ስለ ፀሎት ጥያቄና መልስ
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ፀሎት የጥያቄና መልስ
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሰረት ካህን የሚጸልየው ጸሎት አለ፤ ምእመናንም የሚጸልዩት የራሱ ስርአተ ጸሎት አለ። በዚህኛው ዘመን በምእመናን ዘንድ የሚታየው ትልቁ የጸሎት ከፍተት እንደ ጥንት ክርስቲያኖች ለግል ጸሎት የሚያበቃ ሃይማኖታዊ እውቀት የለንም። በእርግጥ ወደየቋንቋው የተተረጎሙ ቢሆኑም እንኳን ሰው ግን ሁልጊዜ በጸሎት የመትጋት ፕሮግራም የለውምና ያም ሆኖ የሚጸልየው ሰው ያንሳል። ጠያቂው እንዳሉት ለመጸለይ አንድ ሰው የዘወትር ጸሎት በሚለው የጸሎት ክፍል በስመ አብ ከሚለው ጀምሮ ከቻለ እስከ ጸሎተ ማርያም ይጸልያል ፤ ከዚያም ከቻለ የየዕለቱን ውዳሴ ማርያም ይጸልያል። አሁንም የሚችል ከሆነ ቅድሚያ በመስጠት የየዕለቱን መዝሙረ ዳዊት በግዕዙ ባይቻልም በአማርኛው ወይም በሌላ በሚያውቀው ቋንቋ መጸለይ ይችላል።
ከዚህ ወጪ ደግሞ የሚጸለዩ ፦ ውዳሴ አምላክ ፣ የቅዱሳን መልክ ፣ ሰይፈ ሥላሴ፣ ሰይፈ መለኮት እነዚህ እነዚህ ሁሉ አንድ ከርስቲያን ሊጸልይባቸው የሚገባ የጸሎት አይነቶች ናቸው።
ሌለው ጠዋት ሲነሳ ፊቱን አማትቦ በያንስ አቡነ ዘበሰማያትን ሊደግምና ሰላም አውለኝ ብሎ ወደ ስራ መሄድ አለበት። ማታም ሰላም ያዋልከኝ አምላክ ሰላም አሳድረኝ ብሎ በአቡነ ዘበሰማያት አመስግኖ መተኛት አለበት። ይሄ ማንኛውም ክርስቲያን የሚገደድበት ክርስቲያናዊ ሕግ ነው።
ለመፀለይ ፍርሀት ስጋት እና ጥርጣሬ አያስፈልግም። በእምነት ሁነው ብቻ መፀለይ ነው። የዳዊት ፀሎት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊትን ጠላቶቹን ሁሉ በእግሩ እርግጥ በእጁ ጭብጥ አድርጎ እንዲገዛቸው ግርማውንና ሞገሱን ያጎናጽፈው የነበረው በዚህ ፀሎቱ ነው። ዘመኑ ሁሉ ታድሶለት የጠላቸውን ሁሉ ውድቀት አይቶ ግዛቱ ሁሉ ተመቻችቶለት የኖረው በዚሁ ፀሎት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን የዳዊት መዝሙር የየራሱ ክፍል ስላለው በፈለጉት ቋንቋ መዝሙረ ዳዊትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፀለይ ይችላሉ።
በየአለቱ የሚፀለይ የዳዊት መዝሙር ክፍሎች፦
ከመዝሙር 1 – 30 ሰኞ የሚፀለይ መዝሙር ነው
” 31 – 60 ማክሰኞ የሚፀለይ መዝሙር ነው
” 61 – 80 ሮብ የሚፀለይ መዝሙር ነው
” 81 – 110 ሐሙስ የሚፀለይ መዝሙር ነው
” 111 – 130 አርብ የሚፀለይ መዝሙር ነው
” 131 – 150 ቅዳሜ የሚፀለይ መዝሙር ነው
“151በኋላ/ፀሎት ነብያት እሁድ የሚፀለይ ነው
ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት አውራ መንገድ ወይም ድልድይ ወይም ደግሞ የስልክ መስመር ነው። ከዚህ የተነሳ ፀሎት ለመጀመር ምንም አይነት ፕሮግራም መያዝ አያስፈልግም በጊዜውም ያለጊዜውም ማንኛውም ክርስቲያን ሲነሳም ሲተኛም፣ ሲበላም ሲጠጣም፣ ሲሰራም ሲያርፍም ባጠቃላይ በነገር ሁሉ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት ቆንቋ ፀሎት ነው።
ስለዚህ ሰይጣን ስንፍና አብዝቶብን ካልራቅን በስተቀር ፀሎት በምንችለው አቅጣጫ ሁሉ ልንጸልይ፣ እግዚአብሔርን በፀሎት ልንለምነው፣ ልናመሰግነው እና ልናመልከው ይገባል። ያው የፀሎት አቀራረብ እንደየአቅማችን ይለያያል። አብዝቶ የጸለየ እግዚአብሔርን አብዝቶ ስለወደደ ብዙ በረከት ከእግዚአብሔር ያገኛል። በጥቂቱ የጸለየ ደግሞ እግዚአብሔርን በጥቂቱ ስለወደደ ጥቂት በረከት ከእግዚአብሔር ሊያገኝ ይችላል።
ስለዚህ ወንድሜ በዚህ ፈተና በበዛበት አለም እሾህ እና አሜኬላ በሚፈራረቁበት ህይወት እየኖርን ያለፀሎት መኖር ማለት ከህይወት የተለየ ስጋ እንዳለው አስክሬን ማለት እንሆናለን። ምክንያቱም ጨርሶ የእግዚአብሔር ረድኤትና ጥበቃ ሊለየን ይችላል። ሌላው ባይቻልዎት ቢያንስ እንኳን አባታችን ሆይ የሚለውን ፀሎት የሁሉም ክርስቲያን መለያ በመሆኑ በቅርብ ካሉ አባቶች ወይም ምእመናን በመጠየቅ መጸለይ እንደሚያስፈልግዎት አንመክራለን።
መልስ፦ በመካከላችን ሊባርክ የሚችል ካህን ከሌለ እኛም ክርስቲያኖች ስለሆንን በስላሴ ስም መባረክ ስላለብን በመጀመሪያ በስመ አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በማለት በትእምርተ መስቀል ፊታችንን እና ማዕዱን ከባረክን በኋላ አቡነ ዘበሰማያትን ጸልየን ጌታ ሆይ ይህን ማዕድ የህይወት ምግብ ይሆን ዘንድ ባርከህ ቀድሰው ብለን መመገብ።
የቦታ ችግር ከሌለብን ራሱን የቻለ ቦታ ጠዋትም ማታም ራሳችንን ለይተን የዘወትር ፀሎታችንን የምናደርስበት የተለየ ቦታ ቢኖረን መልካም ነው። ከሌለን ደግሞ የኛን ችግር ከኛ በላይ እግዚአብሔር ያውቀዋልና በዛችው በምንኖርባት ጎጇችን ውስጥ ጠዋት ከመኝታችን ተነስተን ተጣጥበን ሳሎን ላይም ቢሆን ቁመን መፀለይ ይቻላል።
ቅዱሳን ስእሎችን በምንበላበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንተኛበት ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ እንደ ጌጥ ማንጠልጠል በልማድ የመጣ እንጂ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ስርአት አይደለም። መክንያቱም ስእላቶቹ በቤተመቅደስ ውስጥ ከታቦታቱ ጋር አክብረን ስርአተ አምልኮት የምንፈፅምባቸው ስለሆኑ የተለየ ቦታ አዘጋጅተን በቤታችን አካባቢ የተለየ ቦታ ከምንተኛበትና ምግብ ከምንበላበት ውጪ የተለየ ቦታ አዘጋጅተንላቸው ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አባት አስባርከን በንፅህና ሆነን እንድንፀልይባቸው ይፈቀዳል። ቅዱሳት ስእል ግን ቅባ ቅዱስ አይቀባም።
