ትምህርት ስለ ተዋሕዶ

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ማን ናት?

በሰው ልጅ የማዳን ሥራ ያላት ድርሻ ምንድን ነው?

ክፍል አንድ ቁ.1

በቅድሚያ ‘ኦርቶ’ – ‘ዶክስ’ – ‘ተዋሕዶ‘ ‘ሃይማኖት‘ የሚለውን ቃል፥ በምስጢራዊ አተረጋጎሙ እና በነገረ መለኮት አስተምሮ የአገላለጽ ዘይቤና ስልት መሰረት በአጭሩ መረዳት ያስፈልጋል።

  1. ኦርቶ ዶክስ” ፡- ማለት፤ ቃሉ የግሪክ ሲሆን፤ “ቀጥተኛ መንገድ (እውነተኛ ሃይማኖት)” ማለት ነው።

በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም በ325 ዓ.ም. 318 ሊቃውንት (የቤተክርስቲያን አባቶች) በኒቅያ ከተማ  የሃይማኖት ጉባኤ (የሲኖዶስ ጉባኤ) በማድረግ፤ በወቅቱ አርዮስ የተባለው የክሕደት ሰው “ፈጣሪን፤ ፍጡር ነው”፤ በሚል የክሕደት ትምሕርት ብዙዎች እንዲክዱ አድርጓል። በመሆኑም ፤ የቤተክርስቲያናችን ታሪክ እንደሚመሰክረው፤  በዚህ ጉባኤ ሊቃውንትም፥ እውነተኛዋን ፣ ቀጥተኛዋን የተዋሕዶ ሃይማኖት ከ አርዮስ  የክሕደት ሃይማኖትና፣ የክህደት ትምህርት ለመለየት  “ኦርቶ ዶክስ (ቀጥተኛ መንገድ) ሃይማኖት” በማለት ሰይመውታል።  

ነብዩ ኤርምያስም ስለ እውነተኛዋና ቀጥተኛዋ መንገድ (ሃይማኖት) ሲናገር “የቀደመችውን ቀጥተኛዋን መንገድ ጠይቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁ” ብሏል (ኤር 6፤16)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “እኔ መንገድ እውነት ሕይወት ነኝ” ብሏል (ዩሐ 14፤6)

ሐዋርያው ቅ/ጰውሎስም ለእብራውያን ወገኖቹ (ተከታዮቹ) በጻፈው መልእክቱ፦ “የመጀመሪያ እምነታችንን፥ እስከ መጨረሻው አጽንተን እንጠብቅ”፤ በማለት ስለቀደምት፣ እና ስለመጀመሪያዋ ቀጥተኛ ሃይማኖት አስተምሯል (ዕብ 3፤14)

2.“ተዋሕዶ” ማለት ቃሉ የግእዝ ቃል ነው። በ 431 ዓ.ም. 200 ሊቃነ ጰጰሳት (የቤተክርስቲያን አባቶች) በኤፌሶን ከተማ በሲኖዶሳዊ ጉባኤ ተሰብስበው ነበር። የመለኮት እና የስጋን መዋሐድ :- እግዚአብሔር ወልድ፥ በድንግል ማርያም ማሐፀን አድሮ፤ ከሥጋዋ ፥ ሥጋ ፤ ከነፍሷ ፥ ነፍስ፤ ነሥቶ ፤ በ ተወለደ ጊዜ ፤ “ቃልና ሥጋ፥ በተዋሕዶ ከበረ”። ንስጥሮስ የተባለው የክሕደት ሰው ግን ይህንን እውነተኛ እና ቀጥተኛ አስተምሮ በመቃወም፤ ስለ ‘የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ’ እያፋለሰ ያስተምርም ነበር። ስለሆነም ፥ ‘ኦርቶዶክስ’ በሚለው ቃል ላይ፤ ‘ተዋሕዶ’ የሚለውን ቃል ፥በመጨመር ፤ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት” ፥ ተብሎ እንዲጠራ ፥ሊቃነጳጳሳቱ ፥በዚህ ጉባኤ ፥ወስነዋል። በትምሕርትና በተግሣጽ ከክሕደቱ አልመለስም አሻፈረኝ በማለት የክሕደት አመጹን የቀጠለበትን ንስጥሮስንም ፤ አውግዘው ከቤተክርስትያን ለይተውታል።

3.“ሃይማኖት” ማለት ምንድን ነው? ብለው ጥይቄ ለሚያቀርቡ ወገኖች ሁሉ ፥ሊያውቁት የሚገባቸው ዋና ቁም ነገር ፥ ፈጣሪና ፍጡር፣ ጽድቅና ኩነኔ፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ሕይወትና ሞት፣ ገነትና ሲኦል፥ ተለይተው የሚታወቁበት ፥የሁላችንም የሕሊና መነፅር በ ፥ ‘ሃይማኖት’ ነው። የሰው ልጅ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ፤ በአይን የማይታየውን፣ በእጅ የማይዳሰሰውን፣ ረቂቁን አምላክ (ፈጣሪ)፣ ለማወቅ እና ለመድረስ የሚችልበት እውነተኛ መንገድ ሃይማኖት ነው።

ሃይማኖት ማለት እግዚአብሔርን የምናምንበትና የምናውቅበት ረቂቅ መንገድ ነው፤ ሲባል፦ በዓይነ ሥጋ ተመልክተን፣ በዕዝነ ሥጋ ሰምተን ፣ በልብ አስበን እና፣ በስሜት ሕዋሳታችን አድምጠን ፣ ልንመረምረውና ልንደርስበት የማይቻለን እና፤ ከእኛ ሥጋ ደካማነትና ከፀጋ ብቃታችን ማነሥ የተነሣ ነው። ስለዚህ ሩቅ እና ረቂቅ የሆነብንን መለኮታዊ ጥበብ፤ ይሆናል፥ እና ይደረጋል ብለን፤ በእምነት ለመቀበል ፥ የምንችልበት ምስጢር ስለሆነ ነው።

ሐዋርያው ቅ/ጰውሎስ ለእብራውያን ተከታዮቹ ስለ እምነት በተናገረበት መልእክቱ ላይ “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፤ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው” ፤ ሲል፤ ሃይማኖት፤ በዓይነ ሥጋ የማናየውን እግዚአብሔርና ረቂቅ ሥራውን የምናይበት፤ ልዩ ፀጋ መሆኑን ተናግሯል (ዕብ 11፤1)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በሰው ልጅ የማዳን ሥራ ያላት ድርሻ  ምንድነው ስለሚለው ትምህርት በክፍል ሁለት ላይ እንዲደርሳችሁ እናደርጋለን።

ወገኖች፦ ዕዝነ ልቡናችሁን አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያብራላችሁ

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

የክፍል አንድ ቁ.2

የክፍለ አንድ ቁ.2
 
በ ክፍል አንድ ላይ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት” ስለሚለው ስያሜ እና ትምህርታዊ ትንታኔ እንዲሁም የሰው ልጅ ከፈጣሪ ጋር የሚገናኝበት ቀጥተኛ መንገድ መሆኑን አጠር ያለ መልእክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል። ዛሬም ወደ ክፍል ሁለት ከማለፋችን በፊት በክፍል አንድ ስር መካተት ያለበትን ፍሬ ሃሳብ ካለፈው የቀጠለ የሃይማኖት ትምህርት እናቀርባለን።
 

በመሠረቱ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ስንል የእግዚአብሔርን አንድነት እና ሦስትነት፥ እና በስጋዊ አይናችን የማናየውን፣ በእጃችን የማንዳስሰዉን፣ እሮጠን የማንቀድመውን፣ ተመራምረን የማንደርስበት፥ አምላክ (ፈጣሪ ) አለ ብሎ ማመን ነው። በስነ ተፈጥሮ ህግ በኩልም ፥ሰማይ እና ምድርን፣ ጨለማን እና ብርሃንን፣ ቀኑንና ሌሊቱን ፣ሰውን እና መላእክትን፣ የዱር አራዊትን እና እንሰሳትን፣ አዝርእትን እና አትክልትን፣ በየብስ እና በባህር ውስጥ የሚሽከረከሩ፣ በደረታቸው የሚሳቡ፣ በክንፉቸው የሚበሩ ልዩ ልዩ ፍጥረታትን ፥ በአጠቃላይም 22 ስነፍጥረታትን ፥ ፈጥሮ ፥  ስነፍጥረታትን ሁሉ የሚመግብ እና፣ የሚመራ ፈጣሪ መሆኑን አምነን የተቀበልንበት ቀጥተኛ መንገድ ‘ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት’ ነው። ከሌሎቹ የእምነት አይነቶች የተለየ የሚያደርገውም ዋናው ሚስጢር ይህ ነዉ። ምክንያቱም እምነት ሁሉ ሃይማኖት አይደለም፤ ለምሳሌ ፦ በሠይጣን የሚያምኑ፣ በአምልኮ ጣኦት የሚያምኑ፣ በዛር መንፈስ የሚያምኑ፣ በእሳት፣ በወንዝ፣ በዛፍ፣ በድንጋይ፣ በልዩ ልዩ መንፈስ፣ የሚያመልኩ ሰዎች የሚያምኑትን እምነት ሁሉ ሃይማኖት አንለውም። እውነተኛውና ቀጥተኛው ሃይማኖት እግዚአብሔርን ብቻ   አምላክ ፈጣሪ፣  መጋቢ ፥ብለን ፥ ለማመን ፥ የተሰጠን የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ነው።ታላቁ የሃይማኖት አባት ቅዱስ- ዩሐንስ አፈወርቅ፤ “ሃይማኖት የሁሉ ነገር መሠረት ናት፤ ሌሎቹ ግን ህንፃ እና ግንብ ወይም ደግሞ ጣራ አና ግድግዳ ናቸው” በማለት እንደ ህንፃ እና እንደ ግንብ ከሚቆጠሩት የምግባር እና የትሩፋት ስራዎች ሁሉ በፊት ሃይማኖት ተቀዳሚ እና መሠረት መሆንዋን አረጋግጦልናል። የአንድ ቤት መሠረት ህንፃውን ሁሉ አንደሚሸከም፤ እምነት ፣ ምግባር፣  አና ልዩ ልዩ በጎ ስራዎችን ሁሉ ሃይማኖት ትሸከማለች።ህንፃ ያለ መሠረት እንደማይቆም ምግባርም ያለ ሃይማኖት አይኖርም፤ ወይም ትርጉም የለውም።  ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ስራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው”  በማለት ሃይማኖት እና ምግባር ፤ ተለያይተው የማይነገሩ እንደ አንድ ሳንቲም ገፅታ መሆናቸውን በዚህ ተናግሯል።

 
ሃይማኖት የሁሉ ነገር መሠረት ነው፣ ጥልቅ እና ረቂቅ መንገድ ነው የምንልበት ምክንያትም፦ በባህሪው የማይታየውን እና የማይዳሰሰውን አምላክ አለ ብሎ ማመን ስለሆነ ነው።
ሃይማኖት፦ የምናምነውን እና የምናመልከውን ዘለአለማዊ እና ሰማያዊ አምላክ ፦
–  የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ነው
–  የፍጥረታት ሁሉ መጋቢ ነው
–  የፍጥረታት ሁሉ ጠባቂ ነው
–  የአማልክት አምላክ ነው
–  የነገስታት ሁሉ ንጉሥ ነው
–  የጌቶች ሁሉ ጌታ ነው
–  ከአለም በፊት የነበረና፣ አለምን አሳልፎ የሚኖር፣ ዘለአለማዊ አምላክ ነው
–  የምህረትና የፅድቅ አምላክ ነው
–  የሰላምና የፍቅር አምላክ ነው
–  የህይወት እና የድነት አምላክ ነው
–  የይቅርታ እና የምህረት አምላክ ነው
–  ሰውን ለማዳን ብሎ ሰው የሆነ አምላክ ነው
–  የኀጢያተኞችን ሞት የማይወድ አምላክ ነው
–  ስለ ሰው ልጅ መዳን እስከ መስቀል ሞት ድረስ የታመነ አምላክ ነው
በማለት በፍፁም ልባችን የምናመልከውን አምላክ አምነን እንድንቀበል እና እስከ አለም ፍፃሜ የምንጓዝበት የብርሃን መንገዳችን እና የፅድቅ በራችን ነው።
ሃይማኖት፦ የሰው ልጅ በተፈጥሯዊ አይምሮው ተመራምሮ እና በህሊናዊ ጥበቡ እውነቱን ተረድቶ፤ የፈጣሪውን አምላክነት  እና ሁሉን ቻይነት አምኖ እውነት ነው፣ እርግጠኛም ነው ብሎ ለመቀበል ያስችላል። እግዚአብሔር የሚለው መለኮታዊ ስም በፈጣሪነቱ፣ በመግቦቱ፣ በመለኮታዊ ስራው፣ በባህሪው፣ በስልጣኑ፣ በአገዛዙ አንድ አምላክ ብለን የምናምነው ሲሆን፤  በስም፣ በግብር፣  እና በአካል የስላሴን ሦስትነት የምናውቅበት ሲሆን ሃይማኖት ‘አንድም፣ ሦስትም’ ብለን የምናምነው የዘላለም አምላክ እንደሆነ የምናውቅበት ረቂቅ ሚስጢር እና የሀሳባችን ሁሉ መደምደሚያ ነው።
 
