ስለ ቤተክርስቲያን ስርዓት

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ቤተክርስቲያን ስርዓት

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

በኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት ማንኛውም ክርስቲያን ከሚያገኘው ሀብቱ ላይ ለሁሉም ነገር በድርሻ ወይም በፐርሰንት መድቦ፦

1ኛ የራሱን ድርሻ ማለትም ለራሱ ኑሮ የተፈቀደለትን ይወስዳል፣

2ኛ ለቤተክርስቲያን ድርሻ (ለቤተ እግዚአብሔር) ፦ ከሚያገኘው ሀብቱ ከአስሩ አንዱን አስራቱን በኩራቱንና ቀዳማይቱን ይሰጣል፣

3ኛ ከሀብታችን ውስጥ ለድሆች ድርሻ ስላላቸው እነርሱንም እንመፀውታለን

ያደረግነው መልካም ነገር ሁሉ ከኛ እጅ የወጣው ገንዘብ ለግዜው የጎዳን ይመስላል እንጂ በመጨረሻው ግን ገንዘብ የማይገዛው ሰማያዊ ርስት ይገዛል። ስለዚህም ጠያቂያችን አሁን ከላይ በሰጠንዎ ማብራሪያ መሰረት የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የቄሳርን ለቄሳር ተብሎ እንደተፃፈ አስራት በኩራቱን ለሚመለከተው ለቤተክርስትያን ድርሻ መድበው በሌላ እጅ እንዳይገባ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲሰጡ፤ ለነዳያንም (ለተቸገረ ሰው) በመራራት የሚችሉትን ነገር ሁሉ በድርሻቸው እንዲያደርጉ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን። 

በእለተ ሰንበት/እሁድ፣ በ21 የእመቤታችን በአል፣ እና በ29 ባለወልድ፦ እነዚህ በአላት የማይሰገድባቸው ቀናት እንደሆኑ በቤተክርስቲያን ቀኖና የተደነገገ ነው። 

 
መልስ፦ በመቼም ግዜ ለመጾም ለአካለመጠን ያልደረሱ ህፃናት ሁሌም መቁረብ ያለባቸው በጠዋት ቅዳሴ ነው። ከ7 ዓመት በላይ ያሉ ህፃናት እንደቤተሰብ አስተዳደግና አያያዝ ሊጾሙ ይችላሉ። ሌላው ደግሞ በእናታቸው ጡት እየጠቡ ታዝለው የሚሄዱ ህፃናት ቅዳሴ ከተገባ በኋላ ጡት ይከለከላሉ- የጠዋትም ይሁን የከሰአት ቅዳሴ።
መልስ፦   ጠያቂያችን ስለ አለባበስ ያቀረቡት ጥያቄ በዘመናችን ስላለው ያልተገባ ስርአት በድፍረት ለመናገር ቢያስቸግርም ነገር ግን እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ አዳምን እና ሄዋንን ሲፈጥራቸው የየራሳቸውን ሀብተ ፀጋ ተጎናጽፈው እንዲኖሩ አምላካዊ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። ወንድ ወይም ሴት ሆኖ መፈጠር ራሱን የቻለ ሀብተ ፀጋ ስለሆነ በአለባበስም ሆነ በማህበራዊ አኗኗር ልዩነት አለው። አባታችን ረዳት እና የኑሮ አጋር እንድትሆነው ከአካሉ የተፈጠረችውን ሄዋንን ከወንድ ስለተገኘች በፆታዋ ሴት እንደሆነች ቅዱስ መፅሐፍ ይናገራል። ስለዚህ ሴት ሁና የተፈጠረች ሁሉ የራስዋን የተፈጥሮ ፀጋ የምትገልጽበት አለባበስ እና ልዩ ልዩ የስነምግባር መገለጫ አላት። ከጥንት ጀምሮ ለወንዶች የተፈቀደ አለባበስ ሴቶች እንዲለብሱት አይፈቀድም፤ ሴቶች የሚለብሱት ያለባበስ ስነምግባርም ለወንዶች አይፈቀድም። በተፈጥሯቸው ያለው የፀጋ ልዩነት በራሱ ማስረጃ ነው። ቀሚስ መልበስ ፣ ነጠላ መልበስ፣ የራስ ፀጉር መሰራት፣ በጆሮ በአንገት በፀጉር ላይ ልዩ ልዩ ጌጣጌጥ ማድረግ የሴቶች መገለጫ ነው። ሱሪ መልበስ፣ ኮት መልበስ፣ ጃኬት መልበስ የመሳሰሉት የወንድ መገለጫወች ወይም አልባሳት በሴቶች ዘንድ እንዲለበሱ ስርአት አይደለም። ስለዚህ ዘመን የሚያመጣው ተጽዕኖ ወንዶቹ የሴቶችን የአለባበስ ስርአት ሴቶቹ ደግሞ የወንዶቹን የአለባበስ ስርአት በመከተል በ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚታየው ስርአት አልበኝነት እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው። የሃይማኖት አባቶችም እንዲህ አይነቱን ያልተገባ ክርስቲያናዊ ስነምግባር መክረውና ገስፀው ከማስጣል ይልቅ ፤ ከግዜ ወደ ግዜ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ ያለውን የዘመኑን የትውልድ ማዕበል እየፈሩና እየተሳቀቁ በጉዳዩ ተግስፅና ምክር ከመስጠት ይልቅ ዝም ማለትን መርጠዋል። ስለዚህ ጠያቂያችን በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ለምትኖር ማንኛዋም ሴት አለባበስዋ ዘመኑ ካመጣው የእብደት አለባበስ ተለይታ ለፆታና ለመንፈሳዊነት የሚስማማ አልባሳት መልበስ እንደሚገባ ምክራችንን እንሰጣለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ሴቶች በአለባበስ ለሰው ሁሉ መሰናክልና ፈተና ከመሆን እንዲጠነቀቁ ሐዋርያዊ ምክር ሰጥቷል።
መልስ፦  በማህበራዊም ሆነ በሌላ የመገናኛ መስመር መፍትሔ ስራይ እያሉ ለግል ጥቅማቸው እና ለቢዝነስ ቢያስተዋውትም ማንኛውንም መፍትሔ ስራይ ቤተክርስቲያናችን አትቀበለውም። ምክንያቱም ቤተክርስቲያናችን ከዚህ የበለጠ በሰው ላይ በነፍስም ሆነ በስጋ ያደረውን ጽኑ ደዌ የመመለስ ሀብትና ፀጋ አላትና ማንም ሰው እንደሚገባው በፍፁም እምነት ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጥቶ ድኅነትን እና ፈውስን ቢጠይቅ እንደፈለገው ሆኖለት በሰላም ይመለሳል። ስለዚህ የቤተክርስቲያን የመፍትሔ ስራይ መድሀኒት ቅዱስ ቁርባንን መቀበል፣ ፀበል መጠጣት፣ ፀበል መጠመቅ፣ በመስቀል መዳሰስ ወይም መባረክ፣ እምነቱን መቀባት፣ መፆም፣ መፀለይ፣ መስገድ፣ መታዘዝ ለንስሓ ህይወት ግዜ መስጠት እነዚህ ሁሉ የሃይማኖት ስነምግባሮች ለበሽታችን መድሀኒት ናቸው። ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉም ሰው እንደ ሞያ መጠኑ ለስጋው መተዳደሪያ የሚያስተዋውቅ የንግድ ስራ እንጂ ከቤተክርስቲያን ቀኖና ጋር የሚያያይዘው አንዳችም ነገር እንደሌለ መረዳት ያስፈልጋል።
 
ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ፦
 
መልስ፦ 40 እና 80 ቀን ላልሞላቸው ህፃናት ጠያቂያችን እንዳሉት ለሞት የሚያበቃ ህማም ቢያጋጥማቸው ለቤተክርስቲያን አባቶች ተነግሮ እንዲጠመቁ የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል። ስለዚህ እንደተባለው እግዚአብሔር ክፉ ነገርን ያርቅልን እንጂ ምንም እንኳን ህፃናቱ ስጋዊ ኀጢአት ያልሰሩ ቢሆንም ክርስትናው ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመግባት አርማ ወይም ልዩ ምልክት ስለሆነ ጥምቀት ማግኘት እንዳለባቸው እናታችን ቅድስት ተዋህዶ ቤተከርስቲያናችን የቀኖና ስርዓት አስቀምጣለች።    
ምናልባት የቤተክርስቲያን መምህራን እና አባቶች በአካባቢያችን ሳይኖሩ ሳያስረዱ ወይም ወላጆችም የዚህን አይነት የጥምቀት ስርአት ሳያውቁ ቀርተው እንደዚህ አይነት ፈተና ቢያጋጥም የተወለዱት ህፃናት የክርስቲያን ልጆች ከሆኑ የወላጆቻቸው ሃይማኖት መለያቸው ስለሆነ ፤ ማለትም የፍየል ልጅ ፍየል የበግ ልጅ በግ እንደማለት ነውና እግዚአብሔርም ከሁሉም በላይ አዋቂና ቸር ይቅር ባይ አምላክ ስለሆነ እንደኀጢአተኞች አይቆጠሩም ማለት ነው።
 
መልስ፦ ጠያቂያችን እንዲገነዘቡት የምንፈልገው በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው 22 ስነፍጥረታት መካከል ብርሀን እና ጨለማ ይገኙበታል። እነሱም የቀን እና የለሊት መገለጫወች ናቸው። ነብዩ ሙሴ እንደነገረን “እግዚአብሔርም፦ብርሃን ይኹን አለ ብርሃንም ኾነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ኾነ አየ እግዚአብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ጨለማውንም ሌሊት አለው።ማታም ኾነ፥ጧትም ኾነ፥አንድ ቀን።” በማለት የአንድ ቀን አቆጣጠር የሌሊቱን 12 ሰአትና የቀኑን 12 ሰአት በመደመር 24 ሰአት አንድ ቀን መሆኑን ፅፎልናል። (ዘፍ 1፥3-5) 
ስለዚህ የአንድ ቀን ቁጥር የሚጀምረው ከማታው 12 ሰአት ጀምሮ ነው። ይሄም ማለት የቅዳሜን 24 ሰአት የምንጀምረው ከአርብ የቀኑ 12 ሰአት በኋላ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ የቀኑ 12 ሰአት ድረስ  ነው። ይሄ 1 ቀን ይባላል ከዚህም ጋር በጌታ ሞትም እንዳየነው 3 መአልት 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ተነሳ ስንል በዚህ አይነት የጊዜ አቆጣጠር ተደምሮ ነው። ስለሆነም የአንድ ቀን የ24 ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ በፊት ያለው ለሊት ተቆጥሮ እንደሆነ ጠያቂያችን ይረዱት ዘንድ ይችን አጭር መልእክት ልከንልዎታል።
መልሱ ፦ አርብ የ 24 ሰአት ወይም የ 1 ቀን አፈጣጠር የሚጀምረው ከሌሊቱ ክፍለ ግዜ ጀምሮ እንደሆነ በኦሪቱ ህግ የተፃፈ ስርአት ነው። አይሁድ በስርዓታቸው ቅዳሚት ሰንበትን ለማክበር ከእለተ አርብ ከሰርክ ወይም አርብ ከ 11 ሰዓት ጀምሮ ከተቀመጡበት አይነሱም ከዘረጉ አያጥፉም የፈሰሰ አያቃኑም መንገድ አይሄዱም በአመጋገብ በኩልም ከተፈቀደው ስርአት ውስጥ አያልፉም። ምክንያቱም የቅዳሜው በአል አከባበር የሚጀምረው ከዋዜማው ጀምሮ ስለሆነ ነው። ይህ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በተለይ ሙሴ በፃፋቸው 5ቱ ብሄረ ኦሪት መፅሐፍት ተደንግጎ በተለያየ ቦታ   ይገኛል። ጠያቂያችን እንዳሉት የሰው ልጅ ሲፈጠር በቀን እና በሌሊት መስራት የሚገባውን ነገር ተለይቶ ተሰጥቶታል። በቀን ለስጋውና ለነፍሱ የሚጠቅሙትን ተግባራት ሲያከናውን ይውላል። ሌሊቱን ደግሞ ወደማረፍያው ቦታ ተሰብስቦ እረፍተ ስጋ ያደርጋል። በሌሊቱ ክፍለ ግዜ ሰው ሊበሉ የሚችሉ አራዊትና አጋንንት ይሰለጥናሉ፤ ጊዜውም ጨለማ ስለሆነ እነሱም ስራቸው የጨለማ ስለሆነ ነው። ስለዚህ በብርሃን እና በቀን የሰው ልጅ ይሰራል ለስጋው የሚያስፈልገውንም ምግብ ይመገባል። ከዚህ ውጭ ሌሊት የእረፍት ጊዜ ስለሆነ የመብላት ግዜም የመጠጣት ግዜም ለሆድ የሚያስፈልግ ነገር የምናዘጋጅበት ግዜም አይደለም። በአለማችን ኅጢአት የተስፋፋበትን ዋና ምክንያት ስንመለከት የሰው ልጆች የተሰጣቸውን የብርሃን ግዜ ከመጠቀም አልፈው በጨለማ የማይገባቸውን ስራ ሲፈፅሙ መታየታቸው ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ሰአት አለማችን የምታስተናግደው ከባድ የሚባለውን የኅጢአት ስራ በጨለማ ወይም በሌሊት የሚፈፀመውን ናይት ክለብ፣ የጭፈራ ቤት፣ በተለያየ ምክንያት የስርቆት ስራ የሚፈፅሙ፣ የሰውን ህይወት የሚያጠፉ እነዚህን የሚመስሉ ሁሉ በጨለማ የሚፈፀሙ ስለሆነ በብርሃን ለኛ ለሰው ልጅ የተፈቀደውን መፈፀም ብቻ ጠቃሚያችን ስለሆነ ቅዳሜ ለምንበላው ነገር አርብ እናርዳለን ወይም እንበላለን የሚለው ሊያስጨንቀን እንደማይችል በዚህ ማብራሪያ መረዳት ያስፈልጋል። በሌላ መልኩ በቅዱስ መፅሐፍ እንደተፃፈው ሁሉም መብል ለሆድ የተፈቀደ ቢሆንም አይጠቅምም ነገር ግን ለፆም ማድላት ከሁሉ ይጠቅማል በማለት በመልዕክቱ የፆምን ጥቅም አስተምሮናልና ለሚበላ ነገር እንቅልፍ አጥተን ከማሰብ ይልቅ የዘላለማዊ ህይወት ለምናገኝበት ለነፍሳችን ጉዳይ ጥቂት ማሰብ ከሁሉ በላይ ስለሚሻል ጠያቂያችን በዚህ መልኩ ይረዱት ዘንድ ይህን መልእክት ልከንልዎታል።
መልስ፦ ከዋዜማ ጀምሮ ስለመፆም እኛው ራሳችን ክርስቲያኖችም ሳንቀር እንዳሉት ቢያንስ ከ12 ሰአት በኋላ በሚቀጥለው ፆም ለመዘጋጀት መብላት የለብንም ነገር ግን አንዳንድ ስርዓቶችን ወይም የእግዚአብሔርን ሕግጋት እየሸራረፍንም በድፍረት በሰራናቸው ቁጥርም ደጋግመን ባደረግናቸው ጊዜ በሕግ እንደተፈቀደ የምናደርጋቸው ጥፋቶች በጣም ብዙ ናቸው እንጂ በአል ለማክበርም ሆነ ለመፆም ከዋዜማው ጀምሮ ማክበር ስለሚጀመር ማለትም አንድ ቀን ሆነ የምንለው ከቀኑ በፊት ያለው ለሊት ተቆጥሮ ስለሆነ ፤ አርብ ለመፆም ከሐሙስ 11 ሰዓት ወይም ቢያንስ 12 ሰዓት ጀምሮ መብላትና መጠጣት እናቆማለን ማለት ነው።
መልስ፦  ጠያቂያችን በመንፈሳዊ ትምህርት እየተማሩ መኖርና እንዲሁም ደግሞ አስረ ክህነት ሳይኖረው መፅሐፍትን እየተረጎሙና እያስተማሩ መኖር የትኛው ይሻላል ለሚለው ፤ ሁሉም ነገር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚፈፀም ቢሆንም ሁለቱም ትልቅ መንፈሳዊ በረከት የሚያሰጡ ስለሆነ  ፤በመጀመሪያ ሰው የእውቀት መሰረት በሆኑ በአብነት መምህራን እና በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዋጋ ከፍሎ እውቀትን በእግዚአብሔር ስም የእለት ጉርሱን እያገኘ ገንዘብ የማይገዛውን እውቀት መሸመት ትልቅ መንፈሳዊ ተጋድሎና ከሁሉ የሚጠቅም ተግባር ነው ። በመቀጠልም የተማሩት ጥልቅ መንፈሳዊ እውነት በመዝራት ሌሎችን ወገኖችን በማስተማር ከሰማያዊ ሞት እና ከጨለማ ህይወት ማዳን ሌላው ከበረከት የሚያሰገኝ ተጋድሎ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያ  ሰው ራሱን ለመካድም ሆነ ወደዚህ አላማ ለመግባት በስጋዊ ስሜትና ፍላጎት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅና በአላማው ያለፉ አባቶችን ማማከር ያስፈልጋል። ስለጉዳዩም በግል ከፈጣሪ ጋር በፀሎት ወይም በልዩ ሱባዔ ማነጋገር ያስፈልጋል እንዲህ ከሆነ እግዚአብሔር የሚጠቅመንን እና የሚጎዳንን ነገር  አሱ ስለሚያውቅ ሁሉ ነገር  በሱ ፈቃድ ይወሰናል ማለት ነው። ከዚህ ውጭ የሚያማክሩን ሃሳብ ካለ በውስጥ መስመር ሊያናገኙን ይችላሉ።
መልስ፦ ጠያቂያችን በማስተዋል እንዲመለከቱት የምንፈልገው የሞተ ሰው የመቃብር ቦታ ተዘጋጅቶለት እሬሳው በዛ በልዩ ቦታ እንዲያርፍ የመደረጉ ስርዓት በቅዱስ መፅሐፍት የተደገፈ ነው። ከህገ ልቦና ዘመን ጀምሮ የታወቁ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች በሞቱ ግዜ ስጋቸው የሚያርፍበት የቀብር ቦታ ተለይቶላቸው በክብር እንዲያርፍ የእግዚአብሔር ትእዛዝ እንዳለበት በቅዱስ መፅሐፍ ተመዝግቦ እናገኛለን። በሳጥን የመቅበር ስርአት እንደየአካባቢያችን ሁኔታ በየሀገሩ ባህል የሚተረጎም ነው። ለምሳሌ በእስራኤል የስርአተ ቀብር ልማድ ከሳጥን በተሻለ ሁኔታ ከአለት የተፈለፈለ አዲስ መቃብር እያዘጋጁ የሞቱን ሰወች እንደየክብራቸው መጠን አስክሬናቸውን ይቀብሩ ነበር። ጌታችን እያሱስ ክርስቶስንም በዚሁ ስርአት ማንም ያልተቀበረበትን አዲስ መቃብር ለሱ ክብር ይመጥናል ባሉት አዲስ ስፍራ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ናቸው ገንዘው የቀበሩት። ሌሎችንም ቅዱሳን በተጋድሎ ከሞቱበት ቦታ ላይ አስክሬናቸው ፈልሶ ወደ ተዘጋጀላቸው ስፍራ እንዲቀበሩ የሚደረገው በዚሁ ስርዓት መሰረት ነው። ስለዚህ በሳጥን የመቀበርን ሁኔታ በኢኮኖሚ ካልጎዳን በስተቀር ከፅድቅና ከኩነኔ ጋር አያይዘን አናየውም። ምክንያቱም የሞተው ሰው በሰሌን ወይም በጨርቅ ወይንም በሳጥን ወይንም በሌላ ነገር ጠቅልለን ብንቀብረው ለሱ ምንም አይነት ለውጥ የለውም። ለሱ የሚጠቅመው በህይወተ ስጋ ሳለ የሰራው የፅድቅ ስራ እና በእኛ በኩል የምናቀርብለት መስዋእትና ፀሎት ነው። 
በመቃብር ላይ ሃውልት ስለመስራት የጠያቁንን በሚመለከት፦ ሀውልት የሚለው ቃል ለማንኛውም ነገር መለያ ምልክት ወይም ምስክር ማለት ነው። ቅዱስ አባታችን ያእቆብ በፈጣሪውና በሱ መካከል ለምስክርነት ይሆን ዘንድ ሀውልት እንዳቆመ ቅዱስ መፅሐፍ የመሰክራል። በቤተክርስቲያን ስርአት መሰረት ክርስቲያኖች በህይወተ ስጋ በሞት ምክንያት ሲለዩ አስክሬናቸው የሚያርፍበት ቦታ በትውልድ የታሪክ ምስክር ወይም ደግሞ መለያ እንዲሆን የእግዚአብሔር ቃል የተፃፈበት ልዩ ምልክት ይደረግላቸዋል። ነገር ግን ሀብት ያላቸው አንዳንድ የሟች ቤተሰቦች የእምነበረድ ወይም ደግሞ የጥርብ ድንጋይ ሃውልት በመከመር የሚሰሩት ሀውልት ለሟቹም ሆነ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ነገር የለውም። ይልቁንም ገንዘቡን በዚህ ለማይጠቅም ግንባታ ከማዋል ይልቅ ለነዳያን ወይም ለቤተክርስቲያን ቢያውሉት ለሟች እረፍተ ነፍስ ያሰጣቸዋል። በእርግት አንዳንድ አስተዋይ ሰወች ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር በመመካከር ለሞቱ ሰወች መታሰቢያ እንዲሆን ለሞቱ ሰወች መቃብር ቤት ሰርተው ለንዋየ ቅዱሳት ማረፊያ፣ ለአገልጋዮች ማረፊያ፣ በቤተክርስቲያን ዙሪያ ለወደቁ ነዳያን ማረፊያ ወዘተ ለመሳሰሉት አገልግሎት እንዲውል ከተደረገ ይህም የትሩፋት ስራ ስለተሰራበት የሞቱትን ሰወች በፀሎት እንዲታሰቡ ያደርጋቸዋልና መልካም አርአያ እንደሆነ ጠያቂያችን በዚህ እንዲረዱት ያስፈልጋል። አስፈላጊ ከሆነም ከዚህ ሃሳብ ጋር ተያይዘው የተመዘገቡ የመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ወደፊት እንዲደርስዎ እናደርጋለን።
መልስ ፦ አስራት በኩራትን መስጠት በህገ እግዚአብሔር የተደነገገ ስርዓት ነው። አስራት ከምን ከምን ማዋጣት እንዳለብንም የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። እግዚአብሔር እኛ ምንም ሳይኖረን እንዲሁ በበረከትና በልግስና አብዝቶ ከሰጠን ነገር በልጅነት መንፈስ ለመታዘዝ ያህል አለምና በአለም ሁሉ ያለው የሱ የሆነ አምላክ ከሰጠን ነገር ለመቀበል “አስራት በኩራቴን አትስረቁ፤ ሰው ፈጣሪውን አይሰርም፤ እኔ ያሳጣኋችሁ ነገር ካለ እስኪ ጠይቁኝና ፈትኑኝ” በማለት ሰጥቶ የሚቀበል እግዚአብሔር የአስራት በኩራትን አስተዋፅኦ ያስተማረንና ያዘዘን እሱ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን ያለው አስራት በኩራት አፈፃፀም ስርዓትን የጠበቀ አይደለም። እያንዳንዱ አስራት በኩራት የምናወጣበት ከእያንዳንዱ ገቢያችን በእግዚአብሔር ፊት ተሰፍሮና ተቆጥሮ የእግዚአብሔርን ድርሻ ለእግዚአብሔር፣ የእኛን ድርሻ ደግሞ ለእኛ የምናደርግበት ስርአት ፈፅሞ አይታይም። በቤተክርስተያን አስተዳደር ውስጥም አስራት በኩራት የመቀበሉና የማስተዳደር ሂደቱ ከእውነተኛ አሰራር የራቀ ሆኖ ይታያል። አንዳንዱ ከእምነቱ ፅናት አብዝቶና አትርፎ የሚሰጥ አለ፣ አንዳንዱ ደግሞ መስጠት የሚገባውንም የሚያስቀር አለ፣ አንዳንዱ ደግሞ የመጣውንም ሲሰርቅ የሚታይበት አሰራር አለ። ስለዚህ ጠያቂያችን እንዲረዱት የሚፈለገው በሰው ዘንድ እንዲታወቅ በማድረግ አስራት በኩራቱን መስጠት፣ ወይም በሚሰበሰብበት ህጋዊ የገቢ ደረሰኝ አስራት በኩራትን መስጠት ፣ ወይም ደግሞ የእግዚአብሔር ገንዘብና ሀብት ለማስቀመጥ በተዘጋጀው ሳጥንና ልዩ ልዩ ቦታ ማስገባት ይቻላል። ከእርስዎ የሚጠበቀውን ካደረጉ ከዛ በኋላ ገንዘቡን የሚቆጣጠር እራሱ ባለቤቱ ስለሆነ እርስዎ ከእዳው ነፃ ነዎት። ስለዚህ ይሄን አሰራር ተከትለው የሚገባዎትን እንዲያደርጉ እንመክራለን። በተጨማሪም ከዚህ በፊት “አስራት በኩራቴን ለተቸገረ ሰው ብሰጥስ?” ብለው ለጠየቁን አባላችን ሰጥተን የነበረውን ምላሽ ከዚህ በታች በማንበብ ይረዱት።
 
በኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት ማንኛውም ክርስቲያን ከሚያገኘው ሀብቱ ላይ ለሁሉም ነገር በድርሻ ወይም በፐርሰንት መድቦ፦
 
1ኛ የራሱን ድርሻ ማለትም ለራሱ ኑሮ የተፈቀደለትን ይወስዳል፣
 
2ኛ ለቤተክርስቲያን ድርሻ (ለቤተ እግዚአብሔር) ፦ ከሚያገኘው ሀብቱ ከአስሩ አንዱን አስራቱን በኩራቱንና ቀዳማይቱን ይሰጣል፣
 
3ኛ ከሀብታችን ውስጥ ለድሆች ድርሻ ስላላቸው እነርሱንም እንመፀውታለን
 
ያደረግነው መልካም ነገር ሁሉ ከኛ እጅ የወጣው ገንዘብ ለግዜው የጎዳን ይመስላል እንጂ በመጨረሻው ግን ገንዘብ የማይገዛው ሰማያዊ ርስት ይገዛል። ስለዚህም ጠያቂያችን አሁን ከላይ በሰጠንዎ ማብራሪያ መሰረት የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የቄሳርን ለቄሳር ተብሎ እንደተፃፈ አስራት በኩራቱን ለሚመለከተው ለቤተክርስትያን ድርሻ መድበው በሌላ እጅ እንዳይገባ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲሰጡ፤ ለነዳያንም (ለተቸገረ ሰው) በመራራት የሚችሉትን ነገር ሁሉ በድርሻቸው እንዲያደርጉ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን
መልስ፦ በዚህ ጥያቄ ላይ ከዚህ በፊትም መጠነኛ አጭር መልስ እንዲተላለፍ ያደረግን ሲሆን ፤ ለመረዳት እና ለማወቅ ለሚጠይቁን የቤተክርስቲያን ልጆች መልስ ለመስጠት ፈቃደኞች ስለሆንን የሚሰገድባቸውን እና የማይሰገድባቸውን በእለት ወይም በጊዜያት ተለይተው እንዲቀርቡ አሁንም ከዚህ በታች በዝርዝር ልከናል፦ 
የማይሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት፦ 
1ኛ/ እለተ ሰንበት (እሁድ)፣ 2ኛ/ በ12 በቅዱስ ሚካኤል ፣ 3ኛ/ በ21 የእመቤታችን በአል ፣ 4ኛ/በ29 ባለወልድ፣ 5ኛ/ በዘጠኙ የጌታ አበይት በአላት ለምሳሌ ጥምቀት፣ ልደት…፣ 6ኛ/ ከትንሳኤ እስከ ጴራቅሊጦስ (በአለ ሃምሳ) እነዚህ የማይሰገድባቸው ጊዜያት ናቸው። 
የሚሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት ደግሞ ፦ 
ልዩ የንስሃ ቀኖና ሲሰጠን፣ በምንፀልይበት ግዜ፣ ስለስግደት በሚነገርበት ቃል ላይ፣ ቅዳሴ በምናስቀድስበት ግዜ ስገዱ ሲባል፣ በሰሞነ ህማማት፣ እናዚህን በሚመሳስሉ በአምልኮት ስርዓት በሚከናወኑ ስግደት እንድንሰግድ በቤተክርስቲን ፍትሓ ነገስት ተደንግጓል። በተጨማሪም ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስንገባ በየትኛውም ቦታ መስቀል ስንሳለም፣ በቅዱሳን ስዕላት ፊት፣ ለቅዱስ ወንጌሉ እንሰግዳለን። 
በምንሰግድበትም ጊዜ በጌታ ላይ የደረሰውን የመስቀሉን መከራ የምናስታውስበት ጊዜ ስለሆነ የኛ መከራ ከሱ መከራ ጋር ባይወዳደርም እንኳን ግንባራችንን እና ጉልበታችንን መሬት አስነክተን እንሰግዳለን። በዚህን ግዜ ከሰውነታችን ላብ ሊወጣ ይችላል። በበአላት ግዜ እንዳንሰግድ የተደረገበት ምክንያት ስግደት በራሱ መንፈሳዊ ስራ ስለሆነ እና ነፍስ ፍሬ የምታፈራበት ስራ ስለሆነ ልክ እንደ ስራ ከበአላት ውጭ ግዜ ወስደን መፈፀም ስላለብን ይህን ለማስተማር ነው እንጂ በበአላት ቀን ሳናውቅ ብንሰግድም እንደ ኀጢአት ይቆጠርብናል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችንም እና ሌሎች አባላቶቻችን ይህን መልእክታችንን አንብባችሁ የመንፈስ ፍሬ እንድታፈሩበት ሁላችሁንም አደራ እንላለን።
መልስ፦  በመሰረቱ ጠያቂያችን እና ማንኛውም ክርስቲያን ከሁሉ በፊት መረዳት ያለበት የስጋ ነገሮችን (ለስጋዊ ህይወታችን የሚያስፈልጉንን) የምንሰራባቸውን ቀናት እግዚአብሔር ባርኮና ቀድሶ ሰጥቶናል። እንዲሁም ለመንፈሳዊ ህይወታችን ደግሞ በመፆም፣ በመፀለይ በመስገድ በዓላትን በማክበርና ልዩ ልዩ የቱሩፋት ስራዎችን በመስራት የነፍስ ተግባራትን የምንሰራባቸውን ቀናት ለይቶና ወስኖ ሰጥቶናል።  እግዚአብሔር አምላክ ያከበራቸው ቅዱሳን አባቶቻችንም በየጊዜውና በየዘመኑ ከርስቲያኖች የነፍስ ምግባራትን እና የስጋ ተግባራትን ሊያከናውኑ የሚችሉባቸውን ጊዜያት ለይተውና ወስነው ሰፍረውና ቆጥረው በተለያዩ የቀኖና መፃህፍት አስተምረውናል። ይህንን ለማለት የተፈለገበት ዋናው ምክንያት ጠያቂያችን በሰንበት ውሃ መቅዳት ቡና መቁላት ክልክል ነው ወይ ብለው ለጠያቁን የስጋ ጥቅም ስለሆነ ለስጋችን የምንፈልገውን እንድንሰራ በተፈቀዱት ቀናት ብናደርገው መልካም ነው። በእርግጥ እለታዊ ምግብ ስለሆነ በሰንበት ውሃ ቀዳችሁ ቡና ወቅጣችሁ ጠጣችሁ በሎ እግዚአብሔር አይኮንነንም። የስጋ እና የነፍስ ተግባራት እምንሰራባቸው ቀናት ግን በህገ ቤተክርስቲያን ተለይተው ስለተቀመጡ በዚያው በተፈቀደው ቀን ብናደርገው መልካም ነው ከሚለው አንፃር እንጂ በዚህ በበአል ቀን የእለት ምግባችንን አዘጋጅተን ብንበላ በእግዚአብሔር ዘንድ ሊያስወቅሰን የሚችል አይደለም። 
ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የምናደርገው ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን ሐዋሪያት ጋር ሆኖ በእርሻ መካከል ሲያልፉ ደቀመዛምርቱ እርቧቸው ስለነበር የእለት ምግባቸውን ለማግኘት ከእሸቱ ቀጥፈው በበሉ ግዜ ፈሪሳውያን እና የአይሁድ ማኅበር ጌታን እንዲህ ብለው ጠይቀውታል “ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ።” እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ እርሱ ያደረገውን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደባላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኅጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን፥ ነገር ግን እላችኋለሁ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ምህረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም …. የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና” በማለት መልሶላቸዋል። (ማቴ12፥1-8፣1ኛ ሳሙ1-6፣ ዘሌ24፥5-9)
 
ስለዚህ ጠያቂያችን ቡና በክርስቲያናዊ ስነምግባር ክልክል የሚሆነው  በልዩ አምልኮትና ልማድ ሁነን በሱስ መንፈስ የምናደርገው ከሆነ የአምልኮት ስርዓታችንን ወደማይፈለግ መንገድ ስለሚያመራ ያኔ ቡና ለክርስቲያኖች የተከለከለ ይሆናል። ምክንያቱም የሰይጣናዊ መንፈስ መስዋዕትና የጣኦት (የባዕድ አምልኮት) ሆኖ ስለቀረበ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ለምግበ ስጋ ከምናውላቸው የእለት ምግቦቻችን እና መጠጦቻችን ከቆጠርነው ግን ከምንም ነገር ጋር ሳናያይዝ የተጠቀምነው ስለሚሆን ሆዳችንን ከመሙላት አልፎ ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር የሚያጣላ ምስጢር የለውም። አንዳንድ ባህታውያን አባቶች ቡና አትውቀጡ ቡና አትጠጡ እያሉ ምዕመናንን ክብር እንዲበዛላቸው ያስተምራሉ ይሄንንም ቢሆን እንደ ፅድቅ መንገድ ልናስበው እንችላለን እንጂ እንደ ግዴታ ማየት ግን የለብንም።  
መልስ: የቆረበ ሰው በሰንበት ልብሱ ቢታጠብ ችግር አለው ወይ ላሉት፦  ለዚህም ጥያቄዎ መልስ ከላይ ለጥያቄ ቁጥር 1 የሰጠነዎት ምላሽ እንዳለ ሆኖ ፤ ጠያቂያችን እንዳሉት የበለጠ ክብር ለማግኘት የቆረበን ሰው ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ልብስ ለማጠብ በሰንበት ቀን ባናደርገው ይመረጣል፤ ብናደርገውም ግን እግዚአብሔር የእኛን የውስጥ ችግራችንን ከእኛ በላይ ስለሚያውቀው እንደ ኀጢአት የሚቆጠርብን አይደልም በማለት ይህን አጭር መልእክት ልከንልዎታል።
መልስ፦  ጠያቂያችን የጥቅምት ፆም የሚገባው መቼ ነው? ብለው ያሉት ምናልባት የፅጌ ፆም ለማለት የቀረበ ጥያቄ ከሆነ ወርሓ ፅጌ ወይም የፅጌ ፆም የፈቃድ ፆም ቢሆንም ብዙ ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናን የእመቤታችን ድንግል ማርያም የስደትዋን ወቅት እና የደረሰባትን መከራ በማሰብ ይህንን ግዜ በፆም ያሳልፉታል። አሁን አሁንማ እግዚአብሔር ይመስገንና ከታላላቅ አባቶችና እናቶች ጀምሮ ወጣቶቹም ሳይቀሩ እየፆሙት ይገኛሉ። ስለዚህ በየአመቱ የፅጌ ፆም ወይም ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚጀመረው መስከረም 27 ፤ ፆሙ የሚያልቅበት ደግሞ ህዳር 6 ቀን ወደ ደብረ ቁስቋም የገባችበትን ቀን በምናከብርበት ጊዜ ነው። ስለዚህ ጠያቂችን ጥያቄዎ ይህ ከሆነ ባጭሩ መልሱ ከዚህ በላይ የተገለፀው መሆኑን እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት አድርሰናል።
 

መልስ፦  ጠያቂያችን መገንዘብ ያለብዎት በቀኖና በዕዝል የሚቀደስባቸው እና በግዕዝ የሚቀደስባቸው ተለይተው ተወስነዋል። ስለዚህ በዕዝል የሚቀደስባቸው ግዜያት ከትንሳኤ ጀምሮ እስከ ሰኔ 17 ከዚያም ከመስከረም 26 – ህዳር 6 ከዚያም በገና ፆም ውስጥ ከታህሳስ 7 ጀምሮ እስከ አብይ ፆም መግቢያ ዋዜማ ድረስ እነዚህ በቤተክርስቲያን ውስጥ ዘወትር በዕዝል የሚቀደስባቸው ግዜያት ናቸው። ከዚህ ውጭ ያልጠቀስናቸው ጊዜያት ደግሞ በቤተክርስቲያን ስቡህ ተብሎ ማህሌት ካልተቆመ በስተቀር በግእዝ የሚቀደስባቸው ናቸው። ሚስጢራዊ ትርጓሜውን በሚመለከት ወደፊት ሰፋ አድርገን ልንልክ የምንችል ሲሆን፤ ለጊዜው ግን ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልስ ልከንልዎታል።

