ስለ ቤተክርስቲያን ስርዓት
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ስለ ቤተክርስቲያን ስርዓት
ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች
በኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት ማንኛውም ክርስቲያን ከሚያገኘው ሀብቱ ላይ ለሁሉም ነገር በድርሻ ወይም በፐርሰንት መድቦ፦
1ኛ የራሱን ድርሻ ማለትም ለራሱ ኑሮ የተፈቀደለትን ይወስዳል፣
2ኛ ለቤተክርስቲያን ድርሻ (ለቤተ እግዚአብሔር) ፦ ከሚያገኘው ሀብቱ ከአስሩ አንዱን አስራቱን በኩራቱንና ቀዳማይቱን ይሰጣል፣
3ኛ ከሀብታችን ውስጥ ለድሆች ድርሻ ስላላቸው እነርሱንም እንመፀውታለን
ያደረግነው መልካም ነገር ሁሉ ከኛ እጅ የወጣው ገንዘብ ለግዜው የጎዳን ይመስላል እንጂ በመጨረሻው ግን ገንዘብ የማይገዛው ሰማያዊ ርስት ይገዛል። ስለዚህም ጠያቂያችን አሁን ከላይ በሰጠንዎ ማብራሪያ መሰረት የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የቄሳርን ለቄሳር ተብሎ እንደተፃፈ አስራት በኩራቱን ለሚመለከተው ለቤተክርስትያን ድርሻ መድበው በሌላ እጅ እንዳይገባ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲሰጡ፤ ለነዳያንም (ለተቸገረ ሰው) በመራራት የሚችሉትን ነገር ሁሉ በድርሻቸው እንዲያደርጉ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
በእለተ ሰንበት/እሁድ፣ በ21 የእመቤታችን በአል፣ እና በ29 ባለወልድ፦ እነዚህ በአላት የማይሰገድባቸው ቀናት እንደሆኑ በቤተክርስቲያን ቀኖና የተደነገገ ነው።
መልስ፦ ጠያቂያችን መገንዘብ ያለብዎት በቀኖና በዕዝል የሚቀደስባቸው እና በግዕዝ የሚቀደስባቸው ተለይተው ተወስነዋል። ስለዚህ በዕዝል የሚቀደስባቸው ግዜያት ከትንሳኤ ጀምሮ እስከ ሰኔ 17 ከዚያም ከመስከረም 26 – ህዳር 6 ከዚያም በገና ፆም ውስጥ ከታህሳስ 7 ጀምሮ እስከ አብይ ፆም መግቢያ ዋዜማ ድረስ እነዚህ በቤተክርስቲያን ውስጥ ዘወትር በዕዝል የሚቀደስባቸው ግዜያት ናቸው። ከዚህ ውጭ ያልጠቀስናቸው ጊዜያት ደግሞ በቤተክርስቲያን ስቡህ ተብሎ ማህሌት ካልተቆመ በስተቀር በግእዝ የሚቀደስባቸው ናቸው። ሚስጢራዊ ትርጓሜውን በሚመለከት ወደፊት ሰፋ አድርገን ልንልክ የምንችል ሲሆን፤ ለጊዜው ግን ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልስ ልከንልዎታል።
መልስ፦ አንዲት ሴት ወልዳ ክርስትና ስታስነሳ የሴቶች ልማድ ከመጣባት ህፃኑን ወይም ህፃንዋን በሌላ ሞግዚት በእለቱ ወደ ቤተክርስቲያን ተወስደው ጥምቀቱ ይፈፀማል። እናቲቱ ግን ከሴቶች ልማድ ስትነፃ ህፃኑን ይዛ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድና እሷም ፀበል ተረጭታ በመስቀል እንድትባረክ ይደረጋል፤ ህፃኑንም ታቆርባለች። በእርግጥ ጠያቂያችን ከሚያውቁት ወይም ከደረሰባቸው ተነስተው ጥያቄ ያቀረቡ እንደሆነ ቢታመንም ብዙ ጊዜ በተለመደው ገጠመኛችን ግን የወለደች ሴት ከ 80 ቀን በፊት ወንድ ልጅም ብትወልድ እስከ 40 ቀን የተለመደው የሴቶች ልማድ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ከመውለድ ጋር ተያይዞ ሴቶች እስከ 40 እና 80 ቀን እራሱን የቻለ ፈሳሽ የማይነፁበት ግዜ በመሆኑ ዘር ለመተካት ምክንያት የሚሆነው የወርሃዊ የሴቶች ልማድ ግን ይመጣል ተብሎ ለማሰብ ቢከብድም አልፎ አልፎ ግን እንደ መንፈሳዊም ሆነ እነደ ሳይንሱ ሊያጋጥም ይችላል ብለን ስለተቀበልነው ጠያቂያችን ያቀረቡት ጥያቄ በዚህ ማብራሪያ መልስ ለመስጠት የተሞከረ ስለሆነ እንዲመለከቱት ልከንልዎታል።
መልስ ፦
“አባትህን ወይም መምህርህን ጠይቅ ይነግሩህማል ” (ዘዳ 32፥7)
የጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ እና ስለ አብይ ፆም ያለውን የጊዜ እርቀት በሚመለከት ከቤተክርስቲያን አስተምሮ አንፃር የተሰጠ መንፈሳዊ ትምህርት።
እጅግ የምናከብራችሁ እና የምንወዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገጽ አባላቶቻችን፤ አንድ አባላችን በጌታችን ጥምቀት እና በፆሙ መካከል ያለውን የጊዜ ልዩነት ለምን እንደሆነ ማወቅ ፈልገው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ለሁላችሁም ጠቃሚ ስለሆነ አንብባችሁ እንድትረዱት ይህን ትምህርታዊ ምላሽ ሰጥተንበታል፤