መቼም ግዜ ቢሆን፤ የእግዚአብሔርን ሀልዎት አምኖ ለመቀበል፤ የሰው ልጅ የመረጃ ምንጭ አድርጎ ከሚያረጋግጥባቸው ዋና ዋና ማስረጃዎች የሚከተሉት ናቸው፦
1. የራስ ህሊና
2. ቅዱሳት መፃህፍት እና
3. ስነ-ፍጥረት 
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለሮማውያን ሰወች በፃፈው ክታቡ፦ “የማይታየው ባህርይው፣ እርሱም የዘላለም ኀይሉ፣ ደግሞም አምላክነቱ፣ ከአለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሰሩት ታዉቆ ግልፅ ሆኖ ይታያል። ስለዚህ፦ እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ ስላላከበሩት እና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙትበት  አጡ።” በማለት፤ ‘እግዚአብሔር አለ’ ብሎ ለማወቅ፦ ከፍጥረታት በላይ ማስረጃ ሊሆን የሚችል እንዳልተገኘ ገልጾ፤ በክህደታቸው እና በከንቱ ሀሳባቸው እየሄዱ የሚጠራጠሩትን ሰወች አስረግጦ መክሯል። ሮሜ 1፥20-21
 
‘ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት’ ቀጥተኛ መንገድ ነዉ የምንለው፦ 
– የስላሴን፤ አንድነት እና ሦስትነት፤ (ሚስጥረ ስላሴን)፣ ‘የእግዚአብሔር አብ የባሕሪይ ልጁ’ የሆነው፤ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ፤ ቅድመ አለም፤ ከባህርይ አባቱ  ከእግዚአብሔር አብ፤ ያለ እናት፣ መወለዱን፣ 
– ድህረ አለም ወይም በኋለኛው ዘመን ደግሞ ያለአባት ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍቱም ድንግልናዋ ሳይለወጥ መወለዱን፤ እንዲሁም 
– ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ፤ ስለ ሰው ልጅ ኀጥያት፤ እስከ እርገቱ ድረስ የከፈለልንን የሞት ዋጋ፣  
– በመጨረሻ ዘመን የሰውን ልጅ ለፍርድ በፊቱ ሊያቆም ዳግም እንደሚመጣ፤   
 በስሙ አምነው እስከሞት ድረስ የታመኑ ቅዱሳንን በዘለአለም ቃል ኪዳን ያከበራቸው መሆኑን፣
– እነዚህንና ሌሎችንም በዚህ ትምህርት ያልጠቀስናቸውን 
የአምላክ ስራዎችን አንዱንም ሳናጎድል፣ እና ሳንነጣጥል የምናይበት መንፈሳዊ መነፅራችን ሃይማኖት ስለሆነ ነው ቀጥተኛ መንገድ ነው የምንለው ።
 
ስለ ሚስጢረ ስላሴ፣ ስለ ሚስጢረ ስጋዌ፣ ስለ ሚስጢረ ጥምቀት፣ ስለ ሚስጢረ ቀንዲል፣ ስለ ሚስጢረ ንስሐ፣ ስለ ሚስጢረ ተክሊል፣ ስለ ሚስጢረ ክህነት፣ ስለ ፆም፣ ፀሎት፣ ምፅዋት፣ ስግደት ጥቅም፣ ስለ መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ስለ ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናዋ እና አማላጅነቷ፣ ስለ ቅዱሳን ክብር እና አማላጅነት እና ቃል ኪዳን የመሳሰሉትን፤ ቅዱሳት ሚስጥራት ለትውልድ የምታስተምር እና ከእኛም ዘመን በኋላ ለትውልድ ፀንታ የምትኖር መሆኑን በአደባባይ የምትመሰክር እውነተኛ ቤተክርስቲያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ናት።
 
እግዚአብሔርን የምናስደስትበት ትልቁ መንፈሳዊ ስጦታችንን የምናይበት አይናችን ሃይማኖት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ “እግዚአብሔርን ያለ እምነት ደስ ማሰኘት አይቻልም”፤ በማለት ሳይጠራጠሩ እና በኀጢአት ሳይወድቁ ፣ እውነተኛ ሃይማኖተኛ (ታማኝ) ሆኖ መገኘት፤ እግዚአብሔርን ደስ እንደሚያሰኘው፤ ለዕብራውያን ወገኖቹ በፃፈው መልዕክቱ ላይ አስተምሮናል። ዕብ11፥16
 
ይቀጥላል
ክፍል ሁለት
 
ነገረ ሃይማኖት (የሃይማኖት ትምህርት) 
 
ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት በሰው ልጅ የመዳን ምስጢር ያላት ድርሻ!
 
የተወዳችሁና የተከበራችሁ ፥በዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ (ፔጅ) የሚሰጠውን መንፈሳዊ ፕሮግራም የምትከታተሉ ኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን ሁላችሁም :-ከሁሉ አስቀድሞ ፤እውቀትና ጥበብ የባህሪይ ገንዘቡ የሆነው ቅዱስ እግዚአብሔር ፤በነገር ሁሉ አስተዋዮች እና ጥበበኞች እንሆን ዘንድ የሁላችንንም ፥አይነ ልቦናችን ያብራልን:ዕዝነ ህሊናችንን ይክፈትልን፤ ምስጢሩን እና ጥበቡንም ይግለፅልን። ከዚህ በፊት ፥ ‘የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት’ ማን እንደሆነች ፥በቤተክርስቲያናችን አስተምሮ መሰረት ለአንባቢዎችና ትምህርቱን ለሚከታተሉ አባላቶቻችን ሁሉ በቀላል መንገድ ሊረዱትና ግልፅ ሊሆንላቸው በሚችል አቀራረብ “ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት” ከሚለው ቃል ትርጉም በመነሳት ትምህርት ማስተላለፉችን ይታወሳል፡፡በምስጢራዊ ትርጉሙም ፥ሃይማኖት :-ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት የፅድቅ መንገድ እንደሆነ እና ፤ንጽሂትና ቅድስት የሆነችውን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ፥ከሌሎቹ የስም ሃይማኖቶች ፥ከቃል ትርጉም ጀምሮ የምትለይበት ቀኖናዊ ይዘት ምን እንደሚመስል ፥በቀላሉ መረዳት ይቻል ዘንድ ፥በቤተክርስቲያን የአስተምሮ ዘይቤ ተዘጋጅቶ የቀረበ ስለሆነ ፥ሁላችሁም ተከታትላችሁ እንደተረዳችሁትና መንፈሳዊ ግንዛቤን እንዳገኛችሁበት ተስፋ እናደርጋለን። 
 
ለቀጣዩ የትምህርት ክፍል መሰረትና መግቢያ ይሆን ዘንድ ፥ከዚህ በፊት በክፍል አንድ የገለፅናቸውን ዋና ዋናዎቹን ለማስታወስ፦
 
ሃይማኖት፦
 
1. ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባት ረቂቅ መንገድ ነው፣ 
2. ሀለውተ እግዚአብሔርን ያወቅንባት፣ 
3. የስላሴን አንድነት ሦስትነት የተረዳንባት ፣ 
4. የእግዘኢአብሔርን ፈጣሪ አለምነቱን ወይም የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት ፣ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ያወቅንባት ፣ 
5. የፍጥረታት ሁሉ መጋቢና ገዢ መሆኑን ያስተዋልንበት፣ 
6. ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው መሆኑን ያረጋገጥንበት፣ 
7. በ30 ዘመኑ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን ያየንበት 
8. በመዋእለ ስጋዊው ሳለ በትምህርትና በተአምራት ያደረገውን መለኮታዊ ግብሩን ያየንበት፣ 
9. የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል በመስቀል ላይ የተቀበለውን ነገረ ህማማቱን ያየንበት፣ 
10. ነገረ ሞቱንና ስለ ነገረ ትንሳኤውን የረጋገጥንበት፣ 
11. ነገረ እርገቱን እና ዳግም ምፅአቱን ያየንባት፣ 
12. በገዛ ደሙ የዋጃትን እና የመሠረታትን ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘወትር በውጧ የሚፈፀሙትን ምስጢራት ያወቅንባት በኅጢአት የወደቁትን ሁሉ ዘወትር በንስሓ ይቅር እንደሚላቸው የተማርንበት
 
እና ሌሎቹንም ጠቃሚ መልዕክቶችን ወደእናንተ እንዲደርሱ በትምህርታችን ማስተላለፋችንን እናስታውሳለን። በክፍል ሁለት ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የሰው ልጅ የነፍስና የስጋ ድህነትን ያገኝ ዘንድ ያላትን ትልቅ ድርሻ ከላይ እንደተገለፀው ቀጥተኛ የእግዚአብሔር መንገድ (ፍኖተ እግዚአብሔር) የሆነችው የተዋህዶ ሃይማኖታችን በሰው ልጅ የመዳን ስራ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይዛለች። ሃይማኖት ለሰው ልጅ የመዳን ምስጢር አማራጭ የሌለው ብቸኛ እና እውነተኛ መንገድ ነው። ከምንም በላይ የሰው ልጅ ወደ ፈጣሪው ለመድረስ የሚችልበት ቀጥተኛ መንገድ ሃይማኖት ብቻ እንደሆነ ያስረዳን እና በዚህ የብርሃን መንገድ እንድንሄድ ያዘዘን እራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር አምላክ ነው።
 
እግዚአብሔር አምላክ በነብዩ ኤርምያስ ላይ አድሮ “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱን መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ፣ በእርስዋም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” በማለት የቀደመችው እና ከእግዚአብሔር ጋር የምታገናኝ ለነፍስም እረፍት የምታሰጥ መንገድ ሃይማኖት መሆኗን በሚስጥራዊ ቃሉ ነግሮናል። (ኤር 6፤16)
 
ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስም በቅዱስ ወንጌል ፦ 
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።” (ዮሐ 3፥16) 
“በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሁሉ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል….ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ” በማለት በፍፁም ሃይማኖት ለሚኖሩ ሁሉ በእሱ ስም አምነው የሚለምኑትን ሁሉ እንደሚፈፅምላቸው እና ከዚህም በላይ የሚያስደንቀውን የእግዚአብሔርን ስራ ለመፈፀም እንደሚችሉ ለቅዱስ ሐዋሪያት በትምህርቱ አረጋግጦላቸዋል። ( ዮሐ 14፥12 እና 14) 
እግዚአብሔር አምላክ በጥንተ ተፈጥሮ በአርአያው እና በምሳሌው የፈጠረውን የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ ክፉውን እና መልካሙን፣ የሚጎዳውን እና የሚጠቅመውን ፣ ኅጢአትን እና ጽድቅን፣ ሞትን እና ህይወትን ለይቶ የሚያውቅበት መንፈሳዊ ጥበብ ከእግዚአብሔር ዘንድ የህይወት እስትንፋስ የተሰጠው ስለሆነ በፈጣሪው ዘንድ በተዘጋጀለት ልዩ ስፍራ ያለአንዳች ድካም እና ያለአንዳች መታከት እንዲኖር የእግዚአብሔርን ፀጋ የታደለ ልዩ ፍጡር ቢሆንም እንኳን በፈጣሪው የተሰጠውን ትዕዛዝ በማፍረሱ እና አታድርግ የተባለውን በማድረጉ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት ቀጥተኛ የሆነችው የሃይማኖት መንገድ ስለጠፋችበት በክህደት እና በሞት ጉድጓድ ውስጥ ሊወድቅ ችሏል። (ዘፍ 2፤8-11)
 
