ስለ እኛ ጥያቄና መልስ
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ እኛ
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
መልስ ፦ ጠያቂያችን ያቀረቡልን ጥያቄ ብዙም ግልፅ ባይሆንም የዮሐንስ ንስሓ የሚለው አገላለፅዎ እንዲስተካከል ሆኖ ነገር ግን የዚህ ድረገፃችን ዮሐንስ ንስሓ በሚል ስያሜ መጠራቱን በሚመለከት ከሆነ፤ እንደሚታወቀው መጥምቁ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የጌታን መገለጥ እና የመጨረሻውን የሰው ልጅ ድህነት ሊያረጋግጥ መምጣቱን ለመናገር ከሱ መገለጥ አስቀድሞ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ በማለት የአዲስ ኪዳን የንስሓ ህይወት ሰባኪ እና ሐዋርያ ሆኖ በግልፅ ስለመሰከረ ይሄንን የቅዱስ ዮሐንስን ስብከት መሰረት በማድረግ የተሰጠ ስያሜ ስለሆነ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመቅረብ ሰወችን ሁሉ ለማበረታታት እና ከተኙበት የኀጢአት እንቅልፍ ለማንቃት የንስሓ ደውልና ጥሪ እንዲሆናቸው የተጠቀምንበት መንገድ መሆኑን እንዲያውቁት። ስለዚህ መዳን በዮሐንስ ንስሓ ብቻ የሚለውን አነጋገር ትተው ማንኛውም ሰው እውነተኛ ክርስቲያናዊ ህይወት ለማግኘት ተፀፅቶ ንስሓ ከገባ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ እንደነገረን የእግዚአብሔር መንግስትን መውረስ ይቻላል። የእግዚአብሔር መንግስት ደግሞ በብዙ ውጣ ውረድ በብዙ ድካምና ጥረት በብዙ ሃይማኖታዊ ተጋድሎና መንፈሳዊ ህይወት የምትወረስ ስለሆነ እንደ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ለንስሓ የሚያበቃ እውነተኛውን የኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ስብከት የሚነግረን ሁሉ ለመንግስተ ሰማይ ስለሚያበቃን ሃሳቡን በዚህ መንገድ ይረዱት ዘንድ ይህን መልእክት እንዲደርስዎ አድርገናል።
መልስ፦ ጠያቂያችን በንስኀ አባቶች ዙርያ የሰጡት የጥርጣሬ ሃሳብ ከትክክለኛ አማኝ ወይም ክርስቲያን ዘንድ የሚጠበቅ አባባል አይደለም። የስልጠና ክህነት ፀጋ በምድራዊ የሹመት ደረጃ የሚታይ ስላልሆነ ፤ ፀጋው የክህነት ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ የሚጨበጥ ወይም በአይን የሚታይና በስጋዊ ጥበብ ሊመረመር የሚችል አይደለም :: በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲያሥሩና እንዲፈቱ የሰጣቸው ስልጣነ ክህነት የጊዜና የቦታ ርቀት የማይወስነው ስለሆነ ፤ በአካባቢው አባት የሚሆን ካህን ከጠፋ ያለጠባቂ ብንኖር ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍሳችንን እንዳይነጥቃት የንስሐ አባት በርቀትም መያዝ እንችላለን። ስለዚህ ጠያቂያችን ማወቅ ያለብዎት ንስኀ በአካልም ይሁን በርቀት-በመገናኛ መንገድ ፤ ዋነኛው አላማው የሰራነውን በደላችንን እና ኀጢአታችንን በንስሓ ማጥፋት ነው። የካህኑ ክህነት የሚመዘነው በሃይማኖቱ እና በምግባሩ ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር በተሰጠው አደራ መሰረት መንጋውን በስርዓት የሚያሰማራ የእግዚአብሔርን ቃል የሚፈፁም ፣ ስጋ ደሙን ተቀበሉ የሚል ፣ ኀጢአት አትስሩ የሚል፣ በምግባር በሃይማኖት ፀንታችሁ ኑሩ የሚል ፣ በነገሮች ሁሉ ከሰዎች ጋር በሰላምና በፍቅር አንድንኖር የሚመክር፣ የቱሩፉት ስራ አብዝተን እንድንሰራ የፅድቅን አቅጣጫ ወይም የጽድቅን በር የሚያሳይ አባት ከሆነ ትክክለኛ ካህን መሆኑን የምናረጋግጥበት ምስጢር ይህ ነው :: ከዚህ ውጭ በአንዳንድ ሰዎች ህሊና የሃይማኖት ህፀፅ የኑፋቄ እና የክህደት ትምህርት ሲያድርባቸዉ እንዲህ አይነት የነቀፉ ጥያቄ ሲቀርቡ የመሰማታችን ጉዳይ የተለመደ ስለሆነ ነገር ግን በዚህ ፕሮግራም ይህን ጥያቄ ያቀረቡ አባል ከምን አኳያ እንደሆነ ብዙ ግልፅ አይደለም :: ምክንያቱም ካህናትን ለመንቀፍ ታስቦ ይሁን ወይም እኛ ያልተረዳነው ችግር አጋጥሞዎት ይሁን ለመረዳት የሚያዳግት ሃሳብ ስለሆነ አመለካከትዎን ቢያስተካክሉት ከሁሉ የተሻለ መሆኑን እንመክራለን :: ለቅዱሳን የመማፀኑ እና የአማላጅነት ጥያቄ ማቅረቡ እኛንም የሚያስደስተን ዋና አላማችን ቢሆንም ነገር ግን ዛሬ ላይ በመከራም በደስታም በመካከላችን የሚያገለግሉንን ካህናትን ለመንቀፍ የተጠቀሙበት ሃይለ ቃል ከሆነ ግን እንዲያስተካክሉ ምክራችንን በታላቅ አክብሮት እና ትህትና እንለግሳለን። በተጨማሪም ስለ ስልጣነ ክህነት ከመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ማስረጃ ለጠየቁት ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን ትምህርት እንደሚከተለው ልከንልዎታልና አንብበው እንዲረዱ እመክራለን።
“የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ ፲፮᎓፲፱) ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸው የክህነት ስልጣን ማሰር እና መፍታት የሚችሉበት ረቂቅ እና ሰማያዊ ስልጣንን ነው። ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባትም ሆነ ከመንግስተ ሰማያት ለመከልከል የሚያስችል ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው ስልጣንም ነው። ይህ ማለት ስልጣን ሁሉ የራሱ ገንዘብ የሆነው የባህርይ አምላክ እየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ሐዋርያት እና 72ቱን አርድእት ከዓለም መካከል መርጦ በሾማቸው ግዜ ኀጥያት ሰርተው በደል ፈጽመው ወደ ሐዋርያት ቀርበው በኀጢአታቸው ተጸጽተው የተናዘዙትን ኀጥያታቸውን የማስተሰረይ ስልጣን ስለተሰጣቸው ኀጥያታችሁ ይቅርላችሁ ያሏቸው ሁሉ የተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ኅጥያታቸው ሁሉ እንዲደመሰስ ያደርጋል።
በሰሩት ጥፋት ሳይጸጸቱ እና ከበደላቸው የማይመለሱትን ደግሞ በተሰጣቸው ረቂቅ ስልጣን ሲፈርዱባቸው በስጋቸው ሞትና ልዩ ልዩ መቅሰፍት ይቀጣሉ ማለት ነው።
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፦
– ግያዝ የተባለው የነብዩ ኤልሳዕ ደቀመዝሙር ከመምህሩ ተሰውሮ ከለምጽ በሽታ ካዳነው ሶርያው ንጉስ ከንዕማን ላይ የማይገባውን ጥቅም በመውሰዱ ምክንያት ነብዩ ኤልሳዕ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ ግያዝን በለምጽ ደዌ አንደቀጣው እንመለከታለን። 2ኛ ነገስት 5፥20-27
– ሐናንያ እና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች በሐዋርያት ፊት ያላቸውን የሀብታቸውን እኩሌታ ለእግዚአብሔር ሊሰጡ ቃል ከገቡ በኋላ ሳይፈጽሙ በመቅረታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን አታላችኋል ብሎ በተሰጠው የክህነት ስልጣኑ የሞት ቅጣት እንዲደርስባቸው አድርጓል። የሐዋ 5፥1-10
