ስለ ንስሓ አባት
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ንስሓ አባት
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
ጌታችን በወንጌሉ ካህናትን “እናንተ የአለም ብርሃን ናችሁ” ማቴ 5 -14 ይላቸዋልና ከርኩሰት አረንቁዋ ከጨለማውና ከኀጢአት ሥራ ሁሌ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚመሩንና ኀጢአትን ጠልተን በበጎ ምግባር እንድንኖር መንገዱን የሚመሩን ናቸው፡፡
የንስሐ አባት ማለት ምስጢረኛችን በመንፈሳዊም በሥጋዊም ህይወታችን የቅርብ አማካሪዎቻያችን ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሲራክ “ብዙ ሰዎች ወዳጆች ይሁኑህ ከብዙዎች አንዱ ምክርህን የምትነግረው ከልቡናህ ጋር አንድ ይሁን፡፡” ሲራክ 6-6 በማለት ይናገራል፡፡ ይህ ማለት ምእመናን ስለ ሃይማኖትና በጎ ምግባር የሚያስተምሩዋቸው ብዙ ካህናት ሊኖሩዋቸው ቢችሉም ከብዙዎች አንዱ ግን ንስሃቸውን የሚናዘዙለት መምህረ ንስሃ ሊሆናቸው እንደሚገባ ያስረዳልና መምህረ ንስሕ ማለት ምስጢረኛና አማካሪ ማለት ነው ፡፡
አበ ነፍስ ማለት ኃጢአታችንን የምንናዘዝለት ማለት ነው፡፡ ኀጢታችንን ለካህን ስንናዘዝ ለእግዚአብሄር መናዘዝና ክብር መስጠት ነው፡፡ ኢያሱ እንዳለ “ልጄ ሆይ ለአምላክ ከብርን ስጥ፡ ለእርሱም ተናዘዝ፡ ያደረግከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ” ኢያሱ 7-19፡፡ ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ለእግዚአብሄር ክብር መስጠት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ አበዉ ካሀናትም ኑዛዜን ከተቀበሉ በኋላ “እግዚአብሔር ይፍታህ” እንጂ ”ፈትቼሃለሁ ” አይሉም፡፡ ኀጢአተዘችንን በነሱ ፊት ብንናገርም ሰሚዉም ሆነ በእነርሱ እጅ ስርየተ ኀጪአት የሚሰጠዉ እርሱ ባለቤቱ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም አበ ነፍስ ማለት ኀጢአታችንን በዝርዝር ምንም የሚያስፈራ ኀጢአት ቢኖረንም እያሰታወስን አንዳች ሳናስቀርና ሳንጠራጠር በዝርዝር የምንነግረው የእግዚአብሔር አይን ነው ማለት ነው፡፡
የንስሐ አባት/አበ ነፍስ ወይም መምህረ ንስሐ ማለት የንስሐ ልጆቹ ትክክለኛውን ዓላማ ይዘው የንስሐ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ በጎ መሪ ማለት ነው፡፡
መምህረ ንስሐ ማለት ልጆቹን መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያስተምርና የልጁቹን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚከታተልና ስለ በጎቹ የሚጨነቅ እረኛ ማለት ነው፡፡
የንስሐ አባት ማለት ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ፣ ምግባራቸውን እንደይስቱ በርካቶችም ለጠንቋዮችና ለአሳቾች ሰለባ እንዳይሆኑ የጠራውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከምንጩ ማስጎንጨት የሚችልና እሄንንም የማድረግ ግዴታ ያለበት ባላደራ ማለት ነው፡፡
