ስለ ንስሐ

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ንስሐ አገልግሎት መሰረታዊ ትምህርት

ስለ አበነፍስ (ስለ ንስሐ አባት) አገልግሎት በሚመለከት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መርጦ የመንጋው እረኞች እንዲሆኑ ለሾማቸው ቅዱሳን ሐዋርያት በአንብሮተ እድ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ከኃጢአት ማሰሪያ የሚፈታ፣ አመፀኞችን የሚያሥሩበት፤ ቦታ እና ጊዜ የማይወስነው ረቂቅ ስልጣን ነው። ስልጣኑን የሰጣቸውም ራሱ ባለቤቱ “የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለው በምድር የምታሥረው ሁሉ በሰማያት የታሠረ ይሆናል በምድር የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” ማቴ 16:19 “እውነት እላችኋለው በምድር የምታሥሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል” በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ እና ለሁሉም ሐዋርያት አስተምሯቸዋል። የክህነቱ ስልጣን ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነው፤ ከምድራዊ ስልጣን ጋር የማይነፃፀርና ከፈጣሪ በስተቀር ማንም የማይሽረው መሆኑን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ገልጾላቸዋል።

ስለክህነት በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ያለውን አመጣጥና አገልግሎት ወደፊት በስፋት የምንገልጸው ሆኖ፤ አሁን ግን በአጭሩ በንስሐ አባት አያያዝ ዙሪያ ጥያቄ ላላችሁ የምናስተላልፈው መልእክት፤ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ክህነት የእግዚአብሔር ስጦታ ከሆነና የስልጣኑ አገልግሎትም ቦታ እና ጊዜ የማይወስነው ከሆነ፤ በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች ሁሉ በሚኖሩበት ከተማ /አካባቢ/ ቤተክርስትያንና አባቶች ካህናት በቅርብ ከሌሉ፤ በዕውቀታቸውና በሕይወታቸው አስተምረውና መክረው ወደ ንስሐ ሕይወት በማቅረብ በክርስቲያናዊ ስነምግባር እና በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ እንድትኖሩ የሚጠብቋችሁን አባቶች ከየትኛውም ክፍለ ዓለም መርጦ መያዝ ይቻላል። ምክንያቱም በአካባቢያችን በጠዋትና በማታ በቅርበት የንስሐ አባት የሚሆንዎ ካህን ከሌለ ዓለጠባቂና ዓለአስተማሪ አንድም ቀን መኖር ስለማይገባን በቅርብ ከእኛ ጋር በአካለ ስጋ ሆኖ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጠን አባት ከሌለ፤ ያለብንን የውስጥ ችግር ከምንም በላይ እሱ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ስለሚያውቀው በሃይማኖታቸውና በስነምግባራቸው የተመሰከረላቸውን አባቶች በማነጋገር የንስሐ አባት ማድረግ ይገባናል።

የአንድ እውነተኛ የንስሐ አባት ለንስሐ ልጆቹ ማስተማር የሚገባው እንዲጾሙ፣ እንዲፀልዩ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲማሩ፣ እንዲያስቀድሱ፣ ንስሐ እንዲገቡ፣ የክስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ (እንዲቆርቡ) አሥራት በኩራት እንዲከፍሉ፣ ለተቸገሩ ወገኖች የርሕራሄ ሥራ እንዲያደርጉ በአጠቃላይ በተዋሕዶ ሃይማኖታቸውና በክርስትያናዊ ሕይወታቸው ጸንትው እንዲኖሩ ስለሆነ፤ ይህ ደግሞ ከየትም ቦታ ሆኖ ዘመኑ በአስገኘው ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ከንስሐ አባቱ ጋር በየቀኑ መገናኘት ስለሚቻል የተፈለገውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት እንችላለን ማለት ነው። ከባዱ ፈተና ግን በአንዳንድ አጉል አማካሪ ግራ ተጋብተን የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ ከሆኑት አባቶች ተለይተን መኖር ግን በዱርና በሜዳ ያለእረኛ እንደተሰማራ መንጋ እንሆናለን። እንደሚታወቀው እረኛ የሌለው መንጋ በተኩላና በአውሬ ይበላል። ማንኛውም ስጋዊ ሀብታችን ጠባቂና ተቆጣጣሪ ከሌለው በነጣቂዎችና በወንበዴዎች እንደሚዘረፍ ሁሉ በጧት በማታ በአባትነት የሚጠብቁን አበነፍስ (ንስሐ አባት) ከሌለን ከምንም በላይ ክፉና ጨካኝ የሆነው ዲያብሎስ ነፍሣችንን የማይገባትን የክፋትና የአመጽ ሥራ ስለሚያሠራት ያለጠባቂና ያለመካሪ አባት አንድ ቀን መኖር የለብንም።

“ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም” (ሉቃ 5፡32)

ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች​

ንስሓ ማለት ምን ማለት ነው?
 
ንስሓ የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን በአማርኛ ትርጓሜው ወይም የቃሉ ፍች እና ማብራሪያ፦ ማዘን፣ መፀፀት፣ መቆጨት፣ መቀጣት፣ ቀኖና መቀበል፣ ስለተሰራው ኀጢአት ካሳ መክፈል።፣ የሰሩትን በደል እና ጥፋት ማመን፣  አና በአጠቃላይ ማንኛውም ክርስቲያን ስለሰራው ኀጢአት ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው ሲመለስ የሚቀበለውን የቀኖና ንስሐ ያመለክታል።
 
አንድ ክርስቲያን ንስሓ ለመግባት ተዘጋጀ ወይም ንስሓ ገባ ሲባል ማመኑን፣ መፀፀቱን፣ ወደ እግዚአብሔር መመለሱን፣ ክፉ ፀባዩን መተዉን፣ ከጥፋት ስራ መቆጠቡን እና መታረሙን የምናውቅበት መንገድ ነው። በተጨማሪም ንስሓ ማለት አንድ ክርስቲያን በሰራው ጥፋት በፈፀመው ኅጢያት እና ባደረገው ስህተት ሰለተፀፀተ እና ስለተቆረቆረ ሌላ ጊዜ ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላውን እና ሰማያዊ የዘላለም ህይወት ሊያሳጣው የሚችል ኀጢያትን ላለመፈፀም የመጨረሻ ውሳኔ የሚደርስበት የመደምደሚያ ሃሳብ ነው።
 
በአጠቃላይ ንስሓ የቃሉ ማብራሪያ እና የጽንሰ ሃሳቡ ትንታኔ ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ሲሆን፤ የንስሓን አስፈላጊነት በሚያምኑ ክርስቲያኖች ዘንድ የንስሓ ህይወት ያለውን ጠቀሜታ ስንመለከት የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ይዞ እናገኘዋለን።
 
1/ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ማስረጃ፦
 
–       የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ሚልክያስ እንደተናገረው  “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርአቴ ፈቀቅ ብላችኋል። ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሣለሁ” በማለት ከእግዚአብሔር ሕግ በመተላለፍና ትእዛዙን በማፍረስ ለበደሉት ሰወች የንስሓ ጥሪ እንዳቀረበላቸው እንመለከታለን።(ሚል 3፥7)
 
–       ጠቢቡ ሰለሞን “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፣ የሚናዘዝባት እና የሚተዋት ግን ምህረትን ያገኛል” በማለት ስለ ኀጢአት ግልፀኝነትና ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚሆንልን ምህረት ተናግሯል። (ምሳሌ 28፥13)
 
–       ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ሲናገር በኀጢአት ወድቆ በንስሓ ስለተመለሰው  የሰው ልጅ ኅጥያቱን ተመራምሮ እና በልቡ ተጸጽቶ ወደ ሰማያዊ አምላክ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ውሳኔ ላይ ቢደርስ የምህረት እና የቸርነት አባት እግዚአብሔርም በደስታ እና በፍቅር እንዴት እንደሚቀበለው  ተመዝግቦ እናገኛለን (ሉቃ 15፥1824)
 
2/ ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅን ያመለክታል፦
 
የሰው ልጅ በ 40 እና በ 80 ቀን በጥምቀት ያገኘውን የእግዚአብሔር ልጅነት በገቢረ ኀጢአት ወይም ኀጢአት በመስራት ከእግዚአብሔር ጋር የልጅነት ክብሩን ያጣል ከፈጣሪው ጋርም ይጣላል ለክርስቲያናዊ ህይወቱ የነበረውን ክብርና ቅድስና ያጎድፋል። በእግዚአብሔር እና በእሱ መካከልም የጥል ግድግዳ ይፈጥራል፤ በመሆኑም ንስሓ የተባለውን የበደል ካሣ በመክፈል ከፈጣሪ ጋር እና ከራሱ ጋር መታረቅ ይቻላል።
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጰውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በፃፈላቸው መልእክቱ ስለዚህ ሲናገር “እንግዲህ እግዚአብሔር ለእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን እንለምናችኋለን” ሲል ተናግሯል። (2ቆሮ5፥20) በመሠረቱ ንስሓ መግባት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰዎች ልቦና እንደሚያድር የምናውቅበት መንገድ ነው። የሰው ልጅ ኀጢአትና በደሉን ትቶ በንስሓ እንደገና ተቀድሶ ከህይወቱ ካላስወገደ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እና የመንግስቱ ወራሽ ሊሆን ስለማይችል ከሰማያዊ አባቱ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ለመሆን መላ ህይወቱን ማዘጋጀት አለበት። ( 2ኛ ቆሮ 5፥19)
 
3/ ንስሓ ክርስቲያን ከኀጢአት እንቅልፉ የሚነቃበት ደወል ነው፦
 
ክርስቲያን ኀጢአትን በሰራ ጊዜ በመንፈሳዊ ህይወቱ እና በክርስቲያናዊ ስነምግባሩ ማንቀላፋቱን የምናስተውልበት ምልክት ነው። “የሰው ልጅ ኅጢአተኛ መሆን ሲጀምር በክርስቲያናዊ ህይወቱ የነበሩት እሴቶች ሁሉ ከሱ ጨርሰው ስለሚጠፉ ኀጢአት የሚያሰራው የክፉ መንፈስ ባለቤት የሆነው ሰይጣን በኀጢአት የማደንዘዣ መርፌ አይምሮውን ስለሚያሣጣው የቆመበትን ስፍራ  እና የወደቀበትን ጉድጓድ ፈፅሞ ሊያውቀው አይችልምና በንስሓ ደወል እንድንቀሰቅሰው ያስፈልጋል።
 
በትምህርቱ የአለም ብርሃን የተባለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በፃፈላቸው መልእክቱ ላይ “ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ” በማለት ከኀጢአት እንቅልፍ ነቅተው ንስሓ እንዲገቡ አስረግጦ መክሯቸዋል (ሮሜ 13፥11)። የሰው ልጅ በኀጢአት አንቀላፍቶ የተኛበት ዘመን ይበቃኛል ብሎ በንስሓ ህይወት ወደ ቀደመው ማንነቱ ለመመለስ የሚችልበት የጽድቅ መንገዱ ሰፊ እና ቀና ጉዞ ስለሆነ በቤተክርስቲያን አባቶች ምክር እና ተግሳጽ ወደ ቀደመው ክብሩ መመለስ ይገባዋል (ሉቃ 15፥7)
 
4/ ንስሓ በኀጢአት ምክንያት ወድቆ የነበረ ክርስቲያን ወደ መንፈሣዊ ህይወቱ መመለሱን ያመለክታል፦
 
የኀጢአት ደዌ ያደረበት ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በንስሓ ህክምና ፈውስ ካላገኘ በመጨረሻ የሚገጥመው እድል የነፍስ ሞት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስም ያበራልሃልና ሲል ተናግሯል (ኤፌ 5፤14)። ወንጌላዊ ቅዱስ ዩሃንስም “እኛ ……ከሞት ወደ ህይወት እንደተሻገርን እናውቃለን። በማለት ስለ ህይወት መንገድ መስክሯል።
 
ሐዋርያው ቅዱስ ያእቆብ በመልእክቱ ላይ “ኅጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኀጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ” ሲል ኀጢአተኛ መሆን በነፍስ መሞት እንደሆነ በንስሓ መመለስ ደግሞ በህይወት መኖር እንደሆነ መስክሯል። (ያዕ 5፤20)
 
ስለሆነም ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ከርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ማወቅ እና መረዳት ያለበት በንስሓ ህይወት ወደ እግዚአብሔር መመለስ የህይወት ትንሳኤ ማግኘት ሲሆን ፀፀት በሌለው ኀጢአት ፀንቶ መኖር ደግሞ በመንፈሣዊ ህይወት የነፍስ ሞት መሆኑን ነው።
 
5/ ንስሓ ከሃጢያታችን እድፍ የምንታጠብበት ንጹህ ውሃ መሆኑን እና ጽድቅ እና ኩነኔን ለይተን የምናውቅበት አዲስ ልብ ነው።
 
ክርስቲያን ሁሉ በኀጢአት እድፍ የጎሰቆለውን መንፈሣዊ ማንነቱን ንስሓ በተባለ ንፁህ ውሃ ታጥቦ በጠራ ጊዜ ወደ ቀደመው ውበቱ እና ክብሩ ይመለሳል።
 
