ስለ ቅዱስ ቁርባን

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ስለ ቅዱስ ቁርባን

ምስጢረ ቅዱስ ቁርባን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜንበአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ፣ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብዬ ምንም እንኳ በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት ብዬ ባምንም በመለኮት፣ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በህልውና፣ በባህሪ፣ የሚታየውንና የማይታየውን አለም ፈጥሮ በመመገብና በመምራት፣ አለሙንና ፍጥረታትን ሁሉ ከነበረበት የተፈጥሮ ህልውና ወደ መጨረሻው የአለም ፍፃሜ በማሳለፍ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ በማመን፣ በሁለት ወገን ቅድስት ድንግል ንፅህት በምትሆን በቅድስት ድንግል ማሪያም፣ በቅዱሳን ፃድቃን፣ በቅዱሳን ሰማእታት እና በቅዱሳን መላእክት አማላጅነት አምኜ ስለ ምስጢረ ቅዱስ ቁርባን እና ስርዓቱ የምስጢሩ ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር በፈቀደልን መጠን ከዚህ ቀጥለን እንማራለን።
 
ቅዱስ ቁርባን የሁሉ ነገር መሰረትና መደምደሚያ እንደመሆኑ መጠን በዚህ እርዕስ መነሻነት መማር ያስፈለገን ስለ ምስጢረ ቁርባን አመሰራረት እና አስፈላጊነት እንዲሁም በዘመነ አበው እና በዘመነ አርኢት (በብሉይ ኪዳን ዘመን) የነበረው የቁርባን አይነት (የመስዋዕት ዓይነት) ከሀዲስ ኪዳን መስዋዕት (ቁርባን) ጋር ሲነፃፀር ያለው ልዩነትና አንድነት ምን እንደሚመስል በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት መማርና መረዳት እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ከሁሉ በማስቀደም እናንተ የዮሐንስ ንስሓ ድረ ገፅ ላይ የምናስተላልፈውን ተከታታይ ትምህርት የምትከታተሉ ወገኖቻችን ሁላችሁም ከምንም በላይ ስለ ቅዱስ ቁርባን እውነቱን ታውቁ ዘንድና የክርስቶስን ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል ተዘጋጅታችሁ የዘለአለም ህይወትን ለመውረስ ትበቁ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ አይነ ልቦናችሁን ያብራላችሁ።

ስለ ቅዱስ ቁርባን​

ምስጢረ ቅዱስ ቁርባን
ሚስጥረ ቁርባን በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሰረት ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስተያን አንዱና ዋነኛው ነው። ስለ ሚስጢረ ቅዱስ ቁርባን ትርጉምና ስለቃሉ ማብራሪያ በሚመለከት ቁርባን ማለት ቃሉ የሱርስትና የግሪክ (የአረብ) ቃል ሲሆን ትርጉሙም በቁሙ ገፀ በረከት፣ የገንዘብ፣ የእውቀት፣ የጉልበትና የጊዜ ስጦታ ማለት ነው። በሌላም በኩል ይህንን ምስጢር “የጌታ እራት፣ ምስጢራዊ የፍቅር ማዕድ ተብሎ ይገለፃል። ቁርባን የሚለው ቃል በምስጢራዊ አገላለፁ ብንመለከተው ሰው በፈጣሪው ሲያምን ለሰማያዊ አምላክ በገፀ በረከት የሚያቀርበውን መንፈሳዊ አምሀ በሙሉ አጠቃሎ የሚገልፁበት ቋንቋ ነው። የምስጢረ ቅዱስ ቁርባን ትምህርት እጅግ ጥልቅ እና ረቂቅ ቢሆንም እንኳን፤ በዚህ ፅሁፍ ግን የምንመለከተው አማናዊ ስጦታችን ስለሆነው ስለ እየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጋ እና ክቡር ደሙ  በተመለከተ ነው። አማናዊ የሆነው የክርስቶስ ቅዱስ ስጋ እና ክቡር ደም ከሰው ዘንድ ለእግዚአብሔር የቀረበ ሳይሆን ከፈጣሪ ዘንድ ለሰው ልጅ ሁሉ በልግስና የተሰጠ የዘለአለም ህይወት ለመውረስ የታደልንበት የመንፈስቅዱስ ስጦታና መለኮታዊ ጥበብ ነው።
 
የሰው ልጅ በእምነት መኖር ሲጀምር ከራሱ ፈቃድ የተነሰ ለእግዚአብሔር የሚሆነውን ንፁህ መስዋዕት  መርጦ በፈጣሪው ፊት ያቀርባል። እግዚአብሔር አምላክ ደግሞ የሰውን ልጅ መታዘዝ እና ፍፁም እምነት ተመልክቶ ምድራዊውን ወደ ሰማያዊ፣ የሚያልፈውን ወደ ማያልፈው ዓለም፣ ጊዜያዊውን ወደ ዘለአለማዊው ክብር ይለውጣል። ይህም አገላለፅ ሚስጥረ ቁርባን በመባል ይነገራል።
 
ከአበው ዘመን ጀምሮ የነበሩት በዘመነ ኦሪት እና በብሉይ ኪዳን  የነበሩ የታወቁ አበው ቅዱሳን በእግዚአብሔር እና በነሱ መካከል በኀጢአት ምከንያት የጥል ግድግዳ ሲፈጠር ከእንስሳት መካከል እና ከሌሎቹም ለመስዋዕት ከሚሆኑ ስጦታዎች መርጠው በፍፁም እምነታቸው ለእግዚአብሔር መስዋዕት በማቅረብ ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቃሉ። እግዚአብሔርም በእምነት ያቀረቡትን መስዋዕታቸውን ተቀብሎ ኀጢአታቸውን ይቅር ይላቸዋል። በህገ ልቦና እና በህገ ኦሪት ፀንተው እግዚአብሔርን በማመን በአላማቸው የፀኑ የእግዚአብሔር ህዝቦች በዚህ ቅዱስ ስርዓት ተወስነው በማስተዋል ጊዜያቸውን አሳልፈዋል።
 
አባታችን አበ ብዙሀን አብርሀም ከፈጣሪው በደረሰው ጥሪ መሠረት ልጁ ይስሐቅን ለመሥዋዕት ሊያቀርበው ወደ ታላቁ የሞሪያ ተራራ ይዞት መውጣቱ፤ ዓለምን ለማዳን በኋለኛው ዘመን ሰው ሆኖ ስጋን ተዋሃዶ የመጣው የእየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው።
 