የንስሐ አባት ማለት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ያለመታከት የሚተጋ ማለት ነው፡፡ የንስሐ አባት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ሁሌም መጐትጐትና መቀስቀስ አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በኃይል፣ በማጣደፍ ወይም በማስፈራት አይደለም፡፡ ካህኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወኪል፣ የእግዚአብሔር አደረኛ ስለኾነ ሁሌም ማትጋት፣ መጐትጐት፣ መቀስቀስ ይጠበቅበታል፡፡
የንስሐ አባት ለእያንዳንዱ ልጆቹ እንደየ አቅማቸውና እንደየሃይማኖት እውቀት መጠናቸውና እንደየ መንፈሳዊ እውቀታቸው አቻ እስከሚሆኑለት ለያይቶ በማስተማር ማብቃት አለበት፡፡
የንስሐ አባት ማለት በንስሐ ልጆቹ መካከል ፍጹም መቀራረብ እንዲኖር የሚያደርገ ነው፡፡ የንስሐ ልጆች ለብዙ ችግሮች የመፍትሔ አካል ኾነው እንዲያገለግሉ ዕድል ይሰጣልና፡፡ የተቸገሩትን ከመርዳት ዠምሮ አንዱ ለሌላው አርአያ ኾኖ በተግባር እስከማስተማር ድረስ ማድረግም የንስሐ አባት ድርሻ ነው፡፡ ይህ ማለት የአንድ ካህን ንስሐ ልጆች ከአንድ የሥጋ አባትና እናት የተወለዱ እህትማመቾች እና ወንድማማቾች ያህል ከዚያም በበለጠ ሁኔታ መቀራረብ አለባቸው ማለት ነው፡፡የንስሀ አባት ማለት ይህን የሚተገብር ማለት ነው፡፡
ከቊርባን በፊት ንስሐ ይቀድማልና፡፡ ሰው ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ ስለሌለ ጧት የሠራውን ለማታ፤ ማታ የሠራውን ለጧት ለመምህረ ንስሐው ነግሮ መምህረ ንስሐው ያዘዘውን ሠርቶ ሊቀበል ይገባዋልና ይህ ታላቅ ሀላፊነት የተጣለው ደግሞ በመምህረ ንስሀው ላይ ነው፡፡
የንስሐ አባት ማለት ባለአደራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በበረኻ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ማን ነው?” ሉቃ.15 -5 ያለው፡፡ ካህናት ከእግዚአብሔር በአደራ እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ኹሉንም ሳይዘነጉ እያንዳንዱን በነፍስ ወከፍ ሊጠብቁና ሊያገለግሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡
የንስሐ አባት ከንስሐ ልጆቹ ጋር የሚፈጥረው ግላዊ ግንኙነት ከቤተሰባዊነት ያልተሻገረ ኾኖ ሲቀነጭርና እጅጉን ያነሰ ሲሆን ነው፡፡ ብዙ ካህናት ወደ ምእመናን ቤት መጥተው ሲያበቁ መስቀል ከማሳለምና ጠበል ከመርጨት ያለፈ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ካህናት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስቀመጠላቸው ከሥራቸው ኹሉ ቅድሚያውን ሰጥተው ማስተማር፣ መምከር፣ ኑዛዜን መቀበል፣ ማጽናናትና መገሰጽ ይገባቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የንስሐ ልጃቻቸውን በጥንቃቄ ይዘው ለሥጋ ወደሙ ማብቃት ግባቸው ስለኾነ ትኩረታቸው ኹሉ ወደዚኽ ዋነኛ የክህነት ዓላማቸው መሆን አለበት ፡፡ ይህም የካህኑ ትልቁ ሀላፊነት ነው፡፡
የንስሐ አባት የንስሐ ልጀቹን የቤተ ሰብ አባላት ቁትርና እያንዳንዱን በሚገባ ማወቅ አለበት፡፡
አንድ የንስሐ አባት ልጆቹንና አጠቃላይ ቤተሰቡን እያሰታወሰ አዘውትሮ ስለ ሁለንተናቸው መጠየቅ አለበት፡፡
