ልዩ ልዩ ጥያቄና መልስ ቁ.2
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ልዩ ልዩ ጥያቄና መልስ ቁ.2
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
ጠያቂያችን በአንድ መጠጥ ቤት ተቀጥሮ በመስራት መተዳደሪያው የሆነ ሰው መጠጥ ጠጥቶ የሰከረው ሰውና በስካር መንፈስም በሚያደርገው ያልተገባ ነገር ሰራተኛው (አስተናጋጁ) በነፍስም ሆነ በሥጋ ሊያስጠይቀው አይችልም። እንኳንስ አስተናጋጁን ይቅረና የንግድ ቤቱ ባለቤት የሆነው ሰው ሳይቀር ምናልባት ሰዎችን በመጠጥ የሚያደነዝዙበትን የመጠጥ ቤት ከፍቶና ሰውየውን የሚጎዳውን መጠጥ የማቅረቡ ሁኔታ ያስጠይቀው እንደሆነ እንጂ ተጠቃሚው ወዶና ፈቅዶ በራሱ ገንዘብ በሚጠጣው ግን ተጠያቂ አይሆንም። ምክንያቱም በዚህ በፈተናው ዓለም ውስጥ በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ህይወትን ለመምራት የማይገቡበት የስራ መስክ የለምና ሰውን አጠጥቶ ለማስከር አስበው ሳይሆን እነሱ ጉልበታቸውን አድክመው እና ማድረግ የማይገባቸውን ሳይቀር ለኑሮ ሲሉ እራሳቸውን ዝቅ አድርገው በመታዘዝ በሚያገኙት እለታዊ ወይም ወርሃዊ ደሞዝ ራሳቸውን እና ቤተሰብ ለመምራት እስከሆነ ድረስ የእነዚህ ሰዎች ህይወት ያሳዝን እንደሆን እንጂ አልፎ ተርፎ ገንዘብ ተርፎት ጠጥቶ በስካር መንፈስ የማይገባውን ለሚፈፅመው ኀጢአት አስተናጋጆች ሊጠየቁም ሊወቀሱም እንደማይችሉ በአጭሩ እያሳወቅን በተጨማሪም ስለ ስካርና ስለሰካራሞች መፅሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን መመልከት ይቻላል።
ከራስ ጋር የዝሙት ሃሳብ በስጋችን ላይ የስነልቦና ተፅኖ ከማሳደሩም በላይ ነፍሳችንንም በኀጢአት የሚያስጠይቃት ኢክርስቲያናዊ ግብር ስለሆነ እንደምንም ታግሎ ማሸነፍና ከዚህ ፆር ፈጽሞ መለየት ያስፈልጋል። ለዚህ አይነት ችግር እንዴት መዳረግ እንደሚቻል በደንብ መለየት ከቻልን የነገሩን መንስኤና ዋና ምክንያት እራሱ ግለሰቡ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ሰይጣን አንድን ክርስቲያን በኀጢአት የሚጥልበትን መንገድ ወይም ምክንያት የሚያገኘው ከሰው ልጅ የዝንባሌ አስተሳሰብ ተነስቶ ነው። ምክንያቱም የተከፈተን በር ማንም ሰይ ሊገባበት ይችላልና ነው። ሌባና ወንበዴ አጥር የሌለው ግቢ ቢያገኝ በፈለገው ጊዜ ገብቶ የፈለገውን ማድረግ ይችላልና በደንብ ታስቦበት ሌባነና ወንበዴን ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ ቤቱን ያጠረ እና በሩን ያጠበቀ ሰው እንኳንስ ሌባ ቀርቶ ለሰላማዊ ዝምድና ለሚመጣ እንግዳ እንኳን በስርዓት በሩን አንኳክቶ ሲከፈትለት ብቻ በስርአት ሊገባ ይችላል። በዚህ መሰረት ጠያቂያችን እራሳችንን ለማይረባ ነገርና እጅግ የመንፈስ እረፍት ለሚነሳ ኀጢአት አሳልፈን ከመስጠታችን በፊት በፅናትና በትዕገስት ሆነን በአባቶች ምክርና ፀሎት ራሳችንንም በፀሎት በጾምና በስግደት ወስነን ሳንሰለች በትጋት ብንታገል ይህ የኀጢአት ፈተና ከኛ እንደሚወገድ አያጠራትርም። በእርስዎ በኩልም እንደተነገረው ለአንድ ሳምንት ያህል እስካሁን ከነበሩበት ፈተና ተለይተው መቆየትዎ የድህነት ምልክት ስለሆነ ከዚህ ኀጢአትም ለመለየት እየታሉ ስለሆነ አሁንም ወስነውና ጨክነው ሃሳቡ በመጣብዎት ጊዜ እራሶትን ወደዚያ የጥፋት ሃሳብ ከመገፋፋት ተቆጥበው የኀጢአቱም መጠን ከፍተኛ ደረጃ መሆኑን ተገንዝበው በፅናት ሆነው ከበረቱ በአንድ ጊዜ ማቆም ይችላሉና አሁንም በፀሎት እና የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ ያቺን የፈተና ጊዜ እያሳለፉ ያለዎትን መንፈሳዊ ትግል ሳያቋርጡ በመቀጠል ማቆም አለብዎት። በተጨማሪ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያሉትን ፈተናዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያና ምላሽ ስለሰጠንበት እሱንም ከድረገፁ ላይ እንዲያነቡት እንመክራለን። ተጨማሪ ምክር እና መንፈሳዊ እገዛ ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር በምንልክልዎ ቁጥር ደውለው ቢያገኙን ተከታታይ ትምህርት እና ምክር ለመስጠት እንችላለን።
ጠያቂያችን በሙሴ ህይወት ታሪክ ውስጥ የተመዘገበና ሙሴ የፃፋቸው የኦሪት መፃህፍት በሃይማኖታችን ሊቃውንት የታወቀና የተረዳ ስለሆነ በህይወተ ስጋ እያለ እንጂ ከሞተ በኋላ አይደለም። ምናልባት በጠቀሱት ቃል ውስጥ ለማለት የተፈለገው ሌላ ትርጓሜ ሊኖረው ስለሚችል ጥያቄዎን በውስጥ መስመር ደውለው በደንብ ቢገልፁልን ልናብራራልዎት እንችላለን።
ጠያቂያችን፤ ለድቁና የሚያበቃ ትምህርት ማለት በቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥበት ለእግዚአብሔርም ምስጋና የምናቀርብበት እውቀት ስለሆነ መማር አይከለከልም። ምክንያቱም ከርስቲያን ክህነት ባይኖረውም ሁሉንም የቤተክርስቲያናችንን መንፈሳዊ እውቀት የመማር እና የማወቅ ክርስቲያናዊ መብት አለው። ክህነት ደግሞ እራሱን የቻለ ፀጋ ስለሆነ ወደ ክህነት ለመጠራትም ራሱን የቻለ መስፈርት ስላለው ጠያቂያችን እንዳሉት እኛን በአካል ቀርበው ሲያነጋግሩን የቤተክርስቲያን ቀኖናና ስርዓተ በሚመራን መንገድ መሰረት ተገቢውን መፈፀም ይቻላል። ስለዚህ ትምህርቱን ቢማሩት ተፈላጊ ነው በማለት ይህ አጭር መልዕክት እንዲደርስዎት አድርገናል።
