ስለ ንስሓ አባት ቁ.2
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ንስሓ አባት ቁ.2
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
ጠያቂያችን በጥልቀት መረዳት ያለብዎት የሚሰጡት ምላሾች የእያንዳንዱን ጠያቂ ጥያቄ መሰረት ያደረገ እና ያንን ምክር እና ትምህርት ለመስጠት የተገደዱበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲያነቡት የተሰጠው መልስም በዚያው አንፃር ስለሆነ መልሱ ያኔ በትክክል እና የቤተክርስቲያንን ቀኖና መሰረት ያደረገ መሆኑን ሊገነዘቡ ይችላሉ። በእኛ ማብራሪያ የተሰጠውን አንብበው የተሰጠውን ተረድተውት ከሆነ አንድ ክርስቲያን የንስሐ ህይወቱን ለመናዘዝ በንስሐ አባት ላይ እምነት ቢያጣ ወይም ምስጢር ይባክንብኛል ብሎ ከተጠራጠረ ያ ነገር ደግሞ በህይወቱ ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ ካሰበ ከተቻለ አባቱን በደንብ አነጋግሮ መተማመን ላይ ቢደርስ፤ ይህን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ በስርአቱ ተሰናብቶ ሌላ አባት መያዝ እንደሚኖርበት እንመክራለን። ሲጀመር በአባት እና በመንፈሳዊ ልጅ መካከል መተማመን እና ጥርጣሬ ካለ በእንዲህ አይነት የሰው ሰውኛ ይሉኝታ መቀጠል የሌለበት ህይወት ስለሆነ ሌላ አባት መያዝ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። በመሰረቱ እኛ የበተክርስቲያን አባቶች የንስኀ አባት ሆነን የምናገለግላቸውን ልጆቻችን ዘንድ እምነት ካጡብን በብዙ ነገር ከተጠረጠሩን እንኳንስ በነፍስ ሊድኑበት ቀርቶ በማንነታችን ላይም ሚዛን ላይ ስለጣሉን እንዲህ አይነት የአባት እና የልጅ ጉዞ ፈፅሞ መቀጠል የለበትም። ካስተካከልን ቅድሚያ ሰጥተን ማስተካከል ይገባል፤ ካላስተካከልን ደግሞ በስርዓት ተሰናብቶ መለያየት እንጂ፤ ስርአተ ቤተክርስቲያን ለመንቀፍ አይደለም። ስለዚህ ምንግዜም ለምን እንደተነገረና በምን ምክንያት እንደተፃፈ ማስተዋልና አጥብቆ መረዳት ያስፈልጋልና ቸኩሎ ከመንቀፍ ጠይቀው ለመረዳት እንዳሰቡ በማመን ይህን ምላሽ ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በሃይማኖቱ እና በምግባሩ ፅንቶ በትክክለኛው ክርስቲያናዊ ስነምግባር ተወስኖ የሚኖር ከሆነ እንደተባለውም ለሌላ መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ደግሞ ወደ ገዳማት እና ቅዱሳት መካናት ወይም ቦታዎች ሄዶ በዛ ቦታ ላገኛቸው አባት፥ አለኝ የሚለውን አነጋግሮ ወይም ኅጢአቱን ተናዞ አስፈላጊውን የንስሓ ህይወት መቀበል ይችላል የፈፀመውን ኀጢአት ሳይሰውር በመናዘዝ ንስሓ መግባት ይችላል። ምክንያቱም፤ ዋናው አላማ የተፈፀመውን በደልና ኀጢአት በንስሓ ለማስፋቅ በፍጹም ልባዊ እምነት በካህኑ አማካኝነት የተቀበልነውን የንስሃ ህይወት የኀጢያት ስርየት እንደሚያስገኝልን ማመን ብቻ ስለሆነ ነው። የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይደለም። በእርግጥም በሰራነው ኀጢአት አፍረን እና ተሸማቀን ክብራችን እንዳይነካ ለመሰወር እና ጥፋታችንን ለመደበቅ የምናደርገው ስጋዊ አስተሳሰብ ካለ ሰውን ብናሞኝ እግዚአብሔርን ማታለል ስለማንችል የዚህ አይነት አካሄድ ከእውነተኛ ክርስቲያን የማይጠበቅ ተግባር ነው። በ አባት እና በመንፈሳዊ ልጅ መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም። በደረስንበት መንፈሳዊ ቦታ ሁሉ እውነተኛ የቤተክርስቲያን አባቶችን በማነጋገር የዋለው ኀጢአታችን እንዳያድርብን ያደረውም እንዳይውልብን በጊዜውም ያለጊዜውም በአባቶች ጥበቃ የንስሓ ህይወት መኖር ከክርስቲያን የሚጠበቅ ምግባር ነው። ለጠያቂያችንም ሆነ ለሌላው ሁሉ ምክር የምንሰጠው ምናልባት የሰራነውን ኀጢአት ሁሉ ለመደበኛ የንስሓ አባታችን ለመናዘዝ የምናፍርበት ወይም በካህኑ ላይ እምነት