ስለ ቤተክርስቲያን ስርዓት ቁ.2

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ቤተክርስቲያን ስርዓት ቁ.2 

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

 ጠያቂያችን፤  በቤተክርስቲያን አስተምሮ መሰረት ማንኛውም ክርስቲያን ነፍሱ ከስጋው በተለየችበት ቀን በዛኑ እለት በ24 ሰዓት ውስጥ ቀብሩ መፈፀም አለበት። ሌሊትም ቢሞት ጠዋትም ቢሞት ወደ ሁለተኛ ቀን መሸጋገር የለበትም። ይህንንም ስለሙታን ስርዓተ ቀብር የሚናገር የቤተክርስቲያን መፅሐፍ ይነግረናል።
በዋናነት መታወቅ ያለበትን ዛሬ ላይ በዓለም ፍልስፍና አንድን እሬሳ ለረጅም ጊዜ በህክምና በሚሰጥ መድሃኒት ምክንያት ለረጅም ጊዜ የማቆየቱ ልማድ ከቤተክርስቲያን ውጪ ነው። ልክ በፍሪጅ ውስጥ እንደሚቆይ ስጋ ማለት ይቻላል። እንደ ህጋችንና እንደ ቤተክርስቲያን ስርዓት አንድ ሰው በምድር ላይ በህይወተ ስጋ የሚቆይባትን የእድሜውን ክልል ጨርሶ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነፍሱ ከስጋው ከተለየች ስጋ ከምድር በላይ የሚቆይበትን የእድሜ ወሰኑን ስለጨረሰው ወዲያውኑ በመቃብር ነው ማረፍ ያለበት ። 
ስለዚህ በዚህ ዘመን በአለማዊያን ብቻ ሳይሆን በእኛም በመንፈሳዊያን ሰዎች ዘንድ ይህ መጥፎ ልማች እየበረታ ስለመጣ ሁላችንም የዚህ ጥፋት ተባባሪ እየሆንን መምጣታችን የማይካድ ሃቅ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን በአጭሩ አንድ የሞተ ሰው ስርዓተ ቀብሩ መፈፀም ያለበት በሞተበት እለት ወይም በሞተ በ 24 ሰዓት ውስጥ መሆኑን እንገልፃለን።
 
ራሱን በራሱ ላጠፋ ክርስቲያን ስርዓተ ፀሎት ወይም ፀሎተ ፍትሃት ሊደረግለት እንደማይገባ በቤተክርስቲያን ቀኖና ተደንግጓል።
ጠያቂያችን ማንኛውም ለንግድ ስራ የቀረበ እንኳንስ በቤተርስቲያን ቀኖና ያልተፈቀደውን የወይራ ዘይት ቀርቶ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ፀሎት የከበረውን ቅባ ቅዱስ እንኳን ሳናምንበት እና ሳይገባን ለፈለግነው አገልግሎት ብናውል ከጥቅም ይልቅ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ጠያቂያችን ለንግድ ስራ ወይም ቢዝነስ ተኮር በሆነ የገበያ አቅርቦት ያገኘነውን ማንኛውም ቅባ ቅዱስ መሰል ፈሳሽ ገዝተን መጠቀም አንችልም። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምሮ ቅባቅዱስ ወይም ሜሮን የምንለው የተቀደሰ ቅባት በልዩ ምስጢራዊ ረቂቅ ስርአት በጸሎት ከብሮ አገልግሎት ላይ የሚውል ልዩ ቅዱስ ቅባት ስለሆነ ሃይማኖት የሌላቸውና መናፍቃን በድፍረት እንደሚያስቡት አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በራስዋ የሃይማኖት አባቶች ፀሎት እና ቡራኬ የከበረውን እና የተባረከውን ቅባ ቅዱስ ያውም ደግሞ ለምን አገልግሎት መዋል እንዳለበት ምስጢራዊ ትርጓሜውን ከአባቶቻችን በጥንቃቄ በመረዳት መጠቀም አለብን እንጂ ከሜዳ ላይ ተነስተን ለስጋዊ አካላችን መገለጫ ይሆናል ብለን የምናስበውን በንግዱ ስርአት ከገበያ ላይ የገዛነውን ዘይት እንደ ቅባቅዱስ መቁጠር እንደሌለብን እንመክራለን።
 
ቅብዓ ቅዱስ ጥቅሙ በሚስጥረ ቀንዲል እንደተፃፈው የታመሙ ሰወችን ወይም ልዩ ልዩ መንፈስ እርኩስ ያለባቸው ሰወች ሲጠመቁ የሚቀቡት ካህናት አባቶች ለመንፈስ ልጆቻቸው በፀሎት እና በቡራኬ አክብረው ከጦረ አጋንንት እንዲጠበቁ የሚሰጧቸው ካህናትም ሆኑ ምእመናን በየቤታቸው ዘወትር በግል ፀሎት እንደመዝገበ ፀሎት አድርገው የሚገለገሉበት መንፈሳዊ ሃብት  ነው።
 
የቅብዓ ቅዱስ አገልግሎትና ጥቅም ለታመመ ሰው ብቻ ሳይሆን ፤ የአጋንንት ውግያ ለመቋቋምና በእለታዊ ጉዟችን ፈተና እንዳያመጡብን፣ ቀኑም ሌሊቱም የሰላም ግዜ እንዲሆን፣ ውስጣዊ ልቦናችን እንዲበረታና ከፍተኛ እንዲሆን፣ በሰው ዘንድ ፍቅርና ሰላም እንዲያመጣልን፣ እንዲሁም በረቂቅ ሚስጥራዊ አላማ የሚዋጉንን እርኩሳን መናፍስት ከእኛ ህይወት ለመለየት ቅብዓ ቅዱስ ከላይ እንደገለጽነው በእውነተኛ አባቶች ተፀልዮበት ተባርኮና አክብረውት ከፀበል ጋር ዘወትር እንድንጠቀምበት ከሰጡን በቤታችን ወይም በፀሎት ቦታችን በክብር አስቀምጠን  ልንገለገልበት ስለምንችልና፤ ለመንፈሳዊ ህይወታችን የጠቀምባቸውን እንደ እምነትና እንደ መስቀል የምንገለገልበት መሳሪያችን መሆኑን ስለሆነ ጠያቂያችን ሃሳብን በዚህ እንዲረዱት ይህ መልዕክት እንዲደርስዎ ልከንልዎታል።
ጠየቂያችን ከዚህ በፊት በንስኀ ስለሚመለሱ እና ስለማይመለሱ ፀጋዎች መልዕክት ማስተላለፋችንን እናስታውሳለን።
 
1ኛ/ አንድ ሰው የክህነት ፀጋውን የሚያሳጣ ፈተና ወይም መሰናክል ቢያጋጥመው በሰራው ጥፋት ተፀጽቶ ንስኀ ቢገባ መንግስተ ሰማያትን መውረስ ይችላል እንጂ ወደ ክህነት ስራው ተመልሶ ስርዓተ ክህነትን መፈፀም አይችልም። ይህም ማለት፦ቀድሶ ማቁረብ አይችልም፣ መናዘዝ፣ መባረክ ፣ የንስኀ አባት መሆን፣ ማጥመቅ የመሳሰሉትን በክህነት ስልጣን የሚፈፀሙትን አገልግሎቶች ሁሉ ማድረግ አይችልም ማለት ነው።
 
