ትምህርት ስለ ተዋሕዶ
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ማን ናት?
በሰው ልጅ የማዳን ሥራ ያላት ድርሻ ምንድን ነው?
ክፍል አንድ ቁ.1
በቅድሚያ ‘ኦርቶ’ – ‘ዶክስ’ – ‘ተዋሕዶ‘ ‘ሃይማኖት‘ የሚለውን ቃል፥ በምስጢራዊ አተረጋጎሙ እና በነገረ መለኮት አስተምሮ የአገላለጽ ዘይቤና ስልት መሰረት በአጭሩ መረዳት ያስፈልጋል።
- “ኦርቶ ዶክስ” ፡- ማለት፤ ቃሉ የግሪክ ሲሆን፤ “ቀጥተኛ መንገድ (እውነተኛ ሃይማኖት)” ማለት ነው።
በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም በ325 ዓ.ም. 318 ሊቃውንት (የቤተክርስቲያን አባቶች) በኒቅያ ከተማ የሃይማኖት ጉባኤ (የሲኖዶስ ጉባኤ) በማድረግ፤ በወቅቱ አርዮስ የተባለው የክሕደት ሰው “ፈጣሪን፤ ፍጡር ነው”፤ በሚል የክሕደት ትምሕርት ብዙዎች እንዲክዱ አድርጓል። በመሆኑም ፤ የቤተክርስቲያናችን ታሪክ እንደሚመሰክረው፤ በዚህ ጉባኤ ሊቃውንትም፥ እውነተኛዋን ፣ ቀጥተኛዋን የተዋሕዶ ሃይማኖት ከ አርዮስ የክሕደት ሃይማኖትና፣ የክህደት ትምህርት ለመለየት “ኦርቶ ዶክስ (ቀጥተኛ መንገድ) ሃይማኖት” በማለት ሰይመውታል።
ነብዩ ኤርምያስም ስለ እውነተኛዋና ቀጥተኛዋ መንገድ (ሃይማኖት) ሲናገር “የቀደመችውን ቀጥተኛዋን መንገድ ጠይቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁ” ብሏል (ኤር 6፤16)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “እኔ መንገድ እውነት ሕይወት ነኝ” ብሏል (ዩሐ 14፤6)
ሐዋርያው ቅ/ጰውሎስም ለእብራውያን ወገኖቹ (ተከታዮቹ) በጻፈው መልእክቱ፦ “የመጀመሪያ እምነታችንን፥ እስከ መጨረሻው አጽንተን እንጠብቅ”፤ በማለት ስለቀደምት፣ እና ስለመጀመሪያዋ ቀጥተኛ ሃይማኖት አስተምሯል (ዕብ 3፤14)
2.“ተዋሕዶ” ማለት ቃሉ የግእዝ ቃል ነው። በ 431 ዓ.ም. 200 ሊቃነ ጰጰሳት (የቤተክርስቲያን አባቶች) በኤፌሶን ከተማ በሲኖዶሳዊ ጉባኤ ተሰብስበው ነበር። የመለኮት እና የስጋን መዋሐድ :- እግዚአብሔር ወልድ፥ በድንግል ማርያም ማሐፀን አድሮ፤ ከሥጋዋ ፥ ሥጋ ፤ ከነፍሷ ፥ ነፍስ፤ ነሥቶ ፤ በ ተወለደ ጊዜ ፤ “ቃልና ሥጋ፥ በተዋሕዶ ከበረ”። ንስጥሮስ የተባለው የክሕደት ሰው ግን ይህንን እውነተኛ እና ቀጥተኛ አስተምሮ በመቃወም፤ ስለ ‘የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ’ እያፋለሰ ያስተምርም ነበር። ስለሆነም ፥ ‘ኦርቶዶክስ’ በሚለው ቃል ላይ፤ ‘ተዋሕዶ’ የሚለውን ቃል ፥በመጨመር ፤ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት” ፥ ተብሎ እንዲጠራ ፥ሊቃነጳጳሳቱ ፥በዚህ ጉባኤ ፥ወስነዋል። በትምሕርትና በተግሣጽ ከክሕደቱ አልመለስም አሻፈረኝ በማለት የክሕደት አመጹን የቀጠለበትን ንስጥሮስንም ፤ አውግዘው ከቤተክርስትያን ለይተውታል።
3.“ሃይማኖት” ማለት ምንድን ነው? ብለው ጥይቄ ለሚያቀርቡ ወገኖች ሁሉ ፥ሊያውቁት የሚገባቸው ዋና ቁም ነገር ፥ ፈጣሪና ፍጡር፣ ጽድቅና ኩነኔ፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ሕይወትና ሞት፣ ገነትና ሲኦል፥ ተለይተው የሚታወቁበት ፥የሁላችንም የሕሊና መነፅር በ ፥ ‘ሃይማኖት’ ነው። የሰው ልጅ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ፤ በአይን የማይታየውን፣ በእጅ የማይዳሰሰውን፣ ረቂቁን አምላክ (ፈጣሪ)፣ ለማወቅ እና ለመድረስ የሚችልበት እውነተኛ መንገድ ሃይማኖት ነው።
ሃይማኖት ማለት እግዚአብሔርን የምናምንበትና የምናውቅበት ረቂቅ መንገድ ነው፤ ሲባል፦ በዓይነ ሥጋ ተመልክተን፣ በዕዝነ ሥጋ ሰምተን ፣ በልብ አስበን እና፣ በስሜት ሕዋሳታችን አድምጠን ፣ ልንመረምረውና ልንደርስበት የማይቻለን እና፤ ከእኛ ሥጋ ደካማነትና ከፀጋ ብቃታችን ማነሥ የተነሣ ነው። ስለዚህ ሩቅ እና ረቂቅ የሆነብንን መለኮታዊ ጥበብ፤ ይሆናል፥ እና ይደረጋል ብለን፤ በእምነት ለመቀበል ፥ የምንችልበት ምስጢር ስለሆነ ነው።
ሐዋርያው ቅ/ጰውሎስ ለእብራውያን ተከታዮቹ ስለ እምነት በተናገረበት መልእክቱ ላይ “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፤ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው” ፤ ሲል፤ ሃይማኖት፤ በዓይነ ሥጋ የማናየውን እግዚአብሔርና ረቂቅ ሥራውን የምናይበት፤ ልዩ ፀጋ መሆኑን ተናግሯል (ዕብ 11፤1)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በሰው ልጅ የማዳን ሥራ ያላት ድርሻ ምንድነው ስለሚለው ትምህርት በክፍል ሁለት ላይ እንዲደርሳችሁ እናደርጋለን።
