ልዩ ልዩ ጥያቄና መልስ
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ልዩ ልዩ ጥያቄና መልስ
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
በመሰረቱ ጠያቂያችን ማስተዋል ያለብዎት በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ውጊያችን ከስጋና ከደም ጋር ሳይሆን ረቂቅ እና ስውር ከሆነው ጠላታችን ከዲያብሎስ (ከሰይጣን) ጋር ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሲናገር “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችኹ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ዅሉ ልበሱ።መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋራ አይደለምና፥ከአለቃዎችና ከሥልጣናት ጋራ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዢዎች ጋራ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋራ ነው እንጂ።…እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ …የመዳንንም ራስ ቍር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ ርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በልመናም ዅሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ” በማለት በልዩ ልዩ ረቂቅ አሰራር የሰውን ህይወት ፈተና ላይ የሚጥል ሰይጣን እንዴት እንደሚታገለን እና ድላችንን ሁሉ እንዴት እንደሚያመሰቃቅለው ከነገረን በኋላ የሰይጣንን ውግያ የምናሸንፍበትን ሃይል እና ጥበብን አስረግጦ ነግሮናል። (ኤፌ 6፥11-18)
ወደ ጥያቄው ስንመለስ ሰይጣን ወደ ቤታችንም ሆነ ወደ ግል ህይወታችን ለመግባት እና ኑሯችንን ለማመሰቃቀል ብዙ ረቂቅ የጥፋት መንገድ ስላለው በሱ ላለመሸነፍ ከእኛ የሚጠበቀው መንፈሳዊ ጽናት እና ተጋድሎ ያስፈልጋል። ይህም ማለት ፦
1/ ወደ ቤተክርስቲያን አባቶች ቀርቦ የደረሰብንን የሰይጣን ፈተና መናገር እና የተሰጠንን መንፈሳዊ ምክር ስራ ላይ ማዋል፣
2/ ዘወትር ያለማቋረጥ የግል ፀሎት መጸለይና ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እየተማሩ በመንፈሳዊ አገልግሎት መሳተፍ፣
3/ በምንኖርበት ቤታችን ፀበል፣ መስቀል ፣ ስዕል አጠገባችን እንዲኖር ማድረግ፣
4/ በራሳችንም ሆነ በቤተሰባችን ያስለመድነው የባእድ አምልኮ ካለ የቤተክርስቲያን አባቶችን ምክር እና ትምህርት በመቀበል ወደ መንፈሳዊ ህይወት ለመመለስ ጥረት ማድረግ።
ከዚህ በላይ በሰጠንዎት ምክር መሰረት ከፈጸሙ በቤት ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚጠፋ እርግጠኛ በመሆን፤ እግዚአብሔርም በፍጥረታቱ ላይ የማይጨክን ቸር እና መሐሪ አምላክ ስለሆነ እስከአሁን የነበረውን ፈተና በእሱ ፈቃድ ተጠራርጎ ከቤታችሁ እንደሚወጣ በማመን ይህንን መንፈሳዊ ምክር እንዲደርስዎ አድርገናል። በምክርና በሃሳብ እንድንረዳዎት ሲፈልጉ በውስጥ መስመር ያግኙን።
እርኩስ ፊልም በማየት ወደ መጥፎ አቅጣጫ የሚያስኬድ እና መንፈሳዊ ህይወትን ሊዋጋ የሚችል ነገር ሁሉ ከአንድ በክርስቲያናዊ ህይወት ከሚኖሩ ምእመናን የማይጠበቅ ስለሆነ ይሄንን ክፉ ልማድ ለመተው ሁል ጊዜ መጸለይና የተለያዩ የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን በማንበብ እንዲሁም በዚህ ምትክ በድምፅ አና በምስል የተዘጋጁ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፉ ትምህርቶች፣ መዝሙሮች እና ድራማዎችን መከታተል ማዘውተር። ግን ያም ሆነ ይህ እርሶ እና ፈጣሪ በሚያውቀው ከፊልሙ ጋር ተያይዞ ከባድ የሆነ ጥፋት ካለብዎ ለንስሓ አባትዎ በመናገር ንስሓ መቀበል። ከቅዱስ ቁርባን ግን ፈጽሞ መራቅ የለብዎትም። ይህን ሁሉ ፈተና የሚያርቅልዎ እና በኀጢአት የረከሰውን ህይወታችንን የሚቀድሰው ቅዱስ ቁርባን ስለሆነ ሁል ጊዜ ፣ከቁርባን መራቅ የለብንም።
በመሰረቱ ስለ ቡና ስናነሳ ቡና እግዚአብሔር ከፈጠራቸው እፅዋት አንዱ ነው። እራሳችን ወደን ለአምልኮ ካዋልነው ከእግዚአብሔር የምንርቅበት ከሰይጣን ጋር የምንዛመድበት ሊሆን ይችላል።ከዚህ ውጪ ግን ለምግበ ስጋ ከምናውላቸው የእለት ምግቦቻችን እና መጠጦቻችን ከቆጠርነው ግን ከምንም ነገር ጋር ሳናያይዝ የተጠቀምነው ስለሚሆን ሆዳችንን ከመሙላት አልፎ ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር የሚያጣላ ምስጢር የለውም። እንደውም እኮ እውነተኛ ክርስቲያን በፍጹም እምነት መኖር ከጀመረ እንኳንስ ቡና ቀርቶ መርዝ ቢጠጣ እንኳን አይጎዳውም። ጌታችን መድኃኒታችን በቅዱስ ወንጌል “ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል በሰሜ አጋንንትን ያወጣሉ፣ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፣ እባቦች ይይዛሉ፣ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይገላቸውም” በማለት ክርስቲያን በሀይማኖት ጽናቱ ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ነግሮናል። በእርግጥ ይህን ስንል አንዳንዱ በግል የትሩፋት ስራ ለመስራት ወደ አንዳንድ የተቀደሱ ገዳማት እና የቃል ኪዳን ቦታዎች ደርሰው ከመጡ በኋላ ቡና አንጠጣም፣ አልኮል አንጠጣም፣ ወተትና ስጋም አንበላም ሊሉ ይችላሉ፥ ያ ከቦታው ጋር የገቡት የግል ቃልኪዳናቸው ነው።
መልስ፦ ጠያቂያችን እንዳሉት ጫት የሰውን አይምሮ ወይም ስነ ተፈጥሮ ከሚቀይሩ ከአደንዛዥ ዕጽዋቶች የሚቆጠር ነው ስለዚህ የጫት መከልከል ለመንፈሳዊ ሰው ብቻ ሳይሆን በዓለም ለሚኖሩ እና በሃይማኖት ሥርዓት ለማይኖሩ አለማውያን ሰዎችም ጎጂ እንደሆነ መንፈሳዊያን ሊቃውንትና ሥጋዊያን ሊቃውንትም ያወግዙታል :: በሌላ መልኩ እንደ መንፈሳዊነትም ካየነውን ጫት እና ሌሎችም አደንዛዥ ዕፅዋት የሰውን አይምሮ ከመስረቃቸውምና ሃሳባቸውን ከማስቀየራቸውም በላይ የአምልኮ እርኩሳንን የሚጠሩ ጠንቆዪች ወይም ሟርተኞች ለአጋንንት አምልኮ የሚያቀርቡበት መንፈስ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን አሁንም አጥብቀው እንዲረዱት የምንፈልገው ስለ ጫት ጐጂነት ለማወቅ ምንም ትምህርት ሳያስፈልግ ጫት የቃሙ ሰዎችን ማየት ብቻ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በጫት መቃም የመረቀነ ሰው የሚሰራው ኀጢአት አስቦት እና አቅዶት ሳይሆን የጫቱ አደንዛዥነት እና በጫቱ ላይ ያደረው ክፍ መንፈስ የሰውየውን ማንነት ቀይረው ኀጢአት ሲያሰሩት እንመለከታለን :: ስለ ጫት ብዙ መናገር እና ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልገን ጫት ለማንም እንደማያስፈልግ መረዳት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ምናልባት እንደጠያቂያችን ሂሳብ በሃገራችን አካባቢ እና በሌላም ዓለም ሳያውቁና ሳይረዱ ከህፃንነታቸው ጀምሮ ጫት እንደባህላዊ የሚጠቀው ካሉ ትምህርት እና ምክር በመስጠት ከዚህ ክፉ ልማድ እንዲወጡ መፀለይ እና ሳያውቁ ካደረጉት ባይፈረድም እየተናገራቸው እና እያወቁ የሚያደርጉት ግን ይጠየቁበታልና ጠያቂዎችን እና አባላቶቻችን ሁሉ ይህን ትረዱት ዘንድ አደራ እንላለን።
መልስ፦ ጠያቂያችን ከዚህ ቀደም ስለ ሰዶማዊነት እና ተዛማጅ ጉዳዮች በሚመለከት ከፍተኛ የኅጢአት አይነት እንደሆነ መልእክት ማስተላለፉችንን እናስታውሳለን :: አሁንም ከራስም ጋር ሆነ የሰዶማዊነት መንፈስ ባለበት የዝሙት ኀጢአት ስራ ፤እንኳን ክህነት ሊኖረው ቀርቶ በነፍሱም በኩል ከባድ የንስሃ ቀኖና ካልፈጸመ በስተቀር በፈጣሪው ዘንድ ያስጠይቀዋል :: በእርግጥ የሰው ልጅ ለኅጢአት ባይፈጠርም ለኀጢአት የሚሰማማ ስጋ ስለለበስ በዚሁ ደካማ ስጋው አስቦበትም ይሁን ሳያሰበው ሰይጣን ደካማ ጐኑን ወይም የሃሳብ ዝንባሌውን ፈልጎ በሰውየው ላይ በረቂቅ መንፈሱ አድሮ ስለሚዋጋ ሁሉም ሰው በተለያ የጥፋት መንገድ ሲስናከል ማየት የተለመደ ነገር ነው።ከጥቂት ፍፁማን በስተቀር ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ ፣ከአዋቂ እስከ ህፃን ድረስ በተለያየ ጥፋት ውስጥ ሁሉም የተጠመደ ነው ::የሆነ ሆኖ ብዙ ሰዎች ኀጢአት ሰለሰሩ እና ብዙ ኀጢአት ስለተፈጸመ ፥ኀጢአትን ቀላል አያደርግም ወይም ደግሞ የእኔ ኀጢአት ከእከሌ ኀጢአት ያንሳል ወይም የእከሌ ኀጢአት ከእኔ ኀጢአት ይበልጣል በሚል የማሻሻያ ሃሳብ ሊወሰን የሚችል አይደለም ::ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ አባላቶቻችን ከኀጢአት ጋር በተያያዘ የሚኖረን አመለካከት ጥልቅና ቁርጠኝነት ሊኖረን ያስፈልጋል :: ይህ ማለት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቤተክርስቲያን ከውስጡ ክፍል ከካህናት እስከ ምእመናን ብዙ ያልተለመዱ እና የሚዘገንኑ የኀጢአት አይነቶች ማየት እየተለመደ ስለመጣ ይህ መጥፎ ልምድ ደግሞ ኀጢአትን እንድንለማመድና እንድንንቅ ወይም ቸላ እንድንል ሰይጣን በስውር ምስጢሩ ሁላችንንም የማደንዘዣ መርፌ የወጋን እስኪመስል በኀጢአት እንቅልፍ ውስጥ ያለን ሰዎች እጅግ ብዙ ነን።
ስለዚህ ካህንም ሆነ ምእመን በሰራው ኀጢአት ከክብሩ ይዋረዳል፤ በእግዚአብሔር ፀጋ የተሰጠው ክህነትም ሆነ መንፈሳዊ ሃይል ከሱ ይወስድበታል :: በንስሓ ሲመለስ ግን ለክህነታዊ አገልግሎት መብቃት ባይችልም የእግዚአብሔርን ሰማያዊ መንግስት ለመውረስ ግን ይታደላል።