2ኛ / የስርዓተ ተክሊልን መፈፀም የማይቻላቸው ከጋብቻ በፊት የድንግልና ህይወታቸውን ያጡ ክርስቲያኖች ሲሆኑ፤ ንስኀ ገብተው በስርዓተ ቁርባን መወሰን የሚችሉ ሲሆን በኀይማኖታቸው እና በክርስቲያናዊ ስነምግባራቸው በሚፈፅሙት የክርስትና አግልግሎት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ እንጂ በድንግልና ህይወት ውስጥ እንደሚኖሩ አማኞች ስርዓተ ተክሊልን መፈፀም ግን አይችሉም ማለት ነው።
 
አንድ ካህን በጳጳስ ወይም በሊቀጳጳስ አንብሮተ ዕድ የተሾመበትን የክህነት ፀጋ የሚያሳጣ ወይም የሚያሽር የኀጢአት ጥፋት ቢሰራ እንደማንኛውም ክርስቲያን ወደአገኘው አባት ቀርቦ የፈፀመውን ጥፋት በግልፅ ባስረዳ ጊዜ የፈፀመው ኀጢአትም ክህነትን የሚያሽር መሆኑን እና አለመሆኑን በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት ወደ ሊቃውንት ጉባኤ ቀርቦ በሚወሰነው መሰረት የሚፈፀም ይሆናል። ምክንያቱም፥ በፍትሐነገስት (በሐዋርያት ቀኖና) ከክህነት የሚያገሉ ምክንያቶች በግልጽ ተደንግገው ስለሚገኙ በዚያው መሰረት የሚፈጸም መሆኑን ያውቁ ዘንድ ጠያቂያችን ይሄንን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 
ስለ ጽዋ ማህበር ለጠየቁን አባላችን  በመጀመሪያ የጽዋ ማህበር ወይም የማህበር ጽዋ ሃይማኖታዊ ቀኖናው እና ስርዓቱ በቤተክርስቲያን አስተምሮ ምን አይነት ትውፊት እንዳለው ለሁሉም ክርስቲያን ማስተማር ያስፈልጋል። ምክንያቱም መናፍቃን ‘ጽዋ ማህበር’ ጥቅም እንደማይሰጥና ልማዳዊ እንደሆነ ሲያጥላሉ ይሰማል። ስለ ጽዋ ማህበር ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሚል በደንብ ካላወቅንና ትምህርት ከሌለን እኛም ነገ በተራ አሉባልታ ተመተን እንወድቃለንና ነው።
 
ስለዚህ ‘ጽዋ’ እና ‘ማህበር’ የሚሉትን ቃላቶች ምስጢራዊ ትርጓሜ ማወቅ ያስፈልጋል።
1ኛ/ ማህበር ማለት ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ማህበርን ሊያመለክት ስለሚችል: እኛ የምናወራው መንፈሳዊ ማህበርን ስለሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጸንተው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ማህበርን፦
1.1   በባለቤቱ ማለትም በሥላሴ፣ በአማኑኤል ፣ በእግዚአብሔር ወልድ፣ በእግዚአብሔር አብ፣ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ተሰባስበው  በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ወይም ደግሞ ለዚሁ በተመረጠ ቦታ ላይ ማህበረ ካህናት እና ምእመናን በማህበር  የሚጠጡት ጽዋ ነው። 
1.2 በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማሪያም፣ በቅዱሳን ፃድቃነ እና ሰማዕታት፣ በቅዱሳን መላእክት ስም ካህናትና ምእመናን የሚጠጡት ማህበር ነው።
 
ይህ አይነት ስርዓት ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በስርዓተ ኦሪት ውስጥ እብራዊያን ወይም የእስራኤል ማህበር እንደነበረ ቅዱስ ማፅሐፍ ይነግረናል። እነሱ በያሉበት ቦታ ሆነው በማህበር እግዚአብሔርን ያስባሉ በተለይ በአመት 3 ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው የሚያስፈልገውን መባ እያቀረቡ በእግዚአብሔር ስም የተባረከውን እየበሉ እየጠጡ እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።
 
በአዲስ ኪዳን ደግሞ የክርስቶስ ሐዋሪያት ማህበር፣ የእስጢፋኖስ ማህበር፣ የአባቶች ማህበር እስከ ዘመናችንና ከእኛም በኋላ ማህበረ ካህናት እና ምዕመናን በቤተከርስቲያን እና በክርስቲያኖች ቤት ሁሉ በጽዋ ማህበር ስም እየተሰባሰቡ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፣  ወንጌል ይማራሉ፣ ቅዳሴ ያስቀድሳሉ፣ፀሎት ያደርጋሉ፣ ይዘምራሉ በአጠቃላይ በማህበሩ ስም በተሰበሰቡ ቁጥር በሃይማኖታቸው ይፀናሉ አብዝተው የትሩፋት ስራ ይሰራሉ ማለት ነው።
 
‘ማህበር’ ማለት ከ 1 ቁጥር በላይ ካህናተ ወይም ምእመናን በእግዚአብሔር ስም ተሰባስበው በእግዚአብሔር ስም ያዘጋጁትን ፀበል ፀዲቅን ወደ ካህናት አባቶች አቅርበው እንዲፀለይበት በመስቀል ተባርኮ እንዲከብር ካደረጉ በኋላ የሚፈፀም ስርዓት ነው።
 
‘ጽዋ’ ማለት ለሁሉ በተራ ወይም በዙር ተመለስ የሚደርስ ነው። ምክንያቱም ጽዋ በሞት ይመሰላል ሞት ለሁሉ እንደማይቀር ጽዋም ለሁሉም ማህበርተኞች በተራ እና በዙር ይደርሳቸዋል ማለት ነው። የሐዋሪያው ቅዱስ ያዕቆብ እና የቅዱስ ዮሐንስ እናት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ልጆችዋ በግራ እና በቀኝ ሆነው የሱ ባለሟሎች እንዲሆኑለት በጠየቀችው ጊዜ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ይጠጣሉ ወይ ብሏት ነበር። (ማቲ 20፥20) ጌታ የሚጠጣውን ጽዋ በመስቀል ላይ በእለተ አርብ የሚቀበለውን መከራ እና የሚጠጣውን የሞት ጽዋ የሚያመለክት ነው።
እንዲሁም ጌታችን መድኃኒተችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ መጽሐፍ “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም  የሚቀበል  የላከኝን ይቀበላል ነቢይን  በነቢይ ስም የሚቀበል  የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥  ጻድቅንም  በጻድቅ ስም  የሚቀበል የጻድቁን  ዋጋ  ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ  ለአንዱ  ቀዝቃዛ ጽዋ  ውኃ ብቻ  በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው  አይጠፋበትም።” (ማቴ 10፥40) በማለት በእግዚአብሔር ስም ክርስቲያኖች በማህበር ተሰባስበው ቀዝቃዛ ውሀ እንኳን ቢያቀርቡ ፣ ለጠማው ቢያጠጡ ዋጋ እንዳላቸው በቃሉ አስተምሮናል። 
 
