ስለ ቅዱስ ቁርባን ጥያቄና መልስ
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ቅዱስ ቁርባን ጥያቄና መልስ
ሰሞኑን በቴሌግራም ግሩፓችን የተነሱ ጥያቄዎች
ስጋ ደሙን ከመቀበል በፊት አንድ ክርስቲያን ማሟላት ወይም ማድረግ ያለበት ነገር፦
1/ የንሰሓ አባትቱን በማነጋገር ኀጢአት ካለ ንስሓ መግባት፣
2/ በስጋ ደሙ ከተወሰኑ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልምና ከቤተሰብዎም ይሁን ከማህበራዊ ኑሮ የሚያገናኙና የሚያጨቃጭቁ ቂም በቀል የሚያመጡ ሃሳቦች እንዳይኖሩ በተቻለ መጠን ሁሉንም ነገር ከመቁረብ በፊት ማስተካከል፣
3/ የተቀየምነው የተቀየመን፣ ያስቀየምነው ያስቀየመን፣ የተጣላነው የተጣላን ማንኛውም ሰው ካለ በንስሓ አባት ወይም በሽማግሌ አማካኝነት ይቅርታ ጠይቆ ቂም በቀልን መተዉ፣
4/ በግል ህይወታችን ሁል ግዜ በቋሚነት የምንጸልየው የጸሎት ፕሮግራም ለኖረን ያሰፈልጋል። ሰይጣን እንዳይዋጋንና በቅዱስ ቁርባን ያገኘነውን በረከት እንዳያሳጣን የምንቋቋምበት መንፈሳዊ ተጋድሎ በጸሎት ስለሆነ ነው፣
5/ ለመቁረብ ሁሉን ነገር አሳክተን ከወሰንን በኋላ ከምንቆርብ 3 ቀን በፊት ወንድ ይሁን ሴት ቤተሰብ ካለ ከግንኙነት (ፆታዊ ግንኙነት) መቆጠብ ያስፈልጋል።
6/ በሰጋ ወደሙ አንድ ሰው ተወሰነ ማለት እንደ ቤተክርስቲያን ስርአት ፈጽሞ ከአለማዊ ጠባይ ወጣ ማለት ስለሆነ በተቻለ መጠን አቀሙ የሚችለውን የበጎ ስራና የርህራሄ ስራ መስራት፣ ቅዱስ ቁርባን በበጎ ስራ መገለጽ ስላለበት ለድኆች ርህራሄ ማድረግ፣ ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊ ስራ ላይ መሳተፍ፣
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁሉ ለቅዱስ ቁርባን የምንበቃባቸው ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቁ መልካም እሴቶች ናቸዉ።
በተጨማሪም ለቅዱስ ቁርባን በምንቀርብበት ግዜ የምንለብሰው ልብሳችን ለዚህ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ መንፈሳዊነትን ሊገልጽ የሚችል ራሱን የቻለ ልብስ ሊኖረን ይገባል። ንጹሕ ባሕርይ እግዚአብሔር ንጹሕ ነገርን ይወዳልና። በአለም ላይ ስንኖር በአለም ራሳችንን ለመግለጥ ልዩና ውድ ልብስ የምንገዛ ከሆነ ከዚህ በላይ በከበረው በእግዚአብሔር ጉባኤ ራሱን የቻለ ልብስ ቢኖረን፤ ባይኖረን እንኳ ያንኑ ልብሳችንን በጽዳት ልንይዘው ይገባል። አንፃራዊ ትርጓሜው በልብሱ አንፃር ውስጣችንንም ንጹሕ አድርገን ቀርበናል አንተም ንጹሕ ባሕርይ አምላክ ነህ ለማለት ነው።
ሴትም ሆነ ወንድ በሱባኤ እያለ እንዲህ አይነት ፈተና ቢገጥመው ፈተናው ባጋጠመው እለት የሱባኤውን ጋብ ፈጥሮ ሱባኤውን እንደገና በሚቀጥለው እለት መፈጸም ይችላል። ኢሄ ካጋጠመው ከ 3 ቀን በኋላ ቁርባንም መቁረብ ይችላል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው በህልም እርኩስ መንፈስ ለፈተነው እንጂ ራሱ አስቦት የፈጸመው ዝሙት ካለ ግን እንደገና ለንስሓ አባቱ ተናዞ ባለፈዉ ከተሰጠው ንስሓ በላይ በእጥፍ ቀኖና መቀበል እንዳለበት የቤተክርስቲያን ስርዓት ያዛል።
ጠያቂያችን እንዳሉት ሲቆርቡ ኑረው በመካከል ወደ ቅዱስ ቁርባን የማያቀርብ ነውር ካጋጠማቸው ወይም ደግሞ በኀጢአት ከተሰናከሉ ለጊዜው መቁረባቸውን አቁመው ወደ ንስሓ አባታቸው ቀርበው የፈጸሙትን በደል ከተናዘዙ እና ንስሓቸውን ከጨረሱ በኋላ መቁረባቸውን መቀጠል ይችላሉ። ነገር ገን ጥፋቱን በመደጋገም ሁል ጊዜ በንስሓ እመለሳለሁ በሚል መንፈስ መሄድ እንደሌለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። ዋናው ቁም ነገር ማንኛውም ክርስቲያን በምንም ይሁን በምን ከቅዱስ ቁርባን ላለመለየት በየጊዜው መንፈሳዊ አላማውን በማጽናት መታገል እንዳለበት እንመክራለን።