1ኛ/ እንደሚታወቀው የጌታችን ልደቱ ታህሳስ 29 በዋሻ በእንስሳት በረት እንደተወለደ ፣በቅዱስ መፅሐፍም የሰው ልጆች ሁሉ ደስ ብሎዋቸው የአለም መድኃኒት ክርስቶስ እንደ ድሀ ተቆጥሮ በበረት መወለዱን መስክረዋል :: ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ እረኞች እና የሰማይ መላዕክትም በአንድ ላይ ዘምረዋል፤ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እስከ 30 ዘመን ድረስ (እስከተጠመቀባት እለት) የባህርይ አምላክነቱን እና እሱ ማን እንደሆነ ከእናቱ እና ምስጢሩን ከገለፀላቸው ከጥቂት ሰዎች በስተቀር ማንም ሳያውቀው እራሱን ሰውሮ አምላክ ነኝ ብሎ ዘመናትን ሳይጠቀልል (እድሜውን) ፣ የኦሪት ሕግንም ሳይሽር እና ሳይንቅ ከእናቱ ጋር እና ከዘመዶቹ ጋር እንደ ህፃናት እየታዘዘ በየጥቂቱ አደገ። እንደ አብራዊያን ወንድ ልጆችም ወደ ቤተ መቅደስ በመሄድ ህገ ኦሪትን እየፈፀመ አደገ : በዚህም ምስጢራዊ ጥበቡ ለብዙዎቹ በነብያት አፍ እንደተናገረ አስቀድሞ የሚፈፅማቸው ተአምራት አምላክ ከሆነ በስተቀር ሌላ ፃጽድቅም ቢሆን እንደማይፈፅማቸው እናቱ ድንግል ማርያም እና ከልደቱ ጀምሮ በ30 ዘመን ቆይታው ያደረጋቸውን ሁሉ በቅርብ የተመለከቱ የእግዚአብሔር ሰዎች የምስክርነት ቃል ያስረዳል። መድኃኒታችን ከእስራኤላዊያን ወይም ከአይሁድ ወገን እንደተወለደ ዜናውን የሰሙ ቢሆንም እንኳን፣ እንደተወለደ ምልክቶችን ያዩ ቢሆንም፣ እንደሚወለድም በነብያት እና በቅዱሳት መጽሐፍት የተነገራቸውም ቢሆን እውነቱን ከማየት እና አስቀድሞ ከመረዳት አይነ ህሊናቸው ስለተሰወረ ሳይረዱት ቆይተዋል :: እስከተጠመቀበት ግዜ በዚህ አይነት ጥርጣሬ ቆይተዋል :: በጥምቀተ መለኮት ዮሐንስም ከእሱ መምጣት አስቀድሞ ስለሱ መገለጽና ስለ ባህርይ አምላክነቱ ገልፆ በነገራቸው ግዜ በእምነት እና በጥርጣሬ መካከል እንዳሉ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ዮሐንስ እንደተናገረ ንስሃ ግቡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ያለውን፤ እሱም በመለኮታዊ ቃሉ አረጋግጦ እራሱ ገልፆላቸዋል።
2ኛ/ የጌታ ጥምቀት ጥር 11 ቀን (ጥር 10 ለ11 አጥቢያ ከሌሊቱ 6 ሰዓት በኋላ) በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቋል :: ጠያቂያችን እንዳሉት ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንጦስ በራሱ ፈቃድ ሄዶ 40 መአልት እና ሌሊት ከቆመበት ሳያርፍ የሚበላ የሚጠጣ ሳይቀምስ ፆሟል ::የፆምን ጠቃሚነት እና ታላቅት ለማስረዳትና የሁለችንም አብነት ለመሆን በፆሙ ግዜ ከፈታኙ የቀረቡለትን ፈተና ሁሉ ድል ነስቶ ዖሙን በሰላም እንዳጠናቀቀ በወንጌል ተመዝግቧል። (ማቴ 4 ከቁጥር 1 ጀምሮ)
የ40ው ቀን ቁጥርም ከጥር 11 ጀምሮ (ከጥር ውስጥ 20 ቀን እና ከየካቲት ውስጥ 20 ቀን ይሄን ስንደምረው 40 ቀን ይሆናል) የተፈፀመው የካቲት 20 ቀን ሲሆን ፆሙን እንደጨረሰ ወድያውኑ ወደ ቅድስት ከተማ ሄዶ ማስተማር ጀመረ :: ነብዩ ኢሳያስ እንደተናገረ በጨለማ የነበረ ህዝብ ብርሃንን እየ። (ኢሳ 9፥2)
ፆሙን በጨረስ በ 3ኛ ቀን በቃና ዘገሊላ መንደር ዶኪማስ የተባለ የታወቀ አይሁዳዊ ባዘጋጃው የሰርግ በአል ላይ ተገኝቶ በእናቱ አማላጅነት ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምራት አደረገ :: ይህ የሆነበት ቀን ማክሰኞ የካቲት 23 ቀን ነው :: ጠያቂያችን እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብዎት የቤተክርስቲያን አባቶቻችን ሊቃውንት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባሳዳረባቸው ታላቅ ፀጋ የበአላት አከባበር እና አፆፆም ስርዓት ባወጡ ጊዜ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በአላት ሁሉም ከውሃ ጋር የተገናኘ ምስጢር ስላላቸው እንዲሁም ሁለቱም የጌታ በዓላት ስለሆኑ ጥር 11 እና 12 ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ በተከታታይ እንዲከበሩ ደነገጉ :: በዚህ መሰረት የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 ጀምሮ “በዛን ቀን ቃና ዘገሊላ ሰርግ ተደረገ ጌታ ኢየሱስም ከእናቱ እና ከደቀ መዛምርቱ ጋር ተገኙ ” በማለት ‘ከ3ኛ ቀን’ የሚለው ቃል ፆሙን የጨረሰበትን ለማመልከት ነው :: ስለዚህ ዛሬም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ይሄንን በአል የምታከብረው በዚሁ ስርዓት ነው።
3ኛ/ አብይ ፆም በመጋቢት አካባቢ ለምን ሆነ ለተባለው ጌታችን መድኃኒታች እየሱስ ክርስቶስ እንደተጠመቀ ወድያውኑ ወደ ገዳመ ቆረንጦስ ሄዶ የፆመው ፆም ቢሆንም እንኳን፤ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ በቤተክርስቲያን እና በክርስቲያኖች ላይ ብዙ ስደት እና መከራ በመድረሱ የአጽዋማትን አጿጿምና የበአላትን አከባበር እንዴት መከናወን እንዳለባቸው ግራ እየተጋቡ ብዙ ወጣ ወረድ ስላጋጠመ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና አባቶች በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ምክንያት፤ ስርዓት እና ጊዜ ተወስኖላቸው ክርስቲያኖች ግራ እንዳይጋቡ፤አጿማት መቼ ተጀምረው