ስለ ንስሓ አባት

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ንስሓ አባት

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

ጌታችን በወንጌሉ ካህናትን “እናንተ የአለም ብርሃን  ናችሁ”  ማቴ 5 -14 ይላቸዋልና ከርኩሰት አረንቁዋ ከጨለማውና  ከኀጢአት ሥራ ሁሌ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚመሩንና ኀጢአትን ጠልተን በበጎ ምግባር እንድንኖር መንገዱን የሚመሩን ናቸው፡፡

 የንስሐ አባት ማለት ምስጢረኛችን በመንፈሳዊም በሥጋዊም ህይወታችን የቅርብ አማካሪዎቻያችን ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሲራክ  “ብዙ  ሰዎች ወዳጆች  ይሁኑህ  ከብዙዎች  አንዱ ምክርህን  የምትነግረው  ከልቡናህ  ጋር አንድ  ይሁን፡፡”  ሲራክ  6-6  በማለት ይናገራል፡፡ ይህ ማለት    ምእመናን ስለ  ሃይማኖትና  በጎ ምግባር የሚያስተምሩዋቸው  ብዙ  ካህናት ሊኖሩዋቸው  ቢችሉም  ከብዙዎች  አንዱ ግን  ንስሃቸውን  የሚናዘዙለት መምህረ ንስሃ  ሊሆናቸው እንደሚገባ ያስረዳልና መምህረ ንስሕ ማለት ምስጢረኛና አማካሪ ማለት ነው ፡፡

አበ ነፍስ ማለት ኃጢአታችንን የምንናዘዝለት ማለት ነው፡፡ ኀጢታችንን ለካህን ስንናዘዝ ለእግዚአብሄር መናዘዝና ክብር መስጠት ነው፡፡ ኢያሱ እንዳለ “ልጄ ሆይ ለአምላክ ከብርን ስጥ፡ ለእርሱም ተናዘዝ፡ ያደረግከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ”  ኢያሱ 7-19፡፡ ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ለእግዚአብሄር ክብር መስጠት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ አበዉ ካሀናትም ኑዛዜን ከተቀበሉ በኋላ “እግዚአብሔር ይፍታህ” እንጂ  ”ፈትቼሃለሁ ” አይሉም፡፡ ኀጢአተዘችንን በነሱ ፊት ብንናገርም ሰሚዉም ሆነ በእነርሱ እጅ ስርየተ ኀጪአት  የሚሰጠዉ እርሱ ባለቤቱ ስለሆነ ነው፡፡  በመሆኑም አበ ነፍስ ማለት ኀጢአታችንን በዝርዝር ምንም የሚያስፈራ ኀጢአት ቢኖረንም እያሰታወስን አንዳች ሳናስቀርና ሳንጠራጠር  በዝርዝር የምንነግረው የእግዚአብሔር አይን ነው ማለት ነው፡፡ 

የንስሐ አባት/አበ ነፍስ ወይም መምህረ ንስሐ ማለት የንስሐ   ልጆቹ ትክክለኛውን ዓላማ ይዘው የንስሐ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ በጎ መሪ ማለት ነው፡፡ 

መምህረ ንስሐ ማለት ልጆቹን መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያስተምርና የልጁቹን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚከታተልና ስለ በጎቹ የሚጨነቅ እረኛ ማለት ነው፡፡

የንስሐ አባት ማለት ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ፣ ምግባራቸውን እንደይስቱ በርካቶችም ለጠንቋዮችና ለአሳቾች ሰለባ እንዳይሆኑ የጠራውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከምንጩ ማስጎንጨት የሚችልና እሄንንም የማድረግ ግዴታ ያለበት ባላደራ ማለት  ነው፡፡ 

የንስሐ አባት ማለት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ያለመታከት የሚተጋ ማለት ነው፡፡ የንስሐ አባት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ሁሌም መጐትጐትና መቀስቀስ አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በኃይል፣ በማጣደፍ ወይም በማስፈራት አይደለም፡፡ ካህኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወኪል፣ የእግዚአብሔር አደረኛ ስለኾነ ሁሌም ማትጋት፣ መጐትጐት፣ መቀስቀስ ይጠበቅበታል፡፡

የንስሐ አባት ለእያንዳንዱ ልጆቹ እንደየ አቅማቸውና እንደየሃይማኖት እውቀት መጠናቸውና እንደየ መንፈሳዊ እውቀታቸው አቻ እስከሚሆኑለት ለያይቶ በማስተማር ማብቃት አለበት፡፡

የንስሐ አባት ማለት በንስሐ ልጆቹ መካከል ፍጹም መቀራረብ እንዲኖር የሚያደርገ ነው፡፡ የንስሐ ልጆች ለብዙ ችግሮች የመፍትሔ አካል ኾነው እንዲያገለግሉ ዕድል ይሰጣልና፡፡ የተቸገሩትን ከመርዳት ዠምሮ አንዱ ለሌላው አርአያ ኾኖ በተግባር እስከማስተማር ድረስ ማድረግም የንስሐ አባት ድርሻ ነው፡፡ ይህ ማለት የአንድ ካህን ንስሐ ልጆች ከአንድ የሥጋ አባትና እናት የተወለዱ እህትማመቾች እና ወንድማማቾች ያህል ከዚያም በበለጠ ሁኔታ መቀራረብ አለባቸው ማለት ነው፡፡የንስሀ አባት ማለት ይህን የሚተገብር ማለት ነው፡፡

ከቊርባን በፊት ንስሐ ይቀድማልና፡፡ ሰው ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ ስለሌለ ጧት የሠራውን ለማታ፤ ማታ የሠራውን ለጧት ለመምህረ ንስሐው ነግሮ መምህረ ንስሐው ያዘዘውን ሠርቶ ሊቀበል ይገባዋልና ይህ ታላቅ ሀላፊነት የተጣለው ደግሞ በመምህረ ንስሀው ላይ ነው፡፡

 የንስሐ አባት ማለት ባለአደራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በበረኻ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ማን ነው?” ሉቃ.15 -5 ያለው፡፡ ካህናት ከእግዚአብሔር በአደራ እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ኹሉንም ሳይዘነጉ እያንዳንዱን በነፍስ ወከፍ ሊጠብቁና ሊያገለግሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡

የንስሐ አባት ከንስሐ ልጆቹ ጋር የሚፈጥረው ግላዊ ግንኙነት ከቤተሰባዊነት ያልተሻገረ ኾኖ ሲቀነጭርና እጅጉን ያነሰ ሲሆን ነው፡፡ ብዙ ካህናት ወደ ምእመናን ቤት መጥተው ሲያበቁ መስቀል ከማሳለምና ጠበል ከመርጨት ያለፈ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ካህናት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስቀመጠላቸው ከሥራቸው ኹሉ ቅድሚያውን ሰጥተው ማስተማር፣ መምከር፣ ኑዛዜን መቀበል፣ ማጽናናትና መገሰጽ ይገባቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የንስሐ ልጃቻቸውን በጥንቃቄ ይዘው ለሥጋ ወደሙ ማብቃት ግባቸው ስለኾነ ትኩረታቸው ኹሉ ወደዚኽ ዋነኛ የክህነት ዓላማቸው መሆን አለበት ፡፡ ይህም የካህኑ ትልቁ ሀላፊነት ነው፡፡

የንስሐ አባት የንስሐ ልጀቹን የቤተ ሰብ አባላት ቁትርና እያንዳንዱን በሚገባ ማወቅ አለበት፡፡

አንድ የንስሐ አባት ልጆቹንና አጠቃላይ ቤተሰቡን እያሰታወሰ አዘውትሮ ስለ ሁለንተናቸው መጠየቅ አለበት፡፡

የንስሐ አባት ከልጆቹ ጋር አብሮ በመጸለይ ጸሎትን ማለማመድ፤ ሆኖ በማሳየት እውነተኛ የአባትና የልጅ ፍቅርን  ማሳየት፤ በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በሥጋዊም ሕየዋታቸው መጨነቅ፤  ስራቸው እንዲባረክ አዘውትሮ፤መጸለይ በአጠቃላይ ልጆቹን በቅርበት መከታተል፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ተግባሩ እሄ ነው፡፡ 