ቅዱስ ቁርባን የሚቀበል ማንኛውም ሰው ለንስሐ አባቱ መናገር ያለበት ራሱ የሚያውቀው ጥፋት ከሌለበት በስተቀር ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል በተዘጋጀ ቁጥር መናገር አይጠበቅበትምና ይህንን የጠየቁን አባላችን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያሳስብዎት ነገር የለም።
መልስ፦ ስርአተ ተክሊል አስባችሁ በመካከል ላይ ራሳችሁን ለመግዛት ሳትችሉ በመቅረታችሁ በመካከል ባደረጋችሁት የስጋ ድካም ከስርአተ ተክሊል በፊት የድንግልናችሁን ክብር ስላጣችሁት የፈፀማችሁትን ጥፋት ለንስሓ አባት በመናገር ቀኖና ከተቀበላችሁ በኋላ በስጋው ደሙ መጋባት ትችላላችሁ። ስርአተ ተክሊል ግን መፈፀም አይቻልም። ዋናው ነገር ለስጋዊ ስም እና ዝና ተብሎ እግዚአብሔርን በሚያሳዝን ሁኔታ የማይገባንን ስርአተ ተክሊል ከመፈፀም ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ እውነቱን አረጋግጠን የምናገኘው ክብር በስርአተ ተክሊል ከምናገኘው ክብር እኩል ስለሆነ የሚያሳስበን እና የሚያስጨንቀን ነገር አይኖርም።
መልስ፦ ማንኛውም ክርስቲያን በ40 ቀን በ80 ቀን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነት ከተቀበሉ ጀምሮ ከቅዱስ ቁርባን እንዲለዩ አይፈቀድላቸውም። ቅዱስ ቁርባን ለነፍሳችን ዘለአለማዊ ህይወት በስጋዊ ህይወታችን ደግሞ በበረከት እና በእግዚአብሔር አጋዥነት እንድንኖር ስለሚረዳን በእግዚአብሔር ፈቃድ በሞት እስከምንጠራበት ዘመን ድረስ ቅዱስ ቁርባን መቀበል ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው። በመንፈሳዊ ህይወታችን ውስጥ በሃይማኖትም በምግባርም ያበረከትናቸው የትሩፋት ስራዎች ሁሉ ማሳረጊያውና መደምደምያው ቅዱስ ቁርባን ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ምናልባት በስራ ብዛት የማንበብ እድል ካልገጠመዎ በስተቀር ስለቅዱስ ቁርባን እጅግ ሰፊ ትምህርት ማስተላለፋችንን እናስታውሳለንና እሱንም መልሰው መላልሰው ቢመለከቱት ለጥያቄዎ ይበልጥ መልስ ያገኛሉ። በዋናነት አሁንም መረዳት ያለብዎት የሰው ልጅ በራሱ ድካም የኀጢአት ሸክም ሲበዛበት ወደ ቅዱስ ቁርባን ለመቅረብ ድፍረት እና ብቃት ስለሚያጣ ማንም ሳያርቀው ራሱን ከቅዱስ ቁርባን እያራቀ ስለሚሄድ የነፍስ ረሃብና መታረዝን ያስከትላል እንጂ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ማንኛውም ክርስቲያን ከህፃንነቱ ጀምሮ እስከ መጨረሻ የእድሜ ዘመኑ ከቅዱስ ስጋውና ከክቡር ደሙ እንዳይለይ ዘወትር ታስተምራለች ትመክራለች። እኛን ዘወትር ኀጢአት የሚያሰራን ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ የዘላለም ህይወት እንዳናገኝ ራሳችንን በኀጢአት ወጥመድ እየጠለፈ ወደ ዘለአለማዊ ሞት እንድንወድቅ ያስገድደናል ማለት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ቅዱስ ቁርባንን መቀበል የማይቋረጥ ቀጣይነት ያለው መንፈሳዊ ስርአት እንደሆነ እንዲረዱት ይህን መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
ስለ ቅዱስ ቁርባን ድረገጻችን ላይ ያንብቡ፦ https://yohannesneseha.org/ስለ-
