ስለ ዝሙት

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ዝሙት

ከዝሙት ጠንቅ ለመውጣት ምን ማድረግ ይገባናል?
(የማንቂያ ደወል)

በእርግጠኝነት፥ የሁሉም ሰው ፆር ዝሙት ነው! በዘመናችን ሰዎች ለቢዝነስ ብለው በፊልምና በኢንተርኔት የሚያሰራጩት የዝሙት ሃሳብ የሰውን አይነ ህሊና አሳውሮ በምኞት እያቃጠለ ከትንሽ እስከ ትልቁ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ገብተውበት ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመቀየር ሌላ የኀጢአቱ ተጋሪ ፈልገው ሲዘሙቱ ማየት የተለመደ ሆኗል። በአጠቃላይ ሰይጣን አለምን ወደ አንድ አጠቃሎ በእጁ ካስገባበት ዋነኛው የኀጢአት አይነት ዝሙት ነው። እኛም እንደተወደደ ነገር ደጋግመን ስሙን የመጥራታችን ምክንያት ዝሙት ከባድ የኀጢአት አይነት መሆኑን በመፅሐፍ ቅዱስ ማስረጃነት ተደግፈን ማሳወቅና በግልፅ ማስተማር የግድ ሆኖ ከማግኘታችን አንፃር እንደሆነ በቅድሚያ እንድትረዱት ያስፈልጋል።

ይህን ስንል ግን በኀጢአቱ የወደቁትን ሰዎች እያጥላላን በሸክም ላይ ሸክም እየደራረብንባቸውና እያሸማቀቅናቸው ከእኛ ተገልለው ርቀው እንዲኖሩ ወደ ፈጣሪ ለመመለስ እድል እንደሌላቸው ዝም ብለን ነገር ልናከብድ ሳይሆን ፤ ሰይጣን በነሱ ላይ የወጋውን የማደንዘዛ መርፌ ነቅለን ከእንቅልፋቸው ባነው ከዚህ የዝሙት ኀጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመላቀቅ እየወደቁም፣ እየተነሱም እንዲታገሉና ከእጁ እንዲወጡ ለማስቻል ታስቦ የተሰጠ ትምህርት ነው። በአንፃሩ ደግሞ ወደዚህ ኀጢአት ላልገቡ ሰዎች በቅዱስ መፅሐፍ እንደተፃፈ “ከዝሙት ሽሹ” (1ቆሮ 6፥18) ተብሏልና እግዚአብሔር ከዚህ ጉድ እንዲጠብቃቸውና እነሱም የዝሙትን ኀጢአት አስከፊነት አስቀድመው ተረድተው ከዚህ ጠንቅ እንዲታቀቡ ለማስገንዘብ ታስቦ የቀረበ ትምህርት ነው።

ስለዚህ የዚህ ትምህርት አላማ በዋናነት በዚህ ፆር ውስጥ የወደቁትን ከሰይጣን እጅ ፈልቅቀን ለማውጣት ስለሆነ በቅድሚያ ዝሙት ምን ማለት እንደሆነና ከፍተኛ የኀጢአት አይነት ስለመሆኑ፣ የዝሙት አይነቶች ምን ምን እንደሆኑና የዚህ ዘመን ዋነኛ የዝሙት አይነትስ የትኛው ነው፣ በዝሙት መንፈስ ለመውደቅ መንስኤው ምንድነው የሚሉትን ካብራራን በኋላ ከዝሙት ጠንቅ ለመውጣት ደግሞ ምን ማድረግ እንደሚገባን እንመለከታለን። በመጨረሻም መፅሐፍ ቅዱስ ስለ ዝሙት ምን እንደሚል አንድ በአንድ እያነሳን እናብራራለንና ሁላችሁም በማስተዋል ሆናችሁ እስከመጨረሻው ታነቡት ዘንድ በአፅንኦት እንመክራለን።

ስለ ዝሙት ትምህርት

ግብረ ዝሙት​

ከዝሙት ጠንቅ ለመውጣት ምን ማድረግ ይገባናል? (የማንቂያ ደወል)
ከዚህ ስር ያሉትን ጥያቄዎች ቢጫኑ መልሳቸውን ያገኛሉ

ከባል ጋር ከሚስት ጋር ያልሆነ፣ በህግ ያልተፈቀደ በጋብቻ ያልተመሰረተ ከጋብቻ ውጪ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ሴሰኝነት፣ አመንዝራነት፣ እና ቅንዝረኝነት ዝሙት ይባላል። ነገር ግን ባልና ሚስት በህጋዊ መንገድ ተጋብተው የሚፈፅሙት የሩካቤ ስጋ በህግ የተደገፈ የህግ ሩካቤ ነው እንጂ ዝሙት አይባልም።

እግዚአብሔር ከሚፀየፈው፣ ከሚጠላውና ከሚያዝንብን ኀጢአት ዋናውና አንዱ ዝሙት ነው። ለዚህም ነው ጠላታችን ሰይጣን ዲያቢሎስ እኛን ከፈጣሪ ጋር ለማጣላትና የተቀደሰውን ልጅነታችንን የሚያሳጣንን ይህን የተጠላ ኀጢአት እያለማመደ ሳንወድ በግድ ወጥመዱ ውስጥ አስገብቶ የግብሩ ፈፃሚ እና አስፈፃሚ የሚያደርገን። በመሆኑም የዝሙት ዋና ተግባር ህገ እግዚአብሔርን በህገ ዲያብሎስ መለወጥ ሲሆን ይህም ዘለዓለማዊ ህይወታችንን በዘላለማዊ ሞት መለወጥ ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። በማህበራዊ ህይወት ትላንት አብሮን ሆኖ ዛሬ በሞት ከጎናችን ስለሌለ እንደዚያኛው ሰው ሲሞቱና ስንቀብራቸው ስላላየን ነው እንጂ በዝሙት ኀጢአት የወደቁ በቁማቸው ሞተዋል።

ሰው ሁሉ በኀጢአት ሲተባበር የሚያመጣው ጥፋት በራሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገርም በምድርም ላይ ጥፋት ያመጣል። እንደምናውቀው በኖህ ዘመን የነበሩ የሰዎች ኀጢአት ዋናው ዝሙትና መዳራት፣ ሴሰኝነትና አመንዝራነት ነበር። ህግ እና ሃይ ባይ የሌላቸው መደዴዎች ልጓም ሳይኖራቸው እንደፈለጋቸው የሚዘሉ በአጠቃላይ ከሰው አይምሮ የወጣ ሰውኛቸውን ሁሉ የጣሉ ስለነበር ምድርና በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተቃጣው መቅሰፍትና ቁጣ በተላከው ቅጣት ጠፍተዋል። ይህንን መቅሰፍት ያመጣው በዋናነት የዝሙት ኀጢአት ነው።

የዝሙት አይነቶችን ከነቅጣታቸው በሙሴ ላይ አድሮ ነግሮናል። (ኦሪ ዘሌ 20፥7-22)

1. በስጋዊ ፍትወት እና ስሜት እየተቃጠሉ ዘርን በምድር ላይ ማፍሰስ፤ (ኦሪ ዘፍ 38፥6-11)
2. ከምድር ከድንጋይ ጋር መዘሞት፤ (ኦሪ ዘሌ 20፥15)
3. ከዕፅዋት ጋር መዘሞት ፣ ከእንስሳት ጋር መዘሞት፤ (ኦሪ ዘሌ 20፥15)
4. በስጋ ተዛምዶ ከሚቀርቡን ዘመዶቻችን ጋር መዘሞት፤ (ኦሪ ዘሌ 18፥6 እና 17)
5. ወንድ ከወንድ ጋር መዘሞት፤ (ኦሪ ዘፍ 19፥9) (መሳፍ 19፥22)
6. ሴት ከሴት ጋር መዘሞት፤ (ኦሪ ዘሌ 20፥15)
7. ከስርዓተ ጋብቻ ውጪ የሆነና በጋብቻ ያልተመሰረተ ሴትና ወንድ የሚፈፅሙት ዝሙት (ኦሪ 23፥17)
8. ከራስ ጋር መዘሞት፤ (1ቆሮ 6፥18)
9. በሚጠጣ፣ በፍቅረነዋይ፣ በሌሎቹም ስጋዊ ሃሳቦች መዘሞት፤ (1ኛ ቆሮ6፥13)
10. በአምልኮ ጣኦት መዘሞት፤ (የሐ 21፥25)
11. በመብል እየጎመጁ ወይም ወንድምን ሃብቱን ንብረቱንና ጉልበቱን ሚስቱን እየተመኙ መጎምጀትም ዝሙት ነው።

ለመሆኑ በዚህ ዘመን ከትንሽ እስከ ትልቁ እጅግ በከፍተኛ ቁጥር እየተፈተነበት ያለው የዝሙት አይነት የትኛው ነው? በአፍታ በደቂቃ ለሚፈተኑበት ሴሰኝነት ስሜት መታገስ አቅቷቸው በዝሙት ሃሳብ በመቃጠል ወንዱም ሴቱም የቤታቸውን በር ዘግተው ብቻቸውን ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው እየፈተኑ ዘራቸውን በማፍሰስ ስሜታቸውን ለማርካት የሚፈፅሙት ከራስ ጋር መዘሞት ይባላል። ይህ አይነት ዝሙት ከተፈጥሮአዊ ስርአት ውጭ ስለሆነ አካላዊ የዝሙት ግብረ ስጋ ከሚፈፅሙትም ሰዎች የበለጠ ኀጢአት ነው። እንዲያውም የሰዶማዊነትም ሃሳብ ከዚህ ይጀምራል በዚህም ከሰዶማዊነት መንፈስ ጋር ይያያዛል ማለት ነው። ከራስ ጋር ዝሙት፣ ወንድ ከወንድ ጋር፥ ሴት ከሴት ጋር፤ እንደው ንግግሩ ራሱ አይቀፍም?! እንዲህ አይነቱ ኀጢአት በዘመናችን በሰይጣን መንፈስ የሚመሩ ሰወች ያመጡት አዲስ የኀጢአት ፍልስፍና ሲሆን ብዙዎች ገና ከልጅነታቸው ከእንቡጥነታቸው ጀምሮ በማወቅም ባለማወቅም ጀምረውት እየተፈተኑበትና ተባብረው እየጠፉበት ያለ የዘመኑ የዝሙት አይነት ነው።


የሚገርመው ነገር እራሳችን ለፈቃደ ስጋችን የምናገኘውን ጊዜያዊ ጥቅምና ስሜት በማሰብ በድፍረት ለፈፀምነው ኀጢአት ሁሉ ከፈፀምነው በኋላ ብድግ ብለን ምክንያት የምንሰጠው ሰይጣን አሳስቶኝ ነው በማለት ሲሆን፤ ተጠያቂና ባለቤት የምናደርገው ሰይጣን ግን አንድ ቀንም ኀላፊነቱን ወስዶልን አያውቅም። በእርግጥም ሰይጣን የእኛን ፍላጎት አይቶ እንደ ደካማ ጎናችን ለያንዳንዳችን የምንወድቅበትን ክፋት የሆነውን ስራ ሁሉ እያሸከመ የግብሩ ፈፃሚና አስፈፃሚ ያደርገናል።

 

የዝሙት መንስኤዎች እና የዝሙት ዋዜማዎች በአብዛኛው ህጋዊ ከሆነ ጋብቻ ውጪ ያሉ የሴት እና የወንድ መሳሳም፣ በስሜት እየተቃጠሉ መተሻሸት ፣ አብሮ መተኛት፣ ስሜትን የሚያነሳሱ እርኩስ ፊልም እና ኢንተርኔት ማየት ወይም ማንበብ፣ ስለዚህ ጉዳይ አብዝቶ ማውራት፣ ህሊናን ለዚህ ቦታ መስጠት እና ከዚህ ጋር በተያያዙ ተግባሮች የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋው ወደ ዝሙት ሃሳብ ሲያመራበት ሃሳቡን በድብብቆሽ ሲለማመድ ቆይቶ የሴሰኝነት መንፈስ አይሎበት ራሱን መቆጣጠር ሲያቅተው ወደዋናው የዝሙት ኀጢአት ይወድቃል ማለት ነው።

ይህ በመፅሐፍ ቅዱስ ማስረጃነት የተደገፈ የእግዚአብሔርን ድምፅ የያዘ የማንቂያ ደወል ትምህርት ስለ ሁሉም የዝሙት አይነት አስከፊነት እና በማህበራዊ ህይወታችን እና በነፍሳችን ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ከላይ በዘረዘርነው መሰረት በአንድም በሌላም ተገልፇልናልና በዚህ ትምህርት ብቻ እንኳን እያንዳንዳችን ካንቀላፉንበት የኀጢአት አዚም ባነን እርም ብለን ለመውጣት የቆረጥን መሆን ይጠበቅብናል። በመሰረቱ ብዙዎቻችን የመውጫው በሩ ተዘግቶብን እንዴት እንውጣ የምንለው፥ ውስጣዊ ፍላጎቱ የእኛ ስለሆነና ጊዜያዊም ቢሆን ደስታን እርካታን ያመጣል ብለን ስለምናስብ፣ ከመብል በላይ ትልቅ ቦታ ሰጥተነው ስለምንንገበገበለትና ብንተወው የምንኖር ስለማይመስለን ነው እንጂ፥ በአላማ ቆራጥ ሆነን ስሜታችንን ገዝተን ይህን የዝሙት ስራ ሳንሰራው ብንቀርኮ አንሞትም ወይም አንቆስልም። ሰውኮ በዚህ ምድር ለአላማው ቆርጦ ከፀና እንኳንስ ለደቂቃ መጥቶ ለሚያልፈው ሥጋዊ ስሜቱ ይቅርና የወገኑንና የሀገሩን ክብር ለማስከበር ወስኖ ጦርሜዳ ከሰው በሚተኮስ ጥይት ለመሞት ደረቱንና ግንባሩን ሰጥቶ ስንት የጀግንነት ስራ ይሰራየለም እንዴ?! ታዲያ እኛ ተፈለጡ ተቆረጡ የሚለን ሳይኖር፥ የዝሙት መንፈስ ከማይዳሰሰው እና ከማይታየው ውስጣዊ የአስተሳሰብ ምኞታችን ጋር በረቂቅ ከሚዋጋን የእርኩስ መንፈስ ውጊያ እንደሆነ ሚስጥሩ በግልፅ ከተነገረንና ካወቅን፤ በአባቶች መሪነትና ከእግዚአብሔር በተሰጠን ረቂቅ በሆነ መንፈሳዊ መሳሪያ ታግለን ማሸነፍ እንዴት ያቅተናል? ክርስቲያኖች፤ ለሰይጣን ቦታ አትስጡት! የመንፈሳዊ ህይወታችን እድገት፣ የኀጢአታችን አይነት፣ እና የጥፋታችን መጠን ከአንዳችን የአንዳችን ቢለያይም ዋናው ነገር በምንችለው አቅም ደረጃ በደረጃ መንፈሳዊ ህይወታችንን ለማሳደግ ሳናቋርጥ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ ሐሳቦች ለመፈፀም ብንተጋ እግዚአብሔርም የእኛን የመከላከል አቅምና ፀጋችንን ሁሉ ያሳድገዋልና በረቂቅ የሚዋን የዝሙት መንፈስም በእርግጠኝነት ተማሮና ተቃጥሎ ትግሉን አቋርጦ ከእኛ ይለያል። (ኤፌ 6፥11-18)

ንስሐ

በዝሙት ኀጢአት ለወደቅን ሰዎች አንደኛና አይነተኛ መፍትሄው፥ ንስሐ መግባት ነው። ንስሐ የበደለውን እንዳልበደለ ዘማዊውን እንደ ድንግል ታደርጋለች። ልክ በስጋ ደዌ ስንያዝ ወደ ሃኪም ቤት በመሄድ የህክምና አገልግሎትና ክትትል አድርገን እንደምንድን ሁሉ፤ የዝሙት መንፈስ ገዳይነቱ በስጋ ብቻ ሳይሆን በነፍሳችንም ሞትን የሚያስከትል አስከፊ ደዌ ስለሆነ ከዚህ ለመውጣት፦

1ኛ/ እንደመፃጉ ለመዳን ፈቃደኛ የሆነ ልቦና እና ስለፈፀምነው የዝሙት ኀጢአት ከልብ የሆነ ፀፀት ሊኖረን ይገባል። ለእውነተኛ ንስሐ መሰረቱና ዋነኛው መስፈርቱ ህሊናችን የሰራነውን ጥፋት አምኖ ስንፀፀት ነው።

2ኛ/ ለነፍሳችን ሃኪም የሆነ እንደደዌያችን አይነትና መጠን ቀኖና የተባለውን መድኀኒት እየሰጠ በየጊዜው ክትትል አድርጎ ሙሉ ለሙሉ እስከምንፈወስ ተመላልሰን የሚያክመንና የሚመክረን ፀጋውና ትሩፋቱ የበዛለት ጥሩ የንስሐ አባት ያስፈልገናል። “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ ፲፮᎓፲፱) ስለዚህ ንስሓ መግባትም ሆነ ንስሐ አባት መያዝ የሰው ትዕዛዝ ሳይሆን የፈጣሪ መመሪያ ነው።

3ኛ/ እግዚአብሔር ያዘዘልንን ንስሐ የተባለውን ፍቱን መድሐኒት በንስኀ አባታችን አማካኝነት ወስድን የሚሰጡንን ቀኖና በአግባቡ መፈፀም አለብን፤ ለዘመናት ከሰራነው ኅጢአት ይልቅ ንስኀ ገብተን በተወሰነ የቀኖና ግዜ የሰራናት ፅድቅ ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ጥፋት አስፍቃ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት እንድንበቃ ታደርጋለችና።