– በጥንቆላ መንፈስ የሚኖር ሲሞን መሠሪ የተባለው ሰው ሐዋርያት እጅ በመጫን የመንፈስ ቅዱስ ኅይል የሚሰሩትን አስደናቂ ሚስጥር ባየ ግዜ እንደእናንተ ይሄንን ታላቅ አስደናቂ ስራ ለመስራት እንድችል ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን ስልጣን በገንዘብ ሽጡልኝ ባላቸው ግዜ እድል ፋንታውን ከክፉዎች ጋር እንዲሆን እና የጥፋት ሰው አንደሆነ ረግመውታል። ዩሐ 8፥18-24
ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ማስረጃዎች የመንግሰተ ሰማያት መክፈቻ ለሐዋርያት ተሰጠ ሲባል በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት መንግስተ ሰማያት ማስገባት እንደሚችሉ እና የማይገባቸውን መከልከል የሚችሉ መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ የቤት ወይም የበር ቁልፍ መክፈቻና መዝጊያ ቁሳዊ ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማሰር መፍታት የሚለውም በዚህ አለም ላይ ሰው በፈጸመው ወንጀል የሚታሰርበት እግር ብረት ወይም ገመድ ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን ከላይ እንደገለጽነው በተሰጣቸው ረቂቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣን ኅጥያትን የማስተሰረይ፣ የኀጥያተኞችን ኅጥያት የመያዝ ፀጋ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ጠያቂያችን እንዲሁም ሌሎች የዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ አባላት፤ በልዩ ምክንያት ወይም ለተጨማሪ ምክርና ማብራሪያ ደውለው ሊያገኙን እንደሚችሉ ገልፀን ስልክ ቁጥር በውስጥ መስመር አንዲደርሳችሁ ካደረግን በማንኛውም ጊዜ ማለትም ከሰኞ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት ከጠዋቱ 3 ሰአት እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ባለው ጊዜ ውስጥ ደውለው ሊያናግሩን እንደሚችሉ እንገልፃለን።
መልስ፦ጠያቂያችን የንስኅ አባት በመያዝ በደወሉ ጊዜ በመጀመርያ መግባባት እንዳልቻሉና ሆኖም የደወሉላቸው አባት ለበጎ ነገር እንደሆነ በመገንዘብ ተቀብለው እባት እንደሆኑዎት የገለፁልንን አስተያየት ተመልክተነዋል። በእርግጥ በኛ በኩል በሁሉም ቦታ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየክልሉና በየአካባቢው የሚገኙ አባቶችን አመቺ በሆነ ሁኔታ በወቅቱ የንስኅ አባት እንዲሆኑ በማዘጋጀት አላማውንም በማስረዳት የሚደውሉላቸውን የመንፈሳዊ ልጆች ተቀብለው የንስኅ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ መስራታችን እውነት ነው። በዚህም አንዳንድ አባቶች እንደተደወለላቸውና አገልግሎቱንም እየሰጡ እንደሆነ እናውቃለን፤ ከአባላቶቻችን በየጊዜው ከሚደርሱን መልዕክትና አስተያየትም በዚሁ ድረገፅ አማካኝነት የንስኅ አባት አግኝተው በአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሆኑ መስክረዋል። ነገር ግን አንዳንድ አባቶች ጋር በወቅቱ አባት ፈልጎ የደወለላቸው ሰው ባለመኖሩ ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ሲደወልላቸው ሊዘነጉ እንደቻሉ ከአባላት ከደረሰን አስተያየት ተነስተን ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ካናገርናቸው አባቶች ተገንዝበናል። የሆነ ሆኖ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው እንዲሉ ዋናው ነገር እንዲህ አይነት ጥቃቅን ችግር በሚገጥም ጊዜ መበርገግ እንደሌለባችሁ እየመከርን፤ ምንም አይነት የተቸገራችሁበት ነገር ካለ በቀላሉ እዛው ድረገፁ ላይ ባስቀመጥነው ስልክ ቢደውሉ በኛ ዘንድ አስፈላጊውን አገልግሎት ያገኛሉ። እናንተ የሚያስተምር እና የሚመክር አባት ለማግኘት ለንስኅ ህይወት አላማ ፀንታችሁ ከተጋችሁ እኛም ለእናንተ ምቹ ሁኔታዎችን ለማዘጋጀት የሚከብድ አይደለምና አባት የሚሆናችሁን በአድራሻችሁ የምንሰጣችሁ መሆኑን ተገንዝባችሁ በዚህ ሁኔታ አንዳችም ነገር የሚያስጨንቃችሁ አጋጣሚ እንደማይኖር ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
ጠያቂያችን በዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፖሮግራም ተደራሽ የምናደርገውን ተከታታይ ትምህርትና እና ጥያቄና መልሶችን በማንበብዎና በመከታተልዎ እኛም እጅግ አድርገን እናመሰግናለን። በእንዲህ አይነት መንፈሳዊ አገልግሎት ፀንተን እንድንኖር እግዚአብሔር ለሁላችንም የፅድቅ መንገድ ያመቻቸልን ስለሆነ ከጠፋንበትም ተመልሰን በእግዚአብሔር እቅፍ ስር እንድንሆን አስተማሪዎችን መካሪዎችን ያላሳጣን ስለሆነ ሁላችንም ተያይዘን የእግዚአብሔርን መንግስት የምንወርስበትን በጎ ስራ ሁሉ ማስቀደም ስላለብን፤ እርስዎም የእግዚአብሔርን ቃል ለመመከር ቅድሚያ መስጠትን ወደፊትም ቸል እንዳይሉ አደራ በማለት ለጠየቁን ጥያቄም በውስጥ መስመር በሰጠነው አድራሻ ያገኙን ዘንድ የኛም ፈቃድ ነው።
የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስሐ ድረ-ገጽ አባላት፤ እንደሚታወቀው ያለ መቋረጥ ዘወትር ጠዋት እና ማታ በቀን ሁለት ጊዜ ትምሕርተ ሃይማኖት እና ከአባላት የሚቀርቡልንን ልዩ ልዩ ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በቴሌግራም አና በፌስቡክ ቻናላችን እያስተላለፍን እንገኛለን እናንተም በትምህርቱ ተጠቃሚ እንደሆናችሁ ከምትልኩልን መልእክቶች ተገንዝበናል። አሁንም የእናንተን ጥያቄና አስተያየት ተቀብለን በቴሌግራም አና በፌስቡክ ከምናስተላልፈፈው በተጨማሪ የዩቱብ ቻናል የድምፅ ስርጭት ከፍተን አገልግሎት መጀመራችንን በደስታ እንገልፃለን!
አስረግጠን እውነቱን የምንነግራችሁ በዚህ አላማችን ውስጥ ከእውነተኛ ኦርቶዶክስ አስተምሮ አንፃር አባቶች የሚያስተላልፉልን ትምህርት እና ምክር የመናፍቅነት፣ የክህደት፣ የስነምግባር ችግሮች ቦታ እንዳይኖራቸው ሰይጣንን ከብዙ ህይወት ውስጥ ሳይወድ በግድ ታግለን በእግዚአብሔር ሃይል እና ጥበብ ለመለየት በዘመኑ የሰለጠነውን የኀጢአት እና የክፋት መንገድ አስቀርተን ፣ እንዲሁም ትክክለኛ ትምህርት ካለማግኘት በጥርጥር ፈተና ላይ የወደቁትን ወገኖች እያስተማርንና እየመከርን ሁላችሁም የዘላለም ህይወት እንድታገኙ እስካሁንም ብዙ ተጉዘናል ወደፊትም እግዚአብሔር ከኛ ጋር እስከሆነ ድረስ የሚያቆመን የለም።