የንስሐ አባት ከልጆቹ ጋር አብሮ በመጸለይ ጸሎትን ማለማመድ፤ ሆኖ በማሳየት እውነተኛ የአባትና የልጅ ፍቅርን ማሳየት፤ በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በሥጋዊም ሕየዋታቸው መጨነቅ፤ ስራቸው እንዲባረክ አዘውትሮ፤መጸለይ በአጠቃላይ ልጆቹን በቅርበት መከታተል፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ተግባሩ እሄ ነው፡፡
መልስ (ለጥያቄ #1) ፦ ንስሓ አባት እያለን ሳንሰናበት ወይም እስካሁንም የነበሩንን የንስሓ አባት ምንም አይነት ምክንያት ሳናገኝባቸው በራሳችን ምክንያት ብቻ ተነሳስተን ወደ ሌላ ንስሓ አባት ብንሄድ ስርአተ ቤተክርስቲያን አይፈቅድም። ምክንያቱም ጉዳዩ የነፍስ አባት እስከሆነ ደረስ የነፍስ አባት የመያዛችን ስርአትም አሰራሩ መንፈሳዊ ምሥጢር ስለሆነ የነበሩንን የንስሓ አባት ተሰናብተን ወደ ሌላው ለመሄድ በቂ ምክንያት ሊኖረንና፤ ሌላ አባት የፈለግንበትንም ምክንያት ያለምንም ማፈር ነግረናቸው ተሰናብተን መሄድ መብታችን ነው። ካህኑም በስርአት ካልጠበቁን ለምን ማለት አይችሉም። (ለጥያቄ #2) ዝም ብሎ ተነስቶ ሳይሰናበት የሄደ ግን እንደ ስርአተ ቤተክርስቲያን ትክክል ባይሆንም ነገር ግን የሄደውም ወደ ካህን ስለሆነ ይህ ንስሓ የሚያስገባ ጉዳይ አይደለም።
መልስ፦ መንፈሳዊ እና ክርስቲያናዊ ህይወታችንን በአባትነት እንዲጠብቁን የያዝናቸው የንስሓ አባት ያደረግናቸው ካህን በራሳቸው ምክንያት እና ስንፍና ምንደኛ ቢሆኑ ማለትም ጠዋት ማታ እየገሰጹ እየመከሩ የማይጠብቁን አና ይበልጥ ወደ መንፈሳዊ አገልገሎት የማያተጉን ከሆነ ለአውሬ ወይም ደግሞ ለነጣቂ ለዲያብሎስ የሚያሰጥ ሰነፍ እረኛ ስለማያስፈልገን ያለምንም ቅድመ ሀኔታ ትጉህ እና ቅን የሆነ ለንስሓ ልጆቹ አገልግሎት ቅድሚያ ሁኔታ የሚሰጥ አባት መያዝ አለብን። በዚህ ጉዳይ ድረድርም ሆነ ማመንታት አያስፈልግም።
ከዚህ በታች ያለውን የድረገጻችንን አድራሻ በመጫን በመኖሪያ ስፍራዎት መሰረት ፎርሙን ይምሉ፤ ምንም አይነት መሰናክል ካጋጠሞት ያሳውቁን፤ እንረዳዎታለን፦ https://yohannesneseha.org/
መልስ፦ ጠያቂያችን የንስኀ አባት ወይም የነፍስ አባት አድርገን ረቂቁንና ሰማያዊውን ህይወት ያቀዳጀናል ብለን አባት ካደረግናቸው ካህናት ወይም አባቶች በገንዘብ የሚመዘን ክፍያ በቀጥታ አያስፈልግም። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተቀበሉት አዳራ እኛን ለነሱ እንደ ሀብትና እንደ ንብረት አድርጎ ሲያስረክበን እነሱ ደግሞ በኛ ህይወት ላይ ሊናዝዙና ሊያስተዳድሩ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። በኦሪቱ ስርዓት የሌዊ ልጆች በህዝቡ ላይ ካህናት ሆነው ሲሾሙ ህዝቡን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለው ይላል። በአዲስ ኪዳንም በቅዱስ ወንጌል “በፀጋ ያገኛችሁትን እንዲሁ በልግስና ስጡ” በማለት ለቅዱሳን ሐዋሪያት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም “ሄዳችሁም መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ ድውዮችንም ፈውሱ ሙታንንም አስነሱ ለምፃሞችን አንፁ አጋንንትን አውጡ በከንቱ ተቀብላችሁ በከንቱ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ። ለሰራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።” በማለት የሚያስፈልጋቸውን ፈቅዶላቸው በአባትነት የተሰጣቸውን ፀጋ በልግስና እንዲያደርጉትና ህዝቡንም በነፃ እንዲያገለግሉ ታዘዋል። (ማቴ 10፥7፡9)