መልስ፦  አንዲት ሴት ወልዳ ክርስትና ስታስነሳ የሴቶች ልማድ ከመጣባት ህፃኑን ወይም ህፃንዋን በሌላ ሞግዚት በእለቱ ወደ ቤተክርስቲያን ተወስደው ጥምቀቱ ይፈፀማል። እናቲቱ ግን ከሴቶች ልማድ ስትነፃ ህፃኑን ይዛ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድና እሷም ፀበል ተረጭታ በመስቀል እንድትባረክ ይደረጋል፤ ህፃኑንም ታቆርባለች። በእርግጥ ጠያቂያችን ከሚያውቁት ወይም ከደረሰባቸው ተነስተው ጥያቄ ያቀረቡ እንደሆነ ቢታመንም ብዙ ጊዜ በተለመደው ገጠመኛችን ግን የወለደች ሴት ከ 80 ቀን በፊት ወንድ ልጅም ብትወልድ እስከ 40 ቀን የተለመደው የሴቶች ልማድ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ከመውለድ ጋር ተያይዞ ሴቶች እስከ 40 እና 80 ቀን እራሱን የቻለ ፈሳሽ የማይነፁበት ግዜ በመሆኑ ዘር ለመተካት ምክንያት የሚሆነው የወርሃዊ የሴቶች ልማድ ግን ይመጣል ተብሎ ለማሰብ ቢከብድም አልፎ አልፎ ግን እንደ መንፈሳዊም ሆነ እነደ ሳይንሱ ሊያጋጥም ይችላል ብለን ስለተቀበልነው ጠያቂያችን ያቀረቡት ጥያቄ በዚህ ማብራሪያ መልስ ለመስጠት የተሞከረ ስለሆነ እንዲመለከቱት ልከንልዎታል።

መልስ፦ ከዚህ በፊት እንደገለፅነው  እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው 22 ስነፍጥረታት መካከል ብርሀን እና ጨለማ ይገኙበታል። እነሱም የቀን እና የለሊት መገለጫወች ናቸው። ነብዩ ሙሴ እንደነገረን “እግዚአብሔርም፦ብርሃን ይኹን አለ ብርሃንም ኾነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ኾነ አየ እግዚአብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ጨለማውንም ሌሊት አለው።ማታም ኾነ፥ጧትም ኾነ፥አንድ ቀን።” በማለት የአንድ ቀን አቆጣጠር የሌሊቱን 12 ሰአትና የቀኑን 12 ሰአት በመደመር 24 ሰአት አንድ ቀን መሆኑን ፅፎልናል። (ዘፍ 1፥3-5) 
 
ስለዚህ የአንድ ቀን ቁጥር የሚጀምረው ከማታው 12 ሰአት ጀምሮ ነው።  ስለሆነም የአንድ ቀን የ24 ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ በፊት ያለው ለሊት ተቆጥሮ እንደሆነ ጠያቂያችን ይረዱት ዘንድ ይችን አጭር ማብራርያ ለተጨማሪ ግንዛቤ እንዲረዳዎት እየላክንልዎት፤ ወደ ጥያቄዎ ስንመጣ የተወለደችው ህፃን ሰኞ እለት ከቀኑ በ5 ሰአት እንደሆነ በተገለፀው መሰረት ከተወለደችበት ቀን ጀምሮ ማለትም ሰኞ ተቆጥሮ (የተወለደው ህፃን ወንድ ከሆነ 40 ቀን ሲሞላው፣ ሴት ከሆነች ደግሞ 80 ቀን ሲሞላት) ክርስትና ትነሳለች ማለት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ተረድተው እንዲቆጥሩት ይህን አጭር ምላሽ ልከንልዎታል።

መልስ ፦

“አባትህን ወይም መምህርህን ጠይቅ ይነግሩህማል ” (ዘዳ 32፥7)

የጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ እና ስለ አብይ ፆም ያለውን የጊዜ እርቀት በሚመለከት ከቤተክርስቲያን አስተምሮ አንፃር የተሰጠ መንፈሳዊ ትምህርት።

እጅግ የምናከብራችሁ እና የምንወዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገጽ አባላቶቻችን፤ አንድ አባላችን በጌታችን ጥምቀት እና በፆሙ መካከል ያለውን የጊዜ ልዩነት ለምን እንደሆነ ማወቅ ፈልገው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ለሁላችሁም ጠቃሚ ስለሆነ አንብባችሁ እንድትረዱት ይህን  ትምህርታዊ ምላሽ ሰጥተንበታል፤ 

1ኛ/    እንደሚታወቀው የጌታችን ልደቱ ታህሳስ 29 በዋሻ በእንስሳት በረት እንደተወለደ ፣በቅዱስ መፅሐፍም የሰው ልጆች ሁሉ ደስ ብሎዋቸው የአለም መድኃኒት ክርስቶስ እንደ ድሀ ተቆጥሮ በበረት መወለዱን መስክረዋል :: ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ እረኞች እና የሰማይ መላዕክትም በአንድ ላይ ዘምረዋል፤ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እስከ 30 ዘመን ድረስ (እስከተጠመቀባት እለት) የባህርይ አምላክነቱን እና እሱ ማን እንደሆነ ከእናቱ እና ምስጢሩን ከገለፀላቸው ከጥቂት ሰዎች በስተቀር ማንም ሳያውቀው እራሱን ሰውሮ አምላክ ነኝ ብሎ ዘመናትን ሳይጠቀልል (እድሜውን) ፣ የኦሪት ሕግንም ሳይሽር እና ሳይንቅ ከእናቱ ጋር እና ከዘመዶቹ ጋር እንደ ህፃናት እየታዘዘ በየጥቂቱ አደገ። እንደ አብራዊያን ወንድ ልጆችም ወደ ቤተ መቅደስ በመሄድ ህገ ኦሪትን እየፈፀመ አደገ : በዚህም ምስጢራዊ ጥበቡ ለብዙዎቹ በነብያት አፍ እንደተናገረ አስቀድሞ የሚፈፅማቸው ተአምራት አምላክ ከሆነ በስተቀር ሌላ ፃጽድቅም ቢሆን እንደማይፈፅማቸው እናቱ ድንግል ማርያም እና ከልደቱ ጀምሮ በ30 ዘመን ቆይታው ያደረጋቸውን ሁሉ በቅርብ የተመለከቱ የእግዚአብሔር ሰዎች የምስክርነት ቃል ያስረዳል። መድኃኒታችን ከእስራኤላዊያን ወይም ከአይሁድ ወገን እንደተወለደ ዜናውን የሰሙ ቢሆንም እንኳን፣ እንደተወለደ ምልክቶችን ያዩ ቢሆንም፣ እንደሚወለድም በነብያት እና በቅዱሳት መጽሐፍት የተነገራቸውም ቢሆን እውነቱን ከማየት እና አስቀድሞ ከመረዳት አይነ ህሊናቸው ስለተሰወረ ሳይረዱት ቆይተዋል :: እስከተጠመቀበት ግዜ በዚህ አይነት ጥርጣሬ ቆይተዋል :: በጥምቀተ መለኮት ዮሐንስም ከእሱ መምጣት አስቀድሞ ስለሱ መገለጽና ስለ ባህርይ አምላክነቱ ገልፆ በነገራቸው ግዜ በእምነት እና በጥርጣሬ መካከል እንዳሉ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ዮሐንስ እንደተናገረ    ንስሃ ግቡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ያለውን፤ እሱም በመለኮታዊ ቃሉ አረጋግጦ እራሱ ገልፆላቸዋል።

2ኛ/ የጌታ ጥምቀት ጥር 11 ቀን (ጥር 10 ለ11 አጥቢያ ከሌሊቱ 6 ሰዓት በኋላ) በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቋል :: ጠያቂያችን እንዳሉት ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንጦስ በራሱ ፈቃድ ሄዶ 40 መአልት እና ሌሊት ከቆመበት ሳያርፍ የሚበላ የሚጠጣ ሳይቀምስ ፆሟል ::የፆምን ጠቃሚነት እና ታላቅት ለማስረዳትና የሁለችንም አብነት ለመሆን በፆሙ ግዜ ከፈታኙ የቀረቡለትን ፈተና ሁሉ ድል ነስቶ ዖሙን በሰላም እንዳጠናቀቀ በወንጌል ተመዝግቧል። (ማቴ 4 ከቁጥር 1 ጀምሮ) 

የ40ው ቀን ቁጥርም ከጥር 11 ጀምሮ (ከጥር ውስጥ 20 ቀን እና ከየካቲት ውስጥ 20 ቀን ይሄን ስንደምረው 40 ቀን ይሆናል) የተፈፀመው የካቲት 20 ቀን ሲሆን ፆሙን እንደጨረሰ ወድያውኑ ወደ ቅድስት ከተማ ሄዶ ማስተማር ጀመረ :: ነብዩ ኢሳያስ እንደተናገረ በጨለማ የነበረ ህዝብ ብርሃንን እየ። (ኢሳ 9፥2) 

ፆሙን በጨረስ በ 3ኛ ቀን በቃና ዘገሊላ መንደር ዶኪማስ የተባለ የታወቀ አይሁዳዊ ባዘጋጃው የሰርግ በአል ላይ ተገኝቶ በእናቱ አማላጅነት ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምራት አደረገ :: ይህ የሆነበት ቀን ማክሰኞ የካቲት 23 ቀን ነው :: ጠያቂያችን እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብዎት የቤተክርስቲያን አባቶቻችን ሊቃውንት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባሳዳረባቸው ታላቅ ፀጋ የበአላት አከባበር እና አፆፆም ስርዓት ባወጡ ጊዜ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በአላት ሁሉም ከውሃ ጋር የተገናኘ ምስጢር ስላላቸው እንዲሁም ሁለቱም የጌታ በዓላት ስለሆኑ ጥር 11 እና 12 ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ በተከታታይ እንዲከበሩ ደነገጉ :: በዚህ መሰረት የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 ጀምሮ “በዛን ቀን ቃና ዘገሊላ ሰርግ ተደረገ ጌታ ኢየሱስም ከእናቱ እና ከደቀ መዛምርቱ ጋር ተገኙ ”  በማለት ‘ከ3ኛ ቀን’ የሚለው ቃል ፆሙን የጨረሰበትን ለማመልከት ነው :: ስለዚህ ዛሬም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ይሄንን በአል የምታከብረው በዚሁ ስርዓት ነው። 

3ኛ/  አብይ ፆም በመጋቢት አካባቢ ለምን ሆነ ለተባለው ጌታችን መድኃኒታች እየሱስ ክርስቶስ እንደተጠመቀ ወድያውኑ ወደ ገዳመ ቆረንጦስ ሄዶ የፆመው ፆም ቢሆንም እንኳን፤ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ በቤተክርስቲያን እና በክርስቲያኖች ላይ ብዙ ስደት እና መከራ በመድረሱ የአጽዋማትን አጿጿምና የበአላትን አከባበር እንዴት መከናወን እንዳለባቸው ግራ እየተጋቡ ብዙ ወጣ ወረድ ስላጋጠመ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና አባቶች በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ምክንያት፤ ስርዓት እና ጊዜ ተወስኖላቸው ክርስቲያኖች ግራ እንዳይጋቡ፤አጿማት መቼ ተጀምረው መቼ ማለቅ እንዳለባቸው ወይም ለስንት ቀን መፆም እንዳለባቸው ስለ 7ቱ የአዋጅ አጿማት ስርዓት ሰርተዋል። በዚሁ መሰረት ጥምቀት እና ልደት የሚውለበት ግዜ የደስታ እና የኃሴት ግዜ ስለሆኑና ፆም ስለማይፆምባቸው በሌላ በኩል ዘመነ  መርዐዊ ዘመነ ቅበላም ስለሚባሉ የአብይ ፆም የሚገባበት ግዜ ከየካቲት መጀመሪያ ጀምሮ እንዲሆን በባሕረ ሃሳብ ቀመር ውስነው አስቀምጠዋል:: የፆሙ መጀመሪያ ቀን አንድ ግዜ ወደ የካቲት ዝቅ፣ እንድ ግዜ ደግም ወደ መጋቢት ከፍ የሚልበት ምክንያት የባሕረ ሃሳብ የቀመር እና የተውሳቅ አሰራሩ እንደሆነ ማወቅ ይገባል። ይህንን ሃሳብ በውል ለመረዳት በባሕረ ሃሳብ አመቅቴ መጥቅዕ ተውሳክ እና መባጃ ሐመር የሚባሉትን ቁጥሮች ማወቅ ያስፈልጋል።ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዮሐንስን ንስኀ ድረገፅ አባላቶቻችን በሙሉ በዚህ ማብራሪያ ሃሳቡን እንድትረዱት ይህን አጭር ትምህርታዊ መልዕክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል።

 ጠያቂያችን ፤ በመጀመርያ የጽሉላትን  ትርጉም ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ጽሉላት የሚባለው ትርጉሙ በፍስክ ጊዜ ከምንበላው ምግብ ማለትም ከስጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት የመሳሰሉት ተከልክለን በፆም ጊዜ የምንበላቸውን ምግቦች ብቻ የምንጠቀምበት የአመጋገብ ስርአት ነው። ለምሳሌ በፆም ወራት ቅዳሜና እሁድን ጠዋት ከቅዳሴ በኋላ እንደሌሎቹ ቀናት ፆመን ሳንውል የምንመገበው የፆም ምግብ ወይም ያመጋገብ ስርአት ጽሉላት ይባላል። ስለዚህ ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት በማንኛውም የፆም ጊዜ ጽሉላት አለ።

የገና ፆም ከ 7ቱ የአዋጅ አፃዋማት አንዱ ሲሆን የፆሙ ብዛት 44 ቀናት ነው ። 40ውን ቀን የፆመው ነብዩ ሙሴ ነው። ወልደ እግዚአብሔር መሲ ክርስቶስ የመወለዱን የመውረዱን ምስጢር ትንቢት የተናገረበትንና ሁሉም ነቢያት መሲ ክርስቶስ ይወርዳል ይወለዳል እያሉ ትንቢት የተናገሩበት ቃል አማናዊ ሆኖ መኖሩን በማሰብ ነው። 4ቱ ቀናት ደግሞ ደጉ አብርሐም ሶርያዊ የተባለ አንድ ሰው ባሕር ከፍሎ ተራራ አፍርሶ የሰራውን ድንቅ የሆነ ተአምራዊ ስራ የምናስብበት ነው። ይህንን ነብያት የፆሙትን 40 ቀንና አብርሐም ሶርያዊ የፆመውን ስንደምረው 44 ቀን ይሆናል። 
ፆሙ የሚጀምርበትን ቀን በሚመለከት በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ከህዳር 15 እስከ ታህሳስ 28 ሲሆን፤ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ከህዳር 14 እስከ ታህሳስ 27 ቀን ይፆማል።የጋድ ፆምን በሚመለከት ለጥምቀት እንጂ ለገና  ፆም ወይም ለልደት የገና ፆም የለውም። ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች ስለ 7ቱ አጽዋማት በሚመለከት በቅርብ ቀን እንዲደርሳችሁ የምናደርግ መሆኑን እንገልፃለን።
 ጠያቂያችን አሳ በፆም ይባላል ወይስ አይበላም በሚል ስላቀርቡልን ጥያቄ በቤክርስቲያናችን ቀኖና መሰረት እንደሚከተለው አጭር መልስ ተሰጥቶበታል። 
 
አሳ በመሰረቱ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሰፋ ያለ ታሪክ ያለው የባሕር ውስጥ እንሰሳት ነው። በብሉይ ኪዳን በኦሪቱ ሥርዓት ብዙ እንስሳት እና አእዋፍ ሳይቀሩ ለመስዋዕትነት ሲቀርቡ አሳ ግን አንድ ቀንም ለመስዋዕትነት እንደቀረበ የሚያሳይ ማስረጃ የለም።በድህነት ምክንያት የበሬ ወይም የፍየል መስዋዕት ማቅረብ የማይቻለው የርግብና የድንቢጥ መስዋዕትን የደም መስዋዕት አድርጎ ያቀርብ እንደነበረ ቅዱስ መፅሐፍ ይመሰክራል ::
 
በአዲስ ኪዳንም አሳ ከደም እንስሳት የተለየ እና በጌታ ዘንድ የተመረጠ እንደነበር ተፅፏዋል። ብዙ ከ 5000 ቁጥር በላይ ያላቸው የጌታ ተከታዮች ከና ቤተሰቦቻቸው ጭምር በ2 አሳና በአምስት የገብስ እንጀራ በበረከቱ እጥግቧቸው 12 መሰብ የተረፈው ምግብ እንደተናሳ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እናገኛለን።(ማቴ 14፥17 – 19)
 
ጌታም ከተነሳ በኋላ በጥብርያዶስ ባህር ደቀ መዘምርቱ አሳ በማጥመድ ላይ እንዳሉ ተገልፆላቸው አንዳች የሚበላ የላችሁምን ብሎ በሱ ትዕዛዝ ያጠመዱትን አሳ ወደ እርሱ አቅር በው የተጠበሰውን አሳ ባርኮ ከእሱ ጋር በማዕድ ተቀምጠው እንዲበሉ እንደፈቀደላቸው በቅዱስ ወንጌል አሁንም ተፅፎ እናገኘዋለን :: (ዮሐ 21፥6-13) 
ስለዚህ አሳ ከሌሎቹ የስጋ እና የደም እንስሳት ለየት ባለ መልኩ በጌታ ዘንድ የተወደደና የተፈቀደ የምግብ አይነት መሆኑን በቅዱስ መጽሐፍ ስለ አሳ የተፃፈውን አንብበን መረዳት እንችላለን። ነገር ግን ጠያቂያችን አሳ በፆም ይበላል ወይስ አይበላም? ብለው የጠየቁትን በሚመለከት ለብዙ ዘመናት በእኛ በቤተክርስቲያናችን በጥያቄ ሲያወዛግብና  የቤተክርስቲያን ሊቃውንትንም ሲያከራክር የነበረ ሃሳብ ነው።   አሳ ይበላል የሚሉትንም ሆነ አይበላም የሚሉትን መነሻቸው በፍትሐነገስት በፆም ጊዜ ስጋን አትብሉ  “ኢትብልዑ ሥጋ ዘእንበለ እሳ”፤ ትርጉሙም በአማርኛ   “በፆም ጊዜ ስጋ አትብሉ አሳ ሳይቀር ወይም ያለ እሳ” የሚለው ያማርኛው ትርጉም አሻሚ ስለሆነ መብላት የሚፈልገው ሰው ‘በፆምስጋ አትብሉ ያለ አሳ’ ብለው የሚተረጉሙ አሳ ይበላል ይላሉ። እሳ እንዳይበላ የሚፈልጉ ደግሞ ‘በፆም ጊዜ ስጋ አትብሉ አሳም ሳይቀር’ ብለው በመተርጐም አሳን በፆም ጊዜ ከማይበሉ የደምና የስጋ እንስሳት ይመድቡታል :: ከዚህም በላይ ስንመለከት አሳን ከውሃ አውጥተን ደሙን አፍስሰን ለትንሽ ጊዜ በእቃ ውስጥ ብናቆየው ወደ ውሃነት ይመለሳል። የሌሎቹ የእንስሳ ደም ግን ደምነቱን ሳይለቅ ሲደርቅ እንመለከታለን :: ስለዚህ የሚከራከሩት ሰዎች ይሄንንም ልዩነት በማነፃፀር ነው። የሆነ ሆኖ ግን አሳ ከሌሎቹ እንስሳት፣ ከአትክልት፣ እና ከወተት ተዋፅኦ በላይም በፖሮቲን የበለፀገ አልሚ ምግብነት እንዳለው ሳይንሱም የሚያረጋግጠው ስለሆነ የእኛም የቤተክርስቲያን አባቶች የአሳ ስጋ ከተበላ ሰውነትን የሚገነባና ከሌሎችም የፍስክ ምግብ የሚበልጥ እንደሆነ አባቶቻችን በመንፈሳዊ ሲኖዶስ መክረውበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን በቀኖና ስርአትዋ ትከለክላለች። አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ውሳኔ አሳን በፆም ሲባሉ ቢታይም የቤተክርስቲያን ውሳኔ ጋር የሚታይ አይደለም፤ ምክንያቱም በሃይማኖታችን የምንፈጽመው መንፈሳዊ ግዴታ ከራሳችን እምነት ጋር የተያያዙ ስለሆነ ቤተክርስቲያን ደግሞ ከማስተማርና ከመምከር አልፋ እንደ ስጋዊ ዳኝነት የምታስገድድበት ስርዓት የላትም። ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረ ገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባላቶቻችን ስለ አሳ ፆምነት በዚህ እንድትረዱት ይህን መልዕክት ልከንላችኋል ::
 
