ስለ ዝሙት ቁ. 2
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ዝሙት ጥያቄና መልስ ቁ. 2
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች ቁ. 2
መልስ ፦ ጠየቂያችን እንዳቀረቡት ወንድም ሆነ ሴት ለአካለ መጠን ደርሷል ወይም ለህግ ጋብቻ ደርሷል የምንለው ወንድ ቢያንስ ከ 20 አመት በላይ ሲሆን፣ ሴትም ቢያንስ 15 አመት እድሜና በላይ ስትሆን ነው። በእርግጥም የመጀመሪያዎቹ የሰው ዘር መገኛ የሆኑት አዳም እና ሄዋን ሲፈጠሩ ለአካለ መጠን የደረሱ ሆነው እንደሆነ የስነ-ፍጥረት መፅሐፍ ይነግረናል። ይህ ማለት አዳም አባታችን የ 30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ እንደተፈጠረ እናታችን ሄዋን የ 15 አመት ሴት ሁና እንደተፈጠረች ከዚያም ከተፈጠሩባት ደብር ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላቸው ወደ ምድረ ገነት እንደገቡ የስነ-ፍጥረት መፅሃፍ ያስረዳናል። ይሁን እንጂ ዘመን የራሱን ታሪክ ይዞ የሚጓዝ ስለሆነና የሰዎችን የመኖር ታሪክ እንደየዘመኑ ገፀባህሪ ወይም ስልጣኔ እና እድገት የሚለካ ስለሆነ የወንድ እና የሴት የአካለ መጠን መድረስ እና በጋብቻ መወሰን በቤተክርስቲያን የቀኖና ስርአት ከላይ በተገለፀው መሰረት ተወስኗል። በሌላ መልኩ አንድ ሰው በትክክለኛ አነጋገር ለአካለ መጠን ደርሷል የምንለው የተፈጥሮ ባህሪ አስገድዶት በዝሙት ሃሳብ እንዳይወድቅ ወይም በራሱ ፍላጎት እና አካላዊ ብቃት ለአካለ መጠን ደርሻለው ማግባት አስፈልጎኛል ካለ በዝሙት ጠንቅ እንዳይወድቅ ወይም እንዳትወድቅ መጋባት ይኖርባቸዋል። በእርግጥ በድንግልና ህይወት መኖርም ሆነ በቅዱስ ጋብቻ መወሰን ውሳኔው ከእግዚአብሔር ስለሆነ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለግሪክ ክርስቲያኖች በፃፈው ክታቡ “ሁሉም እንደ እኔ በድንግልና ቢኖር መልካም ነው፤ ነገር ግን በዝሙት ሃሳብ እና ፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላል” ብሏልና የጋብቻ ጉዳይ የግለሰቡ የተፈጥሮ ሁኔታ ይወስነዋል።
ጣራ አለው ወይ ለሚለው ከዝሙት እና ከሴሰኝነት ሃሳብ ነፃ ሆኖ ቅድስናውን ጠብቆ ለሚኖር ሰው እስከ 40ም 50ም ከዛም በላይ አመት መኖር ይችላልና የግድ ካላገባህ ተብሎ የሚገደድበት ሁኔታ አይኖርም፤ ማግባት በሚፈልግበትም ግዜ ማግባት ይችላል።
መልስ፦ ከፍቅረኛዎ ጋር በቃልኪዳን እየኖራችሁ ከጋብቻ በፊት ሩካቤ መፈፀም በቤተክርስቲያን ቀኖና የተከለከለ ነው። ምክንያቱም ወደፊት የትዳር ህይወታችሁ የምታፈሩትም ትውልድና ቤታችሁ ሃብታችሁ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ፤ ገና የትዳሩን ህይወት በእግዚአብሔር ቤት በቃልኪዳን መሰረቱን ሳትጥሉ ይህን የተቀደሰ አላማ ላለማጣት ከጋብቻ በፊት መፈፀም የለባችሁም። ደግሞም በስሜት መቃጠል የስጋ ደካማነት እንጂ ሰውነታችንን የማይጎዳ ወይም ትዕግስት የማጣት ሁኔታ ስለሆነ እንጂ በሽታ ሆኖ የማይገድል ወይም እንደ ምግብና እንደ መጠጥ ብናጣው ሰውነታችንን የማይጎዳ ስለሆነ እየተፈተንንም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜ ታግሶ እዛው ህጋዊ ጋብቻ እስከምትፈፅሙ መቆየት ያስፈልጋል።