መልስ፦ መንፈስ የያዛቸው ሰዎች ሁሉ ጠያቂያችን እንዳሉት ከቅዱስ ቁርባን ሊከለከሉ አይችሉም። የአጋንንት መንፈስ በተለያየ ረቂቅ ምስጢር ሊያድር ይችላል። በፍጹም መንፈሳዊነትም የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ሳይቀር መንፈስ በተለያየ መንገድ ሊዋጋቸው ይችላል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ከቅዱስ ቁርባን ሊከለከሉ አይችሉም። ሆኖም ጨርሶ የለየላቸው ወደ እብደት ደረጃ ያደረሳቸው አይምሯቸውን አስቶ ልብሳቸውን አስወልቆ በሰው ዘንድ ነውር የሆነውን እያሰራና እያናገረ ሰይጣን የማረካቸውን ሰዎች በተለየ የፀሎት ስርዓት እና የጥምቀት ስርዓት ወደ አእምሮዋቸው እስከሚመለሱ ከቅዱስ ቁርባን እንዲከለከሉ ይደረጋል። ስለዚህ አይነት ስርዓት ፍትሐ ነገስት በሚበለው የቤተክርስቲን ቀኖና ስለህሙማን በሚናገረው አንቀፅ በተደነገገው ስርዓት እንዲሁም ስለ ቅዱስ ቁርባን መቀበል ስለሚገባቸው እና ስለማይገባቸው ሰዎችም የተደነገገውን የቤተክርስቲያን ስርዓት መመልከት ይቻላል።
የተከበሩ ጠያቂያችን ወንድ ልጅ ሆነ ሴት ልጅ በ 40ና በ80 ቀን ክርስትና ተነስተው ቅዱስ ቁርባንመቀበል ከጀመሩበት እለት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ከቅዱስ ቁርባን መለየት የለባቸውም። ሴት ልጅ ብትሆንም የወር አበባ ማየት ከጀመረች ከፈሳሹ ንፁህ የምትሆንበትን ጊዜ ትጠብቃለች እንጂ የወር አበባ በማየትዋ ብቻ ከቅዱስ ቁርባን እንድትርቅ የሚያደርጋት ምክንያት የለም። ሴትም ሆነ ወንድ ቅዱስ ቁርባን እንዳይቀበሉ የሚያደርጋቸው ምክንያት ለአካለ መጠን መድረሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአካለ መጠን ደርሰውም ድንግልናቸውን ጠብቀው በስርዓት የሚኖሩ ከሆነ መቁረብ ይችላሉ። ነገር ግን በዝሙት እና በልዩ ልዩ ኢክርስቲያናዊ ምግባር ከወደቁ ግን በአባቶች ተመክረውና ተገስፀው ንስኅ እንዲገቡ ተደርጎ ሁለተኛ ወደ ጥፋት እንዳይገቡ ንስኅ ተቀብለው እንዲመለሱ ከተደረገ በኅላ ብቻ እንዲቆርቡ ይደረጋል ማለት ነው።
ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች ሁላችሁም መረዳት ያለብን በልማድ የምናደርገውን ነገር የሃይማኖታችን ህግ ከሚለን ስርዓት ለይተን ማየት አለብን። ምክንያቱም ብዙ ጥፋቶቻችን ፦1ኛ/ በቂ የሃይማኖት ትምህርት ካለማግኘት የተነሳ ፣ 2ኛ ደረጃ የሃይማኖታችን ስርአት እንደሚከለክለን እውቀቱም እያለን ያዋቂ አጥፊ በመሆን ብዙ ጥፋቶችን በድፍረት ስንፈፀም መታየት የተለመደ ነው። ኀጢአትን ደጋግመው ከሰሩት እንደ ፅድቅ እንቆጥረዋለን ማለት ነው።ይህንን ቅድመ ሁኔታ ልንገልፅበት የቻልነው ዋናው ምክንያት በስርዓተ እርግዝና ጊዜ ማንኛውም ሰው ራሱን መግዛት ስለሚያቅተው ጥፋት እንደሚፈፅም የሚታወቅ ቢሆንም እንደ ሃይማኖታችን ቀኖና ግን ራስን መግዛትና ሥጋዊ ስሜትን በመቆጣጠር በእርግዝና ወቅት የወንድ እና የሴት ተራክቦ የተከለከለ ነው።ይህ ሲባል የሰው ልጅ ለኀጢአት የሚሰማማ ደካማ ሥጋን ለብሶ የተፈጠረ ስለሆነ የዚህ አይነቱ ስህተት በሁሉም ዘንድ እንደሚያጋጥም በመንፈሳዊ አይናችን መገመት እንደምንችል ይታወቃል :: ነገር ግን ብዙ ሰዎች ስለተባበሩበት ኀጢአት ፅድቅ ሊሆን ስለማይችል እውነተኛውና ትክክለኛው ነገር ከላይ የተገለፀው መሆኑን ትረዱ ዘንድ ይህን አጭር መልዕክት ልከንላችኋል።