‘የፀሎት ውሀ’ ያሉት አነጋገሩ የቤተክርስቲያን ቋንቋ ባይሆንም ጠያቂያችን ግን ይረዱት ዘንድ ቤታችን ውስጥም ዘወትር ስንፀልይ ከቤተክርስቲያን በእቃ ያመጣነውን ፀበል ወይም ደግሞ የቤተክርስቲያን አባት ፀሎት አድርሰውበት በእቃ ያስቀመጥነውን ፀበል ልዩ ቦታ ላይ አስቀምጠን ግቢያችንን ልንረጨው እኛም ልንጠመቅበት ብንችል የእግዚአብሔር በረከት እና ቸርነት ወደ እኛ ይቀርባል። ዘወትር የሚቃወመን የሰይጣን መንፈስ ደግሞ ከእኛ እንዲርቅ ይሆናል በዚሁ መሰረት ፀበል ማለት በቤታችን ውስጥ ዘወትር የሚኖር መዝገበ ፀሎት ወይም ከቤተክርስቲያን የምናመጣው ፀበል በመባል ይታወቃል።
መጀመርያ 7ቱ ሊቃነ መላእክት ያሉትን ዝርዝራቸውን እነማን እንደሆኑ ቢገልፁ ለጥንቃቄ መልካም ነው። ያገኙት የፀሎት መፅሃፍ በአንድ ላይ የታተመ መሆኑን እና በየራሳቸው መሆኑን ቢገልፁልን መልካም ነው። ይህን ካልን በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እውቅና ሰጥታ ያሳተመቻቸው የፀሎት መፅሐፍ ሁሉ የሚከለከልበት የለምና መፀለዮት ተገቢ ስለሆነ በርትተው በፀሎቱ ይቀጥሉ። ነገር ግን በኤሌክትሮኒክስ/በኮምፒውተር የተጫኑ ማንኛውም የፀሎትም ሆነ የትምህርተ ሃይማኖት መፅሐፍ በውስጡ የምንፍቅና እንክርዳድ እንዳይኖርበት ከዋናው መፅሐፍ ጋር ማገናዘብ ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ፀሎት ለስጋችንም ሆነ ለነፍሳችን ህይወት እጅግ አስፈላጊና የሰይጣን መዶሻ ስለሆነ ምንም ከልካይ ሳይኖር በጀመሩት ፀሎት እንዲቀጥሉ እንመክሮታለን። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ፀልዩ” ፣ “ይህ ክፉ መንፈስ እርኩስ ያለፆምና ፀሎት አይወጣም” ተብሎ ተፅፏልና።
ጸሎተ ንድራ የተባለው መጽሐፍ አብዛኛው በእጅ የተጻፈ ሲሆን በሕትመት ላይ የዋለም ይገኝበታል አገልግሎቱን በሚመለከት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት አንደ ሌሎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት ለጸሎትም ሆነ ለሌላ አገልግሎት እንዲውል አልተፈቀደም። የመጽሐፉን ምስጢራዊ ይዘት ለማወቅ ከተፈለገ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥብርያዶስ ባሕር ሴት መሥላ የተገለጠችውን ክፉ መንፈስ በሚያስፈራ ሁኔታ ለ12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት እንደ አሳያቸውና በሰውና በእንስሳት ላይ የምታደርሰውን ጥፋትም እንደ ገለጸላቸው።በውስጡ ያለው ቃሉም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢራዊ ስሞች ናቸው (ስሙ ሕቡአ ይባላሉ)። ስለመጽሐፉ ጥቅም በሚመለከት በሴት አምሳል ለሐዋርያቱ ያሳያቸው ክፉ መንፈስ በሰውና በእንስሳት ላይ አድራ ጥፋት እንዳታደርስ የሚጸለይ ነው ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው ካህናትም ሆኑ ምእመናን በጸሎትነት እንዲጠቀሙበት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አልተፈቀደም።
