ፋሲካና የፋሲካ ሳምንት
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ፋሲካና የፋሲካ ሳምንት
ፋሲካ ማለት ማለፍ ወይም መሻገር ማለት ሲሆን ይህ ስም ከየትና እንዴት መጣ? ለሚለው “ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ።” ዘፀ. 12 -1
ይህ በአል የሞት መልአክ ግብፃዊያንን ሊያጠፋ ሊመጣ ባለበት ጊዜ እግዚአብሔር በሙሴ ለእስራኤላዊያን ከበጎች ወይም ከፍየሎች ጠቦት እንዲያርዱ እና ደሙን በጉበናቸው ላይ እንዲቀቡ የሞት መላክ በመጣ ጊዜ ያንን ጉበናቸው ላይ የቀቡት የበጉን ደም ከሞት እንደሚያድናቸው ተናገራቸው፡፡ እስራኤላዊያንም የታዘዙትን አደረጉ፡፡ የሞት መልአክም መጣ ነገር ግን ጉበናቸው ላይ ከቀቡት የበግ ደም የተነሳ ሞት እነሱን እያለፈ ሄደ ግብፃዊያንንም አጠፋ፡፡ ይህ የበጉ ደም የክርስቶስ ደም ምሳሌ ነው፡፡ ዘጸ 12:14 ከዚህም አንጻር እስራኤል መልአከ ሞት በጉበናቸው ላይ የቀቡትን የበጉን ደም አይቶ በማለፉ እና የበጉ ደም ሞትን ያሸነፉበት እና የተሻገሩበት ምልክታቸው በመሆኑ ሞትን አለፍነው ተሸገርነው ሲሉ ፋሲካ ብለውታል ማለፍ መሳገር ማለት ነው፡፡
እኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ግን የአዲስ ኪዳኑ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖልናል፡፡ ዮሀንስ እንዲህ ሲል እንደመሰከረለት መሰከረለት “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህአለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” ዮሐ.1-29 በማለት እንደ ተናገረ
ከሞት ያመለጥንበትና የዳንበት የአዲስ ኪዳን በግ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለኛ ታርዶልናል ። የብሉይ ኪዳን በግ ደም ለዘለአለም አያድንም የሐዲስ ኪዳኑ በግ ደም ለዘለአለም ያድኖናል
የብሉ ኪዳን በግ ከሰፈር የሚመጣ ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ በግ ግን ከሰማየ ሰማያት የወረደ በቤተ በቅደስ ያደገችው የሁላችን መመኪያ የምትሆን ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደችወ ነው። የፋሲካው በግ ክርስቶስ እረኛችን ነው፡፡ እስቲ እንገረም ዮሀንስ በራእዩእንዲህ ይለዋል “በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ነው” ይለናል ራዕ 7-17፡፡ፋሲካችን ክርስቶስ የድንግል ልጅ ሞትን ስለገደለልን ቅዱስ ጳውለስ ቀድሞ አዳምንና ለጆቹን ሲያሰቃይ የነበረ ዲያብሎስነ እንዲህ እያለ ይጠይቀዋል “ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ ሲኦል ሆይድል መንሳትህ የታለ” 1ኛቆሮ 15 -55 ይለዋል፡፡
ብሉ ኪዳን በግ ታርዶ የሞተ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን በግ ታርዶ የተነሳ ነው፡፡ልዑለ ቃል ቅዱስ ኢሳይያስ ስለ ትህትናው በትንቢቱ እንዲህ ይላል፡፡ “ተጨነቀ ተሰቃየ አፉንም አለከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚልም በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” ኢሳ 53 -7 ይለናል፡፡ፋሲካችን ክርስቶሰ ፍቅሩ ልብን ይማርካል፡፡ትህትናው ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ አደነቀው እንደህም አለው እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው እንዲህ ያለ ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው ይላል፡፡እስቲ ፋሲካችን ክርስቶስን እንደ ዮሐንስ ፍቅሩንና ትህትናውን እናስብ እናድንቅም፡፡