ሁላችንም በዚህ ማስተዋል ውስጥ አንድንኖር አይና ህሊናችንን ያብራልን
ጃንደረባ ማለት በሌላ የአገላለፁ ትርጉም ድንግል ማለት ነው።ይህ ማለት ህገ ጋብቻን ንቀው ወይም ትተው ብቻቸውን በድንግልና ህይወት ለመኖር የወሰኑ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው። ጃንደረባነት በ3 አይነት መንገድ ሊገለፁ ይችላል።1ኛ/ ከእናታቸው መሀፀን ጀምሮ አካላዊ የስሜት ምልክት ሳይኖራቸው ጀንደረባ ሆነው የተወለዱ አሉ።2ኛ ደግሞ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ወይም በሌላ ምክንያት በሰው አካላቸው ተሰልቦ ጃንደረባ የሆኑ አሉ። 3 ኛ/ ስለ መንፈሳዊ የእግዚአብሔር መንግስት ብለው (ስለ መንግስተ ሰማያት ብለው) ራሳቸውን ጀንደረባ ያደረጉ አሉ። ስለዚህ ጉዳይ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በፈሪሳዊያን ዘንድ ስለ ጋብቻ በቀረበለት ጥያቄ መነሻነት ማግባትም ሆነ አለማግባት ወይም ጃንደረባ ሆኖ መኖር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለተሰጣቸው መሆኑን በሰጣቸው መልስ የጃንደረባን ምስጢር ነግሮናል።(ማቴ 19፥10-11) ስለዚህ ጠያቂያችን ማንኛውም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠው ሀብት ፀጋ ምን እንደሆነ ለይቶ በማወቅና በመረዳት በፀጋው መኖር አለበት። በጋብቻ ተመስርቶ ትውልድ ማትረፍም ከእግዚአብሔር ፍቃድ የተነሳ እንጂ ሰው በራሱ አቅም ወይም ችሎታ ያመጣው ህልውና አይደለም።በሌላም በኩል አለምን ንቀው ሁሉን ትተው በዱር በገዳም እንደሚኖሩ ባህታውያን ወይም መናንያን ሳያገቡና ዘር ሳይተኩ በጃንደረባነት የሚኖሩ ፍጹማን የእግዚአብሔር ሰዎች ደግሞ የተሰጣቸው ፀጋ ዘመናቸውን ሁሉ እግዚአብሔርን ማገልገልን በነፍስም በሥጋም ለእግዚአብሔር በመገዛት ለማገልገል ከልጅና ከትዳር የበለጠ ስም ወይም ክብር ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛሉ።ነብየ እግዚአብሔር ኢሳያስ ጃንደረባን “እነሆ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ አይበል፤ እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያስኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረባዎች እንዲህ ይላልና ፤ በቤቴ በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ የማይጠፋም የዘላለም ስም ሰጥቻቸዋለሁ” በማለት ለጀንዳረባዎች በጋብቻና በትዳር ከሚገኘው ትውልድ በላይ በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘላለም የማይጠፋ ስም እንደሚሰጣቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል (ኢሳ 56፥3-5) ስለዚህ ጠያቂዎችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረ ገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባሎቻችን ስለ ጃንደረባ በዚህ ትረዱት ዘንድ ይህን አጭር ማብራሪያ ልከንላችኋል።
ጠያቂያችን የዘንባባ ትርጉመና ምሳሌ ዝርዝር ሁኔታውን የሰማዕትዋ እናታችን የቅድስት አርሴማ ገድሏን አንብበው መረዳት እንዳለብዎት እንመክራለን። ከቅዱሳን ተጋድሎ ጋር ተያይዘው የሚገለፁ ምሳሌዎች የነሱን የተጋድሎ ህይወት የሚገልፁና ከፈጣሪያቸው ዘንድ የተሰጣቸውንም ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ጌታም በሆሳእና እስራኤላውያን የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሆሳእና በአርያም እያሉ ያመሰግኑት የነበረው ቀደም ሲል በአባቶቻቸው ዘንድ አንድ ሰው ለሹመት ተመርጦ በነገሰ ጊዜ ወይም ወንድ ልጅ በወለደ ጊዜ ደስታቸውን የሚገልፁበት እንደሆነ ተመልክተናል። እንዲሁም አሁን የቅድስት አርሴማ ዘንባባ የሷን ንፅህናና ቅድስና ያመለክታል ፣ በስምዋ የተማፀኑ፣ የታመሙ ወይም የተለየ በረከት ከእሷ የፈለጉ በዚህ በዘንባባው አማካኝነት አጋንንት ይወጣሉ፣ ህሙማን ይፈወሳሉ፣ ሰዎች ሁሉ ለድህነት እንደ ቄጤማ በሰማዕትዋ ስም ወደ ቤተክርስትያን ቢወስዱት የእግዚአብሔር በረከት ይበዛላቸዋል ማለት ነው። ጠያቂያችን ቃል በቃል ያለውን የዘንባባ ምስጢር ግን ገድሏን እና ሌሎችንም ቅዱሳት መፅሐፍት ቢያነቡ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚያገኙ እንገልፃለን።
አመሀ ማለት ቃሉ የግእዝ ሲሆን ስጦታ ወይም ገፀበረከት ወይም መባ ማለት ነው ። አመሀ ወይም ስጦታ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ሰባሰገል ወይም የሩቅ ምስራቅ ነገስታት ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ ለአምላክነቱ የሚገባውን ክብር ያቀረቡት ስጦታ ወይም ገፀበረከት አመሀ ይባላል። በዚህ አስተምሮ መሰረት በክርስትና በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሀይማኖት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ቤተክርስቲያን የሚያመጡት መባ ወይም ስጦታ አመሀ ይባላል። ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከት የሚያገኙበት ስለሆነ በበረከት ካገኙት ሀብታቸውና ንብረታቸው ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ሁል ግዜ ያቀርባሉ። አመሀ ለሌላ ሰው ለሚያከብረውና ለሚወደው ሰው የፍቅሩን እና የክብሩ መገለጫ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ስጦታ አመሀ አድርጎ ማቅረብ የተለመደ ስርአት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን አመሀ በሃይማኖታችን አገላለፅ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ቢሆንም እንኳን ለጊዜው ግን ባቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ይሆንዎታል ብለን በማሰብ ይህን አጭር ምላሽ እንዲደርስዎ አድርገናል።
ጥያቄ ፦ አንደ ሰው ንስኀ ገብቶም ይሁን ቅባቅዱስ፡ የወሰደ፡በእግዚአብሔር፡እቅፍ ውስጥ ያለ ሰው፡ሰርግ ፡ክርስትናም ይሁን ብቻ፡ተጠርቶ ሲሄድ፡የተጋበዘበት ቦታ ፡ መጨፈር፡ መዝፈን፡ ይገባዋል ወይ? ማብራረያ ብስጡን
መልስ፦ ጠያቂያችን ፤ ምናልባት በማህበራዊ አኗኗራችን እንደ አካባቢው ባህል ወደ ሰርግ ቦታም ሆነ ወደ ምግብ ቤትና መጠጥ ቤት ለስጋችን የሚያስፈልገውን ለማግኘት በምንሄድባቸው ቦታዎች የምንሰማውና የምናየው የዘፈን አይነት እኛን እንደ ኅጢአተኛ ሊያስቆጥረን አይችልም። ምክንያቱም አስበንበትና ተዘጋጅተንበት ፣ ለመዝፈንና ለማዘፈን፣ ለመጨፈርና ለማስጨፈር ያደረግነው አይደለም። ከሁሉም በላይ በእንዲህ አይነት ስጋዊ ግፊት ወደ ሌላ ኅጢአት ለመግባት ያደረግነው ጥፋት የለምና ነው። ነገር ግን በቤተክርስቲያን አስተምሮ ዘፈን እና የሴሰኝነት ስራዎች ሁሉ የኅጢአት ስራዎች ናቸው። ምክንያቱም በዘመናችን በዘፋኝነት ፆር ውስጥ የወደቁ ሰዎች ሌሎቹንም ተጓዳኝ ኅጢአት ለማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ባለንበት ዓለም ውስጥ ዘወትር የምንመለከተው ትዕይንት በመሆኑ ነው።
ስለዚህ ዋናው ነገር ከዘፈኑና ከጭፈራው በስተጀርባ ያልተገቡና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ አላማዎችን ፈጽመን በኅጢአት እንዳንወድቅ በማስተዋል መጠንቀቅ ነው። ያለበለዚያ ግን ከንስኅ ህይወት በኋላ ወደ ኀጢአት ተመልሶ ለመውደቅ ምክንያት ወደሚሆኑ የጥፋት ስራዎች መመለስ ታጥቦ ጭቃ ማለት ነው።
ስለዚህ እርስዎ የማይቀሩበት አስገዳጅ ማህበራዊ ስብስብ ወይም የተጠሩበት ቦታ ሄደው የዝምድና ተሳትፎ ቢያደርጉ የዘፋኞችንና ያቀንቃኞችን ድምፅ ስለሰሙ ኅጢአተኛ አያደርግዎትምና ጥቃቅን ነገሮችን በማሰብም መጨናነቅ አያስፈልግም። ዘፈን ቤትና ጭፈራ ቦታ ሄደው የአላማው ተካፋይ ሳይሆኑና እራሳቸውን በአላማቸው በማፅናት ኅጢአት የማይሰሩ አሉ። ሌሎች ደግሞ በቤታቸው ወይም ባሉበት ቦታም ተቀምጠው የዘፋኞችንና የጨፋሪዎችን አላማ ተካፋይ ሆነው ኀጢአት የሚሰሩ አሉ። ስለዚህ ዋናው ጉዳይ የአላማ ፅናት ነው። በዓለም እየኖሩ መንፈሳዊ መሆን ይቻላል፤ በመንፈሳዊ ስም እያስመሰሉ ቅልጥ ያለ አለማዊ መሆንም ይቻላል። ልዩነቱ የአላማና የፅናት ጉዳይ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ተረድተውት በማስተዋል እንዲኖሩ ይህ መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት ስለ ዘፈን የሚከተሉት ጥያቀረዎች ቀርበውልን ያስተላለፍነውን ምላሽ እንዲመለከቱት ከዚህ በታች ልከንልዎታል።
1) ዘፈን መስማት ሃጢኣት ነው?እኔ ዘፈን መዳመጥ እወዳለሁ ግን ወደ ጭፈራ ቦታ ኣልሄድም?!
2/በገጠር ኣከባቢ ሠርግ የሚፈፀም በዘፈን ነው በዚህ ወቅት ሙሽራ ሁነህ መጨፈር እንዴት ነው?ኣመሰግናለሁ!
