋውን የሚያሳጣ ፈተና ወይም መሰናክል ቢያጋጥመው በሰራው ጥፋት ተፀጽቶ ንስኀ ቢገባ መንግስተ ሰማያትን መውረስ ይችላል እንጂ ወደ ክህነት ስራው ተመልሶ ስርዓተ ክህነትን መፈፀም አይችልም። ይህም ማለት፦ቀድሶ ማቁረብ አይችልም፣ መናዘዝ፣ መባረክ ፣ የንስኀ አባት መሆን፣ ማጥመቅ የመሳሰሉትን በክህነት ስልጣን የሚፈፀሙትን አገልግሎቶች ሁሉ ማድረግ አይችልም ማለት ነው።
 
2ኛ / የስርዓተ ተክሊልን መፈፀም የማይቻላቸው ከጋብቻ በፊት የድንግልና ህይወታቸውን ያጡ ክርስቲያኖች ሲሆኑ፤ ንስኀ ገብተው በስርዓተ ቁርባን መወሰን የሚችሉ ሲሆን በኀይማኖታቸው እና በክርስቲያናዊ ስነምግባራቸው በሚፈፅሙት የክርስትና አግልግሎት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ እንጂ በድንግልና ህይወት ውስጥ እንደሚኖሩ አማኞች ስርዓተ ተክሊልን መፈፀም ግን አይችሉም ማለት ነው።
 
አንድ ካህን በጳጳስ ወይም በሊቀጳጳስ አንብሮተ ዕድ የተሾመበትን የክህነት ፀጋ የሚያሳጣ ወይም የሚያሽር የኀጢአት ጥፋት ቢሰራ እንደማንኛውም ክርስቲያን ወደአገኘው አባት ቀርቦ የፈፀመውን ጥፋት በግልፅ ባስረዳ ጊዜ የፈፀመው ኀጢአትም ክህነትን የሚያሽር መሆኑን እና አለመሆኑን በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት ወደ ሊቃውንት ጉባኤ ቀርቦ በሚወሰነው መሰረት የሚፈፀም ይሆናል። ምክንያቱም፥ በፍትሐነገስት (በሐዋርያት ቀኖና) ከክህነት የሚያገሉ ምክንያቶች በግልጽ ተደንግገው ስለሚገኙ በዚያው መሰረት የሚፈጸም መሆኑን ያውቁ ዘንድ ጠያቂያችን ይሄንን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 
በመሰረቱ ኀጢአት እራሱን የቻለ በነፍስም በስጋም በህግ የሚያስጠይቅ በደል ወይም ወንጀል ስለሆነ ልንረሳው የምንችል አይደለም። ነገር ግን እርስዎ ይህንን ሲጠይቁን በእርግጥም ከልብዎ ተጨንቀው ወይም ለጠቅላላ እውቀት ከሆነ እንደ ቤተክርስቲያን አስተምሮ ጥቃቅን ነገሮች ካልሆኑ በስተቀር መደበኛ የንስሓ ህይወት የሚያስፈልጋቸው ጥፋታችንን መርሳትም መዘንጋትም የለብንም። በምድር ላይ ባለው ሕይወታችን ሃብታችንን ፣ ንብረታችንን፣ ኑሯችንን ፣ የሚደርስብንን በደልም ሆነ የሚያጋጥሙንን መልካም ነገሮች ሁሉ ለይተንና ተቆጣጥረን እንደምናውቅ ሁሉ ፤ የሰራናቸውንም የኀጢአት አይነቶች በስጋም በነፍስም የሚያስጠይቁ ስለሆኑ ሊረሱ አይችሉም፤ ሆኖም ጠያቂያችን እንዳሉት እንዲህ አይነት የመርሳት ነገር ወደፊት እንዳይገጥምዎ ቢቻል የመጀመርያ አቋምዎ ሊሆን የሚገባው ኀጢአት ላለመስራት ዘወትር ተግቶ መፀለይና ከጥፋትና ከኀጢአት ሁሉ መራቅ ነው። ነገር ግን አንዳንዴ ሰው ሆነን በመፈጠራችን በለበስነው ስጋ ተፈትነን የሰራነው ኀጢአት ካለ እስከሚረሳን ድረስ እንዲሁ ተኝተን እያንቀላፋን በዋዛ በፈዛዛ መክረም ስለሌለብን ወዲያውኑ ግዜ ሳንሰጥ የኀጢአት እዳችንን ስላጠፋነው ጥፋት በንስሓ ህይወት ሆነን ካሳ መክፈል አለብን ወይንም ንስሓችንን ተናዘን ከኀጢአታችን መታጠብ አለብን። የዋለው ኀጢአታችን እንዳያድርብን ያደረውም እንዳይውልብን ሳንዘናጋ በጊዜውም ያለጊዜውም በአባቶች ጥበቃ በንስኀ ህይወት መኖር ከሁሉም ክርስቲያን ይጠበቃል። 
 
