ስለ ንስሐ ጥያቄና መልስ ቁ.3

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ንስሐ ጥያቄና መልስ ቁ.3

ስለ ንስሐ ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች

ጠያቂያችን፤   የንስኀ ጾም ራሱን የቻለ የነፍስ ጥቅም ወይም ትርፍ የምናገኝበት ስለሆነ በአዋጅ ፆም ላይ ተደርቦ ሊሰጥ አይገባም። ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ ጥያቄዎች ባስተላለፍነው  መልዕክት ዝርዝር ተጨማሪ ግንዛቤ ያገኙ ዘንድ ከዚህ በታች አያይዘን ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት ። 

👉ቀርቦ የነበረው ጥያቄ፦  ሰላም አባቴ……አንዳንድ ሰዎች በፆም ግዜ ንስሀ አይሆንም…. ንስሀ ራሱን የቻለ ፆም እና ስግደት ያለው ነው ከአፅዋማት ቀናት ጋር መገናኘት የለበትም ሲሉ ሰምቻለው…….አሁን ንስሀ መግባት የሚፈልግ ሰው የግድ የአብይ ፆም እስኪያልቅ መጠበቅ አለበት?…..አሁን ንስሀ ልግባ ቢል እንኳን ቀኖና ሳይጨርስ የካቲት 29 አብይ ፆም ቢገባበትስ?….ወይስ የእኔ አረዳድ ስህተት ነው ምናልባት በአብይ ፆም ወቅት ንስሀ መግባት ይቻል ይሁን?

👉ያስተላለፍነው ምላሽ፦ በመሰረቱ ማንኛውም ክርስቲያን የሚሰራው የኀጢአት አይነትና መጠን የተለያየ እስከሆነ ድረስ  ንስኀ ገብተን የምንቀበለውም ቀኖና እንዲሁ የተለያየ ይሆናል። ማለትም፦ ላንዱ ከፍተኛ ቀኖና የሚያስፈልገው ሲሆን ሌላው ደግሞ መካከለኛ የቀኖና አይነት የሚያስፈልገው ይሆናል፣ አንዳንዱ ደግሞ ጥቃቅን ወይም መለስተኛ አይነት ቀኖና የሚሰጥበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ፤ ንስኀ ለመስጠት ወይም ኀጢአትን ለመናዘዝ ስልጣነ ክህነት ወይም የንስኀ አባቶቻችን ካህናት ለእያንዳንዱ የኀጢአት አይነት ንስኀ ሲሰጡን የቤተክርስቲያናችን ቀኖና አንቀፀ ንስኀው በሚያዘው መሰረት ስለሆነ እንደ ኀጢአታችን አይነት ለንስኀው ቀኖና መቼ መግባት እንዳለብን የቀኑን ብዛትም ሆነ የጊዜውን ውሳኔ እነሱ በሚያዙን መሰረት ይሆናል። ንስኀውም በፆም ወይም በስግደት ፣ ወይም በፀሎት፣ ወይም በምፅዋት ፣ ወይም ደግሞ በሌላ የቱሩፋት ስራ መፈፀም ካለበት እነሱ በሚነግሩን መሰረት የሚከናወን ይሆናል።

በዚሁ መሰረት ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላት ስለ ንስኀ ቀኖና መረዳት ያለብን፦

1ኛ/ ብዙ የፆም እና የስግደት ጊዜ የሚያስፈልገው ከባድ ኀጢአት ሰርተን ብንገኝ የምንፆምበት የሰዓት ገደብ እንደመደበኛው ፆም መሆን ስለሚችልና ፣ የምንሰግደውም የንስኀ ስግደት ብዙ ከሆነ ከመደበኛው የፆም ስግደት ጋር ደምረን ብንፀፆም እና ብንሰግድ እኛም ልንጎዳ ስለምንችል የመደበኛ ፆም ጊዜ እና ለንስኀ የምንፆምበት ጊዜ ስለሚጋጭ ወይም የንስኀውን የፆም ጊዜ ስለማይሸፍን ለዚህ ነው ለያይተን መፆም ያለብን ወይም በፆም ላይ ንስኀ የማይሰጠው።  

ያ ማለት ግን ሰው በኀጢአት ተጨማልቆ መቼ ፈተና እንደሚገጥመው ወይም በሞት እንደሚጠራ እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ፥ መደበኛ የፆም ጊዜ እስከሚያልቅ ብሎ በስንፍና የኀጢአት ሀብት እያካበተ ወይም የኀጢአት የቀጠሮ ጊዜውን እያስረዘመ መቆየት የለበትም። ለዚህም መፍትሄው በቤተክርስቲያን ቀኖና ስለ ንስኀ የተደነገገውን በመመርመር በመደበኛ ፆምም ላይ ቢሆን የንስኀውን ፆም ጊዜ እና ሰዓት ጨምሮ በመፆም፣   የንስኀውን ስግደትም በመደበኛው የጾም ስግደት ላይ በመጨመር፣ ሌላውንም ትዕትዕዛዛችንን ከዚሁ ጋር አካተን መፈፀም እንችላለን።

2ኛ/ ሌላው፤ መደበኛ ፆም ገብቶ እስከሚያልቅ ከመጠበቅ ይልቅ ከመደበኛ ፆም ቀድመን ንስኀ መግባት እንችላለን። ዋናው መታወቅ ያለበት፥ ክርስቲያን መሆን ከስጋ ፆም መጾም ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ መስጠት ስለሚገባው ቅድሚያ እየሰጡ በሁሉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ለማግኘት ስጋንም ቢሆን በመጉዳት ለስጋዊ የምናውለውን ጊዜያችንን ቀንሰን ለነፍሳችን በማትረፍ ንስኀ ልንገባ ያስፈልጋል።

3ኛ/  ክርስቲያን በሀሳብም ፣ በንግግርም፣ በገቢርም ሳናውቅም እያወቅንም የምንሰራቸው የኀጢአት አይነቶች ብዙ ስለሆኑ ፥ ቀን የዋለው ቢያድር፣ ሌሊት ያደረው ቢውል የኀጢአት ብዛት ስለሚያመጣ በየቀኑ ወደ ንስኀ አባታችን ቀርበን መደበኛ ንስኀ ባንቀበልም እንኳን እየፀለይን፣ እየሰገድን፣ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደን የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምህረት እየጠየቅን፣ በአባቶቻችን እጅ መስቀል እየተባረክን፣ ፀበል እየተጠመቅን፣ ቃለ እግዚአብሔር እየሰማን፣ ኪዳን እያደረስን፣ ቅዳሴ እያስቀደስን፣ቅዱስ ቁርባን እየተቀበልን፣ አቤቱ ጌታ ሆይ ይቅር በለን፥ እራራልን፥ የኀጢአት ስርየት ስጠን፥ ሰው የማያውቅብንን አንተ የምታውቅብንን በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ እያልን ዘወትር ስንማፀነው በልምድም ሆነ በተለያየ ምክንያት በየሰዓቱ በየእለቱ የምንሰራውን ጥቃቅን ኀጢአታችንን በዚህ ስርዓት እንደሚደመስስልን እና የኀጢአት ስርየትም እንደምናገኝ ለነፍሳችንም እረፍት እንደሚሰጠን ማመን ይገባናል።

ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል፥ ተጨማሪ ማብራሪያ ከፈለጉ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።

ጠያቂያችን፤ ከዚህ በፊት አንድ ሰው ሱባኤ ከመግባቱ በፊት እና ሱባኤ ከገባ በኋላ ምን ምን ነገሮች ሊያሟላ ይችላል? በሚል ተጠይቀን ያስተላለፍነውን ትምህርት አሁን እርሰዎ ላቀረቡት ጥያቄ አጠቃላይ ሃሳብ እና ተያያዥ ግንዛቤ እንደሚያገኙበት በማመን  ይህንኑ አያይዘን ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት። ምናልባት በዚህ ግልጽ ያልሆኘልዎ ሃሳብ ካለ ደግመው በውስጥ መስመር ያሳውቁንና ተጨማሪ ትምህርት እና ምክር እንሰጥዎታለን።

ከሁሉ በፊት ስለ ስባኤ መረዳት ያለብን ምስጢራዊ ትርጒሙንና በሱባኤ ስለሚገኝበት መንፈሳዊ ጥቅም ነው።  ሱባኤ ማለት በግዕዝ  ቋንቋ 7 ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ይህ 7 ቁጥር ደግሞ የአንድ ሱባኤ ጊዜ ማለት ነው። 7 ቁጥር በዕብራዊያን ዘንድ ፍጹም ቁጥር ነው። የቃሉ ምስጢራዊ ትንታኔ ይህ ከሆነ፤ ሱባኤ የተጀመረው በአባታችን በአዳም ነው።  አባታችን አዳም  7  አመት ከ1ወር ከ 17 ቀን በገነት ውስጥ በደስታ ከኖረ በኋላ አታድርግ የተባለውን ትዕዛዝ በማድረጉና አትብላ የተባለውን ዕፀበለስ በመብላቱ ከገነት ርስቱ መባረሩ ምክንያት ስለ ስራው በደል ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው በማልቀሱና በመጮሁ ምክንያት ከፈጣሪው ዘንድ  ይቅርታን ያገኝ ዘንድ 5 ሱባኤ ማለትም 35 ቀናትን በሱባኤ ተወስኖ ወደፈጣሪው ያቀረበው ልመና ተቀባይነት አግኝቶ ከፈጣሪው ዘንድ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ተገብቶለታል። ስለዚህ ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ በኀጢዓትና በልዩ ልዩ ምክንያት የሱባኤ ጊዜ እየወሰኑ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ምህረትን እና ይቅርታን አግኝተውበታል። 

ሱባኤ የሚገባው በ2 ምክንያት ነው:- 1ኛው ማንኛውም ክርስቲያን የኀጢአት ፈተና ደርሶበት የበደለውን በደል አስቦ በመፀፀት ከሰውና ከማህበራዊ ኑሮ ራሱን ደብቆና ሰውሮ በለቅሶ በፀሎት ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት ሂደት ነው።  2ኛው ደግሞ ማንኛውም ክርስቲያን ፀጋውን ለማሳደግና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ልዩ ልመና ሲኖረው ጊዜ ወስኖ ቦታ ለይቶ ሱባኤ ይገባል ማለት ነው። በፆም በፀሎት ተወስኖም ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል። በጠየቀውና በለመነው ፍፁም ክርስቲያናዊ ሕይወት አንፃር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለግል ህይወቱና ለቤተሰቡ፣ ለወገንና ለሀገርም የሚጠቅም በጐ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።

ሌላው የሱባኤ አስፈላጊነት ፤ እግዚአብሔር አምላክ ስላደረገልን ነገር ሁሉ እና ስለቸርነቱ ብዛት ምስጋና ለማቅረብ፣ ወደፊትም ጠብቆቱና መግቦቱ እንዳይለየን ለመማፀን ፣ ከእናታችን ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳን ሁሉ በረከት ለማግኘት፣ በግል ህይወትም ሆነ በሀገር ላይ ከተቃጣው መቅሰፍት ለመዳን፣ በሃይማኖትና በሥነምግባር ፀንተን በፆም በፀሎት እንድንተጋ የሚዋጋንን ጥንተ ጠላታችንን ዲያብሎስን ድል ለመንሳት፣ የተሰወረና የረቀቀ ምስጢር እንዲገለጽልን በመሳሰሉት መንፈሳዊ ጉዳዮች ሰባኤ መግባት የምንችል መሆኑን በቀኖና ቤተክርስቲያን ታዟል።

በግል ሱባኤ ለመግባት መወሰን የተቀደሰ አላማ ቢሆንም ሰይጣን የበጎ ነገር ጠላት ስለሆነ ፈተና እንዳይገጥመን ለንስኀ አባት ሱባኤ ልገባ ነው በፀሎት ቢያስቡኝ ብሎ መንገር የተሻለ ይሆናል። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ሳይመች ቢቀር ምንም እንደ ጥፋት የሚያስቆጥርብን ስላልሆነ ወደ ሱባኤ ሄደን የፈለግነውን መንፈሳዊ አላማ ለማሳካት የሚከለክለን ስርአት የለም። ይሁን እንጂ የምንሄድበት ሱባኤ ምክንያት ኀጢአት ሰርተን ቀኖና ለመቀበል ወይም ንስኀ ለመግባት ከሆነ ከንስኀ አባት ጋር ተነጋግረን በተፈፀመው የኀጢአት ጥፋት መጠን እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና የንስኀ አባታችን የሚሰጡንን ቀኖና ተቀብለን መሄድ አለብን እንጂ በራሳችን ውሳኔ ንስኀ እገባለው ብለን መሄድ ግን ከሃይማኖት ስርአት ውጪ ነው።

ሱባኤ ለመግባት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ፤ በግላችን በሰራነው በደልም ሆነ ስለሀገርና ስለወገን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት ለመጠየቅ ሱባኤ ለመግባት ባሰብን ጊዜ፦ 

1/   ህሊናዊና አካላዊ ቁርጠኝነትና ስነልቦናዊ ውሳኔን ይጠይቃል። 

2/  ሱባኤ የምንገባበት ምክንያት እንዴትና ለምን እንደሆነ ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር መነጋገርና ምክር መቀበል ያስፈልጋል።

3/  በሱባኤ የምንቆይበት ጊዜ ምን ያህል ሰባኤ እንደሆነ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ፣ እና የሱባኤውን ቦታ (በአትን) መወስን ያስፈልጋል። 

4/   በሱባኤ ጊዜ የምናደርጋቸውን መንፈሳዊ ስርዓት ማለትም እንዴት እንደምንፆም ፣ እንዴት እንደምንፀልይ፣ እንዴት እንደምንሰግድና በመሳሰሉት በስርዓተ ቀኖና መሰረት መንፈሳዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል። 

5/    ሱባኤ በገባን ጊዜ በግል ህይወትና በቤተሰብ ጉዳይ ወይም በማህበራዊ ጉዳይ የሚያሰናክል ፈተና እንዳይመጣብን አስቀድመን ሁኔታዎችን ማስተካከል ያስፈልጋል።