ጠያቂያችን እንዳሉት ሰርክ ወይም ከ 11 ሰዓት ጀምሮ የምንፀልየው ፀሎት የሚቀጥለው እለት ዋዜማ ስለሆነ የዋልንበትን እለት ሳይሆን አድረን የምናገኘውን እለት ፀሎት እንፀልያለን ማለት ነው። ውዳሴ ማርያም ብናደርስ ወይም ሌላ ስርዓተ እግዚአብሔር የምናደርስ ከሆነ የቀጣዩን እለት ነው። ለምሳሌ ቅዳሜ የምናከብረው በአል ቢኖረን በዋዜማው አርብ ማታ የሚደገው የዋዜማው ቃለ እግዚአብሔር ቅዳሜ የምናከብረውን በአል በተመለከተ ነው። እንደገና አርብ ማታ ከ 11 ጀምሮ የምናደርሰው የማህበርም ሆነ የግል ፀሎት ካለ የቅዳሜውን እለት ነው የምንፀልየው ማለት ነው። ሌላው በ 24 ሰአታት ውስጥ አንድ ክርስቲያን ወይም አንድ ኦርቶዶክሳዊ የሚፀልያቸውን የፀሎት ጊዜያት እና የፀሎት አይነቶች ሰፋ በማድረግ በቀጣይነት እንዲደርሳችሁ እናደርጋለንና በትእግስት ይጠብቁን ዘንድ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
የፀሎት ዋናው ጥቅም በእምነት ሁነን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው። ስለዚህ የምንጸልየውን የፀሎት ንባብ ሁሉንም ትርጓሜውን እና ምስጢሩን ላናውቅ እንችላለን። ምክንያቱም ለፀሎት የምንጠቀመው የእግዚአብሔር ቃል ሰማያዊውን እና ምድራዊውን ምስጢር የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ የእግዚአብሔር ባህሪይ የሚገለጽባቸው ስሞች ረቂቅ እና ጥልቅ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉም ሰው ትርጓሜያቸውን ሊያውቅ ባይችልም እግዚአብሔር ምስጢሩን እና ጥቡን የገለፀላቸው ቅዱሳን አባቶቻችን የተጠቀሙበት የፀሎት ክፍል ሰለሆነ ሁላችንም በፍፁም ልቦናችን ለምነን ብንፀልየው ፍፁም ዋጋ ያስገኛል። ሰለዚህ እያንዳንዱ የፀሎት መፅሐፍ የራሱ የሆነ የሚያሰጠው ፀጋ ስላለ ማንኛውም ክርስትያን በእምነት ሆኖ መፀለይ እንጂ ትርጓሜውን ወይም ቋንቋውን ያለመቻላችን ሁኔታ በእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን በረከት አያስቀርም። በእርግጥ ይበልጥ የምንፀልየውን የእግዚአብሔር ቃል ምስጢሩን ለመረዳት በግእዝም በተለያየ ቆንቋ ስንፀልይ መስጢሩን ብናውቀው የበለጠ ደስተኛ እንድንሆን ያደርጋል። ባጠቃላይ ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት ትርጉሙንም በውል ባያውቁትም በግእዝ ቢፀልዩ የሚያገኙትን በረከት አያስቀርብዎትም ። በአማርኛም ሆነ በሌላ ቆንቋ መፀለይ ሲፈልጉም ዋናው ምስጢር በእምነት ሆነው መፀለይ ስለሆነ በፈለጉት ቆንቋ ፍፁም ክርስቲያናዊነት ባለው ስርአት ቢፀልዩ እግዚአብሔር አምላክ የለመኑትን መንፈሳዊ ዋጋ እንዲያገኙ ፈቃዱ ነው።
ጥያቄ፦ እንዴት ብለን መፀለይ ይገባናል? ( እንዴት መፀለይ እንዳለብን?)
