ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቁ.2

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቁ.2

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

ጠያቂያችን፤ መንፈሳዊ ዝለት የሚለው አነጋገር በእርስዎ ጥያቄ አቀራረብ በኩል ምን ለማለት እና ምንን ለመረዳት እንዳሰቡ ብዙ ግልፅ ባይሆንልንም እንኳን ፥ በቤተክርስቲያን ቋንቋ መንፈሳዊ ዝለት ማለት አንድ ልጅ ከፈጣሪው ዘንድ መለኮታዊ ጥሪ ደርሶት ወይም የአባታችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ሆኖለት በልጅነት ወይም በጥምቀት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮ በሃይማኖቱም በምግባሩም ፀንቶ እና ጠንክሮ እንዲኖር የሃይማኖታችን ህግ ወይም ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል። ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ ክፉውን እና በጎውን ከለየበት ጊዜ ጀምሮ ፣ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ስነምግባር አስተምረው ሁሉን ለይቶ እንዲያውቅ ካደረጉት ጊዜ ጀምሮ፣ በመንፈሳዊ ህይወቱ ውስጥ አንድም ቀን ለአፍታም ቢሆን ቸላ ሳይል ስንፍናን እና ቸልተኝነትን ፈፅሞ ከእሱ በማራቅ በሃይማኖቱ ንቁ እና ትጉህ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባው መንፈሳዊ ግዴታው ነው። የእግዚአብሔርም ቃል የሚያስተምረን ይህንኑ ነው።

በምሳሌነት ማወቅ ያለብን ጠላት ያለበት ወታደር ወይም አንድ ሰው አንድ ቀንም ቢሆን ለጠላትነት የሚያፈላልገውን ጠላቱን መቼ እንደሚመጣ ስለማያውቅ አንድም ቀን አንድም ጊዜ ቸላ የሚልበት ጊዜ ሳይኖረው ሁል ጊዜም ነቅቶ ተግቶ ጠላቱን በመጠበቅ ከሚመጣበት አደጋ እና ፈተና ሁሉ ይከላከላል። እንዲሁ ሁል ጊዜ የእኛን ቸልተኝነት ፈተና ወይም የዋዛ ፈዛዛ ተግባር፣ በአጠቃላይ በሃይማኖት እና በምግባር ወይም በመንፈሳዊ ህይወት የምንዝልበትን ሙሉ ቀን ብቻ ሳይሆን አፍታ ጊዜም ቢሆን ሰይጣን ስለሚጠባበቃት በዛ ክፍተት ገብቶ እኛን ጠልፎ ለመጣል እና ለዘመናት የገነባነውን አላማ ስለሚያፈራርሰው መፍትሄውም ሁል ጊዜ በሃይማኖት እና በክርስቲያናዊ ስነምግባር ነቅቶ እና ተግቶ መኖር ያስፈልጋል።

ዘወትር የሚፀልይ ሰው፣ ዘወትር የሚጾም ሰው፣ ዘወትር የሚሰግድ ሰው ፣ ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰማ ሰው፣ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገሰግስ ሰው፣ ዘወትር በቤተክርስቲያን ቆሞ የሚያስቀድስ ሰው፣ ቅዱስ ቁርባን የሚቀበል ሰው፣ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያከናውን ሰው፣ በተለያየ አጋጣሚ ያንን ያስለመደውን ቢተው ጠላት ዲያብሎስ በዛ አጋጣሚ ጥፋት ይገባና የበለጠ በክርስቲያናዊ ህይወታችን እንድንዝል ክፍተቱን ያበዛዋል ማለት ነው። አንድ ሰው ከአቅሙ በላይ የሆነ ከባድ እቃ ቢሸከም ሰውነቱ ይጎዳል ፣ ከባድ ህመም ቢያጋጥመውም ሰውነቱ ይጎዳል ፣ የሚበላው የሚጠጣው ባያገኝም እንደዚሁ፣ በአጠቃላይ ከሰውነቱ የመሸከም አቅም በላይ የሆነ ጉዳይ ቢያጋጥመው ሰውነቱ ይዝልና ተዝለፍልፎ ሊወድቅ ወይም ለሞት ሊያበቃው ይችላል። እንዲሁ ሁሉ በመንፈሳዊ ህይወታችን ውስጥ ለሚመጣው ክፍተት ሰይጣን ብዙ ፈተናዎችን በእኛ ላይ ሲረበርብብን ከእኛ መንፈሳዊ አቅም በላይ ሆኖ መሸከም ሲያቅተን መንፈሳዊ ዝለት ብቻ ሳይሆን የሚያጋጥመን ከነአካቴውም በሰይጣን ፈተና ተዝለፍልፈን ልንወድቅ እንችላለን። በዚህም  ስለ መንፈሳዊ ህይወት መፅሐፍ ቅዱሳዊ ሰፊ ትምህርት እና ማብራሪያ ቢኖርም ጠያቂያችን ላቀረቡልን ጥያቄ ግን በዚህ መረዳት ስለሚቻል ለጠያቂያችንም እና በአጠቃላይ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ አባላቶቻችን ሁላችሁም ስለ መንፈሳዊ ዝለት ይህንን አጭር መልዕክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል።