በህገ ልቦና እና በዘመነ ኦሪት የሚቀርበው መስዋእት ምድራዊ እና ሀላፊ ነው። መስዋዕቱን የሚያቀርበውም ካህኑ ምድራዊ እና ዘመን የሚያሳልፈው ሃላፊ ነው። ለአባቱ መታዘዝን የመረጠ ይሥሐቅም እንደተለመደው የመስዋእት አቀራረብ ስርዓት ለመስዋእት የሚሆነው በግ እንዳልተያዘ ባየ ጊዜ “አባቴ ሆይ…እሳቱ እና እንጨቱ ይኸው የመስዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?” ብሎ አባቱን ጠይቆ ነበር። በአብርሃም ህሊና ለመስዋእት የሚቀርበው በግ ይሥሐቅ ነበር። ይሁንና አብርሃም የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳቀበለው “ልጄ ሆይ የመስዋእቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ በእግዚአብሔር በኩል በይሥሐቅ  ፋንታ ስለተዘጋጀው መሥዋዕት በምስጢራዊ አገላለፅ መለሠለት። (ዘፍ 22፥7-8)
 
ለጊዜው አብርሃም የፈጣሪውን ትዕዛዝ ለማክበር እና ፈጣሪውን ለማስደሰት ሲል ከእውነተኛ እምነቱ የተነሣ እግዚአብሔር በእርጅና ዘመን የሠጠውን አንድ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ቢዘጋጅም ንጹህ የመስዋእት በግ በእፀ ሳቤቅ ተይዞ ከሠማይ ወረደ በይሥሐቅም  ፋንታ ቤዛ ሆኖ ለመሥዋዕት ቀረበ (ዘፍ 22፥13)
 
ይህ በእግዚአብሔር በኩል የተዘጋጀው ሚስጥራዊ ስራ በይሥሐቅ ፋንታ ቤዛ ሆኖ የተሰዋው ንጹህ በግ በኋለኛው ዘመን ዓለምን ለማዳን በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ስጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ መሥዋዕእት ይሆን ዘንድ ስለ እኛ ኅጢአት መከራ የተቀበለው የአለም መድኃኒት የእየሱስ ክርስቶስ ምሣሌ መሆኑን እንመለከታለን።
 
ሰውን ለማዳን በባህሪያችን የተገለፀ ንፁሁ የመስዋእት በግ ሆኖ የቀረበ እየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ስለ ንስሓ ጥምቀት እና ስለ ኅጢአት ስርየት በዮርዳኖስ ማዶ እየሰበከ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ እየጮኸ የተናገረው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፤ ጌታችን እየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ “ እነሆ የዓለምን ኅጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ከእኔ በፊት የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኳችሁ ይህ ነው፤ እሱ ከኔ አስቀድሞ ነበርና።” በማለት የሀዲስ ኪዳን መሥዋዕት እየሱስ እንደሆነ መስክሯል (ዮሐ 1፥ 29-30) ዮሐ 1፥29-30
 
የሀዲስ ኪዳን ንፁህ መስዋዕት የሆነው የድንግል ማርያም ልጅ የሆነው መድኃኒያለም እየሱስ ክርስቶስ የሱ መሥዋእት በይሥሐቅ ፋንታ ቤዛ ሆኖ እንደቀረበው የመሥዋዕት በግ ለአንድ ሰው ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ቤዛ ለመሆን ሳይሆን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ የቀረበ ነው። መስዋእት ሆኖ የሚቀርበውም እንደ ኦሪት መስዋዕት በየጊዜው በተደጋጋሚ የሚቀርብ ሳይሆን አንድ ጊዜ ብቻ ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ ነው፤ መስዋዕት አድርጎ ያቀረበውም የራሱን ስጋና ደም ነው።
 
ስለዚህ ምስጢረ ቁርባን ስንል ከዚህ በላይ ለማብራራት እንደተሞከረው ስለአለሙ ሀሉ ድህነትና ቤዛነት መስዋእት ሆኖ ከቀረበው ከእየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጋና ክቡር ደም ጋር ህብረትና ተሳትፎ ይኖረን ዘንድ ስለ ሁላችንም በነፃ የተሰጠን ዘለአለማዊ ህብስት ነው። የቤተክርስቲያናችን ታላቁ አባት አባ ህርያቆስ ስለ ቅዱስ ቁርባን ክብር መንፈስ ቅዱስ ምስጢሩን ገልፆለት ምስጢሩን ሲናገር ፦ “ዛሬ በዚች ቀን በፍቅርና በትህትና ግሩም በሚሆን በዚህ ምስጢር ፊት እቆማለው። በዚህም ማዕድና ቁርባን ፊት መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከእርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት ቁርባን ነው። በበግ፣ በጊደርና በላም ደም እንደነበረ እንደቀደሙ አባቶች መስዋዕት አይደለም፥ እሳት ነው እነጂ፤ ፈቃዱን ለሚሰሩ ልቦናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፤ ስሙን ለሚክዱ ለአመፀኞች ሰዎች የሚባላ እሳት ነው” (ምንጭ ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 5-7) በማለት የሀዲስ ኪዳን መስዋእት የሆነው  የክርስቶስ ቅዱስ ስጋና ክቡር ደም ከኦሪቱ የፆምና የቁርባን መሥዋዕት ይልቅ ያለውን ክብርና ዘላለማዊ ድህነት አስተምሯል።
 
ምስጢረ ቁርባን ምስጢር የተባለበት ምክንያት ላላመኑ፣ ላልተጠመቁና በንስሓ ህይወት ከኅጢአት ነፅተው ላልተዘጋጁ ሰዎች የማይሰጥ ስለሆነና፤ እግዚአብሔር በሾማቸው የቤተክርስቲያን ካህናት (ቀሳውስት) በቤተመቅደስ ውስጥ በታቦቱ ላይ በቅዳሴ በምስጢር የሚያከብሩትና ለቅዱስ ቁርባን ተዘጋጅተው ለቀረቡት ምዕመናን ብቻ በፍፁም ሃይማኖት የሚያቀብሉት ምስጢራዊ ስርዓት ስለሆነ ነው።
 
ቅዱስ ቁርባን የተባለበትም ምክንያት በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ የሆኑ ሁሉ የአብ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስን ሦስትነት አንድነት፣ የክርስቶስን ሰው መሆን አምነው፣ በንፁህ ክርስቲያናዊ ህይወት ተዘጋጅተው ለቀረቡ የተለየ ሰማያዊ የነፍስ ምግብ ሆኖ ስለቀረበ ነው። 
 
ከዚህ ቀጥለን በህገ ልቦናና በዘመነ ኦሪት የአዳም ልጆች ያቀርቡት የነበረውን የመስዋዕት አይነት በአጭሩ እንመለከታለን።
 
የብሉይ ኪዳን መስዋዕት (ቁርባን)
 