ጠያቂያችን ፤ ዝኒ ከማሁ ለሚለው ዘይቤያዊ አፈተቱን እና ትርጉሙን ብንገልፅ እርስዎ መልስ ለማግኘት ለጠየቁን ጥያቄ ጠቃሚ ላይሆንልዎት ስለሚችል፥ ወይም ሁሉም መፅሐፍ ላይ እንደዚህ ስለማይል፥ ይህን ቃል ያገኙበትን ፎቶ ኮፒ አድርገው ወይም ፎቶ አንስተው በውስጥ መስመር ቢልኩልን አይተን ከተረዳን በኋላ ምን ለማለት እንደተፈለገ ምስጢራዊ ትርጉሙን በመግለፅ ልናስረዳዎት እንችላለን። ከዚህ ውጪ ግን በዘይቤ ወይም የግእዝ ነጠላ ትርጓሜ ግሱን ብንፈታልዎት እርስዎ ለጠየቁት ሃሳብ ምላሽ ላይሆን ይችላል።
ስለ እራስን በራስ ማርካት ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ መልስ፦ ይህ የኀጢአት አይነት ብዙ ወገኖችን የሚዋጋ መንፈስ እንደሆነ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጥያቄው እየቀረበ በእኛም በኩል ከቤተክርስቲያን ቀኖና አንፃር መልስ የሰጠንበትን ጊዜ እናስታውሳለን። አሁንም በዚሁ የእርኩስ መንፈስ ፈተና የወደቁ ወገኖችን መንፈሳዊ ምክር እንድንሰጣችሁ እስከፈለጋችሁን ድረስ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ከእያንዳንዱ ወገናችን ላይ ይህንን ሰይጣናዊ እርኩሰት ከሁሉም ሰው ተለይቶ ይጠፋ ዘንድ ወገኖችን መምከራችንን እና ማስተማራችንን አናቆምም።
እንደዚህ ያለውን የኀጢአት አይነት በአሁኑ ዘመናችን ብዙ ሰዎች የሚፈፅሙት የኀጢአት አይነት ቢሆንም እንኳን ነገር ግን በጣም የሚገርመው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር ፍትወተ ስጋ ቢያሸንፈው እንኳን ለተፈጥሮ በባህሪው በሚስማማ ደረጃ ተፈጥሮአዊ ክብሩንም ሳያዋርድ ለወንድ ሴትን፥ ለሴት ደግሞ ወንድን ፈጥሮ ጊዜያዊ የስጋ ፈቃዳችንን እግዚአብሔርን ሳናሳዝን ራሳችንንም በኀጢአት ላይ ሳንጥል የተፈጥሮ ስብእናችንን ጠብቀን በህጋዊ መንገድ ስጋዊ ሩካቤ ማድረግ እየቻልን እንዲህ አይነቱን ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ከፍተኛ የኀጢአት አይነት ግን ከማን እንደተማርነው? እንዴትስ ሃሳቡ እንደመጣልን? ዝም ብለን ስናስበው ሰይጣን በእኛ ህይወት ላይ ዘወትር የኀጢአት ፈጠራን እያመነጨ የሰውን ልጅ እንዴት እንደሚያጠፋው እና እንዴት ከፈጣሪው እንደሚለየው የሚያሳይ ሰይጣናዊ ፈተና ነው።
ስለዚህ ይሄንን ፆር ወይም ፈተና ከእኛ ፈፅሞ እስከሚለይ ድረስ ሳንሰለች እና ተስፋ ሳንቆርጥ መዋጋት አለብን። ይህን የምንዋጋበት ዋናው መንፈሳዊ መሳሪያችን እና ማድረግ ያለብንም፦
1ኛ/ በየጊዜው ስንተኛም ስንነሳም ሳናቋርጥ የምንፀልየው የግል ፀሎት መኖር አለበት። ስለዚህ ዘወትር በፀሎት የእግዚአብሔርን ስም እየጠራን መለመን፣
2ኛ/ በተቻለን መጠን ይህው መንፈስ እስከሚለቀን ድረስ የቤተክርስቲያን አባቶችን በማማከር ራሱን የቻለ የቀኖና ሱባኤ መያዝ፣
3ኛ/ አብዝተን በመስገድ፥ አብዝቶ በመስገድ እርኩስ መንፈስን መዋጋት ይቻላል።
4ኛ/ በምንተኛበት ክፍል አካባቢ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳይርቀን መዝገበ ፀበል፣ መስቀል ወይም የቅዱሳን ገድላት እና ድርሳናት ብቻ ከእርኩስ መንፈስ የመንከላከልበት የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን ከእኛ አለማራቅ።
5ኛ/ ከዚህ በላይ በተለያየ ውጊያ የማይላቀቅ እርኩስ መንፈስ ከሆነ የተለየ ሱባኤ ይዞ መጠመቅ ፤ እነዚህን ሁሉ በእምነት በመፈፀም ከዚህ ውጊያ እንደሚላቀቁ እናምናለን።
በአጠቃላይ ግን በዋናነት አብዝቶ መፆም ፣ መፀለይ እና መስገድ ለዚህ አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን በመረዳት እና በማመን እየወደቁም እየተነሱም ቢሆን ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋት ያስፈልጋል።
ከዚህ ውጪ እርስዎ እንዳሉት ያዯትን ሴት ሁሉ ለዝሙት ማሰብም ሆነ ከሴት ጋር መግባባት አለመቻል ወይም ህልመ ሌሊት ማየት እንዲሁም በእምነት ደካማ እና ተጠራጣሪ መሆን ይሄን ሁሉ ነገር የሚያደርገው የእርኩስ መንፈስ ውጊያ መሆኑን በደንብ ሊረዱትና ሊነቁ ይገባል። ስለዚህ አሁንም በአጽንዎት የምንመክርዎት የጀመሩትን መንፈሳዊ ብርታት ሳያቋርጡና ሳይጠራጠሩ ከላይ የዘረዘርናቸውን መንፈሳዊ ምክር በመጠቀም ያለማቋረጥ በማከናወን ተግተው ሊጋደሉት ይገባል። ባጠቃላይ ይህን ከራስ ጋር የዝሙት ሃሳብ መፈፀም ከፍተኛ የኀጢአት አይነት መሆኑን አውቀው እንደውም ከሰዶማዊነት ጋር የተያያዘ ሰይጣናዊ መንፈስ መሆኑን ተገንዝበው ጨርሶ ሊጠየፉትና ሊያቆሙት ይገባል። መክንያቱም ኀጢአትን ለማቆም የኀጢአቱን ስራ ከመሰረቱ መጥላት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ሁሌ ይህ የኀጢአት ሃሳብ ወደ እርስዎ እየመጣ በተዋጋዎት ቁጥር የእግዚአብሔርን ስም፣ የእናታችንን የድንግል ማሪያምን ስም፣ የቅዱሳን መላዕክትን ስም፣ እና የቅዱሳን ፃድቃን ሰማእታትን ስም በመጥራት ወዲያውኑ ሰይጣን በአይምሮዎት ላይ የፈጠረውን ክፉ ምኞት ለመቃወምና ከእርስዎ ለማራቅ መቻል አለብዎት። ይህን ማድረግ ሲችሉ በእርግጠኝነት ከዚህ ፈተና እንዲወጡ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ይረዳዎታል፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም እና ቅዱሳኑም በፀሎት እና በምልጃቸው ከዚህ ፈተና ነፃ እንዲወጡ ያግዞታልና ይበርቱ!