መልስ፦ ድካመ ስጋችንን ለማሳረፍ፣ በቋሚነት ህይወታችንን ሊጎዱ የማይችሉ ለግዜው ግን ወደ ጥፋት ወደ ኀጢአት ሳንገባ ስጋችንን ሊያዝናኑ ይችላሉ ወይም ከድካም ያሳርፉናል ብለን ያልናቸውን ማድመጥና ማየት በኃጢአት ደረጃ አክብደን ማየት የለብንም። ዘፋኝነትም ሆነ ዘፈን ኅጢአት ሊሆን የሚችለው በዘፈኑ ምክንያት ከዘፈኑ በስተጀርባ ያልተገባ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ስራዎች ስንፈፅም ነው። ምክንያቱም ከዘፈኑ ጋር በተያያዘ ወይም ከዘፈኑ በስተጀርባ ወይም ደግሞ ተመልካች ካለው፣ የዝሙት መንፈስ ካለ፣ በዘፈኑ የመጠጥ መንፈስ ካለ፣ ያልተገባ መዳራት ካለ፣ ያልተገባ የመዋለ ንዋይ መሰብሰብ ካለ፣ አነዚህና የመሳሰሉት በቀጥታ ኅጢአተኛ ወደምንሆንበት መንገድ ስለሚመሩን በዚህ ደረጃ ዘፈንን ከተመለከትነው ኀጢአት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን በሬ ጠምደን እርሻ አያረስን፣ እየቆፈርን፣ ረጅም ጉዞ እየተጓዝን፣ ብቻችንን ጫካ ውስጥ ተቀምጠን፣ በራሳችን የምናጉረመርመው አና የምናዳምጠው ዘፈን እንደ ኀጢአት አይቆጠርምና ሊያሳስብዎት አይገባም።
ጠያቂያችን የዚህ አይነት ፈተና የመንፈስ ውጊያ ስለሆነ ክርስቲያናዊ ፅናት ያስፈልገዋል። እርኩስ መንፈስ ወደ እኛ የሚመጣበት መንገድ ረቂና ዘርፈ ብዙ ነው ። የሰይጣን ውጊያ እኛ ባናውቀው መንገድም ሊሆን ይችላል።ስለዚህ ጠያቂያችን ለሰው የሚያደርጉት ነገር እየተሳካልዎ ለእርስዎ ለሚያደርጉት ነገር ግን የሚይዞት ነገር ወይም ለመፈፀም የማይሳካልዎት ጉዳይ ለግዜው በእርስዎ ህይወት ላይም ተጽኖ ስለሚፈጥር ፤ እንዲህ አይነት ፈተና ሲገጥምዎ ወዲያው መንፈሳዊ ውግያ መሆኑን ተገንዝበው በመንፈሳዊ ፅናት እና ማስተዋል ቀጥ ብለው በመቆም ለሌሎች እንደሚያደርጉትና እንደሚሮጡት የእርስዎንም ጉዳይ ለመጨረስ እስከመጨረሻ ድረስ ፈተናውን አሸንፈው ያሰቡትን ጉዳይ ወይም ስራ ፈጽመው ድል ማድረግ መቻል አለብዎት፤ ያኔ በሂይወትዎ ላይ የከበደው ነገር ሁሉ እየቀለለና እየሸሸ ይሄዳል። ለዚህ ፈተና መሰረታዊ ቁልፍ አጋዥ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው፦
1ኛ ጠንካራ ወደ ሆኑ አባቶችቀርበው ጉዳዩን በዝርዝር በመንገር የምክርና የትምህርት አገልሎት ማግኘት
2ኛ ዘወትር የሚዋጋዎትን መንፈስ ነገሮችን ሁሉ የሚያጨልምብዎትን ሃይል ከእርስዎ ለማራቅ የማይቋረጥ ቋሚ ፀሎት መፀለይ ያስፈልግዎታል
በተጨማሪም ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመሄድ ከፈተና ሀሉ እንዲጠብቆት ፈጣሪን መለመንና የቅዱሳንን ስም ጠርቶ መማፀን ያስፈልጋል።
ከዚህ ውጪ ምናልባት እኛ ያልተረዳንዎት ችግር ካለ በውስጥ መስመር አግኝተው ቢያብራሩልን ተጨማሪ ምክርና መፍትሄ ልንሰጥዎት እንችላለን።
መልስ ፦ጠያቂያችን ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ቅዳሴም ሆነ ዝማሬ አባቶቻችን ካህናት በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚያገለግሉበት ሰአት እኛ ሙሉ እውቀት ባይኖረንም እንኳን ከነሱ ጋር አብረን የቅዳሴውን ተሰጥኦ (ምስጋና) በፍጹም እምነት ሆነን ይሆንልናል ይደረግልናል እያልን እግዚአብሔርን ማመስገን እንደምንችል መረዳት ያስፈልጋል። ቢቻል ቢቻል ወደ ቤተክርስቲያን አባቶች ጠጋ ብሎ የቅዳሴውን ተሰጥኦ ለመማር መሞከር ይቻላል። ካልቻልን ግን እርስዎ እንዳሉት ዝም ከማለት ይልቅ በማስተዋል ሆነን ተሰጦውን ከህዝቡ በማዳመጥ የምንችለውን እየሞከርን እግዚአብሔርን ማመስገኑ አስፈላጊ ነው።
ጠያቂያችን ስፖርት ኀጢአትም ጽድቅም ነው ብሎ ለማለት መጀመሪያ የስፖርቱን አይነት ለይተን ማወቅ አለብን። ምክንያቱም በስፖርት ስም የሚፈፀሙ ኢክርስቲያናዊ ተግባራት ስላሉ ነው። ከዚህ ወጪ ሰው ለጤናው ሲል የሚያደርገው ጥንቃቄ ከኀጢአት ጋር አይያያዝም። ሆኖም አብዛኛው የሰው ልጅ ጤና ካለው ምስጋና በሌለው ወይም ደግሞ ሪከርድ በማይሰብርበት በሜዳ ላይ ከሚሮጥ ይልቅ ቤተክርስቲያን አብዝቶ ቢሰግድ ለነፍሱም ለስጋውም ይጠቅመዋል። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱት ዘንድ እየገለጽን ነገር ግን እርስዎ ያሉት የስፖርት አይነት ያልተረዳነው ከሆነ በውስጥ መስመር ቢያብራሩልን ተጨማሪ የመፍትሄ ሃሳብ ልንሰጥዎት እንችላለን።
መልስ፦ጠያቂያችን አይምሮዬ ወቅታዊ በሆነው ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ወይም ከፍተኛ ተቋማት በመዘጋታቸውና ከዚህ በፊት በትምህርት ገበታ ሳሉ የነበረዎትን መንፈሳዊ አገልግሎትና ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን የመሄድዎ ልምድ በመቋረጡ ከፍተኛ የአይምሮ መጨናነቅ ላይ እንደወደቁ በመግለፅ ምን ማድረግ እንዳለብዎ በኛ በኩል የመፍትሄ ምክር እንድንሰጥዎ ባቀረቡልን ጥያቄ መሰረት ይህን ምላሽ ልከንልዎታል።