መልስ፦ ጠያቂዎችን በሌላ ልማድ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሰዎች አንድም ቀን ወደ መንፈሳዊ ነገር ቀርበው እራሳቸውን ያላስመረመሩና ትምህርት ያላገኙ ሰዎች ሳያውቁት እና ሳይረዱት እርኩስ መንፈስ በረቂቅ ሥራው ወደ እግዚኣብሔር እንዳይመለሱ አድርጓቸው ስለኖረ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እንፀልይ፣ እንፁም፣ እንስገድ ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደን እናስቀድስ፣ ቃለ እግዚአብሔር እንማር፣ ብለው ሲወስኑ አላማቸውን ለማሰናከልና ለማደናቀፍ ሰይጣን በተለያየ ምክንያት ሊፈትናቸውና ሊያሰቃያቸው ስላሚችል እንዲህ አይነት ፈተና የደረሰበት ወይም የደረሰባት አባል በአንድ ጊዜ ወደማይችሉት ፈተና ላለመግባት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ እንድንሰጣቸው በውስጥ መስመር ያግኙን :: እስከዚያው ድረስ በእርስዎ በኩልማድረግ ያለብዎት ወደ ቤተክርስቲያን ቀርበው ከአባቶች ምክር መቀበል፣ ሰይጣን የሚያደርስብዎትን ፈተና በግልፅ ማስረዳት፣ ብዙ የማይከብድ ፀሎትን መፀለይ፣ ፀበል መጠጣት እና መጠመቅ፣ በመስቀል መባረክና እምነት መቀባት እነዚህን ሁሉ በማድረግ በቁርጠኝነት ከታገሉት ሰይጣን በራሱ ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል አሸንፈውት ፈጽሞ እንዲለይዎት ማድረግ ይቻላል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። በመንፈሳዊ ምክርና ፀሎት እንድናግዝዎት ካስፈለገም በውስጥ መስመር በላክንልዎት ቁጥር ደውለው ሊያገኙን ይችላሉ።
የእግዚአብሔር ቸርነት አይለይዎት ::
ጠያቂያችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምሮ መሰረት አይንን ጨፍኖ መፀለይ አይፈቀድም። መፅሐፍ እንደሚነግረን በሰማይ ያለውን አባታችንን ስም ስንጠራ አይናችንን ወደሰማይ አንስተን ልባችንን እና ህሊናችንን ሰብስበን ወደ ላይ አንጋጠን እጆቻችንን ዘርግተን መፀለይ እንደሚገባን የሃይማኖታችን ስርዓት ያዘናል። ስለዚህ አይንን ማጨለም ወይም መጨፈን የጨለማ መገለጫ ስለሆነ አይነ ህሊናችንንም ማሳወር እንደሆነ ስለሚቆጠር እንዲህ አይነት የፀሎት ስርዓት እንዲኖረን አያስፈልግም። ነገር ግን ጠያቂያችን አንዳንድ ሰዎች በግል ልማድ ያሰቡት ነገር እንዳይጠፋባቸውና አይምሮዋቸው እንዲሰበሰብላቸው ሲሉ አይናቸውን የመጨፈን ልማድ ቢኖር እንደ ግል ልማድ ይቆጠራል እንጂ እንደ ኀጢአተኛ ሊያስቆጥራቸው አይችልም። እንደ ቤተክርስቲያን ስርዓት ክልክል የሚሆነው መናፍቃን እንደሚያደርጉት የፀሎት አይነት አይንን ጨፍኖ በቋሚነት መፀለይ ግን እጅግ ክልክል መሆኑን ታውቁ ዘንድ ይሄንን አጭር ማብራሪያ ልከንላችኋል።
