ስለ ፀሎት ጥያቄና መልስ

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ፀሎት የጥያቄና መልስ 

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሰረት ካህን የሚጸልየው ጸሎት አለ፤ ምእመናንም የሚጸልዩት የራሱ ስርአተ ጸሎት አለ። በዚህኛው ዘመን በምእመናን ዘንድ የሚታየው ትልቁ የጸሎት ከፍተት እንደ ጥንት ክርስቲያኖች ለግል ጸሎት የሚያበቃ ሃይማኖታዊ እውቀት የለንም። በእርግጥ ወደየቋንቋው የተተረጎሙ ቢሆኑም እንኳን ሰው ግን ሁልጊዜ በጸሎት የመትጋት ፕሮግራም የለውምና ያም ሆኖ የሚጸልየው ሰው ያንሳል። ጠያቂው እንዳሉት ለመጸለይ አንድ ሰው የዘወትር ጸሎት በሚለው የጸሎት ክፍል በስመ አብ ከሚለው ጀምሮ ከቻለ እስከ ጸሎተ ማርያም ይጸልያል ፤ ከዚያም ከቻለ የየዕለቱን ውዳሴ ማርያም ይጸልያል። አሁንም የሚችል ከሆነ ቅድሚያ በመስጠት የየዕለቱን መዝሙረ ዳዊት በግዕዙ ባይቻልም በአማርኛው ወይም በሌላ በሚያውቀው ቋንቋ መጸለይ ይችላል።

ከዚህ ወጪ ደግሞ የሚጸለዩ ፦ ውዳሴ አምላክ ፣ የቅዱሳን መልክ ፣ ሰይፈ ሥላሴ፣ ሰይፈ መለኮት እነዚህ እነዚህ ሁሉ አንድ ከርስቲያን ሊጸልይባቸው የሚገባ የጸሎት አይነቶች ናቸው። 

ሌለው ጠዋት ሲነሳ ፊቱን አማትቦ በያንስ አቡነ ዘበሰማያትን ሊደግምና ሰላም አውለኝ ብሎ ወደ ስራ መሄድ አለበት። ማታም ሰላም ያዋልከኝ አምላክ ሰላም አሳድረኝ ብሎ በአቡነ ዘበሰማያት አመስግኖ መተኛት አለበት። ይሄ ማንኛውም ክርስቲያን የሚገደድበት ክርስቲያናዊ ሕግ ነው።

ለመፀለይ ፍርሀት ስጋት እና ጥርጣሬ አያስፈልግም። በእምነት ሁነው ብቻ መፀለይ   ነው። የዳዊት ፀሎት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊትን ጠላቶቹን ሁሉ  በእግሩ እርግጥ በእጁ ጭብጥ አድርጎ እንዲገዛቸው ግርማውንና ሞገሱን ያጎናጽፈው የነበረው በዚህ ፀሎቱ ነው። ዘመኑ ሁሉ ታድሶለት የጠላቸውን ሁሉ ውድቀት አይቶ ግዛቱ ሁሉ ተመቻችቶለት የኖረው በዚሁ ፀሎት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን የዳዊት መዝሙር የየራሱ ክፍል ስላለው በፈለጉት ቋንቋ መዝሙረ ዳዊትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፀለይ ይችላሉ።

በየአለቱ የሚፀለይ የዳዊት መዝሙር ክፍሎች፦

 

ከመዝሙር 1 – 30 ሰኞ የሚፀለይ መዝሙር ነው          

    ”   31 – 60 ማክሰኞ የሚፀለይ መዝሙር ነው

    ”   61 – 80 ሮብ የሚፀለይ መዝሙር ነው

    ”   81 – 110 ሐሙስ የሚፀለይ መዝሙር ነው

    ”  111 – 130 አርብ የሚፀለይ መዝሙር ነው

    ”  131 – 150 ቅዳሜ የሚፀለይ መዝሙር ነው

   “151በኋላ/ፀሎት ነብያት እሁድ የሚፀለይ ነው

ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት አውራ መንገድ ወይም ድልድይ ወይም ደግሞ የስልክ መስመር ነው። ከዚህ የተነሳ ፀሎት ለመጀመር ምንም አይነት ፕሮግራም መያዝ አያስፈልግም በጊዜውም ያለጊዜውም ማንኛውም ክርስቲያን ሲነሳም ሲተኛም፣ ሲበላም ሲጠጣም፣ ሲሰራም ሲያርፍም ባጠቃላይ በነገር ሁሉ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት ቆንቋ ፀሎት ነው። 

ስለዚህ ሰይጣን ስንፍና አብዝቶብን ካልራቅን በስተቀር ፀሎት በምንችለው አቅጣጫ ሁሉ ልንጸልይ፣ እግዚአብሔርን በፀሎት ልንለምነው፣ ልናመሰግነው እና ልናመልከው ይገባል። ያው የፀሎት አቀራረብ እንደየአቅማችን ይለያያል። አብዝቶ የጸለየ እግዚአብሔርን አብዝቶ ስለወደደ ብዙ በረከት ከእግዚአብሔር ያገኛል። በጥቂቱ የጸለየ ደግሞ እግዚአብሔርን በጥቂቱ ስለወደደ ጥቂት በረከት ከእግዚአብሔር ሊያገኝ ይችላል። 

ስለዚህ ወንድሜ በዚህ ፈተና በበዛበት አለም እሾህ እና አሜኬላ በሚፈራረቁበት ህይወት እየኖርን ያለፀሎት መኖር ማለት ከህይወት የተለየ ስጋ እንዳለው አስክሬን ማለት እንሆናለን። ምክንያቱም ጨርሶ የእግዚአብሔር ረድኤትና ጥበቃ ሊለየን ይችላል።  ሌላው ባይቻልዎት  ቢያንስ እንኳን አባታችን ሆይ የሚለውን ፀሎት የሁሉም ክርስቲያን መለያ በመሆኑ በቅርብ ካሉ አባቶች ወይም ምእመናን በመጠየቅ መጸለይ እንደሚያስፈልግዎት አንመክራለን።

መልስ፦ በመካከላችን ሊባርክ የሚችል ካህን ከሌለ እኛም ክርስቲያኖች ስለሆንን በስላሴ ስም መባረክ ስላለብን በመጀመሪያ በስመ አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በማለት በትእምርተ መስቀል ፊታችንን እና ማዕዱን ከባረክን በኋላ አቡነ ዘበሰማያትን ጸልየን ጌታ ሆይ ይህን ማዕድ የህይወት ምግብ ይሆን ዘንድ ባርከህ ቀድሰው ብለን መመገብ።

 

የቦታ ችግር ከሌለብን ራሱን የቻለ ቦታ ጠዋትም ማታም ራሳችንን ለይተን የዘወትር ፀሎታችንን የምናደርስበት የተለየ ቦታ ቢኖረን መልካም ነው። ከሌለን ደግሞ የኛን ችግር ከኛ በላይ እግዚአብሔር ያውቀዋልና በዛችው በምንኖርባት ጎጇችን ውስጥ ጠዋት ከመኝታችን ተነስተን ተጣጥበን ሳሎን ላይም ቢሆን ቁመን መፀለይ ይቻላል።

ቅዱሳን ስእሎችን በምንበላበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንተኛበት ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ እንደ ጌጥ ማንጠልጠል በልማድ የመጣ እንጂ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ስርአት አይደለም። መክንያቱም ስእላቶቹ በቤተመቅደስ ውስጥ ከታቦታቱ ጋር አክብረን ስርአተ አምልኮት የምንፈፅምባቸው ስለሆኑ የተለየ ቦታ አዘጋጅተን በቤታችን አካባቢ የተለየ ቦታ ከምንተኛበትና ምግብ ከምንበላበት ውጪ የተለየ ቦታ አዘጋጅተንላቸው ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አባት አስባርከን በንፅህና ሆነን እንድንፀልይባቸው ይፈቀዳል። ቅዱሳት ስእል ግን ቅባ ቅዱስ አይቀባም። 

‘የፀሎት ውሀ’ ያሉት አነጋገሩ የቤተክርስቲያን ቋንቋ ባይሆንም ጠያቂያችን ግን ይረዱት ዘንድ ቤታችን ውስጥም ዘወትር ስንፀልይ ከቤተክርስቲያን በእቃ ያመጣነውን ፀበል ወይም ደግሞ የቤተክርስቲያን አባት ፀሎት አድርሰውበት በእቃ ያስቀመጥነውን ፀበል ልዩ ቦታ ላይ አስቀምጠን ግቢያችንን ልንረጨው እኛም ልንጠመቅበት ብንችል የእግዚአብሔር በረከት እና ቸርነት ወደ እኛ ይቀርባል። ዘወትር የሚቃወመን የሰይጣን መንፈስ ደግሞ ከእኛ እንዲርቅ ይሆናል በዚሁ መሰረት ፀበል ማለት በቤታችን ውስጥ ዘወትር የሚኖር መዝገበ ፀሎት ወይም ከቤተክርስቲያን የምናመጣው ፀበል በመባል ይታወቃል።

መጀመርያ 7ቱ ሊቃነ መላእክት ያሉትን ዝርዝራቸውን እነማን እንደሆኑ ቢገልፁ ለጥንቃቄ መልካም ነው። ያገኙት የፀሎት መፅሃፍ በአንድ ላይ የታተመ መሆኑን እና በየራሳቸው መሆኑን ቢገልፁልን መልካም ነው። ይህን ካልን በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እውቅና ሰጥታ ያሳተመቻቸው የፀሎት መፅሐፍ ሁሉ የሚከለከልበት የለምና መፀለዮት ተገቢ ስለሆነ በርትተው በፀሎቱ ይቀጥሉ። ነገር ግን በኤሌክትሮኒክስ/በኮምፒውተር የተጫኑ ማንኛውም የፀሎትም ሆነ የትምህርተ ሃይማኖት መፅሐፍ በውስጡ የምንፍቅና እንክርዳድ እንዳይኖርበት ከዋናው መፅሐፍ ጋር ማገናዘብ ያስፈልጋል። 

በአጠቃላይ ፀሎት ለስጋችንም ሆነ ለነፍሳችን ህይወት እጅግ አስፈላጊና የሰይጣን መዶሻ ስለሆነ ምንም ከልካይ ሳይኖር በጀመሩት ፀሎት እንዲቀጥሉ እንመክሮታለን። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ፀልዩ” ፣ “ይህ ክፉ መንፈስ እርኩስ ያለፆምና ፀሎት አይወጣም” ተብሎ ተፅፏልና።  

ጸሎተ ንድራ የተባለው መጽሐፍ  አብዛኛው በእጅ የተጻፈ ሲሆን በሕትመት ላይ የዋለም  ይገኝበታል       አገልግሎቱን በሚመለከት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት አንደ ሌሎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት ለጸሎትም ሆነ  ለሌላ አገልግሎት እንዲውል አልተፈቀደም። የመጽሐፉን ምስጢራዊ ይዘት ለማወቅ ከተፈለገ  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥብርያዶስ ባሕር ሴት መሥላ  የተገለጠችውን ክፉ መንፈስ በሚያስፈራ ሁኔታ ለ12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት እንደ አሳያቸውና በሰውና በእንስሳት  ላይ የምታደርሰውን ጥፋትም እንደ ገለጸላቸው።በውስጡ ያለው ቃሉም  የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ምስጢራዊ ስሞች ናቸው (ስሙ ሕቡአ ይባላሉ)። ስለመጽሐፉ ጥቅም በሚመለከት  በሴት አምሳል ለሐዋርያቱ ያሳያቸው ክፉ መንፈስ  በሰውና በእንስሳት ላይ አድራ ጥፋት እንዳታደርስ  የሚጸለይ ነው ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው ካህናትም ሆኑ ምእመናን በጸሎትነት እንዲጠቀሙበት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አልተፈቀደም።

ጠያቂያችን እንዳሉት ሰርክ ወይም ከ 11 ሰዓት ጀምሮ የምንፀልየው ፀሎት የሚቀጥለው እለት ዋዜማ ስለሆነ የዋልንበትን እለት ሳይሆን አድረን የምናገኘውን እለት ፀሎት እንፀልያለን ማለት ነው። ውዳሴ ማርያም ብናደርስ ወይም ሌላ ስርዓተ እግዚአብሔር የምናደርስ ከሆነ የቀጣዩን እለት ነው። ለምሳሌ ቅዳሜ የምናከብረው በአል ቢኖረን በዋዜማው አርብ ማታ የሚደገው የዋዜማው ቃለ እግዚአብሔር ቅዳሜ የምናከብረውን በአል በተመለከተ ነው። እንደገና አርብ ማታ ከ 11 ጀምሮ የምናደርሰው የማህበርም ሆነ የግል ፀሎት ካለ የቅዳሜውን እለት ነው የምንፀልየው ማለት ነው። ሌላው በ 24 ሰአታት ውስጥ አንድ ክርስቲያን ወይም አንድ ኦርቶዶክሳዊ የሚፀልያቸውን የፀሎት ጊዜያት እና የፀሎት አይነቶች ሰፋ በማድረግ በቀጣይነት እንዲደርሳችሁ እናደርጋለንና በትእግስት ይጠብቁን ዘንድ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

የፀሎት ዋናው ጥቅም በእምነት ሁነን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው። ስለዚህ የምንጸልየውን የፀሎት ንባብ ሁሉንም ትርጓሜውን እና ምስጢሩን ላናውቅ እንችላለን። ምክንያቱም ለፀሎት የምንጠቀመው የእግዚአብሔር ቃል ሰማያዊውን እና ምድራዊውን ምስጢር የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ የእግዚአብሔር ባህሪይ የሚገለጽባቸው ስሞች ረቂቅ እና ጥልቅ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉም ሰው ትርጓሜያቸውን ሊያውቅ ባይችልም እግዚአብሔር ምስጢሩን እና ጥቡን የገለፀላቸው ቅዱሳን አባቶቻችን የተጠቀሙበት የፀሎት ክፍል ሰለሆነ ሁላችንም በፍፁም ልቦናችን ለምነን ብንፀልየው ፍፁም ዋጋ ያስገኛል። ሰለዚህ እያንዳንዱ የፀሎት መፅሐፍ የራሱ የሆነ የሚያሰጠው ፀጋ ስላለ ማንኛውም ክርስትያን በእምነት ሆኖ መፀለይ እንጂ ትርጓሜውን ወይም ቋንቋውን ያለመቻላችን ሁኔታ በእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን በረከት አያስቀርም። በእርግጥ ይበልጥ የምንፀልየውን የእግዚአብሔር ቃል ምስጢሩን ለመረዳት በግእዝም በተለያየ ቆንቋ ስንፀልይ መስጢሩን ብናውቀው የበለጠ ደስተኛ እንድንሆን ያደርጋል። ባጠቃላይ ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት ትርጉሙንም በውል ባያውቁትም በግእዝ ቢፀልዩ የሚያገኙትን በረከት አያስቀርብዎትም ። በአማርኛም ሆነ በሌላ ቆንቋ መፀለይ ሲፈልጉም ዋናው ምስጢር በእምነት ሆነው መፀለይ ስለሆነ በፈለጉት ቆንቋ ፍፁም ክርስቲያናዊነት ባለው ስርአት ቢፀልዩ እግዚአብሔር አምላክ የለመኑትን መንፈሳዊ ዋጋ እንዲያገኙ ፈቃዱ ነው።

