ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
ስለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት ይህን የድረ ገጻችንን አድራሻ በመጫን ያንብቡ: https://yohannesneseha.org/ትምህርት-ስለ-ተዋሕዶ
የቤተክርስቲያን ምሥጢራት 7 ናቸው። እነርሱም፦
1/ምሥጢረ ጥምቀት፣ 2/ምሥጢረ ሜሮን፣ 3/ምሥጢረ ቁርባን፣ 4/ምሥጢረ ክኀነት፣ 5/ምሥጢረ ንስሓ ፣6/ምሥጢረ ቀንዲል፣7/ምሥጢረ ተክሊል ናቸው።
የማይደገሙት ምሥጢራት ፦1/ምሥጢረ ጥምቀት፣ 2/ምስጢረ ሜሮን፣ 3/ምሥጢረ ክኀነት እና 4/ምሥጢረ ተክሊል ናቸው።
የሚደገሙት ምሥጢራት፦ 1/ምሥጢረ ንስሓ፣ 2/ምሥጢረ ቀንዲል፣እና 3/ምሥጢረ ቁርባን ናቸው።
የማይደገሙበት ምከንያት፦
1/ምሥጢረ ጥምቀት፦ በ40 እና በ80 ቀን የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኀየ ዮርዳኖስ በጥምቀት የተወለድንበት ምሥጢር ነው። በስጋ ልደት ሰው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚወለድ ሁሉ በመንፈስም የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን አንድ ጊዜ ብቻ እንወለዳለን። ለዚህም ነው ምሥጢረ ጥምቀት የማይደገመው። ያ ማለት የቄደር ጥምቀትን፣ በየፀበሉ ቦታ የምንጠመቀውን፣ በተለያየ ምክንያት የምንጠመቀውን ጥምቀት እና በካህናት እጅ የምንረጨውን ፀበል አይመለከትም።
2/ ምሥጢረ ሜሮን፦ የእግዚአብሔር ልጅ ስንሆን በጥምቀት ቅዱስ ሜሮንን ካህኑ ሲያጠምቀን የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የታተምንበት ምክንያት ስለሆነ ከጥምቀት ጋር በመሳሳይ ምሥጢራት ልጅነትን ያገኘንበት ምሥጢር ስለሆነ አይደገምም።
3/ ምሥጢረ ክህነት፦ አንድ ጊዜ ብቻ በእግዚአብሔር ልዩ ፈቃድ ለክህነት ተመርጦ ይሾማል። ካህን ሁኖ ለማገልገል ከብዙ የነውር መንገድ አርቆና ተጠንቅቆ የሚኖርበት ህይወት እንደ ነጭ ነገር ስለሆነ ትንሽም ብትሆን ነውር ብትገኝበት ወይም ብትታይበት የሁሉም አይን እሱ ላይ ስለሚያርፍ ካህን ከማንኛውም የነውር ስራ እርቆና አርአያ ክህነቱን አስከብሮ መኖር እንዳለበት ሕገ ቤተክርስቲያን ይደነግጋል። በዚህ ሁሉ መንገድ ራሱን ለመጠበቅ ወይም ለመግዛት ሳይሆንለት የቀረ በክህነቱ ነውር ተገኝቶበት ከክህነቱ ቢሻር ስለሰራው ኀጢአት ንስሓ ገብቶ መንግሥተ ሰማያትን ሊወርስ ይችላል እንጂ ክህነት ግን ስለማይደገም መልሶ ካህን መሆን አይቻልም።
4/ምሥጢረ ተክሊል፦ በድንግልና ህይወት ጸንተው የኖሩ ወይም ድንግልናቸውን አክብረው የኖሩ ሰወች በቤተክርስቲያን የሚያደርጉት የክብር አገልግሎት ስለሆነ አንድ ጊዜ ስርዓተ ተክሊል ከተፈጸመ በኋላ ሁለተኛ ደግሞ ያስፈልጋል በሚል አይደገምም።
“ከጴንጤዎች ጋር ንግግር አድርጌ ነበር ……” በማለት ጥያቄ ላቀረቡልን አባላችን የሚሰጠው መልስ ለቴሌግራም አባላቶቻችን ሁሉ ጥቅም ስለሚሰጥ መልሱን አንብባችሁ ትረዱት ዘንድ ከሁሉ በማስቀደም በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።
መልስ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ ሀገር ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር” (1 ቆሮ 2፥8) በማለት አይሁድ በመካከላቸው ሙት ሲያስነሳ፣ አይን ሲያበራ፣ ጎባጣ ሲያቃና፣ በሁለት አሳ እና በአምስት የገብስ እንጀራ በበረከቱ አብዝቶ ሲያጠግባቸው፣ አጋንንት ሲያወጣ፣ ባህር ላይ ሲራመድ፣ በመስቀል ላይ ሆኖ አባት ሆይ ይቅር በላቸው ብሎ ለጠላቶቹ ሳይቀር ታላቅ ፍቅሩን ሲገልጽ፣ በቃሉ ብቻ ሙታን ሲያስነሳ፣ አለቶችና መቃብሮች ሲታዘዙ፣ ሞትንና መቃብርን ረግጦ በ3 ቀን ሲነሳ በአጠቃላይ ከአምላክ በስተቀር ፍጡር የማይሰራውን ስራ ሲሰራ በፈጠጠው አይናቸው እየተመለከቱ እና ስለድንቅ ስራውም እየተገረሙበት አምላክ ነው ብለው እውነቱን ለመቀበል ስለተከለከሉ እና አይነልቦናቸው ስለታወረባቸው የክህደት አባታቸው ሰይጣን በዛው በክህደት አላማቸው እንዲፀኑ ስላደረጋቸው ለንስሓ ሳይበቁ እስከ መጨረሻ ድረስ ጠፍተው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል። ጠያቂያችን ከሁሉ በፊት መረዳት ያለብዎት የክህደት እና የምንፍቅና ሰዎች የመጀመሪያ ዋና አላማቸው የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም የሰውን አይምሮ በጥርጣሬ ማዕበል መበጥበጥ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኙትን ጥሬ ቃል በመለቃቀም ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን የነገረ መለኮት ቃል አንድም ቀን በጉባኤ ቤት ውለው ሳይማሩ ከእውቀት ነፃ በሆነ አነጋገር በትምህርተ ሃይማኖት ያልበሰለውን ክርስቲያን ግራ ሲያጋቡም መታየት የተለመደ ተልኳቸው ነው። በመሰረቱ እየሱስን አማላጅ አድርገው የሚናገሩበት ለስህተት ትምህርታቸው መነሻ የሚያደርጓቸው የመፅሐፍ ቅዱስ ቃላት (ሮሜ 8፥27) ላይ እና ቁጥር 34 ላይ ያለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ነው። ይሁን እንጂ እየሱስ ክርስቶስ ከባሕሪይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ እና ከባሕሪይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትና በሶሥትነቱ የሚቀደሰውን የሚሰለሰውን አምላክ፤ በደነዘዘ አይምሮ ድንቁርና በተሞላበት ድፍረት ፈራጁን አምላክ አማላጅ ነው (ይማልደን)፣ የለመኑትን ሁሉ የሚሰጠውን አምላክ ይለምናል ብሎ ማመን አምላክነቱን ካልተቀበሉት ከአይሁድ ጋር በእምነት አንድ መሆን ነው። ጥቅሱን በሚመለከት ግን የባሕሪ አምላክ እየሱስ ክርስቶስን ይማልዳል፣ ይለምናል፣ ያስታርቃል፣ ይፀልያል የሚሉትና የመሳሰሉት ቃላት በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲያጋጥሙን ማስተዋል ያለብን፦
