ሰሙነ ሕማማትና ሆሣዕና
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
ሰሙነ ሕማማትና ሆሣዕና
ሆሣዕና ማለት ‹‹ ኦ እግዚኦ አድኅንሶ ኦ እግዚኦ ሠርሕሶ፤ አቤቱ እባክህ አድነን አቤቱ እባክህ አሁን አቅና›› መዝ 118÷25 ማለት ሲሆን መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ይህም የአዳም ዘር ካጣው ልጅነትና ከደረሰበት ሞት ለመላቀቅ የሚያሰማው ድምጽ እና የሚፈልገው መድኃኒት ነው፡፡ ‹‹ ለሊነ ጠየቅነ ወሰማዕነ ከመዘንቱ ውእቱ ክርስቶስ በአማን መድኅነ ዓለም፤ በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ አወቅን›› ዮሐ 4÷42 ተብሎ እንደተፃፈው፡፡
ይኸውም መድኃኒት ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ሱባኤ የቆጠሩለት በዳዊት ከተማ የተወለደው፣ ከጽዮን የወጣውና መዳንን ለሚሹ ሁሉ የተሰጠ መድኃኒት ነው፡፡ በዓለ ሆሣዕና ከዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት አንዱና የዐቢይ ጾም ስምንተኛው እሑድ ነው፡፡
ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜው እንደደረሰ ለማጠየቅ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጴጥሮስንና ዮሐንስን ‹‹ ሑሩ ሀገረ ዘቅድሜክሙ ወይእተ ጊዜ ትረክቡ ዕድግተ ዕሥርተ ምስለ ዕዋላ፤ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫዋንም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ›› ማቴ 21÷2 አላቸው፡፡
ይህንንም ዘካሪያስ ከዘመናት ቀድሞ በትንቢት ተመልቶ ‹‹አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል›› ዘካ 9÷9 ብሎ የተናገረው ይፈፀም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡
ከዘመናት በፊት ማዳኑን አይተው በእልልታ የዘመሩለት፣ ከሩቅ አይተው የተጣሩት፣ ያለዘርዓ ብዕሲ ከእመቤታችን የተወለደው፣ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ አቤቱ እባክህ አሁን አድን›› ብሎ የዘመረለት ጻድቁ፣ የዋሁ እና አዳኙ ንጉስ እነሆ ማዳኑን ሊያሳይ ከጽዮን ደጃፍ ቀረበ
የዋህ ኅዳጌ በቀል ንጉሥ ያላት ሀገር ፣ በትህትናው ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን፣ከተማይቱን እያየ የሚያለቅስላት፣ የታሰሩትን አስታውሶ ያስፈልጉኛል ፍቱልኝ እያለ የሚጣራ ፣ የተናቁትን የሚያከብር፣ የተዋረዱትን የሚያነሳ እና ግዑዛን ፍጥረታት በሰው አንደበት ያመሰገኑት ንጉሥ ያላት ሀገር፣ ዘንባባ ተይዞ የተዘመረለትንጉሥ ያላት ሀገርና ሰላምሽ ዛሬ ነው የተባለላት ሀገር ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት ? ይህንንም የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሲተረጉሙ የጽዮን ልጅ የተባሉት እስራኤላውያን ሲሆኑ ጽዮን የተባለች ደግሞ ኢየሩሳሌም እንደሆነች ነው፡፡‹‹ደቀመዛሙርቱም አህያይቱንና ውርንጫይቱን አመጡለት›› በዚያ የእሳት ዙፋን ላለው አህያይቱን ከውርንጫይቱ ጋር አመጡለት፣ ኪሩቤልና ሱራፌል ከግርማው የተነሳ ለሚንቀጠቀጡለት፣ የመባርቅት ብልጭልጭታ ለሚገለባበጥለት፣ ሰማይ መንበሩ ምድር የእግሩ መረገጫው ለሆነችለት ደመናትን አዝዞ፣ ነፋሳትን ጠቅሶ በእሳት መንኮራኩር ላይ ለሚረማመደው ጌታ አህያይቱንና ውርንጫይቱን አመጡለት፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ ስለዚኽ ነገር ሲናገር፡- ‹‹ ፍቅርህ ከዛበነ ኩሩብ አውርዶ በአህያ ጀርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደህ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደድክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠህክብርህን ማሳየት አልወደድክምና፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠህ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙርትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጎበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጎበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱሳን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኮላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡›› ያስረዳል፡፡
ይህም የሆነው ትንቢቱ ምሳሌው ይፈፀም ዘንድ ነው፡፡ ትንቢቱ ከላይ ያየነው በትንቢተ ዘካርያስ 9÷9 ላይ ያለው ሲሆን ምሳሌውደግሞ ቀድሞ አባቶቹ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ፡፡ ዘመነ ሰላም ከሆነ ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ እና የሰላም ዘመን እንደደረሰ ለማጠየቅ የሰላሙ መሪ የሰላሙ ዳኛ መድኃኔዓለም በአህያይቱ ላይ ተቀምጦ ታዬ፡፡ ምሲጥሩ ግንበአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝምና እርሱም ካልፈለጋችሁኝ አልገኝም ከፈለጋችሁኝም አልታጣም ለማለት በአህያ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም የቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ሊቃውንት አህያይቱን የእስራኤልና የኦሪት ምሳሌ ናት ይላሉ፡፡ የእስራኤል ምሳሌ ናት ሲሉ አህያይቱ ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነች ሁሉእስራኤልም ሕግን መጠበቅ የለመዱ ናቸውና ነው፡፡ የኦሪት ምሳሌ ናት ሲሉ ደግሞ አህያይቱ ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነች ሁሉ ኦሪትም የተለመደች ሕግ ናት እና ነው፡፡ ውርንጫይቱንም በ አሕዛብና በወንጌል ይመስሏታል፡፡ በአህዛብ ሲመስሏት ውርንጫይቱ ቀንበር መሸከም እንዳለመደች ሁሉ አሕዛብም ሕግን መጠበቅ አለመዱምና በወንጌል ሲመስሏት ደግሞ ውርንጫይቱ ቀንበር መሸከም እንዳለመደችሁሉ ወንጌልም ያልተለመደች አዲስ ሕግ ናት በማለት ያስረዳሉ፡፡እርሱም ተቀመጠባቸው ከእየሩሳሌም እስከ ቤተመቅደስ አስራ ስድስት ምዕራፍ ነው መድኃኒታችን አስራ አራቱን ምዕራፍ በእግሩ ሄዶ ሁለቱን ምዕራፍ በአህያይቱ ላይ ተቀምጦ ከቤተመቅደስ ደረሰ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ቤተመቅደሱን ሶስት ጊዜ ዞሯል፡፡ ይህም የሶስትነት ምሳሌ ነው፡፡ አህያ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪክ አላት በለዓም መንፈሳዊ ዐይኑ ታውሮ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከውን መልአክ ባያየውም አህያይቱ ግን የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ የእግዚአብሔርን መልአክ አይታዋለች፡፡ ዘኅ 22÷23 ጌታም በተወለደ ጊዜ እስትንፋሷን ገብራለታለች ታዲያ ሸክም ያቆሰላትንና እረፍት የናፈቃትን አህያ ክርስቶስ ፈታችሁ አምጡልኝ ብሎ ዙፋኑ ዞፋኑ አደረጋት ስንል ለአህያይቱ ብቻ የተሰጠ ክብር እንዳይመስለን፤ እኛም እንደ አህያይቱ ጀርባችን ባይቆስልም የልባችን ጀርባ ግን በሀጢያት ሸክም የጎበጠና በበደል ብዛት የቆሰልን ነንና መድኃኔዓለም ያኔ የላካቸውን ካህናት ዛሬም ወደኛ ልኮ ፈታችሁ አምጡልኝ እያለ ዘወትር እንደሚፈልገን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ የተናቀችውንና የተዋረደችውን አህያ ለምን መረጣት ቢባል ትህትናውን ለመናገር ነው፡፡ በሌላ መልኩ አህያ ከሌሎች እንስሳት አንፃር ስትታይ የማታስፈራ ናት ጌታም እንደ ነገሥታት ሥርዓት በከበረ ሠረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ መታየቱ መንግሥቱ የትህትና መሆኗን ያስረዳል፡፡ የመገለጡም ዓላማ ለድህነት እንጂ ለክብር አይደለምና
በዚያ የነበሩትም ሁሉ አንተ ከባቴ አበሳ በደልንም የምትደመስስ ነህ ሲሉ በአህያይቱ ላይ ልብሳቸውን ጎዘጎዙ አነጠፉም፡፡ የማትቆረቁር ሕግ ሰራህልን ሲሉም የሚቆረቁረውን ኮርቻ ሳያስቀምጡ ልብሳቸውን አንጥፈውለታል፡፡ ይህም ኢዩ በእስራኤል ሲነግሥ እስራኤላውያን ልብሳቸውን አንጥፈውለታልና በዚያ ልማድ ነው፡፡ እንኳን አንተ የተቀመጥክባትም አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ እጅግ የሚበዙትንም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፡፡ እኩሌቶቹም ከዘንባባ ዝንጣፊ እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር ይህም ዘንባባ የድል ምልክት፣ የደስታ መገለጫና የምሥጋና ማቅረቢያ ነው፡፡ አብርሃም ይስሃቅን በወለደ ጊዜ፣ ይስሃቅም ያዕቆብን በወለደ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን አመስግነውበታል፡፡ እስራኤልም ከግብጽ በወጡ ጊዜ ማርያም እህተ ሙሴ ከበሮ እየመታች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ ዮዲት እስራኤልን እየገደለ ያስቸገራቸውን ሆሎፎርኒስን አንገቱን ቆርጣ በገደለችው ጊዜ እስራኤል ዮዲትን አሸናፊና ኃያል ነሽ እያሉ ዘንባባ ይዘው አመስግነዋል፡፡
ዘንባባ እሾሀማ ነው፡፡ አንተም ኃያል አሸናፊ ነህ ሲሉ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፤ ዘንባባን እሳት አያቃጥለውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አንተም ባህርይህ የማይመረመር ረቂቅ ነው ለማለት፤ ዘንባባ የነፃነት ምልክትነው ከባርነት የምታወጣን አንተ ነህ ለማለት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው አመስግነውታል፡፡
የተምር ዛፍ ዝንጣፌ ይዘው ያመሰገኑትም አሉ፤ ተምር ልዑል ነው አንተም ልዑለ ባህርይ ነህ ለማለት፤ የተምር ፍሬ በሾህ የተከበበ ነው ባህርይ አይመረመርም ለማለት የተምር ዛፍ ይዘው አመስግነውታል፡፡
የዘይትም ዛፍ ቅጠል ይዘው አመስግነውታል፤ ዘይት ጹኑዕ ነው አንተም በባህርይህጽኑዕ ኃያል ነህ ለማለት፤ ዘይት ለመብራት ያገለግላል፤ ጨለማውንም አሸንፎ ብርሃንን ይገልጣል አንተም የጨለመ ህይወታችንን ታበራለህ ሲሉ የዘይት ዛፍ ቅጠል ይዘው አመስግነውታል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማም በገባ ጊዜ ይህ ማነው በማለት ከተማይቱ ተረበሸች የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዝ አይታ የሕፃናትንም ምስጋና ሰምታ ተናወጠች፡፡መድኃኔዓለምም የሕፃናቱን፣ የደቀመዛሙርቱንና የሕዝቡን ምስጋና ተቀበለ ሆሣዕህና በአርያም በእግዚአብሄር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው እያሉ በእናቶቻቸው ጀርባ እና እቅፍ ያሉ ሕፃናትና የቤታንያም ድንጋዮች ሁሉ ሳይቀሩ በታላቅ ደስታና ሀሴት ሆነው በአንድ ድምጽና በንጹሕ አንደበት ዘመሩለት አመሰገኑትም በዚህም ምስጋና ሰማይ ሰማየ ሰማያት በምድርም ያሉ ፍጥረታት ሁሉ በዚህ ልዩ የሕፃናት ዝማሬ በደስታ እንደንቦሳ ዘለሉ፡፡ እኛንም እንደ ሕፃናቱ እሱን አመስግነን መንግሥቱን እንድንወርስ በቸርነቱ ይርዳን፡፡
ከሆሣዕና ማታ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕታቱም የዓመተ ፍዳ፤ የዓመተ ኩነኔ ምሳሌ ናቸው ናቸው፡፡ ዓመተ ፍዳ፤ዓመተ ኩነኔ ማለት የሰው ልጅ በሲኦል ባርነት፤ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ የኖረበት ያ5500 የመከራ ዘመን ነው፡፡ሕማማት ስንል መድኃኒታችን ክርስቶስ ሰውን ሁሉ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ለማላቀቅና ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወዶ ፈቅዶ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራ የሚያመለክት ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት የተከናወኑ ተግናት፡-
- ይህ ሳምንት በጌታ ላይ የሞት ምክር የተመከረበት
- በጲላጦስ ፊት የቆመበት
- ብዙ መከራና ሕማም የተቀበለበት
- በሀሰት የተመሰከረበት
- የሰው ልጅ ከጨለማ ወደ ብርሀን ከሞት ወደ ህይወት የተሸጋገረበት
- የጌታ የመስቀሉ ሕማሞች የሚዘከሩት
- ስጋውን የቆረስበት ደሙን ያፈሰሰበት
- ብሉይ ኪዳን ተሸሮ ሀዲስ ኪዳን የተተካበት
- ሰባት ተአምርት የታዩበት 4ቱ በምድር 3ቱ በሰማያት ናቸው፡፡
በምድር 1.ሙታን ተነስተዋል 2.አለቶች ተፈረካክሰዋል 3.መቃብራት ተከፍተዋል 4.የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፍሉአል፡፡
በሰማይ 1.ፀሀይ ጨልማለች 2.ከዋክብት ረግፈዋል 3.ጨረቃ ደም ሆናለች
በሕማማት የሚከለከሉ ተግባራት፡-
1. መስቀል አለመሳለም ነው፡- ምክንያቱም የመስቀል ክብር እና ኃይል የታወቀው ጌታችን በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ስለሆነ ነውና ያንን ለማሰብ ነው፡፡
2 አለመሳሳምም፡-ይሁዳ ጌታውን በመሳም አሳልፎ ሰጥቶታልና እኛም ክፋት ካለው መሳሳም መለየታችችንን ለማሰረዳና በአመተ ፍዳ በአመተ ኮነኔ ፍፁም ሰላም እንዳልነበረ ለማሳየት ነው፡፡ 3.ማንኛውም ለስጋ የሚያደሉ ተግባሮችን መተው;- የጌታችነን መከራና ሕማም በማሰብ በፆም በስግደት በጸሎት ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡
አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል፡-
በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን ጸዋትወ መከራዎች አሥራ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡
1. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)፡-መድኃኒታችን ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱን ግን ጲላጦስ ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ 27¸24፤ ማር 15¸15፤ ሉቃ 23¸25፤ ዮሐ 18¸39)፡፡በዚህም ምክንያት መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡
2. ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)፡-አምላካችን እጃቸው በደም በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ 27¸27)፡፡ ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መተውታል (ዮሐ 19¸2-4)፡፡
3. ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)፡-ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው ፊት ላይ የሚያስጸይፍ ምራቃቸውን እንደተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደተነገረ ኢሳ 50-6 እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት (ማቴ 27¸29-3ዐ፤ ማር 15¸19)፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የሆነውን ምራቅ ተቀበለ፡፡
4. ሰትየ ሐሞት ( መራራ ሐሞት መጠጣት)፡-ጌታችን በመልዕልተ መስቀል ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡ መዝ 68-21 ላይ ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› ተብሎ እንደተነገረ፡፡ ተጠማሁ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ 27¸34)፡፡ከዚህ ቦሀላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ (ማቴ 27¸48፤ ማር 15¸36፤ ሉቃ 23¸36፤ ዮሐ 19¸29)፡፡
5. ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)፡-መድኃኒታችን ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ (ማቴ 27¸28፤ ማር 15¸15፤ ዮሐ19¸1)፡፡ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ተገረፈ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› ኢሳ 5ዐ¸6 ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡
6. ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)፡-አምላካችን ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡(ማቴ 27¸27)፡፡ 7. ርግዘተ ገቦ (ጎንን መወጋት)፡-ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር መወጋቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ (ዮሐ 19¸33)፡፡(1ቆሮ 15¸54-55፤ ኢሳ 25¸8፤ ሆሴ 13¸14)፡፡እኛም ከተወጋው ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን አገኘን (ዮሐ 3¸5፤ ዮሐ 6¸54)፡፡
8. ተአስሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)፡- እጆቹን ወደኋላ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ እጀፐቹን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎተቱት፡፡(ዮሐ 18¸12)፡፡ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ መድኃኔዓለም በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡
9. አምሥቱ ቅንዋተ መስቀል፡- በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸው የብረት ችንካሮች ናቸው፡፡
1. ሳዶር ማለት ቀኝ እጁ ከመስቀሉ የተወጋበት ነው፡፡
2. አላዶር ማለት ግራ እጁ ከመስቀሉ የተወጋበት ነው፡፡
3. ዳናት ማለት ሁለቱ እግሮቹ በአንድነት ከመስቀሉ የተወጋበት ነው፡፡
4. አዴራ የመስቀሉ ቁዋሚና አግድም ያለው መስቀልኛ የተመታበት ነው፡፡
5. ሮዳስ ማለት መስቀሉ ጫፍ ላይ ኢየሱስ ናዝራዊ ንገሰ አይሁድ የሚለው ጽሁፍ የተመታበት ነው፡፡ (ኢሳ. 53¸1-13፤ ዮሐ. 10¸18፤ ዮሐ. 19¸30፤ 1ኛቆሮ. 5¸7)፡፡ በዚህ የተቀደሰው ሳምንት ይህንን የጌታን ውለታና የድኅነት ሥራ እናስተውል፡፡
ይህች ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ (ቤተ መቅደስን የመንጻት) እና መርገመ በለስ የተፈጸመባት ዕለት ናት፡፡ «በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ በመንገድም አጠገብ በለስ አይት ወደ እርስዋ መጣ ከቅጠልም ብቻ በቀር ፍሬ አላገኘባትም እርሱም ለዘለአለም ፍሬ አይገኝብሽ አላት በለሲቱም ያን ጊዜ ደረቀች» ማቴ.21-18-22 ማር.11-11 ፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስም «ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም» ሉቃ.13-6-9 ፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ድቅ ከአምልኮተ ጣት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲመለስና ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር መድኃኒታችን ክርስቶስ ማሳሰቡን ያስረዳናል፡፡
ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለ ሰውም በለሷ እንደ ጠወለገችና እንደ ተቆረጠች ሁሉ የሰውም ልጅ የንስሀ ፍሬ ባለማፍራቱ እንደሚቆረጥ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣል ቅዱሳት መጽሕፍት በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ «አሁን ምሳር በዛፍ ስር ተቀምጦአል እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደእሳትም ይጣላል» ፡፡ ማቴ 3-10 በለስ የተባለችው ቤተ እስራኤል ስትሆን ፍሬ የተባለው ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ናቸው፡፡
ሁላችንም ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖትንና ምግባርን አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆንና ጌታም ሲመጣ እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ «በበጎ ስራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ ኑሩ»፡፡ ቆላስ 1-11 ስለተባልን በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡
የሕማማት ማክሰኞ የጥያቄ ቀን ትባላለች፡፡
ለምን ተባለች?