እንዲሁም ስሞን መሰሪ የተባለ በሰይጣን መንፈስ ተነሳስቶ ቅዱሳት ሐዋሪያት ከመንፈስ ቅዱስ በተሰጣቸው ስልጣን ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ “ስሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን አኔ ታላቅ ነኝ ብሎ እየጠነቆለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ በከተማ ነበረ … ስሞንም በሐዋሪያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሀልና ብርህ ከአንተጋራ ይጥፋ ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስኅ ግባ ምናልባትም የልብህን ሃሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና (የሐዋ ስራ 8፥9 እና 18-22)
ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ ሌሎቻችሁ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መገንዘብ ያለባችሁ አባቶቻችን የሚሰጡን በረከትና የሚፈፅሙት የክህነት አገልግሎት በገንዘብ የማይሸጥ መሆኑን ማወቅ አለብን። ነገር ግን ካህናት ካለባቸው መንፈሳዊ የአባትነት ሃላፊነት አንፃር ስለኛ ሲፀልዩ፣ ቀድሰው ሲቆያርቡ፣ በመስቀል ሲባርኩ በመሳሰለው ሁሉ በግልም በማህበርም ስለኛ የሚሰጡን አገልግሎት በነፍስም በስጋም በረከት የሚያሰጥ ስለሆነ ፤ እነሱም ደግሞ ዘወትር ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሚተጉ እራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት ራሱን የቻለ የግል ሀብት ስለሌላቸውና ስላልሰበሰቡ መንፈሳዊ ቅናት ያለው አንድ ክርስቲያን በራሱ ተነሳስቶ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ከመግለፅ አንፃር ቢፈልግ ቤት ሰርቶ መስጠት ቢፈልግ መኪና መስተጥ ቢፈልግ ገንዘብ ቆጥሮ መስጠት ይችላል። ይህ ግን ከግዴታ የተነሳ ሳይሆን በራሱ ካለው መንፈሳዊ ፍቅር ተነሳስቶ የሚያደርገው መልካም ምግባር እንደሆነ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚህ ውጪ ከላይ በጠያቂያችን ሃሳብ የተነሳው ለስልጣነ ክህነት አገልግሎት ተብሎ ለካህናት የገንዘብና የሌላ ድርድር ፈፅሞ የማይደረግ እና የማይፈፀም መሆኑን ግን ማወቅ አለብን።
መልስ፦ ጠያቂያችን ንስኅ ለመቀበል ወደ መንፈሳዊ አባትዎ በሄዱ ጊዜ በኅጢአቱ መጠን ቀኖና ከመስጠት ይልቅ እግዚአብሔር የልባችሁን መፀፀት አይቶ ይቅር ይላችኋል፣ ፀሎት ብቻ አድርጉ በሚል ነገሩን በማቅለል እንዳሰናበትዎት ፣ ይህ ድርጊታቸው ደሞ ለመንፈሳዊ ህይወት ያለዎትን አቋም እያዘናጋው እንደመጣ በመግለጽ ምን ላድርግ በሚል ጥያቄ አቅርበውልናል። በመሰረቱ የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ ሁላችሁም ከሁሉ በፊት አጥብቃችሁ እንድትገነዙቡልን የምንወደው፤ ጥያቄያችሁ እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሄርን ቃል እንድናስተምራችሁና