ስለ ቅዱስ ቁርባን ጥያቄና መልስ ቁ.2
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ቅዱስ ቁርባን ጥያቄና መልስ ቁ.2
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
ጠያቂያችን፤ ልጆች ስንት አመት ሲሆናቸው ነው በቤተሰባቸው ስር ሆነው መቁረብ የሚያቆሙትና በራሳቸው ንስኀ አባት የሚይዙት? ብለው ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ ምላሽ። ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ለማስረዳት እንደሞከርነው ማንኛውም ልጅ ወንድ በ40 ቀኑ ሴት በ80 ቀንዋ ክርስትና ተነስተው የእግዚአብሔር ልጅ ሲሆኑ ሴትም ሆነ ወንድ ክርስትናን ከተቀበሉበት ጀምሮ እግዚአብሔር ፈቅዶ በአካለ ስጋ እስካሉበት ቀን ድረስ መላ ጊዜያቸውን ከቅዱስ ቁርባን መለየት እንደሌለባቸው ክርስቲያናዊ መብታቸውም ግዴታቸውን ነው። በቤተክርስተያን የተደነገገውም ይህው ነው።
በሌላ መልኩ ጠያቂያችን እንዳሉት ለልጆቹ ከቤተሰብ በኩል ሃላፊነት የሚኖረው የልጆቹ የእድሜ ክልል እስከምን ድረስ ሲሆን ነው? ለሚለው ዋናው የጥያቄ ሃሳብ መልስ የሚገልፀው፦ አንድን የተዘራ ዘር ወይም መሬት ላይ ከተከልነው ተክል አስፈላጊውን እንክብካቤ አድርገን መአድን ወይም ለም መሬት አመቻችተን የሚያቀጭጨውን አረሙን ነቅለንለት በአስተዳደጉ እንዳይወላገድ አድርገን በየጊዜው ከተከታተልነው ብቻ ለተክሉ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ካደረግንለት በመጨረሻ ተገቢውን አገልግሎት እንደሚሰጥ ሁሉ ፤ ህፃናትም በሃይማኖታቸውና በክርስትና ህይወታቸው ታንፀውና አስፈላዊን መንፈሳዊ ህይወት አግኝተው ካደጉ በመጥፎ ስነምግባር እንዳይወድቁም የተስተካከለ መንፈሳዊ እድገትና አቋም እንዲኖራቸው አድርገን እውነተኛውን መንገድ መርተን ካሳየናቸውና በዚያ መንገድ እንዲሄዱ ካደረግናቸው ለአካለ መጠን ቢደርሱም እንኳን ለሃይማኖታቸውና መንፈሳዊ ህይወታቸው የማይጠቅም የሆነውን ነገር ሁሉ ስለሚጠየፉና ከሃይማኖት አባቶቻቸውና ከወላጆቻቸው የተማሩትን መልካም ስነምግባር ብቻ ይዘው እስከ መጨረሻ ድረስ ስለሚቀጥሉ ምንም አይነት የጊዜ ገደብ ሊሰጣቸው ከቶ አይገባም።
ይሁንና ፤ የጠያቂያችንን ሃሳብ ለማብራራት ያህል ሴት ልጅ ለአካለ መጠን በደረሰች ማለትም 15 አመትዋ፣ ወንድ ልጅ ለአካለ መጠን ከደረሰ ቢያንስ 18 አመት በላይ የራሳቸውን እድልና መብት የሚያስከብሩበትን በመንፈሳዊ እና በማህበራዊ ጉዳይ ራሳቸው ሃላፊነት ወስደው ህይወታቸውን ስለሚያስቀጥሉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሃይማኖታቸውም አንፃር የሚያደርጉትን ሁሉ አውቀውና ተረድተው ወስነውበት ስለሚሆን ቤተሰብ እዚህ ደረጃ እስከሚደርሱ በስርዓቱ ካሳደገ ሃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት ይቻላልና ሊያስጠይቀው የሚችል ጉዳይ አይኖርም።