ጠያቂያችን ንስኀ የገባ ሰው ስለሚያከናውነው የንስኀ ሕይወት ምን ማድረግ እንዳለበት ንስኀ የሰጡት አባት በሰጡት ምክር የሚከናወን ስርዓት ነው። ምክንያቱም አባቶች የሚሰጡት የቀኖና ንስኀ በአንቀፀ ንስኀ የተደነገገውን መሠረት በማድረግ ሲሆን ይህም እንደ ኀጢአቱ የክብደት መጠን ይለያያል። በተጨማሪም የጤና ወይም ከአቅም በላይ የሆነ የታወቀና የተረዳ ችግር ካለ፤ አባቶች ይህንንም በመረዳትና በማገናዘብ የቀኖና ንስኀን እንዴት ማከናወን እንዳለብን የሚሰጡት ምክርና መመሪያ የአንድ ሰው ከሌላው ሰው እንደ ሁኔታው የሚለያይ ሊሆን ይችላልና ነው። ስለሆነም  አንድ ክርስቲያን ከአንድ ቀን ጀምሮ የሚሰጠው የንስኀ ቀኖና ሲኖር ምን መፀለይ እንዳለበት ፣ እንዴት መፆም እንዳለበት ፣ እንዴት መስገድ እንዳለበት ፣ እነዚህን የሚመሳሰሉትን ስርአት እና ጠያቂያችን ያነሷቸውን ሀሳቦች ሁሉ የሚወሰኑት እንደ ኀጢአቱ ክብደትና ቅለት የንስሃ አባቱ አገናዝበው በሚሰጡት  መመሪያ መሰረት የሚከናወን ነው። እንደ አጠቃላይ ግን የቀኖና ንስኀን በማከናውን ሂደት ውስጥ ችግር የሚያጋጥማችሁ ወገኖች፤ ስለ ሰራችሁት ጥፋት ተፅፅታችሁ ንስኀ እስከከገባችሁበት ድረስ ስለሚያጋጥማችሁ ጥቃቅን ነገሮች መጨነቅ የለባችሁም:: ዋናው ነገር ከልብ መፀፀትና ወደ እግዚአብሔር መመለሱ ስለሆነ ነው። ከዚህም በላይ በተደጋጋሚ ብዙ ጊዜ መመሪያ እንዲሆናችሁ ለተመሳሳይ ጥያቄዎች ምላሽ የፃፍንላችሁ ስለሆነ ደጋግማችሁ እንድትመለከቱት እንመክራለን።
 

አዎ ከቅዳሴ በኋላ ማንኛውም ያስቀደሰ ሰው የቅዳሴ ፀበል መጠጣትም ሆነ ፀበል መጠመቅ ይችላል። የቀደሱት ካህናት እና የቆረቡት ምእመናን ግን ከቅዳሴ በኋላ ፀበል መጠጣት እንጂ መጠመቅ አይችሉም። ስለዚህ ጠያቂያችን ስርዓቱን በዚህ ይረዱት ዘንድ ለጥያቄዎ ይህን አጭር ምላሽ ልከንልዋታል።

ጠያቂያችን ፤ ህፃናት ክርስትና በተነሱ ጊዜ ፀጉራቸው ቢላጭም ባይላጭም ይችላል። በቤተክርስቲያን ቀኖና እንዲላጩ የሚያስገድድ ነገር የለም። ምናልባት በልምድ የሚደረግ ነገር ካለ ብናደርገውም ባናደርገውም እንችላለን ማለት ካልሆነ በስተቀር ስለዚህ ጉዳይ ሌላ የተለየ ስርዓትና ህግ የለም።

ጠያቂያችን ከዚህ በፊት በእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን የተዘጋጀን ምግብ መብላት ከክርስትና ሃይማኖት አንፃር እንደቀኖናችን መሰረት ትክክል የሆነውን ነገር በግልጽ ማስረዳታችንን እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ የሃይማኖቱ ቀኖና የሚከለክለው በተለይ በፍስክ ስለምንመገባቸው የምግብ አይነቶች ማለትም ስለ ስጋ እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በራሳቸው የሃይማኖት ስርዓት ባርከው ስለሚመገቡት የምግብ አይነት ይመለከታል። ምክንያቱም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ወይም በጌታችን በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ስም ባርኮ ያዘጋጃውን ምግብ ሲበላ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ግን የሃይማኖታቸው ስርአት በሚፈቅደው መሰረት ቢስሚላሂ በማለት የአላህን ስም ጠርተው ምግባቸውን ስለሚበሉ በዚህ በሁለቱም መካከል የስርአትና የሃይማኖት ልዩነት ስላለ ልዩነታችን ከዚህ የተነሳ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ሃይማኖታዊ አቋም ሊኖርዎ በችልም ሳይጨናነቁ ተጨማሪ ምክር እንድንሰጥዎ የሰው ልጅ በሥጋ ተዛምዶ ቤተሰብ ሆኖ በሃይማኖት ሊለያይ ስለሚችል በማህበራዊ ኑሮ አብሮ ውሃ መጠጣት ደረቅ እንጀራ መብላት ወይም ቆሎ መብላት ቡና መጠጣት ሰላምታ መስጣጠት እነዚህን የሚመስል ጤናማ ግንኙነት የምናሳልፈው የጋራ ግንኙነት ኀጢአት  ሊሆን አይችልም። ከምንም በላይ በሃይማኖት በማይመስሉን ዘንድ ሊያስመሰግን በሚችል ማህበራዊ ጉዳይ መተባበር የበለጠ በሰው ዘንድ ፍቅር ቢያበዛልን እንጂ የሚያመጣብን ፈተና ስለማይኖር ከዚህ ጋር ተያይዞ ፈተና እንዳሌለ ሊረዱ እና ሊገነዘቡ እንደሚያስፈልግ ይህን መንፈሳዊ ምክር እንዲደርስዎ አድርገናል፡

። አሁንም ደግመን የምንለው ሁሉም ነገር መነሻው ወይም መሰረታዊ ሃሳቡ ትውፊት ነው። ለብሉይ ኪዳን መነሻ በፅሁፍ የተቀመጠ መረጃ ሳይኖር በትውፊት የተነገውን ነገር መዝግቦ እናገኘዋለን። ለምሳሌ፦ 1) አባታችን አዳም የንስኀ ፀፀት መስዋዕት የማቅረብ ስርዓት፣  2) የአቤልና የቃየል የመስዋዕት አይነት አቀራረብ፣ 3)በኖህ ዘመን ስለሆነው የጥፋት ውሀ፣ 4) ፃድቁ ኖህ ለእግዚአብሔር ያቀረበው መስዋዕት አይነት እና ሌሎችም እነዚህን የመሳሰሉ በመፅሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡ ታላላቅ ጉዳዮች በትውፊት ለትውልድ በቅብብሎሽ የወረዱ ናቸው። ብሉይ ኪዳን የተፃፈው እስራኤል ዘስጋ በሙሴ መሪነት ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ የተደረገ ነው። ስለዚህ በመፅሐፍ ሳይመዘገቡ በሰው ህሊና ውስጥ ተፅፈው ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ የመጡ ምስጢራት ሁሉ ትውፊት ይባላሉ። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰራቸውን ስራዎች ሁሉ ሁሉም በአዲስ ኪዳን እንዳልተመዘገቡ እራሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል። በዮሐንስ ወንጌል እንደተፃፈ “እየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ሁሉም በእያንዳንዱ ቢፃፍ ለተፃፉት መፅሐፍት አለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” በማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የባህሪይ አምላክ ስለሆነ የሚናገረው መለኮታዊ ቃልና የሚያደርገው ተዓምራት ከሰው አይምሮ በላይ ስለሆነ ሁሉም ነገር ቢነገርና ቢፃፍ ኖሮ ከቶም ሊወስነው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ይህ ኅይለ ቃል ያመለክታል። 
ስለዚህ ጠያቂያችን ባጭሩ የትውፊትን መሰረታዊ አመጣጥና ስለሚሰጠው ጥቅም በዚህ ሃሳብ እንዲረዱት ይህን መልዕክት ልከንልዎታል።

ጠያቂያችን በኦርቶዶክስ እምነት ደም ለሌላ ሰው መለገስ ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ፤ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ አስተምሮ የፍጡር ደም ለሰው መለገስ እንደሚቻል የተገለፀና የተብራራ ማስረጃ ባይኖርም እንኳን የሰውን ህይወት ለማትረፍ ምክንያት መሆን በጎ ስራ ስለሆነ እንደ ኀጢአት የሚያስቆጥርብን ባለመሆኑ የወገንን ህይወት ለማትረፍ መተባበራችን የተቀደሰ ሃሳብ ነው። በእርግጥ ቅዱስ መጽሐፍ እንዳስተማረን አለም የዳነው በክርስቶስ ደም ብቻ መሆኑን ነው። ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ እኛን ከመውደዱ የተነሳ ቅዱስ ስጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የአለም መድኃኒት መሆኑን አረጋግጦልናል። በዚህ ሰው የሚያድንና ለዘለአለማዊ ህይወት የሚያበቃ የክርስቶስ ደም ብቻ እንደሆነ ለሁላችንም የታወቀና የተረዳ ነው። ነገር ግን ከላይ ለሁላችንም እንደተገለፀው በህክምና ባለሞያዎች በተደረሰበት ጥናት መሰረት የአንድን ሰው ህይወት ለማትረፍ ደም መለገስ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የዛን ህይወት ለማትረፍ በበጎ ፈቃደኝነት ደሙን ቢሰጥ እጅግ ለወገን ያለውን ፍፁም ፍቅር ከመግለፁም በላይ ስራውም ከበጎ ስራ የሚቆጠር ስለሆነ ታላቅ የሆነ ምስጋናንና አድናቆትን ስለሚያተርፍ በሃይማኖት በኩል የሚያስነቅፍ አይደለም። ስለዚህ ጠያቀያችን በየትኛውም የአለም ክፍል በተጨባጭ የህክምና ሞያ በልዩ ልዩ ምክንያት ችግር የደረሰባቸውን ህሙማን ህይወት ለማትረፍ የደም ልገሳ ጉዳይ አለም አቀፍ ትኩረትን ያገኘ ስለሆነ በሃይማኖታችንም በኩል በጎ ለሆነው ተግባር ሁሉ መተባበር  አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚታመን ጠያቂያችንም ሆኑ የዮሐንስ  ንስኀ ድረገፅ አባላቶቻችን የጥያቄውን ፍሬ ሃሳብ በዚህ ባስተላለፍንላችሁ አጭር መልስ ትረዱት ዘንድ ይህን መልዕክት ልከንላችኋል።

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ አባሎቻችን ይህንን ሰፋ ያለ ትምህርታዊ ማብራሪያ ለሁላችሁ እንዲደርስ ያደረግንበት ምክንያት ከዚህ በታች ከአንድ አባል ጥያቄ በቀረበልን ምክንያት ነው።
 
ጥያቄው፦ የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውጪ ቆማ ነው መፀለይ መሳለም የምትችለው ነው መሰለኝ ሃሳቡ ባጠቃላይ ። እዚህ ጋር አንዲት ጥያቄ አለችኝ ጌታችን በሚያስተምርበት ወቅት 12 አመት ደም የሚፈሳት ሴት የልብሱን ዘርፍ ነክታው ነበር። ለምን እንዲህ አደረግሽ? ብሎ አልተናገራትም ይህን እንዴት ትመለከቱታላችሁ? አዎ በእርግጥ ልክ ነው የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ይቅርና ካልሲው የሚሸት ሰው ቤተመቅደስ ውስጥ መግባት አይቻልም ለንጽህና ሲባል ። እና ቅጥር ግቢ ውስጥ ስለምን ተከለከለ በአዲስ ኪዳን እኮ በብሉይ ኪዳን የነበሩ እንደነዚህ አይነት ህጎች ተሽረዋል እና ደሞ ሌላው በዚህ ቻናል ላይ መሰለኝ ከዚህ በፊት ተጠይቆ ወርሃዊ ጉዳይ ላይ መስቀል መሳለም አይቻልም የተባለው እሺ አንገትችን ላይ ያለው መስቀል እሱ የወር አበባ ላይ ስንሆን እናወልቀዋለን? ያነበብኩት በዚ ቻናል ላይ ካለሆነ በጣም ይቅርታ ከሆነ ግን እንዲብራራልኝ በትህትና እጠይቃለሁ።
 
ለጥያቄው የተሰጠ መልስ ፦
 
የወር አበባ በሴቶች ላይ በየወሩ የሚከሰት በተፈጥሮ የተሰጣቸው ፀጋ ሲሆን ይህም የማይቋረጥ የደም መፍሰስ ኡደት ነው። በቤተክርስቲያን ቀኖናዊ አስተምሮ የሴቶች የወር አበባ ‘ደመ ፅጌ’ ወይም ‘የአበባ ደም’ በመባል ይጠራል። ይህም በየወሩ ኡደቱን ጠብቆ እስከተወሰነ የእድሜ ደረጃ ድረስ የሚዘልቅ ነው። በወር አበባ ላይ ያለች ሴት ከደም እስከምትነፃ ድረስ የረከሰች ናት ይባል የነበረበት ዋናው ምክንያት ወይም የሴቶች የወር አበባ (የሴቶች ግዳጅ) የመርገም ደም ነው ይባል የነበረበትን ምክንያት በሁለት ከፍለን እንመለከታለን፦
 
1ኛ / ዘመነ ኦሪት – የሴቶች የወር አበባ የመርገምና የርኩሰት ምልክት ነበር። ነብዩ ሙሴ የሴት ወር አበባ የመርገም ደም ወይም የርኩሰት እንደነበረ በህጉ መፅሀፍ እንዲህ ሲል ገልፆታል “እርሷም በመርገምዋ ርኩሰት ሳለች አፍረተስጋዋን ትገልፅ ዘንድ ወደ ሴት አትቅረብ” (ዘሌ 18፥19 ) እንዲሁም ደግሞ “ማናቸውም ሰው ከባለመርገም ሴት ጋር ቢተኛ አፍረተስጋዋንም ቢገልፅ ፈሳሽዋን ገልፇልና እርስዋም የደምዋን ፈሳሽ ገልፃለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ”(ዘሌ20፥18) በማለት በዚህ የመርገም ደም ስለመሆኑና በዚህ ሰአትም ወደ ሴትዋ የቀረበ ወንድ እርኩስ መሆኑን በሁለቱም ዘንድ  መንፈሳዊ ቅጣት እንደሚያስፈልጋቸው ይገልፃል። ይህ የሴቶች ወርሃዊ አበባ የመርገም ደም የተባለበትም ዋናው ምክንያት እናታችን ሄዋን እንዳይበሉ የተከለከሉትን እፀበለስን ከበለስዋ ዛፍ ላይ ቆርጣ ወይም ቀጥፋ ለመብላት  የእግዚአብሔርን ህግ አፍርሳ በፈፀመችው በደል ምክንያት እግዚአብሔር አምላክዋም ሄዋንን “የዚህችን እፀበለስ ደም እንዳፈሰስሻት ሁሉ አንቺም በየወሩ ደምሽን ስታፈሽ ትኖሪያለሽ” በማለት በየወሩ የሚፈሰው ደምዋ የእርግማን ምልክት እንደሚሆንባት ከፈጣሪዋ ዘንድ የመጣባት መርገም ነው። ከዚያን ዘመን ጀምሮ በክርስቶስ ደም መርገሙ እስከሚሻር ድረስ የመርገም ደም እየተባለ በሴቶች ላይ ሃፍረትን እና ሰቀቀንን ሲያስከትል ኖሯል። (ዘፍ3፥16)
 
