ቤተክርስቲያን መሄድ ካልቻልን ቅዱሳን ስዕላን በፊታችን አድርግን በተመስጦ ቤታችን መፀለይና መስገድ ይቻላል፥ ይሄ ይፈቀዳል። ስንሰግድ ፊታችንን ወደ ምስራቅ አዙረን፥ መስቀል ወይም ስዕለ አድህኖ ወይም ቅዱሳን ስዕላት ወይም ወንጌል በፊታችን አድርገን በትዕምርተ መስቀል እያማተብን ጉልበታችንን እና ግንባራችንን መሬት እያስነካን ቤት ውስጥ በተመስጦ መስገድ ይቻላል።
ነገር ግን ቤተክርስቲያን የምንሄድባቸው ሰዓቶች አሉ፦ ይህም ቤተከርስቲያን በቅርባችን ካለ ወይም ከተመቸና ቅርብ ከሆነ ጠዋት በሌሊት እና ማታ ሰርክ ላይ መሄድ ያስፈልጋል። ራቅም ቢል ደግሞ ቢያንስ እለተሰንበትን እንኳን ቤተክርስቲያን መሄድ ያስፈለጋል። ቤተክርስቲያን በሌለበት አካባቢ ደግሞ የክርስቲያን ቤት ማለት ቤተክርስቲያን ማለት ነው በቀደመው ዘመን ቤተክርስቲያን ባይኖር እኮ የቀደሙት አባቶች በሰዎች ቤት ነበር ስርዓትን የሚፈፅሙትው። ስለዚህ አሁንም ቤተክርስቲያን በሌለበት አካባቢ ክርስቲያኖች ስለሆንን ቤታችን ሁነን ፀሎት ብናደርግ እግዚአብሔር አልሰማችሁም አይልም ። ዋናው ትልቁ ነገር በአግባቡ በተመስጦ ልቦናን ቤተከርስቲያን ማድረግ ነው። ነገር ግን ቤተክርስቲያን በቅርብ ካለ ከላይ እንደገለፅነው ጠዋት በሌሊት እና ማታ ደግሞ በሰርክ ማድረግ አለብን፥ ከዛ ቤታችን መጥተን ፀሎት ማድረግ እንችላለን። ባጠቃላይ ቤት ውስጥ ፀሎትና ስግደት ማድረግ አይከለክልም ነገር ግን ቅድሚያ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሄድ ያስፈልጋል ፦ ጠዋት እና ማታ። እሩቅ ከሆነ ግን አንዳንዴ እንደ ሁኔታዎች እያየን ቢያንስ እለተ ሰንበትን ሳንደርስ መቅረት እንደሌለብን እንመክራለን።
በተጨማሪም፤ የቦታ ችግር ከሌለብን ራሱን የቻለ ቦታ ጠዋትም ማታም ራሳችንን ለይተን የዘወትር ፀሎታችንን የምናደርስበት የተለየ ቦታ ቢኖረን መልካም ነው። ከሌለን ደግሞ የኛን ችግር ከኛ በላይ እግዚአብሔር ያውቀዋልና በዛችው በምንኖርባት ጎጇችን ውስጥ ጠዋት ከመኝታችን ተነስተን ተጣጥበን ሳሎን ላይም ቢሆን ቁመን መፀለይ ይቻላል።
ለፀሎት የምንገለገልባቸውን መፅሐፍት እና ሌሎችን የመንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ማንኛውንም ነገር የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው መቀመጥ አለባቸው። እኛም ለመፀለይ ስንፈልግ ካደርንበት መኝታችን ተነስተን የአድህኖ እና የምንፀልይበት ቦታ ላይ ሄደን የተለመደውን የእለት ፀሎታችንን ማድረስ። በተለይ ባል እና ሚስት የግብረስጋ ግንኙነት አድርገው በአደሩበት ቀን ወይም እዛ ቦታ ላይ ቅዱሳት ስዕላት ማስቀመጥ ስርዓተ ቤተክርስቲያን የተከለከለ ነው።
ቅዱሳን ስእሎችንም በምንበላበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንተኛበት ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ እንደ ጌጥ ማንጠልጠል በልማድ የመጣ እንጂ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ስርአት አይደለም። ምክንያቱም ስእላቶቹ በቤተመቅደስ ውስጥ ከታቦታቱ ጋር አክብረን ስርአተ አምልኮት የምንፈፅምባቸው ስለሆኑ ብንችልና በቂ ቦታ ካለን በቤታችን ከምንተኛበትና ምግብ ከምንበላበት ውጪ የተለየ ቦታ አዘጋጅተንላቸው ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አባት አስባርከን በንፅህና ሆነን እንድንፀልይባቸው እንመክራለን።