መቼ ማለቅ እንዳለባቸው ወይም ለስንት ቀን መፆም እንዳለባቸው ስለ 7ቱ የአዋጅ አጿማት ስርዓት ሰርተዋል። በዚሁ መሰረት ጥምቀት እና ልደት የሚውለበት ግዜ የደስታ እና የኃሴት ግዜ ስለሆኑና ፆም ስለማይፆምባቸው በሌላ በኩል ዘመነ መርዐዊ ዘመነ ቅበላም ስለሚባሉ የአብይ ፆም የሚገባበት ግዜ ከየካቲት መጀመሪያ ጀምሮ እንዲሆን በባሕረ ሃሳብ ቀመር ውስነው አስቀምጠዋል:: የፆሙ መጀመሪያ ቀን አንድ ግዜ ወደ የካቲት ዝቅ፣ እንድ ግዜ ደግም ወደ መጋቢት ከፍ የሚልበት ምክንያት የባሕረ ሃሳብ የቀመር እና የተውሳቅ አሰራሩ እንደሆነ ማወቅ ይገባል። ይህንን ሃሳብ በውል ለመረዳት በባሕረ ሃሳብ አመቅቴ መጥቅዕ ተውሳክ እና መባጃ ሐመር የሚባሉትን ቁጥሮች ማወቅ ያስፈልጋል።ስለዚህ ጠያቂያችንም ሆኑ የዮሐንስን ንስኀ ድረገፅ አባላቶቻችን በሙሉ በዚህ ማብራሪያ ሃሳቡን እንድትረዱት ይህን አጭር ትምህርታዊ መልዕክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል።
ጠያቂያችን ፤ በመጀመርያ የጽሉላትን ትርጉም ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ጽሉላት የሚባለው ትርጉሙ በፍስክ ጊዜ ከምንበላው ምግብ ማለትም ከስጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት የመሳሰሉት ተከልክለን በፆም ጊዜ የምንበላቸውን ምግቦች ብቻ የምንጠቀምበት የአመጋገብ ስርአት ነው። ለምሳሌ በፆም ወራት ቅዳሜና እሁድን ጠዋት ከቅዳሴ በኋላ እንደሌሎቹ ቀናት ፆመን ሳንውል የምንመገበው የፆም ምግብ ወይም ያመጋገብ ስርአት ጽሉላት ይባላል። ስለዚህ ጠያቂያችን መረዳት ያለብዎት በማንኛውም የፆም ጊዜ ጽሉላት አለ።
አዎ ከቅዳሴ በኋላ ማንኛውም ያስቀደሰ ሰው የቅዳሴ ፀበል መጠጣትም ሆነ ፀበል መጠመቅ ይችላል። የቀደሱት ካህናት እና የቆረቡት ምእመናን ግን ከቅዳሴ በኋላ ፀበል መጠጣት እንጂ መጠመቅ አይችሉም። ስለዚህ ጠያቂያችን ስርዓቱን በዚህ ይረዱት ዘንድ ለጥያቄዎ ይህን አጭር ምላሽ ልከንልዋታል።
ጠያቂያችን ከዚህ በፊት በእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን የተዘጋጀን ምግብ መብላት ከክርስትና ሃይማኖት አንፃር እንደቀኖናችን መሰረት ትክክል የሆነውን ነገር በግልጽ ማስረዳታችንን እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ የሃይማኖቱ ቀኖና የሚከለክለው በተለይ በፍስክ ስለምንመገባቸው የምግብ አይነቶች ማለትም ስለ ስጋ እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በራሳቸው የሃይማኖት ስርዓት ባርከው ስለሚመገቡት የምግብ አይነት ይመለከታል። ምክንያቱም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ወይም በጌታችን በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ስም ባርኮ ያዘጋጃውን ምግብ ሲበላ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ግን የሃይማኖታቸው ስርአት በሚፈቅደው መሰረት ቢስሚላሂ በማለት የአላህን ስም ጠርተው ምግባቸውን ስለሚበሉ በዚህ በሁለቱም መካከል የስርአትና የሃይማኖት ልዩነት ስላለ ልዩነታችን ከዚህ የተነሳ ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ሃይማኖታዊ አቋም ሊኖርዎ በችልም ሳይጨናነቁ ተጨማሪ ምክር እንድንሰጥዎ የሰው ልጅ በሥጋ ተዛምዶ ቤተሰብ ሆኖ በሃይማኖት ሊለያይ ስለሚችል በማህበራዊ ኑሮ አብሮ ውሃ መጠጣት ደረቅ እንጀራ መብላት ወይም ቆሎ መብላት ቡና መጠጣት ሰላምታ መስጣጠት እነዚህን የሚመስል ጤናማ ግንኙነት የምናሳልፈው የጋራ ግንኙነት ኀጢአት ሊሆን አይችልም። ከምንም በላይ በሃይማኖት በማይመስሉን ዘንድ ሊያስመሰግን በሚችል ማህበራዊ ጉዳይ መተባበር የበለጠ በሰው ዘንድ ፍቅር ቢያበዛልን እንጂ የሚያመጣብን ፈተና ስለማይኖር ከዚህ ጋር ተያይዞ ፈተና እንዳሌለ ሊረዱ እና ሊገነዘቡ እንደሚያስፈልግ ይህን መንፈሳዊ ምክር እንዲደርስዎ አድርገናል፡
ጠያቂያችን በኦርቶዶክስ እምነት ደም ለሌላ ሰው መለገስ ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ፤ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ አስተምሮ የፍጡር ደም ለሰው መለገስ እንደሚቻል የተገለፀና የተብራራ ማስረጃ ባይኖርም እንኳን የሰውን ህይወት ለማትረፍ ምክንያት መሆን በጎ ስራ ስለሆነ እንደ ኀጢአት የሚያስቆጥርብን ባለመሆኑ የወገንን ህይወት ለማትረፍ መተባበራችን የተቀደሰ ሃሳብ ነው። በእርግጥ ቅዱስ መጽሐፍ እንዳስተማረን አለም የዳነው በክርስቶስ ደም ብቻ መሆኑን ነው። ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ እኛን ከመውደዱ የተነሳ ቅዱስ ስጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የአለም መድኃኒት መሆኑን አረጋግጦልናል። በዚህ ሰው የሚያድንና ለዘለአለማዊ ህይወት የሚያበቃ የክርስቶስ ደም ብቻ እንደሆነ ለሁላችንም የታወቀና የተረዳ ነው። ነገር ግን ከላይ ለሁላችንም እንደተገለፀው በህክምና ባለሞያዎች በተደረሰበት ጥናት መሰረት የአንድን ሰው ህይወት ለማትረፍ ደም መለገስ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የዛን ህይወት ለማትረፍ በበጎ ፈቃደኝነት ደሙን ቢሰጥ እጅግ ለወገን ያለውን ፍፁም ፍቅር ከመግለፁም በላይ ስራውም ከበጎ ስራ የሚቆጠር ስለሆነ ታላቅ የሆነ ምስጋናንና አድናቆትን ስለሚያተርፍ በሃይማኖት በኩል የሚያስነቅፍ አይደለም። ስለዚህ ጠያቀያችን በየትኛውም የአለም ክፍል በተጨባጭ የህክምና ሞያ በልዩ ልዩ ምክንያት ችግር የደረሰባቸውን ህሙማን ህይወት ለማትረፍ የደም ልገሳ ጉዳይ አለም አቀፍ ትኩረትን ያገኘ ስለሆነ በሃይማኖታችንም በኩል በጎ ለሆነው ተግባር ሁሉ መተባበር አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚታመን ጠያቂያችንም ሆኑ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ አባላቶቻችን የጥያቄውን ፍሬ ሃሳብ በዚህ ባስተላለፍንላችሁ አጭር መልስ ትረዱት ዘንድ ይህን መልዕክት ልከንላችኋል።
ጠያቂያችን፤ በወር አበባ ክፍለ ጊዜ ያለች ሴት ከፈሳሽ እስከምትነፃ የትኛው የቤተክርስቲያን ክፍል ቆማ ማስቀደስና መፀለይ እንዳለባት ፣ መንፈሳዊ ፕሮግራሙን እንዴት ማግኘት እንዳለባት ሁሉ በስፋት ስለተገለፀ ደግመው እንዲያነቡት አሁንም አደራ እንላለን። ስላሉት ነገር ተጨማሪ ማድረግ የምንፈልገው የወር አበባ ላይ ያለች ሴት ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ መግባትና ቆሞ ማስቀደስ፣ የቀደሰውን የካህን መስቀልን የመሳለም ስርዓት መፈፀም፣ ፀበል ቦታ መጠመቅና በመስቀሉ መዳበስ ወደ ቋሚ ቅዱሳት ስዕላትና መስቀሉ ባለበት ወይም ልዩ ልዩ የፀሎት መፅሐፍት በሚገኝበት ልዩ የፀሎት ቤት ገብቶ መፀለይ እነዚህን የሚመሳስሉ ነገሮች ላይ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አሁንም በድጋሚ እንመክራለን። ሆኖም ግን ባለንበት መኖሪያ ቤታችንም ይሁን ከዋናው የቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውጪም ቢሆን መስቀል አትሳለሙ፣ ቁማችሁ፣ አታስቀድሱ፣ አትፀልዩ፣ ቤተክርስቲያን አትሳለሙ የሚል ህግ የለም። በመቀጠልም እርስዎ ያነሱትን በሚመለከት በግልዎት የሚፀልዩበትን የፀሎት መፅሐፍ አንስተው መፀለይ አይከለከሉም። አንገታችን ላይ ከጠላት እንዲጠብቀን ያሰርነውን መስቀል ወይም ደግሞ ስዕል ወይም ደግሞ የፀሎት መፅሐፍ ቢኖር ከኛ አንድናርቀው አንገደድም። ዋናው ቁም ነገር በውስጣችን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖር ንፁህ የሆነውን አምላክ በንፅህና በቅድስና እንድናመሰግነው በፍፁም እምነት ሆነን እንድናመሰግነው ለማጠየቅ ስንል የወር አበባ ክፍለ ጊዜ ላይ ያሉ ሴቶችም ሆኑ ሌላ የተለያየ ኅጢአትም ሆነ የሥጋ ነገር የገጠማቸው ሰዎች ከዚያ ነገር እስከሚነፁና እግዚአብሔርን ሳይዳፈሩ በርቀት ሆነው ማመስገን የተለመደ ስርዓት ነው። ስለዚህ ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ከዚህ ቀደም የሰጠናቸውን ትምህርታዊ መልእክቶችንም አሁንም መላልሰው ለማንበብና ለመረዳት እንዲሞክሩ መንፈሳዊ ምክራችንን እንለግሳለን።
ጠያቂያችን ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን 7ቱንም የአዋጅ አፅዋማት እንዲፆም መንፈሳዊ ግዴታው ነው። ይሁን እንጂ እንደ ሃይማኖታችን ስርዓት አንዱን የፆም ግዜ ሳይፆም ሌላውን ፆም ለመፆም ቢፈልግ የሚከለክለው ነገር የለም። ምክንያቱም ከብዙ ጥፋት አንድ ጥፋት ስለሚሻል፣ ከብዙ ጥያቄ ሁሉንም መልስ አልባ በመሆን ዜሮ ውጤት ከማግኘት ይልቅ አንድ መልስ ማግኘትም ነጥብ ስለሚያሰጥ ነው። ጠያቂያችን የሰኔን ፆም መፆም እንዳለብዎት ብናምንም ሳይፆሙ ከቀሩ ግን የገናን ፆም በመፆም ለሚቀጥለው የሰኔ ፆም ለመፆም ቅድመዝግጅት በማድረግ መንፈሳዊ ህይወትዎን ለማሳደግ መሰረት ስለሚሆንዎ የገናን ፆም መፆምዎ አስፈላጊ እንደሆነ ያለንን ምክር እንዲደርስዎ አድርገናል።
መልስ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከ 1 እስከ 30 ያሉት በየወሩ የሚከበሩ በዓላት፦
በ 1 ልደታ ፣ ራጉኤል ኤልያስ፣ በርተሚዎስ
በ 2 ታዲዎስ ሐዋርያ እዮብ ፃዲቅ ፣አቤል
በ 3 በዓታ ነአኩቶ ለአብ ፣ ፋኑኤል፣ ዜና ማርቆስ አባሊባኖስ
በ 4 ሐዋርያው ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ እንድርያስ፣ አብረሓ ወአጽብሐ፣ አባ መልከጻዲቅ
በ 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ፣ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ
በ 6 እየሱስ፣ አርሴማ፣ ቁስቋም፣ ማርያም መግደላዊት
በ 7 አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ፣ አትናቲዎስ፣ ዲዮስቆሮስ
በ 8 ፃድቁ አባ ኪሮስ ፣ አርባዕቱ እንስሳ
በ 9 እስትንፋስ ክርስቶስ ፣ ቶማስ ዘመርእስ
በ 10 መስቀለ እየሱስ፣ ፂዲንያ ማርያም፣ ተቀፀል ጽጌ
በ 11 ቅድስት ሃና፣ አቡነሐራ ድንግል፣ፋሲለደስ፣ ቅዱስ ያሬድ
በ 12 ቅዱስ ሚካኤል፣ ማቲዎስ፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ ድሚጥሮስ
በ 13 እግዚአብሔር አብ፣ ሩፋኤል ፣አቡነዘርእ ብሩክ
በ 14 ፃድቁአቡነ አረጋዊ፣ ፃድቁ ገብረክርስቶስ
በ 15 ሕፃን ቂርቆስ ሰማእት፣ ናትናኤል ሐዋርያ፣ ኤፍሬም ሶሪያዊ
በ 16 እናታችን ቅድስት ኪዳነ ምህረት፣ ቅድስት እየሉጣ
በ 17 ቅዱስ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ፣ አባገሪማ
በ 18 ፊሊጶስ ሐዋርያ ፣ ሰበር አጽሙ ለጊዮርጊስ
በ 19 ቅዱስ ገብርሔል
በ 20 ሐንጸተ ቤተክርስያን፣ ዮሐንስ ሐዚር፣ ኤልሳ ነብይ
በ 21 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዕዝራ ሱቱኤል
በ 22 ቅዱስ ዑራኤል፣ ሉቃስ ፣ ደቀስዮስ
በ 23 ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማእት
በ 24 ተክለሐይማኖት ፣ ክርስቶስ ሰምራ፣ ሙሴ ጸሊም፣ አባ ጎርጎርዮስ፣ 24ቱ ካህናት ሰማይ
በ 25 ቅዱስ መርቆርዮስ ፣ ሐዋርያው ቶማስ
በ 26 ዮሴፍ የእመቤታችን ጠባቂ፣ አቡነ ሐብተማርያም፣ ቶማስ ሐዋርያው
በ 27 መድኀኒአለም፣ አባ መባጽዮን
በ 28 አማኑኤል፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ
በ 29 ቅዱስ በዓለ ወልድ፣ ተፈጻሜ ሰመዕት ጴጥሮስ
በ 30 መጥምቁ ዮሐንስ ማርቆስ ወንጌላዊ
መልስ፦አስራት በኩራት በስጠትን በሚመለከት በመፅሐፍ ቅዱስ የታዘዘ መንፈሳዊ ግዴታ ነው።
አስራት ማለት ከአስር- አንድ (1/10) ወይም ከመቶ- አስር (10/100) ማለት ነው።
በኩራት ማለት ከሰው እና ከከእንስሳ የመጀመሪያው ክፍል ወይም የመጀመሪያ የበኩር ልጅ ለእግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን መስጠትን ያመለክታል
ቀዳሚያት ማለትም ከአዝሪት ከፍራፍሬው ከመሳሰለው ማንኛውም ሰው በጉልበቱ ደክሞ ወቶ ወርዶ ከሚያገኘው ሁሉ ለእግዚአብሔር የመጀመርያውን ይሰጣል።
በነዚህ በ3ቱም ዋና ዋና ፍሬ ርዕሶች ላይ ወደፊትም ቢሆን ሰፋ ያለ ትምህርት ልንሰጥበት እንችላለን። ለጊዜው ግን ጠያቂያችንም ሆኑ የዚህ የዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች ስለ አስራት በኩራት መገንዘብ ያለባችሁ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዝ መሆኑን ነው። ለዚህም ማስረጃ ፦
– አብርሃም አባታችን ለካህኑ ለመልከፀዴቅ አስራት እንደሰጠ በወንጌል ተጽፏል። (ዘፍ 14፥20)
– ያዕቆብም እግዚአብሔር ከሰጠው በረከት ሁሉ ለፈጣሪው አስራት ለመክፈል ያለውን ልባዊ ደስታ በመግለፅ ተስሏል። (ዘፍ28፥22)
– ከምእመናን የሚመጣው አስራት ለካህናቱ መተዳደሪያና የኑሮ መደጎምያ መሆን እንደሚገባው በብሉይ ኪዳን ተደንግጓል። ለምሳሌ እግዚአብሔር አምላክ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ ርስት እንዳይከፍሉ ሲከለክላቸው እንዲህ ብሎ ተፅፏል። “በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንላቸውም …. ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ አሥራት አድርጌ ሰጥቻቸዋአለሁ። በማለት የእግዚአብሔርን ቤት በማገልገል ላይ ተጠምደው ለግልና ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሃብት ማፍራት ያልቻሉትን የእግዚአብሔር ከህዝቡ የሚቀበለውን አስራት በኩራት በስርአት እንዲያስተዳድሩና እንዲያዙበት የተቀፈቀደ መሆኑን ያስረዳል ።”(ዘሁ 18፥21-32)
– በምድር ላይ ከሚገኘው ሀብትና ንብረት ከእንስሳትም ወገን ከሌሎችም ሁሉ አስራት መስጠት እንደሚገባ ታዟል። (ዘሌ 27፥30-33)
– እግዚአብሔር አምላክ አስራቱን በኩራቱን በበጎ ፈቃድ እንደ ህጉና እንደ ስርዓቱ ለሚያዋጡና በእግዚአብሔር ፊት ለሚያቀርቡ ሁሉ እንደሚባረኩ እንዲህ ተብሎ ተፅፏል።
“ ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ። …… አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ …. “ (ዘዳ 12፥ 5-18) ዘዳ 26፥13-15
እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ለሚልኪያስ አስራት በኩራትህን ለሚደብቁና ከእግዚአብሔርፊትለሚሰውሩ እንዲህ ብሎ እንደተናገራቸው እንመለከታለን “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምር ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን። የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው። እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።“ (ሚልኪያስ 3፥7-12) በማለት በአስራት በኩራት ለእግዚአብሔር ታማኝ ከሆንን የምናገኘውን በረከት፤ ታማኞች ባንሆን ደግሞ በረከታችን እርግማን እንደሚሆን በወንጌል ተፅፏል።
በአዲስ ኪዳንም አማኞች ሁሉ ካላቸው ነገር ላይ አስራት በኩራቱን እንደሚከፍሉ በቅዱስ ወንጌል ተመዝግቦ እናገኛለን። ለምሳሌ ወንጌላዊ ማቲዎስ እንደፃፈው “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።“ በማለት ፈሪሳውያን ህዝቡን በአስራት በኩራትእያስጨነቀ ከጥቃቅን ገቢ ላይ ሁሉ ደሃውን ሳይቀር እያስጨነቁ እነሱ ግን ከአስራት በኩራት በላይ የሆነውን ነገር እንደሚያጠፉ የሚያስገነዝብ ቃል ቢሆንም ነገር ግን ማንኛውም አማኝ ከሚያገኘው ገቢ አይነት አስራት ማውጣት እንደሚገባው ቃሉ ያስረዳል። (ማቴ 23፥23)
በሌላም በኩል በዚሁ የወንጌል ክፍል የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ ተብሎ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ማስቀረት እንደማይገባ ተፅፏል። (ማቴ 22፥21)
ስለዚህ ጠያቂያችን እርስዎ ማድረግ ያለብዎ አስራት በኩራቱን በፈለጉት መንገድ በጥሬ ገንዘብም ይሁን ለቤተክርስቲያን መገልገያ ንዋየ ቅዱሳትን ገዝተው ወደ ቤተክርስቲያን ከወሰዱ በኋላ ማንኛውም ሰው ተቀብሎ መንገድ ላይ እንዳያስቀረው ህጋዊ በሆነ የቤተክርስቲያን አስተዳደር የአሰራር መንገድ መሄድ አለቦት። ምክንያቱም እርስዎም በትክክለኛ ስራ ላይ መዋሉን ሳይጠራጠሩ አስተውለው ማስረከብ አለብዎት። እራስዎት በሰጡት ገንዘብም እየተጠራጠሩ ኩነኔ ውስጥ ላለመግባት በዚህ አይነት አሰራር አስራቶትን ቢያስረክቡ በግልፅና በአደባባይ የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር ስላስረከቡ እግዚአብሔር ደግሞ ለእርስዎ በምድርላይ በረከትን በኋለኛው ዘመን ሰማያዊ ክብርን ያጎናፅፍዎታል።
ቤተክርስቲያንም የአስራት በኩራት አስተዋጾ የሚውለው በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ለተወሰኑ አገልጋዮች፣ በቤተክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳት ማሟያ እና ለነዳያን የሚሰጥ ሲሆን ለያንዳንዱ ቤተክርስቲያን አሰራርና አፈፃፀም ድርሻ አለው።
ስለዚህ ባጠቃላይ በጥሬ ገንዘብ ከሆነ መስጠት የፈለጉት ቤተክርስቲያኒቱ በዚህ ዘመን ገንዘብንና ንብረትን የምታስተዳድርበት ህጋዊ የሆነ የገቢ ደረሰኝ ስላላት ገንዘቡን በሞዴል 64 የገንዘብ በደረሰኝ ማስቆረጥ ወይም በሙዳይ ማስገባት ይቻላል። ሌላ ንብረት ወይም ንዋየ ቅዱሳት ከሆነ የሚሰጡት በንብረት ገቢ ደረሰኝ አስቆርጠው በሞዴል 19 ማስገባት ወይም በቋሚ መዝገብ አፅፈው ገቢ አድርጎ ደረሰኙን መቀበል ይቻላል። ከዚህ ውጭ ለሚመክሩን ለሚያስተምሩን እለት እለት ለነፍሳችን ለሚያገለግሉን አባቶች በፈቃደኝት ማድረግ የምንፈልገው ካለ ይሄም ቢሆን በጎ ስራ ስለሆነ መልካም ነው፥ ነገር ግን ከአስራት በኩራይ የሚደመር አይደለም።
ስለዚህ በዋናነት ማንኛውም ክርስቲያን በህገ እግዚአብሔር በታዘዘው መሰረት ከሚያገኘው ማንኛውም ገቢ ላይ አስራቱን ማዋጣት እንዳለበት አምኖ በተግባር ለመፈፀም ፈቃደኛ ከሆነ ከላይ በገለፅነው መንገድ መፈፀም ይችላል፤ ከዚህ በተጨማሪ ዝርዝር አፈፃፀሙን በሚመለከት መረዳት እና ማማከር ካስፈለገ ግን ስለቤተክርስቲያን ስርዓትና ቀኖና እንዲሁም ትውፊት ጠንቅቀው የሚያውቁ የቤተክርስቲያን መምህራን (አባቶች) ቀርቦ በማነጋገር የሚፈፀምይሆናል።
ስለዚህ ጠያቂያችን ከዚህ ውጪ ቅድመ ሁኔታ ተዘጋጅተው በስራ ላይ ለማዋል የተቸገሩበት ጉዳይ ወይም ግልፅ ያልሆነልዎት ጉዳይ ካለ በውስጥ መስመር ቢያነጋግሩን በትክክለኛው አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ የሚችሉበትን እውነተኛ አቅጣጫ ልናሳይዎት እንችላለን።
በመሰረቱ በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ሃይማኖት ውስጥ የማይፈቀድ የምግብ አይነት በቤተክርስቲያናችን ቀኖና የተወሰነ ቢሆንም እንኳን ነገር ግን በዋናነት በአዲስ ኪዳን ስርዓት በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ እንኳንስ ለሥጋ የሚስማማ ምግብን ቀርቶ ሰውን የሚጎዳውን መርዝንም እንኳን ሳይቀር ብንጠጣው በኛ ላይ ስልጣን እንደማይኖረው ተፅፏል። ማር16፥18
ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ምግብ ለሆድ ሆድም ለምግብ ተፈጥሯል ሁለቱንም ግን እግዚአብሔር ያሳልፋቸዋል እንዳለው ሁሉ ጠያቂያችን በብሉይ ኪዳን ስርዓት እስራኤል ከግብፅ ለመውጣት ምክንያት የሆናቸውን የፋሲካውን በግ ባረዱ ጊዜ ብሩንዶው ስጋ (ያልበሰለው ስጋ) አትብሉ እንደተባለ በእሳት ያልበሰለ (እሳት ያልነካውን ስጋ) መብላት በኦሪቱ ስርዓት እንደማይፈቀድ ተፅፏል። ይሁን እንጂ በአዲስ ኪዳን ለሥጋችን ስለሚያስፈልገን የምግብ አይነት ከንቱና የማይጠቅም እንደሆነ የተፃፈ ስለሆነ የማይጎደን ሆኖ ያገኘነውን የስጋ ምግብ በመጠኑ የሚያስፈልገንን ያህል መመገብ እንዳለብን አስበን ማድረግ ይቻላል። አስፈላጊ ወዳልሆነ ወደ ኅጢአት ጎዳና የሚያመራንን እና ከሃይማኖታዊ ስርዓት ሊያወጣን ይችላል ብለን የምንጠረጥረውን የስጋ ምግብ ማድረግ ግን አይገባንም። ስለዚህ ጠያቂያችን ስላቀቡት ጥያቄ ይሄን አጭር ምላሽ እንዲደርስዎ አድርገናልና በዚህ ይረዱት። ተጠጨማሪ ማብራሪያ ካስፈለገዎ በውስጥ መስመር ሊያገኙን ይችላሉ።
የአንዲት ሴት ከወር አበባ የመንፃት ጊዜ ተብሎ የተያዘው 1 ሱባኤ ወይም ከ 7 ቀን ነው፤ በልዩ የጤና መታወክ ከ 7 ቀን ካለፈባት ሁለተኛ ሱባኤ ልትጠብቅ ትችላለች፥ ወይም በሴትዋ የጤና ጉዳይ አካላዊ ንፅህና የሚወሰን ይሆናል። 7 ቀን ስላለፈ ብቻ ፈሳሽ እስካልቆመ ወደ ቤተክርስቲያን መግባት አትችልም። የወር አበባ ጊዜ ጠብቆ ባይመጣ ወይም በተለየ ጊዜ ቢመጣ ዋናው ነገር ፈሳሽ በአካል ላይ እንዳለ ወደ ቤተክርስቲያን አይገባም ማለት ነው። ከ7 ቀን በኋላ ከፈሳሽ ስትነጻ ቤተክርስቲያን መግባትም ሆነ አገልግሎቱን ማግኘት ትችላለች ማለት ነው። ጠያቂያችን ሃሳቡን በዚህ ይረዱትና ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ሰፊ ትምህርት የሰጠንበት ስለሆነ ከድረገፃችን ላይ እንዲመለከቱት እንመክራለን።
ጠያቂያችን እርዳታ ለተቸገሩ ወገኖች ማድረግ ወይም ምጽዋት መስጠት የምግባር ዋናው አካል ነው። ከምንም በላይ ችግረኞችን መርዳት በፈጣሪ ፊት ለፍርድ በቀረብን ጊዜ የምንጠየቅበት ዋና ምግባር ነው። ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ብሎ እንደተፃፈ “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል።ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴ25፥ 34፣46) በማለት በጎ ስራ ሰርተው ብሩካን የተባሉ ፃድቃንም ለዚህ ክብር የበቁበት ትልቁ ምግባራቸው በፈጣሪያቸውም ፊት ያስመሰገናቸው ለተቸገሩ ነዳያን ላደረጉት በጎ ስራ ነው። ሌሎቹ ከፈጣሪ ዘንድ ርጉማን የተባሉት ችግረኞችን ባለመርዳታቸውና ልዩልዩ ፈተና ሲደርስባቸው ባለመጠየቃቸው በነፍስ ተጠያቂ አድርጓቸው ወደ ዘለዓለማዊ ኩነኔ እንዲሄዱ እንደተፈረደባቸው ያመለክታል። በአጠቃላይ በመፅሐፍ ቅዱስ ችግረኞችን በሚመለከት በስፋት ተመዝግቦ እናገኛለን። እነዚህ በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉትን ወገኖች መርዳት በቀጥታ ለእግዚአብሔር እንዳደረግንለት እንደሚቆጠር የወንጌሉ ቃል ያስረዳናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልዕክቱ “ለሰው ልጅ ሁሉ በጎ ነገርን አድርጉ ወይንም እርዱ የሚበልጠውን ደግሞ በሃይማኖት ለሚመስሏችሁም አድርጉ” በማለት ሰው ለሆነው ሁሉ በዘር በቋንቋ በቀለም በሌላም ሰውኛ ምክንያት ልዩነት ሳናደርግ መርዳትና በችግር ሁሉ መተባበር እንዳለብን ያስተምረናል። ሰው ሰውን ለመርዳት ሌላ ምንም አይነት መስፈርት ሳያስፈልው ሰው ሆኖ መፈጠሩ ብቻ በቂ ነው። በእርግጥም በሃይማኖት ደረጃ የማንተባበርባቸውና የምንለያቸው መክንያቶች ሃይማኖታችንንና መንፈሳዊ ህይወታችንን ሊያጎድፉ የሚችሉ የኅጢአት ተግባር ሲኖሩ ብቻ ነው። በጎ ስራ ለመስራት ግን አይደለም በተፈጥሮ ለሚመስለን ቀርቶ ለእንስሳና ለአራዊት ፣ ለእፅዋትና ለአዝርዕት ለመሳሰሉት ፍጥረታት ሁሉ በጎ ስራ መስራት የክርስቲያኖች መገለጫና ምግበር ነው።
ይሁን እንጂ ጠያቂያችን ስለሃይማኖትዎ እና መንፈሳዊ ህይወትዎ ቅድሚያ ሰጥተው ነገሮችን በጥንቃቄ ለማወቅና ለመረዳ ካለዎት ፍላጎት አንፃር የጠየቁት ስለሆነ እጅግ የሚያስመሰግኖት ነው። ዋናው ማወቅ ያለብዎት በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር የማንተባበረው በጋብቻ ስርዓት፣ በአምልኮ እና በመሳሰሉት የሃይማኖት ጉዳዮች ነው። በዚህ በእርስዎ ጠያቂነት መሰረት ሁሉም ሰው መረዳት ያለበት ፤ ምፅዋት ማድረግ፣ እርዳታ መስጠት የተለያዩ ድጋፎችን መፈፀም ባጠቃላይ ከሃይማኖት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር ሳይኖር ይሄንን በጎ ስራ በመስራታችን እኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የምናገኝበት ስለሆነ ባለን የኑሮ ደረጃ እንደየአቅማችን ከገንዘባችን ፣ ከጉልበታችን ፣ ከእውቀታችን፣ ከጊዜያችን ለተቸገሩ በመራራትና በፍቅር መርዳትና ማካፈል አለብን።