ወገኖች፦ ዕዝነ ልቡናችሁን አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያብራላችሁ
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
የክፍል አንድ ቁ.2
በመሠረቱ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ስንል የእግዚአብሔርን አንድነት እና ሦስትነት፥ እና በስጋዊ አይናችን የማናየውን፣ በእጃችን የማንዳስሰዉን፣ እሮጠን የማንቀድመውን፣ ተመራምረን የማንደርስበት፥ አምላክ (ፈጣሪ ) አለ ብሎ ማመን ነው። በስነ ተፈጥሮ ህግ በኩልም ፥ሰማይ እና ምድርን፣ ጨለማን እና ብርሃንን፣ ቀኑንና ሌሊቱን ፣ሰውን እና መላእክትን፣ የዱር አራዊትን እና እንሰሳትን፣ አዝርእትን እና አትክልትን፣ በየብስ እና በባህር ውስጥ የሚሽከረከሩ፣ በደረታቸው የሚሳቡ፣ በክንፉቸው የሚበሩ ልዩ ልዩ ፍጥረታትን ፥ በአጠቃላይም 22 ስነፍጥረታትን ፥ ፈጥሮ ፥ ስነፍጥረታትን ሁሉ የሚመግብ እና፣ የሚመራ ፈጣሪ መሆኑን አምነን የተቀበልንበት ቀጥተኛ መንገድ ‘ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት’ ነው። ከሌሎቹ የእምነት አይነቶች የተለየ የሚያደርገውም ዋናው ሚስጢር ይህ ነዉ። ምክንያቱም እምነት ሁሉ ሃይማኖት አይደለም፤ ለምሳሌ ፦ በሠይጣን የሚያምኑ፣ በአምልኮ ጣኦት የሚያምኑ፣ በዛር መንፈስ የሚያምኑ፣ በእሳት፣ በወንዝ፣ በዛፍ፣ በድንጋይ፣ በልዩ ልዩ መንፈስ፣ የሚያመልኩ ሰዎች የሚያምኑትን እምነት ሁሉ ሃይማኖት አንለውም። እውነተኛውና ቀጥተኛው ሃይማኖት እግዚአብሔርን ብቻ አምላክ ፈጣሪ፣ መጋቢ ፥ብለን ፥ ለማመን ፥ የተሰጠን የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ነው።ታላቁ የሃይማኖት አባት ቅዱስ- ዩሐንስ አፈወርቅ፤ “ሃይማኖት የሁሉ ነገር መሠረት ናት፤ ሌሎቹ ግን ህንፃ እና ግንብ ወይም ደግሞ ጣራ አና ግድግዳ ናቸው” በማለት እንደ ህንፃ እና እንደ ግንብ ከሚቆጠሩት የምግባር እና የትሩፋት ስራዎች ሁሉ በፊት ሃይማኖት ተቀዳሚ እና መሠረት መሆንዋን አረጋግጦልናል። የአንድ ቤት መሠረት ህንፃውን ሁሉ አንደሚሸከም፤ እምነት ፣ ምግባር፣ አና ልዩ ልዩ በጎ ስራዎችን ሁሉ ሃይማኖት ትሸከማለች።ህንፃ ያለ መሠረት እንደማይቆም ምግባርም ያለ ሃይማኖት አይኖርም፤ ወይም ትርጉም የለውም። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ስራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” በማለት ሃይማኖት እና ምግባር ፤ ተለያይተው የማይነገሩ እንደ አንድ ሳንቲም ገፅታ መሆናቸውን በዚህ ተናግሯል።
ሰሞኑን በቴሌግራም ግሩፓችን የተነሱ ጥያቄዎች
“ከጴንጤዎች ጋር ንግግር አድርጌ ነበር ……” በማለት ጥያቄ ላቀረቡልን አባላችን የሚሰጠው መልስ ለቴሌግራም አባላቶቻችን ሁሉ ጥቅም ስለሚሰጥ መልሱን አንብባችሁ ትረዱት ዘንድ ከሁሉ በማስቀደም በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።
መልስ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ ሀገር ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር” (1 ቆሮ 2፥8) በማለት አይሁድ በመካከላቸው ሙት ሲያስነሳ፣ አይን ሲያበራ፣ ጎባጣ ሲያቃና፣ በሁለት አሳ እና በአምስት የገብስ እንጀራ በበረከቱ አብዝቶ ሲያጠግባቸው፣ አጋንንት ሲያወጣ፣ ባህር ላይ ሲራመድ፣ በመስቀል ላይ ሆኖ አባት ሆይ ይቅር በላቸው ብሎ ለጠላቶቹ ሳይቀር ታላቅ ፍቅሩን ሲገልጽ፣ በቃሉ ብቻ ሙታን ሲያስነሳ፣ አለቶችና መቃብሮች ሲታዘዙ፣ ሞትንና መቃብርን ረግጦ በ3 ቀን ሲነሳ በአጠቃላይ ከአምላክ በስተቀር ፍጡር የማይሰራውን ስራ ሲሰራ በፈጠጠው አይናቸው እየተመለከቱ እና ስለድንቅ ስራውም እየተገረሙበት አምላክ ነው ብለው እውነቱን ለመቀበል ስለተከለከሉ እና አይነልቦናቸው ስለታወረባቸው የክህደት አባታቸው ሰይጣን በዛው በክህደት አላማቸው እንዲፀኑ ስላደረጋቸው ለንስሓ ሳይበቁ እስከ መጨረሻ ድረስ ጠፍተው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል። ጠያቂያችን ከሁሉ በፊት መረዳት