አመታዊ በዓላት
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!" (ማቴ 3: 1-2)
ተከታታይ ትምህርትና ለጥያቄዎት ምላሽ ለማግኘት ቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ
አመታዊ በዓላት
(አመታዊ የስላሴ ክብረ በዓልን በማስመልከት የተጻፈ)
“ገሀሡ አጋዕዝትየ ቤተ ገብርክሙ አብርሃም”
“ጌቶቼ ወደ ቤት ገብታችሁ እረፉ” ዘፍ 18:3
ሐምሌ 7 ቀን የአጋዕዝተ ዓለም ቅድስ ስላሴ በዓል በየአመቱ የምናከብርበት ዋና ምስጢራዊ ምክንያቱን በአጭሩ እንደሚከተለው እናቀርባለን።
በቅድሚያ ስለ ስላሴ ሦስትነትና አንድነት በአጭሩ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስለሚያስፈልግ፤ ስላሴ የሚለው ቃል “ሠለሰ” ሦስት አደረገ ከሚለው የግእዝ ሥርወ-ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስት መሆን ሦስትነት ማለት ሁኖ በምስጢራዊ አገላለጹም አንድም ሶስትም (አንድነት ከሶስትነት) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የስላሴ ሶስትነታቸው በስም፣ በግብር፣ በአካል ነው። አንድነታቸው ግን በባሕርይ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ፣ ሁሉንም ስነፍጥረት በየወገኑ በመፍጠር ነው።
የስላሴ ሶስትነት ፡ –
- የስም ሶስትነት ማለት፡- አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ማቴ 28:19
- የአካል ሶስትነት ማለት፡- ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ አላቸው (ጥቅስ መዝ 33:14፣ 118:73፣ ኢሳ66:1 ፣ ዘፍ18:1-4 ማቴ 3:16)
- የግብር ሶስትነት ማለት፡- የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ፤ የወልድ ግብሩ መወለድ፤ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ
አብን ወላዲ፣ ወልድን ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ስንል ስለግብር ሶስትነታቸው ነው እንጂ እነሱማ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ፣ አንዱ ከአንዱ የማያንስ ዕለ እሩያን ናቸው።(ዩሓ 10:30) ቅድስት ስላሴ ስንል ቅድስት የሚለው ቅጽል ለሴት የሚሰጥ ቅጽል ቢሆንም ስላሴ በባሕርያቸው እንደ እናት ባሕርይ ስለሚመስሉ ነው። ልጅ ከእናቱ ባሕርይ እንደሚገኝ ይህ ዓለም ከስላሴ ባሕርይ ተገኝቷልና ነው። እናት ለልጇ የሚያስፈልገውን አስባ ተጨንቃ እንደምታቀርብለት ሁሉ፤ ስላሴም ለፈጠሩት ፍጥረት ሁሉ ከወዳድ እናት በላይ ስለሚያስቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድመው አዘጋጅተዋል (ማቴ 6:14)
በ40 በ80 ቀኑ የስላሴን ልጅነት አግኝቶ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሁሉ አስቀድሞ የስላሴን አንድነት ሦስትነት ወይም ስለምስጢረ ስላሴ መማርና ማወቅ መንፈሳዊ ግዴታው ነው። ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ማን ፈጠረህ ተብሎ ቢጠየቅ መልስ እንንዳያጣና መናፍቃንና ኢአማንያን በዘረጉት የክህደት ጉድጓድ ውስጥ እንዳይወድቅ ሊጠነቀቅ ይገባዋል።
ሐምሌ 7 ቀን ወደሚከበረው በዓል ስንመጣ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዘመን ጀምሮ አባታችን አዳምና እናታችን ሄዋን በምክረ ሰይጣን ተጠልፈው ከወደቁ በኋላ የሰው ልጅ የሆነው ሁሉ በዲያብሎስ ቅኝ ግዛት (በሞት ጥላ ሥር) የወደቀ ቢሆንም እንኳ ከአዳም ልጅ ከአቤል ጀምሮ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ብዙ ቀደምት አበው እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል።