ሁልጊዜ በሰው ህይወት ውስጥ ፍርሃትና አለመረጋጋትን የሚያመጣ የጭንቀትና የሁከት መንፈስ የሆነ ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ ወቅታዊ የሆነው ችግር እስከሚወገድ ድረስ ባሉበት ቦታ ሆነው ተረጋግተው የእግዚአብሔርንም ስም መጥራትና መፀለይ አስፈላጊ ነው። የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ብሎ ማሰብ ስላለበት በጊዜውም ያለጊዜውም ባሉበት ቦታ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ቢማፀንና የፈለገውን ነገር ቢለምን በአይነ ስጋ ሁሉንም ነገር ማየት ባይቻል እንኳን በመንፈስ ግን የእግዚአብሔርን ቸርነትና በጎ ምላሽ ከሰው ልጆች አይለይም። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት የማያቋርጥ ስለኛ የማያንቀላፋ ትጉህ ጠባቂ ወይም እረኛ ስለሆነ በያለንበት ሁሉ ጠብቆቱና መግቦቱ ስለማይለየን ጠያቂያችን መንፈስዎን አረጋግተው በአካባቢው የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ የተነሳ ቤተክርስቲያን መሄድ ካልቻሉ፤ እስከጊዜው ድረስ የተለመደውን የዘወትር ፀሎት እየፀለዩ በፊትዎ የጌታን ወይም የቅዱሳንን ስዕል ወይም ቅዱስ መስቀል ወይም ቅዱስ ወንጌል በማድረግ ዝም ብለው የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት የአምልኮት ስርዓት መፈፀም እንደሚችሉ ይህን ምክር ልከንልዎታል። በመጨረሻም ጠያቂያችን ከዚህ ጋር ያለዎትን የአይምሮ መጨናነቅ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አሁን ከዚህ በላይ የሰጠንዎት መንፈሳዊ ምክር እንደሚረዳዎት ያለን እምነት ፅኑ ሆኖ ሳለ ነገር ግን የሰይጣን ፈተናና ውግያው ከባድ ከሆነብዎትና መጨነቁንም ካላቆሙ በውስጥ መስመር ያሳውቁንና በምንልክልዎት ቁጥር ደውለው ቢያገኙን የበለጠ የምክር አገልግሎት እንሰጥዎታለን።
መልስ ፦ ጠያቂያችን፤ በወር አበባ ክፍለ ጊዜ ያለች ሴት ከፈሳሽ እስከምትነፃ የትኛው የቤተክርስቲያን ክፍል ቆማ ማስቀደስና መፀለይ እንዳለባት ፣ መንፈሳዊ ፕሮግራሙን እንዴት ማግኘት እንዳለባት ሁሉ በስፋት ስለተገለፀ ደግመው እንዲያነቡት አሁንም አደራ እንላለን። ስላሉት ነገር ተጨማሪ ማድረግ የምንፈልገው የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ መግባትና ቆሞ ማስቀደስ፣ የቀደሰውን የካህን መስቀልን የመሳለም ስርዓት መፈፀም፣ ፀበል ቦታ መጠመቅና በመስቀሉ መዳበስ ወደ ቋሚ ቅዱሳት ስዕላትና መስቀሉ ባለበት ወይም ልዩ ልዩ የፀሎት መፅሐፍት በሚገኝበት ልዩ የፀሎት ቤት ገብቶ መፀለይ እነዚህን የሚመሳስሉ ነገሮች ላይ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አሁንም በድጋሚ እንመክራለን። ሆኖም ግን ባለንበት መኖሪያ ቤታችንም ይሁን ከዋናው የቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውጪም ቢሆን መስቀል አትሳለሙ፣ ቁማችሁ፣ አታስቀድሱ፣ አትፀልዩ ቤተክርስቲያን አትሳለሙ የሚል ህግ የለም። በመቀጠልም እርስዎ ያነሱትን በሚመለከት በግልዎት የሚፀልዩበትን የፀሎት መፅሐፍ አንስተው መፀለይ አይከለከሉም። አንገታችን ላይ ከጠላት እንዲጠብቀን ያሰርነውን መስቀል ወይም ደግሞ ስዕል ወይም ደግሞ የፀሎት መፅሐፍ ቢኖር ከኛ አንድናርቀው አንገደድም። ዋናው ቁም ነገር በውስጣችን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖር ንፁህ የሆነውን አምላክ በንፅህና በቅድስና እንድናመሰግነው በፍፁም እምነት ሆነን እንድናመሰግነው ለማጠየቅ ስንል የወር አበባ ክፍለ ጊዜ ላይ ያሉ ሴቶችም ሆኑ ሌላ የተለያየ ኅጢአትም ሆነ የሥጋ ነገር የገጠማቸው ሰዎች ከዚያ ነገር እስከሚነፁና እግዚአብሔርን ሳይዳፈሩ በርቀት ሆነው ማመስገን የተለመደ ስርዓት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ከዚህ ቀደም የሰጠናቸውን ትምህርታዊ መልእክቶችንም አሁንም መላልሰው ለማንበብና ለመረዳት እንዲሞክሩ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
መልስ፦ ጠያቂያችን ስለመቁጠሪያ ሃይማኖታዊነት ወይም የመቁጠሪያን መንፈሳዊ ምስጢር እና የቁጥሩን መጠን ከዚህ በፊት ትምህርታዊ ማብራሪያ እንዲደርሳችሁ ማድረጋችንን እናስታውሳለን። መቁጠሪያ ዋና አገልግሎቱ፦ 1ኛ/ አይምሯችንን ሰብስበን ሳንሳሳትና ሳንዘነጋ ፀሎታችንን ለማድረግ ሲሆን ፤ 2ኛ/ እርኩሳን መናፍስት ከእኛ እንዲርቁ የምናደርግበት ኃይላችን ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ፀጋውን ያበዛላቸው ገዳማውያን አባቶች አጋንንትን የሚያስለፈልፉበት፣ ከሰው የሚያወጡበት፣ ልዩ ልዩ ተአምራት የሚያደርጉት በመስቀሉና በመቁጠሪያ ጭምር ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን እንዳሉት በአብዛኛው የመቁጠሪያ አገልግሎት በገዳም ውስጥ ለሚኖሩ መናኞች ነው። ምናልባት በአለም ከእኛ ጋር እየኖሩ መንፈሳዊ ፀጋቸው ወይም መንፈሳዊ ደረጃቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ እናቶችና አባቶችም ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