መልስ፦ ጠየቂያችን፤ እርስዎ እንደገለጹት ኀጢአት መሆኑን ሳያውቅ ጥፋት የሰራ ማንኛውም ክርስቲያን ያ የፈጸመው ጥፋት ኀጢአት መሆኑን ባወቀ ጊዜ ወደዚያ የጥፋት ተግባር ላለመመለስ በቁርጠኝነት መወሰኑ እጅግ የሚያስደንቅ ከርስቲያናዊ ጥንካሬ እና አንዱ የንስኀ መንገድ ቢሆንም እንኳን፤ ነገር ግን ሁሌ ማሰብ ያለብን በቆሻሻ ነገር ንጽህናውን ያጣ ማንኛውም አካል ቆሻሻ እንደሆነ እራሱን ቢያሳምንም እንኳን ከቆሻሻው የሚፀዳበት መፍትሄ ካልተደረገ በስተቀር በእራሱ ጊዜ ከቆሻሻ የሚነፃበት ሁኔታ የለምና፥ የኀጢአትም ፀባይ በዚሁ አንፃራዊ ምሳሌ የምናየው ስለሆነ እኛ ተፅተንና ወስነን ስለተውነው የኀጢአት ጥፋት በተጨማሪም በንስኀ ለመታጠብ ለአባቶች መናዘዝ ያስፈልገናል። ስለ ኀጢአታችን ንስኀ የምንገባበትን የኑዛዜ ቃል ለአባቶቻችን መናገር የሚያሳፍርም፣ ጊዜ የሚያጠፋም ባለመሆኑ ጠያቂያችን ለንስኀ አባትዎ መናዘዝ የግድ ያስፈልግዎታል ማለት ነው። ምክንያቱም እርስዎ ያሳለፉትን ኀጢአት ወደፊት ላለመስራት መወሰንዎ እጅግ የሚያሰደስት ቢሆንም ነገር ግን ስለሰሩት ኀጢአት የንስኀ ቀኖና መቀበል እና ቀኖናውን መፈፀም እንዲሁም ስለፈፀሙት ጥፋትም ምክርና ተግሳፅ ከአባቶች መቀበል ይኖርብዎታል በማለት ይህ አጭር መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
መልስ፦ ጠያቂያችን፤ ለድቁና የሚያበቃ ትምህርት ማለት በቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥበት ለእግዚአብሔርም ምስጋና የምናቀርብበት እውቀት ስለሆነ መማር አይከለከልም። ምክንያቱም ከርስቲያን ክህነት ባይኖረውም ሁሉንም የቤተክርስቲያናችንን መንፈሳዊ እውቀት የመማር እና የማወቅ ክርስቲያናዊ መብት አለው። ክህነት ደግሞ እራሱን የቻለ ፀጋ ስለሆነ ወደ ክህነት ለመጠራትም ራሱን የቻለ መስፈርት ስላለው ጠያቂያችን እንዳሉት እኛን በአካል ቀርበው ሲያነጋግሩን የቤተክርስቲያን ቀኖናና ስርዓተ በሚመራን መንገድ መሰረት ተገቢውን መፈፀም ይቻላል። ስለዚህ ትምህርቱን ቢማሩት ተፈላጊ ነው በማለት ይህ አጭር መልዕክት እንዲደርስዎት አድርገናል።
መልስ፦ ህልመ ሌሊት ወይም ህልመ ዝንየት ማለት በሌሊት ተኝተን ሳለን በህልም የሚከሰት የዝሙት ሃሳብ ነው። አውቀንና በአካለ ስጋ እንቅስቃሴ ያላደረግነው የዝሙት ሃሳብ ወይም አካላዊ የግብረስጋ በሚመስል መገለጥ የምንፈተንበት ኀጢአት ነው። ህልመ ሌሊት በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን በ3 ዋና ዋና ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል ብለን እናስባለን።