በጠቃላይ ሁሉም ወላጅ ወይም ቤተሰብ በወለዳቸው ልጆች ላይ ትልቅ ሃላፊነት ስላለበት የሚችለውን ሁሉ በመንፈሳዊ ህይወትም ሆነ በማህበራዊ ህልውናቸው ላይ የተስተካከለ እንሆኑ ጠያቂያችንም እንዳደረጉት የሚቻለውን ሁሉ ካደረጉላቸው ከዚያ በኋላ ከቤተሰብ የወረሱትን መልካም ስነምግባርና ሌሎቹንም ክርስቲያናዊ መንፈሳዊ ህይወት ይዘው ስለሚቀጥሉ አያሳስብዎትም።
ስለዚህ በአጠቃላይ የዮሐንስ ንስኀ አባሎቻችንም ስለ ህፃናት መንፈዊ አስተዳደግ የቤተሰብ ሃላፊነት ከቤተክርስቲያን አስተምሮ አንፃር ሲታይ ምን መሆን እንዳለበት በጠያቂያችን ሃሳብ ተነስተን ግንዛቤ እንዲኖራችሁ በማሰብ ይህን አጭር ማብራሪያ እንዲደርሳችሁ አድርገናል በተግባር እንድታውሉት እየመከርን፤ ወደፊትም አስፈላጊ ከሆነ በዚህ ርዕስ ሰፋ አድርገን ልናስተምራችሁ የምንችል መሆኑን እንገልፃለን።
ጠያቂያችን፤ እርኩስ መንፈስ ሁልጊዜም ቢሆን የእኛን የቅድስና ህይወት ለማርካት እና መንፈሳዊ ጉዟችንን ለማሰናከል የማያስቀምጠው የፈተና ድንጋይ የለም። ሁል ጊዜ በረቀቀ መንገድ እኛን ጠልፎ ለመጣል የሚያስቀምጥብን የማይታይ የፈተና እንቅፋት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን በውስጥዎም ያለወትን መንፈሳዊ ፍቅር እና ፈሪሀ እግዚአብሔር ታላቅ ስለሆነ ዘወትር ወደ ቤተክርስቲያን ለመገስገስ ሲያስቡ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ቆመው ሲያስቀድሱ፣ ተሰጥኦ ሲቀበሉ፣ ዘወትር ሲፀልዩ፣ ዘወትር ቃለ እግዚአብሔር ሲማሩ፣ ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ ሁሉ ሰይጣን የራሱን ፈተና በህይወትዎ ላይ ማምጣቱ የማይቋረጥ ሂደት ነው። ምክንያቱም ሰው በሃይማኖት እና በክርስቲያናዊ ህይወቱ ሲበረታ ከእሱ እጅ የሚያመልጥበት መንፈሳዊ ጥበብ ስለሆነ፥ ሰይጣን ደግሞ በባህሪው ተስፋ የማይቆርጥ ርካሽ እና ልክስክስ የሆነ ባህሪ ያለው ሁል ጊዜ ከጌታው በር ፍርፋሪ እንደሚጠብቅ ውሻ ሁሉ በየቀኑ ከጌታውና ከፈጣሪው ቤት ሊያወጣቸው እና እንደ ፍርፋሪ ሊለቃቅማቸው የሚፈልጋቸውን በማሳደድ ላይ ያለ ጠላት ስለሆነ እርስዎ ደግሞ በዚህ መንፈሳዊ የፅናት አላማ እያመለጡት እንደሆነ እና እስከመጨረሻው እየተጋደሉትም ቢሆን ድል እንደሚነሱት ስለሚያውቅ ያለውን የክፋት እና ጠላትነት ስራውን ስለሆነ የሚያካሂደው እርስዎም ተረጋግተው ካሉበት እውነተኛ የሃይማኖት ጽናት ቆመው በየጊዜው የሚያጋጥምዎት ጥቃቅን ፈተና ተቋቁመው በዚሁ በተቀደሰ አላማዎ መበርታት ይገባዎታል።
በጥያቄዎ እንደተገለጸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ፀጋውና ቸርነቱ በዝቶለት ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው ለማስቀደስና ለመቁረብ ተዘጋጅተው ባሉበት ሰአት ተከሰተ ያሉትን አጋጣሚ እንደ ትልቅ የኀጢአት አይነት አይተው ከፈጣሪ ጋር ያጣላኝ ይሆን በሚል ሃሳብ መታወክ የለብዎትም። የእግዚአብሔር ምህረት አደባባይ ስንገባ ሰይጣን