ቀኖና ወይም ንስሐ የሚሰጠን በፈጸምነው ኅጥያት መጠን ተለክቶ ስለሆነ እያንዳንዱ ያጠፋነውን ጥፋት ከባድም ቢሆን ሳንፈራ፤ ቀላልም ቢሆን ሳንንቅና ሳንረሳ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለነፍሳችን እረኛ ላደረግነው ካህን መናገር እንዳለብን የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል። ንስሐ የሚሰጡን አባቶችም የኅጥያት ደረጃችን ተለይቶ ሲታወቅ በጥፋታችን መጠን ስለሆነ ንስሓ የሚሰጡን፤ ምናልባት ንስሓ ላልገቡበት ማለትም ከዚህ በፊት ንስሓ በገቡበት ጊዜ ረስተው ሳይናገሩት የቀሩት ኅጥያት ካለም እንደገና በመናገርና ቀኖና መቀበል ያስፈልጋል።
 
ስለዚህ ጠያቂያችንከዚህ ውጪ ለተዘነጋ ወይም ለተረሳ ኀጢአት በትክክልም ከእርስዎ በላይ ስለእርስዎ ሕይወት የሚያውቅ ወይም ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ውስጥዎትን ስለሚያውቀው በትክክል ከእርስዎ አይምሮ ተሰውሮ ከሆነ ወደ መምህረ ንስሓዎ ወይም ንስሓ አባትዎ ቀርበው ይህን ሃሳብ ገልፀውላቸው በጠቅላላ ከኀጢአት ስለሚፈወሱበት የንስሓ እና የምክር አገልግሎት መቀበል አለብዎት። ከምንም በላይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን ደካማነቴን እና በደለኛነቴን አንተ ስለምታውቅ እያወቅኩም ሳላውቅም የበደልኩትን በደሌን ሁሉ ከኔ ህይወት ፋቅልኝ፣ ደምስስልኝ እያሉ ፈጣሪዎትን ይቅር እንዲልዎ በፀሎት ተግተው መለመን እንደሚያስፈልግም እንመክራለን። 
 
ጠያቂያችን ትልቁ ነገር አባቶች እንዳስተማሩን እና ከስርዓተ ቤተክርስቲያንም አንፃር፥  ማንም ክርስቲያን ለፀሎት ሲቆም ውጤታማ የሚሆነው፦ ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው፥ ለፀሎት ደግሞ ስጋን ማድከም ያስፈልጋል ፥ ስጋን አድክሞ ከእግዚአብሔር ጋር ከመነጋገር በፊት ስግደት የመገዛት ምልክት ነው፣ እጅ የመስጠት ምልክት ነው፥ የአምልኮት ስግደት በጣም አስፈላጊ ነው። ስንሰግድ አጋንንት ይሸሻሉ፤ ገዳማዊያን አባቶቻችን ቅጠል እየበሉ እንደነ አቡነ ተክለኃይማኖት ግራቀኝ ጦር ተክለው ይሰግዱ ነበርና ትልቁ ነገር ለእግዚአብሔር ማቅረቢያ አጋንንትን ድል መንሻ ስግደት ነው። አጋንንትን የበለጠ ሊያቃጥለውና ሊያሸሸው የሚችለው ስግደት ብቻ ነው፤ ለመስገድ የጤና ችግር ያለበት ሰው ካልሆነ በስተቀር ስግደት ትልቁ ኀይል ትልቁ መሳሪያ አጋነንትን ማራቂያ መንፈስ ቅዱስን ማቅረቢያ ነው። እንባ ከዚያ በኋለ የሚመጣ ነው ፣ የራስን ኀጢአት እያሰቡ ፣ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ፣ የሰማዕታትን ግፍ ወይም ስለክርስቶስ የተቀበሉትን ግፍ እያሰቡ፣ የእመቤታችንን ስደት እያሰቡ ማንባት ማልቀስ ያስፈልጋል። ትልቁ ነገር ግን ከዚያ በፊትም ሊቀድም የሚገባው ፆምና ስግደት ነው ።  ከሰገድን በኋላ ነው ፀሎት የምንፀልየው የበለጠ ሰማያት ይከፈታሉ እግዚያብሔር ይቀርባል ማለት ነው፤ ስጋ ድል ይነሳል፥ ነፍስ ኃያል ትሆናለች 
ስለዚህ ጠያቂያችን ከፆም ጋር ስግደት ትልቅ ኀይል አለው ተሰሚነትም ይኖረናልና ለፀሎት ስንቆም የተወሰነ መስገድ አለብን። ከዚያ በኋላ ነው ለፀሎት እጆቻችንን ወደእግዚአብሔር መዘርጋት ያለብን። እንባ ከኋላ የሚመጣ ነው፥ ብቻውን ማልቀሱም ትርጉም የለውም፤ ስግደት አስፈላጊነው። ስግደት ለአምላክ መገዛት ነው፥ በግንባር ተደፍቶ አንተ የሁሉ ገዢ የሁሉ የበላይ ነህ ስግደት ይገባሃል በማለት የአምልኮት ስግደትን ለሥላሴ፤ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ብለን በፊታችን ወዝ እስከሚሆን ወይም ላባችን ጠብ ጠብ እስኪል ድረስ እንደ አቅማችን እንሰግዳለን ማለት ነው። ። ከዚያም በኋላ ስንፀልይ ተሰሚነት ይኖረናል፣ስጋ ይደክማል ከዚያ በኋላ ህሊናችን አይበተንም እንደውም ማልቀስ እንጀምራለን፤ የእንባ ምንጭ የሚከሰተው ሰውነታችን በስግደት ከደከመ በኋላ ነው። ሰይጣንም ስግደት ዋጋና ክብር እንዳለው ስለሚያውቅ ስግደትን አይወድምና እንግዲህ ጠያቂያችን ስግደት አባቶቻችንም የተጠቀሙበት መንፈሳዊ መሳሪያ ስለሆነ በዋናነት ተግባራዊ ቢያደርጉት መልካም እንደሆነ እንመክራለን። 
 