ከቀደሙት አበው መካከልም አባታችን አብርሃም ይገኝበታል። አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅና ታማኝ ሰው እንደነበረ በቅዱስ መፅሐፍ ውስጥ በብዙ ቦታ ተጠቅሶ ይገኛል።አብርሃም በዘመኑ ከነበሩ ጣዖት አምላኪዎች ራሱን በመለየት እውነተኛውን አምላክ ፈልጎ ለማግኘት በፍጹም እምነት በስነፍጥረታት ተመራምሮ የፈጣሪን ሥራ እያደነቀ በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር ለሚፈልጉትና ለሚጠሩት ሁሉ አቤት የሚል የቅርብ አምላክ ነውና በከራን ምድር ለወዳጁ ለአብርሃም ተገልጾ “ከሃገርህ ከአባትህ ቤትና ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደማሣይህ ምድር ውጣ” ታላቅ ህዝብም አደርግሃለሁ…የሚባርኩህን እባርካለሁ የሚረግሙህንም እረግማለሁ የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” ዘፍ12:1 በማለት የጥሪ ድምጹን በሰማው ጊዜ አብርሃም ለፈጣሪው ታማኝ ሰው በመሆኑ ሳይጠራጠርና ሣያመነታ ከሀገሩና ከቤተሰቡ (ከዘመዶቹ) ይልቅ የጠራውን አምላክ አምኖ በመቀበል እግዚአብሔር ወደመረጠለትና ወደ አዘጋጀለት ምድር (ወደ ምድረ ከነአን) ሊሄድ ችሏል።
አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብሎ ወደተዘጋጀለት ምድር ካቀና በኋላ እምነቱ ፍጹም ስለነበረ መላ ሕይወቱ የሚመራው በእግዚአብሔር ቸርነት ነበረ። በቅዱሳት መጽሐፍት ታሪክ ውስጥ አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። ዘርህን እነደ ሰማይ ከዋክብት እነደ ምድር አሸዋ አበዛለው ተብሎ እነደ አብርሃም የተባረከ ከቶ ማንም አልነበረም። ከዚህ የተነሳ አባታችን አብርሃም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ቋሚ ሃብትና ንብረት ከማካበት ይልቅ በተመሣቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ተክሎ ዕለት ዕለት የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን እንግድነት እየተቀበለ የሚኖር ሆነ። በዚህ የተቀደሰው ሥራው አብርሃም በፈጣሪው ዘንድ ትልቅ ሞገስና ክብርን አገኘና ፀጋው እየበዛ እንደሆነ ያወቀው ጥንተ ጠላት ሰይጣን በምቀኝነት ተነሣስቶ በምትሃት ራሱን በድንጋይ ገምሶ ደሙን በማፍሰስ አጥንቱ ተከስክሶ የተጎዳ ሰው በማስመሰል በትልቅ ጎዳና ላይ ተጠምጦ ወደ አብርሃም ቤት የሚመጡትን እንግዶች ወዴት ትሄዳላችሁ በሚላቸው ጊዜ ርቦን ሊያበላን ጠምቶን ሊያጠጣን ከአብርሃም ዘንድ እንሄዳለን ሲሉት የወትሮው አብርሃም መሰላችሁ እንዴ እኔም እንደናንተ ያበላኝ ያጠጣኛል ብዬ ብሄድበት ራሴን ገምሶ አጥንቴን ከስክሶ ሰደደኝ ሲላቸው እነሱም እያዘኑ የሚመለሱ ሁነዋል። አብርሃምም ወደ ቤቱ የሚመጣ እንግዳ በመጥፋቱ ያለ አንዳች እንግዳ ምግብ የማይቆርስ መፍቀሬ እንግዳ ስለነበረ በፍጹም ልቡ እያዘነ እስከ 3 ቀን ያለ እንግዳ ግብር አላገባም (ምግብ አልበላም) ብሎ ሣይመገብ ቆይቷል።
በ3ኛው ቀን ግን ቀትር ላይ ከድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሣለ ስላሴ በታላላቅ ሽማግሌዎች ምሳሌ ሆነው በመምሬ አድባር ዛፍ ሥር ተቀምጠው ታዩት። አብርሃምም እነዚህን አረጋውያን ሽማግሌዎች የሚመስሉ እንግዶች በማየቱ ደስ ብሎት ወደ እነሱ ገስግሶ በመሄድ “ጌቶቼ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እረፉ አላቸው” በጣም የደከማቸው መንገደኞች ይመስሉ ስለነበር ደክሞናል ሲሉት አንዱን አዝሎ ወደ ቤቱ ሲገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ቀድመው በቤቱ ውስጥ ተገኝተዋል። አብርሃምና ሣራም ለተከበረ እንግዳ መቅረብ የሚገባው የመስተንግዶ ዝግጅት በማድረግ የፍጥረት ሁሉ ባለቤት ስላሴን በቤታቸው አስተናግደዋል። ወደ ወዳጃቸው ወደ አብርሃም ቤት በዕንግድነት የገቡት ሰለስቱ ስላሴም የእጃቸው ፍጥረት ከሆነው ከአብርሃም እና ከሣራ እጅ የቀረበላቸውን መስተንግዶ (ምግበ ሥጋ) እንደበሉ እንደጠጡ ሁነው ለአብርሃም ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።