መልስ።፦  ጠያቂያችን በስልክዎ ያስጫኑት የፀሎት መፅሐፍ በመሆኑ ካለብዎት የግል ሁኔታ በዋናነት የተለመደውን ፀሎት ማድረስዎ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝዎት ቀጥተኛ መንገድ ስለሆነ በፀሎት መትጋትና ማመን ነው። በእርግጥ የፀሎት መፅሐፍትን በመጠቀም የምንፀልየው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ሳይሆን መፅሐፍቱ ራሱ ቅዱሳን ስእላት በውስጣቸው ስላሉ በወረቀቱም ይሁን በብራና የተፃፈው የእግዚአብሔር ቃልም ልዩ ምስጢር ስላለው ምክንያቱም መፅሐፍ የእግዚአብሔር ማደርያ ስለሆነ እንደ ታቦትም ስለሚቆጠር ፀሎት ስንጀምርም ስንጨርስም እንሳለመዋለን፣ ሰውነታችንን እና ከአካላችን የሚሰማን ደዌ ካለ እንደ መስቀል እንተሻሸዋለን። ቤተሰቦቻችንንም በንፅህና ሆነው ከቀረቡ የፀሎቱን መፅሐፍ እናሳልማቸዋለን በመፅሐፉም ሰውነታቸውን እንዳብሳቸዋለን። በዚህ አገልግሎት በሞባይል እና በኮምፒውተር ከምንፀልየው ይልቅ ጥሙና በረከቱ በመፅሐፍ የምንፀልየው ፀሎት ይበልጣል ማለት ነው።  
ይሁን እንጂ የፀሎት መፅሐፉን ይዞ ለመንቀሳቀስ ካላመቸን ወይም በቅርብ ለማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ ካለ እንደተባለው በሞባይላችን ውስጥ ያስጫነውን ፀሎት መፀለይ ይቻላል፤ እንደጥፋትም እንደነውርም የሚያስቆጥርብን ነገር የለምና ጠያቂያችን በዚህ እንዲረዱት  ይህን መልእክት ልከንልዎታል።
መልስ ፦ መፍትሔ ስራይ የሚለው ቃል በተለመደ አነጋገር አንዳንድ ባህላዊ ጥበብ እንችላለን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች በእፅዋት ወይም በውሀ ወይም ለዚሁ ብለው ባዘጋጁት ሌላ ነገር አስማት እየደገሙ መንፈስ ያደረበትን ሰው እናድናለን በማለት የሚያደርጉት የፀሎት አይነት ነው። እንዲህ አይነት ሰዎች የሚያደርጉት የመፍትሔ ስራይ ድግምት በቤተክርስቲያን ቀኖና ፈፅሞ የተከለከለ ነው። ምክንያቱም ይህ የሚደግሙት አስማት አንዳንዱ ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ቃል የሚጠራ ሲሆን አብዛኛው ደግሞ የአጋንንትን ስም የሚጠራ ስለሆነ ይህ አይነት ፀሎት እርኩስ መንፈስን የሚያርቅ ሳይሆን ለጊዜው ሰይጣን ጥበበኛ ስለሆነ በታማሚው ሰው ላይ የማስመሰል ምልክት ቢያሳይም እንኳን ነገር ግን በታማሚው ላይ ያለውን የተለመደ ቁራኝነቱን አያስለቅቅም። እንዲያውም በስውር ያደረበትን ሰው እንዳይለቅ ከደሙና ከስጋው ጋር ተቆራኝቶ እንዲኖር የበለጠ ያግዘዋል። አይሁድ እና ፈሪሳዊያን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሰራው አስደናቂ ተአምራትን አይተው ከተደነቁ በኋላ “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልኾነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። ኢየሱስ ግን ሃሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ርስ በርሷ የምትለያይ መንግሥት ዅላ ትጠፋለች፥ርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ዅሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከኾነ፥ርስ በርሱ ተለያየ፥እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች፧ እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከኾንኹ፥ልጆቻችኹ በማን ያወጧቸዋል” (ማቴ 12፥24-26) በማለት የአጋንንትን ስም በሚጠራ የአስማት ፀሎት አጋንንትን ማውጣት እንደማይቻል አስረግጦ ነግሮናልና በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት መፍትሔ ስራይ ማለት ትክክለኛው ቋንቋ ሊሆን የሚችለው 1ኛ ወንጌላዊ ዮሐንስን 2ኛ ደግሞ የቅዱሳን መላእክት ድርሳናትን ፣ 3ኛ የቅዱሳን ፃድቃን ገድላቸውን፣ 4ኛ የአባቶቻችን ታላቅ የተአምራት ኃይል የሚያደርጉባቸው የፀሎት መፅሐፍትን በመፀለይ፣ በእምነቱ፣ በቅዱስ መስቀሉ፣ በፀበሉ፣ በቅብዓ ቅዱሱ፣ የታመሙትን ልዩ ልዩ ደዌ ያደረባቸውን ህሙማንን ሲያጠምቋቸው በላያቸው ያለው እርኩስ መንፈስ በእግዚአብሔር ቃል ሲወገዝ እና ሲገሰፅ ቃሉ ስለሚያስረውና ስለሚያቃጥለው ከታማሚው ሰው ወጥቶ ይሰደዳል ማለት ነው።   ይህም የሚሆነው በሽተኛውም ንፅህናውን ጠብቆ በፆም በፀሎት ተወስኖ ልክ እንደ መፃጉ ለመዳን ትወዳለህን ተብሎ እንደተጠየቀው ለመዳን እንደሚችል በማመን ወደ ካህኑ በቀረበ ግዜ ካህኑም በፍፁም እምነት እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት የእግዚአብሔር ሃይል በሱ ላይ አድሮ በሽተኛውን እንደሚፈውስ ስርዓቱን ሲያከናውን በሰውየው ላይ ያደረው የሰይጣን ሃይል ፈፅሞ ከታማሚው እንዲለይ ያደርገዋል። ስለዚህ በመንፈሳዊ ቋንቋ ትክክለኛው መፍትሔ ስራይ ማለት ይህ ነው። (ማቴ 17፥16 -21) 
ስለዚህ ጠያቂያችን ከላይ በዝርዝር ለማስረዳት በሞከርነው አይነት የተፈፀመ ጥምቀት ካልሆነ የእርኩስ መንፈስ ስም የሚጠራበት የአስማት መንፈስ ስም የሚጠራበት ከሆነ የተፈፀመልዎ ጥምቀት ትክክል ስላለሆነ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው ሁል ጊዜ ክርስቲያኖች በሚጠመቁበት ቦታ ለአንድ ቀንም ቢሆን ይጠመቁ። ለንስሓ አባትዎም እንዲህ አይነት ስህተት ፈፅሜያለሁ በማለት ይንገሩዋቸውና እግዚአብሔር ይፈታህ እንዲሉዎት ይህን መልዕክት ልከንልዎታል። 
ከዚሁ ጋር ልዩ ልዩ የፀረ መናፍስት ፀሎት መፃህፍት አሉ መፀለይ እችላለሁ ወይ ብለው ለጠየቁን በግልፅ ስማቸውን ለይተው በውስጥ መስመር ቢልኩልን ልናስረዳዎት እንችላለን።
መልስ፦  ኪዳን ማለት በዋናነት ከቅዳሴ በፊት ዘወትር ጠዋት ጠዋት በቤተክርስቲያን ውስጥ ካህናት የሚያደርሱት መደበኛ የኪዳን ፀሎት ነው። ፀሎተ ኪዳን ተብሎ የሚታወቀው ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤ በኋላ ለ 40 ቀናት ለቅዱሳን ሐዋርያት ያስተማራቸውና የገለፀላቸው እጅግ ረቂቅና ጥልቅ ሚስጥር ያለው የፀሎት ክፍል ነው። ለምሳሌ ከላይ እንደገለፅነው ጠዋት ጠዋት ከቅዳሴ በፊት ካህናት የሚያደርሱት ዘጠኙ ኪዳናት ፦ ቅዳሴ እግዚ፣ ትምህርተ ህቡአት፣ እግዚአብሔር ብርሃናት ወዘተ በውስጣቸው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰራቸውን ተአምራትና የሱን መለኮታዊ ስራ የያዙ ስለሆነ ካህናት አባቶቻችን በዚህ ፀሎት ብዙ  ሃይል ያደርጋሉ። ስለዚህ ጠያቂያችን ፀሎተ ኪዳን ሰፋ ያለ ትምህርት ቢኖረውም ባጭሩ ለጥያቄዎ ምላሽ ይሆን ዘንድ ይህን መልዕክት ልከንልዎታል።
 
መልስ፦  አስማተ መለኮት ማለት የመለኮት ስሞች የተገለፁበት መፅሐፍ ማለት ነው። ነገር ግን ጠያቂያችን ዝቅ ብለው ‘ፀሎተ በእንተ ዐይነጥላ መፍትሔ ሃብት ወመስተፋቅር ወግርማሞገስ’ የሚል ጸሎት እንዳለበትና እንዲሁም የሊቃነ መላዕክት ድርሳናትም እንዳሉበት ገልፀውልናል። በእንዲህ አይነት ሁኔታ የታተሙ መፅሐፍት ለንግድ የተዘጋጁና ቤተክርስቲያን እውቅና ያልሰጠቻቸው የአንዳንድ ደብተራ የግል አስማት የተፃፉበት ሆኖ አልፎ አልፎ ደግሞ ንፁህ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል የሚገልጽ፤ እንዲሁም ደግሞ የመናፍስትንም ስም የሚጠቅስ ተደርጎ የሚታተም የማወናበጃ የመፅሐፍ አይነት አለ። ስለዚህ የዚህን አይነት መፅሓፍ መሆኑን አይተን ለመረዳት እንዲያመቸንና የሚፈቀድ እና የማይፈቀድ የፀሎት መፅሐፍ መሆኑንም ለማስረዳት እንድንችል ጠያቂያችን በውስጥ መስመር ደውለው ስለመፅሐፉ ተጨማሪ መረጃ ቢሰጡን መፅሓፉን ካለበት ቦታ ላይ አስመጥተን ልናጣራው እንችላለን።
 
ነገር ግን ጠያቂያችንም ሆኑ ሌሎቹ የፕሮግራማችን ተከታታዮች በቤተክርስቲያን ቀኖና የተፈቀደና፤ ካህናትም ሆኑ ምእመናን ሁል ግዜ የሚጠቀሙባቸውን የጸሎት መፅሐፎችን ብቻ መጠቀም አለባቸው። እነሱን የማያውቅ ሰው ካለ ዝርዝራቸውን ልንልክ እንችላለን። ከዚህ ውጭ ግን ያልተለመዱና የማወናበጃ ሃሳብ ያላቸውን ለንግድ የተዘጋጁ መፅሐፍት በአንዳንድ ሰወች ግፊት እንዲህ ትሆናለህ እንዲያ ትሆናለህ በሚል ስብከት በስሜት ተነሳስተን መፀለይ የለብንም።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን በስንዴ ማሳ ላይ የበቀለ እንክርዳድ እንዳለ ሁሉ እውነተኛ በሆኑ የፀሎት መፅሐፍት ውስጥም ምእመናንን በስህተት የሚያሰናክሉ የመናፍቃን እና የሃሰተኞች ሰዎች የስህተት እና የጥንቆላ መፅሐፍት ስላሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል በማለት ይህችን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 
መልስ፦ ፀሎት ስንጀምር መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ማማተብ ይገባናል። ምክንያቱም በትምእርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን ፀሎት ከመጀመራችን በፊት የምናማትበው በሃሳብ የሚቃወመንን እና ከፈጣሪያችን ጋር በፀሎት እንዳንገናኝ የሚፈታተነንን እርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሃይል ቀጥቅጠን ከእግራችን ስር ለመጣል ወይም ፈፅሞ ከእኛ እንዲርቅ ለማድረግ ነው። የጨለማ ሃሳብ ተገፎ ከእኛ እንዲርቅ እና በብርሃን ለመመላለስ እንድንችል መላ ሰውነታችንን እና ፊታችንን ስናማትብ ከላይ ወደታች ከግራ ወደቀኝ ማማተብ ይገባል። ስልጣነ ክህነት ያላቸው አባቶች በያዙት መስቀል ሲያማትቡ ምእመናን ደግሞ ከአውራ ጣት ቀጥሎ ያሉትን የጣቶች ክፍል በመስቀል ቅርፅ በማመሳቀል ማማተብ ይገባናል።  የዚህ ምሳሌና መንፈሳዊ ምስጢርም ከላይ ወደታች ስናማትብ ቀዳማዊ ቃል አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሰው ይሆን ዘንድ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ለማመልከት ነው። ከግራ ወደ ቀኝ የምናማትብበት ምክንያት ደግሞ የሰውን ልጅ ለማዳን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ስጋን በመዋሃድ ሰው የሆነው አምላክ ስለኛ ኀጢአት ህማማተ መስቀሉን ተቀብሎ በምልዕተ መስቀል ተሰቅሎ ሞቶ እኛን ከሞት ወደ ህይወት ከአሳር ወደ ክብር ከሲኦል ወደ ገነት አሸጋግሮ ወደ ቀደመ ክብራችን የመለሰበትን ምስጢር ምሳሌ ለመግለፅ ነው። በቀኝ ገነት ትመሰላለች ፤ ግራ ደግሞ የሲኦል ምሳሌ ነው። (ፍትሓ ነገስት አንቀፅ 14) 
 
በትምእርተ መስቀል የምናማትብባቸው ግዜያትም፦ 
– ፀሎት ለመጸለይ ስንፈልግ፣ 
– በምንፀልየው የጸሎት ቃል ውስጥ ስለመስቀል የሚያወሳ ቃል ላይ ስንደርስ፣ 
– በምንበላው እና በምንጠጣው ምግቦች ላይ፣ 
– በምንለብሰው ልብሳችን ላይ፣ 
– ስንተኛ እና ከመኝታ ስንነሳ፣ 
– ማንኛውንም መንፈሳዊ እና ስጋዊ ስራችንን ከመጀመራችን በፊት በትምእርተ መስቀል ማማተብ የገባናል። 
 
1.2 ስንፀልይ በፍፁም እምነት ሁነን መፀለይ ይገባናል። የምናቀርበው ፀሎት ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስ እና እኛም የምንፈልገውን በጎ ምላሽ በፈጣሪ ዘነድ ለማግኘት እንድንችል በፍጹም ልብ እና በፍፁም እምነት ውስጥ ሆነን ልንፀልይ ይገባናል።  
 
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ “አምናችሁ በፀሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” (ማቴ 22፥21) 
 
አሁንም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ፤ ሳይታክቱ ዘወትር ሊፀልዩ እንደሚገባቸው ይህንን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው “ አንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውን የማያፍር አንድ ዳኛ እንደነበረ በመግለፅ ወደዚህ ዳኛም እየቀረበች እለት እለት ዳኝነት የምትጠይቅ አቤት የምትል መበለት እንደነበረችና ያቺ መበለት ወይም ደሃ ሴት ሳትሰለችና ሳትታከት ዘወትር ዳኛውን ፍረድልኝ እያለች ስለጨቀጨቀችው ጥያቄዋን ተቀብሎ ፍርድ እንደሰጣት በሉቃስ ወንጌል ተመዝግቧል። (ሉቃ18፥1-6) 
 
1.3 በንፁህ ልቦና እንዲሁም በቅን መንፈስ ሆኖ መፀለይ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል እንደ ግርዶሽ የሆነውን ክፉ ስራችንን ገርስሶት እግዚአብሔርን ለማየት ስለሚያስችለን ልቦናችንን ንፁህ ማድረግ አለብን። ስለዚህም “የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መካከል እንደወደቀ ዘር ነው” ተብሎ በመፅሐፈ መነኮሳትና በሌሎችም መፅሐፍት ተመዝግ ይገኛል። 
 
1.4 ሃሳብን ሰብስቦ በአንድ ልብ ተወስኖ መፀለይ ይገባል። ቅዱሳን ሐዋርያት እና የመጀመሪያዎቹ የጌታ ተከታዮች (120 ቤተሰቦች) ከጌታ ትንሳኤና እርገት በኋላ በክርስትና አላማቸው ፀንተው በአንድ ቦታ ሆነው ሲፀልዩ ባሉበት ግዜ፤ ከሞቱ በፊት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሚያጽናናቸውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው በገለፀላቸው መለኮታዊ ቃል መሰረት በፀሎት እየተጉ እያሉ መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል። (የሐዋ 2፥1-4)  
 
1.5 በፈሪሃ እግዚአብሔር ሁነን እግዚአብሔርን በመፍራት ህይወታችንን በንስሓ አድሰን መፀለይ ይገባናል። ምክንያቱም ሰው የእምነቱ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ማስቀደም አለበት፤ ቀጥሎም በፀሎት እግዚአብሔርን ለማመስገን ወይም ደግሞ የፈለገውን ለመጠየቅ ሰውነቱን እና መላ ህይወቱን በንስሓ ህይወት መቀደስ አለበት። በዚህ አይነት የምንፀልየው ጸሎት እድሜያችንን ያረዝማል ብዙ በረከትም ያሰጣል። 
 
ንጉሱ ሕዝቂያስ በፈጣሪ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለሰራው ኀጢአቱ ከልቡ ተፀፅቶ እያዘነና እያለቀሰ በመፀለዩ በእድሜው ላይ 15 አመት ተጨምሮለታል። (ሁለተኛ ነገስት 20፥1-8)  
 
1.6 ስንፀልይ ቀጥ ብለን በመቆም መፀለይ ይገባናል። በጸሎት ግዜ ሰማይ እና ምድርን የፈጠረ አምላክ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ አምላክ ዘላለማዊ ንጉስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ስም ስንጠራ ከምንም በላይ በሰውነታችን ልንገዛለት ስለሚያስፈልግ እና በንጉሱ ፊትም ስንቆም ክብር ይገባዋልና ቁመን መፀለይ አለብን። ነብዩ የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት በማለዳ “አቤቱ ወዳንተ ፀልያለሁና በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፤ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ እጠብቃለሁም” በማለት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ በማለዳ በፀሎት ፈጣሪውን እንዳመሰገነ እና የእግዚአብሔርን ቸርነት እንደጠየቀ ይናገራል። (መዝ 5፥3) 
 
1.7 ፊታችንን ወደ ምስራቅ አዙረን መፀለይ ይገባናል። ሁልግዜም ምስራቅ የጌታ መገለጫ ስለሆነች መልካም ነገሮች ሁሉ እንደ ፀሃይ ጮራ ከምስራቅ ስለሚወጡ ወይም ስለሚገለፁ ማንኛውም ካህንም ሆነ ምእመን ሲፀልይ ወደ ምስራቅ ቆሞ መሆን ይገባዋል። ምስራቅ የጌታ ምሳሌ ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልክት ነው። ወደ ምስራቅ ተመልከቱ ተብሎ ተጽፏልና። 
 
