አመታዊ በዓላት

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

አመታዊ በዓላት

(አመታዊ የስላሴ ክብረ በዓልን በማስመልከት የተጻፈ)

“ገሀሡ አጋዕዝትየ ቤተ ገብርክሙ አብርሃም”

“ጌቶቼ ወደ ቤት ገብታችሁ እረፉ” ዘፍ 18:3

ሐምሌ 7 ቀን የአጋዕዝተ ዓለም ቅድስ ስላሴ በዓል በየአመቱ የምናከብርበት ዋና ምስጢራዊ ምክንያቱን በአጭሩ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

በቅድሚያ ስለ ስላሴ ሦስትነትና አንድነት በአጭሩ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስለሚያስፈልግ፤ ስላሴ የሚለው ቃል “ሠለሰ” ሦስት አደረገ ከሚለው የግእዝ ሥርወ-ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስት መሆን ሦስትነት ማለት ሁኖ በምስጢራዊ አገላለጹም አንድም ሶስትም (አንድነት ከሶስትነት) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የስላሴ ሶስትነታቸው በስም፣ በግብር፣ በአካል ነው። አንድነታቸው ግን በባሕርይ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ፣ ሁሉንም ስነፍጥረት በየወገኑ በመፍጠር ነው።

የስላሴ ሶስትነት ፡ –

  1. የስም ሶስትነት ማለት፡- አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ማቴ 28:19
  2. የአካል ሶስትነት ማለት፡- ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ አላቸው (ጥቅስ መዝ 33:14፣ 118:73፣ ኢሳ66:1 ፣ ዘፍ18:1-4 ማቴ 3:16)
  3. የግብር ሶስትነት ማለት፡- የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ፤ የወልድ ግብሩ መወለድ፤ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ

አብን ወላዲ፣ ወልድን ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ስንል ስለግብር ሶስትነታቸው ነው እንጂ እነሱማ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ፣ አንዱ ከአንዱ የማያንስ ዕለ እሩያን ናቸው።(ዩሓ 10:30) ቅድስት ስላሴ ስንል ቅድስት የሚለው ቅጽል ለሴት የሚሰጥ ቅጽል ቢሆንም ስላሴ በባሕርያቸው እንደ እናት ባሕርይ ስለሚመስሉ ነው። ልጅ ከእናቱ ባሕርይ እንደሚገኝ ይህ ዓለም ከስላሴ ባሕርይ ተገኝቷልና ነው። እናት ለልጇ የሚያስፈልገውን አስባ ተጨንቃ እንደምታቀርብለት ሁሉ፤ ስላሴም ለፈጠሩት ፍጥረት ሁሉ ከወዳድ እናት በላይ ስለሚያስቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድመው አዘጋጅተዋል (ማቴ 6:14)

በ40 በ80 ቀኑ የስላሴን ልጅነት አግኝቶ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሁሉ አስቀድሞ የስላሴን አንድነት ሦስትነት ወይም ስለምስጢረ ስላሴ መማርና ማወቅ መንፈሳዊ ግዴታው ነው። ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ማን ፈጠረህ ተብሎ ቢጠየቅ መልስ እንንዳያጣና መናፍቃንና ኢአማንያን በዘረጉት የክህደት ጉድጓድ ውስጥ እንዳይወድቅ ሊጠነቀቅ ይገባዋል።

ሐምሌ 7 ቀን ወደሚከበረው በዓል ስንመጣ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዘመን ጀምሮ አባታችን አዳምና እናታችን ሄዋን በምክረ ሰይጣን ተጠልፈው  ከወደቁ በኋላ የሰው ልጅ የሆነው ሁሉ በዲያብሎስ ቅኝ ግዛት (በሞት ጥላ ሥር) የወደቀ ቢሆንም እንኳ ከአዳም ልጅ ከአቤል ጀምሮ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ብዙ ቀደምት አበው እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል።

ከቀደሙት አበው መካከልም አባታችን አብርሃም ይገኝበታል። አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅና ታማኝ ሰው እንደነበረ በቅዱስ መፅሐፍ ውስጥ በብዙ ቦታ ተጠቅሶ ይገኛል።አብርሃም በዘመኑ ከነበሩ ጣዖት አምላኪዎች ራሱን በመለየት እውነተኛውን አምላክ ፈልጎ ለማግኘት በፍጹም እምነት በስነፍጥረታት ተመራምሮ የፈጣሪን ሥራ እያደነቀ በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር ለሚፈልጉትና ለሚጠሩት ሁሉ አቤት የሚል የቅርብ አምላክ ነውና በከራን ምድር ለወዳጁ ለአብርሃም ተገልጾ “ከሃገርህ ከአባትህ ቤትና ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደማሣይህ ምድር ውጣ” ታላቅ ህዝብም አደርግሃለሁ…የሚባርኩህን እባርካለሁ የሚረግሙህንም እረግማለሁ የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” ዘፍ12:1 በማለት የጥሪ ድምጹን በሰማው ጊዜ አብርሃም ለፈጣሪው ታማኝ ሰው በመሆኑ ሳይጠራጠርና ሣያመነታ ከሀገሩና ከቤተሰቡ (ከዘመዶቹ) ይልቅ የጠራውን አምላክ አምኖ በመቀበል እግዚአብሔር ወደመረጠለትና ወደ አዘጋጀለት ምድር (ወደ ምድረ ከነአን) ሊሄድ ችሏል።

አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብሎ ወደተዘጋጀለት ምድር ካቀና በኋላ እምነቱ ፍጹም ስለነበረ መላ ሕይወቱ የሚመራው በእግዚአብሔር ቸርነት ነበረ። በቅዱሳት መጽሐፍት ታሪክ ውስጥ አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። ዘርህን እነደ ሰማይ ከዋክብት እነደ ምድር አሸዋ አበዛለው ተብሎ እነደ አብርሃም የተባረከ ከቶ ማንም አልነበረም። ከዚህ የተነሳ አባታችን አብርሃም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ቋሚ ሃብትና ንብረት ከማካበት ይልቅ በተመሣቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ተክሎ ዕለት ዕለት የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን እንግድነት እየተቀበለ የሚኖር ሆነ። በዚህ የተቀደሰው ሥራው አብርሃም በፈጣሪው ዘንድ ትልቅ ሞገስና ክብርን አገኘና ፀጋው እየበዛ እንደሆነ ያወቀው ጥንተ ጠላት ሰይጣን በምቀኝነት ተነሣስቶ በምትሃት ራሱን በድንጋይ ገምሶ ደሙን በማፍሰስ አጥንቱ ተከስክሶ የተጎዳ ሰው በማስመሰል በትልቅ ጎዳና ላይ ተጠምጦ ወደ አብርሃም ቤት የሚመጡትን እንግዶች ወዴት ትሄዳላችሁ በሚላቸው ጊዜ ርቦን ሊያበላን ጠምቶን ሊያጠጣን ከአብርሃም ዘንድ እንሄዳለን ሲሉት የወትሮው አብርሃም መሰላችሁ እንዴ እኔም እንደናንተ ያበላኝ ያጠጣኛል ብዬ ብሄድበት ራሴን ገምሶ አጥንቴን ከስክሶ ሰደደኝ ሲላቸው እነሱም እያዘኑ የሚመለሱ ሁነዋል። አብርሃምም ወደ ቤቱ የሚመጣ እንግዳ በመጥፋቱ ያለ አንዳች እንግዳ ምግብ የማይቆርስ መፍቀሬ እንግዳ ስለነበረ በፍጹም ልቡ እያዘነ እስከ 3 ቀን ያለ እንግዳ ግብር አላገባም (ምግብ አልበላም) ብሎ ሣይመገብ ቆይቷል።

በ3ኛው ቀን ግን ቀትር ላይ ከድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሣለ ስላሴ በታላላቅ ሽማግሌዎች ምሳሌ ሆነው በመምሬ አድባር ዛፍ ሥር ተቀምጠው ታዩት። አብርሃምም እነዚህን አረጋውያን ሽማግሌዎች የሚመስሉ እንግዶች በማየቱ ደስ ብሎት ወደ እነሱ ገስግሶ በመሄድ “ጌቶቼ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እረፉ አላቸው” በጣም የደከማቸው መንገደኞች ይመስሉ ስለነበር ደክሞናል ሲሉት አንዱን አዝሎ ወደ ቤቱ ሲገባ ሁለቱ በግብር  አምላካዊ ቀድመው በቤቱ ውስጥ ተገኝተዋል። አብርሃምና ሣራም ለተከበረ እንግዳ መቅረብ የሚገባው የመስተንግዶ ዝግጅት በማድረግ የፍጥረት ሁሉ ባለቤት ስላሴን በቤታቸው አስተናግደዋል። ወደ ወዳጃቸው ወደ አብርሃም ቤት በዕንግድነት የገቡት ሰለስቱ ስላሴም የእጃቸው ፍጥረት ከሆነው ከአብርሃም እና ከሣራ እጅ የቀረበላቸውን መስተንግዶ (ምግበ ሥጋ) እንደበሉ እንደጠጡ ሁነው ለአብርሃም ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።

ስላሴ ምግብ በሉ ማለት እሳት ቅቤን በላ እነደማለት ስለሚቆጠር የአብርሃምን በጎ ስራ በስላሴ ዘንድ የተወደደ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። አብርሃም ፈጣሪውን በእንግድነት የተቀበለ ብቸኛ ሰው ነው። ለመስተንግዶ የታረደው ወይፈንም ተነሥቶ ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና እንደሚገባ መስክሯል። በቤቱ የተገኙት ሦስቱ ስላሴም ለአብርሃም የአንድነትን ነገር ሲገልጹለት “የዛሬ ዓመት እነደዛሬው ወደ አንተ በእውነት እመለሣለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ” (ዘፍ 18:10) የሚለው አገላለጽ የአንድነትን ሚስጥር ያመለክታል። በዚህ መሠረት አብርሃም የስላሴን አንድነትና ሦስትነት (ምስጢረ ስላሴን) የማወቅ ምስጢር ተገልጾለታል። ልጅ በማጣት አዝነው የነበሩትን በእርጅና ዘመናቸው በልጅ ተባርከዋል። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለመኖሩንም አረጋግጠዋል። የወደፊት ተስፋቸውን ከነገራቸው በኋላ በሰዶምና በጎመራ ስለሚሆነው የእግዚአብሔር ቁጣ እና የሰዎች ጥፋት እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጁ ለአብርሃም ሣይደብቅ በግልጽ ተናግሮታል። አባታችን አብርሃም የአማላጅነት ጥያቄ አቅርቦ እግዚአብሔር አምላክም ስለወዳጁ አብርሃም ጥቂት ደጋግ ሰዎች እንኳ ቢኖሩ እንደሚምርለት ቃል እንደገባለት እንመለከታለን። (ኦሪት ዘፍ18) ባጠቃላይ ሐምሌ ስላሴ የምናከብረው በዓል ከላይ የገለጽነውንና ሌሎችን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንዘክርበት ታላቅ በዓል ነው።

የቅድስት ሥላሴ ቸርነት እና ምህረት በሁላችን ላይ ይደርብን።

ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደኋላቸውም ይመለሱ” መዝ 123(129)፥5

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም የሚተላለፈውን ኦርቶዶክሳዊ ተከታታይ የሃይማኖትና ክርስቲያናዊ የስነ ምግባር ትምህርት የምትከታተሉ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሁላችሁም፤ እግዚአብሔር አምላክ እንኳንስ ህዳር 21 ቀን በታላቅ ድምቀት ለሚከበረው አማናዊት ጽዮን ለተባለችው ለቅድስት ድንግል ማርያም አደረሳችሁ፥ አደረሰን።

ከዚህ ቀጥለን በዚህ እለት ስለምናከብረው የጽዮን በዓል በማስመልከት አጠር አድርገን እንናገራለን። እንደሚታወቀው ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተከርስቲያናችን በየአመቱ ህዳር 21 ቀን በእመቤታችን በድንግል ማርያም ሰም በተሰየሙት አብያተክርስቲያናት የፅዮንን በአል በታላቅ ክብርና በታለቅ ድምቀት ታከብራለች። የታሪኩ መነሻ ሊቀ ነብያት ሙሴ በደብረ ሲና 40 ቀን ከፆመ በኋላ አስርቱን ቃላት የተረከበበትን ወይም ታቦተ ጽዮንን ከእግዚአብሔር እጅ እንደተቀበለ ቅዱስ መፅሐፍ የመሰክራል። ታቦተ ጽዮን የሚባልበት ዋናው ምክንያትም ጽዮን በመባል የምትጠራው የንጉስ ዳዊት ከተማ ወደሆነችው ተራራ የእግዚአብሔር ታቦት ከገባበት ቦታ ጀምሮ ታቦተ ጽዮን እየተባለች መጠራት እንደጀመረች ታሪኩ ያስረዳል።

ጽዮን የተባለችው የታላቁ የንጉስ ዳዊት ከተማ ከፍተኛ ግፍ የደረሰባቸው እስራኤላዊያን ሁሉ እውነተኛውን ፍትሃዊ ፍርድ ለማግኘት ከየአቅጣጫው ተሰብስበው የሚማፀኑባት ከተማ ነበረች። ታቦተ ፅዮንን / ጽላተ ሙሴን በዚሁ በዳዊት ከተማ ስለነበረች በርሷ ተማፅነው ችግራቸውን ሁሉ አስረድተው ከደረሰባቸውና ከወደቀባቸው ከባድ ፈተናና አሰቃቂ ነገር ሁሉ ለመሰወርም እንዲሁም ከጠላት ተደብቆና እሩጦ ለማምለጥ ይቺ ጽዮን የተባለችው የእግዚአብሔር ታቦት የሚገኝባት ከተማ መሰወርያና መጠጊያ ስለሆነቻቸው ይህንን ለማመልከት “ታቦተ ጽዮን” ተብላ ለመጠራት አስችሏል። ከዚህ በኋላም የታቦተ ጽዮን ህዳር 21 ቀን የሚከበርበት ዋናው ታሪክ በዘመነ መሳፍንት ሊቀካህናት መስፍንና ሊቀካህናት የነበረው የኤሊ ልጆች በእግዚአብሔር ቤት በሰሩት የኅጢአት ድፍረት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ስለነበረ በነሱ ኅጢአት ምክንያት ታቦተ ጽዮንንና ህዝቡ እንዲማረኩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል። የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉት በአባታቸው እግር ተተክተው የክህነቱን ስራ እያከናወኑ ባሉበት ሰዓት በእግዚአብሔር ፊት እና በህዝቡ ፊት እጅግ አፀያፊ ስራን ይሰሩ ነበር። ከነዚህም 3ቱ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ፦

1ኛ/ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ከመሰዋዕታቸው በፊት ለራሳቸው የሚያስፈልጋቸውንና የተከለከለውን የመስዋዕት አይነት ይወስዱ ነበር፣

2ኛ/ ከማታ እስከጠዋት ድረስ በእግዚአብሔር ቤት እንዳይጠፋ ህግ ሆኖ የተደነገገውን የቤተመቅደሱን መብራት እንዲጠፋ ያደርጉ ነበር፣

3ኛ/ የእግዚአብሔር ታቦት ባለበትና ህዝቡ ለእግዚአብሔር አምልኮት በሚቀናበት በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሴቶችን ያስነውሩ ነበር።

በነዚህ 3 ዋና ዋና ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሊቀካህኑ ኤሊ ደርሶ እንዲህ ሲል ተናገረው “ሰው ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል ስለርሱ የሚማልድ ማን ነው”  በማለት የኤሊ ልጆች የተባሉት ከሰው ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆኑ አስታራቂ ሽማግሌ የሌላቸው እንደሆነ በመግለፅ ተነግሮታል። ሊቀ ካህኑ ኤሊም ከእግዚአብሔር ይልቅ በልጆቹ በመስማማት የሚሰሩትን እያየ ዝም ስላለ በነሱ ምክንያት ህዝቡንም፣  እሱንም፣ ልጆቹንም እንደሚቀጣቸው ነግሮታል፤ (1ኛ ሳሙ 2፥25)

እንዲሁም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ያከበሩኝን አከብራቸዋለሁ የናቁኝም ይናቃሉና … ይህ በሁለቱ ልጆችህ አፍኒን እና ፊንሐስ ላይ የሚመጣ ላንተ መልክት ነው። ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ የታመነን ካህን ለእኔ አስነሳለሁ” ብሎት ነበር። እግዚአብሔር ስለሚያደርገው ነገር ሁሉ ለኤሊ ገልጾለት፤ ከዚህ በኋላ ግን እግዘኢአብሔር የተናገረውን የማይረሳና ያሰበውን የማያስቀር አምላክ ስለሆነ በቤተ እግዚአብሔር የኤሊ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በሰሩት ነውርና የግል ኅጢአታቸው ታቦተ ፅዮንን እና ህዝቡን ለአህዛብ ተላልፈው እንዲሰጡ ምክንያት ሆኑ። ብዙ ጊዜ እስራኤል ለእግዚአብሔር የበኩር ልጆች እንደመሆናቸው መጠን እግዚአብሔርም ለህዝቡ እለት እለት የሚያስብ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እያሟላ እና እየመገበ እየተንከባከበ የሚጠብቅና የሚመራ አምላክ ስለሆነ ይህን ሁሉ ታላቅ የእግዚአብሔር ውለታ ዘንግተው አታድርጉ የተባሉትን በማድረግ አትፈጽሙ የተባሉትን ሲፈፅሙ በታዩ ጊዜ እግዚአብሔር ወዲያውኑ የአባትነት ቅጣቱን ያመጣባቸዋል። ለዚህም ነው ካህኑ ኤሊ ገና በእንጭጩ (በእንቁላሉ) ልጆቹን ሳይመክርና ሳይገስፃቸው በመቅረቱ ለደረቁ የነደደው እሳት እርጥቡን እንደሚለበልብ ሁሉ በነሱ ኅጢአት የመጣው ቅጣት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦትና እስራኤላውያን ሃይማኖት በሌላቸው በፍልስጤማውያን እንደሚማረኩና አልፈው እንዲሰጡ እግዘኢዘብሔርም አለ። ፍልስጤማውያን እጅግ የሚፈሯቸውን እና የሚንቀጠቀጡላቸውን እስራኤል ዘስጋን የድፍረት ሃይል ተሰጥቷቸው በፊታቸው ሊፋለሟቸው ጦርነት ገጠሙ። በመጀመሪያው  የጦርነት ውግያ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጥፋት ስለደረሰባቸው እንደገናም ሃይላቸውን አጠናቀው ከመከራ የምታድናቸውን ታቦተ ፅዮንን ይዘው የኤሊ ልጆችም ታቦትን አጅበው ከህዝብ ጋር ወጡ። ፍልስጤማውያን ጦርነት ለመግጠም ዘመቱ። አሁንም የእግዚአብሔር ቃል አልበረደም ነበርና ፍልስጤማዊያኑ ጋር ሲዋጉ ሰልፍ ባደረጉ ጊዜ በጦርነቱ ከእስራኤል 4000 ያህል ሰዎች ሞቱ (1ኛ ሳሙ 4፥2፣10 እና 11 ) በ2ኛም ጊዜ የእስራኤል ዘንድ 30000 ያህል እግረኞች ተገደሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች ፤ ሁለቱም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም በጦርነቱ ሞቱ።

ፍልስጤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ከማረኩ በኋላ በአቤኔዜር ወደ አዛጦን ወደተባለው ቦታ ይዘውት ከመጡ በኋላ የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ዳጎን የተባለው የጣኦት ቤት ውስጥ አስቀመጡት ። የእግዚአብሔር ታቦት የእግዚአብሔር ኃይል ያለበት ስለሆነ ፍልስጤማውያን የሚንበረከኩለትን ዳጎን የተባለው ጣኦት በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ተደፍቶ በታቦቱ ኃይል ተሰባብሮ እጅና እግሩ ራስና አንገቱ ሁሉም አካሉ ተቀጥቅጦ አመድ ሆኖ የዳጎን ካህናትም ወደ ዳጎን የሚገቡትን ሁሉ በአዛጦንን ያለው የዳጎንን መድረክ እስከዛሬ ድረስ አይረግጡም በማለት መስክረዋል (1ኛ ሳሙ 15፥5)

ታቦተ ጽዮን በፍልስጤማውያን ዘንድ ያደረገው ኃይል፦

1ኛ/ በአዞጦን ከተማ በነበረበት ጊዜ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በእባጭ በሽታ በመምታት ሃይሉን ስላሳያቸው ከከተማቸውና ከሀገራቸው እንዲሄድላቸው መክረው የእግዚአብሔር አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ። ወደ ስፍራውም ይመለስ አሉ። ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ የተመቱ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ። (1ኛ ሳሙ 5፥6-12) በደረሰባቸው የመቅሰፍት እባጭ ምክንያት ብዙ ሰዎች በሞት ስለተቀጡ መቅሰፍቱም እጅግ ከባድ ስለነበር በታላቅ ጩህት እና ለቅሶ የቃልኪዳኑ ታቦት የእግዚአብሔር ኃይል እንዳለበት እየመሰከሩ ወደሌላ አገር እንዲሄድላቸው በጠየቁት መሰረት ታቦቱ ከከተማ ሲወጣ መቅሰፍቱም ከነሱ እንዲወጣ ለታቦቱ የሚገባውን እጅ መንሻ ወይም አመሀ ማድረግ እንዳለባቸው በአዋቂ ሰዎች ስለተመከሩ በአገራቸው ላይና በህዝቡ ላይ ተሰዶባቸው የነበረ የእባጭ በሽታ ምሳሌ የሚሆን በ5ቱ የፍልስጤማውያን ከተሞች ቁጥር 5 የወርቅ እባጮች እንዲሁም በአገራቸው የተላከው ሁለተኛ መቅሰፍት የአይጥ መንጋ ስለነበር 5 የወርቅ አይጦች በምስል አድርገው ሁለት የሚያጠቡ ላሞችን በሰረገላ ጠምደው ታቦታቱን እና ያዘጋጁትን የወርቅ ስጦታ በሳጥን አድርገው በታላቅ ክብር ታቦቱ ወደሚሄድበት ቦታ ሸኝተዋል። ከዚህ በኋላም ያ መቅሰፍትና ደዌ ከነሱ ወጥቷል። ታቦቱም ከፍልስጤማውያን ከተማ በተነሳው ሰረገላ ላይ ሁኖ ወደ ቤትሳሚስ ጉዞውን አቀና (1ኛ ሳሙ 6፥9) በዚያም በቤት ሳሚሳዊው ወደ እያሱ እርሻ በደረሰ ጊዜ ታላቁን ድንጋይ በዚያ አቁመው የሰረገላውን እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መስዋእት አቀረቡ። የእግዚአብሔር ታቦትና የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሳጥን አውርደው በታላቁ ድንጋይ ላይ በክብር አስቀመጡት (1ኛ ሳሙ 6፥10-16)

በዚህ አይነት አኳኋን ከፍልስጤማውያን እጅ የተመለሰው ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ልዩ ልዩ ተዓምራት እያደረገ እግዚአብሔር በፈቀደላት በድንኳን እየኖረ በንጉሱ ዳዊት ዘመን ንግስና ደርሷል። ነብየ ንጉስ ዳዊት ግን ለታቦቱ ከነበረው ታላቅ ፍቅር የተነሳ በታቦቱ ፊት መስዋዕት በታላቅ ዝማሬና እልልታ በታቦቱ ፊት እየሰገደና እያሸበሸበ ለታቦቱ ወዳዘጋጀው ጽዮን ወደተባለችው ከተማ አስገብቷል። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ከመግቢያችን እንደገለፅነው ታቦተ ጽዮን እየተባለ በዚህ ስያሜ መጠራት ተጀምሯል።

እንግዲህ የታቦተ ጽዮን ታሪክ ባጭሩ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህዳር 21 ቀን ታቦተ ጽዮንን በዓል ከምታከብርበት ምክንያት ዋናዎቹ፦-

1ኛ/ በፍልስጤማውያን ዘንድ የተደረገው የእግዚአብሔርን ኃይል በመዘከር ሲሆን ፣

2ኛ/ ታቦተ ጽዮን ከቅድመ ልደት ክርስቶስ በ 1000 አመተ ዓለም ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ በንግስት ሳባ አማካኝነት ወይም በቀዳማዊ ሚኒሊክ መሪነት የመጣችበትን በማሰብ ነው።

ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ ያረፈችው በአገራችን በአክሱም ምድር ስለሆነ ዛሬም ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች አክሱም ጽዮን እየሄዱ የሚማፀኑትና የሚንበረከኩት ለዚህ ነው። ታቦተ ፅዮን በንጉሱ ሰለሞን መልካም ፈቃድ ለንግስት ሳባ (ማክዳ/ ንግስት አዜብ) በተሰጠ ጊዜ ከነካህናቱና ከነንዋየ ቅዱሳቱ ከነመፅሐፍቱ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ አገራችን ከክርስቶስ ልደት በፊት ለ1000 ዘመናት የኦሪትን መስዋዕት እየሰዋች አምልኮት ስትፈፅም ኖራለች የምንለው።

ታቦቱ የእግዚአብሔር ማደርያ እና የኃይሉ መገለጫ ስለሆነ ዛሬም የእግዚአብሔር ታቦት በስሙ ለተማፀኑት ሁሉ ኃይሉን ያሳያል። የእግዚአብሔር ታቦት በአዲስ ኪዳን እንዳልተሻረና እንዲያውም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት የሚሰዋበት መሆኑን ፍቁረ እግዚ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተች በውስጧም ያለችው ታቦተ ህግ ታየች” በማለት መስክሯል። (ዮሐ ራዕ 11፥19)

ስለዚህ በዋናነት የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዛሬው እለት የምናከብራት አማናዊት ፅዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ ወይም የመንፈስ ቅዱስ ታቦት የሆነችው ማህደረ መለኮት ድንግል ማርያም ናት። በብዙ የመፅሐፍ ቅዱስ ጽዮን ጽዮን የሚሉት ቃላቶች ፍፃሜው ለአማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም የተነገሩ እንደሆነ በውስጣቸው ያሉ የምስጢር ትርጓሜ ያመለክታል። ለምሳሌ ነብየ እግዚአብሔር ዳዊት “ሰው ሁሉ ጽዮንን እናታችን ነሽ ይሏታል፤ በውስጧ ሰው ተወልዷልና” መዝ 85 (86)፤5

እንዲሁም “እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታል ማደርያውም ትሆን ዘንድ ወዷታል እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚች አድራለሁ።” (መዝ132፥13)  በማለት ጽዮን የሚለው ቃል አማናዊ ለሆነችው ለአምላክ እናት ለድንግል ማርያም የተነገረላት መሆኑን የጥቅሶቹ ምስጢር ያመለክታል። ምክንያቱም በውስጧ ሰው ተወልዷል ሲል መድኅንያለም ክርስቶስ ከእርሷ መወለዱን የሚያመለክት ሲሆን፤ ማደርያውም ትሆን ዘንድ መርጧታል ሲል የሱ ማደርያና ከእንስት አለም ሁሉ ለይቶ ለእናትነት የመረጣት መሆኑን ለዘላዓለምም ማህደረ መለኮት ስትባል መኖሯን የሚያመለክት ቃል ነው።

ነብየ እግዚአብሔር ኢሳያስም ስለዋ ትውልድ ሁሉ እንደሚንበረከክ አማናዊ ጽዮን እያሉ እንደሚሰግዱላት በትንቢቱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደአንቺ ይመጣሉ የናቁሽም ሁሉ ከእግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፥ የእስራኤል ቅድስት የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።” (ኢሳ 60፥14)

 

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም “እነሆም ከዛሬ ጀምሮ የሰው ልጅ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል፥ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ስራ አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው።” ብፅኢት፣ ቅድስት፣ ንጽሂት፣ ድንግል በማለት ትውልድ ሁሉ እንደሚያመሰግኗት በራሷ አንደበት የተናገረችውን ምስክርነት ነግሮናል። (ሉቃ 1፥48)

በአጠቃላይ፥ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላቶቻችን እግዚአብሔር ከዚህ ጭንቅ ዘመን ሰውሮን ለዛሬው ለእመቤታችን ለወላዲተ አምላክ ለጽዮን በዓል ስላደረሰን በረከት ለመካፈል ይችን አጭር ትምህርታዊ መልዕክት እንዲደርሳችሁ ስናደርግ እናንተም በያላችሁበት ቦታ ሆናችሁ ለእናታችሁ ለድንግል ማርያም የሚገባትን ክብር በአማላጅነትዋ በአስታራቂነትዋ በመተማመን የምትችሉትን ሁሉ በጎ ስራ ልታደርጉና፤ እርስ በእርሳችሁም በፍቅር ለመኖር፣ ለመረዳዳት፣ ለመተጋገዝ ፣ ተባብሮ ለመኖር ህሊናችሁን ሁሉ እንድታዘጋጁት በስራም እንድትገልፁት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።

