ስለ ትዳር የጥያቄና መልስ ቁ.2

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ትዳር ቁ.2

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

ጠያቂያችን ያቀረቡት ጥያቄ 80 ሳይፈርስ የተለያዩ ባልና ሚስት በየግላቸው መቁረብ ይችላሉ ወይ? ላሉት የተሰጠ ምላሽ፦

በመሰረቱ ጋብቻው በምን እንደሆነ መገለፅ አለበት፤ ማለትም በባህላዊ ነው? በማዘጋጃ ቤት ነው?  ወይስ ደግሞ በሃይማኖት ነው? ምንያቱም ጋብቻቸውን በስርዓተ ቤተክርስቲያን የፈፀሙ ከሆነ፤ ወይም ደግሞ ጋብቻ ከፈፀሙ በኋላ በስርዓተ ቁርባን የተወሰኑና በሆነ ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ ቢለያዩ መጀመሪያ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ለንስኀ አባታቸው እና ለሽማግሌዎች አወያይተው ቢታይና ችግሩን ለመፍታት ቢሞከር። ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት ከአቅም በላይ የሚሆን አጋጣሚ ከሆነ በየግላቸው  ጠያቂያችን እንዳሉት ቂም በቀላቸውን ትተው ወይም ያዘኑበት ምክንያት ለእግዚአብሔር በመስጠት ይህንኑ ኑዛዜያቸውን ለንስኀ አባታቸው በመናገር ህሊናቸውን ነፃ አድርገው እንደተባለው እየቆረቡ መቆየት ይችላሉ።

በመጨረሻ ችግሩ የሚፈታው በመለያየት ከሆነና  በየግላቸው ለመኖር ቢወስኑ እንኳን ቅዱስ ቁርባኑን አፍርሰው ወደ አለማዊ ስራ እንዳይገቡ በመጠንቀቅ አንድም በአላማ እነሱን የሚመስል እና በስጋወደሙ ተወስኖ የሚኖሩ ሰዎችን መርጠው ማግባት የሚችሉ ሲሆን፤ ከዚህ ውጪ ግን ለየብቻቸው በቅዱስ ቁርባን ተወስነው ዘመናቸውን ለማሳለፍ መወሰን አለባቸው።

ይህን ምክን እየሰጠን ያለነው ማንኛውም ክርስቲያን ከብዙ ሰይጣናዊ ፈተና ተለይቶ ያገኘውን ታላቅ እድል በስጋዊ ፈተና ወይም በአጋጣሚ በተፈጠረ ጠብ ዘለዓለማዊ ክብራቸውን ማጣት ስለሌለባቸው ቅዱስ ቁርባንን ከሁሉ በፊት ማስቀደም ስላለብን እንጂ በቂም በቀል እርስ በእርስ በሚያካስስ መለያየት እያሉ በድፍረት ሊቀበሉት የማይገባ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።

ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከናል፤ ለተጨማሪ ትምህርት እና ምክር  በውስጥ መስመር ሊያገኙን የሚችሉ መሆኑን እየገለጽን፤ ለበለጠ ግንዛቤ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦልን ያስተላለፍነውን ምላሽ እንደሚከተለው ልከንለዎታልና አንብበው ይረዱት።

👉ቀረቦ የነበረው ጥያቄ፦ በትዳር የነበሩ ባልና ሚስት ከተፋቱ በኃላ ሌላ ባል/ሚስት እሰከሚያገቡ ንሰሃ ወስደው መቁረብ ይችላሉ?

የሰጠነው መልስ፦ ጠያቂያችን፤ በመሰረቱ ከዚህ በፊትም እንደመከርነው ባል እና ሚስት የስጋ አስተሳሰብ በሆነ ፈተና ለሚያጋጥማቸው ችግሮች እንዲፋቱ አይፈቀድላቸውም። ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከተፋቱ እንኳን፦

1. በየግላቸው ስጋው ደሙን ለመቀበል የሚችሉት በቀጣይ ህይወታቸው ሴቷም እንደስዋ በቁርባን ተወስኖ የሚኖረውን ለማግባት፣ ወንዱም እንደሱ በቁርባን ተወስና የምትኖረውን ለማግባት ከሆነ እየቆረቡ ለመኖር ይችላሉ።