በዚህም ፊታችንን ወደ ምስራቅ ማድረግ እንደሚገባን በፍትህ መንፈሳዊ ወስነዋል። 
እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመንም ይሄንን አለም ሊሰበስብ እኛንም በዳግም ትንሳኤ ሊጠራን ከምስራቅ እንደሚመጣ ቅዱስ መፅሐፍ ስለሚነግረን ወደ ምስራቅ ዞረን መፀለይ የሚገባን ከዚህ የተነሳ ነው። 
 
1.8 በፀሎት ግዜ መስገድ ይገባል። ፀሎት ስንጀምርና ስንጨርስም በምንፀልየው የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለስግደት ከሚናገርበት ቦታ ወይም አንቀፅ ላይ ስንደርስ መስገድ ይገባናል (ፍትሓነገስት አንቀጽ 14) 
 
እንኳንስ ሰማያዊ ንጉስ ለሆነው ለፈጣሪያችን ይቅርና በዚህ ምድር ላይ ላሉ ባለስልጣናትና ታላላቅ ሰዎች እንሰግዳለን። በዚህ በህሊና ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት መስመር ፀሎት ስለሆነ በአንተ ፊት የማቀርበውን ፀሎቴን ከኔ ደካማ ባህሪ እና ከማደርገው ኅጢአት የተነሰ የማቀርበውን ጸሎቴን አትናቅብኝ (ቸል አትበልብኝ) በማለት እየወደቅን እየተነሳን ልንፀልይ ስለሚገባን ነው።
 
 
 
አይናችንን ወደ ሰማይ በማቅናት መፀለይ ይገባናል። ምክንያቱም እኛ እንደ አህዛብ ወይም እንደ መናፍቃን በቀጲፀ ተስፋ (ተስፋ በመቁረጥ) የምንኖር ሳይሆን በዳግም ትንሳኤ ቀና ብለን ከመቃብር በላይ ተነስተን ለኛ የተዘጋቸውን ሰማያዊ ርስት እንደምንወርስ ተስፋ ያለን ስለሆነና በፈጣሪ ዘንድ ቀና ብለን ለመሄድ የሚያስችለን ሃይማኖትና ምግባር መሆኑን ለማረጋገጥ አይኖቻችን በትሁት ሰብና በአንቃእዳዎ ልቦና ሆነን አይናችንን አስፍተን መፀለይ ይገባናል። ለዚህም ዋና ማስረጃችን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አይኖቹን ወደ ሰማይ በማቅናት እንደፀለየ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ይነግረናል። (ዮሐ11፥4)  
 
1.9 ስለራሳችን እና ስለሌሎችም ወገኖች መፀለይ ይገባናል። እኛ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች መፀለይ ያለብን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለሌሎቹ ወገኖቻችን፦ 
 
– በተለያየ ፈተና ላሉ  
– በአልጋ ቁራኛ ለሚገኙ 
– በእስር ቤት ለሚኖሩ 
– በዳር ድንበር የአገርን ሰላም ለማስከበር በውትድርና ለሚኖሩ  
– በባእድ አገር ለሚኖሩ 
 
በአጠቃላይ በተለያየ ፈተና ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖቻችን እና ለአገርም ጭምር መፀለይ ይገባናል። ነብዩ ኤርምያስ ስለአገር መፀለይ እንደሚገባ ሲናገር “በእርሷ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርሷ ላስማረክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ ስለ እርሷም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ። (ት.ኤር 29፥7)
 
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም ስለሌሎች መፀለይ እንደሚገባን “ትድኑ ዘንድ እያንዳንዳችሁ ለሌሎቻችሁ ፀልዩ” በማለት መክሮ አስተምሯልና። (ያዕ 5፥16) ምክንያቱም አንዱ ስለሌላው የሚፀልየው ፀሎት ታላቅ ሃይል ያደርል። ይሄ ይቅርና የሰው ልጅ ስለ አራዊቱ ስለ እንስሳቱ ስለ አዝሪቱ ስለ አትክልቱ ስለ ፈሳሹ ወንዝ ስለ ዝናባቱ ስለ መሳሰሉት ብዙሃንን እና ጥቃቅንን ፍጥረት ሁሉ እንድንፀልይ የእግዚአብሔር ቃል ያዘናል። 
መልስ፦  ወደ ፈጣሪ የምናቀርባቸው ፀሎቶች በ2 ከፍለን እንመለከታቸዋለን፦
 
1. የረቀቀውን የሃይማኖት ሚስጢር የሚያውቁ እና ጥልቅ የሆነ የሃይማኖት እውቀት ያላቸው የቤተክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት የሚፀልዩት ፀሎት ንባቡና ትርጉሙ የረቀቀና የጠለቀ ስለሆነ እነሱ ብቻ የሚፀልዩት ፀሎት ነው።
 
2. ምእመናን ሁሉ የሚፀልዩት ፀሎት በየደረጃቸው ቢፀልዩት የማይከብድ እና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት የጸሎት አይነት ነው። ካህናትም ሆኑ ምእመናን የሚፀልዯቸው የፀሎት መፃህፍትም፦
 
– የ150 መዝሙረ ዳዊት እና 15 ነብያት እና መሃልየ ሰለሞን እነዚህ ከሰኞ እስከ እሁድ የሚፀለዩ የፀሎት ክፍል ናቸው 
– የ7 ቀን ውዳሴ ማርያምና አንቀፀብርሃን እንዲሁም መልክአ ማርያምና መልክአ እየሱስ 
– ውዳሴ አምላክና ሰኔ ሎለጎታ 
– ሰይፈ ሥላሴና ሰይፈ መለኮት  
– የፃድቃንና የሰማእታት መልካቸውና ገድላቸው  
– የቅዱሳን መላእክት  መልካቸውና ድርሳናቸው 
– ወንጌለ ዮሐንስ 
ሌሎችም ብዙ የፀሎት አይነት አሉ። በገዳማት ውስጥ የሚኖሩ መናኞች እና አንዳንድም እግዚአብሔር ፀጋውን ያበዛላቸው በከተማም ሆነ በተለያየ ቦታ እየኖሩ አብዝተው የሚፀልዩ የእግዚአብሔር ሰዎች አሉ።  
 
ፀሎት ለማድረግ ወይም ለመፀለይ ፈፅሞ ማመን እና ህሊናን ንፁህ ማድረግ እንጂ የእውቀት ብዛት እና የፀሎት ብዛት ለፀሎቱ ተቀባይነት ወይም ቅቡል መሆን ዋናው ምክንያት ላይሆን ይችላል። በሃይማኖት ውስጥ ያሉትን የፀሎት መፅሐፍት በቀላሉ ለመረዳትና በቂ እውቀት የሌላቸው ምእመናን ከሆኑ ቢያንስ የክርስቲያን አጭር ፀሎት አቡነ ዘበሰማያት፣ ፀሎተ ሃይማኖት፣ ፀሎተ እግዚተነ ማርያምን አጥንተውም ቢሆን ከንስሓ አባት ወይም በቅርብ ከሚያገኟቸው የቤተክርስቲያን አባቶች በመጠየቅ አጥንቶ መፀለይ ያስፈልጋል። 
 
ሲጀመር አንድ ክርስቲያን ለስጋው ምግብ ልብስ እንዲሁም መጠለያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለነፍስም ከሚያስፈልጓት የነፍስ ተግባራት አንዱ እና ዋናኛው ፀሎት ስለሆነ ለሁሉም ጉዟችን በር ከፋችና በጎውንና ክፉውን ነገር ለማየትም የምንችልበት ብርሃን ስለሆነ ፀሎት በክርስቲያናዊ ህይወት ላይ እጅግ አስፈላጊ ነው። የግዜ እጥረት ያለባቸው ሰዎች እንደ ስጋዊ ምክንያት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚያውቀው ከአቅም በላይ የሆነ ፈተና ሲያጋጥመን ከዚህ በላይ የተገለፁትን አጫጭር ፀሎቶች ፀልየን ፈጣሪያችንን በወጣንበት በገባንበት ተከተለን ብለን ከእሱጋ ያለንን ግንኙነት አጠንክረን ወደ ስራችን ብንገባ ሁሉም ነገር ይሳካልናል ማለት ነው። 
 
🚥🚥🚥🚥🔷🚥🚥🚥🚥

👉ጥያቄ፦ እንዴት ብለን መፀለይ ይገባናል? ( እንዴት መፀለይ እንዳለብን?)
መልስ፦ ፀሎት የሚቀርብበት የራሱ ስርዓት እና ቀኖናዊ ትውፊት አለው። መፀለይ ስላሰብን ብቻ ቦታና ግዜን ሳንወስን እኛም ራሳችን ሰባዊ አካላችን ሳንሰበስብና ለፀሎት ሳናዘጋጅ ከሜዳ ተነስተን ብናነበንብ ፀሎታችን የአህዛብ ፀሎት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ፀሎት፦
 
– በቅጥረ ቤተክርስቲያን ሆነን መፀለይ ይገባናል 
– በምንኖርበት ቤት ውስጥም ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ የፀሎት ቦታ ላይ ሆነን መፀለይ አለብን 
– በግል ሆነን እና በማህበር ሆነን ስንፀልይ በቀስታ ወይም በለሆሳ (በምላስ) የሚፀለይ ፀሎት ልንፀልይ እንችላለን። የቤተክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት በንባብ እና በዜማ ሊፀልዩ ይችላሉ። 
-እግዚአብሔር አምላክ የእለት እለት የግል ህይወታችንን እና የማህበር ስራችንን ከመጀመራችን በፊት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ ይኖርብናል 
– ለመንፈሳዊ አገልግሎት የታነፀ ቤተክርስቲያን አለ፣ ሌሎችም ለመንፈሳዊ ተግባር የሚውሉ የተገነቡ የልማት ስራዎች ካሉ በአባቶቻችን በፀሎት ተባርከው አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በግል ወጥቶና ወርዶ ያተረፈውን የእጁን ስራ እግዚአብሔር እንዲባርክለት የሚሰራበትን የመኖርያ ቤትም ቢሆን የንግድ ቤትም ቢሆን መኪናም ቢሆን ፋብሪካም ቢሆን ኢንዱስትሪም ቢሆን በመሬት ላይ የምናለማውን ማንኛውም ተግባር ይሁን በፀሎት ልናስባርክና ልንገለገልበት ይገባል (2ኛ ዜና 7፥15)
 
-ጠዋት በነግህ ወይም በጠዋት የምንፀልየው ፀሎት ምግብ ሳንበላ እና ሰውነታችንን ከገቢረ ኅጢአት ጠብቀን ሊሆን ይገባል፣
 
-ከ9 ሰአት በኋላ የምናቀርበው የሰርክ ጸሎት ከሌላ የኀጢአት ስራ ተጠብቀን ፀሎት ልንፀልይ እንችላለን።
 
-ተበልቶ የማይፀለየው፦ የቅዳሴ ፀሎት እና አባቶች በሚስጢረ ቤተክርስቲያን ቤተ መቅደስ የሚያከናውኑት የፀሎት ስርዓት ምግብ ሳይበላ የሚጸለይ የፀሎት ክፍል ነው
 
በአጠቃላይ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ ፕሮግራም ተከታታዮች ወገኖቻችን፤ ፀሎት የአጋንንትን ወጥመድ የሚሰባብር፣ ሃይላቸውን የሚያዳክም ከኛ ህይወት ተለይተው እንዲጠፋ የሚያደርግ እንደ ሰይፍ የሚቆራርጣቸው እንደ እሳት የሚያቃጥላቸው ስለሆነ ለእኛ ትልቁ ሃይላችን እና ጉልበታችን ረቂቅ መሳሪያችን ስለሆነ ማንኛውም ክርስቲያን የጀመረው ጉዞ የተቃና እንዲሆንና ዘወትር ከሚያጋጥመው ፈተና ለመውጣት እንዲችል ፀሎትን ማዘውተር ስላለበት ሁላችሁም በተቻለ አቅም ከፀሎት እንዳትለዩ ባለን የአገልጋይነት ሃላፊነታችን አደራ እንላችኋለን።
 
ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስም ለቅዱሳን ሐዋርያት በማስመሰል እና ከአፋዊ (ግብዝነት) የጸሎት ስርዓት እርቀው እውነተኛ ፀሎት የሚፀልዩ ሰወች ስለሚያገኙት መንፈሳዊ ድል ለቅዱሳን ሐዋሪያት አስተምሯቸዋል። የፀሎትንም አይነት ከዚሁ ጋር አያይዞ ነግሯቸዋል። (ማቴ 6፥5-13) 
 
እንዲሁም በምሴቴ ሐሙስ (በሐሙስ ማምሻ) ለአርብ አጥቢያ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ተላልፎ በሚሰጥበት ሌሊት ንዲት ሰአት ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ፀልዩ” በማለት ፀሎት ከከባድ ፈተና እና ከአሰቃቂ መከራ የሚያድን መሆኑን አስተምሯቸዋል (ማቴ 26፥41)
 
ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በነገር ሁሉ በፀሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ አቅርቡ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ አይምሮን ሁሉ የሚያውቅ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁን አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4፡6)
መልስ፦ ፀሎት የሚቀርብበት የራሱ ስርዓት እና ቀኖናዊ ትውፊት አለው። መፀለይ ስላሰብን ብቻ ቦታና ግዜን ሳንወስን እኛም ራሳችን ሰባዊ አካላችን ሳንሰበስብና ለፀሎት ሳናዘጋጅ ከሜዳ ተነስተን ብናነበንብ ፀሎታችን የአህዛብ ፀሎት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ፀሎት፦
 
– በቅጥረ ቤተክርስቲያን ሆነን መፀለይ ይገባናል 
– በምንኖርበት ቤት ውስጥም ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ የፀሎት ቦታ ላይ ሆነን መፀለይ አለብን 
– በግል ሆነን እና በማህበር ሆነን ስንፀልይ በቀስታ ወይም በለሆሳ (በምላስ) የሚፀለይ ፀሎት ልንፀልይ እንችላለን። የቤተክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት በንባብ እና በዜማ ሊፀልዩ ይችላሉ። 
-እግዚአብሔር አምላክ የእለት እለት የግል ህይወታችንን እና የማህበር ስራችንን ከመጀመራችን በፊት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ ይኖርብናል 
– ለመንፈሳዊ አገልግሎት የታነፀ ቤተክርስቲያን አለ፣ ሌሎችም ለመንፈሳዊ ተግባር የሚውሉ የተገነቡ የልማት ስራዎች ካሉ በአባቶቻችን በፀሎት ተባርከው አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በግል ወጥቶና ወርዶ ያተረፈውን የእጁን ስራ እግዚአብሔር እንዲባርክለት የሚሰራበትን የመኖርያ ቤትም ቢሆን የንግድ ቤትም ቢሆን መኪናም ቢሆን ፋብሪካም ቢሆን ኢንዱስትሪም ቢሆን በመሬት ላይ የምናለማውን ማንኛውም ተግባር ይሁን በፀሎት ልናስባርክና ልንገለገልበት ይገባል (2ኛ ዜና 7፥15)
 
-ጠዋት በነግህ ወይም በጠዋት የምንፀልየው ፀሎት ምግብ ሳንበላ እና ሰውነታችንን ከገቢረ ኅጢአት ጠብቀን ሊሆን ይገባል፣
 
-ከ9 ሰአት በኋላ የምናቀርበው የሰርክ ጸሎት ከሌላ የኀጢአት ስራ ተጠብቀን ፀሎት ልንፀልይ እንችላለን።
 
-ተበልቶ የማይፀለየው፦ የቅዳሴ ፀሎት እና አባቶች በሚስጢረ ቤተክርስቲያን ቤተ መቅደስ የሚያከናውኑት የፀሎት ስርዓት ምግብ ሳይበላ የሚጸለይ የፀሎት ክፍል ነው
 
በአጠቃላይ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ ፕሮግራም ተከታታዮች ወገኖቻችን፤ ፀሎት የአጋንንትን ወጥመድ የሚሰባብር፣ ሃይላቸውን የሚያዳክም ከኛ ህይወት ተለይተው እንዲጠፋ የሚያደርግ እንደ ሰይፍ የሚቆራርጣቸው እንደ እሳት የሚያቃጥላቸው ስለሆነ ለእኛ ትልቁ ሃይላችን እና ጉልበታችን ረቂቅ መሳሪያችን ስለሆነ ማንኛውም ክርስቲያን የጀመረው ጉዞ የተቃና እንዲሆንና ዘወትር ከሚያጋጥመው ፈተና ለመውጣት እንዲችል ፀሎትን ማዘውተር ስላለበት ሁላችሁም በተቻለ አቅም ከፀሎት እንዳትለዩ ባለን የአገልጋይነት ሃላፊነታችን አደራ እንላችኋለን።
 
ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስም ለቅዱሳን ሐዋርያት በማስመሰል እና ከአፋዊ (ግብዝነት) የጸሎት ስርዓት እርቀው እውነተኛ ፀሎት የሚፀልዩ ሰወች ስለሚያገኙት መንፈሳዊ ድል ለቅዱሳን ሐዋሪያት አስተምሯቸዋል። የፀሎትንም አይነት ከዚሁ ጋር አያይዞ ነግሯቸዋል። (ማቴ 6፥5-13) 
 
እንዲሁም በምሴቴ ሐሙስ (በሐሙስ ማምሻ) ለአርብ አጥቢያ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ተላልፎ በሚሰጥበት ሌሊት ንዲት ሰአት ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ፀልዩ” በማለት ፀሎት ከከባድ ፈተና እና ከአሰቃቂ መከራ የሚያድን መሆኑን አስተምሯቸዋል (ማቴ 26፥41)
 
ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በነገር ሁሉ በፀሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ አቅርቡ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ አይምሮን ሁሉ የሚያውቅ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁን አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4፡6)
መልሰ፦ ጠያቂያችን ውዳሴ ማሪያም ፀሎት ከምግብ በኋላ ማድረግ ይቻላል ወይ በማለት ያቀረቡልንን ጥያቄ በሚመለከት፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ለማመስገን እና ወደ ፈጣሪ የምስጋና እና የልመና ፀሎት ለማቅረብ ጊዜ አይወስነንም። የሰው ልጅ በነፍስ የተፈጥሮ ባህሪው መላእክትን የሚመስል፤ የመላእክት ደግሞ ቋሚ ግብራቸው እግዚአብሔርን ማመስገናቸው እንደ ምግብ፣ እንደ መጠጥ፣ እንደ ልብስ ሆኗቸው ይኖራሉ። ማለትም ዘወትር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ እግዚአብሔርን ማመስገን ስራቸው ነው። በሌሊትም በቀንም ሳያርፉና ሳይታክቱ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ፀጋ ሲበዛለት በቅድስና ህይወት ሲኖር ስጋ ለነፍስ ስትገዛ የዘወትር ስራው ምስጋና ይሆናል። ስለዚህ እግዚአብሔርን ለማመስገን የግዜ ገደብ አይኖረውም ማለት ነው። እንዳናመሰግን የሚከለክለን ኀጢአት ብቻ ነው። በእርግጥ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት በሚበላውና በሚጠጣው ሆዳችንን ከሞላን በኋላ የበላነውና የጠጣነው ሆዳችንን እያስጨነቀን እና እያስገሳን ወደታቦት ቀርበን ወይም ወደ ቤተመቅደስ ገብተን ማመስገን እና ፀሎት መፀለይ ለህሊናችንም ሆነ ለተመልካች ስለሚከብድ ሳንበላ ሳንጠጣ ብንፀልይ ጥሩ ነው። በተለይ ከዚህ ቀደምም እንደገለፅነው በሌሊትና በነግህ የምንፀልየው ፀሎት ከምግብ እርቀን ነው። ፈፅመን በፆም ተወስነን የምናደርጋቸው ስርአቶችም፦1ኛ/ ቅዳሴ መቀደስና ማስቀደስ፣ 2ኛ/ ቅዱስ ቁርባን መቀበል፣ 3ኛ/ የነግህ (የጠዋት) ፀሎት ኪዳን ማድረስ፣ ውዳሴ ማርያም እና ሌሎችም ፀሎት መፀለይ የሚገባን ከምንበላ ከምንጠጣ በፊት ነው።  
በሰርክ የምናደርሰው ፀሎት ከሌላ ሃጢአት እንከለከላለን እንጂ መብላት መጠጣታችን እንደዳንፀልይ አይከለክለንም። በአብነት ወይም በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ጉባኤ ዘርግተው የሚያስተምሩ የቤተክርስትያን መምህራን በሰርክ ወይም በማታ ግዜ ውዳሴ ማርያምንና ቅዱስ ያሬድ በዜማ ያቀረበውን የምስጋና ፀሎቶች በዜማ ይፀልያሉ። ለምሳሌ፦ ለሰኞ የሚቀርበውን ውዳሴ ማርያም እሁድ ማታ በዋዜማው ይፀልያሉ። በዚህ ፀሎት በመንፈሳዊ አብነት ትምህርት ቤት እና በገዳማት የሚኖሩ አባቶች የተጠቀሙበት (ዋጋ ያገኙበት) የፀሎት አይነት ነው።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን ለግንዛቤ ያህል ከላይ ለማብራራት እነደሞከርነው ከምግብ በፊት የሚፀለየው የጠዋት እና የሌሊት ፀሎት ሲሆን ከምግብ በኋላ ደግሞ የሰርክ ፀሎት እንደሆነ እንዲያውቁት ይህን መልዕክት ልከንልዎታል።

መልስ፦  ጠያቂዎችን በሌላ ልማድ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሰዎች አንድም ቀን ወደ መንፈሳዊ ነገር ቀርበው እራሳቸውን ያላስመረመሩና ትምህርት ያላገኙ ሰዎች ሳያውቁት እና ሳይረዱት እርኩስ መንፈስ በረቂቅ ሥራው ወደ እግዚኣብሔር እንዳይመለሱ አድርጓቸው ስለኖረ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እንፀልይ፣ እንፁም፣ እንስገድ ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደን እናስቀድስ፣ ቃለ እግዚአብሔር እንማር፣ ብለው ሲወስኑ አላማቸውን ለማሰናከልና ለማደናቀፍ ሰይጣን በተለያየ ምክንያት ሊፈትናቸውና ሊያሰቃያቸው ስላሚችል እንዲህ አይነት ፈተና የደረሰበት ወይም የደረሰባት አባል በአንድ ጊዜ ወደማይችሉት ፈተና ላለመግባት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ እንድንሰጣቸው በውስጥ መስመር ያግኙን :: እስከዚያው ድረስ በእርስዎ በኩልማድረግ ያለብዎት ወደ ቤተክርስቲያን ቀርበው ከአባቶች ምክር መቀበል፣ ሰይጣን የሚያደርስብዎትን ፈተና በግልፅ ማስረዳት፣ ብዙ የማይከብድ ፀሎትን መፀለይ፣ ፀበል መጠጣት እና መጠመቅ፣ በመስቀል መባረክና እምነት መቀባት እነዚህን ሁሉ በማድረግ በቁርጠኝነት ከታገሉት ሰይጣን በራሱ ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል አሸንፈውት ፈጽሞ እንዲለይዎት ማድረግ ይቻላል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። በመንፈሳዊ ምክርና ፀሎት እንድናግዝዎት ካስፈለገም በውስጥ መስመር በላክንልዎት ቁጥር ደውለው ሊያገኙን ይችላሉ።

የእግዚአብሔር ቸርነት አይለይዎት ::

 ጠያቂያችን የሰው ልጅ መሰረታዊ ችግር አንዱና ዋናው የተናገረውን የሰማውን ወይም በሌላ የተማረውን እና የተነገረውን አለማስተዋል ወይም ልብ አለማለት ነው። ምክንያቱም ሥጋዊ አካላችን የስሜት መገለጫ በሆኑት በአፍ መናገር ፣ በጆሮ መስማት ፣በአይን ማየት የመሳሰሉት ለውስጣዊ ስሜት እውነተኛ መገለጫ ላይሆኑ ይችላሉ:: ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስም በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል “ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ፣ እየሰሙ ስለማይሰሙም ፥ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችኹና አትመለከቱም። በአይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሯቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ህዝብ ልብ እንድኗል፥ ጆሯቸውም ደንቁሯል፥ አይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነሱ ይፈፀማል።” (ማቴ13፥ 13-14)
 
ስለዚህ ጠያቂያችን እንዳሉት እንኳንስ ብዙ የመንፈስ ፈተና ያለበት የእግዚአብሔርን ቃል አንብቦ ለመረዳትና ለማስተዋል ይቅርና በዚህ አለም ላይ እንኳን በየትኛውም እንቅስቃሴያችን የምናየውን ባለማስተዋላችን ለብዙ ውድቀት ስንዳረግ ማየት የተለመደ ሂደት ነው። በተለይ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተን እንዳናስተውል የመልካም ነገር ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በመንፈስ እየተዋጋን እውነቱን እንዳንረዳ ከአይነ ህሊናችን ስለሚሰውረው፤ ያነበብነውን እና የተማርነውን እንዳናስተውልና ወደ መልካም ሥራ አንዳንቀይር እኛ በማናውቀው መንገድ የሚዋጋን ክፉ መንፈስ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በፃፈው መልዕክቱ “ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው” ብሏል(ገላ 3፥1):: አዚሙም  ከላይ እንደገለፅነው የመልካም ነገር ጠላት የሆነው ክፉ መንፈስ ነው፡፡
 
ስለዚህ ጠያቂዎችን የመዘንጋትና ያለማስተዋል ችግርዋን ለማስተካከል ፦ 1ኛ/  እርስዎ እንዳሉት ለንስኀ አባት ወይም ለቤተክርስቲያን አባቶች ችግርዎን በግልጽ ነግረው በፀሎታቸው እንዲያስብዎት ማድረግ፤ 2ኛ/ በግል የሚፀልዩትን የተለመደ ፀሎት አጽንተውና አጠናክረው መቀጠል፤ 3ኛ/ የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ሲያነቡም ሃሳብን ሰብሰቦ ለመረዳት መሞከር ፣ (የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብና ፀሎት ስንጀምር መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ማማተብ ይገባናል። ምክንያቱም በትምእርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን ፀሎት ከመጀመራችን በፊት የምናማትበው በሃሳብ የሚቃወመንን እና ከፈጣሪያችን ጋር በፀሎት እንዳንገናኝ የሚፈታተነንን እርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሃይል ቀጥቅጠን ከእግራችን ስር ለመጣል ወይም ፈፅሞ ከእኛ እንዲርቅ ለማድረግ ነው) ፤ በ4ኛ ደረጃ ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ መስገድ ፣ ፀበል መጠመቅ፣ በመስቀል መዳሰስ ፣ እነዚህን ሁሉ ሲያደርጉ የሚፈታተንዎት መንፈስ ከእርስዎ እንዲርቅ ያደርጉታል። ለመንፈሳዊ ነገር ቀርቶ ለሥጋዊ ነገሮች እንኳን በርትተውና ጠንክረው ተስፋ ሳይቆርጡ መንፈሳዊ ትግሎትን ይቀጥሉ ዘንድ ይችን አጭር መልዕክት ልከንሎታል:: ከዚህ ውጭ ለተጨማሪ ምክር ካስፈለገዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
 
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር አጋዥነት አይለይዎ ::
ጠያቂያችን በቅዳሴ ጊዜ ሌላ የግል ፀሎት መፀለይ አይፈቀድም፤ ምክንያቱም ቅዳሴ ከሁሉ በላይ የሆነ ካህናትም ሆኑ ምእመናን በማህበር ሆነው የሚጸልዩት ፀሎት ስለሆነ ነው። ማንኛውም ካህንም ሆነ ምእመን  በግሉ የሚፀልየውን ፀሎት ከቅዳሴ በፊት ወይም ከቅዳሴ በኋላ ሊፀልይ ይችላል። ቅዳሴ የክርስቶስን አማናዊ ሥጋውና ደሙ የሚከብርበት እና ለቅዱስ ቁርባን ራሳቸውን ያዘጋጁ ምዕመናንም ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ተቀብለው የዘለዓለም ሕይወት የሚያገኙበት የመጨረሻና የመደምደምያው ስርዓት ስለሆነ ቅዳሴ እየተቀደሰ የግል ፀሎትም ሆነ ሃሳብን የሚሰርቅ እንቅስቃሴና ንግግር ማድረግ የተከለከለ ነው።መውጣት መግባት ወይም ማውራት መነጋገር፣ መንቀሳቀስ ፣መቀመጥ፣ እግርን አነባብሮ መቆም ፣ልብስን መስቀለኛ ሳይለብሱ መቆምና እነዚህን የመሳሰሉ አስነቃፊ ነውሮችን ማድረግ ፈጽሞ የተከለከለ ስለሆነ ጠያቂያችን በዚህ በተሰጠዎት ማብራሪያ ሃሳቡን ይረዱት ዘንድ እንመክራለን።
 ጠያቂያችን ከፀሎት ጋር በተያያዙ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን ትምህርት አንብበው ሃሳቡን ይረዱት ዘንድ ሊንኩን እንደሚከተለው ልከንልዎታል ::http://Yohannesneseha.org/ትምህርት-ስለ-ተዋሕዶ/መሰረታዊ-ትምህርት
ጠያቂያችን እንዳቀረቡት በቅዳሴግዜም ሆነ ፀሎት በምንፀልይበት ወይም በምንጀምርበት ጊዜ እኛን ሊቆጣጠረን በዙሪያችን የከበበውን ክፉውን መንፈስ የእግዚአብሔር ቃል ሲቃወመው ያኔ እርኩስ መንፈስ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከእኛ ጋር የረቀቀ የመንፈስ ጦርነት በማድረግ ስለሚዋጋን መንፈሳችን ሁሉ ሊረበሽ ይችላል ምክንያቱም ሰይጣን የእኛን ሕይወት እንደ መኖሪያ ቤት ስለሚቆጥረው እኛ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ቤት በተመለሰን ጊዜ በእርኩስ መንፈስ ተይዞ የነበረ ህይወታችን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ይሆን ዘንድ በንስኀ እና በቃለ እግዚአብሔር እየፀዳ ስለሆነ ያንጊዜ ደግሞ የሽግግር ሰዓት ስለሆነ መንፈሳችንን ሁሉ ሊረብሸውና ረቂቅ የጦር አውድማ ሊያደርገው ይፈልጋል።
 
እኛ ደግሞ በአላማችን ፀንተን በተለያየ ምልክት ቢዋጋን እንኳን ቅዳሴ ከማስቀደስ፣ ቃለ እግዚአብሔር ከመስማት ፀሎት ከማድረግ፣ ከመፆም፣ ከመስገድ በአጠቃላይ አጋንንትን ሊዋጉልን ከሚችሉ መንፈሳዊያን ፀጋዎች ሳንላይ አላማችንን በጽናት ማስቀጠል አለብን። በዚያን ጊዜ ሰይጣን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ከእኛ ይሄዳል፣ የሚቃወመን መንፈስ ሁሉ ከኛ ፍፁም 40 ክንድ ተላይቶ ይሄዳል። እኛ ባናየው እንኳን ከኛ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ፀጋ ሰይጣንን ለማስወገድ መንፈሳዊ ትጥቃችን ስለሆነ ዳግም ሰይጣን እኛን ሊደፍር ስልጣን ስለማይኖረው ጠያቂያችን የፈለገውን ያህል አሁን ላይ ሰይጣን ቢዋጋዎትም ወደኋላ እንዳይመለሱ ፤ አብዝተው ይፀልዩ ፣ አብዝተው የእግዚአብሔርን ቃል ይስሙ፣ አብዝተው ቅዳሴ ያስቀድሱ፣ ፀበል ይጠጡ፣ መስቀል ይሳለሙ፣ ዘወትር የአባቶችን ምክር እና ተግሳፅ ይቀበሉ፣ እለት እለት ወደ ቤተክርስቲያን መሄድን ያዘውትሩ፤ ያኔ በሰይጣን ላይ መንፈሳዊ ድሎ የእርስዎ እንደሚሆን አንጠራጠርም።
 

ጠያቂያችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምሮ መሰረት አይንን ጨፍኖ መፀለይ አይፈቀድም። መፅሐፍ እንደሚነግረን በሰማይ ያለውን አባታችንን ስም ስንጠራ አይናችንን ወደሰማይ አንስተን ልባችንን እና ህሊናችንን ሰብስበን ወደ ላይ አንጋጠን እጆቻችንን ዘርግተን መፀለይ እንደሚገባን የሃይማኖታችን ስርዓት ያዘናል። ስለዚህ አይንን ማጨለም ወይም መጨፈን የጨለማ መገለጫ ስለሆነ አይነ ህሊናችንንም ማሳወር እንደሆነ ስለሚቆጠር እንዲህ አይነት የፀሎት ስርዓት እንዲኖረን አያስፈልግም። ነገር ግን ጠያቂያችን አንዳንድ ሰዎች በግል ልማድ ያሰቡት ነገር እንዳይጠፋባቸውና አይምሮዋቸው እንዲሰበሰብላቸው ሲሉ አይናቸውን የመጨፈን ልማድ ቢኖር እንደ ግል ልማድ ይቆጠራል እንጂ እንደ ኀጢአተኛ ሊያስቆጥራቸው አይችልም። እንደ ቤተክርስቲያን ስርዓት ክልክል የሚሆነው መናፍቃን እንደሚያደርጉት የፀሎት አይነት አይንን ጨፍኖ በቋሚነት መፀለይ ግን እጅግ ክልክል መሆኑን ታውቁ ዘንድ ይሄንን አጭር ማብራሪያ ልከንላችኋል።