2ኛ/ በአዲስ ኪዳን ዘመን የሴቶች የወር አበባ የመርገም ምልክት ሳይሆን ወርሃዊ የተፈጥሮ ግዳጅ (የተፈጥሮ ፀጋ) ይባላል። ምክንያቱም የሰው ልጅ ራሱን የሚመስለውን ዘር ለመተካት በወንድና ሴት መካከል የሚደረገው የሩካቤ ስጋ ግንኙነት ወደ ዘር ማስገኘት ለሁለታቸውም የተሰጣቸው ዘርን የመተካት ፀጋ ነው። ስለዚህ የወር አበባ በምታይበት ጊዜ የሚቆጠርባት እንደ ዘመነ ኦሪቱ ስርአት እንደ እርኩሰት ሳይሆን እንደ እድፍና እንደ ቆሻሻ ነገር ነው። እርኩሰት ነገር ከቆሻሻና ከእድፍ በእጅጉ ይለያል። እርኩሰት ውስጣዊ ማንነታችንን በረቂቅነት ተቆራኝቶ የተቀደሰውን ህይወት የሚያረክስ እና ንፅህናን የሚያጎድል ስለሆነ ማስወገድ የሚቻለውም በንስኅ ህይወት እንጂ በውሀ በመታጠብ የሚጠራ አይደለም። እድፍና ቆሻሻ ግን በግዙፋን ውጫዊ አካል ላይ የሚታይ ለእይታም ሆነ ለሽታ የሚዳርግ ቢሆንም እንኳን በውሀ በመታጠብ የሚፀዳና የሚታጠብ ጊዜያዊ ነገር ነው። በአዲስ ኪዳን የወር አበባም በሴቶች ዘንድ በየወሩ የሚታይ ተፈጥሮወዊ ባህሪ እንጂ እንደ እርግማን ደም ወይም ደግሞ እንደ እርኩስ ነገር አያስቆጥርም። በወር አበባ ላይ ባሉበት ጊዜም የፈሳሽ ጊዜው እስከሚያበቃ እንደ እድፍና እንደ ቆሻሻ ሊቆጠር ይችላል።  ለምሳሌ የማይገባ ልብስ ለብሰን በሰው ፊት ለመቅረብ ወይም በአካላችን የሚታይ ነውር ይዘን ወይም የተለየ ጠረን ካለብን በሰው ፊት ለመቅረብ እንደምንሳቀቅ ሁሉ ከዚህም በላይ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ተብሎ ተፅፏልና ንፁኅ ባህሪይ ዘላለማዊ አምላክ በሆነው አምላክ ፊት ስንቀርብ ታላቅ አክብሮትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ወይም ንፅህናንናና ቅድስና ያስፈልገናል። ስለዚህ እንኳንስ ንፁሃ ባህሪይ የሆነ አምላክን ይቅርና ሰውንም ሊፈትን ስለሚችል አንዲት ሴት የወር አበባዋ እስኪቆም ድረስ ወደ ቤተክርስቲያን የውስጠኛው ክፍል ገብታ እንዳታስቀድስና ቅዱስ ቁርባንን እንዳትቀበል ትከለከላለች። ሆኖም ከመጀመርያው የቤተክርስቲያን ግቢ ቆማ እንድትሳለምና እንድታስቀድስ በቤተክርስቲያን ቀኖና ተደንግጓል። ስለዚህ በወር አበባ ላይ ያለች ሴት ከደም እስከምትነፃ ማግኘት የማትችለው መንፈሳዊ አገልግሎት፦ ቅዱስ ቁርባን አትቀበልም፣ ወደ ፀበል መጠመቂያ ቦታ ሄዳ መጠመቅ አትችልም የተቀደሰበትን ፀበል መጠጣት አትችልም፣ የቀደሰው ካህን ከቅዳሴ በኋላ አስቀዳሾቹን የሚባርካቸውን መባረክ ስርአት አታገኝም ሆኖም ካህናት አባቶች ህዝቡን ሲባርኩና እግዚአብሔር ይፍታ ሲሉ ባለችበት  ቦታ ቆማ ይሁንልኝ ይደረግልኝ በማለት በረከቱን ማግኘት ይቻላል።  ይህም እንደ ኦሪቱ ህግ እንደ እርኩስ ወይም እንደተረገመ አካል በመቁጠር ሳይሆን ንፅህናንና ቅድስናን ወይም ፈሪሃ እግዚአብሔርን ከማሰብ አንፃር ነው። በእርግማን ምክንያት የመጣውን የዘር ኡደት ጥንተ አብሶ በክርስቶስ ሞት ሁላችንንም ከመርገም ኅጢአት ነፃ እንዳወጣን ቤተክርስቲያን ዘወትር ታስተምራለች። ሐዋርያዊ ቅዱስ ጳውሉስም “… ክርስቶስ ስለኛ እርግማን ሆኖ ከህግ እርግማን ዋጀን” በማለት በህግ የተፃፈውን እርግማናችንን በመስቀሉ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈፅሞ እንደሻረው ለገላትያ ሰዎች በፃፈው መልዕክቱ አስተምሮናል። (ገላ 3፥13)
 
ወደ ቤተክርስቲያን እንዳንገባ የምንከለከልባቸው ምክንያቶች የወር አበባ ብቻ ሳይሆን ከጉንፋን ወይም ከሌላ መሰል የጤና መታወክ ፣ ከአፍንጫችን እና ከአፋችን ፈሳሽና ሽታ የሚያስከትል ነገር ሲኖር፣ ወደታች ወይም ወደላይ የሚያሰኝ በሽታ ሲይዘን፣ በአካል ላይ ሽታ ያለው ቁስለት ወይም ደዌ ሲያጋጥም፣ በአይምሮ ደዌ የተያዘ ሰው ልብሱን የሚያስወልቀውና እርቃኑን ሊያስቆመው የሚችል ደዌ ሲደርስበት ባጠቃላይ ባለቤቱንም ሆነ ሌላውን ተመልካች መንፈሳዊ ስነልቦናውን ሊያሰናክል የሚችል ሆኖ ሲታይ ወደ ቤተከርስቲያን ወደ ውስጥ ክፍል እንዳይገቡ ሆኖ በርቀት ቤተክርስቲያን መሳለም የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት ባሉበት ቆመው ማግኘት ይችላሉ።
 
ከወር አበባ ሳትነፃ በድፍረት ወደ ቤተከርስቲያን ገብታ እንድትቆርብ ያደረገ ካህን ቢኖር ከክህነቱ እንዲሻር የቤተክርስቲያን የቀኖና ህግ የሆነው ፍትሐ ነገስት ይደነግጋል። ነገር ግን ጠያቂያችንም ሌላውም አካል መገንዘብ ያለባችሁ በአዲስ ኪዳን ዘመን ማንኛውም ወደ ቤተክርስቲያን እንዳንገባ የምንከለከልበት ጉዳይ ጊዜያዊ ችግራችን ከኛ እስከሚወገድ ለኛም ሆነ ለእግዚአብሔር ጉባኤ ፈተናና መሰናክል እንዳንሆን ታስቦ እንጂ እንደ ብሉይ ኪዳን ኅጢአት ተቆጥሮብን እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን። ለዚህም ነው ፈፅሞ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ሳይከለከሉ በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ክፍል በመጠለያው ክፍል ሆነው እንዲማሩ፣ እንዲፀልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በስርዓት ደንብ የተደነገገው።
 
ጠያቂያችን በጥያቄዎ ያነሱት 1ኛ/ ደም እየፈሰሳት የነበረች ሴት የጌታን የልብሱን ጫፍ ዳሳ ስለመዳንዋ የተገለፀው፤ ሲጀመር ይህች ሴት የወር አበባ ሳይሆን የምታየው ቋሚ የሆነ የማይቋረጥ የደም መፍሰስ በሽታ ነበር። ይህ የበሽታ አይነት በሌሎች ሴቶች ተከስቶ የማያውቅና ሀብቷን ንብረቷን ትዳርዋን በዚህ ምክንያት አጥታለች። ወደ ሃኪምም ፣ እግዚአብሔር በማይወደው መንገድም ወደ ጠንቋይ ቤቶች ስራዬኛ ቤትም ሄዳ ከበሽታዋ ለመዳን ያላደረገችው ነገር የላትም። ነገር ግን ህሙማነ ስጋን በተአምራቱ እየፈወሰ ህሙማነ ነፍስን በቃሉ እያፀና የመጣውን እውነተኛ መድሃኒትና የስጋና የነፍስ ሃኪም የሆነውን መድኅኒአለምን ባገኘችው ጊዜ ድህነቷ የሚረጋገጠው በሱ እንደሆነ ስላመነች በድፍረትም ቢሆን ልብሱን ዳሳ ተፈውሳለች። የዚህች ሴት እምነት ለሌሎቹ ትምሀርት እንዲሆን በወንጌል ተመዝግቦላታል። ምክንያቱም ምንም እንኳን ኅጢአተኛ ብሆን የኔ ኅጢአት የሱን ቅድስና ሊያረክሰው አይችልም በማለት ከሱም በላይ እኔን ሊያድንና እና ከዚህ ደዌ ሊፈውሰኝ የሚችል የለም ብላ አምና በመቅረብዋ ጌታም እምነቷን አድንቆ ለተከታዮቹ መስክሮላታል። ስለዚህ ጠያቂያችን ያቀረቡት የዚህች ሴት ደም መፍሰስ ከወር አበባ ጋር አይገናኝም።
 
2ኛ/ ጠያቂያችን ከአንገት ላይ መስቀል መሳለም አትችልም ወይ ለሚለው ጥያቄ ባለችበት ቦታ ወይም በቤተክርስቲያን ውጭ ቦታ ሁሉ ካህንም ብታገኝ በመስቀል ከመሳለም የሚከለክላት ነገር አይኖርም። ለቅዱስ መስቀሉ ካላት ክብር የተነሳ ለካህኑ ያለችበትን ሁኔታ ልትገልፅ ብትችል እንኳን የእምነትዋን ጥንካሬ ያመለክታል እንጂ መስቀል በመሳለምዋ የመስቀሉን ክብር ሊያጎድፍ አይችልም።
 
3ኛ/ በአንገታችን ላይ ያደረግነውን መስቀል በሚመለከት በ40 እና በ80 ቀን የእግዚአብሔርን ልጅነት ስናገኝ የታተምንበት ምልክት ስለሆነ ጊዜያዊ የተፈጥሮ ጉዳይ ምክንያት የሃይማኖታችን መገለጫ የሆነውን መስቀል እንድንፈታ የሚያደርገን ስርአት ባለመኖሩ ካልተጠመቁ አህዛብ ተለይተን የምንታወቅበት እለት እለት የሚዋጉንን አጋንንት ድል የምንነሳበት ስለሆነ የሴቶች የወር አበባን አስመልክቶ ከታዘዘው የቤተክርስቲያን ቀኖና ጋር አያይዘን መመልከት የለብንም።
 
በአጠቃላይ በዚህ ሃሳቡን እንድትረዱትና ይሄንንም የእግዚአብሔር ድንቅ እና ታላቅ ስራ እንድታደንቁ ይህን አጭር ትምህርታዊ የማብራሪያ ምላሽ እንዲደርሳችሁ አድርገናል።

ጠያቂያችን፤ በወር አበባ ክፍለ ጊዜ ያለች ሴት ከፈሳሽ እስከምትነፃ የትኛው የቤተክርስቲያን ክፍል ቆማ ማስቀደስና መፀለይ እንዳለባት ፣   መንፈሳዊ ፕሮግራሙን እንዴት ማግኘት እንዳለባት ሁሉ በስፋት ስለተገለፀ ደግመው እንዲያነቡት አሁንም አደራ እንላለን። ስላሉት ነገር ተጨማሪ ማድረግ የምንፈልገው የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ መግባትና ቆሞ ማስቀደስ፣ የቀደሰውን የካህን መስቀልን የመሳለም ስርዓት መፈፀም፣ ፀበል ቦታ መጠመቅና በመስቀሉ መዳበስ ወደ ቋሚ ቅዱሳት ስዕላትና መስቀሉ ባለበት ወይም ልዩ ልዩ የፀሎት መፅሐፍት በሚገኝበት ልዩ የፀሎት ቤት ገብቶ መፀለይ እነዚህን የሚመሳስሉ ነገሮች ላይ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አሁንም በድጋሚ እንመክራለን። ሆኖም ግን ባለንበት መኖሪያ ቤታችንም ይሁን ከዋናው የቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውጪም ቢሆን መስቀል አትሳለሙ፣ ቁማችሁ፣ አታስቀድሱ፣ አትፀልዩ፣ ቤተክርስቲያን አትሳለሙ የሚል ህግ የለም።  በመቀጠልም እርስዎ ያነሱትን በሚመለከት በግልዎት የሚፀልዩበትን የፀሎት መፅሐፍ አንስተው መፀለይ አይከለከሉም። አንገታችን ላይ ከጠላት እንዲጠብቀን ያሰርነውን መስቀል ወይም ደግሞ ስዕል ወይም ደግሞ የፀሎት መፅሐፍ ቢኖር ከኛ አንድናርቀው አንገደድም። ዋናው ቁም ነገር በውስጣችን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖር ንፁህ የሆነውን አምላክ በንፅህና በቅድስና እንድናመሰግነው በፍፁም እምነት ሆነን እንድናመሰግነው ለማጠየቅ ስንል የወር አበባ ክፍለ ጊዜ ላይ ያሉ ሴቶችም ሆኑ ሌላ የተለያየ ኅጢአትም ሆነ የሥጋ ነገር የገጠማቸው ሰዎች ከዚያ ነገር እስከሚነፁና እግዚአብሔርን ሳይዳፈሩ በርቀት ሆነው ማመስገን የተለመደ ስርዓት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ከዚህ ቀደም የሰጠናቸውን ትምህርታዊ መልእክቶችንም አሁንም መላልሰው ለማንበብና ለመረዳት እንዲሞክሩ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።

መልስ፦ (ተጨማሪ የማብራሪያ ምላሽ) ውድ ጠያቂያችን፤ ስለመሪጌታና ስለ ቄስ የክህነት አገልግሎት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ምላሽ መስጠታችንን እናስታውሳለን። አሁንም በድጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ሲደርሰን ልዩነቱን እንዳልተረዱት ተመልክተናል። አሁንም በደንብ እንዲያስተውሉ የምንፈልገው፦
 
1ኛ/ መሪጌታ ማለት የዜማ፣ የቅኔ፣ የአቋቋም እውቀት ኖሮት የማህሌት ስርዓቱን የሚያከናውን እና ባለበት በተለይ ጉባኤ ዘርግቶ ተተኪ ትውልድን አስተምሮ በእውቀት የሚያፈራ፤ ይሄም ማለት ዲያቆን፣ ቄስ፣ መሪጌታ መሆን የሚችሉ ደቀመዛሙርትን የምያስተምር ማለት ነው። ይህ ማለት የሞያውን ደረጃ ያመለክታል።
 
2ኛ/ ቄስ ማለት በድቁና ክህነት ተቀብሎ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በስርዓተ ተክሊል ቅዱስ ጋብቻ ከፈፀመ በኋላ የቅስና ክህነት ከጳጳስ ይቀበላል። ከዛ በኋላ ቄስ ሆኖ እየቀደሰ ያቆርባል፣ በመስቀል ይባርካል፣ ፀበል ያጠምቃል እነዚህን የመሳሰሉ አገልግሎት ይፈፅማል።
 
3ኛ/ የቅስና ክህነት ያለው ሆኖ የመሪጌታ ሞያ ሊኖረው ይችላል። ይህም ማለት መሪጌታም ሆኖ ቄስም መሆን ይችላል ማለት ነው። ስለዘህ በስም ስንጠራ በሁለቱም የቅስና እና መሪጌታ ሞያ ያለው ከሆነ ቀሲስ እከሌ ወይም መሪጌታ እከሌ እያልን እንጠራለን። ምክንያቱም የመሪጌታም የቅስናም ሞያና ስልጣን ስላለው ነው። በዚህ ማብራሪያ መሰረት እርስዎ ያሉዋቸው መሪጌታ ካጠመቁ፣ የቅስና ክህነት ኖሯቸው መስቀል ይዘው የሚባርኩ ከሆነ በትክክልም ማጥመቅ ይችላሉ ማለት ነው። ያለዚያ የቅስና ክህነት ሳይኖራቸው መሪጌታ ሆነው የሚያጠምቁ ከሆነ ግን በቤተክርስቲያን ቀኖና ፈፅሞ እንደማይፈቀድላቸው ሊያውቁት ያስፈልጋል። ስለዚህ ጠያቂያችን በድጋሚ በሰጠንዎት ማብራርያ ያልተረዱት ነገር ካለ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
 
 በመጀመሪያ ቀርቦ የነበረው ጥያቄ እና የላክነውን ምላሽ ይህ ነበር፦

 

ጥያቄ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማጥመቅ የሚችለው መሪጌታ ነው ወይስ ቄስ ነው? እኔ በማገለግልበት ቤተክርስቲያን አጥማቂው ቄስ ነው፤ እና ብዙ ጥያቄ እያስነሳ ነው፤ እና ምን ትላላችሁ?
 
መልስ፦ ጠያቂያችን፤ ቄስ የሚለው ቃል እራሱ የክህነት ስልጣንን ያመለክታል። በእርግጥ መሪጌታም ሆኖ ቄስ ይኖራል። ሆኖም መሪጌታ የሚባሉት ሁሉ የቅስና ስልጣን ላይኖራቸው ይችላል ፥ ያላቸውም አሉ። ስለዚህ መስቀል ይዘው የሚባርኩ፣ ቀድሰው የሚያቆርቡና ፣ የሚያጠምቁ መሪጌታ፦ ቄስም ናቸው ማለት ነው። ወይም መሪጌታ ሆኖ የማጥመቅም ክህነተ ስልጣን ያለው ቄስም ነው ማለት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር ማብራሪያ ልከንልዎታል።
ጠያቂያችን በክርስቲያናዊ ስነምግባር ለመኖር ለመረዳት መጠየቅዎ እጅግ የሚያስደንቅዎ እና የሚያስመሰግንዎ ነው። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ተጠይቆ ያስተላለፍነው መልዕክት  አሁን እርሶ ላቀረቡት ጥያቄም መልስ ሊሆን ስለሚችል ልብንሎታልና መጀመርያ ይህንን ማብራሪያ አንብበው ሃሳብን በመረዳት  በመረጡት ክርስቲያናዊ የህይወት መንገድ  በቅዱስ ቁርባን ተወስነው መኖር ይችላሉ ዘንድ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን። ምናልባት በዚህ ምላሽ ግልፅ ያልሆነልዎ ነገር ካለ ወይም ያልተመለሰ ሃሳብ ካለ ደግመው ያሳውቁን ወይም በውስጥ መስመር ያግኙን።
 
ተጠይቆ የነበረውጥያቄ፦ በትዳር የነበሩ ባልና ሚስት ከተፋቱ በኃላ ሌላ ባል/ሚስት እሰከሚያገቡ ንሰሃ ወስደው መቁረብ ይችላሉ?
 