ጠያቂያችን በጋብቻ ተወስነው ኑሯቸውን ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በሆነ አጋጣሚ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ቢያፈርሱና (ቢፋቱና) ሌላ የጋብቻ ቃል ኪዳን ለመፈጸም ቢፈልጉ ቀደም ሲል ያሳለፉትን የጋብቻም ሆነ የግል ህይወታቸውን ለንስኀ አባታቸው በመናዘዝ አባታዊ እና መንፈሳዊ ምክር ተቀብለው ንስኀ የሚያስፈልጋቸው ከሆነም የንስኀቸውን ቀኖና ተቀብለው ከፈፀሙ በኋላ ፤ ሌላ 2ኛ ጋብቻ ለመፈጸም በፈልጉ ከንስኀ አባታቸው ወይም ደግሞ ስለ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት እውቀት ያላቸውን መምህር በማነጋገር ለ2ኛ ጊዜ የሥርዓተ ጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ለመፈጸም ንስኀ ገብተው በቅዱስ ቁርባን ተወስነው መፈጸም ይችላሉ። ስለዚህ በስርዓተ ተክሊል የሚፈፀምና በንስኀ የሚፈጸም ስርአት ጋብቻ ልዩነቱ ከዚህ አንፃር እንደሆነ ጠያቂያችን እንዲገነዘቡት በማለት ከዚህ በፊት ከላክንልዎ ምላሽ በተጨማሪ ላቀረቡት ጥያቄ ይህን ማብራሪያ ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን ፤ ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ የለበሱትን ነጠላ ወይም ልብስ በሌላ ጊዜ ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ መልበስ እችላለሁ ወይ? በማለት በእኛ በኩል ምክር እንድንሰጥዎ ያቀረቡትን ጥያቄ ይመለከታል።
ወደ ቅዱስ ቁርባን እና ወደ እግዚአብሔር ቤት ስንቀርብ ራሱን የቻለ ለዚህ አገልግሎት ብቻ የሚውል ሙሉ ልብስ ቢኖረን ይመረጣል። ምክንያቱም ይህን በማድረጋችን በውስጣችን ፍጹም የሆነ ልባዊ ሃይማኖትና ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳለ ያመለክታልና። ስለዚህ ጠያቂያችን ያንን በቁርባን ጊዜ የለበሱትን ነጠላ ሌላ ጊዜም እያጠቡ እርሶ እንዳሉት መገልገል ይችላሉ።
በሌላም በኩል የተለየ ልብስ ወይም ትርፍ ልብስ የሌላቸው በድህነት ያሉ ክርስቲያኖች ያንን ያላቸውን የድህነት ልብሳቸውን ባላቸው አቅም በንፁህ አጥበው መቁረብ እንዳለባቸው ደግሞ መዘንጋት የለበትም። ምክንያቱም ገና ሀብታሞች እንደሚለብሱት የተለየ ልብስ የለንም በሚል ምክንያት ከቅዱስ ቁርባን እርቀው መኖር ስለማይገባቸው ነው።
ስለዚህ ጠያቂያችን ሀሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
መልስ፦ ጠያቂያችን አንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲየን ቅዱስ ቁርባን ከተቀበለ በኋላ 1ኛ/ የማቁረሪያ ምግብ እስከሚቀምስ ድረስ ከሰው ጋር መነጋገር የማይችልበት ምክንያት መለኮታዊ እሳት የተዋሀደውን ቅዱስ ሥጋና ክብር ደሙን በተቀበለ ጊዜ ለነፍስ መድኅኒት ለስጋም በረከትን የሚያመጣውን የከርስቶስን ስጋውንና ደሙን ተቀብሎ ሌላ የሰውኛ ንግግርን መነጋገር ሃሳብን ማውጣትና ማውረድ ፈፅሞ ስለማይፈቀድ ነው። ከቅዱስ ቁርባን በላይ የሚከብር ነገር ባለመኖሩ በብዙ ፈተና የረከሰውን ህይወታችንን የቀደሰውንና የተዋረደውን ማንነታችንን ያከበረውን ቅዱስ ቁርባን ማቃለል ለኛም ከቅዱስ ስጋውና ከክቡር ደሙ ያገኘነውን ክብር ስለሚያሳንስብን ባጠቃላይ አፋችንን የመሸፈናችን ነገር ክፉ ከመናገር፣ ክፉ ከማሰብ፣ ክፉውን ድርጊት ከመፈፀም የራቅን ለመሆናችን የሚያመለክት ስርዓት ነው። ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ እህል ውሀ ቀምሰንም ቢሆን ከአንደበታችን የሚወጣው ነገር የተቀደሰና በጎ ነገር ሊሆን ይገባዋል ወይም ክፉ ሃሳብና ክፉ ድርጊት ከኛ እንዳይወጣ ያስፈልጋል ለማለት ነው። በዋናነት እንደማስረጃ የምናደርገው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ቤዛ ለመሆን በመስቀል ላይ ቅዱስ ስጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ ለኛ ያለውን ፍቅር በመስቀል ካረጋገጠ በኋላ 3 መአልትና 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር በቆየ ጊዜ ቅዱሳን ሐዋሪያትና ሌሎችም ተከታዮቹ በሀዘንና በለቅሶ የላመ የጣመ እህል ውሀ ሳይቀምሱ መቆየታቸውን የሚያመላክት ነው። ስለዚህ ዛሬ ለኛ ህይወት መድሃኒታችን የሚሆነው የሚሰጠን የተገኘው መራራ በሆነ የመስቀል መከራ ስለሆነ እኛም ዛሬ ከሚበላ ከሚጠጣ፣ ከነገር እና ከክፉ ድርጊት ራሳችንን ቆጥበን መቀበል እንደሚገባን የሚያመለክት ነው።