4ኛ/ ንስኀ ገብተን ቀኖናችንን ከፈፀምን በኋላ ከዘለዓለም ሞት ወደ ዘለዓለም ህይወት ተሸጋግረናልና ደግመን በኀጢአቱ እንዳንወድቅ እንደ ንስኀ ሳናቋርጥ የምንወስዳቸው አማራጭ የሌላቸው የፈውስ መድሃኒቶች ወይም መንፈሳዊ ትጥቃችን ደግሞ አብዝቶ መፆም ፣ አብዝቶ መፀለይ፣ አብዝቶ መስገድ ናቸው። እያንዳንዱ ሰፊ የሆነ ትምህርት የሚሰጥበት ቢሆንም እንኳን ነገር ባበዛን ቁጥርም ዋናውን ግንዛቤ ሳናስጨብጥ እንዳንቀር በማሰብ በአጭሩ እንደሚከተለው ገልጸናልና በንስኀ አባቶቻችን መሪነትና መካሪነት በፅናትና በእምነት ሆነን ሁሉንም በአንድ ጊዜ ሳይሆን እንደ መንፈሳዊ እውቀታችን መጠን ደረጃ በደረጃ መፈፀም አለብን። ዋናው ነገር የእያንዳንዳችን የዝሙት አይነት ስለሚለያይ በየግላችን የምንፈተንበት የዝሙት ሃሳብ በምን ምክንያት እየመጣ እንደሚዋጋን በተከታታይ ከሚያጋጥሙን ፈተና አንፃር በራሳችን የህሊና ዳኝነት መዝነን መንስኤውን ካገኘነው መፍትሔው ግልፅ ስለሚሆንልን በዚህ አግባብ እንጠቀምባቸዋለን ማለት ነው።

5ኛ/ ፀሎትን በሚመለከት ጠዋትም ማታም የምንፀልየው ከዘወትር ፀሎትና ውዳሴ ማርያም ውጪ ጊዜ የምናገኝ ከሆነ ፥ እንደ መንፈሳዊ እወቀት ደረጃችን መጠን በግላችን በቋሚነት የምንፀልየው ፀሎት ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊትን፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ ወንጌለ ዮሐንስን፣ ድርሳናትን፣ መዝገበ ፀሎት እና ስለ ንስኀ ትምህርት የሚሰጡ መፃህፍትን በተጨመሪ ማንበብና መፀለይ ይቻላል።

6ኛ/ ስግደትን በሚመለከት፦ አብዝቶ በመስገድም እርኩስ መንፈስን መዋጋት ይቻላል። ስንሰግድ በፊታችን መስቀል ወይም ቅዱሳን ስዕላት ወይም ወንጌል አድርገን በትዕምርተ መስቀል እያማተብን ጉልበታችንን እና ግንባራችንን መሬት እያስነካን መስገድ ይገባል።

7ኛ/ በምንተኛበት አካባቢ በክፍላችንም በቅፅረ ቤታችንም በመኝታ ዙሪያችንም ሁሉ አጋንንት እንዳይቀርቡ እንደ አጥር ሆኖ የሚከላከል ጋሻና መከታ ሊሆን የሚችለውን መስቀሉን ብንቀስረው ወይም ብንከበው ያን ጊዜ አጋንንት ስለሚያቃጥላቸው ሃይላቸው ስለሚደክምና ወደዚህ የተቀደሰ ቦታ መቅረብም የእነሱ አቅም ስለማይፈቅድ ጨርሶ ይጠፋሉ። ምክንያቱም ፀሎቱ አጥር ነው፣ መስቀሉም አጥር ነው፣ በዙሪያችን የምንፀልይባቸው ቅዱሳን መፃህፍት እና መዝገበ ፀሎቱ አጥር ናቸው።

8ኛ/ በዋናነት ግን ክርስቲያኖች ፤ ተስፋ መቁረጥ የለብንም! ተስፋ አይቆረጥም!!! ጠላት ዲያብሎስ ከእጁ ልናመልጠው ስንል እረፍት በማሳጣት እንደገና ወደኋላ ለመጎተት የሚያደርገው ጥረት ይኖራልና ፈተና ሲገጥማችሁ በአንድ ጊዜ ተስፋ በመቁረጥ ቶሎ ብላችሁ ከነበራችሁበት አላማ ወደኋላ ለመውደቅ ማመንታትና መጠራጠር የለባችሁም። እንዲያውም ጠላቴን እርኩስ መንፈስን እውነትም አሸንፌዋለሁ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከእኔ ጋር መሆኑን በዚህ አውቄዋለሁ ብላችሁ እግዚአብሔር ጋሻዬና መከታዬ ነው ማንም አያሸንፈኝም የሚለውን መንፈሳዊ ምስጋና ወይም ዝማሬ ምስክርነት እየሰጣችሁ በመንፈስእንድትጠነክሩ ያስፈልጋል እንጂ ተስፋ ቆርጠን መቅረት ወይም ከዚህ በላይ መዘግየት የለብንም። እግዚአብሔር በነብዩ ላይ አድሮ እንደነገረን የኀጢአተኛውን ሞት አልወድም ፥ ወደ እኔ መመለሱን ነው እንጂ ይላል። ስለዚህ ከነኀጢአታችን ሆነን እግዚአብሔር ይታገሰናል። ኀጢአታችንን ሊያዘገይ ወይም የኀጢአት እድሜያችንን ሊያራዝም አይደለም የሚታገሰን፤ ነገር ግን ምንም እንኳን የገባንበትን የዝሙት ኀጢአት ቢጠላውም እስከመጨረሻ ድረስ እድሜ ሰጥቶ ቃሉን ሰምተን አንድ ቀን በንስኀ እንድንመለስ የሚጠብቀን አምላክ ከሆነ እንዴት ተስፋ እንቆርጣለን? ስለዚህ እሱ አግዞን በዚህ የማንቂያ ደወል ከዚህ ከጠላሁት ህይወቴ እንድወጣ ዛሬ የጠራኝ አምላክ የሱ ፈቃድ ይሁንልን ብለን ከኀጢአቱ ለመውጣት ተጋድሏችንን ጀምረን እስከመጨረሻው ማስቀጠል አለብን ማለት ነው። ስለዚህ ከላይ የጠቀስናቸውን መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ሁሉ ደረጃ በደረጃ በማሳደግ አንድ ጊዜ ሳይሳካልን ብንወድቅ እንኳን ደጋግመንም ቢሆን በንስኀ እየተነሳን በየጊዜው በምናደርገው ፅኑ ተጋድሎ እና የንስኀ አባታችን በሚሰጡን ተከታታይ ትምህርትና ምክር ተግባራዊ ስናደርግ ኀጢአቱን ለመጥላትና ለመጠየፍ የምንወስነው ልባዊ ውሳኔ በእውነት በሂደት ስለሚያድግ መንፈሱ ራሱ ተቃጥሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእኛ ይለያል ማለት ነው።

9ኛ/ ሌሎች ተጨማሪ አጋዝ መንፈሳዊ ምክሮች፦ ቤተክርስቲያን መሳለም፣ ማስቀደስ፣ ፀበል መረጨት በራሱ በፈጣሪ በእግዚአብሔር ስም እና በቅዱሳን ስም ወደፈለቀው ፀበል ቦታ በመሄድ በአባቶች እጅ መጠመቅ ፣ በመስቀል መባረክ፣ እምነቱን መቀባት ፀበሉን መጠጣት ለተወሰነ ሱባኤ ግዜ ከአባቶች ጋር በመመካከር ከስጋዊ ህይወት እርቆ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተወስኖ መቆየት፤ የተለያዩ የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን በማንበብ እንዲሁም በድምፅ አና በምስል የተዘጋጁ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፉ ትምህርቶች፣ መዝሙሮች መከታተልን ማዘውተር። በዚህ ጊዜ በዛ ሰው ላይ ያደረው እርኩስ መንፈስ ከሱ ባህሪ የሚስማማውን ነገርስለሚያጣ እና በእግዚአብሔር ቃል ስለሚቃጠል ከታማሚው ሰው ተለይቶ ይሄዳል። ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እና ቅዱሳን አባቶቻችን በዚህ ታላቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል ስለተሰጣቸው ልዩ ልዩ ተአምራትን ማድረግ የተለመደ ስራቸው ስለሆነ አስፈላጊውን አገልግሎት ማግኘትና በፀሎታቸው መረዳት አለብን።

በአጠቃላይ የዮሐንስ ንስሐ ድረገፅ አባላቶች ሁላችሁም፤ አብዝቶ በመናገር፣ አብዝቶ በመማርም ፣ አብዝቶ በማስተማርም፣ አብዝቶ በማንበብም በማነብነብም የሚለካ ፅድቅ እና የተሰበረ ልቦናም ሊኖር አይችልም። ሰው ልብ ማለት ያለበት የሚገባው ማስተዋልም ያለበት ብዙ በተማርን ቁጥር ፣ ብዙ በሰራን ቁጥር፣ ብዙ በአመንን ቁጥር ፅድቃችን የሚበዛ መሆኑ እውነት ቢሆንም እንኳን ለማያምኑና ለማይመለሱት ፣ ልብ ለማይሉ ሰዎች ግን ስፍር ቁጥር የሌለውን ምክራችንን ትምህርታችን ብናፈስባቸውም አንድ ግዜ ላለመመለስና ሰው ላለመሆን ከዚሁ ከጠላት የግብር አባታቸው ከሰይጣን ጋር ተጣብቀው እድሜያቸውን በከንቱ የሚያጠፉ ስለሆነ ላይመለሱበት ላይመከሩበት ይችላሉ። ነገር ግን ለሚመከርና የእግዚአብሔር ድምፅ ሰምቶ ለሚመለስ ሰው ከሆነ ግን ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ ተነግሮት የሚሰማ ልቦና የሚያስተውል አይምሮ አለውና ከዘለዓለም ሞት ወደ ዘለአለም ህይወት እንደሚሸጋገር እርግጠኞች ነን። ለምሳሌ በዚህ በእኛ አገልግሎት በምናስተላልፈው ትምህርትና ምክር እንኳን እግዚአብሔር ረድቶን ብዙ ሰዎች ይሄን ከመሰለ ኀጢአት ወጥተው ወደቅዱስ ቁርባን መአረግ እንደደረሱ ነግረውናል፤ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይህም የሆነው የእመቤታችን አማላጅነትዋ የፃድቃን ሰማእታት ተራዳይነታቸው ምልጃቸውና ፀሎታቸው ስለረዳን ነው። ስለዚህ ይህን የማንቂያ ደወል የሰማችሁ ወገኖች ሁሉ፤ የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ ወደ ይቅር ባይ አምላክ በንስኀ ተመለሱ በማለት ምክራችንን እንለግሳለን። ኅጢአት ሠርቶ የንስሐ ሕክምና ያላገኘ ሰው በነፍሱ ምውት ነው። (ሉቃ 15፥24) በመጨረሻም የበለጠ ትምህርትና መንፈሳዊ ምክር እንድንሰጥዎ ከፈለጉ፣ ንስኀ አባት ከሌለዎት በእኛ በኩል ለአባትነት የመረጥናቸው የቤተክርስቲያን አባቶች በሃይማኖታቸውና በእውቀታቸው የታመነባቸው አባቶች ስላሉ አነጋግረው ንስኀዎን መፈፀም እንዲችሉ እንዲሁም ንስሐ አባት በማድረግ መያዝ ወይም ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎተ ማግኘት እንዲችሉ እናደርጋለን ።

በመሰረቱ ዝሙት የተጠየፈ ከመኀበረሰቡ የሚያገለንና ከክብራችን የሚያወርደን እንደሆነ መፅሐፍ ቅዱስ ሳይነግረን አስተማሪ ቁሞ ሳያስተምረን አይምሯችን እራሱ ህግ ነውና በተሰጠን ህገ ልቦና ክፉውንና በጎውን መለየት እንችላለን። ነገር ግን እኛ ለስጋዊ ፍላጎታችን ተገዚ ስለሆንን ከተጠያቂነት ለመውጣት ከኀጢአት ያመለጥን እየመሰለን ጥፋታችንን ላለመቀበል በአይነደረቅነት መፅሐፍ ቅዱስ ስለ ዝሙት የጻፈውን ካልጠቀሳችሁልኝ የሚል ምክንያት የሚያቀርቡ ወገኖች ስላሉ ስለዝሙት ከየመፅሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን ሁሉ ዘርዝረን ማስተማር ስላስፈለገን ፣ ቅዱሳት መፃህፍትም በዝሙት ሃሳብ አስከፊነት ላይ እንዴት ተባብረው እንደሚገልፁት ራሱም ባለቤቱም ስለ ዝሙት ህግ አድርጎ የሰራልንን ሁሉ ማወቅ ስለሚገባን ከላይ ከተዘረዘሩት የዝሙት አይነቶች ጋር በማነፃፀር እያንዳንዱን ቃል እንደሚከተለው ጠቅሰን እናብራራለን።

1. “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።” (ዕብ 13፥4) በህጋዊ መንገድ ተጋብተው የሚኖሩ ባልና ሚስት ሩካቤ ስጋ በእግዚአብሔር የታወቀ የተፈቀደና የተረዳ የህግ ሩካቤ ነው። ከዚህ ውጪ የሆነ ግን ዝሙት ይሆናል ማለት ነው።

2. እኔ ግንእላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው።” (ማቴ19፤9) ከዚህ ቃል የምነረዳው ያለበቂ ምክንያት ሌላ አማራጭ በመፈለግ ቃል ኪዳን በማፍረስ ባሏን የምትፈታ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ራሱም አመንዝራ ነው እሷንም አመንዝራ አድርጓታል ወይም አድርጋቸዋለች፤ እንዲሁም ሌላ ከሱጋርም ከሷጋርም የሚያመነዝሩ የኀጢአት ጓደኛ ጨምረዋል ማለት ነውና፤ በዚህ አይነት የዝሙት ኀጢአት ጥፋቱን ወደ ብዙ ሰዎች ማዳረስ በመቻሉ የኀጢአቱን ደረጃና ተጠያቂነቱንም እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ማለት ነው።

3. “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽመው ይገደሉ።” (ኦሪ ዘሌ 20 ከቁ. 10ጀምሮ) በዚህ ቃል የምንማረው ከስርዓተ ጋብቻ ውጪ የሆነ በጋብቻ ያልተመሰረተ ሴትና ወንድ የሚፈፅሙት የዝሙት አይነትን ነው። አመንዝራውም አመንዝራይቱም እስከሞት ይቀጡ ይላል።

4. “ከእስራኤል ሴቶች ልጆች ሴትጋለሞታ አትገኝ፥ ከእስራኤልም ወንዶች ልጆች ወንድ ጋለሞታ አይገኝ።” (ኦሪ 23፥17) ይህ ለብዙ የዝሙት ኀሳብ የሚጋለጡ ጋለሞታዎች ወይም በህገ ጋብቻ ተጠምዶ በዚህ ልጓም ውስጥ ላለመግባት በልቅነት በስድነት በመደዴነት እንዲሁ እንደፈለጉ ሲራገጡ የሚኖሩ ሰዎች በህገ እግዚአብሔር አይፈቀድላቸውምና በዚህ አትውደቁ በማለት ይሄ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ያስተምረናል።

5. “ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” (1ኛ ቆሮ7፥2) ይህ አንዱ ከዝሙት ለመራቅ መፍትሄ ነው።

6. “ ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ …” (ኦሪ ዘሌ 18፤6-18) የህ የጋብቻም ይሁን የስጋ ዝምድና ግንኙነት ካላቸው የዝሙት ሃሳብ እንዳይፈፅም ይህን ያደረገ እስከ ሞት ድረስ ቅጣት የሚያስከትል እንደሆነ ልንረዳው ያስፈልጋል።

7. “ማናቸውም ሰው ከእንስሳ ጋር ቢገናኝ ፈጽሞ ይገደል፤ እንስሳይቱንም ግደሉአት።” (ዘሌ 20 ከቁ. 15ጀምሮ)” እንግዲህ ይታያችሁ ሰው ብሶበት ከቤት እንስሳትም ጋር ዝሙት ይፈፅማል ማለት ነው። በተለይ ሰለጠን በሚሉት በፈረንጁ አለም ውስጥ የሚታይ አሳፋሪ አሰቃቂ በሃይማኖት ቋንቋ ለመግለፅና ለመናገር ሁሉ የሚያሳቅቀን ቢሆንም መፅሐፍ ቅዱስ ግን የሰው ልጅ በምድር መኖር እስከሚያቆምበት ጊዜ ድረስ የሚሰራውን የዝሙት ኀጢአት አይነት በግልፅ ተናግሯል። አእግዚአብሔር ከዚህ ክፉ ነገር ይጠብቀን ይሰውረን እንጂ አንድ ጊዜ ለዲያብሎስ እጅ ከሰጠን በኋላ የሱ ተገዚ ከሆንን በኋላ ያኔ በምክር በትምህርት ሳይሆን ቀጥታ ሰይጣን በደማችን ነው ያንን ክፉ መንፈስ የሚያሳድርብን። እንስሳትን እስከመገናኘት መድረስ ማለት እንዲሁ በጤናማ አይምሯችን ስናስበው ምን ያህል ያስቀይማል፣ ምን ያህል የሰውን ከንቱነት ያሳያል?