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ ላይ ያገኛሉ
የወር አበባ በሴቶች ላይ በየወሩ የሚከሰት በተፈጥሮ የተሰጣቸው ፀጋ ሲሆን ይህም የማይቋረጥ የደም መፍሰስ ኡደት ነው። በቤተክርስቲያን ቀኖናዊ አስተምሮ የሴቶች የወር አበባ ‘ደመ ፅጌ’ ወይም ‘የአበባ ደም’ በመባል ይጠራል። ይህም በየወሩ ኡደቱን ጠብቆ እስከተወሰነ የእድሜ ደረጃ ድረስ የሚዘልቅ ነው።
የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ከደም እስከምትነፃ ማግኘት የማትችለው መንፈሳዊ አገልግሎት፦ ቅዱስ ቁርባን አትቀበልም፣ ወደ ፀበል መጠመቂያ ቦታ ሄዳ መጠመቅ አትችልም የተቀደሰበትን ፀበል መጠጣት አትችልም፣ የቀደሰው ካህን ከቅዳሴ በኋላ አስቀዳሾቹን የሚባርካቸውን መባረክ ስርአት አታገኝም ሆኖም ካህናት አባቶች ህዝቡን ሲባርኩና እግዚአብሔር ይፍታ ሲሉ ባለችበት ቦታ ቆማ ይሁንልኝ ይደረግልኝ በማለት በረከቱን ማግኘት ይቻላል። እንዲሁም ወደ ቋሚ ቅዱሳት ስዕላትና መስቀሉ ባለበት ወይም ልዩ ልዩ የፀሎት መፅሐፍት በሚገኝበት ልዩ የፀሎት ቤት ገብቶ መፀለይ እነዚህን የሚመሳስሉ ነገሮች ላይ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ እንመክራለን። ሆኖም ግን ባለንበት መኖሪያ ቤታችንም ይሁን ከዋናው የቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውጪም ቢሆን መስቀል አትሳለሙ፣ ቁማችሁ፣ አታስቀድሱ፣ አትፀልዩ ቤተክርስቲያን አትሳለሙ የሚል ህግ የለም። በግልዎት የሚፀልዩበትን የፀሎት መፅሐፍ አንስተው መፀለይም አይከለከሉም።
ጠያቂያችንም ሌላውም አካል መገንዘብ ያለባችሁ በአዲስ ኪዳን ዘመን ማንኛውም ወደ ቤተክርስቲያን እንዳንገባ የምንከለከልበት ጉዳይ ንፅህናንና ቅድስናን ወይም ፈሪሃ እግዚአብሔርን ከማሰብ አንፃር እንዲሁም ለኛም ሆነ ለእግዚአብሔር ጉባኤ ፈተናና መሰናክል እንዳንሆን ታስቦ እንጂ እንደ ኦሪቱ ህግ እንደ እርኩስ ወይም እንደተረገመ አካል በመቁጠር አይደለም። በእርግማን ምክንያት የመጣውን የዘር ኡደት ጥንተ አብሶ በክርስቶስ ሞት ሁላችንንም ከመርገም ኅጢአት ነፃ እንዳወጣን ቤተክርስቲያን ዘወትር ታስተምራለች። ሐዋርያዊ ቅዱስ ጳውሉስም “… ክርስቶስ ስለኛ እርግማን ሆኖ ከህግ እርግማን ዋጀን” በማለት በህግ የተፃፈውን እርግማናችንን በመስቀሉ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈፅሞ እንደሻረው ለገላትያ ሰዎች በፃፈው መልዕክቱ አስተምሮናል። (ገላ 3፥13)
ዋናው ቁም ነገር በውስጣችን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖር ንፁህ የሆነውን አምላክ በንፅህና በቅድስና እንድናመሰግነው በፍፁም እምነት ሆነን እንድናመሰግነው ለማጠየቅ ስንል የወር አበባ ክፍለ ጊዜ ላይ ያሉ ሴቶችም ሆኑ ሌላ የተለያየ ኅጢአትም ሆነ የሥጋ ነገር የገጠማቸው ሰዎች ከዚያ ነገር እስከሚነፁና እግዚአብሔርን ሳይዳፈሩ በርቀት ሆነው ማመስገን የተለመደ ስርዓት ነው።
ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ተጨማሪ ማብራርያ ከፈለጉ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀረቦልን ያስተላለፍነውን ሰፊ ትምህርታዊ ማብራሪያ ከድረገጻችን ላይ ለማንበብና ለመረዳት እንዲሞክሩ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
ጠያቂያችን፤ “ስለ ጸሎተ ባርቶስ እየሰማነው ያለው ነገር እውነት ነው?” የሚለው የጥያቄዎ ሃሳብ ግለጽ ስላልሆነልን ፤ በትክክል ተረድተን ምላሽ መስጠት እንዲያስችለን በዋናነት ለማወቅ የፈለጉትን ሃሳብ በቀጥት ግልጽ አድርገው በጽሁፍ ቢስቀምጡልን በዚያ መሰረት አድርገን ማብራሪያ ልንሰጥበት እንችላለን።
ጠያቂያችን፤ ከዚህ በፊት ቀርቦልን የነበረውን ተመሳሳይ ጥያቄ መሰረት በማድረግ ያስተላለፍነው ምላሽ ውስጥ እርስዎ አሁን ላቀረቡት ጥያቄ መልስ የሚሆን ማብራርያ ሰጥተንበታልና አንብበው ሃሳቡን ይረዱት ዘንድ ከዚህ በታች ልከንልዎታል።
ቀርቦ የነበረው ጥያቄ: ፦ ሴት ልጅ በወር_አበባዋ ጊዜ ዳዊት ይዛ መፀለይ ትችላለች በጣም ማወቅ እፈልጋለሁ ትክክለኛውን መልስ ይቻላል አይቻልም እያሉ እያወዛገቡኝ ስለሆነ ነው።
የሰጠነው መልስ ፦ የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ መግባትና ቆሞ ማስቀደስ፣ የቀደሰውን የካህን መስቀልን የመሳለም ስርዓት መፈፀም፣ ፀበል ቦታ መጠመቅና በመስቀሉ መዳበስ ወደ ቋሚ ቅዱሳት ስዕላትና መስቀሉ ባለበት ወይም ልዩ ልዩ የፀሎት መፅሐፍት በሚገኝበት ልዩ የፀሎት ቤት ገብቶ መፀለይ እነዚህን የሚመሳስሉ ነገሮች ላይ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ እንመክራለን። ሆኖም ግን ባለንበት መኖሪያ ቤታችንም ይሁን ከዋናው የቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውጪም ቢሆን መስቀል አትሳለሙ፣ ቁማችሁ፣ አታስቀድሱ፣ አትፀልዩ ቤተክርስቲያን አትሳለሙ የሚል ህግ የለም። በመቀጠልም እርስዎ ያነሱትን በሚመለከት በግልዎት የሚፀልዩበትን የፀሎት መፅሐፍ አንስተው መፀለይ አይከለከሉም። አንገታችን ላይ ከጠላት እንዲጠብቀን ያሰርነውን መስቀል ወይም ደግሞ ስዕል ወይም ደግሞ የፀሎት መፅሐፍ ቢኖር ከኛ አንድናርቀው አንገደድም። ዋናው ቁም ነገር በውስጣችን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖር ንፁህ የሆነውን አምላክ በንፅህና በቅድስና እንድናመሰግነው በፍፁም እምነት ሆነን እንድናመሰግነው ለማጠየቅ ስንል የወር አበባ ክፍለ ጊዜ ላይ ያሉ ሴቶችም ሆኑ ሌላ የተለያየ ኅጢአትም ሆነ የሥጋ ነገር የገጠማቸው ሰዎች ከዚያ ነገር እስከሚነፁና እግዚአብሔርን ሳይዳፈሩ በርቀት ሆነው ማመስገን የተለመደ ስርዓት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ተጨማሪ ማብራርያ ከፈለጉ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀረቦልን ያስተላለፍነውን ሰፊ ትምህርታዊ ማብራሪያ ከድረገጻችን ላይ ለማንበብና ለመረዳት እንዲሞክሩ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
ጥያቄ፦ ሰላም ለናንተ ይሁን!አንድ ጥያቄ አለኝ! ስለ #ሩካቤ_ስርዓት #ቅድስት_ቤተክርስቲያን ምን ትላለች?አስተምህሮዋ እንዴት ነው?ከይቅርታ ጋር አብራሩልኝ!
መልስ፦ ጠያቂያችን፤ ያቀረቡት ጥያቄ በደንብ ግልፅ ባይሆንልንም፤ ነገር ግን እርስዎ እንዳሉትም የሩካቤ ስጋ ግንኙነትን በሚመለከት ከቤተክርስቲያናችን አስተምሮ አንፃር የአንድ ኦርቶዶክሳዊ ከርስቲያን የስነ ምግባር ጉዞ እና መንፈሳዊ ህይወቱ ምን መምሰል እንዳለበት የተቀመጠ ህግና ስርዓት አለ። ይህንንም ስርዓት ማንም ሰው ሊያውቀው ስለሚገባ ተያያዥ ትምህርት እና ለሁሉም ጠቃሚ የሆነ ምክር እንድንሰጥበት ጥያቄውን እንደ መነሻ ሃሳብ በማድረግ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውልን ያሰተላለፍናቸውን ምላሾች በአንድነት አድርገን እንደሚከተለው ልከናልና አንብበው እንዲረዱት እንመክራለን።
በመሰረቱ የሰው ልጅ ልዩ ክቡር ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን ክብሩን አብዝቶ ወይም አሳንሶ እራሱን እንዳያዋርድ እና በስጋው ፍትወተስጋ ነግሶበት በኀጢአት እንዳይወድቅ፣ ብቸኝነትም እንዳይሰማው ለክብሩ የምትመጥነውንና ፥ የሚመጥናትን አካላዊ ተፈጥሮ ራሱ በመምረጥ፤ ማለትም አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ፥ ወይም አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት ፈጥሮ ባል እና ሚስት በመሆን አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው በክብር አብረው እንዲኖሩና በዚህ ህግ ኑሩ ብሎ የወሰነልን የፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር አሳምሮ እና በስነተፈጥሮ የምንመራበትን ህግም አዘጋጅቶልናል።
ከነዚህም አንዱ ጠያቂያችን ያነሱት የሥጋ ሩካቤ (የግብረ ስጋ ግንኙነት) ሲሆን፤ ይህ የሰው ልጅ ራሱን የሚመስለውን ዘር ለመተካት በወንድና ሴት መካከል የሚደረገው የሩካቤ ስጋ ግንኙነት ወደ ዘር ማስገኘት ለሁለታቸውም የተሰጣቸው ዘርን የመተካት ፀጋ ነው። በመሆኑም ከሁሉ በፊት በቅዱስ ጋብቻ መወሰንና ልጅ ወልዶ መተካት የእግዚአብሔር በረከትና ስጦታ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ትክክለኛ በሆነ ክርስቲያናዊ ስነምግባር በቃል ኪዳን የፀኑ እጮኞች ጋብቻቸውን መፈጸም ያለባቸው በቤተክርስቲያን ስርአት መሆን አንዳለበት የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። በዚህም የእግዚአብሔር በረከትና ጠብቆት ይበዛላቸዋል የሚያፈሩትም ትውልድ ይባረካል ማለት ነው። ሁለቱ ማለትም ሴት እና ወንዱ ድንግልናቸውን ጠብቀው ከቆዩ በኋላ በስርዓተ ተክሊል፥ ቤተክርስቲያን አዋጅ ብላ ልጆቿን ለክብር ለመዓረግ የምታበቃበት ስርዓተ ምስጢረ ተክሊል ይባላል። ስለ ድንግልናቸው ክብር ምድራዊ የምናየው ዋጋ ሁሉ ሰማያዊ ዋጋ በኋላ ያሰጣልና። ይህ የአክሊል ሽልማት የሰማይ አክሊል ምሳሌ ነው።
በመሆኑም ለትዳር የተጫጩ ወንድና ሴት ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት የሚያደርጉት የግብረስጋ ሩካቤ እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ስንመለከተው በዝሙት መንፈስ የተፈፀመ ግንኙነት እንጂ በስርአተ ቤተክርስቲያን የተፈቀደ አይደለና እንደ ዝሙት ይቆጠራል።
ከዚህ አንጻር ከጋብቻ በፊት ከሁለት አንዳቸው ወይም ድንግልናዋን ያጣች ሴት ወይም ያጣ ወንድ በንስኀ አባታቸው የንስኀ ቀኖና እና ቀጣይ ምክር እና ትምህርት ይሰጣቸውና ንስኀ ገብተው ቀኖና ጨርሶው ስጋ ደሙን በመቀበል ጋብቻ መፈፀም ይችላሉ። ስረዓተ ተክሊል ግን አይፈጸምላቸውም።