–      አባታችን አዳም የፈጣሪውን ትዕዛዝ ተላልፎ አትብላ ያለውን እፀበለስ ቀጥፎ በበላ ጊዜ ከፈጣሪው ጋር ያጣላውንና ከገነት እርስቱ ያወጣውን ኅጢአቱን ይቅር ይለው ዘንድ ለፈጣሪው የደም መስዋዕትና የእህል ቁርባን መስዋዕት አቅርቧል። የአዳም ልጅ አቤልም ከወንድሙ ከቃዬል ይልቅ የተሻለውን ንፁህ መስዋእት ከበጎቹ መካከል ፀጉሩ ያላረረ፣ ቀንዱ ያልከረረ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ንፁህ በግ መርጦ ለፈጣሪው በማቅረቡ እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ እንደተመለከተና የአቤልን መስዋዕት ወዶ እንደተቀበለ እንመለከታለን። ቃዬል ግን በትዕቢትና በግድ የለሽነት ያቀረበውን መስዋዕቱን እግዚአብሔር እንዳልተቀበለው ተመልክተናል። (ዘፍ 4፥2-7)
 
–      አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው አባታችን ፃድቁ ኖህም ከጥፋት ውሀ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ቃል ኪዳን ለማፅናት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዳቀረበ እናያለን። “ኖህም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ሰራ፣ ከንፁህም እንስሳ ሁሉ፣ ከንፁሀን ወገኖችም ሁሉ ወሰደ በመሰውያም ላይ መሥዋዕቱን አቀረበ። እግዚአብሔርም መልካሙን መአዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔር በልቡ አለ፥ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም የሰው ልብ ሃሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግኩት ሕያዋንን ሁሉ እንደገና አልመታም” ተብሎ ተፅፏል (ዘፍ 8፥20-21)
 
–      አባታችን አበ ብዙሃን አብረሃም ምድር ሁሉ በሱ እንደምትባረክና ዘሩን እንደ ምድር አሸዋና እንደ ሰማይ ከዋክብት ዘሩን እንደሚያበዛለት እግዚአብሔር ቃል በገባለት ጊዜ በተራራው ላይ ድንኳን በመትከል መሰዊያ ሰርቶ ለፈጣሪው መሥዋዕት እንዳቀረበ እንመለከታለን (ዘፍ 12፥7)
 
–      እስራኤላዊያን በግብፅ ምድር 430 ዘመን ያህል በባርነት አገዛዝ ከኖሩ በኋላ ጩኸታቸውን እና ለቅሷቸውን ተመልክቶ በነብዩ ሙሴ አማካኝነት ከግብፅ የባርነት አገዛዝ ሊያወጣቸው ዘንድ ለድህነታቸው ምክንያት ይሆን ዘንድ ቀንዱ ያልከረረ፣ ፀጉሩ ያላረረ፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረ የበግ ጠቦት መርጠው እንዲያርዱና መሥዋዕት እንዲያቀርቡ አዘዛቸው። ከዚሁ ጋርም የእህል ቁርባን እንዲያቀርቡ ታዘዋል። ይህም ስርአት ለልጅ ልጆቻቸው ያፋሲካ በአል ሆኖ እየታሰበ አማናዊ ፋሲካ እስከሆነው እስከ እየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሞትና የትንሳኤው ምስጢር ድረስ መቀጠሉን እንመለከታለን (ዘፀ12፥1-51፣ የሐዋ7፥6)
 
ይቀጥላል 
(በሚቀጥለው ተከታታይ ትምህርት ይጠብቁን)
“ምሥጢረ ቅዱስ ቁርባን” ክፍል ሁለት
(ከባለፈው የቀጠለ የመጨረሻው ክፍል)
 
በተለይ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው መሠዊያ ላይ በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ ስለሚገባው መሥዋዕት (ቁርባን) በሕገ ኦሪት ደንግጓል።
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለእብራውያን ወገኖቹ ስለቀደመው የመሥዋዕት አቀራረብ ሲገልጽ “ሙሴም ትዛዛትን ሁሉ እንደ ሕጉ ለህዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችና የፍየሎች ደም ከውሀና ከቀይ የበግ ጠጉር ከሂስጵም ጋር ይዞ እግዚአብሔር ያዘዛላቸው የኪዳኑን ደም ይህ ነው ብሎ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው። እንዲሁም በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጨ። እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነፃል፣ ደምም ሣይፈስ ሥርየት የለም። በማለት ሕዝቡ ስለፈጸሙት በደላቸው የኅጢአት ስርየት የሚያገኙት በደም መፍሰስ መሆን እንዳለበት አማናዊ የሆነው የክርስቶስ ደም ምሳሌና ጥላ ስለሆነው የኦሪት የደም መሥዋዕት ተናግሯል። (ዕብ9፥22)
 
ስለ ኦሪቱ መሥዋዕት ተጨማሪ የመፅሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን እንመልከት፦
 
– “የደሙንም እኩሌታ በመሠዊያው ረጨው” (ዘጸ29፥6)
 
– “ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ” (ዘፀ29፥12፡20)
 
– “ደሙን በመገናኛው ድንኳን ደጆች ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል” (ዘሌ 1፥5፡11)
 
– የአሮን ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል
 
– ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደስ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል” ዘሌ 4፥6
 
– “የኅጢአታቸውም መሥዋዕት ሁሉ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ ለአንተ ለልጆችህም የተቀደሰ ይሆናል፤…” (ዘኅ18፥9-11)
 
እግዚአብሔር አምላክ ከእስራኤላውያን ዘንድ መቅረብ የሚገባው የመሥዋዕት (የቁርባን) ዓይነት ከምን መሆን እንዳለበት ለነብዩ ሙሴ እንዲህ በማለት ተናግሮታል፦
 
“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው…ማናቸውም ሰው ስርዓቱን ሁሉ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቁርባን ቢያቀርብ ይሠምርላቸው ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባዕቱን አቅርቡ” (ዘሌ22፥17-21)
 
እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን ስለ ሕዝቡ የኅጢአት ሥርየት እንዲቀርቡ ያዘዛቸው የመሥዋዕት ዓይነት 5 ናቸው። እነሱም፦
 
1/    የሚቃጠል መሥዋዕት
2/   የእህል ቁርባን
3/   የድኅንነት መሥዋዕት
4/   የኅጢአት መሥዋዕት
5/   የበደል መሥዋዕት
 