በእርግጥ በዚህ ዘመን እውነተኛውን ስርዓት በመሳት በየከተማውና በየመንደሩ የሚታየው አንዳንዱ በጽዋ ማህበር ስም የሚታየው ከእውነተኛ ቤተክርስቲያን ስርዓት የራቀ ነገር ይታያል። ይህም ችግር የመጣው ስለ ፅዋ ማህበር መንፈሳዊ ጥቅም ትምህርት በደንብ ካለመማርና ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ ስለሌለን ሊሆን ስለሚችል ወደፊት በሰፊው ትምህርት የምናስተላልፍላችሁ ይሆናል። 
 
ሰአልናክ ስላሉት ከቅዳሴ በኋላ ምዕመናን ምግብ ሳይበሉ ካህናቱም ቅዳሴ ጨርሰው ከቤተመቅደስ ወጥተው ፅዋ ማህበሩ በተዘጋጀበት ቦታ ቁመው ሰአልናክ የሚበለውን እና ሌላውንም የማህበር ፀሎት ከፀለዩ በኋላ  የጽዋ ማህበርተኞች ከሚቀጥለው ምግብ በፊት የሚቀምሱት ስርዓት ስለሆነ ማንም ሰው ከምግብ በፊት እና ከሌላም የኀጢአት አይነት ቅድስናውን እና ንፅህናውን ጠብቆ የሚፈፀም ነው።
 
ለጽዋ ማህበር ምን ያስፈልገዋል ለሚለው ከላይ እንደገለፅነው በእግዚአብሔር እና በቅዱሳን ስም በፍፁም ተዋህዶ ሃይማኖት ፀንቶና በክርስቲያናዊ ሥነምግባር ተወስኖ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ካለን ነገር ለዚሁ የተቀደሰ አላማ በፅዋ ማህበር ስም የሚዘጋጀውን ምግብ እና መጠጥ እና የምናቀርብበት እቃም ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ በማድረግ በጥንቃቄ ብንፈፅመው የበለጠ ዋጋ የሰጠናል ከሌለንም ደግሞ እንደ ኀጢአት አይቆጠርብንም ማለት ነው።
 
ተጨማሪ ማብራሪያ ፦ፅዋ ማህበርን የመሰረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅዱስ ማቴዎስ እንደሆነ የቤተክርስቲያናችን አስተምሮ ተገልፇል በዋልድባ ማህበረ ጻድቃን የሚባል ቦታ ላይ ነው። ማህበረ ፃድቃን ዋልድባ ውስጥ ይገኛል፤ 3000 ማህበርተኞች በበዓሉ ስም ተሰባስበው በዓለ እግዚአብሔርን በ29 ጽዋ ማህበር ይጠጡ ነበረ። ጽዋ ማህበሩን እራሱ ወንጌላዊ ማቴዎስ በኢትዮጵያ ምድር መጥቶ ወንጌልን ሲያስተምር ማህበር አቋቁሟል፥ ጽዋ እንዲጠጡ አዘዛቸው። እነዛ 3000 ፃድቃን በየወሩ በ29 በ29 በጌታችን ስም ፅዋ ይጠጡ ነበር። እንግዲህ ጽዋ ማህበር የተመሰረተው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ጌታችንም ተገኝቶ የባረከው ነው ይላሉ አበው አባቶቻችን እንዳስተማሩን። በነዳያን አምሳል እራሱ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ማቴዎስ የመሰረተው ማህበር ላይ ተሳትፎም ነበር፥ ያ ማህበረ ፃድቃን የሚባለው ጌታችን እራሱ ጽዋ የጠጣበት ነው። ጽዋይቱም እስከዛሬ ድረስ አለች። መቼም የኔቢጤ ደሃ ጥንትም ዛሬም የተናቀ ነበርና ቦታ አይሰጡትም እና ከ3000 ፃድቃን አንዱ ለእኔ ደግሞ ተራ ስጡኝ አለ ፥ፅዋ ሁሉም አወጥቶ እሱ አላወጣም ነበርና ብቻዬን ተቀምጬ ለምን እጠጣለሁ እባካችሁን ሲል ላውጣ አላቸው። አንተ ደሃ ነህ ዝም ብለህ ጠጣ አንተ ማውጣት አትችልም፥ እንዴት ትችላለህ አሉት፥ ደሀ መስሏቸው ነበርና ። ሙሴውም ናቀውና ፈቃደኛ አልነበረም ፥በስንት ልመና ተሰጠውና ማህበር ሊያወጣ ተዘጋጀ። ጠላ የሚጠምቅበትን ውሀ ሊቀዳ ሲሄድ አንድ እረኛ ያገኝና እረኛውን እባክህ ውሃ ቅዳልኝ አለውና እሺ ሲለው እቃውን ሰጠው።   ጌታችን በነዳያን አምሳል የተገለፀ ነዳይ መስሎ በትሩን ሲወረውር በትሩ ያረፈበት ቦታ ላይ ውሀ ሲፈልቅ በል ከዚያ አምጣልኝ አለው። ያን ቀድቶ አምጥቶለት በጋን አደረገና ያንን በጋን የሞላውን ውሀ በተዓምር የጣፈጠ ወይን አደረገው፥ ያን ጽዋ ማህበር አውጥቷል ማለት ነው። ጌታም በናንተ መሃል ሙሴ በድሎኛልና አፋርዱኝ አላቸው 3000 ፃድቃንን። ሙሴም ለናንተ አንድ ፅዋ ስሰጥ ለሱ ሁለት ፅዋ እሰጥ ነበር ምን ብላችሁ ታፋርዱኛላችሁ እንዴትስ አላግባብ ይከሰኛል ፥ ዋሽቶ ነው አላቸው። ጌታችንም የጠጣሁባት ጽዋ መጥታ ትመስክር አላቸው፤ መጥታ ከምድር 3 ክንድ  ከፍ ብላ ያቺ ጽዋ አምላኬ ጌታዬስ በእኔ ጠጥቶ አያውቅም ብላ መሰከረች ፤ ያቺ ጽዋ እስከዛሬ አለች ይላሉ አባቶቻችን።
 
ስለዚህ ጽዋ በጌታችን በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ስም ወይም በበዓለ እግዚ ቢጀመርም ከላይ እንደገለፅነው በእመቤታችንም፣ በፃድቃንም፣ በመላእክም ስምም ሊሆን ይችላል። ሁሌም በስሙ ስንሰባሰብ የተዘጋጀው ወይን ወይም ጠላ ሁሉ እግዚአብሔር ያልተለየው ነው። አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገድል ላይ ልጅዋ የሞተባት የቅዱስ ገብረመንፈስ ቅዱስን ማህበር ታወጣ ነበርና ፥ ልጇን በጋኑ ውስጥ በጠላው ውስጥ ስትከተው አፈፍ ብሎ እንደተነሳ ተዓምሩ ላይ ተገልፆ እናገኘዋለን። ቃሉም በቅዱሳን ስም መታሰቢያዬ ለዘላለም ይኖራል ስለሚል በእነሱ ስም ስንሰባሰብ በነሱ ስም የተዘጋጀውን ወይን፣ ጠላ፣ ቁርስ ስንቀምስ እነሱ ደስ ይላቸዋል፥ በዚያ ቦታ ላይ ሁነን ደግሞ የነሱን ገድል የነሱን ተዓምር ሊነገር ይገባልና ያው ሙሴ ከዚህ አንፃር የመጣ ነው የፅዋ ማህበርም በአገራችን በተለያየ ቦታ ይደረጋል ማለት ነው። ጽዋ ማህበር በጣም አስፈላጊ ነው፥ በስሙ ተሰባስበን የጌታችንን ነገር፣ የእመቤታችንን ነገር፣ የጻድቃንን ነገር እየተነጋገርን ጸሎት አድርገን በመካከላችን ካህን ተገኝቶ ጽዋው ቢጠጣ ፀጋ እንጎናፀፍበታለን፣ እግዚአብሔር ምስጢሩን ጥበቡን ይገልፅልናል ብዙ በረከትም እናገኛለን። ይሄ በገዳማትም እየተደረገ ነው፤ አሁንም ደግሞ አንዳንድ ቦታ ላይ የሃይማኖት አባቶች ያልተለዯቸው ምእመናን ዘንድ ይሄ ስርዓት እንዲቀጥል እያደረጉ ነው። ስለዚህ አሁንም መቀጠል አለበት፥ በዘመናዊነት ያልተሞላበት በቢራ ወይ ሌላ ሳይሆን፥ ከተገኘ ጠላ ካልተገኘም ውሀም ቢሆን አብረው ተገናኝተው ፀሎት አድርገው ካለይ የተጠቀሰውን አገልግሎት ባህላችንን እና ሃይማኖታችንን የጠበቀ የክርስቲያን ትህትና ደግነት የሞላበት ስርዓት ብንፈፅመው መልካም ነው።