6/   ሱባኤ በገባን ጊዜም እንዴት መተኛት እንዳለብን ምን መልበስ እንዳለብን ባጠቃላይ በሱባኤ የምናሳልፍበት ጊዜያችን የሚያስፈልገንን እና የማያስፈልገንን ነገር ለይተን ለማወቅ ከቤተክርስቲያን አባቶች መመሪያ መቀበል አለብን። 

ይህን ሁሉና የመሳሰሉትን ሱባኤ ከመግባ በፊት ልናሰባቸውና በሱባኤ ወቅት ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ናቸው። 

ሱባኤ ከጨረስን በኋላ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ደግሞ፦

1/   ሱባኤ የገባንበት ምክንያት ኀጢአት ከሆነ ደግመን ላለማድረግ በተቻለ መጠን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳችንን ለበለጠ የሃይማኖት ፅናት ማትጋት ነው። 

2/ ሱባኤ በገባንበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ያገኘነው በጎ ምላሽ ካለም የበለጠ የእግዚአብሔር ፀጋ እንዲበዛልን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ነው።

3/   ማንኛውም ክርስቲያን ቦታና ጊዜ ላይቶ በሱባኤ ፈጣሪውን የሚለምን ከሆነ በፀጋ እያደገ ከመጣ ብዙ ጊዜ ለውድቀት ከሚያበቁት የኀጢአት ምክንያቶች መራቅ።

4/   በፆም በፀሎት በቅዱስ ቁርባን በአጠቃላይ በክርስቲያናዊ ስነምግባር መንፈሳዊ ጉዞን መቀጠል።

5/   ሥጋዊ ፍላጎትን እና ምኞትን ገዝቶ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝቶ የትሩፋት ሥራ መስራት። 

6/  በአጠቃላይ አለማዊ ሰዎች ከሚሰሯቸው ስራዎች ሁሉ እርቆ በመንፈሳዊ አላማ ፀንቶ መኖርን ይጠይቃል። 

እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ምክር የሚሰጠው በአለም እየኖሩ በሱባኤ እግዚአብሔርን ለሚለምኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንጂ ለገዳማውያን ወይም በምናኔ ለሚኖሩ መነኮሳት አይደለም፤ የነሱ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ቀኖናዊ ስርዓት ስላላቸው ነው።

ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባሎቻችን ሁላችሁም፤ ስለ ሱባኤ መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ በዚህች አጭር ፅሁፍ መልዕክት ልከንላችኋልና አንብባችሁ እንደተረዳችሁ እናምናለን። ጠያቂያችንም ለሱባኤ ወደ ገዳም ለመሄድ አስበው ከሆነ ከላይ የዘረዘርነውን ምክራችንን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አደራ እያልን፥ ያሰቡትን መንፈሳዊ አላማ በሰላም ፈፀመው የእግዚአብሔርንም በረከት አግኝተው እንዲመለሱ እየተመኘን፤  በገዳም በፍጹም እምነት ሆነው እንዲጸልዩና ለረዥም ጊዜ በቦታው የቆዩ የእግዚአብሔር ፀጋ አብዝቶ ያደረባቸው አባቶች ስለሚኖሩ ወደነርሱ ቀርበው ትምህርትና ምክር ማግኘት እንዳለብዎም እንመክራለን። 

ጠያቂያችን፤ ከንስኀ በኋላ ዳግም ስለፈፀሙት ኀጢአት ምን ማድረግ እንዳለብዎት ላቀረቡት ጥያቄ የተሰጠ ምክር። ማንኛውም ክርስቲያን ከሁሉ በፊት ተግቶ እና ነቅቶ መጋደል ያለበት ኀጢአትን ላለመስራት ነው። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቀድሶ እና አክብሮ የፈጠረውን አካል መልካም ነገር መስራት እየተቻለ የምንሰራው የጽድቅ ስራም ቀርቶ እያደረ ይሄንን የተቀደሰ አካል በሰይጣን ስራ ወይም በገቢረ ኀጢአት ማርከስ ግን እኛን ብቻ ሳይሆን ፈጣሪንም የሚያሳዝን እርኩስ ተግባር ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ ክፉውን እና መልካሙን ፣ ሞትን እና ህይወትን፣ ጨለማን እና ብርሃንን፣ ኩነኔን እና ጽድቅን፣ እውነተኛ አምላክን እና ጠላት ዲያበሎስን ለይቶ የሚያውቅበትና ለይቶ የሚያይበት ልቦና ተሰጥቶት እያለ ለዘለዓለም ለነፍሱ ሞት የሚያመጣበትን የኀጢአት ስራ መስራት የፈቃድ ሞት ወይም ህሊናዊ እብደት ስለሆነ ከሁሉ በማስቀደም እግዚአብሔር ቢያግዘን እኛም ኀጢአት ላለመስራት እርም ብለን ወደ ኀጢአት እንዳንመለከት በመወሰን እና አብዝተን መንፈሳዊ ተጋድሎ ማድረጋችን ከምንም በላይ የተቀደሰ ተግባር ነው ። ነገር ግን እንዲህ አይነት ተጋድሎን አድርገንም ይሁን ወይም ለፈቀደ ሥጋችን ተገዝተን ኀጢአት በመፈፀማችን ወደ ንስኀ ህይወት ቀርበን ቀኖና ተቀብለን እንደ ስርቱና እንደ ህጉ የንስኀ ቀኖናችንን ከፈፀምን በኋላ ደግመን ያለፈውን ኀጢአታችንን በሚመስል ወይም በሌላ ኀጢአት ብንወድቅ የአዋቂ አጥፊዎች ስለሚያሰኘን አጥፊነታችንም እጥፍ ስለሚሆን ያሳለፍነውን ህይወት ሳንደብቅ ለንስኀ አባት በመናገር ዳግም የንስኀ ቀኖና መቀበል ይኖርብናል። ምክንያቱም የሰው ልጅ ከዚህ በፊት ታሞ የዳነበት በሽታ ዳግም ተመልሶ ቢያመው ከዚህ በፊት ታምሜ ስለዳንኩኝ በዚህ በሽታ ሁለተኛ ወደ ሃኪም አልሄድም ወይም መድሃኒት አያስፈልገኝም እንደማይባል ሁሉ፥ ኀጢአትም እንዲሁ እንዳንሰራው የምንከለከል ቢሆንም ከሰራነው ግን በማይወሰን የጊዜ ገደብ ደግመን ንስኀ መግባት እንዳለብን የቤተክርስቲያን ህግ ስለሚያዘን አሁንም ጠያቂያችን በድጋሚ በሰሩት ኀጢአት ንስኀ መግባት እንዳለብዎት እንመክራለን።  በተጨማሪም በፆም፣ በፀሎት፣ በስግደት እና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ቢታገሉ የሚፈተኑበት የኀጢአት አይነት ወደእርስዎ ተመልሶ እንዳይደርስ ማድረግ ይችላሉ። እንዲሁም ከዚህ በፊት ስለንስኀ ህይወት ካስተላለፍናቸው ትምህርቶች ከድረገፃችን ላይ እንዲመለከቱ እየመከርን ከንስኀ በኋላ ምን ማድረግ እንደሚገባዎት የሚመክረውን ክፍል ከዚህ በታች ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት።