በ 2ኛ/ ደረጃ የተቀደሰ ሰላምታ አስፈላጊ በሆኑ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በአካልም ሆነ በስልክ እኛንም ሆነ ቁርባኑን አያረክሰውም፤ ብቻ በህሊናችን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ያስፈልጋል ለማለት ነው።
3ኛ/ ቅዱስ ቁርባን የተቀበለ ሰው ከቁርባን በኋላ ብቻውን አይሄድም የሚባለው የቆረበ ሰው ከምንም በላይ ህይወቱ የከበረና መንፈሳዊ ሙሽራ ስለሆነ የተለየ ክብርም ስለሚያስፈልገው ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን አማናዊ ክብር ለማመልከት ነው። በሌላ በኩል በዚህ ህይወትና መድኅኒት በሆነው በቅዱስ ቁርባን የከበረውን ሰው ሰይጣን በክፉ መንፈስ በጠላትነት ስለሚቃወመው አንደ አንዳንድ ባለስልጣናት ወይም በሙሽርነት የከበረ ሰው ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያስፈልጉት ሁሉ ከዚህም በላይ የሰው ልጅ ፍጹም ሰማያዊ ክብር የሚያገኝበትን ቅዱስ ቁርባን በተቀበለ ጊዜ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ ስለሚያስፈልገው ብቻ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌሎችም ብዙ አይነት ምሳሌና ሃሳብ ማቅረብ ቢቻልም ለጊዜው ግን ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱትና ለተጨማሪ መረጃ በቀኖና ቤተክርስተያንም ዝርዝር ሁኔታውን መመልከት የሚቻል መሆኑን እንገልፃለን።
ይሁን እንጂ መረዳት ያለብን ከላይ የገለፅናቸው ምክንያቶች ለስጋ ደሙ ክብር ከመስጠት የተነሳ እንጂ ስጋ ደሙን የተቀበለ ሰው ለሌላ አደጋ የተጋለጠ ይሆናል ብሎ ማሰብ የተሳሳተ ነው። እንዲያውም ከምንም በላይ ስጋውን ደሙን የተቀበለን ሰው የአጋንንት መንፈስም ሆኑ ሌላ ሃይል እንዳይቃወመው ታላቅ ግርማ ሞገስና ሃይልና ጉልበት ስለሚሆነው ብቻውን ስለሄደ ችግር ያጋጥመዋል ብሎ ማመን የተሳሳተ ሃሳብ ነው። በየገዳማትም ሆነ በየአብያተክርስቲያናት ቅዳሴ አስቀድሰው ቅዱስ ቁርባን የሚቀበሉና የሚያቀብሉ ብቻቸውን አገር አቋርጠው ሲሄዱ እነሱ ለሌላው ክብርና ሞገስ ይሆናሉ እንጂ በነሱ ላይ የሚደርስባቸው አንዳችም ክፉ ነገር የለም።
ስለ ቅዱስ ቁርባን የጠየቁን አባላችን ሆይ፤ በመጀመሪያ ከዚህ ቀደምም ደጋግመን እንደገለፅነው ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በ40 ቀን እና በ80 ቀን የእግዚአብሔርን ልጅነት በጥምቀተ ክርስትና አግኝቶ በቅዱስ ቁርባን ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻ የዘመኑ ፍፃሜው ድረስ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ መለየት እንደሌለበት ክርስቲያናዊ ግዴታውም እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህም በቅዱስ መፅሐፍ በግልፅ ታዟል። ምክንያቱም የጌታን ቅዱስ ሥጋ ካልበላን ክቡር ደሙን ካልጠጣን የዘለዓለም ህይወት የለንም። ሰው በሥጋው በህይወት ለመኖር ዘወትር ለስጋው ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በነፍሱም የዘላለም ህይወት ለመውረስ የነፍሳችን ምግብ ቅዱስ ቁርባን ስለሆነ ነፍሳችን ደግሞ ቅዱስ ቁርበንን ካጣች እንደሞተች ወይም ህይወት እንደሌላት ማመን ያስፈልጋል።