ጠያቂያችን ሃሳብን በመሰብሰብ በአንድ ልብ ሆኖ በእምነት መፀለይ የፈለግነውን በጎ ምላሽ ከፈጣሪ ዘንድ መልስ እንድናገኝ ያስችላል። መቼም ቢሆን የበጎ ስራ ጠላት ዲያብሎስ በሃይማኖታችን ስለምናደርጋቸው በጎ ስራዎች ሁሉ ተቃዋሚ ስለሆነ በፀሎት ጊዜ በማስቀደስ ጊዜም በመሳሰሉት መንፈሳዊያን አገልግሎቶች ሁሉ በሃሳበችን ጣልቃ እየገባ የማሰናከል ስራው ስለማይቋረጥ በምንፀልይበት ጊዜም የጀመርነውን ፀሎት ሳንጨርስ በመካከል ሃሳባችንን እየቆራረጠ የምንፈልገውን ነገር እንዳናስብ ፈተና ያበዛብናል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ክርስቲያን እንዲህ አይነት ሃሳብ በመጣበት ጊዜ ወደ ህሊናው እየተመለሰ የጀመረውን ፀሎት በመንፈሳዊ ተጋድሎም ቢሆን መልሶ መላልሶ መፈፀም አለበት። 
 
እንግዲህ ጠያቂያችን ህሊናችን ተሰብስቦ በምንም አይነት ሃሳባችን ሳይሰናከል የጀመርነውን ፀሎት ቀጥ ብለን ለመፀለይ የምንችለው ወደ ፍፁምነት ደረጃ ስንደርስ ብቻ ስለሆነ ዛሬ ላይ ግን በአለም ላይ እየኖርን ግማሽ ለሥጋ ህይወታችን ግማሽ ለነፍስ በምንኖርበት ጊዜ ሃሳባችን እየተሰናከለም ቢሆን ፀሎታችንን ሳናቋርጥ መቀጠል እንጂ ማቋረጥ የለብንም፤ ፈተናውም የእግዚአብሔርን ፀጋ እንደሚያበዛልን እንጂ ፀሎታችንን እግዚአብሔር እንደማይቀበለው መቁጠር የለብንም። 
 
ስለዚህ ጠያቂያችን በርትተውና ጠንክረው ሳያቋርጡ መንፈሳዊ ትግሎትን ይቀጥሉ ፤ በተጨማሪም በምንጸልይበት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባን ከዚህ በፊት ስለ ጸሎት ካስተላለፍነው ትምህርት ውስጥ ባጭሩ ወስደን እንደሚከተለው ዘርዝረንልዎታልና አንብበው ይረዱት። 
 
በምን አይነት መንገድ መፀለይ ነው የሚገባን?
 
-ፀሎት ስንጀምር መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ማማተብ ይገባናል።
– ስንጸልይ በፍፁም እምነት ሁነን መፀለይ ይገባናል።
-በንፁህ ልቦና እንዲሁም በቅን መንፈስ ሆኖ መፀለይ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል እንደ ግርዶሽ የሆነውን ክፉ ስራችንን ገርስሶት እግዚአብሔርን ለማየት ስለሚያስችለን ልቦናችንን ንፁህ ማድረግ አለብን። ስለዚህም “የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መካከል እንደወደቀ ዘር ነው” ተብሎ በመፅሐፈ መነኮሳትና በሌሎችም መፅሐፍት ተመዝግ ይገኛል። 
-በፈሪሃ እግዚአብሔር ሁነን እግዚአብሔርን በመፍራት ህይወታችንን በንስሓ አድሰን መፀለይ ይገባናል። ምክንያቱም ሰው የእምነቱ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ማስቀደም አለበት፤ ቀጥሎም በፀሎት እግዚአብሔርን ለማመስገን ወይም ደግሞ የፈለገውን ለመጠየቅ ሰውነቱን እና መላ ህይወቱን በንስሓ ህይወት መቀደስ አለበት።
– ስንፀልይ ቀጥ ብለን በመቆምና አይናችንን ወደ ሰማይ በማቅናት ሃሳብን ሰብስቦ በአንድ ልብ ተወስኖ መፀለይ ይገባል። በፀሎት ግዜ መስገድ ይገባል፣ 
 
ጠያቂያችን ከዚህ ተጨማሪ ምክር ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ጠያቂያችን ፤ እንዳሉትም አንድ ክርስቲያን በ24 ሰዓታት ውስጥ 7 ጊዜ እንዲፀልይ ታዟል። እነዚህ 7ቱን የፀሎት ጊዜያት ለምን እንደምንፀልይ የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን 7ቱን የፀሎት ጊዜያት ጠብቀን ለመፀለይ የማንችልበት በቂ ምክንያት ካለ ቢያንስ የጠዋቱንና የማታውን ፀሎት ባጭሩ ማድረስ ይገባል። ስለዚህ ጠያቂያችን እንዳሉትም በ7ቱም የፀሎት ክፍለ ጊዜ ለመፀለይ ቢችሉ በነፍስም ሆነ በሥጋ ህይወታችን በረከትን እናበዛለን። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ልዩ ልዩ ምክንያት ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ከነሱ በላይ እርሱ ስለሚያስብ ለፈጣሪያቸው የሚገባውን ምስጋና እና የሚፈልጉትን ልመና ለማቅረብ ከላይ እንደተገለፀው በ24 ሰአት ውስጥ 2 ጊዜ ማለትም ጠዋት እና ማታ ቢፀልዩ እግዚአብሔር የማያውቀው ነገር ስለሌለ የፈለግነውን የእግዚአብሔር በረከት እናገኝበታለን። ነገር ግን ጠያቂያችን ለፀሎት በማያመቹኝ ያሏቸውን ሰአታት በምን መልኩ መፀለይ እንደሚችሉ ለምንሰጥዎት ምላሽ እርስዎ ያሉበት ሁኔታ፣ የሚሰሩት የስራ ባህሪ፣ የሚኖሩበት አካባቢና የመሳሰሉት ስለሚወስነው ወይም ደግሞ ከዚህ አንፃር አይተን ስለሚሆን ምክር የምንሰጥዎት በውስጥ መስመር በሚደርስዎ ቁጥር ደውለው ትንሽ ሊያያብራሩልን ቢችሉ የበለጠ መንፈሳዊ ትምህርት እና ምክር እንዲደርስዎ እናደርጋለን። 
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር አጋዥነት አይለይዎ ::
ጠያቂያችን ከዚህ በፊት ‘ስርዓተ ፀሎት’ በሚል ርዕስ ስለ  7ቱ የጸሎት ጊዜያት፣ በምን አይነት መንገድ መፀለይ እንደሚገባን ፣ ምን እያልን መፀለይ እንዳለብን፣ እንዴት መፀለይ እንደሚገባን በሁለት ክፍል ትምህርትባስተላለፍነው ሰፊ ማብራሪያ ለዚህ እና ለሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች መልስ የሚሆን መልዕክት እንደላክንላችሁ እናስታውሳለን።ይሁንና ምናልባት ጠያቂያችን ትምህርቱን አላዩት ወይም አላነበቡት ከሆነ፤ አሁን እርሶ ላቀረቡት ጥያቄ መልስ የሚሆነውን አጭር ክፍል ትምህርት ካስተላለፍነው ውስጥ ወስደን እንደሚከተለው ልብንሎታልና አንብበው ይረዱት። የትምህርቱን ሙሉ ክፍልም ከድረገፃችን ያገኙታልና እንዲያነቡት እየመከርን፤ ምናልባት በዚህ ግልፅ ያልሆነሎት ወይም ያልተመለሰ ሃሳብ ካለ ቢያሳውቁን ምላሽ እንሰጥዎታለን ::
 
ምን እያልን እንፀልይ?
 
ወደ ፈጣሪ የምናቀርባቸው ፀሎቶች በ2 ከፍለን እንመለከታቸዋለን፦
 
1. የረቀቀውን የሃይማኖት ሚስጢር የሚያውቁ እና ጥልቅ የሆነ የሃይማኖት እውቀት ያላቸው የቤተክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት የሚፀልዩት ፀሎት ንባቡና ትርጉሙ የረቀቀና የጠለቀ ስለሆነ እነሱ ብቻ የሚፀልዩት ፀሎት ነው።
 
2. ምእመናን ሁሉ የሚፀልዩት ፀሎት በየደረጃቸው ቢፀልዩት የማይከብድ እና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት የጸሎት አይነት ነው። ካህናትም ሆኑ ምእመናን የሚፀልዯቸው የፀሎት መፃህፍትም፦
 
– የ150 መዝሙረ ዳዊት እና 15 ነብያት እና መሃልየ ሰለሞን እነዚህ ከሰኞ እስከ እሁድ የሚፀለዩ የፀሎት ክፍል ናቸው 
– የ7 ቀን ውዳሴ ማርያምና አንቀፀብርሃን እንዲሁም መልክአ ማርያምና መልክአ እየሱስ 
– ውዳሴ አምላክና ሰኔ ሎለጎታ 
– ሰይፈ ሥላሴና ሰይፈ መለኮት  
– የፃድቃንና የሰማእታት መልካቸውና ገድላቸው  
– የቅዱሳን መላእክት  መልካቸውና ድርሳናቸው 
– ወንጌለ ዮሐንስ 
 
ሌሎችም ብዙ የፀሎት አይነት አሉ። በገዳማት ውስጥ የሚኖሩ መናኞች እና አንዳንድም እግዚአብሔር ፀጋውን ያበዛላቸው በከተማም ሆነ በተለያየ ቦታ እየኖሩ አብዝተው የሚፀልዩ የእግዚአብሔር ሰዎች አሉ።  
 
ፀሎት ለማድረግ ወይም ለመፀለይ ፈፅሞ ማመን እና ህሊናን ንፁህ ማድረግ እንጂ የእውቀት ብዛት እና የፀሎት ብዛት ለፀሎቱ ተቀባይነት ወይም ቅቡል መሆን ዋናው ምክንያት ላይሆን ይችላል። በሃይማኖት ውስጥ ያሉትን የፀሎት መፅሐፍት በቀላሉ ለመረዳትና በቂ እውቀት የሌላቸው ምእመናን ከሆኑ ቢያንስ የክርስቲያን አጭር ፀሎት አቡነ ዘበሰማያት፣ ፀሎተ ሃይማኖት፣ ፀሎተ እግዚተነ ማርያምን አጥንተውም ቢሆን ከንስሓ አባት ወይም በቅርብ ከሚያገኟቸው የቤተክርስቲያን አባቶች በመጠየቅ አጥንቶ መፀለይ ያስፈልጋል። 
 
ሲጀመር አንድ ክርስቲያን ለስጋው ምግብ ልብስ እንዲሁም መጠለያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለነፍስም ከሚያስፈልጓት የነፍስ ተግባራት አንዱ እና ዋናኛው ፀሎት ስለሆነ ለሁሉም ጉዟችን በር ከፋችና በጎውንና ክፉውን ነገር ለማየትም የምንችልበት ብርሃን ስለሆነ ፀሎት በክርስቲያናዊ ህይወት ላይ እጅግ አስፈላጊ ነው። የግዜ እጥረት ያለባቸው ሰዎች እንደ ስጋዊ ምክንያት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚያውቀው ከአቅም በላይ የሆነ ፈተና ሲያጋጥመን ከዚህ በላይ የተገለፁትን አጫጭር ፀሎቶች ፀልየን ፈጣሪያችንን በወጣንበት በገባንበት ተከተለን ብለን ከእሱጋ ያለንን ግንኙነት አጠንክረን ወደ ስራችን ብንገባ ሁሉም ነገር ይሳካልናል ማለት ነው። 
 
መልስ #1፦ ስለተመስጦ የጠየቁ አባላችን ሆይ፤ ስለ ተመስጦ እና ስለ ራዕይ በመፅሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ሰፋ ያለ እና ረቂቅ የሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርት አለ። ነገር ግን ባጭሩ ያቀረቡትን ጥያቄ ለማብራራት ይቻል ዘንድ  ተመስጦ ማለት እንደ ቅዱስ መፅሐፍ ሲተረጎምና ሲብራራ ተመስጦ የሚለው ስርወ ቃሉ ከግሪክ ቋንቋ የተገኘ ሲሆን የአማርኛ ትርጓሜውም በራዕይ፣ በመገረም፣ በመደነቅ፣ በመደመም፣ በሰመመን ማሰብ፣ ህሊናን መሰብሰብ፣ አይምሮን መግዛት፣በመንፈስ ሆኖ ማሰብ፣ በአይነ ሥጋ የማይታየውንና በአካባቢ የሌለውን አንድን ነገር በዓይነ ህሊና ማየት እነዚህን የመሳሰሉትን ሁሉ ሊያስተነትን የሚችል ቃል ነው።
 
ስለ ተመስጦ ወይም ራዕይ በመፅሐፍ ቅዱስ የተገለጡ ማስረጃዎችን ለማየት ያህል ፦
 
1ኛ/  “ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ…” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በተመስጦ ያየውን ነገር በሚያየውና በፈጠጠው ዓይኑ ሳይሆን በመንፈሳዊ አይን የተሰወረውንና የረቀቀውን ነገር ለማየት እግዚአብሔር ምስጢሩን እንደገለፀለት ያመለክታል። (የሐዋ 10፥9-10)
 
2ኛ/  ቅዱስ ጴጥሮስ እራሱ ስለተመስጦ ሲገልፅ “እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ…” በማለት አሁንም በተመስጦ ያየውን ራዕይ ይህ ቃል ያመለክታል። (የሐዋ 11፤5-8)
 
3ኛ/  “ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፥ እርሱም። ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት…” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ በኋላ ስለሚሆነውና ሰለሚፈፀመው ነገር እግዚአብሔር አምላክ ምስጢሩን በተመስጦ እንደገለፀለት ያመለክታል። (ሐዋ 22፥17-18)
 
4ኛ/   ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ እንዲሁም። የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ…” በማለት በተመስጦ ወይም በመንፈስ ሆኖ ስላየው የእግዚአብሔር ምስጢር ተገልፆለት ተናግሯል። (ራዕ 1፥10-11)
 
እንግዲህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ ድረገጽ መንፈሳዊ ፖሮግራም ተከታታይ አባላት የተመስጦ እና የራዕይ ትምህርቱ ሰፊና ረቂቅ ቢሆንም በአጭሩ ለጥያቄዎ አጭር ግንዛቤ እንዲሰጥ ይህን ልከንልዎታል።
 
መልስ#2፦ በፀሎት ሰዓት ህሊናዬን ሰብስቤ ትኩረት ሰጥቼ ለመፀለይ እጅጉን ተቸግሪያለሁና ምን ትመክሩኛላችሁ ያሉን ጠያቂያችን፤ በእርግጥ የእርስዎ ችግር በፀሎት ወይም በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው የሚፈተንበትና የሚቸገርበት ጉዳይ ነው። በጸሎት ጊዜ ህሊናን ሳይሰበስቡ መፀለይ የሰበሰቡትን እንደመበተን ስለሆነ እንደምንም ሃሳባችንን ከሚሰርቀው ረቂቅ መንፈስ ጋር እየታገልን አንዳንድ ጊዜ ከአይምሯችን እያወጣንና ከአይምሯችን እንዳንሆን ቢፈታተነንም ነገር ግን በመንፈስ እየታገልንም ቢሆን የረሳነውን ሃሳባችን እየመላለስን መፀለይ ብናዘወትር ሃሳባችንን የሚበታትንብን ጠላታችን እርኩስ መንፈስ ተማሮ እና የእግዚአብሔር ቃልም ስለሚዋጋው ከኛ ፈፅሞ እንዲርቅ ያደርግልናል።  ስለዚህ ዋናው ነገር ሳንሰለችና ተስፋ ሳንቆርጥ ህሊናን ሰብስቦ የመጸለይ መንፈሳዊ ህይወታችንን ደረጃ በደረጃ ለማሳደግ መለማመድ  ነው።
 
በቤተክርስቲያን ቁመን እያስቀደስን፣ ቃለ እግዚአብሔር እየተማርን፣ እየፀለይን ባጠቃላይ ስጋችን በቤተክርስቲያን ሆኖ ያለንበትንና የቆምንለትን ዋናውን አላማችንን አስረስቶ በመንፈስ ወደማይገባን የሥጋ ሃሳብ ወስዶ አይምሯችንን ሲበትነው ማየት የተለመደ ፈተና ቢሆንም እንዲህ አይነቱን ፈተና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሳንሰለች ከቤተክርስቲያን አባቶች ምክር እና መንፈሳዊ አገልግሎት እየተቀበልን ሃሳብን ሰብስቦ በትጋት መፀለይን አብዝተን መለማመድ አለብን።
 
ለምሳሌ አባታችን ሆይ የሚለውን ፀሎት በምንፀልይበት ጊዜ ስንጀምር ከህሊና ሆነን ከጀመርን በኋላ እስከመጨረሻው ለመፀለይ የሚያዘናጋ ሃሳብ ከመጣብን እንደገና አማትበን አባታችን ሆይ ብለን ጀምረን ህሊናችንን ሰብስበን እስከመጨረሻው በአንድ ልብ መፀለይን ራሳችንን ማለማመድ አለብን።
 