1ኛ/ ቀን ስናየውና ስናስበው የዋልነውን የዝሙት ሃሳብ በሌሊት በህልም ልናየውና ልንፈፅመው እንችላለን። የክፉ መንፈስ ዋና የመነሻ ምክንያት የእኛ ደካማ ሃሳብና ምኞት ወይም የአመለካከት ዝንባሌን መሰረት ያደረገ ነው። በማየትም በመስማትም በመናገርም የዝሙት ፈተናዎች ይመጣሉ ይፈፀማሉ። ለምሳሌ ስሜትን የሚያነሳሱ ነገሮችን መመልከት፣ ስለዚህ ጉዳይ አብዝቶ ማውራት፣ ህሊናን ለዚህ አስገዝቶ ቦታ መስጠት የመሳሰሉትን ስንፈፅም ፍትወታት ይሰለጥኑብንና የምናስበው ይሄን ብቻ ይሆናል። በእርግጥ አንዳንዴ በቀን ስንመኘውና ስናስበው የዋልነውን ተኝተን በህልም ከምናውቀው ሰው ጋር ከፈፀምነው፥ ኀጢአቱን አስበን እንዳደረግነው ይቆጠራል። ምክንያቱም ፍላጎቱ ኖሮን ነገር ግን እድሉና ሁኔታው ስላልገጠመልን እንጂ ቢሳካልን በአካል ከማድረግ አንመለስም ነበርና ነወ። ይህ ደግሞ ትልቅ ኀጢአት ነውና ንስሐ ልንገባበት ያስፈልገናል።
2ኛ/ አብዝተን በመብላትና አብዝተን በመጠጣትም ህልመ ሌሊት ሊከሰት ይችላል። አንድ እቃ ከሚይዘው ልክ ያለፈውን ነገር ስናሸክመው እንደሚያፈስ ሁሉ ስጋችንም ለመኖር ወይም ለቁመተ ስጋ ከሚያስፈልገን በላይ በምግብና በመጠጥ ስንሞላው ከአቅም በላይ የሆነው ነገር ፈሶ ወደ ተለያዩ ኀጢአቶች የምንወድቅበትና በዋናነት ወደ ዝሙት ሃሳብ የምንገፋፋበትን ሁኔታ ስለሚፈጥር ህልመ ሌሊት ሊያጋጥም ይችላል።
3ኛ/ ከላይ በተራ ቁ 1 እና 2 ከተጠቀሱት ወይም ከሃሳብም አብዝቶ ከመብላትና ከመጠጣት ከሚመጣ ኀጢአት ውጪ ሆነን እራሳችንን ጠብቀን እየኖርንም ግን፤ ጠላታችን ዲያብሎስ ባልጠበቅነው ሰዓት እራሳችንን ላላስገዛንለት ኀጢአት እንድንወድቅ በራሱ ጊዜ በሌሊት መጥቶ ሴት ከሆነች ወንድን በመምሰል ወንድ ከሆነ ሴትን በመምሰል አንዳንድ ጊዜ የማናውቀውን ሰው አንዳንድ ጊዜም የምናውቀውን ሰው በማስመሰል በህልመ ሌሊት መጥቶ ምትሃታዊ ስራ በመስራት ሊፈትነን ይችላል። በዚህም አንዳንዶቻችን ዘር ልናፈስ እንችላለን አንዳንዶቻችን ደግሞ በእውኑ አለም እንደምናደርገው በዝሙት ሃሳብ ሲያሰቃየን ልናድር እንችላለን። ስለሆነም ለዝሙት ሃሳብ ራሳችንን ሳናስገዛ እና አብዝተን ሳንመገብ ወይም የአልኮል መጠጦችን ሳንወስድ በመጠን የምንኖር ሆነን የሚከሰት እንዲህ አይነቱ ህልመ ለሊት ከሆነ ፈተናው ከሰይጣን ነውና በኀጢአት የሚያስጠይቀን አይሆንም። ስለዚህ መደበኛ የንስሓ ቀኖና አያስፈልገውም። ሰይጣን ቤተክርስቲያን እንዳንገባ በተለያየ ምክንያት በጣም ተፅዕኖ ከሚያደርግብን መንገዶች ዋናው ህልመ ሌሊት ነው። ስለሆነም ለጊዜው በህልመ ሌሊት የመጣብን ፈተና ወደ ቤተመቅደስ ገብተን ለመቁረብ ወይም ለመቀደስ ወይም ለማስቀደስ አያስችለን ይሆናል። ምክንያቱም ንፁሐ ባህሪይ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ህሊናን ስለሚመለከት ምንም እንኳን የእኛ ኀጢአት የእሱን ቅድስና ባያረክስም ዝም ብለን ዘው ብለን ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመግባት ድፍረትም ስለሚሆንብን ፣ ከሁሉ ነገር የምናስቀድመውም እግዚአብሔርን መፍራት ስለሆነ ከእንዲህ አይነት ስቃይና ከእንዲህ አይነት ፈተና ፈፅሞ ንፁህ እንዲያደርገን በፀሎት መጠየቅና