የአዲስ ኪዳን በግ ለዘለአለም ደሙ ያነፃል ደሙ ይቀድሳል ደሙ ያፀድቃል የኢየሱስ ደም ለዲያቢሎስ ረመጥ ነው ደሙ ሰውን ያረጋል፡፡ የፋሲካችን ክርስቶስ ደሙ ጠላት ዲያብሎስን ድል መንሻችን ነው፡፡ ራዕ 12 -11
“እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና” 1ኛ ቆሮ 5 -7
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን የእርሾን ምሳሌ ያቀርባል በአይሁድ የፋሲካ በአል ቂጣ እንጂ እርሾ ያለበት ነገር አይበላም፡፡ ይህም ከግብፅ ባርነት ትተው በነፃነት እንዳሉ አዲስ ህይወታቸውን የሚያስረዳ ነው። አሁንም እኛም ክርስትያኖች የአለምን መጥፎ ስራዎች ማስወገድ አለብን። “ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም” 1ኛ ቆሮ 5 – 8
ክርስትያን በክርስቶስ ሞት ከኃጢያት ባርነት ነፃ የወጣ ስለሆነ እንደገና ወደ ኃጢያት ቦርነት መሸጥ የለበትም። ሮሜ 6:12-14
የትንሰኤ የመጀመሪያው ሰኞ ማዕዶት ይባላል፡፡
ማዕዶት ማለት ምን ማለት ነው?
ማእዶት ማለት ማለፍ መሻገር ማለት ነው፡፡ ይህ ዕለት በዕብራይስጥ (ፓሳሕ) ይባላል፡፡ ትርጉሙ ግን ያው ማለፍ ማለት ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ሊቃውንት መተርጉማንም ማእዶት፤ፋሲካ ፤ፓሳሕ የሚሉትን ቃላት ሦስቱንም በአንድ ተርጉመው ማለፍ መሻገር ማለት ነው ብለውታል፡፡
የቃሉ ትርጉም ይህን ከመሰለ ጥያቄው ከምን ማለፍ? የሚል ይሆናል፡፡
1ኛ. የእሥራኤል ልጆች በግብፅ ሀገር በፈርኦን ቤት ከ430 ዓመታት በላይ በባርነት ከኖሩ ቦሀላ እግዚአብሔር የህዝቡን ግፍና ጭኸት መከራቸውንም ሰማ፡፡ “በግብጽ ያሉትን የህዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ“፡፡ ሐዋ 7 -34 ተብሎ እንደተጻፈው እግዚአብሔር የህዝቡን ግፍና ጭኸት መከራቸውንም በሰማ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ቀንዱ ያልከረከረ፤ጥፍሩ ያልዘረዘረ፤ጸጉሩ ያላረረ ነውር የሌለበት የዓመት ጠቦት አርደው ደሙን የደጃፋቸውን መቃንና ጉበን እንዲቀቡት በሊቀ ለቢያት ሙሴ አማካኝነት አዘዛቸው፡፡ የእስራኤልም ልጆች እንደታዘዙት አደረጉ፡፡ መልአከ ሞትም በመጣ ጊዜ ደሙ የተረጨበትን ቤት የበኩር ልጃቸውን እያለፈ ስለሔደ ቀኑ ፋሲካ ተባለ፡፡ ፋሲካ ማለት ደግሞ መልአከ ሞት ከእስራኤል ልጆች በማለፉ ምክንያት ማእዶት፤ፋሲካ ፤ፓሳሕ ይባላል፡፡ ዘጸ 121-13
2ኛ. የእስራኤል ልጆች በግብፅ ሀገር በፈርኦን ቤት ከ430 ዓመታት በላይ በባርነት ከኖሩ ቦሀላ እግዚአብሔር የህዝቡን ግፍና ጭኸት መከራቸውንም ተመልክቶ ከግብጽ ሲወጡ ፈርኦንን ከነሰራዊቱ አስጥሞ የእስራኤልን ልጆች ግን የኤርትራን ባሕር በደረቅ አሻግሮ ከግብፅ ምድር ማርና ወተት ወደምታፈልቀው ወደ ከነዓን አውጦቶአቸዋል፡፡እስራኤልም ከባርነት መላቀቃቸውን ወደ ነጻነት መሻገራቸውን ያመለክታል፡፡ይህም የእስራኤል ፋሲካቸው ነው፡፡ ዘጸ13 – 18