ለሁሉም ነገር የእመቤታችን አማላችነትዋና የእናትነትዋ ፍቅር በሁላችንም ላይ አድሮ ይኑር ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ኪዳነ ምሕረት
 
ኪዳነ ምሕረት የሚለውን ቃል ከማየታችን በፊት ስለ ቃል ኪዳን እንመልከት :
 
ቃል ኪዳን፦ ተካየደ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መሐላ ፣ስምምነት ፣ቃልኪዳን መግባትን ፣ በቃል መጽናናትን ያመለክታል።
 
ስለ ቃል ኪዳን ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል :- 
 
ነብዩ ዳዊት መዝሙሩ “ከመረጥኩት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ ” (መዝ 88፥3)
 
ነብየ እግዚአብሔር ኤርምያስም በትንቢቱ ስለ ሐዲስ ኪዳን ቃል እግዚአብሔር አምላክ ከህዝቡ ጋር ስለሚያደርገው የሐዲስ ቃል ኪዳን ውል ሲናገር “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል እግዚአብሔር … ከነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል እግዚአብሔር፥ ሕጌን በልቦናቸው አኖራለው በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነሱም ህዝብ ይሆኑኛል።” በማለት እረፍተ ዘመን ስለማይገድበው ዘላለማዊ ስለሆነው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕግ ተናግሯል፡(ኤርያቱ31፥3)
 
ነብዩ ሙሴም በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ “እግዚአብሔር በከሬብ ባደረገው ቃል ኪዳን ሌላ በሞአብ ምድር ከእስራኤል ልጆች ጋር ያደርገው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው የቃል ኪዳን ቃሎች እነዚህ ናቸው” በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለቃል ኪዳን ከመረጣቸው ከእስራኤል በሥጋ ጋር በየጊዜው ስለ አደረገው ቃል ኪዳን ተናግሯል :: ( ዘግ29፥13)
 
ቃል ኪዳን ሁለትና ከዚያም በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአንድ የጋራ አላማ ላይ ተነጋግረው የጋራ ስምምነት ላይ ሲደርሱ የስምምነቱ ቃል የሚጸናበት ሰነድ ወይም ምልክት ቃል ኪዳን ይባላል።
 
በሚታየው በዚህ አለም እና በማይታየው ዓለም ውስጥ ተፈጥረው የሚኖሩት ስነፍጥረታት ሁሉ በተገኙበት የሕግ ተፈጥሮ ባሕሪያቸው በየነገዳቸው ፀንተው (ተወስነው) የሚኖሩት እና የሚተዳደሩበት መሰረታዊ ሕጋቸው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው የቃል ኪዳን ስርዓት ነው ::
 
በማንኛውም የቃል ኪዳን ስርዓት ውስጥ : 
– ቃል ኪዳን ሰጪው ፣ 
– ቃል ኪዳን ተቀባዩ፣ እና
 -የቃል ኪዳን የስምምነት ውል (ምልክት) መኖር የግድ ነው፡፡ 
 
ይህ ማለት በዓለማችን ያለውን ቃል ኪዳን ወደ ጐን ትተነው ስለእውነተኛው እና ስለማይሻረው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስንናገር :-
 
– ቃል ኪዳን ሰጭ የፍጥረት ሁሉ ባለቤት የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ነው ::
 
-ቃል ኪዳን ተቀባይ የተባለው በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር የመረጣቸውና ያከበራቸው ቅዱሳን እና በሃይማኖት የሚኖሩ የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ናቸው። 
 
– የቃል ኪዳኑ ሥርዓት (ምልክት) የተባለውም በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን የሕጉ መፅሐፍ ላይ በእግዚአብሔር እና በህዝቦቹ መካከል የተገቡት የቃል ኪዳኑ ምልክቶች በተለይ በሐዲን ኪዳን የቃል ኪዳኑ ምልክት (ውል)፦ 
 
-በ40 እና በ80 ቀን ዳግም የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የታታምንበት ጥምቀተ ክርስትናችን ፣ 
 
– የኀጢአት ስርየት የምናገኝበት ዘለዓለማዊውንና ሰማያዊውን የእግዚአብሔር መንግስት ለወረስ የምንበቃበት የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ (ቅዱስ ቁርባን ) ፣ 
 
-በሐዲስ ኪዳን ዘመን ስለ እኛ ብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞት ዋጋ በከፈለልን በክርስቶስ ቃል ኪዳን ፀንተው የሚኖሩ የእግዚኣብሔር ልጆች ሕገ ወንጌል እና ሌሎችም በፈጣሪ እና በሰው ልጅ መካከል ያለው ቃል ኪዳን እንዳይፈርስ እና እንዳይረሳ በየጊዜው የሚያፀኑን እና የሚያበረቱን ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የቃል ኪዳኑ ታቦት፣ ቅዱስ መስቀሉ፣ ቅዱስ ፀበሉ፣ እምነቱ፣ ጾሙ፣ ፀሎቱ፣ ስግደቱ፣ ምጽዋቱ፣ የንስኅ ህይወቱ እና የመሳሰሉት ናቸው ::
 
ከዚህ በላይ ስለቃል ኪዳን በሚመለከት ጠቅለል አድርጎን አጭር ትንታኔ መስጠት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በዮሐንስ ንስኀ ድረገፃችን የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከታተሉ አባላቶቻችን በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና በዓለማችን እንደፈለግን እንደምናፈርሰውና እንደምንሽረው ሥጋዊ ቃል ኪዳን እንዳልሆነ ለማስረዳት ነው፡፡
 
ከዚህ በመቀጠል የምናየው ለትምህርታችን የመግቢያ ርዕሰ አድርገን የመረጥነው “ኪዳነ ምሕረት” የሚለው ቃል ይሆናል :: ኪዳነ ምሕረት የሚለው ቃል ምሕረት መስጠት የባሕርዮ የሆነው ልጇ የዓለም መድኃኒት እየሱስ ክርስቶስ ለእናቱ ለድንግል ማርያም የገባላትን የአማላጅነት ቃል ኪዳን ይመላከታል ::
 
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ የምህረትና የቸርነት አምላክ ከሆነው ከልጇ ከወዳጅዋ ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በየወሩ ወር በገባ 16ኛ ቀን የሚከበረው ወርሐዊ እና አመታዊ በዓል ኪዳነ ምሕረት በሚል ስያሜ ይጠራል። ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእሷ አማላጅነት እና ወላዲተ እምላክ መሆንዋን አምነው በሰሟ ለሚማፀኑ ሁሉ ከልጇ ዘንድ ምህረትን እንደምታሰጥ የተገባላትን ቃል ኪዳን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መሰረታዊ አገልግሎት ታከብራለች። በተለይም በየዓመቱ የካቲት 16 ቀን ” ኪዳነ ምህረት” እያልን የምናከብረው በዓል የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በመካነ ጎለጎታ በልጇ መቃብር ላይ ሁና ”ልጄ ወዳጄ ሆይ፥ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመሆንህ ፣ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማሕፀኔ፣ ከአንተ ጋር በአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ስለመሰደዴ ስለአጠቡህ ጡቶቼ፣ ስለ አቀፉህ እጆቴ፣ ብለህ በዚህ ቅዱስ ስጋህ ባረፈበት ቦታ ላይ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ “እያለች ስትፀልይ ጌታ እልፍ አእላፉት መላዕክቱን አስከትሎ ወደ እናቱ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም መጥቶ የሰላምታ ቃል ካቀረበላት በኋላ፤ እንዳደርግልሽ የምትለምኝኝ ምንድነው በማለት የእናቱን የአማላጅነት ቃል ተቀብሎ ይፈፀምላት ዘንድ ፈቃዱ መሆኑን በቃሉ አረጋገጠላት::
 
እመቤታችን ድንግል ማርያምም ወደ ልጇ ያቀረበቸው ልመና ለራስዋ ተድላ እና ደስታ ፈልጋ ሳይሆን በዚህ አለም የጥፋት እና የክህደት መረቡን ዘርግቶ ብዙዎቹን የሚያሰናክላቸው የሀሰት አባት ዲያብሎስ በልዩ ልዩ ወጥመድ ውስጥ የወደቁትን ወገኖቿን እንዲምርላት እና ሃጥያታቸውን ይቅር እንዲልላት ያቀረበችው ልመና እና የአማላጅነት ጥያቄ ነው :: በእመቤታችን አማላጅነት ምህረት ያገኙ ዘንድ በስምዋ የሚማፀኑ እና መታሰብያዋን የሚያደርጉ፣ ለችግረኞች የሚራሩትን፣ ቤተክርስቲያን የሚያንጹትን፣ አምሀ (መብአ) ለቤተ እግዚአብሔር የሚሰጡትን፣ እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ ልጆቻቸውን በስምዋ የሰየሙትን ሁሉ ክኖተ ነፍስ ክኖተ ሥጋ እንዲማሩላት (እንዲያድንላት) ያቀረበችውን ልመና እንዲፈፀምላት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በራሱ፣ በባሕሪይ አባቱ በአብ እና በባሕሪይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ምሎ ቃል ኪዳን ገብቶላታል።
 
ቅዱስ ዘርዓያቆብ በራሱ ስም ባቀረበው የቅዳሴው ምስጋና “ዳግመኛ በእናትህ በማርያም ተማፅነናል ይኸውም አንተን በመውለድ እመቤታችን የባህሪያችን መመኪያ ናት : አንተ መታሰቢያሽን ያደረገ ስምሽንም የጠራ የዘለዓለም ድህነትን ይድናል ብለሀታልና።” በማለት ስለተሰጣት ቃል ኪዳን ለብዙዎች ምህረት የማሰጠትዋ የእናትነት ፀጋ ዘመን የማይሽረው እና ግዜ የማይገድበው ነው :: 
 
ከሴቶች ሁሉ ተለይታ እሷ ብርክት እና ቅድስት እንደሆነች እና የጌታ እናቱ ትሆን ዘንድ አለም ሳይፈጠር ጀምሮ በአምላክ ልቦና ታስባ የቆየች ማህደረ መለኮት ስለሆነች እሱን ከመውለድዋ በፊት ቅዱሳን ነብያት ስለ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋ፣ ስለ አማላጅነትዋ፣ስለመመኪያነትዋ በትንቢታቸው ተናግረዋል።
 
ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ እሷ የተነገሩትን ጥቂቶቹን እንመልከት:-
 
1. በበአንተ እና በሴቲቱ መካከል ፥ በዘርህ እና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ ፤ እሱ እራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣላህ በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለአባታችን አዳም በተናገረው ቃል በሴቲቱ መካከል ተብሎ የተገለፀው ስለ ድንግል ማርያም እንደሆነ እንረዳለን :: (ዘፍ 3፥15)
 
ይቀጥላል …

በዓታ ለቅድስት ድንግል ማርያም

ዛሬ ታሀሳስ 3 ቀን በየአመቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ የገባችበትን እለት በማሰብ የሚከበር በአል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 5485 አመተ አለም ገደማ ከእናትዋ ከቅድስት ሀና እና ከአባትዋ ከቅዱስ እያቄም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች። የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናትዋ እና አባትዋ በስእለት ያገኟት ልጃቸው ስለነበረች ለእግዚአብሔር አገልጋይ እንድትሆን በተወለደች በ 3 አመትዋ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወስደው በሊቀካህናቱ አማካኝነት መባ አድርገው ባቀረቧት ጊዜ ወላጆቿም ዘንድ ሆነ በእግዚአብሔር ቤት በአገልግሎት ላይ ላሉት በቤተመቅደሱ ካህናት ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄ ፈጥሯል። ይሁን እንጂ የእመቤታችን መወለድዋም ሆነ በ3 አመትዋ ወደ ቤተመቅደስ የመምጣትዋ ሁኔታ የሰው ሀሳብ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበረው ወላጆችዋ ወደ ቤተመቅደስ አምጥተው ለሊቀ ካህናቱ ሊያስረክቧት በተዘጋጁ ጊዜ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ የሆነው መልአከ ቅዱስ ፋኑኤል ከመላዕክት ማህበር ወደ እመቤታችን እና ወላጆችዋ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሰዎች በተገኙባት የቤተመቅደሱ ዙሪያ በሰው አምሳል ተገልፆ ሰማያዊ ህብስትና ሰማያዊ ፅዋ ይዞ በተገለፀላቸው ጊዜ በመልአኩ እጅ ያለውን በረከት ለመቀበል የቤተእግዚአብሄሩ አገልጋዮች ካህናት ሙከራ ቢያደርጉም መልአኩ የመጣበት ዋና አላማ ለብዙዎቹ ያልተረዳቸው ምስጢር ስለሆነ ያመጣውን በረከት ይዞ ከነሱ ተለይቶ በመራቅ ላይ እንዳለ እመቤታችን ድንግል ከናትዋ እቅፍ ወርዳ በቅድስናው አደባባይ ላይ እንደ ህፃናት ድክ ድክ በማለት ባለችበት ሰአት መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል አንድ ክንፉን ምንጣፍ አንድ ክንፉን መጋረጃ አድርጎ ሰማያዊ ብስቱን መግቧት እና ሰማያዊ ፅዋውን አጠጥቷት የተላከበትን መንፈሳዊ መልዕክቱን ከፈፀመ በኋላ ከህዝቡ ተለይቶ ወደ ሰማይ አርጓል። እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የፅንሰትዋም ሆነ የልደትዋ እንዲሁም ወደ ቤተመቅደስ የመግባትዋን ሚስጢር ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ የወደደውና የፈቀደው ኀይል ስለሆነ ነው። 

እመቤታችን ድንግል ማርያም 3 አመት ከእናትና ከአባትዋ ቤት ከቆየች በኋላ ወላጆቿ አስቀድመው ለእግዚአብሔር በገቡት ቃል ኪዳን መሰረት ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወስደዋት መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ሰማያዊ ህብስት እና ፅዋ መግቧት ልብሰ ቅድስና አልብሷት ካረገ በጓላ ወላጆችዋም ሆኑ ሃላፊነት የነበራቸው የቤተእግዚአብሔር አገልጋዮች ባዩት ተአምራዊ ምስጢር እጅግ ተደስተው የምግቧና የልብሷ ነገር ከተያዘላት በቤተመቅደስ እያገለገለች እንድትኖር አስረክበዋት ከሄዱ በጓላ በቤተመቅደሱ ውስጥ የሚያስፈልገውን አገልግሎት እየፈፀመች 12 አመት ቆይታለች። 

ስለ እመቤታችን ወደ ቤተመቅደስ የመግባትዋ ምስጢር በቅዱሳት መፅሐፍት በነገረማርያም በስፋት ተገልፆል። በተለይም ኢትዮጲያዊ ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ በድጓ ድርሰቱ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ ስለመግባትዋ ምስጢርና በቤተመቅደስ 12 ዓመት ስትቆይ በእግዘኢአብሔር በኩል የተሰጣትን የቅድስናና የድንግልና ህይወት በስፋት ተናግሯል። በቤተ መቅደስ በነበራት ቆይታም እለት እለት ቅዱሳን መላእክት በረቀቀ ሚስጢር እንደሚያረጋጓትና እንደሚያፅናኗት ተፅፏል።

ስለዚህ ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም የቅድስናና የድንግልና ህይወት በተለያየ የትምርታችን ክፍል የማትገለፅበት ቦታ ስለሌለ ወደፊትም ስለ ድንግል ማርያም በትምህርታችን ለመግለፅ የምንችልበት ፕሮግራም ስለሚኖረን ነገር ግን ታህሳስ 3 ቀን የሚከበረውን በአልዋን ሁላችንም በያለንበት ሆነን አቅማችን በሚፈቅደው መጠን በረከት ለማግኘት የየራሳችሁን መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከበአሉ በረከት እንድታገኙ ይሄን አጭር መልዕክት ወደናንተ እንዲደርስ አድርገናል።

እመቤታችን ድንግል ማርያም ለዛሬው እለት ወደ ቤተመቅደስ በገባች ጊዜ በመልአኩ በቅዱስ ፋኑኤል እጅግ የሚያስደንቅና ከሰው አይምሮ በላይ የሆነ ተአምር እንደተደረገው ዛሬም በእናታችን ቃልኪዳን እና አማላጅነት በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ከተቃጣው ልዩ ልዩ ፈተናና መቅሰፍት እንድትጠብቀን ሁላችንም በእምነት ሆነን በእናትነት ፍቅርዋ እንማፀናታለን፤ ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን

የመስቀል ደመራ በአል
 
የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሓ ድረገጽ ተከታታይ ሁላችሁም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከሁሉ በማስቀደም የዘመኑ ባለቤት ቸሩ አምላካችን እንደኛ በደል እና ኀጢአት ሳይሆን እንደሱ ቸርነትና ይቅር ባይነት ዘመኑን አሳልፎና ከመከራ ሁሉ ጠብቆ ለዚህ ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለሱ ይሁን። እንኳን ለ2013 የመስቀል ደመራ በአል አደረሳችሁ በማለት ስለ ደመራ በአል አከባበር፣ ሃይማኖታዊ ታሪክ አመጣጡን እና መሰረቱን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት ይህን ትምህርት ወደናንተ እንዲደርስ አድርገናል።
የመስቀል ደመራ በአል ቁጥሩ ከዘጠኙ ንኡሳት የጌታ በዓላት አንዱ ሲሆን የሚከበረው በየአመቱ መስከረም 17 ቀን እና መጋበት 10 ቀን ነው። ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገራዊ እና ሃይማኖታዊ በዓል ሆኖ የሚከበር ነው። በተለይ መስከረም 17 ቀን ከዋዜማው ጀምሮ ስለሚከበረው የደመራ በአል ስለቅዱስ መስቀሉ ክብር በሚያውቁ ክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የእምነት ተከታዮች እና በመንግስት ተቋማትም ደረጃ ልዩ ክብር ተሰጥቶት ሲከበር እስከዛሬ የቆየ በአል ነው፤ በተለይም ከ2 አመት ወዲህ የመስቀል የደመራ በዓል በአለም አቀፍ የብርቅዬ መዝገብ (UNESCO) ተመዝግቦ አለም አቀፍ አድናቆትን እና ዝናን አትርፏል።
የደመራ መስቀል አከባበር ሃይማኖታዊ ታሪካዊ አመጣጥ፦
የንጉስ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት እሌኒ በሮም እና በግሪክ አገሮች ላይ ንጉሰ ነገስት ሆኖ የተሾመው በሃይማኖት አህዛባዊ የነበረው ንጉስ ቁንስጣ የተባለ ታዋቂ ሰው አግብታ የነበረች አይሁዳዊ ሴት ናት። አይሁድ ጌታ የተሰቀለበትን መስቀል ህሙማንን እየፈወሰ፣ አይን እያበራ፣ ለምፅ እያነፃ ፣ ጎባጣ እያቃና ፣ አጋንንትን እያስወጣ በአጠቃላይ ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ይሰራቸው የነበሩትን የተአምራት ስራ በመስቀሉ ሃይል ይሰራ ስለነበር በዚ የመስቀሉ አስደናቂ ተአምራት ብዙ ክርስቲያኖች ከአህዛብም ወገን ከአይሁድም ዘንድ እያመኑ በመስቀሉ ሃይል ምህረት እያገኙ በቁጥራቸው እየበዙ በመምጣታቸው ጌታን ሰቅለው የገደሉት አይሁድ በምቀኝነት ተነሳስተው መስቀሉን ለምልክት ግራ በሚያጋባ ቦታ እና ሰዎች ሁሉ መረጃ እንዳይሰጡ በማድረግ፤ ሁለቱ ወንበዴዎች በግራ እና በቀኝ የተሰቀሉባቸው ሁለቱን መስቀሎች አንዱን ከአንድ ተራራ፣ አንዱን ከሌላ ተራራ አድርገው በመካከል ጌታ የተሰቀለበትን መስቀል ለማሳሳት እና ግራ ለማጋባት በሚያመች ሁኔታ የጌታ መስቀል የተቀበረበትን ቦታ በከፍተኛ ደረጃ እያስተባበሩ በየቀኑ በአካባቢ ያሉ ሰዎች ሁሉ ቆሻሻ እንዲጥሉበት ወይም እንዲደፉበት ይደረግ ስለነበር ከጊዜ በኋላ ቦታው ቀደም ሲል የነበረበትን ቅርፅ አጥቶ ከፍተኛ ተራራ መሆን ችሏል።
ምንም እንኳን መስቀል ለማውጣት የሚያስችል መብትና አቅም ያለው አካል ባይገኝም በትክክል መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቁ በአካባቢው ብዙ ክርስተያኖች እና ተቆርቋሪዎች ይኖሩ ነበር። ከጌታ ልደት በኋላም በ 70 ዘመን በንጉሱ ጥጦስ የወረራ ምክንያት ቅድስት አገር እየሩሳሌምና አካባቢዋ ስለፈራረሰችና በህዝቡ ላይ ከፍተኛ እልቂት በመድረሱ ከጊዜ በኋላ መስቀሉ የተደፈነበት ቦታ የት እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም። በዚህ ምክንያት የተለያዩ የእግዚአብሔር ሰዎች የመስቀሉ መቀበር ቢያሳዝናቸውም ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው ከ30 አመት በላይ በመሬት ተዳፍኖ ቆይቷል። ከዚህ በኋላ ግን በ400 ክፍለ ዘመን (327) ከላይ እንደገለፅነው የንጉስ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ ባለችበት አገር ሆና ይህን ታሪክ ትሰማ ስለነበር መስቀሉን አስቆፍራ ለማስወጣት ከልጇ ከንጉስ ቆስጠንጢኖስ ፈቃድ ተቀብላ ወደ እየሩሳሌም ጉዞዋን አቅንታለች። ምክንያቱም አህዛባዊ ከሆነው ከቁንስጣ የወለደችውን ልጇን ቆስጠንጢኖስን ክርስቲያን እንዲሆንላትና የእግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆንላት እግዚአብሔርን ትለምነውና መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣትም ሁሌ ፈጣሪዋን ትለምነው እንደነበረ የቤተክርስቲያን ታሪክ ይናገራል። ንግስት እሌኒ እየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ አስቀድማ ባጠናችው ታሪክ መሰረት መስቀሉ ይገኝበታል ብላ የምትገምተውን ጉብታ ቦታ ወይም ተራራማውን ቦታ ሁሉ ለማስቆፈር ብትሞክርም ልታገኘው ባለመቻልዋ፤ በአካባቢው የሚኖሩትን አይሁዳውያንም ጠይቃ ለመረዳት ብትሞክርም ስለ ጉዳዩ እውነቱን የሚያውቅ ባለማግኘትዋ በልዩ ፀሎት እግዚአብሄርን መጠየቅ ቀጠለች በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ስለነበረ በዋሻ ውስጥ ተሰውሮ የሚኖር ኪራኮስ የሚባል አንድ አረጋዊ (ሽማግሌ) የንግስቲቱን ድካም ተመልክቶ ስለመስቀሉ ምስጢራዊ ታሪክ ይሰማ ስለነበረ የሚከተለውን ምስጢር ነገራት “አንቺም አትድከሚ ሰውም በከንቱ አታድክሚ ፤ ብዙ እንጨት ሰብስበሽ እንጨቱን በአንድ ቦታ ከምረሽ (ደምረሽ) ብዙ እጣንም ጨምረሽ በእሳት ደመራውን ብታቃጥይው የእጣኑ ጭስ ወደሰማይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ መስቀሉ ባለበት በማረፍ መስቀሉ ያለበትን አቅጣጫ የት ቦታ ላይ እንዳለ ትረጂያለሽ” አላት። እሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። የደመረችውንም ደመራ በከፍተኛ ፀሎትና ምህላ እሳቱ ሲቃጠል ከደመራው የወጣው የእጣኑ ጭስ ወደላይ ወደ ሰማይ ወጣና ቅድመ እግዚአብሔር መሄዱን አመላክቶ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ቦታ ላይ እንደ ከዘራ ተቆልምሞ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በእጅ ጠቁሞ የማሳየት ያህል ለንግስት እሌኒ ቦታውን አረጋግጦላታል። ስለዘህ ጉዳይ ታላቁ ኢትዮጲያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ሲናገር “እጣኑ ወደላይ አመላከተ፤ የእጣኑ ጭስ ደግሞ ወደመሬት ሰገደ ፤ አይሁድ በጎለጎታ የቀበሩት እፀ መስቀል ዛሬ ተገኘ” በሏል።
ንግስት እሌኒ ማስቆፈር የጀመረችው መጋቢት 10 ቀን ነው፤ መስቀሉ የወጣበት ደግሞ መስከረም 17 ቀን ነው ተብሎ በቤተክርሰቲያን ታሪክ ይነገራል። በዚህም ምክንያት መስከረም 16 ቀን በዋዜማው በየአመቱ የደመራ በአል በአደባባይ በከተማም በገጠር አካባቢዎችም ችቦ እየተበራ ይከበራል፣ እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ እየተባለ በባህላዊ ዜማ ይከበራል። ዘመኑ የፅጌ ዘመን ወይም የአደይ በመሆኑ ይሄንን ወቅቱን እና ግዜውን የሚገልፅ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ዝማሬ እንደየአካባቢው ሁኔታ ለደመራ በአል በተጋጀው ቦታ ላይ የአካባቢው ምእመናን በሃይማኖት መሪነት መስቀሉን ይለኩሳሉ። ለመስቀሉ ክብር በየአካባቢው ባህላዊ ሁኔታ በዚሁ ስርዓት ይከናወናል። አንዳንዶች ከሃይማኖታዊ ስርዓት ወጣ ባለ ሁኔታና አላማውን እየለቀቁ የመምጣታቸው ሁኔታ በስፋት ይታያል። ያም ሆነ ይህ የደመራ በአል ወይም የመስቀል በአል በተለይ በአገራችን ዋና መዲና በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ እጅግ አለምን የሚያስደምም ደረጃ በከፍተኛ መንፈሳዊ ተመስጦ በየአመቱ ሲከበር እናያለን። ይህንን በአል ለማክበር ከአለም ዙርያ የሚመጡ ቱሪስቶችም ስፍር ቁጥር የላቸውም። ምንም እንኳን ዛሬም የመስቀሉ ጠላቶች ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በዚሁ የበአሉ ተካፋዮች በመሆን ያሳልፋሉ።
ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሲነሳ፤ በተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ትዝ የሚለን እና የማይረሳን ታላቅ ሚስጢር አለ፤ ይህም በቀራኒዮ አደባባይ ስለኛ በደል የሞት ካሳ ሊከፍል ወይም ስለኛ ቤዛ ሊሆን በመስቀል ላይ የዋለው እና ታላቅ ፍቅሩን የገለፀልን ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህን ታላቅ ምስጢር ዘወትር የሚያስታውሱ ክርስቲያኖች ሁሉ የመስቀሉ ምስጢር ከልባቸው አይጠፋም። ፈጣሪ እግዚአብሔር ለነብዩ ሙሴ ህገ ኦሪትን ሲያስተምረው “ማንም ሰው ለሞት የሚበቃውን ኅጢአት ቢሰራ እንዲሞትም ቢፈረድበት በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።” ዘዳ 21፥22- 23
ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ለሞት በሚያበቃ ወንጀል በእንጨት ተሰቅለው የሞቱ ሰዎች እንደ እርኩስ ነገር ይቆጠሩና ምድርንም ያረክሷታል ተብሎ ይቆጠር እንደነበረ የአለም መድኅኒት እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ለቤዛነትና ለካሳ እራሱ ቅዱስና ብሩክ አድርጎ በሕግ ከእኛ እርግማንን አርቆ ነፃ እንድንወጣ አድርጎናል። ለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተፅፏልና፤ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን።” ገላ 3፥13
ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የአለምን ኅጢአት በመስቀሉ ከማስወገዱም በላይ የተጣሉትን 7ቱን መስፃርራን አስታርቆበታል። ለአህዛብም ሰላሙንና ታላቅ ፍቅሩን ገልፆበታል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግደ አፍርሶ ጥልን ሻረ ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በስርዓቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ “ ኤፌ 2፤14 -17
እግዚአብሔር ሁሉንም ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሁሉ ሰላምን አደረገ” ቆላ 1፤20
እንግዲህ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ብዙዎቹ የመስቀሉ ጠላት ሆነው እናያለን፤ እነዚህ የመስቀሉ ጠላቶች ይመጡ ዘንድ የግድ እንደሆነ ሲናገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ ወንድሞች ሆይ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዙወች የክርስቶስ ጠላት ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ግዜ ስለነሱ እንደምነግራችሁ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ ብዙዎች አሉና አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ በግልፅ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ” ፊልጰ 3፤17
እንግዲህ ክርስቲያኖች ሁላችሁም ስለ ክርስቶስ መስቀል መመስከርና መናገር ክብር ስንጂ ውርደት ስላለሆነ ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የሚወደኝ ቢኖር መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ እንዳለ መስቀሉን የመሸከም ሃላፊነት የሁሉም ክርስቲያኖች አላማ መሆን ይገባዋል። በእርግጥ ግዜ እና ዘመን በሚያመጣቸው ፈተናወች የመስቀሉ ወዳጆች ሆነን በመገኘታችን እንደየአካባቢው ብዙ መከራ ሊመጣብን ይችላል። ይህንን ደግሞ እኛ ክርስቲያኖች በጠላቶች ዘንድ ስንሞት እየበዛን እንደሆነ፣ ስናዝንም እየተደሰትን እንደሆነ፣ ስንሸነፍም እያሸነፍን እንደሆነ ልናምን ይገባል። ክርስቶስም ሞትን ለሚመስል ሞት ሞቶ ነው የሁላችንንም ሞት የደመሰሰልን። ከዚህ የተነሳ የ 2013ዓም የደመራ በአልን እስካሁን እንደተለመደው በታላቅ ድምቀት ለማክበር በዘመናችን የአገራችንና የአለማችን ፈተና ሆኖ የተከሰተው የዘመኑ ወረርሽኝ ወይም ኮቪድ 19 ይህን ለማድረግ ባያስችለንም ክርስቲያን ፈተናን እና ሞትን እንዳይፈራ የእግዚአብሔር ቃል ቢነግረንም ለሌሎቹ ፈተና ምክንያት እንዳንሆን ባለንበት ሆነን ከመስቀሉ በረከት ለመካፈል የልጅነት ድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል።
በአጭሩ ለበረከት የህል ስለ መስቀል ደመራ በአል አከባበር እና መሰረታዊ ታሪኩን በተነሳንበት የትምህርት ርዕስ ይህንን ያህል ካልን ወደፊት ስለ መስቀሉ ክብር በስፋት ልንማማር ስለምንችል ለግዜው መልእክቱን እዚህ ላይ እንፈፅማለን።
የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የመስቀሉ በረከት በሁላችን ይደርብን፤ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀን።
 