መልስ (ለጥያቄ #1) ፦ ንስሓ አባት እያለን ሳንሰናበት ወይም እስካሁንም የነበሩንን የንስሓ አባት ምንም አይነት ምክንያት ሳናገኝባቸው በራሳችን ምክንያት ብቻ ተነሳስተን ወደ ሌላ ንስሓ አባት ብንሄድ ስርአተ ቤተክርስቲያን አይፈቅድም። ምክንያቱም ጉዳዩ የነፍስ አባት እስከሆነ ደረስ የነፍስ አባት የመያዛችን ስርአትም አሰራሩ መንፈሳዊ ምሥጢር ስለሆነ የነበሩንን የንስሓ አባት ተሰናብተን ወደ ሌላው ለመሄድ በቂ ምክንያት ሊኖረንና፤ ሌላ አባት የፈለግንበትንም ምክንያት ያለምንም ማፈር ነግረናቸው ተሰናብተን መሄድ መብታችን ነው። ካህኑም በስርአት ካልጠበቁን ለምን ማለት አይችሉም።  (ለጥያቄ #2) ዝም ብሎ ተነስቶ ሳይሰናበት  የሄደ ግን እንደ ስርአተ ቤተክርስቲያን ትክክል ባይሆንም ነገር ግን የሄደውም ወደ ካህን ስለሆነ ይህ ንስሓ የሚያስገባ ጉዳይ አይደለም።

መልስ፦ መንፈሳዊ እና ክርስቲያናዊ ህይወታችንን በአባትነት እንዲጠብቁን የያዝናቸው የንስሓ አባት ያደረግናቸው ካህን በራሳቸው ምክንያት እና ስንፍና ምንደኛ ቢሆኑ ማለትም ጠዋት ማታ እየገሰጹ እየመከሩ የማይጠብቁን አና ይበልጥ ወደ መንፈሳዊ አገልገሎት የማያተጉን ከሆነ ለአውሬ ወይም ደግሞ ለነጣቂ ለዲያብሎስ የሚያሰጥ ሰነፍ እረኛ ስለማያስፈልገን ያለምንም ቅድመ ሀኔታ ትጉህ እና ቅን የሆነ ለንስሓ ልጆቹ አገልግሎት ቅድሚያ ሁኔታ የሚሰጥ አባት መያዝ አለብን። በዚህ ጉዳይ ድረድርም ሆነ ማመንታት አያስፈልግም።

 
መልስ ፦ አባት ያደረግናቸው የንስሓ አባት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ወደ ሌላ አባት ስንሄድ በስርአተ ቤተክርስቲያን ካህኑ በስርአት አሰናብተውን እንዲያሸጋግሩን የኃላፊነት ድርሻ አለባቸው። ያንን የማያደርጉ ከሆነ ግን ከምእመን ይልቅ ካህኑ ስለሆነ ትልቅ ኃላፊነት ያለው፣ በኛ ጉዳይም በቅድሚያ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠየቀው ካህኑ ስለሆነ የሱን ድርሻ ባለመወጣቱ በተሻለ መንፈሳዊ ጥበቃ ሊመራን እና ሊያስተምረን ወደሚችል ካህን ከመሄድ የሚያግደን ስርአት የለም። ስለዚህ ጠያቂያችን አሁን ከጠየቁት እና ከሚያሳስብዎት ጉዳይ ነፃ ስለሆኑ ሌላ አባት ይዘው ከመኖር የሚያግድዎት ሕግ ወይም ስርአት የለም።
መልስ ፦ አባት ያደረግናቸው የንስሓ አባት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ወደ ሌላ አባት ስንሄድ በስርአተ ቤተክርስቲያን ካህኑ በስርአት አሰናብተውን እንዲያሸጋግሩን የኃላፊነት ድርሻ አለባቸው። ያንን የማያደርጉ ከሆነ ግን ከምእመን ይልቅ ካህኑ ስለሆነ ትልቅ ኃላፊነት ያለው፣ በኛ ጉዳይም በቅድሚያ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠየቀው ካህኑ ስለሆነ የሱን ድርሻ ባለመወጣቱ በተሻለ መንፈሳዊ ጥበቃ ሊመራን እና ሊያስተምረን ወደሚችል ካህን ከመሄድ የሚያግደን ስርአት የለም። ስለዚህ ጠያቂያችን አሁን ከጠየቁት እና ከሚያሳስብዎት ጉዳይ ነፃ ስለሆኑ ሌላ አባት ይዘው ከመኖር የሚያግድዎት ሕግ ወይም ስርአት የለም።
መልስ ፦ ማንም ክርስቲያን ባለበት ደብር ወይም አካባቢ ንስሓ አባት እያለው፤ ለሌላ መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ደግሞ ወደ ገዳማት እና ቅዱሳት መካናት ወይም ቦታዎች ሄዶ በዛ ቦታ ላገኛቸው አባት፥ አለኝ የሚለውን አነጋግሮ ወይም ኅጢአቱን ተናዞ አስፈላጊውን የንስሓ ህይወት መቀበል ይችላል። የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይደለም።
መልስ  ፦ ኅጢአቶን በመናዘዝ ከልብ ተጸጽተው ወይም ተመልሰው፤ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት በማገልገል ላይ ለሚገኘው የንስሐ አባትዎ (ካህን) ራስዎን በማስመርመርና ከፈጸሙት በደል የሚነፁበትን ንስሐ ተቀብለው ከሄዱና ከዳግም ጥፋትም እርቀው በካህኑ የተሰጠዎትን ንስሐ በትክክል ከፈጸሙ፤ ከተያዙበት የኅጥያት ማሰሪያ ስለተፈቱ ንስሐም ገብተው ስለተናዘዙበት እንደገና ይፍቱኝ ለማለት ወደ ካህኑ የሚያስኬድ ጉዳይ አይኖርብዎትም።  ምክንያቱም በኅጥያት እድፍ የቆሸሸውን ህይወትዎን ከካህኑ በተቀበሉት የንስሐ ውሃ ታጥበው ከኅጥያት እድፍ ፀድተዋልና። ዳግም እንዳይበድሉ፣ ኅጥያት ሰርተውም የቅድስና ሕይወትዎን እንዳያቆሽሸው፣ በየጊዜው ከቤተ ክርስቲያን መምህራንና የንስሐ አባቶች ትምህርትና ተግሳጽ እያገኙ ምንም እንኳን የኑሮ ፈተና ቢበዛብዎ ከእናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳይርቁ እየፆሙና እየፀለዩ ከገንዘብዎ፣ ከእውቀትዎ እና ከጉልበትዎም አስራት በኩራት እያወጡ በጎ ስራ በመስራት ከሰይጣን ወጥመድ ለማምለጥ የሚችሉበትን መንፈሳዊ ፀጋዎትን በተቻለ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለብዎ እመክራለው። ለዚህም ዋናውና መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ክርስቲያን ያለጠባቂና ያለመካሪ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌበት ወደ ንስሐ አባትዎ (ካህን) መሄድ ያለብዎ በየጊዜው የእለት እለት ህይወትዎን በካህኑ ምክር እንዲመራ ለማድረግ ነው።
 