እንደሆኑ በኦሪት ዘሌዋውያን ከምዕራፍ 1-5 ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የመሥዋዕቱ ዓይነትና ዝርዝር ሁኔታው ተመዝግቦ እናገኘዋለን።
 
በብሉይ ኪዳን ራሱን የቻለ የመሥዋዕቱ አቀራረብ በሥርዓትና በሕግ የታዘዘ ነበር።
 
ለምሣሌ፦ ለመሥዋዕት የሚቀርበው እንስሳ ነውር የሌለበት ንጹህ መሆን እንዳለበት ታዟል። (ዘፀ12፥5፣ ዘሌ 22፥24፡25፣1ጴጥ1፥18፡19)
 
-ኅጢአት ለፈጸመው ሰው ቤዛ እንዲሆን በቀረበው እንስሳ ላይ ካህኑ እጁን በመጫን የሰውዬውን ኅጢአትና በደል አሸክሞ ወደ ምድረበዳ ይለቀዋል። (ዘለወ1፥4፣16፥21) ይህም በእኛ ኅጢአትና በደል ቤዛ ሆኖ ለሞተልን ለክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን እንመለከታለን። (ኢሳ53፥6 1ጴጥ2፥24)
 
– ለፈጸመው በደል ቤዛ እንዲሆነው እንስሳውን ያቀረበው መስዋዕት አቅረቢው ያርደዋል። የኅጢአት ደመወዝ ሞት ነውና። (ሮሜ 6፥23፣ ዕብ 9፥28)
 
ካህኑ የመሥዋዕቱን ደም በእግዚአብሔር ፊት አቅርቦ እንደሥርዓቱ ይረጨዋል። (ዘሌዋ 1፥5፣ 17፥11፣ ዕብ9፣12) 
 
የሀዲስ ኪዳን ምስጢረ ቁርባን አመሠራረት እና አፈፃፀም
 
የሀዲስ ኪዳን አማናዊ መስዋዕት (ቁርባን) የእየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጋ እና ክቡር ደም ነው። ለሀዲስ ኪዳን ስርዓት ቁርባን ምሣሌ እና ጥላ የነበረውን የኦሪት መስዋእት አሣልፎ በራሱ ስጋ እና ደም የሚፈፀመውን ምስጢረ ቁርባን ለመተካት ጌታችን መድኅኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በእለተ ሃሙስ ወይም ሀሙስ ምሽት በወዳጁ በአላዛር ቤት በተዘጋጀለት የፋሲካ የበአል ግብዣ ላይ ስርዓተ ቁርባንን መሠረተ።
 
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቲዎስ እንደተናገረው “ሲበሉም እየሱስ እንጀራን አንስቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሠጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ስጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንስቶ አመሥግኖም ሠጣቸው እንዲህም አለ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች ኅጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሀዲስ ኪዳን ደሜ ይሄ ነው አለ” (ማቴ26፥26-29)
 
ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ የተቀበላቸው 13ቱን ህማማተ መስቀል፤ የአዲስ ኪዳን ቁርባን የሆነው የክርስቶስ ቅዱስ ስጋ መገለጫወች እንዲሆኑ ህብስቱን ከ 13 እንደቆረሰው እንመለከታለን። 13ቱ ህማማተ መስቀል ማለት፦
 
1/   የኋሊት መታሰሩ፣
2/   በገመድ ታስሮ መጎተቱ፣
3/   በመሬት ላይ መውደቁ፣
4/   በአይሁድ እግር መረገጡ፣
5/   በግንድ መካከል እያጋፉ መጎተቱ ፣
6/   ፊቱን በጥፊ መመታቱ፣
7/   ጀርባውን ባለፋ ጠፍር መገረፉ፣
8/   እራሱን በዘንግ መደብደቡ፣
9/   የሾክ አክሊል በራሱ መድፋቱ፣
10/  የሚሰቀልበትን መስቀል መሸከሙ፣
11/  በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ መሰቀሉ፣
12/  ኮምጣጤ ከርቤና ሃሞት መጣቱ፣
13/   በ5 ቅንዋት መከነቸሩ (ጌታ የተቸነከረባቸው ቅንዋት ስም ዝርዝር ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ ይባላሉ)
ጌታ ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን አፍስሶ በመስቀል ተሠቅሎ አለምን ለማዳን ስለሚከፍለው የካሳ ቤዛነት እንደሚያረጋግጥ ለቅዱሳን ሐዋርያት አስቀድሞ ሲያሳያቸው ህብስቱን ከ 13 ቆርሶ ለ 12ቱ ደቀመዛምርት ማደሉ አንዱን እራሱ መቀበሉ ዛሬ ካህናት አባቶቻችን በስርዓተ ቅዳሴ ስጋውን እና ደሙን ቆርሰው እነሱ ተቀብለው ለህዝቡም ማቀበላቸው የዛ ምሣሌ ነው።
 
ጌታ እራሱ ባርኮ የፈተተውን ህብስት እራሱም ተቀብሎ ለሐዋሪያት እንዳቀበላቸው ሁሉ ዛሬ ካህናት (ቀሳውስት) በስርዓተ ቅዳሴ ያከበሩትን ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን እነሱ ከተቀበሉ በኋላ ህዝቡ እንዲቆርብ የሚያደርጉት ያንን አብነት በማረግ ነው። (ማር 14፥21)
 
በብሉይ ኪዳን ስርዓት ይቀርብ የነበረው ቅዱስ ቁርባን በኋላ ዘመን ለሚመጣውና በክርስቶስ ስጋ እና ደም ለሚተካው አማናዊ ቁርባን ምሳሌ እና ጥላ ሁነው የሚያልፉ ሲሆን፤ የቀደመው የኦሪት መስዋዕትም ለሰው ልጅ ከሚያስገኘው የኀጢአት ስርየት በጊዜያዊነት እና በድጋሚ መስዋዕት ማቅረብ የሚጠይቅ አድካሚ ስርዓት ነበር። በብሉይ ኪዳን መስዋእቱን የሚያቀርቡ ካህናትም አንድ ጊዜ ስለራሳቸው ኀጢአት፣ ሌላ ጊዜ ስለ ህዝቡ ኀጢአት የደም እና የቁርባን መስዋእት በማቅረብ የሚሰጡት አገልግሎት በህዝቡ ዘንድ የተላከውን መቅሰፍት ወይም የእግዚአብሔር ቁጣ ከስጋዊ ጥፋት የሚታደግ ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ዘለአለማዊ ህይወትን ለነፍሳቸው የሚያስገኝ ቋሚ ስርዓት አልነበረም። መስዋእት የሚያቀርቡትን የኦሪቱን ካህናት እና ለቁርባን የሚሆነውን መስዋእት እንዲያቀርቡ የሚታዘዙትን ህዝቡን ሁሉ ያማረረ እና አድካሚ ህግ እንደነበረ ቅዱስ መፅሐፍ ያስረዳል።
 
ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ በህገ ልቡና እና በህገ ኦሪት የነበሩ ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች (አበው ቅዱሳን) ወደ ፈጣሪያቸው የሚያቀርባቸውን እና ከሱ ጋር የሚያስታርቃቸውን አማናዊ መስዋዕት ወይም ቁርባን በየጊዜው በማቅረብ በፍፁም እምነት ሁነው የጩኸት እና የለቅሶ ድምፃቸውን ቢያሰሙም ዘላቂ እና
 
ዘለአለማዊ የሆነውን ድኅነትየማያመጣ አድካሚ ስርዓት እንደሆነ ስለተረዱ ከነፍስ እና ከስጋ ሞት የሚያድናቸውን ዘለአለማዊ ህይወትን የሚያድላቸውን አማናዊ መድኃኒት የሆነውን የእሱን ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን እንደሚሠጣቸው አስቀድሞ በገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው ቀዳማዊ ቃል የባህሪ አምላክ እየሱስ ክርስቶስ ለሠው ልጅ ካለው ፍፁም ፍቅር የተነሣ በሌላ በምንም ሳይሆን ስለ ሰው ልጅ ኀጢአት እና በደል እራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት የሱን ስጋ እና ደም “እንካችሁ ብሉ ጠጡ ይህ ስጋዬ ነው ይህ ደሜ ነው፤ ከሱም ብሉ ጠጡ የዘለአለም ህይወትም ታገኛላችሁ፤ ከኔ ጋርም ትኖራላችሁ” በማለት እንደ ስጋዊ ምግብ በልተነው የማያስርበውን እና ጠጥተነው የማያስጠማውን ዘለአለማዊ እና ሰማያዊ የህይወት ምግብ ሰጥቶናል።
 
እስራኤል ዘስጋ የተባሉ ቤተ አይሁድ ሰው ሆኖ ስጋን ተዋህዶ በመካከላቸው የተገለጠውን የድንግል ማርያም ልጅ እየሱስ ክርስቶስ የባህሪይ አምላክ መሆኑን ለመቀበል እንዳይችሉ ሰይጣን
እውነቱን እንዳይረዱ አይነ ልቦናቸውን ሰለጋሰደው በክህደት ጨለማ ውስጥ እየተድበሰበሱ ባሉበት ሰዓት አምስት የገብስ እንጀራን እና 2 አሣን በመካከላቸው አቅርቦ በባረከው ጊዜ ሴቶቹ እና ህፃናቱ ሳይቆጠሩ 5000 ያህል አባወራዎች ተመግበውት የተረፈው ቁርስራሽ 12 መሶብ ሞልቶ በመነሣቱ ለተደረገላቸው የበረከት ስራ ተደንቀው ሊያነግሱት እንደነብይም ቆጥረውት ሊሾሙት እና ሊያነግሱት ወደው ነበር። እሱ ግን ስለሚጠፋው እና ከሞት ስለማያድነው ስጋዊ ምግብ መጨነቅ እንደሌለባቸው ከነገራቸው በኋላ ነገር ግን ህይወት ስለሚሰጠው ዘለአለማዊ እና ሰማያዊ የነፍስ ምግብ መስራት እንዳለባቸው በቅዱስ ቃሉ አስተምሯቸዋል። (ዮሐ 6፥9-15፣ ዮሐ6፥25-34፣ዮሐ6፥49-58)
 
ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ዘወትር በቤተ መቅደሱ ውስጥ በታቦቱ ላይ የምታቀርበው መስዋእት እንደ ኦሪቱ ስርዓት ሳይሆን፤ ሊቀካህናት እየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ፈፅሞ በራሱ ፈቃድ የሰጠውን የማያዳግም መስወዕታችን የክርስቶስ ስጋ እና ደም ነው። ዘወትር ሳይቋረጥ በቅዳሴ አገልግሎት የከበረውን አማናዊ ቅዱስ ስጋ እና ክቡር ደም የመቅረቡ ሁኔታ በስሙ አምነው ክርስቲያን ለሆኑ ሁሉ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ተዘጋጅተው ለቆሙ ወገኖች ሁሉ የማይቋረጥ የነፍስ ምግብ ስለሆነ ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደ ህብስት (እንጀራ) “እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ከዚህ ጽዋ ቢጠጣ ለዘላለም ይኖራል እኔም ለዘላለም ህይወት የምሰጠው እንጀራ ስጋዬ ነው” ብሎ በነገረን መሰረት ዛሬ የቤተክርስቲያን ቀሳውስት አባቶቻችን ወይም ቀዳሲያን ህብስቱን በጻህል ወይኑን በጽዋ አክብረው ታቦቱ በክብር በሚኖርበት በመንበሩ ላይ ሰይመው “አሐዱ አብ ቅዱስ”፣  “አሐዱ ወልድ ቅዱስ”፣ ” አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት የቅዳሴውን አገልግሎት በልዩ ልዩ ምስጢራዊ ስርዓት ጀምረው እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን አገልግሎት በእውነተኛ ሃይማኖት እና ክህነታዊ ስርዓት በእግዚአብሔር ፊት ምስክርነት ሲሰጡበት ህብስቱ ፍፁም የክርስቶስ ስጋ ወደመሆን ወይኑ ፍፁም የክርስቶስ ደም ወደመሆን ይለወጣል። ይህ ማለት ህብስቱ ተለውጦ ስጋ መለኮት ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት ይሆናል። ምንጭ፦ የ14ቱ ቅዳሴ ትርጓሜ፣ ኮኩሐ ሃይማኖት ገጽ 109
 
በመንበሩ ላይ መስዋዕት ለማክበር ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚያቀርቡ 5ቱ ቀዳሲያን ቀሣውስት አባቶች “ይህ ህብስት የአምላካችን እና የፈጣሪያችን የአማኑኤል ስጋ ነው፤ ይህ ጽዋም የአማኑኤል ክቡር ደም ነው” ብለው ሲያቀብሉን የጌታ ስጋ እና ደም ነው ብለን አምነን እንቀበላለን። ባለቤቱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እራሱ ህዝቡን ይህ ስጋዬ ነው፤ ወይኑንም ይህ ደሜ ነው በማለት ለ12ቱ ደቀመዛሙርት በሐሙስ ምሽት እንዳቀበላቸው በቅዱስ ወንጌል ተነግሯል። (ማቴ 26፥26)
 