 
“እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ ” ( ዳን 10፥13) 
 
 
በዚህ ኃይለቃል ስለ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት እና ታዳጊነት አጭር መልዕክት  እናስተላልፋለን : እንደሚታወቀው በአገራችን በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 12 ቀን የቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ መታሰቢያ በአሉ ነው። መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በ12ቱ ወራት ያደረጋቸው ተአምራት በየወሩ በ12 ቀን በሚነበበው ድርሳኑ ተጽፎ እናገኛዋለን። 
 
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሐ ድረ ገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች ከምንም በላይ እግዚአብሔር የሀሳባችሁን እና የውስጥ መሻታችሁን ተመልክቶ በበረከቱ በቸርነቱ በምህረቱ ብዛት ያኖራችሁ ዘንድ የቅዱሳን መላእክትም አማላጅነት እና ተራዳይነትን ጠንቅቃችሁ መረዳት እንደሚገባችሁ አውቀን እንመክራለን ::
 
ቅዱስ ሚካኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላዕክት የመጀመሪያውን የአለቅነት መአረግ የተቀዳጀ ታዳጊ መልአክ ነው :: ሚካኤል ማለት የስሙ ትርጉም ማን እንደ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቅዱስ ሚካኤል :- መጋቤ ብሉይ፣ መላከ መክሩ፣ መላከ ኃይል፣ ወዘተ በማለት በሚሰራቸው የታዳጊነት ስራዎቹ በነዚህ ስሞች ይገለጻል። ይህ መልአክ ለሰው ልጅ እና ለእንስሳት ሁሉ ከፈጣሪው ዘንድ ምህረቱን ለመለመን የተሾመ መልአክ ነው።
 
በዛሬው ጥቅምት 12 ቀን መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ከፈጣው ዘንድ በተሰጠው መለኮታዊ ትዕዛዝ መሰረት የእስራኤል ነብይ እና መስፍን ወደሆነው ወደ ነብዩ ሳሙኤል ዘንድ ሄዶ ” በቤተልሔም ወደሚሆነው ወደ ነብዩ ዳዊት አባት ወደ ሆነው ወደ እሴይ በመሄድ በንጉሱ በሳኦል ፋንታ የእሴይን ልጅ ዳዊትን ቀብቶ በእስራኤል ላይ እንዲያነግሰው ከእግዚአብሔር የተላከውን መልዕክቱን ያደረሰበትን መልአኩን የምናስብበት እለት ነው :: ነብዩ ሳሙኤልም በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል ትዕዛዝ መሰረት ነገስታቱ የሚቀቡበትን የዘይት ቀንድ (ቅብዓ ንጉስ) ይዞ ወደ እሴይ ቤት በመሄድ ከልጆቹ መካከል እግዚአብሔር በእስራኤል ዘንድ ንጉስ ይሆን ዘንድ ቀብቼ እንዳነግሰው አዞኛል እና ልጆችህን ሁሉ አቅርብልኝ ባለው ጊዜ በእድሜ እና በአካለ መጠን የሚበልጡትን ባቀረባቸው ጊዜ ለንግስና የተዘጋጀው ቅባ መንግስት አልከፈት ስላለው እግዚአብሔር የመረጠው ሰው እንዳልቀረበ በዚህ ምልክት ማወቁን ነብዩ ሳሙኤል ለእሴይ በነገረው ግዜ ከልጆቹ መካከል የመጨረሻው እና በእድሜም ሆነ በአካሉ መጠን ከሁሉ ያነሰውን ዳዊትን ሲያቀርብለት የዳዊት መሾም የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበረ ቅባ መንግስቱ ተከፍቶለት የበግ ጠባቂ የነበረው ብላቴናው ዳዊትን የእስራኤል ንጉስ እና ጠባቂ እንዲሆን ቀብቶ እንግሷል፡፡ ይህን ታላቅ መለኮታዊ ምስጢር የተፈጸመው ከመላኩ በቅዱስ ሚካኤል መልዕክት ነው።
 
መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ተዋግቶ ለማሸነፍ ከፈጣሪው የተቀዳጀው መልአካዊ ግርማ ስላለው ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በመላእክት አማላጅነት እና ተራዳይነት አምነው የሚማፀኑ ሁሉ በየጊዜው የሚዋጋቸውን እርኩስ መንፈስ የማሸነፍ ሃይል አላቸው። የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ድርሰትን የሚፀልዩ፣ በስሙ የሚዘክሩ፣ እና በስሙ በተሰራው ቤተክርስቲያን ሄደው የሚፀልዩ ሁሉ መልአኩ በወጡበት በገቡበት፣ በሄዱበት እና በደረሱበት ሁሉ እንደ እስራኤል ዘስጋ ከመከራ በአማላጅነቱ ይቆምላቸዋል።
 
ስለዚህ የሁላችን አማላጅ የሆነውን የቅዱስ ሚካኤልን ተአምራት ተናግረን የማንጨርሰው ቢሆንም እንኳን፡ – . ወርሃዊ በአሉን በማሰብ በረከት እናገኝ ዘንድ ያህል ለመግለፅ የቻልን ሲሆን እግዚአብሔር በቸርነቱ እና በምህረቱ የህዳር ቀን በሚከበረው በዓል ላይ ሰፊ እና ጥልቅ የሆነውን የመልአኩን ታዳጊነት እና አማላጅነት ተራዳይነት በስፋት የምንናገር ስለሆነ የመልአኩን አማላጅነት ተራዳይነት የዚህ ፕሮግራም ተከታታይ ወገኖቻችን እንድትረዱ እና ከበረከቱ እንድትሳተፉ ይህንን አጭር መልዕክት እንዲደርሳችሁ አድርገናል።
 
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በአማላጅነቱና በታዳጊነቱ ሁለችንንም ይረዳን ዘንድ የአምላካችን የቅዱስ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንልን
 
 
 
“እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” 
(ሉቃ 1፥19) 
 
 
የተከበራችሁና የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረ ገፅ የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ፕሮግራም የምትከታተሉ ሁላችሁም እንኳንስ ለመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወርሃዊ በአል አደረሳችሁ። ከዚህ በመቀጠል ከመልአኩ በረከት እናገኝ ዘንድ ስለ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይህን አጭር መልዕክት ወደ እናንተ እንዲደርስ አድርገናል።
 
ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔር ሰው ፣የእግዚአብሔር አገልጋይ እና ፣ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ማለት ነው:: ይህም ምስጢራዊ ስያሜ የተሰጠው ብዙ ጊዜ በሰው ምሳሌ እየተገለፀ የእግዚአብሔርን መልዕክት ወይም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሰው ልጅ ስለሚያደርስ ነው። ቅዱስ ገብርኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላዕክት ከቅዱስ ሚካኤል ቀጥሎ በ2ተኛ መአረግ የተሾመ መልአከ ኃይል ነው። እግዚአብሔር አምላክ በመጀመሪያው ቀን ከፈጠራቸው 8 ፍጥረታት መካከል መላዕክት ይገኙበታል ። መላዕክት በሥነተፈጥሮዋቸው እምሃ በአልቦ በእግዚአብሔር የክሁነት ቃል የተገኙ ሲሆን በግብራቸው ደግሞ እሳታዊና ነፋሳዊ ናቸው። እግዚአብሔር 99 ነገደ መላዕክትን በሦስቱ ሰማያት አሰልፏዋቸዋል ::
 
1ኛ/ በእዮር ያሉት መላዕክት በ 4 አለቃ፣ በ40 ነገድ ከፍሎዋቸዋል :: 
 
2ኛ/ራማ በተባለው የብርሃን ሰማይ የሰፈሩት መላዕእክት በ3 አለቃ በ30 ነገድ፣ በ3 ከተማ ከፍሎዋቸዋል።
 
3ኛ / ኤረር በተባለው ሰማይ ከ3 ክፍሎበ30 ነገድ በ3 ከተማ በ3 አለቃ ከፍሎዋቸዋል። 
 
ይህ የመላዕክት የአኗኗር ሁኔታ እጅግ ረቂቅ እና ሰፊ የሆነ ትምህርት ያለው ስለሆነ ወደፊት በዝርዝር የምንገልፀው ሆኖ ወደተነሳንበት ርዕስ ስንመለስ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በራማ የብርሃን ሰማይ ከሚኖሩት 30 ነገደ መላእክት 4 ነገደ አርባብ የተባሉት መላእክት አለቃቸው ሆኖ የተሾመ መላእክ ነው :: መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እና በተራዳይነቱ ከመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እኩል በቅዱሳት መጻሕፍት የትገለፀ ነው። መላእክት በተፈጠሩበት ስፍራ የፈጠራቸው አምላካቸው እግዚአብሄር የሃይማኖታቸውን ጽናት ለማረጋገጥ በቅጽበታዊ ሰዓት ከአይናቸው ቢሰወርባቸው፣ ማን ፈጠረን? ከየትስ መጣን? የሚል ጥያቄ በመላእክት ማህበር ውስጥ በተነሳ ጊዜ የጥፋት ሰው ዲያቢሎስ በድፍረትና በክህደት ቃል እኔ ፈጠርኋችሁ ባለ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ግን ባለንበት ፀንተን እንቁም በማለት እልፍ አእላፋት የቅዱሳን መላዕክት ማህበር አረጋግቷል ::መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከፈጣሪው ከተሰጠው ፀጋ የሚታወቅባቸው ዋና ዋና የአማላጅነት እና የተራዳኢነት ሥራዎቹ መካከል :-
 
1ኛ/ ለነብዩ ዳንኤል በራዕይ ተገልፆ ስለሚሆነው ነገር እንዲህ ሲል ተናገረው “እኔም ዳንኤል ራእዩን ባየሁ ጊዜ ማስተዋሉን ፈለግኩ እነሆም የሰው አምሳያ ከፊቴ ቆሞ ነበር። በኡባልም ወንዝ መካከል ገብርኤል ሆይ ራዕዩን ለዚህ ሰው አስታውቀው ብሎ የሚጮህ የሰው ድምፅ ሰማሁ፡፡”(ዳን 8፥ 15:16)
 
2ኛ /እንዲሁም ነብዩ ዳንኤል ዳግም ባየው ራዕይ ስለ መልአኩ እንዲህ ሲል ተናገረ “ገናም በፀሎት ስናገር አስቀድሜ በራዕይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ … ዳሰሳኝ አስተማረኝም ተናገረኝም… ዳንኤል ሆይ ጥበብ እና ማስተዋል እሰጥህ ዘንድ አሁን መጣሁ ” ፡(ዳን 9፥21-23)
 
3ኛ/ ቅዱስ ገብርኤል ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ መልአክ ነው። 
 
4ኛ/ ሰልሦቱ ደቂቃንን ከእቶን እሳት አድኗቸዋል ።
 
5ኛ/ ለካህኑ ዘካርያስ እና ለቅድስት ኤልሳቤጥ በእርጅና ዘመናቸው መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን እንደሚወልዱ አብስሮዋቸዋል ።
 
6ኛ የዓለም መድኃኒት የሆነው አካላዊ ቃል እየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንደሚወለድ አብስሮዋታል። 
 
7ኛ/ ቅድስት እየሉጣን እና ህፃኑ ቂርቆስን በብረት ጋን ውስጥ ከፈላው እሳት አድኗቸዋል።
 
8ኛ/ ሰብአ ሰገልን በኮከብ ምልክት እየመራ ጌታ ወደተወለደበት ወደ ቤተልሄም ከተማ አድርሷቸዋል።
 
9ኛ/ አረጋዊ ዮሴፍ እናቱን እና ህፃኑን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሽሽ በህልም ተናግሮታል 
 
በአጠቃላይ የዚህ መልአክ አማላጅነትና ተራዳኢነት በቅዱሳን መፅሐፍት በብዙ ክፍለ ንባብ የምናገኘው ሲሆን ራሱን የቻለ ስለ መላዕክት አማላጅነትና ተራዳኢነት ወደፊት ሰፊ ትምህርት የምንሰጥበት ሲሆን፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነትና በረከት እናገኝ ዘንድ ይህንን ወርሃዊ በአሉን ምክንያት በማድረግ አንድንፅፍላችሁ እግዚአብሔር አግዞናል።. እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክ በማታም በጠዋትም በቀንም በሌሊትም በመንገድም በቤትም ስንተኛም ስንነሳም ይጠብቀን ዘንድ መልአክቱን ባያቆምልን ኖሮ በሰው ልጅ ጠላትነት የተሰደዱ የሳጥናኤል ሰራዊት በዚህ አለምም ሆነ በዚያኛው አለም ህይወት እንዳይኖረን ባደረጉንም ነበር።
 
ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “መቅስፍት ወደ ቤትህ አይገባም፤ በመንገድህም ይጠብቁህ ዘንድ መላዕክትን ስለ አንተ ያቆማቸዋልና፤እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል… ” በማለት ስለ መላዕክት ጠባቂነት እና ተራዳኢነት ተነግሮናል :: 
 
በሌላም አንቀጽ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል” በማለት የመላዕክትን ተራዳኢነት እና አማላጅነት አምነው የሚፀልዩትን እንደሚያድኑ እና ከስጋዊም ሆነ ከነፍስ መከራ እንደሚታደጉን ተናግሯል። (መዝ 33፥7፣ 90/91፥10′)     
 
መላእክት በሁሉም ፍጥረታት ላይ ስልጣን እንዲኖራቸው የተሾሙ ስለሆነ ነብዩ ሄኖክ በእባቦች ላይ በገነትም ባሉ ፃድቃን ላይ በኪሩቤልም ላይ የተሾሙ ከከበሩ መላዕክት አንዱ ቅዱስ ገብርኤል በፍጥረታት ላይ ያለውን የአማላጅነትና የታዳጊነት ስልጣኑን ነግሮናል። (ሄኖክ 6፥7)
 
በመሆኑም ዛሬም በዘመናችን እንደ ሰልሦቱ ደቂቅና እንደ ቅድስት እየሉጣ እንደ ቅዱስ ቂርቆስ ሊያቃጥለን እና ሊበላን የነደደ ብዙ የቁጣ እሳት ስላለ ሁለችንም ከዚህ በዘመናችን ከነደደብን የመቅሰፍት እሳት አንድን ዘንድ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እና በተራዳኢነቱ ከፈጣሪው ዘንድ እንዲያስታርቀን በመልአኩ አማላጅነት አምነን በመማፀን ወደ ፈጣሪያችን አንቀርብ ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡
 
ከዚህ ታላቅ የብርሃን መልአክ ፀሎትና ምልጃ በሁለችን ላይ ይደርብን
እነሆ መልአኬ ይምራችሁ (ዘፀ 20፥23)
 
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፓሮግራም ተከታታዮች እንኳንስ እግዚአብሔር አምላክ ህዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ለምናከብረው የመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በዓለ ንግስ አደረሳችሁ። መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃ ሆኖ የተሾመና እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ያወጣበትን በማሰብ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በአሉን በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳንም ሰዎች እና ሌሎችንም ስነፍጥረታት ለመርዳትና ለመታደግ ሲጠሩት ፈጥኖ የሚደርስ የምህረት መልአክ እንደሆነ ተመዝግቧል። መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆነ አሀዜ መንጦላዕት ቅርብ እግዚአብሔር መጋቢ ብሉይ ሰአሌ ምህረት የሆነ መልእክ ነው፡፡ ነብየ እግዚአብሔር ዳንኤል በትንቢቱ ላይ ”ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ” በማለት በጭንቅና በመከራ ጊዜ በአማላጅቱና በተራይነቱ ወይም በታዳጊነቱ አምነው ለሚማፀኑት የሚረዳና ከገባንበት ፈተና ለማውጣት የሚረዳን እንደሆነ ነግሮናል። (ዳን10፥13) በዚህም አባታችን ያዕቆብ ከልጆቹ ጋር በስደት ወደ ምድረ ግብፅ ከሄደ በኋላ አስቀድሞ ለወንድሞቹ ሰባዊ ጭካኔ በባርነት ተሽጦ በነበረው በዮሴፍ አማካኝነት በግብፃዊያን ዘንድ ክብር በዝቶላቸው ታዋቂዎችና ተፈሪዎች ሆነው ሲኖሩ ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ፈርኦን በግብፅ በነገሰ ጊዜ በያዕቆብና በልጆቹ ላይ አገዛዝን ያፀኑባቸው ዘንድ በንጉሱ ትዕዘዝ ፅኑ የባርነት ቀንበር በጫኑባቸው ጊዜ ወደ ሰማያዊ አምላካቸው ስለደረሰባቸው ግፍና መከራ እንባቸውን እየረጩ አለቀሱ። ጆሮ እንደሌለው እንደማይሰማ አይን እንዳሌለው ጩኸታቸው እስከ መንበረ ፀባኦት በደረሰ ጊዜ ያንን የእስራኤል ዘስጋን የባርነት ቀንበር እንዲሰብር በ430 ዘመን ከኖሩበት የባርነት ዘመን እንዲያወጣቸው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ወደነሱ ተላከ።
የመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የታዳጊነትና የተራዳይነት ስልጣኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠው በምድራዊ ሰዎች ያልተሾመ ስለሆነ የማይገደብ ዘለአለማዊ ቃል ኪዳን ነው።ከዚህ የተነሳ ከዕብራዊያን ወገን የሆነውን ምስኪኑን እና በአንደበቱ ኮልታፋ የሆነውን ተናግሮ ለማሳመን ኃይሉን አሳይቶ ለመፈራት አቅም የሌላውን የእግዚአብሔር ሰው ነብዩ ሙሴን አስነስቶ በጠባቂነት ከሱጋር በመሆን ፤ በዘመኑ ‘ማን እንደሱ?!’ ተብሎ በመንግስቱና በስልጣኑ በሚፈራው በግብፅ ንጉስ በፈርኦን ዙፋን የችሎት ፊት ቀርቦ “ህዝቤ እስራኤልን ልቀቃቸው ይልሃል” በማለት የፈጣሪውን ትዕዛዝ ለፈርኦን በነገረው ጊዜ ፈርኦንም ጨካኝ እና ልበ ደንዳና ስለነበረ ሰውንም በባርነት ቀጥቅጦ መግዛት እንደትልቅ የባርነት መገለጫ አድርጎ ስለነበር፤ ‘እግዚአብሔር ማነው? ህዝቤን አለቅም’ በማለት አሻፈረኝ ብሏል። በቅዱስ ሚካኤልና በነብዩ ሙሴ አማካኝነት የእስራኤል ከግብፅ ባርነት መወጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበር ንጉሱ ፈርኦን ልቡን አዳንድኖ በቁጣና በብስጭት ቃል ህዝቡን እንዳማይለቅ እግዚአብሔርም ማን እንደሆነ እንዳማያውቅ በድፍረት ቢናገርም ነብዩ ሙሴም “እህያ ሸራህያ ኤልሻዳይ ያገለግሉኝ ዘንድ ህዝቤን ልቀቅ ብሎሀል ” አለው። ምን ምልክት አለህ ባለው ጊዜ የያዛትን በትር ምድር ላይ ጣላት እባብም ሆነች፥ ጅራቷን ይዞ ቢያነሳት ተመልሳ በትር ሆነች፤ ደግመኛም እጁን ከብብቱ አስገብቶ ቢያወጣው ለምፅ ሆነ እሳት እንደነካው ጅማትም ተሰበሰበች፤ እንደገናም ወደ ብብቱ አስገብቶ ቢያወጣው ከለምፁ ዳነች፤ በቅል የያዘውን ቢደፉው የግብፅ ወንዞች ሁሉ ደም ሆኑ :: እነዚህን ሁሉ ምልክቶች ለፈርኦን ሲያሳየው በቤተመንግስቱ የነበሩ አስማተኛና ሟርተኞች እያሜስና እያንበሬስ የተባሉት አስማተኞች ጠርቶ ሙሴ ያደረገውን እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ቢሰጣቸውም በትራቸውን እባብ ለማድረግ ቢሞክሩም ተመልሶ በትር መሆን አልቻለም፡ እንዲያውም አባቡ እነሱን የሚያሳድድ ሆኖዋል። እጃቸውን ከብብታቸው አስገብተው ቢያወጡ ለምፅ ሆኖ ቀርቷል። ስለዚህ የነሱ የጥንቆላ አስማትና የምትሀት ሥራ በእግዚአብሔር ኃይል የተደረገውን የሙሴን ተአምራት ሊያደርግ አልቻለም።
ከዚህ በኋላ ፈርኦን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ህዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በንጉሱ ላይና በሀገሩ በግብፅ ህዝብ ላይ 9 ልዩልዩ መቅሰፍቶች፣ 10ኛው ደግሞ ሞተ በኵር፣ 11ኛው ስጥመተ ባህር የተባሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮበታል። የመጀመሪያዎቹ መቅሰፍቶች : የግብፅ ወንዞች ሁሉ በደም ተጥለቅልቀዋል፣ በሰዎችና በእንስሳት ሁሉ የእባግጭ ደዌ ወይም ቁስል ተልኮባቸዋል፣ የቅማል ፣የዝንብ መንጋ ተልኮባቸዋል፣ ከሰማይ የበረዶ ዝናብ ዘንቦባቸዋል፣ በአዝመራው ላይ ልዩልዩ ተባይ ተልኮባቸዋል፣ የ ጓጉንቸር መንጋ ተልኮባቸዋል፣ ድቅድቅ ጨለማ በአገራቸው ላይ ተልኳል። በእነዚህ ሁሉ 9 መቅሰፍቶች ፈርዖን እስራኤልን ሊለቅ ባለመቻሉ ለ10ኛ ጊዜ የበኵር ልጆቻቸውን የሚገድል መቅስፍት ተልኮባቸዋል። ከዚህ በኋላ ግብፃዊያን ሁሉ በበኩር ልጆቻቸው ሞት ከፍተኛ ለቅሶና ሀዘን በሰሙ ጊዜ ይሄንን ሁሉ መቅስፍት ያመጣባቸው የእግዚአብሔር ህዝብ አገልጋይ የሆኑትን ንጉሱ ባለመልቀቁ እንደሆነ ስላወቁ ለእስራኤላዊያን ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ስጦታ ሁሉ አሟልተውላቸው በአስቸኳይ ከግብፅ ወጥተው አምላካቸውን የሚላቸውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእኛም ላይ ሌላ ጥፋት እንዳይመጣብን ልናደርግ ያስፈልገናል ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ንጉሱም ስለ ተሰማማበት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሙሴ መሪነት በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳይነት ከግብፃዊያን ዘንድ የተሰጣቸውን ሀብት (ስጦታ) ይዘው በችኮላና በፍጥነት ከግብፅ ምድር ወጥተው በምድረበዳ ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል መስዋዕትንም ሰውተዋል።
በመጨረሻም ቅዱስ ሚካኤል ሌሊት ሌሊት በጨለማው ክፍለ ጊዜ የብርሃን አምድ ከፈታቸው እያቆመ፣ ቀንቀን የፀሐዩ ኃይል እንዳያቃጥላቸው በዳመና ድንኳን እየጋረደ፣ ከፊትም ከኋላም ጠላት እንዳያጠቃቸው እሱ እንደ ወታደር ጠባቂ ሆኖ ነብዩ ሙሴም በመሪነቱና በመምህርነቱ እንዲተጋና እንዲበረታ ኃይል እየሰጠ፣ ከሰማይ መና አውርዶ፣ ከደረቅ አለት ውሃ አፍልቆ ፣ እየመገባቸው 40 ዘመን በምድረበዳ ይህ መልአክ ረድቷቸዋል።
የእስራኤላዊያን ጥንተ ጠላት የሆነው ንጉሱ ፈርኦን እና ወታደሮቹ በእስራኤላዊያን ከግብፅ መወጣት ተቆጭተው ለመያዝ እያሳደዱ በተከተሏቸው ጊዜ በጠላቶቻቸው ላይ ድካምንና ጥፋትን እያደረገ በመጨረሻም በፊታቸውና በመንገዳቸው ላይ እንደሰማይ ስባሪ ተንጣሎ የነበረውን ባህረ ኤርትራን በሙሴ አማካኝነት በያዘው በትረ መስቀል ባህሩን እንዲመታው ባዘዘው ጊዜ እንደ ግድግዳ በመቆም መሀሉ የጥርጊያ መንገድ ሆኖላቸው እስራኤላውያን በደስታ በየብስ እንደሚሻገር መንገደኛ ባህሩን እንዲሻገሩ ረድቷቸዋል።ግብፃዊያን ግን እነሱን ለማሳደድ ወደ ወደ ባህሩ እንደገቡ በግብፃዊያን በላያቸው ላይ ተከድኖባቸው ሰጥመው እንዲቀሩ አድርጐቸዋል። መልአኩ በጠባቂነትና በተራዳይነት ከጠላታቸው ባህረ ኤርትራን በየብስ ስለተሻገሩ ይሄንን ድህነት ስላደረገላቸው ለእግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ዝማሬ አቅርበውለታል።
እንግዲህ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ አባላት ህዳር 12 ቀን የምናከብረው የቅዱስ ሚካኤል በአል በብዙ ምስጢርና ትርጉም የሚገለፅ ቢሆንም ከበአሉ በረከት ለማግኘት እና እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን መጠን በዚህ እለት ቅዱስ ሚካኤል ያደረገውን ገቢረ ተአምራት ማወቅም ስላለብን ከዚህም በላይ እስራኤል ዘስጋን ከግብፅ ባርነት እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም በዘመናችን ከሚቃጣብን መቅሰፍት መከራ የደዌ መከራና ጦርነት እንዲያወጣን እስራኤልን ባህረ ኤርትራን ከፍሎ እንዳሻገራቸው እኛንም ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት፣ ከሞት ወደ ህይወት፣ ከሲኦል ወደገነት እንዲያሻግረን የመልአኩን አማላጅነትና ተራዳይነት መለመን ያስፈልገናል። እስራኤላውያን ስለ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አማላጅነትና ተራዳኢነት ሲናገሩ “እነሆ ወደ እግዚአብሔርም በጮህን ጊዜ እነሆ መልአኩን ልኮ ከግብፅ አወጣን” (ዘሁልቅ 20፥16)። እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክ ስለ መላእክት ጠባቂነት ሲነግረን “በመንገድ ይጠብቅኽ ዘንድ ወዳዘጋጀኹትም ስፍራ ያገባኽ ዘንድ፥እንሆ፥እኔ መልአክን በፊትኽ እሰዳለኹ። በፊቱ ተጠንቀቁ፥ቃሉንም አድምጡ ስሜም በርሱ ስለ ኾነ ኀጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።” በማለት መላዕክት ከፊታችን የሚቀድሙ ከሚመጣብን መከራና ድንገተኛ ፈተና የሚጠብቁን እንደሆኑና መላዕክትን ብናሳዝን ታዳጊነታቸውን ተራዳይነታቸውን ብንንቅ ይቅር እንደማይባል ጥፋት እንደሚያጋጥመን በቃሉ ነግሮናል።(ዘፀ 23፥ 20 )
ስለዚህ ሁላችንም በሀገራችን እና በህዝባችን ላይ ከተቃጣው መቅስፍት እና ጦርነት በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና አማላጅነት እንዲያወጣን እንደ እስራኤላውያን ተባብረን በአንድ ልብ ሆነን ወደ እግዚአብሔር ልንጮህ ይገበናል። እግዚአብሔር አምላክ የበአሉን ክብር በታላቅ ድምፅ እንድንገልፅ ሁላችንም በያለንበት በተለያየ ምክንያት ጊዜ ብናጣም የምንችለውን ሁሉ በጐ ነገር ማድረግ እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን።
በመጨረሻም የእናታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት የመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት የመድኃኒዓለም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን

ጥር 21-እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ

 
የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገጽ ተከታታይ ወገኖቻችን በቅድሚያ እንኳን ለ 2013 ዓም በየአመቱ ጥር 21 ቀን የምናከብረውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም #በዓለ_ዕረፍት መታሰቢያ ታላቅ በዓል አደረሰን፡፡
 
በዓሉን በሚመለከት ከዚህ ቀጥለን አጭር ትምህርታዊ መልእክት እንዲደርሳችሁ ስላደረግን በማስተዋል አንብባችሁ በመረዳት ስለበዓሉ ግንዛቤ ታገኙበት ዘንድ አደራችንን አናስቀድማለን።
በቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደተፃፈ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአባቷ ከቅዱስ እያቄም እና ከእናቷ ከቅድስት ሀና ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተራራ ከተወለደች በኋላ 3 አመት በቤተሰቧ ቤት፣ 12 አመት በቤተመቅደስ፣ 33 አመት ከ 3 ወር ከልጇ ጋር፣ እና ከጌታችን ሞት በኋላ 15 አመት ከ 9 ወር በቅዱስ ዪሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ ቤት በድምሩ 64 አመት የነበራትን የእድሜ ቆይታ ከጨረሰች በኋላ በልጇ ውሳኔ በሞት ተጠርታ የጌታ ደቀመዛሙርት ቅዱሳን ሐዋርያት በቅዱስ ዩሐንስ ወልደ ነጎድጓድ አማካኝነት ከመስቀሉ ስር በአደራ የተቀበሏት የቃል ኪዳን እናታቸው ስለሆነች (ዮሐ 19፥25) በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ከነበሩበት የወንጌል አገልግሎት (ሐዋርያዊ ስምሪት) ተሰብስበው ሥጋዋን በክብር ገንዘው በመጨረሻው ሰዓት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ተአምራት በአደረገበት ስፍራ በጌተሴማኒ ሊቀብሯት በጉዞ ላይ እንዳሉ የልጇን ትንሳኤ እና ዕርገት ይቃወሙ የነበሩ ማህበረ አይሁድ ሰይጣናዊ በሆነ የቅናት መንፈስ ተነሳስተው አስክሬኗን ከሐዋርያት እጅ ቀምተው ለማቃጠል በአመፅና በኀይል በተፈታተኑ ጊዜ ፈጣሪዋና ልጇ የሆነው ቸሩ መድኃኔዓለም በልዩ ምስጢር በቅዱሳን መላእክት ተልዕኮ ታጅባ ከሐዋርያው ቅዱስ ዩሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር በክብር እንድትኖር አድርጓታል።
 
የእመቤታችን ዕረፍቷ ጥር 21 ቀን በመሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያት የድንግል ማርያም ሥጋዋ በዕፀ ሕይወት ሥር ማረፉን ለማየት የታደለው ቅዱስ ዩሐንስ ብቻ ስለነበረ እኛስ ለምን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ከእናታችን በረከት አልተካፈልንም በሚል መንፈሳዊ ቅንዓት ተናሣሥተው በዐረፈችበት በ8ተኛው ወር ላይ ከነሐሴ 1 እስከ 14 ቀን ድረስ በሱባኤ ተወስነው ከቆዩ በኋላ በ 14ኛው ቀን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሥጋዋን የማግኘት ምስጢር ተገልፆላቸው በዚያውኑ ቀን በጸሎት ምህላና በታላቅ ደስታ በጌተሴማኒ ለሥርዓተ ቀብር በመረጡት ስፍራ ላይ አሣርፈውታል።
 
ነሐሴ 16 ቀን በተቀበረችበት በ 3ኛው ቀን የሚሳነው ነገር የሌለ ሁሉን ቻይ የሆነው ልጇ በራሱ ስልጣን አሳርጓታል። በተቀበረችበት ቀን ከሐዋርያት ጋር ያልነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ስታርግ ለማየት ዕድል ገጥሞት ስለነበረ የዕርገቷን ምስጢር ያላዩት ቅዱሳን ሐዋርያትም ቅዱስ ቶማስ ያየውን የዕርገቷን እና የትንሣኤዋን ክብር እኛም ማየት አለብን ብለው በዓመቱ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ሱባኤ በመግባት የትንሣኤዋንና የዕርገቷን ነገር ለማየት ችለዋል።
 
ተጨማሪ፦
ከመጽሐፈ ተአምሯ፡- እመቤታችን ከዚህ ዓለም ታልፍ ዘንድ የጸለየችው ጸሎት ይህ ነው፡- ‹‹አቤቱ ቸር ጌታዬ ሆይ! ከዚህ ሑከትና ኀዘን ከመላበት ዓለም ደገኛውን መልአክህን ልከህ ወደኝ› ስትል በጸለየች ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸላት፡፡ እንዲህም እያለች ስትጸልይ ሰማይ ተከፈተ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ወደ እመቤታችን ወርዶ ‹ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ› በማለት የደስታ መልእክት ነገራት፡፡ ዳግመኛም ‹‹እነሆ ጸሎትሽ ከአንቺ ከተወለደው ከእግዚአብሔር ዘንድ ደረሰ፡፡ እንደፈቃድሽ ከዚህ በኃላፊው ዓለም ወደ ዘላለም ሕይወት ትሄጂ ዘንድ ልመናሽ ተሰምቶልሻል›› አላት፡፡
እመቤታችንም ይህንን ነገር ከመልአኩ በሰማች ጊዜ ወደ በዓቷ ተመለሰችና ከዚያ የሚያገለግሏትን ደናግል ሰብስባ ‹አይሁድ ሁልጊዜ የልጄን መቃብር ይጠብቃሉና ስለዚህ የእኔን ከዚያ መገኘት አንድ ቀን ይገለጽላቸውና ከዚያ መግባት ይከለክሉኛል ብዬ ፈራሁ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ራሳችሁን ችላላችሁ በሰላም ትኖራላችሁ እኔ ወደ ቤተልሔም እሄዳለሁና› አለቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ሁሉም በአንድነት ቃላቸውን አስተባብረው ‹ከአንቺ ጋር እንሄዳለን፡፡ ስለ አንቺ እናት አባታችንን፣ እኅት ወንድሞቻችንን ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሻልና እነሆ አሁንም አንቺ ከሄድሽበት እኛም አብረንሽ እንሄዳለን፣ ባለ ዘመናችን ሁሉ ከአንቺ አንለይም› አሏት፡፡ እመቤታችንም በዚያን ጊዜ ይዛቸው ወደ ቤተልሔም ሄደች፣ በዚያም ተቀመጠች፡፡ እንዲህም ያለቻቸው ስለ አይሁድ ፍራቻ ሳይሆን ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት የመለየቷ ጊዜ ስለመድረሱ ነበር፡፡ እናንት የፍቅሯን ፈለግ የተከተላችሁና በፍቅሯ ቀምበር የተጠመዳችሁ የወንጌል ልጆች ሆይ እንግዲህ እመቤታችን በቤተልሔም ተቀምጣ ሳለች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከዚህ ዓለም በሞት የምትለይበትን ጊዜ በክብር እንደነገራት አስተውሉ፡፡ ልመናዋ ክብሯ ለዘለዓለሙ በዕውነት ይደርብን፡፡
እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፡- በ50 ዓ.ም ገደማ በዕለተ እሑድ ጌታችን እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ ‹‹እናቴ ሆይ! ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?›› አለችው፡፡ ጌታችንም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳያትና ‹‹እናቴ ሆይ! ሞትሽ ለእኒህ ቤዛ ይሆናቸዋል›› አላት፡፡ ለፍጥረታት ሁሉ እጅግ የምትራራ እመቤታችንም ‹‹እነዚህን ከማርክልኝስ ይሁን ልሙት›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ቅድስት ነፍስዋን ከክብርት ሥጋዋ ለይቶ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ ‹‹እመቤታችሁን ቅበሩ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ይዘዋት ወደ ጌታ ሰማኔ ወሰዷት፡፡
አበው ‹‹እመቤታችን ሆይ! ሞትሽ ሠርግን ይመስላል›› እንዳሉት የእመቤታችን እረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት ቅዱሳን መላእክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት እንጂ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፤ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች›› በማለት ዘምሯል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር ‹‹አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ 131፡8፡፡ ይህም ‹‹ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ›› ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ከኖረች በኋላ ነብሷ ከሥጋዋ ተለይቶ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ‹‹ታቦት›› ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡
 
ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌ ሲናገር «ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ መዐዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ» አለ፡፡ መኃ 2፡10-14፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ሲተረጎም በውስጡ ብዙ ምሥጢራዊ ነገሮችን ያያዘ ነው፡፡ «በክረምትና በዝናብ» የተመሰሉ የእመቤታችን መከራዎች ናቸው፡፡ የመከራሽ ጊዜ አልፏል ሲላት «አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ» ማለቱ ከልጅሽ እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረው ወንጌልን የተቀበሉ ሐዋርያት አንቺን በእናትነት የተረከቡ የሐዋርያት ድምፅ ወይም ስብከት በምድር ሁሉ መሰማቱን ያጠይቃል፡፡
 
ጠቢቡ ሰሎሞን «የዜማ ጊዜ ደረሰ» ያለው የመከሩን ወቅት ነው፡፡ መከር የፍሬ ጊዜ እንደመኖኑ ሐዋርያት የዘሩት ዘር ማለትም ስብከታቸው ፍሬ አፈራና ክርስቲያኖች በዙ፤ «በለሱ ጎመራ» በጎ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በሐዋርያት ስብከት ተምረው ምግባር መሥራት ጀመሩ፤ «ወይኖች አብበዋል መዐዛቸውንም ሰጥተዋል» በመላው ዓለም ያሉ ምዕመናን በሃይማኖት ማበብ፣ መዐዛ ምግባራቸውን ማቅረብ መስጠት ጀመሩ በማለት ሊቃውንት አባቶች ምሥጢሩን ያብራሩታል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ‹‹ወደጄ ሆይ! ተነሽ›› እያለ የሚናገረው ተወዳጁ ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ድንግል ማርያምን በመለኮታዊ ስልጣኑ ከሙታን ለይቶ ማስነሣቱን ሲያስረዳን ነው፡፡
ስለዚህ ድንቅ ምስጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› (መዝ 131፡8) ብሎ የተናገረው ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍትና ትንሳኤ እንዲሁም ፍልሰት (ዕርገት) ከማሳየቱም በተጨማሪ የአምላክ እናት በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብር መኖሯንም በግልጽ ያስረዳል ያስገነዝባል፡፡ ‹‹በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› (መዝ 44፡9) የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ትንቢታዊ ቃል ሊቃውንት አባቶች በተለይም የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መተርጉማን ‹‹ንግሥተ ሰማይ ወምድር ድንግል ማርያም በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና›› ተሸልማና አጊጣ በሰማያዊው ዓለም በልጇ መንግሥት በክብር መኖሯን የሚያመለክት መሆኑን አስረግጠው አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሰማያዊው አባታቸውን እግዚአብሔርን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት፤ በሰማያት የምትኖር አባታችን›› እያሉ ዘወትር ሲያመሰግኑ፤ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊት እናታቸውን ድንግል ማርያምን ‹‹በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ፤ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ›› እያሉ ዘወትር ያከብሯታል ያመሰግኗታልም፡፡ ሉቃ 1፡28፡፡
 
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዘወትር በምንጸልየው የእሑድ የእመቤታችን ውዳሴ ላይ ‹‹ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር፣ ምልዕተ ውዳሴ የሆንሽ ድንግል ሆይ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልኝ ዘንድ ለአንቺ ይገባል፡፡ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከቅዱሳን ነቢያት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት ከሰብዓ አርድእትም ትበልጫለሽ፡፡ ዳግመኛም ከሱራፌልና ከኪሩቤል ይልቅ የሚበልጥ የመወደድ የመፈራት ግርማ አለሽ፡፡ በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፡፡ ለሰውነታችንም ሕይወትን፣ ድኅነትን የምትለምኚና የምታማልጅን አንቺ ነሽ›› በማለት የእመቤታችን ልዕልናዋን የጸጋዋን ፍጹምነትና የክብሯን ታላቅነት በአጽንኦት ገልጾ መስክሯል፡፡
እመቤታችን በጥር ሃያ አንድ ቀን በታላቅ ክብር ካረፈች በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በፈቃደ እግዚአብሔር ከያሉበት መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የፈጣሪያችን እናት ድንግል ማርያምን በጸሎትና በማዕጠንት አክብረው ገንዘው ጥልቅ በሆነ ኃዘን ሊቀብሯት ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና «ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ ተነሣ እያሉ ሕዝቡን አስኮበለሉ አሁን ደግሞ እናቱን ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያውኩ ሥጋዋን እናቃጥል» በሚል የክፋት ምክር ተነሳሱ፡፡ በተለይም ደግሞ በእመቤታችን ላይ በክፋትና በተንኮል ከተነሳሱት ከእኒህ አይሁድ መካከል ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ
አማናዊት ታቦተ እግዚአብሔር የሆነችው የድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ ያረፈበትን አልጋ ለመያዝ እጁን በድፍረት ዘረጋ፡፡ በዚህን ጊዜ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን (2ኛ ሳሙ 6፡6፤ 1ኛ ዜና 13፡7-10) ላይ የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ እጁን በታቦተ ጽዮን ላይ በድፍረት በመዘርጋቱ ምክንያት ተቆጥቶ እንደቀጣው ታውፋንያንም ሰማያዊው መልአክ ሰይፍ እጆቹን ቀጣው ቆረጠው፡፡ «እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንም (1ኛ ሳሙ 26፡9) እንደተባለ እጆቹም አልጋው ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡
 
ታውፋንያም ስለተቆረጡት እጆቹ ወደ እመቤታችን አምኖ ወደ እርሷ ቢጮህ ቢማጸናት፤ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካይኝነት እጆቹን እንደ ቀድሞ ሆነው ድነውለታል፡፡ በጌታችን ትእዛዝ መልአኩ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥጋ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር በክብር አኑሮታል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ዮሐንስ ከተመለሰ በኋላ ‹‹እመቤታችን እንደምን አለች?›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም «ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ጥር አርፋ በነሐሴ ወር ሁለት ሱባኤ ይዘው ሲጨርሱ በነሐሴ 14 መልአኩ ቅዱስ ሥጋዋን ከገነት አምጥቶ ሰጥቷቸው በጸሎትና በምሕላ ቀብረዋታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም፡፡ በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት አዝኖ ‹‹በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከደመናው ለመውደቅ ተመኘ፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡ ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ሌላ እንዳላየ ነገራው ለምስክር እንዲሆነው ሰበኗን/መግነዝ ሰጥታው ዐረገች፡፡
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ ክብርት እናቱ እመቤታችም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጇ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ ‹‹እንደ ልጅዋ ትንሣኤ›› ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡
ዮሐንስ ንስሐ, [29.01.21 12:18]
ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ምስጢሩን ደብቆ ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› አላቸው፡፡ ሐዋርያትም ‹‹አንተ ተጠራጣሪ ነህ›› ብለው መቃብሩን ሊያሳዩት ሲከፍቱ አጧት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች›› ብሎ ሁኔታውን ተረከላቸው፡፡ ‹‹ለምስክር ይሁንህ›› ብላ የሰጠቸውንም ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን አይተው ትንሣኤዋን አመኑ። ሰበኗን ቆራርጠው ለበረከት ተከፋፍለው ወደየሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል፡፡ ዛሬም በመጾር መስቀልና በካህናት እጅ መስቀላቸው ላይ የሚያስሯት ‹‹መሀረብ›› የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡
 
በዓመቱም ሐዋርያት ‹‹ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን!›› ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ 16 ቀንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አሳርጎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቅዳሴ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገቷን በዓይናቸው አይተውና በሚገባ ተረድተው ዓለምን ዙረው አስተምረዋል፡፡
ስለዚህ የእመቤታችንን ተአምራት ተናግረን የማንጨርሰው ቢሆንም እንኳን፡ – . ወርሃዊ በአሏን በማሰብ በረከት እናገኝ ዘንድ ያህል ለመግለፅ ያህል ስለሆነ የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታታይ ወገኖቻችን ሆይ ይህ ዘመን ከኀጢአታችን ተመልሰን ንስኀ የምንገባበት ፣ የምንሰጥበት፣ በዓሉን በልዩ ልዩ መተጋገዝ የምንገልፅበት እንዲሆንና ሁላችንም እግዚአብሔር ከበረከቱ እንዲሰጠን የምንችለውን የቱሩፋት ስራ ሁሉ እናደርግ ዘንድ ይገባናል።
 
የድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን።
መልአኩን ልኮ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ” (ዳን 3፥28)
 
 
በየአመቱ ታህሳስ 19 የታላቁ መልአክ የ ቅዱስ ገብርኤልን በአል፥ 
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ በዮሐንስ ንስኀ ድረገፃችን የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ፕሮግራም 
የምትከታተለሉ ኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን በሙሉ፤ እንሚታወቀው በየአመቱ ታህሳስ 19 የታላቁ መልአክ የ #ቅዱስ_ገብርኤልን በአል፥ እናከብራለን። ይሄን ትልቅ በአል ለማክበር የምትሳተፉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆናችሁ ሁሉ እገዚኢአብሔር አምላክ ከበአሉ በረከትን እና ድህነትን ያድለን ዘንድ ሁላችሁም በአሉ የሚከበርበትን ምክንያት ማወቅ ትችሉ ዘንድ ይሄንን አጭር ትምህርት ወደእናንተ እንዲደርስ ስላደረግን በፅሞና ተከታተሉ።
 
በአሉ 3 ዋና ዋና ምክንያቶች የያዘ ነው።
 
1ኛ/ የእግዚአብሔርን አዳኝነት
 
2ኛ/ የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት ወይም ታዳጊነት
 
3ኛ/ ሰለስቱ ደቂቅ ከሃይማኖታቸው ፅናት የተነሳ ከእሳት እቶን (የእሳት ነበልባል) መውጣታቸውና መዳናቸው።
 
እነዚግ 3 ዋና ዋና ምክንያቶች የበአሉ መገለጫዎች ናቸው። ታሪኩንም ከዚህ እንደሚከተለው እንመለከታለን።
 
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በተፈጥሮ የመላእከት ወገን ሲሆን ከ7ቱ ሊቃነ መላእከት አንዱ እና ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ታማኝና የእግዚአብሔር ባለሟል መልአክ እንደሆነ ተፅፏል። (ሉቃ 1፥22)
 
የእግዚአብሔር ሰው ታላቁ ነብይ ሄኖክ ስለ ነገረ መላእክት በተናገረበት ትንቢቱ በእባቦች ላይ በገነት በፃድቃን ላይ በከኪሩቤልም ላይ የተሾሙ ከከበሩ መላእክት አንዱ ገብርኤል ነው” በማለት የነገደ መላእክት ላይ የተሾመ የመላዕክት አለቃ እንደሆነ ይገልፃል። (ሄኖ 6፥7) የሹመቱንም ደረጃ በ3ኛው ማዕረግ በመላእክት ሁሉ ላይ የተሾመ ቅዱስ ገብርኤል ነው በማለት የመልአኩን ክብርና የሹመት መአረግ ይነግረናል። (ሄኖ 10፥14) ገብርኤል ማለት የጌታ አገልጋልይ ወይም የጌታ ባለሟል ማለት ሲሆን በሌላም እንደ ቤተክርስቲያን አገላለፅ ገብርኤል የሚለውን ቃል የ2 ቃላት ጥምረት በማድረግ “ገብር” እና “ኤል” ሲሆን ገብር ማለት የአምላክ አገልጋይ ወይም የእግዚአብሔር ልጅን የሚመስል የአምላክ ባለሟልና  መልዕክተኛ ማለት ነው። ይሄንንም ቃል የተወሰደው ነብዩ ዳንኤል ስለ 3ቱ ልጆች የትንቢት ቃል “የዚያን  ጊዜም  ንጉሡ  ናቡከደነፆር  ተደነቀ  ፈጥኖም  ተነሣ፤  አማካሪዎቹንም  ሦስት  ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት፤ እርሱም እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ (የእግዚአብሔርን መልዕክተኛ) ይመስላል ብሎ መለሰ።” በማለት እራሱ እንደመሰከረለት እንመለከታለን። (ዳን 3፥23-26)
 
ስለዚህ በዚህ መሰረት ገብርኤል የሚለው ስም ከመላእኩ አገልግሎት እና የተፈጥሮ ባህሪ አንፃር ትርጓሜ ከዚህ በላይ ያየነውን ይመስላል። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በመሀበረ መላእክት መካከል ፈጣሪያቸው ለቅፅበታዊ ሰዓት በተሰወራቸው ጊዜ በመካከላቸው ሁከትና ብጥብጥ ክህደትና ጥርጣሬ በገባቸው ጊዜ እውነተኛውን ፈጣሪያችንንና አምላካችንን እስከምናገኘውና እስሚገለፅልን ድረስ ሁላችንም በያለንበት ፀንተን እንቁም በማለት በማህበረ መላእክት ዘንድ መረጋጋትን እና ፀጥታን ያወጀ መልአክ ነው።
 
ወደ እለቱ በአል ስንመለስም በፋርስና በባቢሊን ሀገር (በመካከለኛው ምስራቅ) ናቡከነደፆር የተባለው ኃያል ንጉስ በምድር ላይ ማን እንደ እኔ? ብሎ በኃያልነቱና በጉልበቱ በተመካሂቱ ምድርን ያስጨነቀና  እግዚአብሔርን በሚያመልኩትና እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ላይ በጭካኔ ሞትን እየፈረደ ከኔ በቀር ሌላ ገዢም ሆነ ንጉስ የለም ብሎ በትምክህትና በትዕቢት የሰማይን ጣራ ሊነካ የደረሰ እብሪተኛ ንጉስ ነበረ። በዘመኑ ሁሉንም ክፍለ ዓለም በአንድ ላይ እንደብራና ጠቅልዬ በእጄ ውስጥ አስገባለው አገዛዜንም አፀናለው ብሎ ያለምንም ከልካይ ሲንቀሳቀስና የአገዛዝ አድማሱን ለማስፋት ድንበር ጥሶ ከሱ ትዕዛዝ ውጭ የሆኑትን አገሮች እየማረከና  በቅኝ ግዛት ለማስተዳደር በሚያደርገው ሙከራ የእግዚአብሔር ሀገር የሆነችውን ቅድስት ሀገር እየሩሳሌምን እና ህዝቦቿን በመክበብ በዘመኑ እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ ሀገሩ ሲወስዳቸው እሩሳሌምንም እንዳልነበረች አድርጎ እንዳጠፋት ቅዱስ መፅሐፍ ይናገራል። የቤተመቅደስን የከበሩትን ንዋየ ቅዱሳት እንዳጠፋቸውና እንደመዘበራቸው ነብዩ ዳንአል በትንቢቱ ይነግረናል።
 
ይህ ትምክተኛ ንጉስ ናቡከነደፆር በቁመቱ 60 ክንድ ወርዱ 60  ክንድ ነሆነውን ወርቅ ምስል በባቢሎን አውራጀ በዱራሜዳ አቁሞ በሱ ግዛት ስር ያሉ የማረካቸው የእግዚአብሔር ልጆች በአንድ ልቡና መታዘዝ ውስጥ ሆነው ንጉስ ላቆመው ለምስሉ እንዲሰግዱ አዋጅ አወጀ። ይህንን አዋጅ የማይፈፅሙ የንጉሱ ባለሟሎችም ከንጉሱ የተሰጣቸው ስልጣን እንደሚሻሩ እና ትዕዛዙን ተቀብለው ለጣኦቱ ያልሰገደው ሁሉ እስከ ሞት በሚያደርስ ቅጣት እንደሚፈረድባቸው ተወስኗል።  በዚህን ጊዜ በምርኮ ወደ ፋርስ ከሄዱት የዕብራውያን ልጆች መካከል እጅግ አስተዋይ ጥበበኛ የነበሩ በንጉሱ ቤተመንግስት የባቢሎናውያን ቋንቋና ጥበብ እየተማሩ ያደጉ ንጉሱ ዘንድም ባለሟሎች ሆነው ከመወደዳቸው የተነሳ በባበሎን አውራጃዎች የተሾሙ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጎ የተባሉ  ወጣቶች ነበሩ። በንጉሱ አዋጅ መሰረት ንጉሱ ላስቆመው የወርቅ ጣኦት የማይሰግዱ ሁሉ  ወደ ታች ጥልቀቱ እና ወደ ላይም ምጥቀቱ የሚያስፈራና የነጎድጓድ ድምፅ ያለበት ፤ እሳትንም ለማንደድ ተሰጥኦ ካላቸው ዕፅዋትና ፈሳሽ ነገር ሁሉ ተቀላቅሎ በእሳት ውስጥ የተጨመረበት ነበልባል   እንዲነድና የእሱን ትዕዛዝ ያላከበሩ ሁሉ ወደ እሳቱ እንደሚጣሉ አዋጅ ወጥቶ ስለነበረ እነዚህ 3 ወጣቶች (ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጎ) የነደደው እሳትም ሳያስፈራቸው፣ የተሾሙበትም ስልጣን ሳያማርካቸው ለጣኦት አንሰግድም፤ እኛ የምንሰግደው ፍጥረታትን ሁሉ ለፈጠረ የጌቶች ሁሉ ጌታ የነገስታት ሁሉ ንጉስ ፣ የአማልእክት ሁሉ አምላክ ለሆነው ለሰማዩ ንጉስ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ የለንም። እግዚአብሔርን አምላክህን አምልክ ተብሏልና። ሌሎቹ ሰው ሰራሽ ለሆኑ አይን እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፣ እጅ እያላቸው ለማይዳስሱ፣ በሰው እጅ ለተዘጋጁ፣ የሰይጣን መንፈስ ላደረባቸው ለጣኦታት አንሰግድም በማለት በፍጹም እምነት እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው አረጋግጠው የእግዚአብሔርን አምላክነት የሚያስክደውን የንጉሱን ትዕዛዝ አንቀበልም አሉ። በዚያን ጊዜ የንጉሱ የናቡከነደፆር ቁጣ እንደ እሳት ነዶ አማካሪዎቹ በሰለስቱ ደቂቅ ላይ የነበራቸው ጥላቻ የተነሳ ነገሩን እያከበዱና እያባባሱ ለንጉሱ በነገሩት ጊዜ ንጉሱ ጊዜ ሳይሰጥ እነዚህን 3ቱን የእግዚአብሔር አገልጋዮች በአስቸኳይ ወደተዘጋጀው እሳት ውስጥ እንጣለሉ ትዕዛዝ ሰጠ።  የንጉሱ ወታደደሮችና አገልጋዮች ሰለስቱ ደቂቅን የኋሊት አስረው በጭካኔ ወደ እሳቱ ውስጥ ጣሏቸው። የእሳቱንም ነበልባል 7 እጥፍ አድርገው እንዲያነዱት በታዘዘው መሰረት እጅግ የጉድጓዱ ጥልቀት የእሳቱ ነበልባል ልብን የሚያርድና የሚያንቀጠቅጥ ነበር።
 