3ኛ. በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፍሳት ከሲዖል ወደ ገነት ተሸጋግረዋል ፡፡ከሰይጣን ቁራኝነት ተላቀዋል፡፡ከባርነት ወደ ነፃነት ተሸጋግረዋል ፡፡ “እርሱ ጻድቅ ሆኖ ሳለ ስለአመጸኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና“ 1ጴጥ 3፡19፡፡ ለ5555 ዓመታት አዳምና ልጆቹ በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቀው አዝነው ተከዘው ይኖሩ የነበሩት በበጉ በክርስቶስ ደም ከሞት ወደ ህይወት ከባርነት ወደነተጸጻነት ተሸጋግረዋልና ፋሲካችን ክርስቶስ ነው፡፡ዮሐንስ በራዕዩ የወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ያጠበን እርሱ ነው፡፡ ራዕ 1 4 ይለናል፡፡ ከዚህ አንጻር መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በሞቱና በትንሳኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ የሆነች እለት በመሆንዋ ጸአተ ሲኦልም ትባላለች፡፡ ዮሐ 19 -18 ሮሜ 5 -10
የትንሰኤ የመጀመሪያው ማክሰኞ ቶማስ ይባላል፡፡
የትንሰኤ የመጀመሪያው ማክሰኞ ቶማስ ለምን ተባለ?
ይህ እለት ቶማስ የተባለበት ምክንያት የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በዚያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት የጌታን ትንሣኤውን ቢነግሩት በዚህ ዕለት ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን በሚስማር የተቸነከረ እጁን እግሩ ካላየሁ አላምንም በማለቱ ምክንያት ክርስቶስም ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ እንጂ ያላመነህ አትሁን አለው። ቶማስም ጌታዬ አምላክዬ ብሎ መለሰለት ኢየሱስም ስለ አየኸኝ አምነሃል ‘ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው’፡፡ ዮሐ 20÷27-29 ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ በዚህ ዕለት ቶማስም የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን የማመኑ ነገር የሚታሰብበት ቀን ሆኖ ስለተወሰነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች።
መድኃኒታችን ለቶማስ ጎኑን እንዲዳስስ የፈቀደበት ለሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት የተቸነከረውን እጅና እግሩን ያሳየበት ምክንያቱ ካህናት ሥጋውን እንዲፈትቱ ደሙን እንዲቀዱ ስልጣነ ክሕነት እንደተሰጣቸው ለማጠየቅ ነው። ዮሐንስም በእጃችን ዳሰስነው ብሏል ሉቃ 24 -39፡፡ 1ኛዮሐ 1 -1 ለማርያም መግደላዊት ግን የተነሣ ዕለት አትንኪኝ ማለቱ ለሴቶች ሥጋውን ደሙን መፈተት እንዳልተፈቀደላቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ብለው ሊቃውንት ያትታሉ።
የቅዱስ ቶማስ የስሙ ትርጉም፡- ቶማስ ማለት በአራማይክ ዲዲሞስ በግሪክ መንታ ማለት ነው፡፡ ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ከመጠራቱ በፊት ስሙ ዲዲሞስ ነበር ትርጉሞም ጨለማ ማለት ነው፡፡ ቁጥሩም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ ነው፡፡ ማቴ 10 -3 ዩሐ. 20 -24 ሐዋ 1 -3
የቅዱስ ቶማስ መንፈሳዊ እድገት፡- ቅዱስ ቶማስ ሲጠራ ከሰዱቃውያን ወገን ስለነበር በትንሣኤ ሙታን ማለትም በሙታን መነሳት ከማያምኑት ሰዱቃውያን የወሰደውን ትምህርት ይዞ ጌታችን ከሙታን በተነሳ ጊዜ እጆቹን ዳሶ በጦር የተወጋ ጎኑን አይቶ ዳሶ ካረጋገጠ በኋላ ያመነ ደቀመዝሙር ነው፡፡ በሰዱቃውያን ትምህርት ሰው ከሞተ ሊነሳ አይችልም ብለው ያምናሉና፡፡
ቅዱስ ቶማስ ያስተማረባቸው ሀገራት፡- በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በፋርስና በሕንድ ወንጌልን እንዳስተማረ ይነገራል፡፡
ከትንሣኤው በኋላ ያለው አራተኛው ቀን ረቡዕ “አልዓዛር” ይባላል፡፡
የፋሲካ አራተኛው ቀን ረቡዕ “አልዓዛር“ ለምን ተባለ?