በመሆኑም፤ ወደንስሃ አባትዎ ወይም ንስሐ ወደተቀበሉበት ካህን መሄድ የሚኖርብዎ ካህናት አባቶች የነፍሳችን እረኛ ሆነው በነፍስ ጉዳይ ላይ በሃላፊነት እግዚአብሔር ስለሾማቸው ሁልግዜም ቢሆን ከአባቶች ምክርና ተግሳጽ ላለመራቅ ነው እንጂ ቀደም ሲል ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያት ይፍቱኝ ለማለት አለመሄድዎን እንደጥፋት ቆጥረው እንደገና ንስሐ እንዲገቡበት አያስፈልግዎትም በማለት መንፈሳዊ ምክሬን እለግሳለው። (ማቴ18፤18) ዩሐ(20፤21-23) ዩሐ (21፤15-18)
መልስ ፦  ጠያቂያችን እንዳሉት ለመንፈሳዊ ህይወታችን ጊዜ ማራዘም እና ቀጠሮ ማስረዘም አስፈላጊ ስላልሆነ በፆመ ፍልሰታ በቅርብ ላገኟቸው አባት ኀጢአትዎን በመናዘዝ ወደ ንስሓ ህይወት መቅረብዎ እጅግ የሚያስመሰግን አና ከአንድ ትጉህ ክርስቲያን የሚጠበቅ ተግባር ነው። በሌላ መልኩ በዚህ ዮሐንስ ንስሓ ድረ ገፅ ላይ ባገኙት የአባቶች ዝርዝር መሰረት ቋሚ ንስሓ አባት ለመያዝ ያለዎት ፍላጎት በኛም በኩል የምንደግፈው እና ብዙዎችን በነፍስ እንዳይጠፋ ለማትረፍ እግዚአብሔር የፈቀደውን ያህል የበኩላችንን ጥረት እያደረግን መሆኑን በመረዳት ለአባትነት የመረጥናቸው የቤተክርስቲያን አባቶች በሃይማኖታቸውና በእውቀታቸው የታመነባቸው ስለሆነ ቅፁን ሞልተው በደረሰዎት ስልክ ቁጥር ደውለው የንስሓ አባት እንዲይዙ በእኛም በኩል አደራችን የጠበቀ ነው። የዚህ ድረገፅ ዋና አላማ የንስሓ ህይወትን ለማሳደግ የምክር እና የትምህርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በተለያየ የአለም ወጥመድ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በመንፈሳዊ ትምህርት በማነቃቃት በቅርብ ሆነው በጠዋት በማታ ምክር እና ተግሳፅ እየሰጡ የሚያገለግሉ አባቶች ጋር ማገናኘት ዋናው ቅድሚያ የምንሰጠው ስለሆነ የንስሓ አባት ለመያዝ ከኛ አቅም በላይ የሚያደርግ መስፈርት ሰለሌለው ለዚህ አላማ ቅድሚያ መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ከሁሉ ከስቀድመን እንመክራለን።
 
መልስ ፦  ጠያቂያችን እንዲረዱት የምንፈልገው አንድ ክርስቲያን የሚያስፈልገው የንስሓ አባት አንድ ነው። ምናልባት አንድ ሰው በሆነ አጋጣሚ ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ እሩቅ ቦታ ሄዶ ወይም ወደ ገዳም ለተወሰነ ጊዜ  በረከት ለማግኘት ቢሄድ እዛ ካሉት አባቶች እንዲመክሩትና ትምህርት ሃይማኖት እንዲሰጡት ሊጠይቅ ይችላል። ምክንያቱም አላማው አንድም ቀን ቢሆን ለነፍሳችን እረኛ ሳይኖራት መቆየት ስሌለብን በደረስንበት ቦታ ሁሉ ያገኘናቸውን አባት ወይም ካህን አባቴ በፀሎት አስቡኝ በአባትነት ጠብቁኝ ብሎ መንፈሳዊ ህይወቱን ከሰይጣን ንጥቂያ ለመታደግ ሁሌ በትጋት ሊኖር ያስፈልጋል። ስለዚህ ወደ ጠያቂያችን ሃሳብ ስንመለስ አንድ ምእመን በሚኖርበት አካባቢ አንድ ንስሓ አባት ሊኖረው ይገባል ማለት ነው። ሌሎችም አባቶች ባለን ቀረቤታ በፀሎት እንዲያስቡን፣ እንዲያስተምሩን፣ ወደ ቤታችን መጥተው ፀበል እንዲረጩን ብናደርግ መደበኛና ቋሚ ከሆኑት የንስሓ አባት ጋር የሚያጣላ ሳይሆን አላማውን ይበልጥ የሚያፀናው ነው። ምክንያቱም የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አለመሆኑን ጠያቂያችን በዚህ መልኩ ሊረዱት ያስፈልጋል።
 
የንስሓ አባት መያዝ የሚያስፈራ፣ የሚያስጨንቅ፣ ቅድመ ዝግጅትም የሚያስፈልገው አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ከራሳቸው የግል ገጠመኝ በመነሳት እና እንዲሁም የካህናትን ክብር ከሚያቃልሉ ሰዎች ጥራዝ ነጠቅ ሃሳብ በመውሰድ ንስሓ አባት መያዝ ጠቃሚ እንዳልሆነ እና ሌላ ችግርና መዘዝ እንዳለው ይናገራሉ።
 
በእርግጥም ምእመናን በውል ያልተገነዘቡት አንዳንድ ክፍተቶች ይታያሉ። ለካህናት የተሰጠው ፀጋ ብዙወችን ስለሚያስቀናቸው እንደ ስምኦን መሰሪ የእግዚአብሔር የክህነት ፀጋ በጥቅም ለመለወጥ ወይም ምድራዊ ቢዝነስ ለመሰብሰብ ሲሉ ክህነት ሳይኖራቸው ቄስ ነን፣ ምንኩስና ሳይኖራቸው መነኩሴ ነን፣ የሃይማኖት እውቀት ሳይኖራቸው አዋቂ ነን በማለት በአስመሳይነት ህይወቱ ሳይኖራቸው ልብሰ ክህነቱን ከገበያ በመግዛት በድፍረት በመልበስ አንድ ቀንም በቅፅረ ቤተክርስቲያን ድርሽ ብለው የማያውቁ የዋሁን እና ሰነፉን ክርስቲያን በየከተማው እና በየመንደሩ ሲያደናግሩ የሚውሉ የከተማ ጆቪራ ወይም ወሮበላዎችን የንስሓ አባት የምናደርግ ከሆነ የቀበሮ ባህታዊ እንደሚሉ የነፍሳችን ብቻ ሳይሆን ስጋችንንም ለበላተኛ መስጠት ማለት ነው። በትክክለኛው የቤተክርስቲያን ስርአት በህዝቡና በእግዚአብሔር ፊት በቋሚነት እያገለገሉ ሃላፊነት ወስደው ተጠያቂም ሆነው እለት እለት በማህበራዊ ችግራችን ደራሽ የሆነ እውነተኛ ካህን የንስሓ አባት ማድረግ ግን የሚያስፈራ ነገር የለውም።ጥቅሙም በስጋ ብቻ ሳይሆን በነፍስም ስለሆነ እንደማንኛውም ቁሳዊ ነገር ግምት የሚሰጠውም አይደለም። ሰው ሁነን በመፈጠራችን ብቻ አንዳንዴ እንደ እውቀታችን እንደ እድሜያችንም መጠን ልዩነት ስለሚኖር በአንዳንድ አባቶች ጥቃቅን ድክመቶች አየን ብለን ተፈጥሮአችንን እንደመላእክት በመቁጠር ለምን ይሄ ተፈጠረ ለምን ይሄ ተደረገ ብለን መጠበቅ የለብንም። ብዙውን ነገር ለእግዚአብሔር መስጠት ያስፈልጋል። ሃሳባችሁን ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ጣሉ ተብሎ ተፅፏልና። ስለዚህ ጠያቂያችን ጥንቃቄዎትን እያደነቅን ምናልባት እርስዎ ያሰቡትን የውስጥ ጥያቄ እኛ ሳናገኘው ቀርተን ከሆነ ለበለጠ መረዳትና ምክረ ሃሳብ በውስጥ መስመር ደውለው ያግኙን።
 