ሌላው፤ በአለማዊ ጋብቻ መጋባት ቤተክርስቲያን ስርዓት አይደለም ። በዓለማዊ ጋብቻ መጋባት የአሕዛብ እንጂ የክርስቲያን ጋብቻ አይደለም። ፀጋ መንፈስ ቅዱስን ያርቃል። ስለዚህ በኋላ ቆርባለሁ አሁን በዓለማዊ ጋብቻ ልጋባ ማለት የክርስቲያን ስነምግባር ውጪ የሆነ እና የዝሙት ሃሳብ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ሳያውቁና ሳይማሩ ቀርተው ወይም እንደተባለውም ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ጋብቻ ከገቡ ግን የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ኀጢአት የመውደቁ ሁኔታ የደካማ ስጋ ባህሪ ቢሆንም በሰራነው ኀጢአት ተጸጽተን አሁንም ወደ ንስኀ ህይወት ተመልሰን ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል የሚከለክለን ህግ የለም። ባወቅንና በተረዳን መጠን ለስርዓቱ በመታዛችን እኛ የማናውቀው እግዚአብሔር ሊሰጠን የሚችለው ፀጋ አለ ፤ ነገር ግን ያ ፀጋ እንደ አለማዊ ንብረታችን ለፈለግነው ጊዜ በቀጠሮ አቆይተን ልንጠቀም የማንችለው ሰማያዊና ረቂቅ ጸጋ በመሆኑ ፤ እንደ ህጉ የመኖር ውሳኔያችንን ምክንያት እየደረደርን በዘገየን መጠን ጨርሶ የምናጣው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የጊዜ ቀጠሮ ሳናራዝም ራሳችንን በንፅህና በቅድስና ስንጠብቅና በቤተክርስቲያን ስርዓት ጸንተን በቅዱስ ቁርባን በመኖር ስንተጋ እኛ የማናውቀው እግዚአብሔር የሚያውቀውን ፀጋ በጊዜው እንጎናፀፋለን፣ ትዳራችንም፣ ልጆቻችንም ኑሮዋችንም ይባረካል ማለት ነው።
ስለዚህ ማንኛውም ሃይማኖት ያለው ክርስቲያን ለአካለ መጠን ወይም ለአካለ ጋብቻ ደርሶ እና በሃይማኖት ስርዓትና በባህላዊ ትውውቅና በስርዓተ በጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት ማንኛውንም የአካለ ስጋ ሩካቤ ማድረግ ፈፅሞ ክልክል ነው። ለዚህም ነው በቅዱስ ጳውሎስ ስጋችሁን ለመግዛት ፍላጎታችሁን ለማሸነፍ ካልቻላችሁ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላል ያለው። በዚህ መሰረት ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ክርስቲያን የስጋውን ፍላጎት መግዛትና መቆጣጠር በማይችልበት የእድሜ ደረጃ ሲደርስ በሃይማኖት ስርዓትና በአገራዊ ባህል የፈለጋትን ወይም የፈለገችውን ተስማምተው ማግባት እንደሚችል ተፈጥሮዋዊ ማንነት ከእግዚአብሔር ተሰጥቷል። ከዚህ የተነሰ የተሰጠንን የነፃነት ፀጋ መጠቀም መቻል እንጂ ከጋብቻ በፊት የድብብቆሽ ስራወች መፈፀም እኛንም በነፍስ ይጎዳናል ከፈጣሪ ጋርም ያጣላናል በሰው ዘንድም መኀበራዊ ማንነታችንን ያዛባል። ስለዚህ ለስርዓቱና ህጉ ተገዝተን ስራ ላይ ብናውለው በእግዚአብሔር ዘንድም በረከትና መንፈሳዊ እድገት ያሰጠናል ማለት ነው።
ሌላው፤ በትዳር ውስጥ እያሉ ከህጋዊ ጋብቻ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የሥጋ ግንኙነት እና ሴሰኝነት ወይም አመንዝራነት ዝሙት ይባላል። ማለትም አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ወይም አንዲት ሴት ከሌላ ሰው ባል ጋር ወይም በህጋዊ ጋብቻ ጓደኛው ወይም ጓደኛዋ ካልሆነ ወንድ እና ካልሆነች ሴት ጋር የግብረ ስጋ ተራክቦ በማድረግም ሆነ በዝሙት ሃሳብ እየተቃጠሉ መኖር ዝሙተኝነትና አመንዝራነት ነው።
በተጨማሪም ከቤተክርስቲያንን ስርአትና አስተምህሮ አንጻር መገንዘብ ያለብን፦
– ለመቁረብ ሁሉን ነገር አሳክተን ከወሰንን በኋላ ከምንቆርብ 3 ቀን በፊት ወንድ ይሁን ሴት ቤተሰብ ካለ ከግንኙነት (ፆታዊ ግንኙነት) መቆጠብ ያስፈልጋል።
– አንድ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን በተቀበለበት እለት ከሕግ ጋብቻ ጋር ቢሆንም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የለበትም ፣
– በአፇማት እና የበዓል ቀናት ግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ የተከለከለ ነው። ይህንንም እንዴት ማክበር እንዳለብን በሚመለከት፦
1ኛ/ ስለአፇማት፦ ለምሳሌ ሮብ ለመፆም ማክሰኞ ለሮብ፣ ሐሙስ ለአርብ መታቀብ አለብን ማለት ነው።
2ኛ/ ሌሎችን የአዋጅ ፆም በሚመለከት ፦ ወንዱ ከሴቷ፣ ሴቷም ከወንዱ እርቃ በሱባኤ ተለይቶ ማሳለፍ እንዳለብን የቤተክርስቲያናችን ቀኖና ያዛል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል።
3ኛ/ በአላትን በሚመለከት እለተ ሰንበት፣ የእመቤታችን በዓል፣ የባለቤቱ የጌታችን የመድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአላት ፣ እና ሌሎችም ታላላቅ የታወቁ በዓላት ከዋዜማቸው ጀምሮ ከሩካቤ እርቀን ማክበር አለብን። ማለትም በማንኛውም ግዜ የፆም የፀሎት ሱባኤ በራሳችንም ይሁን በአባቶቻችን ቀኖና ተሰጥቶን የፆምና የፀሎት ሱባኤ በያዝን ግዜ፣ በእለተ ሰንበት እና በታወቁ በአላት ቀን ፈፅሞ ሚስትም ከባልዋ ተለይታ ወንድም ከሚስቱ ተለይቶ መኝታቸውንም የተለየ አድርገው በአጠቃላይ ፈቃደ ስጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው መጾም ያስፈልጋል።ይህን ስንል በቀኖና የተደነገጉ 7ቱ አፅዋማትና እንደገናም በአባቶቻችን ሱባኤ ተሰጥቶን የምንፆምባቸው አፅዋማትን ይመለከታል።