ከትንሣኤው በኋላ ያለው አራተኛው ቀን ረቡዕ “አልዓዛር” የተባለበት ምክንያት አልዓዛር ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀን በሁዋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሳው ለአልአዛር መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ይህችን ዕለት በረድኤተ እግዚአብሔር የተመሩ አባቶቻችን ሊቃውንት አልአዛር በማለት ሰይመዋታል፡፡
አልዓዛር ማለት “እግዚአብሔር ረድቶናል” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው የተመዘገቡ ሦስት አልዓዛሮች አሉ፡፡ አንደኛው፡- የአሮን የልጅ ልጅ ሲሆን ዘጸ 6 -23፡፡ ሁለተኛው፡- ጌታችን በምሳሌ የገለጠው ከሀብታሙ ከነዌ ደጅ ተኝቶ የነበረው ድኃ ሰው ነው፡፡ ሉቃ 16፡20፡፡ ሦስተኛው፡- በዛሬው ዕለት የሚታሰበው የማርታና የማርያም ወንድም የሆነውና ከሞተ ከአራት ቀን በኋላ ጌታችን ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ነው፡፡ ዮሐ 11 -38 በዚህ ዕለትም መድኃኒታችን ክርስቶስ በአራተኛው ቀን አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሣው ቅድሰት ቤተ ክርስቲያናችን የምታስተምርበትና የምትዘክርበት ዕለት ነው፡፡
በቢታንያ ይኖር የነበረው አልዓዛር በታመመ ጊዜ “የምትወደው ታሟል” ብለው እህቶቹ ወደ መድኃኒታችን ክርስቶስ መልእክትን ላኩ፡፡ ጌታችን ግን መልእክንቱ በሰማ ጊዜም የአልዓዛር ሕመም ለሞት ሳይሆን “የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ” እንደሆነ ተናገረ፡፡ በኋላም መልእክቱ ከተነገረው ዕለት በኋላ ሁለት ቀን ዘግይቶ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል ነገ ርግን ላስነሣው እሄዳለው” ብሎ ወደ ቢታንያ ሄደ፡፡ በደረሰ ጊዜም የታመመው አልዓዛር ሞቶ አራት ቀን ሞልቶት ነበር፡፡ ማርታም ጌታችንን ባየች ጊዜ፡- “ጌታ ሆይ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው፡፡ ክርስቶስም፡- “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ይሆናል” በማለት ጌታችን አልዓዛርን ከሞት አስነሥቶታል፡፡ ዮሐ 11 -19-46
ይህን በማስመልከትም ከትንሣኤው በኋላ በዐራተኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ “ትንሣኤና ሕይወት” በሆነ በጌታችን አልዓዛር በተቀበረ በአራት ቀኑ ከሞት እንደተነሣ እኛም በጌታችን ትንሣኤ ነፍሳችን ከሥጋችን ተለይታ ብንሞት እንኳን ክርስቶስ ሲመጣ መዋቲና በስባሽ የሆነ ተፈጥሯችንን አራግፈን ሕያዋን ሆነን እንደምንነሣ የምናስብበት ዕለት ነው፡፡
“አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል ሞት በሰው በኩል (በአዳም) ስለመጣ ትንሣኤ ሙታንም በሰው በኩል (በክርስቶስ) ሆኗል፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉ” 1ቆሮ 15- 20 -22 ተብሎ እንደተጻፈ፡፡
ሰው በህይወት አለ አልሞተም ሊባል የሚቻለው በህሊናው ሲኖር ህገ እግዚአብሔርን ሳይተላለፍና ባልባከነ አና ባልጎሰቆለ በበጎ ህሊና በእግዚአብሔርና በሰው የሚወደድ ተግባር ሲኖረው ነው፡፡ እኛ ሰዎች ደግሞ ከጽድቃችን በደላችን ከበጎ ምግባራችን በክፉ ተግባር መሞላታችን ከርህራሄ ይልቅ ጭካኔአችን እጀጉን ይበዛል፡፡ይህ ደግሞ ሁላችንንም ሙታነ ህሊና አድርጎናልና አምላካችን ካነቀላፋንበት የሀጢአት እንቅልፍ በቸርነቱ አስነስቶን ለንስሀ ሞት ያብቃን፡፡