 እንግዲህ የሰው ልጅ በምድር ላይ በወንድሙና በወገኑ ላይ ሲጨክን ማየት የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው ከምንለው ከሰይጣንም እነኳን ቢሆን ይከፋል ማለት እንችላለን። እነዚህ 3ቱ ወጣቶች እነሱን ለመግደል ቢያስቡ እንኳን ከዚህ ባነሰ ጥፋት መግደል እየቻሉ እንዲህ አይነት ምሳሌ የሌለው የሞት ቅጣት አዘጋጅተው ያለምንም ርህራሄ ወደ እሳቱ ጉድጓድ ሲጥሏቸው ስንመለከት ዛሬም በዘመናችን ያለውን የሰው ልጅ ክፋት ስናይ ከዚሁ ጋር ማነፃፀር እንችላለን። ምክንያቱም ዛሬም ቢሆን ከዛ ዘመን ክፋት የሚብስ በማንኛውም እይታ የሚጨበጥን በምድር ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ኀጢአት የሚፈፅም ሰው ስናይ እጅግ አሳዛኝ ነው።
 
ወደ ተነሳንበት ርዕሳችን ስንመለስ፤ ሰለስቱ ደቂቅ ወደ ነደደው የእሳት ነበልባል በተጣሉ ገዜ እነሱን ይበላል ተብሎ የነደደውን እሳት በርቀት  ሆነው ሲመለከቱ 3ቱ ወጣቶች በእሳት ሲነዱና መራራ ሞትን ሲቀምሱ  ሊመለከቱ በዙርያው ቆመው የነበሩትን ሰወች የእሳቱ ወላፈን ለቃቅሞ እንደ እሳት ጅማት ሲያደርጋቸው እንዲሁም በአካባቢ ያለውን ሳርና ዛፉን ከተማውን ሁሉ አመድ አድርጎታል የእግዚአብሔር ሰዎች 3ቱ ወጣቶች ልክ በቪላ ቤት ውስጥ ወይም በባህር ዋና ላይ እንዳሉ እሳቱ ሳያቃጥላቸው ከመታየታቸውም በላይ በመካከላቸው ደግሞ የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል እጅግ የሚያስደንቅ 4ኛ ሰው ተመለከቱ። ይህም ድግሞ በመግበያችን ላይ እንደገለፅነው ለሰለስቱ ደቂቅ አማላጅነትና ታዳጊነት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው ቅዱስ ገብርኤል ነበር፤ ያን የነደደ እሳት ወደ ውሀነትና ቀዝቃዛ የሆነ ለሰልስቱ ደቂቅ ሊስማማ የሚችል የአየር ፀባይ አድርጎ የእሳቱን ነበልባል ያጠፋው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው።
 
 የእግዚአብር መልአክት ሁሌ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ሆነው በየጊዜውና በየዘመኑ በሰው ኀጢአት ምክንያት በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ጥፋት ወደዚህ አለም የሚመጣውን መቅሰፍት ሁሉ በታዳጊነትና በተራዳይነት መላላክ ቋሚ አገልግሎትና ስራቸው ነው። በዚሁ መሰረት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለሰለስቱ ደቂት የነደደውን የእሳት ነበልባል እንዳያቃጥላቸው ሲያጠፋላቸው፤ አመፀኞቹን ደግሞ በእሳቱ እንዲቃጠሉ ለሰልስቱ ደቂቅ ባዘጋጁት ጥፋት እነሱ እንደጠፉ፣ ባነደዱት እሳት እነሱ እንደነደዱ፣ በቆፈሩት ጉድጓድ እነሱ እንደወደቁ ፣ የተማመኑበትም ጣኦት እንዳላዳናቸው፤ በአንፃሩ ደግሞ በእውነተኛ አምላክ የተማመኑትም ሰለስቱ ደቂቅን እንዴት እንዳዳናቸው እንመለከታለን ማለት ነው።
 
ይሄንን ነገር የተመለከትነውም ናቡከደፆር በጉዳዩ እጅግ ተገርሞና ስለሆነው ነገርም ከባድ ድንጋጤ ስለመጣበት ሃይማኖት ያልነበረው ትምክህተኛና ከኔ በቀር ሃያልስ ማነው?፣ አምላክስ ማነው?፣ ንጉስስ ማነው? ፣ ሁሉስ ከእኔ እጅ ማን ያድነዋል? እያለ ይመካ የነበረው ንጉስ ናቡከነደፆር ከላይ በትምህርታችን ርዕስ ላይ እንደገለፅነው  “መልአኩን ልኮ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ ” በማለትና የእግዚአብሔርን ሀልዎትና አምላክነት፣ ፈጣሪነት ፣ ንጉስነት፣ ዘለዓለማዊነት፣ ሁሉ በራሱ አንደበት መስክሯል ሰለስቱ ደቂቅንም የሚያመልኩት እውነተኛ አምላክ ስለሆነ ከዛሬ ጀምሮ የእነሱ አምላክ የኔ አምላክ ይሆናል ብሏል። ሰለስቱ ደቂቅ እና እብራዊያን ሁሉ ማንም ሳይገድላቸው ፈጣሪያቸውን እንዲያመሰግኑ ንጉሱ ትዕዛዙን ለውጧል።(ዳን 3፥28-30)
 
እንግዲህ ናቡከነደፆር በሰልስቱ ደቂቅ ላይ የተገለፀው የእግዚአብሔር አዳኝነትና ድንቅ ስራ  ተመለክቶ እንዲሁም የቅዱስ ገብርኤልንም ተራዳይነትና ታዳጊነት የሰለስቱ እምነትና ፅናትን ተመልክቶ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር እንደሰጠ ስንመለከት ዛሬም ቢሆን ሰዎች በአንድ ዘመን ኀጢአተኞች ቢሆኑም በስልጣናቸውና በሃብታቸው ቢመኩም ያለማወቅን ዘመን እና የነበሩበትንም የክህደት ጊዜ አሳልፈውና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ እውነተኛው አምላክ እንደ አቡከነደፆር ቢመለሱ የሚጠበቃቸው ውርደት ሳይሆን ክብር ነው። ናቡከነደፆር በሰልስቱ ደቂቅ ላይ የእግዚአብሔርን ክብር ካየ በኋላ ስንመለከት “ከንጉሱ ከናቡከነደፆር በምድር  ሁሉ  ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ ሰላም ይብዛላችሁ፤ ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ፤ ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።” በመለት እግዚአብሔር ስላደረገው ድንቅ ስራና ስለ ተአምራቱም መንግስቱም ለዘለዓለም እንደሆነ ግዛቱም ለልጅ ልጅና ፍፃሜ እንደሌለው ያ አህዛብ የነበረው በአንድ ጊዜ ተገልፆለት ማንም ተናግሮት የማያውቀውን ምስክርነት ሰጥቷል። (ዳን 4፥1-3)
 
ስለዚህ የፕሮግራማችን የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታዮች በዚህ በአል ላይ ጎልቶ የምናየው የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳይነት ነው።ይህ መልአክ ከላይ እንደተገለፀው  ወደ ካህኑ ዘካርያስ በተላከ ጊዜ ካህኑ ዘካርያስ መልአኩም የሚነግረውን አምኖ ለመቀበል በተቸገረ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው እኔ ገብርኤል ነኝ በማለት የመላእክት ቃልና ቋንቋ ከእግዚአብሔር ዘነድ ወደ ሰው የሚመጣውን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ መናገር ስለመሆኑ እራሱ አረጋግጧል። 
 
ይህ መልአክ ወደ እመቤታችን ወደ ድንግል ማርያምም በተላከ ጊዜ ለድንግል ማርያም ያበሰራትን የምስራች ቃል ከእግዚአብሔር የተላከውንና የመጣው ህያው ቃል ነበር። ለሌሎቹ ቅዱሳን ተነግሮ የማያውቅ አዲስ  እና የመጀመርያ ቋንቋ ወይም የብስራት ቃል ነበር። ከእሷ የሚወለደውም አምላክ እንደሆነና ህዝቦችን ከኀጢአታቸው እንዴት ነፃ እንደሚያወጣቸው ለመንግስቱ ፍፃሜ እንደሌለው በወንጌሉ ተፅፎ እናገኘዋለን።
 
ስለዚህ የተከበራችሁ አባላቶቻችን እና ኦርቶዶምክሳዊያን ክርስቲያን ሁላችሁ ከዚህ ከእሳት የመውጣት ቀን በኛ በኦርቶዶክሳዊያን ዘንድ ታላቅ በአል ሆኖ ሲከበር ሁላችንም እንደ እምነት መጠናችን ከገባነበት ልዩ ልዩ ፈተና ለመውጣት መልአኩ በተራዳይነቱ በአማላጅነቱ ያደረገልንን እናስታውሳለን። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአል በአመት 2 ጊዜ በልዩ ስነስርአት እንደምታከብር የተለመደና የታወቀ ነው። በዚህም በአል ላይ በአገራችንና በዓለም ዙሪያ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት የሚያምኑ ሁሉ በቁልቢ ገብርኤልና በሌሎቹም የቅዱስ ገብርኤል በአል በሚከበርባቸው ቅዱሳን ቦታዎች ተገኝተው እየተማፀኑ እየፀለዩ እግዚአብሔር አብዝቶ ከሰጣቸው በረከት ሁሉ መባቸውን ይዘው በመቅረብ፥ ያጡትንና የፈለጉትን ነገሮች ሁሉ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት እንደሚያገኙ አምነው በእምነታቸው ይሳላሉ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በአይኑ ያያቸው፣ በአንደበቱ ያነጋገራቸው፣ በጆሮው የሰማቸው ይመስል ፈጥኖ ሲደርስላቸው በልዮ ልዩ ምስክርነት ማየት የተለመደ ነው። ከተቸገሩበትና ከገቡበት  አዘቅት ውስጥ ሲወጡና መልአኩ ሲታደጋቸውም እንመለከታለን። ብዙ ክርስቲያኖች ከአይምሮ በላይ የሆነውን የእግዚአብሔርን ስራና የመልአኩን ተራዳይነት በቃልና በፅሁፍ ሲገልጹና  ምስክርነት ሲሰጡ ማየትም የተለመደ ሂደት ነው።
 
እንግዲህ ሁላችሁም ባጭሩ ከ3ቱ ደቂቅ ከእሳት መዳን ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል ተራዳይይነት ከእግዚአብሔር ቸርነትና አዳኝነት በረከትን እናገኝ ዘንድ እንዲሁም በዘመናችን በተቃጣብን ልዩ ልዩ ፈተናና መከራ ለመውጣት መልአኩ እንደ ሰለስቱ ደቂቅ እንዲታደገንና እንዲያማልደን ሁላችንም ከቃልና ከንግግር ውጭ ሆነን በፍፁም ልብ ሆነን ለአዳኛችን ለእግዚአብሔር  የልባችንን መሻት እንዲያደርስልን ፣ እንዲያማልደን፣ እንዲታደገን በመንፈሳዊ አካል ቁመን በያለንበት በሀሊና ለመልአኩ ሃሳባችንን እና ልመናችንን ልንነግረው ያስፈልጋል።
 
እግዚአብሔር አምላክ ይሄንን በምድር ላይ የነደደውን የዘመናችንን የመቅሰፍት እሳት እንዲያጠፋልንና ሁላችንንም ከዘመኑ የመቅሰፍት እሳት እንዲያድነን ወደ ፈጣሪ ቀርበን ልንነግረው ያስፈልጋል።
 
ለሁሉም ነገር አምላክ ይጠብቀን የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳይነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን፤ አሜን
ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል (መዝ 91፥12)
 
 
ታህሳስ 24 ቀን የአባታችን የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የተወለዱበት የልደታቸውን በዓል የምናከብርበት ቀን ነው። 
 
የተከበራችና የተወደዳችሁ በዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ የሚተላለፈውን መንፈሰዊ ትምህርት በመከታተል ላይ የምትገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን፤ ከሁሉ በማስቀደም የዘመናት ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እንኳንስ ለአባታችን ለጻድቁ ተክለሃይማኖት አመታዊ የልደት በዓል አደረሳችሁ። ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን የአባታችን የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የተወለዱበት የልደታቸውን በዓል የምናከብርበት ቀን ነው። ለኢትዮጵያ አዲስ ሐዋሪያ ሆነው በአምላካቸው በፈጣሪያቸው ዘንድ የተሾሙ ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ሲሆኑ አባታቸው ጸጋ ዘአብ እናታቸው እግዚእኃረያ ይባላሉ። አባታቸው ጸጋ ዘአብ ትውልዳቸው ከካህናት ወገን እንደሆኑ ገድላቸው ይመሰክራል። አባታቸው ጸጋ ዘአብ እና እናታቸው እግዚእኃረያ ልጅ በማጣት ምክንያት ከፈጣሪያቸው ልመናቸውን ሲያቀርቡ ቆይተው በጨረሻ ሁል ጊዜ የለመኑትን የማይረሳ የነገሩትን የማይዘነጋ እውነተኛ ጻድቅና ታማኝ የሆነው አምላክ በመጨረሻው ዘመን ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ሁሉ በቅድስናውና በሐዋሪያነቱ ብርሃን የሆነውን ልጅ እንዲያገኙ ባርኳቸዋል። የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት መወለድ ልጅ አጥተው ለነበሩት በመጨረሻው የእርጅና ዘመናቸው ልጁን ላገኙት ለእናት ለአባታቸው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሀገራችን እና በልዩ ልዩ የአምልኮ ጣኦት እየተሰቃዩ በሰይጣን ውጊያ ውስጥ ላሉ ህዝበ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው።
 
አባታቸው ካህኑ ፀጋ ዘአብና እናታቸው እግዚእኃረያ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የሃብት ብዛት፣ የእድሜ ብዛት፣ እንዲሁም በቤትና በውጭ በአገልጋይነት ያቆሟቸው አገልጋዮችም ወይም ገንጠሮቻቸው ብዛትና ለነሱ የሚሰጡት ክብር ሳያስደስታቸውና ሳያጓጓቸው ፥ ፈጣሪያቸውን የሚለምኑት ነገር በእግራቸው የሚተካ ትውልድ፣ ሃይማኖታቸውን እና የቀናውን ምግባራቸውን ከነሱ ተቀብሎ ለፈጣሪው የታመነና ከቤተሰቦቹ አደራን ተቀብሎ ታሪክ የሚያስቀጥል ልጅ እንዲሰጣቸው ብቻ አስቀድመው በፈጣሪ ፊት ይማፀኑ እንደነበረ በቤተክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። 
 
እግዚአብሔር የባረካቸው ሰዎች ከምድራዊና ከሃላፊ ሀብትና ንብረት ይልቅ ዘለዓለማዊ የሆነውን ሰማያዊ መንግስት ሊያወርሳቸው የሚችለውን በጎ ነገር መፈለግና መመኘት የተለመደ ነው። እንዲያውም ከዚህ በላይ የሚበልጥ ክብር ከቶ አይኖርም። እነዚህ የጻድቁ ተክለሃይማኖት አባት እና እናት ወደ እግዚአብሔር የሚማፀኑበት ልመናቸው ተቀባይነት ባገኘ ጊዜ ብዙ ልጆችን ከወለዱ ሰዎች ይልቅ እጅግ የላቀውንና የተባረከውን በመጨረሻ አባታችንን ተክለሃይማኖትን በመውለድ የሀዘን ዘመናቸው በደስታ እንዲለወጥ አድርጎታል። 
 
አባታችን ጻድቁ ተክለሃይማኖት የተጸነሱት በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳይነት ከእግዚአብሔር ዘንድ በመጣው ረቂቅ መልዕክት መጋቢት 23 ለ24 አጥቢያ ተጸነሱ። የመፀነሳቸው ምስጢር ለአባታቸውና ለእናታቸው በራዕይ ወይም በህልም ከእግዚአብሔር የተላከላቸውን ምስጢር በመረዳት እግዚአብሔርም በልጅ እንደጎበኛቸው ስለተደረገላቸው የአምላክ ቸርነት ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል። የጻድቁ የአባታችን ተክለሃይማኖት የፅንሰታቸውና የመወለዳቸው ምስጢር በተለያየ መንፈሳዊ ረቂቅ መንገድ እንዲረዱ አድርጓቸዋል። እነሱም ከእግዚአብሔር ወደነሱ የመጣውን ምስጢራዊ ረቂቅ ከተረዱ በኋላ ደግ ልጅ ሊሰጠን ነው ብለው ደስታቸው ከአይምሮ በላይ ሆኗል። እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር አምላክ ስለሆነ የእናታችን የእግዚእኃረያ የፅጽስ ጊዜዋ ሲፈፀም ታሀሳስ 24 ቀን በዚህ እለት ብጹዕ አቡነ ተክለሃይማኖት ብሩህ ሆነው (ብርሀን ተጎናፅፈው) ተወልደዋል። እናት አባታቸውም ሃብታቸውን ንብረታቸውን በመመፅወት እና በበጎ ስራ ወይም በትሩፋት ጨርሰውት ስለነበረ በቤታቸው ውስጥ ተክለሃይማኖት በተወለዱ ቀን ባዶ የነበረው የዘይቱ፣ የቅቤው፣ የማሩ፣ የማሰሮው፣ የማድጋው የእህል ጎተራው እቃ ሁሉ በእግዚአብሔር በረከት ሞልቶ ተገኝቷል። ያንን በበረከት ያገኙትን በቤታቸው የሞላውን ሁሉ እግዚአብሔር ስላደረገላቸው ነገር ሰው ሁሉ የነሱን ደስታ እንዲካፈልና ልጅ የሰጣቸውን ፈጣሪ እንዲያመሰግኑ ጠርተው በማብላት ፈጣሪያቸውን አስመስግነዋል የልጃቸውንም የልደት በአል አክብረዋል ።
 
በዚህ የፃድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት የልደት ቀን ስለሆነ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ በድርሰቱ እንዲህ ሲል የተናገረው ቅዱስ ያሬድ “ተከለሃይማኖት በተወለደበት ቀን ተራሮች ወይም ድንጋዮች ዳቦ ሆኑ፥ የዱር እፅዋትም የበረከት ፍሬን አፈሩ፥ የወንዝ ውሃም ወተትና ማር ሆነ” ሲል በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ መስክሯል። በመሆኑም ታህሳስ 24 ቀን በየአመቱ አባታችን ፃድቁ በተወለዱበት ከብሄረ ቡልጋ በኢቲሳ ገዳም በታላቅ ድምቀት ብዙ ኦርቶዶክሳዊያን ካህናትና ምዕመናን በመገኘት የልደታቸውን በዓል ያከብራሉ። እንዲሁም የምንኩስና ተጋድሏቸውን የፈፀሙበት በደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ በደብረ አሰቦ ገዳም እንዲሁም የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ፅላታቸው ባለበትና በስማቸው ቤተክርስቲያን በተሰራበት ቦታዎች ሁሉ  እጅግ ቁጥሩ ብዙ የሆነ ህዝበ ክርስቲያን ተሰብስቦ በቃልኪዳናቸው እየተማፀነ የልደታቸው በዓል በታላቅ ድምቀትና መንፈሳዊ ስነስርዓት ይከበራል።
 
በአጠቃላይ በሐዋሪያነት ከታወቁ ቅዱሳን እና ፃድቃን አባቶቻችን መካከል ወንጌልን በማድረስ፣ ለጨለመባቸው ብርሀን በመሆን፣  ከኢትዮጵያ እርኩስ መንፈስን በማሰደድ ፣ አምልኮ ጣኦትን በማጥፋት፣ ሃይማኖትን የሚያስክዱ ባለስልጣናትን በመቃወም፣ አብዝተው እየተጋደሉ መከራን የተቀበሉ የሁላችንም የመንፈስ ቅዱስ እና የቃል ኪዳን አባታችን ናቸው። 
 
በርዕሱ ላይ እንደተጠቀሰው ፃድቅ ሰው የሚኖረው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ስለሆነ ፃድቅ ሰው በመንፈስ የሚወልዷቸው ሰዎች በሃይማኖት በምግባር እሱን እንዲመስሉ ስርዓተ ምንኩስናውንና አሰረፍኖቱን የሚከተሉ ብዙ ለፈጣሪያቸው የሚታመኑ መናኒያን በእግሩ ስለሚተካ ዘንባባ ያፈራል የሚለው ቃል ምስጢር ይሄንን የሚገልፅ ነው። 
 
የጻድቁ ቃልኪዳን ሁላችንም በምግባር እንድንበዛ ከእኛ ጋር ጸንቶ እንደሚኖርና የጻድቁ ቃልኪዳን እንደሚረዳን ማመን አለብን።  ጻድቅ የሚለው የቅድስና ስም በከንቱ የተገኘ ስም ሳይሆን የፅድቅ ስራን ሰርተው መላ ዘመናቸውን ሁሉ በገዳማዊ ስርአት በገዳማዊ ህይወት በስርአተ ምንኩስና ተወስነው ድምፀ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ታግሰው  ዳዋ ለብሰው ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው የላመ የጣመ ሳይበሉና ሳይጠጡ ሰውነታቸው አልቆ አጥንታቸው እስከሚቆጠር በፆምና በፀሎት ተወስነው ፈጣሪያቸውን እስከጨረሻው ዘመን እያገለገሉ ለቆሙለት ቅድስት ሃይማኖትና ቤተክርስቲያናቸው እስከሞት ድረስ በመታመን አገልግለው ወደ ጌታቸው የዘለዓለም ደስታ በክብር ከተጠሩም በኋላ የአማላጅነታቸውና የፀሎታቸው ትሩፋት በተሰጣቸው ቃልኪዳን ከእኛ ጋር ለዘለዓለም ፀንቶ ስለሚኖር ሁላችንም በእነዚህ ቅዱሳን ስም ሁልጊዜ እየተማፀንን በየጊዜው ከሚመጣብን ፈተና እንድንጠበቅና ለሰማያዊ መንግስትም እንድንበቃ ያደርገናል።
 
እንግዲህ በፃድቁ ላይ የንቀትና የክህደት የጥርጣሬ የማቃለል ቃል በድፍረት ስለሚናገር ሰው ነብዩ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ተናግሯል “በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።” (መዝ 30፥18)
 
እንግዲህ የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታታይ ኦርቶዶክሳዊያን ሁላችሁም በእያንዳንዱ ቀን ለእኛ በረከት እንድናገኝበት ዘንድ እግዚአብሔር አብዝቶ ቅዱሳንን በቃልኪዳን ስለሰጠን እኛ ደግሞ ገንዘብ ሳናወጣበት፣ ጊዜ ሳንቆጥርበት፣ በጉልበት ሳንደክም በማመልከቻ ሳንጠይቅ እንደው በልግስና ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ልዩ ፀጋ ልንጠቀምበትና ለበረከት ልናውለው ይገባናል። ማንም ሰው በቅዱሳን ስም በሚከብሩበት ቦታ ተገኝቶ በጎ ስራ (የትሩፋት ስራ) ቢሰራ የማያልቀውን በረከት እና የማያልፈውን ሰማያዊ ክብር  ይጎናፀፋል፥ በምድር ላይ ሲኖርም ዘመኑ ህይወቱ ትውልዱ ሁሉ ይባረካል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “እኔን የሚቀበል እናንተን ይቀበላል ፥ እናንተን የተቀበለ እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን የባህሪይ አባቴን ይቀበላል።  ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፥ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፥ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።”(ማቴ 10፥40-42) ማለት በቅዱሳን ስም የምናደርገው በጎ ስራ ወይም የትሩፋት ስራ ዋጋ እንደምናገኝበት ይህ ኃይለ ቃል ይነግረናል።
 
ስለዚህ ቀሪ ዘመናችንን ከፃድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ቃልኪዳን ጋር ተጣብቀን እንድንኖር እግዚአብሔር አምላክ ይርዳን፥ በቸርነቱና በምህረቱ ሁላችንንም ይጠብቀን።
 
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን https://yohannesneseha.org/ ላይ ያገኛሉ
በአለ ልደቱ ለክርስቶስ (በአለ ገና)
 
 
“እነሆ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” (ሉቃ 2፥10:11) 
 
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ በዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ፕሮግራም በመከታተል ላይ የምትገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን እንኳንስ የዓለም መድኀኒት የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ለተወለደበት የልደት ቀን በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን።
እንደሚታወቀው በየአመቱ ታህሳስ 29 ቀን እንዲሁም በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ 28 ቀን የልደቱን በዓል በታላቅ ድምቀትና በልዩ መንፈሳዊ ስነስርዓት የልደቱ በዓል ይከበራል። የበአሉን ታላቅነት በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምሮ መሰረት እንደሚከተለው በአጭሩ እንመልከት፦ 
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አለም ከባህሪይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ የመወለዱ ምስጢርም ከክብሩ እና ከዙፋኑ ከባህሪይ አምላክነቱ ሳያንስ ከባህሪይ አባቱ ከአብ እና ከባህሪይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በእሪና የተካከለ ሁኖ በአንድነት በሦስትነት እየተቀደሰ የሚመሰገንና የሚመለክ አምላክ ሆኖ ሳለ አባታችን አዳም ትዕዛዘ እግዚአብሔርን ተላልፎ እፀበለስ በመብላቱ ምክንያት በሞተ ስጋና እርደተ መቃብር፥ ሞተ ነፍስና እርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ከገነት ከወጣ በኋላ በልጅነት አክብሮ የሚያኖረውን እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ፣ ገነትን ያህል ቦታ አጥቼ ቀረሁ እያለ አብዝቶ ሲያዝን እና መራራ ለቅሶ ሲያለቅስ በፈጣሪው ዘንድ ልመናው ተሰምቶለት ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በ 5 ቀን ተኩል በመስቀል ላይ በምክፍለው ቤዛነት አድንሃለው ብሎ ቃል ገብቶለት ስለነበር በጊዜው የሰጠው የቃል ኪዳኑ ቀጠሮ በደረሰ ጊዜ ከዘመኑ ዘመን ከወሩ ወር ከእለቱ እለት ሳያሳልፍ በገባለት ቃል ኪዳን መሰረት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በድንግል ማሪያም በህቱም ድንግልና ተፀንፆ በህቱም ድንግልና ተወልዷል። የጌታችን የእየሱስ ክረስቶስ የልደቱ ምስጢርም ለእናቱ ድንግል ማርያም የስጋ ተዛምዶ ላለውና በእድሜው አረጋዊ ለሆነ ለዮሴፍ እንዲጠብቃት አደራ ተሰጥቶት ከቤተመቅደስ ተረክቦ ከወሰዳት በኋላ አረጋዊው ዮሴፍ ባልተረዳውና በማያውቀው ምስጢር በግብረ አምላካዊ (በመንፈስ ቅዱስ ስራ) ቀዳማዊ ቃል እየሱስ ክርስቶስ በማህፀንዋ ባደረ ጊዜ ፈጣሪዋን ፀንሳ ተገኝታለች። 
አረጋዊ ዮሴፍም በዚህ መለኮታዊ ግብር ድንግል ማርያም መፀነስዋን ለመረዳት ከሱ የመረዳት አቅም በላይ  ስለበር (ከሱ አይምሮአዊ የመረዳት አቅም በላይ ስለነበረ) እነሆ ድንግል ማርያምን በድንግልናዋ በቅድስናዋ በንፅህናዋ ተከብራ የምትኖር እግዚአብሔር በሁሉ ነገር የቀደሳትና በንፅህና አክብሮ የሚያኖራት እውነተኛ  ድንግልም እንደሆነች ያውቅ ስለነበር ይህ የጽንስ ሚስጥር ከምን እንደመጣ እንዴትም ሊሆን እንደቻለ አብዝቶ እየተጨነቀና እያሰበ ባለበት ሰዓት የዮሴፍን ጭንቀት የተመለከተው እግዚአብሔር መልአኩን ወደሱ ልኮ እንዲህ አለው “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከርሷ የተፀነሰው በመንፈስ ቅዱስ ነውና ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ። እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።” (ማቴ 1፥20-25) በማለት የተነገው የወንጌሉ ኃይለቃል ብዙ ምስጢራትን አጠቃሎ የያዘ ሆኖ እናገኘዋለ። ይህም፦
 
1ኛ/  ድንግል ማርያም የጸነሰነችው በሰው የተፈጥሮ  ልማዳዊ ስርዓት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያስረዳል።
2ኛ/ የድንግል ማርያም የዮሴፍ እጮኛ መሆኗን የሚናገረው ኃይለቃል በዚህ አገላለፅ እጮኛ የሚለው ቃል ሊጠብቃት እና በነገር ሁሉ ሊረዳት፣ ሊታዘዛት፣  ሊንከባከባት ኀላፊነት ወስዶ ተረክቦ በቤቱ ልዩ ስፍራ አዘጋጅቶ የሚያኖራት እና የሚጠብቃት መሆኑን የሚያመለክት ቃል ነው። እጮኛ የሚለው ቃል እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ብዙ ምስጢራዊ አገላለፅ አለው። ለምሳሌ፦
 