ያለብዎት የክህደት እና የምንፍቅና ሰዎች የመጀመሪያ ዋና አላማቸው የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም የሰውን አይምሮ በጥርጣሬ ማዕበል መበጥበጥ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኙትን ጥሬ ቃል በመለቃቀም ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን የነገረ መለኮት ቃል አንድም ቀን በጉባኤ ቤት ውለው ሳይማሩ ከእውቀት ነፃ በሆነ አነጋገር በትምህርተ ሃይማኖት ያልበሰለውን ክርስቲያን ግራ ሲያጋቡም መታየት የተለመደ ተልኳቸው ነው። በመሰረቱ እየሱስን አማላጅ አድርገው የሚናገሩበት ለስህተት ትምህርታቸው መነሻ የሚያደርጓቸው የመፅሐፍ ቅዱስ ቃላት (ሮሜ 8፥27) ላይ እና ቁጥር 34 ላይ ያለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ነው። ይሁን እንጂ እየሱስ ክርስቶስ ከባሕሪይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ እና ከባሕሪይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትና በሶሥትነቱ የሚቀደሰውን የሚሰለሰውን አምላክ፤ በደነዘዘ አይምሮ ድንቁርና በተሞላበት ድፍረት ፈራጁን አምላክ አማላጅ ነው (ይማልደን)፣ የለመኑትን ሁሉ የሚሰጠውን አምላክ ይለምናል ብሎ ማመን አምላክነቱን ካልተቀበሉት ከአይሁድ ጋር በእምነት አንድ መሆን ነው። ጥቅሱን በሚመለከት ግን የባሕሪ አምላክ እየሱስ ክርስቶስን ይማልዳል፣ ይለምናል፣ ያስታርቃል፣ ይፀልያል የሚሉትና የመሳሰሉት ቃላት በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲያጋጥሙን ማስተዋል ያለብን፦
1ኛ/ በመፅሐፍ ቅዱስ በተለያየ ዘመናት የቃላት ትርጉም ማሻሻያ በተደረገበት አጋጣሚ ሁሉ የቃላት መዛባት አጋጥሟል። በተለይ እየሱስ ክርስቶስን በሚመለከት በአዲስ ኪዳን ተፅፎ ስንመለከት ከአምላክነት ክብሩ ለማሳነስ እንደ ፍጡር አማላጅ አድርጎ በመግለፅ በብዙ ቦታ ላይ ተመዝግቦ እናገኛለን። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅሬታዋን ለመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር እና ለሚመለከተው ሁሉ ስታቀርብ ቆይታለች።
ከብዙ ጥረት በኋላም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትን በማሰባሰብ የመፅሐፍ ቅዱስ መሰረታዊ ቋንቋ ከሆነው ማለትም ከእብራይስጡ፣ ከአረብኛው፣ ከግእዙ፣ ከእንግሊዝኛው እና ከግሪክኛው ወዘተ ትርጉም ጋር በማነፃፀር ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን አዘጋጅታ በ 2000 ዓ.ም. በመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ እነዚህ በመናፍቃን ዘንድ ልዩ ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ቃላት ተስተካክለዋል። ለምሳሌ አማላጅ የሚለው ቃል ፈራጅ፣ ወይም ያማለዳል የሚለው ይፈርዳል በሚል ተተክቷል።
2ኛ/ የክርስቶስን ክብር በማሳነስ ምን ማትረፍ እንዳለባቸው አላማቸው ሁሉ በውል ግልፅ ያልሆነ የመናፍቃን ተልእኮ ሲታይ ሁሌ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን፣ ምእመናንን እና ካህናትን የሚያሳዝኑበትን እና ሃይማኖትን የሚሸረሽሩበትን መንገድ ስለሚፈልጉ ነው እንጂ፤ እየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በተዋሃደው ስጋ ከኅጢአት በስተቀር እንደሰውነቱ የሰውን ስራ እየሰራ እስከ መስቀል ሞት ድረስ መከራን የተቀበለ እንደ አምላክነቱ ደግሞ ፈጣሪነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ፈዋሽነቱን፣ መድኃኒትነቱን፣ ትንሳኤነቱን፣ አፅዳቂነቱን፣ ኮናኝነቱን፣ ይቅር ባይነቱን፣ መጋቢነቱን፣ ሰርቶ በክብር ወደሰማይ ማረጉን አይተናል።
3ኛ/ አስተዋይነትና እምነት የጎደላቸው ሰዎች ወደ ትክክለኛው አመለካከት ተመልሰው ማሰብ ያለባቸው በብሉይ ኪዳን እና በሀዲስ ኪዳን ውስጥ ስለሱ የባሕሪይ አምላክነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥቅሶች ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