የትንሣኤ አምስተኛው ቀን “አዳም ሐሙስ” ይባላል፡፡
የመጀመሪያው ሰው አባታችን አዳምና የሁላችን እናት ሄዋን ተድላና ደሰታ ከሞላባት ከገነት ሕግን በመተላለፋቸው ምክንያት ከገነት ከወጡና ከተባረሩ በኋላ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሐ ገብተው ሲለምኑ እግዚአብሔርም ከአምስትን ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅዬ በሞቴ አድንኃለው በማለት ለአዳም ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበርና ይህች እለት የኪዳነ አዳም መታሰቢያ ሆና ትታወሳለች፡፡ መቃ 4፡24-28፡፡
በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ስለሆነ 5500 ዘመን እንደ አምስት ቀን ተኩል ነው ማለት ነው፡፡ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ትጋት ናት›› ፡፡መዝ 89 -4 ብሎ እንደተናግ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ወዳጆች ሆይ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት ሺህም ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ይህን አትርሱ›› በማለት አስተምሮናለ፡፡ 2ኛ.ጴጥ 3 38፡፡
ከዚህም አንጻር የአዳምን ተስፋና የተፈጸመለትን ምስጢር የምናስታውስበትና የምንዘክርበት ዕለት ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ ሰው ለመሆኑ ዋና ምክንያቱ የመጀመሪያው ሰው የአዳምና የእናታችን የሔዋን ጸሎት ስለሆነ ነው፡፡
አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡበት እለት ዓርብ ነው ታዲያ ስለምንድነው ዛሬ ማለትም ሐሙስ የምናከብረው? በዕለቱ አርብ አለመከበሩ ምክንያቱ ምንድነው? በዚህ እለት ሐሙስ የአዳም ተስፋ የተፈጸመበት መከበሩ ለምንድ ነው? ቢባል ዓርብ ዓለም ሁሉ የዳነባት እለት በመሀኑዋ የክርስቶስን ስቅለት በዚች ዕለት አናከብራለንና ነው፡፡ ከእሑድ እስከ ሐሙስ ያሉትን ቀናት ብንቆጥረ አምስት ቀናት ይሆናሉ። ይህ ማለት አምስት ቀን ተኩል (5500) ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎት ነበርና ያ ህያው ቃል እንደደረሰ እንደ ተፈጸመ ለማጠየቅ ነው።
የመጀመሪያው ሰውና የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው አባታችን አዳም በ6ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ነውና የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ ለ5500 ዘመን በመንጸፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ አዝኖ ተክዞ ይኖር የነበረ አዳም ዛሬ በዚች ዕለት የተሰጠው የተስፋ ቃል መፈጸሙን እንዘክራለን እናስብማለን፡፡