ለሰው ልጅ ሁሉ መሠረት የሆኑት አባታችን አዳም እና እናታችን ሄዋን የእውነተኛውን አምላክ መለኮታዊ ትዕዛዝ አፍርሰውና መመሪያውን ጥሰው በእባብ ላይ ተሰውሮ የቀረባቸውን የጠላታቸውን የዲያብሎስን የሃሠት ምክር በተቀበሉ ጊዜ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚያገናኛቸው ቀጥተኛ መንገድ በመውጣታቸው በእውነት ወደሚያምኑትና ወደሚያመልኩት፣ ከሞት ወደሚያድናቸው ከመከራ ሁሉ ወደሚታደጋቸው አምላክ ለመድረስ ተስኗቸው ከእውነተኛው የሃይማኖት መስመር ወጥተው 5500 ዘመን ሁሉ በስጋቸው ሞተ ስጋ፣ በነፍሳቸው ደግሞ ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው ዳግማዊ አዳም እየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በተዋሀደው ስጋ ተገልጦ እውነተኛዋንና ቀጥተኛዋን የሃይማኖት መንገድ እስከሚያሳያቸው ድረስ ሁሉም የሰው ልጆች በጥፋት ጎዳና ይጓዙ እንደነበረ ቅዱሳት መፅሓፍት በስፋት ይናገራሉ።
 
ነብዩ ኢሳያስም “ፅድቃችን ሁሉ የመርገም ጨርቅ ሆነ” በማለት የበደሉትንም ያልበደሉትንም የአዳም ኅጢአት በዘር ስለተቆራኛቸው የተወሰደባቸውን የልጅነት ክብር ማስመለስ የሚችል ከሱ ከባለቤቱ በስተቀር ማንም እንደሌለ የሰው ሁሉ ጩህት ከንቱ መሆኑን ተናግሯል። 
 
ከመጀመሪያ ሰው ከአዳም ጥፋት በኋላ በሕገ ልቦና በሕገ ኦሪት የሚኖሩ የሰው ልጆች በዘር የሚተላለፍባቸው የውርስ ኅጢአት ምክንያት የጥፋቱን መንገድ አጠናክረው ቢቀጥሉበትም እንኳን በየጊዜው እውነተኛዋን መንገድ ለማግኘት እረፍት አጥተው ዘወትር ወደ ፈጣሪያቸው የሞጮሁ፣ እውነተኛውን አምላካቸውን ለማግኘት የሚቃትቱና አካሄዳቸውንም ከፈጣሪያቸው ጋር የደረጉ ብዙ አበው ቅዱሳን በየዘመናቸው ከረቂቅ ጠላታቸው ዲያብሎስ ጋር ባደረጉት ተጋድሎ እውነተኛዋን የድኅነት መንገድ እንደተከተሉ የጽድቅ ገድላቸው ይመሰክራል። 
 
የሰው ልጅ በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ጉዳይ ለመዳን ከሁሉ አስቀድሞ ማመን ያስፈልገዋል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል፤ ብሎ ማመን የሰው ልጅ የመዳን ምስጢር እንደሆነ አስተምሯል። (ማር 16፥16) 
ትክክለኛ ሃይማኖት በምግባር መገለፅ እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል። አንድ እውነተኛ አማኝ ትክክ
 
ለኛ ሃይማኖተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥበት መንገድ ሃይማኖቱን በበጎ ሥራና በቱሩፋት ሲገልፅ ብቻ ነው። ማመን የማይታየውንና የማይዳሰሰውን ረቂቁን አምላክ የምናይበት ውስጣዊ ዓይናችን፣ የምንጓዝበት ምስጢራዊ ስውር መንገዳችን ቢሆንም እንኳ፤ ሃይማኖት ያለምግባር ምግባር ያለሃይማኖት ብቻቸውን ተነጣጥለው እንደማይቆሙና ነፍስ የተለየው ሥጋ እንደሚሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ተናግሯል። (ያዕ1፥20-26) 
አጋንንትም የእግዚአብሔር ፍጥረታት እንደመሆናቸው መጠን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የባህርይ አምላክ እንደሆነ አምነው መስክረዋል። 
በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ “ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮሁ።” (ማር 3፥11) 
“እየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት በታላቅ ድምጽም እየጮኅ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ እየሱስ ሆይ ከአንተጋር ምን አለኝ እንዳታሰቃየኝ በእግዚአብሔር እምልሃለሁ አለ። አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና” (ማር 5፥ 5-8) 
 
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልዕክቱ “እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተም ታምናለህ መልካም ታደርጋለህ አጋንንትም ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። (ያዕ 2፥19) 
ከላይ በመግቢያችን ላይ ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳያችን ጥንተ ነገራችን ስንመለስ ኦርቶ ዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ለሰው ልጅ መዳን ትልቅ ድርሻ አላት ያልንበት ዋና ምክንያት ከሃይማኖታቸው ጽናት የተነሣ ስለሃይማኖታቸው ጥንካሬ ከብዙ አሰቃቂ አስከፊ የሥጋና የነፍስ መከራ እግዚአብሔር አምላክ ያዳናቸውን የቅዱሳን ሰዎች ታሪክ ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን። 
 
ይቀጥላል

ሰሞኑን በቴሌግራም ግሩፓችን የተነሱ ጥያቄዎች

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸው የክህነት ስልጣን ማሰር እና መፍታት የሚችሉበት ረቂቅ እና ሰማያዊ ስልጣንን ነው። ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባትም ሆነ ከመንግስተ ሰማያት ለመከልከል የሚያስችል ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው ስልጣንም ነው። ይህ ማለት ስልጣን ሁሉ የራሱ ገንዘብ የሆነው የባህርይ አምላክ እየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ሐዋርያት እና 72ቱን አርድእት ከዓለም መካከል መርጦ በሾማቸው ግዜ ኀጥያት ሰርተው በደል ፈጽመው ወደ ሐዋርያት ቀርበው በኀጢአታቸው ተጸጽተው የተናዘዙትን ኀጥያታቸውን የማስተሰረይ ስልጣን ስለተሰጣቸው ኀጥያታችሁ ይቅርላችሁ ያሏቸው ሁሉ የተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ኅጥያታቸው ሁሉ እንዲደመሰስ ያደርጋል።
 
በሰሩት ጥፋት ሳይጸጸቱ እና ከበደላቸው የማይመለሱትን ደግሞ በተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ሲፈርዱባቸው በስጋቸው ሞትና ልዩ ልዩ መቅሰፍት ይቀጣሉ ማለት ነው። 
 
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፦
 
–  ግያዝ የተባለው የነብዩ ኤልሳዕ ደቀመዝሙር ከመምህሩ ተሰውሮ ከለምጽ በሽታ ካዳነው ሶርያው ንጉስ ከንዕማን ላይ የማይገባውን ጥቅም በመውሰዱ ምክንያት ነብዩ ኤልሳዕ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ ግያዝን በለምጽ ደዌ አንደቀጣው እንመለከታለን። 2ኛ ነገስት 5፥20-27
 
–  ሐናንያ እና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች በሐዋርያት ፊት ያላቸውን የሀብታቸውን እኩሌታ ለእግዚአብሔር ሊሰጡ ቃል ከገቡ በኋላ ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን አታላችኋል ብሎ በተሰጠው የክህነት ስልጣኑ የሞት ቅጣት እንዲደርስባቸው አድርጓል። የሐዋ 5፥1-10
 
–  በጥንቆላ መንፈስ የሚኖር ሲሞን መሠሪ የተባለው ሰው ሐዋርያት እጅ በመጫን  የመንፈስ ቅዱስ ኅይል የሚሰሩትን አስደናቂ ሚስጥር ባየ ግዜ እንደእናንተ ይሄንን ታላቅ አስደናቂ ስራ ለመስራት እንድችል ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን ስልጣን በገንዘብ ሽጡልኝ ባላቸው ግዜ እድል ፋንታውን ከክፉዎች ጋር እንዲሆን እና የጥፋት ሰው አንደሆነ ረግመውታል። ዩሐ 8፥18-24
 
ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ማስረጃዎች የመንግሰተ ሰማያት መክፈቻ ለሐዋርያት ተሰጠ ሲባል በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት መንግስተ ሰማያት ማስገባት እንደሚችሉ እና የማይገባቸውን መከልከል የሚችሉ መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ የቤት ወይም የበር ቁልፍ መክፈቻና መዝጊያ ቁሳዊ ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማሰር መፍታት የሚለውም በዚህ አለም ላይ ሰው በፈጸመው ወንጀል የሚታሰርበት አግር ብረት ወይም ገመድ ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን ከላይ እንደገለጽነው በተሰጣቸው ረቂቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣን ኅጥያትን የማስተሰረይ፣ የኀጥያተኞችን ኅጥያት የመያዝ ፀጋ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ነገረ ተዋህዶ (ነገረ ክርስቶስ)
 