በተጨማሪም ፀሎት ስንጀምር መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል እንደምናማትበው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ወይም በፀሎት መሃልም አይምሯችን ወደ ሌላ እየበተነ የሚቃወመን ሃሳብ ሲኖር አሁንም ህሊናችንን ሰብስበን  በትምእርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን  በማማተብ ከፈጣሪያችን ጋር በፀሎት እንዳንገናኝ  የሚፈታተነንን እርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሃይል ቀጥቅጠን ከእግራችን ስር ለመጣል ወይም ፈፅሞ ከእኛ እንዲርቅ ለማደረግ እንችላለን።   
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ አባላቶቻችን ሁላችሁም በአንድ ልብ ሆኖ በእምነት መፀለይ የፈለግነውን በጎ ምላሽ ከፈጣሪ ዘንድ መልስ እንድናገኝ ስለሚያስችል ሃሳብን ሰብስቦ መፀለይ እንዳለብን እንመክራለን። 
 

ጠያቂያችን የአርጋኖን መፅሐፍ ለፀሎት እጅግ የሚጠቅም የቤተክርስቲያናችን የፀሎት መፅሐፍ ሲሆን ብዙ በገዳማዊ ስርዓትና በምናኔ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የሚፀልዩት መፅሐፍ ሲሆን ነገር ግን እርስዎ የጠየቁትን ኃይለቃል በሚመለከት መፅሐፉን በእጃችን አግኝተን ኃይለቃሉን በደንብ በማስተዋል አንብበን ከተረዳን በኋላ ምን ማለት እንደሆነ ምስጢራዊ ትርጓሜውን ልናስረዳዎት ስለምንችል በትዕግስት ሆነው ይጠብቁን። ይሄንን ስንል ግን በእርግጠኛ ያለምንም ጥርጣሬ እርስዎም እንደተረዱት ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከቅድመ ዓለም ያለ እናት ከባህሪይ አባቱ ከአብ መወለዱን ፥ድህረ አለም ያለአባት ከእናቱ ከድንግል ማርያም መወለዱን ሁለት ልደትን እናምናለን የሚለው ኃይለቃል ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ሃይማኖት መሆኑን ልንረዳ ያስፈልገል። በዚያ እርስዎ ባቀረቡት የአርጋኖን  ኃይለ ቃል ሌላ ምስጢር ለመጥቀስ የተጠቀሰ ሊሆን ስለሚችል መፅሐፉን ተመልክተን በጊዜው ልናስረዳዎት የምንችል መሆኑን እንገልፃለን።

ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ገና በእናቱ ማህጸን ሳለ ጀምሮ እግዚአብሔር ለታላቅ ነገር የመረጠው ሰው ነው።  በዚህ ምክንያት ወደ ታላቁ የንግስና መመረጥ ደረጃ ሳይመጣ ጀምሮ እግዚአብሔር ከሱ ጋር እንደሆነና ከአባቱ እሴይ ልጆች መካከል ታናሽ የሆነውን ዳዊትን ለታላቅ አገልግሎት ፈጣሪው እንደመረጠው የሚታወቀው መራጩ ባለቤቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። በዚህ ምክንያተ ዳዊትን ብላቴናውን እና ከወንድሞቹ ሁሉ ያነሰውን ዳዊትን የመረጠ እግዚአብሔር ስለሆነ የእስራኤል ጠባቂና ንጉስ ሆኖ እስከሚሾምባት ጊዜ ድረስ በዳዊት ላይ ብዙ መከራ እና ፈተና ተፈራርቆበታል። ከዚህ የተነሳ ጠያቂያችን እነዳነሱት ለእግዚአብሔር ሰው ለዳዊት አታማኝ የሆኑት አገልጋዮቹ የንጉሱ የዳዊት አሳዳጆች እና ለሞት የሚፈልጉትን ጠላቶቹ ሊገሉት በሚያሳድዱት ጊዜ በታማኝነት የቆሙ ወታደሮቹ የንጉሱን ህይወት ከሞት ለማትረፍ ራሳቸውን ለመከራ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆን በጠላት ዘንድ ስለ ንጉሱ ስለ ዳዊት ዋጋ በመክፈል ወደሱ የተመለሱትን ታማኞች ንጉሱ በተመለከተ ጊዜ የከፈሉትን መስዋእትነት ተመልክቶ በነሱ የህይወት መስዋዕትነት የመጣውን ደስታ በፀጋ ለመቀበል አይምሮው ስላልፈቀደ የታማኞቹን የህይወት መስዋዕት በማድነቅ በፈጣሪው ዘንድ ታማኝ የሆነው ንጉስ ዳዊት በሰጠው እኔ በእናንተ ሞት ዋጋ የተፈፀመውን ወይም እናንተ ስለእኔ ደማችሁን ስላፈሰሳችሁ እኔ ደግሞ በእናንተ ደም መፍሰስ ወይም የህይወት ዋጋ በመክፈል ተለውጦ የመጣውን የህይወት ውሀ አልጠጣም በማለት እነሱ ስለ ንጉሱ ተለውጠው እስከሞት ድረስ ታማኝ ሲሆኑ ንጉሱ ደግሞ ታማኝ በሆኑት አገልጋዮቹ የህይወት ዋጋ ከፍለው ያቀረቡትን ውሀ አልጠጣም በማለቱ በፈጣሪው ዘንድ እንደ ፅድቅ እንደተቆጠረለት የሚያሳይ ቃል ነው። ጠያቂያችን ምናልባት ሁሉንም ነገር ለእውቀትና ለመረዳት የሚጠይቁ ቢሆንም ነገር ግን ይህንን ሃሳብ ለመረዳት የቻሉበት ምክንያት የተሻለ መንፈሳዊ እውቀት እንዳልዎት የሚያስረዳ ቢሆንም በሌላ መልኩ ያለዎትን መንፈሳዊ ደረጃ በእርግጠኝነት ለመረዳት ስላልቻልን እንጂ በቤተክርስቲያን የእውቀት ደረጃ መገለፅ ያለባቸውን የትርጓሜ ደረጃዎች መሰረት በማድረግ ማስረዳት ስለሚቻል ይሄንን ምስጢር ከዚህ በላይ በስፋት እንድናብራራልዎት ካስፈለገ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

 ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት ሰይፈ ስላሴን ወይም ሌሎችን ምእመናን ሁሉ በየደረጃቸው የሚፀልይዋቸው የፀሎት አይነቶች  ማንም ሰው በፈቃዱ የሚጸልያቸው ስለሆነ እርስዎ እንዳሉት አንዱን ስለጸለየ ሌላውንም ለመጸለይ የሚገደድበት ሁኔታ ግን  አይኖረውም። ስለዚህ ተረጋግተው ጊዜ ኖሮት የሚፀልዩ ከሆነ በብዙ የሚፀልይን በረከትና ጠባቆቱ ይበዛለታልና ከቻሉ ተአምራቱንም ጨምረው ይጸልዩ። ዋናው ነገር ሁል ግዜ እንዲህ አይነት ነገር ላይ መገንዘብ ያለብን አብዝተን ስንፀልይ፣ አብዝተን ስንፆም፣ አብዝተን ስንሰግድ፣ አብዝተን በቃሉ ስንፀና እና አብዝተን መንፈሳዊ አገልግሎት ስናደርግ እግዚአብሔርም አብዝቶ ይባርከናል፥ ይጠብቀናል ማለት እንደሆነ ነው እንጂ እንደግዴታ እያሰብን በጥቃቅን ነገር መጨነቅ የለብንም። 
 
ሰኔ ጎልጎታ ምግብ በልተን መፀለይ /ማንበብ እንችላለን ወይ ላሉን፤  ባጠቃላይ ጸሎት የሚባለው ለፀሎትነት የምንጠቀመው ከሆነ ሳንበላ ሳንጠጣ ወደ እለቱ የስጋ ተግባራት ሁሉ ሳንገባ መፀለይ አለብን። በውስጥ ያለውን ቃልና የምስጢሩን ትርጓሜ ለመረዳት ከሆነ ደግሞ በማንኛውም ሰዓት ማንበብ ይቻላል።   ከምግብ በፊት የሚፀለየው የጠዋት እና የሌሊት ፀሎት ሲሆን ከምግብ በኋላ ደግሞ የሰርክ ፀሎት ነው። በሰርክ የምናደርሰው ፀሎት ከሌላ ኀጢአት እንከለከላለን እንጂ መብላት መጠጣታችን እንዳንፀልይ አይከለክልም።  በእርግጥ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት በሚበላውና በሚጠጣው ሆዳችንን ከሞላን በኋላ የበላነውና የጠጣነው ሆዳችንን እያስጨነቀን እና እያስገሳን ወደታቦት ቀርበን ወይም ወደ ቤተመቅደስ ገብተን ማመስገን እና ፀሎት መፀለይ ለህሊናችንም ሆነ ለተመልካች ስለሚከብድ ሳንበላ ሳንጠጣ ብንፀልይ ጥሩ ነው።  
ፈፅመን በፆም ተወስነን የምናደርጋቸው  የጸሎት ስርአቶች፦1ኛ/ ቅዳሴ መቀደስና ማስቀደስ፣ 2ኛ/ ቅዱስ ቁርባን መቀበል፣ 3ኛ/ የነግህ (የጠዋት) ፀሎት ኪዳን ማድረስ፣ ውዳሴ ማርያም እና ሌሎችም ፀሎት መፀለይ የሚገባን ከምንበላ ከምንጠጣ በፊት ነው።  በመጨረሻም ጠያቂያችን  ለተጨማሪ ለመረዳት እንዲሆንዎ ከዚህ በፊት ከፀሎት ጋር ያስተላለፍነውን ተከታታይ ትምህርት አንብበው ሃሳቡን ይረዱት ዘንድ ሊንኩን እንደሚከተለው ልከንልዎታል።

ጠያቂያችን የሰርክ ፀሎት ስርዓት በገዳማት የሚኖሩ መናንያኖችም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያሉ መምህራን እና ደቀመዛሙርት ማታ በሰርክ ክፍለ ጊዜ የሚቀጥለውን እለት ውዳሴ ማርያም በንባብ ብቻ ሳይሆን በዜማ በመፀለይ ለፈጣሪያቸው ምስጋና ያቀርባሉ። ለእነሱም የፈለጉት የእግዚአብሔር በረከት ይለምኑበታል እና ማታ ከመተኛትዎ በፊት የሚቀጥለውን እለት ውዳሴማርያምን መፀለይ በቤተክርስቲያን የተፈቀደ ስለሆነ ተገቢ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

ጠያቂያችን የንስኀ ቀኖና ተሰጥቶን ሱባኤ ስንገባ መፀለይ ያለብን፦ 1ኛ ሁሌም የመንፀልየው ፀሎታችን ወይም ሁል ግዜ በዘወትር የምንፀልየውን ፆሎት ሳናቋርጥ ልንፀልይ ይገባናል።   2ኛ አንድ ክርስቲያን ንስኀ ወደ ንስኀ አባቱ ቀርቦ ኀጢአቱን በተናዘዘ ጊዜ የንስኀ አባቱ ደግሞ በፍትሐነገስት ወይም በሐዋሪያት ቀኖና ወይም በአንቀፀ ንስኀ የታዘዘውን ስርዓት ተመልክተው እንደ ንስኀው ከባድነትና ቀላልነት አገናዝበው ንስኀውን ስለሚሰጡ በዚያ በአንቀፀ ንስኀ ላይ ማንኛውም ንስኀ የተቀበለ ክርስቲያን ምን ማድረግ እንዳለበት ራሱ ስለሚመራና ስለሚያብራራ ሲሰግድ እና ሲፆምም አብሮ ማከናወን ያለበትን ስርዓት ንስኀ አባታችን በዝርዝር ሊነግሩን ይገባል። ነገር ግን አብዛኞቹ የንስኀ አባቶች እንዲህ አይነቶቹን ሂደቶች በጥልቀት ካለማየት ወይም የግንዛቤ ችግር ሆነ ለንስኀ ህይወትም ቦታ ካለመስጠት፥ እንዲሁ በልማድ ስለሚናዝዙ ምእመናን ሊቸገሩ እንደሚችሉ ስለሚታወቅ፥ ጠያቂያችን ላነሱት ጥያቄ  እንደአጠቃላይ የምንሰጥዎ ምክር፦
 
-ፀሎትን በሚመለከት ከተለመደው ፀሎት ውጪ ጊዜ የሚሰጡት ከሆነ ፥ እንደ እወቀት ደረጃዎት መጠን መዝሙረ ዳዊትን፣ ወንጌለ ዮሐንስን፣ ድርሳናትን እና ስለ ንስኀ ትምህርት የሚሰጡ መፃህፍትን በተጨመሪ ማንበብና መፀለይ ይቻላል።
 
-ስግደትን በሚመለከት ደግሞ ሲሰግዱ በፊትዎ መስቀል ወይም ቅዱሳን ስዕላት ወይም ወንጌል በፊትዎ አድርገው በትዕምርተ መስቀል እያማተቡ ጉልበትዎትን እና ግንባርዎትን መሬት እያስነኩ መስገድ እንደሚገባ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን ሃሳብን በመሰብሰብ በአንድ ልብ ሆኖ በእምነት መፀለይ የፈለግነውን በጎ ምላሽ ከፈጣሪ ዘንድ መልስ እንድናገኝ ያስችላል። መቼም ቢሆን የበጎ ስራ ጠላት ዲያብሎስ በሃይማኖታችን ስለምናደርጋቸው በጎ ስራዎች ሁሉ ተቃዋሚ ስለሆነ በፀሎት ጊዜ በማስቀደስ ጊዜም በመሳሰሉት መንፈሳዊያን አገልግሎቶች ሁሉ በሃሳበችን ጣልቃ እየገባ የማሰናከል ስራው ስለማይቋረጥ በምንፀልይበት ጊዜም የጀመርነውን ፀሎት ሳንጨርስ በመካከል ሃሳባችንን እየቆራረጠ የምንፈልገውን ነገር እንዳናስብ ፈተና ያበዛብናል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ክርስቲያን እንዲህ አይነት ሃሳብ በመጣበት ጊዜ ወደ ህሊናው እየተመለሰ የጀመረውን ፀሎት በመንፈሳዊ ተጋድሎም ቢሆን መልሶ መላልሶ መፈፀም አለበት። ለምሳሌ አባታችን ሆይ የሚለውን ፀሎት በምንፀልይበት ጊዜ ስንጀምር ከህሊና ሆነን ከጀመርን በኋላ እስከመጨረሻው ለመፀለይ የሚያዘናጋ ሃሳብ ከመጣብን እንደገና አማትበን አባታችን ሆይ ብለን ጀምረን ህሊናችንን ሰብስበን እስከመጨረሻው በአንድ ልብ መፀለይን ራሳችንን ማለማመድ አለብን።
 
–  ፀሎት የሚቀርብበት የራሱ ስርዓት እና ቀኖናዊ ትውፊት አለው። መፀለይ ስላሰብን ብቻ ቦታና ግዜን ሳንወስን እኛም ራሳችን ሰባዊ አካላችን ሳንሰበስብና ለፀሎት ሳናዘጋጅ ከሜዳ ተነስተን ብናነበንብ ፀሎታችን የአህዛብ ፀሎት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ፀሎት በምንጸልይበት ጊዜ ማድረግ የሚገቡን፦
 
– በቅጥረ ቤተክርስቲያን ሆነን ወይም በምንኖርበት ቤት ውስጥም ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ የፀሎት ቦታ ላይ ሆነን ወይም  በሌላ  መንፈሳዊ ስፍራዎች ሆነን መፀለይ አለብን ፣
 
–  ፀሎት ስንጀምር መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ማማተብ ፣ምክንያቱም በትምእርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን ፀሎት ከመጀመራችን በፊት የምናማትበው በሃሳብ የሚቃወመንን እና ከፈጣሪያችን ጋር በፀሎት እንዳንገናኝ የሚፈታተነንን እርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሃይል ቀጥቅጠን ከእግራችን ስር ለመጣል ወይም ፈፅሞ ከእኛ እንዲርቅ ለማድረግ ነው። 
– ስንጸልይ በፍፁም እምነት ሁነን መፀለይ ይገባናል፣
-በፈሪሃ እግዚአብሔር ሁነን እግዚአብሔርን በመፍራት 
– ህይወታችንን በንስሓ አድሰን መፀለይ፣
– 
 
በአጠቃላይ ፤ በንፁህ ልቦና እንዲሁም በቅን መንፈስ ሆኖ መፀለይ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል እንደ ግርዶሽ የሆነውን ክፉ ስራችንን ገርስሶት እግዚአብሔርን ለማየት ስለሚያስችለን ልቦናችንን ንፁህ ማድረግ አለብን።  “የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መካከል እንደወደቀ ዘር ነው” ተብሎ በመፅሐፈ መነኮሳትና በሌሎችም መፅሐፍት ተመዝግ ይገኛል። 
 