ጠያቂያችን ከሊባኖስ ንስጎ ለመግባት በማሰብ እንዴት ንስኀ አባት መያዝ እንዳለብዎት ከሊባኖስ ቤሩት ጥያቄ ያቀረቡልን አባላችን፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስለ ንስኀ ህይወት አስፈላጊነትና ንስኀ ለመግባት የንስኀ አባት ሊኖረን እንደሚገባን እና በቦታ ርቀት የንስኀ አባት ካህን ብናጣ እንኳን አባቶችን ባሉበት ቦታ መርጠን በመያዝ በስልክም ሆነ ወይም በጽሑፍ መልዕክት ብቻ ለመገናኘት አመቺ በሆነ መስመር ከንስኀ አባታችን የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ትምህርት ማግኘት፣ ንስኀ መግባት፣ ልዩ ልዩ የትሩፋት ሥራ መስራት ፣ በአጠቃላይ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ፀንተን ለመኖር እንደምንችል በስፋት መልዕክት እንዳስተላለፍን እናስታውሳለን።
አሁንም ጠያቂያችን ፤ እግዚአብሔር አምላክ ስለ ልጆቹ የሚያስብ የሚራራ አምላክ ስለሆነ በተለያየ ምክንያት በስደት ዓለም የሚኖሩ ወገኖችንም ፥ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በግብፅ  ምድር በስደት ሳለ አብሮት እንደነበረ ሁሉ እና በግብፃዊያን ዘንድ ሞገስና ክብርን እንዲጐናፀፍ ያስቻላ አምላክ ስለሆነ ዛሬም በተለያየ ክፍለ ዓለም እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን እና የቤተክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት በሌሉበት አካባቢ የሚኖሩ ምእመን ወገኖቻችንን በልዩ መለኮታዊ ጥበብ አፅንቶና አረጋግቶ የሚያኖር አምላክ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል።
ስለዚህ ጠያቂያችን ንስኀ አባት አሁን ባሉበት የሊባኖስ ከተማ ከሚገኙት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህናት መርጠውና አጥንተው  የንስኀ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ። ይህን ለማድረግ የማይችሉበት ምክንያት ካለ ፤ አገር ቤት ካሉት አባት ጋር ተነጋግረው በስልክ፣ በፅሁፍ ንስኀ መቀበል ይችላሉ።
 
ስለዚህ ማድረግ የሚገባን ዋና አላማ በአካልም ሆነ በስልክ እውነተኛ እና ለህይወታችን መድኃኒት ሊሰጥ የሚችል አባትን አግኝቶ የዘላለም ሕይወት እንወርስ ዘንድ የሚያስችለንን የፅድቅ መንገድ እንዲመሩን የማድረጉ ትጋት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ላቀረቡልን የጥያቄ ሃሳብ ይህን አጭር ማብራሪያ ልከንልዎታል። ምናልባት ከዚህ በላይ የሚያሳስብዎት ችግር ካለ በውስጥ መስመር በምንልክልዎት ስልክ ቁጥር ደውለው ሊያገኙን ይችላሉ :: 
 
ለሁሉም የእግዚአብሔር ፀጋና ፍቅር ባሉበት ቦታ ይብዛልዎት

ከዚህ በታች ያለውን የድረገጻችንን አድራሻ በመጫን በመኖሪያ ስፍራዎት መሰረት  ፎርሙን ይምሉ፤ ምንም አይነት መሰናክል ካጋጠሞት ያሳውቁን፤ እንረዳዎታለን፦ https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/

መልስ፦ ጠያቂያችን የንስኀ አባት ወይም የነፍስ አባት አድርገን ረቂቁንና ሰማያዊውን ህይወት ያቀዳጀናል ብለን አባት ካደረግናቸው ካህናት ወይም አባቶች በገንዘብ የሚመዘን ክፍያ በቀጥታ አያስፈልግም። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተቀበሉት አዳራ እኛን ለነሱ እንደ ሀብትና እንደ ንብረት አድርጎ ሲያስረክበን እነሱ ደግሞ በኛ ህይወት ላይ ሊናዝዙና ሊያስተዳድሩ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። በኦሪቱ ስርዓት የሌዊ ልጆች በህዝቡ ላይ ካህናት ሆነው ሲሾሙ ህዝቡን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለው ይላል። በአዲስ ኪዳንም በቅዱስ ወንጌል “በፀጋ ያገኛችሁትን እንዲሁ በልግስና ስጡ” በማለት ለቅዱሳን ሐዋሪያት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም “ሄዳችሁም መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ ድውዮችንም ፈውሱ ሙታንንም አስነሱ ለምፃሞችን አንፁ አጋንንትን አውጡ በከንቱ ተቀብላችሁ በከንቱ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ። ለሰራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።” በማለት የሚያስፈልጋቸውን ፈቅዶላቸው በአባትነት የተሰጣቸውን ፀጋ በልግስና እንዲያደርጉትና ህዝቡንም በነፃ እንዲያገለግሉ ታዘዋል። (ማቴ 10፥7፡9)

 

እንዲሁም ስሞን መሰሪ የተባለ በሰይጣን መንፈስ ተነሳስቶ ቅዱሳት ሐዋሪያት ከመንፈስ ቅዱስ በተሰጣቸው ስልጣን ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ “ስሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን አኔ ታላቅ ነኝ ብሎ እየጠነቆለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ በከተማ ነበረ … ስሞንም በሐዋሪያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሀልና ብርህ ከአንተጋራ ይጥፋ ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስኅ ግባ ምናልባትም የልብህን ሃሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና (የሐዋ ስራ 8፥9 እና 18-22)

 

ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ ሌሎቻችሁ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መገንዘብ ያለባችሁ አባቶቻችን የሚሰጡን  በረከትና የሚፈፅሙት የክህነት አገልግሎት በገንዘብ የማይሸጥ መሆኑን  ማወቅ አለብን። ነገር ግን ካህናት ካለባቸው መንፈሳዊ የአባትነት ሃላፊነት አንፃር ስለኛ ሲፀልዩ፣ ቀድሰው ሲቆያርቡ፣ በመስቀል ሲባርኩ በመሳሰለው ሁሉ በግልም በማህበርም ስለኛ የሚሰጡን አገልግሎት በነፍስም በስጋም በረከት የሚያሰጥ ስለሆነ ፤ እነሱም ደግሞ ዘወትር ለመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሚተጉ እራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት ራሱን የቻለ የግል ሀብት ስለሌላቸውና ስላልሰበሰቡ መንፈሳዊ ቅናት ያለው አንድ ክርስቲያን በራሱ ተነሳስቶ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ከመግለፅ አንፃር ቢፈልግ ቤት ሰርቶ መስጠት ቢፈልግ መኪና መስተጥ ቢፈልግ ገንዘብ ቆጥሮ መስጠት ይችላል። ይህ ግን ከግዴታ የተነሳ  ሳይሆን በራሱ ካለው መንፈሳዊ ፍቅር ተነሳስቶ የሚያደርገው መልካም ምግባር እንደሆነ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚህ ውጪ ከላይ በጠያቂያችን ሃሳብ የተነሳው ለስልጣነ ክህነት አገልግሎት ተብሎ ለካህናት የገንዘብና የሌላ ድርድር ፈፅሞ የማይደረግ እና የማይፈፀም መሆኑን ግን ማወቅ አለብን።

መልስ፦ ጠያቂያችን ንስኅ ለመቀበል ወደ መንፈሳዊ አባትዎ በሄዱ ጊዜ በኅጢአቱ መጠን ቀኖና ከመስጠት ይልቅ እግዚአብሔር የልባችሁን መፀፀት አይቶ ይቅር ይላችኋል፣ ፀሎት ብቻ አድርጉ በሚል ነገሩን በማቅለል እንዳሰናበትዎት ፣ ይህ ድርጊታቸው ደሞ ለመንፈሳዊ ህይወት ያለዎትን አቋም እያዘናጋው እንደመጣ በመግለጽ ምን ላድርግ በሚል ጥያቄ አቅርበውልናል። በመሰረቱ የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ ሁላችሁም ከሁሉ በፊት አጥብቃችሁ እንድትገነዙቡልን የምንወደው፤ ጥያቄያችሁ  እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሄርን ቃል እንድናስተምራችሁና ለጥያቄወቻችሁም ከቤተክርስቲያን አንፃር በቂ መልስ እና ምክር እንድንሰጣችሁ ከመጠየቅ አንፃር ይሁን እንጂ አባቶችንም ሆኑ ሌላ ሰዎች በራሳቸው አካሄድ ስለፈፀሙት ጠንካራም ሆነ ደከማ ጎን በመጥቀስ የዳኝነት አስተያየት እንድንሰጥበት ከመፈለግ አንፃር ግን መሆን የለበትም። ምክንያቱም የሌሎችን ሰዎችን ህይወት ስለማንዳስስ በአገልግሎቱም ዙርያ ክፋትንና መቃቃርን ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንመክራለን።