እግዚአብሔር አምላክ በፀጋው ያከበራቸው ቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶች የወንጌሉን ቃል መሰረት አርገው ህብስቱ ተለውጦ ስጋ መለኮት፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት እንደሚሆን መስክረዋል።
 
– ቂሳርያ ኤጲስ ቆጶስ የሆነው ቅዱስ ባሥልዮስ “ውዳሴ አምላክ” በተሰኘው ድርሳኑ ሲናገር “ጌታዬ ናፍቆቴ እየሱስ ክርስቶስ ሆይ! በዚህ ቅዱስ ቁርባን በስጋ በደም መለኮትህ እንደተዋሃደው አውቃለሁ። በዚህ በሚታየው ህብስት መልክ እንድቀበል አምናለሁ ከክብር ሁሉ የከበረ ደምህን በሰማያዊ ክብር ሁሉ ጋር አከብራለሁ። በዚህ በሚታየው እንድቀበል አምናለሁ። ስግደት የሚገባው ግሩም መለኮትህንም እንድቀበል በፍፁም ልብ አምናለሁ። እንዲህም ከሆነ አንድ ቀን ፈጣሪዬን፣ ጠባቂዬን ፈራጄ፣ መድኃኒቴን እቀበላለሁ። ዳግመኛም ይህንን ቅዱስ ቁርባን በህብስት እና በወይን አካል እንዳገኘው አምናለሁ። ህብስት እና ወይንም መሆን እንደሌለበት አምናለሁ። የአለም ሁሉ ፈጣሪ በመንግስተ ሰማይ ኪሩቤል ሱራፌል የሚሰግዱልህ ንጉሰ ነገስት አንተ ተሰውረህበት እንዳለህ አውቄ አምኜ እቀበላለሁ። አምላኬ ሆይ! ይህ ቃል እንደተናገርከው ነውና ያንተ ቃል ነው እንጂ የሌላ ቃል አይደለም። ያንተ ቃል ስለመሆኑ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን የምታምነውን ሁሉ አምናለው እውነተኛ ምስጢር አይደለም ለሚለኝ ሁሉ ነፍሴን ለሞት አሳልፌ ሰጥበታለሁ።” ብሎ የክርስቶስ ስጋ እና ደም መለኮት የተዋሀደው እና በህብስት እና በወይን የሚቀርበው ቅዱስ ቁርባንም ወደ ስጋ መለኮትነት እና ወደ ደመ መለኮትነት እንዴት እንደሚለወጥ በስፋት እንዳስተማረ ተመልክተናል።
ቀደም ሲል ጀምሮ ዛሬም ቢሆን ተረፈ አይሁድ የሆኑ አንዳንድ የኑፋቄ እና የክህደት ሰዎች የጌታን ቃል ለማስተባበል የማይፈነቅሉት የሀሰት ድንጋይ፣ የማይቆፍሩት የክህደት ጉድጓድ የለም። በአንድ በኩል የክርስቶስ መድኅኒትነት እና አዳኝነት እናምናለን እያሉ በሌላ በኩል ነገረ ድኅነት የተፈፀመበት እሱ እራሱ የዘለአለም ህይወት እንድናገኝበት በልግስና የሰጠን ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን አምኖ በመቀበል ዘለአለማዊ ድኅነት ለማግኘት አለመቻላቸውን ስናይ የእነዚህ ሰዎች ክህደት ከፈሪሳውያን እና ከአይሁድ ክህደት የባሰ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
 
በእውነተኛ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ስነምግባር ፀንቶ ለሚኖር ክርስቲያን ይህ የክህደት እና የኑፋቄ አስተሳሰብ ሊያስደነቀው እና ሊያሰናክለው ፈፅሞ አይገባም። ምክንያቱም እውነተኛ አማኝ ባለበት ሁሉ መናፍቅ አለ። ንፁህ ስንዴ ባለበት እንክርዳድ አለ፣ ሰው ባለበት ቦታ ኩርንችት አለ፣ ብርሃን ባለበት ጨለማ አለ፣ ህይወት ባለበት ሞት አለ፣ ደግነት ባለበት ክፋት አለና ነው። እውነተኛ ክርስቲያን ግን ሁሉን ቻይ አልፋና ኦሜጋ የሆነው እምነቱን ለዘለአለም በማይለወጠው እና በማይሻረው አማናዊ ቃሉ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ስጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ህይወት የላችሁም።” በማለት ዘለአለማዊ ድኅነን ለማግኘት የመንፈሣዊ አገልግሎታችን ሁሉ መደምደሚያ እና የጽድቃችን ሁሉ ማረጋገጫ ቅዱስ ቁርባን እንደሆነ አስረግጦ ነግሮናል። (ዮሐ6፥53)
 
የክርስቶስን ቅዱስ ስጋ እና ክቡር ደም መታሰቢያ ነው እንጂ አማናዊ አይደለም ብሎ የሚያስተምር እና የሚያምን ቢኖር የክርስቶስ ጠላት ነው። ክህደቱንም ከሰይጣን ክህደት የከፋ ያደርገዋል። ምክንያቱም ሰይጣን ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ ነህ በማለት የባህሪይ አምለክ መሆኑን እንደመሰከረ በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል። እውነተኛ ክርስቲያን ዘላለማዊ ህይወትን ለማግኘት እና የእግዚአብሔርን መ
 
ንግስት ለመውረስ ይችል ዘንድ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ህይወት አለው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ ስጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።” (ዮሐ6፥54 እና55)
 
ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንጦስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በፃፈው መልዕክቱ ላይ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብዬዋለሁና ጌታ እየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዛች ለሊት እንጀራን አንስቶ አመሰገነ፣ ቆርሶም…እንካችሁ ብሉ ይህ ስለእናንተ የሚሆን ስጋዬ ነው…እንዲሁም ከራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንስቶ ይህ ደግሞ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው…ይህንን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።” በማለት የክርስቶስን ስጋ እና ደም ስንቀበል ቸሩ መድኅንያለም ከቤተልሔም ጀምሮ እስከ ቀራንዮ አደባባይ ድረስ ስለእኛ ኅጢአት እዳ ሊከፍል (ካሳ ለመክፈል) የተቀበለውን መከራ፣ ህመሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ እርገቱን እና ዳግም ምፃቱን እያሰብን እንድንቀበል ሲያስረዳን ነው። (1ቆሮ11፥23-26)
 