ይህች ዕለት አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብባታል፡፡ ክርስቶስ ሞትን ገድሎ የተነሳባት አምስተኛዋ ቀን አዳም ሐሙስ ትባላለች፡፡ አዳምና ሔዋን ተድላና ደሰታ በሞላባት በገነት 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ የእግዚአብሔርን ትእዛዙን በመተላለፋቸውና የጠላትን ምክር በመቀበላቸው ምክንያት ከኤደን ገነት ገነት ወጡ ተባረሩ፡፡ በገነት ያደርጉት የነበረውን ተድላ ደስታ አጡ፡፡ ኑሮአቸውም እሾህና አሜከላ በምታበቅል ምድር ሆነ፡፡ የአዳምም ሀዘኑ ጸና በረታም አባታችን አዳም ያዝን ይተክዝ የነበረው በገነት አደርገው የነበረው ተድላ ደስታ ቀረብኝ በማለት ሳይሆን ጌታዬ አትብላ ያለኝን እፀበለሥ በልቼ ትእዛዙን አፍርሼ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ታህል ቦታ አጣሁ በማለት ነበረ፡፡ ውድ ኦርቶዶክሳውያን የእግዚአብሔርን ትእዛዙን አፍርሰን ከህጉም ተላልፈን በኃጢአት አድፈንና ጎስቁለን እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ታህል ቦታ እንዳናጣ አድፈናልና በንስሀ እንታጠብ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እያለ ያስተምረናልና ‹‹በተወደደ ሰአት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና ፤እነሆ የተወደደ ሰአት አሁን ነው፡፡የመዳንም ቀን ዛሬ ነው››፡፡ 2ኛቆሮ.6-2
ማስታወሻ፡- የሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን እሁድ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ እሁድ ማለት አንደኛ መለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሰኞ የሳምንቱ 2ኛ ቀን ነው ማለት ነው፡፡
የፋሲካ ሥድስተኛዋ ቀን ዓርብ ቤተክርስቲያን ትባላለች፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተዋጅታ የተመሠረተች ደመ መለኮት የነጠበባት ናትና ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር የሚፈተትባት በመሆኑዋ ይቺን እለት ሊቃውንት አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን ብለዋታል ፡፡
ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በክርስቶስ ደም በመሆኑ ይህች ዕለት ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ ሆና ተሰጥታለች፡፡ የቤተ ክርሰቲያን ሊቃውንት መምህራን እንደሚያስተምሩት ዛሬ ቤተክርስቲያን የምትታነጸው እርሱ እግዚአብሔር በሚያውቀው ድንቅ ጥበቡ በእለተ ዘርብ ቅዱሳን መላእክት ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብለው ነበርና ዓለምን ዙረው የክርስቶስን ደም ረጭተዋልና ዛሬ ቤተ ክርሰቲያን የምትታነጸው ደሙ ባረፈበት ወይም በነጠበበት እንደሆነ የነገራል፡፡ከዚህ አንጻር የዛሬዋ እለት ቤተ ክርስቲያን ትባላለች፡፡
በሌላ መልኩ የዛሬዋ ዓርብ ፀአተ ሲኦልም ትባላለች፡- ነፍሳት ከ5500 ዘመናት በሁዋላ ከሲዖል የወጡባት ጌታችን በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ በሲዖል ያላችሁ ውጡ በጨለማ ያላችሁ ተገለጡ ብሎ ግእዛነ ነፍስን የነፍስን ይኸውም የነፍሳትን ነፃነት ሰበከላቸው ሰይጣንን አሰረው ሲዖልንም መዘበረው ነፍሳትን ነፃ አወጣቸው ልምላሜ ገነትን አወረሳቸው ይህ ዕለት ጌታችን በተነሳ በስድስተኛው ቀን ዓርብ እንዲታሰብ ፀአተ ሲኦልም የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ንስሐ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የመንግሥቱ ዋራሾች እንሆን ዘንድ አምለከ ቅዱሳን በቸርነቱ ያደለን፡፡
የፋሲካ 7ኛዋ ቀን ቅዳሜ አንሰት ወይም ቅዱሳት አንስት በመባል ትታወቃለች፡፡
ለምን የፋሲካ 7ኛ ቀን ቅዳሜ አንሰት ወይም ቅዱሳት አንስት ተባለች?