ጠያቂያችን በኋለኛው አለም እግዚአብሔር እንደ ህጉና እንደ ስርዓቱ ለኖሩት ለወዳጆቹ የሚያወርሳቸው ሰማያዊ መንግስቱን ለመውረስ ይችሉ ዘነድ በዚህ በሚያልፈው ዓለም እና በሚያልፈው ሥጋችን የእግዚአብሔርን ህግ እና ትዕዛዝ ጠብቀው መኖር ይገባናል እንጂ ሰዎች ነፍስ ይማር በማለት ስለተናገሩ ብቻ ያንድን ሰው ነፍስ ለመንግስተ ሰማይ ማብቃት አይቻልም። በእርግጥ ነፍስ ይማር የሚለው ቃል የበተክርስቲያናችን አስተምሮ የቤተክርስቲያን አባቶች ስለዚያ ስለሞተው ሰው በህይወትም ሳለ ይሁን በሞተ ጊዜ እና ከሞተም በኋላ በስሙ በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርቡት የማማለድ ፀሎት የሞተውን ሰው ነፍስ እንደሚያስምራት ወይም የእግዚአብሔርን መንግስት እንድትወርስ እንደሚያበቃት እናምናለን። የዚህ አይነት ስርዓተ ፀሎት ረቂቅ የሆነ አፈፃፀም ያለው ሃይማኖታዊ ቀኖና ነው። ነገር ግን ጠያቂያችን፤ የሞተው ሰው ላይ ለቅሶ ለመድረስ የመጣው ሁሉ ወይም ደግሞ የዚያን ሰው ሞት የሰማ ማንኛውም መንገደኛ ነፍስ ይማር በማለቱ የሞተውን ሰው ማፅደቅ እንደማይቻል ማወቅ አለብን። ይህንንም በሚመለከት መፅሐፍ ቅዱሳዊ መልስ ያለው ትምህርት ወደፊት በዚህ ርዕስ ትምህርት ልናስተላልፍ ስለምንችል ለጊዜው ግን ጠያቂያችን ላቀረቡት ጥያቄ ሃሳቡን በዚህ ይረዱት ዘንድ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል

በቤተከርስቲያን ትርጓሜ ወይም በመፅሐፍ፥ ፅጌ የእመቤታችን እና የጌታችን የመድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሲሆን በሌላ መስጢራዊ አተረጓጎም ደግሞ የደስታ እና የመልካም ነገር ሁሉ መገለጫ ነው። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሰማያዊ አምላክ ምስጋና እና ዝማሬ ስናቀርብ አበባ ይዘን ብናመሰግን ክብራችንን ያበዛዋል ፣ ለእግዚአብሔር አምልኮትም ያለንን መንፈሳዊ ቅናት ያመለክታል። እመቤተችን በስደትዋ የደረሰባትን መከራ በማሰብ አባቶች በቤተክርስቲያን ማህሌተ ፅጌ ሲቆሙ ፅጌ በጣም በመንፈሳዊ ብቃት ከእስዋ ጋር ለሚገናኙ ሰዎች በሚስጥር እየተገለፀችላቸው ድካማቸውን ላባቸውን ወይም የፊታቸውን ወዝ በፀበልዋ እየጠረገች እረፍት እንደምትሰጣቸውና ዘመኑም የአበባ እና የፅጌ ዘመን ስለሆነ በእጃቸው አበባ እየያዙ ለሷ ያላቸውን ፍቅር ስለገለፁ ከዚህ ጋር የተያያዘ ምስጢር ስላለው ነው። ሁል ጊዜ በጎውን ነገር የበጎ ነገር መገለጫ ስለሆነ ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር  እና መታዘዝ ብናደርገው ከሌላ ከምንም ነገር ጋር የሚያያዝ አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን ስለ ፅጌ ብዙ ምስጢር ቢኖረውም እርስዎ ለጠየቁን ጥያቄ ግን ይህ አጭር መልክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
 

ጠያቂያችን፤ እንዳሉትም የአንድ ቀን ቁጥር የሚጀምረው ከዋዜማው ወይም ከማታው 12 ሰአት ጀምሮ እስከ የቀኑ 12 ሰዓት በድምሩ 24 ሰዓት 1 ቀን ይባላል። ይሄም ማለት ለምሳሌ  የቅዳሜን 24 ሰአት የምንጀምረው ከአርብ የቀኑ 12 ሰአት በኋላ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ የቀኑ 12 ሰአት ድረስ  ነው። ይሄ 1 ቀን ይባላል።  ስለዚህ ለምሳሌ የእሁድን በዓል ማክበር የምንጀምረው ከቅዳሜ 12 ሰዓት ጀምሮ ይሆናል ማለት ነው። 

ስለዚህ ከዋዜማ ጀምሮ ስለመፆም እኛው ራሳችን ክርስቲያኖችም ሳንቀር  ቢያንስ ከ12 ሰአት በኋላ በሚቀጥለው ፆም ለመዘጋጀት መብላት የለብንም ነገር ግን አንዳንድ ስርዓቶችን ወይም የእግዚአብሔርን ሕግጋት እየሸራረፍንም በድፍረት በሰራናቸው ቁጥርም ደጋግመን ባደረግናቸው ጊዜ በሕግ እንደተፈቀደ የምናደርጋቸው ጥፋቶች በጣም ብዙ ናቸው እንጂ በአል ለማክበርም ሆነ ለመፆም ከዋዜማው ጀምሮ ማክበር ስለሚጀመር ማለትም አንድ ቀን ሆነ የምንለው ከቀኑ በፊት ያለው ለሊት ተቆጥሮ ስለሆነ ፤ አርብ ለመፆም ከሐሙስ ቢያንስ 12 ሰዓት ጀምሮ መብላትና መጠጣት እናቆማለን ማለት አንደሆነ ሃሳቡን በዚህ የአቆጣጠር ሂደት ይረዱት  ዘንድ ይህን መልእክት ልከንልዎታል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ተጠይቆ የተላለፈውን ማብራሪያ ልከንሎታልና አንብበው ሃሳቡን ይረዱት።

የተጠየቀው ጥያቄ፦ ስለዚህ አርብ ማታ 12 በኋላ ማረድም መብላትም ይቻላል?