እየሱስ ክርስቶስ በእውነት የባሕሪይ አምላክ ነው
 
ቀዳማዊ ቃል እየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሥጋን ተዋህዶ ሰው በሆነ ጊዜ ከተጠራባቸው የተዋህዶ ስሞቹ እየሱስ የሚለው ስም አንዱ ሲሆን ምስጢራዊ ትርጓ ሜውም መድኃኒት ማለት ነው ::
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የጌታ ቃል የሆነውን ቅዱስ ወንጌል ሲፅፍ “እርሱ ህዝቡን ከኅጢአታቸው ያድናቸዋልና ሰውንም እየሱስ ትለዋለህ በማለት አዳኝነቱን ገልጿልናል :(ማቴ1፣ 21)
ቅዱስ ሉቃስም በፃፈው ቅዱስ የወንጌል ቃል ላይ ” መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” በማለት መድኃኒት የሆነው እየሱስ ክርስቶስ መወለዱን ባበሰረበት የወንጌል ቃል ይገልፃል።(ሉቃ 2፥11)
ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስም “ሳምራዊቷ ሴት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነጋገራት ጊዜ የአምላክነቱ ምስጢር ተገልፆላት የእርሱም በእውነት ክርስቶስ የአለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን ይሏት ነበር” (ዮሐ 4፥42)
እየሱስ ክርስቶስ ማለት ብቻ የመለኮታዊ ቃል ብቻ የትስብዕት ስም ያልሆነ ከ2 ባህርይ አንድ ባሕሪይ፤ ከ2 አካል አንድ አካል ሆኖ ” አምላክ ወሰብእ” ተብሎ የተጠራበት የሥጋዌ ስሙ ነው። ሌሎቹም ስሞቹ ለምሳሌ ክርስቶስ፣አማኑኤል ፣መድኀኔዓለም ወዘተ የተባሉት ስሞቹ አካላዊ ቃል ሥጋን በተዋሀደ ጊዜ የተጠራባቸው ሲሆኑ ትርጓሜውም በዚሁ ዓለም ሳለ በአምላክነቱ እና እንደ ሰውነቱ የፈፀማቸውን ልዩ ልዩ ተአምራትና የቃሉ ትርጉም ያመላክታል ::
የእሱ ስሞች እንደ ሰብአዊ ፍጡር ስም ፤ ክፉው ሰው በመልካሙ ሰው ስም፣ ደጉ ሰው በክፉው ሰው ስም እንደሚጠራው ሳይሆን የእሱ ስሞች ባሕሪይውን እና ግብሩን የገለፀባቸው ስለሆኑ በመንፈሳዊ ጥበብ ካልሆነ በስተቀር በሥጋዊ እውቀት ለመመርመር አይቻልም። እየሱስ ክርስቶስ የባሕሪይ አምላክ ነው ሲባል፤ ለሁሉም ፍጥረት የራሱ የሆነ ደካማም ይሁን ጠንካራ ባሕሪይ የሌለው ፍጡር የለም፤ የእግዚአብሔር ባሕሪይ ግን ሥጋን እንደለበሰ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ባሕሪይ ወይም ሰብዓዊ ባሕሪይ ማለት ሳይሆን ፤ የማይጨበጠውንና የማይዳሰሰውን የእግዚአብሔርነት ባሕሪይ ማለታችን ነው።
እንዲህ ሲባል ግን ለልባሞች ካልሆነ በስተቀር ለሰነፎች ፈፅሞ ሊረዳቸውም ሆነ ሊገባቸው አይችልም። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ካልገለፀለት በስተቀር፣ የእግዚአብሔርን ባሕሪይ የፍጡር ሰብአዊ እውቀት ሊመረምረው ስለማይችል በሃይማኖት እና በምግባር ልባሞች ያልሆኑ ሰነፍ ሰዎች በስጋ ጥበብ ባሕሪየ ክርስቶስን ይመረምሩ ዘንድ ፈጽሞ አይቻላቸውም። (1ኛ ቆሮ 2፥ 7 -16)
በ325 ዓ.ም.አርዮስና ተከታዮቹ በምሳሌ 8 ፥22 ባለው ቃል ባልተረዱት እና ባላወቁት ምስጢር የክርስቶስን ባሕሪይ በስጋ ጥበብ ሊመረምሩ በመሞከራቸው ክርስቶስን ያህል አምላክ መንግስተ ሰማያትን ያህል ርስት አጥተዋል።
ዛሬም በዘመናችን ለብዙዎቹ ያልተረዳቸው ይኸው ክርስቶስ የባሕሪይ አምላክ ነው የሚለው ምስጢር ነው። ይህን ጥበብ ከማየት የተከለከሉ እጅግ ብዙዎችም ናቸው። “የእግዚአብሔር ኀይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የኾነው ክርስቶስ ነው።” (በ1ኛ ቆሮ 1፥24) ጥበብ በክርስቶስ ተጠቅሷል :: “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና ::” (ቆላ 2፥3)
ክርስቶስ ወልድ፤ አባቴ ወለደኝ ከአብ ወጥቼ ወደ አለም መጣሁ ይላል እንጂ በአንድም ቦታ ፈጠረኝ አላለም፡ (የሐ16፥ 28 ፣ መዝ 110፥3)
መውለድ እና መፍጠር የሰማይ እና የምድር ያህል የተለያዩ እና የተራራቁ ሁለት ነገሮች ናቸው። ማንም የሚወልደውን አይፈጥረውም፤ የሚፈጥረውንም አይወልደውም።
የአብ መውለድ የወልድ መወለድ በሥጋ ለባሽ ስርዓት/ ድርጊት ሕግ የሚተረጐም አይደለም።ሰዉ ህልውናውን የሚጀምረው በዘመን ነው፤ ለእሱ ግን ዘመን አይቆጠርለትም።
በአንድ ወቅት ልጅ ይባል የነበረው በሌላ ጊዜ አባት ይባላል ልጅ ያለ አባት አይኖርም። በአብ እና በወልድ ግን እንደዚህ አይነት የለም። የስም ለውጥም ሆነ የአካል ለውጥ የለም ፤ አብም አባት ሲባል ይኖራል ወልድም ሁልግዜ ፍጻሜ ማይኖረው ወልድ ሲባል ይኖራል።
ወደመጀመሪያ ርዕሰ ስንመለስ እየሱስ ክርስቶስ ፍፁም የባሕሪይ አምላክ እንጂ መናፍቃን እንደሚሉት በአብ የተዘጋጀ ትንሽ አምላክ አይደለም :: ከአንድ አምላክ ሌላ ትንሽ አምላክ እንዳለ የሚመሰክር መጽሐፍም ሆነ እውነተኛ አማኝ እስካሁን አልተገኘም።
ቅዱሳት መጻሕፍትም የክርስቶስን የባሕሪይ አምላክነት (እግዚአብሔርነት)በእርግጠኝነት ይመሰክራሉ።
ማስረጃ: –
1ኛ / “ህፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ከሰጥቶናልና አለቅነት በጫንቃው ላይ ነው:: ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ 9፥2)
2. “አንቺ ቤተ ልሔም ኤፍራታ… ከአንቺ የወጣው ከቀድም ጀምሮ የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል” (ሚካ5፤ 3)
3. “ከዚች ዓለም ገዥዎች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀውም፤ አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር” (የ1ቆሮ 2፥8 )
4. “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።(ቆላ2፥9:10)
5 “ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው” (ሮሜ9፥5)
6. “አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” (1ኛ ተሰ3፥ 11) .
7. “የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የእየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በፅድቅ እግዚአብሔርን በመምሰል በአሁኑ ዘመን አንኑር” .( ቲቶ2፥ 13:14)
8- “እርሱ የዘለዓለም አምላክ እና የዘለዓለማዊ ሕይወት ነው።”( 1 ዮሐ5፥20)
9. ” በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና.” (2ኛ ዮሐ 1፥9-11)
10. “ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው
ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።” (ይሁዳ 24፥ 25)
11. “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።” (ዮሐ2፥19)
12. “ህይወቴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣትም ዘንድ አስነሳትምዘንድ ስልጣን አለኝ” (ዮሐ10፥18)
13. ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ።(ዮሐ12፥8)
14.ሰንበትን የፈጠረ እግዚአብሔር ሲሆን ፈሪሳውያን ስለ ሰንበት መሻር ሲጠይቁት እሱ የሰንበት ጌታ መሆኑን ገለፀላቸው” (ማቴ12፣ 8)
15 “ቶማስም ጌታዬ አምላኬ ባለው ጊዜ አምላክ አትበለኝ አላለውም ….. አለው እንጂ (የሐ20፥2፣8፥28)
16. በሥጋ የተገለጠው ክርስቶስ ዋጋ ከፋይ እንደሆነ እና ፊተኛውና መጨረሻው እሱ እንደሆነ በራዕ 22፥ 12፣ 1፥8 እና 11 እንደተናገረችው በብሉይም ኢሳ 41፥4፣ 44፥6፣ 48፥12
17 ” አባቴ ሁል ጊዜ ይሰራል እኔም ደግሞ እሰራለሁ” (ዮሐ5፥17)
18. በተጨማሪም:-
– “ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።” (መዝ2፥12)
– “ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?”ምሳሌ30፥4
– “እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና::” (መክ12፥14)
– “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።” (ማቴ11፥27)
– “በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና።”(ማቴ3፥3)
– “አምላክ ሆይ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሰራል የመንግስትህም በትር የቅንነት በትር ነው”(ዕብ 1፥68)
ስለ እየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት መፅሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይመስክራል።
1ኛ/ እየሱስ ክርስቶስ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው
ማስረጃ: –
– “እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።” (ማቴ 3፥1)
-“በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት።” (ማቴ 14፥33)
– “ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።” (ማቴ 16፥16)፣
– “ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።” (ማር 9፥7)
– “እግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።” (ማር1፥1)
– “በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ።በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ።” (ማር 15፥39)
– “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም። እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው።” (ማር 15፥39)
– “ማርታም አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው። ” (ዮሐ 11 ፥27 )
– “እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።” (የሐዋ 9 ፥ 20)
– “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” (ገላትያ 2 ፥ 20)
– “በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።” (ኤፌ 2 ፥ 12)
– “ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ምንም ብትጸኑ፥ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም።” (2ኛ ጴጥ 1 ፥12 )
– (ዕብ 1-15)
2ኛ/ እየሱስ ክርስቶስ በእውነት የሰው ልጅ ነው
ማስረጃ: –
– “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ 7 ፥ 14)
– “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ( 9 ፥6 )
– “እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው።” (ማቴ 1 ፥ 117)
– “ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ” (ማቴ 8፥20 )
– “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።” (ማቴ 16፥13 )
– “የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። ” (ማር 8 ፥ 31)
– “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።” (ማር 13 ፥26 )
– “በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። ” (ማር 15 ፥39 )
– “ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር ” (ሉቃ 3፥ 23)
– “እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤ ” (ሉቃ 12፥ 8)
– “የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። ” (ዮሐ 5 ፥ 27)
– “ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። ” (ዮሐ 8 ፥ 40)
– “ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።” (ሮሜ 9፥5 )
– “እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” (1ኛ ጢሞ 2 ፥ 5)
– “እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።” (1ኛ ወደ ጢሞ 3 ፥ 16)
– “የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥” (1ኛ ዮሐ 4፥ 2)
3ኛ/ እየሱስ ክርስቶስ በእውነት እርሱ ክርስቶስነው
ማስረጃ: –
– “ዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።” (ማቴ 1፥1 )
– “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” (ማቴ 16፥1 8)
– “የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው እነርሱም።.. አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።” (ማቴ 2፥4-6 )
– “ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። … ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። … ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ። አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።” (ማቴ 16፥16፡20፡22 )
– “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ (ማቴ 13.41)
– “እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ …. ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ።” (ማቴ 27፥17፡22)
– “እግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።… በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።” (ማር 1፥ 1፡34)
– “ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።” (ማር 8 ፥ 30)
– “የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ።” (ማር 9 ፥ 41)
– “ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።” (ማር14 ፥ 62)
– “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” (ሉቃ 2፥11 )
– “አጋንንትም ደግሞ። አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ” (ሉቃ 4፥41 )
 ” ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ብነግራችሁ አታምኑም፤” (ሉቃ 22፥67)
 “ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም። እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር። ” (ሉቃ 23፥2)
– “ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። ” (ሉቃ 24፥5)
– “ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። ” (ዮሐ 1 ፥17፡20 )
– “ሳምራዊቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው።” (ዮሐ 4 ፥25 )
– “ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” (ዮሐ 6 ፥68 )
– “እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? ” (ዮሐ 7 ፥25 )
4ኛ/እየሱስ ክርስቶስ በእውነት እውነተኛ አምላክ ነው
ማስረጃ: –
– “መጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ” (ዮሐ 1 ፥1 )
– “እኔና አብ አንድ ነን።አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ።ኢየሱስ። ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ። እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ።” (ዮሐ 10 ፥30-39 )
– “ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።” (ዮሐ 20 ፥28 )
– “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ “ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (የሐዋ 20 ፥28 )
– “አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን። ” ( ሮሜ 9 ፥5 )
– “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥” (ፊልጵ 2 ፥ 6)
– “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” (ቲቶ 2 ፥ 13)
– “ስለ ልጁ ግን። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።” (ዕብ 1፥ 8)
– “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። ” (1ኛ ዮሐ 5 ፥ 20)
– “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” (ዮሐ 3 ፥ 13)
5. እየሱስ ክርስቶስ በእውነት የጌቶች ሁሉ ጌታ ነው .
ማስረጃ: –
– “ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ። ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም። እንኪያስ ዳዊት። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው” (ማቴ 22፥42-45)
– “እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ።ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ።ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት” (ማቴ 20፥30-33 )
– “ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው።” (ማር 11 ፥ 3)
– “ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።” (ማር 16 ፥ 19-20)
– “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። (ሉቃ 2፥11 )
– “ሐዋርያትም ጌታን። እምነት ጨምርልን አሉት። ” (ሉቃ 17፥5)
– “አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።” (ሉቃ 22፥30)
– ” እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት።….እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው። ” (ዮሐ 11 ፥12፡27 )
– “ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው።…እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ።” (ዮሐ 13 ፥6፡13 )
– “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” (የሐዋ 2፥34-36 )
– “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ” (ሮሜ 10 ፥9 )
– “ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር። ኢየሱስ የተረገመ ነው የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር። ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። ” (1ኛ ቆሮ12 ፥3 )
– ” ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን።” (2ኛ ቆሮ4 ፥5 )
ስለዚህ የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የዚህ የዮሐንስ ድረ ገጽ ተከታታይ አባባቶቻችን ሁላችሁም ፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በራሱ አላማ ያሰለፋቸው የክህደት እና የምንፍቅና ሰዎች በፈጠጠው አይናቸው ያዩትን፣ በጆሮዋቸው የሰሙትን፣ በእጃቸው የዳሰሱትን እውነተኛውንና የተረጋገጠውን ትምህርተ መለኮት ማወቅ እና መረዳት ሲገባቸዉ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ዓለማዊ እውቀት እና የልብ ወለድ ትምህርት በመቁጠር እንደራሳቸው ሃሳብ እና በራሳቸው አገላለፅ የእግዚአብሔርን ቃል እየመነዘሩ ትርጉምን እያጣመሙ የባሕሪይ አምላክ የሆነውን ክርስቶስን እንደ ፍጡር በመቁጠር ወይም እንደ አማላጅነት በማድረግ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳንን እና እናቱን ወላዲት አምላክን ማማለድ እንደማይችሉ በድፍረት ቃል እየተናገሩ በሚዘሩት እንክርዳድ ትምህርታቸው ሳትሰናከሉና ሳትወናበዱ የመንፈስ ብዥታም ሳይፈጥርባችሁ እናታችን ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምስጢር ባለቤት፣ ትርጓሜ ባለቤት፣ የብዙ ሊቃውንት ባለቤት ስለሆነች ገንዘብና ቁሳዊ ካልሆነ በስተቀር ሃይማኖት እንዳትበደሉ ወይም በክህደት ትምህርት እንዳትወሰዱ ይህንን የክርስቶስ የባሕሪይ አምላክነት ትምህርት በአጭሩም ቢሆን ለብዙዎቻችሁ አንድት ጠቀሙበት የቀረበላችሁ ስለሆነ ጥቅሶችንና ማብራሪያዎችን በደንብ አንብባችሁ ትረዱ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላችኋለን።
እግዚአብሔር ምስጢርና ጥበቡን ይግለጽልን።
ወስብሀት ለእግዚአብሔር