በቤተክርስቲያን ውስጥ ቆመን ስናስቀድስ በምንቀበለው የቅዳሴ ስርዓት ውስጥ ተፅፎ እንደምናገኘው “አቤቱ ሞትህን እና ቅድስት ትንሣኤህን እንናገራለን” በማለት ተሰጥኦ የምንቀበለውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል መሰረት በማድረግ ነው።
 
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምሮ መሠረት ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሊያደርጉት የሚገባ ጥንቃቄ የሚከተለው ነው፦
 
በመሰረቱ ማንኛውም ክርስቲያን የክርስቶስን ስጋ እና ደም መቀበል ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው። ይሁን እንጂ ወደ ቅዱስ ስጋው እና ክቡር ደሙ ከመቅረቡ አስቀድሞ ሊያደርገው የሚገባው ቅድመ ዝግጅት፦
 
1/ የሚቀድሱ ቀሳውስት እና የሚቆርቡ ክርስቲያኖች በስርዓተ ጋብቻ ተወስነው የሚኖሩ ከሆኑ ከመቀደሳቸው እና ከመቁረባቸው በፊት 3 ቀን፣ ከቀደሱ እና ከቁርባኑ በኋላ ደግሞ 2 ቀን ከሩካቤ ስጋ ርቀው ንጽህናቸውን ሊጠብቁ ይገባቸዋል።
 
2/  ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል ያሰበ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ እራሱን ለካህን በማስመርመር የሚሰጠውን የንስሓ ቀኖና ፈፅሞ ከኅጢአት ንፁህ ሳይሆን በድፍረት ቢቀበለው እዳ በደል ስለሚሆንበት መጠንቀቅ ይገባዋል።
 
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ “ስለዚህ ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ስጋ እና ደም እዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፣ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ ሳይገባው የሚበላ እና የሚጠጣ የጌታን ስጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና ይጠጣልና” (1ኛ ቆሮ 11፤27-29)
 
3/   ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የተዘጋጁ ካህናትም ሆኑ ምዕመናን 18 ሰዓታት ከሚበላ እና ከሚጠጣ ምግብ ተከልክለው በጾም ተወስነው መቆየት ይገባቸዋል
 
4/   ካህኑ በሚቀድስበት ቀን እንቅፋት ቢያገኘው ይህ ማለት ቢነስረው፣ ትውኪያ ቢመጣበት፣ የበላው ምግብ ብስና ቢሆንበት፣ የአካል መድማት ቢያጋጥመው፣ አካሉ ላይ ቁስል እና የመሳሰሉ ሁሉ ቢያጋጥመው በዚያን ዕለት መቀደስም ሆነ መቁረብ አይገባውም።
 
5/   ለመቁረብ የተዘጋጁ ምዕመናን የቅዳሴው ስርዓት ከመጀመሩ በፊት ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው ቁመው ማስቀደስ አለባቸው። ቅዳሴ ሲጀመር ያልነበረ ካህንም ሆነ ምዕመን ስጋውን ደሙን ሊያቀብልም ሆነ ሊቀበል አልተፈቀደለትም። (ፍትሐ ነገስት አንቀፅ 12 ገጽ 137/97)
 
6/   ስለ ምስጢረ ቁርባን ተገቢውን ትምህርት አግኝቶ መድኃኒት እና ህይወት መሆኑን ያላመነ ሰው ቅዱስ ሰጋውን እና ከቡር ደሙን በድፍረት ሊቀበል አይገባም። አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት እንዳይቆርብ መቆጣጠር እና በጥንቃቄ መከታተል እንደሚያስፈልግ በቀኖና ቤተክርስቲያን ተደንግጓል። (ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 13 ገጽ 140/44)
 
7/   ንስሓ ተቀብሎ የቀኖና ጊዜውን ሳይፈጽም ለሞት የሚያሰጋ ደዌ ቢታመም ስጋውን እና ደሙን ከመቀበል አይከለከልም። ስጋውን እና ደሙን ከተቀበለ በኋላ ከበሽታው ከዳነ ከምእመናን ጋር በፀሎት ሊሳተፍ ይችላል። በቀኖና (በንስሓ) ወደ ተለዩ ሰወች እንዲመለስ አይገደድም። (ፍትሐ ነገስት 13 ገጽ 139/15)
 
8/   የሚጥል እና አረፋ የሚያስደፍቅ በሽታ ያለበት፣ ጋኔን (ሠይጣን) ያደረበት ሰው፣ ልዩ ልዩ የባዕድ አምልኮት የሚፈፅም ሰውማለትም የሚጠነቁል፣ የሚያስጠነቁል፣ በዛፍ በተራራ የሚያመልክ፣ ለዛር እና ለመናፍስት መስዋእት የሚያቀርብ እና የመሳሰለውን ሁሉ በሃይማኖት ስርአት የማይፈቀደውን ጥፋት የሚፈጽም ክርስቲያን ስጋውን እና ደሙን ከመቀበል ይከለከላል።
 
9/ ቀዱስ ቁርባን ከተቀበልን በኋላ መደረግ ሰለሚገበው ጥንቃቄ በሚመለከት ፦
 
–  ቅዱስ ቁርባን በተቀበሉበት እለት ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ መሟገት እና በማናቸውም የጭቅጭቅ ቦታ መገኘት ክልክል ነው፣
–  በቆረቡ እለት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ ፣ ከሚስት ወይም ከባል ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ፣ አብዝቶ መብላት እና መጠጣት፣ ፀጉርን መላጨት፣ ጥፍርን መቁረጥ፣ ከአካሉ ደም ማውጣት፣ በውሀ መታጠብ፣ ልብስን አውልቆ ራቁትን መሆን፣ የመሳሰሉትን ጥፋቶች መስራት ክልክል ነው።
 
የተወደዳችሁ እና የተከበራችሁ የ ዮሐንስ ንስሓ ድረገጽ ተከታታዮች ፤ የምስጢረ ቅዱስ ቁርባን ትምህርት እጅግ ሰፊ እና ጥልቅ ምስጢር ከመሆኑ የተነሳ አብዝቶ ለመጻፍም ሆነ እውነቱን ለመረዳት ሰፊ ጊዜ የሚያስፈልገው ቢሆንም አንኳን፤ በዚህኛው ክፍል የምስጢረ  ቅዱስ ቁርባን ትምህርታችን በቂ ግንዛቤ እና ትምሀርት ልታገኙበት ትችላላችሁ ብለን ያሰብነውን አጭር የቁርባን ትምህርት በዚህ መልክ ሰለቀረበላችሀ ያለመሰልቸት አና ያለመታከት አንብባችሁ በመረዳት የነፍሳችን መድኃኒት ወደሆነው እና ዘለአለማዊ ህይወት ወደምናገኝበት ወደ ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙ እንድትቀርቡ፤ ቅዱስ ቁርባን የተቀበላችሁም ሳትሰለቹ እንድትቀጥሉ በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላችኋለን።
 