ስላሴ ምግብ በሉ ማለት እሳት ቅቤን በላ እነደማለት ስለሚቆጠር የአብርሃምን በጎ ስራ በስላሴ ዘንድ የተወደደ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። አብርሃም ፈጣሪውን በእንግድነት የተቀበለ ብቸኛ ሰው ነው። ለመስተንግዶ የታረደው ወይፈንም ተነሥቶ ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና እንደሚገባ መስክሯል። በቤቱ የተገኙት ሦስቱ ስላሴም ለአብርሃም የአንድነትን ነገር ሲገልጹለት “የዛሬ ዓመት እነደዛሬው ወደ አንተ በእውነት እመለሣለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ” (ዘፍ 18:10) የሚለው አገላለጽ የአንድነትን ሚስጥር ያመለክታል። በዚህ መሠረት አብርሃም የስላሴን አንድነትና ሦስትነት (ምስጢረ ስላሴን) የማወቅ ምስጢር ተገልጾለታል። ልጅ በማጣት አዝነው የነበሩትን በእርጅና ዘመናቸው በልጅ ተባርከዋል። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለመኖሩንም አረጋግጠዋል። የወደፊት ተስፋቸውን ከነገራቸው በኋላ በሰዶምና በጎመራ ስለሚሆነው የእግዚአብሔር ቁጣ እና የሰዎች ጥፋት እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጁ ለአብርሃም ሣይደብቅ በግልጽ ተናግሮታል። አባታችን አብርሃም የአማላጅነት ጥያቄ አቅርቦ እግዚአብሔር አምላክም ስለወዳጁ አብርሃም ጥቂት ደጋግ ሰዎች እንኳ ቢኖሩ እንደሚምርለት ቃል እንደገባለት እንመለከታለን። (ኦሪት ዘፍ18) ባጠቃላይ ሐምሌ ስላሴ የምናከብረው በዓል ከላይ የገለጽነውንና ሌሎችን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንዘክርበት ታላቅ በዓል ነው።
የቅድስት ሥላሴ ቸርነት እና ምህረት በሁላችን ላይ ይደርብን።
“ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደኋላቸውም ይመለሱ” መዝ 123(129)፥5
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስሓ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም የሚተላለፈውን ኦርቶዶክሳዊ ተከታታይ የሃይማኖትና ክርስቲያናዊ የስነ ምግባር ትምህርት የምትከታተሉ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሁላችሁም፤ እግዚአብሔር አምላክ እንኳንስ ህዳር 21 ቀን በታላቅ ድምቀት ለሚከበረው አማናዊት ጽዮን ለተባለችው ለቅድስት ድንግል ማርያም አደረሳችሁ፥ አደረሰን።
ከዚህ ቀጥለን በዚህ እለት ስለምናከብረው የጽዮን በዓል በማስመልከት አጠር አድርገን እንናገራለን። እንደሚታወቀው ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተከርስቲያናችን በየአመቱ ህዳር 21 ቀን በእመቤታችን በድንግል ማርያም ሰም በተሰየሙት አብያተክርስቲያናት የፅዮንን በአል በታላቅ ክብርና በታለቅ ድምቀት ታከብራለች። የታሪኩ መነሻ ሊቀ ነብያት ሙሴ በደብረ ሲና 40 ቀን ከፆመ በኋላ አስርቱን ቃላት የተረከበበትን ወይም ታቦተ ጽዮንን ከእግዚአብሔር እጅ እንደተቀበለ ቅዱስ መፅሐፍ የመሰክራል። ታቦተ ጽዮን የሚባልበት ዋናው ምክንያትም ጽዮን በመባል የምትጠራው የንጉስ ዳዊት ከተማ ወደሆነችው ተራራ የእግዚአብሔር ታቦት ከገባበት ቦታ ጀምሮ ታቦተ ጽዮን እየተባለች መጠራት እንደጀመረች ታሪኩ ያስረዳል።