– ቅዱስ ዩሐንስ በራእዩ “አትፍራ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ህያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ዮሐ ራዕይ 1፥17)
– ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስም “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ” በማለት ከእመቤታችን የነሳውን ስጋ አምላክነትን ተዋህዶአልና ከሰማይ የወረድኩ ሲል አምላክነቱን እንደሚያመለክት አንድ አካል አንድ ባሕሪይ መሆኑን ለማረጋገጥ የተናገረው ቃል ነው። (ዮሐ 6፥51)
– ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ “ከመጀመሪያውም የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን…” ብሎ ያለው ማንን ነው? ቀዳማዊ መለኮትን አይደለን? ቃል ከስጋ ጋር በተዋህዶ አንድ ባሕሪይ ካልሆነ በስተቀር ቅድመ አለም የነበረውን መለኮት እንዴት አየነው እንዴትስ ዳሰስነው አለ? የሚታይና የሚዳሰስ ግዙፍ የሆነ ነው እንጂ ረቂቅ የሆነ እንዴት ይታያል? እንዴትስ ይዳሰሳል? ቃል ከስጋ ጋር በተዋህዶ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ ካልሆነ በስተቀር (1ኛ ዮሐ 1፥1)
– “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስትያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ተብሎ በዚህ ኃይለቃል ላይ እየሱስ ክርስቶስ እራሱ እግዚአብሔር ተብሎ በግልጽ ተቀምጦ እናገኘዋለን (የሐዋ 20፥28)
– ነብዩ ዳዊት “እግዚአብዜር፦ አሁን እነሳለሁ ይላል መድኅኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ” በማለት ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ ከተነሳው ስለእየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ነው። መዝ 11፥8
– የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ዳዊት “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔርም በመለከት ድምፅ አረገ ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ” በማለት ያረገው እየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ እየሱስ ክርስቶስን ግን አምላክና እግዚአብሔር መባል የባሕርይ ስልጣኑ እንደሆነ በዚህ ቃል አረጋግጦልናል። (መዝ 46፥ 5 እና 6)
– አሁንም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔርም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ፈጥኖ ተነሳ፥ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኅያልም ሰው ተነሳ…” በማለት እየሱስ ክርስቶስ ከ3 ቀን በኋላ ከመቃብር የመነሳቱን በገለፀባት ሃይለቃል እግዚአብሔር ተነሳ ብሎ በትንቢት ተናግሮዋል (መዝ 67)
– ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም “ከሰማይ ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት ከሰማይ የወረደው የባህሪይ አምላክ እና ከድንግል ማርያም ተወልዶ የተዋሀደው ስጋ ደግሞ ፈራጅና አዳኝ መሆኑን ነግሮናል (ዮሐ 3፥13)
እንግዲህ ጠያቂያችን እነዚህን ሁሉ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለመረጃ ያህል እንዲጠቀሙባቸው አቀረብንልዎት እንጂ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ እየሱስ ክርስቶስ የሚነገሩ ጥቅሶች አምላክ እንደሆነ የሚያመለክቱ እንጂ ፍጡር እንደሆነ ወይ አማላጅ እንደሆነ የሚያመለክት በአንድም ቦታ አይገኝም። እንደ አስታራቂና እንደ አማላጅ አስመስለው በአንዳንድ ቦታ የተገለጹትም እንኳ በለበሰው ስጋ የፆመውን የፀለየውን በመስቀል ላይ ሆኖ ስለኛ የተገረፈውን አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለውን በአጠቃላይ በለበሰው ስጋ እንደሰውነቱ የፈፀመውን አገልግሎት እንጂ ከባሕሪይ አምላክነቱ የሚያሳንሰው አንዳችም ነገር አለመኖሩን በጥበብና በማስተዋል መረዳት ያስፈልግዎታል። አይምሮ መረበሽ መንፈስን መበጥበጥ የጥርጣሬ ማዕበል ውስጥ ማስገባት የሰይጣን እና የመናፍቃን ፀባይ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ደግሞ ባለበት ፀንቶ ይቆማል እንጂ የሚታወክና የሚበጠበጥ መንፈስ የለውም። በእርግጥም የእኛ አማላጅ ድንግል ማርያም ናት፣ የእኛ አማላጅ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን ፃድቃን፣ ቅዱሳን መላእክት ናቸው። እሱ ግን እየሱስ ክርስቶስ ወደ እሱ የሚቀርበውን ልመና እና ምልጃ ተቀብሎ እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥ አምላክ እንደሆነ ጠያቂያችች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችሁም ትረዱት ዘንድ ይሄን ማብራሪያ ሰጠን።
በተጨማሪም ጠየቂያችን የቅዱሳንን እና የመላዕክትን ምልጃን በሚመለከት የሚከተለውን ምላሽ ይመልከቱ፦
በኅጢአተኛ እና በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ የሚፀልዩ የሚያማልዱን እግዚአብሔር አስቀድሞ ያከበራቸው የመረጣቸው ያፀደቃቸው ለዘለአለም አገልጋዮች ያደረጋቸው በቃል ኪዳን ያፀናቸው ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላዕክት ናቸው።
ስለአማላጅነት እና ስለቅዱሳን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ወደፊት ሰፋ አድርገን እምንማማርበት እራሱን የቻለ ግዜ ቢኖርም እንኳን ከተጠየቀው ፍሬ ሃሳብ ጋር ለማዛመድ ያህል አንዳንድ ስለ ቅዱሳን ሰዎች እና ቅዱሳን መላእክት ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቂት ማስረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
1/ ቅዱሳን ሰዎች አማላጅነት
– የቅዱሳን አማላጅነት በሚመለከት “…አባታችን አብርሃም በሚስቱ በሳራ ላይ ነውር ስራ ሊሰራ በነበረው የጌራራ ንጉስ አቤሜሌክ ከእግዚአብሄር በመጣበት ቁጣ በደዌ በተመታ ጊዜ በማላውቀው ኅጢአት ተመትቻለሁና ብሎ ወደ ፈጣሪው ሲጮህ እግዚአብሔርም ከዚህ ደዌህ ትድን ዘንድ አብርሃም ይፀልይልህ ብሎታል” ኦሪ ዘፍ 20፥1-18
– ጻድቁ እዮብ ልዩ ልዩ ፈተና ደርሶበት በከፍተኛ ደዌ እየተሰቃየ ባለበት ግዜ እግዚአብሔር ኤለፋዝን በልዳዶስ እና ሶፋር የተባሉ ወዳጆቹ ሊጠይቁት መጥተው በማይሆን አነጋገር አሳዝነውት ስለነበረ እግዚአብሔር ተቆጣቸው። በደረሰባቸው ቁጣም በዛኑ ግዜ “…እዮብ ወዳጄ ስለ እናንተ ይፀልያል እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና” አላቸው። እዮብም ስለወዳጆቹ በፀለየ ግዜ የእዮብ ፀሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ምህረት እንዲያገኙ አድርጓል። እዮ42፥7-11
– ዳታንና አቤሮንም እንዲሁም ደቂቀ ቆሬ የተባሉ እብራውያን የእስራኤልን ማህበር አስተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ በምቀኝነት አመፅ ባስነሱባቸው ግዜ እግዚአብሔር በዚህ ኅጢአታቸውው ተቆጥቶ በቅፅበት ያጠፋቸው ዘንድ ሙሴን እና አሮንን ከጉባኤያቸው ፈቀቅ በሉ ባላቸው ግዜ ሙሴና አሮንም በፊቱ በግንባራቸው ተደፍተው አቤቱ አምላክ ሆይ አንተ የሰው ነፍስ አምላክ አይደለህምን ለምን አንድ ሰው ኅጢአት ሰራ ብለህ በማህበሩ ላይ ለምን ትቆጣለህ ብለው ለመኑት ጥፋተኞቹ ዳታንና አቤሮንም እና ደቂዘ ቆሪ ተለይተው ይጠፉ ዘንድ ይገባል ህዝቡን ግን አድናቸው ብለው በፀለዩት ፀሎት ህዝቡን ከኅጢአተኞቹ ለይተው አድነውታል። (ዘህልቅ 16፥20-36 እና ከ41-50)
– የእስራኤል መሀበር ሁሉ ተሰብስበው በመሄድ ነብዩ ኤርምያስን “ስለኛ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ፀልይልን” ብለው በጠየቁት ግዜ እሺ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እፀልይላችኋለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚሰጣችሁን መልስ እነግራችኋለሁ ብሏቸው እስከ 10 ቀን ድረስ ከፀለየላቸው በኋላ የእግዚአብሔር ነገር ወደ ኤርምያስ መጣ ህዝቡንም ሰብስቦ ፀሎታችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቀርብ ዘንድ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በዚች ምድር ብትቀመጡ እሰራችኋለው አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለው አልነቅላችሁም እናንተ በሰራችሁበት ኅጢአት ከደነገጣችሁበት እኔም ባደረግሁባችሁ ጥፋት እፀፀታለው ብሎ እግዚአብሔር በኤርምያስ ፀሎት ኅጢአታቸውን ይቅር እንዳለው እና እንዳዳናቸው የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክራል። (ኤር 42፥2-13)
– መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያቶችን ያላቸውን የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የሚቀበሏቸው እና በረከታቸው እንዲደርሳቸው ለሚጠሯቸው ያሳደረባችውን ፀጋ ሲናገር “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል ነብይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብይን ዋጋ ይወስዳል ፃድቅንም በፃድቅ ስም የሚቀበል የፃድቁን ዋጋ ይወስዳል ማንም ከነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም”(ማቴ 10፥40-44)
– ቅዱስ ያእቆብን በመልእክቱ የቅዱሳን ፀሎት በስራዋ እጅግ ታላቅ ሃይል እንደምታደርግ ይገልፃል። ያዕ 5፥14-19
– ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ የሚያማልዱት በፀሎታቸው እና በህይወታቸው ብቻ ሳይሆን በጥላቸውና በልብሳቸው ሳይቀር ተአምራትን እንደሚያደርጉት ስለዚህም “ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋ እና በወስካ ያኖሯቸው ነበር…ድውያንን እና በእርኩሳን መናፍስት የተሰቃዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር ሁሉም ይፈወሱ ነበር” ተብሎ ተፅፏልና
– እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳን ላይ የማማለድን እና የማስታረቅን ቃል ኪዳን እንዳስቀመጠ “የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው…በኛም ያማስታረቅ ቃል አሮረ እንግዲህ እግዚአብሔር በኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን” በማለት እንዴት እንደሚያማልዱ ሐዋርያው በስፋት ገልፀዋል (2ኛ ቆሮ 5፥18-21)
2/ የመላዕክት አማላጅነት
– ስለመላእክት አማላጅነት በሚመለከት መላኩ ቅዱስ ገብርኤል የእግዚአብሔር አገልጋይ የነበረው ካህኑ ዘካርያስን “ፀሎትህ ተሰምቶልሃል አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች ፤ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ” ባለው ግዜ ዘካርያስም “እኔ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም በእድሜዋ አጅታለች ይህን በምን አውቃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን ቃል ስለተጠራጠረ መልአኩም “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ እንድናገርህም ይችን የምስራችም እንድሰብክልህም ተልኬ ነበር አሁንም በግዜው የሚፈፀመውን ቃሌን ስላላመንክ ይህ ነገር እስከሚሆንልህ ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገር አትችልም አለው” ከዚህ በኋላ ዘካርያስ የመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ቃል እስከሚፈፀም ድረስ ዲዳ ሆኖ ቆይቷል። በመጨረሻ ግን መላኩ እንደተናገረው ኤልሳቤጥም ዮሐንስን ከወለደች በኋላ የተወለደው ህፃን ስም በእስራኤል ዘንድ ባለው ልማድ የልጅን ስም የሚሰይመው አባት ስለነበረ ዲዳ የሆነው አባቱ ዘካርያስን በጥቅሻ ሲጠይቁት ብራና ላይ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ፃፈ ያኔም አፉ ተከፈተ ምላሱም ተፈታ (ለሉቃ1፥13-20)
– ነብዩ ዳንኤል በባቢሎን አገር በምርኮ እያለ በመከራው ሰአት መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እንዴት እንደረዳው ሲናገር እነሆም ከዋናዎቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሲረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገስታት ጋር በዛ ተውሁት በማለት ተናግሯል” ዳን10፥13)
– እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ሳሉ የእግዚአብሔር መላእክ በምድረበዳ እንዴት እንደመራቸውና እንደጠበቃቸው ነብዩ ሙሴ ሲናገር “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀውትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እልካለው። ስሜም በእርሱ ላይ ስለሆነ ኅጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት…መላኬ በፊትህ ይሄዳልና በማለት ስለመላእክት ጠባቂነት እና አማላጅነት ተናግሯል (ዘፀ 23፥20-23)
– አሁንም ነብዩ ሙሴ እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤልን ድምፃቸውንና ለቅሷቸውን ተቀብሎ ሰምቶ ከግብፅ ባርነት ባወጣቸው ግዜ በመላእክት ጥበቃ እንደሚመሩ ሲናገር “ወደ እግዚአብሔር በጮህን ግዜ ድምፃችንን ሰማ መላኩንም ሰዶ ከግብፅ አወጣን” በማለት የመላዕክትን ተራዳይነት እና አማላጅነት አረጋግጧል (ዘሁ 20፥16)
– ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለውና” በማለት መላእክት ዘወትር የሰው ልጅን ለመጠበቅ የቆሙ እረኞች እንደሆኑ ማንም በእግዚአብሔር ሰው ላይ እጁን ቢያነሳ በፈጣሪ ዘንድ ዘወትር ስለሱ የሚቆሙ ጠባቂ ምስክሮች እንዳሉት አረጋግጧል።
ጠያቂያችን እና ባጠቃላይ የዮሐንስ ንስሓ ቴሌግራም አባሎቻችን በአጭር ጥያቄ ተነስተን ሰፋ ወዳለ የመልስ አሰጣጥ ትንታኔ ውስጥ የገባነው ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጠው የሃይማኖት ጉዳይ በመሆኑ ለሁላችሁም ግንዛቤ ይሆናችሁ ዘንድ እና ዘወትር በጥፋት እና በመሰናክል ከሚቆሙባችሁ መናፍቃን ዘንድ እንድትጠበቁ ስለሆነ ይህንን መልእክት ደጋግማችሁ በማንበብ መሰረታዊ እውቀት ታገኙበት ዘንድ አደራ እንላለን።
በተጨማሪም በድረገፃችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት በስፋት እየሰጠን ስለሆነ ይህን ሊንክ በመጫን አንብበው እንዲረዱ እንመክራለን።
እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያንን እና ምዕመናንን ከጠላት ዲያብሎስ ንጥቂያ ይጠብቅልን
ጸሎት ማለት፡-ጸለየ፣ለመነ፣ ጠየቀ አማለደ፣ ማለደ ካለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ጸሎት ማለት መለመን፤ መማለድ፤ ማመጸን፤ መጠየቅ፤ መናዘዝ፤ መታረቅ፤ ልሎችን ይቅር ማለት፤ ስለተደረገልንና ስለተሰጠን ልዩ ጸጋ ማመስገን ማለት ነው፡፡ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር፤ ምህረትንና ይቅርታን መጠየቅ፡፡ መሻት መለመን ማለት ነው፡፡ “ሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁ ምቱ ይከፈትላችኋል” ማቴ 7-7፡፡ ኃጢአትን ተረድቶ ይቅርታን መጠየቅ ማለት ነው፡፡ መዝ. 32- 5 ኃጢአቴን ላንተ አስታወቀሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፣ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ ፣ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውክልኝ፡፡ መዝ 66፡18
ጸሎት በሦስት ይከፈላል
1፡-ጸሎተ አኮቴት፡ ከሁሉም አስቀድሞ ስለተደረገልን ነገር በማመስገን የሚጀመር ጸሎት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-“ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን” ይልና ምክንኀያቱን ሲገልጥ ጠብቆናልና፥ አቅርቦናልና፥ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፥ እስከዚችም ሰዓት አድርሶናልና” ይላል፡፡ ይህ አይነቱ ጸሎጽ ጸሎተ አኰቴት ይባላል፡፡
2.፡-ጸሎተ ምህላ፡- ይህ ጸሎት ስለፈውሰ ሕሙማን፤ ስለ ሀገርና ስለነገሥታት፤ ስለ ጳጳሳት፣ ስለካህናት ዲያቆናት፣ ስምዕመናን ሕይወት፤ ስለቸነፈር፣ ሰለጦርነት፣ ስለረሀብ፣ ስለድርቅ ወይም አሁን እንደሆነብን አስጊ ነገር ሲሆን በማኅበር የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ ዘኁ.16-46-50፡፡ የምህላ ጸሎት ነገሠታት ከዙፋናቸው ወርደው ሙሽሮች ከጫጉላቸው፣ ከመጋረጃቸው ለምግብ የደረሱ ልጆች ከምግብ ለምግብ ያልደረሱ ከጡት ተከልክለው የሚጸልዩ ጸሎት ነው፡፡ ኢዩ.2-12-18፣ ዮና.3፥5