1ኛ/ በመፅሐፍ ቅዱስ በተለያየ ዘመናት የቃላት ትርጉም ማሻሻያ በተደረገበት አጋጣሚ ሁሉ የቃላት መዛባት አጋጥሟል። በተለይ እየሱስ ክርስቶስን በሚመለከት በአዲስ ኪዳን ተፅፎ ስንመለከት ከአምላክነት ክብሩ ለማሳነስ እንደ ፍጡር አማላጅ አድርጎ በመግለፅ በብዙ ቦታ ላይ ተመዝግቦ እናገኛለን። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅሬታዋን ለመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር እና ለሚመለከተው ሁሉ ስታቀርብ ቆይታለች።
ከብዙ ጥረት በኋላም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን በማሰባሰብ የመፅሐፍ ቅዱስ መሰረታዊ ቋንቋ ከሆነው ማለትም ከእብራይስጡ፣ ከአረብኛው፣ ከግእዙ፣ ከእንግሊዝኛው እና ከግሪክኛው ወዘተ ትርጉም ጋር በማነፃፀር ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን አዘጋጅታ በ 2000 ዓ.ም. በመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ እነዚህ በመናፍቃን ዘንድ ልዩ ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ቃላት ተስተካክለዋል። ለምሳሌ አማላጅ የሚለው ቃል ፈራጅ፣ ወይም ያማለዳል የሚለው ይፈርዳል በሚል ተተክቷል።
2ኛ/ የክርስቶስን ክብር በማሳነስ ምን ማትረፍ እንዳለባቸው አላማቸው ሁሉ በውል ግልፅ ያልሆነ የመናፍቃን ተልእኮ ሲታይ ሁሌ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን፣ ምእመናንን እና ካህናትን የሚያሳዝኑበትን እና ሃይማኖትን የሚሸረሽሩበትን መንገድ ስለሚፈልጉ ነው እንጂ፤ እየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በተዋሃደው ስጋ ከኅጢአት በስተቀር እንደሰውነቱ የሰውን ስራ እየሰራ እስከ መስቀል ሞት ድረስ መከራን የተቀበለ እንደ አምላክነቱ ደግሞ ፈጣሪነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ፈዋሽነቱን፣ መድኃኒትነቱን፣ ትንሳኤነቱን፣ አፅዳቂነቱን፣ ኮናኝነቱን፣ ይቅር ባይነቱን፣ መጋቢነቱን፣ ሰርቶ በክብር ወደሰማይ ማረጉን አይተናል።
3ኛ/ አስተዋይነትና እምነት የጎደላቸው ሰዎች ወደ ትክክለኛው አመለካከት ተመልሰው ማሰብ ያለባቸው በብሉይ ኪዳን እና በሀዲስ ኪዳን ውስጥ ስለሱ የባሕሪይ አምላክነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥቅሶች ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
– ቅዱስ ዩሐንስ በራእዩ “አትፍራ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ህያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ዮሐ ራዕይ 1፥17)
– ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስም “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ” በማለት ከእመቤታችን የነሳውን ስጋ አምላክነትን ተዋህዶአልና ከሰማይ የወረድኩ ሲል አምላክነቱን እንደሚያመለክት አንድ አካል አንድ ባሕሪይ መሆኑን ለማረጋገጥ የተናገረው ቃል ነው። (ዮሐ 6፥51)
– ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ “ከመጀመሪያውም የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን…” ብሎ ያለው ማንን ነው? ቀዳማዊ መለኮትን አይደለን? ቃል ከስጋ ጋር በተዋህዶ አንድ ባሕሪይ ካልሆነ በስተቀር ቅድመ አለም የነበረውን መለኮት እንዴት አየነው እንዴትስ ዳሰስነው አለ? የሚታይና የሚዳሰስ ግዙፍ የሆነ ነው እንጂ ረቂቅ የሆነ እንዴት ይታያል? እንዴትስ ይዳሰሳል? ቃል ከስጋ ጋር በተዋህዶ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ ካልሆነ በስተቀር (1ኛ ዮሐ 1፥1)
– “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስትያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ተብሎ በዚህ ኃይለቃል ላይ እየሱስ ክርስቶስ እራሱ እግዚአብሔር ተብሎ በግልጽ ተቀምጦ እናገኘዋለን (የሐዋ 20፥28)
– ነብዩ ዳዊት “እግዚአብዜር፦ አሁን እነሳለሁ ይላል መድኅኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ” በማለት ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ ከተነሳው ስለእየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ነው። መዝ 11፥8
– የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ዳዊት “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔርም በመለከት ድምፅ አረገ ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ” በማለት ያረገው እየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ እየሱስ ክርስቶስን ግን አምላክና እግዚአብሔር መባል የባሕርይ ስልጣኑ እንደሆነ በዚህ ቃል አረጋግጦልናል። (መዝ 46፥ 5 እና 6)
– አሁንም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔርም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ፈጥኖ ተነሳ፥ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኅያልም ሰው ተነሳ…” በማለት እየሱስ ክርስቶስ ከ3 ቀን በኋላ ከመቃብር የመነሳቱን በገለፀባት ሃይለቃል እግዚአብሔር ተነሳ ብሎ በትንቢት ተናግሮዋል (መዝ 67)
– ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም “ከሰማይ ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት ከሰማይ የወረደው የባህሪይ አምላክ እና ከድንግል ማርያም ተወልዶ የተዋሀደው ስጋ ደግሞ ፈራጅና አዳኝ መሆኑን ነግሮናል (ዮሐ 3፥13)
እንግዲህ ጠያቂያችን እነዚህን ሁሉ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለመረጃ ያህል እንዲጠቀሙባቸው አቀረብንልዎት እንጂ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ እየሱስ ክርስቶስ የሚነገሩ ጥቅሶች አምላክ እንደሆነ የሚያመለክቱ እንጂ ፍጡር እንደሆነ ወይ አማላጅ እንደሆነ የሚያመለክት በአንድም ቦታ አይገኝም። እንደ አስታራቂና እንደ አማላጅ አስመስለው በአንዳንድ ቦታ የተገለጹትም እንኳ በለበሰው ስጋ የፆመውን የፀለየውን በመስቀል ላይ ሆኖ ስለኛ የተገረፈውን አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለውን በአጠቃላይ በለበሰው ስጋ እንደሰውነቱ የፈፀመውን አገልግሎት እንጂ ከባሕሪይ አምላክነቱ የሚያሳንሰው አንዳችም ነገር አለመኖሩን በጥበብና በማስተዋል መረዳት ያስፈልግዎታል። አይምሮ መረበሽ መንፈስን መበጥበጥ የጥርጣሬ ማዕበል ውስጥ ማስገባት የሰይጣን እና የመናፍቃን ፀባይ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ደግሞ ባለበት ፀንቶ ይቆማል እንጂ የሚታወክና የሚበጠበጥ መንፈስ የለውም። በእርግጥም የእኛ አማላጅ ድንግል ማርያም ናት፣ የእኛ አማላጅ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን ፃድቃን፣ ቅዱሳን መላእክት ናቸው። እሱ ግን እየሱስ ክርስቶስ ወደ እሱ የሚቀርበውን ልመና እና ምልጃ ተቀብሎ እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥ አምላክ እንደሆነ ጠያቂያችች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችሁም ትረዱት ዘንድ ይሄን ማብራሪያ ሰጠን።
በተጨማሪም ጠየቂያችን የቅዱሳንን እና የመላዕክትን ምልጃን በሚመለከት የሚከተለውን ምላሽ ይመልከቱ፦
በኅጢአተኛ እና በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ የሚፀልዩ የሚያማልዱን እግዚአብሔር አስቀድሞ ያከበራቸው የመረጣቸው ያፀደቃቸው ለዘለአለም አገልጋዮች ያደረጋቸው በቃል ኪዳን ያፀናቸው ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላዕክት ናቸው።
ስለአማላጅነት እና ስለቅዱሳን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ወደፊት ሰፋ አድርገን እምንማማርበት እራሱን የቻለ ግዜ ቢኖርም እንኳን ከተጠየቀው ፍሬ ሃሳብ ጋር ለማዛመድ ያህል አንዳንድ ስለ ቅዱሳን ሰዎች እና ቅዱሳን መላእክት ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቂት ማስረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
1/ ቅዱሳን ሰዎች አማላጅነት
– የቅዱሳን አማላጅነት በሚመለከት “…አባታችን አብርሃም በሚስቱ በሳራ ላይ ነውር ስራ ሊሰራ በነበረው የጌራራ ንጉስ አቤሜሌክ ከእግዚአብሄር በመጣበት ቁጣ በደዌ በተመታ ጊዜ በማላውቀው ኅጢአት ተመትቻለሁና ብሎ ወደ ፈጣሪው ሲጮህ እግዚአብሔርም ከዚህ ደዌህ ትድን ዘንድ አብርሃም ይፀልይልህ ብሎታል” ኦሪ ዘፍ 20፥1-18
– ጻድቁ እዮብ ልዩ ልዩ ፈተና ደርሶበት በከፍተኛ ደዌ እየተሰቃየ ባለበት ግዜ እግዚአብሔር ኤለፋዝን በልዳዶስ እና ሶፋር የተባሉ ወዳጆቹ ሊጠይቁት መጥተው በማይሆን አነጋገር አሳዝነውት ስለነበረ እግዚአብሔር ተቆጣቸው። በደረሰባቸው ቁጣም በዛኑ ግዜ “…እዮብ ወዳጄ ስለ እናንተ ይፀልያል እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና” አላቸው። እዮብም ስለወዳጆቹ በፀለየ ግዜ የእዮብ ፀሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ምህረት እንዲያገኙ አድርጓል። እዮ42፥7-11