– ቅዱስ ጳውሎስ በትምህርቱ ያሳመናቸውን ክርስቲያኖች ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለው ይላል። ይህ ማለት የክርስቶስ ልጆች እንድትሆኑ በክርስቶስ እንድታምኑ በትምህርተ ወንጌል ከእርሱ ጋር አንድ እንድትሆኑ ወይም የሱ ተከታዮች እንድትሆኑ አጭቻችኋለሁ ማለት ነው።
 
– በነብያት ቃል ”እየሩሳሌም ሆይ ፈትቼሻለሁ” የሚል ቃል እናገኛለን። ይህ ቃል እየሩሳሌምን እንደ ሴት እንደምትገባ ሆና ሳይሆን በእግዚአብሔር እና በእሷ መካከል ያለው ቃል እንደሚፈርስ የሚያመለክት ቃል ነው ።
 
–  እጮኛ የሚለው ቃል አሁንም ለሹመት መታጨት፣ ለክህነት መታጨት፣ ለታማኝነት መታጨት፣ ለጓደኝነት መታጨት፣ ለዕውቀት መታጨት እነዚህን ለሚመስሉ መልካም ነገሮች ሁሉ መታጨት እንዳለ በማህበረሰቡ ዘንድም የታወቀ ትውፊት ነው። ስለዚህ እጮኛ የሚለውን ቃል የግድ ከጋብቻ ጋር አያይዘን በተለይ በእመቤታችን እና በዮሴፍ መካከል ከሌላ ስጋዊ አስተሳሰብ ጋር አያይዞ መመልከት ከበጎ ነገር ጠላት ሰይጣን እና የሱ መንፈስ ተገዚ የሆኑ ወገኖች አስተሳሰብ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
 
3ኛ/  ነብዩ ኢሳያስ በትንቢቱ እንደተናገረ ድንግል በድንግልና ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ስሙም አማኑኤል እንደሚባል አማኑኤል የሚለው ተርጉምም እግዘኢአብሔር ከእኛ ጋር የሚል እንደሆነ የተገለፀበት ኃይለቃል ከጌታ ልደት አስቀድሞ 700 ሀርፍተ ዘመን እንደ ግድግዳ ወይም እንደተራራ በፊቱ ቆሞ ሳለ የዘመኑ ርዝመት ሳይከለክለው የድንግል ማርያምን ድንግልናና በድንግልና መጸነስ ከሷ የሚወለደው ሰማያዊ አምላክ በአዲስ ኪዳንም ስሙ አማኑኤል እንደሚባል አማኑኤል ማለትም ትርጓሜው ሰው በአዳኝነት እና በፍቅሩ ከእኛ ጋር መሆኑን እንዲሁም እየሱስ እንደሚባል እየሱስ ማለትም መለኮት መሆኑን ያስረዳል። አረጋዊ ዮሴፍም ድንግል ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ (በእግዚአብሔር መለከታዊ ጥበብ እንደሆነ ተረድቶ ለዚህም ታላቅ ክብር እግዚአብሔር እንደመረጠው ደስ እያለው ሳይፈራ ሳይሳቀቅ በጠባቂነት ከእሱ ጋር ያለችውን እና ፈጣሪዋን የፀነሰችውን ድንግል ማርያምን ወደ አይሁድ አደባባይና ጉባኤ ለመውሰድ እንዳይፈራ በመልአኩ የተረጋገጠ መሆኑን እንመለከታለን። 
 
ከዚህ በኋላ ወደ መጀመሪያው ርዕሳችን ስንመለስ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እለታዊ ምስጢር እነዚህ ናቸው፦
 
በዚያን ጊዜ ከተወለደበት ወቅት አለሙ ሁሉ እንዲፃፍ ማለትም ሁሉም እስራኤላዊያን እንዲመዘገቡ እና አጠቃላይ በቤተ አይሁድ ዘንድ የህዝብ ቆጠራ እንዲደረግ በዚያን ዘመን የነበረው የሮማው ንጉሰ ነገስት ከአውግስጦስ ቄሣር ዘንድ ትዕዛዝ ወጥቶ ነበር በዚያን ጊዜም ሁሉም ቤተ አይሁድ ወይም እስራኤላውያን ሁሉ በየነገዶቻቸውና በየትውልድ ሀረጋቸው ለመቆጠር በተዘጋጀላቸው ህዝብ ቆጠራ ጣቢያ ጉዟቸውን ባቀኑ ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍም ከመልአኩ በተነገረው እመቤታችን ድንግል ማርያምን ይዞ ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ ቤተልሄም ወደምትባል ወደ ይሁዳ ከተማ ወጣ በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደርሶ ስለነበር የእንግዶች ማረፍያ ቦታ ስላልነበራቸው በእንስሳት በረት ልጇን መድኃኒአለምን ወለደች። 
 
ጌታ በተወለደበት በከብቶች በረት ወይም ግርግም አካባቢ ከእንስሳት በስተቀር እና በአካባቢው ከብት ለመጠበቅ ተረኛ ከነበሩ እረኞች በስተቀር ሌላ ምንም አይነት የቅርብ ዘመድም ሆነ ወዳጅ አልነበረም። ዮሴፍ ብቻ ከእግዚአብሔር በተቀበለው አደራ መሰረት የከድንግል ማር ያም አልተለየም። ቅዱስ ሉቃስ ስለ ነገረ ልደቱ እንዲህ በማለት ዘግቦ እናገኘዋለን። “ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥  የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።” በማለት በሆነውን ነገር ሁሉ ያስረዳናል። (ሉቃ 2፥1 7)
 
ድንግል ማርያምም ህፃኑን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በወለደች ጊዜ የመውለዷ ምስጢር የሴቶች ልማድ ሳያገኛት ይህ ማለት የደም መፍሰስ ሳያገኛት፣ የምጥ ህማም ሳይሰማት፣ ማህተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ወልዳዋለች። ይህም ደግሞ ልደቱን ያለዘር ያለ ሩካቤ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ያ ማለት ቅድመ አለም ያለ እናት የተወለደውን ቀዳማዊ ልደቱን፥ ድረአለም ያለ አባት ያለዘርና የለሩካቤ ከድንግል ማርያም የመወለዱን ምስጢር ያስረዳል። ሰለስቱ በሃይማኖት አበው እንደተናገሩት ፊተኛው ልደት በኋለኛው ልደት ታወቀ እንዲሉ፥ በዚያም ጌታ በተወለደበት በከብቶቹ በረት አካባቢ ዮሴፍ ባዘጋጀትላት ጊዜያዊ የዳስ መጠለያ በወለደች ጊዜ ህፃኑን የምታለብሰው እና እርቃኑን የምትሸፍንበት እንዳልነበራት እና በመንገድ ጉዞ ያለና በእንግድነት  ያለ እንግዳ እንኳንስ መውለድ ቀርቶ በሰላም አድሮ ለመሄድ ብዙ የማይመች ነገር እንደሚያጋጥመው ሁሉ እሷም ሁሉም ነገር ፈጥሮ ያዘጋጀ የባለሃብቶችን የባለስልጣናቱን ቤት ሁሉ በሃብት እና በልዩ ልዩ በረከት አትረፍርፎ የሞላ የሀብታሞችና የነገስታትን ልጆች በተሻለ ቤተመንግስትና በቪላ ቤቶቻቸው እንዲወለዱ ከመወለዳቸው ቀን አስቀድሞ በልደታቸው የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ያስቻለ በአጠቃላይ ፍጥረታትን ሁሉ በየስነፍጥረታቸው እንዲከብሩ ያደረገ አምላክ እሱ ግን ማረፍያ ቦታ አጥቶ የሚለብሰው ልብስ ጠፍቶ በከብቶች በረት መወለዱና በእፅዋት ቅጠል ተጠቅልሎ እንደተገኘ ስናስብ ምን ያህል እንደወደደንና የኛን ውርደት በሱ ክብር እንደለወጠና ወደ የልጅነት ክብራችንንም እንዴት ሊመልሰን እንደቻለ እንደረዳለን።
 
በልደቱ ቀን የታዩ አስዳናቂ ተአምራት እንደሚከተለው እንመለከታለን፦
 
1ኛ/  በሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞችና የሰማይ መላእክት በአንድ ላይ ሆነው ሲዘምሩ መታየታቸው
2ኛ/  ጌታ በተወለደበት ቀን እና አካባቢ በዙርያው የእግዚአብር ክብር እንደተገለፀ 
3ኛ/  የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ጌታ ልደት መልክት ገልፆ መናገሩ 
4ኛ/  ብዙ የሰማይ ሰራዊትም ከመልአኩ ጋር ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በአርያም ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን ሰላም በሰው ልጆችና በምድር ላይ ሁን እያሉ መግለፃቸውን ተመልክተናል 
5ኛ/ በመልአኩ አስረጅነት እረኞች ወደ ቤተልሄም ጌታ ከተወለደበት ቦታ ተነስተው የሆነውን ነገር ሁሉ ለህዝቡ ስላዩትና ስለሰሙት መግለፃቸውንም እንመለከታለን። 
6ኛ/ ለጌታ የቀረቡለትን የሰባ ሰገል ስጦታ አመሀ በኮከብ ምልክት የተመሩ የሩቅ ሀገር ነገስታት በዘመናቸው ለተወለደው የሰማይና የምድር ሁሉ ንጉስ ለሆነው አምላካቸው በእግዚአብሔር ልዩ አሰራር ነገሩን በምስጢር ተረድተው የአይሁድ ንጉስ መቼ፣ ለምን፣ በየት፣ በማን እንደሚወለድ ምልክቱንና ምስጢሩን ተረድተው በአባቶቻቸው ዘንድ አደራ ተሰጥቷቸው የሱን መወለድ ይጠባበቁ የነበረበትን ልዩ ገፀበረከት (ስጦታ) ይዘው በፊቱ ቀርበው እየሰገዱለት ወርቅ እጣን እና ከርቤ እንደገበሩለት ተመልክተናል።  እነዚህ በምድር ላይ ስማቸውና ክብራቸው ከፍ ያለ ማንነታቸው የገነነ ነገስታት ጌታ ወደተወለደበት በረት ተጉዘው የጌቶች ጌታ የነገስታት ንጉስ የአማልእክት አምላክ የተወለደ መሆኑንና ለሱ ስጦታ መገዛታቸው ለአምላክነቱ ከቶ የማይገዛ እንደሌለ ትልቅ ማስረጃ ናቸው። (ማቴ2፥1-12)
6ኛ/ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወለደው እንደ ሰው ልደት በአጋጣሚ ወይም እንደ እንግደ ደራሽ ሆኖ ሳይታሰብና ሳይታቀድ ሳይሆን አስቀድሞ እንዴት እና በምን፣ በማን ተፀንሶ እንደሚወለድ በነብያት ላይ አድሮ ትንቢት አናግሯል። እነሱም፦
– ነብየ እግዚአብሔር ኢሳያስ በትንቢቱ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” (ኢሳ 7፥14) እንዲሁም “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ 9፥6:7) በማለት ድንግል ማርያም በድንግልና ፀንሳ ፈጣሪዋን እንደምትወለድና እሱም የዘላለም አምላክና ንጉስ እንደሆነ አለቅነት እና ስልጣን ሁሉ የባህሪይው መሆኑን ይህ የነብዩ ቃል ያመለክታል።
-ነብየ እግዚአብሔር ሚክያስ በተናገረው ትንቢቱ “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልና”(ሚክ 5፥2) በማለት በቤተልሄም በኤፍራታ እንደሚወለድ ያስረዳናል። ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ”እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው።” በማለት የቤተልሄም እጣ በምትሆነው በኤፍራታ በዛፍ ስር በኤፍራታ በምትሆን በዛፍ ስር ወይም በከብቶች በረት አካባቢ የመወለዱን ምስጢር ነግሮናል። 
ሌሎችም ነብያት በተለያየ ምስጢራዊ አገላለፅ የጌታን መወለድ በትንቢታቸው ተናግረውታል ፥ምሳሌም መስለውለታል። 
 
እንግዲህ የጌታ ልደት የአዲስ ኪዳን መሰረት እና መጀመሪያ ስለሆነ እኛ ሁላችንም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች ከልደቱ ያገኘናቸውን ስጦታዎች እንመልከት፦  
 
1ኛ ሰላም፦ በልደቱ ሰላምን አግኝተናል። እንደሚታወቀው በአባታችን በአዳም በመጣው ኀጢአት ምክንያት የሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው፣ ከሰማይ መላእክት፣ ከራሳቸውም ጋር፣ ከምድር ፍጥረታት ሁሉ ጠበኞች  ነበሩ። በመካከላቸውም ሰላም አልነበራቸውም።ይሁን እንጂ የሰላም አምላክ መድኃኒአለም እየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ የመጀመሪያው የመላዕክት ስብከት ለሰው ልጆች ሰላም ይሆን ዘንድ ነበር። ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዳስተማረው “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ” በማለት የጥል ግድግዳን አፈርሶ በልደቱ ሰላምን እንዳጎናፀፈን የሐዋርያው መልዕክት ያመለክታል። (ኤፌ 2፥14-16) 
 
2ኛ የእግዚአብሔርን ልጅነት፦ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን በልደቱ ተመልሶልናል። በኀጢአት ምክንያት ተወስዶ የነበረው የልጅነት ክብራችን በሱ ልደት ዳግም የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ስልጣን ተሰጥቶናል። ወንጌላዊ ዮሐንስ በቅዱስ ወንጌል “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” በማለት ዳግም በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን በመንፈስ መወለዳችንን እና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይህ የወንጌል ቃል ያመለክታል (ዮሐ1፥12-13) 
 
በጌታ ልደት የሰው ልጆች የመንፈስ ነፃነታቸውን (የነፍስ ነፃነታቸውን አግኝተውበታል) በኀጢአት መክንያት የተወሰደውን የሰው ልጅ ነፃነታቸው ተገፎ የሰይጣን ባሪያዎች ሆነው በነፍስ ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው 5500 ዘመን በኀጢአት በርነት ይማቅቁ ስለነበር ጌታ በተወለደበት እለት የተወሰደው የልጅነት ነፃነት ክብር እንደተመለሰላቸው ተረጋግጧል። ቅዱስ ጳውሎስ በገላያት አገር ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በፀጻፈላቸው መልዕክቱ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።” በማለት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ያገኘውን ነፃነት እንዲያጣ ተመልሶም የኀጢአት ባርያ እንዳይሆን አስረግጦ መክሮናል። (ገላ5፥1)
 
3ኛ ፍቅር፦ ፍጹም እና እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር በጌታ ልደት አግኝተናል። ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ስጋን መዋሃድ ያስፈለገበት ሰውን አክሎ ካለኀጢአት በስተቀር የሰው ስራ ሰርቶ የሰው ልጅ የተቀበለውን መከራ ሁሉ ተቀብሎ እንዲሁም ሰው ሊሸከመው የማይችለውን ሁሉ በተዋሀደው ስጋ ተቀብሎ ፍጹም ፍቅሩን አረጋግጧል። አባ ህርያቆስ በቅዳሴው ላይ “ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከሞትም አደረሰው” በማለት እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ በመንበረ ፀባኦት በዘፋኑ ላይ ሆኖ ምሬሃለው ማለት ሲችል እውነተኛ ፍቅሩን እንደሚያረጋግጥለት ዘንድ ለአምላክነት ባህሪይው የማይስማማውን መርጦ ተወሰነ ፣ ተወለደ፣ ስጋን ተዋሃደ ፣ በየጥቂቱ አደገ፣ በምድር ላይ ተመላለሰ፣ ተጠመቀ፣ ዞሮ አስተማረ፣ ተራበ፣ ተጠማ፣ ታመመ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ፣ ተቀበረ፣ የሚሉትን የደካማ ሥጋ ባህሪይ የሆኑትን እንደሰውነቱ ገንዘቡ አድርጎ ፍፁም ፍቅሩን ለሰው ልጅ አረጋግጧል። ይህ ደግሞ ክርስቶስ ፍቅር የተጀመረውና መሰረት የተጣለው በልደቱ ቀን ነው። እንስሶችም እንኳን ሳይቀሩ በተፈጥሯቸው ባገኙት ፀጋ ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ በእስትንፋሳቸው ፍቅራቸውን ሲገልፁ ተመልክተናል። ሰውና መልአክም በተፈጥሮ እንኳን የማያገናኛቸው፥ በክርስቶስ ልደት አንድ ሆነው በፍፁም ፍቅር እና ክብር አምላክነቱን ሲገልፁ ተመልክተናል። ቅዱስ ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ እውነተኛው የጌታ ፍቅር ሲናገር “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” በማለት የግዚአብሔር እውነተኛ ፍቅር የተገለፀው በጌታ ሰው መሆን ወይም ስጋን መዋሃድ መሆኑን ይህ ኃይለቃል ያረጋግጥልናል (ዮሐ3፥16)
 
በጌታ ልደት በአጠቃላይ 500 ዘመን አጥተነው ነበረውን በጥንተ ተፈጥሮ ከፈጣሪ ዘንድ በልግስና ተሰጥተውን የነበሩትን ፀጋዎች ሁሉ አግኝተናቸዋል። በጌታ ልደት አይደለም እሱን (ሰውን) ለማዳን ለተወለደበት ሰው ለሆነለት ስጋን ለተዋሃደለት ለሰው ልጅ ቀርቶ በደማዊ ለሚንቀሳቀሱ ግኡዛን ፍጥረታት ሁሉ ክብሩን በነሱ ገልፇል። ለምሳሌ መፃህፍት እንደሚነግሩን በጌታ በልደቱ ተራሮችና አለቶች (ድንጋዮች) ሁሉ ዳቦ ሆነዋል፣ የዱር እፅዋትም የበረከት ፍሬን አፍርተዋል፣ ፈሳሾች ወተትና ማር  ሆነዋል፣ የዱር አራዊትና የቤት እንስሳትም ሁሉ በደስታ ዘለዋል፣ እንዲያውም ጌታ በተወለደበት በረት የነበሩ እንስሳት እስትንፋሳቸውን ገብረዋል። በዚህ ሁሉና ጌታ የልደቱ ምስጢር ሲገልፅ ስናይ እሱ ከሁሉ ባነሰና ድሆች እንኳን ሳይቀሩ በማይወለዱበት ስፍራ መወለዱን ስንመለከት የእኛን ውርደት ለእሱ ወስዶ የሱን ክብር ለእኛ እንዳጎናፀፈልን አረጋግጠናል። ሰው መሆንን የመረጠ እሱ በራሱ ፈቃድ እንጂ እኛ አስገድደነው ሰው እንዲሆንልን ለምነነው አይደለም። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ይደንቃል ይረቃል የሚባለው ለዚህ ነው። 
 
በአጠቃላይ በልደቱ በማያምኑም በሚያምኑም ዘንድ የተገለፀው ክብሩን ስንመለከት እግዚአብሔር ሁሌም በጊዜውም ያለጊዜውም  ለሰው ልጅ መዳን እና በክብር መኖር አብልጦ ምን ያህል እንደሚያስብልን እና ምን ያህል ጊዜ እንደሚያዘጋጅልን በዚህ ምስጢር አረጋግጠናል።
 
ከልደቱ መማር ያለብንን እና እኛ ከልደቱ በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን  ብለን ማሰብ ይገባናል። ምክንያቱም ከላይ አንደገለፅነው በበረት ውስጥ ያሉ እንስሳት  ለጌታ እስትንፋስ ሲሰጡ በዚያ በቁር ዘመን የሚበላ የሚለበስ የሚሞቅ መጠለያ በሌለበት በሜዳ ላይ እራቁቱን ተወልዶ ያዩትን ጌታቸውን (ፈጣሪያቸውን) ሌላ ማድረግ እንኳን ባይችሉ እስትንፋሳቸውን ሲያቀብሉት፣ አመሀ አድርገው ሲገብሩለት እኛን የእያንዳንዳችንን ህይወት አስበን ከዚህ በላይ ለሱ ክብር ማድረግ እየቻልን ያላደረግነውን ስናስብ እውን ሰው ከእንስሳት ያንሳል እንዴ? ብንል መሳሳት አይሆንም። ሰው ሰው መሆን ሲያቅተው ወይም ሰው ሆኖ መቀጠል ቢያቅተው እግዚአብሔር እራሱ ሰው ሆኖ ስጋን ተዋህዶ መጣ። እኛ ሰዎች ደግሞ ሰው መሆናችንን በራሳችን ብናጣው ሰው በሆነው ክርስቶስ ላይ በበረት አገኘነው። እንደገናም ሰው እንድንሆን የክርስቶስ ሰው መሆን ዳግም አስተማረን። ዳግም ሰው እንድንሆን በመንፈስ ወለደን። ስለዚህ እኛ ሰው ያልሆንበትና እግዚአብሔርን ያሳዘንበት የተለያዩ የክፋት ስራ ስላለብን የጌታን ልደት በትክክለኛ ልጅነት መንፈስ ለማክበርም ሆነ ልጅነታችንን ተቀብለን ማድረግ ያለብን መታዘዝን ልንፈፅም ይገባናል። ምን ማድረግ እንዳለብን ማንም ሳይነግረን ህሊናችን የሚነግረን ነገር አለ። በእርግጥም ቤተክርስቲያን እና የሃይማኖት መምህራን ሰው ሆነን እንድንገኝና ምን ማድረግ እንዳለብን ዘወትር ሲነግሩን ኖረዋል። ታድያ በዚህ ዘመን ሰው ሰው ቢሆን ኖሮ እጅግ ተፈጥሮን በሚያስጠላና አሳዛኝ እና አስፈሪ በሆነ ድርጊት ሰው ሰውን ሲያሰቃየው ሲገድለው ሲያሳድደው አንመለከትም ነበር። ክርስቶስ ፍጹም ፍቅር ነው ካልን፣ የክርስቶስን ልደት እናከብራለን ካልን ክርስቶስ ደግሞ ለሚያምነው ሁሉ እውነተኛ የፍቅር አምላክ ከሆነ እሱ ደግሞ ሰዎች በፍቅር እና በሰላም እንዲኖሩ የሚፈቅድ ከሆነ፥ የሰው ልጆች ይህንን የተቀበሉትን ሰላም እና ፍቅር በሚጠፋፉበትና ፍርድን በሚያመጡበት የሰይጣን ስራ መተባበር  የለባቸውምና እንግዲህ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታታይ ወገኖቻችን ሆይ ይህ ዘመን ከኀጢአታችን ተመልሰን ንስኀ የምንገባበት ፣ የምንሰጥበት፣ ልደቱን በልዩ ልዩ መተጋገዝ የምንገልፅበት እንዲሆንና ሁላችንም እግዚአብሔር ከበረከቱ እንዲሰጠን የምንችለውን ሁሉ እናደርግ ዘንድ ይገባናል።
 
ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር አምላክ የዘንድሮን የልደት በዓል እንድናከብር የረዳን እሱ ስለሆነ ቀጣዩን አመት ደግሞ እንድናከብር የከርሞ ሰው ይበለን።
 
“ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው” (ዘፍ11፥7)
 
 
(ጥር 7 ቀን ለሚከበረው አመታዊ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል)
 
የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላት በሙሉ፥ የፍጥረታት ሁሉ ባለቤት አጋዕዝተ አለም ቅድስት ሥላሴ እንኳንስ ለጥር 7 ቀን ለሚከበረው አመታዊ የሥላሴ ክብረ በዓል አደረሳችሁ። በዚህ እለት ስለሚከበረው የቅድስት ሥላሴ አመታዊ በዓል አጭር ትምሀርት ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን፦
 
በመሰረቱ ስለ ቅድስት ሥላሴ መናገር ወይም ማስተማር በፍጡር አንደበት የማይደፈርና  ከአይምሮ በላይ የሆነ ምስጢር ስለሆነ እፁብ ድንቅ ብለን በአንክሮና በተዘክሮ የምናምን የምንመሰክረው ቢሆንም እንኳን እግዚአብሔር አይምሯችንን እና አይነ ህሊናችንን ከፍቶ የገለፀልንን ያህል እንመሰክራለን። በዚህ ጥር 7 ቀን የሚከበረው ስለአጋዕዝተ አለም ቅድስት ሥላሴ ከመናገራችን በፊት ማንኛውም ሃይማኖት ያለው ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ መመስከር ያለበት ስለ ምስጢረ ሥላሴ መሆን ስላለበት ከዚህ በፊት ሐምሌ 7 ቀን የሚከበረውን የቅድስት ሥላሴ በዓል ምክንያት በማድረግ ስለ ሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት የሚያስተላልፈውን የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት እያስታወስን ዛሬም ቢሆን ከምስጢረ ሥላሴ ትምህርት በላይ የምናስቀድመው እና የሚበልጥብን ምንም አይነት የሃይማኖት ምስጢር ባለመኖሩ ወደ እለቱ የበአሉ ታሪክ እና ሃተታ ከመግባታችን በፊት በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን ስለሚስጥረ ሥላሴ መፅሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚናገር እንመለከታለን።
 
1ኛ/ በብሉይ ከዳን ስለ ምስጢረ ሥላሴ የተነገረውን ኀይለቃል በማስመልከት፦
 
1. “እግዚአብሔርም  አለ፥  ሰውን  በመልካችን  እንደ  ምሳሌአችን  እንፍጠር” በማለት ‘እግዚአብሔር  አለ’ የሚለው ቃል የአንድነትን ምስጢር የሚያመለክት ሲሆን  ‘ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር’ የሚለው ቃል ደግሞ ከአንድ በላይ የሚያመለክት ሲሆን የሦስትነትን ምስጢር ያስረዳል። (ኦሪ ዘፍ 1፥6)
 
2.  “እግዚአብሔር አምላክም አለ ፥  እነሆ አዳም መልካምንና  ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለውን ቃል ስንመለከት ‘እግዚአብሔር አምላክ አለ’ የሚለው አንድነትን፣ ‘አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ’ የሚለው ደግሞ የ ሦስትነትን ምስጢር የሚገልፅ ሆኖ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ከአዳም ዘር መወለዱን እና ሥጋ መዋሃዱን የሚያመለክት ምስጢር ነው።
 
3.  እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም ረዳቱ የምትሆነውን ሄዋንን ለመፍጠር መለኮታዊ ፈቃዱ በሆነ ጊዜ “እግዚአብሔር አምላክ አለ፤ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት  እንፍጠርለት” በሚለው ኀይለቃል የእግዚአብሔርን የአንድነት እና የሦስትነት ምስጢር መረዳት እንችላለን።
 
4.  በትምህርታችን መነሻ ርዐስ አድርገን  የመረጥነው  ኀይለቃልም “ኑ፥  እንውረድ፤  አንዱ የአንዱን  ነገር  እንዳይሰማው  ቋንቋቸውን  በዚያ  እንደባልቀው”  ‘ኑ፥ እንውረድ’ የሚለው ቃል የሥላሴን ሦስትነት የሚያመለክት ቃል ነው። (ዘፍ11፥7)
 
5. አባታችን አብርሀም በመምሪ አድባር ዛፍ በተገለፁለት ጊዜ ፤ ሦስት በእድሜ ሽማግሌ የሆኑ የተከበሩ ሰዎችን ባገኘ ጊዜ እንግዳ በመቀበል በረከት ለማግኘት ከነበረው ጉጉት አንፃር ወደ ቤቱ ይገቡለት ዘንድ የክብር ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ ጌቶች ሆይ ወደቤቴ ግቡ በማለት  ያቀረበውን የክብር መስተንግዶ ተቀብለው ከእሱ ጋር ማዕድ እንደቆረሱ ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል። አባታችን አብርሐም ከመምሬ ዛፍ እግዚአብሔር እንደተገለፀለት የሚገልፅ ሲሆን በመቀበሉም እግዚአብሔር አንድም ሦስትም እንደሆነ የሥላሤን አንድነት እና ሦስትነት እንዲያውቅ ስለተፈቀደለት ሦስቱም ሥላሴ በቤቱ እንደተገኙለት ቅዱስ መፅሐፍ ያስረዳል። (ኦሪ ዘፍ 18፥1-8)
 
6. እንዲሁም ነብየ እግዚአብሔር ኢሳያስ ሦስትነትን ሲገልፅ “አንዱም ለአንዱ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ፥ቅዱስ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮህ ነበረ” የሚለው ኀይለቃል የሚያመለክተው የስላሴን አንድነት እና ሦስትነት ነው። (ኢሳ 6፥3)
 