የመቁጠርያ ትልቁ አገልግሎት በፀሎት ጊዜ ፀሎታችንን የምንቆጥርበት ስለሆነ ነው። ዛሬ ላይ ግን አንዳንድ ሰዎች ለምን እንደሆነ ትርጉሙ ባይገባንም አንገታቸው እና እጃቸው ላይም ደርድረውት ማየት የተለመደ ሆኖዋል። ያውም ስለመቁጠርያ ትክክለኛ እውቀትና ግንዛቤ ስለሌላቸው እኛ ካህናትም ስለመቁጠርያ ያስተማርነው ትምህርት ባለመኖሩ እንደ ስጋዊ ጌጥ ሲጠቀሙበት እናያለን። ፀሎት እንኳን የሚደርስበት መሆኑን ብዙዎች አያውቁም። ከአንገታቸውና ከእጃቸው ላይ ከማሰር ያለፈ ሌላ ምንም አገልትግሎት አይሰጥበትም። በሌላም በኩል ከየት እንደመጣ፣ ከምን እንደተሰራ፣ ማን እንደባረከው ማረጋገጫ በሌለበት ሀኔታ ሲጠቀሙበትና ሲገለገሉበት እናያለን።
ስለዚህ ጠያቂያችን በመንፈሳዊ ህይወት ለየት ያለ ፀጋ ኖሮን ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን የምንኖር ከሆነ አባቶችን በማነጋገር እንዴት በመቁጠሪያ መገልገል እንዳለብን በመጠየቅ መያዝ የምንችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል እንጂ ማንም ሰው ግን ከመሬት ተነስቶ መቁጠሪያን ማንጀርገግ እጅግ ነውር መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ልንገልፅ እንወዳለን።
መልስ፦ጠያቂያችን ፤ በቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት ካህናትም ሆኑ ምእመናን ለፀሎት የሚጠቀሙባቸው የፀሎት መፅሐፍት የታወቁና በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ዘወትር በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ናቸው። ፀሎተ ቱሉዳነ የሚለውና ሌሎችም አንዳንድ መፅሐፍት በውስጣቸው ያለው ቃል ለምእመናንም ሆነ ስለ እግዚአብሔር ቃል መንፈሳዊ እውቀት ለሌለው ሰው ግልፅ ያልሆነና አንዳንዴ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠሩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከእግዚአብሔር ውጪ የሆኑ ስሞችና ቃላት የሚገኙበት ስለሆነ ቱላዳን የሚባለው መፅሐፍ ለገቢ ምንጭ ተብሎ የተዘጋጀ ሲሆን አንዳንድ ሰወች ደግሞ አጋንንትን እናወጣለን መንፈስ እናውቃለን እያሉ የሚጠቀሙበት መፅሐፍ ስለሆነ፤ ጠያቂያችን መፅሐፈ ቱሉዳን በቤተክርስቲያን ቀኖና ለፀሎትም ሆነ ለሌላ አገልግሎት እንድንጠቀምበት ያልተፈቀደ መሆኑን አውቀው፥ ለግል ፀሎታችንም ሆነ ለማህበራዊ ፀሎት ብዙ ያልተጠቀምንባቸው የፀሎት መፅሐፍት ስላሉ ስለነሱ ብቻ ትኩረት ሰጥተን በማስተዋል ተጠቃሚዎች እንሆን ዘንድ በአጽንዎት እንመክራለን።
ባጠቃላይ ጠያቂያችንም ሆኑ ሌሎቹ የፕሮግራማችን ተከታታዮች በቤተክርስቲያን ቀኖና የተፈቀደና፤ ካህናትም ሆኑ ምእመናን ሁል ግዜ የሚጠቀሙባቸውን የጸሎት መፅሐፎችን ብቻ መጠቀም አለባቸው። ከዚህ ውጭ ግን ያልተለመዱና የማወናበጃ ሃሳብ ያላቸውን ለንግድ የተዘጋጁ መፅሐፍት በአንዳንድ ሰወች ግፊት እንዲህ ትሆናለህ እንዲያ ትሆናለህ በሚል ስብከት በስሜት ተነሳስተን መፀለይ የለብንም በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
መልስ፦ የተከበሩ ጠያቂያችን በእስር ቤት ወይም በማረሚያ ቤት ውስጥ እያሉ እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ያሳለፉትን አንድነት ገልፀው ለዚህ ስህተት የቄደር ጥምቀት ያስፈልገኛል ወይ? በማለት ስላቀረቡልን ጥያቄ በሚመለከት በእርግጥ በጥያቄዎ ውስጥ ከገለፁት ፈተናዎች ውስጥ እርስዎ የወሰዱት አማራጭ መፍትሄ በኛም በኩል እንደ ሰው ሰወኛ የምናደርገው ነገር ነው። በሌላ መልኩ በዚያ እርስዎ እንደገለፁት በነበሩበት አሰቃቂ እስር ቤት ወስጥ ነገበሩት ካለአደነዛዥ ዕፅ ራሳቸውን መግዛት የማይችሉ ሃይሎች ይህ ቀረሽ የማይባል ኀጢአት ከመስራታቸውም ባለይ እርስዎንም በህይወትዎ ላይ አደጋ ከሚያደርሱብዎትና የነሱን ቡድን ከሚቀለቀሉ እንደ አማራጭ ወስደው ወደ እስልምና ተከታይ የሆኑ ግሮፕ መጠጋትዎ ከዛኛው ኀጢአት ይልቅ ለጊዜው ይሄኛው የተሻለ መሆኑን እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ወደ እስር ቤት የሚገባው የፅድቅ ስራ ሰርቶ ሳይሆን በምድር ላይ የሚያስጠይቀውን ጥፋት ፈፅሞ እስከሆነ ድረስ ከሥጋዊ ጥፋት በላይ የነፍስ ቅጣት የሚያስከትል ኀጢአት በመስራት ሥጋን ማትረፍ ቢቻልም በነፍስ ግን ከተጠያቂነት አያመልጥም።