– ዳታንና አቤሮንም እንዲሁም ደቂቀ ቆሬ የተባሉ እብራውያን የእስራኤልን ማህበር አስተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ በምቀኝነት አመፅ ባስነሱባቸው ግዜ እግዚአብሔር በዚህ ኅጢአታቸውው ተቆጥቶ በቅፅበት ያጠፋቸው ዘንድ ሙሴን እና አሮንን ከጉባኤያቸው ፈቀቅ በሉ ባላቸው ግዜ ሙሴና አሮንም በፊቱ በግንባራቸው ተደፍተው አቤቱ አምላክ ሆይ አንተ የሰው ነፍስ አምላክ አይደለህምን ለምን አንድ ሰው ኅጢአት ሰራ ብለህ በማህበሩ ላይ ለምን ትቆጣለህ ብለው ለመኑት ጥፋተኞቹ ዳታንና አቤሮንም እና ደቂዘ ቆሪ ተለይተው ይጠፉ ዘንድ ይገባል ህዝቡን ግን አድናቸው ብለው በፀለዩት ፀሎት ህዝቡን ከኅጢአተኞቹ ለይተው አድነውታል። (ዘህልቅ 16፥20-36 እና ከ41-50)
– የእስራኤል መሀበር ሁሉ ተሰብስበው በመሄድ ነብዩ ኤርምያስን “ስለኛ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ፀልይልን” ብለው በጠየቁት ግዜ እሺ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እፀልይላችኋለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚሰጣችሁን መልስ እነግራችኋለሁ ብሏቸው እስከ 10 ቀን ድረስ ከፀለየላቸው በኋላ የእግዚአብሔር ነገር ወደ ኤርምያስ መጣ ህዝቡንም ሰብስቦ ፀሎታችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቀርብ ዘንድ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በዚች ምድር ብትቀመጡ እሰራችኋለው አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለው አልነቅላችሁም እናንተ በሰራችሁበት ኅጢአት ከደነገጣችሁበት እኔም ባደረግሁባችሁ ጥፋት እፀፀታለው ብሎ እግዚአብሔር በኤርምያስ ፀሎት ኅጢአታቸውን ይቅር እንዳለው እና እንዳዳናቸው የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክራል። (ኤር 42፥2-13)
– መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያቶችን ያላቸውን የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የሚቀበሏቸው እና በረከታቸው እንዲደርሳቸው ለሚጠሯቸው ያሳደረባችውን ፀጋ ሲናገር “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል ነብይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብይን ዋጋ ይወስዳል ፃድቅንም በፃድቅ ስም የሚቀበል የፃድቁን ዋጋ ይወስዳል ማንም ከነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም”(ማቴ 10፥40-44)
– ቅዱስ ያእቆብን በመልእክቱ የቅዱሳን ፀሎት በስራዋ እጅግ ታላቅ ሃይል እንደምታደርግ ይገልፃል። ያዕ 5፥14-19
– ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ የሚያማልዱት በፀሎታቸው እና በህይወታቸው ብቻ ሳይሆን በጥላቸውና በልብሳቸው ሳይቀር ተአምራትን እንደሚያደርጉት ስለዚህም “ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋ እና በወስካ ያኖሯቸው ነበር…ድውያንን እና በእርኩሳን መናፍስት የተሰቃዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር ሁሉም ይፈወሱ ነበር” ተብሎ ተፅፏልና
– እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳን ላይ የማማለድን እና የማስታረቅን ቃል ኪዳን እንዳስቀመጠ “የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው…በኛም ያማስታረቅ ቃል አሮረ እንግዲህ እግዚአብሔር በኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን” በማለት እንዴት እንደሚያማልዱ ሐዋርያው በስፋት ገልፀዋል (2ኛ ቆሮ 5፥18-21)
2/ የመላዕክት አማላጅነት
– ስለመላእክት አማላጅነት በሚመለከት መላኩ ቅዱስ ገብርኤል የእግዚአብሔር አገልጋይ የነበረው ካህኑ ዘካርያስን “ፀሎትህ ተሰምቶልሃል አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች ፤ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ” ባለው ግዜ ዘካርያስም “እኔ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም በእድሜዋ አጅታለች ይህን በምን አውቃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን ቃል ስለተጠራጠረ መልአኩም “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ እንድናገርህም ይችን የምስራችም እንድሰብክልህም ተልኬ ነበር አሁንም በግዜው የሚፈፀመውን ቃሌን ስላላመንክ ይህ ነገር እስከሚሆንልህ ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገር አትችልም አለው” ከዚህ በኋላ ዘካርያስ የመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ቃል እስከሚፈፀም ድረስ ዲዳ ሆኖ ቆይቷል። በመጨረሻ ግን መላኩ እንደተናገረው ኤልሳቤጥም ዮሐንስን ከወለደች በኋላ የተወለደው ህፃን ስም በእስራኤል ዘንድ ባለው ልማድ የልጅን ስም የሚሰይመው አባት ስለነበረ ዲዳ የሆነው አባቱ ዘካርያስን በጥቅሻ ሲጠይቁት ብራና ላይ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ፃፈ ያኔም አፉ ተከፈተ ምላሱም ተፈታ (ለሉቃ1፥13-20)