1ኛ. ወንጌላዊው ማቴዎስ በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ሌላ ምንም አላገኘባትምና። ያን ጊዜ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያን ጊዜውን ደረቀች። ማቴ 21-18 አስከ 22 በማለት እንደ ነገረን ደቀ መዛሙርቱም ይህን የበለሲቱን መድረቅ አይተው። በለሲቱ ያን ጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው በመደነቅ የጠየቁበት እለት ናት። መድኃኒታችንም መልሶ። እውነት እውነት እላችኋለሁ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል በማለት ደቀመዛሙርቱን አስተምሮአቸዋል፡፡ ፍሬ ያልተገኘባትና ተረግማ የደረቀች በለስ የተባለችው ቤተ እስራኤል እንድሆነች መዘንጋት የለብንም፡፡ ጌታ በመጣ ጊዜ ከቅጠል በቅር ፍሬ እንዳያጣብንና እንዳንደርቅ ለዘለአለም ፍሬ አይገኝባችሁ እንዳንባል ዛሬ የንስሀ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡ ጌታችን እንዲህ ይለናልና በተወደደ ሰአት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና እነሆ የተወደደ ሰአት አሁን ነው የመዳንም ቀን ዛሬ ነውና፡፡2ኛ ቆሮ 6-2
2ኛ. የማይሾሙት ንጉስ ፣የማያበድሩት ባለጸጋ ፣ሰማይን በጥበቡ የዘረጋ ፣ምድርን በውሃ ላይ ያጸና ፣ሰማይ መንበሩ ፣ምድር የእግሩ መረገጫ የሆነችለት መድኃኔዓለም ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ-መቅደስ (ቤተ መቅድስን ማንጻት) ምክንያት፣ በዚህ ዕለት (ማክሰኞ) በማን ስልጣን ይህን እንደሚያደርግ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጠይቀውታል፡፡ከኛ ያይደለ እንደኛ ያይድለ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? ብለው ጠይቀውታል፡፡ (ማቴ.21፤23-27፣ ማር.11፤27-30፤ ሉቃ.20፤1-8) እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን ትምህርቶችና ተአምራት እንዳደርግ እነግራችኋለሁ አላቸው፡፡የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ናትን? ወይስ ከሰው? አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም? ይለናል ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል እንደ መምሕርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው፡፡ ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸው ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂ፡፡ ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው? ድንቁም እንዴት ጽኑእ ነው? መንግሰቱም የዘለዓለም መንግሥት ነው ገዛቱም ለልጅ ልጅ ነው፡፡ትን ዳን 4-3
3ኛ. በሌላ መልኩ ይህች ዕለት የትምህርት ቀንም ትባላለች፡፡ በመዝ 119 103 ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ ተብሎ እንደ ተጻፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፤ መክሮ መመለስ እንደሚገባን ሲገልጽልን ነው፡፡ በማቴ.21፤23-27፣ማር.12፤2-13፤37፣ ሉቃ. 20፤9፣ 21፤38
ጌታችን ሰኞ ለት ባደረገው አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ ሰጥቶ ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የትምህርት ቀን በመባል ትታወቃለች፡፡ ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ እንደነገረን «ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል» ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/
የአይሁድ ክፉ ምክርየ
የዛሬዋ የህማማት ረቡዕ የሚከተሉት ተግባራት ተከነውነውባታል፡፡
1.ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡
ዛሬ በዚች ዕለት አይሁድና ሊቃነ ካህናት መድኃኒታችን ክርስቶስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር የፈጸሙበት ቀን ነው። ልበ አምላክ ዳዊት “አንድ ሆነው በአንተ ላይ ተማከሩ በአንተ ላይም ቃል ኪዳን አደረጉ” መዝ 83: 5 ብሎ እንደተናገረው ከመስቀል ላይ አውጥተው እስኪሰቅሉት ድረስ እህል ላይቀምሱ ቃል ተገባቡብ፡፡ “በምድር ነገስታት ተነሱ አለቆችም በእግዚአብሔረና በመሲሁ ላይ እንዲ ሲሉ ተማከሩ” መዝ 2-2 በሎ በአፈ ዳዊት ያናገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘነድ ይህ ሆነ፡፡
ቀድሞ እስራኤል ዘሥጋ ወንድማቸው ዮሴፍን በቅንአት ተነሳስተው ሊገድሉት ተማክረው እንደ ነበር። ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ “እነርሱም በሩቅ ሳለ ዮሴፍን አዩት ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። አሁንም ኑ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን” ዘፍ 37-18 አሉ፡፡ ብሎ እንዳስተማረን ክፉዎች አይሁድ ዛሬም በመድኃኔዓለም ላይ ክፉውን መከሩበት፡፡
በሌላ መልኩ በመንገድ እያገለገሉ ይመሩዋቸው የነበሩትን ሙሴና አሮንን ሊገድሏቸው የተነሱበት ጊዜም ነበር። “ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ” ኦሪት ዘኍልቍ 14: 10 ክፉዎች አይሁድ ዛሬም በመድኃኔዓለም ላይ ክፉውን መከሩበት፡፡
ዛሬ መድኃኒታችንን ለመክሰሰ የክስ ምክር ያጸኑባችው (የተስማሙባቸው) ነጥቦች
- ረራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጓል፡፡ ሐዮ 19-7
- እኔ ንጉሥ ነኝ ይላል ። ማቴ 2-1
- .እኔ ከአብርሀም በፊት ነበርኩ ይላል ። ዮሐ 8-58
- እኔ እና አብ አንድ ነን ብሎ ተናግሮአል ። ዮሐ 10-30
- እኔን ያየ አብን አየ ብሎ ስለተናገረ ። ዮሐ 14-9
- የሰነመትን ቀን የሽራል፡፡ ዮሐ 5-18
- ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን እሰራዋከሁ፡፡ ዮሐ 2-19 ስላለ፡፡
በዚህ ምክንያት ሊገድሉትና መራራ በሆነ የመስቀል ላይ ሞት እንዲሞት ምክራቸውንም አጸኑ፡፡ወትሮ በህጋቸው የሚሰቀል አይገረፍም የሚገረፍም አይሰቀልም በክርስቶሰ ላይ ግን እጥፍ ድርብ መከራ እንደሚያጸነበት በአንድነት ተስማሙ፡፡ 6666 ጊዜ እንደሚገርፉት፤ በመስቀል ላይ ሰቅለው በ5 የብረት ችንካር አንደሚቸነከሩት ፤የረከሰ ምራቃቸውን በተዋበ ፊቱ ላይ እነደሚተፉበት ፤ጎኑን በጦር እንደሚወጉት ፤በተጠማ ጊዜም መራራውን እንደሚያስጎነጩት፤ በትር አሲዘው አነገሥንህ በማለት እንደሚዘባበቱበተ ፤ንጹሁን የባህርይ አምላክ በቀማኞች ወንበዴዎች መሐል እንደሚሰቅሉት ምክራቸውን ዘሬ አጸኑበት፡፡ እርሱ ግን ጌታ ትሁት እና ሩህሩህ ነው ። ከአንደበቱ ሀሰት አልተገኘበትም፡፡ከአንደበቱ ልዝብነት የተነሳ የምትነድ የጧፍ ኩስታሪ አያጠፋም።
2.የበጎ መአዛ ቀን ይባላል፡፡ የመልካም መአዛ ቀን መባሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ ማርያም እንተ እፍረት (ሽቱዋ ማርያም) ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ ይዛ በጸጉሩ ላይ በማፍሰሷ የመልካም መግዣ ቀን ተብሏል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ እነሆ በዚያ ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት ሰፈሪሳዊው ቤት በማእድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ ዋጋው ሽጹየሞላበት የአልባስጥሮስ ብለቃጥ አመጣች፡፡በስተሁዋላውም በእግሩ አጠገብ እያለቀሰች ቆማ በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር በራስ ጠጉርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቶም ትቀባው ነበረ ይለናል ሉቃ 7-37-39፡፡ ይህች ሴት ዘመኑዋን በነውርና በሀጢአት የጨረሰች ነገር ግን የእግዚአብሄርን የባሀረርይ አምላክነት ሰምታና ተረድታ ምህረቱን ያገኘች በእንባዋና በትህትናዋ ሀጢአትዋ የተሰረየላት ለሁላችንም ምሳሌ የምትሆን ሴት ናት፡፡ ዛሬ በዚች ሴት ምክንያት የበጎ መአዛ ቀን የባላል፡፡