ለጥያቄወቻችሁም ከቤተክርስቲያን አንፃር በቂ መልስ እና ምክር እንድንሰጣችሁ ከመጠየቅ አንፃር ይሁን እንጂ አባቶችንም ሆኑ ሌላ ሰዎች በራሳቸው አካሄድ ስለፈፀሙት ጠንካራም ሆነ ደከማ ጎን በመጥቀስ የዳኝነት አስተያየት እንድንሰጥበት ከመፈለግ አንፃር ግን መሆን የለበትም። ምክንያቱም የሌሎችን ሰዎችን ህይወት ስለማንዳስስ በአገልግሎቱም ዙርያ ክፋትንና መቃቃርን ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንመክራለን።
ወደ ዋናው ጥያቄ ስንመለስ ግን አንድ ክርስቲያን በፈፀመው ጥፋት ተፀፅቶ ወደ ንስኅ አባቱ በሄደ ጊዜ ካህኑም እንደ ኅጢአቱ ክብደትና መጠን ቀኖናውን ለመስጠት የቤተክርስቲያን የቀኖና መፅሐፍ ወይም አንቀፀ ንስኅ በሚያዘው መሰረት መፈፀም አለበት እንጂ ዝም ብሎ በልብወለድ አካሄድ ነገርን በማቅለል ምንም ማለት አይደለም ፣ ከልብህ ከተፀፀትክ በቂ ነው፣ ዝም ብለህ ፀልይ ወዘተ በሚል የዋዛ ፈዛዛ አይነት አነጋገር የንስኅ ቀኖና አይሰጥም። እንዲህ አይነት አፈፃፀም ደግሞ ከእውነተኛ አባቶችና ጠባቂዎች አይጠበቅም። አንዳንዶቹ ካህናት ከትምህርት እጥረትም ሊሆን ይችላል ወይም በጉዳዩ ትኩረት ካለመስጠት ወይም ከጊዜ እጥረት በግልፅ ባይገባንም እንዲህ አይነት ድርጊት እንደሚያጋጥም ግን ተረድተናል። ስለዚህ ቢቻል ሁላችሁም ስለመንፈስ ልጆቻቸው ዘወትር የሚያስቡትን ስለ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖትና ቀኖና ስርአትና ትውፊት ጠንቀው ማስተማር የሚችሉና ዘወትር የመንፈስ ልጆቻቸውን የሚመክሩ የሚገስፁ ካህናትን የነፍስ አባት አጥብቀው እንዲያደርጉ እንመክራለን። ጠያቂያችንም ከዚህ በላይ በሰጠነዎት የመፍትሄ ሃሳቡን እንዲወስዱ ይህን መልዕክት እያስተላለፍን ተጨማሪ ምክረ ሃሳብ ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን።
መልስ፦ጠያቂያችን በመሰረቱ የእርስዎ ጥያቄ በተግባር የተፈፀመውን ድርጊት ስለሆነ የገለፁልን በጣም እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ የንስኅ አባት (የነፍስ አባት) የማትታየውን ፣ የማትጨበጠውን፣ የማትዳሰሰውን ረቂቅ የሆነችውን የነፍሳችን ሃላፊ ስለሆኑና እንዲሁም በአይነ ስጋ የማናየውን በእጅ የማንዳስሰውን በምርምርና በእውቀት የማይደረስባትን በኋለኛው ዘመን የምንወርሰውን ሰማያዊ መንግስት ለማውረስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስልጣን የተሰጣቸው ስለሆኑ በአባትነት የንስኅ አባት አድርገን የምንይዛቸው አባት በእውቀታቸው፣ በስነምግባራቸው፣ በፆም በፀሎታቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በምግባራቸው የተመሰከረላቸውና ስለ ንስኅ ልጆቻቸው በትጋትና በንቃት ዘወትር ሃላፊነት ወስደው የሚያገለግሉ መሆን ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ ከአንድ በላይ የሆነ ንስኅ አባት በመያዝ የሚደረገው አሰራር በቤተክርስቲያን ቀኖና አይፈቀድም። የንስኅ አባት ያደረግናቸው ካህን ለአገልግሎት ብቁ ካልሆኑ የተሻለ አባትና አስተማሪ ፈልገን መያዝ ክርስቲያናዊ መብታችን ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ከአንድ በላይ የንስኀ አባት በሪዘርቭነት ወይም በተጠባባቂነት መያዝ በተቀደሰው