ይሁን እንጂ ቅዱስ ቁርባን በሰው ህይወት ሲገለፅ በህፃንነት እድሜ ደረጃ ያሉ ክርስቲያኖች ሲቆርቡ ቆይተው አካለ መጠናቸው ወደ አዋቂነት ሲደርስ ይበልጥ ስለሚስጥረ ቁርባን ተምረውና አውቀው መቀጠል ሲገባቸው፤ ይባስ ብለው ቅዱስ ቁርባን እንደማይጠቅም በማሰብ ይሁን ባለማወቅ ባይገባንም ከቅዱስ ቁርባን የሚርቁ ብዙዎች ናቸው። ይሄም ነገር የቤተክርስቲያን አባቶች በእግዚአብሔር ቤት ዘንድ የሚያስጠይቃቸው የክህነት ሃላፊነት ነው። ምእመናንም ቢሆኑ የቅዱስ ቁርባንን ዘለዓለማዊ ህይወትነቱ እየተነገራቸው እያወቁና እየተረዱ ከቅዱስ ቁርባን የሚርቁ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።
ስለዚህ ጠያቂያችን ምንም እንኳን የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ኅጢአት የመወደቁ ሁኔታ የደካማ ሥጋ ባህሪ ቢሆንም በሰራነው ኅጢአት ተፀፅተን ወደ ንስኅ ህይወት ተመልሰን ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል የሚለክለን ህግ ግን የለም። ጠያቂያችን እንዳሉት ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ ቆይተው በመሃከሉ በዝሙት ተሰናክለው ከቅዱስ ቁርባን ከራቁ ወይም ርቀው ከቆዩም አሁን ማድረግ ያለብዎት ፦
1ኛ የክርስቶስ ሥጋና ደሙ ከኅጢአት የሚያፀዳና የሚቀድሰንና የሚያነፃን እንጂ የሚያርቅ ስላልሆነ በኅጢአት መውደቆትን ቢያምኑም በንስኅ ተመልሰው ሥጋ ደሙን የመቀበሉን ስርዓት እንደገና መቀጠል አለብዎት።
በ2ኛ ደረጃ ሚስት ለማገባት እቅድ ካለዎት በሥጋ ህይወት ውስጥ ባይገደዱበትም እንደ መንፈሳዊነት ግን ወደ ትዳር ህይወት ሲገቡ በቅዱስ ቁርባን ቢሆን በሥጋም ሆነ በነፍስ በረከትንና ክብሮትን ያበዛዋል።
በ3ኛ ደረጃ ማግባት ካልፈለጉም ስለሰሩት ኅጢአት በንስኅ የኅጢአት ስርየት በማግኘት ብቻዎትን በቁርባን ተወስነው መኖር ይችላሉ።
ለሁሉም ነገር ግን ስለ አንቀፀ ንስኅ ጠንቅቀው የሚያውቁ የቤተክርስቲያን አባቶች (ሊቃውንት) ሁልጊዜ በማነጋገርና በማማከር ትምህርት እያገኙ ማንኛውንም ነገር እንደ ስርዓቱና እንደ ህጉ ማስቀጠል የሚችሉበትን ፕሮግራም እንዲያደርጉ ይህን አጭር መልእክት ለእርስዎ እና ለዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም አንብባችሁ ትረዱት ዘንድ መልዕክቱ እንዲደርሳችሁ አድርገናል።
ጠያቂያችን እንዳሉት ንስኀ ገብተው ለቅዱስ ቁርባን ከበቁ በኋላ ተመልሰው በኀጢአት ከተሰናከሉ ወይም ሲቆርቡ ኑረው በመካከል ወደ ቅዱስ ቁርባን የማያቀርብ ነውር ካጋጠመዎት ለጊዜው መቁረብዎን አቁመው ወደ ንስኀ አባትዎ ቀርበው የፈጸሙትን በደል ከተናዘዙ እና ንስኀዎትን ከጨረሱ በኋላ ለመቁረብ መቀጠል ይችላሉ። ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ ቅዱስ ቁርባን ለመቅረብ እዳ በደል እንዳይሆንበት አስቀድሞ ከኀጢአት እና ወደ ቅዱስ ቁርባን ለመቅረብ ከሚከለከልባቸው ጥፋቶች መራቅ አለበት። ምክንያቱም ቅዱስ ቁርባን ከተቀበለ በክርስቲያናዊ ህይወት ውስጥ የመጨረሻው ክብር ላይ የደረሰ ሰው ነውና፤ ይሄንን ታላቅ ክብር በማቃለል ተመልሶ የማይገባውን ነውር መፈፀም ማለት ግን ታጥቦ ጭቃ እንደማለት ይቆጠራልና ተመልሰን ንስኀ መግባት ብቻ ሳይሆን የንስኀውም ደረጃ እጥፍ ድርብ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበን ራሳችንን በመግዛት በምግባርና በሃይማኖት ጸንተን ለመኖር መታገል አለብን፤ በኀጢአት ከወደቅንም ቶሎ በንስኀ ልንነሳ ያስፈልጋል። ሆኖም ጥፋቱን በመደጋገም ሁል ጊዜ በንስኀ እመለሳለሁ በሚል መንፈስ መሄድ እንደሌለብን የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። ዋናው ቁም ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን በምንም ይሁን በምን ከቅዱስ ቁርባን ላለመለየት በየጊዜው መንፈሳዊ አላማውን በማጽናት መታገል እንዳለበት እንመክራለን።