በዚች ዕለት ከመቶ ሃያው ቤተሰብ መካከል የሆኑት ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ይታሰባሉ፡፡ በዘመነ ሥጋዌው ጌታችንን በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ላገለገሉት በስቅለቱም ዕለት በቀራንዮ በጌታችን ላይ የሆነውን መከራ በማያታቸው መስቀሉን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሳ ምራቅ ሲተፋበት እጆቹ በሚስማር ሲወጉ ጉኑ በጦር ሲወጋ 6666 ጊዜ ሲገረፍ በርባን እንዲፈታ ጻድቁ እንዲሰቀል ሲፈረድበት ክብር ይግባውና ሲንገላታ እያዩ ዋይ ዋይ እያሉ እያነቡ እያለቀስ እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት በትንሣኤው ዕለትም ገና በሌሊቱ ሴትነታቸው ሳያሸንፋቸው በድቅድቅ ጨለማ ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው በመገሥገሣቸው ትንሣኤው ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መልካም መታሰቢያ ሆና ይህች እለት «አንስት» ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ 28 -1-18 ሉቃ.23 -27 ማቴ. 25 -1-11 መድኃኒታችን ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው ለሴቶች ክብርን ይሰጥ ስለነበረ ብዙ ሴቶች እርሱን በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለማገልገል ይከተሉት ነበር፡፡ ሉቃ 8- 2-3
የመጀመሪያዋ ሴት እናታችን ሄዋን ከገነት ለመውጣታችን ለመባረራችን ምክንያት ብትሆንም ዳግሚት ሔዋን በተባለች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ዳግመኛ ወደ ርስታችን ተመልሰናባታልን፡፡ በሴት ምክንያት ያጣንውን በሴት ምክንያት አግኝተናልና ሴቴችን ማክበር ምርጫችን ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡
በተለይም በብሉይ ኪዳን ዘመን ከወነወዶች በስተቀራ ሴቶች ከርስት ገብተው አይቆጠሩም ነበር፡፡ ርስትም አይካፈሉም ነበር፡፡ በዘር ኀረግም አይቆጠሩም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ርስታችንን ገነትን የምታህል የከበረች ስፍራ ያጣንው በእናንተ ነውና ርስት አይገባችሁም ይባሉ ነበር ነገር ግን በእመቤታችን ምክንያት የርስት ተካፋይ ሆነናልና ሴቴችን ማክበር ምርጫችን ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡
በመጀመሪያዋ ሴት በሄዋን ምክንያት የገነት ደጃፍ ቢዘጋብንን በዳግሚት ሄዋን በእመቤታችን ምክንያት የገነት ደጃፍ ተከፍቶልናልና፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴዋ “በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛም በድንግል ማርያም ተከፈተልን ከእፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን በማለት የገለጠው ለዚህ ነውና ሴቴችን ማክበር ምርጫችን ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያትን ምሥክሩ ይሆኑ ዘንድ እንደላካቸው ለሰማርያ ሰዎች “ያደረግኹትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ትመሰክር ዘንድ ጌታችን አምስት ባሎች የነበሯትን ሴት መርጦ ነበር፡፡ ዮሐ 4 -18፡፡
በበአለ በጰራቅሊጦስም ከመቶ ሃያው ቤተሰብ ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት የሚባሉት ሴቶች ነበሩ፡፡ በመልካም ሥራቸው የተመሰገኑ ሮምናን የመሠሉ ሴቶችም ታሪክ ተገልጦ መገኘቱ 2ዮሐ 1 በክርስትና ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ከፍ ያለ ድርሻና ክብር የሚያመላክት ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም የሴቶችን ርህራሄ ለመግለጥ ሥላሴ እንኩዋን በሴት አንቀጽ ቅድስት ሥላሴ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ይህ ማለት ሴት በወለደችው በልጅዋ መጠርጠር እንደሌለባት ሥላሴም በፍጥረታቸው መጠርጠር የለባቸውምና ነው፡፡ ሴት ርህሩህ እንደሆነች ሥሳሴም ለፈጠሩት ፍጥረት ይራረሉና ነው፡፡ ሴት የወለደችውን ልጅዋን ፈጽሞ እንደማትረሳው ሥላሴም እኛን አይረሱንምና፡፡ ሥላሴም በሴት አንቀጽ ይጠራሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የሴቶች ክብር ከፍ ከፍ ያለ እንደሆነ ያሳየንል፡፡