የሰጠነው መልስ ፦ አርብ የ 24 ሰአት ወይም የ 1 ቀን አፈጣጠር የሚጀምረው ከሌሊቱ ክፍለ ግዜ ጀምሮ እንደሆነ በኦሪቱ ህግ የተፃፈ ስርአት ነው። አይሁድ በስርዓታቸው ቅዳሚት ሰንበትን ለማክበር ከእለተ አርብ ከሰርክ ወይም አርብ ከ 11 ሰዓት ጀምሮ ከተቀመጡበት አይነሱም ከዘረጉ አያጥፉም የፈሰሰ አያቃኑም መንገድ አይሄዱም በአመጋገብ በኩልም ከተፈቀደው ስርአት ውስጥ አያልፉም። ምክንያቱም የቅዳሜው በአል አከባበር የሚጀምረው ከዋዜማው ጀምሮ ስለሆነ ነው። ይህ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በተለይ ሙሴ በፃፋቸው 5ቱ ብሄረ ኦሪት መፅሐፍት ተደንግጎ በተለያየ ቦታ   ይገኛል። ጠያቂያችን እንዳሉት የሰው ልጅ ሲፈጠር በቀን እና በሌሊት መስራት የሚገባውን ነገር ተለይቶ ተሰጥቶታል። በቀን ለስጋውና ለነፍሱ የሚጠቅሙትን ተግባራት ሲያከናውን ይውላል። ሌሊቱን ደግሞ ወደማረፍያው ቦታ ተሰብስቦ እረፍተ ስጋ ያደርጋል። በሌሊቱ ክፍለ ግዜ ሰው ሊበሉ የሚችሉ አራዊትና አጋንንት ይሰለጥናሉ፤ ጊዜውም ጨለማ ስለሆነ እነሱም ስራቸው የጨለማ ስለሆነ ነው። ስለዚህ በብርሃን እና በቀን የሰው ልጅ ይሰራል ለስጋው የሚያስፈልገውንም ምግብ ይመገባል። ከዚህ ውጭ ሌሊት የእረፍት ጊዜ ስለሆነ የመብላት ግዜም የመጠጣት ግዜም ለሆድ የሚያስፈልግ ነገር የምናዘጋጅበት ግዜም አይደለም። በአለማችን ኅጢአት የተስፋፋበትን ዋና ምክንያት ስንመለከት የሰው ልጆች የተሰጣቸውን የብርሃን ግዜ ከመጠቀም አልፈው በጨለማ የማይገባቸውን ስራ ሲፈፅሙ መታየታቸው ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ሰአት አለማችን የምታስተናግደው ከባድ የሚባለውን የኅጢአት ስራ በጨለማ ወይም በሌሊት የሚፈፀመውን ናይት ክለብ፣ የጭፈራ ቤት፣ በተለያየ ምክንያት የስርቆት ስራ የሚፈፅሙ፣ የሰውን ህይወት የሚያጠፉ እነዚህን የሚመስሉ ሁሉ በጨለማ የሚፈፀሙ ስለሆነ በብርሃን ለኛ ለሰው ልጅ የተፈቀደውን መፈፀም ብቻ ጠቃሚያችን ስለሆነ ቅዳሜ ለምንበላው ነገር አርብ እናርዳለን ወይም እንበላለን የሚለው ሊያስጨንቀን እንደማይችል በዚህ ማብራሪያ መረዳት ያስፈልጋል። በሌላ መልኩ በቅዱስ መፅሐፍ እንደተፃፈው ሁሉም መብል ለሆድ የተፈቀደ ቢሆንም አይጠቅምም ነገር ግን ለፆም ማድላት ከሁሉ ይጠቅማል በማለት በመልዕክቱ የፆምን ጥቅም አስተምሮናልና ለሚበላ ነገር እንቅልፍ አጥተን ከማሰብ ይልቅ የዘላለማዊ ህይወት ለምናገኝበት ለነፍሳችን ጉዳይ ጥቂት ማሰብ ከሁሉ በላይ ስለሚሻል ጠያቂያችን በዚህ መልኩ ይረዱት ዘንድ ይህን መልእክት ልከንልዎታል።

 
ያቂያችን፤  ለክርስቲያን መስቀል አርማው ስለሆነ፣ የክርስቶስን መከራ የምናስታውስበትና የምናስብበትም ስለሆነ፣ እኛም በክርስትናችን እና በሃይማኖታችን የሚመጣብንን መከራ ለመቀበል የምንችልበት አርማችን ስለሆነ ፣ እንዲሁም ባላመኑት እና ባልተጠመቁትም ፊት የክርስቶስን ፍቅር የምንሰብክበት ጭምር ስለሆነ፥ ለሌላ ስጋዊ ክብር እስካልፈለግነው ድረስ በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ከሆነ የምናንጠለጥለው ወይም የምናስረው፣ ወይም በልብሳችንም ላይ የመስቀል ምልክት  የምናደርገው ብቻ በተለያየ አጋጣሚ ለሰው በሚታይ ወይም በሚገለጽ ቦታ ላይ  ሁሉ መስቀሉን ብናሳይ ወይም ብንይዘው ወይም ብናስረው መንም ነውር የለውም። 
ስለዚህ ጠያቂያችን ማንኛውም ሰው ወይም በሚያምኑ እና ስለ መስቀሉ ክብር በሚያውቁ ሰዎች ዘንድ መስቀል አስሮ መታየቱ ለሃይማኖቱ ካለው ፍቅር ይሆናል እንጂ ሌላ ለምንም ታስቦ እንዳልሆነ እናምናለን እና ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን፤   ከዚህ በፊት ስለ ሰንበት አከባበር ጥያቄ ቀርቦልን ያስተላለፍነውን አጭር መልዕክት  ከዚህ በታች አያይዘን ልከንልዎታልና አንብበው ሃሳቡን በመረዳት እርስዎ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች አጠቃላይ ግንዛቤ ያገኙበታል። ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆኘልዎ ነገር ካለ ደግመው በውስጥ መስመር ያሳውቁንና ተጨማሪ ማብራሪያ  እንሰጥዎታለን።
 
ቀርበው የነበሩት ጥያቄዎች፦
 
ጥያቄ#1 ፦ ስለ ሰንበት መጠየቅ ፈልጌ ነበር ስለ ቅዳሜና እሑድ አከባበር። ሰንበትን መስራት ንስሓ ያስገባል? 
 
ጥያቄ#2 ፦ የመስክ ሠራተኛ ነኝ ሰንበትን በ ትርፍ ሰዓት እንድንሰራ እንገደዳለን ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዴት ይታያል አመሰግናለሁ!
 