2. ወንዱም ሆነ ሴቷ አብረው የነበሩበት የጋብቻ ቆይታቸውንና የተፋቱበትን ዋና ምክንያት ተናዘው እንደነሱ በሃይማኖትና በምግባር የሚወሰነውን ባል ወይም ሚስት በማግባት እየቆረቡ መንፈሳዊ ህይወታቸውን ማስቀጠል።  

3. ሁለተኛ ላለማግባት የወሰኑ ከሆነ ንፅህናቸውን እና ቅድስናቸውን ጠብቀው በየግዜው የነፍስ አባታቸውን እያማከሩ በስርዓተ ቁርባን ህይወታቸውን ማስቀጠል ይችላሉ። 

4. ሌላው ቀጣይ ህይወታቸውን ስርዓተ ምንኩስና በመወሰን መንፈሳዊ ልባዊ ውሳኔ ካላቸውም በስርዓተ ቁርባኑ ተወስነው ከቆዩ በኋላ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት የንስሓ አባታቸውን አማክረው ለምንኩስና የሚያበቃቸውን መስፈርት ሲያሟሉ እንዲመነኩሱ ይደረጋል ማለት ነው።

5. ዲያቆን ወይም ቄስ ሚስቱ ብትሞትበት ወይም ከሱ አቅም በላይ በሆነ ፈተና ቢፋታ፤ ያለ ሚስት የሚቀድሰውም ሆነ አባት የሚሆነው እስከ 6 ወር እንደሆነ በፍትሐ ነገስት ተወስኗል። ከዚያ በኋላ ግን ወይ መንኩሶ በክህነቱ ይቀጥላል፤ ወይም ፈተናውን የማይችለው ከሆነ ለቤተክርስቲያን አባቶች በግልፅ ተናግሮ በቅዱስ ቁርባን ተወስና የምትኖረውን ያገባል። ከዚህ በኋላ ግን መቀደስም ሆነ አባት መሆን አይችልም። የውጭ አገልግሎቱን እያከናወነ እየፀለየ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃውን የቱሩፋት ስራ እነሰራ መኖር ይችላል።

ስለዚህ ጠያቂያችን በአጭሩም ቢሆን ይህንን ማብራሪያ እንዲደርስዎ ስላደረግን አንብበው እንዲረዱት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።

ጠያቂያችን ከምንም በላይ መገንዘብ ያለብዎት ኀጢአት ባንሰራው መልካም ሆኖ ሳለ ከሰራነው ግን የመጨረሻ አማራጫችንና ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት መንገድ ንስሐ ነውና፤ የነፍስ እረኛ እንዲሆኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የክህነት ስልጣን የተሰጣቸው አባቶች ካህናት ስለሆኑ ጠያቂያችን ለንስሓ አባትዎ ኀጢአቶን ተናዘው ቀኖናዎትን መውሰድ አለቦት። ያን ግዜ በግል ኑሮዎትም በማህበራዊ ህይወቶትም ያለው ግንኙነት ሰላም ይሆንልዎታል፤ የተረጋጋ መንፈስም ይኖርዎታል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፀጋና ሰላም ከእርስዎ ጋር ስለሚሆን። ከእውነተኛ ሃይማኖትና ምግባር ስንርቅ ግን የንስሐ ህይወታችን ጨርሶ ይቀጭጫል። ያኔ ደግሞ በሰራነው ኀጥያት (ጥፋት) ነፍሳችን ፈፅሞ ትቃተታለች ትጨነቃለችም። ስጋችን ምድራዊ የሆነውን የስጋ ስራ ለመስራት ነፍሳችን ደግሞ ሰማያዊ የሆነውን የፅድቅ ስራ ለመስራት ለኛ ግልፅ ሆኖ በማይታወቅና በማንረዳው ሁኔታ ሁለቱም ህይወታችንን የጦር አውድማ ሲያደርጓት በኛ ላይ የፍርሃት መንፈስ ይነግስብናል። ከጥፋታችን ተመልሰን ንስሐ እንዳንገባ ደግሞ የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው እና የእኛን ፅናት የማይፈልገው ሰይጣንም ግራ እንዲገባን እና የፍርሃቶቻችን ምክንያቶች እንዲበዙ ያባብስብናል። ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲሰያን ሁል ጊዜ ሊዘነጋው የማይገባው የሰይጣን ቋሚ ተግባር እኛን ለመፈተን እና ከመንፈሳዊ ህይወት ለማፈናቀል ዘወትር እንቅልፍ ስሌለው  በእያንዳንዳችን ላይ እንደየደካማ ጎናችን ፈተናችንን እንደሚያበዛው እና ለውድቀት የምንበቃበትን ጉድጓድ ዘወትር እንደሚቆፍርልን መዘንጋት የለብንም። የሰው ልጅ መላ ዘመኑን ለፅድቅ ስራ ከሚያሳልፈው ግዜ ይልቅ ለኅጢአት የሚያውለው ግዜ ብዙ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በኅጢአት ጠፍተን እንዳንቀር ተመልሰን ንስሓ እንድንገባ የሚፈቅድ አምላክ ስለሆነ ለዘመናት ከሰራነው ኅጢአት ይልቅ በተወሰነ የቀኖና ግዜ የሰራነው ፅድቅ ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ጥፋት ፍቆ ንስሐ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት እንድንበቃ ታደርጋለች። 