8. “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋውጭ ነው፤ዝሙትን የሚሠራግ-ን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።” በቀጥታ እኛው ላይ የምንሰራው ወደን ራሳችንን ለሞት አሳልፈን የምንሰጥበት የኀጢአት አይነት ነው (1ቆሮ 6፥18)

9. “አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር። ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው” (ኦሪ ዘፍ 38፥6-11) ይህ ከላይ ዘርን በምድር ላይ ማፍሰስ በማለት የገለፅነው የዝሙት አይነት ነው።

10. “በግልሙትናዋምበመቅለልዋምምድሪቱረከሰች፤እርስዋምከድንጋይናከግንድጋርአመነዘረች” (ኤር 3፥9 -10) ነበዩ ኤርሚያስ በዚህ በትንቢቱ ከምድር ጋር መዘሞትንና የዝሙትን አፀያፊነትና ኀጢአተኝነት ገልፇል።

11. “ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት። በዚህ ሌሊት ወደቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው” (ኦሪ ዘፍ 19፥9) (መሳፍ 19፥22) ይህ ቃል ወንድ ከወንድ ጋር መዘሞት ወይም ግበረሰዶማዊነትን ያመለክታል።

12. “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።” (1ኛ ቆሮ 6፥9-11)

13. “በምድርምውስጥሰዶማውያንነበሩ፤ከእስራኤልምልጆችፊትእግዚአብሔርያሳደዳቸውንየአሕዛብንርኵሰትሁሉያደርጉነበር።” (1ኛ ነገስት14፥24)የዚህን የአይን አውጣነት የዝሙት ኀጢአት አይነት የሚፈፀምበት የግብሩ መገለጫሰዶማዊነት ነው። በእብደት በመደዴነት በራሳቸው ፍትወተ ስጋ እየተቃጠሉ ለሞትና ለኀጢአት እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ፣ ሰውነታቸውን በፍትወተ ስጋ የሚያቃጥሉ ብቻ ሳይሆኑ የሚያሰቃዩ ናቸው።

14. “ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብይወጣልና።” (ማቴ 15፥19) በዚህ ቃል አመንዝራነት እና ዝሙት መንገዳቸው አንድ ሆኖ በአፈፃፀም የሚለያዩ ቢሆንም ሁለቱም ተጠቅሰዋል። ለሁለቱም ሃሳብ መነሻውና መፀነሻው ልብ ነው።

15. “ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤” (ማር 7፥22) እነዚህን የኀጢአት አይነቶችን ሲዘረዝር ዝሙትን በመጀመሪያ ጠቅሶ እግዚአብሔር የሚጠላቸው ክፉ ነገሮች ሲሆኑ ሰውን በነፍስ የሚያጠፉ የሰውን ቅድስና እና ክብር የሚያጎድፉ እንደሆኑ ነግሮናል።

16. “እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት።” (ዮሐ 8፤41)በዝሙት መፀነስ ኀጢአት ባይሆንም እንኳን የአመፃ ልጅ መባልን እንዳያመጣ ለልጆቹም ስድብና ነቀፌታ እንዳያመጣባቸው በማለት ከዝሙት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስተምራል።

17. “ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ፤ ጤና ይስጣችሁ።” (የሐ15፤28-29) ይህም ቃል ዝሙት የኀጢአት አይነት መሆኑንና በነፍስም በስጋም ቅጣት ቁጣ የሚያስከትል መሆኑን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋሪያት ላይ አደሮ ተናገረን ማለት ነው።

18. “አምነው ስለነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል። (የሐ 21፥25) ይህ ቃል ከላይም እንደጠቀስነው በአምልኮ ጣኦት መዘሞት፣ በሚበላ በሚጠጣ መጎምጀትን ይመለከታል።

19. “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን” (ሮሜ 13፥13)

20. “በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና።” (1ኛቆሮ5፤1) ቅዱስ ውሎስ ሃይማኖት የሌላቸውና ያልተማሩ የማያደርጉትን እንኳን በእናንተ እንደምታደርጉት ደርሼበታለው እያለ በግብር እነሱን መምሰላችሁ አሳዝኖኛል እያለ እየወቀሳቸው ነው።ሰው በእውነቱም በግብሩ ከሰይጣን ይከፋልን እስከምንል ሰዎች አካላቸውን በስለት ቀደው ወይም በስተው ያደረጉ ያህል ነው በስሜት በተቃጠሉ ቁጥር የሚያደርጉትን አያውቁም፤ በማለት ቅዱስ ጵውሎስ እስከመጨረሻው ዘመን የሚሰሩት ኀጢአት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልፆለት ይሄን ተናግሯል ማለት ነው።

21. “መብልለሆድነው፥ሆድምለመብልነው፤እግዚአብሔርግንይህንምያንምያጠፋቸዋል።ሥጋግንለጌታነውእንጂለዝሙትአይደለም፤ጌታምለሥጋነው” (1ኛ ቆሮ6፥13)

22. “እንደገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ።” (2ኛ ቆሮ12፥21) የዝሙትና መዳራትን ኀጢአትን ዋና አድርጎ ገልፆ ስለሰሩት ኀጢአት ተፀፅተው ንስኀ ስላልገቡት ሰዎች እጅግ በጣም ማዘኑን ገልፆልናል።

23. ገላ 5፥19-20 “የሥጋሥራምየተገለጠነው፤ እርሱምዝሙት፥ርኵሰት፥ መዳራት፥” ሌሎቹንም ኀጢአት አብሮ ከዚሁ ጋር ዘርዝሮ የዝሙትና መዳራትን ኀጢአትን ግንበዋናነትገልፇል።

24. “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ” (ኤፌ 5፥3) ቅዱስ ጵውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በፃፈው መልእክቱ ዝሙትና ርኩሰት እነዚህን የኀጢአት አይነቶች ምሎ እርም ብሎ ትቶ ለፅድቅ አገልግሎት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የቆመ ሰው እንደገና ተመልሶ የወደቀ የረከሰ ስራ ተመልሶ የሚሰራ የወደቀ የረከሰና የሚያሳፍር ስለሆነ፥ ከቶ እንደዚህ ያለው በእናንተ ዘንድ እንዳይሰማ ብሏል።

25. “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትን ምማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው።” (ቆላ 3፥5)

26. “ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ” (1ኛ ተሰ 4፥4-5)

27. “እንዲሁም እንደእነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።” (ይሁ 1፥7) ይህ ቃል ለሀገርም፣ ለሀገር መሪዎቹም፣ ለባለሃብታሞችም፣ ለአዋቂዎችም፣ ለህዝቦችም፣ ለእያንዳንዳችንም በምሳሌ የተገለጠ የዮሐንስ ራህይ ነው። የንስሐ ጊዜ ተሰጥቶን ፈቃደኛ አለመሆናችን አንድ ቀን ወደ ፀፀት ተመልሰን በንስሐ ያለመንቃታችን የሚያሳይ ነው (ዮሐ ራዕ 2፥21)

28. “አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቍጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች እያለ ተከተለው።”፣ …. “ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች” (ዮሐራዕ 14፥8፣ ዮሐራዕ 17፥4 (ዮሐራዕ 14፥8፣ ዮሐራዕ 17፥4) ከዚህ ቃል እንደምንረዳው በሰው በአይን እንደሚታይ ክብር ያሸበረቀችው የወርቅ መጎናፀፍያ የለበሰችው በእግርዋ በራስዋ በአልማዝ ወርቅ ያጌጠችና የተሸለመች በምድር ላይ ከፍ ከፍ ያለችው በሴት አንቀፅ የተገለጠችው በእጅዋ ግን የሚያስጠይፍ የዝሙትን እርኩሰት የሞላበት የወርቅ ፅዋ ይዛ በመንፈሳዊ ህይወትዋ ባዶ የሆነች በዚህም ከባድ ኀጢአት ቅጣት የሚጠብቃት መሆኑን ነው ዮሐንስ በራዕዩ የሚገልፅልን ።

29. “አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ።” ይሄ ለሀገርም ለሰውም ይሰጣል ተባብረን ሁላችንም እንደ ሀገር ስንዘሙት አስደንጋጭ የሆነ ፍርድና መቅሰፍት ያመጣል ማለት ነው (ዮሐ ራዕ 18፥3)

30. ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወይስ አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግስት እንዳይወርሱ አታውቁምን፥ አትሳቱ ሴሰኛዎች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሰሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በእየሱስክርስሠቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ታድሳችኋል ፀድቃችኋል” በማለት የዝሙትን አይነት እና ዝሙት ከፍተኛ ኅጢአት መሆኑን ከሌሎቹ የኀጢአት አይነቶች አስቀድሞ ከዘረዘረ በኋላ በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሔርን በመፍራት በንስሐ ብስንመለስ እንዴት ከኅጢአታችን እድፍ እንደምንታጠብና እንደምንቀደስ እንደምንፀድቅም በግልፅ አስተምሮናል። (ቀኛቆረ 6፥9፤10)

31. “በዚህም በዘማዊና በኅጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔ እና በቃሌ የሚያፍር የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላዕክት ጋር በመጣ ጊዜ በርሱ ያፍርበታል” (ማር 8፥37) በማለት የዝሙትን የኅጢአት ምክንያት ከአምልኮ ባዕድ ጋር በማያያዝ ተናግሮናል።

እንግዲህ ወገኖች እነዚህን ሁሉ የዝሙት ኀጢአት አይነቶች በመጠኑም ቢሆን ከዚህ የሚሰፉና ከዚህ የሚበዙ ቢሆኑም እንኳን እኛ ከዝሙት ጠንቅ ለመላቀቅና ለመለየት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከወሰንን ሊያስተምሩን የሚችሉ ናቸው ብለን ያሰብናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች በዚህ አይነት ማየት ችለናልና በዚህ ኀጢአት የወደቅን እንድንወጣ ያልገባነው ደግሞ ራሳችንን እንድንጠብቅ የሚያስችል ትምህርት ነው። ከዚህ ኀጢአት ለመውጣት ወይም ለመከላከል መንፈሳዊ ትጥቃችን ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ከዚህ በፊት ባለው ክፍል በደንብ እንደመከርንበት ተስፋ በማድረግ ይህን ስለ ዝሙት የተሰጠ የማንቂያ ደወል ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ

በህይወታችን በመንፈሳዊ ፀጋችን ልናድግና ልንበረታ እንደሚገባ እየመከርን፤ ለተጨማሪ ትምህርትና ምክር ከፈለጋችሁ በቴሌግራም ገፃችን ወይም በውስጥ መስመር አግኝታችሁ ልትጠይቁን እንደምትችሉ እናስታውቃለን።

አነሳስቶ ላስጨመረን አስጀምሮ ላስፈፀመን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁን

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ

👉ጥያቄ፦ ሰላም ለናንተ ይሁን!አንድ ጥያቄ አለኝ! ስለ #ሩካቤ_ስርዓት #ቅድስት_ቤተክርስቲያን ምን ትላለች?አስተምህሮዋ እንዴት ነው?ከይቅርታ ጋር አብራሩልኝ!

መልስ፦ ጠያቂያችን፤  ያቀረቡት ጥያቄ በደንብ ግልፅ ባይሆንልንም፤ ነገር ግን እርስዎ እንዳሉትም የሩካቤ ስጋ ግንኙነትን በሚመለከት ከቤተክርስቲያናችን አስተምሮ አንፃር የአንድ ኦርቶዶክሳዊ ከርስቲያን የስነ ምግባር ጉዞ እና መንፈሳዊ ህይወቱ ምን መምሰል እንዳለበት የተቀመጠ ህግና ስርዓት አለ። ይህንንም ስርዓት ማንም ሰው ሊያውቀው ስለሚገባ ተያያዥ ትምህርት እና ለሁሉም ጠቃሚ  የሆነ ምክር እንድንሰጥበት ጥያቄውን እንደ  መነሻ ሃሳብ በማድረግ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውልን ያሰተላለፍናቸውን ምላሾች በአንድነት አድርገን እንደሚከተለው ልከናልና  አንብበው እንዲረዱት እንመክራለን።

በመሰረቱ የሰው ልጅ ልዩ ክቡር ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን ክብሩን አብዝቶ ወይም አሳንሶ  እራሱን እንዳያዋርድ እና በስጋው ፍትወተስጋ ነግሶበት በኀጢአት እንዳይወድቅ፣ ብቸኝነትም እንዳይሰማው ለክብሩ የምትመጥነውንና ፥ የሚመጥናትን አካላዊ ተፈጥሮ ራሱ በመምረጥ፤ ማለትም አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ፥ ወይም አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት ፈጥሮ  ባል እና ሚስት በመሆን አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው በክብር አብረው እንዲኖሩና በዚህ ህግ ኑሩ  ብሎ የወሰነልን የፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር አሳምሮ እና በስነተፈጥሮ የምንመራበትን ህግም አዘጋጅቶልናል።

ከነዚህም አንዱ ጠያቂያችን ያነሱት የሥጋ ሩካቤ (የግብረ ስጋ ግንኙነት) ሲሆን፤ ይህ የሰው ልጅ ራሱን የሚመስለውን ዘር ለመተካት በወንድና ሴት መካከል የሚደረገው የሩካቤ ስጋ ግንኙነት ወደ ዘር ማስገኘት ለሁለታቸውም የተሰጣቸው ዘርን የመተካት ፀጋ ነው። በመሆኑም ከሁሉ በፊት በቅዱስ ጋብቻ መወሰንና ልጅ ወልዶ መተካት የእግዚአብሔር በረከትና ስጦታ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።

ትክክለኛ በሆነ ክርስቲያናዊ ስነምግባር በቃል ኪዳን የፀኑ እጮኞች ጋብቻቸውን መፈጸም ያለባቸው በቤተክርስቲያን ስርአት መሆን አንዳለበት የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። በዚህም የእግዚአብሔር በረከትና ጠብቆት ይበዛላቸዋል የሚያፈሩትም ትውልድ ይባረካል ማለት ነው። ሁለቱ ማለትም ሴት እና ወንዱ ድንግልናቸውን ጠብቀው ከቆዩ በኋላ በስርዓተ ተክሊል፥ ቤተክርስቲያን አዋጅ ብላ ልጆቿን ለክብር ለመዓረግ የምታበቃበት ስርዓተ ምስጢረ ተክሊል ይባላል። ስለ ድንግልናቸው ክብር ምድራዊ የምናየው ዋጋ ሁሉ ሰማያዊ ዋጋ በኋላ ያሰጣልና። ይህ የአክሊል ሽልማት የሰማይ አክሊል ምሳሌ ነው። 

በመሆኑም ለትዳር የተጫጩ ወንድና ሴት ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት የሚያደርጉት የግብረስጋ ሩካቤ እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ስንመለከተው በዝሙት መንፈስ የተፈፀመ ግንኙነት እንጂ በስርአተ ቤተክርስቲያን የተፈቀደ አይደለና  እንደ ዝሙት ይቆጠራል።

ከዚህ አንጻር ከጋብቻ በፊት ከሁለት አንዳቸው ወይም ድንግልናዋን ያጣች ሴት ወይም ያጣ  ወንድ በንስኀ አባታቸው የንስኀ ቀኖና እና ቀጣይ ምክር እና ትምህርት ይሰጣቸውና ንስኀ ገብተው ቀኖና ጨርሶው ስጋ ደሙን በመቀበል ጋብቻ መፈፀም ይችላሉ። ስረዓተ ተክሊል ግን አይፈጸምላቸውም።

ሌላው፤  በአለማዊ ጋብቻ መጋባት ቤተክርስቲያን ስርዓት አይደለም ። በዓለማዊ ጋብቻ መጋባት የአሕዛብ እንጂ የክርስቲያን ጋብቻ አይደለም። ፀጋ መንፈስ ቅዱስን ያርቃል። ስለዚህ በኋላ ቆርባለሁ አሁን በዓለማዊ ጋብቻ ልጋባ ማለት የክርስቲያን ስነምግባር ውጪ የሆነ እና የዝሙት ሃሳብ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ሳያውቁና ሳይማሩ ቀርተው ወይም እንደተባለውም ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ጋብቻ ከገቡ ግን  የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ኀጢአት የመውደቁ ሁኔታ የደካማ ስጋ ባህሪ ቢሆንም በሰራነው ኀጢአት ተጸጽተን አሁንም ወደ ንስኀ ህይወት ተመልሰን ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል የሚከለክለን ህግ የለም። ባወቅንና በተረዳን መጠን ለስርዓቱ በመታዛችን  እኛ የማናውቀው  እግዚአብሔር ሊሰጠን የሚችለው ፀጋ አለ ፤ ነገር ግን ያ ፀጋ እንደ አለማዊ ንብረታችን ለፈለግነው ጊዜ በቀጠሮ አቆይተን ልንጠቀም የማንችለው ሰማያዊና ረቂቅ ጸጋ በመሆኑ ፤ እንደ ህጉ የመኖር ውሳኔያችንን ምክንያት እየደረደርን በዘገየን መጠን ጨርሶ የምናጣው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የጊዜ ቀጠሮ ሳናራዝም ራሳችንን በንፅህና በቅድስና ስንጠብቅና በቤተክርስቲያን ስርዓት ጸንተን በቅዱስ ቁርባን በመኖር ስንተጋ እኛ የማናውቀው እግዚአብሔር የሚያውቀውን ፀጋ በጊዜው እንጎናፀፋለን፣ ትዳራችንም፣ ልጆቻችንም ኑሮዋችንም ይባረካል ማለት ነው።