ጠያቂያችን የአርጋኖን መፅሐፍ ለፀሎት እጅግ የሚጠቅም የቤተክርስቲያናችን የፀሎት መፅሐፍ ሲሆን ብዙ በገዳማዊ ስርዓትና በምናኔ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የሚፀልዩት መፅሐፍ ሲሆን ነገር ግን እርስዎ የጠየቁትን ኃይለቃል በሚመለከት መፅሐፉን በእጃችን አግኝተን ኃይለቃሉን በደንብ በማስተዋል አንብበን ከተረዳን በኋላ ምን ማለት እንደሆነ ምስጢራዊ ትርጓሜውን ልናስረዳዎት ስለምንችል በትዕግስት ሆነው ይጠብቁን። ይሄንን ስንል ግን በእርግጠኛ ያለምንም ጥርጣሬ እርስዎም እንደተረዱት ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከቅድመ ዓለም ያለ እናት ከባህሪይ አባቱ ከአብ መወለዱን ፥ድህረ አለም ያለአባት ከእናቱ ከድንግል ማርያም መወለዱን ሁለት ልደትን እናምናለን የሚለው ኃይለቃል ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ሃይማኖት መሆኑን ልንረዳ ያስፈልገል። በዚያ እርስዎ ባቀረቡት የአርጋኖን ኃይለ ቃል ሌላ ምስጢር ለመጥቀስ የተጠቀሰ ሊሆን ስለሚችል መፅሐፉን ተመልክተን በጊዜው ልናስረዳዎት የምንችል መሆኑን እንገልፃለን።
ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ገና በእናቱ ማህጸን ሳለ ጀምሮ እግዚአብሔር ለታላቅ ነገር የመረጠው ሰው ነው። በዚህ ምክንያት ወደ ታላቁ የንግስና መመረጥ ደረጃ ሳይመጣ ጀምሮ እግዚአብሔር ከሱ ጋር እንደሆነና ከአባቱ እሴይ ልጆች መካከል ታናሽ የሆነውን ዳዊትን ለታላቅ አገልግሎት ፈጣሪው እንደመረጠው የሚታወቀው መራጩ ባለቤቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። በዚህ ምክንያተ ዳዊትን ብላቴናውን እና ከወንድሞቹ ሁሉ ያነሰውን ዳዊትን የመረጠ እግዚአብሔር ስለሆነ የእስራኤል ጠባቂና ንጉስ ሆኖ እስከሚሾምባት ጊዜ ድረስ በዳዊት ላይ ብዙ መከራ እና ፈተና ተፈራርቆበታል። ከዚህ የተነሳ ጠያቂያችን እነዳነሱት ለእግዚአብሔር ሰው ለዳዊት አታማኝ የሆኑት አገልጋዮቹ የንጉሱ የዳዊት አሳዳጆች እና ለሞት የሚፈልጉትን ጠላቶቹ ሊገሉት በሚያሳድዱት ጊዜ በታማኝነት የቆሙ ወታደሮቹ የንጉሱን ህይወት ከሞት ለማትረፍ ራሳቸውን ለመከራ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆን በጠላት ዘንድ ስለ ንጉሱ ስለ ዳዊት ዋጋ በመክፈል ወደሱ የተመለሱትን ታማኞች ንጉሱ በተመለከተ ጊዜ የከፈሉትን መስዋእትነት ተመልክቶ በነሱ የህይወት መስዋዕትነት የመጣውን ደስታ በፀጋ ለመቀበል አይምሮው ስላልፈቀደ የታማኞቹን የህይወት መስዋዕት በማድነቅ በፈጣሪው ዘንድ ታማኝ የሆነው ንጉስ ዳዊት በሰጠው እኔ በእናንተ ሞት ዋጋ የተፈፀመውን ወይም እናንተ ስለእኔ ደማችሁን ስላፈሰሳችሁ እኔ ደግሞ በእናንተ ደም መፍሰስ ወይም የህይወት ዋጋ በመክፈል ተለውጦ የመጣውን የህይወት ውሀ አልጠጣም በማለት እነሱ ስለ ንጉሱ ተለውጠው እስከሞት ድረስ ታማኝ ሲሆኑ ንጉሱ ደግሞ ታማኝ በሆኑት አገልጋዮቹ የህይወት ዋጋ ከፍለው ያቀረቡትን ውሀ አልጠጣም በማለቱ በፈጣሪው ዘንድ እንደ ፅድቅ እንደተቆጠረለት የሚያሳይ ቃል ነው። ጠያቂያችን ምናልባት ሁሉንም ነገር ለእውቀትና ለመረዳት የሚጠይቁ ቢሆንም ነገር ግን ይህንን ሃሳብ ለመረዳት የቻሉበት ምክንያት የተሻለ መንፈሳዊ እውቀት እንዳልዎት የሚያስረዳ ቢሆንም በሌላ መልኩ ያለዎትን መንፈሳዊ ደረጃ በእርግጠኝነት ለመረዳት ስላልቻልን እንጂ በቤተክርስቲያን የእውቀት ደረጃ መገለፅ ያለባቸውን የትርጓሜ ደረጃዎች መሰረት በማድረግ ማስረዳት ስለሚቻል ይሄንን ምስጢር ከዚህ በላይ በስፋት እንድናብራራልዎት ካስፈለገ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ጠያቂያችን የሰርክ ፀሎት ስርዓት በገዳማት የሚኖሩ መናንያኖችም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያሉ መምህራን እና ደቀመዛሙርት ማታ በሰርክ ክፍለ ጊዜ የሚቀጥለውን እለት ውዳሴ ማርያም በንባብ ብቻ ሳይሆን በዜማ በመፀለይ ለፈጣሪያቸው ምስጋና ያቀርባሉ። ለእነሱም የፈለጉት የእግዚአብሔር በረከት ይለምኑበታል እና ማታ ከመተኛትዎ በፊት የሚቀጥለውን እለት ውዳሴማርያምን መፀለይ በቤተክርስቲያን የተፈቀደ ስለሆነ ተገቢ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን፤ አዎ ልክ ነው ፥ ፀሎት መኝታ ቤት ማድረግ ይቻላል። የተለየ ፀሎት ቤት ከሌለን ቤታችን ጠባብ ከሆነ ባለችን ቤት ውስጥ ህሊናችንን ሰብሰብ አድርገን እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር ዘርግተን መጮህ ነው፥ ማልቀስ ነው፤ ባለንበት ቦታ፤ ‘ድረስልን አባቴ’ ብለን ስሙን ደጋግመን መጥራት ነው። ያኔ እግዚአብሔር የልጆቹን ልመና ይሰማል። በየትም ቦታ ይሁን ዋናው ትልቁ ነገር ልብ ነው፤ ‘እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው‘’ ይላል መዝሙረ ዳዊት። እና እንደውም አንዳንድ ቅዱሳት መፃህፍት ስናይ ጣማ ፌሬን የምትባል ሆስፒታል ውስጥ ነው የምትኖረውና ሽንት ቤት ሄዳ ትፀልይ ነበር ፤ ሽንት ቤት የምትፀልይበትም ምክንያት የፀሎት ሰዓት እንዳታጎልባት ነበርና በተመስጦ ትጸልይ ነበር። ይቺን ሴት እመቤታችን በገኀድ ተገልፃ የምታነጋግራት የምታወራት እጇን ይዛ ልጄ በርቺ የምትላት ናትና፤እግዚአብሔር ለተዓምር የፈጠራት ሰው ነበረች። ውጭ አገር ለህክምና ሄዳ ነው፤ እግአዚአብሔር ውጭ የላካት የእግዚአብሔር ተዓምር እንዲገለፅ ነው እንግዲህ። እና ጣማ ፌሬን አልጋ ላይ ሆና እመቤታችን ተገለጻ አየቻትና ‘አብረን እንፀልይ’ ስትላት፤ ‘አልችልም አለቻት’፤ ‘ለምን?’ አለቻት፤ ‘እኔ የምፀልየው ሽንት ቤት ነው’ አለቻት። ቅዱሳን አንስት የሚለውን መፅሐፍ ማንበብ ይቻላል። እና የቦታ ጉዳይ አይደለም ዛሬ ሽንት ቤት እየሆነ ያስቸገረን ልባችን እንጂ ቦታው አይደለም። ቢያንስ በረግረግ ውስጥ በገደል ውስጥም ቢሆን ውስጣችንን የተመቸ፣ እግዚያብሄር የሚነግስበት አድርገን በእንባ እየታጠብን ብንጠራው እግዚአብሔር ፈጥኖ ይደርሳል።ዮናስ በአሳ አንበሪ ውስጥ ሆኖ ነው እጆቹን የዘረጋው ስለዚህ ዋናው ትልቁ ነገር በንፅህና ፣በቅድስና፣ በእንባ ፣ከቂም በቀል ነፃ ሆኖ ፈጣሪን መጥራት ነው እንጂ በየትም ቦታ ሆኖ እግዚአብሔር ይሰማል። የተህዶ አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር የሞትከው አባቴ አምላኬ ሆይ ልጅህን አቤት በለኝ ብለን የትም ቦታ ሆነን እንጥራው ቅርብ ነው፥ እሩቅ አይደለም። ስለዚህ የትም ቦታ ሆነን መጥራት እንችላለን ቅርብ ነው ሩቅ አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን የትም ቦታ ሆነን እግዚአብሔርን መጥራት እንችላለን።
የበሃይማኖት (በተአምኖ) የሚኖር ክርስቲያን ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገርበት ምስጢራዊ ቋንቋ ነው። ማንኛውም ክርስቲያንም ሆነ ምእመን በየዕለቱና በየሰዓቱ መጸለይ ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው። የሰው ልጅ በሥጋዊ ባሕርይው ሣይበላ እና ሳይጠጣ መኖር እንደማይችል ሁሉ በየሰዓቱና በየጊዜያቱ ካልፀለየ ነፍስ ትራባለች፣ ትጠማለች መላ ሕይወቱም ከእግዚአብሔር በረከት ይርቃል። ስለዚህ ጸሎት በክርስትና ሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ከዚህ በፊት ስለ “ስርዓተ ጸሎት” በተከታታይ ክፍል ያስተላለፍነው መደበኛ ትምህርት ላይ፦
1ኛ/ ስለ 7ቱ የጸሎት ጊዜያት፣
2ኛ/ በምን አይነት መንገድ መፀለይ እንዳለብን፣
3ኛ/ ምን መፀለይ እንዳለብን፣
4ኛ/ እንዴት መፀለይ እንዳለብን አጭር መልእክት እናስተላልፋለን።
ስለዚህ ጠያቂያችን፤ ጸሎት ራሱን የቻለ ሰፊ ተምህርት ሲሆን እርስዎ ለማወቅ የፈለጉትን ክፍል ለይተው ስላልገለጹልን፤ ምናልባትም ከዚህ በፊት ስለጸሎት ያስተላለፍነውን ካላይ የጠቀስነውን የትምህርት ክፍል አልተመለከቱት ከሆነ ሊንኩን ከዚህ በታች ልከንልዎታልና ሊንኩን በመጫን እንዲያነቡት በአጽንዎት እንመክራለን። በተጨማሪም ስለ ጸሎት ቀርበውልን የነበሩ ጥያቄዎችን መሰረት አድርገን ያስተላፍናቸውን መልዕቶችም እንዲመለከቱ ሊንኩን አያይዘንልዎታል
በአጠቃላይ ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን መልዕክት በድጋሚ ልከንልዎታልና በመጀመርያ ይህን አንብበው ተረድተው ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆነልዎት ሃሳብ ካለ ቢያሳውቁን ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥዎ እን ችላለን።