 

ወደ ዋናው ጥያቄ ስንመለስ ግን አንድ ክርስቲያን በፈፀመው ጥፋት ተፀፅቶ ወደ ንስኅ አባቱ በሄደ ጊዜ ካህኑም እንደ ኅጢአቱ ክብደትና መጠን ቀኖናውን ለመስጠት የቤተክርስቲያን የቀኖና መፅሐፍ ወይም አንቀፀ ንስኅ በሚያዘው መሰረት መፈፀም አለበት እንጂ ዝም ብሎ በልብወለድ አካሄድ ነገርን በማቅለል ምንም ማለት አይደለም ፣ ከልብህ ከተፀፀትክ በቂ ነው፣ ዝም ብለህ ፀልይ ወዘተ በሚል የዋዛ ፈዛዛ አይነት አነጋገር የንስኅ ቀኖና አይሰጥም። እንዲህ አይነት አፈፃፀም ደግሞ ከእውነተኛ አባቶችና ጠባቂዎች አይጠበቅም። አንዳንዶቹ ካህናት ከትምህርት እጥረትም ሊሆን ይችላል ወይም በጉዳዩ ትኩረት ካለመስጠት ወይም ከጊዜ እጥረት በግልፅ ባይገባንም እንዲህ አይነት ድርጊት እንደሚያጋጥም ግን ተረድተናል። ስለዚህ ቢቻል ሁላችሁም ስለመንፈስ ልጆቻቸው ዘወትር የሚያስቡትን ስለ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖትና ቀኖና ስርአትና ትውፊት ጠንቀው ማስተማር የሚችሉና ዘወትር የመንፈስ ልጆቻቸውን የሚመክሩ የሚገስፁ ካህናትን የነፍስ አባት አጥብቀው እንዲያደርጉ እንመክራለን። ጠያቂያችንም ከዚህ በላይ በሰጠነዎት የመፍትሄ ሃሳቡን እንዲወስዱ ይህን መልዕክት እያስተላለፍን ተጨማሪ ምክረ ሃሳብ ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን። 

መልስ፦ጠያቂያችን በመሰረቱ የእርስዎ ጥያቄ በተግባር የተፈፀመውን ድርጊት ስለሆነ የገለፁልን በጣም እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ የንስኅ አባት (የነፍስ አባት) የማትታየውን ፣ የማትጨበጠውን፣ የማትዳሰሰውን ረቂቅ የሆነችውን የነፍሳችን ሃላፊ ስለሆኑና እንዲሁም በአይነ ስጋ የማናየውን በእጅ የማንዳስሰውን በምርምርና በእውቀት የማይደረስባትን በኋለኛው ዘመን የምንወርሰውን ሰማያዊ መንግስት ለማውረስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስልጣን የተሰጣቸው ስለሆኑ በአባትነት የንስኅ አባት አድርገን የምንይዛቸው አባት በእውቀታቸው፣ በስነምግባራቸው፣ በፆም በፀሎታቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በምግባራቸው የተመሰከረላቸውና ስለ ንስኅ ልጆቻቸው በትጋትና በንቃት ዘወትር ሃላፊነት ወስደው የሚያገለግሉ መሆን ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ ከአንድ በላይ የሆነ ንስኅ አባት በመያዝ የሚደረገው አሰራር በቤተክርስቲያን ቀኖና አይፈቀድም። የንስኅ አባት ያደረግናቸው ካህን ለአገልግሎት ብቁ ካልሆኑ የተሻለ አባትና አስተማሪ ፈልገን መያዝ ክርስቲያናዊ መብታችን ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ከአንድ በላይ የንስኀ አባት በሪዘርቭነት ወይም በተጠባባቂነት መያዝ በተቀደሰው ክርስቲያንነታችን እንደማፌዝና እንደማሾፍ ስለሚቆጠር እንዲህ አይነት ስርዓት መስተካከል እንዳለበት በአፅንዎት እንመክራለን። ለሁሉም ነገር ጥፋቱ እና ድክመቱ የኛ የቤተክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች እንጂ የምእመናን ግን አይደለም። እውነቱን አስረግጦ የሚነግራቸውና የሚመራቸው ባለመኖሩ በየዋህነትና በቅንነት የሚያደርጉት ስለሆነ እነሱን ለመውቀስ አንደበት አይኖረንም። ነገር ግን በዚህ በዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ ፕሮግራማችን በምናስተላልፈው እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ብዙ ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች እንደሚስተካከሉበት እምነታችን የፀና ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ከላይ በዘረዘርነውን መመዘኛ ተጠቅመው አንዱን አባት መርጠው መያዝ  እንዳለብዎትና ሌሎችን አባቶች እንዲያሰናብትዎ መጠየቅ እንዳለብዎት እንመክራለን።  ሌሎችን አባቶች ባለን ቀረቤታ በፀሎት እንዲያስቡን እንዲያስተምሩን ወደቤታችን መጥተው ፀበል እንዲረጩልን ብናደርግ መደበኛና ቋሚ ከሆኑት የንስኅ አባት ጋር የሚያጣላ ሳይሆን አላማውን ይበልጥ የሚያፀናው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የአባቶቻችን ፀጋ የአንዱ ፀጋ ከሌላው ፀጋ ይለያልና ሁሉም አባቶች ባላቸው ፀጋ በረከት ቢያድሉን ፀጋችንን ያበዛዋል እንጂ ነውር አይሆንም። ነገር  ግን አንድ ምእመን በአንድ ጊዜ ሊኖረው የሚገባው አንድ ንስኅ አባት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ለበለጠ መረጃ እና ምክር ካስፈለገዎት በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።   

ስለ ጸሎት  4 Q (H-3, C-1)

መልስ ፦ ጠያቂያችን፤ የሚያስታውሱትንና የሰሩትን ኅጢአት አንዱንም ሳያስቀሩ ለንስኅ አባትዎ በዝርዝር ማስረዳት የግድ አስፈላጊ ነው። የእርስዎ ንስኅ አባት ሊናዝዙ ስልጣን ያላቸው የንስኅ አባትዎም በስነስርዓት አድምጠው የሰሩትን ኅጢአት በዝርዝር ካወቁ በኋላ ለእያንዳንዱ ጥፋት የቤተክርስቲያን ቀኖና በሚያዘው መሠረት ንስኅውን በፆም በፀሎት በስግደት ወይም በሌላ ቀኖና እንዲፈፅሙ ትዕዛዝ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ጠያቂያችን ግን እንዳሉት ገና ስለፈፀሙት ጥፋት ዘርዝረው ሳይጨርሱ ወይም ሃሳብዎን እስከመጨረሻው ባለማዳመጥ ቀላል አድርገው የሚተዉት ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ሊያስጠይቃቸው ስለሚችል ምንም እንኳን ጥፋቱ የካህኑ ቢሆንም  እርስዎ የህሊና ነፃነት ያገኙ ዘንድ፦ 1ኛ ለመንፈስ ልጆቻቸው ቅድሚያ ሰጥተው የሚያስተምሩና ዘወትር የሚፀልዩ ንስኅ አባት መርጠው በመያዝ ንስኅ መግባት፣ ወይም ደግሞ 2ኛ ወደ ገዳም አባቶች ሄዶ ንስኅ መቀበል፣ 3ኛ እንደ ደግሞ አማራጭ ማድረግ ያለብዎት ወደ እግዚአብሔር ቤት  ሄዶ በህሊና ፀፀት የሰሩትንና ተናግሬ ሳልጨርስ አቋረጡኝ ያሉትን ኅጢአት ሁሉ በመናዘዝ የሱባኤ ጊዜ ይዘው መፆም፣ መፀለይ፣ ልዩ ልዩ የቱሩፋት  ስራ በመስራት የግልዎትን ቀኖና መፈፀም ይችላሉ። የበለጠ ምክርና እገዛ ካስፈለገዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።.