ጽድቅ እና ኩነኔን፣ ህይወት እና ሞትን፣ ብርሃን እና ጨለማን፣ ገነት እና ሲኦልን፣ ታቦት እና ጣኦትን፣ መንግስተ ሰማያትን እና ገሃነመ እሳትን፣ እግዚአብሔርን እና ሰይጣንን (ቤልሆር) ለይተን ለማወቅ እና ለማስተዋል የምንችልበትን ንጹህ የሆነ የንስሓ ልቦና እግዚአብሔር እንዲሰጠን መለመን ያስፈልጋል። (2ኛ ቆሮ 6፥14-16)
 
የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ሕዝቅኤልም ስለዚህ ሲናገር “ጥሩ ውሃንም ረጭባችኋለው እናንተም ትጠራላችሁ፣ ከርክሠታችሁ ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለው አዲስ ልብ ሰጣችኋለሁ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከስጋችሁ አወጣለሁ የስጋንም ልብ እሰጣችኋለው መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትዕዛዜም አስኬዳችኋለው ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ” በማለት አስተምሯል። (ሕዝ 36፥25-27)
 
6/ ንስሓ የዲያቢሎስን ስራ በመቃወም ከኀጢአት ባርነት ነፃ የሚወጣበት መንገድ ነው። 
 
ክርስቲያን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የክርስትና ስሙን ከተቀበለበት ቀን ጀምሮ ከዲያብሎስ አገዛዝ እና ከኀጢአት ባርነት ነፃ መውጣቱን ያረጋገጠበት ልዩ ማህተሙ ነው። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ጥንተ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በክርስቶስ የመስቀል ሞት ዳግም ያገኘነውን ክብራችንን ለማስጣል ዘወትር የምንወድቅበት የኅጥያት ወጥመድ ከፊታችን ለማጥመድ በያዘን ጊዜ በንስሓ ህይወት የተያዝንበት የኀጢአት ወጥመድን ሰባብረን ለማምለጥ እንድንችል ለንስሓ የተዘጋጀ ልቦና ያስፈልገናል። ዲያብሎስ ያደረበት ሰው ሁል ጊዜም የኀጢአት ባርያ ነው። 
 
መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኀጢአትን የሚያደርግ ሁሉ የኀጢአት ባርያ ነው፣ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም…. እንግዲህ ልጅ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። በማለት ከዚህ አለም የኀጢአት ባርነት ነፃ መውጣት የሚቻልበት ዋናው መንገድ ለንስሓ የተዘጋጀ እና የወሰነ ንፁህ ልቦና መሆኑን አስተምሯል። ከምንም በላይ ንስሓ ለመግባት የተዘጋጀ እና በቁርጠኝነት ወስኖ ኀጢአትን የተወ ሰው ለእውነትም ከኀጢአት ባርነት ነፃ እንደወጣ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛምርቴ ናችሁ እውነትንም ታቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት አስተምሯል።(ዩሐ 8፥32)። “እንግዲህ የዲያብሎስን ስራ በመቃወም ለእግዚአብሔር መታዘዝ እና መገዛት ያስፈልጋል” (ያዕ 4፥7)
 

ጌታችን በወንጌሉ ካህናትን “እናንተ የአለም ብርሃን  ናችሁ”  ማቴ 5 -14 ይላቸዋልና ከርኩሰት አረንቁዋ ከጨለማውና  ከኀጢአት ሥራ ሁሌ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚመሩንና ኀጢአትን ጠልተን በበጎ ምግባር እንድንኖር መንገዱን የሚመሩን ናቸው፡፡

 የንስሐ አባት ማለት ምስጢረኛችን በመንፈሳዊም በሥጋዊም ህይወታችን የቅርብ አማካሪዎቻያችን ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሲራክ  “ብዙ  ሰዎች ወዳጆች  ይሁኑህ  ከብዙዎች  አንዱ ምክርህን  የምትነግረው  ከልቡናህ  ጋር አንድ  ይሁን፡፡”  ሲራክ  6-6  በማለት ይናገራል፡፡ ይህ ማለት    ምእመናን ስለ  ሃይማኖትና  በጎ ምግባር የሚያስተምሩዋቸው  ብዙ  ካህናት ሊኖሩዋቸው  ቢችሉም  ከብዙዎች  አንዱ ግን  ንስሃቸውን  የሚናዘዙለት መምህረ ንስሃ  ሊሆናቸው እንደሚገባ ያስረዳልና መምህረ ንስሕ ማለት ምስጢረኛና አማካሪ ማለት ነው ፡፡

አበ ነፍስ ማለት ኃጢአታችንን የምንናዘዝለት ማለት ነው፡፡ ኀጢታችንን ለካህን ስንናዘዝ ለእግዚአብሄር መናዘዝና ክብር መስጠት ነው፡፡ ኢያሱ እንዳለ “ልጄ ሆይ ለአምላክ ከብርን ስጥ፡ ለእርሱም ተናዘዝ፡ ያደረግከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ”  ኢያሱ 7-19፡፡ ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ለእግዚአብሄር ክብር መስጠት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ አበዉ ካሀናትም ኑዛዜን ከተቀበሉ በኋላ “እግዚአብሔር ይፍታህ” እንጂ  ”ፈትቼሃለሁ ” አይሉም፡፡ ኀጢአተዘችንን በነሱ ፊት ብንናገርም ሰሚዉም ሆነ በእነርሱ እጅ ስርየተ ኀጪአት  የሚሰጠዉ እርሱ ባለቤቱ ስለሆነ ነው፡፡  በመሆኑም አበ ነፍስ ማለት ኀጢአታችንን በዝርዝር ምንም የሚያስፈራ ኀጢአት ቢኖረንም እያሰታወስን አንዳች ሳናስቀርና ሳንጠራጠር  በዝርዝር የምንነግረው የእግዚአብሔር አይን ነው ማለት ነው፡፡ 

የንስሐ አባት/አበ ነፍስ ወይም መምህረ ንስሐ ማለት የንስሐ   ልጆቹ ትክክለኛውን ዓላማ ይዘው የንስሐ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ በጎ መሪ ማለት ነው፡፡ 

መምህረ ንስሐ ማለት ልጆቹን መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያስተምርና የልጁቹን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚከታተልና ስለ በጎቹ የሚጨነቅ እረኛ ማለት ነው፡፡

የንስሐ አባት ማለት ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ፣ ምግባራቸውን እንደይስቱ በርካቶችም ለጠንቋዮችና ለአሳቾች ሰለባ እንዳይሆኑ የጠራውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከምንጩ ማስጎንጨት የሚችልና እሄንንም የማድረግ ግዴታ ያለበት ባላደራ ማለት  ነው፡፡ 

የንስሐ አባት ማለት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ያለመታከት የሚተጋ ማለት ነው፡፡ የንስሐ አባት ልጆቹ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ሁሌም መጐትጐትና መቀስቀስ አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በኃይል፣ በማጣደፍ ወይም በማስፈራት አይደለም፡፡ ካህኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወኪል፣ የእግዚአብሔር አደረኛ ስለኾነ ሁሌም ማትጋት፣ መጐትጐት፣ መቀስቀስ ይጠበቅበታል፡፡

የንስሐ አባት ለእያንዳንዱ ልጆቹ እንደየ አቅማቸውና እንደየሃይማኖት እውቀት መጠናቸውና እንደየ መንፈሳዊ እውቀታቸው አቻ እስከሚሆኑለት ለያይቶ በማስተማር ማብቃት አለበት፡፡

የንስሐ አባት ማለት በንስሐ ልጆቹ መካከል ፍጹም መቀራረብ እንዲኖር የሚያደርገ ነው፡፡ የንስሐ ልጆች ለብዙ ችግሮች የመፍትሔ አካል ኾነው እንዲያገለግሉ ዕድል ይሰጣልና፡፡ የተቸገሩትን ከመርዳት ዠምሮ አንዱ ለሌላው አርአያ ኾኖ በተግባር እስከማስተማር ድረስ ማድረግም የንስሐ አባት ድርሻ ነው፡፡ ይህ ማለት የአንድ ካህን ንስሐ ልጆች ከአንድ የሥጋ አባትና እናት የተወለዱ እህትማመቾች እና ወንድማማቾች ያህል ከዚያም በበለጠ ሁኔታ መቀራረብ አለባቸው ማለት ነው፡፡የንስሀ አባት ማለት ይህን የሚተገብር ማለት ነው፡፡

ከቊርባን በፊት ንስሐ ይቀድማልና፡፡ ሰው ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ ስለሌለ ጧት የሠራውን ለማታ፤ ማታ የሠራውን ለጧት ለመምህረ ንስሐው ነግሮ መምህረ ንስሐው ያዘዘውን ሠርቶ ሊቀበል ይገባዋልና ይህ ታላቅ ሀላፊነት የተጣለው ደግሞ በመምህረ ንስሀው ላይ ነው፡፡

 የንስሐ አባት ማለት ባለአደራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በበረኻ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ማን ነው?” ሉቃ.15 -5 ያለው፡፡ ካህናት ከእግዚአብሔር በአደራ እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ኹሉንም ሳይዘነጉ እያንዳንዱን በነፍስ ወከፍ ሊጠብቁና ሊያገለግሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡

የንስሐ አባት ከንስሐ ልጆቹ ጋር የሚፈጥረው ግላዊ ግንኙነት ከቤተሰባዊነት ያልተሻገረ ኾኖ ሲቀነጭርና እጅጉን ያነሰ ሲሆን ነው፡፡ ብዙ ካህናት ወደ ምእመናን ቤት መጥተው ሲያበቁ መስቀል ከማሳለምና ጠበል ከመርጨት ያለፈ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ካህናት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስቀመጠላቸው ከሥራቸው ኹሉ ቅድሚያውን ሰጥተው ማስተማር፣ መምከር፣ ኑዛዜን መቀበል፣ ማጽናናትና መገሰጽ ይገባቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የንስሐ ልጃቻቸውን በጥንቃቄ ይዘው ለሥጋ ወደሙ ማብቃት ግባቸው ስለኾነ ትኩረታቸው ኹሉ ወደዚኽ ዋነኛ የክህነት ዓላማቸው መሆን አለበት ፡፡ ይህም የካህኑ ትልቁ ሀላፊነት ነው፡፡

የንስሐ አባት የንስሐ ልጀቹን የቤተ ሰብ አባላት ቁትርና እያንዳንዱን በሚገባ ማወቅ አለበት፡፡

አንድ የንስሐ አባት ልጆቹንና አጠቃላይ ቤተሰቡን እያሰታወሰ አዘውትሮ ስለ ሁለንተናቸው መጠየቅ አለበት፡፡

የንስሐ አባት ከልጆቹ ጋር አብሮ በመጸለይ ጸሎትን ማለማመድ፤ ሆኖ በማሳየት እውነተኛ የአባትና የልጅ ፍቅርን  ማሳየት፤ በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በሥጋዊም ሕየዋታቸው መጨነቅ፤  ስራቸው እንዲባረክ አዘውትሮ፤መጸለይ በአጠቃላይ ልጆቹን በቅርበት መከታተል፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ተግባሩ እሄ ነው፡፡ 

የንስሐ አባት ይህን የድረ ገጻችንን አድራሻ በመጫን ይያዙ: https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/

 

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸው የክህነት ስልጣን ማሰር እና መፍታት የሚችሉበት ረቂቅ እና ሰማያዊ ስልጣንን ነው። ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባትም ሆነ ከመንግስተ ሰማያት ለመከልከል የሚያስችል ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው ስልጣንም ነው። ይህ ማለት ስልጣን ሁሉ የራሱ ገንዘብ የሆነው የባህርይ አምላክ እየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ሐዋርያት እና 72ቱን አርድእት ከዓለም መካከል መርጦ በሾማቸው ግዜ ኀጥያት ሰርተው በደል ፈጽመው ወደ ሐዋርያት ቀርበው በኀጢአታቸው ተጸጽተው የተናዘዙትን ኀጥያታቸውን የማስተሰረይ ስልጣን ስለተሰጣቸው ኀጥያታችሁ ይቅርላችሁ ያሏቸው ሁሉ የተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ኅጥያታቸው ሁሉ እንዲደመሰስ ያደርጋል።
 
በሰሩት ጥፋት ሳይጸጸቱ እና ከበደላቸው የማይመለሱትን ደግሞ በተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ሲፈርዱባቸው በስጋቸው ሞትና ልዩ ልዩ መቅሰፍት ይቀጣሉ ማለት ነው። 
 
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፦
 
–  ግያዝ የተባለው የነብዩ ኤልሳዕ ደቀመዝሙር ከመምህሩ ተሰውሮ ከለምጽ በሽታ ካዳነው ሶርያው ንጉስ ከንዕማን ላይ የማይገባውን ጥቅም በመውሰዱ ምክንያት ነብዩ ኤልሳዕ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ ግያዝን በለምጽ ደዌ አንደቀጣው እንመለከታለን። 2ኛ ነገስት 5፥20-27
 
–  ሐናንያ እና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች በሐዋርያት ፊት ያላቸውን የሀብታቸውን እኩሌታ ለእግዚአብሔር ሊሰጡ ቃል ከገቡ በኋላ ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን አታላችኋል ብሎ በተሰጠው የክህነት ስልጣኑ የሞት ቅጣት እንዲደርስባቸው አድርጓል። የሐዋ 5፥1-10
 
–  በጥንቆላ መንፈስ የሚኖር ሲሞን መሠሪ የተባለው ሰው ሐዋርያት እጅ በመጫን  የመንፈስ ቅዱስ ኅይል የሚሰሩትን አስደናቂ ሚስጥር ባየ ግዜ እንደእናንተ ይሄንን ታላቅ አስደናቂ ስራ ለመስራት እንድችል ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን ስልጣን በገንዘብ ሽጡልኝ ባላቸው ግዜ እድል ፋንታውን ከክፉዎች ጋር እንዲሆን እና የጥፋት ሰው አንደሆነ ረግመውታል። ዩሐ 8፥18-24
 
ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ማስረጃዎች የመንግሰተ ሰማያት መክፈቻ ለሐዋርያት ተሰጠ ሲባል በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት መንግስተ ሰማያት ማስገባት እንደሚችሉ እና የማይገባቸውን መከልከል የሚችሉ መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ የቤት ወይም የበር ቁልፍ መክፈቻና መዝጊያ ቁሳዊ ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማሰር መፍታት የሚለውም በዚህ አለም ላይ ሰው በፈጸመው ወንጀል የሚታሰርበት አግር ብረት ወይም ገመድ ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን ከላይ እንደገለጽነው በተሰጣቸው ረቂቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣን ኅጥያትን የማስተሰረይ፣ የኀጥያተኞችን ኅጥያት የመያዝ ፀጋ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይቻላል ወይ? ንስሐስ በስልክ ይሆናል ወይ?
 
ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ (አማኝ) የሆነ ክርስቲያን ለአካለ መጠን ከደረሰበት ግዜ ጀምሮ የንስሐ አባት መያዝ ክርስትያናዊ ግዴታው እንደሆነ በቤተክርስቲያን የቀኖና መጽሐፍ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን ኑሮዋቸውን ለማሸነፍና የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ሲሉ ቤተክርስቲያንና ካህናት አባቶች ወደማይገኙበት ክፍለ ዓለም በልዩ ልዩ ምክንያት ተበትነው እንደሚኖሩ ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ አገራችን ሳይቀር በረሃማና ጠረፋማ በሆነ አካባቢ እንዲሁም አህዛብ በሚበዛበት ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በመከራና በፈተና ግዜ የሚያጽናናቸውና የሚመክራቸው አባት ሊያገኙ አይችሉም። የሚጸልዩበት እና ፈጣሪያቸውን የሚማፀኑበት ቤተክርስትያንም አያገኙም።
 
ስለዚህ በቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ሰውን በነፍስ የማዳን ሥራ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ቤተክርስቲያንና አባቶች ካህናት በቅርብ የማይገኙበት ክፍለ ዓለም (አካበቢ) የሚኖሩ ማለትም በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በአረብ አገሮች እና በሌላውም ክፍለ አለም ሁሉ እየኖሩ የንስሐ አባት ለመያዝ ቢፈልጉ ከምንም በላይ እግዚአብሔር የኛን የውስጥ ችግር ያውቀዋልና አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ያለ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌለበት የንስሐ አባት እንዲኖረው በሃይማኖቱና በመንፈሳዊ ህይወቱ የመረጠውን ካህን እርቀት ሳይገድበው መያዝ ይችላል። ካለው ችግር አንፃርም በስልክ እና በሌላ መልእክት በመገናኘት መንፈሳዊ ትምህርት እና ከንስሐ አባት የሚሰጠውን የንስሃ ቀኖና  መቀበል ይችላል። ማንኛውንም በጎ ስራ ሁሉ አባቱ የሚመክሩትን እና የሚያዙትን ሁሉ በመፈፀም የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ስለሚችል የግድ በአካል ካላገኘኋቸው አብሬ በአንድ አጥቢያ ካልኖርኩኝ የንስሐ አባት መያዝ አልችልም በሚል ምክንያት ያለጠባቂ መኖር የለበትም።
 
ይህን በሚመለከትም ከዚህ በፊት ስለ ንስሐ አባት አያያዝ ጥያቄ ቀርቦ በአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እና በቤተክርስትያን መምህራን ንስሐ አባት በርቀት መያዝ እንደሚቻል በተደጋጋሚ ምላሽ የተሰጠበት ሃሳብ ስለሆነ ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲያሥሩና እንዲፈቱ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ጊዜና የቦታ ርቀት የማይወስነው ስለሆነ ፤ በአካባቢው አባት የሚሆን ካህን ከጠፋ ያለጠባቂ ብንኖር ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍሳችንን እንዳይነጥቃት የንስሐ አባት በርቀት መያዝ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ምእመናን መጨናነቅ እንደማያስፈልጋችሁ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
 
ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር አጋዥነትና ጠባቂነት ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
ንስሐ ለመግባት ፈራሁ ፍርሐቴን ላለመፍራት ምን ላድርግ? ብለው ለጠየቁን አባል የሚከተለውን መልስ ጽፈንልዎታል።
ከእውነተኛ ሃይማኖትና ምግባር ስንርቅ የንስሐ ህይወታችን ጨርሶ ይቀጭጫል። ያኔ ደግሞ በሰራነው ኀጥያት (ጥፋት) ነፍሳችን ፈፅሞ ትቃተታለች ትጨነቃለችም። ስጋችን ምድራዊ የሆነውን የስጋ ስራ ለመስራት ነፍሳችን ደግሞ ሰማያዊ የሆነውን የፅድቅ ስራ ለመስራት ለኛ ግልፅ ሆኖ በማይታወቅና በማንረዳው ሁኔታ ሁለቱም ህይወታችንን የጦር አውድማ ሲያደርጓት በኛ ላይ የፍርሃት መንፈስ ይነግስብናል። ከጥፋታችን ተመልሰን ንስሐ እንዳንገባ ደግሞ የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው እና የእኛን ፅናት የማይፈልገው ሰይጣንም ግራ እንዲገባን እና የፍርሃቶቻችን ምክንያቶች እንዲበዙ ያባብስብናል። ስለዚህ፤ ጠያቂያችን ለዚህ ችግርዎ የምንመክርዎት የሰይጣን ውግያ ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ የፍርሃት አምላክ ሳይሆን የፍቅርና የሰላም አምላክ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወምዎትን ክፉ መንፈስ እንደምንም ታገሉት። የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ በአካባቢዎ ወደመረጥንልዎ የንስሐ አባት ከድረገፃችን ያገኛሉና ቀርበው በማማከር የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለው ቢያምኑም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና ፍርሃቶትን አርቀው ወደ ይቅር ባይ አምላክ ይቅረቡ በማለት ምክሬን እለግሳለሁ። የበለጠ መንፈሳዊ ምክር እንድንሰጥዎ ከፈለጉ በውስጥ መስመር ያነጋግሩን፤ የደረሱበትንም ሂደት ይግለፁልን። ለሁሉም ነገር ወላዲት አምላክ ድንግል ማርያም በአማላጅነትዋ ታግዝዎ።
 
መጀመሪያ ንስሐ አባት ለመቀየር ያሰቡበት መንገድ መታወቅ አለበት ወይም ደግሞ ግልፅ መሆን አለበት። ምክንያቱ የቦታ ርቀት ከሆነ፣ ወይም ግዜ ሰጥተው የማያስተምሩ፣ የማይመክሩ ከሆነ፣ ዘወትር ክትትል እያደረጉ የማይጠብቅዎ ከሆነና ይሄን በመሰለ በቂ ምክንያት መቀየር ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ግን ስላልፈለግኩኝ በሚል ሰበብ እንደ ምድራዊ ፍላጎት መንፈሳዊ አባትን ብዙም መቀያየሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንመክርዎታለን። በበቂ ምከንያት አባት ተሰናብቶ ሌላ ይመክሩኛል፣ ያስተምሩኛል፣ በሃይማኖት እና በስነምግባር ያበረቱኛል ብለው ያሰቡትን አባት በማነጋገር በቤተክርስቲያን ስርአት መሠረት አባት ማድረግ ይችላሉ። ከንስሐ አባትዎ እንዴት እነደሚሰናበቱና እንዴት ሌላ ንስሐ አባት እንደሚይዙ የንስሐ አባቶችን እንጂ እርስዎን ስለማይመለከትዎ አያሳስብዎትም።
 