ይህን ትምህርታችንን አስጀምሮ ያስፈጸመን አምላካችን ሁላችንንም ለቅዱስ ቁርባን ያብቃን
 
 
ምስጢረ ቅዱስ ቁርባን  ክፍል አንድ ትምህርትን ለመመልከት ይህን ይጫኑ፦ https://yohannesneseha.org/ስለ-ቅዱስ-ቁርባን/
 
ስለ ምስጢረ ቅዱስ ቁርባን ጥያቄና መልስ ለመመልከት ይህን ይጫኑ፦ https://yohannesneseha.org/ጥያቄና-መልስ/ስለ-ቅዱስ-ቁርባን/

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ

ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” (ዮሐ 6፡51)

ሰሞኑን በቴሌግራም ግሩፓችን የተነሱ ጥያቄዎች

ስጋ ደሙን ከመቀበል በፊት አንድ ክርስቲያን ማሟላት ወይም ማድረግ ያለበት ነገር፦

1/   የንሰሓ አባትቱን በማነጋገር ኀጢአት ካለ ንስሓ መግባት፣

2/  በስጋ ደሙ ከተወሰኑ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልምና ከቤተሰብዎም ይሁን ከማህበራዊ ኑሮ የሚያገናኙና የሚያጨቃጭቁ ቂም በቀል የሚያመጡ ሃሳቦች እንዳይኖሩ በተቻለ መጠን ሁሉንም ነገር ከመቁረብ በፊት ማስተካከል፣

3/   የተቀየምነው የተቀየመን፣ ያስቀየምነው  ያስቀየመን፣ የተጣላነው የተጣላን ማንኛውም ሰው ካለ በንስሓ አባት ወይም በሽማግሌ አማካኝነት ይቅርታ ጠይቆ ቂም በቀልን መተዉ፣ 

4/   በግል ህይወታችን ሁል ግዜ በቋሚነት የምንጸልየው የጸሎት ፕሮግራም ለኖረን ያሰፈልጋል። ሰይጣን እንዳይዋጋንና በቅዱስ ቁርባን ያገኘነውን በረከት እንዳያሳጣን የምንቋቋምበት መንፈሳዊ ተጋድሎ  በጸሎት ስለሆነ ነው፣

5/   ለመቁረብ ሁሉን ነገር አሳክተን ከወሰንን በኋላ ከምንቆርብ 3 ቀን በፊት ወንድ ይሁን ሴት ቤተሰብ ካለ  ከግንኙነት (ፆታዊ ግንኙነት) መቆጠብ ያስፈልጋል። 

6/   በሰጋ ወደሙ አንድ ሰው ተወሰነ ማለት እንደ ቤተክርስቲያን ስርአት ፈጽሞ ከአለማዊ ጠባይ ወጣ ማለት ስለሆነ በተቻለ መጠን አቀሙ የሚችለውን የበጎ ስራና የርህራሄ ስራ መስራት፣ ቅዱስ ቁርባን በበጎ ስራ መገለጽ ስላለበት ለድኆች ርህራሄ ማድረግ፣ ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊ ስራ ላይ መሳተፍ፣ 

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁሉ ለቅዱስ ቁርባን የምንበቃባቸው ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቁ መልካም እሴቶች ናቸዉ።

በተጨማሪም ለቅዱስ ቁርባን በምንቀርብበት ግዜ የምንለብሰው ልብሳችን  ለዚህ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ መንፈሳዊነትን ሊገልጽ የሚችል ራሱን የቻለ ልብስ ሊኖረን ይገባል። ንጹሕ ባሕርይ እግዚአብሔር ንጹሕ ነገርን ይወዳልና። በአለም ላይ ስንኖር በአለም ራሳችንን ለመግለጥ ልዩና ውድ ልብስ የምንገዛ ከሆነ ከዚህ በላይ በከበረው በእግዚአብሔር ጉባኤ ራሱን የቻለ ልብስ ቢኖረን፤ ባይኖረን እንኳ ያንኑ ልብሳችንን በጽዳት ልንይዘው ይገባል። አንፃራዊ ትርጓሜው በልብሱ አንፃር ውስጣችንንም ንጹሕ አድርገን ቀርበናል አንተም ንጹሕ ባሕርይ አምላክ ነህ ለማለት ነው።

ሴትም ሆነ ወንድ በሱባኤ እያለ እንዲህ አይነት ፈተና ቢገጥመው ፈተናው ባጋጠመው እለት የሱባኤውን ጋብ ፈጥሮ ሱባኤውን እንደገና በሚቀጥለው እለት መፈጸም ይችላል።  ኢሄ ካጋጠመው ከ 3 ቀን በኋላ ቁርባንም መቁረብ ይችላል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው በህልም እርኩስ መንፈስ ለፈተነው እንጂ ራሱ አስቦት የፈጸመው ዝሙት ካለ ግን እንደገና ለንስሓ አባቱ ተናዞ ባለፈዉ ከተሰጠው ንስሓ በላይ በእጥፍ ቀኖና መቀበል እንዳለበት የቤተክርስቲያን ስርዓት ያዛል።

ጠያቂያችን እንዳሉት ሲቆርቡ ኑረው በመካከል ወደ ቅዱስ ቁርባን የማያቀርብ ነውር ካጋጠማቸው ወይም ደግሞ በኀጢአት ከተሰናከሉ ለጊዜው መቁረባቸውን አቁመው ወደ ንስሓ አባታቸው ቀርበው የፈጸሙትን በደል ከተናዘዙ እና ንስሓቸውን ከጨረሱ በኋላ መቁረባቸውን መቀጠል ይችላሉ። ነገር ገን ጥፋቱን በመደጋገም ሁል ጊዜ በንስሓ እመለሳለሁ በሚል መንፈስ መሄድ እንደሌለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ይደነግጋል። ዋናው ቁም ነገር ማንኛውም ክርስቲያን በምንም ይሁን በምን ከቅዱስ ቁርባን ላለመለየት በየጊዜው መንፈሳዊ አላማውን በማጽናት መታገል እንዳለበት እንመክራለን።

ቅዱስ ቁርባን የሚቀበል ማንኛውም ሰው ለንስሐ አባቱ መናገር ያለበት ራሱ የሚያውቀው ጥፋት ከሌለበት በስተቀር ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል በተዘጋጀ ቁጥር መናገር አይጠበቅበትምና ይህንን የጠየቁን አባላችን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያሳስብዎት ነገር የለም።

ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