የተላከው ምላሽ፦  ጠያቂያችን የቀረቡት ሃሳብ ባል እና ሚስት ከተፋቱ በኋላ ከሌላ የትዳር አጋር ጋር ጋብቻ እስከሚፈፅሙ እየቆረቡ መቆየት ይችላሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት፦ በመሰረቱ ከዚህ በፊትም እንደመከርነው ባል እና ሚስት የስጋ አስተሳሰብ በሆነ ፈተና ለሚያጋጥማቸው ችግሮች እንዲፋቱ አይፈቀድላቸውም። ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከተፋቱ እንኳን፦ 
 
1. በየግላቸው ስጋው ደሙን ለመቀበል የሚችሉት በቀጣይ ህይወታቸው ሴቷም እንደስዋ በቁርባን ተወስኖ የሚኖረውን ለማግባት፣ ወንዱም እንደሱ በቁርባን ተወስና የምትኖረውን ለማግባት ከሆነ እየቆረቡ ለመኖር ይችላሉ።
 
2. ወንዱም ሆነ ሴቷ አብረው የነበሩበት የጋብቻ ቆይታቸውንና የተፋቱበትን ዋና ምክንያት ተናዘው እንደነሱ በሃይማኖትና በምግባር የሚወሰነውን ባል ወይም ሚስት በማግባት እየቆረቡ መንፈሳዊ ህይወታቸውን ማስቀጠል።  
 
3. ሁለተኛ ላለማግባት የወሰኑ ከሆነ ንፅህናቸውን እና ቅድስናቸውን ጠብቀው በየግዜው የነፍስ አባታቸውን እያማከሩ በስርዓተ ቁርባን ህይወታቸውን ማስቀጠል ይችላሉ። 
 
4. ሌላው ቀጣይ ህይወታቸውን ስርዓተ ምንኩስና በመወሰን መንፈሳዊ ልባዊ ውሳኔ ካላቸውም በስርዓተ ቁርባኑ ተወስነው ከቆዩ በኋላ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት የንስሓ አባታቸውን አማክረው ለምንኩስና የሚያበቃቸውን መስፈርት ሲያሟሉ እንዲመነኩሱ ይደረጋል ማለት ነው።
 
5. ዲያቆን ወይም ቄስ ሚስቱ ብትሞትበት ወይም ከሱ አቅም በላይ በሆነ ፈተና ቢፋታ፤ ያለ ሚስት የሚቀድሰውም ሆነ አባት የሚሆነው እስከ 6 ወር እንደሆነ በፍትሐ ነገስት ተወስኗል። ከዚያ በኋላ ግን ወይ መንኩሶ በክህነቱ ይቀጥላል፤ ወይም ፈተናውን የማይችለው ከሆነ ለቤተክርስቲያን አባቶች በግልፅ ተናግሮ በቅዱስ ቁርባን ተወስና የምትኖረውን ያገባል። ከዚህ በኋላ ግን መቀደስም ሆነ አባት መሆን አይችልም። የውጭ አገልግሎቱን እያከናወነ እየፀለየ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃውን የቱሩፋት ስራ እነሰራ መኖር ይችላል።
 
ስለዚህ ጠያቂያችን በአጭሩም ቢሆን ይህንን ማብራሪያ እንዲደርስዎ ስላደረግን አንብበው እንዲረዱት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።
የገና ፆም ከ 7ቱ የአዋጅ አፃዋማት አንዱ ሲሆን የፆሙ ብዛት 44 ቀናት ነው ። 40ውን ቀን የፆመው ነብዩ ሙሴ ነው። ወልደ እግዚአብሔር መሲ ክርስቶስ የመወለዱን የመውረዱን ምስጢር ትንቢት የተናገረበትንና ሁሉም ነቢያት መሲ ክርስቶስ ይወርዳል ይወለዳል እያሉ ትንቢት የተናገሩበት ቃል አማናዊ ሆኖ መኖሩን በማሰብ ነው። 4ቱ ቀናት ደግሞ ደጉ አብርሐም ሶርያዊ የተባለ አንድ ሰው ባሕር ከፍሎ ተራራ አፍርሶ የሰራውን ድንቅ የሆነ ተአምራዊ ስራ የምናስብበት ነው። ይህንን ነብያት የፆሙትን 40 ቀንና አብርሐም ሶርያዊ የፆመውን ስንደምረው 44 ቀን ይሆናል። 
ፆሙ የሚጀምርበትን ቀን በሚመለከት በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ከህዳር 15 እስከ ታህሳስ 28 ሲሆን፤ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ከህዳር 14 እስከ ታህሳስ 27 ቀን ይፆማል።የጋድ ፆምን በሚመለከት ለጥምቀት እንጂ ለገና  ፆም ወይም ለልደት የገና ፆም የለውም። ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች ስለ 7ቱ አጽዋማት በሚመለከት በቅርብ ቀን እንዲደርሳችሁ የምናደርግ መሆኑን እንገልፃለን።

ጠያቂያችን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን 7ቱንም የአዋጅ አፅዋማት እንዲፆም መንፈሳዊ ግዴታው ነው። ይሁን እንጂ እንደ ሃይማኖታችን ስርዓት አንዱን የፆም ግዜ ሳይፆም ሌላውን ፆም ለመፆም ቢፈልግ የሚከለክለው ነገር የለም። ምክንያቱም ከብዙ ጥፋት አንድ ጥፋት ስለሚሻል፣ ከብዙ ጥያቄ ሁሉንም መልስ አልባ በመሆን ዜሮ ውጤት ከማግኘት ይልቅ አንድ መልስ ማግኘትም ነጥብ ስለሚያሰጥ ነው። ጠያቂያችን የሰኔን ፆም መፆም እንዳለብዎት ብናምንም ሳይፆሙ ከቀሩ ግን የገናን ፆም በመፆም ለሚቀጥለው የሰኔ ፆም ለመፆም ቅድመዝግጅት በማድረግ መንፈሳዊ ህይወትዎን ለማሳደግ መሰረት ስለሚሆንዎ የገናን ፆም መፆምዎ አስፈላጊ እንደሆነ ያለንን ምክር እንዲደርስዎ አድርገናል።

መልስ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከ 1 እስከ 30 ያሉት በየወሩ የሚከበሩ በዓላት፦

በ 1 ልደታ ፣ ራጉኤል ኤልያስ፣ በርተሚዎስ

በ 2 ታዲዎስ ሐዋርያ እዮብ ፃዲቅ ፣አቤል

በ 3 በዓታ ነአኩቶ ለአብ ፣ ፋኑኤል፣ ዜና ማርቆስ አባሊባኖስ

በ 4 ሐዋርያው ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ እንድርያስ፣ አብረሓ ወአጽብሐ፣ አባ መልከጻዲቅ

በ 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ፣  ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ

በ 6 እየሱስ፣ አርሴማ፣ ቁስቋም፣ ማርያም መግደላዊት

በ 7 አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ፣ አትናቲዎስ፣ ዲዮስቆሮስ

በ 8 ፃድቁ አባ ኪሮስ ፣ አርባዕቱ እንስሳ

በ 9 እስትንፋስ ክርስቶስ ፣ ቶማስ ዘመርእስ

በ 10 መስቀለ እየሱስ፣ ፂዲንያ ማርያም፣ ተቀፀል ጽጌ

በ 11 ቅድስት ሃና፣ አቡነሐራ ድንግል፣ፋሲለደስ፣ ቅዱስ ያሬድ

በ 12  ቅዱስ ሚካኤል፣ ማቲዎስ፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ ድሚጥሮስ

በ 13  እግዚአብሔር አብ፣ ሩፋኤል ፣አቡነዘርእ ብሩክ

በ 14  ፃድቁአቡነ አረጋዊ፣ ፃድቁ ገብረክርስቶስ

በ 15  ሕፃን ቂርቆስ ሰማእት፣ ናትናኤል ሐዋርያ፣ ኤፍሬም ሶሪያዊ

በ 16  እናታችን ቅድስት ኪዳነ ምህረት፣ ቅድስት እየሉጣ

በ 17  ቅዱስ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ፣ አባገሪማ

በ 18  ፊሊጶስ ሐዋርያ ፣ ሰበር አጽሙ ለጊዮርጊስ

በ 19  ቅዱስ ገብርሔል

በ 20  ሐንጸተ ቤተክርስያን፣ ዮሐንስ ሐዚር፣ ኤልሳ ነብይ

በ 21  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዕዝራ ሱቱኤል

በ 22 ቅዱስ ዑራኤል፣ ሉቃስ ፣ ደቀስዮስ

በ 23  ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማእት

በ 24 ተክለሐይማኖት ፣ ክርስቶስ ሰምራ፣ ሙሴ ጸሊም፣ አባ ጎርጎርዮስ፣ 24ቱ ካህናት ሰማይ

በ 25  ቅዱስ መርቆርዮስ ፣ ሐዋርያው ቶማስ

በ 26  ዮሴፍ የእመቤታችን ጠባቂ፣ አቡነ ሐብተማርያም፣ ቶማስ ሐዋርያው

በ 27  መድኀኒአለም፣ አባ መባጽዮን

በ 28  አማኑኤል፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ

በ 29  ቅዱስ በዓለ ወልድ፣ ተፈጻሜ ሰመዕት ጴጥሮስ

በ 30  መጥምቁ ዮሐንስ ማርቆስ ወንጌላዊ

መልስ፦አስራት በኩራት በስጠትን በሚመለከት በመፅሐፍ ቅዱስ የታዘዘ መንፈሳዊ ግዴታ ነው።

አስራት ማለት ከአስር- አንድ (1/10) ወይም ከመቶ- አስር (10/100) ማለት ነው።

በኩራት ማለት ከሰው እና ከከእንስሳ የመጀመሪያው ክፍል ወይም የመጀመሪያ የበኩር ልጅ ለእግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን መስጠትን ያመለክታል

ቀዳሚያት ማለትም ከአዝሪት ከፍራፍሬው ከመሳሰለው ማንኛውም ሰው በጉልበቱ ደክሞ ወቶ ወርዶ ከሚያገኘው ሁሉ ለእግዚአብሔር የመጀመርያውን ይሰጣል።

በነዚህ በ3ቱም ዋና ዋና ፍሬ ርዕሶች ላይ ወደፊትም ቢሆን ሰፋ ያለ ትምህርት ልንሰጥበት እንችላለን። ለጊዜው ግን ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች ስለ አስራት በኩራት መገንዘብ ያለባችሁ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዝ መሆኑን ነው። ለዚህም ማስረጃ ፦

– አብርሃም አባታችን ለካህኑ ለመልከፀዴቅ አስራት እንደሰጠ በወንጌል ተጽፏል። (ዘፍ 14፥20)

–  ያዕቆብም እግዚአብሔር ከሰጠው በረከት ሁሉ ለፈጣሪው አስራት ለመክፈል ያለውን ልባዊ ደስታ በመግለፅ ተስሏል። (ዘፍ28፥22)

–  ከምእመናን የሚመጣው አስራት ለካህናቱ መተዳደሪያና የኑሮ መደጎምያ መሆን እንደሚገባው በብሉይ ኪዳን ተደንግጓል። ለምሳሌ እግዚአብሔር አምላክ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ ርስት እንዳይከፍሉ ሲከለክላቸው እንዲህ ብሎ ተፅፏል። “በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንላቸውም …. ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ አሥራት አድርጌ ሰጥቻቸዋአለሁ። በማለት የእግዚአብሔርን ቤት በማገልገል ላይ ተጠምደው ለግልና ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሃብት ማፍራት ያልቻሉትን የእግዚአብሔር ከህዝቡ የሚቀበለውን አስራት በኩራት በስርአት እንዲያስተዳድሩና እንዲያዙበት የተቀፈቀደ መሆኑን ያስረዳል ።”(ዘሁ 18፥21-32)

– በምድር ላይ ከሚገኘው ሀብትና ንብረት ከእንስሳትም ወገን ከሌሎችም ሁሉ አስራት መስጠት እንደሚገባ ታዟል። (ዘሌ 27፥30-33)

– እግዚአብሔር አምላክ አስራቱን በኩራቱን በበጎ ፈቃድ እንደ ህጉና እንደ ስርዓቱ ለሚያዋጡና በእግዚአብሔር ፊት ለሚያቀርቡ ሁሉ እንደሚባረኩ እንዲህ ተብሎ ተፅፏል።

“ ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ። …… አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ …. “  (ዘዳ 12፥ 5-18) ዘዳ 26፥13-15

እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ለሚልኪያስ አስራት በኩራትህን ለሚደብቁና ከእግዚአብሔርፊትለሚሰውሩ እንዲህ ብሎ እንደተናገራቸው እንመለከታለን “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምር ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን። የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው። እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።  በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።  ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።“ (ሚልኪያስ 3፥7-12) በማለት በአስራት በኩራት ለእግዚአብሔር ታማኝ ከሆንን የምናገኘውን በረከት፤ ታማኞች ባንሆን ደግሞ በረከታችን እርግማን እንደሚሆን በወንጌል ተፅፏል።

በአዲስ ኪዳንም አማኞች ሁሉ ካላቸው ነገር ላይ አስራት በኩራቱን እንደሚከፍሉ በቅዱስ ወንጌል ተመዝግቦ እናገኛለን። ለምሳሌ ወንጌላዊ ማቲዎስ እንደፃፈው “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።“ በማለት ፈሪሳውያን ህዝቡን በአስራት በኩራትእያስጨነቀ ከጥቃቅን ገቢ ላይ ሁሉ ደሃውን ሳይቀር እያስጨነቁ እነሱ ግን ከአስራት በኩራት በላይ የሆነውን ነገር እንደሚያጠፉ የሚያስገነዝብ ቃል ቢሆንም ነገር ግን ማንኛውም አማኝ ከሚያገኘው ገቢ አይነት አስራት ማውጣት እንደሚገባው ቃሉ ያስረዳል። (ማቴ 23፥23)

በሌላም በኩል በዚሁ የወንጌል ክፍል  የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ ተብሎ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ማስቀረት እንደማይገባ ተፅፏል። (ማቴ 22፥21)

ስለዚህ ጠያቂያችን እርስዎ ማድረግ ያለብዎ አስራት በኩራቱን በፈለጉት መንገድ በጥሬ ገንዘብም ይሁን ለቤተክርስቲያን መገልገያ ንዋየ ቅዱሳትን ገዝተው ወደ ቤተክርስቲያን ከወሰዱ በኋላ ማንኛውም ሰው ተቀብሎ መንገድ ላይ እንዳያስቀረው ህጋዊ በሆነ የቤተክርስቲያን አስተዳደር የአሰራር መንገድ መሄድ አለቦት። ምክንያቱም እርስዎም በትክክለኛ ስራ ላይ መዋሉን ሳይጠራጠሩ አስተውለው ማስረከብ አለብዎት። እራስዎት በሰጡት ገንዘብም እየተጠራጠሩ ኩነኔ ውስጥ ላለመግባት በዚህ አይነት አሰራር አስራቶትን ቢያስረክቡ በግልፅና በአደባባይ የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር ስላስረከቡ እግዚአብሔር ደግሞ ለእርስዎ በምድርላይ በረከትን በኋለኛው ዘመን ሰማያዊ ክብርን ያጎናፅፍዎታል።

ቤተክርስቲያንም የአስራት በኩራት አስተዋጾ የሚውለው በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ለተወሰኑ አገልጋዮች፣  በቤተክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳት ማሟያ እና ለነዳያን የሚሰጥ ሲሆን ለያንዳንዱ ቤተክርስቲያን አሰራርና አፈፃፀም ድርሻ አለው።

ስለዚህ ባጠቃላይ በጥሬ ገንዘብ ከሆነ መስጠት የፈለጉት ቤተክርስቲያኒቱ በዚህ ዘመን ገንዘብንና ንብረትን የምታስተዳድርበት ህጋዊ የሆነ የገቢ ደረሰኝ ስላላት ገንዘቡን በሞዴል 64 የገንዘብ በደረሰኝ ማስቆረጥ ወይም በሙዳይ ማስገባት ይቻላል። ሌላ ንብረት ወይም ንዋየ ቅዱሳት ከሆነ የሚሰጡት በንብረት ገቢ ደረሰኝ አስቆርጠው በሞዴል 19 ማስገባት ወይም በቋሚ መዝገብ አፅፈው ገቢ አድርጎ ደረሰኙን መቀበል ይቻላል። ከዚህ ውጭ ለሚመክሩን ለሚያስተምሩን እለት እለት ለነፍሳችን ለሚያገለግሉን አባቶች በፈቃደኝት ማድረግ የምንፈልገው ካለ ይሄም ቢሆን  በጎ ስራ ስለሆነ መልካም ነው፥ ነገር ግን ከአስራት በኩራይ የሚደመር አይደለም።   

ስለዚህ በዋናነት ማንኛውም ክርስቲያን በህገ እግዚአብሔር በታዘዘው መሰረት ከሚያገኘው ማንኛውም ገቢ ላይ አስራቱን ማዋጣት እንዳለበት አምኖ በተግባር ለመፈፀም ፈቃደኛ ከሆነ ከላይ በገለፅነው መንገድ መፈፀም ይችላል፤ ከዚህ በተጨማሪ ዝርዝር አፈፃፀሙን በሚመለከት መረዳት እና ማማከር ካስፈለገ ግን ስለቤተክርስቲያን ስርዓትና ቀኖና እንዲሁም ትውፊት ጠንቅቀው የሚያውቁ የቤተክርስቲያን መምህራን (አባቶች) ቀርቦ በማነጋገር የሚፈፀምይሆናል።

ስለዚህ ጠያቂያችን ከዚህ ውጪ ቅድመ ሁኔታ ተዘጋጅተው በስራ ላይ ለማዋል የተቸገሩበት ጉዳይ ወይም ግልፅ ያልሆነልዎት ጉዳይ ካለ በውስጥ መስመር ቢያነጋግሩን በትክክለኛው አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ የሚችሉበትን እውነተኛ አቅጣጫ ልናሳይዎት እንችላለን። 

በመሰረቱ በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ሃይማኖት ውስጥ የማይፈቀድ የምግብ አይነት በቤተክርስቲያናችን ቀኖና የተወሰነ ቢሆንም እንኳን ነገር ግን በዋናነት በአዲስ ኪዳን ስርዓት በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ እንኳንስ ለሥጋ የሚስማማ ምግብን ቀርቶ ሰውን የሚጎዳውን መርዝንም እንኳን ሳይቀር ብንጠጣው በኛ ላይ ስልጣን እንደማይኖረው ተፅፏል። ማር16፥18

 

ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ምግብ ለሆድ ሆድም ለምግብ ተፈጥሯል ሁለቱንም ግን እግዚአብሔር ያሳልፋቸዋል እንዳለው ሁሉ ጠያቂያችን በብሉይ ኪዳን ስርዓት እስራኤል ከግብፅ ለመውጣት ምክንያት የሆናቸውን የፋሲካውን በግ ባረዱ ጊዜ ብሩንዶው ስጋ (ያልበሰለው ስጋ) አትብሉ እንደተባለ በእሳት ያልበሰለ (እሳት ያልነካውን ስጋ) መብላት በኦሪቱ ስርዓት እንደማይፈቀድ ተፅፏል። ይሁን እንጂ በአዲስ ኪዳን ለሥጋችን ስለሚያስፈልገን የምግብ አይነት ከንቱና የማይጠቅም እንደሆነ የተፃፈ ስለሆነ የማይጎደን ሆኖ ያገኘነውን የስጋ ምግብ በመጠኑ የሚያስፈልገንን ያህል መመገብ እንዳለብን አስበን ማድረግ ይቻላል። አስፈላጊ ወዳልሆነ ወደ ኅጢአት ጎዳና የሚያመራንን እና ከሃይማኖታዊ ስርዓት ሊያወጣን ይችላል ብለን የምንጠረጥረውን የስጋ ምግብ ማድረግ ግን አይገባንም። ስለዚህ ጠያቂያችን ስላቀቡት ጥያቄ ይሄን አጭር ምላሽ እንዲደርስዎ አድርገናልና በዚህ ይረዱት። ተጠጨማሪ ማብራሪያ ካስፈለገዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

የአንዲት ሴት ከወር አበባ የመንፃት ጊዜ ተብሎ የተያዘው 1 ሱባኤ ወይም ከ 7 ቀን  ነው፤ በልዩ የጤና መታወክ ከ 7 ቀን ካለፈባት ሁለተኛ ሱባኤ ልትጠብቅ ትችላለች፥ ወይም በሴትዋ የጤና ጉዳይ አካላዊ ንፅህና የሚወሰን ይሆናል። 7 ቀን ስላለፈ ብቻ ፈሳሽ እስካልቆመ ወደ ቤተክርስቲያን መግባት አትችልም። የወር አበባ ጊዜ ጠብቆ ባይመጣ ወይም በተለየ ጊዜ ቢመጣ ዋናው ነገር ፈሳሽ በአካል ላይ እንዳለ ወደ ቤተክርስቲያን አይገባም ማለት ነው። ከ7 ቀን በኋላ ከፈሳሽ ስትነጻ ቤተክርስቲያን መግባትም ሆነ አገልግሎቱን ማግኘት ትችላለች ማለት ነው። ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ሰፊ ትምህርት የሰጠንበት ስለሆነ ከድረገፃችን ላይ እንዲመለከቱት እንመክራለን።

 

https://yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ/

ጠያቂያችን እርዳታ ለተቸገሩ ወገኖች ማድረግ ወይም  ምጽዋት መስጠት የምግባር ዋናው አካል ነው። ከምንም በላይ ችግረኞችን መርዳት በፈጣሪ ፊት ለፍርድ በቀረብን ጊዜ የምንጠየቅበት ዋና ምግባር ነው። ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ብሎ እንደተፃፈ “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ?  እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?  ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።  በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል።ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴ25፥ 34፣46) በማለት በጎ ስራ ሰርተው ብሩካን የተባሉ ፃድቃንም ለዚህ ክብር የበቁበት ትልቁ ምግባራቸው በፈጣሪያቸውም ፊት ያስመሰገናቸው ለተቸገሩ ነዳያን ላደረጉት በጎ ስራ ነው። ሌሎቹ ከፈጣሪ ዘንድ ርጉማን የተባሉት ችግረኞችን ባለመርዳታቸውና ልዩልዩ ፈተና ሲደርስባቸው ባለመጠየቃቸው በነፍስ ተጠያቂ አድርጓቸው ወደ ዘለዓለማዊ ኩነኔ እንዲሄዱ እንደተፈረደባቸው ያመለክታል። በአጠቃላይ በመፅሐፍ ቅዱስ ችግረኞችን በሚመለከት በስፋት ተመዝግቦ እናገኛለን። እነዚህ በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉትን ወገኖች መርዳት በቀጥታ ለእግዚአብሔር እንዳደረግንለት እንደሚቆጠር የወንጌሉ ቃል ያስረዳናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልዕክቱ “ለሰው ልጅ ሁሉ በጎ ነገርን አድርጉ ወይንም እርዱ የሚበልጠውን ደግሞ በሃይማኖት ለሚመስሏችሁም አድርጉ” በማለት ሰው ለሆነው ሁሉ በዘር በቋንቋ በቀለም በሌላም ሰውኛ ምክንያት ልዩነት ሳናደርግ መርዳትና በችግር ሁሉ መተባበር እንዳለብን ያስተምረናል። ሰው ሰውን ለመርዳት ሌላ ምንም አይነት መስፈርት ሳያስፈልው ሰው ሆኖ መፈጠሩ ብቻ በቂ ነው። በእርግጥም በሃይማኖት ደረጃ የማንተባበርባቸውና የምንለያቸው መክንያቶች ሃይማኖታችንንና መንፈሳዊ ህይወታችንን ሊያጎድፉ የሚችሉ የኅጢአት ተግባር ሲኖሩ ብቻ ነው። በጎ ስራ ለመስራት ግን አይደለም በተፈጥሮ ለሚመስለን ቀርቶ ለእንስሳና ለአራዊት ፣ ለእፅዋትና ለአዝርዕት ለመሳሰሉት ፍጥረታት ሁሉ በጎ ስራ መስራት የክርስቲያኖች መገለጫና ምግበር ነው።

ይሁን እንጂ ጠያቂያችን ስለሃይማኖትዎ እና መንፈሳዊ ህይወትዎ ቅድሚያ ሰጥተው ነገሮችን በጥንቃቄ ለማወቅና ለመረዳ  ካለዎት ፍላጎት አንፃር የጠየቁት ስለሆነ እጅግ የሚያስመሰግኖት ነው። ዋናው ማወቅ ያለብዎት  በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር የማንተባበረው በጋብቻ ስርዓት፣ በአምልኮ እና በመሳሰሉት የሃይማኖት ጉዳዮች ነው። በዚህ በእርስዎ ጠያቂነት መሰረት ሁሉም ሰው መረዳት ያለበት ፤ ምፅዋት ማድረግ፣ እርዳታ መስጠት የተለያዩ ድጋፎችን መፈፀም ባጠቃላይ ከሃይማኖት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር ሳይኖር ይሄንን በጎ ስራ በመስራታችን እኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የምናገኝበት ስለሆነ ባለን የኑሮ ደረጃ እንደየአቅማችን ከገንዘባችን ፣ ከጉልበታችን ፣ ከእውቀታችን፣ ከጊዜያችን ለተቸገሩ በመራራትና በፍቅር መርዳትና ማካፈል አለብን።

እርዳታ ሲባል በብዙ አይነት አገላለፅ ነው። ምክንያቱም ካለን ሀብታችን ውስጥ ድሆች የራሳቸው ድርሻ ስላላቸው ትንሽም ቢሆን  የቱሩፋት ስራ በራሳችን ፈቃድ ለእርዳታ ብለን ያዘጋጀነውን ስጦታችንን መረዳት ለሚገባው አካፍለን ልንለግስ ይገባል። ይህ ማለት ለቤተክርስቲያን ነዳያንና ለሌሎቹም በጎ ስራዎች ሁሉ ማድረግ እንደሚገባን በሃይማኖታችን ስርዓት በተፈቀደው መሰረት በጎ አድርገን ምፅዋት ሰጥተን በፈጣሪ ዘንድ ማግኘት የሚገባንን ሰማያዊ ዋጋ ለማግኘት እንድንችል ሁላችንም ለበጎ ስራ እንዳይረፍድብን ተግተን መስራት ይገባናል።

እግዚአብሔር አምላክ ለበጎ ምግባር እና ለቱሩፋት ስራ እንድንበረታ እሱ ያግዘን።

ጠያቂያችን ማንኛውም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በተለየ በራሱ መንፈሳዊ ውሳኔ ቃልኪዳን የገባበትን በዓል በልዩ መንፈሳዊ ስርዓት ማክበር የተለመደ ነው። በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በልዩ ቃልኪዳን በሚማፀነው ፃድቅ ስም፣ ወይም ቅዱሳን መላዕክት ስም፣ ወይም በባለቤቱ ስም፣ ወይም በድንግል ማርያም ስም ፣ በተሰየመው ቤተክርስቲያን ስም ራሱ በልዩ ምስጢራዊ ግንኙነቱ እየተማፀነ በአሉን ያከብራል፣ በዚያን እለትም ልዩ ልዩ የትሩፋት ስራዎች ሊያከናውን ይችላል።
 
ሁላችንም ኦርቶዶክሳዊያን የእግዚአብሔር ልጆች በተለየ ቃልኪዳን የምናከብረው ፃድቅ ወይም ሰማዕት ወይም መላዕክት ሊኖር ስለሚገባ ያንን በዓል በምናከብርበት ጊዜ ከብዙ የሥጋ ተግባራት ተቆጥበን ከማክበራችንም በላይ ለመንፈሳዊ አገልግሎትም የምናደርጋቸውን ነገሮች በዚያን ጊዜ ለመፈፀም ሊከብደን ይችላል። ይህ ግን እንደ ፈቃድ እንጂ እንደ ግዴታ ተደርጎ መታየት የለበትም።
 
ስለሆነም የንስኀ ስግደትም ሆነ በግል ፈቃዳችን ስለምንሰግደው ስግደት ከዚህ በፊትም ባስተላለፍነው መልዕክት መሰረት በቀኖና ህግ የሚሰገድባቸውንና የማይሰገድባቸውን ቀናት በግልፅ ለማሳየት ሞክረናል። ከዚህ ውጭ በግላችን የቅዱስ ገብርኤልንም ሆነ የሌሎቹን በዓላት ስናከብር ላለመስገድ የምንችለው በእራሳችን ፈቃድ እንጂ በቤተከርስቲያን ታዘን እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። መክንያቱም በቤተክርስቲያን ቀኖና ከተደነገገው ውጪ በእራሳችን ቃልኪዳን ስለገባንበት ሁኔታ ከዛ ጋር ግንኙነት አይኖረውም። ነገር ግን በገባነው ቃልኪዳን በረከት ለማግኘት በልዩ ሃይማኖታዊ ፀጋ በበዓሉ ቀን ባይሰግዱም አይገደዱም፤ ቢሰግዱም የሚከለክላቸው እንደሌለ መረዳት ያስፈልጋል። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ስለ ገና ዛፍ የጠየቁን አባላችን የገናን አመጣጥ እና ምንነት ወቅቱና ጊዜው አሁን ስለሆነ የጌታችን የመድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የልደቱን በዓል ምክንያት በማድረግ ሰፋ ያለ ትምህርት በቀጣይነት እንዲደርሳችሁ እናደርጋለን። ይሁን እንጂ ለጊዜው የቀረበልንን ጥያቄ ለመመለስ ያህል ገና ማለት የቃሉ ትርጉም “ከዕፅዋት የሚገኝ እና ከራሱ ላይ ቆልማማ የሆነ የከዘራ ቅርፅ ያለው ሰው የሚያዘጋጀው” ሲሆን በዚሁ በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል መገለጫ የሚሆነውን የትውፊት ስርዓት የሚከተሉ አማኞች ውርውር የሚጫወቱበት ስርዓት ነው። ይህም የመንፈሳዊ ትውፊት የተገኘው ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ገዜ የልደቱን ምስጢር ለማየት የታደሉ እረኞች ስለነበሩ ይህ የገና ጨዋታ የእረኞች ስራ ስለነበረ ከዚህ ሥርዓት ጋር ለማያያዝ ገና የሚለው ስያሜ ተገኝቷል። ይሁን እንጂ በሃይማኖት ትውፊት የተገኘውን የእግዚአብሔር በረከት በብዙ የዘመን ቆይታ ሂደት ቀጥተኛውን ትውፊት የሚያዛባ የበአልና አስፈላጊ ያልሆነ ከኛ ትውፊት ጋር የሚቃረን ብዙ ጣልቃ ገብነቶች ሥርዋጾች ሲከሰቱ ይታያሉ። ይህንን ያልንበት ምክንያት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የመወለዱን እለት (የገና በዓል) ከማክበር ጋር ተያይዞ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉምና ምክንያት የሌለው የገና ዛፍ፣ የገና አባት በሚል በየጊዜው እየጎላና ተቀባይነት እያገኘ የበዓል አከባበር ሥርዓት ከእውነተኛው የቅድስት ኦርቶዶክሳዊ የሃይማኖት ትውፊት ጋር የማይስማማ ሂደት ነው። በገና በዓል የፅድ ዛፍ በመቁረጥም ይሁን አርቴፊሻል የገና ዛፍ በማዘጋጀት እንዲሁም የገና አባት በሚል ምስል ያለውን አርማ በማዘጋጀት ለበአሉ ማድመቂያ የሚደረገው ሂደት ከእውነተኛው የሃይማኖት ጋር የማይዛመድ ነው። በእርግጥ ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው፥ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤” በማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ብዙ ሰዎች በሚኖሩበት መንደር የተወለደ ሳይሆን እንስሳት በሚኖሩበትና ለከብቶች በተዘጋጀ በረት ውስጥ ከብቶችን የሚጠብቁ እረኞች የሚኖሩበት በረት የዱር ዕፅዋት በሚታዩበት ስፍራ ስለተወለደ የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምስጢራዊ መገለጫነታቸውን ልናስብ እንችላለን። 
 
ከዚህ ውጭ የዱር ደንን በመመንጠር ወይም ለቢዝነስ ስራ ወይም ገቢ ምንጭ ተብሎ የተዘጋጀውን የፅድ ዛፍ መሰል የሆነውን አርቴፊሻል በውድ ገንዘብ ገዝቶ የገና አባት በሚል የተዘጋጀውን አርቴፊሻል ምስል በማቆም የገናን በዓል ለማክበርና የሚደረገው ሂደት እጅግ ከእውነታኛ የሃይማኖት ስርዓት የራቀ ልምድ ነው። ጠያቂያችን የገና ዛፍ ጣኦት ማምለክ እንደሆነ ያቀረቡት ሃሳብ የተጋነነ ምክንያት ቢሆንም እንኳን ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር በማያያዝ የገና ዛፍ የሚለው አገላለፅ በጥንታዊያን የእንግሊዝ እና የግሪክ የጣኦት አምልኮ ስርዓት ጋር በተያያዘ አረንጓዴ መሰል እፅዋትንና ሌሎችን ነገሮች በዘመኑ ለሚያመልኩት የጣኦት የክብር መገለጫ ያደርጉት የነገረውን ስርዓት በማያያዝ የመጣ ጣልቃ ገብ ስርዓት እንደሆነም የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ። ነገር ግን ለማያምኑበት ሰዎች ምንም አይነት ትርጉም የለሽ ስለሆነ ምናልባት እንደ እውነተኛ ክርስተና ስንመለከተው ከጌታ ልደት የበለጠ ደሰታ ባለመኖሩ ለሌላ ተጓዳኝ አምልኮት ሳናውለው እውነተኛውን የጌታን ልደት ለማክበር በፍጹም እምነት ሆነን የምናደርገው ነገር ሁሉ ከአምልኮ ጣኦት ጋር የሚያያዝ አንዳችም የሚሰጠው ትርጉም ስለማይኖር ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ አግባብ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት እንዲደርስዎ አድርገናል፤ የሚበልጠውን ማብራሪያ ግን የመደበኛው ትምርታችን ላይ የምናስተላልፍ ስለሚሆን በዚያ ይጠብቁን።
የአምልኮት ስግደት ማለት ወደ ቤተክርስቲያን ሄደን በስእሉ ፊት፣በመስቀሉ ፊት በታቦቱ ፊት የምንሰግደው ሲሆን ይህ ደግሞ መቼም ቢሆን የሚቋረጥ ስላልሆነ በየትኛውም ሰዓት ልናደርገው የምንችለው ነው።በተጨማሪም ከዚህ በፊት እንደገለጽነው የሚሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት፦ ልዩ የንስሃ ቀኖና ሲሰጠን፣ በምንፀልይበት ግዜ፣ ስለስግደት በሚነገርበት ቃል ላይ፣ ቅዳሴ በምናስቀድስበት ግዜ ስገዱ ሲባል፣ በሰሞነ ህማማት፣ እነዚህን በሚመሳስሉ በአምልኮት ስርዓት በሚከናወኑ ስግደት እንድንሰግድ በቤተክርስቲን ፍትሓ ነገስት ተደንግጓል። እንዲሁም ከላይ እንደገለጽነው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስንገባ በየትኛውም ቦታ መስቀል ስንሳለም፣ በቅዱሳን ስዕላት ፊት፣ ለቅዱስ ወንጌሉ እንሰግዳለን። 
 
በምንሰግድበትም ጊዜ በጌታ ላይ የደረሰውን የመስቀሉን መከራ የምናስታውስበት ጊዜ ስለሆነ የኛ መከራ ከሱ መከራ ጋር ባይወዳደርም እንኳን ግንባራችንን እና ጉልበታችንን መሬት አስነክተን እንሰግዳለን። በዚህን ግዜ ከሰውነታችን ላብ ሊወጣ ይችላል። በበአላት ግዜ እንዳንሰግድ የተደረገበት ምክንያት ስግደት በራሱ መንፈሳዊ ስራ ስለሆነ እና ነፍስ ፍሬ የምታፈራበት ስራ ስለሆነ ልክ እንደ ስራ ከበአላት ውጭ ግዜ ወስደን መፈፀም ስላለብን ይህን ለማስተማር ነው እንጂ በበአላት ቀን ሳናውቅ ብንሰግድም እንደ ኀጢአት ይቆጠርብናል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ አንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል። 
ሁልጊዜ በዓል በመጣ ቁጥር የሚያሳስበኝ ጥያቄ አለ ካልተሳሳትኩ በቤተክርስቲያናችን ሰዓት አቆጣጠር የሚቀጥለው ቀን የሚገባው ከምሽቱ 12ሰዓት ነው።ይህን መነሻ በማድረግ ከምሽቱ 12ሰዓት በኋላ እርድ ማከናወን ይቻላልን?ብዙ ሰዎች በበዓሉ ዕለት ካልታረደ በፆም እንደታረደ ይቆጠራል ይላሉ።
ጠያቀያችን በመሰረቱ የክርስትና ስም የሚወጣው በባለቤቱ ስም ፣ በእመቤታችን ስም፣ በቅዱሳን ሰዎች ስም እና በቅዱሳን መላዕክት ስም እንደሆነ የቤተክርስቲያን ስርአት ቀኖና ይነግረናል። በመሆኑም አንዳንድ ትምህርት የሌላቸው ካህናት በልማድ መባል የሌለበትን የክርስትና ስም እንደሚያወጡ በብዙ አጋጣሚ ተመልክተናል።
 
ይሁን እንጂ አሁንም ከላይ እንደገለፅነው እንዲያው ያለእውቀት ስለ ክርስትና ስም አወጣጥ የማያውቅ ሰው ስላጋጠመዎት እንጂ ወልደ መድኅን የተባለው እራሱ መድኃኒአለም ስለሆነ የመድኀኒዓለም ልጅ ማለት ነው። ገብረ መድኅን ማለት ደግሞ የመድኃኒዓለም አገልጋይ ባርያ ማለት ነው። እንደ ሃይማኖት ነው እንጂ በሰው ሰውኛ ስናየው ከባርነት ይልቅ ልጅነት  ክብር ስላለው ‘ወልደ መድኅን’ የሚለው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ ይህን ስም የሰጠዎት ምርጥ ስም ነው። መባል የሌለበት የክርስትና ስያሜ ግን ‘ወልደ ሰንበት’፣ ‘ወለተ ሰንበት’ … ነው ምክንያቱም ሰንበት የእለት ወይም የቀን ስያሜ ስለሆነ የቀን ልጅ አይባልም።  የእርስዎ ስም ግን ትክክለኛ የክርስትና ስያሜ ስለሆነ በዚህ ይረዱት ዘንድ ያስፈልጋል በማለት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 ጠያቂያችን በዚህ ጥያቄ ላይ ከዚህ በፊትም መጠነኛ አጭር መልስ እንዲተላለፍ ያደረግን ሲሆን ፤ ለመረዳት እና ለማወቅ ለሚጠይቁን የቤተክርስቲያን ልጆች መልስ ለመስጠት ፈቃደኞች ስለሆንን የሚሰገድባቸውን እና የማይሰገድባቸውን በእለት ወይም በጊዜያት ተለይተው እንዲቀርቡ አሁንም ከዚህ በታች በድጋሚ በዝርዝር ልከናል፦ 
 
የማይሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት፦ 
 
1ኛ/ እለተ ሰንበት (እሁድ) እና ቅዳሜ፣ 2ኛ/ በ12 በቅዱስ ሚካኤል ፣ 3ኛ/ በ21 የእመቤታችን በአል ፣ 4ኛ/በ29 ባለወልድ፣ 5ኛ/ በዘጠኙ የጌታ አበይት በአላት ለምሳሌ ጥምቀት፣ ልደት…፣ 6ኛ/ ከትንሳኤ እስከ ጴራቅሊጦስ (በአለ ሃምሳ) እነዚህ የማይሰገድባቸው ጊዜያት ናቸው። 
 