3.የእንባ ቀን ይባላል፡፡ የዕንባ ቀን መባሉም ይህች ሴት ስለበደሉዋና ስለሐጢአትዋ በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ እያለቀሰች መላ ኃጢያቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን እያጠበች በጸጉርዋም እያበሰች ኃጢአትዋን በመናዘዝዋ የዕንባ ቀን ይባላል ።ማቴ 26- 6-13 ማር. 14 -9 ሉቃ 7-37 ዮሐ 12 -8 ለኛም ለንስሀ የሚሆን እንባ በቸርነቱ ያድለን፡፡
4.ስመዖን ዘለምጽ የተወቀሰበት ዕለት ነው፡፡ይህች ሴት ስለበደሉዋና ስለሐጢአትዋ በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ እያለቀሰች መላ ኃጢያቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን እያጠበች በጸጉርዋም እያበሰች ኃጢአትዋን ስትናዘዝ ጌታችንም ሰለትህትናዋ በመደነቅዞር ብሎ ስምዖንሆይ የምንግርህ ነገር አለኝ አለው ስምዖንም እነሆኝ መምህር አለው
5.ይሆዳ ጌታውን ለመሸጥ በ30 ብር የተስማማበትብ ቀን ነው፡፡ህዝቡ እሱን ከተክተለ ክብራችን ይቀርብናል በማለት ተጨንቀዋልና በእለተ ረቡእ የመጨረሻውን ምክር አድርገው ከሐዋርያት መካከል ይሁዳን በገንዘብ አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከተዋዋሉ በኋላ የምስመው እሱ ነው ያዙት ብሎ እንዲይዙት አድረጎአል። ምክራቸው ፍጻሜ በማግኘቱ በጌታ ላይ እየተሳለቁ መከራ አጽንተው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል።
ይህ ዕለት ታላላቅ ተግባራት የተከናወኑበትና የጌታ ጸዋትወ መከራ የጀመረበት ዕለት ነው፡፡በዚህም ምክንያት የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡
ስያሜዎቹን በተወሰነ መልኩ እንመለከታለን፡፡
ሀ. ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡– የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ ጠላቶቹ መጥተው እኪይዙት ድረስ ለኛ አርአያ ይሆነን ዘንድ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ማቴ.26-36-46
ለ. የምሥጢር ቀን ይባላል፡– ይህም የተባለበት ‹‹ይህ ስለእናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ›› ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ ‹‹ይህ ስለእናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ›› ማቴ.26 26-29፡፡ማር.14-20-24 በማት ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ምስጢረ ቁርባንን የገለጠበት ቀን በመሆኑ የምሥጢር ቀን ይባላል፡፡
ሐ. የሐዲሱ ኪዳን ሐሙስም ይባላል፡-መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን የገለጠበትና ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ የሐዲሱ ኪዳን ሐሙስም ይባላል፡፡ ‹‹ ይህ ስለእናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፡፡ ይህ ጽዋዕ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚፈሰው ደሜ ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ››፡፡ ሉቃ.22-20 በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ነው ፡፡
መ. ሕጽበተ ሐሙስ (እግር) ይባላል፡- “ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። እንግዲህ እኔ መምህርና ጌታ ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።” ዮሐ 13:5-15 በማለት የባህርይ አምላክ የአገልጋዮቹን እግር በማጠቡ ፈጹም ትህትናውን ያየንበት ቀን ነው፡፡
ሠ. የፋሲካ ዝግጅት የተደረገበት ዕለት ነው፡-ፋሲካ ማለት ማለፍ መሻገር ማለት ነው፡፡ ማቴ. 26 -17-19 /ማር 14 -1-16 /ሉቃ. 22 – 6 -13፡፡ ይኸውም እሥራኤላውያን በግብጽ ምድር በባርነት ሳሉ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ በሙሴ መሪነት በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ከግብጽ ምድር ከባርነት ከፈርኦን እጅ የወጡበትን እለት በየዓመቱ ፋሲካቸው ነውና ያከብሩታል፡፡ ዛሬም መድኃኔዓለም በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ቀርቶልናልና፡፡‹‹ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው፡፡›› 1ኛ ቆሮ. 5 -6 /1ኛ.ጴጥ.1 -10
ረ. በዚህ ዕለት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ለ30 ብር አሳልፎ ሽጦታል፡– ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለ ጌታ ሆይ መምህር ሆይ ብሎ በመሳም አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነው፡፡ “አሳልፎ የሚደጠውም የምስመው እርሱ ነው ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጣቸው”፡፡ ማቴ.26 -49 ፤ ማር.14 -44፡፡
ከዚህ በሁዋላ እረኛው ክርስተሰ የሚመታት በጎቸ ሀዋርያት የሚበተኑበት ሰአት ደረሰ፡፡ ይሁዳም የዘለዓለም ህይወቱን፤ ለክብር የመረጠውን፤ አልአዛርን ከሞት ሲያስነሳ ያየውን፤ መጻጉእን የፈወሰውንና ድንቅ ድንቅ ተአምራት ሲያደርግ በአይኖቹ የተመለከተውን ጌታውን ለ30 ብር አሳልፎ የሚሰጥበት ሰአት ደረሰ፡፡
ጌታሆይ አብሮ መብላት አብሮ መጠጣት አብሮ ለመሞት ነው፡፡ሌሎቹ እንኩዋን ቢክዱህ ጌታ ሆይ እኔ ግን እልክድህም ብሎ የተናገረው እርሱ የሐዋርያት አለቃቸው የሚሆን የቅዱስ ጴጥሮስ እምነቱ የሚፈተንበትም ሰአት ደረሰ፡፡
ከዚህ በሁዋላ የሐዋርያት አይኖቻቸው በእንቅልፍ ተሞላ ወደፈተና እንዳይገቡ ተገተውም እንዲጸልዩ ነገራቸው፡፡እነርሱ ግን ተኙ፡፡ የማያንቀላፋው እረኛችን ክርስቶስ እርሱ ግን ኪህ በሁዋላ እረፉ ብሎአቸው በሐዋርያት በኩል ሀላችንንም ተናገረን፡፡ የእርሱ ግን የመከራው ሰአት ጀመረች፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ በማለት ያስተምረናል፡፡
ሀ. በአንደኛው ሰዓት ሌሊት ሐሙስ ለአርብ ምሽት፡– ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ልብሱን አኖረ፤ማበሻ ጨርቅም አንስቶ ወገቡን ታጠቀ ፤የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡
ለ. በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ምሽት፡- ‹‹ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ›› ብሎ ሕብስቱን ባርኮ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ ›› ጽዋውንም ባርኮ ‹‹ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡
ሐ. ከሦስተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ አምስተኛይቱ ሰዓተ ሌሊት ድረስ፡- ለብቻው ፈቀቅ ብሎ ወዙ እንደ ደም እስኪፈስ እየሰገደ ጸለየ፤ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመለሰ፤ ተኝተው አገኛቸው፤ ቀሰቀሳቸው፤ ጴጥሮስንም አንድ ሰዓት ያህል እንኳን ከእኔ ጋር መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ አለው! ሉቃ.22 -14-፡፡