ጠያቂያችን ስለ በአለሃምሳ ከዚህ በፊትም ይህንኑ ጥያቄ በተመለከተ ንስኀ የማይገባባቸው፣ የማይሰገድባቸው፣ የማይፆምባቸው ጊዜያትን በሚመለከት ባስተላለፍነው ማብራሪያ ላይ በዓለ ሃምሳ መፆም መስገድ ክልክል ስለሆነ፥ ዋናው የንስኀ ህይወት ደግሞ መጾምና መስገድ ስለሆነ ስለዚህ በበዓለ ሃምሳ ማንኛውም ክርስቲያን የንስኀ ቀኖና አይሰጠውም። በዓለ ሃምሳ ወይም ዘመነ ትንሳኤ የቀኑ ብዛት 50 ስለሆነ በዚህ ጊዜ ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ለእኛ የትንሳኤያችን በኩር ሆኖ የተነሳበትን የትንሳኤውን ነገር እያሰብን ደስ እያለን ለእኛም ዳግም ትንሳኤያችን ተስፋ በማድረግ የምንቆይበት ልዩ የሆነ የበአል አከባበር ስለሆነ በዚያን ጊዜ ልንፆም፣ ልንሰግድ፣ ልናዝን፣ ልንተክዝ እንደማይገባን በቤተክርስቲያን ስርዓት ተደንግጓል።

በመሰረቱ የሰው ልጅ ገና ኀጢያት እሰራለው ብሎ እቅድ መያዝ ወይም በበዓለ ሃምሳ ኀጢአት መስራቴ አይቀርምና መቼ ልናዘዝ እችላለው ብለን ማሰብ ክርስቲያናዊ ተግባር አይደለምና ቢቻል ሰይጣን ፈትኖን ከአቅማችን በላይ ሆኖ የስጋ ፈተና ካልገጠመን በስተቀር መቼም ቢሆን ኀጢአትን መስራት የለብንም። ከሰራንም ደግሞ በተፈቀደልን ጊዜ ራሳችንን ለንስኀ ማዘጋጀት አለብን። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር ማብራሪያ እንዲደርስዎ አድርገናል።

እሁድ የአዲስ ኪዳን ሰንበት ጌታ የተፀነሰባት፣ የተወለደባት፣ የተነሳባት፣ በአለም ሁሉ ድኅነትን ያረጋገጠባት ሰንበት ስለሆነች ሰንበተ ክርስቲያን እየተባለች ትከበራለች። በእለተ ሰንበት እናስቀድሳለን፣ እንቆርባለን፣ እንፀልያለን፣ ምፅዋት እንሰጣለን፣ የታመመ እንጠይቃለን፣ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ስራ እንሰራባታለን ፣ በእስር ቤት ያሉትን እንጎበኛለን፣ የሞቱ እንቀብራለን፣ በአጠቃላይ እነዚህን እና የመሳሰሉትን በጎ ስራ እንሰራባታለን፤ ከዚህ ውጭ ግን ለስጋ ፍላጎት የሚሆን የምናውለውን ስራችንን በእለተ ሰንበት መስራት ክልክል ነው። በስርአተ ገዳም የሚኖሩ መናኞች እንዲሁም ደግሞ ስጋ ደሙን የተቀበሉ ምእመናን እና የካህናት ቤተሰብ የሆኑ ሁሉ ባጠቃላይ የሰንበተ ክርስቲያን ጥቅም የገባቸው ክርስቲያኖች ሰንበትን በልዩ ሁኔታ አክብረው ይውላሉ። ስለዚህ ሰንበተ ክርስቲያንን የሻረ ምእመን እንደጥፋቱ መጠን ለካህን መናገር አለበት።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች ካለባቸው የስራ ፀባይ አንፃር ባለው ችግር ውስጥ ከእነሱ አቅም በላይ በሆነ ጉዳይ በዚህ እለት በአሉን ማክበር ካልቻሉ፤ ከሁሉ በማስቀደም እግዚአብሔር የነሱን የውስጥ ችግር ስለሚያውቀው ወደፊት በእግዚአብሔር ቤት ተገኝተው ተገቢውን ሁሉ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያከናውኑ እግዚአብሔር ይረዳቸው ዘንድ እየፀለዩ አሁን ላይ ግን ከአቅም በላይ የሆነ የስራ ጉዳይ ካጋጠማቸው ችግራቸውን እግዚአብሔር እንደሚረዳ አምነው ስራቸውን እንዲቀጥሉ እንመክራለን።