እግዚአብሔርን በተለያየ መታዘዝና ማገልገል እራሳችንን ማስገዛት ስላለብን ከኀጢአት የመንፃት ምሳሌ በሚሆነው ስርአት ሰውነታችንን በውሀ ታጥበን ከዚህ ከህጥበቱ ጋር ደግሞ የሚፀለይ ፀሎት አለ “አቤቱ ጌታ ሆይ እንደበደል እንደ ጥፋት እንደ ድክመት ከሚቆጠርብኝ ሰውነቴን ወይም መላ ህይወቴን ከሚያረክስብኝ ኀጢአት ሁሉ አንፃኝ ቀድሰኝ” እያልን እየፀለይን መላ ሰውነታችንን ታጥበን በውስጡ ክፍል ሳይሆን በውጩ የቤተክርስቲያን ክፍል (በቤተክርስቲያን ቅፅር) ቆመን መፀለይ እንችላለን ማለት ነው።
ስለዚህ ጠያቂያችን ከላይ የተዘረዘሩትን የህልመ ሌሊት መንስኤዎች ከተረዱ በኋላ በእርስዎ ህይወት በተከታታይ የሚፈትንዎት በምን ምክንያት እንደሆነ የራስዎን የህሊና ዳኝነት በመውሰድ ለዚህም መደረግ ያለባቸውን የመፍትሔ ሃሳቦችን በገለፅንልዎት መሰረት እንዲፈፅሙ እየመከርን በአጠቃላይ ግን በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ፈተና የሚገጥመን ከሆነ የተቆራኘን ክፉ መንፈስ ስላለ መፀለይ እና በአባቶች ፀሎት መረዳት አለብን። ከኛ እስከሚይም ድረስ በተለያየ መንፈሳዊ ተጋድሎ መትጋት አለብን። ይህም፦
- ያጋጠመዎትን ፈተና ለመንፈሳዊ አባትዎ በግልፅ በማስረዳት ልዩ ፀሎት፣ ስግደት፣ እና ጥምቀት እንዲሁም አስፈላጊውን ምክርና መንፈሳዊ አገልግሎት ያግኙ፤ እንዲሁም የተለያየ ልዩ ፀጋ ያላቸው አባቶች በፀሎት እንዲያስቡዎት በማድረግ እርስዎም በግል በሚችሉት አቅም ዘወትር መፀለይ አለብዎት፤
- በፀበሉ በቅዱስ መስቀሉና በእምነቱ ከአጋንንት ውጊያ ለመዳን እንደሚችሉ በማመን አስፈላጊውን አገልግሎት ማግኘትና በቤተክርስቲያን አባቶችም በፀሎት እንዲያግዙዎት ይጠይቁ፤
3. በእርስዎ በኩል የማይቋረጥ ቋሚ የፀሎት ፕሮግራም በማድረግ አብዝቶ መፀለይ፣ መፆም፣ መስገድ ያዘውትሩ፡ መስቀሉን በአንገታችን መያዝ፣ ፀበሉን መረጨት እና መጠጣትም ያስፈልጋል። - በሚተኙበት አካባቢና በቅፅረ ቤትዎ አጋንንት እንዳይቀርቡ መስቀሉን ይቀስሩ። መስቀሉ አጥር ነው፣ ፀሎቱ አጥር ነው፣ መዝገበ ፀሎቱ አጥር ነው።
በአጠቃላይ ጠያቂያችንም እነዚህን ሁሉ በቻልነው አቅም ተስፋ ሳንቆርጥ ብንፈጽምና መንፈሳዊ ህይወትችንን ደረጃ በደረጃ ብናሳድግ ፤ የሰይጣን መንፈስ በእግዚአብሔር ቃል እየተቃጠለ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ከእኛ ፍፁም 40 ክንድ ተለይቶ ይሄዳል። ተጨማሪ ትምህርትና ምክር ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
ስለ ቅዱስ ቁርባን የጠየቁን አባላችን ሆይ፤ በመጀመሪያ ከዚህ ቀደምም ደጋግመን እንደገለፅነው ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በ40 ቀን እና በ80 ቀን የእግዚአብሔርን ልጅነት በጥምቀተ ክርስትና አግኝቶ በቅዱስ ቁርባን ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻ የዘመኑ ፍፃሜው ድረስ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ መለየት እንደሌለበት ክርስቲያናዊ ግዴታውም እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህም በቅዱስ መፅሐፍ በግልፅ ታዟል። ምክንያቱም የጌታን ቅዱስ ሥጋ ካልበላን ክቡር ደሙን ካልጠጣን የዘለዓለም ህይወት የለንም። ሰው በሥጋው በህይወት ለመኖር ዘወትር ለስጋው ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በነፍሱም የዘላለም ህይወት ለመውረስ የነፍሳችን ምግብ ቅዱስ ቁርባን ስለሆነ ነፍሳችን ደግሞ ቅዱስ ቁርበንን ካጣች እንደሞተች ወይም ህይወት እንደሌላት ማመን ያስፈልጋል።
ይሁን እንጂ ቅዱስ ቁርባን በሰው ህይወት ሲገለፅ በህፃንነት እድሜ ደረጃ ያሉ ክርስቲያኖች ሲቆርቡ ቆይተው አካለ መጠናቸው ወደ አዋቂነት ሲደርስ ይበልጥ ስለሚስጥረ ቁርባን ተምረውና አውቀው መቀጠል ሲገባቸው፤ ይባስ ብለው ቅዱስ ቁርባን እንደማይጠቅም በማሰብ ይሁን ባለማወቅ ባይገባንም ከቅዱስ ቁርባን የሚርቁ ብዙዎች ናቸው። ይሄም ነገር የቤተክርስቲያን አባቶች በእግዚአብሔር ቤት ዘንድ የሚያስጠይቃቸው የክህነት ሃላፊነት ነው። ምእመናንም ቢሆኑ የቅዱስ ቁርባንን ዘለዓለማዊ ህይወትነቱ እየተነገራቸው እያወቁና እየተረዱ ከቅዱስ ቁርባን የሚርቁ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።
ስለዚህ ጠያቂያችን ምንም እንኳን የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ኅጢአት የመወደቁ ሁኔታ የደካማ ሥጋ ባህሪ ቢሆንም በሰራነው ኅጢአት ተፀፅተን ወደ ንስኅ ህይወት ተመልሰን ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል የሚለክለን ህግ ግን የለም። ጠያቂያችን እንዳሉት ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ ቆይተው በመሃከሉ በዝሙት ተሰናክለው ከቅዱስ ቁርባን ከራቁ ወይም ርቀው ከቆዩም አሁን ማድረግ ያለብዎት ፦
1ኛ የክርስቶስ ሥጋና ደሙ ከኅጢአት የሚያፀዳና የሚቀድሰንና የሚያነፃን እንጂ የሚያርቅ ስላልሆነ በኅጢአት መውደቆትን ቢያምኑም በንስኅ ተመልሰው ሥጋ ደሙን የመቀበሉን ስርዓት እንደገና መቀጠል አለብዎት።
በ2ኛ ደረጃ ሚስት ለማገባት እቅድ ካለዎት በሥጋ ህይወት ውስጥ ባይገደዱበትም እንደ መንፈሳዊነት ግን ወደ ትዳር ህይወት ሲገቡ በቅዱስ ቁርባን ቢሆን በሥጋም ሆነ በነፍስ በረከትንና ክብሮትን ያበዛዋል።
በ3ኛ ደረጃ ማግባት ካልፈለጉም ስለሰሩት ኅጢአት በንስኅ የኅጢአት ስርየት በማግኘት ብቻዎትን በቁርባን ተወስነው መኖር ይችላሉ።
ለሁሉም ነገር ግን ስለ አንቀፀ ንስኅ ጠንቅቀው የሚያውቁ የቤተክርስቲያን አባቶች (ሊቃውንት) ሁልጊዜ በማነጋገርና በማማከር ትምህርት እያገኙ ማንኛውንም ነገር እንደ ስርዓቱና እንደ ህጉ ማስቀጠል የሚችሉበትን ፕሮግራም እንዲያደርጉ ይህን አጭር መልእክት ለእርስዎ እና ለዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም አንብባችሁ ትረዱት ዘንድ መልዕክቱ እንዲደርሳችሁ አድርገናል።