ጽዮን የተባለችው የታላቁ የንጉስ ዳዊት ከተማ ከፍተኛ ግፍ የደረሰባቸው እስራኤላዊያን ሁሉ እውነተኛውን ፍትሃዊ ፍርድ ለማግኘት ከየአቅጣጫው ተሰብስበው የሚማፀኑባት ከተማ ነበረች። ታቦተ ፅዮንን / ጽላተ ሙሴን በዚሁ በዳዊት ከተማ ስለነበረች በርሷ ተማፅነው ችግራቸውን ሁሉ አስረድተው ከደረሰባቸውና ከወደቀባቸው ከባድ ፈተናና አሰቃቂ ነገር ሁሉ ለመሰወርም እንዲሁም ከጠላት ተደብቆና እሩጦ ለማምለጥ ይቺ ጽዮን የተባለችው የእግዚአብሔር ታቦት የሚገኝባት ከተማ መሰወርያና መጠጊያ ስለሆነቻቸው ይህንን ለማመልከት “ታቦተ ጽዮን” ተብላ ለመጠራት አስችሏል። ከዚህ በኋላም የታቦተ ጽዮን ህዳር 21 ቀን የሚከበርበት ዋናው ታሪክ በዘመነ መሳፍንት ሊቀካህናት መስፍንና ሊቀካህናት የነበረው የኤሊ ልጆች በእግዚአብሔር ቤት በሰሩት የኅጢአት ድፍረት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ስለነበረ በነሱ ኅጢአት ምክንያት ታቦተ ጽዮንንና ህዝቡ እንዲማረኩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል። የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉት በአባታቸው እግር ተተክተው የክህነቱን ስራ እያከናወኑ ባሉበት ሰዓት በእግዚአብሔር ፊት እና በህዝቡ ፊት እጅግ አፀያፊ ስራን ይሰሩ ነበር። ከነዚህም 3ቱ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ፦
1ኛ/ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ከመሰዋዕታቸው በፊት ለራሳቸው የሚያስፈልጋቸውንና የተከለከለውን የመስዋዕት አይነት ይወስዱ ነበር፣
2ኛ/ ከማታ እስከጠዋት ድረስ በእግዚአብሔር ቤት እንዳይጠፋ ህግ ሆኖ የተደነገገውን የቤተመቅደሱን መብራት እንዲጠፋ ያደርጉ ነበር፣
3ኛ/ የእግዚአብሔር ታቦት ባለበትና ህዝቡ ለእግዚአብሔር አምልኮት በሚቀናበት በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሴቶችን ያስነውሩ ነበር።
በነዚህ 3 ዋና ዋና ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሊቀካህኑ ኤሊ ደርሶ እንዲህ ሲል ተናገረው “ሰው ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል ስለርሱ የሚማልድ ማን ነው” በማለት የኤሊ ልጆች የተባሉት ከሰው ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆኑ አስታራቂ ሽማግሌ የሌላቸው እንደሆነ በመግለፅ ተነግሮታል። ሊቀ ካህኑ ኤሊም ከእግዚአብሔር ይልቅ በልጆቹ በመስማማት የሚሰሩትን እያየ ዝም ስላለ በነሱ ምክንያት ህዝቡንም፣ እሱንም፣ ልጆቹንም እንደሚቀጣቸው ነግሮታል፤ (1ኛ ሳሙ 2፥25)
እንዲሁም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ያከበሩኝን አከብራቸዋለሁ የናቁኝም ይናቃሉና … ይህ በሁለቱ ልጆችህ አፍኒን እና ፊንሐስ ላይ የሚመጣ ላንተ መልክት ነው። ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ የታመነን ካህን ለእኔ አስነሳለሁ” ብሎት ነበር። እግዚአብሔር ስለሚያደርገው ነገር ሁሉ ለኤሊ ገልጾለት፤ ከዚህ በኋላ ግን እግዘኢአብሔር የተናገረውን የማይረሳና ያሰበውን የማያስቀር አምላክ ስለሆነ በቤተ እግዚአብሔር የኤሊ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በሰሩት ነውርና የግል ኅጢአታቸው ታቦተ ፅዮንን እና ህዝቡን ለአህዛብ ተላልፈው እንዲሰጡ ምክንያት ሆኑ። ብዙ ጊዜ እስራኤል ለእግዚአብሔር የበኩር ልጆች እንደመሆናቸው መጠን እግዚአብሔርም ለህዝቡ እለት እለት የሚያስብ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እያሟላ እና እየመገበ እየተንከባከበ የሚጠብቅና የሚመራ አምላክ ስለሆነ ይህን ሁሉ ታላቅ የእግዚአብሔር ውለታ ዘንግተው አታድርጉ የተባሉትን በማድረግ አትፈጽሙ የተባሉትን ሲፈፅሙ በታዩ ጊዜ እግዚአብሔር ወዲያውኑ የአባትነት ቅጣቱን ያመጣባቸዋል። ለዚህም ነው ካህኑ ኤሊ ገና በእንጭጩ (በእንቁላሉ) ልጆቹን ሳይመክርና