ይህንን ጥያቄ ያቀረቡ አባላችን ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም እንኳን ማንኛውም ክርስቲያን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙን ተቀብሎ በቆረበበት እለት ማንኛውም የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ስለማይፈቀድለት ለስጋችን የምንፈልገውን ማንኛውንም የእርድ ስርአት ማከናወን አይፈቀድለትም፤ ከሁሉ ነገር ራሱን መቆጠብ ስላለበት። ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙን ባልተቀበለበት ቀን ግን ማንኛውም የእርድ ስጋ ምግብ ይሆን ዘንድ ማረድ ማለት ወጥ ሰርቶ እንጀራ ጋግሮ ምግብ እንደማዘጋጀት ነውና ይቻላል።
ጠያቂያችን ስለ አጿማት ያለው የቤተክርስቲያን ስርዓት ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከ7 አመት ጀመሮ የፆም ስርዓት እንዲለማመዱ ያዛል። ከእርስዎ እንደተረዳነው 10 አመት የሆነው ወይም የሆናት በጤና ምክንያት አይፆምም ወይም አትፆምም እንደተባለው ያጋጠመውን የጤና ችግር በእኛ በኩል የተወቀ ነገር ባይኖርም ፤ ነገር ግን ማድረግ ያለብዎት የቁርባን ስረዓት በጠዋት ቅዳሴ እንዲሆን ማድረግ የአማራጭ መንገድ ነው። በ2ኛም ደረጃ ምናልባት የህመሙን አይነት ብናውቀው መፆም ወይም አለመፆም ስለመቻሉ ጉዳይ መልሱን ከተጨማሪ ምክረ ሃሳብ ጋር ልናሳውቅዎት እንችላለን። ስለዚህ ጠያቂያችን ለሁሉም ነገር በውስጥ መስመር በላክንልዎ ቁጥር ደውለው ቢያገኙን መልካም ነው።
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ ላይ ያገኛሉ
ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የንስኀ አባትዎን አነጋግረው የንስኀ ቀኖና ተቀብለው በትክክል ከፈፀሙ በኋላ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ይችላሉ። ነገር ግን ሳንረዳውና ሳይዘረዝሩት የቀረ ሃሳብ ካለ እርስዎም እኛም ህሊናችን ነፃ ይሆን ዘንድ ደውለው ቢያገኙን መልካም ሲሆን ያም ሆነ ይህ ግን የምንችለውን ያህል ንስኀ ከገባንና በውስጣችን ፈሪሀ እግዚአብሔር ካለ ከቅዱስ ቁርባን እንድንርቅ የሚከለክለን ህግ ስለሌለ፥ እኛንም የሚያስደስተን ነገር የምዕመናን ለዚህ መብቃት ነውና ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ተረድተው እንዲፈፅሙ እንመክራለን።
ጠያቂያችን በእርስዎ በኩል ያቀረቡልን ጥያቄ ተገቢ ስለሆነ የመፍትሄ ሃሳብ ለማግኘት እስከሆነ ድረስ እጅግ እናበረታታለን። ምክንያቱም የሰው ልጅ በህይወት በሚያጋጥመው መንፈሳዊም ሆነ ስጋዊ ፈተና መፍትሄ የሚሆን ምክር ከመንፈሳዊ አባቶችም ሆነ ከሌላ ባለሞያዎች ማማከር እጅግ ብልህነት ነው። ይሁንና በጤና ባለሞያዎች መድሃኒት ህክምና ላይ ያለውን ሰው እንደገና በመንፈሳዊ ስርዓት እውነተኛ መድኃኒት የሆነውንና ዘለዓለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን ቅዱስ ቁርባን እንደ 2ኛ አማራጭ በማሰብ ሃኪም ባዘዘው መድኀኒት ላይ ደርቦ በአንድ ጊዜ ለመውሰድ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት አግባብነት አይኖረውም። እንዳሉትም በፍፁም እምነት ላለ አንድ ክርስቲያን ከቅዱስ ቁርባን በላይ እውነተኛ መድኀኒት የለምና የህክምና ክትትሉንና መድኀኒቱንም አቋርጥ ብንለው ታማሚውን አደጋ ላይ እንዳንጥለው የጤና ባለሞያዎችም ወይም ሀኪሞችም በተሰጣቸው ዕውቀት የሰውን ልጅ አክመው እንዲያድኑ የሚያደርጉት ጥበብ የእግዚአብሔር ፀጋም ስለሆነ፥ በተወሰነ ጊዜ መድኀኒቱን የሚጨርስበት ወይም ለተወሰኑ ቀናት የሚያቆምበትን ሁኔታ ካለ ሀኪሙን በማማከር በዚያ ባለው የጊዜ ክፍተት ውስጥ ቅዱስ ቁርባን እንዲወስድ ማድረግ ይቻላል። እስከዚያው ድረስ ግን ፀሎተ ቀንዲል የሚባለው ፀሎት ደርሶለት፣ ቅባቅዱስ እየተቀባ፣ የሚችል ከሆነም ፀበል እየተጠመቀ ካልቻለም እየጠጣ፣ በራሱ እምነቱን እየተቀባ የእግዚአብሔርን ቸርነት እና ምህረት መለመን ይችላል። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ ይረዱት ዘንድ ይህን አጭር ማብራሪያ ልከንልዎታል።
እርግዝና እራሱን የቻለ ልዩ እንክብካቤ እና ክብር የሚያስፈልገው የህይወት መሰረት ነው። ያረገዘች ሴት በተፈጥሮ ፀጋ ያገኘችው የእግዚአብሔር ስጦታ ቢሆንም እግዚአብሔር በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረውን ስነፍጥረት በመሀፀንዋ 9 ወር ከ 5 ቀን ሃላፊነት ወስዳ መሀፀንዋን እንደ አለም አድርጋ በእግዚአብሔር ልዩ ጥበብ ፅንሱ ከእርሰዋ የህይወት እስትንፋስ እያገኘ የመቆየቱ ሂደት ከንስሓ ህይወት የበለጠ ፈጣሪዋን እንድታውቅ የሚያደርጋት ህይወት ስለሆነ ጠያቂያችን እንዳሉት ያረገዘች ሴት ንስሓ በመግባት መስገድም ሆነ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል አትችልም። በፆም ያረገዘች ሴት በቤተክርስቲያን ለፀሎት፣ ለማስቀደስ እና ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ብዙ እንድትቆምም አትገደድም። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጉባኤ እና ከእግዚአብሔር ጸጋ እንዳትለይ ብቻ ድካመ ስጋ እስከሚሰማት ድረስ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ መስቀል መሳለም፣ ፀበል መጠጣት እምነት መቀባት ትችላለች። ጤነኛው ሰው በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ቁሞ መስማት ሲገደድ እስዋ ግን ልክ እንደታመመ ሰው ቁጭ ብላ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት የእርግዝና ቆይታዋን ታሳልፋለች። ያረገዘች ሴት በእርግዝና ግዜ ንስሓ መውሰድ የማትችልበት ምክንያት መስገድን፣ ለረጅም ሰዓት መፆምን፣ ቁሞ መፀለይን የሚጠይቅ መንፈሳዊ አላማ ስለሆነ እነዚህን አይነት ንስሓ እንዲቀበሉ አይደረግም። የታመሙ ሰወችም እንዲሁ። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ አግባብ እንዲረዱት ይህን መልእክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን፤ በመጀመሪያ በተቻለ መጠን ይህ እንዳይሆን በመንፈሳዊ ስርዓት ሆነን ህሊናችንን ሰብስበን ለስጋዊ አስተሳብ ቦታ ሳንሰጥ፥ በፀሎት በመትጋት ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወይም ደግሞ እርስዎ እንዳሉት ከእኛ አቅም በላይ በሆነ ፈተናው ገፍቶ ቢያጋጥም ግን ገና ለገና ቤተሰብም ሆነ ሙሽሮቹ ተዘጋጅተዋል በሚል ምክንያት የእግዚአብሔርን ህግ መጣስ ስለማይቻል ቅዱስ ቁርባን የመቀበሉን ስርዓት ለሌላ ጊዜ እንዲዛወር ይደረጋል እንጂ ሰውን ላለማሳዘን ተብሎ የእግዚአብሔርን ህግ መተላለፍ እንደማይገባ ማወቅ አለብን። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።