ስለዚህ ማንኛውም ሃይማኖት ያለው ክርስቲያን ለአካለ መጠን ወይም ለአካለ ጋብቻ ደርሶ እና በሃይማኖት ስርዓትና በባህላዊ ትውውቅና በስርዓተ በጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት ማንኛውንም የአካለ ስጋ ሩካቤ ማድረግ ፈፅሞ ክልክል ነው። ለዚህም ነው በቅዱስ ጳውሎስ ስጋችሁን ለመግዛት ፍላጎታችሁን ለማሸነፍ ካልቻላችሁ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላል ያለው። በዚህ መሰረት ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ክርስቲያን የስጋውን ፍላጎት መግዛትና መቆጣጠር በማይችልበት የእድሜ ደረጃ ሲደርስ በሃይማኖት ስርዓትና በአገራዊ ባህል የፈለጋትን ወይም የፈለገችውን ተስማምተው ማግባት እንደሚችል ተፈጥሮዋዊ ማንነት ከእግዚአብሔር ተሰጥቷል። ከዚህ የተነሰ የተሰጠንን የነፃነት ፀጋ መጠቀም መቻል እንጂ ከጋብቻ በፊት የድብብቆሽ ስራወች መፈፀም እኛንም በነፍስ ይጎዳናል ከፈጣሪ ጋርም ያጣላናል በሰው ዘንድም መኀበራዊ ማንነታችንን ያዛባል። ስለዚህ  ለስርዓቱና ህጉ ተገዝተን ስራ ላይ ብናውለው በእግዚአብሔር ዘንድም በረከትና መንፈሳዊ እድገት ያሰጠናል ማለት ነው።

ሌላው፤ በትዳር ውስጥ እያሉ ከህጋዊ ጋብቻ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የሥጋ ግንኙነት እና ሴሰኝነት ወይም አመንዝራነት ዝሙት ይባላል። ማለትም አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ወይም አንዲት ሴት ከሌላ ሰው ባል ጋር ወይም በህጋዊ ጋብቻ ጓደኛው ወይም ጓደኛዋ ካልሆነ ወንድ እና ካልሆነች ሴት ጋር የግብረ ስጋ ተራክቦ በማድረግም ሆነ በዝሙት ሃሳብ እየተቃጠሉ መኖር ዝሙተኝነትና አመንዝራነት ነው።

በተጨማሪም ከቤተክርስቲያንን ስርአትና አስተምህሮ አንጻር መገንዘብ ያለብን፦

–    ለመቁረብ ሁሉን ነገር አሳክተን ከወሰንን በኋላ ከምንቆርብ 3 ቀን በፊት ወንድ ይሁን ሴት ቤተሰብ ካለ  ከግንኙነት (ፆታዊ ግንኙነት) መቆጠብ ያስፈልጋል።

–    አንድ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን በተቀበለበት እለት  ከሕግ ጋብቻ ጋር ቢሆንም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የለበትም ፣

– በአፇማት እና  የበዓል ቀናት ግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ የተከለከለ ነው። ይህንንም እንዴት ማክበር እንዳለብን በሚመለከት፦

1ኛ/ ስለአፇማት፦ ለምሳሌ ሮብ ለመፆም ማክሰኞ ለሮብ፣ ሐሙስ ለአርብ መታቀብ አለብን ማለት ነው።

2ኛ/  ሌሎችን የአዋጅ ፆም በሚመለከት ፦ ወንዱ ከሴቷ፣ ሴቷም ከወንዱ እርቃ በሱባኤ ተለይቶ ማሳለፍ እንዳለብን የቤተክርስቲያናችን ቀኖና ያዛል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል።

3ኛ/ በአላትን በሚመለከት እለተ ሰንበት፣ የእመቤታችን በዓል፣ የባለቤቱ የጌታችን የመድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአላት ፣ እና ሌሎችም ታላላቅ የታወቁ በዓላት ከዋዜማቸው ጀምሮ ከሩካቤ እርቀን ማክበር አለብን። ማለትም በማንኛውም ግዜ የፆም የፀሎት ሱባኤ በራሳችንም ይሁን በአባቶቻችን ቀኖና ተሰጥቶን የፆምና የፀሎት ሱባኤ በያዝን ግዜ፣ በእለተ ሰንበት እና በታወቁ በአላት ቀን ፈፅሞ ሚስትም ከባልዋ ተለይታ ወንድም ከሚስቱ ተለይቶ መኝታቸውንም የተለየ አድርገው በአጠቃላይ ፈቃደ ስጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው መጾም ያስፈልጋል።ይህን ስንል በቀኖና የተደነገጉ 7ቱ አፅዋማትና እንደገናም በአባቶቻችን ሱባኤ ተሰጥቶን የምንፆምባቸው አፅዋማትን ይመለከታል። 

ስለመንፈሳዊ ወይም ስለ ክርስቲያናዊ ህይወት ከባልና ሚስት አንዱ ጥንካሬ ካለው ማሸነፍ ያለበትና ተቀባይነት ያለው የሃይማኖቱና የነፍሱን ጉዳይ ተቀዳሚ እና ተፈፃሚ መሆን ያለበት መሆን አለበትና ሃሳቡን በዚህ መረዳት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል።

4ኛ/ በተጨማሪም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል፣ ወይም ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ ወይም  ፀበል ለመጠመቅ ለ 3 ቀናት ከስጋ ስርአት እርቀን ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን መቆየት  ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ ሰው እሁድ ቤተክርስቲያን ለመግባት ቢያንስ ከአርብ ማታ ጀምሮ ከስጋ ሩካቤ መቆጠብ አለበት ማለት ነው። ከዚህ ውጪ በፈተና ከወደቅን ግን የተለመደ የዘወትር ፀሎታችንን በቤታችን አካለ ስጋችንን ታጥበን በፀሎት ቤታችን ቆመን ማድረስ እንችላለን ወይም ወደ ቤተክርስቲያን ሄደን ከመግቢው ቅጽር ሆነን መፀለይ እንችላለን ማለት ነው።  

በመሰረቱ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ 3 ቀን ከስጋ ስርዓት እንድንርቅ የሚደረግበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለኛ በተቀበለው መከራ በእለተ አርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው ለይቶ 3 መአልትና 3 ለሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ሐዋሪያት እና ከሱ ጋር ይከተሉት የነበሩት ደቀመዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ሳናይ የሚበላ አንበላም የሚጠጣም አንጠጣም ብለው በፆም ተወስነው ስለቆዩ ነው። ስለዚህ ዛሬም የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን አማናዊ ስጋና አማናዊ ደም ስለሆነ ያንን መነሻ አብነት አድርገን ለ 3 ቀናት ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን የምንቆየው ነው።

በመሆኑም ህግ እና ቀኖና የሆነውን ነገር በህግነትና በቀኖናነቱ የተወሰነውን እውነቱን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በደካማ ስጋችን ተፈትነንና ስጋዊ ምኞት አሸንፎን ቀኖናን የሚሽር ስህተት ፈፅመን ብንገኝ ወይም ደግሞ ከ 3 ቀን ባነሰ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን ጠያቂያችን ያነሱትን ስህተት ፈፅሞ ቢገባ ያ ክርስቲያን ፈፅሞ የተወገዘ የተረገመ ነው ማለት አይደለም። የቤተክርስቲያን ስርዓት እና ቀኖና በመሻሩ ተግሳፅና ምክር ሊሰጠው ይችላል። ወደፊት እያወቀ እንዲህ አይነት ጥፋት እንዳትፈፅም ተብሎ ምክር ይሰጠዋል። ይሄ የሚሆነው በህጋዊ ጋብቻ ተወስነው ለሚኖሩ ነው። ከዚህ ውጭ ለሚፈጸመው የስጋ ሩካቤ ግን እንኳን ቤተክርስቲያን በድፍረት ለገባንበት ይቅርና ከሕግ ውጭ ላደረግነው ግንኙነትም ከባድ የቀኖና ቅጣት ይጠብቀዋል። በዚሁ መሰረት ቀኖና ባለመሻር እና ከእግዚአብሔር በረከት ለማግኘት በምናደርገው መንፈሳዊ አገልግሎት በነፍስ የምንጎዳበት እርግማን እንዳያመጣብን ከወዲሁ ክርስቲያናዊ ስነምግባር እና ጥንቃቄ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው።

5ኛ/ ለፀሎት የምንገለገልባቸውን መፅሐፍት እና ሌሎችን የመንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ማንኛውንም ነገር የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው መቀመጥ አለባቸው። እኛም ለመፀለይ ስንፈልግ ካደርንበት መኝታችን ተነስተን የአድህኖ እና የምንፀልይበት ቦታ ላይ ሄደን የተለመደውን የእለት ፀሎታችንን ማድረስ።  ቦታ ባይኖረንም እንኳን ከተኛንበት ቦታ ላይ ርቀን በውጭም ሆነ በሳሎን ውስጥ ሆነን መፀለይ፤ ከአቅም በላይ የሆነ የቦታ ችግር ካለ ግን ከጸሎት አንከለከልም ፤ ሌላው ባል እና ሚስት የግብረስጋ ግንኙነት አድርገው በአደሩበት ቀን ወይም እዛ ቦታ ላይ ቅዱሳት ስዕላት ማስቀመጥ ስርዓተ ቤተክርስቲያን የተከለከለ ነው።

6ኛ/ ከማያውቁት ወንድ ወይም ሴት ጋር በህልመ ለሊት ግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የሰው ልጅ በራሱ ስጋዊ ስሜት አስቦበትና ፈልጎት ያደረገው ኅጢአት ካልሆነ መደበኛ የንስኀ ቀኖና አያስፈልገውም። ነገር ግን አንዳንዴ ቀን ስንመኘውና ስናስበው የዋልነውን ተኝተን በህልም ከምናውቀው ሰው ጋር ከፈፀምነው ኀጢአቱን አስበን እንዳደረግነው ይቆጠራል። ምክንያቱም ስላልቻልን እንጂ በአካልም ለማድረግ ፍላጎቱ ነበረን ወይም እንደዚህ አስበንና አቅደን ስላልተሳካልን ብቻ በተግባር ያላዋልነውን ተኝተን በህልም ካደረግነው እንደ ኀጢአት የሚያስቆጥርብን ይሆናልና የንስኀ ቀኖና እና ምክር ያስፈልገዋል።

7ኛ/  አንድ ክርስቲያን በሃይማኖት ከማይመስለው ወንድ ወይም ሴት ጋር የግብረ ስጋ (የስጋ ሩካቤ) ቢፈፅም ወይም ብትፈፅም በቀጥታ የቄደር ጥምቀት እንደሚያስፈልጋቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል።

በመጨረሻም፤  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን  “ወይስ አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግስት እንዳይወርሱ አታውቁምን፥ አትሳቱ ሴሰኛዎች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሰሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ታድሳችኋል ፀድቃችኋል” በማለት የዝሙትን አይነት እና ዝሙት ከፍተኛ ኅጢአት መሆኑን ከዘረዘረ በኋላ እግዚአብሔርን በመፍራት ወደ ንስኅ ስንመለስ ግን እንዴት ከኅጢአታችን እድፍ እንደምንታጠብና እንደምንቀደስ እንደምንፀድቅም አስተምሮናል። (ቀኛ ቆረ 6፥9፤10)

በመሆኑም፤ በዮሐንስ ንስሐ ድረ-ገጽ ያለ መቋረጥ ዘወትር የሚተላለፈውን ትምሕርተ ሃይማኖት እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ፕሮግራም በመከታተል ላይ የምትገኙ ወገኖች ሁላችሁም በዋናነት ይህን ትምህርታዊ መልዕክት አንብባችሁ ተግባራዊ እንድታደርጉ  እየመከርን ፤ በኀጢአት መውደቅ ቢኖር እንኳን “የይቅርታ አምላክ  ማንም ወጥቶ እንዲቀር አይፈልግም ፥ ልጆቹን ይፈልጋቸዋል ” በውኑ ኀጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” (ሕዝ18፥23) እግዚአብሔር ልጆቹን ከነኀጢአታቸው እንዲሞቱ አይፈልግምና እድል ይሰጣቸዋል በዚህ በምድር ላይ እንዲፀፀቱ ንስኀ እንዲገቡ ከልብ በመነጨ ንስኀ እንዲመለሱ ነው እንጂ።

ስለዚህ፤ ወገኖች ከህግ ውጪ የሆነ ሩካቤ ስጋ  የሰይጣን ውግያ ነውና፤ እግዚአብሔር ደግሞ የምህረት አምላክ ስለሆነ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወመንን ክፉ መንፈስ እንደምንም ታግለን ማሸነፍ ያስፈልጋል።

ስለዚህ ወገኖች አሁንም በዚህ ጉዳይ ያልተገባ ሩካቤ ሥጋ ፈጽመን በኀጢአት ወደቀን ከሆነ የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳናራዝም ወደ ንስሐ አባታችን ቀርበን በማማከር የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለን በናምንም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና ፍርሃትን አርቀን ወደ ይቅር ባይ አምላክ መቅረብ እንደሚያስ እንመክራለን።

ስለዚህ ጠያቂያችንም ጥያቄዎን እኛ በተረዳነውን መልኩ  ከዚህ በላይ በላይ በሰጠነውን ማብራሪያ ውስጥ ምላሽ እንዳገኙበት እንገምታለን። ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆነልዎት ወይም ያልተመለሰለዎት ሃሳብ ካለ ግን ጥያቄዎን ትንሽ አብራርተው በድጋሚ ቢያሳውቁን ተጨማሪ ማብራሪያ እንሰጥዎታለን።

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org ላይ ያገኛሉ

ስለ ዝሙት ጥያቄና መልስ

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

ከዚህ ስር ያሉትን ጥያቄዎች ቢጫኑ መልሳቸውን ያገኛሉ

መልስ፦ የዝሙት የመነሻው ምንጩ ሃሳብ ነው። ከሃሰብ ሲወጣ በአንደበት ይነገራል፣ ከአንደበት የተነገረው ደግሞ ጊዜ ሲገጥም በተግባር ይውላል።  ስለዚህ የመጀመሪያው የዝሙት ድርጊት ፅንሱ ማሰብ ነው። በሃሳብና በአፍ በዝሙት ጉዳይ ላይ አብዝቶ የማይነጋገርና በሃሳቡ የማይቃጠል የለም ማለት ይቻላል። የዝሙት ስራ በሰው ስነልቦና ውስጥ የሚያደርሰው ፈተና እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በሥጋ ያቃታቸው እንኳን በልባቸው ይመኙታል ባፋቸው ያወሩታል።  

ሌላው፤ የዝሙት መንስኤዎች እና የዝሙት ዋዜማዎች በአብዛኛው ህጋዊ ከሆነ ጋብቻ ውጪ ያሉ የሴት እና የወንድ መሳሳም፣ በስሜት እየተቃጠሉ መተሻሸት ፣ አብሮ  መተኛት፣  ስሜትን የሚያነሳሱ እርኩስ ፊልም እና ኢንተርኔት ማየት ወይም ማንበብ፣ ስለዚህ ጉዳይ አብዝቶ ማውራት፣ ህሊናን ለዚህ ቦታ መስጠት እና ከዚህ ጋር በተያያዙ ተግባሮች የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋው ወደ ዝሙት ሃሳብ ሲያመራበት ሃሳቡን በድብብቆሽ ሲለማመድ ቆይቶ የሴሰኝነት መንፈስ አይሎበት ራሱን መቆጣጠር ሲያቅተው ወደዋናው የዝሙት ኀጢአት ይወድቃል ማለት ነው። 

ሌላው መንስኤ ደግሞ ዝሙት ከፍተኛ የኀጢአት አይነት ስለመሆኑ በቂ ግንዛቤ ካለመኖርና መጽሐፍ ቅዱስ ስለዝሙት አስከፊነት ምን እነደሚል ካለመረዳት የተነሳም ሊሆን ይችላል። በአብዛኛው ግን እራሳችንን ለፈቃደ ስጋችን በማስገዛት ወይም የምናገኘውን ጊዜያዊ ጥቅምና ስሜት በማሰብ በድፍረት የምንፈጽመው ሲሆን ለዚህም ሰይጣን አሳስቶኝ ነው በማለት ተጠያቂና ባለቤት የምናደርገው ሰይጣንን ቢሆንም ሰይጣን አንድ ቀንም ኀላፊነቱን ወስዶልን አያውቅም። በእርግጥም ሰይጣን የእኛን ፍላጎት እና ሃሳብ አይቶ እንደ ደካማ ጎናችን ለያንዳንዳችን የምንወድቅበትን ክፋት የሆነውን ስራ መርጦ እያሸከመ የግብሩ ፈፃሚና አስፈፃሚ ያደርገናል። 

መልስ፦በዝሙት ኀጢአት ለወደቅን ሰዎች አንደኛና አይነተኛ መፍትሄው፥ ንስሐ መግባት ነው። ለዚህም፦

1ኛ/ በመጀመሪያ ስለፈፀምነው የዝሙት ኀጢአት መሆኑን አምነን ከልብ የሆነ ፀፀት ሊኖረን ይገባል።

2ኛ/ የንስሐ አባት ሊኖረን ይገባል። እንደ ኀጢአታችን አይነት እና መጠን ቀኖና እየሰጠ በየጊዜው ክትትል አድርጎ  ሙሉ ለሙሉ ከዚህ ኀጢአት እስከምንወጣ የሚመክረን ፀጋውና ትሩፋቱ የበዛለት ለነፍሳችን እረኛ ጠባቂ የሆነ ጥሩ የንስሐ አባት ያስፈልገናል። 