ጠየቂየችን፤ መፅሐፍ ቅዱስን በትክክለኛውና በእውነተኛው መንገድ ለሚረዱት ሰዎች፥ የተለየ የሚባል ወይም የፕሮቴስታንት ዶግማ ለብቻው የተሰጠ መፅሐፍ ቅዱስ የለም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ዘመናት ለህትመት በዋለ ጊዜ የፕሮቴስታንቱ አለም ከእውነተኛው ሃይማኖት ወይም ዶግማ እየተንሸራተቱ ለራሳቸው በሚያመቻቸው አካሄድ መፅሐፍ ቅዱስን በተራ ቋንቋ አገላለፅ እየተረጎሙና፥ የተቃናውን ትርጉም እያጣመሙ ፥ በተለይ ስለ ክርስቶስ የባህሪይ አምላክነት እና ስለ ቅዱሳን አማላጅነት በመፅሐፍ ቅዱስ የምናገኘውን እውነተኛ ቃል እያዛቡ በመተርጎም ያሳተሙት መፅሐፍ ቅዱስ ብዙ ህጸጽ ስለተገኘበት እና ትርጓሜውም እየተጣመመ የተፃፈ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዚህ ዙሪያ ያላትን ቅሬታ ለመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ስታቀርብ ከቆየች በኋላ ፥ እሷ የምትቀበለው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል 66ቱን ብቻ ሳይሆን 80 አሀዱን እንደሆነ፣ በተለይ ደግሞ በውስጡ አዲስ ኪዳን በነጠላ አገላለፅ እየተጣመሙ ተተርጉሞ የታተመውን ከትክክለኛ የአገላለፅ አገባቡ ትርጓሜውን ከነሚስጥሩ በማስተካከል በእራስዋ ሊቃውንት የተዘጋጀውና  በመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ቀርቦ ተቀባይነት ስላገኘ ታትሞ ስራ ላይ ስለዋለና ለኦርቶዶክስ ማህበረ ካህናትም ሆነ ምእመናን እንዲደርሳቸው ስለተሰራጨ በአሁኑ ሰዓት የፕሮቴስታንት መፅሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚታመንበትና ብዙ የቃላት ስህተት ያለበትን መፅሐፍ ቅዱስ ከመጠቀም ይልቅ ቤተክርስቲያን በራስዋ አዘጋጅታ ያሳተመችውን መፅሐፍ ቅዱስ የእኛ የራሳችን ብለን መገልገል እንድንችል ስለተደረገ ጠያቂያችንም ሃሳቡን በዚህ መሰረት እንዲረዱት ይህን  አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። ምናልባት በዚህ ግልፅ ያልሆነልዎት ወይም የተቸገሩበት ጉዳይ ካለ በውስጥ መስመር ይግለጹልን ተጨማሪ ማብራሪያ እንሰጥዎታለን።

ጠያቂያችን በ40ና በ80 ቀን የተሰየመልንን የክርስትና ስማችን ከጠፋብን ቤተሰብም፣ ንስሐ አባትም፣ ክርስትና አባት ወይም እናትም ካላወቁልን ትልቅ የሃይማኖት ድክመት ነው። ምክንያቱም ይህ፤ ስማችንን ስንጠየቅ ስሜን አላውቀውም እንደማለት ቢቆጠርም ነገር ግን አሁንመስ ቢሆን ያለክርስትና ስም መኖር የለብንምና ወደ ቤተክርስቲያን ቀርበን ካህን በማነጋገር የተወለድንበትን ቀን ወይም ክርስትና የተነሳንበትን ቀን ከታወቀ በዚያው መነሻነት ተገቢውን ፀሎት አድርገው ሊሰይሙን ይችላሉ።  