– ነብዩ ዳንኤል በባቢሎን አገር በምርኮ እያለ በመከራው ሰአት መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እንዴት እንደረዳው ሲናገር እነሆም ከዋናዎቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሲረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገስታት ጋር በዛ ተውሁት በማለት ተናግሯል” ዳን10፥13)
– እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ሳሉ የእግዚአብሔር መላእክ በምድረበዳ እንዴት እንደመራቸውና እንደጠበቃቸው ነብዩ ሙሴ ሲናገር “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀውትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እልካለው። ስሜም በእርሱ ላይ ስለሆነ ኅጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት…መላኬ በፊትህ ይሄዳልና በማለት ስለመላእክት ጠባቂነት እና አማላጅነት ተናግሯል (ዘፀ 23፥20-23)
– አሁንም ነብዩ ሙሴ እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤልን ድምፃቸውንና ለቅሷቸውን ተቀብሎ ሰምቶ ከግብፅ ባርነት ባወጣቸው ግዜ በመላእክት ጥበቃ እንደሚመሩ ሲናገር “ወደ እግዚአብሔር በጮህን ግዜ ድምፃችንን ሰማ መላኩንም ሰዶ ከግብፅ አወጣን” በማለት የመላዕክትን ተራዳይነት እና አማላጅነት አረጋግጧል (ዘሁ 20፥16)
– ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለውና” በማለት መላእክት ዘወትር የሰው ልጅን ለመጠበቅ የቆሙ እረኞች እንደሆኑ ማንም በእግዚአብሔር ሰው ላይ እጁን ቢያነሳ በፈጣሪ ዘንድ ዘወትር ስለሱ የሚቆሙ ጠባቂ ምስክሮች እንዳሉት አረጋግጧል።
ጠያቂያችን እና ባጠቃላይ የዮሐንስ ንስሓ ቴሌግራም አባሎቻችን በአጭር ጥያቄ ተነስተን ሰፋ ወዳለ የመልስ አሰጣጥ ትንታኔ ውስጥ የገባነው ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጠው የሃይማኖት ጉዳይ በመሆኑ ለሁላችሁም ግንዛቤ ይሆናችሁ ዘንድ እና ዘወትር በጥፋት እና በመሰናክል ከሚቆሙባችሁ መናፍቃን ዘንድ እንድትጠበቁ ስለሆነ ይህንን መልእክት ደጋግማችሁ በማንበብ መሰረታዊ እውቀት ታገኙበት ዘንድ አደራ እንላለን።
በተጨማሪም በድረገፃችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት በስፋት እየሰጠን ስለሆነ ይህን ሊንክ በመጫን አንብበው እንዲረዱ እንመክራለን።
እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያንን እና ምዕመናንን ከጠላት ዲያብሎስ ንጥቂያ ይጠብቅልን
የቄደር ጥምቀት ለመጠመቅ የሚያስፈልግባቸው የሃይማኖት እና የስነ-ምግባር ሕጸጾች የሚከተሉት ናቸው።
ሃይማኖትን በሚመለከት፦
ጨርሶ ለይቶለት ወደእስልምና ሃይማኖት፣ ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት፣ ወደ ፕሮቴስታንት ሃይማኖት ከሄደ በኋላ በንስሐ ለመመለስ ቢፈልግ፣
በቤተክርስትያን ውስጥ እያለም ቢሆን በክህደትና በኑፋቄ የኖረና ከሃይማኖቱ ሕጸጽ ተመክሮና ንስሐ ተሰጥቶት የተመለሰ፣
ጋኔን የሚስብና የሚያስብ፣
በዛር መንፈስ የሚጠነቁልና የሚያስጠነቁል በዚህም ሰውን ሁሉ የሚያሰግድ እና የሚያስገብር፣
በልዩ ልዩ የአምልኮ ባእድ ቦታ አምኖ በተለያየ ቦታ የሚሰግድና የሚገብር ።
ክርስቲያናዊ ስነምግባርን በሚመለከት፦
እስላም ያገባ/ች፣ ካቶሊክ ያገባ/ች፣ ፕሮቴስታንት ያገባ/ች፣
ለጣኦት የታረደውን የበላ፣
በቅዱስ መጽሐፍ የተከለከሉትን አራዊትና የእንስሳት የበላ።
እነዚህ ከዚህ በላይ የተገለፁት በሃይማኖትና በስነምግባር ሕጸጽ ናቸው ተብሎ የሚታመኑ ስለሆነ የቄደር ጥምቀትም እንደሚያስፈልጋቸው በቤተ ክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍት የተደነገጉ መሆኑን ጠያቂያችን በማስተዋል እንዲረዱ ይህ መልእክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
መልስ፦ ጠያቂያችን በተዋህዶ እና በቅባት እምነት መካከል የሰማይና የምድር ያህል ከፍተኛ ልዩነት አለ። የቅባት ሃይማኖት ፈላስፋና ክህደቱን ያመነጨው ንስጥሮስ የተባለው መናፍቅ ነው። ይሄንን የንስጥሮስ ክህደት 200 የሚሆኑ አባቶች በኤፌሶን ከተማ ባደረጉት የሃይማኖት ጉባኤ አውግዘው ከቤተክርስቲያን ለይተውታል። ከዚህ በኋላ አላማውን የሚያራምዱ ብዙ ንስጥሮሳዊያን የክህደት ሰዎች በሁሉም ክፍለ አለም ይህንን የክህደት ትምህርት ሲያስተላልፉ ኖረዋል። ወደ እኛም ወደ ኢትዮጵያ አገራችን ካቶሊካውያን ከእርዳታ ጋር በተያያዘ የወዳጅነት አጋጣሚ በአፄ ልብነ ድንግል ተጀምሮ ከሞቱም በኋላ በልጃቸው በአፄ ገላውዲዎስ እንደተጀመረ ታሪክ ያስረዳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት ድጋፍ ሰጭነት በኢትዮጵያ አገራችን በተለያዩ ቦታዎች በመንግስት ባለስልጣናት ጫና ጭምር እንዲስፋፋ ተደረጎ ነበር።