2ኛ/ በአዲስ ኪዳን የሥላሴ ሦስትነት በብዙ ቦታ ተገልፆ እንመለከታለን
 
1. “ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወለድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለው ቃል አንድነትን ሦስትነትን የሚገልፅ ኀይለ ቃል ነው። (ማቴ 28፥19)
 
2 “እኔ እና አብ አንድ ነን እኔን ያየ አብን አይቷል፥ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን” ‘እኔ በአብ እንዳለሁ’ የሚለው ቃል የአብን የወልድን የመንፈስ ቅዱስን ሦስትነት እና አንድነት የሚያመለክት ነው። (ዮሐ14፥9:10)
 
በአጠቃላይ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ስለሚስጥረ ሥላሴ በብዙ ሁኔታ ተገልፆ የምናገኘው ኀይለቃል እጅግ ረቂቅ እና ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ ለብዙዎች የማይረዳ ምስጢር ቢሆንም እንኳን እውነተኛ ለሆኑ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በልዩ መለኮታዊ ጥበብ በተሰጠን የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የምንረዳው ነው። ጠቅለል ባለ አገላለፅ የሥላሴ ሦስትነታቸው በምን እና በምን ተብሎ ቢጠየቅ፦ ሦስትነታቸው በስም፣ በግብር፣ በአካል ሲሆን አንድነታቸው ደግሞ በባህሪይ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በስልጣን፣ በፈቃድ፣ ይህንን አለምና የማይታየውን አለም በመፍጠር እና በማሳለፍ ነው፦
 
የሥላሴን  የአንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን የማያምን ክርስቲያን  የኀጢአት ስርየትን እና ተስፋ መንግስተ ሰማያን ፈፅሞ ሊያገኝ አይችልም። ሥላሴ የሚታየውን እና የማይታየውን ሁሉ ፍጥረት ካለመኖር ወደ መኖር አምጥተው የፈጠሩ ህማም ድካም የማይሰማቸው፣ በሞት የማይለወጡ፣ ዘለዐለማዊ ሀልዎት ያላቸው፣ ገዢ ፈጣሪ ናቸው። ሥላሴ አለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ባህሪያቸው ባህሪያቸውን ሲያመሰግን የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖር ሲሆን ሆኖም  ክብራቸው በባህሪያቸው እንዳይቀር አውቀው ሰውና መላዕክትን ስማቸውን ለመወደስ ክብራቸውን ለመውረስ እንደፈጠሩ በቅዱሳን መፃህፍት ያስረዳናል። ሌላውን ስነፍጥረት ግን ለአንክሮ፣ ለተዘክሮ፣ ለምግበ ስጋ ፣ለምግበ ነፍስ ፣እንዲደፈጠሩ እንረዳለን። የሰውን ልጅ በምድር ላይ ለተፈጠሩ ፍጥረታት ሁሉ በኩርና ገዢ አድርገው ሹመውታል። (መዝ8፥6)
 
የመጀመሪያው ሰው አዳም እና ሄዋን በገነት 7 አመት ከ 1 ወር ከ17 ቀን ኑረው እፀበለስን ቀጥፈው በመብላታቸው ምክንያት ከርስታቸው ከገነት ተባረው በምድረ ኤልዳ ተቀምጠዋል። (ኩፋ5፥6)
 
በዚያም በስደት ባረፉበት ቦታ በዝተው ወልደው ተዋልደው ምድርን እንዲሞሏት በሥላሴ ዘንድም ተፈቅዶላቸዋል።
 
የአዳም 10ኛ ትውልድ የሆነው ፃድቁ አባታችን ኖህ በዘመኑ የሰው ልጆች ምድርን በኀጢአት ስላረከሷት አጋዕዝተ ሥላሴ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እና ንጉስ ሥላሴ፥ ኖህን እና ቤተሰቦቹን ከጥፋት ውሀ አስቀርተው ሌላው የሰው ልጅ እና ፍጥረታት ሁሉ በንፍር ውሀ ጠፍተዋል። (ዘፍ8፥15)
 
ከጥፋት ውሀ በኋላ የኖህ ልጆች በስነ ተዋልዶ በዝተው ምድርን እንዲሞሏት ዳግም እግዚአብሔር ባርኳቸዋል። በባቢሎን ምድር የነበሩት የትውልደ ኖህ የኖህ ልጆች በሰናኦር ምድር እጅግ ሰፊና ምቹ የሆነ ሜዳ አግኝተው ሳንሞት ስማችንን ሊያስጠራ የሚያስችል ፅኑ ግንብ እንስራ ብለው በዓመፃ ተነሳስተው በመከሩት የኀጢአት ምክር ታላቅ የሆነ ግንብ ሰሩ፤ አለቃቸውም ላምሩድ ይባል ነበር። ላምሩድም እጅግ ሃያልና አርበኛ አዳኝም ነበረ። ከዚህ የተነሳ በምድር ላይ ካሉ ነገደ አህዛብ ሁሉ አለቃቸው ስለነበረ እሱም በምድር ላይ ማን እንደ እኔ በማለት የእግዚአብሔርን ሀልዎት ስቶ ፈጣሪን የተፈታተነ እብሪተኛና የአመፅ ሰው ነበር። በላምሩድ የአመፅ ስራና የክህደት ስራ የተባበሩ ተከታዮቹ ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸውና እነሱን ተዋግተን ሞትን ድል እናደርጋለን ወደ እኛም የሚመጣውን ጥፋት ሁሉ እንቋቋማለን በሚል ከንቱ የሆነ ፍጥረታዊና ደካማ አስተሳሰብ ተሳስተው የግብር አባታቸው ዲያብሎስ ከክህደት መንገዳቸው እንዳይመለሱ ሃሳባቸውን በጥፋት መንገድ ስላጠናከረባቸው የማይቻለውን ታግለው የማይጥሉትን፣ ተዋግተው የማያሸንፉትን አምላክ እየተገዳደሩ በክህደት ሜዳ ላይ በአመፅ ተሰባስበው ጦር እየሰበቁ ፈጣሪያቸውን ለመውጋት እና ለመቋቋም አመፅን አስነሱ። የሚሰብቁትም ጦርም ሥላሴን ለመዋጋት አስበው ጦራቸውን ይወረውሩ ነበር፦ በክፉ ግብሩ የሚተባበራቸው እርኩስ መንፈስ ሰይጣንም ከደመና ላይ በምትሃታዊ ስራው የሚወረውሩትን የጦር ፍላፃ ደም እየቀባ ይወረውርላቸው ነበር። እነርሱም የወረወሩትን የደም ጦር እያዩ አሁን አብን ወጋነው፣ አሁን ወልድን ወጋነው በማለት በክህደት መንገዳቸው ፀንተው ይዋጉ ነበር። አጋዕዝተ አለም ቅድስት ሥላሴ ምንም እንኳን ቸርነታቸውና ምህረታቸው የበዛ ቢሆንም ሰይጣን ምን ያህል የሰውን ልጅ ህይወት ድል እንደነሳቸው በተመለከቱ ጊዜ “ኑ እንውረድ አንዱን የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን እንደባልቀው” በማለት የምድር አህዛብ ሁሉ በዘመናቸው አንድ አይነት ቋንቋ እና ባህል የነበራቸው ሆኖ ሳለ በፈጣሪያቸው ለይ የፈፀሙት የአመፅ ስራ ወይም የክህደት ምክንያት የነበራቸውን አንድ አይነት ቋንቋ ደበላለቀባቸው፣ መደማመጥም፣ መግባባትም፣ መናበብም፣ መስማማትም ተሳናቸው። አንዱ የአንዱን ቋንቋ እንዳልተረዳው ግራ እየተጋቡ ለማይሆን ነገር አልፈው ተሰጡ። ለምሳሌ ስማቸውን ያስጠሩ ዘንድ ከሰማይ አምላክ አጋዕዝተ አለም ቅዱስ ሥላሴ ጋር ለመዋጋት ሰልፍ ወጥተው ፈጣሪያቸው ላይ ሊቋቋሙ በክህደት መንፈስ ሰፊ በሆነ በሰናፆር ሜዳ ላይ የገነቡት ሰማይ ጠቀስ ግንብ ላይ በሚያደርጉት የግንባታ ስራ ላይ ውሀ አምጣልኝ ሲለው ጭቃ ያመጣለታል፣ ጭቃ አምጣልኝ ሲለው ድንጋይ ያማለታል፣ ድንገይ አምጣልኝ ሲለው እንጨት ያመጣለታል።
 
በአጠቃላይ እየንዳንዱ የሚናገረው ቋንቋ ለአንዱ የማይደመጥና የማይረዳ ሆኗል። በዚህ ምክንያት ፀባቸው ከሥላሴ ጋር ስለነበር የቋንቋና የአይምሮ ባለቤት የሆነ ሥላሴም ሃሳባቸውን ሁሉ በታትነው እርስ በእርሳቸው የማይግባቡ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ ለክህደትና ለአመፅ ተነሳስተው ስለነበር ሃሳባቸውና ምክራቸው ሁሉ ተበታትኗል። ባለማስተዋል እና በክህደት የሰሩትም የአመፅ ግንባቸው ከሥላሴ ዘንድ በታዘዘው አውሎ ንፋስ ተጠራርጎ ጠፍቷል። (ዘፍ11፥1-9)
 
የተከበራችሁና የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም ተከታታይ አባላት ዛሬ ጥር 7 ቀን የምናከብረውና የምንዘክረው በአላችን በዋናነት ይህንን ታሪክ ይዞ እናገኘዋለን። ቅድስት ሥላሴ ለፈጠሩት ፍጥረታት ከወደዱት አባት እና እናት በላይ የሚያስቡ ለፈጠሩን ፍጥረታት እረኛ ናቸው። ሥላሴ የሰው ልጅ በኀጢአት እና በአመፅ በክህደትና በኑፋቄ መስመር እንዳይሄድ ከጥፋት በፊት ረቂቅ በሆነ መንገድ ከጥፋታቸው የሚመክሩበትን የሚገስፁበትን ምክንያት ያመቻቻሉ፥ እስከወዲያኛው ድረስ አሻፈረኝ ብሎ በክህደት እና በኑፋቄ ማእበል ሲሄድ የሚገኘውን ሰው ደግሞ ወደ እውነተኛ አይምሮው እስከሚመለስ ድረስ ተገቢውን ተግሳፅ ይሰጡታል እስከመጨረሻው የሄደው ደግሞ በጥፋቱ አመፅ ስራ መልክ ቅጣቱን ይቀበላል።
 
ለምሳሌ የሰዶምና የጎመራ ሰዎች ከአብርሃምና ከሎጥ ተለይተው የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምህረት ለመቀበል አሻፈረኝ ስላሉ በመካከላቸው እንዲመክሯቸውና እውነትን እንዲነግሯቸው የተላኩትን ከአብርሃምና የሎጥ ድምፅ አልሰማም በማለታቸው ከሰማይ የተላከባቸው የእሳት ዲን እንደ ሻማ አቅልጧቸው ጠፍተዋል። እነዚህ የባቢሎን እና የሰናኦር ሰዎች በራሳቸው የአመፅ ስራ ጥፋታቸውን ተመልክተናል። እግዚአብሔር ትዕግስቱ እና ቸርነቱ ብዙ ስለሆነ ሁላችንም በገሀድም ሆነ በስውር እምንሰራውን ጥፋታችን በቅርብ እየተመለከተን፥ እንዳላየን እና እንዳላወቀብን ዝም ይለናል። ይህም ደግሞ የሱን ቸርነትና ትዕግስት ያመለክታል። በተለይ የእኛን ጥፋት የማይወድ አምላክ ስለእኛ ያለው ፍቅሩና ምህረቱ ቸርነቱና ትዕግስቱ ብዙ መሆኑን ያመለክታል። ዛሬም በሆን ከባቢሎን እና ከሰናኦር ሰዎች በላይ በአመፀኝነት እና በክህደት መንገድ የሚሄዱ ቋንቋቸውን ሁሉ ሰይጣን የደበላለቀባቸው መንገዳቸው የጠፋባቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው። እግዚአብሔር በፍጥረታት መካከል የተፈጥሮ ወሰን ባይገድብ እና በቋንቋም እንድንደማመጥ ባያደርገን በህይወታችንም አንድንቻቻል ባያደርገን በአንድ ቀን ጀንበር ተጠፋፍተን፥ የመኖር ህልውናችንም ሊጠናቀቅ ይችል ነበር። ነገር ግን ከእኛ ኀጢአት እና ክህደት የተነሳ ቋንቋችንን ብንደበላልቀውም እግዚአብሔር ባዘጋጀው ምድር ላይ በሰላምና በፍቅር መኖር ቢያቅተን እንኳን አጋዕዝት አለም ሥላሴ ጨርሶ እንዳንጠፋ ወደቀናው መንገድ እየመራን ተስፋ ከቆረጥንበትና አለቀልን ደቀቀልን ባልንበት ጉዞ ውስጥ እንደገና ከውድቀት አንስቶ እንድንኖር ያደርገናል።
 
የተወደዳችሁ ወገኖቻችን ሆይ በዚህ ዘመን በአገራችንም ሆነ በአለማችን ትልቁ የሰው ውድቀት በሃሳብና በቋንቋ አለመደማመጥ ነው።
 
በአነጋገር ዘይቤ አለማችን የሚደርስባትና የሚግባቡባት ቀን ቢኖር እንኳን አብሮ በሰላም ተስማምቶ ከመኖር ይልቅ ተስማምቶ መጥፋትን መርጦ በሰው ልጅ አመፅ አለማችን እንቅልፍ እና እረፍት አጥታለች። ሰው ግን ከ ቅድስት ሥላሴ የተሰጠውን ክብርና ቸርነት አላወቀም።
 
ስለዚህ ሁላችንም አንድ አይምሮ ሆነን ከጥፋት ተለይተን ቢያንስ እንኳን በስጋችን ተጠቃሚ ባንሆንም እንኳን በነፍስ የዘለአለም ህይወት እንድናገኝ አለምን የከበባትን ይህን የመከራ እና የስቃይ ህይወት እግዚአብሔር እንዲያርቀውና፤ የአለም ጥፋትም በዘመናችን እንዳይሆን በአንድነት ሆነን የሥላሴን ቸርነት እና ምህረት መጠየቅ ይኖርብናል።
 
ለሁሉም ነገር አጋዕዝተ አለም ሥላሴ በአለምና በአገራችን ላይ የምናየውን ይህን አስፈሪ ሰቆቃና መከራ ከእኛ እንዲያርቅልን ተግተን ልንፀልይ እና የሥላሴን ቸርነት ልንለምን ያስፈልጋል።
በዓለ ጥምቀት
 
 
“እየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ” 
(ማቴ 3፥13)
 
የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገጽ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታታይ አባላት፥ እግዚአብሔር የሚወዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ሁላችሁም ከሁሉ በማስቀደም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን የጥምቀት በዓል ጥር 10 እና 11 ቀን ለምናከብረው የጥምቀት በዓል እንኳን አደረሳችሁ። 
 
ከዚህ በመቀጠል ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ለምን እንደተጠመቀ፣ በማን እንደተጠመቀ፣ እንዴት እንደተጠመቀ ፣ ስለ ምስጢረ ጥምቀት በዓሉን አስመልክተን አጭር ትምህርት እናቀርባለን።
 
ጥምቀት ማለት፦ መጠመቅን፣ ውሀ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ማለትን፣ መነከርን የሚያመለክት ነው። ጥምቀት 8 አይነት ናቸው። 5ቱ ምሳሌዎች ሲሆኑ 3ቱ ደግሞ አማናውያን ናቸው። እናሱም፦
 
1ኛ በምሳሌነት የተገለጹት የጥምቀት አይነቶች፦ 
 
1.   በኖህ ዘመን የሰማይ መስኮት ተከፍቶ ምድርን የሸፈናት የጥፋት ውሀ የጥምቀት ምሳሌ ነው።
 
2.  ሙሴን በደብረ ሲና የሸፈነው ደመና እና ባህረ ኤርትራን ከፍሎ በተሻገሩ ጊዜ የነበረው ምስጢር የጥምቀት ምሳሌ ነው።(1ኛ ቆረ 10፥2)
 
3.   ካህናቱ ታቦቱን አክብረው ዮርዳኖስን በተሻገሩ ጊዜ የጥምቀት ምሳሌ ነበር። (እየ 3፥15)
 
4.  ጥምቀተ አይሁድ የጥምቀት ምሳሌ ነው። 
 
5.  ጥምቀተ መለኮት ዮሐንስ ህዝቡን ያጠምቃቸው የነበረው የንስኀ ጥምቀት እሱም የጥምቀት ምሳሌ ነው። 
 
2ኛ የጌታ ጥምቀት / አማናዋዊ ጥምቀት 
1. የጌታ ጥምቀት፣
2. ደመ ሰማእታት፣
3.  የንስኀ እንባ (አንብዐ ንስኀ)።
 
ስለ እለቱ የጥምቀት በዓል ከመናገራችን በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተርስቲያን በየአመቱ ጥር 10 ቀን ከተራ እየተባለ የሚከበረው በዓል ራሱን የቻለ ታሪካዊ አመጣጥ እና መንፈሳዊ ስርዓት ያለው  በዓል ነው።
 
ከተራ ማለት፦ መከተር፣ መክበብ ፣ መገደብ መሙላት የሚለውን ቃል ያስተረጉመናል። ምክንያቱም ለጥምቀቱ በዓል የሚያስፈልገውን ውሀ መገደብና መከተር ወይም ጉድጓድ ቆፍሮ ውሀ መሙላት በአጠቃላይ ለጥምቀቱ እለት የሚያስፈልገውን ውሀ የማዘጋጀቱ ሂደት ከተራ ይባላል። በሌላም አገላለፅ ታቦታቱ የሚከበሩበት ጥምቀተ ባህር ገዳማቱ እና አድባራቱ  በተራ ወይም በቅብብሎሽ በየአመቱ ስለሚያከብሩና ስለሚያስከብሩ ይህም በቀጥታ አማርኛ ‘በተራ’ ማክበርን ሊያስመለክተን ይችላል። የጥምቀት የከተራ በዓል የሚገለፀው ታቦቱ ከየመንበረ ክብራቸው ጥር 10 ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ሲሆን ወደ ተዘጋጀላቸው የጥምቀተ ባህር ጉዟቸውን ቀጥለው ጥምቀተ ባህር ተብሎ በተዘጋጀላቸው ድንኳን ወይም ዳስ ውስጥ በክብር ያርፋሉ። ካህናቱና ምእመናኑም ታቦቱን አጅበው በዚያው ጥምቀተ ባህር በመገኘት ለበአሉ ተስማሚ የሆነ ዝማሬ ይዘምራሉ፣ እግዚአብሔርን  ያመሰግናሉ እንደገናም በባህላዊ መዝሙር  ለፈጣሪያቸው የሚገባውን ምስጋና ያቀርባሉ። ይህንኑ የከተራ በዓል በማስመልከትም የወንጌል ትምሀርት በሰፊው ይሰጣል። እንዲሁም በከተራ በጥምቀተ ባህሩ አካባቢ የሚያስፈልገውን የዝክር ስጦታ ምእመናን ደግሰው ካህናቱን ይመግባሉ። እንደየስርአቱም ነዳያንን ይመፀውታሉ እነሱም የበረኩቱ ተካፋይ ይሆናሉ። 
 
እንግዲህ የከተራ በዓልም ሆነ የጥምቀት በአል የአደባባይ በዓል መሆን የጀመረው ከአፀፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ እንደነበረ የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል። በመቀጠልም በ15ኛ መቶ ክፍለዘመን በተነሳው በአፄ ዘርዓያቆብ ዘመን ንግስናቸውም ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው እንዲያድሩና በዓሉም ጥምቀተ ባህር እየተባለ እንዲጠራ እና እንዲከበር ስርዓት ሆኗል። 
 
እንግዲህ የበአሉ መሰረት ዋና መነሻ የአዳም እና ልጆቹን ለማዳን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነው ቸሩ አምላካችን አካላዊ እየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ አለም መጥቶ በእናቱ እቅፍ ሁኖ በየጥቂቱ እያደገ ለእናቱና ለዘመዶቹ እየታዘዘ እንደ ኦሪቱ ስርዓት ወደ ቤተመቅደስም በመሄድ ለኦሪቱ ስርአት እየታዘዘ እስከ 30 ዘመን ድረስ አምላክነቱን ሳይገልፅ በምስጢራዊ ጥበብ ከእናቱ እና እሱ ምስጢሩን ከገለፀላቸው ቅዱሳን በስተቀር ማንም ሳያውቀው  ቆይቷል። 30 ዘመን ሲሆነው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጥቶ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን አጥምቀኝ እንዳለው በርእሳችን ላይ በተጠቀሰው ኃይለቃል መረዳት እንችላለን።
እንግዲህ ጌታን እና ዮሐንስን የሚያገናኛቸው ብዙ ምስጢር እንዳሉ ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል። ከነዚህም፦
–   ጌታ ከመፀነሱ 6 ወር ቀድሞ ዮሐንስ እንደተፀነሰ፣ 
–  ጌታ ከመወለዱ 6 ወር አስቀድሞ ዮሐንስ እንደተወለደ፣ 
–  ጌታ መዋእለ ትምህርቱን ከመጀመሩ 6 ወር ቀድሞ መጥምቀ ዮሐንስ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስኀ ግቡ እያለ የንስኀ ጥምቀት ያጠምቅ እንደነበረ፣ ወንጌላዊያን ይነግሩናል።
 
ከዚህም ጋር የሚገርመውና የሚደንቀው ምስጢር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም አክስቷን ቅድስት ኤልሳቤጥን ልትሳለማት ወይም ሰላምታ ልታቀርብላት ወደ ተራራማው ሀገር በሄደች ጊዜ ገና በእናቱ መሀፀን ሳለ በደስታ እንደዘለለና እንደሰገደ ወንጌላዊ ሉቃስ ይነግረናል። (ሉቃ 1፥43-45) ምክንያቱም እየሱስ ክርስቶስ እና ዮሐንስ ገና በአይነ ስጋ ሳይተያዩ ዮሐንስ በእናቱ መሀፀን እያለ ጌታ ደግሞ በባህሪየ መለኮቱ ለዮሐንስ ምስጢሩን እንደገለፀለት በዚህ ቃል እንረዳለን ። 
 
ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም “ከማህፀን ጀምሮ በአንተ ታመንኩ፥ ከእናቴ ሆድ ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ ብሎ ተናግሯል።” (መዝ21፥10)
 
ነብየ ኤርሚያስም “በእናቴ ሆድ ሳለሁ አውቄዋለሁ” በማለት እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች ገና በማህፀን ሳሉ ያውቃቸዋልና።
 
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በእናቱ መሀፀን ሰገደም በደስታም ዘለለ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ በእናቱ መሀፀን ለጌታው ያቀረበውን ምስጋና በሚመለከት በድግዋ ድርሰቱ ተናግሯል።
 
እንግዲህ ቅዱስ ዮሐንስ ገና በእናቱ መሀፀን ጀምሮ ጉልበቱ ሳይፀና ለፈጣሪው የአምልኮ ስግደት ሰገደለት የባህሪይ አምላክ መሆኑንም መሰከረለት ፣ ሁሉም ዘረ አዳም በልጅነት ጥምቀት ወደሚወለዱበት ወደ መሃፀነ ዮርዳኖስ ጌታችን ሲመጣ ዮሐንስ ባየው ጊዜ ፥ ገና በእናቱ መሀፀን ሳለ ከ 30 አመት በፊት በመንፈስ ያገኘውን በአይነሥጋ ግን አልተያዩም ነበር። በድመፅ መልዕክት ተለዋውጠዋል ነገር ግን በአይነ ሥጋ አልተነጋገሩም ነበር።ለዚህ ነው ዮሐንስ “አላውቀውም ነበር” ያለው (ዮሐ1፤31)  
 
ወደ ዮሐንስ የሚመጡት ሰዎች ሁሉ ኅጢአት ያለባቸው ስለነበሩ ኅጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮሐንስ እጅ ተጠምቀው  ከኅጢአት ለመንፃት የኅጢአት ስርየት ለማግኘት ነበር የሚፈልጉት። ነገር ግን እጅግ የሚያስደንቀው ምስጢራዊ ጥበቡ ግን  ወደ ዮሐንስ  ሊጠመቅ የመጣው ንፀሐ ባህሪይ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ነበር። ክርስቶስ ከራስዋ ከጥምቀት የበለጠ ንፁህ ነውና የእሱ ወደ ዮሐንስ መምጣት በጣም የሚያስደንቅ ነበረ።
 
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ ሊጠመቅ ወደ እሱ ሲመጣ በዮርዳኖስ ዳርቻ ባየው ጊዜ ህዝቡ እንደ ኀጢአተኛ ቆጥረውት እንዳይሰናከሉና ወደ ክህደት ጉድጓድ እንዳይገቡ እንዲህ ሲል እየተናገረ ጮኸ “የዓለሙን ኅጢአት የሚያስወግደው እነሆ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ 1፥29) እነሆ እሱ ከሚያጠምቃቸው የንስኀ ጥምቀት ይልቅ የምትበልጠውን እና ዳግም ልጅነተ የምታሰጠውን አማናዊት ጥምቀት ሊሰጥ የመጣን አምላክ መሆኑን መሰከረለት። (ጌታችን ወደ እርሱ ሲመጣ ባየ ጊዜ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅግ ተጨንቆ ነበረ። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም
 
የጌታዬ እናቱ አንቺ እንዴት ወደ እኔ ትመጫለሽ እንዳለቻት ሁሉ፥ እሱም በአንፃሩ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ እንዴት በባሪያህ በእኔ እጅ ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ በማለት ፍፁም የሆነ የትህትና ጥያቄ አቀረበለት። ቅዱስ ያሬድ “የማትዳሰስ ራሱን ዳሰሰው” በማለት በዜማ ድርሰቱ እንደተናገረው  ሁሉ መለኮታዊ የተዋሀደውን ሥጋ እጁን ጭኖ ሲያጠምቀው ማየት የማይሆነው ሆነ፣ የማይፈፀመው ተፈፀመ ማለት ነውና።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የባህሪይ አምላክ ስለሆነው ስለ እየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር “የእግሩን ጫማ ተጎንብሼ ልፈታና ልሸከም አይገባኝም”  (ዮሐ1፥27) ብሎ ለህዝበ አይሁድ ምስክር ሰጥቷል ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እጠመቅ አይል አጥማቂ ነው ፣ እነፃ አይል ንፁሕ ነው፣ እቀደሳለው አይል ቅዱስ ነው፣ እከብራለሁ አይል ክቡር ነው፣ እፀድቅ አይል ፃድቅ ነው፣  እነግሳለሁ አይል ንጉስ ነው፤ በዚህ ሁሉ ክብሩ የሁሉ አጥማቂ ሊጠመቅ መጥቷልና መጥምቀ ዮሐንስም ከጭንቀቱ የተነሳ እኔ ባንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛልና አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን? በማለት እሱን ማጥመቅ ያለውን ትህትና በአክብሮት ቃል ገለጸለት። (ማቴ 3፥14) 
ቅዱስ ያሬድ ጌታ በባሪያው መሪነት ወደ ባህረ ዮርዳኖስ ወርዶ መጠመቁን በማድነቅ “ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ” (ተጠምቀ ሰማያዊ በእደመሬታዊ) በማለት የሰማይ አምላክ፣ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ በመለኮታዊ ባህሪይው የማይዳሰሰው፣ የማይጨበጠው፣ የማይታየው እና የማይወሰነው እሱ በፈጠረው የፍጥረቱ እጅ ሊጠመቅ ማጎንበሱን ስናይ ምን ያህል የእሱ ስራ እፁብ ድንቅ ነው እንላለን። በዮሐንስ እጅ ጌታ እራሱን ዝቅ አድርጎ የመጠመቁን ምስጢር በምሳሌ ስናይ፦
 
– በባሪያው ፊት የሚቆም ጌታ ማነው?
– በወታደሩ ፊት የሚያጎነብስ ንጉስ ማነው?
– መንጋውን ወይም በጉን መንገድ ምራኝ ወይም አሰማራኝ የሚል እረኛስ ማነው?
– የሻማ ብርሃን ከፀሃይ እንዴት ሊበራ ይችላል?
– መዳብ ከወርቅ እንዴትስ ሊበልጥ ይችላል?
– የምንጭ ውሀስ ከባህር ጋር እንዴትስ ማወዳደር የቻላል?
-የውሀስ ጠብታ ውቅያኖስን እንዴት ለመሙላት ይችላል?
-በአደፈ እጅ ንፁሕ የሆነውን እንዴት ሊያጥብ የችላል?
 