በተጨማሪም፦ ወደ ንስኀ ህይወት የሚቀርቡ ክርስቲያኖች ስለ ሰሩት ኀጢአታቸው ከልብ ተፀፅተው ወደ ንስኀ አባቶቻቸው ቀርበው ኀጢአታቸውን ሲናዘዙ የሚሰጣቸው የንስኀ ቀኖና እንደ ኀጢአቱ ክብደትና ቅለት በፆም ወይም በፀሎት ወይም በስግደት ወይም በሌላ የቱሩፋት ስራ ሊፈፀም ይችላል። ስለዚህ የንስኀ ቀኖና የሚሰጥበት መንገድ በፍትኀነገስት ወይም በአንቀፀ ንስኀ በተደነገገው መንፈሳዊ ስርዓት መሰረት ነው። 
ስለዚህ ጠያቂችን እርስዎ በስግደት የሚፈፀም የንስኀ ቀኖናን በእንባ ይገለፃል ወይ ብለው ወደአቀረቡት ጥያቄ ስንመጣ፤ ሁሉም የንስኀ መገለጫዎች ቢሆኑም እንኳን አንድ ተነሳሂ ክርስቲያን ስለሰራው ጥፋት ተፀፅቶ ኀጢአቱን እያሰበ እንባውን ማፍሰስም መስገድና መፆምም ሆነ የመፀለይ መንፈሳዊ ስርዓቶች አንዱ አንዱን ሊተካው ይችላል ብሎ ማሰብ ግን የሰው ሰውኛ አስተሳሰብ ነው። በመሆኑም ከዚህ በፊትም ደጋግመን እንደተናገርነው የሰራነውን የኀጢት አይነት ለንስኀ አባታችን ወይም ለመምህረ ንስኀችን ገልፀን ስንነግር ለኀጢአት አይነት የሚያስፈልጉ ቀኖና በቤተክርስቲያን ህግ መሰረት ስለሚሰጡን፥ በዚህ ላይ የግል ፍልስፍና እና አመለካከትን መጨመር አያስፈልገውም። ምክንያቱም ፆም፣ ፀሎት፣ ስግደት፣ እንባ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ የንስኀ መገለጫዎች ናቸው። ለምሳሌ ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ዶሮ ሳይጮህ 3 ጊዜ ትክደኛለህ ብሎ በነገረው ትንቢት መሰረት የፈፀመውን ስህተት አስቦ ምርር ብሎ በማልቀሱ ምክንያት የሰራውን በደል በማስተሰረይ ከፈጣሪው ጋር በመታረቁ እንባን ከልብ ምርር ብሎ በማልቀስና እንባን ማፍሰስን የንስኀ አካል መሆኑን በዚህ መረዳት እንችላለን። ነገር ግን ከላይ ለማብራራት እንደሞከርነው አንዱ አንዱን አየተካውም።
 
ይሁን እንጂ ጠያቂያችን ሌላ እኛ ያልተረዳነው እና በዚህ ማብራሪያ መልስ ያልሰጠንበ ትምክንያት ካለዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን እንደሚችሉ እየገለፅን ለጊዜው ለጥያቄዎ ምላሽ ይሆናል ያልነውን ይህን ማብራሪያ አንብበው እንዲረዱት ልከንልዎታል።