ጠያቂያችን፤ የጠየቁት ጥያቄ ጥሩ ጥያቄና ማንም ሰው ሊያውቀው የሚገባ ነው። በቤተክርስቲያናችን አስተምሮ አንፃር በቁርባን መጋባት እና ከተጋቡ በኋላ አብሮ መቁረብ ፍጹም የተለያየ ነው። በመሰረቱ ማንኛውም ክርስቲያን በ 40 ቀን እና በ80 ቀን የእግዚአብሔር ልጅነት በጥምቀተ ክርስትና አግኝቶ በቅዱስ ቁርባን ከታተሙበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻ የህይወት ፍፃሜ ድረስ ከቅዱስ ስጋውና ከክቡር ደሙ መለየት እንደሌለበት ክርስቲያናዊ ግዴታ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ ማህተምነትም በመስቀል ምልክት ታትምና ይሄን ዘግቻለሁ አትሜያለሁ ብላ ቤተክርስቲያን ራሳቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ሴትም ወንዱም ስርዓት ሰርታ ቃለ እግዚአብሔር እየተማሩ ለአቅመ አዳም ለአቅመ ሄዋን እስኪደርሱ ድረስ ተጠብቀው እንዲቆዩ ታደርጋለች። በኋላ ለአቅመ አዳም ለአቅመ ሄዋን ሲደርሱ ቤተክርስቲያን የአክሊል ሽልማት ታደርጋለች ። ይህ የአክሊል ሽልማት የሰማይ አክሊል ምሳሌ ነው ። ስለዚህ እህቶች ወንድሞች ድንግልናቸውን ቢያጡ በሰማይ ቅጣት አለ በምድር ደግሞ የሚያገኙትን ክብር ይነፈጋሉ፥ አክሊላቸውን ያጣሉ፣ አክሊል ሽልማት ነው።
አሁን አሁን ግን ቅዱስ ቁርባን በሰው ህይወት ሲገለፅ በህፃንነት እድሜ ደረጃ ያሉ ክርስቲያኖች ሲቆርቡ ቆይተው አካለ መጠናቸው ወደ አዋቂነት ሲደርስ ይበልጥ ስለሚስጥረ ቁርባን ተምረውና አውቀው መቀጠል ሲገባቸው፥ ይባስ ብለው ቅዱስ ቁርባን የሚርቁ ፥ ይህም አልበቃ ብሏቸው ጋብቻቸውን ከቤተክርስቲያን ስርዓት ውጪ በሆነ አለማዊ ጋብቻ የሚፈፅሙ ብዙዎች ናቸው። ይሄም ነገር የቤተክርስቲያን አባቶችን በእግዚአብሔር ቤት ዘንድ የሚያስጠይቃቸው የክህነት ሃላፊነት ነው። ምእመናንም ቢሆኑ የቅዱስ ቁርባንን ዘለዓለማዊ ህይወትነቱን እያወቁና እየተረዱ ከቅዱስ ቁርባን የሚርቁ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ምክንያቱም ለትዳር የተጫጩ ወንድና ሴት ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት የሚያደርጉት የግብረስጋ ሩካቤ እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ስንመለከተው በዝሙት መንፈስ የተፈፀመ ግንኙነት እንጂ በስርአተ ቤተክርስቲያን የተፈቀደ አይደለምና እንደ ዝሙት ይቆጠራል። ነገር ግን የጥፋቱ መጠን ታይቶ በንስኀ አባታቸው የንስኀ ቀኖና እና ቀጣይ ምክር እና ትምህርት የሚሰጣቸውና ንስኀ ገብተው ቀኖና ጨርሶው ስጋ ደሙን በመቀበል ጋብቻ መፈፀም ይችላል። ተክሊል ግን አይፈጸምላቸውም።