ሳይገስፃቸው በመቅረቱ ለደረቁ የነደደው እሳት እርጥቡን እንደሚለበልብ ሁሉ በነሱ ኅጢአት የመጣው ቅጣት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦትና እስራኤላውያን ሃይማኖት በሌላቸው በፍልስጤማውያን እንደሚማረኩና አልፈው እንዲሰጡ እግዘኢዘብሔርም አለ። ፍልስጤማውያን እጅግ የሚፈሯቸውን እና የሚንቀጠቀጡላቸውን እስራኤል ዘስጋን የድፍረት ሃይል ተሰጥቷቸው በፊታቸው ሊፋለሟቸው ጦርነት ገጠሙ። በመጀመሪያው የጦርነት ውግያ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጥፋት ስለደረሰባቸው እንደገናም ሃይላቸውን አጠናቀው ከመከራ የምታድናቸውን ታቦተ ፅዮንን ይዘው የኤሊ ልጆችም ታቦትን አጅበው ከህዝብ ጋር ወጡ። ፍልስጤማውያን ጦርነት ለመግጠም ዘመቱ። አሁንም የእግዚአብሔር ቃል አልበረደም ነበርና ፍልስጤማዊያኑ ጋር ሲዋጉ ሰልፍ ባደረጉ ጊዜ በጦርነቱ ከእስራኤል 4000 ያህል ሰዎች ሞቱ (1ኛ ሳሙ 4፥2፣10 እና 11 ) በ2ኛም ጊዜ የእስራኤል ዘንድ 30000 ያህል እግረኞች ተገደሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች ፤ ሁለቱም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም በጦርነቱ ሞቱ።
ፍልስጤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ከማረኩ በኋላ በአቤኔዜር ወደ አዛጦን ወደተባለው ቦታ ይዘውት ከመጡ በኋላ የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ዳጎን የተባለው የጣኦት ቤት ውስጥ አስቀመጡት ። የእግዚአብሔር ታቦት የእግዚአብሔር ኃይል ያለበት ስለሆነ ፍልስጤማውያን የሚንበረከኩለትን ዳጎን የተባለው ጣኦት በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ተደፍቶ በታቦቱ ኃይል ተሰባብሮ እጅና እግሩ ራስና አንገቱ ሁሉም አካሉ ተቀጥቅጦ አመድ ሆኖ የዳጎን ካህናትም ወደ ዳጎን የሚገቡትን ሁሉ በአዛጦንን ያለው የዳጎንን መድረክ እስከዛሬ ድረስ አይረግጡም በማለት መስክረዋል (1ኛ ሳሙ 15፥5)
ታቦተ ጽዮን በፍልስጤማውያን ዘንድ ያደረገው ኃይል፦
1ኛ/ በአዞጦን ከተማ በነበረበት ጊዜ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በእባጭ በሽታ በመምታት ሃይሉን ስላሳያቸው ከከተማቸውና ከሀገራቸው እንዲሄድላቸው መክረው የእግዚአብሔር አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ። ወደ ስፍራውም ይመለስ አሉ። ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ የተመቱ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ። (1ኛ ሳሙ 5፥6-12) በደረሰባቸው የመቅሰፍት እባጭ ምክንያት ብዙ ሰዎች በሞት ስለተቀጡ መቅሰፍቱም እጅግ ከባድ ስለነበር በታላቅ ጩህት እና ለቅሶ የቃልኪዳኑ ታቦት የእግዚአብሔር ኃይል እንዳለበት እየመሰከሩ ወደሌላ አገር እንዲሄድላቸው በጠየቁት መሰረት ታቦቱ ከከተማ ሲወጣ መቅሰፍቱም ከነሱ እንዲወጣ ለታቦቱ የሚገባውን እጅ መንሻ ወይም አመሀ ማድረግ እንዳለባቸው በአዋቂ ሰዎች ስለተመከሩ በአገራቸው ላይና በህዝቡ ላይ ተሰዶባቸው የነበረ የእባጭ በሽታ ምሳሌ የሚሆን በ5ቱ የፍልስጤማውያን ከተሞች ቁጥር 5 የወርቅ እባጮች እንዲሁም በአገራቸው የተላከው ሁለተኛ መቅሰፍት የአይጥ መንጋ ስለነበር 5 የወርቅ አይጦች በምስል አድርገው ሁለት የሚያጠቡ ላሞችን በሰረገላ ጠምደው ታቦታቱን እና ያዘጋጁትን የወርቅ ስጦታ በሳጥን አድርገው በታላቅ ክብር ታቦቱ ወደሚሄድበት ቦታ ሸኝተዋል። ከዚህ በኋላም ያ መቅሰፍትና ደዌ ከነሱ ወጥቷል። ታቦቱም ከፍልስጤማውያን ከተማ በተነሳው ሰረገላ ላይ ሁኖ ወደ ቤትሳሚስ ጉዞውን አቀና (1ኛ ሳሙ 6፥9) በዚያም በቤት ሳሚሳዊው ወደ እያሱ እርሻ በደረሰ ጊዜ ታላቁን ድንጋይ በዚያ አቁመው የሰረገላውን እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መስዋእት አቀረቡ። የእግዚአብሔር ታቦትና የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሳጥን አውርደው በታላቁ ድንጋይ ላይ በክብር አስቀመጡት (1ኛ ሳሙ 6፥10-16)