3ኛ/ ንስሐ መግባትና የንስሐ አባታችን የሚሰጡንን ቀኖና በአግባቡ መፈፀም አለብን፤

4ኛ/ አብዝቶ መፆም ፣ አብዝቶ መፀለይ፣ አብዝቶ መስገድ ያስፈልገናል። ዘወትር ሳያቋርጡ የሚፀልዩት የግል ፀሎት መኖር አለበት። ጠዋትም ማታም የምንፀልየው ከዘወትር ፀሎትና ውዳሴ ማርያም ውጪ ጊዜ የምናገኝ ከሆነ ፥ እንደ መንፈሳዊ እወቀት ደረጃችን መጠን በግላችን በቋሚነት የምንፀልየው ፀሎት ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊትን፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ ወንጌለ ዮሐንስን፣ ድርሳናትን፣ መዝገበ ፀሎት እና ስለ ንስኀ ትምህርት የሚሰጡ መፃህፍትን በተጨመሪ ማንበብና መፀለይ ይቻላል።  ከዚህ ጋር አብዝቶ በመስገድም እርኩስ መንፈስን መዋጋት ይቻላል። ስንሰግድ በፊታችን መስቀል ወይም ቅዱሳን ስዕላት ወይም ወንጌል አድርገን በትዕምርተ መስቀል እያማተብን ጉልበታችንን እና ግንባራችንን መሬት እያስነካን መስገድ ይገባል።

5ኛ/ በምንተኛበት አካባቢ በክፍላችንም በቅፅረ ቤታችንም በመኝታ ዙሪያችንም ሁሉ አጋንንት እንዳይቀርቡ እንደ አጥር ሆኖ የሚከላከል ጋሻና መከታ ሊሆን የሚችለውን መስቀሉን ብንቀስረው ወይም ብንከበው ያን ጊዜ አጋንንት ስለሚያቃጥላቸውና ሃይላቸው ስለሚደክም ጨርሶ ይጠፋሉ።  ምክንያቱም ፀሎቱ አጥር ነው፣ መስቀሉም አጥር ነው፣ በዙሪያችን የምንፀልይባቸው ቅዱሳን መፃህፍት እና መዝገበ ፀሎቱ አጥር ናቸው።

6ኛ/ ሁሌ ከዚህ ክፉ ሃሳብ መለየት እንዲችሉ ይህ የኅጢአት ሃሳብ ወደ እርስዎ እየመጣ በተዋጋዎት ቁጥር የእግዚአብሔርን ስም፣ የእናታችንን የድንግል ማርያምን ስም፣ የቅዱሳን መላዕክትን ስም እና የቅዱሳን ፃድቃን ሰማእታትን ስም በመጥራት ወዲያውኑ ሰይጣን በአይምሮዎት ላይ የፈጠረውን ክፉ ምኞት ለመቃወምና ከእርስዎ ለማራቅ መቻል አለብዎት።

7ኛ/  ከነዚህም በተጨማሪ፦  ቤተክርስቲያን መሳለም፣ ማስቀደስ፣ ፀበል መረጨት በራሱ በፈጣሪ በእግዚአብሔር ስም እና በቅዱሳን ስም ወደፈለቀው ፀበል ቦታ በመሄድ በአባቶች እጅ መጠመቅ ፣ በመስቀል መባረክ፣ እምነቱን መቀባት ፀበሉን መጠጣት ለተወሰነ ሱባኤ ግዜ ከአባቶች ጋር በመመካከር ከስጋዊ ህይወት እርቆ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተወስኖ መቆየት፤ የተለያዩ የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን በማንበብ እንዲሁም በድምፅ አና በምስል የተዘጋጁ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፉ ትምህርቶች፣ መዝሙሮች መከታተልን ማዘውተር።

8ኛ/ ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው!!!  አንድ ጊዜ ሳይሳካልን ብንወድቅ እንኳን ደጋግመንም ቢሆን በንስኀ እየተነሳን እስከመጨረሻው መቀጠል አለብን። በንስኀ አባቶቻችን መሪነትና መካሪነት በፅናትና በእምነት ሆነን ከዚህ ኀጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርም ብለን እስከምንላቀቅ ድረስ በፅናት መትጋት እንደሚገባ እንመክራለን።

በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩትን መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ሁሉንም በአንድ ጊዜ ሳይሆን እንደ መንፈሳዊ እውቀታችን እና እንደ ተፈተንበት የዝሙት አይነትና መጠን በማገናዘብ እየፈፀምን መንፈሳዊ ህይወታችንን ደረጃ በደረጃ በማሳደግ ሳናቋርጥ በምናደርገው ፅኑ ተጋድሎ መንፈሱ ራሱ ተቃጥሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእኛ ይለያል።

መልስ፦ የዝሙት ስራ መጀመሪያ በመሳሳም እንደሚገለፅ እነሆ በአለማችን የምናየው ትርኢት ነው። በአጠቃላይ ህጋዊ ከሆነ ጋብቻ ውጪ ያሉ የሴት እና የወንድ መሳሳምም ይሁን፣ በስሜት እየተቃጠሉ መተሻሸትም ይሁን የዝሙት መንስኤዎች እና የዝሙት ዋዜማዎች ናቸው። ስለዚህ እራሳችንን መቆጣጠር አቅቶን እነዚህን ድርጊቶች እየጨመርንበት ስንሄድ ዋናው የዝሙት ኀጢአት ሩካቤ ስጋ መፈፀምም ስለሚመጣ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቀናል ማለት ነው።  በመሰረቱ  በእኛ በቤተክርስቲያን አስተምሮ በበጎ ፈቃድ የምንለዋወጠው ሰላምታ መሳሳምን የሚተካው የክርስቲያናዊ የሰላምታ አይነት ነው። ምክንያቱም ራሱን የገዛ እና ከህሊናው ጋር የሚኖር ማንኛውም ክርስቲያን ከትዳር ጓደኛውም ጋር ቢሆን ከሌላው ሰው ጋርም ቢሆን እውነተኛ ፍቅርን እና ናፍቆትን የሚገልፅበት መሳሳም በሰው ፊትም ይሁን በእግዚአብሔር ፊትም በጉባኤ ፊትም ቢሆን የማያሳፍር የማያሳቅቅ ትክክለኛ እና እውነተኛ ሰላምታ የሚገለፅበት የሰላምታ አሰጣጥ ስርአት ነው። ስለዚህ ከትዳር በፊትም ሆነ በትዳር ጊዜ መሳሳም የሚለው ሃሳብ ከሰው መልካም ስነ ምግባር ጋር የማይሄድ ተግባር ነው።

መልስ፦ ከትዳር በፊት አብሮ ማደር የሚለው አባባል ሲጀመር ከጋብቻ ውጭ የሆነ ማንኛውም ተራክቦ ወይም ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም ከዝሙት ኀጢአት የሚቆጠር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ፈቃደ ስጋቸውን መግዛት ያቃታቸው በቃልኪዳን በእጮኝነት ያሉ ወንድ እና ሴት ከጋብቻ በፊት ማንኛውንም ግንኙነት ለማድረግ ቤተክርስቲያን አትፈቅድም። እነሱ በራሳቸው ፈቃድ ቢፈፅሙት እንኳን ንስሐ የሚያስገባ ኀጢአት ነው።

በአጠቃላይ ህጋዊ ከሆነ ጋብቻ ውጪ ያሉ የሴት እና የወንድ መሳሳምም ይሁን፣ በስሜት እየተቃጠሉ መተሻሸትም ይሁን የዝሙት መንስኤዎች እና የዝሙት ዋዜማዎች ናቸው። ስለዚህ እራሳችንን መቆጣጠር አቅቶን እነዚህን ድርጊቶች እየጨመርንበት ስንሄድ ዋናው የዝሙት ኀጢአት ሩካቤ ስጋ መፈፀምም ስለሚመጣ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቀናል ማለት ነው። ነገር ግን ወንድ እና ሴት ከጋብቻ በፊት በቃልኪዳን ተሳስረው ምንም አይነት ሩካቤ ሳያደርጉ የጋብቻቸውን ቀን በማክበር ከቆዩ በኋላ ጋብቻቸው ሲፈፀም በእግዚአብሔር የተቀደሰ በማህበረሰቡም ዘንድ ስለታወቀላቸው የሚያደርጉት የተራክቦ ስጋ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተፈቀደ ህግን ፈፀሙ እንጂ የዝሙት ስራን ስላልፈፀሙ ኑሯቸው ሁሉ ህጋዊ እንደሆነ ይታመናል።

መልስ፦ ጠያቂያችን፦  አንድ ክርስቲያን የተፈፀመውን በደል በራሱ ግዜ አምኖ ተፀፅቶ ንስሓ ገብቶ የተሰጠውንም ቀኖና ጨርሶ ወደፊት ኅጢአት ላለመስራት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ ደግሞ ያንኑ በደል ከፈፀመ ሰውነቱን የተቆራኘው የኀጢአት ደዌ ብሶበታል ማለት ነው።  አሳዛኝ ቢሆንም ስለአድን ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ተስፋ ሳይቆረጥ ይሄን ሰው በተለያየ መንገድ የንስሓ አባቱ ወይም ሌላም አባት በቅርብ ውስጣዊ ችግሩን ተረድተው እና መርምረው አሁንም ወደ ንስሓ ህይወት እንዲቀርብ እና በተደጋጋሚ ከተፈተነበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አቤቱ ወንድሜ ምን ያህል ቢበድለኝ ምን ያህል ይቅር ልበለው እስከ 7 ጊዜ ነውን ብሎ በጠየቀው ጊዜ እስከ 7 አልልህም 7ቱን አንድ እያልክ እስከ 70 ነው እንጂ” በማለት ለኅጢአት ይቅርታ የጊዜ እና የቁጥር ገደብ እንደሌለው አረጋግጦልናል። (ማቴ 18፥21-22)

ንስሐ አባትን በሚመለከት ለገለጹት፥ በሰራነው ኀጢአት አፍረን እና ተሸማቀን ክብራችን እንዳይነካ ለመሰወር እና ጥፋታችንን ለመደበቅ የምናደርገው ስጋዊ አስተሳሰብ ካለ ሰውን ብናሞኝ እግዚአብሔርን ማታለል ስለማንችል የዚህ አይነት አካሄድ ከእውነተኛ ክርስቲያን የማይጠበቅ ተግባር ነው። ከዚህ ውጭ በሆነ በቀና መንፈስ ከሆነ ግን በደረስንበት መንፈሳዊ ቦታ ሁሉ እውነተኛ የቤተክርስቲያን አባቶችን በማነጋገር የዋለው ኀጢአታችን እንዳያድርብን ያደረውም እንዳይውልብን በጊዜውም ያለጊዜውም በአባቶች ጥበቃ የንስሓ ህይወት መኖር ከሁሉም ክርስቲያን ይጠበቃል። ለጠያቂያችንም ሆነ ለሌላው ሁሉ ምክር የምንሰጠው ምናልባት የሰራነውን ኀጢአት ሁሉ ለመደበኛ የንስሓ አባታችን ለመናዘዝ የምናፍርበት ወይም ካህኑንም የምንጠራጠራቸው ነገር ካለ ስርአታዊ መንገድ ተጠቅመን በመንፈሳዊ ጥበብና በትህትና ሁነን ተሰናብተን ፤ ሳንጠራጠር ከልብ የምናምናቸውን ሌላ አባት መርጠን መያዝ ይገባናል። አንዳንዶቻችን ለራሳችን ደህንነትም ሆነ ለማህበራዊ ግንኙነታችን ችግር የሚያመጣብን ቢሆን እንኳን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድና አስፈላጊም ከሆነ ወደሌላ ቅዱስ ቦታ ራቅ ብለን በመሄድ ለቤተክርስቲያን አባቶች መናዘዝና ንስኅችንን ማከናወን ይገባናል። እኛም በዚህ ፕሮግራም ሰዎች ይድኑ ዘንድ በተቻለን መጠን ስለናንተ የምናደርገው ጥረትና የምንሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ከዚህ የተነሳ ስለሆነ የእያንዳንዳንዳችሁንም የውስጥ ችግር በሃሳብም ቢሆን ስለምንረዳችሁ ምናልባት ለንስኅ አባት ለመንገር የሚያስፈራችሁና የሚያሰጋችሁ በቂ ምክንያት ካለ እኛንም በውስጥ መስመር አግኝታችሁ ብታሳውቁን መፍትሄ እንሰጣችኋለን። ይህን የምንልበት ምክንያት ብዙዎቹ ምእመናን ለንስሓ አባቶቻቸው ግልፅ ሆነው የሰሩትን በደል ለመንገር የማይችሉበት ዋናው ምክንያት ምስጢር ይባክንብናል ብለው ከነኀጢአታቸው የሚኖሩ አሉና፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለአባቶቻቸው ግልፅ ለመሆን በአካባቢያቸው በማህበራዊ ህይወት ከመንፈሳዊ አባቶቻቸው ጋር አብረው ስለሚኖሩ የመተፋፈርም ነገር ስለሚያጋጥማቸው በዚህም ምክንያት የሚሳቀቁ ምእመናን እንዳሉ መረጃው ስላለን፤ ከዚህ ሁሉ ስጋት ነፃ ለመሆን የሚያምኑበትን እና የማይጠራጠሩበትን አባት መያዝ እንደሚገባቸው በአፅንዎት እንመክራለን። ለዘላለማዊ የነፍስ ድህነት ጉዳይ የምንሰራውና የምናደርገው ተጋድሎ በስጋዊ አመለካከት ወይም ምድራዊ በሆነ አሰራር የምንኖረው ሂደት ስላልሆነ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። 

መልስ፦ ጠያቂችን ፤ ዝሙት በስሙ ዝሙት ቢባልም በስራው ወይም በኅጢአት ሲገለፅ  ግን እጅግ ከፍተኛ የኅጢአት አይነት ከመሆኑም በላይ የኅጢአቱም ብዛት እና ደረጃም ይለያያል። ለምሳሌ ከአንድ ሰው ጋር መዘሞትና ከብዙ ሰው ጋር መዘሞት ኅጢአትነቱ ልዩነት አለው። በመሆኑም ኅጢአቱን ለማድረግ ካላፈርነው ከብዙ ሰዎች ጋር የዝሙት ኅጢአት ፈፅሜያለሁ ብለን ለካህኑ ለመናገር የሚያሳፍረን ነገር የለም። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለምናምነው ለንስኀ አባታችን የሰራነውን የዝሙት አይነት ዘርዝረን መናገር አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የንስሐ ቀኖና የሚሰጠን በሰራነው ለእያንዳንዳንዱ የዝሙት ኅጢአትና መጠን አንፃር በአንቀፀ ንስሐ ታይቶ የሚሰጠን ቀኖና ስላለ ነው።

መልስ፦ በአፇማት እና  የበዓል ቀናት ግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ የተከለከለ ነው። ይህንንም በሚመለከት፦

 1ኛ/  በቀኖና የተደነገጉ 7ቱ አፅዋማት፦ ወንዱ ከሴቷ፣ ሴቷም ከወንዱ እርቃ በሱባኤ ተለይቶ ማሳለፍ እንዳለብን የቤተክርስቲያናችን ቀኖና ያዛል። ለምሳሌ ሮብ ለመፆም ማክሰኞ ለሮብ፣ ሐሙስ ለአርብ መታቀብ አለብን ማለት ነው።

2ኛ/ በአላትን በሚመለከት እለተ ሰንበት፣ የእመቤታችን በዓል፣ የባለቤቱ የጌታችን የመድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአላት ፣ እና ሌሎችም ታላላቅ የታወቁ በዓላት ከዋዜማቸው ጀምሮ ከሩካቤ እርቀን ማክበር አለብን።

3ኛ/ በማንኛውም ግዜ የፆም የፀሎት ሱባኤ በራሳችንም ይሁን በአባቶቻችን ቀኖና ተሰጥቶን የፆምና የፀሎት ሱባኤ በያዝን ግዜያት፣

ስለመንፈሳዊ ወይም ስለ ክርስቲያናዊ ህይወት ከባልና ሚስት አንዱ ጥንካሬ ካለው ማሸነፍ ያለበትና ተቀባይነት ያለው የሃይማኖቱና የነፍሱን ጉዳይ ተቀዳሚ እና ተፈፃሚ መሆን ያለበት መሆን አለበትና ሃሳቡን በዚህ መረዳት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል፣ ወይም ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ ወይም  ፀበል ለመጠመቅ ለ 3 ቀናት ከስጋ ስርአት እርቀን ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን መቆየት  ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ ሰው እሁድ ቤተክርስቲያን ለመግባት ቢያንስ ከአርብ ማታ ጀምሮ ከስጋ ሩካቤ መቆጠብ አለበት ማለት ነው። ከዚህ ውጪ በፈተና ከወደቅን ግን የተለመደ የዘወትር ፀሎታችንን በቤታችን አካለ ስጋችንን ታጥበን በፀሎት ቤታችን ቆመን ማድረስ እንችላለን ወይም ወደ ቤተክርስቲያን ሄደን ከመግቢው ቅጽር ሆነን መፀለይ እንችላለን ማለት ነው።  

መልስ፦ ጠያቂያችን፤  ከራስ ጋር የዝሙት ሃሳብ ለመፈፀም ተነሳስተው በሃሳብና በምኞት ራሳቸውን በሰይጣናዊ ስራ ተገዢ የማድረጉ ተግባር ብዙ ወገኖቻችን እየተፈተኑበት ያለ ጉዳይ ነው።  በዘመናችን ወቅታዊ የሆነ ብዙ ሰዎችን እየተዋጋ ያለው ኅጢአት አይነት ሲሆን አለምን ሁሉ አንድ ለማድረግ በምድር ላይ ሰይጣን በከፍተኛ ደረጃ የሰውን ልጅ ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣት እየታገለ ያለበት ከተፈጥሮአዊ ስርአት ውጭ የሆነ ከፍተኛ የኅጢአት አይነት ነው።   ከተፈጥሮአዊ ስርአት ውጭ በመሆኑም አካላዊ የዝሙት ግብረ ስጋ ከሚፈፅሙትም ሰዎች የበለጠ ኀጢአት ነው። እንዲያውም የሰዶማዊነትም ሃሳብ ከዚህ ይጀምራልና በዚህም ከሰዶማዊነት መንፈስ ጋር ይያያዛል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከኅጢአት ሁሉ የከፋ ከባድ ውድቀት እንደሆነ በቅዱስ መፅሐፍም አስተምሮ አለምን ለጥፋት ያበቃ የኅጢአት አይነት እንደሆነ መረዳት አለብን።