“ከጴንጤዎች ጋር ንግግር አድርጌ ነበር ……” በማለት ጥያቄ ላቀረቡልን አባላችን የሚሰጠው መልስ ለቴሌግራም አባላቶቻችን ሁሉ ጥቅም ስለሚሰጥ መልሱን አንብባችሁ ትረዱት ዘንድ ከሁሉ በማስቀደም በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።

መልስ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ ሀገር ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር” (1 ቆሮ 2፥8) በማለት አይሁድ በመካከላቸው ሙት ሲያስነሳ፣ አይን ሲያበራ፣ ጎባጣ ሲያቃና፣ በሁለት አሳ እና በአምስት የገብስ እንጀራ በበረከቱ አብዝቶ ሲያጠግባቸው፣ አጋንንት ሲያወጣ፣ ባህር ላይ ሲራመድ፣ በመስቀል ላይ ሆኖ አባት ሆይ ይቅር በላቸው ብሎ ለጠላቶቹ ሳይቀር ታላቅ ፍቅሩን ሲገልጽ፣ በቃሉ ብቻ ሙታን ሲያስነሳ፣ አለቶችና መቃብሮች ሲታዘዙ፣ ሞትንና መቃብርን ረግጦ በ3 ቀን ሲነሳ በአጠቃላይ ከአምላክ በስተቀር ፍጡር የማይሰራውን ስራ ሲሰራ በፈጠጠው አይናቸው እየተመለከቱ እና ስለድንቅ ስራውም እየተገረሙበት አምላክ ነው ብለው እውነቱን ለመቀበል ስለተከለከሉ እና አይነልቦናቸው ስለታወረባቸው የክህደት አባታቸው ሰይጣን በዛው በክህደት አላማቸው እንዲፀኑ ስላደረጋቸው ለንስሓ ሳይበቁ እስከ መጨረሻ ድረስ ጠፍተው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል። ጠያቂያችን ከሁሉ በፊት መረዳት ያለብዎት የክህደት እና የምንፍቅና ሰዎች የመጀመሪያ ዋና አላማቸው የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም የሰውን አይምሮ በጥርጣሬ ማዕበል መበጥበጥ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኙትን ጥሬ ቃል በመለቃቀም ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን የነገረ መለኮት ቃል አንድም ቀን በጉባኤ ቤት ውለው ሳይማሩ ከእውቀት ነፃ በሆነ አነጋገር በትምህርተ ሃይማኖት ያልበሰለውን ክርስቲያን ግራ ሲያጋቡም መታየት የተለመደ ተልኳቸው ነው። በመሰረቱ እየሱስን አማላጅ አድርገው የሚናገሩበት ለስህተት ትምህርታቸው መነሻ የሚያደርጓቸው የመፅሐፍ ቅዱስ ቃላት (ሮሜ 8፥27) ላይ እና ቁጥር 34 ላይ ያለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ነው። ይሁን እንጂ እየሱስ ክርስቶስ ከባሕሪይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ እና ከባሕሪይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትና በሶሥትነቱ የሚቀደሰውን የሚሰለሰውን አምላክ፤ በደነዘዘ አይምሮ ድንቁርና በተሞላበት ድፍረት ፈራጁን አምላክ አማላጅ ነው (ይማልደን)፣ የለመኑትን ሁሉ የሚሰጠውን አምላክ ይለምናል ብሎ ማመን አምላክነቱን ካልተቀበሉት ከአይሁድ ጋር በእምነት አንድ መሆን ነው። ጥቅሱን በሚመለከት ግን የባሕሪ አምላክ እየሱስ ክርስቶስን ይማልዳል፣ ይለምናል፣ ያስታርቃል፣ ይፀልያል የሚሉትና የመሳሰሉት ቃላት በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲያጋጥሙን ማስተዋል ያለብን፦

1ኛ/ በመፅሐፍ ቅዱስ በተለያየ ዘመናት የቃላት ትርጉም ማሻሻያ በተደረገበት አጋጣሚ ሁሉ የቃላት መዛባት አጋጥሟል። በተለይ እየሱስ ክርስቶስን በሚመለከት በአዲስ ኪዳን ተፅፎ ስንመለከት ከአምላክነት ክብሩ ለማሳነስ እንደ ፍጡር አማላጅ አድርጎ በመግለፅ በብዙ ቦታ ላይ ተመዝግቦ እናገኛለን። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅሬታዋን ለመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር እና ለሚመለከተው ሁሉ ስታቀርብ ቆይታለች።

ከብዙ ጥረት በኋላም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን በማሰባሰብ የመፅሐፍ ቅዱስ መሰረታዊ ቋንቋ ከሆነው ማለትም ከእብራይስጡ፣ ከአረብኛው፣ ከግእዙ፣ ከእንግሊዝኛው እና ከግሪክኛው ወዘተ ትርጉም ጋር በማነፃፀር ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን አዘጋጅታ በ 2000 ዓ.ም. በመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ እነዚህ በመናፍቃን ዘንድ ልዩ ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ቃላት ተስተካክለዋል። ለምሳሌ አማላጅ የሚለው ቃል ፈራጅ፣ ወይም ያማለዳል የሚለው ይፈርዳል በሚል ተተክቷል።

2ኛ/ የክርስቶስን ክብር በማሳነስ ምን ማትረፍ እንዳለባቸው አላማቸው ሁሉ በውል ግልፅ ያልሆነ የመናፍቃን ተልእኮ ሲታይ ሁሌ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን፣ ምእመናንን እና ካህናትን የሚያሳዝኑበትን እና ሃይማኖትን የሚሸረሽሩበትን መንገድ ስለሚፈልጉ ነው እንጂ፤ እየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በተዋሃደው ስጋ ከኅጢአት በስተቀር እንደሰውነቱ የሰውን ስራ እየሰራ እስከ መስቀል ሞት ድረስ መከራን የተቀበለ እንደ አምላክነቱ ደግሞ ፈጣሪነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ፈዋሽነቱን፣ መድኃኒትነቱን፣ ትንሳኤነቱን፣ አፅዳቂነቱን፣ ኮናኝነቱን፣ ይቅር ባይነቱን፣ መጋቢነቱን፣ ሰርቶ በክብር ወደሰማይ ማረጉን አይተናል።

3ኛ/ አስተዋይነትና እምነት የጎደላቸው ሰዎች ወደ ትክክለኛው አመለካከት ተመልሰው ማሰብ ያለባቸው በብሉይ ኪዳን እና በሀዲስ ኪዳን ውስጥ ስለሱ የባሕሪይ አምላክነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥቅሶች ይገኛሉ። ለምሳሌ፦

– ቅዱስ ዩሐንስ በራእዩ “አትፍራ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ህያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ዮሐ ራዕይ 1፥17)

– ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስም “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ” በማለት ከእመቤታችን የነሳውን ስጋ አምላክነትን ተዋህዶአልና ከሰማይ የወረድኩ ሲል አምላክነቱን እንደሚያመለክት አንድ አካል አንድ ባሕሪይ መሆኑን ለማረጋገጥ የተናገረው ቃል ነው። (ዮሐ 6፥51)

– ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ “ከመጀመሪያውም የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን…” ብሎ ያለው ማንን ነው? ቀዳማዊ መለኮትን አይደለን? ቃል ከስጋ ጋር በተዋህዶ አንድ ባሕሪይ ካልሆነ በስተቀር ቅድመ አለም የነበረውን መለኮት እንዴት አየነው እንዴትስ ዳሰስነው አለ? የሚታይና የሚዳሰስ ግዙፍ የሆነ ነው እንጂ ረቂቅ የሆነ እንዴት ይታያል? እንዴትስ ይዳሰሳል? ቃል ከስጋ ጋር በተዋህዶ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ ካልሆነ በስተቀር (1ኛ ዮሐ 1፥1)

– “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስትያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ተብሎ በዚህ ኃይለቃል ላይ እየሱስ ክርስቶስ እራሱ እግዚአብሔር ተብሎ በግልጽ ተቀምጦ እናገኘዋለን (የሐዋ 20፥28)

– ነብዩ ዳዊት “እግዚአብዜር፦ አሁን እነሳለሁ ይላል መድኅኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ” በማለት ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ ከተነሳው ስለእየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ነው። መዝ 11፥8

– የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ዳዊት “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔርም በመለከት ድምፅ አረገ ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ” በማለት ያረገው እየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ እየሱስ ክርስቶስን ግን አምላክና እግዚአብሔር መባል የባሕርይ ስልጣኑ እንደሆነ በዚህ ቃል አረጋግጦልናል። (መዝ 46፥ 5 እና 6)

– አሁንም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔርም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ፈጥኖ ተነሳ፥ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኅያልም ሰው ተነሳ…” በማለት እየሱስ ክርስቶስ ከ3 ቀን በኋላ ከመቃብር የመነሳቱን በገለፀባት ሃይለቃል እግዚአብሔር ተነሳ ብሎ በትንቢት ተናግሮዋል (መዝ 67)

– ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም “ከሰማይ ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት ከሰማይ የወረደው የባህሪይ አምላክ እና ከድንግል ማርያም ተወልዶ የተዋሀደው ስጋ ደግሞ ፈራጅና አዳኝ መሆኑን ነግሮናል (ዮሐ 3፥13)