ክርስቲያንነታችን እንደማፌዝና እንደማሾፍ ስለሚቆጠር እንዲህ አይነት ስርዓት መስተካከል እንዳለበት በአፅንዎት እንመክራለን። ለሁሉም ነገር ጥፋቱ እና ድክመቱ የኛ የቤተክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች እንጂ የምእመናን ግን አይደለም። እውነቱን አስረግጦ የሚነግራቸውና የሚመራቸው ባለመኖሩ በየዋህነትና በቅንነት የሚያደርጉት ስለሆነ እነሱን ለመውቀስ አንደበት አይኖረንም። ነገር ግን በዚህ በዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ ፕሮግራማችን በምናስተላልፈው እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ብዙ ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች እንደሚስተካከሉበት እምነታችን የፀና ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ከላይ በዘረዘርነውን መመዘኛ ተጠቅመው አንዱን አባት መርጠው መያዝ እንዳለብዎትና ሌሎችን አባቶች እንዲያሰናብትዎ መጠየቅ እንዳለብዎት እንመክራለን። ሌሎችን አባቶች ባለን ቀረቤታ በፀሎት እንዲያስቡን እንዲያስተምሩን ወደቤታችን መጥተው ፀበል እንዲረጩልን ብናደርግ መደበኛና ቋሚ ከሆኑት የንስኅ አባት ጋር የሚያጣላ ሳይሆን አላማውን ይበልጥ የሚያፀናው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይሆንም። ነገር ግን አንድ ምእመን በአንድ ጊዜ ሊኖረው የሚገባው አንድ ንስኅ አባት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ለበለጠ መረጃ እና ምክር ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ስለ ጸሎት 4 Q (H-3, C-1)
መልስ ፦ ጠያቂያችን፤ የሚያስታውሱትንና የሰሩትን ኅጢአት አንዱንም ሳያስቀሩ ለንስኅ አባትዎ በዝርዝር ማስረዳት የግድ አስፈላጊ ነው። የእርስዎ ንስኅ አባት ሊናዝዙ ስልጣን ያላቸው የንስኅ አባትዎም በስነስርዓት አድምጠው የሰሩትን ኅጢአት በዝርዝር ካወቁ በኋላ ለእያንዳንዱ ጥፋት የቤተክርስቲያን ቀኖና በሚያዘው መሠረት ንስኅውን በፆም በፀሎት በስግደት ወይም በሌላ ቀኖና እንዲፈፅሙ ትዕዛዝ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ጠያቂያችን ግን እንዳሉት ገና ስለፈፀሙት ጥፋት ዘርዝረው ሳይጨርሱ ወይም ሃሳብዎን እስከመጨረሻው ባለማዳመጥ ቀላል አድርገው የሚተዉት ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ሊያስጠይቃቸው ስለሚችል ምንም እንኳን ጥፋቱ የካህኑ ቢሆንም እርስዎ የህሊና ነፃነት ያገኙ ዘንድ፦ 1ኛ ለመንፈስ ልጆቻቸው ቅድሚያ ሰጥተው የሚያስተምሩና ዘወትር የሚፀልዩ ንስኅ አባት መርጠው በመያዝ ንስኅ መግባት፣ ወይም ደግሞ 2ኛ ወደ ገዳም አባቶች ሄዶ ንስኅ መቀበል፣ 3ኛ እንደ ደግሞ አማራጭ ማድረግ ያለብዎት ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዶ በህሊና ፀፀት የሰሩትንና ተናግሬ ሳልጨርስ አቋረጡኝ ያሉትን ኅጢአት ሁሉ በመናዘዝ የሱባኤ ጊዜ ይዘው መፆም፣ መፀለይ፣ ልዩ ልዩ የቱሩፋት ስራ በመስራት የግልዎትን ቀኖና መፈፀም ይችላሉ። የበለጠ ምክርና እገዛ ካስፈለገዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።.