ይሁን እንጂ ብዙዎች የሚፈተኑበት ሰይጣናዊ ሃሳብ ቢሆንም እንኳን የታመመ ሁሉ እንደማይሞት ኅጢአተኛ ሁሉ እንደማይኮነን የወደቀ ሁሉ እንደማይሰበር ሁሉ፥  ክርስቲያን በነፍሱ ላይ ያጋጠመውን የኅጢአት እድፍ በንስሐ ህይወት ታጥቦ ለመፅዳት እስከተዘጋጀ ድረስ ስለወዳጆቹ ወይም ስለልጆቹ አንድ ቀንም የማይጨክነው የርህራሄና የምህረት አምላክ እግዚአብሔር በደላችንን ሁሉ ዘወትር ይቅር ማለት የተለመደ የባህሪይ ሥራው ስለሆነ እርስዎም በዚህ አይነት አቀራረብ ስለፈፀሙት የኅጢአት ስራ በመፀፀት ለንስኅ የተዘጋጀ ህሊና እንዳለዎት ያሳያልና በእርግጠኝነት በዚህ አይነት ፈተና የሚቃወምዎትን ጠላት እንደሚያሸንፉት አይጠራጠሩ።     

ስለዚህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ  ከዚህ አይነት የዝሙት መንፈስ ለመውጣት ይችሉ ዘንድ፦

1ኛ/ በመጀመሪያ ስለፈፀምነው የዝሙት ኀጢአት መሆኑን አምነን ከልብ የሆነ ፀፀት ሊኖረን ይገባል።

2ኛ/ የንስሐ አባት ሊኖረን ይገባል። እንደ ኀጢአታችን አይነት እና መጠን ቀኖና እየሰጠ በየጊዜው ክትትል አድርጎ  ሙሉ ለሙሉ ከዚህ ኀጢአት እስከምንወጣ የሚመክረን ፀጋውና ትሩፋቱ የበዛለት ለነፍሳችን እረኛ ጠባቂ የሆነ ጥሩ የንስሐ አባት ያስፈልገናል። 

3ኛ/ ንስሐ መግባትና የንስሐ አባታችን የሚሰጡንን ቀኖና በአግባቡ መፈፀም አለብን፤

4ኛ/ አብዝቶ መፆም ፣ አብዝቶ መፀለይ፣ አብዝቶ መስገድ ያስፈልገናል። ዘወትር ሳያቋርጡ የሚፀልዩት የግል ፀሎት መኖር አለበት። ጠዋትም ማታም የምንፀልየው ከዘወትር ፀሎትና ውዳሴ ማርያም ውጪ ጊዜ የምናገኝ ከሆነ ፥ እንደ መንፈሳዊ እወቀት ደረጃችን መጠን በግላችን በቋሚነት የምንፀልየው ፀሎት ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊትን፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ ወንጌለ ዮሐንስን፣ ድርሳናትን፣ መዝገበ ፀሎት እና ስለ ንስኀ ትምህርት የሚሰጡ መፃህፍትን በተጨመሪ ማንበብና መፀለይ ይቻላል።  ከዚህ ጋር አብዝቶ በመስገድም እርኩስ መንፈስን መዋጋት ይቻላል። ስንሰግድ በፊታችን መስቀል ወይም ቅዱሳን ስዕላት ወይም ወንጌል አድርገን በትዕምርተ መስቀል እያማተብን ጉልበታችንን እና ግንባራችንን መሬት እያስነካን መስገድ ይገባል።

5ኛ/ በምንተኛበት አካባቢ በክፍላችንም በቅፅረ ቤታችንም በመኝታ ዙሪያችንም ሁሉ አጋንንት እንዳይቀርቡ እንደ አጥር ሆኖ የሚከላከል ጋሻና መከታ ሊሆን የሚችለውን መስቀሉን ብንቀስረው ወይም ብንከበው ያን ጊዜ አጋንንት ስለሚያቃጥላቸውና ሃይላቸው ስለሚደክም ጨርሶ ይጠፋሉ።  ምክንያቱም ፀሎቱ አጥር ነው፣ መስቀሉም አጥር ነው፣ በዙሪያችን የምንፀልይባቸው ቅዱሳን መፃህፍት እና መዝገበ ፀሎቱ አጥር ናቸው።

6ኛ/ ሁሌ ከዚህ ክፉ ሃሳብ መለየት እንዲችሉ ይህ የኅጢአት ሃሳብ ወደ እርስዎ እየመጣ በተዋጋዎት ቁጥር የእግዚአብሔርን ስም፣ የእናታችንን የድንግል ማርያምን ስም፣ የቅዱሳን መላዕክትን ስም እና የቅዱሳን ፃድቃን ሰማእታትን ስም በመጥራት ወዲያውኑ ሰይጣን በአይምሮዎት ላይ የፈጠረውን ክፉ ምኞት ለመቃወምና ከእርስዎ ለማራቅ መቻል አለብዎት።

7ኛ/  ከነዚህም በተጨማሪ፦  ቤተክርስቲያን መሳለም፣ ማስቀደስ፣ ፀበል መረጨት በራሱ በፈጣሪ በእግዚአብሔር ስም እና በቅዱሳን ስም ወደፈለቀው ፀበል ቦታ በመሄድ በአባቶች እጅ መጠመቅ ፣ በመስቀል መባረክ፣ እምነቱን መቀባት ፀበሉን መጠጣት ለተወሰነ ሱባኤ ግዜ ከአባቶች ጋር በመመካከር ከስጋዊ ህይወት እርቆ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተወስኖ መቆየት፤ የተለያዩ የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን በማንበብ እንዲሁም በድምፅ አና በምስል የተዘጋጁ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፉ ትምህርቶች፣ መዝሙሮች መከታተልን ማዘውተር።

8ኛ/ ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው!!!  አንድ ጊዜ ሳይሳካልን ብንወድቅ እንኳን ደጋግመንም ቢሆን በንስኀ እየተነሳን እስከመጨረሻው መቀጠል አለብን። በንስኀ አባቶቻችን መሪነትና መካሪነት በፅናትና በእምነት ሆነን ከዚህ ኀጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርም ብለን እስከምንላቀቅ ድረስ በፅናት መትጋት እንደሚገባ እንመክራለን።

በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩትን መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ሁሉንም በአንድ ጊዜ ሳይሆን እንደ መንፈሳዊ እውቀታችን እና እንደ ተፈተንበት የዝሙት አይነትና መጠን በማገናዘብ እየፈፀምን መንፈሳዊ ህይወታችንን ደረጃ በደረጃ በማሳደግ ሳናቋርጥ በምናደርገው ፅኑ ተጋድሎ መንፈሱ ራሱ ተቃጥሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእኛ ይለያል።   


ስለዚህ ጠያቂያችን፤ ከላይ የተዘረዘሩትን መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ሁሉንም በአንድ ጊዜ ሳይሆን እንደ መንፈሳዊ እውቀታችን መጠን ደረጃ በደረጃ በንስኀ አባቶቻችን መሪነትና መካሪነት በፅናትና በእምነት ሆነን ሳናቋርጥ ብንጋደል ይህን ኀጢአት የሚያሰራን መንፈሱ ራሱ ተቃጥሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእኛ ይለያል።   

መልስ፦ እንዲህ አይነቱ ኀጢአት በዘመናችን በሰይጣን መንፈስ የሚመሩ ሰወች ያመጡት አዲስ የኀጢአት ፍልስፍና ስለሆነ ምንም እንኳን ብዙ ሰወች በዚህ ኀጢአት እየወደቁ መሆኑ ቢታወቅም እንኳን በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነገር አይደለም። በዚህ አይነት ኀጢአት የሚፈተኑ ወገኖች ወደው የገቡበት ቢመስልም ውስጣዊ ግፊቱ ግን የሰይጣን ሃሳብ ስለሆነ ከቤተክርስቲያን አባቶች እና መምህራን ምክር እና ተግሳፅ በመቀበል በዚህ ኀጢአት የተጠናወተን መንፈስ ጨርሶ እስከሚለቀን ዘወትር በፀሎት፣ በስግደት፣ እና በመንፈሳዊ ትምህርት መታገል አለብን። ስለዚህ ጠያቂያችን ኀጢአትን ፈፅመን ንስሓ ለመግባት ምንም አይነት የጊዜ ገደብ አያስፈልገውምና፤ በመጀመርያ የፈፀምነውን በደል በግልፅ በማመን ወድያውኑ ለንስሓ አባታችን መናዘዝ አለብን። ከዚያም እንዳሉትም ፀበል አንዱ የንስሐ መንገድ ስለሆነ ከየኅጢአት ሥራችን ለመመለስ በቁርጠኝነት ወስነን፤ እንዲህ አይነት ኀጢአት ከተፈፀመበት 3 ቀን በኋላ ፀበል ለመጠመቅም ሆነ ለመጠጣት እንችላለን።  ዋናው ግን ንስሓ መግባት እና ዳግም በኀጢአት ወድቀን እግዚአብሔርን ላለማሳዘን አጥብቀን ፈጣሪን በፀሎት መጠየቅ አለብን።  ስለዚህ ጠያቂያችን እስከመጨረሻ ድረስ ከእንደዚህ አይነት ክፉ መንፈስ ለመላቀቅ እንዲችሉ በምክር እንድናግዝዎ ካስፈለገ በውስጥ መስመር ያግኙን።

መልስ፦ ጠያቂያችን ሰዶማዊነት እና ተዛማጅ ጉዳዮች በሚመለከት ከፍተኛ የኅጢአት አይነት እንደሆነ መልእክት ማስተላለፉችንን እናስታውሳለን። አሁንም ከራስም ጋር ሆነ የሰዶማዊነት መንፈስ ባለበት የዝሙት ኀጢአት ስራ ፤እንኳን ክህነት ሊኖረው ቀርቶ በነፍሱም በኩል ከባድ የንስሃ ቀኖና ካልፈጸመ በስተቀር በፈጣሪው ዘንድ ያስጠይቀዋል። በእርግጥ የሰው ልጅ ለኅጢአት ባይፈጠርም ለኀጢአት የሚሰማማ ስጋ ስለለበስ በዚሁ ደካማ ስጋው አስቦበትም ይሁን ሳያሰበው ሰይጣን ደካማ ጐኑን ወይም የሃሳብ ዝንባሌውን ፈልጎ በሰውየው ላይ በረቂቅ መንፈሱ አድሮ ስለሚዋጋ ሁሉም ሰው በተለያ የጥፋት መንገድ ሲስናከል ማየት የተለመደ ነገር ነው።ከጥቂት ፍፁማን በስተቀር ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ ፣ከአዋቂ እስከ ህፃን ድረስ በተለያየ ጥፋት ውስጥ ሁሉም የተጠመደ ነው። የሆነ ሆኖ ብዙ ሰዎች ኀጢአት ሰለሰሩ እና ብዙ ኀጢአት ስለተፈጸመ ፥ኀጢአትን ቀላል አያደርግም ወይም ደግሞ የእኔ ኀጢአት ከእከሌ ኀጢአት ያንሳል ወይም የእከሌ ኀጢአት ከእኔ ኀጢአት ይበልጣል በሚል የማሻሻያ ሃሳብ ሊወሰን የሚችል አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ አባላቶቻችን ከኀጢአት ጋር በተያያዘ የሚኖረን አመለካከት ጥልቅና ቁርጠኝነት ሊኖረን ያስፈልጋል። ይህ ማለት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቤተክርስቲያን ከውስጡ ክፍል ከካህናት እስከ ምእመናን ብዙ ያልተለመዱ እና የሚዘገንኑ የኀጢአት አይነቶች ማየት እየተለመደ ስለመጣ ይህ መጥፎ ልምድ ደግሞ ኀጢአትን እንድንለማመድና እንድንንቅ ወይም ቸላ እንድንል ሰይጣን በስውር ምስጢሩ ሁላችንንም የማደንዘዣ መርፌ የወጋን እስኪመስል በኀጢአት እንቅልፍ ውስጥ ያለን ሰዎች እጅግ ብዙ ነን።

ስለዚህ ካህንም ሆነ ምእመን በሰራው ኀጢአት ከክብሩ ይዋረዳል፤ በእግዚአብሔር ፀጋ የተሰጠው ክህነትም ሆነ መንፈሳዊ ሃይል ከሱ ይወስድበታል።: በንስሓ ሲመለስ ግን ለክህነታዊ አገልግሎት መብቃት ባይችልም የእግዚአብሔርን ሰማያዊ መንግስት ለመውረስ ግን ይታደላል።

በራሳቸው የዝሙት ሃሳብ የፈፀሙ በሌላ በኩል አካላዊ ድንግልናቸውን ያላጡ ወይም የግብረስጋ ስጋ ግንኙነት ያላደረጉ ተክሊል ይገባቸዋል ወይ ተብሎ ስለተጠየቀ በሚመለከት የተሰጠ ምላሽ።

ከሁሉ በፊት መታወቅ ያለበት ከራሳቸው ጋር የዝሙት ሃሳብ ለመፈፀም ተነሳስተው በሃሳብና በምኞት ራሳቸውን በሰይጣናዊ ስራ ተገዚነት የሚያደርጉ ሰወች አካላዊ የዝሙት ግብረ ስጋ ከሚፈፅሙት ሰወች የበለጠ ኀጢአት ነው። እንዲያውም ከሰዶማዊነት መንፈስ ጋር ይያያዛል። ይህ ማለት 21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ሰይጣን በግልፅ የሰለጠነበት የመጨረሻው ዘመን ስለሆነ ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ አዋቂነን እሚሉ ሳይቀሩ አብዛኛው ሰው ለማለት ይቻላል በዚህ ኀጥያት እየወደቁ መሆኑን ብዙ የመረጃ ምንጮች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ እንደ ቅዱስ መጽሐፍት አስተምሮ ከስነ-ተፈጥሮ ሕግ ውጪ የሆነ ድርጊት ስለሆነ በዚህ ክፉ ተግባር እያወቁ የወደቁ ሰወች ቢኖሩ ንስሃ ገብተው መንግስተ ሰማይ መውረስ ይችላሉ እንጂ በስርአተ ተክሊል ጋብቻ መፈፀም ግን አይችሉም። 

ነገር ግን በልጅነት እድሜ ሳያውቁ እና ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ግንዛቤ ወይም መንፈሳዊ እውቀት ሳይኖራቸውና ተፈጥሮአዊ ነውር መሆኑንም ሳይገነዘቡ የፈፀሙት ከሆነ የቅርብ የነፍስ ሀኪማቸው በሆነ የነፍስ አባታቸው የቀኖና ንስሐ ተሰጥቷቸው ንስሃቸውን ሲጨርሱ በስርአተ ተክሊል ጋብቻ መፈፀም ይችላሉ። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የጥፋተኛው ሰው የግንዛቤ ደረጃ እና የጥፋቱ መጠን ነው።

መልስ፦ ጠያቂያችን፤ በዋነኝነት መረዳት ያለብን ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ክርስቲያን  ከጋብቻ በፊት ቃልኪዳን  ገብተው እያሉ ግንኙነት ማድረግ አይፈቀድላቸውም። ምክንያቱም ከጋብቻ በፊት የሚደረገው የግብረስጋ ሩካቤ እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ስንመለከተው በዝሙት መንፈስ የተፈፀመ ግንኙነት እንጂ በስርአተ ቤተክርስቲያን የተፈቀደ አይደለም። ስለዚህ ከጋብቻቸው በፊት ገና በቃል ኪዳን በመተሳሰብ እያሉ የስጋ ሩካቤ ካደረጉ በየግላቸው መቁረብም መቀበልም የለባቸውም። ስለፈፀሙት ስህተት በአንቀፀ ንስኅ መሰረት ንስኅ ገብተው ከግብረ ስጋ ግንኙነት እርቀው የጋብቻቸው እለት ቅዱስ ቁርባን መቀበል ይችላሉ። ስለዚህ ጠያቂያችንም ከጋብቻ በፊት እንዲህ አይነት ስህተት ፈፅመው ከሆነ ወደ ንስኅ አባትዎ ቀርበው በመመካከር ተገቢውን ቀኖና መቀበል አለብዎት በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

መልስ፦ ከትዳር አጋርዎ ጋር በተከሰተው አለመግባባት ምክር እንድንሰጥዎ የጠየቁን አባላችን፤ በሰው ልጅ የህይወት ጉዞ ውስጥ የማያጋጥም ፈተናና ችግር የለም። በእርግጥ በመካከላችሁ ያጋጠማችሁን ፈተና ስንሰማ በእኛም በኩል እንደመንፈሳዊነት ስናየው አሳዛኝ ገጠመኝ ነው። ነገር ግን ጠያቂያችን ጉዳዩን በትዕግስትና በአፅንዎት መመልከት ያለብዎት የከፉ ነገር ሁሉ መነሻና መድረሻ የሆነው እርኩስ መንፈስ በየጊዜው በሰው ልጅ ላይ የማያመጣው ፈተና የለምና በእናንተም ላይ የተከሰተው ፈተና አሳዛኝና አስደንጋጭ አድርገን ብናየውም ነገር ግን በሰው ላይ ያልደረሰ አዲስ ክስተት እንዳልሆነ መገንዘብ አለባችሁ። በመካከላችሁ የተፈጠረውን ፈታኝ ክስተት ብቻ በመመልከት ለ10 ዓመታተ ያህል የደከማችሁበት የትዳር ጉዞ ውስጥ የገነባችሁትን ህይወት ባልተጠበቀ ገጠመኝ የተከሰተውን ነገር በማሰብ አፈራርሶ እንዳልነበረ ማድረግ ጉዳቱ በምድራዊ ኑሯችሁ ብቻ ሳይሆን በሰማያዊ ህይወትም ከእግዚአበሔር የሚለይ ፈተና ነው።

ስለዚህ በግላችንም ሆነ እንደ ሀገራዊ ባህላችንና የማህበረሰቡ አመለካከተ ተፅኖ አንፃር በመካከላችሁ የተከሰተውን ችግር ለመሸከም እጅግ ከባድ ቢሆንም እንደ መንፈሳዊ ህይወት በትዕግስት ሁነን ስናስበው ግን ማንኛውም በደልና ጥፋት በትምህርት በተግሳፅ በንስኀ ህይወት አስተካክሎ ለመመለስ እንደሚቻል በማመን ሁለቱም ወገን ሰከን ብለው እስከመጨረሻው ድረስ ሁሉን ነገር ለእግዚአብሔር በመስጠት በይቅርታና በምህረት ማለፍ ይገባናል። እኛ ኀጢአተኞች ስንሆን በእኛም ላይ የደረሰብንን ችግር እንደ ትልቅ ጥቃትና ውርደት ቆጥረን ኑሯችንን ፣የግል ህይወታችንን ፣ የቤተሰብ ህይወታችንን የሚጎዳ ነገር እንዳንፈፅም ምክራችንን እንለግሳለን።

ከሁሉም በላይ የእኛን ህይወት ማንነት የተደበቀውንም ሆነ የተገለጠውን ድክመታችንን የሚያየው አምላካችን ምን ያህል እንደታገሰን ስንመለከት ሁሉን ነገር በትዕግስት እንድንመለከት ያደርገናልና ጠያቂያችን ማድረግ ያለብዎት፦

1ኛ/ እስካሁን ያሳለፋችሁትን የትዳር ህይወት በማሰብ፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ቸርነት ያፈራችኋቸውን ሁለት ህፃናት በማሰብ፣

2ኛ/ ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ በስህተትና በፈተና የመውደቅ አጋጣሚው ያለና የነበረ ስለሆነ፣

3ኛ/ እውነተኛ ክርስቲያን በፈጠጠ አይኑ ያየውንና በጆሮው የሰማውን ክፉ ነገር ሁሉ በትዕግስትና በፍቅር የሚያሸንፍ መሆን ስላለበት፣ በተቻለ መጠን እስከመጨረሻው ፀጥታ ድረስ ወደ ቀደመው ህይወታችሁ ለመመለስ በራስዎ በኩል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብዎት። የተከሰተውን ጥፋትም በቤተክርስቲያን አባቶች ትምህርት እና ምክር ተግሳፅና የንስኀ ህይወት በማሰጠት ማስተካከል ይቻላል።

 

በአጠቃላይ በእንዲህ አይነት አሳዛኝ ህይወት ውስጥ የወደቁት ባለቤትዎ በንስኀ አባትም ሆነ በሌላ ሽማግሌ አማካኝነት እኛን ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ቢያመቻቹ እግዚአብሔር ቢያግዘን ችግሩ ሊስተካከል ይችላል።

 

ሌላው፥ በአስማትም ሆነ በሟርት ተደረገብኝ የሚሉትን ፈተና ለማስወገድ ወደ ቤተክርስቲያን አባቶች ቀርበው ችግርዎን በመናገር ቢያንስ ለአንድ ሱባኤም ቢሆን ፀበል በመጠመቅ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ከችግሩ ለመውጣት ይችላሉ። ሁልገዜ ሃይላችን እና መፅናኛችን የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ተከታታይ ትምህርት እና ምክር የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በተጨማሪም በግልዎ ዘወትር በቋሚነት የሚፀልዩትን ፀሎት ለይተው ሳያቋርጡ መፀለይ ይገባዎታል። እነዚህን እና የመሳሰሉትን የቤተክርስቲያን አገልግሎት በማግኘት ከችግሩ ፈፅሞ መውጣት ስለሚችሉ ተስፋ ሳይቆርጡ በእምነት ከዚህ በላይ የሰጠንዎትን ስራ ላይ እንዲያውሉ እንመክራለን።

መልስ፦ ጠያቂያችን፤ ወደ ሴቶች በቀረቡ ጊዜ ቀድሞ የዘር መፍሰስ ልምድ ያጋጥመኛል ያሉት ጥያቄ ሃሳቡን ለቤተክርስቲያን መምህራን ወይም ለመንፈሳዊ አባቶች ለማማከር መምረጥዎ እጅግ የሚያስደንቅዎ ቢሆንም ፤ ወደ ዋና ሃሳብዎ ስንገባ ግን በመጀመሪያ ወደ ሴት ስቀርብ ያሉት አገላለፅ ከህጋዊ የትዳር ጓደኛ ጋር ከሆነ ብቻ ነው በእኛ በኩል እንደትክክለኛ ጥያቄ የምንቆጥረው። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ከዝሙት ሃሳብ ከብዙ ሰዎች ጋር መሄዱ እንዲህ አይነት ሁኔታ ማጋጠሙ ስጋዊ ጠባይ ቢሆንም እንደ መንፈሳዊ ግን እጅግ የተከለከለ ነው። ስለዚህ እርስዎ ከህጋዊ ጋብቻ ጋር ይህ ችግር እንዳጋጠመዎት በማመን ብቻ የመንሰጥዎ ምላሽ ይሆናል ማለት ነው።

 እርኩሳን መናፍስት ከሰው በከፋ ሁኔታ ቀናተኛ እና ምቀኛ በመሆናቸው የሰውን ልጅ በተለያየ ጠባይ ይቆራኙታል። ከሰዎች ጋር መቆራኘታቸውንም እራሱ ባለቤቱ ያማያውቀው ነገር ግን በህይወቱ የሚያስተውለው ችግሩ ጎልቶና ተደጋግሞ ሲደርስበት ብቻ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሰው ውጊያው ከስጋዊያን እና ከደማዊያን ጋር ሳይሆን ከረቂቃን መናፍስት ጋር እንደሆነ በመልዕክቱ የገለፀልን።

 በቅዱስ ወንጌል እንደተፃፈ ማርያም መግደላዊት በተባለችው ሴት ላይ 7 አጋንንት ሲያድሩባት  ሰባቱም የተለያየ የ 7 ኀጢአት ያሰሯት እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። ስለዚህ አጋንንት ከቁጥራቸው የክፋት ስራቸው በእኛ ህይወት ላይ ሲሰለጥኑ የተለያየ የክፋት ስራቸውን ያሰራሉ። በሴት የሚመሰሉ አጋንንት የሴት ስራ ያሰራሉ፣ በወንድ የሚመሰሉ አጋንንት የወንድ ስራ ያሰራሉ። ብቻ በምርምርና ቁጭ ብሎ እንደ ሂሳብ በስሌት የማይደረስበት ስፍር ቁጥር የሌለው የክፋት ስራ አላቸውና እርስዎ ከዚህ ክፉ መንፈስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይድኑ ዘንድ ጉዳዩን በዝርዝር ከተረዳን በኋላ የመፍትሄ ሃሳብ የሚሆን ምክር እንድንሰጥዎ በውስጥ መስመር በሚላክልዎት አድራሻ እንዲያገኙን ሆኖ ፤ እስከዚያው ድረስ ግን በሚችሉት አቅም ፀሎት መፀለይ አለብዎት፤ ቢችሉ ድርሳነ ሚካኤልን፣ ወንጌለ ዮሐንስን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ ዳዊትን ቢፀልዩ ፣ እንዲሁም ለተወሰነ ለአንድ ሱባኤም ቢሆን ይህንኑ ችግርዎትን ለካህን ነግረው ቢጠመቁና ሁሌም ከእርስዎ የማይለዩ ፀሎት መፃህፍትን እና መስቀልን መያዝ ቢያዘወትሩ በዚህ ሁሉ ያለውን ለውጥ በገሀድም ቢሆን ወይም በራእይ መልክ ምልክት ሊያዩበት ይችላሉ። በዋነኝት ግን እኛን ማግኘት ቸላ እንዳይሉ እንመክራለን።

መልስ፦አንድ ክርስቲያን የሆነ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ድንግልናቸውን ጠብቀዋል  ሲባል : –

#1- ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት አለማድረጋቸው በራሳቸው ቃለ መሓላ÷ በንስሐ አባትና በቤተሰበ ሲረጋገጥ

#2- በሃይማኖታቸውና በክርስቲያናዊ ስነ ምግባር ጸንተው ከእግዚአብሔር ቤት ሣይለዩ ቅዱስ ቁርባን እየተቀበሉ  ስለመ ኖራቸው ቤተክርስቲያን ስትመሰክርላቸው

#3- ከጋብቻ በፊት  የድንግልና ክብራቸውን  ሊያሳጣ የሚችል ሐጢአት ያልሰሩ ለምሣሌ ÷ የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ ጣዖት ማምለክ፣ ማስጠንቆል መሥረቅ  የመሣሰሉትን ጥፉቶቸ መፈጸም  ናቸው ።

#4- የወንድ ልጅ ድንግልና  ማረጋገጫ በ ራሱ ህሊና አምኖ ለነፍስ አባቱ ከሚገባው ቃል ኪዳን ዉጪ ሌላ አካላዊ ማረጋገጫ  አይኖርም   በእርግጥ ከምንም በላይ  ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ  ከሰው የሰወርነውን በደላችንን ሁሉ ሰለ  ሚያውቀው ለህሊናችንና ለሃማኖታችን ስንል እውነቱን እዉነት ሃሰቱን ሃሰት ልንል ይገባል         

#5- የሴት ልጅ ድንግልና ራሷ ፍጹም ታማኝ  እና ቅድስናዋን የጠበቀች ሁና እያለ :-  በተፈጥሮ ፣ በሕመም ምክንያት ፣ በአስገድዶ መደፈር ፣ በከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ (ክብደት) – በሕክምና እና በመሳሰለው ሁሉ አካላዊ የድንግልና ምልክቷ ባይገኝባት እንደ ቤተክርስቲያ አስተምሮ ሌላ ነውር እሰከአልሠራች ድረስ የድንግልና ክብሯን አያሳጣትም።   

 ስለዚህ ስለድንግልና ማንነት ማወቅ የምንችለው በተፈጥሯዊ ዕውቀትና በሳይንሳዊ ምርምር ወይም በሰውኛ ዕውቀት ሳይሆን ብቸኛ ዐዋቂው የራሳችን ውሳጣዊ ኅሊናና  የሁሉ ባለቤት ፈጣሪ ብቻ በመሆኑ መሠረታዊ የሆነውን ትምሕርተ ሃይማኖት ከማወቅ አልፎ ያለውን ድርሻ ለእግዚአብሔር ብቻ መስጠት አለብን ጠያቂያችን እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁሉ ለሚስጥረ ተክሊል ስርዓት የምንበቃባቸው ሲሆኑ

መልስ፦ ጠያቂያችን የቤተክርስቲያንን ቀኖና እና ስርዓት ለማክበር ብለው ለመረዳት መጠየቅዎ አግባብ ነው። ምክንያቱም “የእግዚአብሔርን ቃል አባትህን ጠይቀው እውነቱንም ይነግርሃል” ይላልና። በመሰረቱ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ 3 ቀን ከስጋ ስርዓት እንድንርቅ የሚደረግበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለኛ በተቀበለው መከራ በእለተ አርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው ለይቶ 3 መአልትና 3 ለሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ሐዋሪያት እና ከሱ ጋር ይከተሉት የነበሩት ደቀመዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ሳናይ የሚበላ አንበላም የሚጠጣም አንጠጣም ብለው በፆም ተወስነው ስለቆዩ ነው። ስለዚህ ዛሬም የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን አማናዊ ስጋና አማናዊ ደም ስለሆነ ያንን መነሻ አብነት አድርገን ለ 3 ቀናት ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን የምንቆየው ነው።

ስለሆነም ለምሳሌ አንድ ሰው እሁድ ቤተክርስቲያን ለመግባት ቢያንስ ከአርብ ማታ ጀምሮ ከስጋ ሩካቤ መቆጠብ አለበት ማለት ነው። ከዚህ ውጪ በፈተና ከወደቅን ግን የተለመደ የዘወትር ፀሎታችንን በቤታችን አካለ ስጋችንን ታጥበን በፀሎት ቤታችን ቆመን ማድረስ እንችላለን ወይም ወደ ቤተክርስቲያን ሄደን ከመግቢው ቅጽር ሆነን መፀለይ እንችላለን ማለት ነው።  

በማንኛውም ግዜ የፆም የፀሎት ሱባኤ በራሳችንም ይሁን በአባቶቻችን ቀኖና ተሰጥቶን የፆምና የፀሎት ሱባኤ በያዝን ግዜ፣ በእለተ ሰንበት እና በታወቁ በአላት ቀን ፈፅሞ ሚስትም ከባልዋ ተለይታ ወንድም ከሚስቱ ተለይቶ መኝታቸውንም የተለየ አድርገው የሚበላውንም የሚጠጣውንም ከተለመደው የአመጋገባቸው ስርአት ቀንሰው አጠቃላይ ፈቃደስጋቸውን ተቆጣጥረው ነው መፆም የሚገባቸው። ፆም ራሱን የቻለ ከእግዚአብዜር ጋር የምንገናኝበት የፅድቅ መንገድ ስለሆነ በዚህን ግዜ ማንኛውም ክርስቲያን የስጋ ፈቃዱን መቆጣጠር እንዳለበት የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። ይህን ስንል በቀኖና የተደነገጉ 7ቱ አፅዋማትና እንደገናም በአባቶቻችን ሱባኤ ተሰጥቶን የምንፆምባቸው አፅዋማትን ይመለከታል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል በማለት ለጠያቂያችን ይሄ ምክር እንዲደርስዎ አድርገናል።

መልስ፦ ስርአተ ተክሊል አስባችሁ በመካከል ላይ ራሳችሁን ለመግዛት ሳትችሉ በመቅረታችሁ በመካከል ባደረጋችሁት የስጋ ድካም ከስርአተ ተክሊል በፊት የድንግልናችሁን ክብር ስላጣችሁት የፈፀማችሁትን ጥፋት ለንስሓ አባት በመናገር ቀኖና ከተቀበላችሁ በኋላ በስጋው ደሙ መጋባት ትችላላችሁ። ስርአተ ተክሊል ግን መፈፀም አይቻልም። ዋናው ነገር ለስጋዊ ስም እና ዝና ተብሎ እግዚአብሔርን በሚያሳዝን ሁኔታ የማይገባንን ስርአተ ተክሊል ከመፈፀም ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ እውነቱን አረጋግጠን የምናገኘው ክብር በስርአተ ተክሊል ከምናገኘው ክብር እኩል ስለሆነ የሚያሳስበን እና የሚያስጨንቀን ነገር አይኖርም።

መልስ ፦ ጥያቄው መቅረቡን በአክብሮት ብንቀበለውም ነገር ግን ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ቅድመ ጋብቻም ይሁን ድህረ ጋብቻ ስላሉት ስለሚፈቀዱና ስለማይፈቀዱ ሁኔታወችም በስፋት መልእክት ማስተላለፋችን ይታወሳል። ይሁን እንጂ ጠያቂያችን ከዚህ በፊትም ያስተላለፍናቸውን መልዕክቶች ማየት ካልቻሉ አሁን ለጠየቁን ጥያቄ መረዳት ያለብዎ ማንኛውም ሃይማኖት ያለው ክርስቲያን ለአካለ መጠን ወይም ለአካለ ጋብቻ ደርሶ እና በሃይማኖት ስርዓትና በባህላዊ ትውውቅና በስርዓተ በጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት ማንኛውንም የአካለ ስጋ ሩካቤ ማድረግ ፈፅሞ ክልክል ነው። ለዚህም ነው በቅዱስ ጳውሎስ ስጋችሁን ለመግዛት ፍላጎታችሁን ለማሸነፍ ካልቻላችሁ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላል ያለው። በዚህ መሰረት ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ክርስቲያን የስጋውን ፍላጎት መግዛትና መቆጣጠር በማይችልበት የእድሜ ደረጃ ሲደርስ በሃይማኖት ስርዓትና በአገራዊ ባህል የፈለጋትን ወይም የፈለገችውን ተስማምተው ማግባት እንደሚችል ተፈጥሮዋዊ ማንነት ከእግዚአብሔር ተሰጥቷል። ከዚህ የተነሰ የተሰጠንን የነፃነት ፀጋ መጠቀም መቻል እንጂ ከጋብቻ በፊት የድብብቆሽ ስራወች መፈፀም እኛንም በነፍስ ይጎዳናል ከፈጣሪ ጋርም ያጣላናል በሰው ዘንድም መሀበራዊ ማንነታችንን ያዛባል። እና ጠያቂያችን በዚህ መልክ ስራ ላይ ብናውለው በእግዚአብሔር ዘንድም በረከትና መንፈሳዊ እድገት ያሰጣል በማለት እንመክራለን።

መልስ ፦ ለትዳር የተጫጩ ወንድና ሴት ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት የሚያደርጉት ግንኙነት እንደቤተክርስቲያን አስተምሮ የዝሙት ሃሳብ ነው። ምክንያቱም አንድ ሆነው ማንኛውንም የጋራ ህይወታቸውን ለመቀጠል ጋብቻቸውንም በአዋጅ በአደባባይ ለማስታወቅ በመንገድ ወይም በቀጠሮ ላይ እያሉ ያንን ቀጠሮ ማክበር አቅቷቸው ፍትወተ ስጋቸው አሸንፏቸው የሩካቤ ስጋ ቢፈፅሙ ግን እንደ ዝሙት ይቆጠራል።   ስለዚህ የጥፋቱ መጠን ታይቶ በንስኀ አባታቸው የንስኀ ቀኖና እና ቀጣይ ምክርና ትምህርት የሚሰጣቸው ይሆናል ማለት ነው።