እንግዲህ ጠያቂያችን እነዚህን ሁሉ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለመረጃ ያህል እንዲጠቀሙባቸው አቀረብንልዎት እንጂ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ እየሱስ ክርስቶስ የሚነገሩ ጥቅሶች አምላክ እንደሆነ የሚያመለክቱ እንጂ ፍጡር እንደሆነ ወይ አማላጅ እንደሆነ የሚያመለክት በአንድም ቦታ አይገኝም። እንደ አስታራቂና እንደ አማላጅ አስመስለው በአንዳንድ ቦታ የተገለጹትም እንኳ በለበሰው ስጋ የፆመውን የፀለየውን በመስቀል ላይ ሆኖ ስለኛ የተገረፈውን አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለውን በአጠቃላይ በለበሰው ስጋ እንደሰውነቱ የፈፀመውን አገልግሎት እንጂ ከባሕሪይ አምላክነቱ የሚያሳንሰው አንዳችም ነገር አለመኖሩን በጥበብና በማስተዋል መረዳት ያስፈልግዎታል። አይምሮ መረበሽ መንፈስን መበጥበጥ የጥርጣሬ ማዕበል ውስጥ ማስገባት የሰይጣን እና የመናፍቃን ፀባይ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ደግሞ ባለበት ፀንቶ ይቆማል እንጂ የሚታወክና የሚበጠበጥ መንፈስ የለውም። በእርግጥም የእኛ አማላጅ ድንግል ማርያም ናት፣ የእኛ አማላጅ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን ፃድቃን፣ ቅዱሳን መላእክት ናቸው። እሱ ግን እየሱስ ክርስቶስ ወደ እሱ የሚቀርበውን ልመና እና ምልጃ ተቀብሎ እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥ አምላክ እንደሆነ ጠያቂያችች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችሁም ትረዱት ዘንድ ይሄን ማብራሪያ ሰጠን።

በተጨማሪም ጠየቂያችን የቅዱሳንን እና የመላዕክትን ምልጃን በሚመለከት የሚከተለውን ምላሽ ይመልከቱ፦

በኅጢአተኛ እና በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ የሚፀልዩ የሚያማልዱን እግዚአብሔር አስቀድሞ ያከበራቸው የመረጣቸው ያፀደቃቸው ለዘለአለም አገልጋዮች ያደረጋቸው በቃል ኪዳን ያፀናቸው ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላዕክት ናቸው።

ስለአማላጅነት እና ስለቅዱሳን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ወደፊት ሰፋ አድርገን እምንማማርበት እራሱን የቻለ ግዜ ቢኖርም እንኳን ከተጠየቀው ፍሬ ሃሳብ ጋር ለማዛመድ ያህል አንዳንድ ስለ ቅዱሳን ሰዎች እና ቅዱሳን መላእክት ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቂት ማስረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

1/ ቅዱሳን ሰዎች አማላጅነት
– የቅዱሳን አማላጅነት በሚመለከት “…አባታችን አብርሃም በሚስቱ በሳራ ላይ ነውር ስራ ሊሰራ በነበረው የጌራራ ንጉስ አቤሜሌክ ከእግዚአብሄር በመጣበት ቁጣ በደዌ በተመታ ጊዜ በማላውቀው ኅጢአት ተመትቻለሁና ብሎ ወደ ፈጣሪው ሲጮህ እግዚአብሔርም ከዚህ ደዌህ ትድን ዘንድ አብርሃም ይፀልይልህ ብሎታል” ኦሪ ዘፍ 20፥1-18

– ጻድቁ እዮብ ልዩ ልዩ ፈተና ደርሶበት በከፍተኛ ደዌ እየተሰቃየ ባለበት ግዜ እግዚአብሔር ኤለፋዝን በልዳዶስ እና ሶፋር የተባሉ ወዳጆቹ ሊጠይቁት መጥተው በማይሆን አነጋገር አሳዝነውት ስለነበረ እግዚአብሔር ተቆጣቸው። በደረሰባቸው ቁጣም በዛኑ ግዜ “…እዮብ ወዳጄ ስለ እናንተ ይፀልያል እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና” አላቸው። እዮብም ስለወዳጆቹ በፀለየ ግዜ የእዮብ ፀሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ምህረት እንዲያገኙ አድርጓል። እዮ42፥7-11

– ዳታንና አቤሮንም እንዲሁም ደቂቀ ቆሬ የተባሉ እብራውያን የእስራኤልን ማህበር አስተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ በምቀኝነት አመፅ ባስነሱባቸው ግዜ እግዚአብሔር በዚህ ኅጢአታቸውው ተቆጥቶ በቅፅበት ያጠፋቸው ዘንድ ሙሴን እና አሮንን ከጉባኤያቸው ፈቀቅ በሉ ባላቸው ግዜ ሙሴና አሮንም በፊቱ በግንባራቸው ተደፍተው አቤቱ አምላክ ሆይ አንተ የሰው ነፍስ አምላክ አይደለህምን ለምን አንድ ሰው ኅጢአት ሰራ ብለህ በማህበሩ ላይ ለምን ትቆጣለህ ብለው ለመኑት ጥፋተኞቹ ዳታንና አቤሮንም እና ደቂዘ ቆሪ ተለይተው ይጠፉ ዘንድ ይገባል ህዝቡን ግን አድናቸው ብለው በፀለዩት ፀሎት ህዝቡን ከኅጢአተኞቹ ለይተው አድነውታል። (ዘህልቅ 16፥20-36 እና ከ41-50)

– የእስራኤል መሀበር ሁሉ ተሰብስበው በመሄድ ነብዩ ኤርምያስን “ስለኛ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ፀልይልን” ብለው በጠየቁት ግዜ እሺ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እፀልይላችኋለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚሰጣችሁን መልስ እነግራችኋለሁ ብሏቸው እስከ 10 ቀን ድረስ ከፀለየላቸው በኋላ የእግዚአብሔር ነገር ወደ ኤርምያስ መጣ ህዝቡንም ሰብስቦ ፀሎታችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቀርብ ዘንድ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በዚች ምድር ብትቀመጡ እሰራችኋለው አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለው አልነቅላችሁም እናንተ በሰራችሁበት ኅጢአት ከደነገጣችሁበት እኔም ባደረግሁባችሁ ጥፋት እፀፀታለው ብሎ እግዚአብሔር በኤርምያስ ፀሎት ኅጢአታቸውን ይቅር እንዳለው እና እንዳዳናቸው የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክራል። (ኤር 42፥2-13)

– መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያቶችን ያላቸውን የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የሚቀበሏቸው እና በረከታቸው እንዲደርሳቸው ለሚጠሯቸው ያሳደረባችውን ፀጋ ሲናገር “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል ነብይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብይን ዋጋ ይወስዳል ፃድቅንም በፃድቅ ስም የሚቀበል የፃድቁን ዋጋ ይወስዳል ማንም ከነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም”(ማቴ 10፥40-44)

– ቅዱስ ያእቆብን በመልእክቱ የቅዱሳን ፀሎት በስራዋ እጅግ ታላቅ ሃይል እንደምታደርግ ይገልፃል። ያዕ 5፥14-19

– ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ የሚያማልዱት በፀሎታቸው እና በህይወታቸው ብቻ ሳይሆን በጥላቸውና በልብሳቸው ሳይቀር ተአምራትን እንደሚያደርጉት ስለዚህም “ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋ እና በወስካ ያኖሯቸው ነበር…ድውያንን እና በእርኩሳን መናፍስት የተሰቃዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር ሁሉም ይፈወሱ ነበር” ተብሎ ተፅፏልና

– እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳን ላይ የማማለድን እና የማስታረቅን ቃል ኪዳን እንዳስቀመጠ “የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው…በኛም ያማስታረቅ ቃል አሮረ እንግዲህ እግዚአብሔር በኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን” በማለት እንዴት እንደሚያማልዱ ሐዋርያው በስፋት ገልፀዋል (2ኛ ቆሮ 5፥18-21)

2/ የመላዕክት አማላጅነት
– ስለመላእክት አማላጅነት በሚመለከት መላኩ ቅዱስ ገብርኤል የእግዚአብሔር አገልጋይ የነበረው ካህኑ ዘካርያስን “ፀሎትህ ተሰምቶልሃል አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች ፤ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ” ባለው ግዜ ዘካርያስም “እኔ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም በእድሜዋ አጅታለች ይህን በምን አውቃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን ቃል ስለተጠራጠረ መልአኩም “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ እንድናገርህም ይችን የምስራችም እንድሰብክልህም ተልኬ ነበር አሁንም በግዜው የሚፈፀመውን ቃሌን ስላላመንክ ይህ ነገር እስከሚሆንልህ ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገር አትችልም አለው” ከዚህ በኋላ ዘካርያስ የመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ቃል እስከሚፈፀም ድረስ ዲዳ ሆኖ ቆይቷል። በመጨረሻ ግን መላኩ እንደተናገረው ኤልሳቤጥም ዮሐንስን ከወለደች በኋላ የተወለደው ህፃን ስም በእስራኤል ዘንድ ባለው ልማድ የልጅን ስም የሚሰይመው አባት ስለነበረ ዲዳ የሆነው አባቱ ዘካርያስን በጥቅሻ ሲጠይቁት ብራና ላይ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ፃፈ ያኔም አፉ ተከፈተ ምላሱም ተፈታ (ለሉቃ1፥13-20)

– ነብዩ ዳንኤል በባቢሎን አገር በምርኮ እያለ በመከራው ሰአት መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እንዴት እንደረዳው ሲናገር እነሆም ከዋናዎቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሲረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገስታት ጋር በዛ ተውሁት በማለት ተናግሯል” ዳን10፥13)

– እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ሳሉ የእግዚአብሔር መላእክ በምድረበዳ እንዴት እንደመራቸውና እንደጠበቃቸው ነብዩ ሙሴ ሲናገር “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀውትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እልካለው። ስሜም በእርሱ ላይ ስለሆነ ኅጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት…መላኬ በፊትህ ይሄዳልና በማለት ስለመላእክት ጠባቂነት እና አማላጅነት ተናግሯል (ዘፀ 23፥20-23)

– አሁንም ነብዩ ሙሴ እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤልን ድምፃቸውንና ለቅሷቸውን ተቀብሎ ሰምቶ ከግብፅ ባርነት ባወጣቸው ግዜ በመላእክት ጥበቃ እንደሚመሩ ሲናገር “ወደ እግዚአብሔር በጮህን ግዜ ድምፃችንን ሰማ መላኩንም ሰዶ ከግብፅ አወጣን” በማለት የመላዕክትን ተራዳይነት እና አማላጅነት አረጋግጧል (ዘሁ 20፥16)

– ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለውና” በማለት መላእክት ዘወትር የሰው ልጅን ለመጠበቅ የቆሙ እረኞች እንደሆኑ ማንም በእግዚአብሔር ሰው ላይ እጁን ቢያነሳ በፈጣሪ ዘንድ ዘወትር ስለሱ የሚቆሙ ጠባቂ ምስክሮች እንዳሉት አረጋግጧል።

ጠያቂያችን እና ባጠቃላይ የዮሐንስ ንስሓ ቴሌግራም አባሎቻችን በአጭር ጥያቄ ተነስተን ሰፋ ወዳለ የመልስ አሰጣጥ ትንታኔ ውስጥ የገባነው ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጠው የሃይማኖት ጉዳይ በመሆኑ ለሁላችሁም ግንዛቤ ይሆናችሁ ዘንድ እና ዘወትር በጥፋት እና በመሰናክል ከሚቆሙባችሁ መናፍቃን ዘንድ እንድትጠበቁ ስለሆነ ይህንን መልእክት ደጋግማችሁ በማንበብ መሰረታዊ እውቀት ታገኙበት ዘንድ አደራ እንላለን።
በተጨማሪም በድረገፃችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት በስፋት እየሰጠን ስለሆነ ይህን ሊንክ በመጫን አንብበው እንዲረዱ እንመክራለን።

እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያንን እና ምዕመናንን ከጠላት ዲያብሎስ ንጥቂያ ይጠብቅልን