በመሆኑም በሚሰጠው ትምህርትና ባጠቃላይ በድረገጹ ለይ ያላችሁን የግል አስተያየት በመስጠት አገልገሎቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየተስፋፋ እንዲሄድ የበኩላችሁን ድጋፍና ተሳትፎ በቴሌግራም ፣ በፌስቡክ፣ በዩቱብ ቻናላችን እንድታደርጉ ፣ በየቀኑ የምናስተላልፈውንም መንፈሳዊ ትምህርት እየተከታተላችሁ አንዱ አንዱን እያበረታው እና እያገዘው የምንሄድበትን አጭር መልዕክት በመለዋወጥ እንዲሁም ከዚህ በታች ያሉትን ሊንኮች በቀላሉ ለሌሎች ወገኖች ሼር በማድረግ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትጋብዟቸው ዘንድ በአጽንዎት እንጠይቃለን።
በአጠቃላይ ይህ ተወዳጅ የሆነውና ታላቅ መንፈሳዊ አላማ የያዘው ቻናላችን በእግዚአብሔር ቸርነት እየታገዘ እና እየተስፋፋ እንዲቀጥል የእናንተ የአባላት ዋና ድርሻ የሚሆነው እና በእግዚአብሔር ስም አደራ የምንላችሁ ይህን የቴሌግራም ግሩፕና የዩቱብ ቻናላችንን ለሌሎች ወገኖች ሼር በማድረግ እንድታስፋፉት ነው !!!
የ #ዩቱብ_ቻናላችን አድራሻ፦https://www.youtube.com/
የ #ድረገፃችን አድራሻ:- yohannesneseha.org
የ #ቴሌግራም ግሩፓችን አድራሻ:- https://t.me/joinchat/
የ #ፌስቡክ ገፅችን አድራሻ:- https://www.facebook.com/
የ #ኢሜል አድራሻችን:- yohannes.neseha@gmail.com
በውስጥ መስመር ወይም በግል ልታገኙን የፈለጋችሁ አባላቶቻችን በቴሌግራም፣ በፌስቡክ ወይም በኢሜል የግል መልእክት ልትልኩልን ትችላላችሁ።
በቴሌግራም የግል መልእክት ለመላክ “ዮን” የሚለውን የአካውንታችንን መለያን በመጫን ወይም የአባሎችን ዝርዝር ተጭነው <<ዮሐንስ ንስሐ >> “owner” የሚለውን በመጫን ሊፅፉልን ይችላሉ።
የዮሐንስ ንስኀ ድረገጽ መንፈሳዊ ትምህርት አና ምክር እንዲሁም ለጥያቄዎ መልስ ለማግኘት፣
ድረገፃችንን:- yohannesneseha.org
ወይም ቴሌግራም ግሩፓችንን:- https://t.me/joinchat/
ወይም የፌስቡክ ገፅችንን:- https://www.facebook.com/
የዩቱብ_ቻናላችን አድራሻ፦https://www.youtube.com/
ወይም ኢሜል አድራሻችንን:- yohannes.neseha@gmail.com
በመጠቀም ሊያገኙን እንደሚችሉ እንገልፃለን።
ጠያቂያችን፤ ተጨማሪ አድራሻ በውስጥ መስመር ለእርስዎ የላክንልዎ ስለሆነ በዚያም ሊያገኙን ይችላሉ።
ጠያቂያችን ለሰጡን ገንቢ ሃሳብ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፤ በእኛም በኩል ትምህርቱን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማዳረስ እቅዳችን ነው። ይህን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት እስከምንችል ግን ለጊዜው አሁን እርስዎ በጠየቁን መሰረት መደበኛ ተከታታይ ትምህርቶችን እና የብዙ ሰው ጥያቄ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ያሰብናቸውን ጠቃሚ መልሶችና ምክር መርጠን በአንድ ላይ አድርገን ወደ ኦሮምኛ በማስተርጎም በድረገጻችን ላይ ስለምናስቀምጥ በትእግስት ሆነው ይጠባበቁን። በሂደትም ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት በአገር ውስጥ እና በአለም ዙሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች ለማዳረስ አንዱ እቅዳችን መሆኑን ለአባላት ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ለማስታወቅ እንወዳለን።
ለሁሉም እግዚአብሔር ይርዳን።