እነዚህን የመሳሰሉ ምሳሌያዊ ምስጢራዊ አገላለፆች ጌታን በባሪያው እጅ የመጠመቁና የፈፀመውን የትህትና ስራ ያመለክታል። 
 
ቅዱስ ዮሐንስ እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል በማለት ያሳየው ትህትና በምሳሌ ሲገለጹ
 
-የሞተው አካል ህያው የሆነውን አካል ሊያስነሳ ይችላልን?
-የታመመው አካል ህያው የሆነውን አካል ሊያስነሳ ይችላልን?
-የታመመው ሰው ሃኪምን ሊፈውስ ይችላልን?
– ደቀመዛሙርት ከመምህር ይበልጣልን?
 
የሚሉትን ወርቃማ የምስጢር ምሳሌዎች እንድናይ ያደርገናል። 
 
ሌላው የዮሐንስ ጥያቄ፦ 
 
– ኪሩቤል ወደ እኔ የሚቀርቡት በፍርሀት አይደለም
-ሱራፌል ለእኔ የምስጋና  ዝማሬ አያቀርቡም፣
-ሰማይ ዙፋኔ ምድር የእግሬ መረገጫ አይደሉም፣
-ብሩህ ኮከብ እንዳንተ ልደት  ለሰባሰገል (የጥበብ ሰዎች) አላሳየም፣
-ለእኔ እንዳንተ ከደመና የሚጮህ ድምፅ አልተሰማም ፣
የሚሉትን ምስጢራዊ ዮሐንስ ፍፁም ትህትና እና በጌታው ፊት ቀርቦ መታዘዝ እንደሚበዛበት ካቀረበው ጥያቄ እንመለከታለን፦
የእግዚአብሔር ባለሟል የሆነው ወዳጅህ ነብዩ ሙሴ እንኳን ጀርባሀን ያያል ተባለ እንጂ ያንተ ፊት ወይም መለኮታዊ ባህሪይማ ማየት ከቶ አልተቻለውም። እኔ ግን እጅግ ንፁሕ የሆነውን የራስህን አካል እነካ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? ፈጣሪዬን ለማጥመቅ የምችልበት እጅ ወይም ድፍረት እና ብቃት የለኝም፤ ይልቁንም እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል በማለት ለሁላችንም አርአያ እና ትምህርት የሚሆን ቃል ሲናገር ተመልክተናል። 
ነገር ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ የመጠመቁ ምስጢር የዮሐንስን ፈቃድ የሚያስጠይቅ ሳይሆን የጌታ መለኮታዊ ፈቃድ እና አምላካዊ ውሳኔ ስለነበረ ጌታ ለዮሐንስ እንዲህ አለው፦ “ፅድቅን እንፈፅም ዘንድ ይገባናል ብሎ መጠመቅን ፈቀደ የጌታ ጥምቀት የሚያፀዳው የሰው ልጅ የመርገም ኅጢአት አለና እሱን ያጥብ ዘንድ ለመለኮታዊ ባህሪይው የማይስማማውን መጠመቅን መርጧልና። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው 30 ዘመን ሲሞላው እንደነበር ወንጌላዊ ሉቃስ  “እየሱስ ሊያስተምር ሲጀምር እድሜው 30 አመት የህል ሆኖት ነበር” በማለት ይገልፃል። (ሉቃ3፥23) በተጠመቀ ጊዜም እጅግ ከሰው አይምሮ በላይ የሆኑ ምስጢራት ተገልፀዋል፦
 
1. የባህሪይ አባቱ እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ እርሱ ነው” አለ። (ማቴ 3፥17)
2. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ እርግብ መጥቶ በራሱ ላይ እንደተቀመጠ ወንጌላዊ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መስክሯል። “መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ እንደ እርግብ ሲወርድ አየሁ በእርሱ ላይም ኖረ” (ዮሐ1፥32) 
እነዚህ ሃይለቃል የሚያሳዩት የአንድነትን እና የሦስትነትን ምስጢር ሰው ፍፁም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ሥጋን ተዋህዶ በምድር ላይ የተገለጠውን ከአምላክነቱ ባህሪይ ሳያንስ ከባህሪይ አባቱ አብ እና ከባህሪይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት እና በሦስትነት እየተመሰገነ በዙፋኑ ላይ በጌትነት ከብሮ ያለ አምላክ መሆኑን ያመለክታል።
 
እንግዲህ የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታታይ ወገኖች ሁላችሁም፤ የጥምቀት በዓል ትምህር እጅግ ጥልቅና ሰፊ ስለሆነ በቀጣይነትም የምናየው ትምህርት ሆኖ ለዛሬው ግን ከበዓለ ጥምቀቱ በረከት እንድናገኝ መሰረታዊ የሆነ የጥምቀት ትምህርት በአጭሩ ለግንዛቤ ያህል የተገለፀ ሲሆን ዋናውና እኛ ልናውቅ የሚገባን፤ የጌታ ፅንሰቱና ልደቱ የክርስቲያን ዋና መገለጫ እንደሆነ ሁሉ የጥምቀትም ምስጢር ከኅጢአታችን እድፍ የታጠብንበት ያጣነውን የልጅነት ክብራችንን  ፣ያጣነውን የልጅነት ክብራችንን  ዳግም በጥምቀት እሱ በከፈለልን ዋጋ በፀጋ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንድንወለድ የሆንበት ስለሆነ ከዚህ በአል የሚበልጥ ሌላ የምንከብርበት በአል ስለሌለን ይህ በዓል ሁላችንም የጥምቀቱን በረከት እናገኝ ዘንድ በልተን ጠጥተን ፈቃደስጋችን እንፈፅም ዘንድ የማይገባንን ከማድረግ ይልቅ የጥምቀቱ መገለጫ የሚሆነውን መንፈሳዊ መታዘዝንና ሃይማኖታዊ ስርዓትን ገንዘብ አድርገን በዓሉን ልናከብረው ይገባል።
 
ከዋዜማው ከከተራ አንስቶ አምላክ በታቦቱ ላይ አድሮ እኛን ሊባርክ በምድረበዳ፣ በወንዝ ዳር ወደተዘጋጀው የጥምቀተ ባህር ወጥቶ እዛ ላይ ሲያድር እኛ ደግሞ  የእሱ ባሪያ ሰራዊት ከንጉሳችን ከእሱ ሳንለይ በተሰጠን ፀጋ መሰረት ልናከብረውና ልናመሰግነው ይገባል። እንዲህ አይነት መታዘዝ ሲኖር እና የሰው ልጆችም ሌሎችም ስነፍጥረታትም ምድርንም ሀገርንም እናስባርካለን ፣ ከሚመጣም መከራና መቅሰፍት እንድንጠበቃለን ማለት ነው። 
 
አምላካችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ጥምቀቱ ለሁላችንም በረከትን ያድለን!
 
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምክርና ትምህርት ድረገጻችን Yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ ላይ ያገኛሉ
 
ቃና ዘገሊላ
 
 
በ3ኛው ቀን ቃና ዘገሊላ ሰርግ ተደረገ 
(ዮሐ 2፥1)
 
በቃና ዘገሊላ በተዘጋጀ ሰርግ ቤት ምን ተደረገ?
 
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆረንጦስ ሄዶ ከቆመበት ሳይቀመጥ፣ የዘረጋውን ሳያጥፍ፣ ፍጹም እረፍት ሳያስፈልገው ፣ የሚበላ የሚጠጣ ሳይቀምስ ፆሙን በጨረሰበት በ3ኛው ቀን በገሊላ አውራጃ ወይም ከተማ በምትገኝ የቃና መንደር ውስጥ በተደረገ ሰርግ ከእናቱ ጋር ተገኝቷል። የሰርጉ ባለቤቶች ሙሽራው ዶኪማስ፥ አባቱ ደግሞ ዮአኪም ይባላሉ። በዚህ የሰርግ ቤት እናታችን እመቤታችን ድንግል ማሪያም የስጋ ተዛምዶ ስለላት እና የቅርብ ዘመድ ስለሆነች በሰርግ ቤቱ ተጠርታ ተገኝታለች። ጌታችን መድኃኒተችን እየሱስ ክርስቶስም ከእናቱ ጋር በዚያ የሰርግ ቤት ተገኝቷል። ደቀ መዛምርቱም ከመምህራቸው ጋር ተገኝተዋል። የሰርጉም እለት የነበረው የካቲት 23 ማክሰኞ ቀን ነው። ምክንያቱም ጌታ ወደ ገዳመ ቆረንጦስ ለፆም ከገባበት ከጥር 11 ቀን ጀምሮ ሲቆጥሩት ቀኑ የካቲት 23 ቀን እንደሆነ ፅንሰ ታሪኩ ያስረዳናል።
 
የውሀን በአል ከውሀ ጋር ለማገናኘት በማሰብ ኦርቶዶክሳዊያን ተዋህዶ ሊቃውንት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝተው ከጥምቀት በዓል ጋር በማያያዝ የጥምቀት ማግስት ጥር 12 ቀን ከ ቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ በዓል ጋር እንዲከበር ቀኖና ሰርተዋል። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤክርስቲያን የበዓል አከባበር ስርዓት መሰረት ኦርቶዶክሳዊያን ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላን በዓል በታላቅ ክብር እና ልዩ በሆነ መንፈሳዊ ስርዓት ያከብሩታል።
 
በርዕሱ ላይ እንደተገለፀው በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሰርግ የሰርጉ አዘጋጆች ወይም የሰርጉ ባለቤት እና ሙሽራው ታዋቂ ሰዎች ስለነበሩ የሰርጉ ዝግጅት በስፋት እና በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ ስለነበረ ወደ ሰርጉ የተጠሩ ሰዎችም እጅግ ታዋቂ እና የተከበሩ ነበሩ። ነገር ግን በዚህ ሰርግ ባዘጋጁት የሰርግ ድግስ እንደተጠበቀው እና እንደተደከመበት ሳይሆን ለሰርጉ የታደመው እንግዳ ሳይጋበዝ እና አስፈላጊው መስተንግዶ ሳይከናወን ድግሱ በማለቁ ምክንያት የሰርጉ ባለቤት በተከሰተው አዲስ ነገር እጅግ ደነገጡ አፈሩም ተሳቀቁም። ማንም ሰው እንደ ሀገራችን ባህልም ቢሆን እንኳንስ ከፍተኛ ድካም የተደረገበት የሰርግ ድግስ ይቅርና አነስተኛ የሆነ የቤታችን ዝግጅት እንኳን ለእንግዳ የሚያስፈልገውን መስተንግዶ ባናደርግ ምን ያህል እንደሚያሳፍር እና እንደሚያሳቅቅ የተወቀ ነው።
በዚሁ አንፃር የሰርጉ ባለቤትም ሙሽራውም የሰርጉ አስተዳዳሪም በተከሰተው ነገር ግራ ስለተጋቡ የጭንቀት መንፈስ ስለገጠማቸው እመቤታችን የጭንቅ አማላጅዋ፣ ወላዲተ አምላክ፣ ሳህሊተምህረት ለእሷ ምስጢሩን አካፍለዋታል። ምክንያቱም በክብር የተጠራች እንግዳ እና የሥጋም ዘመድ ስለሆነች የውስጣቸውን ጭንቀት ሲያካፍሉዋት፥ ውስጣዊ ምስጢሩ ይህን ታላቅ ነገር ባላት አማላጅነት ለእርሷ አቅርበው ለአማላጅነትዋም፥ የማማለድ ሚስጥርን ሰው ሁሉ እንዲረዳ የማድረግ ጥበብ ነው። ወንጌላዊው እንዲህ ሲል መዝግቦታል “ለልጇ እንዲህ ስትል ነገረችው፥ ልጄ ሆይ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው፤ እሱም አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ ፥ ገና ጊዜዬ አልደረሰም አላት።” (ዮሐ 2፥4)
 
እንግዲህ በዚህ 2 ኃይለቃሎችን እንመለከታለን፦
 
1 “አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ”
2 “ገና ጊዜዬ አልደረሰም”።
 
1ኛ  /  አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ”
 
ይሄንን ኃይለቃል ምስጢራዊ ትርጓሜው ያልገባቸው መንፈሰ እግዚአብሔር እና ፀጋ እግዚአብሔር ያልበዛላቸው አንዳንድ የክህደት እና የኑፋቄ ሰዎች ለብዙዎቹ ማሰናከያና የስህተት መንገድ ይሆን ዘንድ እያጣመሙ በመተርጎም ብዙ ሰዎችን ሲያስቱ እንመለከታለን። ይሄንን ቃል እነሱ እንደሚሉት የእናታችን የምልጃዋን ጥያቄ ለማቃለል እና ለማጥላላት  ሳይሆን እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ምስጢራዊ አተረጓጎም እና አገላለፅ በእብራዊያን የአነጋገር ዘይቤ ቃሉ በትክክል የተነገረ መሆኑን ቀጥለን እንመለከታለን።
 
1.1  “አንቺ ሴት” በሚለው ኃይለቃል አገላለፅ ውስጥ  ‘ሴት’ የሚለው ቃል ከእናታችን ከሄዋን ጀምሮ ሴት ሆነው ለተፈጠጠሩ የሴቶች የፆታ የተፈጥሮ ስማቸው ነው። ለዚህም ማስረጃችን አባታችን አዳም ሄዋንን ከእሱ እንደተፈጠረች ባወቀ ጊዜ ይህች ሴት አጥንትዋ ከአጥንቴ፣ ስጋዋ ከስጋዬ ከወንድም የተገኘች ስለሆነ ሴት ትባል በማለት እግዚአብሔር በገለፀለት ቋንቋ እግዚአብሔር አክብሮ የፈጠራትን ሄዋንን እና በተፈጥሮ ሄዋንን የመሰሉ የተፈጥሮ ስማቸው መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል ቃል ነው። (ኦሪ 2፥2)
ሌሎችም አንቺ ሴት የሚሉ አነጋገሮች በአክብሮት አጋኖ እና አክብሮት የመጥራት አነጋገር እንጂ ለማቃለል እና ለማዋረድ የሚነገር አይደለም። አንቺ ሴት ማለት አገላለፁም ‘ንግስት ሆይ’፣ ‘አንቺ ሴት ሆይ’ ማለትን ሁሉ የሚያሳይ አነጋገር ነው። ጌታችን እናቱን እና ጥያቄዋን አክብሮ ተቀብሎ እንደፈፀመላት ወደታች እንመለከታለን።
 
1.2 ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ፦ የሚለው ትክክለኛው አነጋገር እናቴ ሆይ የጠየቅሽኝን እና የለመንሽኝን ሁሉ የማላደርግበት አንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ ወይም ምን ምክንያት አለኝ ማለት እንደሆነ እውነተኛው የቤተክርስቲያን ምስጢራዊ ትርጓሜ ይነግረናል። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው መፅሐፈ ነገስት ላይ እንተመዘገበው ልጅዋ በሞተባት ጊዜ ወደ ነብዩ ኤልሳ በከፍተኛ ለቅሶ እንዲህ ብላው ነበር “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ የወለድኩትን አንድ ልጄን ምንስ በድዬህ ነው ፣ ምንስ አስከፍቼህ ነው እንዲሞትብኝ አደረክብኝ ” በማለት የተናገረችው አባባል የንቀት እና የማቃለል ንግግር ሳይሆን የነበራትን ትህትና እና ፍቅር የተነሳ ነበር። ነብዩም ለዚህች ሴት ከእግዚአብሔር በተሰጠው ሃይል ታላቅ ነገርን እንዳደረገላት በዚህ መፅሐፍ ቅዱስ ቃል ማረጋገጥ እንችላለን። 
-በጌርጌሴኖን ሀገር አጋንንት ያደረበት አንድ ሰው ወደ ጌታችን ቀርቦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ እየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ከንተ ጋር ምን አለኝ በማለት የተናገረውን ቃል ስንመለከት በእውነት ይህ እርኩስ መንፈስ የተናገረበት ቃል የንቀት ንግግር የመስላልን? እንኳንስ ሊያቃልል አይደለም እሱ የጌታችንን እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት እና ፍፁም አምላክ መሆኑን መስክሯል። ሰለዚህ ይህ አነጋገር የአክብሮት እንደሆነ እንመለከታለን። (ሉቃ 8፥ 28-29)  
 
2ኛ  ደረጃ “ጊዜዬ እኮ አልደረሰም” የሚለው አገላለፅ ድንግል ማርያም የጠየቀችውን ጥያቄ ላለመፈፀም ሳይሆን እግዚአብሔር ለስራ ሁሉ ጊዜ አለው እውነት ነው እግዚአብሔር ስራውን የሚሰራበት ወቅት በሱ ዘንድ አስቀድሞ የታወቀና የታቀደ ነው እንጂ እንዲሁ በአጋጣሚ የማታውን ቀን ፣ የቀኑን ሌሊት አይሰራም። በእያንዳንዷ ጊዜያት እና ዘመናት የሱ ፍጥረታት ስለሆንን በእያንዳንዱ ስፍረ ጊዜ ከእኛ አይምሮ በላይ በሆነ የጊዜ ቀመር ውስጥ የሚሆነው ነገር በእግዚአብሔር ቀድሞ የታወቀ ነው። የፍጥረታት ፈጣሪ ሁሉን አዋቂ እግዚአብሔር ይቅርና ደካማ ባህሪይ ያለው የሰው ልጅ እንኳን የሚያቅድበትና የሚፈፅምበት የራሱ ጊዜና ሰዓት አለው። (መክ 3፥1)
 
ታዲያ የእግዚአብሔር ጊዜ ምንድን ነው? የእግዚአብሔርን ጊዜ ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት። የሰርጉ የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ በእመቤታችን የአማላጅነት ጥያቄ መሰረት ውሀውን ወደ ወይን ጠጅ የሚለውጥበት ጊዜና ሰዓቱ አልደረሰም ለማለት እንጂ፥ ከዚያ እሱ በወሰነው ሰዓት ግን የእናቱን ጥያቄ ተቀብሎ ውሀውን ወደ ወይንጠጅ መለወጡን  ፤
አምላካዊ ተአምራቱን የሚፈፅምበት ጊዜ ገና አልደረሰም፣ ሰውን ለማዳን መከራ የምቀበልበት ጊዜ አልደረሰም፣ ሰይጣንን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ፈፅሞ ድል የምነሳበት ጊዜ ወይም በመስቀሉ የሞትን እና የሰይጣንን ሃይል የሚያሸንፍበት ጊዜ አልደረሰም ማለቱ ነው። (ማ17፥9) ፣ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነፃነትን የሚሰብክበት ጊዜ ፣ መንፈስ ቅዱስን የሚልክበት ጊዜ አልደረሰም ማለቱ ነው፣(የሐዋ 1፥1)
 
እግዚአብሔር ስራውን የሚፈፅመው የአምላክነቱ አገልግሎት እና ትዕዛዝ ኖሮበት ሳይሆን በራሱ ፈቃድ ሲናገር ጊዜዬ አልደረሰም በማለት ብዙ ቦታ በወንጌል ተናግሯል። የተናገረውም
አጋንንትም ሳይቀሩ የእግዚአብሔርን ጊዜ ስለሚያውቁ እንዲህ በለው መስከረዋል “ጊዜው ሳይደርስ ልታጠፋን ወደዚህ መጣህን?” (ማቴ 8፥29)
 
እንግዲህ ሰይጣን እንኳን በአቅሙ የእግዚአብሔርን ጊዜ ያውቅ ስለነበር በቅዱስ ወንጌል እንደተፃፈ እስከ ጊዜው ድረስ ተወው ይላለ።
-በአንፃሩ ጌታ ጊዜው እንደደረሰ የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ማየት እንችላለን። ለምሳሌ፦
“ጊዜዬ ቀርቧል ከደቀመዛምርቱ ጋር በአንተ ዘንድ ፋሲካን አርጋሁ ይላል በሉት”(ማቴ26፥18)
-እየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።(ዮሐ 13፥1) 
-አባት ሆይ ሰአቱ ደርሷል
 
እነዚህ ከዚህ በላይ በእናታችን በድንግል እና በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረውን ምስጢራዊ ትርጓሜውን እና ማብራሪያውን ከዚህ በላይ በአጭሩ የተመለከትነው በቂ ነው። በዚህ የሰርግ ቤት የ እመቤታችን ድንግል ማሪያም እና የጌታችን እየሱስክርስቶስ ከደቀመዛምርቱ ጋር መገኘት ፦
 
1 በእብራዊያን ልማድ እመቤታችን የስጋ ዘመድ ስለነበረች ወደ ሰርጉ ክልጇ ጋር በመጠራትዋ ደቀመዛምርቱን ከእሱ ስለማይለይ የሰርጉን ጥሪ አብረው የሄዱ መሆኑን ያመለክታል፣
 
2 የአንድነት እና የሦስትነትን ምስጢሩን የገለጠበት ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑንም በገሀድ ያሳየበት ሲሆን እንደ ሰውነቱ እና እንደ አምላክነቱ የመጣበትን ስራውን በገሀድ ለመስራት የስራው ሁሉ መጀመሪያ በዚሁ በቃና ዘገሊላ የሰርግ ቤት ይሆን ዘንድ የሱ መለኮታዊ ፈቃድ ስለነበረ ይህንን ደግሞ ረቂቅ ምስጢር እናቱ እና እሱ በምስጢር ይተዋወቁ ስለነበር በከፍተኛ ዝግጅት የተዘጋጀውን የሰርግ ድግስ የማለቁ ምስጢር የእናቱን አማላጅነት እና የሱም የእናቱን ጥያቄ ተቀብሎ እንደሚፈፅምላት የሚያረጋግጥበት፥ በተፈጥሮ እሱ ያስገኘውን ንፁህ ውሀ ወደ ወይን ጠጅነት በመለወጥ መለኮታዊ ተአምራቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ዘንድ ሊገልፅ ስለወደደ ነው። ምክንያቱም እመቤታችን ድንግል ማሪያም “ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል” ባለችው ጊዜ ልጇ ወዳጅዋ ከላይ የተገለፀውን ቃል ከተናገራት በኋላ እሷና እሱ በምስጢር ተግባብተው ስለነበረ የአማላጅነት ጥያቄዋን እንደተቀበላት ተረድታለችና ለሰርጉ ባለቤቶችና አገልጋዮች “የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው።  የሰርጉ ባለቤቶች ወእርሱ ቀርበው ትዕዛዝ ሲቀበሉ በአይሁድ ስርዓት የተዘጋጁት 6 የድንጋይ ጋኖች ንጹህ ውሀ እስከ አፋቸው ድረስ ሙሏቸው አላቸው ። እነሱም ጌታ በሰጣቸው ትዝዛዝ እስከ አፋቸው ድረስ ንፁህ ውሀ ሞሏቸው በመቀጠልም ለዳሱ አስተዳዳሪ ቀድታችሁ ስጡ አለ። ጌታ ወደ ወይን ጠጅነት የቀየረውን ቀድተው ለሰርጉ አስተዳዳሪ ሲሰጡት እርሱም በጣም ተደንቆ ለአስተናጋጆቹ “አስቀድሞ ማለፍያውን የወይን ጠጅ ለእንግዳ ይሰጡታል፥ በኋላ ደግሞ ቅራሪውን እና መናኛውን ሊሰጡት ይገባል” በማለት ያለውን አድናቆት በሰርጉ ቤት መሰከረ። ነገር ግን ያ የሰርግ ወይን ጠጅ ሰዎች ያዘጋጁት አልቆ ጌታ በተአምራት ውሀውን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረው ምስጢር እንደሆነ ሲነገረው በተነገረው መለኮታዊ ስራ እሱም ተደንቋል። 
 
በአጭሩ ከዚህ በላይ ለማብራራት እንደሞከርነው የድንግል ማርያም የአማላጅነት ጥያቄ መፈፀሙን እና እግዚአብሔር በፍፁም እምነት ሆነው ወዳጆቹ የሚጠይቁትን እንደሚቀበል አረጋግጧል።
 
ወገኖች ሆይ እስኪ ለመሆኑ በእኛ ልማድ እንኳን ትክክለኛ አይምሮ ያለው ሰው እንኳን የወለደችውን እናት ቀርቶ በእድሜ ደረጃ ታላቅ የሆኑትን ወይም ሊወልዷቸው የሚችሉትን እናቶች በማቃለል ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ልጅ በሰው ዘንድ እንደ ሰው ሊቆጠር ይችላልን? እሱ በራሱ ፍቃድ ከሴቶች መካከል ለእናትነት የመረጣትን ድንግል ማርያምን ይቅርና እግዚአብሔር በእውነተኛ ሃይማኖት ሁነው የጠየቁትን እና የለመኑትን እንኳን የማይረሳ እና የሰወችን ጥያቄ በከንቱ የማያስቀር ስለሆነ ይህን ቃል በቅንነትና በማስተዋል መመልከት ያስፈልጋል። 
 
ይልቁንስ ከቃና ዘገሊላ ክፍተት እኛ በሀይወታችን ብዙ ልንማረው የሚገቡ ነገሮች አሉ። በህይወታችን ብዙ ነገሮች የጎደሉብን አሉ፣ ብዙ የተሳቀቅንበት እና ያፈርንበት ጉዳይ አለ፣ ህይወታችን ሁሉ ባዶ ሆኗል፣ በስጋዊ ህይወታችንም ቢሆን የእግዚአብሔርን በረከት ያጣንበት ነገር በዝቷል፣ የእለት እንጀራችንን የቆረስነው በአመፅ ፣ በጉልበትና በሸፍጥ ነው፣ በእኛ ላይ ትርፍ ሳይሆን ባዶ ነው የሚታሰብብን፣ በልተን ወይም ጠጥተነውም የህይወት እርካታ የማይሰማን ምክንያት የእኛ የሆነው የራሳችን አልቆብናል፣ በነፍሳችንም በህይወታችንም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያቀርበን ምንም አይነት ያስቀመጥነው ስንቅ የለም፤  በአንጻሩ ወደ እሱ ለመሄድ የማንቀርበት ጉዞ ከፊችን አለ፥ ይህ ጉዞ ስንቅ ያስፈልገዋል፥ በወንጌል እንደተፃፈ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ ለሰማያዊው መንግስት የሚያበቃ ስንቅም አዘጋጁ ተብሏልና። ስለዚህ ያ ያለቀብንን ነገር መልሶ በእግዚአብሔር ድንቅ ስራ በበረከት እንዲሞላልን እና ባዶነትን ከእኛ እንዲያርቅልን አሁንም ቢሆን በጉልበትና በሃይል ወይ በሸፍጥ ሳይሆን እውነተኛ የሆነውን የድንግል ማርያም የጭንቅ አማላጅነትዋን አምነን ወደእርሷ  ቀርበን፥ እናታችን ሆይ አማልጂን ፣ባዶነታችንን በበረከት ሙይልን ፣ ጓዳችንን ሁሉ በበረከት አትረፍርፊልን፣ እስካሁን በአመፅና በግፍ የወሰድነውን የቀማነውን ሁሉ እንዳይቆጥርብን  ከልጅሽ ከወዳጅሽ ዘንድ ይቅርታን ለምኝልን፣ እያልን መማዘኑ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።
ስለዚህ ይህ ደግሞ የጊዜ ቀጠሮ የሚያስፈልገው ሳይሆን ዛሬውኑ ለማድረግ የማንከፍልበት መንፈሳዊ ምግባር ብዙዎቹ ወገኖቻችን ተርበውና ተጠምተው እየለመኑን፣ ታርዘው ለእርየቃናቸው ልብስ  እየጠየቁን የከለከልናቸውና የጨከንባቸው ብዙዎች ናቸው። ይህ ሁሉ ደስታን ሳይሆን መከራን፣ ህይወትን ሳይሆን ሞትን፣ ፅድቅን ሳይሆን መገምን የሚያመጣብን እዳችን ነው።
 
ስለዚህ የተወደዳችሁ የዮሐንስ ንስኀ ድረገፅ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታታይ ወገኖቻችን ሆይ ፥ ዛሬ የቃና ዘገሊላ ምስጢር ለሰማያዊ ታላቅ ክብር የሚያበቃን ትምህርት መሆኑን አውቀን በተማርነው ፍሬ እንድናፈራና ለቀጣዩ አመትም በሰላም አድርሶን ይሄንን ታላቅ የቤተክርስቲያን በዓል ለማክበር ያብቃን።
 
የዶኪማስን የሰርግ ቤት በበረከት የሞላ አምላክ የእኛንም ቤት በበረከቱ ይሙላልን