ከጊዜ በኋላ ለተዋህዶ ሃይማኖታቸው የቆሙ ነገስታት ሲተኩ ደግሞ የቅባት እና የፀጋ ሃይማኖት በድብቅና በሚስጥር ውስጥ ውስጡን እስከ ዘመናችን ለመድረስ በቅቷል። ዛሬ በተለይ በአሁኑ ሰአት ለይቶለት በምስራቅ ጎጃም ውስጥ ጳጳሳትን እስከ መሾም ደርሰዋል። የሃይማኖቱ ሚስጥርና የክህደቱ ዝርዝር ግን አጅግ ሰፊና ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ ለብዙ ምእመናን በአጭር መልስ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። ለግዜው ግን በእነሱ በኩል ያለው ሃይማኖት በአጭሩ አብ ቀባኢ ወልድ ተቀባኢ መንፈስ ቅዱስ ቅብ በማለት ወልድን ከአብ በማሳነስ መንፈስ ቅዱስን ደግሞ ከአብ እና ከወልድ በማሳነስ የሚገለፀው የክህደት ትምህርት ስለሆነ ወደፊት በተዋህዶ እና በቅባት ያለውን ልዩነት ሰፋ አድርገን በድረገፃችን ለይ በጀመርነው መንፈሳዊ ትምህርት ጋር አያይዘን መልሱ እንዲደርሳችሁ እናደርጋለን። ለጊዜው ግን በዚህ እንዲረዱት አና ከዚህ በፊት የሰጠነውን ተከታታይ ትምህርት ከታች ያለውን ሊንክ በመጫን እያነበቡ እንዲቆዩን እንመክራለን።
የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ማን ናት? https://yohannesneseha.org/
መልስ፦ ጠያቂያችን ስለ ክህነት ጥልቅ የሆነ እውቀት እንዲኖረን በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን የክህነትን ስራ አስመልክቶ በመፅሐፍ ቅዱሰ የተፃፈውን በማስተዋል መረዳት ያስፈልጋል። በመሰረቱ የክህነት አገልግሎት ከእግዚአብሔር እና ከሰው መካከል ሆኖ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝና የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ወደ ሰው የሚያደርስ ለእግዚአብሔር አምልኮት የሚገባውን ምስጋናና መስዋዕት የሚያቀርብ አገልጋይ ማለትነው። እነዚህ የክህነትን አገልግሎት የሚፈፅሙ ካህናትም፦
1ኛ/ በብሉይ ኪዳን በኦሪቱ ህግ በታዘዘው መሰረት እንደ ስርዓተ ህጉ እየተመረጡ ይሾሙ እንደነበረ መፅሐፍ ቅዱስ በስፋት ይነግረናል። ለምሳሌ አሮንና ልጆቹ ለክህነት አገልግሎት እንደተመረጡ መፅሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። (ዘፀ 28፥1) በተጨማሪም የኤሊ ዘር የሆኑ ሁሉ በክህነት የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ እንዳገለገሉ ተፅፏል። (ዘሁልቅ 3፥5-10) አሮንና ልጆቹ በእግዚአብሔር ፊት የክህነትን አገልግሎት ሲፈፅሙ የተለየ ልብስ እንዲለብሱና አገልግሎታቸውም በብዙ ጥንቃቄ እንዲፈፀም ታዘዋል። (ዘፀ28፥40፣ ዘሌ ከ8 ጀምሮ ፣ ዘፀ30፥17-21) በብሉይ ኪዳን የከህነት አመሰራረትና አገልግሎት እጅግ ሰፊና ረቂቅ ስለሆነ በሌላ ርዕስ ወደፊት እናብራራዋለን።
2ኛ/ የአዲስ ኪዳን ክህነትን በሚመለከት፦ በአዲስ ኪዳን የአዲስ ኪዳን ክህነት የተመሰረተው በጌታችን በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ነው። በአዲስ ኪዳን ካህናት ሆነው እንዲሾሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡት 12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው። የሐዋሪያት የክህነት ክብራቸውም ስራቸውም ረቂቅ ነው። የካህናት አለቃ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ (ሊቀ ካህናት) ለነሱ የሰጣቸው የክህነት ደረጃ በራሱ ቃል እንዲህ ሲል ተናግሯል “እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል” (ማቴ18፥18)
እንዲሁም ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስእንደነገረን “ሰላም ለናንተ ይሁን አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለው አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኅጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።” (ዮሐ 20፥21-23)
ስለዚህ ባጭሩ ጠያቂያችን ያነሱት ሃሳብ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ክህነቱ ከሌላ የተሾመው ሳይሆን የባህሪይ ስልጣኑ ነው። እሱ ሊቀ ካህናት ተብሎ ሲጠራ ካህናት ተብለው የሚጠሩ አገልጋዮች እንደሚያስፈልጉት እንኳን ከቃሉ አገላለፅ መረዳት ያስፈልጋል። በእርግጥ መፅሐፍ ቅዱስ በብዙ ምስጢራት የተሞላ ስለሆነ አንዳንድ ጊዜ እርስ በርሳቸው የሚጋጩና የሚጣረሱ የሚመስሉ ቃላቶችን በአሻሚነት ተመዝግበው ስናገኝ ፈጥነን ወደ ጥርጣሬና ወደ አላስፈላጊ ትርጉም ከመገባት ይልቅ በማስተዋል ሆነን ጠይቀን መረዳት ያስፈልጋል። ሁላችሁም ካህናት ናችሁ የሚለው የሐዋሪያትን ቃል ከመነሻ ጀምሮ ብናነበው በዚህ አንቀፅ ላይ ክህነት ለምን አገልግሎት ተፈልጎ እንደተጠቀሰ እዛው ላይ ትክክለኛውን ትርጉም አንብቦ ለመረዳት ይቻላል። ምክንያቱም ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ህይወት፣ ካለማመን ወደማመን፣ ከአህበዛብነት ወደ ክርስትና፣ ካለመታዘዝ ወደ መታዘዝ መምጣታችንን እና የሰማዩ አባታችን እግዚአብሔር ያዘጋጃትን ሰማያዊት ርስቱን ለመውረስ የተመረጥን ትውልድ ወይም የንጉሱ አገልጋዮች (ካህናት) ቅዱስ ህዝብ ለርስቱና ለመንግስቱ የተለየን መሆናችንን ለማመልከት የተገለፀ ቃል ነው። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ብዙ ርቀን ሳንሄድ በዚህ በአለማዊ የአገዛዝ ስርዓት ንጉሱ ባለበት የንጉሱ ባለሟሎች ወይም ተሿሚዎች ይኖራሉ። እነዚህ ህጉን የሚያስፈፅሙ ከነሱ በታች የተጣለባቸውን ሃላፊነት ተቀብለን እስከታችኛው ክፍል ያለውን ህዝብ የሚመሩ የሚየስተዳድሩ አሉ። ከእርገት በኅላ በአይነ ስጋችን የማናየው ሊቀ ካህናት እሱ በሾማቸው አገልጋዮች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ እኛ ኀጢአት የቆረሰውን ሥጋውን እና ያፈሰሰውን ደሙን እለት እለት በቤተመቅደስ በታቦት ላይ እየሰው ለህዝቡ ያቀብላሉ፣ እሱ ተሰቅሎ የዓለም ቤዛነት በተከፈለበት በቅዱስ መስቀሉ ይባርካሉ፣ እሱ እለተ አርብ ማዕገበ ከፀበሉ ያጠምቀናል ይረጨናል ፀበሉን ጠጥተን ህይወት እንድናኝበት ያደርናል ፣ እሱ ሰጣቸው የማሰርና የመፍታት የክህነት ስልጣን ከኀጢአት ማሰሪት ይፈቱናል። ስለዚህ የዚህ የክህነት አገልግሎት ስርዓት በዚህ አይነት የክርስቶስ ትዕዛዝ ተመስርቶ እስከ ዘመኑ ፍፃሜ ድረስ የሚቀጥል የአገልግሎት ስርዓት መሆኑን ጠንቅቀን ማወቅ ያስፈልጋል። ትምህርት የሌላቸው እውነተኛውን ምስጢር መረዳት የተሳናቸው መናፍቃን ግን እንዲሁ በጉልበትና በድፍረት ራሳቸውን ካህን አድርገው በመሰየም ሲቀልዱና ሲዘሉ በማየታችን በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ውርደትን እንጂ ክብርን ሊያመጣ ከቶ አይችልም። ምክንያቱም በክህነት አገልግሎት ለመኖር ራሱን የቻለ ልዩ ፀጋና ረቂቅ እውቀት ያስፈልጋል ከእግዚአብሔርም የተፈቀደ የክህነት ሹመት ያስፈልጋል።
ሴቶች ካህናት የማይሆኑበት ምክንያት ከጥንተ ተፈጥሮ ጀምሮ ማለትም ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ መስዋዕት የማቅረብ የተሰጣቸው በተፈጥሯቸው ወንድ ለሆኑ ስለሆነ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ወስጥ በአንድም ቦታ ሴት የክህነት አገልግሎት የፈፀመችበት ስርዓት አላየንም። ሴትም ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት የሚከለክላት ብዙ የተፈጥሮ ግዴታ አለባት። ይህም ወርሐዊ ግዳጅ ሲያዩ ፣ ሲያረግዙ፣ ሲወልዱ ወዘተ በመሳሰሉት ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች እንደ ኀጢአተኛ ባያስቆጥርም ወደ ቤተ መቅደስ ቀርቶ በቅፅረ ግቢ ቆመው ለማገልገል የሚከለከሉባቸው ጊዜያትና ስርአት ስላለ እነዚህን የመሳሰሉትን ሁሉ እንደማስረጃነት ይጠቀሳሉ። ነገር ግን ሴቶችም ቢሆኑ ለእግዚአብሔር እና ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ከመሆናቸውም የተነሳ እነሱም ከክህነት የማይተናነስ የሚታዘዙበት የአገልግሎት ድርሻ አላቸው። እጣኑን ሻማውን ለመስዋዕት አገልግሎት የሚያስፈልጉትን መገበርያውን ወይኑን የሚያዘጋጁ እነሱ ናቸው። ከዚህም በላይ ለክህነት የሚሆነውን ሰው ወልደው የሚያበረክቱ እነሱ ናቸውና ክብራቸው ከፍ ከፍ ያለ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ ሴቶችም ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው የራሳቸው ልዩ ፀጋና የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ስላላቸው ነገሮችን ከማደበላለቅና ከማምታታት ይልቅ በተሰጠን ፀጋ ፀንተን በማገልገል የየራሳችንን በረከት የምናገኝበትን አገልግሎት መፈፀም የበለጠ መሆኑን እንገልፃለን።
መልስ፦ ጠያቂያችን ስለ አጥማቂዎችና የፈውስ ስርዓት ስለሚፈፅሙ አገልጋዮች በሚመለከት ሁላችንም በማስተዋል በተረጋጋ መንፈስና አይምሮ መመርመር ያስፈልገናል። እንደ ቤተክርስቲያናችን ቀኖና በፆም በጸሎት ተወስነው በስርዓተ ጥምቀት በክህነታዊ አገልግሎት በመንፈሳዊ ብቃት ህሙማንን የመፈወስ ልዩ ልዩ ተአምራት ማድረግ የእውነተኛ አባቶች ፀጋቸው እንደሆነ ሁላችንም እናምናለን። ይሁን እንጂ ጠያቂያችን እንዳሉት በዘመናችን ብዙ ሰዎች በጥምቀት እና በልዩ ልዩ ምልክት ህሙማንን እንፈውሳለን አጋንንትን እናወጣለን መናፍስት ያለባቸውን እናስጮሃለን እና የመሳሰለውን ተአምራት እንፈፅለን የሚሉ ብዙ አገልጋዮች እንዳሉ ይህንንም ትዕይንት በየአካባቢያችን እንመለከታለን። በቅዱስ መፅሐፍ እንደተነገረው በዚህ በመጨረሻው ዘመን የሚታዩት ሀሰተኛ አስመሳይ ነብያቶች ወይም ደግሞ እናጠምቃለን ፣ ተአምራት እናደርጋለን፣ ህሙማንን እንፈውሳለን በማለት ህዝቡን ግራ የሚያጋቡ በጣም ብዙዎች ናቸው። በመሰረቱ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎች ማስተዋል ያለባችሁ አንዳንድ በአስመሳይነት ብቻ ብቃት ሳይኖራቸው፣ ቅድስና ሳይኖራቸው፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ልዩ ፀጋ ሳይኖራቸው፣ ሃብተ ፈውስ ሳይኖራቸው፣ ክህነት ሳይኖራቸው፣ ምንኩስና ሳይኖራቸው በራሳቸው ፍላጎትና አላማ ብቻ ሲሉ ሰውነታቸውን