መ. በስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት፡– ከዚህ በሁዋላ ይሁዳ ጭፍሮችንና የካህናት አለቆችን ፈሪሳውያንን ሌሎችንም ፋና ጋሻ ጦርም የያዙትን አስከትሎ መጣ፡፡ ጌታችንም ደቀመዛሙርሩን ‹‹ተነሡ እንሂድ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል›› አላቸው፡፡ ይሁዳም ወደርሱ ቀርቦ ‹‹መምህር ሆይ ቸር ውለሃልን? ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፡፡ ይህ መሳም ለአይሁድ ጥቆማ ወይም ምልክት ነበር፡፡ ጌታችንም የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?›› አለው ሉቃ. 22 – 48፡፡
መድኃኔዓለምን ከበውት ወደ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቃ ቀያፋ ወዳለበት ወሰዱት፡፡ ጴጥሮስ ግን ከሩቅ ሆኖ ይከተለው ነበር፡፡ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ከአንደኛው ቅጥር ግቢ ገብቶ ተቀመጠ፡፡ አይሁድም በክርስቶስ ላይ ሁለት የሐሰት ምስክሮችን አመጡ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፡፡ በሦስተኛው ቀን እሰራዋለሁ›› ብሏል ብለው ከሰሱት፡፡ ሊቀ ካህናቱም ተነስቶ ‹‹እንዲህ ሲያጣሉህ አትሰማምን?›› አለው፡፡ ጌታችን ግን ምንም አልመለሰለትም፡፡ሊቀ ካህናቱም ‹‹ክርስቶስ ተብሎ የተነገረልህ የእግዚብሔር ልጅ አንተ እንደሆንክ ንገረኝ›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ አልክ›› አለው፡፡ ያን ጌዜ ሊቀ ካህናቱ ተናዶ ልብሱን ቀደደው፡፡ ራሱንም በብረት ዘንግ መቱት፡፡ድንግል በድንግልና የወለደችው የበኩር ልጅዋ የስቃዩ ጅማሬ እንዲህ ነበር፡፡
ሐሙስ ሌሊት ለአርብ አጥቢያ ከሌሊቱ ሥድስት ሰአት ጀምሮ፡፡
መድኃኒታችን ደቀመዛሙርቱን በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤የመንጋው ጠባቂ ክርስቶስ ይመታል የመንጋውም በጎች ሐዋርያት ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ይህ ይፈጸም ዘንድ ይሆናል አላቸው። የሐዋርያት አለቃቸው የሚሆን ቅዱስ ጴጥሮስም ግን ስለፍቅሩ ቢሳሰ ጌታ ሆይ ዛሬ ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። ብንራብ የምታበላን አንተ፤ብንታመም የምትፈውሰን አንተ፤የእጅህን ተአምራት ያየን ካንተ፤የቃልህንም ትምህርት የተማርነው ካንተ ነውና ጌታ ሆይ ሁሉም ቢክዱህ እኔ ግን አልክድህም፡፡ አብሮ መብላት አብሮ መጠጣት አብሮ ለመሞት ነውና አለው፡፡
እውነት እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።ጴጥሮስ ግን መልሶ ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በሁዋላ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ ከእርሱም ጋርም ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና መምህር ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው። ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በመድኃኔዓለም ላይ ጭነው ያዙት።ከሁሉም የሚደንቀው ትናንት ዘጎንብሶ እግሩን ያጠበው ጌታውን ለማስያዝ ስሞ ምልክትን ሰጣቸው፡፡ይህንን ስናስብ እንደዳዊት “አቤቱ ምህረትህን እንዴት አበዛህ” መዝ.36- 7 ከማለት በቀር ምን እንላለን፡፡ እስቲ ይሁዳን እንጠይቀው፡፡ ይሁዳ ሆይ ጌታ አጎንብዶ እግርህን ሲያጥብህ እንዴት አስቻለህ? ዮሐንስ የጫማውን ጠፍር መፍታት አይችለኝም ያለለት ጌታ አጎንብዶ እግርህን ሲያጥብህ እንዴት አስቻለህ? በ30 ብር የተስማህብት ጌታ አጎንብዶ እግርህን ሲያጥብህ እንዴት አስቻለህ? አንተ ግን ከህይወት ይልቅ ሞትን ከባለጠግንት ይልቅ ድህነትን መረጥህ፡፡
ከዚህ በሁዋላ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዞ ሰለጌታው ፍቅር የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮውን ቈረጠው። ጌታችን ግን እንዲህ አለው። ጴጥሮድ ሆይ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ አለው።
የድንግል የበኩር ልጅ እርሱ ግን ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ ምነው አልያዛችሁኝም አላቸው። “ብዙ ውሾች ከበቡኝ የክፉዎችም ጉባኤ ያዘኝ” መዝ 22 -16 የተባለው ይፈጸም ዘንድ በሰራዊተ መላእክት የሚከበበውን ወነበዴዎች ከበው ያዙት፡፡ “ሁሉን የያዘውን ያዙት ሁሉን የሚገዛውን አሰሩት በቁጣ ጎተቱት በፍቅር ተከተላቸው እንደበግ ለመታረድ ተነዳ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ ዝም አለ” ኢሳ 53 -7 የተባለው ይፈጸም ዘንድ፡፡ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ዘካርያስ በትንቢቱ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ “እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ” ዘካ 13 -7፡፡
እርሱን ግን ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ቅዱሱ ኤፍሬም እንዲህ ይላል “ሁሉን የፈጠረ ዛሬ እንደወንጀለኛ እየተመረመረ ነው፤ ከባያዎቹ አንዱ በጥፊ መታው፤ ጌታ ቆሞ ባሪያው ሊፈርድበት ጠቀመጠ ፤ሀጢአተኛው በንጹኁላይ ፈረደ፤ እነዚህን ነገሮች ባሰብኩ ጊኤ ልቤ በፍርሀት ይንቀጠቀጣል፤ ሰማያትም ይንቀጠቀጣል ፤የምድርም መስረት ይናወጻል ፤መላእክትና ሊቃነ መላእክት ይንቀጠቀጣሉ ፤ሚካኤልና ገብርኤል ቤንፎቻቸው ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤ በጥፊ ሲመታ ባዩ ጊዜ ኪሩቤል ከዙፋኑ ስር ይሸሸጋሉ” በማለት እንደነገረን፡፡ ጴጥሮስም የነገሩን ፍጻሜ ያይ ዘንድ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፡፡
የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር አላገኙም፤ በኋላም ሁለት ቀርበው። ይህ ሰው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ። እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን” አለው። እርሱ ግን ግን ዝም አለ። ቅዱስዮሐንስ አፈወርቅ “እንደዚህ ያለ ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? እንደዚህ ያለ ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? እንደዚህ ያለ ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው?” በማለት ያደነቀዋል፡፡
ከዚህ በሁዋላ በፊቱ ላይ ተፉበት፤ “ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል” መዝ 44 – 2 በማለት ዳወት ውበቱን ያደነቀለት ፊቱ የረከሰ የአይሁድን ምራቅን፡፡ ተቀበለ ጐሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው። ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን አሉ። ህብስት አበርክቶ የመገበውን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለውን ሀጢአትን የሚያሰተሰርየውን በጥፊ መቱት፡፡ ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦያይ ነበር፡፡ በእርሱ ላይ የደረሰው በኔም ላይ ይደርሳል በማለት ፈራ፡፡ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ። አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። የጴጥሮስ ክህደት እዚህ ላይ ጀመረ፡፡ ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት። ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች። ዳግመኛም ሲምል ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ። ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን። አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህን አሉት። በዚያን ጊዜ። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ እንደዚህ ነጋች፡