ጠያቂያችን ያቀረቡት ጥያቄ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ እና የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ዋናው አላማም ጠባቂና ሰብሳቢ የሌላቸውን የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ወደ እውነተኛው መንገድ ለማሰባሰብ እና ዘወትር የሚመክር እና የሚገስፅ አባት እንዲኖራቸው ለማድረግ ስለሆነ፤ እርስዎ እንዳሉት ገና በቤተሰባዊ ልማድ የንስኀ አባት አለን በሚል ብቻ የነፍስ ድህነት ስለማይገኝ እርስዎን በቅርበት እየተከታተለ ዘወትር የሚመክር እና የሚያስተምር የነፍስ አባት ስለሚያስፈልግዎ ለዚህ ጥያቄዎ ተገቢውን ምላሽና መንፈሳዊ አገልግሎት እንድንሰጥዎ በውስጥ መስመር በሚላክልዎ አድራሻ ደውለው ሊያነጋግሩን ይችላሉ በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን አንድ መንጋ ያለጠባቂ ፣ ህዝብና ሀገር ያለአስተዳዳሪ አንድ ቀንም ቢሆን መዋል እና ማደር እንደማይችል አንድ ክርስቲያንም ያለ ንስኀ አባት አንድ ቀንም መዋልና ማደር ስለማይችል እርስዎ እንዳሉት በስራ አጋጣሚ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የንስኀ አባትዎንም ከቦታ ቦታ ይዘው መንቀሳቀስስለማይችሉ በዚያ በሄዱበት የቤተክርስቲያን አባቶችን በማነጋገር አባት አድረገው መያዝ ይችላሉ። ምናልባት በሄዱበት ስፍራ አባት የማያገኙበት አጋጣሚ ካለ ደግሞ በርቀትም ቢሆን ለአባትነት የመረጧቸውን ካህን በስልክ እና በፅሁፍ መልዕክት እየተነጋገሩ ንስኀ፣ ትምህርት እና ምክር መቀበል ይችላሉ።
ውድ የተከበሩ የዘወትር ተከታታይና አጋር የሆኑ አባላችን ሆይ እንኳን አብሮ አደረሰን፤ አህታችንን በማንኛውም ጊዜ ማለትም ከሰኞ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት ከጠዋቱ 3 ሰአት እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ባለው ጊዜ ውስጥ በውስጥ መስመር በላክንለዎት ቁጥር በቴሌግራም ወይም በሻይበር ቢደውሉ ሊያገኙን እንደሚችሉ ያሳውቁልን ዘንድ አንጠይቃለን። ምናልባት ከእኛም ሆነ ከእኛ አቅም ውጪ በሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች መስመሩን ማግኘት ባይችሉ እንኳን ደጋግመው በተለያየ ሰአት እንዲሞክሩ እንመክራለን።
ጠያቂያችን በዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፖሮግራም ተደራሽ የምናደርገውን ተከታታይ ትምህርትና እና ጥያቄና መልሶችን በመከታተል እርስዎም ጠይቀው በመረዳት ትምህርት እንዳገኙበት እናምናለን። ወደፊትም የእግዚአብሔርን ቃል ለመመከር ቅድሚያ መስጠትን ቸል እንዳይሉ አደራ በማለት ለጠየቁን ጥያቄም በውስጥ መስመር በላክንልዎት አድራሻ ያገኙን ዘንድ የኛም ፈቃድ ነው።
ጠያቂያችን፤ ካህኑ የሰጠዎት የስግደት ቀኖና ለአንዱ 100 ለአንዱ 50 ለምን እንደተሰጠ ለጠየቁን ጥያቄ የተሰጠ ማብራሪያ። በመሰረቱ ስለ ኀጢአት ቀኖና በሚመለከት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለቀረቡልን ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠን ሲሆን አሁን ያቀረቡት ጥያቄን በሚመለከት ፦ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ቀኖና እንደ ኀጢአቱ ልዩነት ወይም ክብደት እና ቀላልነት ተመጥኖ ስለሚሆን በቀኖና ቤተክርስቲያንም እያንዳንዱ ክርስቲያንም ለፈፀመው የኀጢአት አይነት ቀኖና ስግደት ፣ ጾም ፣ ፀሎት፣ የቱሩፋት ስራ መፈፀም እንዳለበት በህጉ ላይ በዝርዝር ስለተደነገገ በዚህ አይነት የሚፈፀም በመሆኑ ለምን የ2 ሰዎች የስግደት ቀኖና ተለያየ ተብሎ ሊጠየቅም ሆነ በዋዛ እና በፈዛዛ ሊቀርብ ከቶ አይችልም። ሲጀመር የንስኀ ህይወት ምስጢር ቀኖና ስለሆነ ለማንም ሰው ልናማክረው