ያስተለለፍነው ምላሽ፦
በአጭሩ ቀዳሚት ሰንበት ወይም ቅዳሜ የተባለችው እግዚአብሔር አምላክ በጥንተ ተፈጥሮ ከእሁድ እስከ አርብ የመፍጠር ስራውን ጨርሶ ያረፈባት ቀን ስለሆነች ከዚህ መሰረታዊ ነገር በመነሳት የሰው ልጆች ለፈጣሪያቸው የሚታዘዙባት እና ለመልካም ስራ የሚያውሉባት የተለየች ሁና ኖራለች። በተለይ ነብዩ ሙሴ የቅዳሚት ሰንበት በአል አከባበር ሰፋ ባለ መልኩ በሕግ የተደነገገ ስርዓት አውጥቶ እስራኤልን ሰንበትን አክብሩ በማለት አዟቸዋል። 
 
 ቀዳሚት አምላካችን እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ሁሉንም ስነ ፍጥረት በ6 ቀናት ውስጥ ፈጥሮ ሲጨርስ ከስራው ሁሉ ያረፈባት እለት ስለሆነች ነው። ለዚህም ማስረጃችን በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ “እግዚአብሔር የሰራውን ስራ በ7ኛው ቀን ፈፀመ፤ በ7ኛው ቀን ከሰራው ስራ ሁሉ አረፈ ፤ እግዚአብሔር 7ኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ አርፏልና :: “ስለዚህ በእግዚአብሔር ተባርኮ እና ተቀድሶስ ለሰው ልጅ ሁሉ ስራውን ፈጽሞ ከድካም በስጋ የሚያርፍበት እና ከፈጣሪው ጋር በስርአተ አምልኮት የሚገናኝበት ቀን መሆኑን ያስረዳል :: ( ዘፍ2፥2 እና 3)
 
በቅዱስ ወንጌልም የእንዳትዕዛዝ አረፉ” በማለት ቀዳሚት ሰንበትን አይሁድ እንደ ኦሪት ትዕዛዝ ከስራ አርፈው እንደሚያከብሩ በቅዱስ ሉቃስ ተጽፎል፡ ፡ (ሉቃ 23፥ 50)
 
በአጠቃላይ እለተ ሰንበት አከባበር እና ልዩ የእረፍት እለት እንደሆነች ፣ምንም ምን እንደማይሰራባት በመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን : ስለሆነም በፍትሐ ነገስት ድንጋጌ መሰረት ቀዳሚት ሰንበት (እለተ ቀዳሚት ወይቅ ቅዳሜ) እንዳማይሰገድባት ታዟል :: ይህ ግን በቅዳሜ እለት ማንኛውም ክርስቲያን ወደ ቤተክርስቲያን ሔዶ ለፈጣሪው የአምልኮት ስግደት የሚሰግደውን አይመለከትም ፤ የንስሐ ስግደት ከሆነ ብቻ ነው የሚከለከለው ::
 
ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች መከራ ተቀብሎ 3 ቀን እና 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሞትን እና መቃብርን ድል ነስቶ የተነሳባት ቀን ትንሳኤውን ለአለም ሁሉ ያበሰረባት እንዲሁም የሰው ልጆች ሁሉ ድኅነትን ያረጋገጡባት የአዲስ ኪዳን ሰንበትና ያለፈችው ሰንበት ምትክ እሁድ ናት።
 
ያችኛዋ የብሉይ ኪዳን ቅዳሚት ታስባ ትውላለች ምክንያቱም እግዚአብሔር ከስራው ሁሉ ያረፈባት ስለሆነች በዘመነ ኦሪትም የነበሩ የአዳም ልጆች በጎ ስራ እየሰሩባት አክብረዋት ስለኖረች ይችኛዋ የአዲስ ኪዳን ሰንበት ግን ጌታ የተፀነሰባት፣ የተወለደባት፣ የተነሳባት፣ በአለም ሁሉ ድኅነትን ያረጋገጠባት ሰንበት ስለሆነች ሰንበተ ክርስቲያን እየተባለች ትከበራለች። በእለተ ሰንበት እናስቀድሳለን፣ እንቆርባለን፣ እንፀልያለን፣ ምፅዋት እንሰጣለን፣ የታመመ እንጠይቃለን፣ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ስራ እንሰራባታለን ፣ በእስር ቤት ያሉትን እንጎበኛለን፣ የሞቱ እንቀብራለን፣ በአጠቃላይ እነዚህን እና የመሳሰሉትን በጎ ስራ እንሰራባታለን፤ ከዚህ ውጭ ግን ለስጋ ፍላጎት የሚሆን የምናውለውን ስራችንን በእለተ ሰንበት መስራት ክልክል ነው። በስርአተ ገዳም የሚኖሩ መናኞች እንዲሁም ደግሞ ስጋ ደሙን የተቀበሉ ምእመናን እና የካህናት ቤተሰብ የሆኑ ሁሉ ባጠቃላይ የሰንበተ ክርስቲያን ጥቅም የገባቸው ክርስቲያኖች ሰንበትን በልዩ ሁኔታ አክብረው ይውላሉ። ስለዚህ ሰንበተ ክርስቲያንን የሻረ ምእመን እንደጥፋቱ መጠን ለካህን መናገር አለበት።
 
ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች ካለባቸው የስራ ፀባይ አንፃር ባለው ችግር ውስጥ ከእነሱ አቅም በላይ በሆነ ጉዳይ በዚህ እለት በአሉን ማክበር ካልቻሉ፤ ከሁሉ በማስቀደም እግዚአብሔር የነሱን የውስጥ ችግር ስለሚያውቀው ወደፊት በእግዚአብሔር ቤት ተገኝተው ተገቢውን ሁሉ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያከናውኑ እግዚአብሔር ይረዳቸው ዘንድ እየፀለዩ አሁን ላይ ግን ከአቅም በላይ የሆነ የስራ ጉዳይ ካጋጠማቸው ችግራቸውን እግዚአብሔር እንደሚረዳ አምነው ስራቸውን እንዲቀጥሉ እንመክራለን።
 
በመጨረሻም፤ የሚሰገድባቸውን እና የማይሰገድባቸውን በእለት ወይም በጊዜያት ተለይተው እንዲቀርቡ ከዚህ በታች በዝርዝር ልከናል፦ 
 
የማይሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት፦ 
 
1ኛ/ እለተ ሰንበት (እሁድ) እና ቅዳሜ፣ 
 
2ኛ/  የጌታ አብይት በአላት : – ፅንሰቱ፣ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ሆሳእና ፣ ትንሳኤ፣ በአለ 50 ፣ በአለ እርገት፣ እና ደብረ ታቦር ናቸው።
 
3ኛ/ የእመቤታችን በዓል በ 21 ፣የቅዱስ ሚካኤል በ12 ፣ ባለወልድ በ29 የማይሰገድባቸው በአላት ናቸው። 
 
ነገር ግን ከላይ እንደ ገለፅነው ቤተክርስቲያን ስንሳለም የምንሰግደው ስግደት እና በቅዳሴ ጊዜ እና በሌሎችም የግልና የመሀበር ፀሎት ፣ስለ ስግደት የሚናገረው አንቀፅ ላይ የምንሰግደውን ስግደት የማይጨምር መሆኑን ሁሉም ክርስቲያን ትገነዝቡትና ቋሚ የቤተክርስቲያን ቀኖና መሆኑን ትረዱት ዘንድ እንመክራለን። 
 
የሚሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት ደግሞ ፦ 
 
ልዩ የንስሃ ቀኖና ሲሰጠን፣ በምንፀልይበት ግዜ፣ ስለስግደት በሚነገርበት ቃል ላይ፣ ቅዳሴ በምናስቀድስበት ግዜ ስገዱ ሲባል፣ በሰሞነ ህማማት፣ እናዚህን በሚመሳስሉ በአምልኮት ስርዓት በሚከናወኑ ስግደት እንድንሰግድ በቤተክርስቲን ፍትሓ ነገስት ተደንግጓል። በተጨማሪም ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስንገባ በየትኛውም ቦታ መስቀል ስንሳለም፣ በቅዱሳን ስዕላት ፊት፣ ለቅዱስ ወንጌሉ እንሰግዳለን። 