-በፈሪሃ እግዚአብሔር ሁነን እግዚአብሔርን በመፍራት ህይወታችንን በንስሓ አድሰን መፀለይ ይገባናል። ምክንያቱም ሰው የእምነቱ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ማስቀደም አለበት፤ ቀጥሎም በፀሎት እግዚአብሔርን ለማመስገን ወይም ደግሞ የፈለገውን ለመጠየቅ ሰውነቱን እና መላ ህይወቱን በንስሓ ህይወት መቀደስ አለበት።
 
– ስንፀልይ ቀጥ ብለን በመቆምና አይናችንን ወደ ሰማይ በማቅናት ሃሳብን ሰብስቦ በአንድ ልብ ተወስኖ መፀለይ ይገባል። በፀሎት ግዜ መስገድ ይገባል፣ በፊታችንም ፣ ቅዱሳት ስዕላት፣ መስቀል ወይም ቅዱስ ወንጌል፣ ማድረግ ይገባል።
 
በአጠቃላይ እንደምንም ሃሳባችንን ከሚሰርቀው ረቂቅ መንፈስ ጋር እየታገልን አንዳንድ ጊዜ ከአይምሯችን እያወጣንና ከአይምሯችን እንዳንሆን ቢፈታተነንም ነገር ግን በመንፈስ እየታገልንም ቢሆን የረሳነውን ሃሳባችን እየመላለስን መፀለይ ብናዘወትር ሃሳባችንን የሚበታትንብን ጠላታችን እርኩስ መንፈስ ተማሮ እና የእግዚአብሔር ቃልም ስለሚዋጋው ከኛ ፈፅሞ እንዲርቅ ያደርግልናል።  ስለዚህ ዋናው ነገር ሳንሰለችና ተስፋ ሳንቆርጥ ህሊናን ሰብስቦ የመጸለይ መንፈሳዊ ህይወታችንን ደረጃ በደረጃ ለማሳደግ አብዝተን መለማመድ  ነው።
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ አባላቶቻችን ሁላችሁም በአንድ ልብ ሆኖ በእምነት መፀለይ ወይም ሃሳብን ሰብስቦ መፀለይን ተስፋ ሳንቆርጥ መለማመድ እንዳለብን እንመክራለን። 
ጠያቂያችን ሁል ግዜ በሃይማኖታችን እና በምግባራችን ፀንተን በመንፈሳዊ ህይወታችን ስለምናደርገው ተጋድሎ ሰይጣን ፈተና ያበዛብናል ማለትም ለመፆም ወይም ለመፀለይ ፣ ወይም ለመስገድ፣ ወይም የቱሩፋት ስራ ለመስራት፣ ወይም ለመቁረብ፣ ወይም ቤተክርስቲያን ለመሳለም፣ ይም ቃለ እግዚአብሔር ለመማር፣ ወይም ቃለ እግዚአብሔር ለማንበብ  የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ምግባር ለመፈፀም ባሰብን ጊዜ ስፍር ቁጥር የሌለው ምክንያትና ፈተና ያመጣብናል። የሰው ልጅ በክርስትና ሲኖር እረፍት የሌለው የተጋድሎ ህይወት እንደሚኖር በማስተዋል በአላማ መፅናትና ያሰበውን የፀሎት ሰዓትም ሆነ ሌላ መንፈሳዊ ፕሮግራም ስንፍና ሳያበዛና ምክንያት ሳይደረድር ቅድሚያ በመስጠት ለመፈፀም መጋደል አለበት።  በእርግጥ ክርስቲያን በአለም ሳለ የፈተና አረም እንደሚበዛብን ቢታወቅም እየወደቅንም እየተነሳንም ከራሳችን ክፉ ምኞትና ከውጭ ከሚመጣብን ፈተና ተቋቁመን እስከመጨረሻው የህይወታችን ፍፃሜ ድረስ መበርታት አለብን። ስለዚህ የዘወትር ፀሎታችንን ሆነ ለመፈፀም ያሰብነውን መንፈሳዊ ስርዓት ሳንታክት ከጊዜ ወደ ጊዜ ደረጃ በደረጃ በማሳደግ መፅናትና ላለመሸነፍ መታገል ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ይህን ምክራችንን እንደ አጠቃላይ ሃሳብ ይያዙትና እርስዎ በግልዎ ሊያደርጉ ስለሚገባዎ ተጨማሪ ምክርና ትምህርት ለመስጠት እንድንችል በተደጋጋሚ የሚፈተኑበትን ምክንያት ብናውቀው ቀሪውን ምክር እና ትምህርት ከሚሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ ተነስተን የምንሰጥዎ ይሆናል።
 
በተጨማሪም  ከፀሎት ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን ተከታታይ  ትምህርት አንብበው ሃሳቡን ይረዱት ዘንድ ሊንኩን እንደሚከተለው ልከንልዎታል ::http://Yohannesneseha.org/ትምህርት-ስለ-ተዋሕዶ/መሰረታዊ-ትምህርት
 
 ጠያቂያችን፤  አጋንንት ፈፅመው የሚርቁበት እና የሚጠፉበት ዋናው ጥበብና የሁላችንም መንፈሳዊ ሃይላችን የእግዚአብሔር ቃል ያለበት መፅሐፍ ሁሉ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ባለበት ሁሉ የቅዱሳንም የፀጋ አማላጅነትና ለሰው ልጅ ሁሉ የሚያደርጉት የተራዳይነት ምስጢር በዛ ውስጥ እናገኘዋለን። ስለዚህ በቆዳ ወይም በስፊ በጨርቅ የተጠቀለለ ፣ ታሽጎ ተጠቅልሎ የሚሰጥ፣ በግልፅ የማይታወቅና የማይረዳ ነገር ሁሉ እውነተኛ የፀሎት መፅሐፍ አይደለም፤ ወይም ደግሞ ከቶ ሊረዳን የሚችል እንደማይሆን መገንዘብ አለብን። በመሆኑም በራሱ በባለቤቱ በእግዚአብሔር ስም ወይም በእናቱም በድንግል ማርያም ስም ፣ ወይም በቅዱሳን ስም የተዘጋጁ የፀሎት መፃህፍት በውስጣቸው ያሉ ምስጢራዊ ኃይለቃል ስሙ ኅቡዕ የሚባለው ትርጉሙን ሁሉም ሰው ባያውቀውም ነገር ግን አጋንንትን ለማባረር እና ለማጥፋት ፈጽሞ መዶሻ ነው። ስለዚህ ዋናው ጥቅም እነዚህን የፀሎት መፃህፍትን ከቻልን እኛው እራሳችን መፀለይ፥ ካልቻልን ደግሞ የመፀለይ ፀጋ ያላቸውን አባቶችን እንዲፀልዩልን በማድረግ እንዲሁም በፀበሉ መጠመቅ፣ ቤታችንን እና ንብረታችንንም ሁሉ ማስረጨት እጅግ ጠቃሚ ነው። 
 
ከዚህ ውጪ በተለያየ ምክንያት ሰዎች ለንግድ ሲስተምና ለራሳቸው የግል ጥቅም ያዘጋጁትን አንዳንዶቹ የእግዚአብሔርን ቃል እየቆራረጡ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከጥንቆላ መፅሐፍት እየቀነጣጠቡ፣ አስማት በመፃፍ አጋንንት እናጠፋለን፣ የታመመን እናድናለን፣ ሌላ በረከት እናመጣለን ሲሉ  ፣ አንዳንዴም የሚሸጡ እና የታሸጉ የመፅሐፍትን ገዝቶ ማንጠልጠልም ሆነ መያዙ አስፈላጊ ወይመ ትክክል አይደለም። እንደዚህ ያለ ነገር ሲያጋጥም በውስጡ ያለውን ነገር በደንብ ለመረዳት ወደ ቤተክርስቲየን አባቶችን  መጠየቅ ይገባል።
 
ለህፃናትም ቢሆን በቤተክርስቲያን ተባርኮ እና ተፀልዮለት መስቀል በአንገታቸው እንዲያስሩ ማድረግ የቅዱሳንን ገድላት እና የመላእክትን ድርሳናት በመፀለይ በፀበሉ ማጥመቅ ወይም መርጨት ፣ ወንጌለ ዮሐንስን በመፀለይ ወይም የተለመደ የዘወትር ፀሎት በመፀለይ በፈጣሪያቸው ዘንድ የሚታወቁበትን የክርስትና ስማቸውን በመጥራት ለእነሱ ከተፀለየ ከልዩ ልዩ ፈተና እንዲጠበቁ እና በፀጋ እንዲያድጉ የሚደረግበት መንፈሳዊ ጥበብ ይህ ብቻ ነው እንጂ በአንገትና በወገብ አሸንክታብ ማሰርም ሆነ ማንጠልጠል የቤተክርስቲያን ስርአት አለመሆኑን ጠያቂያችንም ሆኑ የድረገጻችን አባላት ልትረዱት ይገባል።
ሰይፈ ስላሴ ሰይፈ መለኮት እግዚአብሔርን፥ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን የምናመሰግንበት የምስጋና መፅሐፍ ነው። ጠያቂያችን እንደገለፁት ይህን ፀሎት ይፀልዩት እንደነበረ አሁን ግን በስራ ምክንያት ወይም በድካም እንዳቋረጡት ከጥያቄዎ ሃሳብ ተገንዝበናል። ፀሎት የምንችለውን እንፀልያለን፤ ስንችልና ስንበረታ ፀሎታችንን እያሳደግን በምንጨምረው 12 ሰዓትም ሊሆን ይችላል 24 ሰዓትም ልንፀልይ እንችላለን። ካልቻልንም ደግሞ 10 ደቂቃም 20 ደቂቃም እንደአቅማችን እንፀልያለን እንጂ ከዚህ በፊት እፀልየው ነበር አሁን አቋረጥኩት የሚባል ነገር የለም። በመሰረቱ ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት ሰይፈ ስላሴ ወይም ሌሎችን ምእመናን ሁሉ በየደረጃቸው የሚፀልይዋቸው የፀሎት አይነቶች ማንም ሰው በፈቃዱ የሚፀልያቸው ስለሆነ የሚገደዱበት አይደለም። እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የምስጋና መፅሐፍ ነው። ስለዚህ የምንችለውን እንፀልያለን የማንችለውን እንተወዋለን ፤ አብዝተን ስንፀልይ የበለጠ ዋጋ እናገኛለን ፣ የበለጠ ክብር እናገኛለን ፣ትንሽ ስንፀልይ እና ስንተጋ ጸጋው እየበዛልን ይመጣል መንፈሳዊ ህይወታችንም እያደገ ይሄዳል። በእርግጥ ፀሎት መጀምር መተዉ መልካም ባይሆንም ካልቻልን ግን አንገደድም። የምንችለውን እንፀልያለን፥ አቅማችን እየበረታ መንፈሳዊ ህይወታችን እየጠነከረ ሲሄድ የፀሎት ህይወታችንን እያሳደግን 3 ሰአት ፣4 ሰአት፣ 5 ሰዓት ቆመን በፆም በፀሎት ተወስነን ከእንባ ጋር መፀለይ እንችላለን። ስለዚህ እስክንጠነክር የአቅማችንን መፀለይ እንችላለን እንጂ ግዳጅ የሚባል ፀሎት የለም። ምስጋና  ነው ፀሎት፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ በዚህ ሰዓት እፀልየው ነበር አቋረጥኩት ቅጣት አለው ወይ የምንለው ነገር ይሄ አያስኬድም። የምንችለውን እንደአቅማችን፣ እንደጥንካሬያችን ልንፀልይ ይገባል። ይህን ስንል ግን በዚህ ፈተና በበዛበት አለም እሾህ እና አሜኬላ በሚፈራረቁበት ህይወት እየኖርን ያለፀሎት መኖር ማለት ከህይወት የተለየ ስጋ እንዳለው ማለት ስለሆነ ጨርሶ የእግዚአብሔር ረድኤትና ጥበቃ እንዳይለየን ሌላው ባይቻለን እንኳን ቢያንስ አባታችን ሆይ የሚለውን ፀሎት የሁሉም ክርስቲያን መለያ በመሆኑ መፀለይ እንደሚገባ እንመክራለን ።
 
ከዚህ ውጪ ጠያቂያችን ህልም አያለው ስላሉት ከዚህ ጋር የሚገናኝ ስላልሆነ የምናየው ባይሆንም፥ አላማ ማሰናከል እና ለማደናቀፍ ሰይጣን በተለያየ ምክንያት ሊፈትን ስለሚችል ብዙ የማይከብድ ፀሎትን ደረጃ በደረጃ መፀለይ፣ ፀበል መጠጣት እና መጠመቅ በመስቀል መባረክና እምነት መቀባት እነዚህን ሁሉ በማድረግ በመንፈሳዊ ህይወትዎ እንዲበረቱና በአላማዎ እንዲጸኑ  እየመከርን በተጨማሪም ከፀሎት ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን ተከታታይ ትምህርት አንብበው እንዲረዱት ከዚህ በታች ሊንኩን ልከንልዎታል።   
ፀሎት ስናደርግ ስርዓት አለው ። በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ወገብ መታጠቅ ማለት ‘ ወገባችሁ የታጠቀ መብሪታችሁም የበራ ይሁን’ ይላልና  ሉቃ 12፥35 ይህም በንቃት በተመስጦ በሰቂለ ህሊና በአንቃዶኦ ልቦና  የክርስቲያን ህማሙን ስቃዩን እያሰብን ፣ያደረገልልን የፍቅሩን ብዛት ስለሀጢአታችን እያዘን እያለቀስን መሆን አለበት እንድ ነጠላ መጣፋትን ብቻ ለማሳየት አይደለም ልብሳችንን ቀዳደን ራቁታችንን በራሳችን ላይ አመድ እየነሰነስን ብናነባ የበለጠ ክብር አለው ይህን ለማስተማር ነው ።        
  
 ከጸሎት በፊት መስገድ ይገባል ፊታችንን ወደ ምስራቅ አዙረን ስዕለ  አድህኖአችንንም  በዚያ አቅጣጫ አስቀምጠን መሆን አለበት።
 
ስግደት አማትበን መጀመሪያ ለቅድስት ስላሴ ሶስት ጊዜ የአምልኮት ስግደት ግንባራችንን መሬት እያስነካን፤ ከዚያ እንደገና በሚሰገድባቸው ቀናት የምንችለውን ያህል ሰግደን ስጋችን ሲዝል በተመስጦ መጸለይ ተሰሚነቱ የበለጠ ይሆንልናል።
 በተጨማሪ ከዚህ በፊት ስለ ጸሎት ያስተላለፈውን ትምህርት ይመለከቱ ዘንድ እንመክራለን ። https://yohannesneseha.org/ትምህርት-ስለ-ተዋሕዶ/መሰረታዊ-ትምህርት

ጠያቂያችን፤ አዎ ልክ ነው ፥ ፀሎት መኝታ ቤት ማድረግ ይቻላል።  የተለየ ፀሎት ቤት ከሌለን ቤታችን ጠባብ ከሆነ ባለችን ቤት ውስጥ ህሊናችንን ሰብሰብ አድርገን እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር ዘርግተን መጮህ ነው፥ ማልቀስ ነው፤ ባለንበት ቦታ፤ ‘ድረስልን አባቴ’ ብለን ስሙን ደጋግመን መጥራት ነው። ያኔ እግዚአብሔር የልጆቹን ልመና ይሰማል። በየትም ቦታ ይሁን ዋናው ትልቁ ነገር ልብ ነው፤ ‘እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው‘’ ይላል መዝሙረ ዳዊት። እና እንደውም አንዳንድ ቅዱሳት መፃህፍት ስናይ  ጣማ ፌሬን የምትባል ሆስፒታል ውስጥ ነው የምትኖረውና ሽንት ቤት ሄዳ ትፀልይ ነበር ፤ ሽንት ቤት የምትፀልይበትም ምክንያት የፀሎት ሰዓት እንዳታጎልባት ነበርና በተመስጦ ትጸልይ ነበር። ይቺን ሴት  እመቤታችን በገኀድ ተገልፃ የምታነጋግራት የምታወራት እጇን ይዛ ልጄ በርቺ የምትላት ናትና፤እግዚአብሔር ለተዓምር የፈጠራት ሰው ነበረች። ውጭ አገር ለህክምና ሄዳ ነው፤ እግአዚአብሔር ውጭ የላካት የእግዚአብሔር ተዓምር እንዲገለፅ ነው እንግዲህ። እና ጣማ ፌሬን  አልጋ ላይ ሆና እመቤታችን ተገለጻ አየቻትና ‘አብረን እንፀልይ’ ስትላት፤ ‘አልችልም አለቻት’፤ ‘ለምን?’ አለቻት፤ ‘እኔ የምፀልየው ሽንት ቤት ነው’ አለቻት። ቅዱሳን አንስት የሚለውን መፅሐፍ ማንበብ ይቻላል።   እና የቦታ ጉዳይ አይደለም ዛሬ ሽንት ቤት እየሆነ ያስቸገረን ልባችን እንጂ ቦታው አይደለም። ቢያንስ በረግረግ ውስጥ በገደል ውስጥም ቢሆን ውስጣችንን የተመቸ፣ እግዚያብሄር የሚነግስበት አድርገን በእንባ እየታጠብን ብንጠራው እግዚአብሔር ፈጥኖ ይደርሳል።ዮናስ በአሳ አንበሪ ውስጥ ሆኖ ነው እጆቹን የዘረጋው ስለዚህ ዋናው ትልቁ ነገር በንፅህና ፣በቅድስና፣ በእንባ ፣ከቂም በቀል ነፃ ሆኖ ፈጣሪን መጥራት ነው እንጂ በየትም ቦታ ሆኖ እግዚአብሔር ይሰማል። የተህዶ አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር የሞትከው አባቴ አምላኬ ሆይ ልጅህን አቤት በለኝ ብለን የትም ቦታ ሆነን እንጥራው ቅርብ ነው፥ እሩቅ አይደለም። ስለዚህ የትም ቦታ ሆነን መጥራት እንችላለን ቅርብ ነው ሩቅ አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን የትም ቦታ ሆነን እግዚአብሔርን መጥራት እንችላለን።