የማንችል ከእግዚአብሔር በታች ቀኖናውን በሚሰጡት አባት እና ቀኖናውን በሚቀበለው ክርስቲያን መካከል የሚፈፀም ስርዓት ስለሆነ ለማንም ሰው ሚስጢሩን ማካፈል ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ጠላት ዲያብሎስ በሌላ ሰው ላይ አድሮ ፈተና ለማምጣት እና ቀኖናችንን በስርዓቱ እንዳንፈፅም እንቅፋት በመሆን የራሱን ስራ ስለሚሰራ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን አሁሉንም ማሰብ ያለብዎት በትክክለኛ እንደ ቤተክርስቲያን ስርዓት እውነተኛ የሆኑ የንስኀ አባት በቤተክርስቲያን ስርዓት አንፃር የተሰጠንን ቀኖና ተቀብለን ዳግም ወደ ጥፋት እንዳንመለስ እግዚአብሔር ጥፋታችንን የመጨረሻ እንዲያደርግልን እየተማፀንን የተሰጠንን የንስኀ ቀኖና መፈፀም ይኖርብናል እንጂ እንደ ማህበራዊ ጉዳይ ከማንኛውም አካል ጋር በመወያየት እና ትችት መስጠት ፈፅሞ ክርስቲያናዊ ስነምግባር አይደለም። ተጨማሪ ምክር ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ጠያቂያችን በተደጋጋሚ የሚፈተኑበት ኀጢአት እንዳለ ገልጸው በዚህም ንስኀ መግባት እንደሚፈልጉ ነገር ግን ለንስኀ አባትዎ ለመናገር ፍርሃት ወይም ስጋትና ይሉኝታ አይነት የሰው ሰውኛ አስተሳሰብ እንደተሳቀቁ ተረድተናል። የንስኀ አባትዎን ወይም በቅርብ የነፍስ ጠባቂ ሆነው በእርስዎ ህይወት ላይ ሃላፊነት ኖሯቸው የተሾሙትን ካህን ለማነጋገር የማይችሉበት እና ያጋጠመዎ ችግር ከባድ መሆኑን ለመረዳት ከቻልን፥ ችግሩን በሌላ መንገድ ለመፍታት እንዲቻል ተገናኝተን በግልፅ መነጋገር አለብን። ምናልባት ዝም ብሎ ለስጋዊ ክብራችን ወይም ደግሞ ራሳችንን ለንስኀ አባታችን እንኳን ሳይቀር እንደፃድቅ ቆጥረን በአስመሳይነት የምንቀጥለው ህይወት የእኛን ጥፋት እጥፍ ድርብ ያደርገዋል እንጂ ጠቃሚ ስለማይሆን፤ በአጠቃላይ ከንስኀ አባት ጋር ተነጋግረው ችግሩን ለመፍታት የማይችሉበት ሁኔታ በብዙ ምክንያት ሊገለፅ ስለሚችል፣ መተማመንም በመካከል ከሌለ ወይም የካህኑም የዕውቀትም ሆነ የመንፈሳዊነት ብቃት ማነስ ከሆነ ወይም ደግሞ እርስዎ እራሶን ሁል ጊዜ እንደ እውነተኛ ክርስቲያን ከኀጢአት እና ከጥፋት እርቀው እንደሚኖሩ በማስቆጠር የነበሩበት ህይወት ከሆነ በአንድም በሌላ መንገድም በእርስዎ በኩል እንደከባድ የቆጠሩትን ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ በአካል ቢያገኙን መልካም ነው የማይቻል ከሆነም በስልክ ያነጋግሩንና ውስጣዊ ችግርዎን መርምረን እና ተረድተን ትምህርት እና ምክር ሰጥተንዎት በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብዎት የመፍትሄ ሃሳብ ልንሰጥዎት እንችላለን ።
መረዳት ያለብን ከሰይጣን ጋር ያለን ውግያ የማያቋርጥ ስለሆነ አንድ ጊዜ ስንወድቅ አንድ ጊዜ ስንነሳ የምንቀጥልበት አለም የፈተና ጊዜ ስለሆነ ደጋግመው በአንድ ኀጢአት መውደቅዎ እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም በእርስዎ ብቻ የደረሰ አድርገው ግን ተስፋ መቁረጥ የለቦትም። ነገር ግን ምን ጊዜም ከንስኀ በኋላ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ እና ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርትና ምክር በማግኘት በመንፈሳዊ አላማ መጽናት ያስፈልጋል። አሁንም ስለአንድ ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ወደ ንስኀ ህይወት እንዲቀርቡ እና በተደጋጋሚ ከተፈተኑበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነውና የጊዜ ቀጠሮ ሳያራዝሙ ያግኙን በማለት ይህን አጭር መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር ይሁን
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