እርዳታ ሲባል በብዙ አይነት አገላለፅ ነው። ምክንያቱም ካለን ሀብታችን ውስጥ ድሆች የራሳቸው ድርሻ ስላላቸው ትንሽም ቢሆን የቱሩፋት ስራ በራሳችን ፈቃድ ለእርዳታ ብለን ያዘጋጀነውን ስጦታችንን መረዳት ለሚገባው አካፍለን ልንለግስ ይገባል። ይህ ማለት ለቤተክርስቲያን ነዳያንና ለሌሎቹም በጎ ስራዎች ሁሉ ማድረግ እንደሚገባን በሃይማኖታችን ስርዓት በተፈቀደው መሰረት በጎ አድርገን ምፅዋት ሰጥተን በፈጣሪ ዘንድ ማግኘት የሚገባንን ሰማያዊ ዋጋ ለማግኘት እንድንችል ሁላችንም ለበጎ ስራ እንዳይረፍድብን ተግተን መስራት ይገባናል።
እግዚአብሔር አምላክ ለበጎ ምግባር እና ለቱሩፋት ስራ እንድንበረታ እሱ ያግዘን።
ጠያቂያችን የእርስዎ ጥያቄ “…ቅባ-ቅዱስ መቀበል ይችላል” የሚለው አባባልዎ ግልፅ ስላልሆነ እንዲስተካከል ሆኖ፥ ነገር ግን እኛ ለማለት የፈለጉትን በተረዳነው መልኩ ይህን ምላሽ ልከንልዎታልና አንብበው ይረዱት፦ አንድ ካህን በእድሜ እርጅና አቅማቸው ሳይፈቅድ ቅዳሴ ቢያቆሙ የክህነቱ ስልጣን አቁሟል ማለት ግን አይደለም። ቤተ መቅደስ ቆሞ ማስቀደስ፣ መቁረብ፣ ማስተማር፣ ንስኀ አባት መሆን፣ መባረክ፣ እና ማጥመቅን የሚከለክል ህግ የለምና በእድሜ ምክንያት የማይችሉትን አገልግሎት ብቻ መስጠት ባይችሉም በቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ የአባትነት ክብር ተሰጥቷቸው ከላይ የዘረዘርናቸውን የክህነት አገልግሎትም እንደሁኔታው መስጠት ይችላሉ ማለት ነው። ጠያቂያችን በዚህ ያልተመለሰልዎት ሃሳብ ካለ በውስጥ መስመር ጥያቄዎን ቢያብራሩልን ተጨማሪ ምላሽ ልንሰጥዎት እንችላለን።
ባጭሩ ጠያቂያችን የተሰጠን የንስኀ ቀኖና በፆም ራሳችንን ለእግዚአብሔር እንድናስገዛ ከሆነ የተሰጠን የፆም ቀኖና እስከሚያልቅ ድረስ የተወሰነልንን ሰዓት ጠብቀን እየጾምን የፆም ምግብ እንመገባለን እንጂ የፍስክ ምግብ አንመገብም። በንስኀ አባታችን የተሰጠን የንስኀ ቀኖና ስግደት ብቻ ከሆነ ስግደቱን ሳንበላ እየሰገድን የፍስክም ቢሆን መመገብ እንችላለን። ምክንያቱም የእኛ የንስኀ ቀኖና ከቅዳሴው ፀሎት አይበልጥምና ቅዳሴ ተቀድሶ ከአለቀ በኋላ መፈፀም እንችላለን። ስለዚህ ጠያቂያችን የንስኀ ቀኖና አፈፃፀም ሂደትን ወሳኙ ቀኖናውን የሰጠው አባት ነው እንጂ በሌላ ወገን በጥያቄ የሚብራራ ባይሆንም ሃሳቡን ግን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል።
ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ የቀረቡልንን ጥያቄዎች መነሻ አድርገን የማይሰገድባቸውና የማይፆምባቸውን ቀናትና በዓላት አስመልክቶ መልዕክት ማስተላለፋችንን እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ ሁሉም አባላት የየራሳቸውን ጥያቄ ይዘው እየቀረቡ ሊሆን ስለሚችል አሁንም ለእርስዎ የምንሰጥዎ ምክር ቅዳሜን እና እሁድን በቤተክርስቲያን ቀኖና እንኳንስ ለንስኀ ፆም ተሰጥቶን ይቅርና በአዋጅ በተደነገገበት በ 7ቱ አፅዋማት ውስጥ የሚገኙ ቅዳሜ እና እሁድ የፍስክ ምግብ አንበላባቸውም እንጂ ከቅዳሴ በኋላ ሳንፆም ለፆም የተፈቀደ ምግብ እንደምንበላ መታወቅ አለበት። ስለዚህ ንስኀ የሚሰጡን አባቶችም ይህንኑ ምእመናን እንዳይሳሳቱ አብራርተው መክረው የንስኀ ቀኖና መስጠት አለባቸው። ስለዚህ ፆምና ስግደት በማይፈቀድባቸው ቀናትና በዓላት አንፆምም አንሰግድም ማለት ነው። ፆምን በተመለከተ ቅዳሜ እና እሁድ ያልፆምነው በቤተክርስቲያን ቀኖና ስለተደነገገ እንጂ እኛ መፆም ሳንፈልግ ቀርተን ስላልሆነ ሌላ ተለዋጭ እለታት አያስፈልግም። ምክንያቱም ቅዳሜ እና እሁድን ከምንፆማቸው የፆም ቀናት ጋር አብረው ስለሚቆጠሩ ነው። ስግደትን በሚመለከት ግን የማንሰግድባቸውን ቀናት በሌላ ቀን መስገድ ይኖርብናል። በበዓላት ግዜ እንዳንሰግድ የተደረገበት ምክንያት ስግደት በራሱ መንፈሳዊ ስራ ስለሆነ እና ነፍስ ፍሬ የምታፈራበት ስራ ስለሆነ ልክ እንደ ስራ ከበአላት ውጭ ጊዜ ወስደን መፈፀም ስላለብን ይህን ለማስተማር ነው እንጂ በበአላት ቀን ሳናውቅ ብንሰግድም እንደ ኀጢአት ይቆጠርብናል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ ጠያቂያችን ኀሳቡን በዚህ እንዲረዱት ይህን አጭር መልዕክት ልከንልዎታል፤ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲኖርዎት ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ የሰጠናቸውን መልዕክቶች እንዲሁም ስለ አስራት በኩራት ላቀረቡት ጥያቄንም በሚመለከት ከድረገፃችን ላይ ስላለ ወይም አንድ አባላችን ከዚህ በፊት ያስተላለፍነውን መልዕክት ሼር ስላደረጉልዎት አሱን አንብበው እንዲረዱት እንመክራለን።
ጠያቂያችን ንስኀ ራሱን የቻለ የጾም፣ የፀሎት እና የስግደት ጊዜ ስለሚያስፈልገው ከመደበኛ የቀኖና አፇማት ጋር መሆን አይኖርበትም። ምናልባት የንስኀውን አይነት በመረዳት አንቀፀ ንስኀ በሚያዘው መሰረት የሚሰጠው የንስኀ አይነት ቀላል ሆኖ ከተገኘ ንስኀውን የሚያናዝዙ አባቶች የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል እንጂ የንስኀ ጊዜ ግን ከላይ እንደገለፅነው ራሱን የቻለ ከመደበኛ ፆም ውጪ ባለ ጊዜ መሆን ይገባዋል።