ስለዚህ ጠያቂያችን የክርስትና ስም መሰየም ብዙ አስቸጋሪና ውስብስብ ስላልሆነ ወደ አባቶች ብቻ ቀርቦ የክርስትና ስምዎትን እንደማያውቁት ቢነግሯቸው በዚህ መሰረት ሊሰይምልዎት ይችላሉ።   

በአጠቃላይ የክርስትና ስሜ ጠፍቶብኛል ብሎ መጠየቅ በመንፈሳዊ ህይወት የተለመደ ገጠመኝ እየሆነ መምጣቱን ብናፍርበትም፤ በአለማዊ ስም ማህበረሰቡ የሚጠራውን ስሜ ጠፍቶብኛል ብሎ ቢናገር በማንኛውም የሰው አስተሳሰብ ያልተለመደ አጋጣሚ ስለሆነ እጅግ  ያስገርማል እና እንደዚሁ ሁሉ የክርስትና ስማችንን በዚህ አንፃር ብናየውና ሁላችንም ስማችንን ብናውቀው መልካም ነው በማለት እንመክራለን ። ምክንያቱም የክርስትና ስም ለማንኛውም ክርስቲያን መለያ ምልክት ነውና።

ጠያቂያቸሰን፤ ለሁሉም ነገር ተጨማሪ ምክርና ትምህርት ከድረገፃችን ላይ እንዲመለከቱ እንዲሁም በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን እንደሚችሉ እንገልፃለን። 

ጠያቂያችን ፤ ለፀሎት የምንገለገልባቸውን መፅሐፍት እና ቅዱሳት ስዕላትና ሌሎችን መንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ማንኛውንም ነገር በቤታችን ውስጥ የተለየ ቦታ አዘጋጅተን ማስቀመጥ ክርስቲያናዊ ስርአት ነው። እንጂ ስላገባን የሚከለከል ወይም ስላላገባን የሚፈቀድ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ባጠቃላይ ቅዱሳን ስእሎችን በምንበላበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንተኛበት ቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ እንደ ጌጥ ማንጠልጠል በልማድ የመጣ እንጂ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ ስርአት አይደለም።

ስለሆነም፤ የቦታ ችግር ከሌለብን ጠዋትም ማታም ራሳችንን ለይተን የዘወትር ፀሎታችንን የምናደርስበት የተለየ ቦታ ቢኖረን መልካም ነው። በቂ ስፍራ ከሌለን ደግሞ በዛችው በምንኖርባት ጎጇችን ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ለይተን በማስቀመጥ ከመኝታችን ተነስተን ተጣጥበን በዚያ መጸለይና መስገድ ይቻላል። ንፁኅ ባህሪይ ዘላለማዊ አምላክ በሆነው አምላክ ፊት ስንቀርብ ታላቅ አክብሮትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ወይም ንፅህናንናና ቅድስና ያስፈልገናል። ስእላቶቹ በቤተመቅደስ ውስጥ ከታቦታቱ ጋር አክብረን ስርአተ አምልኮት የምንፈፅምባቸው ስለሆኑ ብንችልና ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አባት አስባርከን በንፅህና ሆነን እንድንፀልይባቸው እንመክራለን።

በአጠቃላይ በቤታችን ውስጥ፦ መኝታ ቤት ፣ እቃ ቤት፣ ሳሎን ወይም መመገቢያ ስፍራ እያልን ከፋፍለን ተገቢውን እቃ በተገቢው ስፍራ እንደምናስቀምጥ ሁሉ ለፀሎት ወይም ለቅዱሳን ስዕላትና ሌሎች ለመንፈሳዊ ለአገልግሎት የሚውሉትን ራሱን የቻለ ቦታ ለይተን ብናስቀምጣቸው  መልካም ነው። ምክንያቱም መኝታ ክፍላችንም ይሁን ሳሎን፥ በገቢር ባንፈጽመው በሐልዮና በነቢብ የምንፈጽመው ኀጢአት ስለሚኖር ከዚህ አንጻር መሆኑን ጠያቂያችን እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።