ጠያቂያችን፤   አንዲት ሴት ፅንስ በማህፀንዋ ካደረበት እለት ጀምሮ 9 ወር ከ5 ቀን የእርግዝና ጊዜ የምታሳልፍበት ወቅት ነው። በዚህ የእርግዝና ወቅት ከእርግዝና  በፊት የምትሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ማከናወን አቅምዋ ስለማይፈቅድና ስለሚደክማት ፣ የተሸከመችውም ሃላፊነት ከባድ ስለሆነ ማንኛውንም መንፈሳዊ ግዴታዋን ከሌላ ጊዜ እየቀነሰች እንደምታሳልፍ ስርአተ ቤተክርስቲያን ይፈቅድላታል። በመሆኑም ስለ ጾም፣ ስለ ስግደት ፣ ስለ ፀሎት እና ቆሞ ስለ ማስቀደስ ፣ ስለ መቁረብ የምታደርገውን መንፈሳዊ ስርአት ታደርግ በነበረው መጠን ብትቀጥል በአካልዋ ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግር ስለሚኖሩ ከዚህ አንፃር በቅርብ በመንፈሳዊ አባትነት የሚጠብቋትን የንስኀ አባት እያማከረች ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱ እየቀለላት እንዲሄድ ይደረጋል።  ምንም እንኳን የተረጋጋ አካላዊ እንቅስቃሴዋ የበረታ ከሆነ እስከተወሰነ የፅንስ ጊዜዋ ፆምን ለተወሰነ ጊዜ እየጾመች ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳ ቁማ መፀለይ፣ ቤተክርስቲያን መሳለም፣ ማስቀደስ ፣ መስቀል መሳለም፣ ፀበል መረጨት በአጠቃላይ እነዚህን መንፈሳዊ አገልግሎቶች እያገኘች መመለስ ትችላለች። የፅንሱ ጊዜ እየገፋ እየደከማት ሲመጣ ግን በቤትዋ ሆና ፆሙን እየቀነሰች መፆም ትችላለች፣  ያትችልበት ደረጃ ከደረሰችም ስለእርሷ መንፈሳዊ አባቷ በፆምም በፀሎትም ስለሚያስቧት እሷ ግን እንድትፆምና ሌሎቹን መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንድትፈፅም እንደማትገደድ ቤተክርስተያን ስርዓት ያዛልና ጠያቂያችን ሃሳቡን ከዚህ አንፃር እንዲመለከቱት የህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

እርግዝና እራሱን የቻለ ልዩ እንክብካቤ እና ክብር የሚያስፈልገው የህይወት መሰረት ነው። ያረገዘች ሴት በተፈጥሮ ፀጋ ያገኘችው የእግዚአብሔር ስጦታ ቢሆንም እግዚአብሔር በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረውን ስነፍጥረት በመሀፀንዋ 9 ወር ከ 5 ቀን ሃላፊነት ወስዳ መሀፀንዋን እንደ አለም አድርጋ በእግዚአብሔር ልዩ ጥበብ ፅንሱ ከእርሰዋ የህይወት እስትንፋስ እያገኘ የመቆየቱ ሂደት ከንስሓ ህይወት የበለጠ ፈጣሪዋን እንድታውቅ የሚያደርጋት ህይወት ስለሆነ ጠያቂያችን እንዳሉት ያረገዘች ሴት ንስሓ በመግባት መስገድም ሆነ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል አትችልም። በፆም ያረገዘች ሴት በቤተክርስቲያን ለፀሎት፣ ለማስቀደስ እና ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ብዙ እንድትቆምም አትገደድም። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጉባኤ እና ከእግዚአብሔር ጸጋ እንዳትለይ ብቻ ድካመ ስጋ እስከሚሰማት ድረስ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ መስቀል መሳለም፣ ፀበል መጠጣት እምነት መቀባት ትችላለች። ጤነኛው ሰው በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ቁሞ መስማት ሲገደድ እስዋ ግን ልክ እንደታመመ ሰው ቁጭ ብላ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት የእርግዝና ቆይታዋን ታሳልፋለች። ያረገዘች ሴት በእርግዝና ግዜ ንስሓ መውሰድ የማትችልበት ምክንያት መስገድን፣ ለረጅም ሰዓት መፆምን፣ ቁሞ መፀለይን የሚጠይቅ መንፈሳዊ አላማ ስለሆነ እነዚህን አይነት ንስሓ እንዲቀበሉ አይደረግም። የታመሙ ሰወችም እንዲሁ። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ አግባብ እንዲረዱት ይህን መልእክት ልከንልዎታል።

 አጠቃላይ በአብይ ፆም ያለውን የፆሙን የሰዓት ገደብ በሚመለከት ለቀረበ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ። ጠያቂያችን፤ ስለሰዓቱ ገደብ ከመናገራችን በፊት ስለሚፆሙት ሰዎች መንፈሳዊ የጽናት ደረጃ ማወቅ ይገባናል። ምክንያቱም ፆሙን የሚፆሙ ሰዎች በ3 ደረጃ ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፦
1ኛ ስርዓተ ፆምን በደንብ ያልተለማመዱና መንፈሳዊ ህይወታቸው በደንብ ያልጠነከረ ምእመናን ፆሙን በደንብ እስከሚለምዱት እስከ 6 ሰአትም እስከ 7 ሰአትም ከጾሙ እጅግ ይደነቃል፥ ወደፊትም አብዝተው ስለሚፆሙ ይህም መልካም ነው።
2ኛ ጾሙን በደንብ የለመዱና መንፈሳዊ ጽናት ያላቸው ክርስቲያኖች እስከ 9 ሰአት እስከ 11 ሰአት ቢፆሙ ዋጋቸው እጅግ እጥፍ ድርብ ይሆናል።
3ኛ የጤና ችግር ያለባቸው እና የተረዳ ልዩ ምክንያት ያላቸው ቢሆኑ ደግሞ እነሱን በፍትሐ ነገስቱ በተወሰነው መሰረት እስከ ስንት ሰአት መጾም እንዳለባቸው ንስኀ አባቶቻቸውን በማማከር የሚፈፀም ነው።
ሌላው ስለ አፇማቱ ሳምንታት በሚመለከት የመጀመሪያው የፆም ሳምንት ዘወረደ ስለሚባል ፥ ዘወረደ ማለት ደግሞ የሚቀጥለውን የፆም ጊዜ ለመፆም ራሳቸውን የሚፈትኑበት ጊዜ ስለሆነ ፤ ፆሙንም ህርቃል የተባለ የእስራኤል ንጉስ ከጠላት ለመዳን የፆመው ፆም እንደሆነ በቤተክርስቲያን ታሪክ ተፅፏል። ይህን የመጀመሪያ ሳምንት ፆም ቀድመን ራሳችንን የምናዘጋጅበት ስለሆነ ቢያንስ እስከ 7 ሰአት መፆም ያስፈልገናል። ሌላው ጌታችን የፆመው 40 ቀኑ እስከ 11 ሰአት እንድንፆም ታዘናል። የህማማቱን ሳምንት ደግሞ የክርስቶስን ህማማት ፣ መከራ የተቀበለበትን ፣ የተሰቀለበትን፣ የሞተበትን የምናስብበት ጊዜ ስለሆነ በበርካታ ክርስቲያን እስከ ምሽቱ 1 ሰአት እንዲፆም የቤተክርስቲያን ቀኖና ይፈቅዳል።
ስለዚህ ጠያቂያችን የጾሙ አፈፃፀም እጅግ ሰፊ እና ጥልቅ ቢሆንም ላቀረቡት ጥያቄ ማብራሪያ ይሆን ዘንድ ይህን ምላሽ ልከንልዎታል። በተጨመሪም ፆምን በዘልማድ ሳይሆን አስፈላጊነቱ እና ጥቅሙ ገብቶን ለመፆም እንችል ዘንድ ከዚህ በፊት ስለፆም በድምፅ ያስተላለፍነውን ትምህርት ክፍል 1 እና 2 አዳምጣችሁ እንድትረዱ በቀጣይም ያሉትን ትምህርቶች እንድትጠባበቁ እንመክራለን።