አንድ ክርስቲያን በኅጢአት የጎደፈውን ሰውነቱን ከታጠበ በኋላ መላ ህይወቱ ንፁህ ስለሆነ ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት መንገዱ ሁሉ ቀና ስለሆነ ማድረግ ያለበት ምን እንደሆነ የምናስረዳዎት፦

1ኛ/ ከምንም በላይ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎትን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ፣

2ኛ/ እግዚአብሔር ቢፈቅድልዎት በቅዱስ ቁርባን መወሰን፣ አቅምዎት በሚፈቅደው መጠን ሳያቋርጡ እና ሳይሰለቹ መፆም፣ መፀለይ፣ እና መስገድ፣

3ኛ/ በአቅምዎት ከሚያገኙት ነገር ለድሆችና ለእግዚአብሔር የሚገባውን አስራተ በኩራት ማዋጣት፣

4ኛ/ ዘወትር ከአባቶች ምክር እና መታዘዝ አለመራቅ፣ በፕሮግራም ወደ ቤተክርስቲያን እየቀረቡ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣

5ኛ ሁሌ እንደቅርብ አስተማሪና መካሪ ሁነው የሚያገለግሎትን መንፈሳዊያን መፃህፍትን ማንበብ፣ ከዚህም በላይ በኑሮዎት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ በማህበራዊ ጉዳይ ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር በትዕግስት እና በጥበብ ለመኖር ድርሻዎትን መወጣት።

እነዚህን ሁሉ እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ነገሮችን አጠቃሎ ለመስራት የሚቻለው ሰው ህይወቱ በንስሓ ሲታደስ ስለሆነ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእርስዎን ህይወት በንፅህና በቅድስና እንደሚጠብቃት በማመን ከዚህ በላይ የተሰጠዎትን መንፈሳዊ ምክር በስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ እግዚአብሔር ይርዳዎት።

በተጨማሪም፤ ስለንስሓ ትምህርት በድረገፃችን ላይ የተላለፉና እየተላለፉ ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች ይህን ሊንክ በመጫን ያንብቡ።

መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ኀጢአቱ አይሰረይለትም? ለሚለው እና የዘመድን ልጅ ክርስትና ማንሳት ይቻላል? በማለት ለጠየቁን አባላችን የተሰጠ ምላሽ፦

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋለ ስጋዌው ህሙማነ ስጋን በተአምራቱ ህሙማነ ነፍስን በትምህርቱ እየፈወሰና በቃሉ እያጸና ማንም ሊሰራው የማይችለውን ድንቅ ስራ እየሰራ በሚመላለስበት ጊዜ ፈሪሳውያን እና የአይሁድ ወገኖች የሚያደርገውን ተአምራቱን በእሱ መለኮታዊ ኃይል የተሰራ መሆኑን አምነው ላለመቀበል ሲሉ ሌላ ኃይል ወይም በእርኩስ መንፈስ ኃይል እንደሚሰራ በድፍረት ይናገሩ ስለነበረ ይህ ክህደታቸው ደግሞ የባህሪይ አምላክ መሆኑን ወይም እግዚአብሔርነቱን የካዱ ስለሆነ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ጋኔን ወይም እርኩስ መንፈስ አድሮበታል ብሎ ከመሳደብ የበለጠ ሌላ ምንም ክህደት ስለሌለ በዚህ ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ 1ኛ/ “ስለዚህ  እላችኋለሁ፥  ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች  ይሰረይላቸዋል፥ ነገርግን  መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም።  በሰው ልጅ  ላይ ቃል  የሚናገር  ሁሉ  ይሰረይለታል፤   በመንፈስ  ቅዱስ  ላይ  ግን  የሚናገር  ሁሉ  በዚህ  ዓለም  ቢሆን  ወይም  በሚመጣው  አይሰረይለትም።”  በማለት የተናገረው ከዚህ አንፃር ነው። (ማቴ 12፥31፡32)

እንዲሁም 2ኛ/ “እውነት  እላችኋለሁ፥  ለሰው  ልጆች  ኃጢአት  ሁሉ  የሚሳደቡትም  ስድብ  ሁሉ  ይሰረይላቸዋል፤ በመንፈስ  ቅዱስ  ላይ  የሚሳደብ  ሁሉ  ግን  የዘላለም  ኃጢአት  ዕዳ  ይሆንበታል  እንጂ  ለዘላለም  አይሰረይለትም።  ርኵስ  መንፈስ  አለበት  ይሉ ነበርና።”  በማለት አይሁድ ፥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ፣ የባህሪይ አባቱ እግዚአብሔር የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለትን፣ እንዲሁም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያለመለየት አንድ መሆኑን በእርግብ አምሳል በራሱ ላይ መገለፁን አምነው ሳይቀበሉ ጋኔል ወይም እርኩስ መንፈስ አድሮበታል በማለት መናገራቸው መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ወይም መካድ ስለሆነ፤ የሰው ልጅ ደግሞ ከኀጢአት ሁሉ የመጨረሻ ኀጢአት እና በንስኀም የማይታጠብ ትልቁ በደል ኀጢአትን ይቅር የሚል ፈጣሪን መሳደብ ስለሆነ ፈጣሪውን የተሳደበ ከሆነ ደግሞ በማንም ሊቀር ስለማይችል መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ንስኀ የለውም የሚባለው ለዚህ ነው። (ማር 3፥28፡29)

3ኛ/ ካህኑ ኤሉ በእድሜ በሸመገለ ጊዜ እሱን ተክተው የእግዚአብሔርን ቤት ያገለግሉ የነበሩ ሁለቱ ልጆቹ በእግዚአብሔር ፊት አስጠያፊ የሆነ ኀጢአት በመፈፀማቸው ምክንያት አባታቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንደተጣሉ ሲነግራቸው “ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው?” (1ኛ ሳሙ 2፤25) በማለት ሰው ከሰው ጋር ቢጣላ ወይም ሰውን ቢሳደቡት በእግዚአብሔር ስም በመማፀን ሊታረቅ ይችላል በደሉም ይቅር ይባልለታል ፤ ከፈጣሪ ጋር ከተጣላን አስታራቂ ሽማግሌ ሊኖር ስለማይችል ለዚህ ነው በማቴዎስ ወንጌል መንፈስ ቅዱስን የተሳደበ ኀጢአቱ አይሰረይለትም የተባለው።

ጠያቂያችን ወደ ሁለተኛው ጥያቄዎት ስንመጣ፦ የዘመድን ልጅ ወይም የአክስት እና የአጎት ልጅን ክርስትና ማንሳት ፈፅሞ የተከለከለ ነው። በቤተክርስቲያን ቀኖና ክርስትና ማንሳት አንድም ዝምድናን ለመፍጠር የሚደረግ ስርዓት ስለሆነ ሰው ደግሞ በስጋ ተዛምዶ አጎት ልጅና የአክስት ልጅ ራሱን የቻለ በህገ እግዚአብሔር የፀና ተዛምዶ ስለሆነ፥ ደግሞም ብዙ ክርስቲየኖች በሚኖሩባት ቤተክርስቲያን የሚኖር አንድ ክርስቲያን ልጆችን ክርስትና የሚያነሱ ሰዎች ሳይጠፉ ሆን ብሎ የአክስትና የአጎት ልጅን ማስነሳት ስርአትና ህጉ አይፈቅድለትም ፤ ደግሞም በዝምድና ላይ ዝምድና መደረብ የሚያስፈልግበት ምንም አይነት በቂ ምክንያት የሌለን አንዲህ አይነት ስርአት ለመፈፀም ፈፅሞ ሊታሰብ እንደማይገባ እንመክራለን ።

ስለዚህ ጠያቂያችን ለጠየቁት ሁለት ጥያቄዎች መልስ ከላይ የሰጠነዎትን ምላሽ አንብበው ሃሳቡን እንዲረዱት እየጠየቅን ምናልባት በዚህ ግልፅ ያልሆነልዎት ነገር ካለ ወይም እኛ ያልተረዳንዎት ጉዳይ ካለ በውስጥ መስመር አግኝተው ቢያናግሩን ተጨማሪ ትምህርት እና መንፈሳዊ ምክር ልንሰጥዎ እንችላለን።

ጠያቂያችን በመጀመሪያ የንስኀ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መንፈሳዊ ትርጉሙን እና ሚስጥሩን በማስተዋል መረዳት ያሰፈልጋል። ንስኀ ማለት  ማዘን፣ መፀፀት፣ መቆጨት፣ መቀጣት፣ ቀኖና መቀበል፣ ስለተሰራው ኀጢአት ካሳ መክፈል  አና በአጠቃላይ ማንኛውም ክርስቲያን ስለሰራው ኀጢአት ተፀፅቶ ወደ ፈጣሪው ሲመለስ የሚቀበለውን የቀኖና ሂደት ያመለክታል።

ንስኀ በሚቀበለው ክርስቲያን እና ንስኀ በሚሰጠው አባት መካከል የሚፈፀመው አገልግሎት የሚታይ መንፈሳዊ ስርአት ሲሆን በዚህ መታዘዝ ውስጥ እግዚአብሔር በረቂቅ መለኮታዊ ጥበቡ በካሕኑ ላይ አድሮ በፍጹም እምነት ኀጢአቴ  ይፋቅልኛል ብሎ ከልብ በመታዘዝ ለንስኀ ህይወት የቀረበውም ምእመን ያለምንም ጥርጣሬ ኀጢአቱ ይቅር ይባላል ማለት ነው። ስለዚ በመፅሐፍ ቅዱስ እና በሌሎቹ ቅዱሳን መፃሕፍት በብዙ ቦታ ላይ እንደተገለፀው እግዚአብሔር ኀጢአት ይቅር እንደሚል እኛም ከኀጢአታችን እና ከበደላችን ተፀፅተን ወደ ፈጣሪ እንድንመለስና የእግዚአብሔር እንደራሴ ለሆኑ የሃይማኖት አባቶቻችን እንድንናዘዝ ታዘናል።

ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ንስሓ ለመግባት ተዘጋጀ ወይም ንስሓ ገባ ሊባል የሚቻለው ለንስኀ የሚያበቁ መስፈርቶች እና ቅደም ተከተሎች በትክክል ከተጠበቁ ነው። ማለትም ፦

1/  የተሰራውን ኅጥያት ጥፋት መሆኑን ማመን ፣

2/  ስለተሰራው ጥፋት ከልብ ተፀፅቶ ንሰሐ ለመግባት መዘጋጀት፣

3/  ወደ ንስሐ አባታችን በማምራት ኅጥያታችንን በመናዘዝ ንስሐ መቀበል፣

4/  የተሰጠንን ንስሐ በአግባቡ መፈጸም፣

5/ ዳግመኛ ኅጥያት ላለመስራት በአባቶች ትምህርትና በመንፈሳዊ አገልግሎት መፅናት፣

6/  በፆም፣ በፀሎት፣ በስግደት ዘወትር በመትጋት መንፈሳዊ ህይወትን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር ያስፈልጋል።

ንስኀ ከገቡ በኋላ ደግሞ ከምንም በላይ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎትን እንዳያረክሱት መጠንቀቅና አቅምዎት በሚፈቅደው መጠን ሳያቋርጡ እና ሳይሰለቹ መፆም፣ መፀለይ፣ እና መስገድ ዘወትር ከአባቶች ምክር እና መታዘዝ አለመራቅ፣ እንዲሁም ወደ ቤተክርስቲያን እየቀረቡ ቃለ እግዚአብሔር መማር እና እግዚአብሔር ቢፈቅድልዎት በቅዱስ ቁርባን መወሰን  ያስፈልጋል።

ስለዚህ ጠያቂያችን በእርስዎ በኩል እኛ ያላወቅነውና ያልተረዳነው ችግር ቢኖር እንኳን ሁሉም ነገር በፈጣሪ ዘንድ ኢምንት ስለሆነ ከባድ ያሉትን ጭንቀት እና ሃሳቦትን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ሳይጠራጠሩና ሳያመነቱ ከገቡበት የኀጢአት ደዌ በፍጥነት ለመውጣት ጊዜ ሳይሰጡ ወደ ቤተክርስቲያን እና ወደ አባቶች ይቅረቡ። ታሰር ተፈለጥ በሚል ስጋዊ ዳኝነት የሚጠየቁበት ጉዳይ ስለሌለ ምህረቱና ቸርነቱ ፍቅሩና ትእግስቱ ወደ በዛው ወደ እውነተኛው አምላክ ስለሆነ የሚቀርቡት፤ የንስኀ ህይወትም ለክርስቲያኖች እድል የሚመች አላማ ስለሆነ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲኦል ወደ መንግስተ ሰማያት፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ፅድቅ፣ ከሞት ወደ ህይወት የሚያመጣ ቀና መንገድ ስለሆነ የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጡ ወደ ቤተክርስቲያን አባቶች ቀርበው ችግርዎትን በማስረዳት መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ለማግኘት ህሊናዎትን ያዘጋጁ።

ከዚህ በላይ እኛ ያልተረዳንዎት ከእርስዎም አቅም በላይ የሆነ ችግር ካለ ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና አገልግሎት እንድንሰጥዎት በውስጥ መስመር ያነጋግሩን።

ጠያቂያችን ንስሓ ከመግባትዎ በፊት አና ንስኀ ከገቡ በኋላ ማድረግ ያለብዎትን ከዚህ በታች በዝርዝር ልከንልዎታልና አንብበው በተግባር እንዲያውሏቸው እንመክራለን፦

1. ንስሓ ከመግባትዎ በፊት ማድረግ ያለብዎት፦

በቅድሚያ እርስዎ እንዳደረጉት በድያለሁ ጥፋት ሰርቻለሁ ኅጢአት ፈጽሜያለሁ ብሎ ኅጢአትን ለመናዘዝ ፈቃደኛ መሆንና የኅጢአት ሥርየት ለማግኘት መፈለግ የእውነተኛ ክርስቲያን መገለጫ ነው። በመሠረቱ በአዳማዊ ተፈጥሮ ሰው ሁኖ የተፈጠረ የሰው ልጅ ሁሉ ወዶ ጽድቅ መሥራትም ሆነ ወዶ ኅጢአት ለመሥራት የሚችልበት የተፈጥሮ ነፃነት ያለው ፍጡር ስለሆነ በለበሰው ደካማ ሥጋው ተሸንፎ ኅጢአት እንደሚሠራ ይታወቃል። ሰው ሁኖ ተፈጥሮ በሰውነቱ ፈፅሞ ኅጢአት አልሠራም ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር እራስን ከማታለል አልፎ ስለሁላችንም መዳን በመስቀል ላይ የሞተልንን የኢየሱስ ክርስቶስ አባታዊ ፍቅሩንና ውለታውን እንደመካድ ይቆጠራል። ሁላችንም የሰው ልጆች እንደምንሞት ብናምንም እንኳ፤ ነገር ግን መቼ በሞት እንደምንጠራ ቀንና ሰዓቱን (ዘመንና ጊዜውን) ለይቶ ማወቅ ከእሱ ከባለቤቱ በስተቀር ፈጽሞ የሚያውቅ የለምና ኅጢአትን ለመናዘዝ ቅድሚያ መስጠትና በንስሐ ሕይወት ራስን አዘጋጅቶ መጠበቅና ንስሐ ለመግባት መዘጋጀት ከእውነተኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ ታማኝነት ነው።

ከዚህ የተነሣ ኅጢአት ለመናዘዝና ንስሐ ለመግባት ከሚፈልግ አንድ ክርስቲያን የሚጠበቀው ፡-

1.  በቅድሚያ ኅጢአት መሥራቱን አምኖ ለራሱ ሕሊና መናዘዝ (መፀፀት)።

2.  ስለሠራው ኅጢአት ወይም በደል እየተጸጸተ ጧት ማታ በደሉን በፀሎትና በልመና ለፈጣሪው መናዘዝና ኅጢአትን በእግዚአብሔር ፊት ማመን (መዝ50 ፣ ዳን9፥5፣ ነህ1፥6-7)

3.  ኅጢአትን (በደልን) ለካህን መናዘዝና ንስሐ መግባት። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይና እንደራሴ ስለሆነ የሠራነውን ኅጢአት ለካህኑ በመናዘዝ ንስሐ መግባት፤ ኅጢአታችን እንዲሠረይልን በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ መግባትና መናዘዝ ማለት ነው። (ኢያሱ7፥19 ማቴ3፥6 ዘሌ5፥5-6 የሐዋ19፥18)

4. የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት የጥል ግድግዳ አፍርሰን በፍቅር አሸንፈን ስለዘለዓለማዊ ሕይወት ብለን በፍጹም ሕሊና በሰላም መኖር ነው።

4. ተመልሶ በኅጢአት ላለመውደቅ አዘውትሮ የንስሐ አባትን ወይም የሚቀርቡትን የሃይማኖት መምህር ማማከር፣ ምክር ማግኘት በታቻለ መጠን መጸለይ፣ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድና ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ በቤትም ውስጥ ቢሆን መንፈሳዊ መዝሙርና ትምሕርት ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ የምናስገነዝበው ለጠየቁን ምዕመን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያን እንዲጠቅም ነው።

የንስሓ አባትን በሚመለከት ፦

ይመክረኛል ያስተምረኛል ያሉትን የንስሓ አባት የሚሆን ካህን በአካባቢዎ ካሉ  ይያዙ፤ በአከባቢዎ  ማግኘት የማይችሉ ከሆነ በራስዎትም ሆነ በሚያምኑት ሰው በኩል ያገኙዋቸውን እውነተኛ ካህን በርቀትም ቢሆን ይያዙ፤ ወይም ደግሞ እኛ በህይወታቸው ምሳሌ ይሆናሉ ብለን ከመረጥንልዎ በድረገፃችን በሚያገኙት ስልክ ቁጥር ደውለው  ንስሓ አባት በማድረግ መያዝ ይችላሉ።

2. ንስሓ ከገቡ በኋላ ማድረግ ያለብዎት፦

አንድ ክርስቲያን በኅጢአት የጎደፈውን ሰውነቱን ከታጠበ በኋላ መላ ህይወቱ ንፁህ ስለሆነ ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት መንገዱ ሁሉ ቀና ስለሆነ ማድረግ ያለበት ምን እንደሆነ የምናስረዳዎት፦

1ኛ/ ከምንም በላይ ዳግም ወደ ኀጢአት ተመልሰው የተቀደሰውን ህይወትዎትን እንዳያረክሱት መጠንቀቅ፣

2ኛ/ እግዚአብሔር ቢፈቅድልዎት በቅዱስ ቁርባን መወሰን፣ አቅምዎት በሚፈቅደው መጠን ሳያቋርጡ እና ሳይሰለቹ መፆም፣ መፀለይ፣ እና መስገድ፣

3ኛ/ በአቅምዎት ከሚያገኙት ነገር ለድሆችና ለእግዚአብሔር የሚገባውን አስራተ በኩራት ማዋጣት፣

4ኛ/ ዘወትር ከአባቶች ምክር እና መታዘዝ አለመራቅ፣ በፕሮግራም ወደ ቤተክርስቲያን እየቀረቡ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣

5ኛ ሁሌ እንደቅርብ አስተማሪና መካሪ ሁነው የሚያገለግሎትን መንፈሳዊያን መፃህፍትን ማንበብ፣ ከዚህም በላይ በኑሮዎት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ በማህበራዊ ጉዳይ ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር በትዕግስት እና በጥበብ ለመኖር ድርሻዎትን መወጣት።

እነዚህን ሁሉ እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ነገሮችን አጠቃሎ ለመስራት የሚቻለው ሰው ህይወቱ በንስሓ ሲታደስ ስለሆነ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእርስዎን ህይወት በንፅህና በቅድስና እንደሚጠብቃት በማመን ከዚህ በላይ የተሰጠዎትን መንፈሳዊ ምክር በስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ እግዚአብሔር ይርዳዎት።

በተጨማሪም፤ ስለንስሓ ትምህርት በድረገፃችን ላይ የተላለፉና እየተላለፉ ያሉትን ተከታታይ ትምህርቶች ይህን ሊንክ በመጫን ያንብቡ።

ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ

የንስሐ ኑዛዜ በፅሁፍ ማቅረብ ይቻላል ወይ ተብሎ ለተጠየቀ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ፦ ስለ ንስኀ ጥቅም እና አስፈላጊነት እንዲሁም ንስሐ የሚገቡ ምእመናን በምን አይነት ስርዓት መሄድ እንዳለባቸው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የንስሐ ህይወትን አስመልክቶ ምክር እና ትምህርት መስጠታችንን እናስታውሳለን። በመሰረቱ የንስሐ ህይወት በንስሐ አባት እና ንስሐ በሚቀበለው ምእመን መካከል የሚከናወን ሚስጢራዊ ስርዓት ስለሆነ በሁለቱም መካከል ከምንም በላይ ዳኛው እና እውነተኛ ፍርድ ሰጪው እግዚአብሔር ስለሆነ የንስሐ ልጅ ወደ ንስሐ አባቱ በመቅረብ የሰራውን ኀጢአት ሁሉ ምስክር ሳይኖር ስለ ሰራው ኀጢአት የሚያስገድደው አካል ሳይኖር በራሱ በጎ ፈቃድ በመነሳት ስለሰራው ኀጢአት በመፀፀት ወደ ንስሐ አባቱ ቀርቦ እያንዳንዱን የፈፀመውን የኀጢአት ጥፋት በመዘርዘር ከተናዘዘ በኋላ የንስሐ አባቱ ወይም ካህኑ ምእመኑ ለፈፀመው የኀጢአት ጥፋት  ተመጣጣኝ የንስሐ ቀኖና ሰጥተውት በትክክል ሲፈፅም የንስሐ ህይወቱ ትክክለኛ ይሆናል።