ቢያጣ ወይም ምስጢር ይባክንብኛል ብሎ ከተጠራጠረ፤ ያ ነገር ደግሞ በህይወቱ ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ ካሰበ ከተቻለ አባቱን በደንብ አነጋግሮ መተማመን ላይ ቢደርስ፤ ይህን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ስርአታዊ መንገድ ተጠቅመን በመንፈሳዊ ጥበብና በትህትና ሁነን ተሰናብተን ፤ ሳንጠራጠር ከልብ የምናምናቸውን ሌላ አባት መርጠን መያዝ ይገባናል። ይህን የምንልበት ምክንያት ብዙዎቹ ምእመናን ለንስሓ አባቶቻቸው ግልፅ ሆነው የሰሩትን በደል ለመንገር የማይችሉበት ዋናው ምክንያት ምስጢር ይባክንብናል ብለው ከነኀጢአታቸው የሚኖሩ አሉና፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለአባቶቻቸው ግልፅ ለመሆን በአካባቢያቸው በማህበራዊ ህይወት ከመንፈሳዊ አባቶቻቸው ጋር አብረው ስለሚኖሩ የመተፋፈርም ነገር ስለሚያጋጥማቸው በዚህም ምክንያት የሚሳቀቁ ምእመናን እንዳሉ መረጃው ስላለን፤ ከዚህ ሁሉ ስጋት ነፃ ለመሆን የሚያምኑበትን እና የማይጠራጠሩበትን አባት መያዝ እንደሚገባቸው በአፅንዎት እንመክራለን። ለዘላለማዊ የነፍስ ድህነት ጉዳይ የምንሰራውና የምናደርገው ተጋድሎ በስጋዊ አመለካከት ወይም ምድራዊ በሆነ አሰራር የምንኖረው ሂደት ስላልሆነ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ጠየቂያችን ከዚህ ወጪ እኛ ያልተረዳነው ሃሳብ ካለ ወይም ተጨማሪ ምክር እና መንፈሳዊ አገልግሎት ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ጠያቂያችን ፤ ለፀሎት የምንገለገልባቸውን መፅሐፍት እና ቅዱሳት ስዕላትና ሌሎችን መንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ማንኛውንም ነገር በቤታችን ውስጥ የተለየ ቦታ አዘጋጅተን ማስቀመጥ ክርስቲያናዊ ስርአት ነው። እንጂ ስላገባን የሚከለከል ወይም ስላላገባን የሚፈቀድ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ባጠቃላይ ቅዱሳን ስእሎችን በምንበላበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንተኛበት ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ እንደ ጌጥ ማንጠልጠል በልማድ የመጣ እንጂ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ስርአት አይደለም።
ስለሆነም፤ የቦታ ችግር ከሌለብን ጠዋትም ማታም ራሳችንን ለይተን የዘወትር ፀሎታችንን የምናደርስበት የተለየ ቦታ ቢኖረን መልካም ነው። በቂ ስፍራ ከሌለን ደግሞ በዛችው በምንኖርባት ጎጇችን ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ለይተን በማስቀመጥ ከመኝታችን ተነስተን ተጣጥበን በዚያ መጸለይና መስገድ ይቻላል። ንፁኅ ባህሪይ ዘላለማዊ አምላክ በሆነው አምላክ ፊት ስንቀርብ ታላቅ አክብሮትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ወይም ንፅህናንናና ቅድስና ያስፈልገናል። ስእላቶቹ በቤተመቅደስ ውስጥ ከታቦታቱ ጋር አክብረን ስርአተ አምልኮት የምንፈፅምባቸው ስለሆኑ ብንችልና ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አባት አስባርከን በንፅህና ሆነን እንድንፀልይባቸው እንመክራለን።
በአጠቃላይ በቤታችን ውስጥ፦ መኝታ ቤት ፣ እቃ ቤት፣ ሳሎን ወይም መመገቢያ ስፍራ እያልን ከፋፍለን ተገቢውን እቃ በተገቢው ስፍራ እንደምናስቀምጥ ሁሉ ለፀሎት ወይም ለቅዱሳን ስዕላትና ሌሎች ለመንፈሳዊ ለአገልግሎት የሚውሉትን ራሱን የቻለ ቦታ ለይተን ብናስቀምጣቸው መልካም ነው። ምክንያቱም መኝታ ክፍላችንም ይሁን ሳሎን፥ በገቢር ባንፈጽመው በሐልዮና በነቢብ የምንፈጽመው ኀጢአት ስለሚኖር ከዚህ አንጻር መሆኑን ጠያቂያችን እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።