የሚሰገድባቸው እለታት ወይም ጊዜያት ደግሞ ፦ 
 
ልዩ የንስሃ ቀኖና ሲሰጠን፣ በምንፀልይበት ግዜ፣ ስለስግደት በሚነገርበት ቃል ላይ፣ ቅዳሴ በምናስቀድስበት ግዜ ስገዱ ሲባል፣ በሰሞነ ህማማት፣ እናዚህን በሚመሳስሉ በአምልኮት ስርዓት በሚከናወኑ ስግደት እንድንሰግድ በቤተክርስቲን ፍትሓ ነገስት ተደንግጓል። በተጨማሪም ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስንገባ በየትኛውም ቦታ መስቀል ስንሳለም፣ በቅዱሳን ስዕላት ፊት፣ ለቅዱስ ወንጌሉ እንሰግዳለን። 
 
በምንሰግድበትም ጊዜ በጌታ ላይ የደረሰውን የመስቀሉን መከራ የምናስታውስበት ጊዜ ስለሆነ የኛ መከራ ከሱ መከራ ጋር ባይወዳደርም እንኳን ግንባራችንን እና ጉልበታችንን መሬት አስነክተን እንሰግዳለን። በዚህን ግዜ ከሰውነታችን ላብ ሊወጣ ይችላል። በበአላት ግዜ እንዳንሰግድ የተደረገበት ምክንያት ስግደት በራሱ መንፈሳዊ ስራ ስለሆነ እና ነፍስ ፍሬ የምታፈራበት ስራ ስለሆነ ልክ እንደ ስራ ከበአላት ውጭ ግዜ ወስደን መፈፀም ስላለብን ይህን ለማስተማር ነው እንጂ በበአላት ቀን ሳናውቅ ብንሰግድም እንደ ኀጢአት ይቆጠርብናል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችንም እና ሌሎች አባላቶቻችን ይህን መልእክታችንን አንብባችሁ የመንፈስ ፍሬ እንድታፈሩበት ሁላችሁንም አደራ እንላለን።

ጠያቂያችን የእርስዎ ጥያቄ “…ቅባ-ቅዱስ መቀበል ይችላል” የሚለው አባባልዎ ግልፅ ስላልሆነ እንዲስተካከል ሆኖ፥ ነገር ግን እኛ ለማለት የፈለጉትን በተረዳነው መልኩ ይህን ምላሽ ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት፦ አንድ ካህን በእድሜ እርጅና አቅማቸው ሳይፈቅድ ቅዳሴ ቢያቆሙ የክህነቱ ስልጣን አቁሟል ማለት ግን አይደለም። ቤተ መቅደስ ቆሞ ማስቀደስ፣ መቁረብ፣ ማስተማር፣ ንስኀ አባት መሆን፣ መባረክ፣ እና ማጥመቅን የሚከለክል ህግ የለምና በእድሜ ምክንያት የማይችሉትን አገልግሎት ብቻ መስጠት ባይችሉም በቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ የአባትነት ክብር ተሰጥቷቸው ከላይ የዘረዘርናቸውን የክህነት አገልግሎትም እንደሁኔታው መስጠት ይችላሉ ማለት ነው። ጠያቂያችን በዚህ ያልተመለሰልዎት ሃሳብ ካለ በውስጥ መስመር ጥያቄዎን ቢያብራሩልን ተጨማሪ ምላሽ ልንሰጥዎት እንችላለን።

ባጭሩ ጠያቂያችን የተሰጠን የንስኀ ቀኖና በፆም ራሳችንን ለእግዚአብሔር እንድናስገዛ ከሆነ የተሰጠን የፆም ቀኖና እስከሚያልቅ ድረስ የተወሰነልንን ሰዓት ጠብቀን እየጾምን የፆም ምግብ እንመገባለን እንጂ የፍስክ ምግብ አንመገብም።  በንስኀ አባታችን የተሰጠን የንስኀ ቀኖና  ስግደት ብቻ ከሆነ ስግደቱን ሳንበላ እየሰገድን የፍስክም ቢሆን መመገብ እንችላለን። ምክንያቱም የእኛ የንስኀ ቀኖና ከቅዳሴው ፀሎት አይበልጥምና ቅዳሴ ተቀድሶ ከአለቀ በኋላ  መፈፀም እንችላለን። ስለዚህ ጠያቂያችን የንስኀ ቀኖና አፈፃፀም ሂደትን ወሳኙ ቀኖናውን የሰጠው አባት ነው እንጂ በሌላ ወገን በጥያቄ የሚብራራ ባይሆንም ሃሳቡን ግን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።

ጠያቂያችን ማንኛውም ለንግድ ስራ የቀረበ እንኳንስ በቤተርስቲያን ቀኖና ያልተፈቀደውን የወይራ ዘይት ቀርቶ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ፀሎት የከበረውን ቅባ ቅዱስ እንኳን ሳናምንበት እና ሳይገባን ለፈለግነው አገልግሎት ብናውል ከጥቅም ይልቅ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ጠያቂያችን ለንግድ ስራ ወይም ቢዝነስ ተኮር በሆነ የገበያ አቅርቦት ያገኘነውን ማንኛውም ቅባ ቅዱስ መሰል ፈሳሽ ገዝተን መጠቀም አንችልም። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምሮ ቅባቅዱስ ወይም ሜሮን የምንለው የተቀደሰ ቅባት በልዩ ምስጢራዊ ረቂቅ ስርአት በጸሎት ከብሮ አገልግሎት ላይ የሚውል ልዩ ቅዱስ ቅባት ስለሆነ ሃይማኖት የሌላቸውና መናፍቃን በድፍረት እንደሚያስቡት አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በራስዋ የሃይማኖት አባቶች ፀሎት እና ቡራኬ የከበረውን እና የተባረከውን ቅባ ቅዱስ ያውም ደግሞ ለምን አገልግሎት መዋል እንዳለበት ምስጢራዊ ትርጓሜውን ከአባቶቻችን በጥንቃቄ በመረዳት መጠቀም አለብን እንጂ ከሜዳ ላይ ተነስተን ለስጋዊ አካላችን መገለጫ ይሆናል ብለን የምናስበውን በንግዱ ስርአት ከገበያ ላይ የገዛነውን ዘይት እንደ ቅባቅዱስ መቁጠር እንደሌለብን እንመክራለን።

ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ የቀረቡልንን ጥያቄዎች መነሻ አድርገን የማይሰገድባቸውና የማይፆምባቸውን ቀናትና በዓላት አስመልክቶ መልዕክት ማስተላለፋችንን እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ ሁሉም አባላት የየራሳቸውን ጥያቄ ይዘው እየቀረቡ ሊሆን ስለሚችል አሁንም ለእርስዎ የምንሰጥዎ ምክር ቅዳሜን እና እሁድን በቤተክርስቲያን ቀኖና እንኳንስ ለንስኀ ፆም ተሰጥቶን ይቅርና በአዋጅ በተደነገገበት በ 7ቱ አፅዋማት ውስጥ የሚገኙ ቅዳሜ እና እሁድ የፍስክ ምግብ አንበላባቸውም እንጂ ከቅዳሴ በኋላ ሳንፆም ለፆም የተፈቀደ ምግብ እንደምንበላ መታወቅ አለበት። ስለዚህ ንስኀ የሚሰጡን አባቶችም ይህንኑ ምእመናን እንዳይሳሳቱ አብራርተው መክረው የንስኀ ቀኖና መስጠት አለባቸው። ስለዚህ ፆምና ስግደት በማይፈቀድባቸው ቀናትና በዓላት አንፆምም አንሰግድም ማለት ነው። ፆምን በተመለከተ ቅዳሜ እና እሁድ ያልፆምነው በቤተክርስቲያን ቀኖና ስለተደነገገ እንጂ እኛ መፆም ሳንፈልግ ቀርተን ስላልሆነ ሌላ ተለዋጭ እለታት አያስፈልግም። ምክንያቱም ቅዳሜ እና እሁድን ከምንፆማቸው የፆም ቀናት ጋር አብረው ስለሚቆጠሩ ነው። ስግደትን በሚመለከት ግን የማንሰግድባቸውን ቀናት በሌላ ቀን መስገድ ይኖርብናል። በበዓላት ግዜ እንዳንሰግድ የተደረገበት ምክንያት ስግደት በራሱ መንፈሳዊ ስራ ስለሆነ እና ነፍስ ፍሬ የምታፈራበት ስራ ስለሆነ ልክ እንደ ስራ ከበአላት ውጭ ጊዜ ወስደን መፈፀም ስላለብን ይህን ለማስተማር ነው እንጂ በበአላት ቀን ሳናውቅ ብንሰግድም እንደ ኀጢአት ይቆጠርብናል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን ኀሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል፤ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲኖርዎት ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ የሰጠናቸውን መልዕክቶች እንዲሁም ስለ አስራት በኩራት ላቀረቡት ጥያቄንም በሚመለከት ከድረገፃችን ላይ ስላለ ወይም አንድ አባላችን ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን መልዕክት ሼር ስላደረጉልዎት አሱን አንብበው እንዲረዱት እንመክራለን።

ጠያቂያችን ንስኀ ራሱን የቻለ የጾም፣ የፀሎት እና የስግደት ጊዜ ስለሚያስፈልገው ከመደበኛ የቀኖና አፇማት ጋር መሆን አይኖርበትም። ምናልባት የንስኀውን አይነት በመረዳት አንቀፀ ንስኀ በሚያዘው መሰረት የሚሰጠው የንስኀ አይነት ቀላል ሆኖ ከተገኘ ንስኀውን የሚያናዝዙ አባቶች የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል እንጂ የንስኀ ጊዜ ግን ከላይ እንደገለፅነው ራሱን የቻለ ከመደበኛ ፆም ውጪ ባለ ጊዜ መሆን ይገባዋል።

ጠያቂያችን ከዚህ በፊትም ስለ ህልመ ሌሊት ብዙ አባላቶቻችን ባቀረቡልን  ብዙ ጥያቄዎች ጠይቀውን በቀኖና ቤተከርስቲያን መሰረት የተለያዩ ማብራሪያ መስጠትችንን እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ ‘ታጥቦ መግባት ይቻላል ወይ?’ የሚል ሃሳብ የእግዚአብሔርን ህግ ለመዳፈር ምክንያት ስለሆነ አንዳንድ ሰዎች የሚገጥማቸው እለታዊ ፈተና የሚያደርጉትን የግል ውሳኔ እንደ ቋሚ ህግ መቁጠር ስለሌለብን ማንኛውም ካህንም ሆነ ምእመን እንዲህ አይነት የህልመ ፈተና ሲገጥመን እስከተወሰነ የሰአት ገደብ ወደ ቤተክርስቲያን   እንዳይገባ የቤተክርስቲያን ቀኖናው ስለሚከለክል ፥ በመታጠብ ረቂቅ  ከሆነው የኀጢአት ስራ ልንነጻ ስለማንችል ከሁሉ በፈት እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ስለሆነ በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነን የተወሰነውን ጊዜ መጠበቅ አለብን። እንግዲ ‘ታጥበን መግባት እንችላለን ወይ?’ የሚለውን ነገር ከሰው ሰውኛ አስተሳሰብ ካልሆነ በስተቀር እንደ ቤተክርስቲያናችን ስርአት ፈጽሞ የሚቻል አይደለደም። 
 
በማታ በሀልመ ሌሊት የምናየው ነገር በእኛ በራሳችን ስጋዊ ምኞት የሚገለፅ ስለሆነ አንዳንዱ በገሀዱ ያሰበውን በህልም የሚፈፅም ፣ አንዳንዱ ደግሞ ምንም አይነት ሃሳብና ምኞት ሳይኖረው እርኩስ መንፈስ በህልም መጥቶ የሚፈትነው አጋጣሚ ስላለ፤ ለሁሉም ነገር ከላይ በሰጠነው ማብራሪያ መሰረት እግዚአብሔርን ከመድፈር እና ከማሳዘን ይልቅ በትዕግስት እና በፈሪሀ እግዚአብሔር ሆነን ከሁሉም ፈተናችን እስከምንርቅ ድረስ የቀኑን የግዜ ገደብ መጠበቅ አለብን።
 ጠያቂያችን በንስኀ ቀኖና ስንቀበል አባቶች በሚያዙን መሰረት የሚከናወን ስለሆነ እስከ ስንት ሰዓት መፆም እንዳለብንም በዝርዝር አብራርተው ሊነግሩን ይገባልና ደውለው ቢጠይቋቸው መልካም ነው። ምናልባት በዚህ መፍትሄ ካላገኙ ግን እኛን በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን ይችላሉ። በመሰረቱ የንስኀ ጾም ራሱን የቻለ የነፍስ ጥቅም ወይም ትርፍ የምናገኝበት ስለሆነ በአዋጅ ፆም ላይ ተደርቦ ሊሰጥ አይገባም። ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ ጥያቄዎች ባስተላለፍነው መልዕክት ተጨማሪ ግንዛቤ ያገኙ ዘንድ ከዚህ በታች አያይዘን ልከንልዎታል።
 
ቀርቦ የነበረው ጥያቄ#1፦ ንስሃ ገብተን ቀኖና ሲሰጠን የምንጸልየው ጸሎት ምን ምን ናቸው ስንሰግድስ ምን ምን እያልን ነው የምንሰግደው ብትነግሩኝ ለምታደርጉልኝ መንፈሳዊ ትምህርት በቅድሚያ እግዚያብሔር ይስጥልኝ።
 
የሰጠነው ምላሽ፦ጠያቂያችን የንስኀ ቀኖና ተሰጥቶን ሱባኤ ስንገባ መፀለይ ያለብን፦ 1ኛ ሁሌም የመንፀልየው ፀሎታችን ወይም ሁል ግዜ በዘወትር የምንፀልየውን ፆሎት ሳናቋርጥ ልንፀልይ ይገባናል።   2ኛ አንድ ክርስቲያን ንስኀ ወደ ንስኀ አባቱ ቀርቦ ኀጢአቱን በተናዘዘ ጊዜ የንስኀ አባቱ ደግሞ በፍትሐነገስት ወይም በሐዋሪያት ቀኖና ወይም በአንቀፀ ንስኀ የታዘዘውን ስርዓት ተመልክተው እንደ ንስኀው ከባድነትና ቀላልነት አገናዝበው ንስኀውን ስለሚሰጡ በዚያ በአንቀፀ ንስኀ ላይ ማንኛውም ንስኀ የተቀበለ ክርስቲያን ምን ማድረግ እንዳለበት ራሱ ስለሚመራና ስለሚያብራራ ሲሰግድ እና ሲፆምም አብሮ ማከናወን ያለበትን ስርዓት ንስኀ አባታችን በዝርዝር ሊነግሩን ይገባል። ነገር ግን አብዛኞቹ የንስኀ አባቶች እንዲህ አይነቶቹን ሂደቶች በጥልቀት ካለማየት ወይም የግንዛቤ ችግር ሆነ ለንስኀ ህይወትም ቦታ ካለመስጠት፥ እንዲሁ በልማድ ስለሚናዝዙ ምእመናን ሊቸገሩ እንደሚችሉ ስለሚታወቅ፥ ጠያቂያችን ላነሱት ጥያቄ  እንደአጠቃላይ የምንሰጥዎ ምክር፦
 
-ፀሎትን በሚመለከት ከተለመደው ፀሎት ውጪ ጊዜ የሚሰጡት ከሆነ ፥ እንደ እወቀት ደረጃዎት መጠን መዝሙረ ዳዊትን፣ ወንጌለ ዮሐንስን፣ ድርሳናትን እና ስለ ንስኀ ትምህርት የሚሰጡ መፃህፍትን በተጨመሪ ማንበብና መፀለይ ይቻላል።
 
-ስግደትን በሚመለከት ደግሞ ሲሰግዱ በፊትዎ መስቀል ወይም ቅዱሳን ስዕላት ወይም ወንጌል በፊትዎ አድርገው በትዕምርተ መስቀል እያማተቡ ጉልበትዎትን እና ግንባርዎትን መሬት እያስነኩ መስገድ እንደሚገባ ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
 
ቀርቦ የነበረው ጥያቄ#2 ፦ አብዛኛዎቻችን ንስኀ የምንገባው አፃማትን አስታከን ነው። ይህ ትክክል ነው ወይ? ማለቴ ንስኀ ስንገባ የሚሰጠንን ቀኖና ለምሳሌ ፆም ስግገደት የመሳሰሉት ከመደበኛ አፅዋማት ጋር አብሮ ቀኖናውን መፈፀም ይፈቀዳል ወይ?
 
ያስተላለፍነው ምላሽ፦ ጠያቂያችን ንስኀ ራሱን የቻለ የጾም፣ የፀሎት እና የስግደት ጊዜ ስለሚያስፈልገው ከመደበኛ የቀኖና አፇማት ጋር መሆን አይኖርበትም። ምናልባት የንስኀውን አይነት በመረዳት አንቀፀ ንስኀ በሚያዘው መሰረት የሚሰጠው የንስኀ አይነት ቀላል ሆኖ ከተገኘ ንስኀውን የሚያናዝዙ አባቶች የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል እንጂ የንስኀ ጊዜ ግን ከላይ እንደገለፅነው ራሱን የቻለ ከመደበኛ ፆም ውጪ ባለ ጊዜ መሆን ይገባዋል።
 ጠያቂያችን፤ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበአል አከባበር መሰረት ሰንበትን የምናከብረው ከሥጋ ስራ እርቀን፥ የእግዚአብሔርን ስራ በመስራት ዘለዓለማዊ በረከት ለማግኘት፥  በሥጋችን እና በምድራዊ ህይወታችን ለነፍሳችን ደግሞ ዘለዓለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ የምንችልበትን ቅዱስ ስራ እየሰራን ማለትም በእለተ ሰንበት እናስቀድሳለን፣ እንቆርባለን፣ እንፀልያለን፣ ምፅዋት እንሰጣለን፣ የታመመ እንጠይቃለን፣ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ስራ እንሰራባታለን ፣ በእስር ቤት ያሉትን እንጎበኛለን፣ የሞቱ እንቀብራለን፣ በአጠቃላይ እነዚህን እና የመሳሰሉትን በጎ ስራ፤ በመስራት ነው የምናከብረው እንጂ እንደ አህዛብ ልማድ እጃችንን እና እግራችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን በመዋል ለማክበር አይደለም። በስንፍና ከምናሳልፈው አገልግሎት እግዚአብሔር አይከብርም። 
 
ስለዚህ ጠያቂያችን እርስዎ ካሉበት የስራ ፀባይ አንፃር ባለው ችግር ውስጥ እደነገሩን ከእርስዎ አቅም በላይ በሆነ ጉዳይ በዚህ እለት በአሉን ማክበር ካልቻሉ፤ ከሁሉ በማስቀደም እግዚአብሔር የእርስዎን የውስጥ ችግር ስለሚያውቀው ወደፊት በእግዚአብሔር ቤት ተገኝተው ተገቢውን ሁሉ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያከናውኑ እግዚአብሔር እንዲረዳዎት እየፀለዩ አሁን ላይ ግን ከአቅም በላይ የሆነ የስራ ጉዳይ እንደአጋጠመዎት ስለተረዳን እርስዎም ችግርዎትን እግዚአብሔር እንደሚረዳ አምነው በስራዎት እንዲቀጥሉ እንመክራለን።