መልስ፦ መልካም ስራቸውና ተጋድሏቸው በገድለ ቅዱሳን የተፃፈላቸው ቅዱሳን በእውነተኛ እምነታቸው እስከሞት ድረስ ለፈጣሪያቸው ታማኝ በመሆናቸው የድካማቸውን ዋጋ እና የትሩፋት ተጋድሎዋቸውን በከንቱ የማያስቀረው አምላክ በየዘመኑ በነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደየ ፀጋቸው መጠን ቃል ኪዳን እንደገባላቸው በቅዱስ መፅሐፍ ውስጥ እና በሌሎችም የቤተክርስቲያን መፃህፍት በብዙ ቦታ ተመዝግቦ ይገኛል። ለነዚህ ቅዱሳን ከፈጣሪያቸው ዘንድ ስለተቀበሉት ቃል ኪዳን የተፃፈላቸው የገድላቸውን ድርሳን የጻፉት የየዘመኑ ቅዱሳን በአይናቸው ያዩትን እና የእግዚአብሔር መንፈስ የነገራቸውን እውነተኛ ምስክርነት በማረጋገጥ ነው። ጠያቂያችን እንዳሉት በሃይማኖት ሆነን የምንቀበለውን ነገር ወደ ስጋዊ እውቀት አምጥተን ካላየነው፣ ካልዳሰስነው፣ በዘመኑ ተገኝተን ካላረጋገጥነው አንቀበለውም የሚል የጥርጣሬ መንፈስ ካደረብን፤ እንኳንስ የቅዱሳንን ገድል ቀርቶ እግዚአብሔርንም አለ ብሎ ለመቀበል እንቸገራለን። ስለዚህ የብሉይ ኪዳን እና የአዲስ ኪዳን መፅሓፍ ቅዱስንም ስማቸው የተመዘገበላቸው ቅዱሳን አበው እንደፃፉት በተነገረን መጠን ካላመንን ወይም የእግሔአብሔር ቃል በሚነግረን መጠን ማመን ካልቻልን ሁሉም ነገር ስጋዊ አመለካከት ሊሆን ስለሚችል ማስተዋል እና ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት የሚያስችለንን መንፈሳዊ ምርምር ለማድረግ የራሳችንን ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ስለሆነም ጠያቂያችን በልብወለድ ወይም በገምድልነት ከመሬት ተነስተው በራሳቸው ሃሳብ የእግዚአብሔርን ቃል በመመንዘር ከሚናገሩ የምንፍቅና የክህደት ሰዎች መጠንቀቅ ያስፈልጋል በማለት ምክራችንን እንሰጣለን።
የእግዚአብሔር ፀጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን
መልስ፦ ከሰማይ ከወረደ በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ከነብዩ ኤልያስ እና ከነብዩ ሄኖክ እርገት ጋር ያለውን ልዩነት ወይም ተያዥነት እንዲገለፅልዎ ጥያቄ ያቀረቡ አባላችንን በሚመለከት የተሰጠ መልስ፦
 
በዮሐንስ ወንጌል መዕራፍ 3፥13 ላይ “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” በማለት የተገለፀው መለኮታዊ ቃል ምስጢራዊ አገላለፁን ለማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ከሰማይ የወረደው ከሦስቱ ባሕሪያት አንዱ የሆነው ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም መወለዱን የሚያሳይ ሲሆን፤ ሞትን እና መቃብርን አሸንፎ በተነሳ በ40 ቀን ወደ ሰማይ ሲያርግ የታየው ከድንግል ማርያም የተዋሀደው ስጋ ፍጹም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነው አምላክ ነው። የሱ እርገት በመለኮታዊው ባሕሪው ነው። ምድራዊ እና ሃላፊ የነበረው ስጋ ከሰማይ የወረደውን ባሕሪየ መለኮት ተዋህዶ አምላክ መባልን የባሕሪይ ገንዘቡ አድርጎ ወደ ሰማይ ማረጉን በቅዱሳን መፃህፍትና በቅዱሳን ሐዋርያት ምስክርነት አረጋግጠናል። (የሐዋ 1፥9-11) ስለዚህ የአምላክ እርገት ከፍጡር እርገት ጋር የሚወዳደር ስላልሆነ በተለየ መረዳት ማየት ያስፈልጋል።
 
ነብዩ ሄኖክ እና ነብዩ ኤልያስ ባላቸው ልዩ ፀጋ በዘመናቸው የነበረውን የሰይጣን ውግያ ተቋቁመው እና በአለም ዘንድ ያለውን መንፈሳዊ ተጋድሎ በድል አጠናቀው ለታላቅ ሰማያዊ ክብር የሚያበቃቸውን የፅድቅ ስራ ሰርተው ስለተገኙ ከዚህ ከሚኖሩበት ከኅጢያተኛው አለም ተለይተው እግዚአብሔር ወደአዘጋጀላቸው ልዩ ስፍራ ማለትም ከፅድቅ ስራ በስተቀር ኅጢአት የማይሰራበት ወደ ህይወት ቦታ በልዩ መለኮታዊ ጥበብ ተጠርተው መሄዳቸውን በቅዱስ መፅሐፍ ተፅፎ እናገኘዋለን። በመሆኑም የነብዩ ሄኖክ እና የነብዩ ኤልያስ እርገት በሞት እና በትንሳኤ የተገለጠው ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ ለነሱ ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ገና ሳይሞቱ በህይወተ ስጋ በራሱ ጥበብ ከዚህ አለም ለይቶ እሱ ወደአዘጋጀላቸው ልዩ ስፍራ የወሰዳቸው መሆኑን እንመለከታለን። በኋለኛው ዘመን ግን እግዚአብሔር አምላክ ይሄን አለም ለማሳለፍ የሰጠው የጊዜ ቀጠሮ በደረሰ ግዜ ከሁሉ አስቀድመው ሄኖክ እና ኤልያስ ስለ እውነተኛው ሃይማኖት በሰማዕትነት ለመጋደል እንደሚመጡ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እነሱ ምስክርነት ሰጥቷል። ስለዚህ ጠያቂያችን የጌታን እና የሁለቱን ነብያት እርገት ልዩነት በዚህ አግባብ እንዲረዱት እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም የፈጣሪን እና የፍጡርን ስራ አንድ አድርጎ መመልከት የእውነተኛ ክርስቲያን እምነት ስላልሆነ በማስተዋል ይረዱት ዘንድ ይህን ምክር ልከንልዎታል።

ጸሎት ማለት፡-ጸለየ፣ለመነ፣ ጠየቀ አማለደ፣ ማለደ ካለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ጸሎት ማለት መለመን፤ መማለድ፤ ማመጸን፤ መጠየቅ፤ መናዘዝ፤ መታረቅ፤ ልሎችን ይቅር ማለት፤ ስለተደረገልንና ስለተሰጠን ልዩ ጸጋ ማመስገን ማለት ነው፡፡ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር፤ ምህረትንና ይቅርታን መጠየቅ፡፡ መሻት መለመን ማለት ነው፡፡ “ሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁ ምቱ ይከፈትላችኋል” ማቴ 7-7፡፡ ኃጢአትን ተረድቶ ይቅርታን መጠየቅ ማለት ነው፡፡ መዝ. 32- 5 ኃጢአቴን ላንተ አስታወቀሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፣ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ ፣ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውክልኝ፡፡ መዝ 66፡18

ጸሎት በሦስት ይከፈላል

1፡-ጸሎተ አኮቴት፡ ከሁሉም አስቀድሞ ስለተደረገልን ነገር በማመስገን የሚጀመር ጸሎት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-“ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን” ይልና ምክንኀያቱን ሲገልጥ ጠብቆናልና፥ አቅርቦናልና፥ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፥ እስከዚችም ሰዓት አድርሶናልና” ይላል፡፡ ይህ አይነቱ ጸሎጽ ጸሎተ አኰቴት ይባላል፡፡

2.፡-ጸሎተ ምህላ፡- ይህ ጸሎት ስለፈውሰ ሕሙማን፤ ስለ ሀገርና ስለነገሥታት፤ ስለ ጳጳሳት፣ ስለካህናት ዲያቆናት፣ ስምዕመናን ሕይወት፤ ስለቸነፈር፣ ሰለጦርነት፣ ስለረሀብ፣ ስለድርቅ ወይም አሁን እንደሆነብን አስጊ ነገር ሲሆን በማኅበር የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ ዘኁ.16-46-50፡፡ የምህላ ጸሎት ነገሠታት ከዙፋናቸው ወርደው ሙሽሮች ከጫጉላቸው፣ ከመጋረጃቸው ለምግብ የደረሱ ልጆች ከምግብ ለምግብ ያልደረሱ ከጡት ተከልክለው የሚጸልዩ ጸሎት ነው፡፡ ኢዩ.2-12-18፣ ዮና.3፥5

3.፡-ጸሎተ አስብቊዖት፡-ይህ ጸሎት አንድ ሰው ስለሚፈልገው ነገር ቦታ ለይቶ ሱባኤ ገብቶ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ይህ ጸሎት በተለይ ጣዕመ ጸጋን በቀመሱ በተባሕትዎ፣ በምናኔ በገዳም በሚኖሩ አበው ዘንድ የተለመደና የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ጠቅላላውን በቤተ ክርስቲያን የሚጸልዩ ጸሎታት ከላይ ከዘረዘርናቸው ሦስቱ የጸሎት ክፍሎች አይወጡም፡፡ ከጸሎተ አኰቴት ከጸሎተ ምህላ፣ ከጸሎተ አስተበቊዖት ይመደባሉ፡፡

እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት አሉ፡፡

ቅዱስ ዳዊት ስለ ጽድቅኽ ፍርድ በቀን ሰባት 7 ጊዜ አመሰግንኻለሁ ብሎ  በቀን ሰባት 7 ጊዜ እንዳመሰገነ እኛም በቀን ውስጥ ሰባት 7 ጊዜ እራሳችንን ለእግዚአብሔር በማስገዛት ለጸሎት እንተጋለን፡፡ መዝ.118-164

ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት

  1. ነግኅ ወይም ማለዳ ጧት፡- አባታችን አዳም የተፈጠረበት ሰዓት ነው ዘፋ.1-26፤ ሌሊቱን ጠብቆ የማለዳውን ብርሃን እንድናይ ስለረዳንም እናመሰግነዋለን፡፡ ፤ አምላካችን በጲላጦስ ፊት ቆሞ የተመረመረበት ሰዓት ነውና በዚህ ሰዓት ለጸሎት በፊቱ እንቆማለን፡፡ ማቴ.27-1
  2. ሠለስት ወይም ሦስት ሰዓት፡- እናታችን ሔዋን የተፈጠረችበት ሰዓት ነው፡፡ ዘፍ.2-21-24 ፤ ዳንኤል በዚህ ሰዓት መሰኮቶቹን ወደ ኢየሩሳሌም አንፃር በመክፈት ይጸልይ ነበር፡፡ ዳን 6-10 ፤እመቤታችን የቅዱስ ገብርኤልን ብስራት የሰማችበት እና አምላካችንን የጸነሰችበት ሰዓት ነው፡፡ሉቃ.1-26፤ጌታችን በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት ሰዓት ነው፡፡ማቴ.27-26፤በጽርሃ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ሰዓት ነውና በነዚህ ምክንያቶች በ3 ሰዓት እግዚአብሔርን በጸሎት እናመሰግነዋለን፡፡
  3. ቀትር ወይም ስድስት ሰዓት፡- አዳም እፀ በለስ በልቶ ከክብሩ የተዋረደበት ሰዓት ነውና ወደ ፈተና እንዳንገባ እንጸልያለን፡፡ ዘፍ.3-6፤አምላካችን ክርስቶስ ክብር ይግባውና በዕለት አርብ በመስቀል ላይ የተሰቀለው በ6 ሰዓት ነው፡፡ ዮሐ.19-14
  4. 4.ተሰዓት ወይም ዘጠኝ ሰዓት፡- በዚህ ሰዓት ቅዱሳን መላዕክት የሰውልጅ የጸለየውን፣ ጸሎት፣ ልመና፣ እጣን፣ የሠራውን ሥራ ሁሉ የሚያሳርጉበት ሰዓት ነው፡፡ የሐዋ.10-3፤ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡበት የነበረበት ሰዓት ነው፡፡ የሐዋ.3-1፤አምላካችን በዚህች ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከክብር ሥጋው የለየበት ሰዓት ነው፡፡
  5. ሠርክ ወይም ዐሥራ አንድ ሰዓት፡- እኛ ምግባር ቱሩፋት ሰርተን ዋጋችንን ከአምላካችን የምንቀበልበት ሰዓት ነው፡፡ ማቴ.20÷1-16፤ ዳዊት እንዳለ ‹‹ጸሎቴን በፊትህ እንደዕጣን ተቀበልልኝ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን›› መዝ.140-2 በማለት ይህች ሰዓት ታላቅ የጸሎት ሰዓት መሆኗን ያስተምረናል፡፡፤ኤልያስ በዚህች ሰዓት የሰዋው መሰዋት እና ያቀረበው ጸሎት በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ተወዶለታል፡፡ 1ኛ.ነገ 18-36፤መድኃኒታችን ክርስቶስ እኛን ከሞት እና ከሲኦል ያወጣ ዘንድ በሥጋው ወደ ከርሠ መቃብር በነፍሱ ደግሞ ወደ ሲኦል የወረደበት ሰዓት ነው፡፡ ማቴ.27-45-61
  6. ንዋም ወይም የመኝታ ሰዓት፡-በዚህ ሰዓት ቀኑን ሙሉ ስንወጣ ስንወርድ የጠበቀንን አምላክ አመሰግነን፤ ዳግመኛም የሌሊቱን ሰዓት ባርኮ የሰላም እንቅልፍ ይሰጠን ዘንድ ለጸሎት እንቆማለን፡፡፤ አምላካችን በጌቴሴማኒ ሥርዓተ-ጸሎትን ያስተማረበት ሰዓት ነው፡፡ ማቴ.26-36
  7. መንፈቀ ሌሊት ወይም እኩለ ሌሊት፡- አምላካችን የተወለደበት፣የተጠመቀበት፣ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣበት፤ ዳግመኛም ይህንን ዓለም ለማሳለፍ የሚመጣበት ሰዓት ነውና-ሉቃ.2-7-8፤3÷21.ዮሐ.20÷1፤ማቴ.25÷6፤ማር.13÷35 በዚህም ምክንያት አምላካችን ለእኛ የሆነውን እና ያደረገውን ሁሉ በማስተዋልና በማሰብ በየሰአቱ እንጸልያለን፡፡
መልስ፦   ጠያቂያችን ከእውነተኛ የክርስትና ሃይማኖት የመነጨ ሃሳብ ከሆነ ተገቢውን መልስ እንዲገነዘቡት ማድረግ የኛም ሃላፊነት ስለሆነ ጥያቄዎትን በፀጋ ተቀብለነዋል። ነገር ግን እንዲህ አይነት ወጣ ያሉ ጥያቄዎች የሚቀርቡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምሮን ከሚነቅፉ ወገኖች ስለሆነ ጥያቄውን ለመመለስ የብቃት ችግር ባይኖርም ከምንፍቀና የተነሳ ሃሳብ እንዳይሆን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ከዚህ ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሃሳቦች ከዚህ በፊት ቀርበውልን ተገቢውን መልስ እንደሰጠንበት እናስታውሳለን። የዚህ ጽንስ ሃሳብ የባሕሪይ አምላክ የሆነውን እየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ነው፣ አስታራቂ ነው፣ መካከለኛ ነው በሚል የማደናገሪያ ምክንያት የሚነሱ የመናፍቃን አስተሳሰብ ጋር ይገናኛል። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ስለዚህ ጥያቄ ስለሚሰጠው ምላሽና ትምህርት በሚመለከት 5500 ዘመን አባታችን አዳም እና እናታችን ሄዋን በሰሩት ኅጢአት ምክንያት በዘር የአዳም ልጅ የሆነ ሁሉ ኅጢአት እየተቆራኘው ሁሉም ወደ ጥፋት በሞት ጥላ ስር ወድቀው በስቃይና በመከራ በሚኖሩበት ግዜ ከአባቶቻችን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያቀርቡት መስዋዕትና ልመና ሁሉ የሰውን ልጅ ከሞት እና ከሲኦል ነፃ ለማውጣት ባለመቻሉ ቸርና መሀሪ ሰውን መውደድ የባህሪው የሆነ አምላክ በራሱ ፈቃድ ለአባታችን ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ማንም ሳያስገድደው ራሱ ወዶና ፈቅዶ ወደዚህ ወደ ኅጢአተኛው አለም መጥቶ ስጋን ተዋህዶ በለበሰው ስጋ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ዋጋ ከፍሎ ኅጢአተኛውን የሰው ልጅ ከራሱ ጋር አስታርቆ በመስቀሉ ሰላምን አድርጎ ስጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ በከፈለው ቤዛነት አለሙን ሁሉ ከዘላለም ሞት ነፃ ስላወጣ፤ ይህ ታላቅ ምስጢር ጠያቂያችን እንዳሉት እኛን ለማዳን ለአምላክነቱ ባህሪይ የማይስማማውን ስጋ ተዋህዶ ዘላለማዊ የሰው ልጅ የፈፀመውን ነገረ-ድኅነት የሚያመለክት ነው። ስለዚህ የሱ አስታራቂ መሆን፣ አማላጅ መሆን፣ መካከለኛ መሆን፣ ሊቀካህናት መሆን፣ መስዋእት ሆኖ መቅረቡ በተዋሀደው ስጋ ስለኛ ኅጢአት የከፈለውን የእዳ ካሳ የሚያመላክት እንጂ ከፈጣሪነት ማነሱን የሚያመላክት አይደለም። 
በመናፍቃን ዘንድ እንደሚባለው እየሱስ ክርስቶስ አንድ ግዜ ባቀረበው መስዋእት አንድ ግዜ በሰጠን አገልግሎት ነፃ ወጥተናል እና ከዚህ የሚበልጥ እና የሚሻል ሌላ የኅጢአት ስርየት ባለመኖሩ እንደፈለገን መሆን እንችላለን በሚል የስንፍና አነጋገር ብዙዎቹን ሲያሰናክሉ እንመለከታለን። በአብዛኛው በእብራውያን ላይ ከዚህ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን መልዕክቶች ስንመለከታቸው የቀድሞ የብሉይ ኪዳን መስዋእት እና ሊቀካህናትና የሊቀካህን መስዋዕት የሚያልፍና የሚሻር ለሚመጣውም ምሳሌ ወይም ጥላ ሲሆን፥ የአዲስ ኪዳን ሊቀካህናት እየሱስ ክርስቶስ እና ከሱ ያገኘነው ቅዱስ ስጋና ክቡር ደሙ የማያልፍ ዘላለማዊ ህይወትን የሚያስገኝ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋእት የማይደገም ቋሚ ስርዓት መሆኑን በማነፃፀር ለመለየት የተነገረ እንጂ ዛሬ ቅድስት ቤተክርስቲያን የምትሰጠውን የቅዳሴ እና የቁርባን አገልግሎት ለመቃወም የተነገረ መልእክት እንዳልሆነ ጠያቂያችን ሊረዱት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ ለትክክለኛ መረዳት የጠየቁ ከሆነ ለተጨማሪ ግንዛቤ በውስጥ መስመር ሊያናግሩን ይችላሉ።
ለሁሉም የእግዚአብሔር ሰላም ከእርስዎ ጋር ይሁን
ጠያቂያችን ስለተነገረ ትንቢት ምን እናድርግ የሚለው ጥያቄ መልካም ቢሆንም እንኳን ክርስቲያን ግን የተነገረ የትንቢት መፈፀሚያ ሳይሆን በሁሉም ነገር ጥንቁቅና ዝግጁ ሆኖ ጊዜና ዘመን የሚያመጣውን አንዳንድ ፈተና በሰማና ባየ ቁጥር ሳይበረግግና ሳይረበሽ እግዚአብሔር የወደደውና የፈቀደው ይፈፀማል ስለወዳጆቹና ስለልጆቹ ጥበቃና ከመከራ ይሰወሩ ዘንድ ስለኛ የማያንቀላፉ ትጉህ እረኛችን ነው ብሎ ማመን ያስፈልጋል። ትንቢት የሚለው ቃል ያለፈውንም፣ በዘመናችን ያለውንም፣ ወደፊት የሚመጣውንም እና የሚሆነውንም አጠቃሎ የሚገልፅ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ አስቀድሞ ያልተባለ ያልተነገረ እንደአጋጣሚ በግብታዊነት የሚፈጸም ነገር የለም። እግዚአብሔር አምላክ አለምን ከፈጠረ ጀምሮ እስከ አለም ፍፃሜ ድረስ ያለውን የስነ ፍጥረት ጉዞ ወይም በዚህ ዓለም ስለሚኖር ነገር አንድ ጊዜ አቅዶታል አንድ ጊዜ ወስኖታል። የሰው ልጅ ግን በተፈጥሮም ይሁን በኀጢአት ብዛት የእውቀት ሃሳቡ ውሱን ስለሆነ የእለቱን እና የጊዜውን እንኳን አስቦ መረዳት የተሳነው ፍጥረት ስለሆነ፤ እግዚአብሔር ስለሚሆነውና ስለሚመጣው ነገር ምስጢሩን የገለፀላቸው ቅዱሳን ሰዎች የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዲያመልጡና ከመጣባቸው መቅሰፍት እንዲሰወሩ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እንዲህ ይሆናል እንዲህ ይደረጋል በማለት ትንቢት ይናገራሉ።
 
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባላቶቻችን ዛሬ ከሰማነው ካየነው እና ከደረሰብን የእግዚአብሔር ቍጣ እናመልጥ ዘንድ አይነተኛው መፍትሄ በገዳም በዱር በበረሃ ያሉ የበቁ ሰዎች ትንቢት ተናግረዋል መቅሰፍት ይመጣል፡ ጦርነት ይሆናል፣ ዕልቂት ይበዛል እያልን ከምናሟርት ይልቅ እኛ እለተምጻታችን ወይም መቅሰፍታችን በማሰብ በመንፈሳዊ ሕይወት ራሳችንን መግዛት ሲያቅተን እና ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥተን የሰይጣን ተገዢ ስንሆን ብቻ ነው።
በመሰረቱ እግዚአብሄሔር ያመጣብን መአት የለም፤ ነገር ግን እኛው ራሳችን በኀጢአት ተስማምተን በራሳችን ያነደድነው እሳት እራሳችንን ከሚለበልበን በስተቀር ከአባቶቻችን ዘመን የተለየ አዲስ ነገር አልተፈጸመም። የዘመኑ ፍጻሜ የሚለው ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከጥንት ሐዋርያት ባሉበት ዘመን ጊዜው ዘመኑ አልቆል ከጎጢአታችሁ ተመልሳችሁ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ የሚለው ጥሪ ትላንትም ሲነገርና ሲስበክ የኖረ ነው እንጂ በራሳችን ጊዜ ባመጣነው ጥፋት ስናልቅ ማየት፣ ስንፋጅና ስንተራመስ፣ ስንባላ የመታየታችን ነገር ከእግዚአብሔር ቁጣ የተነሳ ብቻ ሳይሆን ከራሳችን የአመፅ ብዛት ስለሆነ ሁላችንም ልናስተውልና ልንረዳ ያስፈልጋል። አንዳንድ አሸባሪዎች የሚለቁትን አስጨናቂና አስፈሪ ሟርቶችን እየሰማንም በመጨነቅ እምነት አልባ ከመሆን ይልቅ በሃይማኖትና በምግባር ፀንተን በፆምና በፀሎት በርትተን ከመጣብን መአትና መቅሰፍት ለማምለጥ መጋደል ከጥንት ጀምሮ ክርስቲያናዊ አላማ ነው፤  በማለት ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።