እጣን ስንገዛ ለቤተክርስቲያን አና ለቤት እንገዛለን  አንዳንዴም ለቤተክርስቲያን በገዛነው ቀንሰን ቤቱን ጓሮውን እኛም እንታጠናለን  አና  እስከዛሬም ቤታችንን ስናጥን ቆይተናል እጣን ለቤታችን ለስራቦታችን ለግቢ ማጠን እንችላለን ወይስ አንችልም ? አንድ አባት ጉባኤ ላይ እጣን ለቤታቹ እንዳታጥኑ እባካቹ  አሉ ስለዚህ አንችልም ማለት ነው ? እስከዛሬ እግዚአብሔርን አስከፍተነዋል ማለት ነው ?

መልስ፦  እጣን በብዙ መንገድ ምስጢራዊ አገልግሎት አለው። እጣንም እንደ ሃይማኖታችን ስርዓት ከተመለከትነው በዚህ ምድር ላይ በሃይማኖት እና በምግባር ስንኖር ለእግዚአብሔር ተገዚነታችንን በመግለፅ ለእውነተኛ ንጹሐ ባህሪይ የሁላችንም ፈጣሪና አምላክ ለሆነ ለልዑለ ባህሪይ ለእግዚአብሔር በአምልኮቱ ቀንተን ስንገዛለት የምናቀርበውን ምስጋና፣ ፀሎት ፣ መስዋዕት፣ መባ፣ በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር ክብር ይገባል ብለን ባለን የልጅነት መንፈስ በእሱ ፊት የምናቀርበውን ሁሉ እግዚአብሔር ወዶ እንደተቀበለልን የምናረጋገጥ የሁሉ ነገር ማሳረጊያና ማጠቃለያ ከሆነው የቤተክርስቲያን ምስጢር አንዱ ፀሎተ እጣን ወይም ደግሞ በእጣን የምናሳርግበት ስርዓት ነው። እግዚአብሔር ያቀረብንለትን አገልግሎት ወይም መስዋዕት ወይም መታዘዝ ወይም መባ ሁሉ ወዶ ተቀብሎታል የምንለው በእጣኑ አማካኝነት የምንፈፅመው ስርዓተ አምልኮት ነው። ቅዱስ መፅሐፍ እንደሚነግረን የፀሎታችንን እና የመስዋዕታችንን አቅርቦት ወደ እግዚአብሔር በእጣኑ አማካኝነት ስናሳርገው እንደተቀበለው ያረጋግጥልናል።

ስለዚህ ጠያቂያችን ከጥያቄዎ ሃሳብ እንደተረዳነው በቤታችን ውስጥ ወይም ደግሞ በግቢያችን አካባቢ እውነተኛ በሆነ የሃይማኖት ስርዓት ከሁሉ ፈተና ለመዳን ከፈለግን እኛ ከገበያ በገንዘብ ገዝተን ያመጣነውን ዕጣን በራንሳችን ስልጣን እና ዝግጅት ማጠን ሳይሆን፥ የቤተክርስቲያን አባቶችን ወይም ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አገልጋዮች ጠርተን እነሱ እጣኑን የሚያከብሩበትን ስርዓተ ጸሎት አድርሰው እንደ ቤተክርስቲያኑ ስርዓት በቤታችን ግቢ ያለውን ማንኛውንም ፈተና ሁሉ ለማራቅ በሚያስችል መንገድ እነሱ ፀሎተ እጣኑን ያሳርጋሉ ወይም ያጥናሉ እንጂ እኛ ራሳችን ገዝተን እንደ አምልኮ ባእድ  በገል የምናጨሰው እጣን ከስርዓተ አምልኮታችን ጋር የሚሄድ ስርዓት ስላልሆነ፤ እስካሁን ድረስ እንደበጎ ነገር በማሰብ የተደረገውን ጥፋት ሳይታወቅ እና ከአባቶቻችን ሳንረዳ ያደረግነው ስለሚሆን ብዙም የሚያጨናንቅ ጥፋት አይደለም። ከዚህ ጥያቄ መልስ በኋላ ግን እኛ በማናውቀው ልዩ ልዩ ምክንያት የሚመጣውን ፈተና ለማራቅ ግቢያችንን እና ወጥተን ወርደን በድካማችን ያፈራነውን ሃብታችንን ህይወታችንን ለማስባረክ ከፈለግን ሁላችንም የሚገባንን ጥንቃቄ አድርገን በአባቶቻችን ፈቃድ ፕሮግራም አድርገን እነሱ ከእጣን ጋር የሚያሳርጉትን ጸሎት ሁሉ በመፀለይ እጣኑን ባርከውና ቀድሰው በእጣኑ ላይም ሊፀለይ የሚገባውን ፀሎተ እጣን አድርሰው እነሱ ስርዓተ ማዕጠንቱን ሊያደርሱ ይገባቸዋል እንጂ እኛ በራሳችን ልናደርገው በቤተክርስቲያናችን ቀኖና አልተፈቀደልንም። እጣኑ በቤተክርስቲያን ስርዓት በካህናት አማካኝነት ሲታጠን የሚታጠነው እጣን ጭሱ መድሃኒተ ስጋ ነፍስ ነው፣ ደዌያችንን ያርቃል፣ እርኩስ መንፈስን ያባርራል፣ መአዛው መንፈስ ቅዱስን የበለጠ እንዲያድር ያደርጋልና በዚህ ስርዓት መፈፀም እንጂ የድርሻንን አለማወቅ በድፍረት ከአባቶች የክህነት ድርሻ ጋር መጋፋት አይገባም።

ስለዚህ ጠያቂያችን እስካሁን ባለማወቅ ባደረጉት ነገር እራስዎትን ማስጨነቅ አይኖርቦትም ነገር ግን ወደፊት በዚህ ምክር አገልግሎት እነዲፈፅሙ ይህን መልዕክት ለእርስዎ እና በአጠቃላይ ለአባላቶቻችን እንዲሁም ይህን መልዕክት የተመለከታችሁ ሁሉ እንዲህ አይነት ገጠመኝ ሲሆን በዚሁ ማብራሪያ እንድትፈፅሙ አደራ እንላለን።

ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር በቸርነቱ አይለየን