የሚያመጣብንን ፈተና ከፈተናውም በፊት ከሰይጣንም በፊት በእኛም ላይ ይህ አይነት ፈተና ከመከሰቱ በፊት እንደሚመጣብን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው። እኛም አውቀን ፣ ወደን እና ፈቅደን ያመጣነው ፈተና ስላልሆነ በአንዳችም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላንም አይደለም ወይም በኀጢአት የሚያስጠይቀን አይሆንም። እንደውም በመንፈሳዊ ህይወት እያለን የሚከሰቱ ፈተናዎች የእኛን የሃይማኖት ጥንካሬ የሚገልፁ ምስጢር እንደሆኑ መታሰብ አለበት። ቅዱስ ኤፍሬም አባታችን በውዳሴ ማሪያም ኀጢአት እና ፈተና በበዛበት ሁሉ የእግዚአብሔር ፀጋም በዚያ ትኖራለች ወይም የእግዚአብሔር ፀጋ ባለበት ቅድስና በበዛበት ቦታ ደግሞ የሰይጣን ፈተናና ኀጢአት ይበዛል ብሎ እንደተናገረ ሁሉ በመንፈሳዊ አላማ ውስጥ እያለን የሚመጣው ፈተና ሁሉ ፀጋችንን ያበዛልናል በመንፈስም አንድንጠነክር ያደርገናል እንጂ ወደሌላ ጥርጣሬ እና ውድቀት ውስጥ እንድንሄድ አለመሆኑን ተረድተው በነገር ሁሉ በርትተው እንዲጠነክሩ በመንፈሳዊ አላማዎይም ይቀጥሉ ዘንድ ይህን አርጭ መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ጥበቃ አይለይዎት
በጽኑ ህመም ላይ እያሉ በህክምና እየተረዱ ያሉ ወገኖች ስርዓተ ቁርባን እንዴት ይሰጣል ብለው ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ ምልሽ፦ መጀመርያ ማንኛውም ክርስቲያን አጽንዎት ሰጥቶት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ያለምንም መዘንጋት በቁርጠኝነት ማሰብ ያለብን በየጊዜው ዘለአለማዊ ህይወት ከሚሰጠን አና እኛ ሳንጠይቀው የሚያስፈልገንንም ነገር ምን እንደሆነ ሳናውቅ በሁሉ ነገር መለኮታዊ ቸርነቱ ስፍር ቁጥር የሌለበት አምላክ በሚያልፍ ህይወት ሳይሆን ዘለዓለማዊ ህይወት ሊያከብረን፣ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ የሆነውን ህይወት ሊያወርሰን ፈቃዱ ስለሆነ ከጠፋንበት ዳግም መልሶ ከሞት ወደ ህይወት ይመልሰን ዘንድ ስጋን ተዋህዶ የመጨረሻውን ነገረ ምስቀል ተቀብሎ ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን እንካችሁ ዘለዓለማዊ ህይወት አግኙ ብሎ ስለሰጠን ከቅዱስ ቁርባን ሳንለይ መኖር እንዳለብን በእጅጉ መንፈሳዊ ፈቃድ ሳይሆን መንፈሳዊ ግዴታ ነው።
እንግዲህ በብዙ መዝረክረክ ውስጥ እና በብዙ መባዘን ውስጥ የቆዩ ሰዎች ቅድመ ጥንቃቄ ሳያደርጉ እለት እለት ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን ሳይመርጡ እንዲሁ ሲባዝኑ የኖሩ ሰዎች ግን በፅኑ ደዌ ተይዘው ወይም ደግሞ ለመዳን በማያስችል ደዌ ስጋ ከወደቁ የነፍስ እረኛ የሆነው የንስኀ አባት ሄዶ አናዟቸውና አናግሯቸው የነሱን የግል ኑዛዜ ከተቀበለ በኋላ እንደ ስርዓተ ቤተክርስቲያን በሰው