ዝሙት ምንድነው?
ውድ የዮሐንስ ንስሐ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላቶቻችን፤ ስለ ዝሙት ንስኅ መግባት አስፈላጊ መሆኑን አንድ አባላችን ከዚህ በታች ባቀረቡልን ጥያቄ መነሻነት የቀረበ አጭር ትምህርት ስለሆነ ሁላችሁም እንድትከታተሉት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።
👉ጥያቄው፦ (1) ንሰሐ ሰንገባ ማለትም የሰራነውን ስራ ለካህኑ ስንናዘዝ፤ አሁን ለምሳሌ ከብዙ ስዉ ዝሙት ከፈጸምን ከብዙ ስዉ ከሰረቅን ምን ብለንነው የምንናዘዘው? ዝሙት ፈፀሜያለሁ፡አመንዝሬአለው፡ብለን ነው? ወይስ? ቢብራራልኝ።
(2) ንስሐ አባት አለኝ ግን ንስሐ ለመግባት በጣም እፈራለው የንስሓ አባቴን መንገድ ላይ ሳያቸው በጣም እፈራለው ፤ምንላድረግ? ደግምም፡ንስኀ መግባት እፈልጋለው።
መልስ ፦ ንስሓ አባት የነፍስ ሃኪም ነው፥ ስለሆነም አንድ ምእመን ድካመ ስጋ ቢያገኘው የሰራውን ኀጢአት በጥቅሉ ሳይሆን በዝርዝር ማስረዳት አለበት። በቀላሉ ዝሙት ሰርቻለው ብሎ የሚተወው አይደለም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን በዝርዝር ማስረዳት አለበት፤ ካህኑም ወይም የንስሓ አባቱም በዝርዝር መጠየቅ አለበት። ምክንያቱም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለእያንዳንዱ ጥፋታችንና በደላችን ወደ መምሕረ ንስኀችን ቀርበን ኀጥያታችንን ስንናዘዝ ባጠፋነው ደረጃ ንስኀ መቀበል እንዳለብን በቀኖና ቤተክርስቲያን ተደንግጓልና።
ንስኀ የማንኛውንም ምእመን ቁስለ ነፍስ የሚፈውስ መንፈሳዊ መድኃኒት ነው። ካህንም ረቂቋን ነፍስ የሚያድን ሃኪም ነው። አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ያለ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር የለበትም።
ንስኀን ስናስብ ሁል ጊዜ ኀጢአታችንን ማሰባችን አይቀርም ። ምክንያቱም አንድ ሰው የሰራው ኀጢአት በእግዚአብሔር፣ በሌሎች ሰዎች፣ በራሱ ወይም በቤተክርስቲያን ላይ የተፈፀመ ጥፋት ነውና። ኀጢአት ባይኖር ንስሃ ባላስፈለገ ነበር ኀጢአቱንም በምንናስብበት ጊዜ ደግም ምንጩን፣ መነሻውንና የሚያባብሱትን ነገሮች መመርመራችን የግድ ነው፤ ይህም መንፈሳዊ ህይወታችንን በመፈተሽ እንድናሳድግ ይረዳናል። ወደፊትም ቀድመን ለመጠንቀቅ ማለትም አርቆ ለማጠር ይጠቅመናልና ለመናዘዝ ወደንስኀ አባታችን ስንቀርብ የሰራነውን ኀጢአት ወይም በህሊናችን ያለውን ጥፋት በዝርዝር ማስረዳት አለብን ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ወደዚህ ኀጢአት እንዳንመለስ የንስሓ አባታችን ትኩረት ሰጥቶ ሊያስተምረን ይገባል። እኛም በምክረ ካህን ዘመናችንን ሁሉ መኖር አለብን። “የካህኑን ምክሩንና ተግሳፁን አንሰቀቅ፤ ነፍስን የሚያድን ባለመድኃኒት ነውና” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ)
ስለዚህ ጠያቂያችን ማንኛውም ክርሰቲያን የፈፀመውን በደል ከእግዚአብሔር ቀጥሎ በሚስጥር ለንስሐ አባቱ መናገር አለበት፤ የሚሰጠውም ንሰሐ በጥፋቱ መጠን የሚቀበለው መሆን ይገባዋል። ለንሰሐ አባቶቻችን የምንደብቀው ወይም የምናስቀረው የኀጢአት ሚስጥርም የለንም። እንደምሳሌ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄድ ታማሚ ወይም ታካሚ የህመሙ አይነትና መጠን ተለይቶ በሀኪም ዘንድ ሳይረጋገጥ መድሀኒት አይታዘዝለትምና።
ዝሙት ምንድነው?
መልስ ፦
በመፅሐፍ ቅዱስ አስተምሮ ዝሙት ብዙ የኅጢአት አይነቶችን ያካትታል።
1/ ዝሙት ማለት ከህጋዊ ጋብቻ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የሥጋ ግንኙነት እና ሴሰኝነት ወይም አመንዝራነት ዝሙት ይባላል።
2/ ከእግዚአብሔር ያልተሰጠ እና ያልተፈቀደ ስልጣንን ወይም ሹመትን ሥጋዊ ክብርን አብዝቶ መፈለግና መመኘትም ዝሙት ይባላል።
3/ የወንድሙን ሀብት ወይም የሌላውን ሰው ማንኛውም ነገር አጥብቆ መፈለግም ዝሙት ይባላል።
4/ በአምልኮ ባእድ ወይም በአምልኮ ጣኦት ማመን ዝሙት ይባላል።
5/ ከአንዱ ወደ አንዱ ሃይማኖት እያሉ ሃይማኖት መቀያየርም ዝሙት ነው።
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዚህ መንፈሳዊ ፖሮግራም ተከታታዮቻችን አሁን በዚህኛው ትምህርታችን የምናስረዳችሁ ስለ ግብረስጋ ዝሙት በተመለከተ ይሆናል።
በ1ኛ ተራ ቁጥር እንደገለፅነው አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ወይም አንዲት ሴት ከሌላ ሰው ባል ጋር ወይም በህጋዊ ጋብቻ ጓደኛው ወይም ጓደኛዋ ካልሆነ ወንድ እና ካልሆነች ሴት ጋር የግብረ ስጋ ተራክቦ በማድረግም ሆነ በዝሙት ሃሳብ እየተቃጠሉ መኖር ዝሙተኝነትና አመንዝራነት ይባላል። ይህንን የዝሙት ስራ የሚሰሩ ሰዎች በስጋቸው ላይ የነገሰውን የዝሙት መንፈስ ያመጣባቸው ወይም ለዝሙቱ ሃሳብ መነሻ የሆናቸው ለሰው ልጅ ውድቀት ዘወትር በጥፋት መንገድ የቆመው ሰይጣን የሚያመጣው ጠንቅና መዘዝ ነው። የዝሙት ስራ በዚህ ደካማ ስጋችን የነገሰ ቢሆንም እንኳን ለነፍስ ብቻ ሳይሆን ለሥጋ ጤንነትም እንደማይጠቅም በዘመኑ በአለም አቀፍ ከዝሙት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ደዌም ወይም ወረርሽኝ በሰው ልጅን ሁሉ በጅምላ ሲገልና ሲጨፈጭፍ ተመልክተናል። ስለዚህ ዝሙት ነፍስንም ስጋንም የሚገል መሆኑን ከኛ በላይ ሌላ ማስረጃ አያስፈልገንም። እንግዲህ ዝሙት ወይም አመንዝራነት በቃላት ስንገልፀው የሚያሳፍር በተግባር ግን ሁሉ ሰው የሚፈልገውና በተግባር የሚያውለው የሁሉ ሰው ፈተና ነው። ይህ ሲባል አንዳችን ፃድቅ ወይም ከደሙ ንፁህ ሆነን ሌላው ደግሞ በዝሙት ኅጢአት ተጠያቂ በማድረግ ሌሎቹን በመተቸት እጃችንን የምንቀስርበት መንገድ አይደለም። የዝሙት ስራ በሰው ስነልቦና ውስጥ የሚያደርሰው ፈተና እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በሥጋ ያቃታቸው እንኳን በልባቸው ይመኙታል ባፋቸው ያወሩታል። ስለዚህ የዝሙት የመነሻው ምንጩ ሃሳብ ነው። ከሃሰብ ሲወጣ በአንደበት ይነገራል፣ ከአንደበት የተነገረው ደግሞ ጊዜ ሲገጥም በተግባር ይውላል። ስለዚህ የመጀመሪያው የዝሙት ድርጊት ፅንሱ ማሰብ ነው። ብዙዎቻችን በሃሳብና በአፍ በዝሙት ጉዳይ ላይ አብዝቶ የማይነጋገርና በሃሳቡ የማይቃጠል የለም ማለት ይቻላል።
እንግዲህ እንደ ቅዱስ መፅሐፍ የዝሙትን ዓይነት መመልከት ስለሚያስፈልግና ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “በዚህም በዘማዊና በኅጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላዕክት ጋር በመጣ ጊዜ በርሱ ያፍርበታል” (ማር 8፥37) በማለት የዝሙትን የኅጢአት ምክንያት ከአምልኮ ባዕድ ጋር በማያያዝ ተናግሮናል።
እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወይስ አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግስት እንዳይወርሱ አታውቁምን፥ አትሳቱ ሴሰኛዎች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሰሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ታድሳችኋል ፀድቃችኋል” በማለት የዝሙትን አይነት እና ዝሙት ከፍተኛ ኅጢአት መሆኑን ከዘረዘረ በኋላ እግዚአብሔርን በመፍራት ወደ ንስኅ ስንመለስ እንዴት ከኅጢአታችን እድፍ እንደምንታጠብና እንደምንቀደስ እንደምንፀድቅም አስተምሮናል። (ቀኛ ቆረ 6፥9፤10)
እንግዲህ ጠያቂችን ወዳቀረቡልን ጥያቄ ስንመለስ ዝሙት በስሙ ዝሙት ቢባልም በስራው ወይም በኅጢአት ሲገለፅ እጅግ ከፍተኛ የኅጢአት አይነት ከመሆኑም ሌላ የኅጢአቱም ብዛትና ደረጃም ይለያያል ምክንያቱም ከአንድ ሰው ጋር መዘሞትና ከብዙ ሰው ጋር መዘሞት ኅጢአትነቱ ልዩነት አለው። ስለዚህ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው ኅጢአቱን ለማድረግ ካላፈርነው ከብዙ ሰዎች ጋር የዝሙት ኅጢአት ፈፅሜያለሁ ብለን ለካህኑ ለመናገር የሚያሳፍረን ነገር የለም። ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለምናምነው ለንስኀ አባታችን የሰራነውን የዝሙት አይነት ዘርዝረን መናገር አስፈላጊ ነው፤ ይህም ለሰራነው ለእያንዳንዳንዱ የዝሙት ኅጢአት መጠን በአንቀፀ ንስኅ የሚሰጠን ቀኖና ስላለ ነው።
ስለዚህ አንዳንዶቻችን ለራሳችን ደህንነትም ሆነ ለማህበራዊ ግንኙነታችን ችግር የሚያመጣብን ቢሆን እንኳን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድና አስፈላጊም ከሆነ ወደሌላ ቅዱስ ቦታ ራቅ ብለን በመሄድ ለቤተክርስቲያን አባቶች መናዘዝና ንስኅችንን ማከናወን ይገባናል። እኛም በዚህ ፕሮግራም ሰዎች ይድኑ ዘንድ በተቻለን መጠን ስለናንተ የምናደርገው ጥረትና የምንሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ከዚህ የተነሳ ስለሆነ የእያንዳንዳንዳችሁንም የውስጥ ችግር በሃሳብም ቢሆን ስለምንረዳችሁ ምናልባት ለንስኅ አባት ለመንገር የሚያስፈራችሁና የሚያሰጋችሁ ነገር ካለ እኛንም በውስጥ መስመር አግኝታችሁ ብታሳውቁን መፍትሄ እንሰጣችኋለን።
አሁንም ጥያቄ ያቀረቡልን አባላችንና ለሁሉም ጠቃሚ ምክር እንድንሰጥበት የመነሻ ምክንያት ለመሆንና ትክክለኛም የንስኅ ህይወትን ከመፈለግ አንጻርም ስለሆነ ጠያቂያችንን እያደነቅን ወደፊትም በንስኅ ህይወት እንዲበረቱ ምክራችንን እየለገስን ሁላችሁም ኦርቶዶክሳዊያን የእግዚአብሔር ልጆች እንደ ሃይማኖት ወይም እንደ ክርስትና ስንኖር ዘወትር የማንረሳውና ቋሚ ተግባር የምናደርገው የንስኅ ህይወት እንደሆነ ታውቁ ዘንድ ይህንን አጭር የንስኅ መልዕክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል።
ስለ ንስሐ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ፦ https://yohannesneseha.org/ስለ-እኛ/
ንስሐ አባት ለመያዝ እዚህ ይጫኑ፦ https://yohannesneseha.org/የንስሐ-አባት-ገጽ/
 
በመሰረቱ ቀኖና ወይም ንስሐ የሚሰጠን በፈጸምነው ኅጥያት መጠን ተለክቶ ስለሆነ እያንዳንዱ ያጠፋነውን ጥፋት ከባድም ቢሆን ሳንፈራ፤ ቀላልም ቢሆን ሳንንቅ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለነፍሳችን እረኛ ላደረግነው ካህን መናገር እንዳለብን የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል። የኅጥያት ደረጃችን ተለይቶ ሲታወቅ ንስሐ የሚሰጡን አባቶችም በጥፋታችን መጠን ስለሆነ ንስሓ ላልገቡበት ኅጥያት እንደገና መናገርና ቀኖና መቀበል ያስፈልጎታል። 
 
ጠያቂያችን በመጀመሪያ ንሰሐ መግባት ወይም ኀጥያታችንን መናዘዝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መንፈሳዊ ትርጉሙን እና ሚስጥሩን በማስተዋል እና በትእግስት ሆነው መረዳት ያሰፈልጋል። እስካሁን ስለ ንሰሐ በ ዩሐንስ ንስሐ ድረ ገፃችን ላይ ባሰፈርናቸው ፅሁፎች በቂ የግንዛቤ መልእክት እንዳስተላለፍን ተስፋ እናደርጋለን። የእርሶም ጥያቄ እስካሁን ከፃፍናቸው መልእክቶች ጋር አብሮ የሚያያዝ ቢሆንም፤ ነገር ግን ለመረዳት መጠየቅ ከምንም በላይ የሚበረታታ በመሆኑ ለእውነተኛ ንስሐ ህሊናዎትን በማሳመን ተፀፅቻለው፣ ንሰሐ ገብቻለሁ፣ ኅጥያቴን ተናዝዣለሁ ብሎ ማመን የሚቻለው ለንስሐ የሚያበቁ መስፈርቶች እና ቅደም ተከተሎች ተጠብቀው ማለትም ፦
1/  የተሰራውን ኅጥያት ጥፋት መሆኑን ማመን ፣
2/  ስለተሰራው ጥፋት ከልብ ተፀፅቶ ንሰሐ ለመግባት መዘጋጀት፣
3/  ወደ ንስሐ አባታችን በማምራት ኅጥያታችንን በመናዘዝ ንስሐ መቀበል፣
4/  የተሰጠንን ንስሐ በአግባቡ መፈጸም፣
5/ ዳግመኛ ኅጥያት ላለመስራት በአባቶች ትምህርትና በመንፈሳዊ አገልግሎት መፅናት፣
6/  በፆም፣ በፀሎት፣ በስግደት ዘወትር በመትጋት መንፈሳዊ ህይወትን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር ያስፈልጋል።
በዚህ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ስንበረታ ከግዜ ወደ ግዜ መንፈሳዊ ፀጋችን እያደገ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ ጋር ሲሆን፤ ለንስሐ እንዳንዘጋጅና ከልባችን እንዳንፀፀት ዘወትር የሚቃወመንን እና ሠይጣናዊ አዚም የሚጥልብን ክፉ መንፈስ ከዛ ርቆ ለመሄድ ይገደዳል። በአጠቃላይ መንፈሳዊ ፀጋ በሂደት እና በመንፈሳዊ ተጋድሎ የሚመጣ እንጂ በአንድ ግዜ የማይሆን ስለሆነ አባቶቻችንን በማማከር መንፈሳዊ ጉዞዎን በትእግስት እንዲቀጥሉ እንመክራለን። ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያትም 2ኛ መናዘዝ አያስፈልግዎትም።
የንስሐ አባት ይዘው እንደማያውቁና ንሰሐ ለመግባት ፍላጎት እያለዎት ወደ እግዚአብሔርም ለመመለስ እያሰቡ በማያዉቁት ምክንያት የፈለጉትንና የተመኙትን የንስሐ ህይወት ለመፈፀም እንዳልቻሉ በመግለፅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለጠየቁን አባላችን የሚከተለውን የምክር አገልግሎት እንዲደርስዎት አድርገናል።
እንደ ቅዱስ መፅሐፍ አስተምሮ ማንኛውም ክርስቲያን በ 40 እና በ80 ቀን የእግዚአብሔር ልጅ ከሆኑበት ቀን ጀምሮ ከእግዚአብሔር ቤት እና ከምክረ ካህን መለየት እንደሌለባቸው ይደነግጋል። በመፅሐፍ ቅዱስም ሆነ በሌሎች የሃይማኖታችን መፃህፍት እንደምንረዳው የሰው ልጅ ለመኖር ለስጋው ምግብ ፣ ልብስ ፣ መጠለያ ወዘተ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለነፍሱም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጉታል። የነፍስ ምግብ ማለት በተዋህዶ ሃይማኖት ፀንቶ መኖር፣ ንሰሐ መግባት፣ መፆም፣ መፀለይ፣ መስገድ፣ ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ መሳለም፣ አስራት በኩራት ማውጣት፣ ለነዳያን ምፅዋት (ቸርነት) ማድረግ፣ በህመምና በእስር ቤት ያሉትን መጎብኘት፣ የእለት ማስቀደሻ ላጡ አብያተ ክርስቲያናት ንዋየ ቅዱሳት ማሟላት፣ የጌታን ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ባጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስነምግባር ተወስኖ መኖር የማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ ጠያቂያችን መንፈሳዊ ሆኖ መቀጠልን እየወደዱ ወደ አስቡት በጎ ምኞት እንዳይገቡ የሚያከላክልዎት የበጎ ነገር ጠላት የሆነው ክፉ መንፈስ እየተቃወምዎት በመሆኑ መሠረታዊ የአባቶች ምክር እና በፀሎት የሚሆን የንስሐ ጥሪ ያስፈልግዎታል። በፅሁፍ በሚደርስ መልእክት ብቻ  ከገቡበት ፈተና መውጣት ስለማይችሉ ስለእርስዎ በአባቶች በኩል ፀሎት ያስፈልግዎታል። እራስዎም የሚፀልዩበት የግል እና የስግደት ፆም ወዘተ ያስፈልግዎታል። ከፈተና ሊወጡ እንዲችሉ የሚያበቃዎትን የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል። 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‘ነገር ግን ወደ ንሰሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወድዶ ስለእናንተ ይታገሳል። በማለት እግዚአብሔር የእኛን ወደ ንስሐ መመለስ በትእግስት እንደሚጠብቀን አረጋግጧል። (ጴጥ 3፥9) 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በአቴንስ ከተማ ለሚኖሩ የግሪክ ሰዎች ።”እንግዲህ እግዚአብሔር የቀድሞውንስ ያለማወቅ ዘመን አሳልፎታል (በኀጥያት የመኖር ዘመንን) ፤ ዛሬ ግን በመላው አለም ንስሐ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዟል። (የሐዋ 17፥30)
ነብዩ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር የሰውን  ሞት የማይወድ እና ሰው ወደ ንስሐ መመለሱን የሚወድ መሆኑን ሲናገር ”ንሰሐ ግቡ፤ ኀጥያትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኀጥያታችሁ ሁሉ ተመለሱ። የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ። አዲስ ልብ እና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ ..ስለምን ትሞታላችሁ የሟችን ሞት አልፈቅድምና  ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ ተመለሱ እና በህይወት ኑሩ።  (ሕዝ 18፥30-32)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በበዓለ ሃምሰ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ሰወች ሁሉ ዘለአለማዊ ህይወት እንዲቀርቡ የንስሐ ጥሪ ሲያቀብላቸዉ ”እንግዲህ  ከጌታ ፊት የመፅናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ …ኀጥያታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንሰሐ ግቡ ተመለሱም” በማለት አስተምሯል። (የሐዋ 3፥19-20)
ነብዩ ሚልክያስም “ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት ሰው በንሰሐ ሲመለሰ እግዚአብሔርም ይቅር እንደሚል ተናግሯል። (ሚል 3፥7)
ነብዩ እዩኤልም ” አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍፁም ልባችሁ በፆም በለቅሶና  በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ ልባችሁን  እንጂ ልብሳችኹን አትቅደዱ መሓሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔር ፤ ቁጣው የዘገየ ምህረቱም የበዛ ለክፋትም የተፀፀተ ነዉና ወደ እርሱ ተመለሱ” በማለት  የእግዚአብሔርን መሓሪነት እና ቸርነት ይቅር ባይነትንም አስተምሯል። 
ብርሃናተ አለም ቅዱስ ጳውሎስም የሰው ልጅ ከጥፋቱ ተፀፅቶ ወደ ንሰሐ ህይወት እንዳይመለስና ለማድረግ የፈለገዉን በጎ ስራ እንዳይፈፅም ርኩስ መንፈስ እንዴት እንደሚቃወመው ሲናገር “እኔ ግን የኃጢያት በታች ልሆን ተሽጫለሁ…የማደርገውን አላዉቅምና፤ ያንኑ የምጠላውን ብቻ አደርጋለሁና፤ ዳሩ ግን የምወደውን እሱን አላደርገውም፤ የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ…ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም በእኔ የሚያድረው ኀጥያት ነዉ እንጂ” በማለት በአገልግሎት የደረሰበትን የመንፈስ ዉግያ ምሳሌ በማድረግ መክሮናል። ( ሮሜ 7፥14-47)
በመጨረሻም የንስሐ ህይወት ለአንድ ክርስቲያን ቋሚና አስፈላጊ ተግባር ስለሆነ ከልብ በሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ይኸን አጭር መልእክት ደጋግማችሁ እንድታነቡና በተጨማሪ መረጃ ስትፈልጉም በዉስጥ መስመር ማግኘት የምትችሉ መሆኑን አበክሬ እመክራለሁ። 
የድንግል ማርያም ልጅ መድኀኔዓለም ለንሰሐ የሚሆን ጊዜ ለሁላችንም ያድለን።

ለዚህ ጥያቄ መልሱ ንስሀ መግባት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ነጭ ልብስ ገዝተን የተወሰኑ ቀናት ከለበስን ቦሃላ ማደፉ ወይም መቆሸሹ አይቀርም ነገር ግን ስለቆሸሸ አንጥለውም ስናጥበው የቀደመ ጽእዳዌውን ያገኛል አሁንም ይቆሽሸብናል ብለን ሳንለብሰው አንቀርም ሊቆሽሽ ይችላል ከኛ  የሚጠበቀው እንደገና አጥቦ መልበስ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን እንዳይቆሽሽ የምንችለውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የሰውም ሰውነት እንዲሁ ነው በሀጢአት ስናዳድፍ በንስሀ ቶሎ መጣጠብ ተገቢ ነው፡፡ነገር ግን ንስሀ መግባት ስናስብ እግዚአብሔር ይቅር የለኝ ይሆን? በደሌን ይደመስስልኝ ይሆን? እኔንማ ምረኝም ወዘተ ማለት ትልቅ ኃጠእት ከመሆኑም ባሻገር የእግዚአብሔርንም ምህረትና ይቅር ባይነት መጠራር ነው፡፡ ቲቶ 3-5 እንደ ምህረቱ መጠን ለአዲስ ልደት አዳነን፡፡1ኛ ጴጥ1 3-5፡፡  

ሐጢአት በሦስት መንገድ ይሰራል፡፡ ይኸውም ሀ. በሀልየ (በሀሳብ)  ለ. በነቢብ (በመናገር) ሐ. በገቢር (በተገባር) ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሥሩን ትእዛዛት በትክክል ያከበረ ሰው በሦስቱም መንገድ የተዘረዘሩ ሀጢአቶችን ማለትም ሀ. በሀልየ (በሀሳብ)  ለ. በነቢብ (በመናገር) ሐ. በገቢር ማ(በተገባር) አልሰራም ማለት ነው፡፡አስሩን ትእዛዛት ማክበር ያልቻለ ሰው ግን ሀ. በሀልየ (በሀሳብ) ለ. በነቢብ (በመናገር) ሐ. በገቢር (በተግባር)  በሦስቱም መንገድ ሐጢአት ሠራ ማለት ነው፡፡ ጥያቄው ግን አስሩን ትእዛዛት በትክክል ሁላችንም አክብረናል ወይ? ነው፡፡ ከፍጡራን ወገን በሀሳብም  በመናገርም በተገባርም ከእመቤታችን በቅረ ሐጢአት ያልሰራ የለም፡፡ በተግባራ ባንሰራ በመናገር ሰርተናል በመናገር ባንሰራ በሐሳብ ሰርተናልና ነው፡

          1.ከኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ፡፡ በተግባር 

          2.የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡ በመናገር

          3.የሰንበትን ቀን አክብር፡፡ በተግባር

          4.አባትና እናትህን አክብር፡፡ በተግባር

          5.አትግደል፡፡ በተግባር

          6.አታመንዝር፡፡ በተግባር

          7.አትስረቅ፡፡ በተግባር

          8.በሐሰት አትመስክር፡፡ በመናገር

          9.የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፡፡ በሐሳብ

         10.ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚሉት ናቸው፡፡ በተግባረ

በተለያዩ ቦታዎች ሰዎች ሀጢያታቸዉን ይናዘዙ እንደነበር በመፅሀፍ ቅዱስ ተገልÚል፡፡ ሐዋ 19-18 ፡ማቴ3 5-6 ፡ዘሌ 5-16፡ ኢያ 2- 19፡፡ ነገር ግን አባት የግድ ሊኖረን የሚፈለግበት ምክንያት 4ኛ ጥያቄ ላይ በዝርዝር የተቀመጡትን ስንመለከት መለሱን እናገኛለን፡፡ ንስሀ አባቶች ከመንፈሳዊ ህያወታችን ባሻገር በስጋዊ ህይወታችንም በደስታችንንም በሀዘናችንም ሁሌም ከእኛ ጋር ሆንው የሚጋሩንና ሁሌም በቅርበት የምናገኛቸው የየራሳችን ኣባቶች ሊኖሩን የግድ ነው፡፡በምክረ ካህን በ ፈቃደ ካህን የሚኖር ሰው ነፍሱ ከሃጢአት እንደ ምትጠበቅ ይታወቃል፡፡ ካህናትን ደግሞ “እናንተ የአለም ብርሃን ናችሁ” ማቴ 5-14 ነው ያላቸው፡፡ በመሆኑም በሀጢአት የጨለመ ህይወታችንን በንስሀ ብርሃን ያበሩልናል፡፡በሲራክ 6-6 ላይ “ብዙ ሰዎች ወዳጆች ይሁኑህ ከብዙዎች አንዱ ምክርህን የምትነግረው ከልቡናህ ጋር አንድ ይሁን፡፡” ይህ ማለት የየራሳችን ኣባቶች ሊኖሩን እንደሚገባ የሚያስረዳን ነው፡፡

ሀጢያትን በካህን ፊት መናዘዛች የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፡-

  1. ሀጢያትን በዝርዝር በካህን ፊት መናዘዝ ዳግመኛ በዚያ ሀጢያት ላለመያዝ ሀይልን ይሰጣል፡፡ዮሃንስ አፈወርቅ “በበደሉ ላይ ድፍረትና ሽንገላን የሚጨምር (ሀጢያት ሰርቶ እንዳልሰራ ዝም የሚል) ከዚያች ሀጢያት መጠበቅ ይችልም፡፡ እርስዋን በምትመስል ሀጢያት ከመዉደቅም አይድንም” እንዳለ፡፡
  2. ሀጢያታችንን በካሀኑ ፊት ስንዘረዝርም ያለፈዉን ሀጢያታችንን ሽረን በሚመጣዉም ህይወት ያንን ሀጢያት ላለመድገም እየወሰንን ነው፡፡
  3. ኑዛዜ ያሳቅቃል፡፡ መሳቀቁ ደግሞ ለሰራነዉ ሀጢያት ዋጋ ነዉ፡፡ በፍርድ ቀን ጌታ በሰማይ መላእክት ፊት ሀጢያታችንን ገልጦ ከሚያሰቅቀን ይልቅ እኛዉ እራሳችን እዚሁ እንደኛዉ ደካማ ሰዉ በሆነው በካህኑ ፊት በመናዘዝ ለሰራነው ሃጢያት የምንቀበለው ኢምንት ቅጣት ነው፡፡
  1. በሽታውን የደበቀ መድሃኒት የለውም እንደሚባለው የነፍሱን ደዌ ሀጢያቱን የሚደብቅም እንዲሁ መፍትሄ አያገኝም፡፡ የካህኑን ፀሎትና ምክርም ያጣል፡፡ “ሀጢያቱን የሚደብቅ /የሚሰውር አይለማም፡ የሚናዘዛትና የሚተዋት ግን ምህረትን ያገኛል” እንደተባለ ፡፡ምሳ8-13
  1. ሀጢያትን ለካህን መንገር ለእግዚአብሄር መናዘዝና ክብር መስጠት ነው፡፡ እያሱ እንዳለ “ልጄ ሆይ ለአምላክ ከብርን ስጥ፡ ለእርሱም ተናዘዝ፡ ያደረግከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ” ኢያሱ 7-19፡፡ ኢያሱ “ክብርን ስጥ” ያለው ለእግዚአብሄር: “ተናገር” ያለው ግን ለእርስ ለኢያሱ ለራሱ ነው፡፡ አበዉ ካሀናትም ኑዛዜን ከተቀበሉ በ`ላ “እግዚአብሔር ይፍታህ” እንጂ ”ፈትቼሃለሁ ” አይሉም፡፡ 
  1. ካህናት የነፍስ ሀኪሞች ናቸውና እያንዳንዱን የነፍስ በሽታ (ሀጢያት) በዝርዝር በእነርሱ ፊት ልንናዘዝ ይገባል፡፡ በሀኪሙ ፊት ምንናዘዘው የእግዚአብሔርን ፈዋሽነት ክደን እንዳልሆነ ሁሉ በካህናት ፊት የምንናዘዘውም የእግዚአብሔርን ሰሚነት ክደን አይደለም፡፡
  1. ለምን በቀጥታ ለእግዚአብሔር አልናዘዝም? ማለት በራሱ ትዕቢት ነው፡፡ ንስሃ የሚገባ ሰው ሊል የሚገባው ”ከበደሌ ብዛት የተነሳ ቀና ብዬ የሰማይን ርዝመት አይ ዘንድ እንኩዋ አገባቤ አይደለም” ነው፡፡ በወንጌል ”እርስ በርሳችሁ ሀጢያታችሁን ተናዝዙ” ያለው ሰው ከፈጣሪ ይልቅ ሰውን ስለሚፈራና ስለሚያፍር በሃጢያቱ እንዲሳቀቅ ደግሞም እንዳይሰራት ስለፈለገ ነው፡፡ 

ወስብሀት ለእግዚአብሔር 

  በእርገጥ አሁን ከቤት መውጣት አስቸጋሪ ነው እግዚአብሔርም የምህረት እጁን ልኮልን ይህ ጊዜ እንደሚያልፍ  እናምናለን፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አልተዘጋችም ስብሀተ እግዚአብሔርም እየተደረሰ ነው  ቅዳሴም አልታጎለም ማህሌቱም አልቀረም ይህ ሁሉ የቀረ እንደሆነ ተዘጋች ልንል እንችላለን፡፡ በእርገጥ ለምእመናን ክፍት አይደለም ለምእመናን ዝግ ናት በሚለው ቢታረም የተሸለ ነው፡፡  ወደጥያቄው እንግባና ንስሀ መግባት እፈልጋለሁ ለሚለው ጥያቄ ንስሀ አባት ለሌላችሁ የተዋህዶ ልጆች ለእናንተ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ በህይወታቸው ምሳሌ የሚሆኑአችሁ  በጸሎታቸውም ሊያግዙአችሁ የሚችሉ ስለናንተ የሚያገባቸውንና የሚጨነቁላችሁን  አባቶችን በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ለምትኖሩ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች የሚያገለግሉበትን መደበኛ ቦታ (ደብር) ስማቸውን ስልካቸውን በዚህ ሳምንት መጨረሻ በዚሁ ፔጅ እንለቅላችሁአለን  እንደሚቀርባችሁ ቦታ እየደወላትሁ ከእነርሱ ጋር መነጋገር ትችላላችሁ፡፡ እንደተባለውም በበአለ 50 በእርግጥ ንስሐ አይሰጥም ነገር ግን አባቶቻችሁን ካገኛችሁ በሁዋላ የነፍሳችሁ ሀኪሞች እነርሱ ናቸውና ከእነርሱ ጋር መነጋገር ትችላላችሁ፡፡ እዚህ ጋር ሊታወስ የሚገባው አንድ ነገር ምንም አይነት ክፍያ እንደሌለው መገንዘብ ነው፡፡ምክንያቱ ደግሞ የነፍስ ሥራ ስለሆነ ነው፡፡

በእርግጥ በዚህ አስጨናቂ ወቅት ንሰሀ ገብትን እግዚአብሔርን ከመጠባበቅ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ይሁንና ከላይ እንደጠቀስነው  በጸሎታቸውም ሊያግዙአትሁ የሚችሉ አባቶችን በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ለምትኖሩ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችሁ በዚህ ፔጅ ከንስሐ አባት ገጽ ስር ማግኘት ይችላሉ፡፡

የዚህ መልስ ከእረሳቸው ጋር በመነጋገር እርስዎ ሁሌም ሊያገኙአቸው የሚችሉአቸውንና እርሰዎን አሰተምረው ለንስሀ የሚያበቁ አባት መያዝ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የንስሀ አባትና ልጅ ተራርቀው መኖር በፍጹም የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡

ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት ንስሐ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን መሰረታዊ ቁምነገር መመልከቱ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡

ንስሐ ማለት፦ ሐዘን፣ፀፀት፣ቁጭት፣ምላሽ፣፣ቅጣት ፣ቀኖና፣የኃጢአት ካሣ ፤ሰው በሠራው ጥፋት፣ባደረገው ስህተት፣በፈጸመው ኃጢአት ማዘኑና መቆርቆሩን፣መፀፀቱን የሚያሳይ ፤ወደ እግዚአብሔር መመለስ ፤ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ፤ከኃጢአት እንቅልፍ መንቃት፤ወደ መንፈሳዊ ሕይወት መመለስ ፤ከእግዚአብሔር የሚሰጥ እግዚአብሔርን የሚያስወድድ ከንጹሕ ልብ የሚመነጭ ጸጋ ፤ ከኃጢአትና ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ መውጣት ፤ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባ ቁልፍና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ማለት  ነው፡፡

የንስሐ ቅድመ ዝግጅቶች፡-አበ ነፍስ(የንስሐ አባት) መያዝ፤የሰራነውን ኃጢአት ማመን፤በሰራነው ኃጢአት ከልብ ማዘንና ማልቀስ፤እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን በፍጹም ትህትና ራስን በማዋረድ መጠየቅ፤ ከእኛ ኃጢአት ይልቅ የእግዚአብሔር ቸርነት እንደሚበልጥ ማመን፤እና ወዘተርፈ ናቸው፡፡

ንስሐ ማለትና ቅድመ ዝግጅቶቹ ከላይ በተገለጠው መልኩ ከሆነ አንድ ሰው ስለሠራው ኃጢአት ሳይጸጸት ፤ሳይቆጭ እግዚአብሔርን ማሳዘኑን ሳይረዳ ለይሰሙላ ንስሐ ላይ ነኝ ቢል ንስሐው እውነተኛ ንስሐ አይሆንለትም፡፡ ይህንንም ለመረዳት ንስሐ ማለት ምን ማት ነው የሚለውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

ነገር ግን ተነሳሒው ወይም ንስሐ የገባው ሰው ንስሐውን ተቀብሎ መጸጸት አለመጸጸቱን እኛ ማወቅ አንችልም፡፡ ይህን ማወቅ የሚችሉት እርሱና እግዚአብሔር ብቻ ናቸው፡፡ ንስሐ ማለት ግን ከላይ እንዳየንው ከእውነት በእውነት መጸጸት ማለት ነው፡፡

ሌላው በሰው ተገፋፍቶ ኀጢአት ከመስራት በሰው ተገፋፍቶ ንስሐ መግባት እጀግ ተወዳጅ ነው፡፡ መጥፎ ጉዋደኛ መልካሙን አመል እንደሚያጠፋው ሁሉ መለካም ጉዋደኛም በመልካምነጣችን እንድንቀጥል ያግዘናል፡፡ እንደተባለው ጉዋደኛችን ወደ ንስሐ የሚገፋፋን ከሆነ ከልብ እስከምንጸጸት አይተወንምና ለሁላችንም ወደንስሐ የሚገፋፋንን ሰው ይዘዝልን፡፡

የመጨረሻው ነጥብ አንድ ሰው ንስሐ ገባ ማለት ዳግም ኀጢአት አይሠራም ማለት አይደለም፡፡ ሰው ያደፈ ልብሱን እንደሚያጥብ በኀጢአት የጎሰቆለ ማናነታችንን በንስሐ መታጠብ ማለት ነው እንጂ፡፡የታጠበ ልብስ ሲቆሽሽ እንደሚታጠብ ሁሉ ሁሌም ሰውነታችን በኀጢአት ሲቆሽሽ በንስሐ ይታጠባል ማለት ነው እንጂ ንስሐ የገባ ሰው ኀጢአት አይሠራም ማለት አንችልም፡፡ አደራ አደራ ይህን ስንልም ኀጢአት ይሥራ እያልን አለመሆኑን ተረዱን ፡፡እንደሰውነቱ ግን በኀቲአት ሊወድቅ ይችላል እያልን ነው፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱ አሁንም አሁንም በንስሐ መታጠብ ብቻ ነው፡፡

መልስ፦ ሴትም ይሁን ወንድ ልጅ ለአካለ መጠን ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ እያወቁ በፈጸሙት የኀጢአት በደል በነፍስ ስለሚጠየቁ ንስሓ መግባት እንዳለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል።

  ነሰሐ እግዚአብሔር ጠፍተን እንዳንቀር ወሰን በሌለው ፍቅሩ እኛን ወደእርሱ የሚጠራበት የፍቅር ጥሪ ነው። ሐጢአት ግን ከእርሱ የሚለየን የእርሱ ማደሪያዎች ከምንሆን ይልቅ የሰይጣን ማደሪያዎች እንድንሆን ያደርገናል። ደግሞም እርሱ ሐጢአትን እንጂ ሐጢአተኛውን አይንቀውም የምንጠየቀውም ለምን ሐጢአት ሠራህ/ሽ ሳይሆን ለምን ንስሐ አልገባህም/ሽም በሚል ነውና ንስሐ ሐጢአትን አያበረታታም።ንስሐ ሐጢአትን ያበረታታል ካልንማ ከፍጡራን መሐል ከእመቤታችን በቀር ሐጢአትን ያልሠራ ማን ይኖርና። በመሖኑም ንስሐን አርሱ ባያዘጋጅልን ሁላችንም ጠፍተን ነበርና በዚህም ገደብ የሌለው ምህረቱንና ቸርነቱን ማየት ችለናል።ደግሞ እርሱም ሰው ሆኖ በምድር ሲመላለስ የትምሕርቱ መጀመሪያ ንስሐ ግቡ የሚል ነው እንጂ ሐጢአትን ለምን ሠራችሁ የሚል አይደለም በመሆኑም ንስሐ ፈጽሞ ሐጢአትን አያበረታታም።ንስሐ ማለትኮ አንድ ታማሚ ታሞ ሕክምና ሲሄድ የሚሰጠው መድሐኒት እንደማለት ነው። ንስሐ ሐጢአትን ያበረታታል ካልን ለታማሚው መድሐኒት መስጠት ታማሚዎች ቁጥራቸው እንዲጨምር ማበረታታት ማለት ነውና ንስሀ ሐጢአትን አያበረታታም።በአጭሩ ንስሐ ማለት ለታመመ ሰው መድሐኒት መስጠት ማለት ነው። ንስሐማ በይኖር ሑላችንም ሐጢአተኞች ነንና በጠፋን ነበር እርሱ ግን ዛሬም እድሜን ለንስሐ ሰጥቶናልና እናመሰግነዋለን።

አዎ በደንብ ይሰረይለታል ክፋቱ ንስሐ አለመግባት ብቻ ነው።በንሰሐ ሐጢአት በደንብ ይሰረያል።ሲጀመር ስጋ ወደሙ ያልተቀበለ አርቶዶክሳዊ የታለና ስጋወደሙ መቀበል የጀመርነው ገና በእናቶቻችን ጀርባ ሳለን በ40ና በ80 ቀናችን ነውና። መቼም ያ በሕጻንነታችን የተቀበልነው ነው እሱ አይቆጠርም የሚል ማንም አይኖርም። ይህ እንደውም ክርስቶስን ማሳነስ ነውና ሐጢአቱ ይህ ነው።ሁላችንም ስጋወደሙ ተቀብለናል ደግሞም ሁላችንም ሐጢአትን ሠርተናል እርሱ ግን ዛሬም በፍቅር አጠራሩ ወደእርሱ በንስሐ እየጠራን ይገኛል።እውነት ነው ስጋወደሙ የተቀበለ ሰው ሐጢአት ሊሠራ ይችላል ነገር ግን ራሱን ለንስሐ ካዘጋጀ በንስሐ ይሰረይለታል። አደራ አንድ ሰው ንስሐ ገባ ማለት  በቃ የመጨረሻ አይበድልም ቢበድልም ንስሐ የለውም የሚል ሐሣብ እንዳይኖርዎ ይበደላል ደግሞ በነስሐ ሲታጠብ ንጹህ ይሆናል ማለት ነውእንጂ። አንድ ምሳሌ አዲስ ልብስ ገዝተን ይቆሽሽብናል በማለት ሳንለብሰው አንቀርም በእርግጥ እንለብሰዋለን ደግሞ ይቆሽሻል ስለቆሸሸ አንጥለውም አጥበን እንለብሠዋለን። በመሆኑም ንስሐ ስንል ልክ ከላይ እንዳየነው ምሴሌ ነፍሳችንና ሰውነታችን በሐጢአት ሲቆሽሽ በቃ ሐጢአቴ አይሸረይለኝም በማለት ተስፋ መቁረጥ ሳይሖን ምንም በደለኛ ብሆን ንስሐ ብገባ ይቅር ይለኛል ንስሐም የተዘጋጀው ለኔ ለሐጢአተኛው ነው ብሎ በማመን ወደንስሐ መመለስ አስተዋይነት ነው።ነገር ግን እሄንን ሐጢአቴን ይቅር አይለኝም ማለትና ነስሐ በገባንበት ሐጢአት መጸጸት ትልቅ ሐጢአት ነው እግዚአብሔርንም ጨካኝ ማድርግ ነውና ንስሐ ስንገባ ይቅርታውን እንዳገኘን ማመንና ንስሐ የገባንበት ሐጢአቶ እንደጠፋና እንደተሠረዘልን እነደተረሳልን በእርሱ ዳግም ማንም እንደማይወቅሰን እርግጠኞች መሆን አለብን።

 ባልና ሚስት በእግዚያብሄር ዘንድ አንድ አካል ናቸዉና ንስሐ ሲገቡ ሆነ ሲቆርቡ አንድ ላይ ነዉ ማድረግ ያለባቸዉ።

 የንስሐ አባትዎ እርስዎን በስጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወቶ መክረው ገስጸው ማብቃት ካልቻሉና ለእርስዎ በጎ ምሳሌ መሆንም ካልቻሉ ይህንንም እርስዎ ከተረዱ እውነት ነው በትክክለ መቀየር ይችላል።ነገር ግን  ሌላ አባት መቀየር ሲያስቡ በራስዎ ጊዜ ዝም ብለው ጥለው መሔድ ግን አይቻልም። ከእርሳቸው መሰናበት ቸገቢ ነው።እርሳቸውም የእርስዎን ጥያቄ ተቀብለው ፍትሀት ዘወልድ የሚባል ጸሎት አለ ያንን ደግመው እርሰሸዎን ማሰናበት አለባቸው። ነገር ግን እርሳቸው ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ባይሆኑ እርስዎ ወደመረጡት አባት መሄድ ይችላሉ።ከዚህ ጋር መታሰብ ያለበት ስለሚይዟቸው አባት ማንነት እና መንፈሳዊ ህይወት ማወቅ ተገቢ ነውና እዚህ ላይ በትኩረት መመልከት እንዳለብዎ መዘንጋት የለቦትም።

በቅድሚያ በድያለሁ ጥፋት ሰርቻለሁ ኅጢአት ፈጽሜያለሁ ብሎ ኅጢአትን ለመናዘዝ ፈቃደኛ መሆንና የኅጢአት ሥርየት ለማግኘት መፈለግ የእውነተኛ ክርስቲያን መገለጫ ነው። በመሠረቱ በአዳማዊ ተፈጥሮ ሰው ሁኖ የተፈጠረ የሰው ልጅ ሁሉ ወዶ ጽድቅ መሥራትም ሆነ ወዶ ኅጢአት ለመሥራት የሚችልበት የተፈጥሮ ነፃነት ያለው ፍጡር ስለሆነ በለበሰው ደካማ ሥጋው ተሸንፎ ኅጢአት እንደሚሠራ ይታወቃል። ሰው ሁኖ ተፈጥሮ በሰውነቱ ፈፅሞ ኅጢአት አልሠራም ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር እራስን ከማታለል አልፎ ስለሁላችንም መዳን በመስቀል ላይ የሞተልንን የኢየሱስ ክርስቶስ አባታዊ ፍቅሩንና ውለታውን እንደመካድ ይቆጠራል። ሁላችንም የሰው ልጆች እንደምንሞት ብናምንም እንኳ፤ ነገር ግን መቼ በሞት እንደምንጠራ ቀንና ሰዓቱን (ዘመንና ጊዜውን) ለይቶ ማወቅ ከእሱ ከባለቤቱ በስተቀር ፈጽሞ የሚያውቅ የለምና ኅጢአትን ለመናዘዝ ቅድሚያ መስጠትና በንስሐ ሕይወት ራስን አዘጋጅቶ መጠበቅና ንስሐ ለመግባት መዘጋጀት ከእውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ ታማኝነት ነው።

ኅጢአት ማለት የብዙ ጥፋቶች ወይም ስሕተቶች መጠሪያ ስም ነው ኅጢአት የሥጋ ሥራ ሁኖ ነፍስን ከፈጣሪ ጋር አጣልቶ ዘለዓለማዊና ሰማያዊ ሞትን የሚያስከትል ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የኅጢአት ውጤት ሞት እንደሆነ ሲናገር “ኅጢአት ስታድግ ሞትን ትወልዳለች” (ያዕ1$15) ካለ በኋላ “የኅጢአት ደመወዝ ሞት ነው” (ሮሜ 6$23) በማለት ኅጢአት የሕሊናና የመንፈስ ሞት መሆኑን አረጋግጧል።

የሥጋና የመንፈስ (የነፍስ) ሥራዎች አብዛኛዎቹን ቅዱስ ጳውሎስ ወደገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ በምዕ 5$19-22 ላይ የሥጋ ሥራ እና የመንፈስ ፍሬዎች በማለት ዘርዝሯቸዋል።

የሰው ልጅ ኅጢአት ሰርቻለሁ እግዚአብሔርን በድያለሁ፣ ሰውንም አሳዝኛለሁ ብሎ ራሱን ካሳመነ በነፍሱ የኅጢአት ደዌ አድሮበታልና ንስሐ የመግባት ሕክምና ያስፈልገዋል ማለት ነው። “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ “(ማቴ3$8) ኅጢአት ሠርቶ የንስሐ ሕክምና ያላገኘ ሰው በነፍሱ ምውት ነው። ሉቃ 15$24

ከዚህ የተነሣ ኅጢአት ለመናዘዝና ንስሐ ለመግባት ከሚፈልግ አንድ ክርስቲያን የሚጠበቀው ፡-

 

  1. በቅድሚያ ኅጢአት መሥራቱን አምኖ ለራሱ ሕሊና መናዘዝ (መፀፀት)።

 

  1. ስለሠራው ኅጢአት ወይም በደል እየተጸጸተ ጧት ማታ በደሉን በፀሎትና በልመና ለፈጣሪው መናዘዝና ኅጢአትን በእግዚአብሔር ፊት ማመን (መዝ50 ፣ ዳን9$5፣ ነህ1$6-7)

 

  1. ኅጢአትን (በደልን) ለካህን መናዘዝና ንስሐ መግባት። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይና እንደራሴ ስለሆነ የሠራነውን ኅጢአት ለካህኑ በመናዘዝ ንስሐ መግባት፤ ኅጢአታችን እንዲሠረይልን በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ መግባትና መናዘዝ ማለት ነው። (ኢያሱ7$19 ማቴ3$6 ዘሌ5$5-6 የሐዋ19$18)

 

  1. የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት የጥል ግድግዳ አፍርሰን በፍቅር አሸንፈን ስለዘለዓለማዊ ሕይወት ብለን በፍጹም ሕሊና በሰላም መኖር ነው።

 

  1. ተመልሶ በኅጢአት ላለመውደቅ አዘውትሮ የንስሐ አባትን ወይም የሚቀርቡትን የሃይማኖት መምህር ማማከር፣ ምክር ማግኘት በታቻለ መጠን መጸለይ፣ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ በቤትም ውስጥ ቢሆን መንፈሳዊ መዝሙርና ትምሕርት ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ የምናስገነዝበው ለጠየቁን ምዕመን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያን እንዲጠቅም ነው።

 

የእግዚአብሔር ሰላም በያላችሁበት ከእናንተጋር ይሁን።

በቅድሚያ ፀበል ምንድነው? ለሚለው ካህኑ ውሃውን በእግዚአብሔር ቃል እና በቅዱስ መስቀሉ ሲባርከውና ሲቀድሰው ተራ የነበረው ውሃ በጥምቀት የእግዚአብዜር ልጅነት ይገኝበታል።

“ሰው ከውኅና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዩሐ 3፤5) በማለት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ዳግም ለመወለድና ሰማያዊ መንግሥቱን ለመውረስ የእግዚአብሔር መንፈስ ባደረበት በውሃው (በጸበሉ) መጠመቅ እንዳለብን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት ወደ እሱ ለመጣው ለወዳጁ ለኒቆዲሞስ በስፋት እንዳስተማረው ወንጌላዊው ቅዱስ ዩሐንስ ጽፎታል።

ለጥምቀት የተዘጋጀው ውሃ (ፀበል) የቤተክርስቲያን አባቶች ለዚሁ አገልግሎት የተዘጋጀውን ጸሎት ከጸለዩበት እና በመስቀል ከባረኩት በኋላ ልዩ ልዩ ደዌ (በሽታ) ያለባቸው ሰዎች ይፈወሱበታል፣ ርኩሳን መናፍስት (አጋንንት) ያደሩበት ሰውም ሲጠመቅበት በፀበሉና በመስቀሉ ኃይል አጋንንቱ ከታመመው ሰው ዳግም ወደሰውየው እንዳይመለሱ በእግዚአብሔር ቃል ታሥረውና ተወግዘው ይለያሉ።

በጸበሉ ፈዋሽነት የሚያምን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊም ሆነ ሌላው ወገን ሳያውቅም ሆነ እያወቀው የድግምት፣ የመተት፣ የሟርት መንፈስ ቢኖርበት በጸበሉ ከተጠመቀና ቤቱም ንብረቱ ጸበል ከተረጨበት ፈጽሞ ይድናል። ክፉ መንፈስም በእርሱ ላይም ሆነ በሃብቱና በቤቱ ላይ ጥፋት ለማድረስ ስልጣን የለውም።

አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በተለያየ ምክንያት ክርስቲያናዊ ሕይወቱን የሚያጎድፍና በእምነቱ ያልተፈቀደለትን ፈጽሞ ቢገኝ ደግሞ ወደ ካህናት (ወደ ንስሐ አባቱ) ቀርቦ ጥፋቱን መናዘዝ ወይም ንስሐ በመግባት በሥርዓተ ቄዶር እንዲጠመቅ ይደረጋል። ለምሳሌ ሃይማኖቱን ቀይሮ ቢገኝ፣ በሃይማኖት የማይመስለውን ቢያገባ (በዝሙት ቢወድቅ)፣ ለክርስቲያን ያልተፈቀደውን ምግብ ቢበላ ወዘተ የመሳሰለውን ኢክርስቲያናዊ ግብር ፈጽሞ ቢገኝ የቀድር ጥምቀት ያስፈልገዋል ማለት ነው።

በርዕሱ ወደተገለጸው ጥያቄ ስንመለስ ፀበል አንዱ የንስሐ መንገድ ስለሆነ ለንስሐ ከሚያበቃን የኅጢአት ሥራችን ለመመለስ በቁርጠኝነት ከወሰንን ጠያቂው እንዳሉት ፀበል ለመጠመቅም ሆነ ለመጠጣት እንችላለን። ይህን ስንል ግን የሠራነው ኅጢአት ተለይቶ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም ለምሣሌ የወለደች ሴት፣ የሴቶች ልማድ የምታይ ሴት እስከሚነፁ መጠበቅ አለባቸው። ከዚህም በላይ ፀበሉን ብንጠጣውም ሆነ ብንጠመቅበት ከልብ በሆነ እውነተኛ መጸጸት ወደ ንስሐ ሕይወት ተመልሰን ከበደላችን ነፃ ካልሆን ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝራዎች፣ ሟርተኞች ፣ መተተኞች፣ አስማተኞች፣ ቀማኞች፣ ወንበዴዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ፍርድ አጉዳዮች፣ ከሃዲዎች ወዘተ ሁነን በአጠቃላይ ከአንድ ክርስቲያን የማይጠበቅ ክፉ ሥራ እንደፈጸምን እያወቅንና በንስሐ ሣንታጠብ እግዚአብሔርንና ራሣችንን በመደለል በአስመሣይነት ፀበሉን ብንጠመቅበትም ሆነ ብንረጭ ጥቅም አይሰጥም። እንዲያውም ከበረከት ይልቅ መርገምን ያመጣብናል። በመሆኑም ኅጢአተኛ ሰው ስለበደሉ የጊዜ ቀጠሮ ሣይሰጥ የመዳን ቀን ዛሬ ስለሆነ ባለበት ቦታ ሁኖ ያለምንም ድካምና ውጣ ውረድ ከልብ ለሚያምነውና ለነፍሱ እረኛ አባት አድርጎ ለተቀበለው አባቱ ኅጢቱን መናዘዝ አለበት። በእርግጥ የእኛ ኅጢአት የእግዚአብሔርን ቅድስና አያረክስም። እኛ ግን ንስሐ ሳንገባ በድፍረት የምናደርገው ሁሉ ተጨማሪ ኅጢአት ስለሚሆንብን፤ ወደ ቤተክርስቲያን ለመግባትና ፀበል ለመረጨትም ሆነ ለመጠጣት የሚያስከለክለውን በደላችንን ለይቶ ለማወቅ ሁልጊዜም ቢሆን መምህራንን ወይም የቤተክርስቲያን አባቶችን እንድታማክሩ በእግዚአብሔር ስም አደራ እላችኋለሁ።

 

የመድኅኔዓለም ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን

ምላሹም –  ኅጥያቶን በመናዘዝ ከልብ ተጸጽተው ወይም ተመልሰው፤ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት በማገልገል ላይ ለሚገኘው የንስሐ አባትዎ (ካህን) ራስዎን በማስመርመርና ከፈጸሙት በደል የሚነፁበትን ንስሐ ተቀብለው ከሄዱና ከዳግም ጥፋትም እርቀው በካህኑ የተሰጠዎትን ንስሐ በትክክል ከፈጸሙ፤ ከተያዙበት የኅጥያት ማሰሪያ ስለተፈቱ ንስሐም ገብተው ስለተናዘዙበት እንደገና ይፍቱኝ ለማለት ወደ ካህኑ የሚያስኬድ ጉዳይ አይኖርብዎትም።

ምክንያቱም በኅጥያት እድፍ የቆሸሸውን ህይወትዎን ከካህኑ በተቀበሉት የንስሐ ውሃ ታጥበው ከኅጥያት እድፍ ፀድተዋልና። ዳግም እንዳይበድሉ፣ ኅጥያት ሰርተውም የቅድስና ሕይወትዎን እንዳያቆሽሸው፣ በየጊዜው ከቤተ ክርስቲያን መምህራንና የንስሐ አባቶች ትምህርትና ተግሳጽ እያገኙ ምንም እንኳን የኑሮ ፈተና ቢበዛብዎ ከእናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳይርቁ እየፆሙና እየፀለዩ ከገንዘብዎ፣ ከእውቀትዎ እና ከጉልበትዎም አስራት በኩራት እያወጡ በጎ ስራ በመስራት ከሰይጣን ወጥመድ ለማምለጥ የሚችሉበትን መንፈሳዊ ፀጋዎትን በተቻለ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለብዎ እመክራለው። ለዚህም ዋናውና መታወቅ ያለበት ነገር ማንም ክርስቲያን ያለጠባቂና ያለመካሪ ንስሐ አባት አንድ ቀንም መኖር ስለሌበት ወደ ንስሐ አባትዎ (ካህን) መሄድ ያለብዎ በየጊዜው የእለት እለት ህይወትዎን በካህኑ ምክር እንዲመራ ለማድረግ ነው።