ቤተክርስቲያን መሄድ ካልቻልን ቅዱሳን ስዕላን በፊታችን አድርግን በተመስጦ ቤታችን መፀለይና መስገድ ይቻላል፥ ይሄ ይፈቀዳል። ስግደትን መስገድ ፊታችንን ወደ ምስራቅ አዙረን ስዕለ አድህኖ አድርገን ቤት ውስጥ በተመስጦ መስገድ ይቻላል። ነገር ግን ቤተክርስቲያን የምንሄድባቸው ሰዓቶች አሉ፦ ይህም ቤተከርስቲያን በቅርባችን ካለ ወይም ከተመቸና ቅርብ ከሆነ ጠዋት በሌሊት እና ማታ ሰርክላይ መሄድ ያስፈልጋል። ራቅም ቢል ደግሞ ቢያንስ እለተሰንበትን እንኳን ቤተክርስቲያን መሄድ ያስፈለጋል። ቤተክርስቲያን በሌለበት አካባቢ ደግሞ የክርስቲያን ቤት ማለት ቤተክርስቲያን ማለት ነው በቀደመው ዘመን ቤተክርስቲያን ባይኖር እኮ የቀደሙት አባቶች በሰዎች ቤት ነበር ስርዓትን የሚፈፅሙትው። ስለዚህ አሁንም ቤተክርስቲያን በሌለበት አካባቢ ክርስቲያኖች ስለሆንን ቤታችን ሁነን ፀሎት ብናደርግ እግዚአብሔር አልሰማችሁም አይልም ። ዋናው ትልቁ ነገር በአግባቡ በተመስጦ ልቦናን ቤተከርስቲያን ማድረግ ነው። ነገር ግን ቤተክርስቲያን በቅርብ ካለ ከላይ እንደገለፅነው ጠዋት በሌሊት  እና ማታ ደግሞ በሰርክ ማድረግ አለብን፥ ከዛ ቤታችን መጥተን ፀሎት ማድረግ እንችላለን። ባጠቃላይ ቤት ውስጥ ፀሎትና ስግደት ማድረግ አይከለክልም ነገር ግን ቅድሚያ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሄድ ያስፈልጋል ፦ ጠዋት እና ማታ። እሩቅ ከሆነ ግን አንዳንዴ እንደ ሁኔታዎች እያየን ቢያንስ እለተ ሰንበትን ሳንደርስ መቅረት እንደሌለብን እንመክራለን። 
 
በተጨማሪም፤ የቦታ ችግር ከሌለብን ራሱን የቻለ ቦታ ጠዋትም ማታም ራሳችንን ለይተን የዘወትር ፀሎታችንን የምናደርስበት የተለየ ቦታ ቢኖረን መልካም ነው። ከሌለን ደግሞ የኛን ችግር ከኛ በላይ እግዚአብሔር ያውቀዋልና በዛችው በምንኖርባት ጎጇችን ውስጥ ጠዋት ከመኝታችን ተነስተን ተጣጥበን ሳሎን ላይም ቢሆን ቁመን መፀለይ ይቻላል። 
 
ለፀሎት የምንገለገልባቸውን መፅሐፍት እና ሌሎችን የመንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ማንኛውንም ነገር የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው መቀመጥ አለባቸው። እኛም ለመፀለይ ስንፈልግ ካደርንበት መኝታችን ተነስተን የአድህኖ እና የምንፀልይበት ቦታ ላይ ሄደን የተለመደውን የእለት ፀሎታችንን ማድረስ፤ ከላይ እንደገለጽነው ቦታ ባይኖረንም እንኳን ከተኛንበት ቦታ ላይ ርቀን በውጭም ሆነ በሳሎን ውስጥ ሆነን መፀለይ፤ በተለይ ባል እና ሚስት የግብረስጋ ግንኙነት አድርገው በአደሩበት ቀን ወይም እዛ ቦታ ላይ ቅዱሳት ስዕላት ማስቀመጥ ስርዓተ ቤተክርስቲያን የተከለከለ ነው።
 
ቅዱሳን ስእሎችንም በምንበላበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንተኛበት ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ እንደ ጌጥ ማንጠልጠል በልማድ የመጣ እንጂ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ስርአት አይደለም። መክንያቱም ስእላቶቹ በቤተመቅደስ ውስጥ ከታቦታቱ ጋር አክብረን ስርአተ አምልኮት የምንፈፅምባቸው ስለሆኑ የተለየ ቦታ አዘጋጅተን በቤታችን አካባቢ የተለየ ቦታ ከምንተኛበትና ምግብ ከምንበላበት ውጪ የተለየ ቦታ አዘጋጅተንላቸው ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አባት አስባርከን በንፅህና ሆነን እንድንፀልይባቸው ይፈቀዳል።
ጠያቂያችን፤ ጥያቄዎት በደንብ ግልፅ አይደለም። የሆነ ሆኖ ግን በቤተክርስቲያን አንድ ኦርቶዶክስ በምን አይነት መፀለይ እንዳለበት ቀኖና አለው። የፀሎት ሁሉ ጀማሪና መስራች ወይም ባለቤት እራሱ ባለቤቱ መድኃኒአለም ክርስቶስ ነው። እሱም በቅዱስ ወንጌል በብዙ ቦታ እንደተገለፀው ከፊትህ ወዝ እስከሚወጣ ወይም  ሰውነትን እስኪያልብ ተንበርክኮና ወገብንም ታጥቆ እንደፀለየ እንረዳለን። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ፀሎት ከመጀመሩ በፊት ለጸሎት እራሱን በስርዓት ማዘጋጀት አለበት። እርሱም፦
1ኛ የፀሎት ቦታ የት እንደሆነ ወይም ቆሞ የሚፀልይበት ቦታ የትኛው እንደሆነ ለይቶ መወሰን፣
2ኛ ለፀሎት ህሊናውን ወይም አይምሮውን ማዘጋጀት፣
3ኛ ፀሎት ለፈጣሪ ለሰማያዊ አምላክ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ልመና እንደሆነ ማመን፣
4ኛ ፀሎት በሥጋ እና በነፍስ የእግዚአብሔርን በረከት እና ሰማያዊ ዋጋ ለማግኘት እግዚአብሔርን የመንለምንበት ምስጢራዊ ጥበብ መሆኑን በማስተዋል መረዳት፣
5. ፀሎትና ስግጀት ስንጀምር መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ማማተብ ፣ምክንያቱም በትምእርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን ፀሎት ከመጀመራችን በፊት የምናማትበው በሃሳብ የሚቃወመንን እና ከፈጣሪያችን ጋር በፀሎት እንዳንገናኝ የሚፈታተነንን እርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሃይል ቀጥቅጠን ከእግራችን ስር ለመጣል ወይም ፈፅሞ ከእኛ እንዲርቅ ለማድረግ ነው። 
 
6ኛ አለባበሳችን ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መሆናችንን የሚገልፅ መሆኑን መስቀለኛ መልበስ፣ ፊታችንን በትእምርተ መስቀል በአብ፥ በወልድ ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማማተብ፣ መስቀለኛ ለብሰን የምናሳየው ፍጹም ክርስቲያናዊ ትህትና እንዳለን ለመግለፅ ሲሆን በችግር ምክንያት ልብስ የሌለው ሰው ካለ፥ እግዚአብሔር የማያውቀው ነገር የለምና በሚለብሰው ልብስ የምንገልፀው ውስጣዊ ህሊናችንን ለእግዚአብሔር ያስገዛን መሆኑን በትእምርተ መስቀል ስናማትብ የመስቀል አርአያ ስለሆነ በዚህም አጋንንት ድል የምንነሳበት ክፉ መንፈስ ወደኛ እንዳይቀርብ በመስቀል ቅርፅ መንፈሳዊ አጥራችን የምናጥርበት መሆኑን ያሳያል። በአጠቃላይ በዚህ አይነት ፀሎታችንን ልናከናውን እንችላለን። ጠያቂያችን በመግቢያው እንደገለፅነው ጥያቄዎትን በግልፅ ሳንረዳው ቀርተን ያልተመለሰ ሃሳብ አለኝ ካሉ በውስጥ መስመር አግኝተው ቢገልፁልን ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥዎት እንችላለን። 
 
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ ላይ ያገኛሉ

የበሃይማኖት (በተአምኖ) የሚኖር ክርስቲያን ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገርበት ምስጢራዊ ቋንቋ ነው። ማንኛውም ክርስቲያንም ሆነ ምእመን በየዕለቱና በየሰዓቱ መጸለይ ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው። የሰው ልጅ በሥጋዊ ባሕርይው ሣይበላ እና ሳይጠጣ መኖር እንደማይችል ሁሉ በየሰዓቱና በየጊዜያቱ ካልፀለየ ነፍስ ትራባለች፣ ትጠማለች መላ ሕይወቱም ከእግዚአብሔር በረከት ይርቃል። ስለዚህ ጸሎት በክርስትና ሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ከዚህ በፊት ስለ “ስርዓተ ጸሎት” በተከታታይ ክፍል ያስተላለፍነው መደበኛ ትምህርት ላይ፦

1ኛ/ ስለ 7ቱ የጸሎት ጊዜያት፣
2ኛ/ በምን አይነት መንገድ መፀለይ እንዳለብን፣
3ኛ/ ምን መፀለይ እንዳለብን፣ 
4ኛ/ እንዴት መፀለይ እንዳለብን አጭር መልእክት እናስተላልፋለን። 

ስለዚህ ጠያቂያችን፤ ጸሎት ራሱን የቻለ ሰፊ ተምህርት ሲሆን እርስዎ ለማወቅ የፈለጉትን ክፍል ለይተው ስላልገለጹልን፤ ምናልባትም ከዚህ በፊት   ስለጸሎት ያስተላለፍነውን ካላይ የጠቀስነውን  የትምህርት ክፍል አልተመለከቱት ከሆነ ሊንኩን ከዚህ በታች ልከንልዎታልና ሊንኩን በመጫን እንዲያነቡት በአጽንዎት እንመክራለን። በተጨማሪም ስለ ጸሎት ቀርበውልን የነበሩ ጥያቄዎችን መሰረት አድርገን ያስተላፍናቸውን መልዕቶችም እንዲመለከቱ ሊንኩን አያይዘንልዎታል

በአጠቃላይ ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን መልዕክት በድጋሚ ልከንልዎታልና  በመጀመርያ ይህን አንብበው ተረድተው  ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆነልዎት ሃሳብ ካለ ቢያሳውቁን ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥዎ እን ችላለን።

https://yohannesneseha.org/ትምህርት-ስለ-ተዋሕዶ/መሰረታዊ-ትምህርት/

 ጠያቂያችን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የእግዚአብሔር ቃል ያለበትን መፅሐፍ ሁሉ እንዳያነቡና እንዳይጠቀሙበት የሚከለክለው ሌላ ነገር ሳይሆን የሰይጣን መንፈስ ነው። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እርኩስ መንፈስ በመንፈሳዊያን ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ፈተና እጅግ የረቀቀ እና ፈተናውም ተቆጥሮ የማያልቅ እንደሆነ በገለፅነው መሰረት ዛሬም በእርስዎ ላይ ቃሉን በማንበብ መንፈሳዊ ህይወትዎን እንዳይመሩ ከሚከለክልዎት፣ በቃሉ ህይወትነት እንዳይጠበቁ በተያየ መንገድ የሚያሰናክልዎትና በአይምሮ፣ በአይን፣ በጆሮ፣ በአንደበት አዚምን የሚጥል ውስጣዊ ልቦናን የሚያጨልም እርሱ እርኩስ መንፈስ እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል። ሰይጣን ከክፋቱ የተነሳ በእግዚአብሔር ቤት ሁል ጊዜ ለምስጋና እና ለፀሎት የሚተጉት ሰዎችን ከተቀደሰ ቋሚ አላማቸው ያወጣቸው ዘንድ የማይወረውረው የክህደት ድንጋይ የማይቆፍረው የጥፋት ጉድጓድ የለውም። ብቻ እንደ ሰው ልጅ የተለያየ የስራ ብዛት፥ ቢዚ የማያደርገው የጥፋት ስራ የለም። ሁል ጊዜ የሰይጣን አላማውና የስራ ትኩረቱ የሰውን ልጅ በማሳሳት እና ከመንፈሳዊ አላማው ጠልፎ በመጣል ከእግዚአብሔር መንገድ ማውጣት ብቻ ነው። ሰይጣን በረቂቅ ጥፋቱ በቋሚነት የሚሰራው የጥፋት ስራ በመንፈሳዊያን ሰዎች ህይወት ላይ ብቻ ያነፃፀረ ነው።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን አንዳንድ ጊዜ በክርስትናችን ወይም በመንፈሳዊ ህይወታችን የሚያጋጥሙንን እና ደረሰብን የምንላቸውን የሰይጣን ፈተናዎች ለመቋቋም በሚያስችል መንፈሳዊ ፅናት መቀጠል ሳንችል ሰይጣን በብዙ መንገድ የሚያሰለች ፈተና ቢያደርስብን እንኳን አንድ ቀንም ሳንበገር ፈተናውን ከተቋቋምነው ከዚያ ሰይጣን ድል ተነስቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእኛ ይጠፋል። በእርግጥም የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ቃሉ ሰይፍ ስለሆነ ይቆራርጠዋል፣ ቃሉ እሳት ስለሆነ የቃጥለዋልና እኛን በቃሉ ህይወትነት እዳንኖር እና ደጋግመን የእግዚአብሔርን ቃል እንዳናነብ ስሙን እንዳንጠራ እንዳንፀልይ የአዚም መጋረጃውን በእኛ ላይ የመጋረድ ሁኔታ የሱ ቋሚ ሰይጣናዊ ስራ ስለሆነ እንዲህ አይነት ችግር አጋጠመኝ ብለው ፈተናውን እንደ ትልቅ ምክንያት ቆጥረው ከአላማዎ ፈቀቅ ማለት የለብዎትም።
 
ለዚህም መፍትሄው፦
 
– ሳይሰለቹ ቃሉን ማንበብ፣ ህሊናዎትን ቃሉን እንዳይገነዘብ በፈተነዎት ቁጥር እየመላለሱ ማንበብ እና የሚያነቡትን ቃል ምን እንደሚል ትኩረት ሰጥተው ደጋግመው ማንበብ ሲችሉ ያኔ ያ እርኩስ መንፈስ ሰልችቶት ወይም ተሸንፎ ከእርስዎ ይሄዳል። 
-በተጨማሪም መፀለይ አለብዎት፤ ቢያንስ ጠዋት እና ማታ የማያቋርጡት ፀሎት ሊኖርዎት ይገባል። ጸሎት ስንጀምርና መንፈሳዊ መጽሐፍ ስሰናብ መላ ሰውነታችንን በትምእርተ መስቀል ማማተብ ይገባናል። ምክንያቱም በትምእርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን ፀሎት ከመጀመራችን እና ከማንበባችን በፊት የምናማትበው በሃሳብ የሚቃወመንን እና ከፈጣሪያችን ጋር በፀሎት እንዳንገናኝ የሚፈታተነንን እርኩስ መንፈስ በመስቀሉ ሃይል ቀጥቅጠን ከእግራችን ስር ለመጣል ወይም ፈፅሞ ከእኛ እንዲርቅ ለማድረግ ነው። የጨለማ ሃሳብ ተገፎ ከእኛ እንዲርቅ እና በብርሃን ለመመላለስ እንድንችል መላ ሰውነታችንን እና ፊታችንን ስናማትብ ከላይ ወደታች ከግራ ወደቀኝ ማማተብ ይገባል።
– ሌላው ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ በአባቶች እጅ በመጠመቅ እና በመስቀሉም በመባረክ ቅዱስ ቅባትንም በመቀባት ይሄንን የሚፈታተንዎትን እርኩስ መንፈስ ማራቅ ይችላሉ። ተጨማሪ ትምህርት እና ምክር ካስፈለግዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
 
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ኃይል ከእርስዎ ጋር ይሁን!
 
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