በዚህ አይነት አኳኋን ከፍልስጤማውያን እጅ የተመለሰው ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ልዩ ልዩ ተዓምራት እያደረገ እግዚአብሔር በፈቀደላት በድንኳን እየኖረ በንጉሱ ዳዊት ዘመን ንግስና ደርሷል። ነብየ ንጉስ ዳዊት ግን ለታቦቱ ከነበረው ታላቅ ፍቅር የተነሳ በታቦቱ ፊት መስዋዕት በታላቅ ዝማሬና እልልታ በታቦቱ ፊት እየሰገደና እያሸበሸበ ለታቦቱ ወዳዘጋጀው ጽዮን ወደተባለችው ከተማ አስገብቷል። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ከመግቢያችን እንደገለፅነው ታቦተ ጽዮን እየተባለ በዚህ ስያሜ መጠራት ተጀምሯል።
እንግዲህ የታቦተ ጽዮን ታሪክ ባጭሩ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህዳር 21 ቀን ታቦተ ጽዮንን በዓል ከምታከብርበት ምክንያት ዋናዎቹ፦-
1ኛ/ በፍልስጤማውያን ዘንድ የተደረገው የእግዚአብሔርን ኃይል በመዘከር ሲሆን ፣
2ኛ/ ታቦተ ጽዮን ከቅድመ ልደት ክርስቶስ በ 1000 አመተ ዓለም ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ በንግስት ሳባ አማካኝነት ወይም በቀዳማዊ ሚኒሊክ መሪነት የመጣችበትን በማሰብ ነው።
ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ ያረፈችው በአገራችን በአክሱም ምድር ስለሆነ ዛሬም ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች አክሱም ጽዮን እየሄዱ የሚማፀኑትና የሚንበረከኩት ለዚህ ነው። ታቦተ ፅዮን በንጉሱ ሰለሞን መልካም ፈቃድ ለንግስት ሳባ (ማክዳ/ ንግስት አዜብ) በተሰጠ ጊዜ ከነካህናቱና ከነንዋየ ቅዱሳቱ ከነመፅሐፍቱ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ አገራችን ከክርስቶስ ልደት በፊት ለ1000 ዘመናት የኦሪትን መስዋዕት እየሰዋች አምልኮት ስትፈፅም ኖራለች የምንለው።
ታቦቱ የእግዚአብሔር ማደርያ እና የኃይሉ መገለጫ ስለሆነ ዛሬም የእግዚአብሔር ታቦት በስሙ ለተማፀኑት ሁሉ ኃይሉን ያሳያል። የእግዚአብሔር ታቦት በአዲስ ኪዳን እንዳልተሻረና እንዲያውም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት የሚሰዋበት መሆኑን ፍቁረ እግዚ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተች በውስጧም ያለችው ታቦተ ህግ ታየች” በማለት መስክሯል። (ዮሐ ራዕ 11፥19)
ስለዚህ በዋናነት የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዛሬው እለት የምናከብራት አማናዊት ፅዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ ወይም የመንፈስ ቅዱስ ታቦት የሆነችው ማህደረ መለኮት ድንግል ማርያም ናት። በብዙ የመፅሐፍ ቅዱስ ጽዮን ጽዮን የሚሉት ቃላቶች ፍፃሜው ለአማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም የተነገሩ እንደሆነ በውስጣቸው ያሉ የምስጢር ትርጓሜ ያመለክታል። ለምሳሌ ነብየ እግዚአብሔር ዳዊት “ሰው ሁሉ ጽዮንን እናታችን ነሽ ይሏታል፤ በውስጧ ሰው ተወልዷልና” መዝ 85 (86)፤5
እንዲሁም “እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታል ማደርያውም ትሆን ዘንድ ወዷታል እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚች አድራለሁ።” (መዝ132፥13) በማለት ጽዮን የሚለው ቃል አማናዊ ለሆነችው ለአምላክ እናት ለድንግል ማርያም የተነገረላት መሆኑን የጥቅሶቹ ምስጢር ያመለክታል። ምክንያቱም በውስጧ ሰው ተወልዷል ሲል መድኅንያለም ክርስቶስ ከእርሷ መወለዱን የሚያመለክት ሲሆን፤ ማደርያውም ትሆን ዘንድ መርጧታል ሲል የሱ ማደርያና ከእንስት አለም ሁሉ ለይቶ ለእናትነት የመረጣት መሆኑን ለዘላዓለምም ማህደረ መለኮት ስትባል መኖሯን የሚያመለክት ቃል ነው።