ጠያቂያችን ያቀረቡት ጥያቄ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ እና የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ዋናው አላማም ጠባቂና ሰብሳቢ የሌላቸውን የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ወደ እውነተኛው መንገድ ለማሰባሰብ እና ዘወትር የሚመክር እና የሚገስፅ አባት እንዲኖራቸው ለማድረግ ስለሆነ፤ እርስዎ እንዳሉት ገና በቤተሰባዊ ልማድ የንስኀ አባት አለን በሚል ብቻ የነፍስ ድህነት ስለማይገኝ እርስዎን በቅርበት እየተከታተለ ዘወትር የሚመክር እና የሚያስተምር የነፍስ አባት ስለሚያስፈልግዎ ለዚህ ጥያቄዎ ተገቢውን ምላሽና መንፈሳዊ አገልግሎት እንድንሰጥዎ በውስጥ መስመር በሚላክልዎ አድራሻ ደውለው ሊያነጋግሩን ይችላሉ በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

ጠያቂያችን በቅድሚያ በድያለሁ ጥፋት ሰርቻለሁ ኅጢአት ፈጽሜያለሁ ብሎ ኅጢአትን ለመናዘዝ ቅድሚያ በመስጠት በንስሐ ሕይወት ራስን አዘጋጅቶ ለመጠበቅና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ መሆንዎት እና የኅጢአት ሥርየትን ለማግኘት መጓጓትዎ እጅግ የሚያስደስት እና ከእውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ የታማኝነት መገለጫ ነውና በዚህ መንፈሳዊ ትጋትና ጥንካሬና አላማ እንዲቀጥሉ እግዚአብሔር ይርዳዎት።
 
ወደ ጠየቁን ዋና ጉዳይ ስንመጣ የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ ይመክረኛል ያስተምረኛል ያሉትን የንስሓ አባት የሚሆን ካህን በአካባቢዎ ካሉ  ይያዙ፤ በአከባቢዎ  ማግኘት የማይችሉ ከሆነ በራስዎትም ሆነ በሚያምኑት ሰው በኩል ያገኙዋቸውን እውነተኛ ካህን በርቀትም ቢሆን ይያዙ፤ ወይም ደግሞ እኛ በህይወታቸው ምሳሌ ይሆናሉ ብለን  ለአባትነት የመረጥናቸው የቤተክርስቲያን አባቶች በሃይማኖታቸውና በእውቀታቸው የታመነባቸው ስለሆነ በድረገፃችን ላይ ባለው ወይም በውስጥ መስመር በላክንልዎ ቁጥር ደውለው የሚያገኟቸውን አባት አነጋግረው ንስኀ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ።

ጠያቂያችን አንድ መንጋ ያለጠባቂ ፣ ህዝብና ሀገር ያለአስተዳዳሪ አንድ ቀንም ቢሆን መዋል እና ማደር እንደማይችል አንድ ክርስቲያንም ያለ ንስኀ አባት አንድ ቀንም መዋልና ማደር ስለማይችል እርስዎ እንዳሉት በስራ አጋጣሚ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የንስኀ አባትዎንም ከቦታ ቦታ ይዘው መንቀሳቀስስለማይችሉ በዚያ በሄዱበት የቤተክርስቲያን አባቶችን በማነጋገር አባት አድረገው መያዝ ይችላሉ። ምናልባት በሄዱበት ስፍራ አባት የማያገኙበት አጋጣሚ ካለ ደግሞ በርቀትም ቢሆን ለአባትነት የመረጧቸውን ካህን በስልክ እና በፅሁፍ መልዕክት እየተነጋገሩ ንስኀ፣ ትምህርት እና ምክር መቀበል ይችላሉ።

ውድ የተከበሩ የዘወትር ተከታታይና አጋር የሆኑ አባላችን ሆይ እንኳን አብሮ አደረሰን፤  አህታችንን በማንኛውም ጊዜ ማለትም ከሰኞ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት  ከጠዋቱ 3 ሰአት እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ባለው ጊዜ ውስጥ በውስጥ መስመር በላክንለዎት ቁጥር በቴሌግራም ወይም በሻይበር ቢደውሉ ሊያገኙን እንደሚችሉ ያሳውቁልን ዘንድ አንጠይቃለን። ምናልባት ከእኛም ሆነ ከእኛ አቅም ውጪ በሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች መስመሩን ማግኘት ባይችሉ እንኳን ደጋግመው በተለያየ ሰአት እንዲሞክሩ እንመክራለን።

ጠያቂያችን፤  ስለ ንስሓ አባት እና  የንስሓ ልጅ ስለመሆን ለምን እንደሚገባን ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን መልዕክት በድጋሚ ልከንልዎታልና  በመጀመርያ ይህን አንብበው ተረድተው  ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆነልዎት ሃሳብ ካለ ቢያሳውቁን ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥዎ እን ችላለን። 
 
ጌታችን በወንጌሉ ካህናትን “እናንተ የአለም ብርሃን  ናችሁ”  ማቴ 5 -14 ይላቸዋልና ከርኩሰት አረንቁዋ ከጨለማውና  ከኀጢአት ሥራ ሁሌ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚመሩንና ኀጢአትን ጠልተን በበጎ ምግባር እንድንኖር መንገዱን የሚመሩን ናቸው፡፡
 
 የንስሐ አባት ማለት ምስጢረኛችን በመንፈሳዊም በሥጋዊም ህይወታችን የቅርብ አማካሪዎቻያችን ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሲራክ  “ብዙ  ሰዎች ወዳጆች  ይሁኑህ  ከብዙዎች  አንዱ ምክርህን  የምትነግረው  ከልቡናህ  ጋር አንድ  ይሁን፡፡”  ሲራክ  6-6  በማለት ይናገራል፡፡ ይህ ማለት    ምእመናን ስለ  ሃይማኖትና  በጎ ምግባር የሚያስተምሩዋቸው  ብዙ  ካህናት ሊኖሩዋቸው  ቢችሉም  ከብዙዎች  አንዱ ግን  ንስሃቸውን  የሚናዘዙለት መምህረ ንስሃ  ሊሆናቸው እንደሚገባ ያስረዳልና መምህረ ንስሕ ማለት ምስጢረኛና አማካሪ ማለት ነው ፡፡
 
 ስለዚህ ያለንስሓ አባት ወይም ያለ መምረ ንስሓ መኖር ያለ ባል ልጅ መውለድ ነው ወይም ከባል በፊት ልጅ ይስጥሽ ማለት ነው። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊተ ለምንሰራው መንፈሳዊ ስራ ሁሉ ምስክር ሆኖ ሊቆምልን የሚችል ካህን ያስፈልገናል። በረቂቅ እና በሚስጢር አሠራር ቅዱሳን መላዕክት የኛ ጠባቂ ሆነው ይቆማሉ። በዚህ በገሃዱ አለም ደግሞ እንደ አንድ ክርስቲያንበምንኖርበት ህይወት ውስጥ ካህናት አባቶቻችን ለእኛ የነፍስ እረኞች ሆነው በእግዚአብሔር ዘንድ ተሹመዋል።
ስለዚህ ንስሓ አባት መያዝ የሰው ትዕዛዝ ሳይሆን የፈጣሪ መመሪያ ነው። 
 
“የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ ፲፮᎓፲፱) ይህ ማለት ፦
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸው የክህነት ስልጣን ማሰር እና መፍታት የሚችሉበት ረቂቅ እና ሰማያዊ ስልጣንን ነው። ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባትም ሆነ ከመንግስተ ሰማያት ለመከልከል የሚያስችል ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው ስልጣንም ነው። ይህ ማለት ስልጣን ሁሉ የራሱ ገንዘብ የሆነው የባህርይ አምላክ እየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ሐዋርያት እና 72ቱን አርድእት ከዓለም መካከል መርጦ በሾማቸው ግዜ ኀጥያት ሰርተው በደል ፈጽመው ወደ ሐዋርያት ቀርበው በኀጢአታቸው ተጸጽተው የተናዘዙትን ኀጥያታቸውን የማስተሰረይ ስልጣን ስለተሰጣቸው ኀጥያታችሁ ይቅርላችሁ ያሏቸው ሁሉ የተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ኅጥያታቸው ሁሉ እንዲደመሰስ ያደርጋል።
 
በሰሩት ጥፋት ሳይጸጸቱ እና ከበደላቸው የማይመለሱትን ደግሞ በተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ሲፈርዱባቸው በስጋቸው ሞትና ልዩ ልዩ መቅሰፍት ይቀጣሉ ማለት ነው።
 
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፦
 
–  ግያዝ የተባለው የነብዩ ኤልሳዕ ደቀመዝሙር ከመምህሩ ተሰውሮ ከለምጽ በሽታ ካዳነው ሶርያው ንጉስ ከንዕማን ላይ የማይገባውን ጥቅም በመውሰዱ ምክንያት ነብዩ ኤልሳዕ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ ግያዝን በለምጽ ደዌ አንደቀጣው እንመለከታለን። 2ኛ ነገስት 5፥20-27
 
–  ሐናንያ እና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች በሐዋርያት ፊት ያላቸውን የሀብታቸውን እኩሌታ ለእግዚአብሔር ሊሰጡ ቃል ከገቡ በኋላ ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን አታላችኋል ብሎ በተሰጠው የክህነት ስልጣኑ የሞት ቅጣት እንዲደርስባቸው አድርጓል። የሐዋ 5፥1-10
 
–  በጥንቆላ መንፈስ የሚኖር ሲሞን መሠሪ የተባለው ሰው ሐዋርያት እጅ በመጫን  የመንፈስ ቅዱስ ኅይል የሚሰሩትን አስደናቂ ሚስጥር ባየ ግዜ እንደእናንተ ይሄንን ታላቅ አስደናቂ ስራ ለመስራት እንድችል ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን ስልጣን በገንዘብ ሽጡልኝ ባላቸው ግዜ እድል ፋንታውን ከክፉዎች ጋር እንዲሆን እና የጥፋት ሰው አንደሆነ ረግመውታል። ዩሐ 8፥18-24
 
ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ማስረጃዎች የመንግሰተ ሰማያት መክፈቻ ለሐዋርያት ተሰጠ ሲባል በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት መንግስተ ሰማያት ማስገባት እንደሚችሉ እና የማይገባቸውን መከልከል የሚችሉ መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ የቤት ወይም የበር ቁልፍ መክፈቻና መዝጊያ ቁሳዊ ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማሰር መፍታት የሚለውም በዚህ አለም ላይ ሰው በፈጸመው ወንጀል የሚታሰርበት አግር ብረት ወይም ገመድ ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን ከላይ እንደገለጽነው በተሰጣቸው ረቂቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣን ኅጥያትን የማስተሰረይ፣ የኀጥያተኞችን ኅጥያት የመያዝ ፀጋ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
 
ስለዚህ ሁላችሁም ስለመንፈስ ልጆቻቸው ዘወትር የሚያስቡትን ስለ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖትና ቀኖና ስርአትና ትውፊት ጠንቅቀው ማስተማር የሚችሉና ዘወትር የመንፈስ ልጆቻቸውን የሚመክሩ የሚገስፁ ካህናትን የነፍስ አባት አጥብቀው እንዲያደርጉ እንመክራለን።
 
ጠያቂያችን ፤ በመጀመሪያ በዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም በምናስተላልፈው መንፈሳዊ ትምህርትና ምክር ተጠቃሚ መሆኖትን ከአድናቆት ጋር ስለ ገለጹልን በእኛም በኩል ይህን ያህል ፕሮግራማችንን በትኩረት ተሳትፈው ስለተከታተሉን አንዲሁም ሌሎች ወገኖች ወደዚህ በዚህ ግሩፖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለጋበዙ እናመሰግናለን። ወደፊት መንፈሳዊ ህይወትዎን፣ ፀጋዎን፣ የበለጠ እንዲያሳድጉ እኛም  በአገልግሎታችን አብዝተን ተግተን እንድናገለግል ከምንም በላይ እግዚአብሔር ይርዳን።
 
በአሜሪካን ከሚገኙት አባቶች የንስኀ አባት ለመያዝ በውስጥ መስመር በላክንልዎት ቁጥር ፤ ወይም ደግሞ በድረገፃችን ላይ https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/ የንስኀ አባት ከሚለው ገፅ ስር “አሜሪካን” የሚለውን ሲጫኑ በሚመጣልዎት ቁጥር ደውለው የሚያገኟቸውን አባት በማነጋገር ንስኀ አባት መያዝ እንደሚችሉ እንገልፃለን።
 
በተጨማሪም፦ የዮሐንስ ንስኀ ድረገጸ መንፈሳዊ ትምህርት አና ምክር እንዲሁም ለጥያቄዎ መልስ ለማግኘት :-
 
የቴሌትግራም ገፅችን፦https://t.me/joinchat/GA5ccrpz33ESz04q
 
የፌስቡክ ገፅችን፦ https://www.facebook.com/YohannesNeseha/
 
የኢሜል አድራሻችን፦ yohannes.neseha@gmail.com
 
ከዚህ በላይ ያሉትን የድረገጻችንን አድራሻ በመጫንና በመጠቀም ሂደት ምንም አይነት መሰናክል ካጋጠሞት በውስጥ መስመር ያሳውቁን፤ እንረዳዎታለን።
ጠየቀቂያችን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በንስኀ አባት የሚሰጠው ቀኖና እርስዎ ያሉትን መባም የሚያጠቃልል ከሆነ በቀኖና ውስጥ የሚያከናውኑት ይሆናል። መባ የሚለው ነገር የካህኑ ጉዳይ ነው። ያስፈልጋል የሚለው ከሆነ ለቤተክርስቲያን ጧፍ እጣን መብራት ዘቢብም ግዛ ሊለው ይችላል፤ እንደአቅሙ እንደሁኔታው ፥ ይህ የካህኑ ጉዳይ ነው። ካህን ካላዘዘ ማድረግ አይገባም። አንድ ንስኀ አባት ልጁ ንስኀውን ከተናዘዘ በኋላ ቀኖና የሚሰጠው ከልቡ አመንጭቶ ሳይሆን አንቀፀ ንስኀ በሚያዘው መሰረት ተገቢ ነው ያለውን እንደ አባትነቱ አቅሙን አይቶ ቀኖናውን  ይሰጠዋል፥ ምእመኑም ቀኖናውን ከጨረሰ በኋላ ለወደፊት ማድረግ የሚገባውን ወደኀጢአት እንዳይመለስ ልቦናውን ካጸዳ በኋላ እንደገና መንፈሳዊ እንዲሆን የበለጠ እንዲተጋ ይመክረዋል።
 
ጠያቂያችንም ሆኑ ሌሎቻችሁ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መገንዘብ ያለባችሁ የንስኀ አባት አድርገን ረቂቁንና ሰማያዊውን ህይወት ያቀዳጀናል ብለን አባት ካደረግናቸው ካህናት በገንዘብ የሚመዘን ክፍያ በቀጥታ አያስፈልግም። በእግዚአብሔር የሚገኝ አባቶቻችን የሚሰጡን በረከትና የሚፈፅሙት የክህነት አገልግሎት በገንዘብ የማይሸጥ መሆኑን ማወቅ አለብን። ስለዚህ በዚህ አይነት እሳቤ ውለታ ለመመለስ መሞከር ክብራችንን ስለሚያሳንሰው ወይም ስልጣነ ክህነት አገልግሎት ተብሎ ለካህናት የገንዘብና የሌላ ድርድር ፈፅሞ የማይደረግ እና የማይፈፀም መሆኑን መገንዘብ አለብን።
 