ስለመንፈሳዊ ወይም ስለ ክርስቲያናዊ ህይወት ከባልና ሚስት አንዱ ጥንካሬ ካለው ማሸነፍ ያለበትና ተቀባይነት ያለው የሃይማኖቱና የነፍሱን ጉዳይ ተቀዳሚ እና ተፈፃሚ መሆን ያለበት መሆን አለበትና ሃሳቡን በዚህ መረዳት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል።
4ኛ/ በተጨማሪም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል፣ ወይም ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ ወይም ፀበል ለመጠመቅ ለ 3 ቀናት ከስጋ ስርአት እርቀን ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን መቆየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ ሰው እሁድ ቤተክርስቲያን ለመግባት ቢያንስ ከአርብ ማታ ጀምሮ ከስጋ ሩካቤ መቆጠብ አለበት ማለት ነው። ከዚህ ውጪ በፈተና ከወደቅን ግን የተለመደ የዘወትር ፀሎታችንን በቤታችን አካለ ስጋችንን ታጥበን በፀሎት ቤታችን ቆመን ማድረስ እንችላለን ወይም ወደ ቤተክርስቲያን ሄደን ከመግቢው ቅጽር ሆነን መፀለይ እንችላለን ማለት ነው።
በመሰረቱ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ 3 ቀን ከስጋ ስርዓት እንድንርቅ የሚደረግበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለኛ በተቀበለው መከራ በእለተ አርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው ለይቶ 3 መአልትና 3 ለሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ሐዋሪያት እና ከሱ ጋር ይከተሉት የነበሩት ደቀመዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ሳናይ የሚበላ አንበላም የሚጠጣም አንጠጣም ብለው በፆም ተወስነው ስለቆዩ ነው። ስለዚህ ዛሬም የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን አማናዊ ስጋና አማናዊ ደም ስለሆነ ያንን መነሻ አብነት አድርገን ለ 3 ቀናት ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን የምንቆየው ነው።
በመሆኑም ህግ እና ቀኖና የሆነውን ነገር በህግነትና በቀኖናነቱ የተወሰነውን እውነቱን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በደካማ ስጋችን ተፈትነንና ስጋዊ ምኞት አሸንፎን ቀኖናን የሚሽር ስህተት ፈፅመን ብንገኝ ወይም ደግሞ ከ 3 ቀን ባነሰ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን ጠያቂያችን ያነሱትን ስህተት ፈፅሞ ቢገባ ያ ክርስቲያን ፈፅሞ የተወገዘ የተረገመ ነው ማለት አይደለም። የቤተክርስቲያን ስርዓት እና ቀኖና በመሻሩ ተግሳፅና ምክር ሊሰጠው ይችላል። ወደፊት እያወቀ እንዲህ አይነት ጥፋት እንዳትፈፅም ተብሎ ምክር ይሰጠዋል። ይሄ የሚሆነው በህጋዊ ጋብቻ ተወስነው ለሚኖሩ ነው። ከዚህ ውጭ ለሚፈጸመው የስጋ ሩካቤ ግን እንኳን ቤተክርስቲያን በድፍረት ለገባንበት ይቅርና ከሕግ ውጭ ላደረግነው ግንኙነትም ከባድ የቀኖና ቅጣት ይጠብቀዋል። በዚሁ መሰረት ቀኖና ባለመሻር እና ከእግዚአብሔር በረከት ለማግኘት በምናደርገው መንፈሳዊ አገልግሎት በነፍስ የምንጎዳበት እርግማን እንዳያመጣብን ከወዲሁ ክርስቲያናዊ ስነምግባር እና ጥንቃቄ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው።
5ኛ/ ለፀሎት የምንገለገልባቸውን መፅሐፍት እና ሌሎችን የመንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ማንኛውንም ነገር የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው መቀመጥ አለባቸው። እኛም ለመፀለይ ስንፈልግ ካደርንበት መኝታችን ተነስተን የአድህኖ እና የምንፀልይበት ቦታ ላይ ሄደን የተለመደውን የእለት ፀሎታችንን ማድረስ። ቦታ ባይኖረንም እንኳን ከተኛንበት ቦታ ላይ ርቀን በውጭም ሆነ በሳሎን ውስጥ ሆነን መፀለይ፤ ከአቅም በላይ የሆነ የቦታ ችግር ካለ ግን ከጸሎት አንከለከልም ፤ ሌላው ባል እና ሚስት የግብረስጋ ግንኙነት አድርገው በአደሩበት ቀን ወይም እዛ ቦታ ላይ ቅዱሳት ስዕላት ማስቀመጥ ስርዓተ ቤተክርስቲያን የተከለከለ ነው።
6ኛ/ ከማያውቁት ወንድ ወይም ሴት ጋር በህልመ ለሊት ግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የሰው ልጅ በራሱ ስጋዊ ስሜት አስቦበትና ፈልጎት ያደረገው ኅጢአት ካልሆነ መደበኛ የንስኀ ቀኖና አያስፈልገውም። ነገር ግን አንዳንዴ ቀን ስንመኘውና ስናስበው የዋልነውን ተኝተን በህልም ከምናውቀው ሰው ጋር ከፈፀምነው ኀጢአቱን አስበን እንዳደረግነው ይቆጠራል። ምክንያቱም ስላልቻልን እንጂ በአካልም ለማድረግ ፍላጎቱ ነበረን ወይም እንደዚህ አስበንና አቅደን ስላልተሳካልን ብቻ በተግባር ያላዋልነውን ተኝተን በህልም ካደረግነው እንደ ኀጢአት የሚያስቆጥርብን ይሆናልና የንስኀ ቀኖና እና ምክር ያስፈልገዋል።