በነጋ ጊዜም የካህናትቻሸደቀ አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል አንድ ላይ ተማከሩ፡፡ ካሰሩት በኋላ ወስደው ለአገረ ገዢው ለጲላጦስ አስረከቡት። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ ጸጸት ተሰምቶት 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች* ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሽማግሌዎቹ ይዞ በመምጣት “ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ። እነሱም “ታዲያ እኛ ምን አገባን? የራስህ ጉዳይ ነው!” አሉት። ስለዚህ የብር ሳንቲሞቹን ቤተ መቅደሱ ውስጥ በትኖ ወጣ። ከዚያም ታንቆ ሞተ። የካህናት አለቆቹ ግን የብር ሳንቲሞቹን ወስደው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለሆነ ግምጃ ቤት ውስጥ መግባት የለበትም” አሉ። ከተመካከሩም በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። በመሆኑም ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተብሎ ይጠራል”። ማቴ 27 – አገረ ገዢው ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚፈልጉትን ማንኛውንም እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜ በዓመፀኝነቱ የታወቀ በርባን የተባለ እስረኛ ነበራቸው። በመሆኑም ሕዝቡ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ወይስ ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ግን በርባንን ፍታልን አሉት፡፡ ጲላጦስም ኢየሱስን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!”“ ይሰቀል!” እያሉ ጮሁ። ማቴ 27 -24 ፡፡ጻድቀ ባህርይ የድንግል ልጅ ይሰቀል ዘንድ ሽፍታው በርባን ይፈታ ዘንድ በአንድ ላይ ጮሁ፡፡ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” “ይሰቀል!”“ ይሰቀል!” አሉ። ከዚያም በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደቹ ሠራዊቱንም ሁሉ “ልብሶቼን ለራሳቸው ተካፈሉ በቀሚሴም ላይ እጣ ተጣጣል“ መዝ 33- 16 ፡፡ ያለው ይፈጸም ዘንድ ልብሱን ገፈው ቀይ መጎናጸፊያ አለበሱት ለኪሩቤል የብርሃን አክሊል ለሚያቀደጃቸው የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ አነገስንህ በማለት በቀኝ እጁም የመቃ ዘንግ አስያዙት። በፊቱ ተንበርክከውም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ አፌዙበት። ደግሞም ተፉበት፤ እስቲ እኛም እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ያለ ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? እያልን ትእግስቱን እናድንቅ፡፡ ከዚያም በመስቀል ላይ እንዲቸነከር ይዘውት ሄዱ። ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ጌታችን የሚሰቀልበትን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት፡፡ የራስ ቅል ቦታ የሚል ትርጉም ወዳለው ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ በደረሱ ጊዜ ሐሞት የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት እሱ ግን ከቀመሰው በኋላ ሊጠጣው አልፈለገም። ሁለት ዘራፊዎች ከእሱ ጋር፣ አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው ተሰቅለው ነበር። በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡት ነበር፤ራሳቸውንም እየነቀነቁ “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ፣ እስቲ ራስህን አድን! የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት ላይ ውረድ!” ይሉት ነበር። “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! የእስራኤል ንጉሥ+ ከሆነ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት* ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን የሚሉም ነበሩ። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አገሩ በሙሉ በጨለማ ተሸፈነ፡፡ እነእርሱ እርቃኑን ቢሰቅልት ጸሀይ ግን ጨልማ የአምላኩዋን እርቃን ሸፈነች፡፡
ከ6 ሰአት- 9 ሰአት በሰማይ 3 በምድር 4 ተአምራት ይተዋል ነው፡፡
በሰማይ ሦስት ተአምራት፡- እነዚህም ሀ. ፀሐይ መጨለም ለ. የጨረቃ ደም መልበስ ሐ.የክዋክብት መርገፍ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በመስቀል ላይ ያለውን የአምላካቸውን እርቃን ላለማሳየት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ይህንን ‹‹ፀሐይ ፀልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወክዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ አይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ›› ሲል ገልጾታል፡፡
በምድር አራት ተአምራት ታይተዋል፡-እነዚህም ሀ. የቤተ መቅደስ መጋረጃ መቀደድ ለ. የዐለቶች መሰንጠቅ ሐ. የመቃብሮች መከፈት መ. የሙታን በአጸደ ሥጋ መነሳት ናቸው ማቴ.27-45-46፡፡ እነዚህ ተአምራት በመስቀል ላይ የተሰቀለው ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን ለሰው ልጆች ያረጋገጡ ምልክቶች ነበሩ፡፡
በመስቀል ላይ ሆኖ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል (ቃላት) ተናግሩዋል፡፡
1ኛ. ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ ማቴ.27-46፡፡
2ኛ. እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ ሉቃ.23-43፡፡
3ኛ. አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ ሉቃ.23-46፡፡
4ኛ. አባት ሆይየሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው ሉቃ.23 -34፡፡
5ኛ. እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ ዮሐ.19፤26-27፡፡
6ኛ. ተጠማሁ ዮሐ.19፤30፡፡
7ኛ. ሁሉ ተፈጸመ ዮሐ.19 -30 የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡
በ9 ሰዓት በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ስለ ጌታችን በሰማይ 3ት በምድር 4ት ተአምራትን አይቶ በእውነት አምላክ እንደሆነ አመነ ‹‹አቤቱ በመንግሥት በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ባለ ጊዜ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ግን ‹‹እስቲ አምላክ ከሆነ እራሱን ያድን›› ብሎ ተዘባበተ፡፡ ፍያታዊ ዘየማን ግን ‹‹እኛስ በበደላችን ነው የተሰቀልን፤ እርሱ ግን ምንም ሳይበድል ነው፤ እንዴት በአምላክ ላይ ክፉ ነገርን ትናገራለህ›› ብሎ ገሰጸው ፈያታዊ ዘየማንም ጌታችን በጌትነት መንበረ ጸባዖት ሆኖ ታየው እርሱንም አይቶ ‹‹ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ›› ቢለው ጌታችን ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት›› ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታል በኋላ ገነት ሲገባም መልአኩ አንተ ማነህ፤ አዳም ነህ፤ አብርሃም ወይንስ ይስሐቅ? እያለ ጠይቆታል፡፡ መልአኩ ሳያውቅ የጠየቀ ሆኖ አይደለም፤እንኳን በመጨረሻ የጸደቀ ፍያታዊ ቀርቶ በዘመናቸው የኖሩ ጻድቃንን ያውቃል፤ አዳምን ፤አብርሃምን፤ይስሐቅን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት ሲተረጉሙት ‹‹አዳም ነህ›› ማለቱ የአዳምን ያህል ሥራ አለህን? አብርሃም ነህ ሲለው ደግሞ የአብርሃምን ያህል ሥራ አለህን? ለማለት ነው፡፡
በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ ትኩስ ደም አፈሰሰልን ዮሐ. 19 -34፡፡ ዕለተ ዓርብ ተጠምቀን ድኅነት የምናገኝበት ውኃ ከጎኑ የፈሰሰበት፣ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ያገኘንበት ዕለት ነው፡፡ ‹‹በነገው ዕለት ስለ ዓለም የሚቆረሰው ሥጋዬ የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው›› እንዳለ ማቴ 27-27፡፡ ቤተክርስቲያንም የተዋጀችው በዚሁ በዕለተ ዓርብ በፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ በዚህ ዕለት አርማችን መስቀሉ ማኅተማችን ደሙ ሕይወታችን እርሱ ሆነዋል፡፡ ሥጋውንና ደሙን በመስቀሉ ላይ አግኝተናል፡፡ ከመስቀሉ ሥር ድንግል ማርያም በዮሐንስ አማካኝነት እናት እንድትሆነን፣ እኛም ልጅ እንድንሆን የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ እናቱ እናት እንድትሆነን በይፋ የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ ‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› ዮሐ 19፡36 ብሎ ሰጠን፡፡ ርህርህት እናት ከመሰቀል ሥር በዕለተ ዓርብ አግኝተናል፡፡
በአጠቃላይ የስቅለት ዓርብ ጌታችን የቤዛነቱን ሥራ የፈጸመበት ነው፡፡ በቤተልሔም የተጀመረው የሰውን ልጅ የማዳኑ ሥራ የተጠናቀቀበት፣ ጌታም ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ የሠራበት ዕለት ነው፡፡ ዕለተ ዓርብ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የተባለው የተፈጸመበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን በመስቀል ላይ ‹‹ተፈጸመ›› ያለው (ዮሐ 19፡30)፡፡ እኛም በዚህ ታላቅ ዕለት ጌታችን ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ እያሰብን፣ ስለ ኃጢአታችንም እያዘንንና እያለቀስን፣ ስለ ማዳኑም ሥራ ምስጋናን እያቀረብን ስንሰግድ እንውላለን፡፡ እንደ ፈያታዊ ዘየማን ‹‹አቤቱ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበን›› እያልን እንማፀናለን፡፡ እርሱም ዳግመኛ በመጣ ጊዜ እንዲያስበን የጾማችንን ፍጻሜ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ማኅተምነት ማተም ይኖርብናል፡፡ ለዚህም የእርሱ ቸርነት የቅድስት ድንግል እመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ቅዳም ሥዑር ማለት ምን ማለት ነው
ቅዳም ሥዑር ይህ የተባለበት ምክንያት በሰንበት ከእህል ከውሃ መጾም አይፈቀድም ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዕለት ጌታ በመቃብር ውስጥ በመሆኑ ሐዋርያት ትንሣኤውን ሳናይ አንበላም አንጠጣም ብለው በማክፈል ስለጾሙት ነው፡፡
ለምለም ቅዳሜም ይባላል፡– ምክንያቱም በዚህ ዕለት ለምለም ቄጤማ ስለሚታደልበት ነው፡፡ ቄጤማ የሚታደልበት ምክንያት ምሳሌያዊና ምስጢራዊ ትርጉም ስላለው ነው፡፡ ምሳሌያዊ ትርጉም በኖኅ ዘመን የዘነበው ማየ አይኀ መድረቁን ለማረጋገጥ፣ ኖኅ ርግብን በመስኮት አውጥቶ ላከ በመጀመሪያው ዝም ብላ ተመልሳለች በሁለተኛው ስትላክ ‹‹ነትገ ማየ አይኀ ሐፀ ማየ ኃጢዓት›› እያለች ቄጤማ በአፏ ይዛ ስትመለስ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ተቀብሏታል፡፡ የርግቢቱ ድርጊት የጥፋት ውሃ ደረቀ፣ የኃጢዓት ውሃ ደረቀ የሚል የምስራች አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ዘፍ 8፡6-11
ምስጢራዊ ትርጉሙ ደግሞ ርግብ የተባለችው አማናዊት ርግብ እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ እንደመታየት አምላክ ወልደ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን የሚያመለክት ነው፡፡ ከእርሷ የተወለደው ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በሞቱ ሞትን እንዳጠፋልን “ማየ አይኀ” የተባለ ሞተ ነፍስን እንዳስቀረልን ለማመልከት የምስራች ሲሉ ካህናት ቄጤማ ያድላሉ፣ ምዕመናንም እስከ ትንሳኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሥሩታል፡፡
ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡– ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፣ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው መቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎች ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡
በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን የሚፈጸሙ ሥርዓቶች
- መኀልየ መኅልየ ይነበባል ምክንያቱም ተስፋ ትንሳኤ አለባትና
- እስካሁን በሌሎች ዕለታት ሳይደርስ የሰነበተው እግዚአ ሕያዋን (የሕያዋን ጌታ) ፣ ፍትሐተ ዘወልድ፣ ጸሎተ ዕጣን “ዘእንበለ ስኢም” ይደረሳል፣ ያለመሳሳም ወይም ያለ ሰላምታ ማለት ነው፡፡
- ገብረ ሰላመ በመስቀሉ (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ የሚለው መዝሙር ይዘመራል ምክንያቱም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት በርብሮ በገነት ዕረፍተ ነፍስን (ሰላምን) ለሰው ልጅ የሰጠው በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከላይ እንዳየነው ጌታ በዕፀ መስቀል ከመሰቀሉ በፊት መስቀል የሰላም ምልክት አልነበረም፡፡ እርሱ ከተሰቀለበት በኋላ ግን የሰላም ምልክት ሆኗልና ከፊተኛው ለመለየት ነው፡፡
- ከዚህ ሁሉ በኋላ በረከተ ቄጤማ ይዞራል
አክፍሎት፡– ዓርብና ቅዳሜ ይሆናል ያልቻለ አንድ ቅዳሜን ያከፍላል የዚህ አክፍሎት ጦም የተጀመረው በሐዋርያት ነው፡፡ ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ ሳለ ፈሪሳውያን እኛና የዮሐንስ ደቀመዛሙርት እንጦማለን አንተ ደቀመዛሙርት የማይጦሙት ለምንድን ነው? ብለው ጠይቀውት ነበር እርሱም ሙሽራ ከነሱ ጋር ስለ ሚዜዎች ሊጦሙ አይገባም ነገር ግን ሙሽራው ከነሱ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣልና ያን ጊዜ ይጦማሉ ብሎ መለሰላቸው በዚህ መሠረት ሐዋርያት ሙሽራው ክርስቶስ ከነሱ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ከሰው ርቀው፣ ከእህል ከውሃ ተለይተው፣ በዝግ ቤት ተወስነው ጹመዋል ካህናትና ምዕመናን የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ሐሙስ ማታ ከበሉ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ይቆያሉ ሁለቱን ቀን ያልቻሉ ግን ቅዳሜን ብቻ ያከፍላሉ፡፡
በሌላ መልኩ አክፍሎት ማለት፡– ማካፈል ማለት ነው በዚህ ዕለት ካህናት ምዕመናን ካመጡላቸው የትንሣኤ መዋያ በረከት ምእመናንም ካላቸው ሁሉ ለድሆች ያካፍላሉና፡፡