እርዳታ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመጡ ተደርጎ ስርዓተ ቁርባን ሊቀበሉ ይችላሉ፤ ወይም ባሉበት ቦታም አባቶች ወስደው የክርስቶስን ቅዱስ ስጋና ክቡር ደም እንዲቀበሉ ያደርጓቸዋል፤ ምክንያቱም የመጨረሻው የህይወታችን ሁሉ መደምደሚያ ስለሆነ ይህን ክብር እንዳይቀርብን ከማድረግ አንፃር ነው። ምክንያቱም ስጋዬን ያልበላ ደሜን ያልጠጣ የዘለዓለም ህይወት የለውም ስለሚል ቃሉ ምንም ድርድር የለውም የዘላለም ህይወት ሳያገኙ እንዳይቀሩ ሁሌም ቤተክርስቲየን ትደክማለች ትጥራለችና ለዚህ ሳይበቁ እንዳያልፉ ምእመናን ካህናት እንዲህ አይነት ችግሮችን እየተወያዩ የሚገባውን ስርዓት ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ፈቅዶ የታመመው ሰው ከዳነም ንስኀውን እንዲፈፅም ወይም የእዳ ካሳ ሊከፍል ይችላል። የማይድንበት ሁኔታም ካለ እግዚአብሔር አለምን ከፈጠረበት አለምን ያዳነበት ጥበቡ ታላቅ ስለሆነ የራሱ መለኮታዊ ስልጣን ስለሆነ እኛ የሰው ልጅ የሚድንበትን እና ከኀጢአት ወጥመድ የሚያመልጥበትን በፍጹም ሃይማኖታዊ ስርዓት ማድረግ የሚገባንን ነገር ማድረግ እንጂ የማዳን እና የኀጢአት ስርየትን የመስጠት ስልጣን የሱ ስለሆነ፥ ጠያቂያችን እርስዎ እንዳሉትም መፈፀም ያለበት ስርዓት ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን ለመንጋው ለማቀበል ወይም ለመቀበል ወይም እንዲቀበል የሚደረግበት ስርዓት እንዳለ መረዳት ይገባል። ይህንንም ወደፊት በሰፊው ትምህርታዊ ማብራሪያ ልንሰጥበት እንችላለን።
ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ተረድተው ተጨማሪ ምክር እና ትምህርት ከፈለጉ በውስጥ መስመር በስልክ ሊያነጋግሩን ይችላሉ። ዞሮ ዞሮ የሰውን ልጅ በነፍስ ከማዳን የበለጠ በእግዚአብሔር ዘንድ ሌላ የሚወደድ ነገር የለምና በአንድም በሌላም ሰው የሚድንበትን ጥበብ መጠቀም አስፈላጊ ስለሆነ እንዳልነውም በጽኑ ደዌ ያለውን ታማሚ ሰው ቢያንስ በስጋ ከሞት ካልዳነም በነፍስ ህይወት የሚሰጠውን የክርስቶስ ስጋና ደም እንዲቀበል ማድረግ ከሁሉ በላይ የሚቀድም ተግባር መሆኑን በመግለፅ ይህን መልዕክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን ፤ በመሰረቱ የቅዱስ ቁርባን መቀበል ስርአት የማያቋረጥ ስለሆነ ሁሉም ሰው ከጋብቻ በፊትም፣ በጋብቻ ጊዜም፣ ከጋብቻ በኋላም፥ ቅዱስ ቁርባን መቀበል መንፈሳዊ መብቱም ግዴታውም ነው። ስለዚህ ቅዱስ ቁርባን መቀበል እንዳለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። ይሁን እንጂ አንደኛው ወገን ቅዱስ ቁርባን እየተቀበለ ቢቆይና አንደኛው ወገን ደግሞ ቅዱስ ቁርባን አቋርጠው የቆዩ ቢሆኑ በጋብቻው ቀን በጋራ መቀበል እንደሚችሉ ሆኖ ነገር ግን ከቅዱስ ቁርባን እርቆ የነበረው አካል የንስኀ አባትን በማነጋገር ቀኖናውን መቀበልና በቅርበት ከአባቶች ትምህርት በማግኘት በአባቶች ምክር እንዲመራ እንመክራለን።