ስለዚህ ጠያቂያችን ወደጠየቁን የጥያቄ ሃሳብ ስንመጣ ፥ በቁርባን መጋባት ማለት አንደኛው እንደተባለው ተክሊል የሚፈፀመው ሁለቱ ማለትም ሴት እና ወንዱ ድንግልናቸውን ጠብቀው ከቆዩ በኋላ በስርዓተ ተክሊል በቤተክርስቲያን ስርዓት ቤተክርስቲያን አዋጅ ብላ ልጆቿን ለክብር ለመዓረግ የምታበቃበት ነው። ስለ ድንግልናቸው ክብር ምድራዊ የምናየው ዋጋ ሁሉ ሰማያዊ ዋጋ በኋላ ያሰጣልና። ይህ የአክሊል ሽልማት የሰማይ አክሊል ምሳሌ ነው። ሌላው ድንግልናቸውን ያጡ ከሆነ ከላይ እንደተገለፀው ንስኀ ገብተው የሚፈፀም ፀሎት አለ ፀልየው በቅዱስ ቁርባን ይጋባሉ ማለት ነው። አክሊል ግን አይደረግላቸውም። እና እህቶች ወንድሞች ድንግልናቸውን ቢያጡ በሰማይ ቅጣት አለ በምድር ደግሞ የሚያገኙትን ክብር ይነፈጋሉ፣ አክሊላቸውን ያጣሉ፣ አክሊል ሽልማት ነው። ከአንዱ ክብር ሌላው ክብር ሊበልጥ ቢችልም፥ ነገር ግን እነዚህም ንስኀ ገብተው ቀኖናቸውን ፈፅመው በቅዱስ ቁርባን በቤተክርስቲያን ስርዓት ሊጋቡ ይችላሉ።
ከተጋቡ በኋላ አብሮ መቁረብ ላሉት ግን ፤ በመሰረቱ በአለማዊ ጋብቻ መጋባት ቤተክርስቲያን ስርዓት አይደለም ። በዓለማዊ ጋብቻ መጋባት የአሕዛብ እንጂ የክርስቲያን ጋብቻ አይደለም። ፀጋ መንፈስ ቅዱስን ያርቃል። ስለዚህ በኋላ ቆርባለሁ አሁን ልጋባ ማለት የክርስቲያን ስነምግባር ውጪ የሆነ እና የዝሙት ሃሳብ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ሳያውቁ ቀርተው ወይም ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ጋብቻ ከገቡ ግን የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ኀጢአት የመውደቁ ሁኔታ የደካማ ስጋ ባህሪ ቢሆንም በሰራነው ኀጢአት ተጸጽተን ወደ ንስኀ ህይወት ተመልሰን ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል የሚከለክለን ህግ ግን የለም። ሆኖም፦ እኛ የማናውቀው በመዘግየታችን የምናጣው ፀጋ አለ ። ያን ፀጋ ላናገኘው እንችላለን። ልናቆየው የማንችለው እግዚአብሔር ሊሰጠን የሚችለው ጸጋ። ስለዚህ ራሳችንን በንፅህና በቅድስና ስንጠብቅና በቤተክርስቲያን ስርዓት ጸንተን በቅዱስ ቁርባን በመኖር ስንተጋ እኛ የማናውቀው እግዚአብሕር የሚያውቀውን ፀጋ በጊዜው እንጎናፀፋለን፣ ትዳራችንም ከጅምሩ ይባረካል ። በመሆኑም ሲጋቡ መቁረብ እና ከተጋቡ በኋላ መቁረብ አንድ አይደለም።
መልስ፦ ሴትም ሆነ ወንድ በሱባኤ እያለ እንዲህ አይነት ፈተና ቢገጥመው ፈተናው ባጋጠመው እለት የሱባኤውን ጋብ ፈጥሮ ሱባኤውን እንደገና በሚቀጥለው እለት መፈጸም ይችላል። ይሄ ካጋጠመው ከ 3 ቀን በኋላ ቁርባንም መቁረብ ይችላል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው በህልም እርኩስ መንፈስ ለፈተነው እንጂ ራሱ በቀን አስቦት የፈጸመው ዝሙት ሃሳብ ካለ ግን እንደገና ለንስሓ አባቱ ተናዞ ባለፈዉ ከተሰጠው ንስሓ በላይ በእጥፍ ቀኖና መቀበል እንዳለበት የቤተክርስቲያን ስርዓት ያዛል።
አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ቀይሮ ቢገኝ፣ በሃይማኖት የማይመስለውን ቢያገባ ወይም በዝሙት ቢወድቅ፣ ለክርስቲያን ያልተፈቀደውን ምግብ ቢበላ ወዘተ የመሳሰለውን ኢክርስቲያናዊ ግብር ፈጽሞ ቢገኝ የቀድር ጥምቀት እንደሚያስፈልገው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል።