ስለ ፀበል እና ጥምቀት
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ፀበል እና ጥምቀት
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
ጠያቂያችን የጥያቄ አገላለፅዎን የበለጠ እንድንረዳው ማብራሪያ ቢያስፈልገውም፤ ነገር ግን እንደ ስርዓተ ቤተክርስቲያን አፈፃፀም ከሆነ ለቄደር የሚያበቃ ኀጢአት የሰራ ክርስቲያን ከቄደሩ በፊት መጀመርያ ንስኀ መግባት ያስፈልገዋል። ንስኀውን ከጨረስ በኋላም ቄደር ሊጠመቅ ያስፈልገዋል። ወደ ገዳም ሄዶ በጋራ ቄደር መጠመቅ እንዴት እንደሆነ ግልፅ ባይሆንልንም ከቄደሩም በኋላ ቢሆን የሁሉም ሰው ጥፋትና የቄደር ጥምቀት ያስፈለጋቸው ምክንያት አንድ አይነት ስለማይሆን በየግላቸው ከቄደር ጥምቀት በኋላም ቢሆን ንስኀ መግባት መንፈሳዊ ፀጋንና ክብርን ያበዛል እንጂ የሚያገጎለው ነገር ባለመኖሩ እንዳሉትም የቤተክርስቲያን አባቶችን በማናገር ንስኀ መግባት ይችላሉ።
መልስ፦በክርስቶስ የሚኖሩ የእግዚአብሔር ልጆች የመጀመሪያ የልጅነት ጥምቀት ያገኙት ከሐዋሪያት ዘመን ጀምሮ ነው። ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋሪያትና እናቱ ድንግል ማሪያም እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ለማዳን በፍጹም ፍቅሩ በፈፀመው የመስቀል አገልግሎት እና በቆረሰው ሥጋውና ባፈሰሰው ደሙ ከአዳም ጀምሮ ያሉ በአፀደ ነፍስም በአፀደ ሥጋም በራሱ መለኮታዊ ጥበብ በሱ ደም ተዋጅተው እንደ ጥምቀት የተቆጠረላቸው የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ የሚጠሩበትን ሰማያዊ መንግስትን ወርሰዋል። ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ በተነሳ በ50ኛው ቀን የወረደው አፅናኙ መንፈስ በነሱ ላይ በእሳት አምሳል በወረደላቸው ጊዜ እንደ ጥምቀት ሆኗቸዋል። ያ እለት የቤተከርስቲያንም የልደት ቀን ነው ተብሎ ይታመናል። በመሰረቱ ለሁላችንም ደግሞ ከውሃና ከመንፈስ እንድንወለድ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በራሱ መለኮታዊ ቃል ከውሃና ከመንፈስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት አያይም ከማለቱም በተጨማሪ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ደግሞ አይድንም ብሎ እራሱ የልጅነት ጥምቀት እንድንጠመቅ ከነገረን ጊዜ ጀምሮ ስርዓተ ጥምቀት በክርስቲያኖች ዘንድ ህግ ሆኖ ተሰርቷል። ከዚያ በፊት ግን እሱ የተጠመቀው ጥምቀትና በመስቀል ያፈሰሰው ደሙ ለኛ እንደ ጥምቀትም ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመግባት እንደ አርማ ሆኖ የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ አብቅቶናልና ፤ ጠያቂያችን ለግዜው ሃሳቡን በዚህ ተረድተውት ወደፊት በብሉይ ኪዳን እና አማናዊ የልጅነት ጥምቀት በአዲስ ኪዳን ምን እንደሚመስል የምናብራራው ስለሚሆን በትዕግስት ሆነው በመስመር እንዲጠብቁን እንጠይቃለን።
መልስ፦ ጠያቂያችን፤ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦልን ያስተላለፍነው ምላሽ ውስጥ እርስዎ አሁን ካቀረቡት ጥያቄ ጋር ስለሚመሳሰል አንብበው ሃሳቡን እንዲረዱት ልከንልዎታል። ምናልባት በዚህ ምላሽ ውስጥ ግልጽ ያልሆነልዎት ወይም ያልተመለሰልዎት ጉዳይ ካለ ደግመው ቢያሳውቁን ተጨማሪ ማብራሪያ እንሰጥዎታለንና በመስመር ላይ ሆነው ይጠባበቁን ዘንድ እንጠይቃለን።
ተጠይቆባቸው የነበረው ጥያቄ 1 ፦ሁለት በእጮኝነት ላይ ያሉ ጥንዶች ቢኖሩ ለየብቻ መቁረብ ይችላሉ?
መልስ፦ ሁለት በእጮኝነት ያሉ ወንድና ሴት ንፅህናቸውን ጠብቀው በድንግልና ህይወት ካሉ ጠያቂያችን እንዳሉት ጋብቻቸውን እስከሚፈፅሙ ድረስ ለየብቻቸው መቁረብ ይችላሉ። ነገር ግን ቀደም ሲል የፈፀሙት ኀጢአት ኑሮ ንስሓ ካልገቡበትና አሁንም በእጮኝነት ከጋብቻቸው በፊት የሚያደርጉት ነገር ካለ ግን መቁረብ አይችሉም ።
ተጠይቆ የነበረው ጥያቄ 2፦ ሁለት በጓደኝነት ላይ ያሉ ወንድና ሴት ከ ትዳር በፊት ሩካቤ ሲጋ ማድረግ የለባቸውም ግን የበለጠ ማወቅ ያስችለኝ ዘንድ መፅሐፍ ጥቅስ ብትነግሩኝ?
መልስ ፦ ጥያቄው መቅረቡን በአክብሮት ብንቀበለውም ነገር ግን ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ቅድመ ጋብቻም ይሁን ድህረ ጋብቻ ስላሉት ስለሚፈቀዱና ስለማይፈቀዱ ሁኔታወችም በስፋት መልእክት ማስተላለፋችን ይታወሳል። ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎ ማንኛውም ሃይማኖት ያለው ክርስቲያን ለአካለ መጠን ወይም ለአካለ ጋብቻ ደርሶ እና በሃይማኖት ስርዓትና በባህላዊ ትውውቅና በስርዓተ በጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት ማንኛውንም የአካለ ስጋ ሩካቤ ማድረግ ፈፅሞ ክልክል ነው። ለዚህም ነው በቅዱስ ጳውሎስ ስጋችሁን ለመግዛት ፍላጎታችሁን ለማሸነፍ ካልቻላችሁ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላል ያለው። በዚህ መሰረት ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ክርስቲያን የስጋውን ፍላጎት መግዛትና መቆጣጠር በማይችልበት የእድሜ ደረጃ ሲደርስ በሃይማኖት ስርዓትና በአገራዊ ባህል የፈለጋትን ወይም የፈለገችውን ተስማምተው ማግባት እንደሚችል ተፈጥሮዋዊ ማንነት ከእግዚአብሔር ተሰጥቷል። ከዚህ የተነሳ የተሰጠንን የነፃነት ፀጋ መጠቀም መቻል እንጂ ከጋብቻ በፊት የድብብቆሽ ስራወች መፈፀም እኛንም በነፍስ ይጎዳናል ከፈጣሪ ጋርም ያጣላናል በሰው ዘንድም መሀበራዊ ማንነታችንን ያዛባል። እና ጠያቂያችን በዚህ መልክ ስራ ላይ ብናውለው በእግዚአብሔር ዘንድም በረከትና መንፈሳዊ እድገት ያሰጣል በማለት እንመክራለን።
ተጠይቆ የነበረው ጥያቄ 3 ፦ ሁለቱ ተጋቢዎች በተክሊል/በቁርባን ሊጋቡ አስበው ግን ከጋብቻ በፊት ብዙ ጊዜ አብረው በፍቅር ከመቆየታቸው አንፃር ስህተት ቢሰሩ(ግንኙነት ቢያደርጉ) በኋላ(በጋብቻ ጊዜ) ጋብቻቸውን በቁርባን ማድረግ ይችላሉ?
መልስ፦ ስርአተ ተክሊል አስባችሁ በመካከል ላይ ራሳችሁን ለመግዛት ሳትችሉ በመቅረታችሁ በመካከል ባደረጋችሁት የስጋ ድካም ከስርአተ ተክሊል በፊት የድንግልናችሁን ክብር ስላጣችሁት የፈፀማችሁትን ጥፋት ለንስሓ አባት በመናገር ቀኖና ከተቀበላችሁ በኋላ በስጋው ደሙ መጋባት ትችላላችሁ። ስርአተ ተክሊል ግን መፈፀም አይቻልም። ዋናው ነገር ለስጋዊ ስም እና ዝና ተብሎ እግዚአብሔርን በሚያሳዝን ሁኔታ የማይገባንን ስርአተ ተክሊል ከመፈፀም ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ እውነቱን አረጋግጠን የምናገኘው ክብር በስርአተ ተክሊል ከምናገኘው ክብር እኩል ስለሆነ የሚያሳስበን እና የሚያስጨንቀን ነገር አይኖርም።
መልስ፦አዎ ከቅዳሴ በኋላ ማንኛውም ያስቀደሰ ሰው የቅዳሴ ፀበል መጠጣት፣ መጠመቅ መረጨትም ሆነ የቀደሱትን ካህን ቤትን ጸበል ማስረጨት ይችላል። የቀደሱት ካህናት እና የቆረቡት ምእመናን ግን ከቅዳሴ በኋላ ፀበል መጠጣት እንጂ መጠመቅ አይችሉም። ስለዚህ ጠያቂያችን ስርዓቱን በዚህ ይረዱት ዘንድ ለጥያቄዎ ይህን አጭር ምላሽ ልከንልዋታል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት ስለ ፀበል ያስተላለፍነውን ማብራሪያ አንብበው ይረዱ ዘንድ ከዚህ በትች ልከንልዎታል።
ፀበል በ2 ከፍለን ልናየው እንችላለን 1ኛው በቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ወይም ከቤተክርስቲያኑ ርቆ ባለ በፈቃደ እግዚአብሔር የበቁ መንፈሳዊ አባቶች በሰጡት አቅጣጫ የሚፈልቅ ፀበል አለ። 2ኛው ጠያቂያችን እንዳሉት በቅዳሴ ግዜ ከቅዱስ ስጋውና ከክቡር ደሙ ጋር አብሮ የሚሰጥ የቅዳሴ ፀበል አለ። የመጀመሪያው በቅጽር ቤተክርስቲያን ወይም ከቅጽረ ቤተክርስቲያን ውጭ ሁኖ በፈጣሪ ስም እና በቅዱሳን ስም የፈለቀው ፀበል የተለያየ ደዌ እና መናፍስት ያለባቸው እንዲም ደግሞ ጤነኛ ሰወች ለበረከት የሚጠመቁበትና የሚጠጡት እንዲሁም ቤታቸውን ንብረታቸውን ሀብታቸውን ከአጋንንት መንፈስ ለመጠበቅ የሚረጩበት ፀበል በእግዚአብሔር ቃል የተቀደሰ እና ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ፀጋ ያደረባቸው አባቶች በፀሎታቸው እና በቡራኬያቸው ያከበሩት ፀበል ስለሆነ ወደ ቤተክርስቲያን መቅረብ የቻለ ፀበሉን ከቤተክርስቲያን አገልጋዮች እጅ ተቀብሎ ይሄዳል፤ በተለያየ ምክንያት ወደቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ መቅረብ ያልቻሉ ግን በመልእክተኛ ወይም በሞግዚት ፀበሉ ተወስዶላቸው ፈውስ ያገኙበታል ማለት ነው። የዚህ አይነት ፀበል በዚህ አይነት አገልግሎት የሚፈፀም ነው። የዚህ በረከት መነሻ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በራሱ ፈቃድ ከ 38 አመት ጀምሮ በፅኑ ደዌ ታሞ የነበረውን መፃጉን በፈወሰው ግዜ መዳን ትወዳለህን ብሎ ሲጠይቀው ለመዳን ይችል ዘንድ ወደ ፀበሉ የሚያደርሰው የቅርብ ረዳት እንደሌለው እና ከሱ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው ፀበል የገቡ እንደሚድኑ ምስክርነቱን የሰጠበት የቅዱስ ወንጌል ቃል የሚያስረዳ ነው። (ዮሐ 5፥1-15)
2ኛውየቅዳሴ ፀበል ስለተባለው እንኳንስ ሰማያዊና ዘለአለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን ፀበል ቀርቶ በዚህ በምንኖርበት ምድራዊ ስርዓት እንኳን ከመጀመሪያው ጀምሮ በፕሮግራማችን ላይ የተገኘ ሰው ቅድሚያ ተሰጥቶት በአክብሮት ለዚያ ፕሮግራም የተዘጋጀውን የክብር መስተንግዶ እንደሚያገኝ በሁላችንም ዘንድ የተለመደ ስርዓት ነው። ከዚህ በላይ እጅግ የሚከብረውን እና ዘላለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን የቅዳሴ ፀበል በእለተ አርብ ጌታ በመስቀል ላይ ስለኛ በከፈለው ዋጋ ከቀኝ ጎኑ ማየ ህይወት (የህይወት ውሀ) የተገኘ ስለሆነ ቢያንስ እንኳን የበለጠ በረከትና ህይወት እንድናገኝበት ቁመን ካስቀድሰን በኋላ ቅዱስ ቁርባን ባንቀበል እንኳን ፀበሉን በበረከት መጠጣት እንደሚገባን ስርዓተ ቤተክርስቲያን ይፈቅዳል። ከዚህ ውጭ ግን በፈለግነው ሰአት እና ጊዜ መጥተን ቅዳሴውን ቁመን ሳናስቀድስ እና የቅዳሴውን ስርአት ሳንከታተል ፀበሉን ብንጠጣ ወደ ቤታችንም ብንወስደው እንደ ኀጢአተኛ ባያስቆጥርም እንኳን ከሰነፎች እንደ አንዱ ሊያስቆጥረን ይችላል። ምክንያቱም ጌታ በወንጌል እንደተናገረው አብዝቶ የሚወደውን ብዙ ኀጢአቱን ይቅር እንደሚል ወይም ብዙ በረከቱን እንደሚያድል፤ በጥቂቱ የሚወደውን ደግሞ ጥቂት ኀጢአቱን ይቅር እንደሚልና ጥቂት በረከት እንደሚሰጥ የተናገረው ለኛ መንፈሳዊ ህይወት እጅግ አስተማሪ ስለሆነ በዚሁ መሰረት እንድትረዱት መልዕክታችንን አናስተላልፋለን።
የቄደር ጥምቀት በንስኀ ቀኖና ውስጥ የሚካተት ስርዓት ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው የቄደር ጥምቀት የሚታዘዝለት ሃይማኖቱ ወይም ኦርቶዶክሳዊ የክርስትና ስርዓት የማይፈቅድለትን የተከለከለውንና ነውር የሆነውን ተግባር የፈፀመ ክርስቲያን የሚፈፅመው የንስሀ ቀኖና እንደሆነ ማወቅ ይገባል። የቄደር ጥምቀት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች የምግባር ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ከዚህ በፊት ቄደር ለመጠመቅ የሚያስፈልገንን ዋና ምክንያታዊ ነገር በፈፀምነው የኀጢአት ጥፋት ነው። ከዚህ በፊትም ለቄደር ጥምቀት የሚያበቁ የጥፋት ወይም የኀጢአት አይነቶችን በዝርዝር እና በስፋት ገልፀናቸዋል። ስለዚህ ማንኛውም ኦርቶደክሳዊ ክርስቲያን የፈፀመውን ኢክርስቲያናዊ ተግባር ወይም ኀጢአት በራሱ አምኖ እና ተፀፅቶ ለመንፈሳዊ አባቱ ሲናዘዝ እንደ ቤተክርስቲያናችን ቀኖና የቄደር ጥምቀት የሚያስፈልገው ጥፋት ሆኖ ከተገኘ የቄደር ጥምቀት እንዲደረግ ይደረጋል። በአንፃሩ የቄደር ጥምቀት የሚያስፈልገው አይነት ከሆነ ደግሞ አንቀፀ ንስኀው የቤተክርስቲያን ቀኖና በሚያዘው ሌላ የንስኀ ቀኖና ይሰጣል ማለት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን የቄደር ጥምቀት አንዱ የንስኀ ክፍል መሆኑን እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
በሰው ልጅ ዘንድ የሞት አደጋን የሚያስከትሉ ከፍተኛ ደዌ በተከሰተ ጊዜ፥ ለምሳሌ እንደ ኤች አይ ቪ እና እንደ ኮሮና እና ሌሎችም ገዳይ የሚባሉ በሽታዎች በሁሉም እርዳታ መከላከልና መዳን እንዲቻል ቢሆንና፤ ደግሞ መድኀኒቱን በማቋረጥ የሚያስከትለው አደጋ እስከ ሞት የሚያደርስ ስለሆነ በቤተክርስቲያን እነዚህን ታማሚወች መድኀኒቱን ፀበል እየጠጡም ሆነ እየተጠመቁ ማቋረጥ እንደሌለባቸው ከዚህ በፊት ከ ኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ በራስዋ ውሳኔ ፈቅዳለች። ስለዚህ የሀኪሞችም ህክምናም ሆነ መድሃኒት ከእግዚአብሔር ጥበብ የተከገኘ ስለሆነ ፀበሉም በእግዚአብሔር ቃል ተባርኮና ተቀድሶ የሚሰጥ ስለሆነ ሁለቱንም በፍፁም እምነት ለመድኀኒትነት የምንወስደው ስለሆነ ኀጢአት የመያስገባን ወይም ኀጢአተኞች የሚያሰኘን አለመሆኑን መረዳት ያስፈልገጋል።
በቤተክርስያን ቀኖና አንድ የተወለደ ህፃን ለሞት የሚያደርስ ደዌ ቢያሰጋው እንዲጠመቅ ይፈቀዳል። ይህም ሳይሆን ቀርቶ በእግዚአብሔር ቢጠራ ከላይ በ1ኛ ተ.ቁ. ላይ እንደገለፅነው የክርስቲያን ልጅ ክርስቲያን ነው እንዳልነው ሁሉ በዚያ የእድሜ ደረጃም ህፃናት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን፣ ሰውን የሚያስቀይም እዳ በደል የሚሆን ኀጢአት ያልፈፀሙ ስለሆኑ እነሱ የመንግስተ ሰማይ ልጆች ናቸው። ሄሮድስ በግፍ ያስገደላቸው እልፍ የቤተልሔም ሕፃናት ከመላእክት ማህበር እንደተቆሩ ሁሉ የእነዚህም ህፃናት እድል ፋንታ እንደዚህ ይሆናል። በመሰረቱ ስንት ኀጢአተኛ በበዛበት ዘመን እነዚህ ህፃናት ይኮነናሉ ወይ? ብሎ ማሰብ በራሱ የአይምሮን ደህንነት ጥያቄ ያስገባል። ማንኛውም ክርስቲያን እንድንጠመቅ አምላካዊ ትዕዛዝ ቢሆንም ተጠምቀን የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችንንና ፍፁም ክርስቲያን መሆናችን በእርሱ የረቀቀ ጥበቡ ከሰው ስንወለድ እንደሚገለፀው አካላዊ እይታ አይነት ከመንፈስ ቅዱስ ስንወለድ በአይናችን የምናየው በእጃችን የምንዳስሰው አይደለምና፤ ስለዚህ እነዚህ ህፃናት ደግሞ ከመላእክት ማህበር እንደሚደመሩ በረቀቀ ጥበቡ ስለሚፈፅመው እኛ የራሳችንን ስራ መስራት የሚገባንን ትተን በእግዚአብሔር ስራ ውስጥ ገብተን ሊያስጨንቀን የሚገባ አይደለም።
‘ሰው ከመጠመቁ በፊት ከርስቲያን ከሆነ ለምን እንጠመቃለን?’ ብለው ለጠየቁን ፤ በመሰረቱ ሰው ከመጠመቁ በፊት ክርስቲያን ነው የሚል አስተምሮ የለንም። ይህን በዝርዝር ለመረዳት ከፈለጉ ከዚህ በላይ የሰጠናቸውን መልሶች በማስተዋል እንዲያነቡ እንመክራለን።
ጠያቂያችን በጾም ጊዜ መጠመቅ ይቻላል ወይ ብለው ለጠየቁን መልሱ አዎ በደንብ አድርጎ ይቻላል ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ በፆም እና በፀሎት በተወሰነ ጊዜ ከስጋ ፈተና ሁሉ እርቆ እግዚአብሔርን መስሎ የሚኖርበት ህይወት ስለሆነ ያኔ መጠመቅም፣ ቅዱስ ቁርባን መቀበልም፣ ሌሎችንም መንፈሳዊ አገልግሎቶች መቀበል እንደውም ከሌላው ጊዜ የበለጠ እና የመረጠ ጊዜ ያደርገዋል። ስለዚህ ጠያቂያችን በፆም ጊዜ መጠመቅ አይከለከልም በማለት ይህን አጭር መልእክት ልከንልዎታል።
እጣን በብዙ መንገድ ምስጢራዊ አገልግሎት አለው። እጣንም እንደ ሃይማኖታችን ስርዓት ከተመለከትነው በዚህ ምድር ላይ በሃይማኖት እና በምግባር ስንኖር ለእግዚአብሔር ተገዚነታችንን በመግለፅ ለእውነተኛ ንጹሐ ባህሪይ የሁላችንም ፈጣሪና አምላክ ለሆነ ለልዑለ ባህሪይ ለእግዚአብሔር በአምልኮቱ ቀንተን ስንገዛለት የምናቀርበውን ምስጋና፣ ፀሎት ፣ መስዋዕት፣ መባ፣ በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር ክብር ይገባል ብለን ባለን የልጅነት መንፈስ በእሱ ፊት የምናቀርበውን ሁሉ እግዚአብሔር ወዶ እንደተቀበለልን የምናረጋገጥ የሁሉ ነገር ማሳረጊያና ማጠቃለያ ከሆነው የቤተክርስቲያን ምስጢር አንዱ ፀሎተ እጣን ወይም ደግሞ በእጣን የምናሳርግበት ስርዓት ነው። እግዚአብሔር ያቀረብንለትን አገልግሎት ወይም መስዋዕት ወይም መታዘዝ ወይም መባ ሁሉ ወዶ ተቀብሎታል የምንለው በእጣኑ አማካኝነት የምንፈፅመው ስርዓተ አምልኮት ነው። ቅዱስ መፅሐፍ እንደሚነግረን የፀሎታችንን እና የመስዋዕታችንን አቅርቦት ወደ እግዚአብሔር በእጣኑ አማካኝነት ስናሳርገው እንደተቀበለው ያረጋግጥልናል።
ስለዚህ ጠያቂያችን ከጥያቄዎ ሃሳብ እንደተረዳነው በቤታችን ውስጥ ወይም ደግሞ በግቢያችን አካባቢ እውነተኛ በሆነ የሃይማኖት ስርዓት ከሁሉ ፈተና ለመዳን ከፈለግን እኛ ከገበያ በገንዘብ ገዝተን ያመጣነውን ዕጣን በራንሳችን ስልጣን እና ዝግጅት ማጠን ሳይሆን፥ የቤተክርስቲያን አባቶችን ወይም ስልጣነ ክህነት ያላቸውን አገልጋዮች ጠርተን እነሱ እጣኑን የሚያከብሩበትን ስርዓተ ጸሎት አድርሰው እንደ ቤተክርስቲያኑ ስርዓት በቤታችን ግቢ ያለውን ማንኛውንም ፈተና ሁሉ ለማራቅ በሚያስችል መንገድ እነሱ ፀሎተ እጣኑን ያሳርጋሉ ወይም ያጥናሉ እንጂ እኛ ራሳችን ገዝተን እንደ አምልኮ ባእድ በገል የምናጨሰው እጣን ከስርዓተ አምልኮታችን ጋር የሚሄድ ስርዓት ስላልሆነ፤ እስካሁን ድረስ እንደበጎ ነገር በማሰብ የተደረገውን ጥፋት ሳይታወቅ እና ከአባቶቻችን ሳንረዳ ያደረግነው ስለሚሆን ብዙም የሚያጨናንቅ ጥፋት አይደለም። ከዚህ ጥያቄ መልስ በኋላ ግን እኛ በማናውቀው ልዩ ልዩ ምክንያት የሚመጣውን ፈተና ለማራቅ ግቢያችንን እና ወጥተን ወርደን በድካማችን ያፈራነውን ሃብታችንን ህይወታችንን ለማስባረክ ከፈለግን ሁላችንም የሚገባንን ጥንቃቄ አድርገን በአባቶቻችን ፈቃድ ፕሮግራም አድርገን እነሱ ከእጣን ጋር የሚያሳርጉትን ጸሎት ሁሉ በመፀለይ እጣኑን ባርከውና ቀድሰው በእጣኑ ላይም ሊፀለይ የሚገባውን ፀሎተ እጣን አድርሰው እነሱ ስርዓተ ማዕጠንቱን ሊያደርሱ ይገባቸዋል እንጂ እኛ በራሳችን ልናደርገው በቤተክርስቲያናችን ቀኖና አልተፈቀደልንም። እጣኑ በቤተክርስቲያን ስርዓት በካህናት አማካኝነት ሲታጠን የሚታጠነው እጣን ጭሱ መድሃኒተ ስጋ ነፍስ ነው፣ ደዌያችንን ያርቃል፣ እርኩስ መንፈስን ያባርራል፣ መአዛው መንፈስ ቅዱስን የበለጠ እንዲያድር ያደርጋልና በዚህ ስርዓት መፈፀም እንጂ የድርሻንን አለማወቅ በድፍረት ከአባቶች የክህነት ድርሻ ጋር መጋፋት አይገባም።
ስለዚህ ጠያቂያችን እስካሁን ባለማወቅ ባደረጉት ነገር እራስዎትን ማስጨነቅ አይኖርቦትም ነገር ግን ወደፊት በዚህ ምክር አገልግሎት እነዲፈፅሙ ይህን መልዕክት ለእርስዎ እና በአጠቃላይ ለአባላቶቻችን እንዲሁም ይህን መልዕክት የተመለከታችሁ ሁሉ እንዲህ አይነት ገጠመኝ ሲሆን በዚሁ ማብራሪያ እንድትፈፅሙ አደራ እንላለን።
ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር በቸርነቱ አይለየን
ጠያቂያችን በመጀመሪያ በሰው ዘንድ ባልተረጋገጠ እና እውነት ባልሆነ አሉባልታ የሰውን የግል ህይወት የሚያጥላሉ እና ሰውን ኀጢአተኛ በሚያደርጉ ሰወች ዘንድ በሚነገርና በሚወራው ሃሳብ ላይ በመነሳት ባልተረጋገጠ ሁኔታ የመጨረሻ ውሳኔና ድምዳሜ ላይ መድረስ አያስፈልግም። እኚህ አባት በትክክለኛ የሚያገለግሉበትን ወይም ደግሞ አባት ሆነው የሚኖሩበት ቤተክርስቲያን የት እንደሆነ ስናውቅ፣ በግል ህይወታቸውም ከስማቸው ጀምሮ ምን እንደሚመስል ምን እንደሚሰሩ የስራ ድርሻቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ስንችል በትክክለኛ እኚህ አባት የቅባት ሃይማኖት ተከታይ ናቸው ወይስ የእውነተኛ ቤተክርስቲያን አባት ናቸው የሚለውን ነገር መለየት እንችላለን፤ እንጂ መጀመሪያ ባልተረጋገጠ ምክንያት ሽብር ውስጥ መግባት አያስፈልግም።
እኚህን አባት ሰዎች በሚያሙት ነገር የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አገልጋይ ሆነው ሰዎች እንዲህ ነው ብለው የሚያሙት ነገር ከሆነ የፈለገ እሳቸው ራሳቸውን ደብቀው እውነተኛ አባት በመምሰል የሚሰጡት አገልግሎት የሚሰጡት የንስኀ ህይወት ከሆነ ምንም እንኳን ስልጣነ ክህንት ያላቸው አባቶቻችን የክርስቶስ እንደራሴዎች እና መልዕክተኞች ሆነው የንስኀ ህይወትን ቢሰጡንም ንስኀን ይቅር የሚል ኀጢአትን የሚያስተሰርይልን ግን እውነተኛው አምላክ እሱ የሁላችንም ፈጣሪ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው። እንዲህ አይነቶቹ አስመሳዮች አባቶች በህይወቱ ውስጥ ሳይኖሩ እውነተኛ አባት ነን ቢሉ በኀጢአት የሚጠየቁት እራሳቸው እንጂ በየዋህነት እውነተኛ አባቶች ናቸው ብሎ የንስኀ ህይወትን ለመቀበል የሄደ ምዕመን በኀጢአት ስለማይጠየቅ በዚህ መጨናነቅ ፈፅሞ አያስፈልግም።
ነገር ግን እያወቅን እየተነገረን እየተረዳን፣ በግልፅ የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ማስረጃ እያለን፣ እራሳችን በሃይማኖት ለማይመስሉን አባት ወይም ከእውነተኛይቱ ሃይማኖት ያልሆኑት ሰው ጋር በመሄድ ንስኀ ብንቀበል የራሳችን ጥፋት ስለሆነ እንደገና ዳግም ሌላ አባት ጋር ሄደን የመጀመሪያ ስህተታችንን ነግረን ንስኀ የሚያስገባንንም ኀጢአታችንን ተናዘን ንስኀ መግባት አለብን እንጂ በመጠራጠር ገና ሰዎች በሚያሙት ነገር ግን መጨነቅ የሚያስፈልገን እና እኛን የሚያስጠይቀን አይደለም። ማሰብም የለብን፤ ተገቢም ፈፅሞ አይደለም። ሁሌ ጥሩነትና ገርነት የዋህነት በበዛበት ህይወት ውስጥ የምንኖር ክርስቲያኖች ከምንም በላይ እግዚአብሔር ይህን ጥሩነታችንን ገርነታችንን የዋህነታችንን ተመልክቶ ለማንም አሳልፎ የማይሰጠን አምላክ ስለሆነ በዚህ እኛ በማናውቀው የረቀቀ የስህተት መንፈስ የሚሄዱ ሰዎች ያስጠይቃቸዋል በዚህ በደል ወይም በዚህ የስህተት ወጥመድ እነሱ ራሳቸው ይያዛሉ እንጂ በቅንነት እና በየዋህነት ኀጢአታቸውን ለመናዘዝ የቀረቡትን የእግዚአብሔር ሰዎችን የሚያስወቅስና እንደኀጢአተኛ የሚያስጠይቃቸው ስላልሆነ ጠያቂያችን ከእንዲህ አይነት ሃሳብ እራስዎትን ነፃ እንዲያደርጉ ይህንን መልዕክት አስተላልፈናል። ሌሎች አባላቶቻችንም ይህን የሚመስል ፈተና ያጋጠማችሁ እና ወደፊትም የሚገጥማችሁ ካላችሁ በዚሁ ተረዱልን።
ለሁሉም ነገር ቸሩ አምላካችን ልዑለ እግዚአብሔር በየጊዜው ከሚገጥመን ፈተና እና መከራ ሁሉ ይሰውረን፥ ይጠብቀን ፆሙን በሰላም ያስፈፅመን !
ጠያቂያችን ፤ በቤታችን ውስጥ ፀበል መጠመቅ ቢያስፈልገን ሀብተ ክህነት ወይም ክህነት የሌለው ሰው ማጥመቅ አይችልም። ነገር ግን በአካባቢያችን ካህን የማይገኝ ቢሆን ካህኑ በውሀው ላይ ፀሎት ፀልየውበት በመስቀልም ባርከውት አንተው በላይህ ላይ ፀበሉን እያፈሰስክ ተጠመቅ ብለው ከሰጡን መረጨትም ሆነ በራሳችን ላይ ማፍሰስ እንችላለን። ይህ ግን ማጥመቅን የሚተካ ስርዓት አይደለም። ወደ ገዳም ሄደን የምናመጣው ፀበል ከአባቶች ተፈቅዶ በእቃ የምናውለው ፀበል እኛም ራሳችን መረጨትም እንችላለን ቤተሰቦቻችንም ፀበሉን እንዲጠጡትም ሆነ ሰውነታቸውን እንዲቀቡት ማድረግ ይቻላል፤ ካህንን ተክቶ ግን አንዱ አንዱን ማጥመቅ አይችልም።
ለተጨማሪ ግንዛቤ ከዚህ በፊት ስለ ጸበል አጠቃቀምና ወደ ቤት የመውሰድ ስርዓት እንዴት እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦልን ያሰተላለፍነውን ትምህርታዊ ማብራሪያ ከዚህ በታች ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት፦
ከቅዳሴ በኋላ ማንኛውም ያስቀደሰ ሰው የቅዳሴ ፀበል መጠጣት፣ መጠመቅ መረጨትም ሆነ የቀደሱትን ካህን ቤትን ጸበል ማስረጨት ይችላል። የቀደሱት ካህናት እና የቆረቡት ምእመናን ግን ከቅዳሴ በኋላ ፀበል መጠጣት እንጂ መጠመቅ አይችሉም።