በሰንሰለት አስረው በጅራት እየገረፉ የማያምኑበትን መስቀል ተሸክመው ወይም የገዳማውያን መለያ የሆነውን ልብሰ ምንኩስና ለብሰው መቁጠርያ አስረው የራሳቸውንና የጺማቸውን ፀጉር አስረዝመው እውነተኛ አባቶች ሳይሆኑ በማታለል መንፈስ የገቡ ህዝበ ክርስተያኖችን ግራ የሚያጋቡ ሰዎች እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል። በመሰረቱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደነገረን በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፥ በዚህ ቀን ብዙዎች ጌታሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን በስመህስ አጋንንት አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንመን ይሉኛል የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኳችሁም እናንተ እመፀኛዎች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። በማለት በአስመሳይነት እና እንዲሀም በእግዚአብሔር መንፈስ ሳይሆን ሌላ ሀይል ተሞልተው ምዕመናንን የማስለፍለፍ የተለያየ ተአምራትን የሚመስል ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን ሁሉ እውነተኛ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረባቸው እንዳልሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ ጠያቂያችን እንዳሉት ጉዳዩ በእኛም በኩል የሚያሳዝነን ጉዳይ ቢሆንም ለምን ይጣላሉ ለምንስ እርስ በርሳቸው ይወጋገዛሉ ለሚለው ጥያቄ በእርግጥ በቅንነት ካልተመለከትነው ጥያቄው በቀጥታ እኛን የሚመለከት አይደለም። ምክንያቱም የፕሮግራማችን ዋና አላማው እውነተኛ የሆነውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መስጠት በመሆኑና በኛ በኩል መረጃው ስለሌለለን በዚህ ጥፋት ውስጥ ያሉትን ጠይቆ መረዳት የተሻለ እንደሚሆን እናምናለን። ይሁን እንጂ ጠያቂያችን በእምነታቸው ካላቸው መቆርቆር የተነሳ ስለጠየቁን በኛ በኩል ማንኛውንም ወገን ሳንወግን፤ ሁላችንም በማስተዋል በተረጋጋ መንፈስና አይምሮ በመመርመር መኖር እንደሚገባን ለመግለፅ ይህንን ማብራሪያ መስጠት ችለናል። ዋናው መገንዘብ ያለብን ነገር ማንኛውም ክርስቲያን እውነተኛውን ኦርቶዶክሳዊ መንገድ ተከትሎ እስከተጓዘ ድረስ በፈጣሪው ዘንድ የሚያስገኘውን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ክብር አያጣም። ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም ለእንዲህ አይነት አላማ ተሰማርተው ግራ የሚያጋቡትን ወደ ቀጥተኛውና እውነተኛው መስመር እንዲመጡ እስካሁንም እውነቱን ስትመሰክር ቆይታለች ወደፊትም ከማስተማር ከመገሰፅ ወደኋላ አትልም። ጠያቂያችን በስም ጠቅሰው የእከሌና የእከሌ ስላሉት ጉዳይ ግን በኛ በኩል ትክክለኛው መረጃ ስለሌለን በውስገጥ መስመር አግኝተውን ቢገልፁልን ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥዎ እንችላለን።
ጠየቂየችን፤ መፅሐፍ ቅዱስን በትክክለኛውና በእውነተኛው መንገድ ለሚረዱት ሰዎች፥ የተለየ የሚባል ወይም የፕሮቴስታንት ዶግማ ለብቻው የተሰጠ መፅሐፍ ቅዱስ የለም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ዘመናት ለህትመት በዋለ ጊዜ የፕሮቴስታንቱ አለም ከእውነተኛው ሃይማኖት ወይም ዶግማ እየተንሸራተቱ ለራሳቸው በሚያመቻቸው አካሄድ መፅሐፍ ቅዱስን በተራ ቋንቋ አገላለፅ እየተረጎሙና፥ የተቃናውን ትርጉም እያጣመሙ ፥ በተለይ ስለ ክርስቶስ የባህሪይ አምላክነት እና ስለ ቅዱሳን አማላጅነት በመፅሐፍ ቅዱስ የምናገኘውን እውነተኛ ቃል እያዛቡ በመተርጎም ያሳተሙት መፅሐፍ ቅዱስ ብዙ ህጸጽ ስለተገኘበት እና ትርጓሜውም እየተጣመመ የተፃፈ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዚህ ዙሪያ ያላትን ቅሬታ ለመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ስታቀርብ ከቆየች በኋላ ፥ እሷ የምትቀበለው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል 66ቱን ብቻ ሳይሆን 80 አሀዱን እንደሆነ፣ በተለይ ደግሞ በውስጡ አዲስ ኪዳን በነጠላ አገላለፅ እየተጣመሙ ተተርጉሞ የታተመውን ከትክክለኛ የአገላለፅ አገባቡ ትርጓሜውን ከነሚስጥሩ በማስተካከል በእራስዋ ሊቃውንት የተዘጋጀውና በመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ቀርቦ ተቀባይነት ስላገኘ ታትሞ ስራ ላይ ስለዋለና ለኦርቶዶክስ ማህበረ ካህናትም ሆነ ምእመናን እንዲደርሳቸው ስለተሰራጨ በአሁኑ ሰዓት የፕሮቴስታንት መፅሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚታመንበትና ብዙ የቃላት ስህተት ያለበትን መፅሐፍ ቅዱስ ከመጠቀም ይልቅ ቤተክርስቲያን በራስዋ አዘጋጅታ ያሳተመችውን መፅሐፍ ቅዱስ የእኛ የራሳችን ብለን መገልገል እንድንችል ስለተደረገ ጠያቂያችንም ሃሳቡን በዚህ መሰረት እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።