ባልና ሚስት ሆነው ግንኙነት ከፈፀሙ ሦስት ቀን ሳይሞላ ቤተመቅደስ መግባት አይችሉም። በመሰረቱ ወደ ቤተመቅደስ ተጠግተን ለማስቀደስ ወይም ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል፣ ወይመሰ ጸበል ለመጠመቅ 3 ቀን ከስጋ ስርዓት እንድንርቅ የሚደረግበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለኛ በተቀበለው መከራ በእለተ አርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው ለይቶ 3 መአልትና 3 ለሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ሐዋሪያት እና ከሱ ጋር ይከተሉት የነበሩት ደቀመዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ሳናይ የሚበላ አንበላም የሚጠጣም አንጠጣም ብለው በፆም ተወስነው ስለቆዩ ነው። ስለዚህ ዛሬም የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን አማናዊ ስጋና አማናዊ ደም ስለሆነ ያንን መነሻ አብነት አድርገን ለ 3 ቀናት ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን የምንቆየው ነው።

በመሆኑም ህግ እና ቀኖና የሆነውን ነገር በህግነትና በቀኖናነቱ የተወሰነውን እውነቱን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በደካማ ስጋችን ተፈትነንና ስጋዊ ምኞት አሸንፎን ቀኖናን የሚሽር ስህተት ፈፅመን ብንገኝ ወይም ደግሞ ከ 3 ቀን ባነሰ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን ጠያቂያችን ያነሱትን ስህተት ፈፅሞ ቢገባ ያ ክርስቲያን ፈፅሞ የተወገዘ የተረገመ ነው ማለት አይደለም። የቤተክርስቲያን ስርዓት እና ቀኖና በመሻሩ ተግሳፅና ምክር ሊሰጠው ይችላል። ወደፊት እያወቀ እንዲህ አይነት ጥፋት እንዳትፈፅም ተብሎ ምክር ይሰጠዋል። ይሄ የሚሆነው በህጋዊ ጋብቻ ተወስነው ለሚኖሩ ነው። ከዚህ ውጭ ለሚሆነው ግን እንኳን ቤተክርስቲያን በድፍረት ለገባንበት ይቅርና ከሕግ ውጭ ላደረግነው ግንኙነትም ከባድ የቀኖና ቅጣት ይጠብቀናል። በዚሁ መሰረት ጠያቂያችን ቀኖና ባለመሻር እና ከእግዚአብሔር በረከት ለማግኘት በምናደርገው መንፈሳዊ አገልግሎት በነፍስ የምንጎዳበት እርግማን እንዳያመጣብን ከወዲሁ ክርስቲያናዊ ስነምግባር እና ጥንቃቄ ሊኖረን ይገባል በማለት መልዕክታችን እንዲደርስዎት አድርገናል።

ጠያቂያችን ሃሳብ እና ዝሙት የሚለው ቃል በቤተክርስቲያን አተረጓጐም ብዙ ትርጉም አለው ። ይህ ማለት አንድ ክርስቲያን የዝሙት ስራ ሊሰራ ፣ሰው ሊገድል ፣ ገንዘብ ሊሰርቅ፣ አምልኮ ባዕድ ሊፈፀም ወይም ለጣኦት ሊያመልክ ፣ ሊያስጠነቁል፣ ሊጠነቁል ፣ሊያሟርት የቀን ቀጠሮ ይዞ እግዚአብሔርን ለማታለልና ለመደለል ወይም እግዚአብሔርን እንደ አላዋቂ ለመቁጠርና ለመፈታተን ወደ ቅዱስ ቁርባን መቅረብ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ ማስቀደስ፣ መጸለይ ከንቱ ነው ማለት ነው። ሃሳብ ማለት ፍጹም መላ ህይወታችንን ለኀጢአት ተገዢ ለማድረግ መወሰን ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ግዜ በሃሳብ እየተዋጋን ታግለን እያሸነፍነው በአላማችን የምንኖራቸውን እንደማይመለከት መገንዘብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሰው ልጅ የሚያስተውል እና ሁሉን ለይቶ የማወቅ ጥበብ የተሰጠው የሚያስብ ስለሆነ በአይናችን ያየነው ነገር ወዲያውኑ በሃሳብ ሊፈትነን ይችላል ፤ነገር ግን ከዋናው አላማችን እስካልወጣን ድረስ ውስጣችንም ስለሚፀፀትበት እና የህሊና ንስኀም ስለምንገባበት ኀጢአተኞች ሊያስብለን እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል፡፡

መልስ ፦ በመሰረቱ ባል እና ሚስት የስጋ አስተሳሰብ በሆነ ፈተና ለሚያጋጥማቸው ችግሮች እንዲፋቱ አይፈቀድላቸውም። ከአቅም በላይ በሆነ ጉዳይ ለምሳሌ ጠያቂያችን እንዳሉት በዝሙት ምክንያት ከተፋቱ ግን፦

  1. በየግላቸው ስጋው ደሙን ለመቀበል የሚችሉት በቀጣይ ህይወታቸው ሴቷም እንደስዋ በቁርባን ተወስኖ የሚኖረውን ለማግባት፣ ወንዱም እንደሱ በቁርባን ተወስና የምትኖረውን ለማግባት ከሆነ እየቆረቡ ለመኖር ይችላሉ።
  2. ወንዱም ሆነ ሴቷ አብረው የነበሩበት የጋብቻ ቆይታቸውንና የተፋቱበትን ዋና ምክንያት ተናዘው እንደነሱ በሃይማኖትና በምግባር የሚወሰነውን ባል ወይም ሚስት በማግባት እየቆረቡ መንፈሳዊ ህይወታቸውን ማስቀጠል።
  3. ሁለተኛ ላለማግባት የወሰኑ ከሆነ ንፅህናቸውን እና ቅድስናቸውን ጠብቀው በየግዜው የነፍስ አባታቸውን እያማከሩ በስርዓተ ቁርባን ህይወታቸውን ማስቀጠል ይችላሉ።
  4. ሌላው ቀጣይ ህይወታቸውን ስርዓተ ምንኩስና በመወሰን መንፈሳዊ ልባዊ ውሳኔ ካላቸውም በስርዓተ ቁርባኑ ተወስነው ከቆዩ በኋላ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት የንስሓ አባታቸውን አማክረው ለምንኩስና የሚያበቃቸውን መስፈርት ሲያሟሉ እንዲመነኩሱ ይደረጋል ማለት ነው።
  5. ዲያቆን ወይም ቄስ ሚስቱ ብትሞትበት ወይም ከሱ አቅም በላይ በሆነ ፈተና ቢፋታ፤ ያለ ሚስት የሚቀድሰውም ሆነ አባት የሚሆነው እስከ 6 ወር እንደሆነ በፍትሐ ነገስት ተወስኗል። ከዚያ በኋላ ግን ወይ መንኩሶ በክህነቱ ይቀጥላል፤ ወይም ፈተናውን የማይችለው ከሆነ ለቤተክርስቲያን አባቶች በግልፅ ተናግሮ በቅዱስ ቁርባን ተወስና የምትኖረውን ያገባል። ከዚህ በኋላ ግን መቀደስም ሆነ አባት መሆን አይችልም። የውጭ አገልግሎቱን እያከናወነ እየፀለየ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃውን የቱሩፋት ስራ እነሰራ መኖር ይችላል።

ስለዚህ ጠያቂያችን በአጭሩም ቢሆን ይህንን ማብራሪያ እንዲደርስዎ ስላደረግን አንብበው እንዲረዱት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።

መልስ፦ ክርስትናን በአለማ በመግለፅ እስከመጨረሻው ያለውን መንፈሳዊ ግዜያችንን ለማጠናቀቅ እንዳንችል ሰይጣን በብዙ መንገድ የፈተና መሰናክል የማከናወኑ ነገር የተለመደ የህይወት ፈተና ነው። ስለዚህ ራሳችንን ከኅጢአት አግልለን እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን ራሳችንን መካድ ያስፈልጋል፤ ማለትም ክርስቲያን ለመሆን የክርስቲያንን ስራ መስራት ያስፈልጋል። ክርስቲያን ደግሞ በስጋ ምኞት ተፈትኖ የወደቀበት ኀጢአት ቢኖር እንኳን ለሰራው ኅጢአት ጊዜ ሳይሰጥ ወድያውኑ በንስሓ ህይወት ከወደቀበት ይነሳል። 

ጠያቂያችንም ሰወች ሁሉ ከሚፈተኑበት ኅጢአት እርስዎም በዚህ ፈተና ውስጥ መውደቅዎ እንደ መንፈሳዊነት የሚያሳዝን ነገር ቢሆንም በንስሓ ህይወት ተመልሰው ከወደቁበት የኅጢአት ጉድጓድ ለመነሳት ፈቃደኛ መሆኖም እጅግ የሚያስደስት በመሆኑ እርስዎ እየተፈተኑበት ያለውን የስጋ ፈቃድ እኛ ከምንሰጥዎ መንፈሳዊ አባት ጋር በመመካከር እና ትምህርት በመውሰድ እንዲሁም ዘወትር በፀሎት፣ በስግደት፣ ቢጋደሉ  ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ለዘመናት የሚፈታተንዎትን የሰይጣን ፈተና ተላቀው እንዲወጡ ነፃ እንዲሆኑ ያደርጉዎታል። በተለያያ መንገድ የሚፈታተነንን የሰይጣን ሃሳብ በመንፈሳዊ ቁርጠኝነት አላማችንን አፅንተን በእውነተኛ ሃይማኖትና ምግባር መጋደል ከቻልን እንኳንስ ይሄንን ትንሹን የኀጢአት ጥፋት ቀርቶ ሌላውን አስጋራሚ የፅድቅ ስራ ሁሉ ለማከናወን እንድንችል አምላከ ቅዱስ እግዚአብሔር ኃይሉን እና ጥበቡን ያቀዳጀናል። ስለዚህ ከዚህ ከማይጠቅም የዝሙት እና በተፈጥሮ እንኳን ካልተፈቀደው ሰይጣናዊ ዝሙታዊ ስራ ፈጥነው ይወጡ ዘንድ በአስቸኳይ መንፈሳዊ ምክር እንድንሰጥዎ በውስጥ መስመር ያነጋግሩን።  

ከማያውቁት ወንድ ጋር በህልመ ለሊት ግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የሰው ልጅ በራሱ ስጋዊ ስሜት አስቦበትና ፈለጎት ያደረገው ኅጢአት ስላልሆነ መደበኛ የንስሓ ቀኖና አያስፈልገውም። ነገር ግን በህልመ ሌሊት እየመጣ ለወንዱ ሴት መስሎ፣ ለሴትዋ ደግሞ ወንድ መስሎ የሚገናኝ ስጋ የለበሰ እርኩስ መንፈስ ስለሆነ ስጋዊ ህይወታችንንም ሆነ መንፈሳዊ ህይወታችንን ስለሚያበላሸው ከኛም ተለይቶ መወገድ ስላለበት ለአባቶች ቀርቦ በመናዘዝ ልዩ ፀሎት፣ ስግደት፣ እና ጥምቀት ማደረግ ያስፈልጋል። ሁሌ የሚፈታተነን ክፉ መንፈስ ከኛ ተለይቶ እስከሚጠፋልን ድረስ የተለያየ ልዩ ፀጋ ያላቸው አባቶች በፀሎት እንዲያስቡን በማድረግ እኛም በግላችን በምንችለው አቅማችን ዘወትር መፀለይ ያስፈልገናል። እንዲህ በሆነ ግዜ እርኩስ መንፈሱን የእግዚአብሔር ቃል ስለሚያቃጥለውና እኛ ጋር ያለው መንፈሳዊ ህይወትም ስለሚዋጋው ፈፅሞ ይጠፋል ፤ ስለዚህ ጠያቂያችን ይህንን ጉዳይ ንስሓ እንሚያስፈልገው አድርገው ማሰብ የለብዎትም። ስለዚህ ይህ ሲሆን ስንት ቀን ነው ጸበል ከመጠመቅ እና ሌሎች መንፈሳዊ ተግባራት የምከለከለው ላሉት፤ አንኳንስ ለመቆየት እንዲያውም ወድያውኑ ሰይጣን ሊፈትነኝ መጣ ብለን በዛኑ ቀን ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ፀበል መጠመቅና በመስቀል መዳስ እንችላለን

መልስ፦ጠያቂያችን እንዳሉትም በአፇማት እና  የበዓል ቀናት ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ከሩካቤ ስጋ መጠበቅ እንዳለብን የቤተክርቲያን ቀኖና ይደነግጋል። እንዴት ማክበር እንዳለብን በሚመለከት፦

1ኛ/ ስለአፇማት፦ ለምሳሌ ሮብ ለመፆም ማክሰኞ ለሮብ፣ ሐሙስ ለአርብ መታቀብ አለብን ማለት ነው።

2ኛ/  ሌሎችን የአዋጅ ፆም በሚመለከት ፦ ወንዱ ከሴቷ፣ ሴቷም ከወንዱ እርቃ በሱባኤ ተለይቶ ማሳለፍ እንዳለብን የቤተክርስቲያናችን ቀኖና ያዛል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ፈተና ፈቃደስጋችን አሸንፎን በዚህ ምኞት ከወደቅን ላጠፋነው ጥፋት የህሊና ፀፀት ተፀፅተን ለንስሐ አባታችን ወደፊት የምንነግረው ሁኖ ፆምና ፀሎትን ሳናቋርጥ እስከመጨረሻው ልንፈፅም ይገባናል።

3ኛ/ በአላትን በሚመለከት እለተ ሰንበት፣ የእመቤታችን በዓል፣ የባለቤቱ የጌታችን የመድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአላት ፣ እና ሌሎችም ታላላቅ የታወቁ በዓላት ከዋዜማቸው ጀምሮ ከሩካቤ እርቀን ማክበር አለብን።

በተጨማሪም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ለመቁረብ ወይም ለማስቀደስ ከዚህ በፊ ስለ ቅዱስ ቁርባን መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ባስተላለፍነው ትምህርት ለ 3 ቀናት ንፅህናችንን እና ቅድስናችንን ጠብቀን መቆየት እንዳለብን ማብራራታችንን እናስታውሳለን። ስለዚህ በዚህና በሌሎች ጥያቄዎች  ዙርያ ያስተላለፍናቸውን መልእክቶች ከድረገጻችን በመመልከት ተጨማሪ ትምህርት  እንዲያገኙበት ከዚህ በታች ሊንክ ልከንልዎታል።

መልስ፦ ጠያቂያችን እንዲረዱትና እንዲያውቁት የሚያስፈልገው ነገር በስርዓተ ተክሊል መጋባት ያለባቸው ጥንዶች ወይም ወንድና ሴት ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያን ስርዓት ተክሊል ከመፈፀማቸው በፊት ስለወደፊት የጋብቻ ፕሮግራማቸውና ሰለሚቀጥለው የትዳር ኑሯቸው ተነጋግረው ቃል ኪዳን ከፈፀሙ በኋላ መንፈሳዊ ሰላምታ እየተለዋወጡ ለቀጣይ ህይወታቸውም የሚጠቅማቸውን ነገር ለመስራት በሃሳብና በተግባር እየተረዳዱ ስለመንፈሳዊ ህይወታቸውም እንዴት መፀለይና መበርታት እንዳለባቸው እየተመካከሩ፣ ወደ ቤተክርስቲያንም ዘወትር እየቀረቡ ቅዱስ ቁርባን በየግላቸው እየተቀበሉ እስከ ጋብቻቸው ድረስ መቀጠል እና ይሄንን የመሳሰለውን ቅድመ ሁኔታ መመካከር እንጂ ፤ ከዚህ ያለፈ በስጋዊ ፍትወት እየተቃጠሉ መዳራት እና የስሜት ፆራቸውን ከግብረ ስጋ ግንኙነት ባልተናነሰ እየፈፀሙ የቆዩ ከሆነ ስርዓተ ተክሊል አይፈፀምላቸውም። ይልቁንም ስላደረጉት ሰህተት ለንስኀ አባታቸው በግልጽ በመናዘዝና ጥፋታቸውን በማመን በፈፀሙት ጥፋት መጠን እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ንስኀ ተቀብለው ንስኀቸውን ከጨረሱ በኋላ በቅዱስ ቁርባን ሊጋቡ ይችላሉ እንጂ በበረከት ፈንታ መርገም ሊያመጣባቸው የሚችለውን ሰህተት ወይም ድፍረት መፈፀም የለባቸውም። እግዚአብሔር ላስቻለውና ከዝሙት ጠንቅ ጠብቆት በመንፈሳዊ ጽናት ለቆየ የክርስቲያን የድንግልና ዋጋ ወይም የክብር መገለጫ የሆነውን ስርዓተ ተክሊል በመፈጸም ጋብቻቸውን በስጋወ ደሙ ማረጋገጥ ከሁሉ የሚበልጥ የተቀደሰ አላማ ነው። በአንዳንድ ፈተና በኀጢአት ሰህተት ከወደቅን ግን ለስጋዊ ክብራችን ተጨንቀን ወደ ሁለተኛ ጥፋት የሚያገባንን በድፍረት ስርዓተ ተክሊል መፈፀም ግን እጅግ ነውር ስለሆነ ሁላችሁም ይሄንን መልዕክት በአጽንዖት እንድትረዱት አደራ እንላለን።