በሌላ መልኩ ሀገር እንኩዋን ሳትቀር የምትጠራው በሴት አንቀጽነው፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለእናት ሀገሬ ይላሉ ለሀገራቸው ያላቸውን ፈቅር ሲገልጡ ማለት ነው፡፡
ሴቶችን እናከብራቸዋልን እናገናቸዋለን ከፍ ከፍ እናረጋቸዋለን ምክንያቱም ጻድቃንን፤ ሰማእታትን፤ደናግል መነኮሳትን ፤ፓትርያርኮችን፤ጳጳሳትን ሊቃነ ጳጳሳትን፤ካህናት ዲያቆናትን ፤ነገስታቱን መኩዋንንቱን ወለዱልን በማለት ነው፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያንም ከዚህ የተነሳ ከሰላሣ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በተጨማሪ በተለያየ ዘመናት በሰማዕትነትና በቅድስና ሕይወታቸውን ያሳለፉ ቅዱሳት አንስትን የቅድስና ማዕረግን ከወንዶች እኩል በመስጠት፣ ጽላትን በመቅረጽ፣ ምስጋናቸውን የሚገልጡ ድርሰቶችን በማዘጋጀት፣ በቀኖናዋ መሰረት በዓላቸውን በማክበር ክብራቸውን ትዘክራለች፡፡
እንኩዋን ለዳግም ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
ዳግም ትንሣኤ ማለት የትንሣኤው ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ ቤት ገብቶ በመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ቶማስ ከሔደበት ሲመጣ የጌታችንን መነሣትና እንደተገለጸላቸው በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ዐየን ብላችሁ ልትመሰክሩ ፣ ልታስተምሩ ፣ እኔ ግን «ሰምቼአለሁ» ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር ነውን? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ ምክንያቱን ለይቶ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኀኔዓለም ክርስቶስ ልክ እንደመጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» በማለት በመካከላቸው ቆመ፤ ቶማስንም «ያመንክ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ» ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደፍላጎቱ በመረዳቱ «ጌታዬ አምላኬ ብሎ መስክሮ»አመነ፡፡
ስለዚህ እሁድ ዳግም ትንሳኤ ስንል መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ተቀብሮ ዳግም የተነሳ ሳይሆን ከሙታን ተነስቶ ለሐዋርያት በተገለጠላቸው ሳምንት በድጋሚ ቅዱስ ቶማስ ባለበት ልክ በመጀመሪያ እንደተገለጠላቸው ሆኖ ስለታያቸው ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአስሩ ሐዋርያት ሲገለጥላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልነበረም፡፡
ጌታም የቶማስን ጥርጣሬ ያሰወግድለት ዘንድ በተነሳ በስምንተኛው ቀን ቅዱስ ቶማስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ሳለ እንደገና በትንሣኤ እንደታያቸው ሆኖ በዝግ ቤት ገብቶ ሠላምለእናንተ ይሁን ብሎ ለሁሉም ሠላምታ ከሰጣቸው በኋላ ሐዋርያው ቶማስን ለይቶ ‹‹ቶማስ ቶማስ ና በችንካር የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን እይ እንዲሁም እጅህን አምጥተህ በጦር ወደ ተወጋ ጎኔ አግብተህ ዳሰኝ ያመንክ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን ባለው ጊዜ ቶማስም እጁን በጦር የተወጋ ጎኑን በእጆቹ በዳሰሰ ጊዜ ከእሳት እንደገባ ጅማት እርር ኩምትርትር ሲል ጌታዬ አምላኬ ብሎ ጮኸ አምላክነቱን መሰከረ ፡፡ ‹‹አንተ አይተህ አምነኃል ነገር ግን ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአንናቸው ፡፡›› ብሎ ፈውሶታል ፡፡ ዮሐ 20፡29 ይህች ጎኑን የዳሰሰች እጁ ዛሬም ሕያዊት ሁና በሕንድ አገር ከታቦቱ ጋር ትኖራለች፡፡ ሊቀጳጳስ ሲሾም ለዚህ ሹመት የሚበቃውን ቀኝ እጁን በመያዝ ትመርጣለች ፡፡
እንግዲህ ይህ የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ «ዳግም ትንሣኤ» ተብሎ ይጠራበታል፤ ይከበራልም፡፡ ዮሐ. 20-24-30