ፀበል በ2 ከፍለን ልናየው እንችላለን 1ኛው በቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ወይም ከቤተክርስቲያኑ ርቆ ባለ በፈቃደ እግዚአብሔር የበቁ መንፈሳዊ አባቶች በሰጡት አቅጣጫ የሚፈልቅ ፀበል አለ። 2ኛው ጠያቂያችን እንዳሉት በቅዳሴ ግዜ ከቅዱስ ስጋውና ከክቡር ደሙ ጋር አብሮ የሚሰጥ የቅዳሴ ፀበል አለ። የመጀመሪያው በቅጽር ቤተክርስቲያን ወይም ከቅጽረ ቤተክርስቲያን ውጭ ሁኖ በፈጣሪ ስም እና በቅዱሳን ስም የፈለቀው ፀበል የተለያየ ደዌ እና መናፍስት ያለባቸው እንዲም ደግሞ ጤነኛ ሰወች ለበረከት የሚጠመቁበትና የሚጠጡት እንዲሁም ቤታቸውን ንብረታቸውን ሀብታቸውን ከአጋንንት መንፈስ ለመጠበቅ የሚረጩበት ፀበል በእግዚአብሔር ቃል የተቀደሰ እና ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ፀጋ ያደረባቸው አባቶች በፀሎታቸው እና በቡራኬያቸው ያከበሩት ፀበል ስለሆነ ወደ ቤተክርስቲያን መቅረብ የቻለ ፀበሉን ከቤተክርስቲያን አገልጋዮች እጅ ተቀብሎ ይሄዳል፤ በተለያየ ምክንያት ወደቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ መቅረብ ያልቻሉ ግን በመልእክተኛ ወይም በሞግዚት ፀበሉ ተወስዶላቸው ፈውስ ያገኙበታል ማለት ነው። የዚህ አይነት ፀበል በዚህ አይነት አገልግሎት የሚፈፀም ነው። የዚህ በረከት መነሻ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በራሱ ፈቃድ ከ 38 አመት ጀምሮ በፅኑ ደዌ ታሞ የነበረውን መፃጉን በፈወሰው ግዜ መዳን ትወዳለህን ብሎ ሲጠይቀው ለመዳን ይችል ዘንድ ወደ ፀበሉ የሚያደርሰው የቅርብ ረዳት እንደሌለው እና ከሱ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው ፀበል የገቡ እንደሚድኑ ምስክርነቱን የሰጠበት የቅዱስ ወንጌል ቃል የሚያስረዳ ነው። (ዮሐ 5፥1-15)
2ኛውየቅዳሴ ፀበል ስለተባለው እንኳንስ ሰማያዊና ዘለአለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን ፀበል ቀርቶ በዚህ በምንኖርበት ምድራዊ ስርዓት እንኳን ከመጀመሪያው ጀምሮ በፕሮግራማችን ላይ የተገኘ ሰው ቅድሚያ ተሰጥቶት በአክብሮት ለዚያ ፕሮግራም የተዘጋጀውን የክብር መስተንግዶ እንደሚያገኝ በሁላችንም ዘንድ የተለመደ ስርዓት ነው። ከዚህ በላይ እጅግ የሚከብረውን እና ዘላለማዊ ህይወት የሚያሰጠውን የቅዳሴ ፀበል በእለተ አርብ ጌታ በመስቀል ላይ ስለኛ በከፈለው ዋጋ ከቀኝ ጎኑ ማየ ህይወት (የህይወት ውሀ) የተገኘ ስለሆነ ቢያንስ እንኳን የበለጠ በረከትና ህይወት እንድናገኝበት ቁመን ካስቀድሰን በኋላ ቅዱስ ቁርባን ባንቀበል እንኳን ፀበሉን በበረከት መጠጣት እንደሚገባን ስርዓተ ቤተክርስቲያን ይፈቅዳል። ከዚህ ውጭ ግን በፈለግነው ሰአት እና ጊዜ መጥተን ቅዳሴውን ቁመን ሳናስቀድስ እና የቅዳሴውን ስርአት ሳንከታተል ፀበሉን ብንጠጣ ወደ ቤታችንም ብንወስደው እንደ ኀጢአተኛ ባያስቆጥርም እንኳን ከሰነፎች እንደ አንዱ ሊያስቆጥረን ይችላል። ምክንያቱም ጌታ በወንጌል እንደተናገረው አብዝቶ የሚወደውን ብዙ ኀጢአቱን ይቅር እንደሚል ወይም ብዙ በረከቱን እንደሚያድል፤ በጥቂቱ የሚወደውን ደግሞ ጥቂት ኀጢአቱን ይቅር እንደሚልና ጥቂት በረከት እንደሚሰጥ የተናገረው ለኛ መንፈሳዊ ህይወት እጅግ አስተማሪ ስለሆነ በዚሁ መሰረት እንድትረዱት መልዕክታችንን አናስተላልፋለን።