ስለዚህ ጠያቂያችን በወቅቱ ከነበሩበት ሁኔታ አንፃር እንደ አማራጭ መውሰድዎን በእኛ በኩል ብንደግፈውም እንኳን ከእስልምና ተከታዮች ጋር በሃይማኖታችን የማይፈቀደውን እና የተከለከለውን ነገር ከፈፀምን የቄደር ጥምቀት የግድ እንደሚያስፈልገን በቤተክርስትያን የቀኖና ህግ ይደነግጋል። ይሁን እንጂ በእርስዎም በኩል በወቅቱ ስለጉዳዩ ጥልቀት ያለው ግንዛቤ ስላልነበረዎት ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ በራስዎ መንገድ ያደረጉት የንስኀ ህይወት በአግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንደሆነ ብናምንም ፤ ነገር ግን ለቤተክርስቲያን ቀኖና መታዘዝ ስለሚገባዎት አሁንም ቢሆን ወደ አንድ ገዳማት አባት በመሄድ ወይም ደግሞ ስለቀኖና ቤተክርስቲያን በጥልቀት ወደሚያውቁ ካህን በመሄድ ከጊዜ በፊት የሆነውን ነገር በግልፅ በማስረዳት ስለሚገባው የንስኀ ቀኖና በአባቶች በኩል አስፈላገው ስርዓት ተፈፅሞሎት ከህሊና እዳ ነፃ መሆን አለቦት። ይህን ስንል ግን የእርስዎን ክርስቲያናዊ ህይወትና ሃይማኖታዊ ስርዓቶትን እጅግ እያደነቅን ከብዙ የነፍስ እዳም ነፃ እንደሆኑ በማመን ሰሰለሆነ ሳይጨናነቁ ደስ እያለዎት ህሊናዎ የፈቀደውን እንዲያደርጉ እንመክራለን። ተጨማሪ እርዳታና ምክር ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን።
መልስ፦ ጠያቂያችን መፅሐፈ ባርቶስ እመቤታችን ቅድስት ማርያም በጎሎጎታ በልጇ መቃብር ቆማ የፀለየችው መፅሐፍ ነው። ሰዎች ለንግድ ስራና ለሌላ ክፉ ሃሳብ ለማዋል በወቅቱ ሌሎች ቃላት እያስገቡ ያዘጋጁት ወይም ያሳተሙት ነገር ካለ እኛንም ወደ ክህደት መንገድ ስለሚመራንና የሰይጣን ምርኮኛ ስለሚያደርገን እንዲህ አይነቱን መፅሐፍ ወደ ሊቃውንተ ቤተክርስትያን በመውሰድ ማስመርመር ያስፈልጋል። በዋነኝነት ግን እመቤታችን የፀለየችው ስለ ዓለም ሁሉ የአማላጅነትና ያስታራቂነት የቃልኪዳን መፅሐፍ እንደሆነ ነው የሚታወቀው። ጠያቂያችን ያሉትን መፅሐፍ ሲያገኙት ቢልኩልን ግን ተመልክተን መልስ ልንሰጥበት እንችላለን።
በውስጥ መስመር ወይም በግል ልታገኙን የፈለጋችሁ አባላቶቻችን በቴሌግራም ወይም በፌስቡክ የግል መልእክት ልትልኩልን ትችላላችሁ፤ በቴሌግራም የግል መልእክት ለመላክ “ዮን” የሚለውን ወይም የአካውንታችን መለያን በመጫን ሊፅፉልን ይችላሉ። እርሶ እንዳሉት በውስጥ መስመር ጽፈንሎታልና በዚህ መልኩ ሊያገነኙን ይችላሉ።
ጠያቂያችን እርስዎ እንደጠየቁት በፆም ጊዜ ፆማችን ፍጹም ከፈጣሪ ዘንድ ዋጋ እንድናገኝበት እንኳንስ ቅቤ ዕንቁላል እና ሌሎቹንም ለሥጋችን ክብር መገለጫ የሚረዱትን ማድረግ ይቅርና የምንበላውና የምንጠጣው የተወሰነና የተመጠነ መሆን እንዳለበት የቤተክርስቲያናችን ቀኖና ይደነግጋል። ስለዚህ በፆም ጊዜ ስጋችንን ለማስደሰትና ለስጋችን ክብር ብለን እምናደርጋቸውን ሁሉ ከማድረግ መከልከል አለብን። እውነተኛ ፆም ለመፆም ክርስቲያን የሚለብሰው ልብሱ፣ የሚበላውና የሚጠጣው፣ የሚተኛበትና እንዲሁም የሚናገረውና የሚሰራው ሁሉ የተለካና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል።
አንድ ክርስቲያን መዘምራን ለመሆን የሚዘመረው የሚመሰገነውን አምላክ በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል ቅድሚያ መማር የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርቶች ከዚያ መዝሙር ጸሎት ስለሆነ ህማሙን እያሰብን የእመቤታችንም ሲሆን ስደቷን ስለ ልጇ የተቀበለችውን ህማም እያሰብን የምናነባበት መሆኑን መዘንጋት የለብንም ከዚያ ውጭ ይህን ከተረዳን መዘመር ክብር አለው።
ጠያቂያችን በኋለኛው አለም እግዚአብሔር እንደ ህጉና እንደ ስርዓቱ ለኖሩት ለወዳጆቹ የሚያወርሳቸው ሰማያዊ መንግስቱን ለመውረስ ይችሉ ዘነድ በዚህ በሚያልፈው ዓለም እና በሚያልፈው ሥጋችን የእግዚአብሔርን ህግ እና ትዕዛዝ ጠብቀው መኖር ይገባናል እንጂ ሰዎች ነፍስ ይማር በማለት ስለተናገሩ ብቻ ያንድን ሰው ነፍስ ለመንግስተ ሰማይ ማብቃት አይቻልም። በእርግጥ ነፍስ ይማር የሚለው ቃል የበተክርስቲያናችን አስተምሮ የቤተክርስቲያን አባቶች ስለዚያ ስለሞተው ሰው በህይወትም ሳለ ይሁን በሞተ ጊዜ እና ከሞተም በኋላ በስሙ በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርቡት የማማለድ ፀሎት የሞተውን ሰው ነፍስ እንደሚያስምራት ወይም የእግዚአብሔርን መንግስት እንድትወርስ እንደሚያበቃት እናምናለን። የዚህ አይነት ስርዓተ ፀሎት ረቂቅ የሆነ አፈፃፀም ያለው ሃይማኖታዊ ቀኖና ነው። ነገር ግን ጠያቂያችን፤ የሞተው ሰው ላይ ለቅሶ ለመድረስ የመጣው ሁሉ ወይም ደግሞ የዚያን ሰው ሞት የሰማ ማንኛውም መንገደኛ ነፍስ ይማር በማለቱ የሞተውን ሰው ማፅደቅ እንደማይቻል ማወቅ አለብን። ይህንንም በሚመለከት መፅሐፍ ቅዱሳዊ መልስ ያለው ትምህርት ወደፊት በዚህ ርዕስ ትምህርት ልናስተላልፍ ስለምንችል ለጊዜው ግን ጠያቂያችን ላቀረቡት ጥያቄ ሃሳቡን በዚህ ይረዱት ዘንድ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።