ነብየ እግዚአብሔር ኢሳያስም ስለዋ ትውልድ ሁሉ እንደሚንበረከክ አማናዊ ጽዮን እያሉ እንደሚሰግዱላት በትንቢቱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደአንቺ ይመጣሉ የናቁሽም ሁሉ ከእግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፥ የእስራኤል ቅድስት የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።” (ኢሳ 60፥14)
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም “እነሆም ከዛሬ ጀምሮ የሰው ልጅ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል፥ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ስራ አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው።” ብፅኢት፣ ቅድስት፣ ንጽሂት፣ ድንግል በማለት ትውልድ ሁሉ እንደሚያመሰግኗት በራሷ አንደበት የተናገረችውን ምስክርነት ነግሮናል። (ሉቃ 1፥48)
በአጠቃላይ፥ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዮሐንስ ንስኅ ድረገፅ መንፈሳዊ ፕሮግራም አባላቶቻችን እግዚአብሔር ከዚህ ጭንቅ ዘመን ሰውሮን ለዛሬው ለእመቤታችን ለወላዲተ አምላክ ለጽዮን በዓል ስላደረሰን በረከት ለመካፈል ይችን አጭር ትምህርታዊ መልዕክት እንዲደርሳችሁ ስናደርግ እናንተም በያላችሁበት ቦታ ሆናችሁ ለእናታችሁ ለድንግል ማርያም የሚገባትን ክብር በአማላጅነትዋ በአስታራቂነትዋ በመተማመን የምትችሉትን ሁሉ በጎ ስራ ልታደርጉና፤ እርስ በእርሳችሁም በፍቅር ለመኖር፣ ለመረዳዳት፣ ለመተጋገዝ ፣ ተባብሮ ለመኖር ህሊናችሁን ሁሉ እንድታዘጋጁት በስራም እንድትገልፁት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።
ለሁሉም ነገር የእመቤታችን አማላችነትዋና የእናትነትዋ ፍቅር በሁላችንም ላይ አድሮ ይኑር ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በዓታ ለቅድስት ድንግል ማርያም
ዛሬ ታሀሳስ 3 ቀን በየአመቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ የገባችበትን እለት በማሰብ የሚከበር በአል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 5485 አመተ አለም ገደማ ከእናትዋ ከቅድስት ሀና እና ከአባትዋ ከቅዱስ እያቄም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች። የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናትዋ እና አባትዋ በስእለት ያገኟት ልጃቸው ስለነበረች ለእግዚአብሔር አገልጋይ እንድትሆን በተወለደች በ 3 አመትዋ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወስደው በሊቀካህናቱ አማካኝነት መባ አድርገው ባቀረቧት ጊዜ ወላጆቿም ዘንድ ሆነ በእግዚአብሔር ቤት በአገልግሎት ላይ ላሉት በቤተመቅደሱ ካህናት ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄ ፈጥሯል። ይሁን እንጂ የእመቤታችን መወለድዋም ሆነ በ3 አመትዋ ወደ ቤተመቅደስ የመምጣትዋ ሁኔታ የሰው ሀሳብ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበረው ወላጆችዋ ወደ ቤተመቅደስ አምጥተው ለሊቀ ካህናቱ ሊያስረክቧት በተዘጋጁ ጊዜ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ የሆነው መልአከ ቅዱስ ፋኑኤል ከመላዕክት ማህበር ወደ እመቤታችን እና ወላጆችዋ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሰዎች በተገኙባት የቤተመቅደሱ ዙሪያ በሰው አምሳል ተገልፆ ሰማያዊ ህብስትና ሰማያዊ ፅዋ ይዞ በተገለፀላቸው ጊዜ በመልአኩ እጅ ያለውን በረከት ለመቀበል የቤተእግዚአብሄሩ አገልጋዮች ካህናት ሙከራ ቢያደርጉም መልአኩ የመጣበት ዋና አላማ ለብዙዎቹ ያልተረዳቸው ምስጢር ስለሆነ ያመጣውን በረከት ይዞ ከነሱ ተለይቶ በመራቅ ላይ እንዳለ እመቤታችን ድንግል ከናትዋ እቅፍ ወርዳ በቅድስናው አደባባይ ላይ እንደ ህፃናት ድክ ድክ በማለት ባለችበት ሰአት መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል አንድ ክንፉን ምንጣፍ አንድ ክንፉን መጋረጃ አድርጎ ሰማያዊ ብስቱን መግቧት እና ሰማያዊ ፅዋውን አጠጥቷት የተላከበትን መንፈሳዊ መልዕክቱን ከፈፀመ በኋላ ከህዝቡ ተለይቶ ወደ ሰማይ አርጓል። እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የፅንሰትዋም ሆነ የልደትዋ እንዲሁም ወደ ቤተመቅደስ የመግባትዋን ሚስጢር ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ የወደደውና የፈቀደው ኀይል ስለሆነ ነው።
እመቤታችን ድንግል ማርያም 3 አመት ከእናትና ከአባትዋ ቤት ከቆየች በኋላ ወላጆቿ አስቀድመው ለእግዚአብሔር በገቡት ቃል ኪዳን መሰረት ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወስደዋት መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ሰማያዊ ህብስት እና ፅዋ መግቧት ልብሰ ቅድስና አልብሷት ካረገ በጓላ ወላጆችዋም ሆኑ ሃላፊነት የነበራቸው የቤተእግዚአብሔር አገልጋዮች ባዩት ተአምራዊ ምስጢር እጅግ ተደስተው የምግቧና የልብሷ ነገር ከተያዘላት በቤተመቅደስ እያገለገለች እንድትኖር አስረክበዋት ከሄዱ በጓላ በቤተመቅደሱ ውስጥ የሚያስፈልገውን አገልግሎት እየፈፀመች 12 አመት ቆይታለች።
ስለ እመቤታችን ወደ ቤተመቅደስ የመግባትዋ ምስጢር በቅዱሳት መፅሐፍት በነገረማርያም በስፋት ተገልፆል። በተለይም ኢትዮጲያዊ ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ በድጓ ድርሰቱ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ ስለመግባትዋ ምስጢርና በቤተመቅደስ 12 ዓመት ስትቆይ በእግዘኢአብሔር በኩል የተሰጣትን የቅድስናና የድንግልና ህይወት በስፋት ተናግሯል። በቤተ መቅደስ በነበራት ቆይታም እለት እለት ቅዱሳን መላእክት በረቀቀ ሚስጢር እንደሚያረጋጓትና እንደሚያፅናኗት ተፅፏል።
ስለዚህ ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም የቅድስናና የድንግልና ህይወት በተለያየ የትምርታችን ክፍል የማትገለፅበት ቦታ ስለሌለ ወደፊትም ስለ ድንግል ማርያም በትምህርታችን ለመግለፅ የምንችልበት ፕሮግራም ስለሚኖረን ነገር ግን ታህሳስ 3 ቀን የሚከበረውን በአልዋን ሁላችንም በያለንበት ሆነን አቅማችን በሚፈቅደው መጠን በረከት ለማግኘት የየራሳችሁን መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከበአሉ በረከት እንድታገኙ ይሄን አጭር መልዕክት ወደናንተ እንዲደርስ አድርገናል።
እመቤታችን ድንግል ማርያም ለዛሬው እለት ወደ ቤተመቅደስ በገባች ጊዜ በመልአኩ በቅዱስ ፋኑኤል እጅግ የሚያስደንቅና ከሰው አይምሮ በላይ የሆነ ተአምር እንደተደረገው ዛሬም በእናታችን ቃልኪዳን እና አማላጅነት በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ከተቃጣው ልዩ ልዩ ፈተናና መቅሰፍት እንድትጠብቀን ሁላችንም በእምነት ሆነን በእናትነት ፍቅርዋ እንማፀናታለን፤ ለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን
ጥር 21-እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