በመሆኑም፤ ወደንስሃ አባትዎ ወይም ንስሐ ወደተቀበሉበት ካህን መሄድ የሚኖርብዎ ካህናት አባቶች የነፍሳችን እረኛ ሆነው በነፍስ ጉዳይ ላይ በሃላፊነት እግዚአብሔር ስለሾማቸው ሁልግዜም ቢሆን ከአባቶች ምክርና ተግሳጽ ላለመራቅ ነው እንጂ ቀደም ሲል ንስሐ ስለገቡበት ኅጥያት ይፍቱኝ ለማለት አለመሄድዎን እንደጥፋት ቆጥረው እንደገና ንስሐ እንዲገቡበት አያስፈልግዎትም በማለት መንፈሳዊ ምክሬን እለግሳለው። (ማቴ18፤18) ዩሐ(20፤21-23) ዩሐ (21፤15-18)

ከዚህ በላይ ስላቀረቡት ጥያቄ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከፈለጉና ያልተመለሰልዎት ጥያቄ ካለም በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን ይችላሉ። ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር አጋዥነት ከእርስዎ ጋር ይሁን።

ሚስጥረ ተክሊል የሚፈጸምላቸው ተጋቢዎች በሃይማኖትና በምግባር ጸንተው በድንግልና ሕይወት ለተገኙ ሙሽራውና ሙሽራይቱ ብቻ ነው። ሚስጥረ ተክሊልም ለአንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈፀም ስርአት እንጂ አይደጋገምም። ሚስጥር የተባለበት ምክንያቱም ባልና ሚስት አንድ የሆኑበት ስርዓት ስለሆነ ነው። በጥንተ ተፈጥሮ ሴት የተገኘችው ከወንድ በመሆኑ “ይቺ አጥንት ከአጥንቴ ስጋዋም ከስጋዬ ናት” ተብሎ ሄዋን ከአዳም እንደተገኘችና አንድዋ ሄዋን ለአንድ አዳም እንደተፈጠረች ቅዱስ መፅሐፍ ያስረዳል። ዘፍ 2፤24

በስርአተ ተክሊል ጋብቻቸውን የሚፈፅሙ ጥንዶች ሁለቱም በድንግልና ጸንተው የኖሩ ለመሆናቸው በእግዚአብሔር ፊት ቀርበው ለንስሐ አባታቸው እራሳቸውን ሲያስመረምሩ ብቻ ነው። ከሁለት አንዳቸው ከስርዓተ ተክሊል በፊት ድንግልናቸውን ሊያሳጣ የሚችል ጥቃት ከፈፀሙ በቅዱስ ቁርባን አንድ ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ የክብር አክሊል መቀዳጀት የሚችለው በድንግልና ሕይወቱ ጸንቶ የተገኘ ብቻ ነው። ምክንያቱም ስርአተ ተክሊል ማለት በቤተክርስቲያን ውስጥ በካህናት አባቶቻችን የተለየ የክብር ልብስ ሲለብሱ፣ በራሳቸው ላይ የክብር አክሊል ሲቀዳጁ፣ የሚፈፀምላቸው ስርአተ ፀሎት፣ በካህኑ የሚቀቡት የተቀደሰ ቅባት፣ የቃልኪዳኑ ምልክት የሆነው ቀለበት፣ በመጨረሻም ሁለቱም አንድ የሚሆኑበትና የአንድነታቸው ማሰርያ የሆነውን ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉ ነው። ይህ ደግሞ ታላቅ ሚስጥር ስለሆነ እግዚአብሔር ላደለው ሰው በፍፁም መንፈሳዊ ሕይወት ፈሪሃ እግዚአብሔር ኖሮን በምክረ ካህን ንስሐ ተቀብለን ከሰራነው ነውራችን አንዱንም ነገር ሳንፈራና ሳንደብቅ ግልፅ ሁነን የምንፈፅመው ስርዓት ከሆነ ኑሯችን፣ ትውልዳችን፣ ስራችን፣ ጤናችን፣ ሁሉ የተቀደሰና የተባረከ ይሆናል። ጋብቻ ቅዱስ ነው የተባለውም በዚህ ነው። ቅዱስ ጋብቻን የባረከው እግዚአብሔር አምላካችን ነው። ምክንያቱም አዳምና ሄዋንን ሲፈጥር አንድ ወንድን ለአንዲት ሴት ፈጥሮ ያጣመረ እሱ ነውና። በጣና ዘገሊላ በተደረገው የሰርግ ቤት ተገኝቶ ጋብቻን እንደባረከ ወንጌላዊ ዩሐንስ ነግሮናል። (ዩሐ 2፤1-11 እብ13፤4 ኤፌ 5፤31 እና 32)

ለጋብቻ የሚደረገው ጥንቃቄ የአንድ ትውልድ፣ ያንድ ታሪክ፣ ያንድ መንደር፣ ያንድ ሃገር የመነሻ መሠረት ስለሆነ ነው። ስለዚህ ጋብቻ በቅዱስ መፅሓፍ ሰፋ ያለ ታሪክ ያለው ቢሆንም ለጠየቁን አባላችን በመጨረሻ እንዲገነዘቡ የምንፈልገው የስርአተ ተክሊሉ አፈፃፀም ከ ሁለት አንዳቸው ከጋብቻ በፊት በተለየ ስህተት ፈተና ላይ የወደቁ ከሆነ በድንግልና ፀንቶ የቆየው የክብር አክሊል ሲደረግለት ሌላው ግን ንስሐውን በቀኖና ከፈፀመ በኋላ አብረው ስጋውና ደሙን በተቀበሉ ጊዜ አንድ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። በዚህ አይነት ስርዓት ጸንተው እንዲኖሩም ቤተክርስቲያን በፍቅርና በአንድነት ቃል ታገባባቸዋለች። ከዚህ በላይ መረዳት የሚፈልጉት ነገር ካለ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

የአብርሃምና የሳራን ጋብቻ የባረከ አምላክ በስርዓተ ጋብቻ አንድ የሆኑትን ሁሉ ኑሯቸውን ይባርክ ዘንድ እንመኛለን።

አንድ ክርስቲያን የሆነ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ድንግልናቸውን ጠብቀዋል  ሲባል : –

 1- ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት አለማድረጋቸው በራሳቸው ቃለ መሓላ÷ በንስሐ አባትና በቤተሰበ ሲረጋገጥ

  2- በሃይማኖታቸውና በክርስቲያናዊ ስነ ምግባር ጸንተው ከእግዚአብሔር ቤት ሣይለዩ ቅዱስ ቁርባን እየተቀበሉ  ስለመ ኖራቸው ቤተክርስቲያን ስትመሰክርላቸው

   – ከጋብቻ በፊት  የድንግልና ክብራቸው ን  ሊያሳጣ የሚችል ሐጢአት ያልሰሩ ለምሣሌ ÷ የሰው ሕይወት ማጥፋት ጣዖት ማምለክ ማስጠንቆል መሥረቅ  የ   መሣሰሉትን ጥፉቶቸ መፈጸም  ናቸው 

  የወንድ ልጅ ድንግልና  ማረጋገጫ በ ራሱ ህሊና አምኖ ለነፍስ አባቱ ከሚገባው ቃል ኪዳን ዉጪ ሌላ አካላዊ ማረጋገጫ  አይኖርም   በእርግጥ ከምንም በላይ  ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ  ከሰው የሰወርነውን በደላችንን ሁሉ ሰለ  ሚያውቀው ለህሊናችንና ለሃማኖታችን ስንል እውነቱን እዉነት ሃሰቱን ሃሰት ልንል ይገባል                                                               – የሴት ልጅ ድንግልና ራሷ ፍጹም ታማኝ  እና ቅድስናዋን የጠበቀች ሁና እያለ :-     

በተፈጥሮ -በሕመም ምክንያት – በአስገድዶ መደፈር – በከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ (ክብደት) – በሕክምና እና በመሳሰለው ሁሉ አካላዊ የድንግልና ም ልክቷ ባይገኝባት እንደ ቤተክርስቲያ አስ ተምሮ ሌላ ነውር እሰከአልሠራች ድረስ የድንግ ክብሯን አያሳጣትም   ስለዚህ

ስለድንግልና ማንነት ማወቅ የምንችለው በተፈጥሯዊ ዕውቀትና በሳይንሳዊ ምርምር ወይም በሰውኛ ዕውቀት ሳይሆን ብቸኛ ዐዋቂው የራሳችን ውሳጣዊ ኅሊናና  የሁሉ ባለቤት ፈጣሪ ብቻ በመሆኑ መሠረታዊ የሆነውን ትምሕርተ ሃይማኖት ከማወቅ አልፎ ያለውን ድርሻ ለእግዚአብሔር ብቻ መ ስጠት አለብን                                      ለሁሉም ነገር አምላካችን

በመሠረቱ ንሰሐ ማለት በለበስነው ደካማ ስጋችን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ያልተፈቀደውን ሕግ ተላልፈን ስለፈፀምነው ኀጥያታችን ከልብ ተፀፅተን ንሰሐ ለመግባት ወደ ቤተክርስቲያን ካህን (ንሰሐ አባት) ቀርበን የሰራነውን ጥፋት በተናዘዝን ግዜ ካህኑ የሚሰጠን ንሰሐ በፆም ወይም በስግደት ወይም በፀሎት ወይም በምፅዋት የቀኖና ሱባዔ ሲሰጠን በቤታችን ሆነን ወይም ወደ ገዳም ሄደን የተሰጠውን ንሰሐ ልንፈጽም እንችላለን። ሱባዔውን (ንስሐችንን) ከጨረስን በኋላ ደግሞ ያንን ኅጥያት እንዳንሰራ መጠንቀቅ እና ከአባቶች ምክር እንዲሁም ከቤተክርስቲያን እና ከበጎ ስራ መራቅ የለብንም። 
ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባንን የመቀበል መንፈሳዊ ግዴታ ቢኖረውም፤ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ራሱን የቻለ ዝግጅት ከሌለ ንስሐ ስለገባን ብቻ የክርስቶስን ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል አንገደድም። ምክንያቱም ትዳር ያለው ከኑሮ አጋሩ ጋር ተስማምቶ መዘጋጀት ስላለበት፤ ያላገባ ክርስቲያንም ከራሱ እና ከመንፈሳዊ አባቱ ተማክሮ ራሱን የቻለ ፕሮግራም ማድረግ ስላለበት ነዉ።
በየጊዜው በምንሰግድበት ጊዜ ከቤተክርስቲያን ውጭ ከሆነ የምንሰግደው ስንሰግድ በፊታችን የጌታና የቅዱሳን ስእል ወይም መስቀል ሊኖር ይገባል። ወይንም ቅዱስ ወንጌል ከፊታችን አድርገን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አማትበን የተለመደውን የግል ፀሎት አድርጎ በአቡነ ዘበሰማያት በማሳረግ፤ ስግደቱን የበደልነውን ኀጥያት በልባችን እያሰብን እና እየተፀፀትን እንሰግዳለን። በመጨረሻም በአቡነ ዘበሰማያት ይደመደማል።
 
 
ሰው በውስጣዊ ህሊናው አውጥቶና አውርዶ ገና በስራ ላይ ያልዋለው በሃሳቡ ብቻ ያቀደው የክፋት ምኞት ሁሉ ያሃልዮ (የሃሳብ) ኀጥያት ይባላል። በልቡ የታሰበው ኀጥያት በአፍ ሲነገር የነቢብ (የመናገር) ኀጥያት ይባላል። በአፍ የተነገረው ኀጥያት በስራ ላይ ከዋለ የገቢር (የተግባር) ኀጥያት ይባላል።
 
ስለሆነም በልብ ታስቦ ሳይናገርና ስራ ላይ ሳይውል ከቀረ የታሰበውን ኀጥያት የሚያውቀው ልብና ኩላሊትን የሚመረምር እግዚአብሔር በመሆኑ በልብ ታስቦ ስራ ላይ ስላልዋለው ኀጥያት እና አንዳንዴም ጥፋት ሳይመስለን ባለማወቅ የምንፈፅማቸው ጥቃቅን ጥፋቶች በየጊዜው ወደ ካህኑ ቀርበን እና ከልባችን አምነን መስቀሉን ተሳልመን ካህኑ እግዚአብሔር ይፍታህ ቢሉን በውስጣችን የሚዋጋን ክፉ መንፈስ እንደ አሮጌ ልብስ ተገፎ እንዲወልቅ በካህኑ ላይ ያደረው ሃብተ ክህነት ያደርግልናል። ሆኖም በመናገርም ሆነ በመስራት የፈፀምነውን ከባድ በደል ግን እንደማያስፍቅልን መረዳት ያስፈልጋል።