ከዚህ ውጪ ግን እንደ ምድራዊ ህይወት በተልኮና በፅሁፍ ለማድረግ የሚያስገድድ ችግር እንኳን ቢያጋጥም ከምን አኳያ እንደሆነ ካህኑ የምእመኑን ችግር ተረድተው በአካል ቀርበው ለመናዘዝ የሚያስችል በቂ ምክንያት መሆኑን ሲረዱ ያለ ንስሐ ከመቅረት በርቀትም ሆኖ ንስሐ መቀበልና በአባቶች ለመናዘዝ ቢቻል እንደጥፋት አይቆጠርም።

ነገር ግን ቀርቤ ለማናገር ፈርቻለው በሚል ምክንያት ለስጋዊ ክብራችን እና ማንነታችን ቅድሚያ በመስጠት የነፍሳችንን ጉዳይ እንደ ተራ ጉዳይ በመቁጠር እኛም ራሳችን በኀጢአት ምክንያት የሸፈተውን ህይወታችንን ወደ እግዚአብሔር በግልፅ ለማቅረብ እያፈርን እና እየተሳቀቅን ራሳችንን ሰውረን የሰራነው ክፉ ስራችንን በወረቀት ብንልከው ንስሐ የገባው የእኛን ኀጢአት የወሰደው ወረቀቱ ሊሆን ይችላል እንጂ እኛ ስለማንሆን፤ እንዲሁም የንስሐ ህይወት በቤተከርስቲያን ቀኖና የሚፈፀም ስለሆነ በእኛ በኩል የምናሻሽለው አለመሆኑን ጠያቂያችን በዚህ እንዲረዱት ያስፈልጋል።

በዋናነት ግን መታወቅ ያለበት ትልቁ የንስሐ ጥቅም ራስን አዋርዶ ዝቅ አድርጎ ከልብ ተፀፅቶ ያንን ከባድ የምንለውን ኀጢአት በካህኑ ላይ ያደረው አምላክ ይቅር ይለናል ብለን አምነን ስንፈፅመው ነው የኀጢያትን ስርየት ማግኘት የምንችለው። ነገር ግን እኛ የማናውቀው ከአቅምዎት በላይ የሆነ ችግር አጋጥሞዎት ሊሆን ስለሚችል የንስሐ ቀኖናውን በምን አይነት ስርዓት መፈፀም እንዳለብዎት ምክር ስለምንሰጥዎት በውስጥ መስመር አግኝተው ያነጋግሩን። 

እግዚአብሔር የሚጠላቸው  ወይም የጽድቅ ጠላቶች፦

–      ከሀዲነት
–      ትዕቢተኝነት
–      ስስት
–      ፍቅረ ንዋይ
–      ቅናት
–      ምቀኝነት
–      ተነኮለኝነት
–      አመንዝራነት
–      ሴሰኝነት
–      ክፋተኝነት
–      ሰካራምነት
–      ነፍሰ ገዳይነት
–      ጣኦት አምላኪነት
–      ዘረኝነት
–      ሴሰኝነት
–      አድሎተኝነት
–      መናፍቅነት
–      ዘማዊነት
–      መዳራት
–      ቁጣ
–      አድመኝነት
–      ጥልና ክርክር
–      ዘፋኝነት

እነዚህን የሚመስሉ የክፋት እና የክፉ ነገሮች መገለጫ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ በእውነተኛው የሰው ልቦና ላይ ንፁህ በሆነው የስንዴ ዘር ፋንታ ጠላት ዲያብሎስ የዘራቸው እንክርዳዶች ናቸው። በአንድም በሌላም መንገድ የሰው ልጅ በስጋውም ሆነ በነፍሱ የሚፈትኑት እነዚህ ስለሆኑ እግዚአብሔር አጥብቆ ከሚጠላቸው ከእነዚህ የጥፋት ስራዎች ሁሉ ፈፅሞ መራቅ እና መለየት  መንፈሳዊ ግዴታችን ስለሆነ ለግንዛቤ ያህል እንዲረዳችሁ በቀላል አቀራረብ የቀረበ ስለሆነ በእግዚአብሔር ስም እንድታነቡት አደራ እንላለን።

ከዮሐንስ ንስሐ ድረገጽ

 

ጠያቂያችን ከምንም በላይ መገንዘብ ያለብዎት ኀጢአት ባንሰራው መልካም ሆኖ ሳለ ከሰራነው ግን የመጨረሻ አማራጫችንና ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት መንገድ ንስሐ ነውና፤ የነፍስ እረኛ እንዲሆኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የክህነት ስልጣን የተሰጣቸው አባቶች ካህናት ስለሆኑ ጠያቂያችን ለንስሓ አባትዎ ኀጢአቶን ተናዘው ቀኖናዎትን መውሰድ አለቦት። ያን ግዜ በግል ኑሮዎትም በማህበራዊ ህይወቶትም ያለው ግንኙነት ሰላም ይሆንልዎታል፤ የተረጋጋ መንፈስም ይኖርዎታል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፀጋና ሰላም ከእርስዎ ጋር ስለሚሆን። ከእውነተኛ ሃይማኖትና ምግባር ስንርቅ ግን የንስሐ ህይወታችን ጨርሶ ይቀጭጫል። ያኔ ደግሞ በሰራነው ኀጥያት (ጥፋት) ነፍሳችን ፈፅሞ ትቃተታለች ትጨነቃለችም። ስጋችን ምድራዊ የሆነውን የስጋ ስራ ለመስራት ነፍሳችን ደግሞ ሰማያዊ የሆነውን የፅድቅ ስራ ለመስራት ለኛ ግልፅ ሆኖ በማይታወቅና በማንረዳው ሁኔታ ሁለቱም ህይወታችንን የጦር አውድማ ሲያደርጓት በኛ ላይ የፍርሃት መንፈስ ይነግስብናል። ከጥፋታችን ተመልሰን ንስሐ እንዳንገባ ደግሞ የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው እና የእኛን ፅናት የማይፈልገው ሰይጣንም ግራ እንዲገባን እና የፍርሃቶቻችን ምክንያቶች እንዲበዙ ያባብስብናል። ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲሰያን ሁል ጊዜ ሊዘነጋው የማይገባው የሰይጣን ቋሚ ተግባር እኛን ለመፈተን እና ከመንፈሳዊ ህይወት ለማፈናቀል ዘወትር እንቅልፍ ስሌለው  በእያንዳንዳችን ላይ እንደየደካማ ጎናችን ፈተናችንን እንደሚያበዛው እና ለውድቀት የምንበቃበትን ጉድጓድ ዘወትር እንደሚቆፍርልን መዘንጋት የለብንም። የሰው ልጅ መላ ዘመኑን ለፅድቅ ስራ ከሚያሳልፈው ግዜ ይልቅ ለኅጢአት የሚያውለው ግዜ ብዙ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በኅጢአት ጠፍተን እንዳንቀር ተመልሰን ንስሓ እንድንገባ የሚፈቅድ አምላክ ስለሆነ ለዘመናት ከሰራነው ኅጢአት ይልቅ በተወሰነ የቀኖና ግዜ የሰራነው ፅድቅ ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ጥፋት ፍቆ ንስሐ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት እንድንበቃ ታደርጋለች። 