ከዚህ ውጪ ግን ጠያቂያችን የተሰጠዎትን የንስኀ ቀኖና ከጨረሱ በኋላ ተጨማሪ በረከት ለማግኘት የንስኀ ህይወት የነፍስንም ሆነ የስጋ ህይወት የሚጠግን ስለሆነ መባ የሚሉትን በማቅረብ ለቤተክርስቲያን የሚሰጥ፣ ወይም ደግሞ ለነዳያን የሚሰጥ፣ ወይም ደግሞ በማህበራዊ ህይወት አባት ሆነው ላገለገልዎት፥ ፍቅርና አድናቆትን ከመግለፅ አንፃር ከራስ ተነሳስተው በነፃ ፈቃድ የሚሰጥ መባ ማድረግ ይችላሉ እንጂ ከስልጣነ ክህነት አገልግሎት ጋር በማያያዝ ፈፅሞ የማይደረግና የማይፈፀም መሆኑን ማወቅ አለብን። በአባትነት የተሰጣቸውን ፀጋ በልግስና እንዲያደርጉትና ህዝቡንም በነፃ እንዲያገለግሉ ታዘዋልና (ማቴ 10፥7-9)
 

ጠያቂያችን በዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፖሮግራም ተደራሽ የምናደርገውን ተከታታይ ትምህርትና እና ጥያቄና መልሶችን  በመከታተል እርስዎም ጠይቀው በመረዳት ትምህርት እንዳገኙበት እናምናለን። ወደፊትም  የእግዚአብሔርን ቃል ለመመከር ቅድሚያ መስጠትን  ቸል እንዳይሉ አደራ በማለት ለጠየቁን ጥያቄም በውስጥ መስመር በላክንልዎት አድራሻ ያገኙን ዘንድ የኛም ፈቃድ ነው።

ጠያቂያችን፤ ካህኑ የሰጠዎት የስግደት ቀኖና ለአንዱ 100 ለአንዱ 50 ለምን እንደተሰጠ ለጠየቁን ጥያቄ የተሰጠ ማብራሪያ። በመሰረቱ ስለ ኀጢአት ቀኖና በሚመለከት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለቀረቡልን ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠን ሲሆን አሁን ያቀረቡት ጥያቄን በሚመለከት ፦ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ቀኖና እንደ ኀጢአቱ ልዩነት ወይም ክብደት እና ቀላልነት ተመጥኖ ስለሚሆን በቀኖና ቤተክርስቲያንም እያንዳንዱ ክርስቲያንም ለፈፀመው የኀጢአት አይነት ቀኖና ስግደት ፣ ጾም ፣ ፀሎት፣ የቱሩፋት ስራ መፈፀም እንዳለበት በህጉ ላይ በዝርዝር ስለተደነገገ በዚህ አይነት የሚፈፀም በመሆኑ ለምን የ2 ሰዎች የስግደት ቀኖና ተለያየ ተብሎ ሊጠየቅም ሆነ በዋዛ እና በፈዛዛ ሊቀርብ ከቶ አይችልም። ሲጀመር የንስኀ ህይወት ምስጢር ቀኖና ስለሆነ ለማንም ሰው ልናማክረው የማንችል ከእግዚአብሔር በታች ቀኖናውን በሚሰጡት አባት እና ቀኖናውን በሚቀበለው ክርስቲያን መካከል የሚፈፀም ስርዓት ስለሆነ ለማንም ሰው ሚስጢሩን ማካፈል ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ጠላት ዲያብሎስ በሌላ ሰው ላይ አድሮ ፈተና ለማምጣት እና ቀኖናችንን በስርዓቱ እንዳንፈፅም እንቅፋት በመሆን የራሱን ስራ ስለሚሰራ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን አሁሉንም ማሰብ ያለብዎት በትክክለኛ እንደ ቤተክርስቲያን ስርዓት እውነተኛ የሆኑ የንስኀ አባት በቤተክርስቲያን ስርዓት አንፃር የተሰጠንን ቀኖና ተቀብለን ዳግም ወደ ጥፋት እንዳንመለስ እግዚአብሔር ጥፋታችንን የመጨረሻ እንዲያደርግልን እየተማፀንን የተሰጠንን የንስኀ ቀኖና መፈፀም ይኖርብናል እንጂ እንደ ማህበራዊ ጉዳይ ከማንኛውም አካል ጋር በመወያየት እና ትችት መስጠት ፈፅሞ ክርስቲያናዊ ስነምግባር አይደለም። ተጨማሪ ምክር ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

ጠያቂያችን በተደጋጋሚ የሚፈተኑበት ኀጢአት እንዳለ ገልጸው በዚህም ንስኀ መግባት እንደሚፈልጉ ነገር ግን ለንስኀ አባትዎ ለመናገር ፍርሃት ወይም ስጋትና ይሉኝታ አይነት የሰው ሰውኛ አስተሳሰብ እንደተሳቀቁ ተረድተናል። የንስኀ አባትዎን ወይም በቅርብ የነፍስ ጠባቂ ሆነው በእርስዎ ህይወት ላይ ሃላፊነት ኖሯቸው የተሾሙትን ካህን ለማነጋገር የማይችሉበት እና ያጋጠመዎ ችግር ከባድ መሆኑን ለመረዳት ከቻልን፥ ችግሩን በሌላ መንገድ ለመፍታት እንዲቻል ተገናኝተን በግልፅ መነጋገር አለብን። ምናልባት ዝም ብሎ ለስጋዊ ክብራችን ወይም ደግሞ ራሳችንን ለንስኀ አባታችን እንኳን ሳይቀር እንደፃድቅ ቆጥረን በአስመሳይነት የምንቀጥለው ህይወት የእኛን ጥፋት እጥፍ ድርብ ያደርገዋል እንጂ ጠቃሚ ስለማይሆን፤ በአጠቃላይ ከንስኀ አባት ጋር ተነጋግረው ችግሩን ለመፍታት የማይችሉበት ሁኔታ በብዙ ምክንያት ሊገለፅ ስለሚችል፣ መተማመንም በመካከል ከሌለ ወይም የካህኑም የዕውቀትም ሆነ የመንፈሳዊነት ብቃት ማነስ ከሆነ ወይም ደግሞ እርስዎ እራሶን ሁል ጊዜ እንደ እውነተኛ ክርስቲያን ከኀጢአት እና ከጥፋት እርቀው እንደሚኖሩ በማስቆጠር የነበሩበት ህይወት ከሆነ በአንድም በሌላ መንገድም በእርስዎ በኩል እንደከባድ የቆጠሩትን ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ በአካል ቢያገኙን መልካም ነው የማይቻል ከሆነም በስልክ ያነጋግሩንና ውስጣዊ ችግርዎን መርምረን እና ተረድተን  ትምህርት እና ምክር ሰጥተንዎት በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብዎት የመፍትሄ ሃሳብ ልንሰጥዎት እንችላለን ።

መረዳት ያለብን ከሰይጣን ጋር ያለን ውግያ የማያቋርጥ ስለሆነ አንድ ጊዜ ስንወድቅ አንድ ጊዜ ስንነሳ የምንቀጥልበት አለም የፈተና ጊዜ ስለሆነ ደጋግመው በአንድ ኀጢአት መውደቅዎ እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም በእርስዎ ብቻ የደረሰ አድርገው ግን ተስፋ መቁረጥ የለቦትም። ነገር ግን ምን ጊዜም ከንስኀ በኋላ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ እና ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርትና ምክር በማግኘት በመንፈሳዊ አላማ መጽናት ያስፈልጋል።  አሁንም ስለአንድ ሰው መጥፋት ቤተክርስቲያን ዝም ስለማትል ወደ ንስኀ ህይወት እንዲቀርቡ እና በተደጋጋሚ ከተፈተኑበት የኀጢአት መዘዝ ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነውና የጊዜ ቀጠሮ ሳያራዝሙ ያግኙን በማለት ይህን አጭር መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።

ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር ይሁን

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