7ኛ/ አንድ ክርስቲያን በሃይማኖት ከማይመስለው ወንድ ወይም ሴት ጋር የግብረ ስጋ (የስጋ ሩካቤ) ቢፈፅም ወይም ብትፈፅም በቀጥታ የቄደር ጥምቀት እንደሚያስፈልጋቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል።
በመጨረሻም፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን “ወይስ አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግስት እንዳይወርሱ አታውቁምን፥ አትሳቱ ሴሰኛዎች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሰሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ታድሳችኋል ፀድቃችኋል” በማለት የዝሙትን አይነት እና ዝሙት ከፍተኛ ኅጢአት መሆኑን ከዘረዘረ በኋላ እግዚአብሔርን በመፍራት ወደ ንስኅ ስንመለስ ግን እንዴት ከኅጢአታችን እድፍ እንደምንታጠብና እንደምንቀደስ እንደምንፀድቅም አስተምሮናል። (ቀኛ ቆረ 6፥9፤10)
በመሆኑም፤ በዮሐንስ ንስሐ ድረ-ገጽ ያለ መቋረጥ ዘወትር የሚተላለፈውን ትምሕርተ ሃይማኖት እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ፕሮግራም በመከታተል ላይ የምትገኙ ወገኖች ሁላችሁም በዋናነት ይህን ትምህርታዊ መልዕክት አንብባችሁ ተግባራዊ እንድታደርጉ እየመከርን ፤ በኀጢአት መውደቅ ቢኖር እንኳን “የይቅርታ አምላክ ማንም ወጥቶ እንዲቀር አይፈልግም ፥ ልጆቹን ይፈልጋቸዋል ” በውኑ ኀጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” (ሕዝ18፥23) እግዚአብሔር ልጆቹን ከነኀጢአታቸው እንዲሞቱ አይፈልግምና እድል ይሰጣቸዋል በዚህ በምድር ላይ እንዲፀፀቱ ንስኀ እንዲገቡ ከልብ በመነጨ ንስኀ እንዲመለሱ ነው እንጂ።
ስለዚህ፤ ወገኖች ከህግ ውጪ የሆነ ሩካቤ ስጋ የሰይጣን ውግያ ነውና፤ እግዚአብሔር ደግሞ የምህረት አምላክ ስለሆነ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወመንን ክፉ መንፈስ እንደምንም ታግለን ማሸነፍ ያስፈልጋል።
ስለዚህ ወገኖች አሁንም በዚህ ጉዳይ ያልተገባ ሩካቤ ሥጋ ፈጽመን በኀጢአት ወደቀን ከሆነ የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳናራዝም ወደ ንስሐ አባታችን ቀርበን በማማከር የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለን በናምንም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና ፍርሃትን አርቀን ወደ ይቅር ባይ አምላክ መቅረብ እንደሚያስ እንመክራለን።
ስለዚህ ጠያቂያችንም ጥያቄዎን እኛ በተረዳነውን መልኩ ከዚህ በላይ በላይ በሰጠነውን ማብራሪያ ውስጥ ምላሽ እንዳገኙበት እንገምታለን። ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆነልዎት ወይም ያልተመለሰለዎት ሃሳብ ካለ ግን ጥያቄዎን ትንሽ አብራርተው በድጋሚ ቢያሳውቁን ተጨማሪ ማብራሪያ እንሰጥዎታለን።
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org ላይ ያገኛሉ
ጠያቂያችን፤ አንዲት ሴት ፅንስ በማህፀንዋ ካደረበት እለት ጀምሮ 9 ወር ከ5 ቀን የእርግዝና ጊዜ የምታሳልፍበት ወቅት ነው። በዚህ የእርግዝና ወቅት ከእርግዝና በፊት የምትሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ማከናወን አቅምዋ ስለማይፈቅድና ስለሚደክማት ፣ የተሸከመችውም ሃላፊነት ከባድ ስለሆነ ማንኛውንም መንፈሳዊ ግዴታዋን ከሌላ ጊዜ እየቀነሰች እንደምታሳልፍ ስርአተ ቤተክርስቲያን ይፈቅድላታል። በመሆኑም ስለ ጾም፣ ስለ ስግደት ፣ ስለ ፀሎት እና ቆሞ ስለ ማስቀደስ ፣ ስለ መቁረብ የምታደርገውን መንፈሳዊ ስርአት ታደርግ በነበረው መጠን ብትቀጥል በአካልዋ ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግር ስለሚኖሩ ከዚህ አንፃር በቅርብ በመንፈሳዊ አባትነት የሚጠብቋትን የንስኀ አባት እያማከረች ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱ እየቀለላት እንዲሄድ ይደረጋል። ምንም እንኳን የተረጋጋ አካላዊ እንቅስቃሴዋ የበረታ ከሆነ እስከተወሰነ የፅንስ ጊዜዋ ፆምን ለተወሰነ ጊዜ እየጾመች ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳ ቁማ መፀለይ፣ ቤተክርስቲያን መሳለም፣ ማስቀደስ ፣ መስቀል መሳለም፣ ፀበል መረጨት በአጠቃላይ እነዚህን መንፈሳዊ አገልግሎቶች እያገኘች መመለስ ትችላለች። የፅንሱ ጊዜ እየገፋ እየደከማት ሲመጣ ግን በቤትዋ ሆና ፆሙን እየቀነሰች መፆም ትችላለች፣ ያትችልበት ደረጃ ከደረሰችም ስለእርሷ መንፈሳዊ አባቷ በፆምም በፀሎትም ስለሚያስቧት እሷ ግን እንድትፆምና ሌሎቹን መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንድትፈፅም እንደማትገደድ ቤተክርስተያን ስርዓት ያዛልና ጠያቂያችን ሃሳቡን ከዚህ አንፃር እንዲመለከቱት የህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን፤ ጻድቃኔ ማርያም የሄደ ሰው ቡና መጠጣት የለበትም ይባላል ብለው ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ ምላሽ። ከዚህ በፊት ስለ ቡና መጠጣት ወይም አለመጠጣት እንደገለፅነው አሁንም በተጨማሪ የምንለው የቡና እፅዋትና ፍሬ እግዚአብሔር የፈጠረው ሲሆን ማንም ሰው እግዚአብሔር በስነ ተፈጥሮ ለበጎ የፈጠረውን ማንኛውንም አትክልቱንም አዝሪቱንም እፅዋቱንም ሌሎቹንም ፍጥረታት የሰው ልጅ በአግባቡ እንዲገለገልባቸው የተሰጠንን ወደጎን ትተን ለተለያየ አምልኮት ወይም ደግሞ የሰይጣን ግብር ማስፈጸሚ የሚሆን የኀጢአት ስራ ከያዝናቸው ማንኛውም ነገር ከእግአብሔር ጋር ያጣላናል። እኛም ቢሆን መንፈሳዊ ህይወታችንን ያሳጣናል።
ስለዚህ ቡና በክርስቲያናዊ ስነምግባር ክልክል የሚሆነው በልዩ አምልኮትና ልማድ ሁነን በሱስ መንፈስ የምናደርገው ከሆነ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ለምግበ ስጋ ከምናውላቸው የእለት ምግቦቻችን እና መጠጦቻችን ከቆጠርነው ግን ከምንም ነገር ጋር ሳናያይዝ የተጠቀምነው ስለሚሆን ሆዳችንን ከመሙላት አልፎ ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር የሚያጣላ ምስጢር የለውም።
በተጨማሪ ማንም ክርስቲያን በራሱ ውሳኔ ወደ ቅዱሳን መካናት ማለትም እንደ ጻድቃኔ ማርያም ገዳማት ሄደን በቃል ኪዳን ከዛሬ ጀምሮ ይህን አልባለም ፣ ይህን አልጠጣም ብሎ በራሱ ፈቃድ ቃልኪዳን ከገባ አለመብላት፣ አለመጠጣት ይችላል። በቃለመሃላ አንድን ነገር ላለማድረግ ሰው ከወሰነ በራሱ ፀጋ የሚደረግ ቃልኪዳን ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም በገዳማት ያሉ መናኞች በአለም ውስጥ ያለውን የማይበሉ የማይጠጡ ሰውነታቸውን ጎድተው የሚኖሩ አሉና ይህ ልዩ ቃልኪዳን ይባላል። ስለመንፈሳዊ ህይወት አብዝተው ስለተጋደሉ እግዚአብሔር አብዝቶ በበረከት ላይ በረከት ይጨምርላቸዋል።
ስለዚህ ጠያቂያችን እዛ ገዳም ውስጥ ያሉ አባቶች ምናልባት በቃል ኪዳን አንድን ሰው ቃል የሚያስገቡ አባቶች ካሉ እዛ ያሉ አባቶች እና እዛ የሄደውና ቃል የገባው ሰው የሚያውቁት ቃልኪዳን ስለሆነ በእኛ በኩል የሚፈታ ስላልሆነ ሃሳቡ ከዚህ አንፃር መታየት አለበት።
በሁለተኛ ደረጃ ለበአል ፕሮግራም ቡና ሲያፈሉ አረቄ ሲከፍቱ አንዳንድ ቤት ይበትናሉ ያፈሳሉ የተባለውን በሚመለከት ይህ ከባእድ አምልኮት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ፈፅሞ የተከለከለ ነው። እርኩሳን መናፍስት ደግሞ ይህን ልማዳቸውን ለማግኘት ሲሉ በረቂቅ ተሰውረው ያንን የለመዱትን ነገር እንዲሰጣቸው ወደዚያ የአምልኮት አገልግሎት ስለሚቀርቡ በራሱም ህይወት ሆነ በሰው ህይወት ውስጥ ከባድ ፈተና ስለሚያመጡ በቤተክርስቲያን ስርዓት ፈፅሞ የተከለከለ ነው።
በህማማቱ የማህበር ፅዋ መጠጣት (ማውጣት) በተመለከተ ለጠየቁን አባል የተሰጠ ምላሽ፦ በመሰረቱ ሰሞነ ህማማት በመባል የሚታወቀው ሳምንት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን በራሱ ፈቃድ በአይሁድ እጅ የተቀበለውን ህማማተ መስቀል እያሰብን የምንፆምበት ፣ የምንሰግድበት ፣ የምንፀልይበት እና የግብረ ህማማቱን ንባብ የምንሰማበት ሳምንት ነው። በዚህ ሳምንት በቤተክርስቲያን ቀኖና የማይፈፀሙ ብዙ ምስጢራት አሉ። ይህ ማለት ቅዳሴ አይቀደስም፣ ሰው ቢሞት ፀሎተ ፍታት አይደረግም፣ መስቀል መባረክ አይቻልም፣ እግዚአብሔር ይፍታህ አይባልም፣ ድርሳናት እና መልካ መልክ አይፀለይም፣ እንዳሉትም በቤተክርስቲያንም ሆነ ከቤተክርስቲያን ውጪ በማህበር የምንሰበሰብባቸው የፅዋ መሀበር አይጠጣም፣ በአላት አይከበሩም፣ በአጠቃላይ እነዚህን የመሳሰሉ ስርዓቶችን ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የማናከናውንበት ሳምንት ነው ማለት ነው።
ይህ የሆነበት ዋና ምክንያትም ፦
1ኛ/ የሁላችን አምላክ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ የተቀበለውን መከራ በማሰብ በፍፁም ሀዘን ውስጥ ስለሆንን ነው።
2ኛ/ ይቺ ሰሞነ ህማማት ወይም የህማማት ሳምንት የምትባለው የኦሪቱን ስርዓት የምናስታውስበት ስለሆነ በኦሪቱ ስርዓት ደግሞ በአዲስ ኪዳን የሚፈፀሙ ሚስጢራት ስለማይፈፀሙ ያንን በማስታወስ ነው።
3ኛ/ ከክርስቶስ መምጣት በፊት አዳም እና ልጆቹ በመከራ እና በስቃይ ያሳለፉትን የ5500 ውን የጨለማ ዘመን ወይም አመተ ኩነኔ የተባለውን ዘመን ለማስታወስ ስለሆነ በእነዚህና በሌሎቹ ዋና ዋና ምክንያቶች በህማማት ሳምንት ብዙ የማይፈፀሙ ስርዓቶች ስላሉ ጠያቂያችንም ሆኑ ሁሉም አባላቶቻችን ለጥያቄው የሚሆን ይህንን አጭር መልዕክት የሰጠንበት ሲሆን ነገር ግን በፊታችን የጾም መጨረሻ ላይ ፥ እግዚአብሔር አምላካችን እዚያው ያድርሰንና በስፋት ትምህርት የምናስተላልፍበት ስለሚሆን ተከታተሉ።