ስለዚህ፤ ጠያቂያችን ለዚህ ችግርዎ  የምንመክርዎት ፍርሀት አንዱ የሰይጣን ውግያ ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ የፍርሃት አምላክ ሳይሆን የፍቅርና የሰላም አምላክ በሃጥያት የወደቀውን አይዞህ ልጄ ብሎ የሚያነሳ እና ከጠፋንበት ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ስለሆነ የሚቃወምዎትን የፍርሀት መንፈስ እንደምንም ታግለው ያሸንፉት። በመሰረቱ በሰው ዘንድ አዲስ የሆነ ተሰርቶ የማያውቅ ኀጢአት ከቶ አይኖርምና፥ በእርስዎም ላይ የደረሰቦትም፥ ሰው ፈፅሞት በንስኀ ህይወት ያለፈበት የኀጢአት አይነት እንደሆነ ተረድተው፤ የመዳን ቀን አሁን ስለሆነ የቀጠሮ ቀን እና ሰዓት ሳያራዝሙ ወደ ንስሐ አባት ቀርበው ፤ ንስሐአባት ከሌለዎትም በእኛ በኩል ያሉትን አባቶችን በውስጥ መስመር በማማከር የፈለገውን ያህል ከባድ ኀጥያት ሰራው ብለው ቢያምኑም እንኳ በእግዚያብሔር ዘንድ የማይፋቅ በደል የለምና አሁንም ፍርሃቶትን አርቀው ወደ ይቅር ባይ አምላክ ይቅረቡ በማለት ምክራችንን እንለግሳለን።

ጠያቂያችን ፤ ከዚህ በፊት ንስሐ ገብተው እንደማያውቁ ከገለፁልን ሃሳብ ተነስተን ፤ አሁን ምን ማድረግ እንዳለብዎት ከመግለፃችን በፊት ስለንስሐ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲኖርዎት ይህን አጭር የመግቢያ ማብራሪያ ልከንልዎታል።  ንስሓ ማለት ማንኛውም በእግዚአብሔር ሀልዎት የሚያምን እና በክርስቲያናዊ ስነምግባር የሚኖር በየጊዜው በስጋ ምኞት በሚመጣበት ፈተና ከትንሽ እስከ ትልቅ ወይም ቀላልም ይሁን ከባድ ኀጢአት እንደሰራ የሰው ምስክር ሳያስፈልግ ራሱ በህሊናው ተጸጽቶ   የፈፀመውን ኀጢአት ካመነ ወደ ንስሓ አባቱ ቀርቦ የሰራውን ጥፋት በመናዘዝ እንደ ኀጢአቱ ክብደት ቀኖና ይሰጠዋል።

ስለዚህ ከእርስዎ የሚጠበቀው በድያለው አጥፍቻለው እግዚአብሔር ሆይ ማረኝ በማለት ከልብ መፀፀትና በህየወትም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላዎትን የግል ህይወትዎን የሚያረክስብዎትን ኀጢአት ነው ብለው የሚያስቡትን ሁሉ በግልፅ ለንስሐ አባት ወይም ለካህን ቀርቦ መናዘዝ ወይም በዝርዝር መናገር። በተጨማሪም ፣የበደልናቸውንና የበደሉንን ሁሉ ይቅር፥ በማለት በአጠቃላይ የቀጠሮ ጊዜ ሳያራዝሙ ወይም ሳይፈሩ ነገሮችን ሳያከብዱ በአስቸኳይ የነፍሳችን ሃኪም ወደሆኑት የንስሓ አባት በመሄድ ኀጢአትን መናዘዝ ነው። በዚህ ንስሓ በሚቀበለው ክርስቲያን እና ንስሓ በሚሰጠው አባት መካከል የሚፈፀመው አገልግሎት የሚታይ መንፈሳዊ ስርአት ሲሆን በዚህ መታዘዝ ውስጥ እግዚአብሔር በረቂቅ መለኮታዊ ጥበቡ በካሕኑ ላይ አድሮ በፍጹም እምነት ኀጢአቴ  ይፋቅልኛል ብሎ ከልብ በመታዘዝ ለንስሓ ህይወት የቀረበውም ምእመን ያለምንም ጥርጣሬ ኀጢአቱ ይቅር ይባላል ማለት ነው። ስለዚ በመፅሐፍ ቅዱስ እና በሌሎቹ ቅዱሳን መፃሕፍት በብዙ ቦታ ላይ እንደተገለፀው እግዚአብሔር ኀጢአት ይቅር እንደሚል እኛም ከኀጢአታችን እና ከበደላችን ተፀፅተን ወደ ፈጣሪ እንድንመለስና የእግዚአብሔር እንደራሴ ለሆኑ የሃይማኖት አባቶቻችን እንድንናዘዝ ታዘናል። (ኢያሱ7፥19 ማቴ3፥6 ዘሌ5፥5-6 የሐዋ19፥18)

ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቦትን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ሳይጠራጠሩና ሳያመነቱ ወደ ቤተክርስቲያን እና ወደ አባቶች ይቅረቡ። ታሰር ተፈለጥ በሚል ስጋዊ ዳኝነት የሚጠየቁበት ጉዳይ ስለሌለ ምህረቱና ቸርነቱ ፍቅሩና ትእግስቱ ወደ በዛው ወደ እውነተኛው አምላክ ስለሆነ የሚቀርቡት፤ የንስሓ ህይወትም ለክርስቲያኖች እድል የሚመች አላማ ስለሆነ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲኦል ወደ መንግስተ ሰማያት፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ፅድቅ፣ ከሞት ወደ ህይወት የሚያመጣ ቀና መንገድ ስለሆነ የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጡ ሰራሁ የሚሉትን ኀጢአት ለካህኑ በመንገር ቀኖናዎንእና መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ለማግኘት ህሊናዎትን ያዘጋጁ። እንደተፈፀመው የኀጢአት ክብደትና ቅለት ከሰአታት ጀምሮ እስከ ቀናትና ሳምንታት የሚወሰን የፆም ፣ የፀሎት፣ የስግደት ወይም የምፅዋት ቀኖና ሊሰጥዎት ይችላል። ይህንንም ቀኖና ወይም የካሳ ቅጣት መፈፀምና ወደፊት በኀጢአት እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዚህም በአባቶች ምክርና ትምህርት ለመኖር ቋሚ የንስኀ አባት መያዝ ያስፈልጋል።

ጠያቂያቸሰን፤ ለሁሉም ነገር ተጨማሪ ምክርና ትምህርት ከድረገፃችን ላይ እንዲመለከቱ እንዲሁም በውስጥ መስመር ሊያነጋግሩን እንደሚችሉ እንገልፃለን።