3.፡-ጸሎተ አስብቊዖት፡-ይህ ጸሎት አንድ ሰው ስለሚፈልገው ነገር ቦታ ለይቶ ሱባኤ ገብቶ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ይህ ጸሎት በተለይ ጣዕመ ጸጋን በቀመሱ በተባሕትዎ፣ በምናኔ በገዳም በሚኖሩ አበው ዘንድ የተለመደና የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ጠቅላላውን በቤተ ክርስቲያን የሚጸልዩ ጸሎታት ከላይ ከዘረዘርናቸው ሦስቱ የጸሎት ክፍሎች አይወጡም፡፡ ከጸሎተ አኰቴት ከጸሎተ ምህላ፣ ከጸሎተ አስተበቊዖት ይመደባሉ፡፡
እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት አሉ፡፡
ቅዱስ ዳዊት ስለ ጽድቅኽ ፍርድ በቀን ሰባት 7 ጊዜ አመሰግንኻለሁ ብሎ በቀን ሰባት 7 ጊዜ እንዳመሰገነ እኛም በቀን ውስጥ ሰባት 7 ጊዜ እራሳችንን ለእግዚአብሔር በማስገዛት ለጸሎት እንተጋለን፡፡ መዝ.118-164
ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት
- ነግኅ ወይም ማለዳ ጧት፡- አባታችን አዳም የተፈጠረበት ሰዓት ነው ዘፋ.1-26፤ ሌሊቱን ጠብቆ የማለዳውን ብርሃን እንድናይ ስለረዳንም እናመሰግነዋለን፡፡ ፤ አምላካችን በጲላጦስ ፊት ቆሞ የተመረመረበት ሰዓት ነውና በዚህ ሰዓት ለጸሎት በፊቱ እንቆማለን፡፡ ማቴ.27-1
- ሠለስት ወይም ሦስት ሰዓት፡- እናታችን ሔዋን የተፈጠረችበት ሰዓት ነው፡፡ ዘፍ.2-21-24 ፤ ዳንኤል በዚህ ሰዓት መሰኮቶቹን ወደ ኢየሩሳሌም አንፃር በመክፈት ይጸልይ ነበር፡፡ ዳን 6-10 ፤እመቤታችን የቅዱስ ገብርኤልን ብስራት የሰማችበት እና አምላካችንን የጸነሰችበት ሰዓት ነው፡፡ሉቃ.1-26፤ጌታችን በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት ሰዓት ነው፡፡ማቴ.27-26፤በጽርሃ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ሰዓት ነውና በነዚህ ምክንያቶች በ3 ሰዓት እግዚአብሔርን በጸሎት እናመሰግነዋለን፡፡
- ቀትር ወይም ስድስት ሰዓት፡- አዳም እፀ በለስ በልቶ ከክብሩ የተዋረደበት ሰዓት ነውና ወደ ፈተና እንዳንገባ እንጸልያለን፡፡ ዘፍ.3-6፤አምላካችን ክርስቶስ ክብር ይግባውና በዕለት አርብ በመስቀል ላይ የተሰቀለው በ6 ሰዓት ነው፡፡ ዮሐ.19-14
- 4.ተሰዓት ወይም ዘጠኝ ሰዓት፡- በዚህ ሰዓት ቅዱሳን መላዕክት የሰውልጅ የጸለየውን፣ ጸሎት፣ ልመና፣ እጣን፣ የሠራውን ሥራ ሁሉ የሚያሳርጉበት ሰዓት ነው፡፡ የሐዋ.10-3፤ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡበት የነበረበት ሰዓት ነው፡፡ የሐዋ.3-1፤አምላካችን በዚህች ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከክብር ሥጋው የለየበት ሰዓት ነው፡፡
- ሠርክ ወይም ዐሥራ አንድ ሰዓት፡- እኛ ምግባር ቱሩፋት ሰርተን ዋጋችንን ከአምላካችን የምንቀበልበት ሰዓት ነው፡፡ ማቴ.20÷1-16፤ ዳዊት እንዳለ ‹‹ጸሎቴን በፊትህ እንደዕጣን ተቀበልልኝ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን›› መዝ.140-2 በማለት ይህች ሰዓት ታላቅ የጸሎት ሰዓት መሆኗን ያስተምረናል፡፡፤ኤልያስ በዚህች ሰዓት የሰዋው መሰዋት እና ያቀረበው ጸሎት በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ተወዶለታል፡፡ 1ኛ.ነገ 18-36፤መድኃኒታችን ክርስቶስ እኛን ከሞት እና ከሲኦል ያወጣ ዘንድ በሥጋው ወደ ከርሠ መቃብር በነፍሱ ደግሞ ወደ ሲኦል የወረደበት ሰዓት ነው፡፡ ማቴ.27-45-61
- ንዋም ወይም የመኝታ ሰዓት፡-በዚህ ሰዓት ቀኑን ሙሉ ስንወጣ ስንወርድ የጠበቀንን አምላክ አመሰግነን፤ ዳግመኛም የሌሊቱን ሰዓት ባርኮ የሰላም እንቅልፍ ይሰጠን ዘንድ ለጸሎት እንቆማለን፡፡፤ አምላካችን በጌቴሴማኒ ሥርዓተ-ጸሎትን ያስተማረበት ሰዓት ነው፡፡ ማቴ.26-36
- መንፈቀ ሌሊት ወይም እኩለ ሌሊት፡- አምላካችን የተወለደበት፣የተጠመቀበት፣ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣበት፤ ዳግመኛም ይህንን ዓለም ለማሳለፍ የሚመጣበት ሰዓት ነውና-ሉቃ.2-7-8፤3÷21.ዮሐ.20÷1፤ማቴ.25÷6፤ማር.13÷35 በዚህም ምክንያት አምላካችን ለእኛ የሆነውን እና ያደረገውን ሁሉ በማስተዋልና በማሰብ በየሰአቱ እንጸልያለን፡፡