ስለዚህ፤ ጠያቂያችን ለዚህ ችግርዎ  የምንመክርዎት ፍርሀት አንዱ የሰይጣን ውግያ ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ የፍርሃት አምላክ ሳይሆን የፍቅርና የሰላም አምላክ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወምዎትን የፍርሀት መንፈስ እንደምንም ታግለው ያሸንፉት። በመሰረቱ በሰው ዘንድ አዲስ የሆነ ተሰርቶ የማያውቅ ኀጢአት ከቶ አይኖርምና፥ በእርስዎም ላይ የደረሰቦትም፥ ሰው ፈፅሞት በንስኀ ህይወት ያለፈበት የኀጢአት አይነት እንደሆነ ተረድተው፤ የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ ወደ ንስሐ አባት ቀርበው ፤ ንስሐአባት ከሌለዎትም በእኛ በኩል ያሉትን አባቶችን በውስጥ መስመር በማማከር የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለው ቢያምኑም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና አሁንም ፍርሃቶትን አርቀው ወደ ይቅር ባይ አምላክ ይቅረቡ በማለት ምክራችንን እንለግሳለን።

 

ጠያቂያችን፤ ወደ ፕሮቴስታንት ሃይማኖት የሄደው ጓደኛዎ ተመልሷል ሲባል ወደ ሃይማኖቱ ይሁን ወይም ወደ ጓደኝነቱ ግልፅ ባይሆንም ፥ ነገር ግን በጓደኝነት ኖራችሁ ከተለያያችሁ ከጊዜ በኋላ ተመልሳችሁ አብራችሁ መሆን እጅግ የሚያስደስት ነገር ሆኖ፤ ነገር ግን ወደ ቤተክርስቲያን ቶሎ ቶሎ አልሄድም የማለታቸው ነገር የሃይማኖት ችግር እንዳለ የሚያስረዳ ስለሆነ በእንዲህ አይነት ሁለት ሃሳብ መወላወል ስለማያስፈልግ ነገሩን መመርመር ይገባል። ምክንያቱም ከሃይማኖት የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና። ስለዚህ በቅድሚያ በመካከላችሁ ሁለታችሁንም ሊያግባባ በምክርና በትምህርት ለያንፃችሁ ወደሚችሉ መንፈሳዊ አባት ወይም መምህር ቀርባችሁ መሰረታዊ ችግራችሁን በቋሚነት መፍታት እንዳለባችሁ፥ ጓደኛዎትም አቋማቸውን አስተካክለው በሃይማኖት ፀንተው የጋራ ህይወታችሁንም ሆነ መንፈሳዊ አላማችሁን ለማስቀጠል እንዲችሉ በዋናነት መሰረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ማግኘትና ማመን ያስፈልጋቸዋልና ይህን አመቻቹላቸው። ነገር ግን እርስዎም እንዳሉት ይህንን ከላይ የገለፅነውን አማራጭ ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆኑ ግን በእኛ በኩል ሃይማኖትን ማስቀደም አስፈላጊ እንደሆነ እንመክራለን። ምክንያቱም በሃይማኖትም ተፈትነው ነገንና ከነገወዲያ በጋራ አላማችሁ መፅናት ባይችሉ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ስለሚሆን ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል በማለት ይህን አጭር መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል።ተጨማሪ ምክር እና አገልግሎት ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን።